Download as docx, pdf, or txt
Download as docx, pdf, or txt
You are on page 1of 5

ስም ብቻ ምን ሊጠቅመኝ

መጠሪያ ብቻ ከሆነኝ - እኔ ክርስቲያን መባሌ፣


በግብሬ ካላሣየሁት - ካልተዋሐደ ከአካሌ፣
በጨለማ መቅረዝ ሆኖኝ - እግሬን ከእንቅፋት ካላዳነ፣
ስሙ ብቻ ምን ሊጠቅመኝ - ምን ሊሠራልኝ ነው ለኔ፣
በአርባ ቀኔ ስጠመቅ - ክርስቲያን ተብዬ ልጠራ፣
በእምነት ዳብሬ እንዳድግ - መልካም ፍሬን እንዳፈራ፣
ሥነ - ምግባሬ መጨነቄን - እንዲያሳይልኝ አጉልቶ፣
ክርስትናዬን እንዲናገር - በደረስኩበት ሁሉ ገብቶ
የተቀበልኩት ልጅነት - በእኔነቴ ዙሪያ አብርቶ፣
ለዚህ ነበር ምክንያቱ - በጥምቀት ክርስቲያን መሆኔ፣
ከኃጢአቴ ነጽቼ - ልጁ የተባልኩት እኔ፡፡
በአነጋገር በሥራዬ - ክርስትናዬን ካላሣየሁ፣
ጌታዬ በሰጠኝ መክሊት - አትርፌበት ካልተገኘሁ፣
እንደተዘናጋሁ ካለቀ - ከተጨረሰ ዘመኔ፣
ክርስቲያን መባሌ ምን ሊረባኝ - ምን ሊጠቅመኝ ነው ለእኔ፡፡

/ /
ይድረስ ለፈጣሪ መንበረ ጸባዖት
ከትልቁ ሥፍራ ከሰማዩ መንግሥት
ፍርድ ሳይዛነፍ ከሚፈጸምበት፡፡
ላኪው በምድር ላይ ግፍ የደረሰብኝ
ጐስቋላ አገልጋይህ ደካማው ባሪያህ ነኝ፡፡
ሳጥናኤል የሚሉት የቀድሞ ጠላቴ
ቂሙን ሳይዘነጋ እንደ አዳም አባቴ
ከገነት ሊያስቀረኝ ቀጥቅጦ ጥሎኛል
በአፍና አፍንጫዬ ደግሞም በጆሮቼ
መርዙ ተጠቅጥቆ በየብልቶቼ
አውጣኝ እያልኩህ ነው እባሕር ገብቼ፡፡
ደካማ ነኝና ራሴን አልቻልኩም
ለመታገል ሞከርኩ ከእጁም አልወጣሁም
ፍርድ ሰጭው ዳኛ ችግሬን ቃኝተኸው
መፍትሔ እንድትሰጠኝ ወዳንተ እጮኻለሁ፡፡

ኧረ ማን ነው

የበደለውን አስታውሶ
ያጠፋውን ክሶ
ያለውን ለግሦ
ታዛዥ ለፈጣሪ
እውነትን መስካሪ
የእምነትን ፋና አብሪ
ማነው እውነተኛ;
ከኃጢአት ፆመኛ

ኑ ወደ ሕይወት ምንጭ

በዓለም ስመላለስ በጨለማው ሃገር


መግቢያ መውጫው ጠፍቶኝ ሲያንገላታኝ ሐሩር
ፍፁም ግራ ገብቶኝ ተጨንቄ ሳለሁ
ሰይጣን ብዙ ሲጥር ወጥመዱ ሊያገባኝ
ዓለም ተብለጭልጫ ስታጭበረብረኝ
ለዘለዓለም ብላ የሰጠችኝ ደስታ
ጠዋት ብልጭ ብሎ እልም ሲል ማታ
በማይታይ ማዕበል ሕይወቴ ሲመታ
በፍቅር አየኝና አዘነልኝ ጌታ
ሸክሜን አራገፈ እንዳልንገላታ
አደለኝ የማያልቅ የዘላለም ደስታ
በቤቱ አስቀመጠኝ በቅዱሳን ቦታ
ካላችሁ እንደኔ የተንገላታችሁ
ኑ ወደ ሕይወት ምንጭ ዕረፍት አለላችሁ፡፡

