Download as docx, pdf, or txt
Download as docx, pdf, or txt
You are on page 1of 12

ቀሲስ መ/ር ሄኖክ ወ/ማርያም Memehir Henok Weldemariam

4 mins ·
ንስሐ መግባት የመረረው መነኩሴና የአባ ሲሶይ ምክር!
በቀሲስ መ/ር ሄኖክ ወ/ማርያም
ተወዳጆች ሆይ በመጽሐፈ ፊሊክስዮስ በገጽ 178 ላይ ያለውን ታሪክ እንይ፡፡ አንድ መነኩሴ አባ ሲሶይን ‹‹አባቴ በኃጢአት
ተነሰካከያለሁና ምን ላድርግ›› አላቸው፡፡ አባ ሲሶይም ‹‹ንስሐ ግባ›› አለው፡፡ መነኩሴውም ‹‹ብዙ ግዜ እየተሰነካከልኩ
በንስሐ ስመላለስ ኖርኩ እስከ መቼ ስወድቅ ስነሳ እኖራለሁ?›› አላቸው፡፡ አባ ሲሶይም ‹‹እስክትሞት ድረስ፡፡ አንድም
ሞትህን በንስሐ፣ኃጢአትህን በንስሐ፣ወይም በሞት እስክትቀደም ድረስ›› አሉት፡፡
ደግ ሰው ከበጎ ሥረው በሚመለስበት፣ኃጢአቱ በሚሰረየይበት ቀን ቢሞት የቀድሞ ኃጢአቱ አይታሰብበትም ኃላ በሠረው
ኃጢአት ይሞታል እንጂ፡፡ ኃጥእ ከኃጢአቱ ተመልሶ በጎ ሥራ ቢሠራ የቀድሞ ኃጢአቱ አይታሰብበትም፡፡ ጻድቅም ኃጢአት
ቢሠራ በቀደመው በጎ ሥራው አይድንም በመጨረሻ በሠራው ኃጢአት ይኮነናል፡፡ ምክንያቱም ሰው በጊዜው ግብሩ ነው
የሚሄደውና፡፡ ስለዚህ በኃጢአት ስንወድቅ በቶሎ ንስሐ ልንገባ ይገባል፡፡
አንዳንድ ሰነፎች ቀድሞ የጽድቅ ሥራ ሲሠሩ ይኖሩና በኃላ በኃጢአት ይወድቃሉ፡፡ ንስሐ ግቡ ሲባሉ ልባቸውን
የሚያደነድኑት የቀድሞ በጎ ሥራቸውን በማሰብ በዛ ሥራ የሚድኑ፣ከፈጣሪም ሰማያዊ ዋጋ የሚቀበሉ ይመስላቸዋል፡፡ ይህ
ስህተት ነው፡፡ በሕይወታችን መጨረሻ የምንሠራው ሥራ ለገነቱም ሲዖሉም ሕይወት ይወስናሉ፡፡ ለዚህም ነው አባቶች
‹‹ፍጻሜዬን ያሳምርልኝ›› የሚሉት፡፡
የመንፈሳዊ ሕይወታችን የጽድቅና የኃጢአት ፍጻሜ ነው ለሰማያዊ ሽልማት እና ቅጣት የሚዳርገን፡፡ ለዚህም ነው
እግዚአብሔር ለነብዩ ሕዝቅኤል ለሰው ልጅ ንገርልኝ ብሎ ‹‹በበደለበት ቀን የጻድቅ ጽድቁ አያድነውም፣ኃጢአተኛም
ከኃጢአቱ በተመለሰበት ቀን በኃጢአቱ አይሰናከልም፤ጻድቁም ኃጢአት በሠራበት ቀን በጽድቁ በሕይወት አይኖርም፡፡ እኔ
ጻድቁን በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ባልሁ ጊዜ፣እርሱ በጽድቁ ታምኖ ኃጢአት ቢሠራ በሠራው ኃጢአት ይሞታል እንጂ
ጽድቁ አይታሰብለትም፡፡ እኔም ኃጢአተኛውን በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፣እርሱ ከኃጢአት ተመልሶ ፍርድንና ቅን
ንገርን ቢያደርግ፣ኃጢአተኛው መያዣን ቢመልስ የነጠቀውንም ቢመልስ በሕይወት ትእዛዝ ቢሄድ ኃጢአትም
ባይሠራ፣በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም፡፡ የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም፤ፍርድንና ቅን ነገርን
አድርጎአል፤በእርግጥ በሕይወት ይኖራል›› በማለት ዘርዝሮ ቋጥሮ አስቀምጦልናል፡፡ /ት.ሕዝቅ 33÷12-16/
ስለዚህ ያለማነውና ያጠፋነው በእግዚአብሔር ዘንድ ይመዘናል፡፡ ሰው ከዚህ ዓለም በሚለይበት ጊዜ በፈጣሪው ፊት
የሠራው ጽድቅ እና ኃጢአት ያመዘናል፡፡ ያለማነው ካጠፋነው ጋር ይመዘናል፡፡ ያለማነው በልጦ ቢገኝ ይፈረድልናል፡፡
ያጠፋነው በልጦ ቢገኝ ይፈረድብናል፡፡ ወዳጆቼ በፍቃደ ሥጋ ተስበን የሠራነውን ኃጢአት ንስሐ ልንገባበት ይገባል፡፡ በኃላ
በሚያስፈራው ዙፋን ፊት የኃጢአታችን ሒሳብ ሲወራረድ፣ለሲኦል እሳት እንዳንማገድ በንስሐ መንገድ እንጓዝ ጽድቁንም
እንያዝ፡፡
ቸር ዋሉልኝ!
ጥር 2/5/11 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ገድልን በገዳመ ቆሮንጦስ፣ተማር ከክርስቶስ!


<<በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ>> ሉቃ 13÷24
/ለመናፍስት ውጊያ የሚጠቅመን አንዱ መፍትሔ/
በቀሲስ መ/ር ሄኖክ ወ/ማርያም
ተወዳጆች ሆይ ስለ ዓይነ ጥላ ተከታታይ ትምህርት አጠናቀናል፡፡ እናንተም ሳትሰለቹ፣ሳትታክቱ ስላነበባችሁ፣ሼር በማድረግ
ለሌሎች ስላዳረሳችሁ፣ገንቢ ሐሳብ ስለሰጣችሁኝ እጅጉን አመሰግናለሁ፡፡ ይህን ተከታታይ ትምህርት ከዩ ትዩብ ውጪ በዚህ
ፔጅ ላይ አንዱን ክፍል ብቻ ከ 150‚000 -200‚000 /ከመቶ ሃምሳ ሺ እስከ ሁለት መቶ ሺ/ ሰው እንደሚያየው ፔጄ
ይነግረኛል፡፡ በ 42 ክፍል የጻፍኩትን ትምህርት በቀላሉ በአማካይ በመቶ ሃምሳ ሺ ብናበዛው ይህን ተከታታይ ትምህርት
በአጠቃላይ ከስድስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ሰው አንብቦታል ማለት ነው፡፡ ተመስገን እንጂ ሌላ ምን ይባላል፡፡ ይህ ሁሉ
የእናንተ የአንባቢዎቼ ጸሎት እና ምርቃት ብርታት ሆኖኝ ነው ትምህርቱ እዚህ የደረሰው፡፡
መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ፍቃደ ሥጋን ለፍቃደ ነፍስ ለማስገዛት፣ በነፃ ፍቃድህ ወስነህ ክርስቶስን ኃይልህ አድርገህ የውጭ
እና የውስጥ ፈተናህን ለማሸነፍ የምታደርገው ብርቱ ትግል ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ሩጫና ተጋድሎን ያመሳስላቸዋል።
ሁለቱም የማያቋርጥ ብርቱ ልምምድን ይጠይቃሉ። ሁለቱም ብርቱ ፍልምያ ይሻሉ፣ ሁለቱም ያሸልማሉ። ሩጫ ሜዳልያ
ተጋድሎ የጽድቅን አክሊል ያቀዳጃል። ለጥቂት ቀናት ልምምድን ያቋረጠ ሯጭ የመወዳደር ብቃቱ ይሸረሸራል፤ ከተጋድሎ
የራቀ መንፈሳዊ ሰውም መንፈሳዊ አቋሙ ዋዥቆ የቀደመ ጽናቱን ያጣል፤ ቀድሞ ወደነበረው ብቃቱ ለመመለስም
ይቸገራል። ተጋድሎ እንደ ገበሬ መዝራትና ማጨድ ነው። ለመዝራት አስቀድሞ መሬቱን ማረስ ማለስለስ ያስፈልጋል።
ለመጋደልም እንደ አቅም መፈተን መልፋት ያስፈልጋል። ማጨድ ግን የልፋትን ፍሬ መሰብሰብ ነው። ገበሬ የሚያፍሰው
የዘራውን የለፋበትን ነው። ስለዚህ ተጋድሎም በሥጋ ዘርቶ በነፍስ መንፈሳዊ ፍሬን መሰብሰብ ነው።
ለመጋደል መንፈሳዊ ልምምዶችን ማድረግ ይጠበቅብናል። በአጭሩ ተጋድሎ ማለት በነፍስ የሚያውከንን ከሥጋችን ላይ
መቁረጥና ሥጋን አድክሞ ነፍስን ማሳረፍ ነው። ገላ 5÷12 ተጋድሎ ማለት ነፍስን እስከ ሞት ድረስ መውደድ ነው። /ራዕ
12÷11/
ወዳጆቼ ሁለት ዓይነት መንፈሳዊ ተጋድሎ አለ፡፡ አንደኛው ከሥጋ ፍቃድ ጋር የሚደረግ ውጊያ ሲሆን፤ ሁለተኛው ከርኩሳን
መናፍስት ጋር የሚደረግ ረቂቅ ፍልምያ ነው፡፡ ከፈቃደ ሥጋ ጋር የሚደረግ ተጋድሎ የሚታይ ሲሆን ፤ከርኩሳን አጋንንት ጋር
የሚደረገው ጦርነት ግልጽ እና ስውር ነው፡፡ አንድ ሰው በሥጋም በሰይጣንም ሊፈተን ይችላል፡፡ ግን የመጀመሪያ ተጋድሎ
ማለት ከራስህ ጋር የምትጀምረው ትግል ነው፡፡
ከላይ ላየናቸው መንፈሳዊ ተጋድሎ አርአያችን፣ አስተማሪያችን ክርስቶስ ነው፡፡ እሱም በጠባቡ መንገድ እንድንሄድ እና ወደ
መንግሥቱ ደጃፍ እንድንገባ ‹‹ተጋደሉ›› ብሎናል፡፡ ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በመንደሮች እና በከተሞች እያስተማረ
ያልፍ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ሰው የጌታን ትምህርት በመስማት ወደ እርሱም በመጠጋት ስለሚድኑት ሰዎች ብዛትና ማነስ
እንዲህ ብሎ ጠየቀው፡፡ "ጌታ ሆይ የሚድኑት ትቂቶች ናቸውን?" አለው፡፡ ጌታችንም ለጠየቀውና ለሚሰሙት ሁሉ
"በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፤ እላችኋለሁና ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ፤ አይችሉምም" አላቸው፡፡ ሉቃ 12÷23-24
ስለዚህ መንፈሳዊ ተጋድሎ በሰዎች ፍላጎት ሳይሆን በባለቤቱ በክርስቶስ የታዘዘ ነው፡፡ ምክንያቱም በጠባቧ በር ለመግባት
መንፈሳዊ ተጋድሎ ያስፈልጋል፡፡ በሯም ‹‹ጠባብዋ›› የተባለችው በልፋት በተጋድሎ ህይወት ስለሚገባባት ነው፡፡ ጌታም
‹‹ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ አይችሉምም›› ያለው እንዳቅማቸው ለማይጋደሉ ነው፡፡
ወዳጄ እርሱ ያዘዘውን የተጋድሎ ሕይወት በእኛ ፍላጎት እና ትጋት ብቻ ሳይሆን በጸጋው አስጀምሮ ያስፈጽመናል፡፡ ደግሞም
ተጋድሎን ላንጋደል ጀምረን ላንፈጽም አላዘዘንም፡፡ ተጋድሎንም ስንጀምር ‹‹ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን
እችላለሁ›› ብለን ነው ፈተናውን ሁሉ ለመቋቋም በክርስቶስ ኃይል የምንጀምረው። /ፊልጵ 4፥13/ መንፈሳዊ ተጋድሎ
ከጸብአ አጋንንት እና ከሥጋ ፍላጎት የምንላቀቅበት ቢሆንም ዋናው በየዕለቱ ከክርስቶስ ጋር የመሆናችን እርሱም ከእኛ ጋር
የመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡ ከተጋድሎ መራቅ ማለት ከክርስቶስ ጋር መለየት እና በሰይጣን መያዝ ማለት ነው፡፡ ከግንዱ
የተለየ ቅርንጫፍ ፍሬ እንደማያፈራ ሁሉ ከተጋድሎም የሚርቅ ሰው መንፈሳዊ ጸጋን እና መንፈሳዊ ማዕረጋትን ማግኘት
አይቻለውም፡፡ መንፈሳዊ ጸጋዎች እና ማዕርጎች ያሉት በፈተና በመከራ እና በተጋድሎ ውስጥ ነው፡፡
ክርስትና የየዕለት የልፋት ሕይወት ስለሆነ ተጋድሎ ነው፡፡ ተጋድሎ ወደ መንፈሳዊ ከፍታ የሚያደርስ መንፈሳዊ መሰላል
ነው፡፡ ማንም እንዳቅሙ ሳይጋደል ወይም መከራ ሳይቀበል የድሉን አክሊል አይቀዳጅም፡፡ እራሳችንን በዘመናችን ለክርስቶስ
ለማስገዛት ተጋድሎ ያስፈልግኃል፡፡ ምክንያቱም ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን ይዘናልና፤ ሥጋና መንፈስ፡፡ በሥጋችን የፈለግነውን
ሳይሆን ያልፈለግነውን እናደርጋለን፡፡ በዚህም ሕይወታችን ብርቱ ሰልፍ ይሆናል፡፡ "በምድር ላይ የሰው ሕይወቱ ብርቱ ሰልፍ