ምንድን ነው ድርሻዬ

ሰው ሆይ እስቲ ዕወቅ
ዐዋቂውን ጠይቅ
ምንድን ነው ድርሻዬ
ንገረኝ ጌታዬ;
በማለት ጠይቀው
ድርሻህን ሳትለየው
ጉዞ አትጀምር
እንዲያው በግርግር
ምንድን ነው ሥራዬ
ንገረኝ ጌታዬ
በልና ጠይቀው
በጸሎት አሳስበው
ሥራህን ዕወቀው
ድረሻህን ተረዳው
ልከተል ጊዮርጊስን
ቅድስት ኢየሉጣን
ሕፃኑ ቂርቆስን
ሠለስቱ ደቂቅን
የሰማዕቱን ሕይወት
ዋጋ እንዳገኝበት
በኃይልህ በረከት
ወይስ በዓለም ልዙር
ወንጌልን ላስተምር
ላልሰሙት ልናገር
የለደትህን ምሥጢር
ለልምድ ተመላላሽ
በአካል ብቻ ገሥጋሽ
በማያውቁት መኻል
ልናገር ያንተን ኃይል
ላስተምር ጥምቀትን
እንዲሁም ስቅለትን
ልናገር ስለዕርገት
ስለ ዳግም ምፅዓት
ወይንስ ጌታዬ
መካሪ አለኝታዬ
በበአት ልወሰን
በጸሎት ልለምን
ያልተከተለህን
ያላወቀ ሕግህን
እንድታሳውቀው
በፍቅር እንድትቀርበው
ከገባበት ዓለም
እንዲድን በአንተ ደም
አሁንም ጌታዬ
መካሪ አለኝታዬ
የሆነውን ለእኔ
ባለችኝ ዘመኔ
በልና ጠይቀው
ድርሻህን ዕወቀው
ለእኛ የሆነውን
ባለ ዘመናችን
የምንፈጽመውን
እንድታሳውቀን
ቸር ፈቃድህ ይሁን
ማለቱ ይሻላል
እርሱም ይመራናል፡፡
አደራ እልሻለሁ

በዚያ በበረሃ ምንም በሌለበት


ተሰደሽ የኖርሽው ሳይኖርብሽ ኃጢአት
የሰው ልጆች ቤዛ የመለኮት እናት
ቅድስት እናታችን የዋኋ እመቤት
አደራ እልሻለሁ ከጐኔ አትራቂ
ወዳጅ ዘመድ የለኝ ያላንቺ ጠባቂ
አድኝኝ እናቴ ከሥጋ ፈተና
እኔማ ያላንቺ አልችልም ልፀና
ቅድስት ሆይ አትራቂኝ አንቺ የዓለም እናት
በዝቷል መከራዬ አድኝኝ ከጥፋት
ሸክሜ የከበደኝ እንግልት ሆኛለሁ
ከኔ እንዳትለይ አደራ እልሻለሁ፡፡

( ፡ ሐመር ሁለተኛ ዓመት ቁጥር 4፣ ጥር 1987 ዓ.ም)

በክርስቶስ ይህንን አግኝተናል

ሊለካ የማይችል ፍቅር


ሊሞት የማይችል ሕይወት
ሊደመሰስ የማይችል ጽድቅ
ሊረበሽ የማይችል ዕረፍት
ሊጠፋ የማይችል ደስታ
ሊያሳዝን የማይችል ተስፋ
ሊቀንስ የማይችል ክብር
ሊጨልም የማይችል ብርሃን
ሊደክም የማይችል ብርታት
ሊረክስ የማይችል ቅድስና
ሊያልቅ የማይችል በረከት
ሊሻር የማይችል ጥበብ …..

የጽዮንን አሥራት ሀገር፣ የቃል ኪዳኑን ታቦት ምድር፤


በቅዱሳን ጸሎት እሳት፣ በነበልባል የምታጥር፤
ለኢትዮጵያ ተስፋ ፈጻሚ፣ የጉንጯን ዕንባ የምታብስ፤
የተዘረጋ የተማጽኖ እጇን፣ በምሕረትህ የምትዳስስ፣
ቅዱስ ሥጋህን ቆርሰህ፣ በክቡር ደምህ የዋጀኸን፤
ሰማያዊ ምስጢርህን ገልጠህ፣ በተዋሕዶ ያከበርከን
ማዕበል ወጀቡን አሻግረህ፣ ከእሥራ ምዕቱ ያደረስከን
የድንግል ማርያም ልጅ፣ ቸሩ መድኃኔ ዓለም ተመስገን ….

አደራ እልሻለሁ

በዚያ በበረሃ ምንም በሌለበት


ተሰደሽ የኖርሽው ሳይኖርብሽ ኃጢአት
የሰው ልጆች ቤዛ የመለኮት እናት
ቅድስት እናታችን የዋኋ እመቤት
አደራ እልሻለሁ ከጐኔ አትራቂ
ወዳጅ ዘመድ የለኝ ያላንቺ ጠባቂ
አድኝኝ እናቴ ከሥጋ ፈተና
እኔማ ያላንቺ አልችልም ልፀና
ቅድስት ሆይ አትራቂኝ አንቺ የዓለም እናት
በዝቷል መከራዬ አድኝኝ ከጥፋት
ሸክሜ የከበደኝ እንግልት ሆኛለሁ
ከኔ እንዳትለይ አደራ እልሻለሁ፡፡

( ፡ ሐመር ሁለተኛ ዓመት ቁጥር 4፣ ጥር 1987 ዓ.ም)


ተመስገን …..

You might also like