አይደለምን?" ኢዮ 7÷1 ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛል፤ እነዚህም እርስ በእርሳቸው
ይቀዋወማሉ፡፡ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም›› ብሏል፡፡ ስለዚህ ሰው ያላወቀልን ታላቅ ጦርነት ውስጥ
እንገባለን፡፡ /ገላ 5÷17/
ወዳጄ እንደ ሰነፎቹ በክርስቶስ አንዴ አርነት ወጥቻለሁ ብለህ ከመንፈሳዊ ተጋድሎ ብትርቅ ምንም አታገኝም፡፡ በእርግጥ
ክርስቶስ ከዲያቢሎስና ከኃጢአት አርነት ነፃ አውጥቶናል፡፡ ሰው ግን ነፃ ያወጣውን ጌታ በመተው፣ በኃጢአት ላይ ነው
የዘመተው፡፡ ከገባበት ከኃጢአት ባርነት ነፃ ለመውጣት ተጋድሎ ነው የሚያስፈልገው።
ሁለተኛው ተጋድሎ ማለትም ከርኩሳን መናፍስት ጋር የሚደረገው ከባዱ ውግያ ነው፡፡ በዚህ ውጊያ ከአዳም እና ከሔዋን
ጀምሮ የእግዚአብሔር ጸጋ እስካደረባቸው ታላላቆች ወድቀውበታል፡፡ ምክንያቱም ውጊያው ከደም እና ከሥጋ ጋር ስላልሆነ፡፡
ይህንን ውጊያ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና ከአለቆችና ከስልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ
ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊው ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ›› በማለት የተጋድሎውን ክብደት
ይገልጻል፡፡ /ኤፌ 6÷12/
ለብዙዎቻችን መንፈሳዊ ተጋድሎ ለቅዱሳን ለመነኮሳት ለመናንያን ብቻ የተተወ ይመስለናል፡፡ ይህ እሳቤያችን እንዳቅማችን
በትንሹ እንዳንጋደል አድርጎናል፡፡ ወዳጄ ከተጋደልክ ጸጋ ታገኛለህ፤ ካልተጋደልክ ጸጋ ያላቸውን እያየህ በጸጋቸው ትቀናለህ፡፡
ወደድክም ጠላህም እንዳቅምህ ተጋድሎ ያስፈልግኃል። ምክንያቱም በሥጋና በርኩስ መንፈስ ላይ ፈጣሪህ ክርስቶስ
ተጋድሎ፣ ተጋድሎን ስላስተማረህ ነው፡፡ ጌታችን በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ተጠምቆ ዕለቱን ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሄድ ከሰው
ተለይቶ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾሞ ተጋድሎን አስተምሮናል፡፡
ክርስቶስን አርአያ አድርገህ ወደ ተጋድሎ ስትገባ ጌታ በገዳመ ቆሮንጦስ የገጠመው ፈተና ባንተም ላይ ይከሰታል፡፡ ጌታችን
በገዳመ ቆሮንጦስ በጾም በጸሎት ተወስኖ ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ የተገባሉትን ስስትን በትዕግስት፣ ትዕቢትን በትህትና፣
ፍቅረ ነዋይን በጸሊአ ንዋይ ድል እንደነሳ ሁሉ አንተም በእነዚህና በልዩ ልዩ ፈተናዎች ስትፈተን ድል የምትነሳው በተጋድሎ
ነው፡፡
ወዳጄ ተጋድሎ ስልህ ተራራና የማይቻል አድርገህ እንዳታስብ፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ትንሽም ይሁን ትልቅ ተግባራት
ለምሳሌ መጸለይ፣ መስገድ፣ ሰው መርዳት፣ መመጽወት፣ ማስቀደስ፣ መቁረብ፣ በንስሐ ሆኖ ንጽሐ ሥጋን መጠበቅ፣
ከዝሙት መጠንቀቅ እነዚህንና የመሳሰሉትን ያለማቋረጥ ወይም ላለማቋረጥ የምናደርገው ትግል ብርቱ ተጋድሎ ነው፡፡
ከእነዚህም በመነሳት ነው ወደ ከፍተኛ የተጋድሎ ሕይወት የምንገባው፡፡ በውስጣችን የሚመላለሱትን የኃጢአት ፍላጎት እና
ዝንባሌ፣በተለይ ከውጪ ወደ ውስጥ የሚገቡትን ፈተናዎችን ለመቋቋም መሣሪያው ተጋድሎ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ
ተጋድሎ የምንለው አላስፈላጊ ፍላጎቶችን መገደብ እና መቃወምንም ነው፡፡
አንዳንድ የዋሆች "እንዴት የተፈጥሮ ባሕርያችንን እንቃወማለን? ፍላጎታችንንስ እንዴት እንገታለን?" ይላሉ፡፡ ይህንን
የሚሉት ሙሉ ለሙሉ ለሥጋ ፍላጎታቸው ያደሩና ከመንፈሳዊ ሕይወት ውጪ የሆኑት ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች ቅዱስ
ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይመክራቸዋል ‹‹ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ስቀሉ›› ገላ 5÷24 ስለዚህ ሥጋችን የክርስቶስ
ቤተ መቅደስ በመሆኑ የሥጋ ባሕርያችንንና የሰይጣን ፍላጎቶችን በማራቅ ክርስቶስ እንዲከብርበት ማድረግ አለብን፡፡
‹‹ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን? በዋጋ
ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፣ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ›› ተብለናል፡፡ 1ቆሮ 6÷19—20
ወዳጄ በውድቅት ሌሊት ሰው በተኛበት አንተ በክርስቶስ ፊት እንቅልፍህን መስዋዕት አድርገህ ስትጸልይ ይሄ ተጋድሎ ነው፡፡
በተለይ ያስለመድከውን ጸሎት ላለመተው በምታደርገው ብርቱ ትግል፡፡ ሰው ረክሶ ቁስ ነግሶ ባለበት ጊዜ አንተ እንዳቅምህ
ሰውን መርዳትህ ተጋድሎ ነው፡፡ ንስሐ ገብተህ ዳግም በኃጢአት እንዳትረክስ፣ ቆርበህ ላለማፍረስ ከሥጋህ ጋር
የምትገጥመው ጦርነት ትልቅ ተጋድሎ ነው፡፡ በእንዲህ ትግል ውስጥ ላለኸው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይልኃል፡፡ ‹‹መልካም
ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትዕዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ›› 1ጢም 1÷18
ሰይጣን ታስሮ በተፈታበት፣ በታላቅ ቁጣ ወደ እኛ በመጣበት /ራዕ 12÷12/ የዝሙት ሰደድ እሳት ዓለማዊውንም
መንፈሳዊውንም በፈጀበት በዚህ ጊዜ እራስን ከዝሙት ጠንቅ መጠበቅ የዘመናችን ተጋድሎ ነው፡፡ ሰዎች ከፈጣሪያቸው
ይልቅ ገንዘብን በወደዱበት፣ ባመለኩበት ጊዜ አንተ ትልቁ ገንዘቤ ፈጣሪዬ ነው ብለህ በፍጹም ልብህ ፈጣሪህን ወደህ፣ ሕጉን
አክብረህ ከኖርክ በእውነትም ትልቅ ተጋድሎ ላይ ነህ፡፡
በጽኑ ሕመም ተይዘህ፣ አሉኝ ነበሩኝ የምትላቸውን ነገሮችን አጥተህ፣ የሰይጣንን የፈተና በትር፣ የሰውን የመከራ ቀንበር፣
ተሸክመህ ፈጣሪህን ተጠግተህ፣ በደረሱብህ ነገሮች ሁሉ ፈጣሪ ላይ ከማጉረምረም፣ ‹‹የለም›› ‹‹ዝም አለኝ›› ከሚለው
ምሬት ወጥተህ በምስጋና፣ በነገ የተስፋ ጎዳና ላይ ካለህ እንደ ኢዮብ በተጋድሎ በማበብ ላይ ነህ፡፡ ኃጢአት አስመርሮህ
ቅድስና ናፍቆህ ንስሐ ስትገባ፣ በተውከው ኃጢአት ዳግም ስትወድቅ ከዛም ተመልሰህ በጸጸት ንስሐ ስትገባ፣ በዚህ ሂደት
ለረጅም ጊዜ በመውደቅና በመነሳት ውስጥ የምታደርገው ትግል፣ አንድ ቀን የትንሣኤህን ድል እስኪያሳይህ ተስፋ
ካልቆረጥክ ብርቱ ተጋድሎ ውሰጥ ነህና በርታ፡፡ መጋደልህም እስከ ሞት ድረሰ በመዋጋት ይሆናል፡፡
ወዳጄ የትኛውም መንፈሳዊ ሰው ማለትም በማዕረግና በስልጣን ላይ ያለ ቢሆንም የክብር አክሊልን የሚቀዳጀው በክብሩ፣
በስልጣን በትሩ ሳይሆን በተጋድሎ ነው፡፡ ጸጋ ያለው በማዕረግ እና በስልጣን ውስጥ ሳይሆን በመልካም ተጋድሎ ውስጥ
ነውና፡፡ ‹‹እኔ ከሰዎች በክብር፣ በመንፈሳዊ ስልጣን ከፍ ያልኩ ነኝ›› ብሎ ከተጋድሎ መራቅ በራስ ላይ ማፌዝ በነፍስም ላይ
መጫወት ነው፡፡ እንዲህ የሚያስበውን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፣ እንደሚገባ አድርጎ
ባይታገል የድሉን አክሊል አያገኝም›› በማለት ይገስጸዋል፡፡ 2ጢሞ 2÷3÷5
እዚህም ላይ መንፈሳዊ ጸጋንና መንፈሳዊ ሥልጣንን ማጥራት መለየት አለብን። የእኛም ችግር መንፈሳዊ ሥልጣንን እንደ
ተጋድሎ ጸጋ ማየት ነው። መንፈሳዊ ሥልጣን ሰጪው እግዚአብሔር ቢሆንም መስፈርት አለው። ለተማረ፣ የሥጋ
ንጽህናውን ለጠበቀ፣ከነውርና ከነቀፋ የጸዳ ከሆነ ሊሾም ይችላል። አንዳንዴ ሥልጣኑ ጸጋ የሌለው ትከሻ ላይ ሲቀመጥ፤ ቤተ
ክርስትያንንና ምዕመናንን ሊያናውጥ ይችላል። መንፈሳዊ ጸጋ ግን ለምሳሌ ሐብተ ፈውስ፣ ብቃት፣ ሰማያዊ ምስጢራት
መመልከት፣ ትንቢት መናገር ወዘተ በሹመት ሳይሆን በብርቱ የተጋድሎ ሕይወት የሚገኝ ነው። ስለዚህ ሳይጋደሉ
በመንፈሳዊ ሥልጣን ብቻ መንፈሳዊ ጸጋ አለኝ ማለት "አንበሳውን ሳይገድሉ፣ቆዳውን ያስማማሉ" እንደሚባለው ተረት
መሆን ነው። አንዳንዶች ሳይጋደሉ መንፈሳዊ ሐብታትን ማግኘት ይሻሉ። ይሄ የዋህነት ሳይሆኑ ሞኝነት ነው። እንኳን
ከፈጣሪ ከዓለምም ሐብት ለማግኝት ጠንክሮ መሥራት፣እጅጉን መልፋት መውረድ መውጣት ይጠይቃል።
ጌታችን በገዳመ ቆሮንጦስ በጾም በጸሎት ድካም ውስጥ ያለውን መንፈሳዊ ብርታት እና በረከት እንዲሁም ሰይጣንን ድል
መንሳት፣ በመጨረሻም የመላእክትን አገልግሎት ማግኘት እንደምንችል አሳይቶናል። ማር 1÷12—13, ሉቃ 4÷1—13
ጌታችን የወንጌልን አገልግሎት በስፋት የጀመረው ከገዳመ ቆሮንጦስ ከተጋድሎ በኋላ ነው፡፡ ዝናውም በገሊላና በዙሪያው
ባለው አገር የወጣው ከገዳመ ቆሮንጦስ በመንፈስ ኃይል ሲወጣ ነው፡፡ ሉቃ 4—14 ይህ አብነቱ ዛሬም ለእኛ ትምህርት
ስለሆነ መንፈሳዊ ኃይልን የምንላበሰው በተጋድሎ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ የተጋድሎ ትልቁ ጥቅሙ ኃጢአትንና ሰይጣንን
በመዋጋት፣ የሥጋ ሥራን በማስወገድ በምትኩ የመንፈስ ፍሬን እናገኛለን፡፡ እነርሱም ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣
ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የዋህነት፣ ራስን መግዛት ናቸው፡፡ ገላ 5፥22-23 እነዚህንና ሌሎችንም የመንፈስ ፍሬ የምናገኘው
በተጋድሎ ነው፡፡
ተጋድሎአችን በአንድ በኩል ኃጢአትን ከእኛ ለማስወገድ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የመንፈስ ፍሬ የተባሉት እና ሌሎችም
ጸጋዎች ከእኛ ጋር እንዲሆኑ አጥብቀንም እንድንይዛቸው ያደርገናል፡፡ በዚህ የተጋድሎ ሕይወታችን የኃጢአትን ሥራ
እያስወገድን የጽድቅን ሥራ ደግሞ እንድናሳድግ ይረዳናል፡፡ ተጋድሎን እየወደድክ እየለመድክ ስትመጣ እንደ ቅዱሳን
የብቃት ማዕረግ እና ደረጃ ላይ ትደርሳለህ፡፡ በብርቱ ብትጋደል አሥሩ መዓርጋት ከሚባሉት ውስጥ ማግኘት የሚገባህን
ማዕረግ ታገኛለህ። እነሱም ፦
ጽማዊ፦ ዝምታ የልብና የአፍ ፀጥታ፣አለመታወክ
ልባዊ፦ አስተውሎ መናገርና መሥራት
ጣዕመ ዝማሬ፦ በደስታ ያለግዴታ ሳይሰለቹ ፈጣሪን ማመስገን
አንብዕ፦ ያለማቋረጥ ሥጋዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ለቅሶ ለኃጥአን ለአገር…
ኩነኔ፦ ሥጋን ለነፍስ ማስገዛት፣ነፍስን ለፈጣሪ ማስገዛት
ነጽሮተ መላእክት፦ መላእክትን ከእነሥራቸው ማየት
ሑሰት፦ በቅጽበት ያሰቡበት መድረስ
ተሰጥሞ ብርሃን፦ በሚያስደንቅ ብርሃን ውስጥ መስጠም፣ከጨለማ መሰወር
ፍቅር፦ ኃጥእ ጻድቅ አማኒ፣ ዘመድ ባዳ ሳይሉ ሁሉን በአንድ መውደድ
10. ነጽሮተ ሥላሴ {ከዊነ እሳት} ሥላሴን በአንድነት በሦስትነት በኩሩቤል ዙፋን ላይ ሆኖ ማየት/እንደ እሳት ማቃጠል/
ወዳጄ እስኪ ከላይ ከተጠቀሱት መዕረጋት እስኪ አምስተኛ ደረጃን ተመልከት። የመንፈሳዊ ሕይወት ትልቁ ጸጋ ሥጋን ለነፍስ
ማስገዛት ስለሆነ ይህንን በተጋድሎ ማድረግ ከቻልክ አንተ 5ኛ ደረጃን ማግኘት ትችላለህ፡፡ ሰዎችን በዘር፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣
በጽድቅና በኃጢአት ሥራቸው ሳትለይ ከወደድካቸው 9ነኛ ማዕረግን ማግኘት ትችላለህ፡፡ አየህ ይህን ስታነብ "ማዕረጌ
ስንተኛ ነው?" ብለህ እራስህን ትጠይቃለህ። ከአሥሩ ማዓርጋት በአንዱ እራስህን ካላገኘህ እራስህን ትወቅሳለህ፤ አልያም
ማዓረገ ቢስ ትሆናለህ፡፡ ቢያንስ ከአስሩ ማዕረጋት ሁለቱን ማግኘት ትልቅ መንፈሳዊ ስኬት ነው። ይህን የምልህ ከተጋህ
ከተጋደልክ ማዕርጎቹ የተጡት ላንተ ነውና ሌሎችንም ማግኘት ትችላለህ።
በዚህ ዘመን ትልቁ ተጋድሎ ንጽሐ ሥጋን ለመጠበቅ የምናደርገው ተጋድሎ ነው፡፡ ይህም የሥጋን ምኞትንና ሥራን፣ የዓይን
አምሮትንና የልብ መሻትን የምንከላከልበት ነው፡፡ ይህም ተጋድሎ ራስን የመግዛት ተጋድሎ ይባላል። ራስን ለመግዛት
የውጪ ተጽዕኖ ስለሚበዛ ፈተናው ይከብዳል፡፡ ፈቃደ ሥጋን ተቆታጠርክ ማለት የጽድቅ ተገዢ ትሆናለህ፡፡ ግን በዚህ ሂደት
እራስን ለመግዛት ራስን ማወቁ መልካም ነው፡፡ ራስህን ስታውቅ ስትመረምር ጠንካራና ደካማ ጎንህን ለይተህ ካወቅህ
በተለይ የምንፈተንበትን ነገር ካወቅን መፍትሔውና መድኃኒቱ በእጃችን ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው ደካማ ጎኑን ካወቀ የችግሩን
ግማሽ መፍትሔ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ችግሩን በጸሎት ለእግዚአብሔር እያጋራን፣ ከእኛ ለተሻሉት በጸሎት ለበረቱት
እያማከርን፣ በንስሐ እየተጋን፣ ፈተናችንን ለመከላከል መትጋት ያስፈልገናል፡፡
እነዚህን መንፈሳዊ ተግባራት በትጋት እያደረክ ራስህን በአንድ ጊዜ ለመግዛት ትቸገራለህ፡፡ ራስን መግዛት ለረጅም ጊዜ
የሚቆይ የየዕለት ልፋት ነው።ስለዚህ ራሳችንን ለመግዛትና ለመቆጣጠር ልምምድ ትዕግስት ያለመታከት መጋደል
ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዶች በተጋድሎአቸው ወይም ተጋድሎ እንደ ጀመሩ የተጋድሎአቸውን ውጤት በራሳቸው ላይ ቶሎ ማየት
ይፈልጋሉ፡፡ በተጋድሎ ሲበረቱ ምናልባትም የእግዚአብሔር በራዕይ/በሕልም/ መገለጥ፣ ተአምራትን ማድረግና ማየት
ወዘተ… ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ምኞት ለከፋ ውድቀት ይዳርጋል፡፡ ምክንያቱም በተጋድሎዋቸው መገለጥንና ተአምራትን ለማየት
መጓጓት ማለት ባደረጉት ነገር እየታበዩ ወይም ለራሳቸው ትልቅ የጽድቅ ቦታ እየሰጡ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ
ትምክህት ይባላል፡፡
ወዳጄ ተጋድሎህን በገሃድ ስትጀምር በስውር የሚያይህ ፈጣሪህ ዋጋህን ስለማያስቀር በተጋድሎ በርታ እንጂ ሌላ ከበሬታ
አትሻ፡፡ ተጋድሎህን ከፍጻሜ አድርስ እንጂ ከተአምር ለመቋደስ አትጓጓ፡፡ ተጋድሎህ ለራስህ ሐሴት ለሰይጣን ጦርነት ስለሆነ
የክብርን አክሊል በእምነትህ ለመቀበል ታገል፡፡ ያለ ትምክህት በሐሴት የሚጋደሉትን ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹የእምነታችሁን ፍጻሜ
እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሴት ደስ ይላችኋል›› ይላቸዋል፡፡ 1ጴጥ 1÷8—9
በተጋድሎህም ጥለኸው የምትሄደውን ሳይሆን ይዘኸው የምትሄደውን ጸጋ ታተርፍበታለህ፡፡ ስለዚህ የዘልማዱን መንፈሳዊ
አኗኗር ተውና ከክርስቶስ ጋር አንድ የሚያደርግህን፣የመንፈስ ቅዱስ ሱታፌ የሚያሰጥህን የዘውትር ጥረት የሚጠይቀውን
የተጋድሎ ሕይወትን መለማመድን ምረጥ። ከክርስቶስ ጋር በመንግሥቱ ለመኖር፤እንደ ቅዱሳን በተጋድሎ መስመር ተጓዝ!
ተጋድሎ የነብርን ጭራ አይዙትም ከያዙት አይለቁትም ነውና እንዳቅምህ የያዝካትን ተጋድሎ አትተው፡፡
"መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል" 1ጢሞ 6÷12
‹‹ከክርስቶስ ጋር እንዴት እንኑር?›› ከሚለው መጽሐፌ የተወሰደ፡፡
‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል›› ት.ሆሴ 4÷6
‹‹ከትውልዱ ማን አስተዋለ?›› ት.ኢሳ 53÷8
አንብበው ሲጨርሱ ሼር በማድረግ ለወዳጆ ያዳርሱ፡፡
ጥሩ 3/5/11 ዓ.ም
አዲስ አበባ
መተት
/ስውር ትውልድ አውዳሚ አጋንንታዊ ክፉ ተግባር/
መተት ምንድን ነው?
ክፍል አንድ
በቀሲስ መ/ር ሄኖክ ወ/ማርያም
ተወዳጆች ሆይ በዚህ ተከታታይ ትምህርት እራሳችንን የምንፈትሽበት፣የአጋንንትንና የሰዎችን የክፋት ጥግ የምናይበት
ብሎም የምንጠነቀቅበት ይሆናል፡፡ የዚህ ትምህርት ዋና አላማ ሰዎች ሰዎች በጥርጣሬ እንዲያዩና በአጉል ፍረጃ ያለ ስም ስም
እንዲሰጣጡ ሳይሆን የአጋንንትን ክፋትና ተንኮል አውቀው ከችግራቸው እንዲወጡ ነው፡፡ ብዙዎቻችን በአጋንንት እና
ከአጋንንት የባሱ ሥጋ ለበስ አጋንንት በሚመስሉ ሰዎች ብዙ ነገራችንን በአጋንንታዊ ክፋት በማበላሸት ይጎዱናል፡፡ እኛም
ይህንን ሳናውቅ በስውር ተጎድተን ብዙ ነገራችንን ተነጥቀን ግን ለዚህ ሁሉ ችግር መፈጠር አጋንንት ሳይሆን እግዚአብሔር
ይመስለናል፡፡ በዚህም በሥጋዊም በመንፈሳዊ ሕይወት የተስፋ መቁረጥ ሸለቆ ውስጥ ወድቀን መውጣትም አቅቶን
እንቸገራለን፡፡ ስለዚህ በዚህ ትምህርት የአጋንንትን የውጊያ ስልት እና ከእሱም ፈተና የመውጫ ብልሃት፤የሰውንም የተንኮል
እና የምቀኝነት ጥግ እናይበታለን፡፡ የቅዱሳን አበው አምላክ እግዚአብሔር እና የአንድዬ እናት ወለላይቱ እማዋይሽ ድንግል
ማርያም ምስጢሩን ይግለጹልን፡፡
መተት ቃሉ የግዕዝ ሲሆን ‹‹መተት›› የሚለውን ቃል ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ላይ
‹‹መምታት፣መመታት፣የማይታይ ኅብእ ረቂቅ፣ሕማም፣መቅሰፍት›› በማለት ይተረጉሙታል፡፡ ባህሩ ዘርጋው ‹‹ዘርጋው
ከፍተኛ የአማረኛ መዝገበ ቃላት›› በተባለው ላይ ‹‹መተት›› የሚለውን ‹‹አዚም፣ድግምት፣አስማት፣አፍዝ አደንዝዝ፣በሰው
ላይ ጉዳት ለማድረስ፣የራሱ ጉዳይ እንዲፈጸምለት በተለያዩ ነገሮች /በልብስ፣በቤት፣በቁሳቁሶች፣በምግብ …/ ላይ
የሚያስደርገው፣የሚያደርገው ድግምት›› በማለት ይተረጉማል፡፡ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ‹‹መተተኛ››
የሚለውን ቃል ‹‹በርኩስ መንፈስ ኃይል ልዩ ልዩ ድንቅ ነገር የሚሠራ›› በማለት ይተረጉመዋል፡፡ ስለዚህ መተት ማለት
በአጋንንታዊ ክፉ ጥበብ የአንድን ሰው ሕይወት ለማጥፋት፣ለመጉዳት፣እድሉን/ትዳሩን፣እውቀቱን፣ገንዘቡን ጤናውን
ወዘተ/ ለማበላሸት፣ደስታውን ለማጠልሸት እና ለመንጠቅ የሚደረግ ክፉና በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላና የሚያስጠላ
መናፍስታዊ ተግባር ነው፡፡
ወዳጆቼ ስለ መተት እና ስለ አስማት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ ዳራውን ብናይ የሰው ልጆች መተት እና አስማትን መጠቀም
የጀመሩት ገና በጠዋቱ ነው፡፡ በሕገ ኦሪት ሳይሆን በሕገ ልቦና የኖረው ያዕቆብ ‹‹በያዕቆብ ላይ አስማት የለም›› ተብሎ
መጻፉን ስናይ ያስገርመናል፡፡ ምክንያቱም ይህ አጋንንታዊ ጥበብ የሰው ልጅ በቅጡ ሃይማኖትን ባልያዘበት፣ፈጣሪውን
በአግባቡ ባላወቀበት እና ባላመለከበት ዘመን መጀመሩ ነው፡፡ /ዘኅ 23÷23/ ያዕቆብ በዚህ ምድር ላይ 147 ዓመት ከኖረ
በኃላ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ1871 ዓመተ ዓለም አርፏል፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ መተት እና ድግምትን ለተንኮል መጠቀም
የጀመረው ከዛሬ አምስት ሺህ ዓመታት በፊት ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መተት እና ስለ መተተኛ በደንብ ተገልጿል፡፡ መተት መተተኛ የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን
ውስጥ ሰባት ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ /ዘጸ 22÷18‚ ዘዳ 18÷11‚ 2ኛ ዜና 33÷6‚ 2ኛ ነገ 9÷22‚ ት.ሚክ 5÷12‚ ት.ናሆ 3÷4‚ ት.ኢሳ
47÷9/ ድግምት የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን ሁለት ጊዜ ተገልጿል፡፡ /ዘዳ 18÷11‚ ት.ኢሳ 19÷3/
አስማት እና አስማተኛ የሚለው ቃል ደግሞ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ላይ አሥራ አንድ ጊዜ በሐዲስ ኪዳን ላይ ሦስት ጊዜ
ተገልጿል፡፡ /ዘሌ 19÷26‚ ዘኅ 23÷23‚ ዘኅ 24÷1‚ ዘዳ 18÷11‚ 2ኛ ነገ 21÷6‚ 2ኛ ዜና 33÷6‚ ት.ኢሳ 3÷3‚ ት.ኤር 8÷17‚ መዝ
57÷5‚ ት.ኢሳ 57÷3‚ ት.ዳን 2÷10‚ ራዕ 18÷28‚ 21÷8 እና 18÷23 በሚገባ ተቀምተጧል ይመልከቱ/
አንዳንድ ያልታደሉት ስለ መተት በዚህ ደረጃ በእጃቸው ባለው በሚያነቡት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጽፎ ስለ መተት ሲነገር
የፈጠራ ትምህርት ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ግን መተት እና ድግምት በአሁን ሰዓት ትውልድ እየጠፋበት፣ቤተሰብ እና ትዳር
እየፈረሰበት፤ግን ያላወቅነው ብናውቀውም ቸል ያልነው አጋንንታዊ አውዳሜ መሣሪያ ነው፡፡ ዛሬ በየገዳማቱ፣በየጸበሉ
ያሉትን እህት ወንድሞቻችንን ብንመለከቱ መተት ስንቱን ከቤት አስወጥቶት፤ሥራውን፣ትምህርቱን፣ትዳሩን የነገ
ተስፋውን አስትቶት እያንከራተተው ይገኛል፡፡
ችግሩ መንፈሳዊ እውቀት አለን የምንል ሰዎች የአጋንንት ተንኮል እና ክፉ አሠራር ተረት ተረት ስለሚመስለን ካለንበት ደረጃ
ዝቅ ብለን በሺዎች የሚቆጠሩትን በመተት የሚሰቃዩትን ሰዎች ካላየን ልንረዳው አንችልም፡፡ ይህን ዓይነት ትምህርት
አንዳንዶች ሲሰሙ መንፈሳዊ ብዕራቸውን በማንሳት የአጋንንት ተንኮል ከማጋለጥ ይልቅ ሰውን ለመዘርጠጥ ሲጠቀሙበት
እናያለን፡፡ ስለ መናፍስት ተንኮል እና ውጊያ ሳያውቁ፣በስድብ ለሚራቀቁ ወንድም እህቶቼ መልስ በመስጠት ውድ ጊዜዬን
ማባከን ስለማልፈልግ ‹‹ጌታ ሆይ ባለማወቅ ነውና የሚያደርጉት ይቅር በላቸው›› እላለሁ፡፡
የአጋንንት ምስጢር ሲጋለጥ የአጋንንት ጀብድ የተሰበከ የሚመስላቸው፤ስለ አጋንንት ተንኮልና ውጊያ በትምህርት መልክ
ሲሰጥ፣ለምን አንደበታቸው ወደ ስድብ እንደሚለወጥ ብናውቅም አንዳንዶች አጋንንቱ ሲነካ እነሱ የተነኩ ይመስል
በተቃራኒ ጎራ ለአጋንንት ጥብቅና ሲቆሙ፣አድመው ሲያሳድሙ ማየት ቢያሳዝንም አይገርምም፡፡ ምክንያቱም አንዱ
የአጋንንቱ ውጊያ መንገድ በሰው እያደረ ለምን ተነካው እያለ መቆጣት እና ስም ማጥፋት ነው ሥራው፡፡
ልብ አላሉም፣ገድላቱንና ድርሳናቱን አልተመለከቱም እንጂ እነዚህ ቅዱሳት ገድላት እና ድርሳናት የአጋንንትን ተንኮል እና
ክፋት፣ብሎም የውጊያ ስልት ነው የሚያስተምሩን፡፡ የትኛውም ቅዱስና ጻድቅ በአጋንንት ሳይፈተን፣ሥጋዊ መከራን
ሳይቀበል የበቃም፣ሰማያዊ ክብርም ያገኘም፣ቃል ኪዳንም የተቀበለም የለም፡፡ የቅዱሳን ጸጋ እና ሰማያዊ ዋጋ የሚፈተነው
በአጋንንት ውጊያ መሆኑን ካልተረዱ እምነት ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት ብቻ ነው ያላቸው ማለት ነው፡፡ እነዚህ
ሰዎች ብዙ ሊሉ ስለሚችሉ እነሱን ተወት አድርገን ቢቻል በአጋንንት እና በመተት የተያዘው ትውልዳችን ሰማያዊ ዕዳ
እንዳይሆኑብን የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይሻላል፡፡
ጌታችን በሥጋ ማርያም ተገልጦ ወደዚህ ምድር የመጣበት ዓላማ የሰውን ልጆች ለማዳንና የሰው ልጆችን በማሳት፣ከገነት
ለመውጣት ምክንያት የሆናቸውን የዲያቢሎስን ሥራ ለማፍረስ ነው፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ ሰማያዊ ክብሩን ያጣው፣ከገነት
የተባረረው በዲያቢሎስ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ የጌታ አመጣጥ ሰውን ለማዳንና የዲያቢሎስን ሥራ ለማፍረስ ነው ማለት
ነው፡፡ ይህንንም ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹የዲያቢሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ›› ብሎናል፡፡ /1ኛ ዮሐ
3÷9/ ወዳጆቼ እኛ የዲያቢሎስን ሥራ ማፍረስ ባንችልም የተንኮል ሥራውን፣የክፋት ውጥኑን ብናጋልጥ፣ለምዕመናኑ
ብናሳውቅ ምንድነው ጥፋቱ?
ተወዳጆች ሆይ ስለ መተት እየጻፍኩ ‹‹ድግምት እና አስማት ከመተት ጋር ምን አገናኘው?›› ብትሉ መተት፣ድግምት እና
አስማት እንደ ነፍስ እና ሥጋ ናቸው፡፡ መተት ለመሥራት ድግምት እና አስማት ስለሚያስፈልጉ የራሳቸውም ቁርኝት
ስላላቸው አንዱ ከሌለ አንዱም ስለማይኖር ለግንዛቤም ጭምር ነው፡፡ በአጭሩ መተት የሚሠራው በድግምት ነው፡፡
ለምሳሌ አንድ ሰው ላይ መተት ሲሠራበት የሚሠራው ሰው ወይም ጠንቋይ ድግምት እና አስማት ያስፈልገዋል፡፡
ድግምት፦ ማለት መናፍስት የሚጠሩበት፣የሚጎተቱበት፣የሚቀርቡበት አጋንንታዊ ጥበብ ነው፡፡ አስማት ማለት በሁለት
ይከፈላል፡፡ አንደኛው አጋንንታዊ ትርኢት የሚያሳዩበት፣አስደናቂና ምትሃታዊ ነገር የሚያደርጉበት ሲሆን ሁለተኛው
አጋንንቱን የሚጠሩበት፣አስረው የሚያናግሩበት፣የሚያዙበት አጋንንታዊ ኃይል ያለው ስም ነው፡፡ ግልጽ እንዲሆንላችሁ
በድርሳነ ሚካኤል እና በድርሳነ ገብርኤልና በሌሎችም ድርሳናት ላይ እንዳሉት ሕቡዕ ስም ወይም ስመ አምላክ ያለ፤ግን
የአጋንንት ልዩ ስም የሆነ ማለት ነው፡፡ እነዚህን አጋንንታዊ ስሞች ደጋሚዎች ብቻ ናቸው የሚያውቋቸው፡፡
በዚህ ውስጥ ገቢር እና ግብር የሚባል አለ፡፡ ገቢር መተቱ ወይም ድግምቱ እንዲሠራ የሚደረግበት ቅድመ ዝግጅት ነው፡፡
ለምሳሌ የተለየ እፅዋት፣አረቄ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ግብር የሚባው አስደጋሚው በሚያስደግመው ሰው ላይ የሚያወጣው
ወጪ ነው፡፡ ይህም ለደጋሚው የሚከፈለው ገንዘብ እና ሌላም ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ ገንዘቡም እንደ መተቱ ዓይነት ከጥቂት
እስከ መቶ ሺዎች ሊሆን ይችላል፡፡ ተወዳጆች ሆይ ሰው ሰውን ለማጥፋ፣የሰውን ሕይወት ለማበላሸት፣እድሉን ለማኮላሸት
የሚሄድበትን ርቀት ልብ አላችሁ?
እግዚአብሔር ለሙሴ ‹‹መተተኛይቱን በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድላት›› ብሎታል፡፡ /ዘጸ 22÷18/ እንዲሁም
‹‹አስማተኛም፣መተተኛ፣በድግምት የሚጠነቁልም፣መናፍስትንም የሚጠራ፣ጠንቋይም፣ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ
አይገኝ›› በማለት አስጠንቅቆታል፡፡ /ዘዳ 18÷11/ ልበ ደንዳናው ፈርዖን የእግዚአብሔርን ተአምራት በሙሴ ላይ ሲገዳደር
የነበረው በመተተኞች ነበር፡፡ በተለይ ሙሴ በእግዚአብሔር ኃይል ተአምራት ሲያደርግ ፈርዖን ደግሞ
መተተኞችን፣ጠንቋዮችን፣አስማተኞችን ጠርቶ በአጋንንታዊ ጥበብ በትራቸውን እባብ እያደረጉ የፈርዖን ልብ ከባልጩት
ድንጋይ ይልቅ ሲያጸኑት፣በእግዚአብሔር ተአምራት እንዳያምን ሲያደርጉት፣በአስማታቸው ሲያዘናጉት እንደነበር ነብዩ ሙሴ
ከትቦልናል፡፡ /ዘጸ 7÷11-12/
እስራኤል በመተት እግዚአብሔርን ባስቆቱት ጊዜ ‹‹የወላድ መካንነትና መበለትነት በድንገት ይመጣብሻል፣ስለ መተቶችሽ
ብዛትና ስለ አስማቶችሽ ጽናት ፈጽመው ይመጡብሻል›› በማለት መተትን እንደሚያበዙ፣በጨለማ መንገድም እንደሚጓዙ
በዚህም ነብያትን፣ነገሥታትን ወልዳ እንዳልወለደች መካን እንደምትሆን ነግሯታል፡፡ /ት፣ኢሳ 47÷9/
በባቢሎን በስተደቡብ በኩል የነበረው አገር ከላውዴዎን ይባላል፡፡ በዚህች አገር የሚኖሩ ሕዝቦች ደግሞ ከለዳውያን
ተብለዋል፡፡ ከለዳውያን በጥንት በከዋክብት ጥናት፣በአስማት እና በመተት እንዲሁም በአምልኮ ጣዖት ይታወቁ ነበር፡፡
/ት.ዳን 2÷10‚ 8÷10/ በከነዓንም ሟርተኛች፣አስማተኞች፣መተተኞች፣ሞራ ገላጮች፣በድግምት የሚጠነቁሉ፣መናፍስትን
የሚጠሩና ሙታን ሳቢዎች ነበሩ፡፡ /ዘዳ 18÷9-14‚ 1ኛ ሳሙ 28÷14/
የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴም ‹‹መተተኛም ነበረ›› ተብሎ ተጽፏል፡፡ ምናሴ በኢየሩሳሌም ለሃምሳ አምስት ዓመት ነግሶ ነበር፡፡
ምናሴ አባቱ ያፈረሰውን የበኣልን መሠዊያ መልሶ በመሥራት ማምለክ ጀመረ፡፡ በዚህ በጣዖት አምልኮ ውስጥ ገብቶ ነው
ወደ መተት ሕይወት ውስጥ የገባው፡፡ የምናሴን ክፉ ሥራ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ሞራ ገላጭም ሆነ፣አስማትም
አደረገ፣መተተኛም ነበረ›› በማለት ተግባሩን አስረግጦ ጽፎልናል፡፡ /2ኛ ዜና መዋ 33÷6/
ምናሴ በአስተማቱ በመተቱ፣በጣዖት አምልኮቱ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ
ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሰዎች አብዝቶ አሳተ፡፡ /2ኛ ዜና መዋ 33÷9/ በዚህ ሁሉ በምናሴ ጥፋት
እግዚአብሔር ተቀይሞት የአሦርን ንጉሥ የሠራዊት አለቃ አስነስቶበት በዛንጀር ተይዞ፣በሰንሰለት ታስሮ ወደ ባቢሎን
በምርኮ ሄደ፡፡ ምናሴም በጾም በጸሎት እራሱን በፈጣሪው ፊት አዋርዶ እግዚአብሔርን ይቅርታ ጠይቀ፡፡ አስማቱን፣መተቱን
ከሕይወቱ፤ጣዖቱን ከእግዚአብሔር ቤት አርቆ፣ከፈጣሪው ታርቆ ኖሯል፡፡
ሐብተ መርገም የነበረው የሕገ ልቦናው ሰው በለዓም መተተኛ ወይም አስማተኛ እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹አስቀድሞ
ያደርግ የነበረውን አስማት ይሻ ዘንድ አልሄደም›› በማለት በለዓም በፊትም እንደዚህ ዓይነት አጋንንታዊ ጥበብ ይጠቀም
እንደ ነበር የሚያሳይ ነው፡፡ /ዘኅ 24÷1/ ባለቅ በለዓምን ‹‹ያዕቆብን ርገምልኝ፣እስራኤልን ተጣላልኝ›› ሲለው በለዓም
አስማትን በአፉ አድርጎ ሳይረግም በፊት እግዚአብሔር ቃሉን በበለዓም አፉ አድርጎ ያዕቆብን እንዲመርቅና እንዲባርክ
ብሎም የክርስቶስን መወለድ ትንቢት እንዲናገር አደረገው፡፡ /ዘኅ 23÷16‚ 24÷1-9/
ወደ ገድለ ቅዱሳን ስንገባ በተለይም ዛሬ ዛሬ ጆሮ ጭው የሚያደርግ፣ለማመን የሚከብድ ሆኖ የምንሰማው በቅዱስ ላሊበላ
ላይ ቀድሞ የተፈጸመ ነው፡፡ ገድለ ቅዱስ ላሊበላ እንደሚነግረን ላሊበላ የአባቱ ልጁ የሆነች ክፉ እህት ነበረቸው፡፡ የዚህን
ቅዱስ ሰው እህት ገድሉ ‹‹እሷም በሥራዋ የከፋች፣የኤልዛቤል የግብር ልጅ፣የሄሮድያዳ ሁለተኛ ፣ወንድሙን የገደለ የቃየል
ወገን ናት›› በማለት ይገልጻታል፡፡ /ገድለ ላሊበላ ገጽ 51 ቁጥር 9/
የቅዱስ ላሊበላ ወንድም ኃርበይ ነግሦ በነበረበት ወቅት ወንድሙ ላሊበላ እንደሚነግሥ ትንቢት በሰማ ጊዜ ላሊበላ
መንግሥቱን ቀምቶ የሚወስድበት ስለመሰለው በላሊበላ ቀናበት ታወከም፡፡ አንድ ቀን ላሊበላ ሆዱን አሞት ኮሶ ጠጣ፡፡
የጠጣውም ኮሶ እጅጉን ስላደከመው ደክሞት ተኛ፡፡ የላሊባላ እህትም የሚገድል መርዝ በጽዋ መልታ ላከችለት፡፡ ላሊበላ
እንዲጠጣ የላከችለትን ገዳይ መርዝ ገድሉ ‹‹በስራይ የሚችሉት መስሏቸው ተጠበቡበት›› የሚለው ቃል ምን ያህል በመተት
ላሊበላ እንዲሞት መልፋታቸውን ያሳያል፡፡ ላሊበላም ጠላ መስሎት አንስቶ ከቤተሰብ ዲያቆን ለሆነው ልጅ ‹‹አስቀድመህ
ጠጣና ባርከህ ስጠኝ›› አለው፡፡ ቀምሶ መስጠት ልማድ ነውና፡፡ ዲያቆኑም ጠጣ ወዲያውም አስመለሰው ሞተ፡፡ ዲያቆኑ
ያስመለሰውን መርዝ ውሻ ላሰው ውሻውም ፈጥኖ ሞተ፡፡ ላሊበላም ዲያቆኑና ውሻው በእሱ ምክንያት እንደ ሞቱ አስቦ
ደረቱን እየደቃ እያለቀሰ ‹‹ወዮልኝ ይህ የመርዝ ጽዋ የተደረገ ስለእኔ አይደለምን፡፡ ዲያቆኑም ሆኑ ውሻው የሞቱት በእኔ
ምክንያት ነው፡፡ በደሌ በዝቶ በእኔ ምክንያት እሊህ ሞተዋልና›› በማለት ስራይ የተደረገበትን ወይም የተመተተበትን መርዝ
እሱም ጠጣ፡፡
ላሊበላም በጠጣው ስራይ እጅጉን ደከመና ሞተ፡፡ መላእክት ነፍሱን ወደ ሰባቱ ሰማያት አሳርገዋት፣እግዚአብሔር ጋር
አድርሰዋት፣ ብዙ ሰማያዊ ምስጢር አሳይተውት፣ጥበብን ገልጠውለት በሞተ በሦስተኛ ቀኑ ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋህደው
መለሱት፡፡ ቅዱስ ላሊበላ በእህቱ ምክንያት፣በንግስናው በመቅናት የተደረገበት ሥራይ ለሞት ቢያበቃውም ለበጎ ሆኖለት
ዛሬ አስደናቂ አሥረ አንዱን ውቅር አብያተ ክርስትያናትንና ተአምረኛ ገድሉንና ቃል ኪዳኑን አትርፎልናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ
የሰው ልጅ መተትን ስራይን ለተንኮል፣ሰውን ለመግደል ይጠቀም የነበረው ዛሬ ሳይሆን ከሺ ዓመታ በፊት ነው፡፡ ዛሬ በዚህ
በኃጢአት ዘመን ወንድም ወንድሙ ላይ፣እህት በእህት ላይ፣ጓደኛ፣ጓደኛው ላይ የሥጋ ዘመድ ቤተሰቡ ላይ ቢያስመትት
ሊደንቀን አይገባም፡፡ ይህ አይነት አጋንንታዊ ተንኮል በቅዱሳኑ ዘመን በቅዱሳን ላይ ይደረግ ነበረና፡፡
ወደ ኃያሉና ወደ ፍጡነ ረድኤት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሕይወት ጎራ ስንል አሳዛኝ ገድሉ እንደሚነግረን ሰባው ነገስታት
ሟርተኛ፣አስማተኛ፣መተተኛ በመሰብሰብ በድግም መርዝ እየመረዙ ቅዱስ ጊዮርጊስን የመተታቸው መሞከርያ አድርገውት
ነበር፡፡ ሰማዕቱ እምነቱና ጸሎቱ ከእነሱ መተት እና አስማት በላይ ስለሆነ አንድም ለተአምራት የሚሰጡትን መተት
በፈጣሪው ስም እያማተበበት ጭልጥ እያደረገ እየጠጣ የፈጣሪውን ኃይል ያሳያቸው እንደነበር አስገራሚ ገድሉ
ይተርክልናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በድዮቅልጥያኖስ ዘመን የዛሬ አንድ ሺ ሰባት መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ የኖረ ነው፡፡ በዛን
ዘመንም መተት በሰው ልጆች የተንኮል ሕይወት ውስጥ በሰፊውና በክፉው ነበር፡፡
በእኛም አገር በተለይ በነገሥታቱ ዘመን በቤተ መንግስት መተት እጅጉን ይዘወተር ነበር፡፡ መኳንንቱ፣መሳፍንቱ
ጠላቶቻቸውን ከሚያጠቁበት፣ከሚገሉበት ድምጽ አላባ መሣሪያ አንዱ መተት ነው፡፡ የበታች ሾሞችም ከላይ ያሉትን
የሚያስወግዷቸው በመተት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በእኛ አገር ታሪክ እከሌ የሚባል መሪ፣መኳንንት፣መሳፍንት፣ቀኝ አዝማች፣ግራ
አዝማች፣ፊት አውራሪ በመርዝ ነው የሞተው ብለን የምንሰማው በመተት የሞቱትን ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ ይህ መንግስት ያላወቀው፣ሊያውቀውም የማይችላው፣በሚያውቁትም ዘንድ ችላ የተባለው ግን ሰዎችን
የሚያጠፉበት፣የሕይወት እድላቸውን የሚያበላሹበት እና የሚነጥቁበት፣ትዳርን፣ቤተሰብን ስለሚያፈርሱበት፣በሰው ልጅ
ላይ ብዙ ጉዳት እና ኪሳራ ስለሚያደርሱበት ‹‹መተት›› ስለ ተባለው አጋንንታዊ እና ሰዋዊ ተንኮል በሰፊው እንማራለን፡፡
‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል›› ት.ሆሴ 4÷6
‹‹ከትውልዱ ማን አስተዋለ?›› ት.ኢሳ 53÷8
አንብበው ሲጨርሱ ሼር በማድረግ ለወዳጆ ያዳርሱ፡፡
ክፍል ሁለት
በሰው ላይ መተት ለምንና ለምን ተግባር ይሠራል?
መተት ለምን እኛ ላይ ይሠራል?
ስንት ዓይነት መተት አለ?
ይቀጥላል …
ጥር 13/5/11 ዓ.ም
አዲስ አበባ

You might also like