Memualat PDF

You might also like

Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 3

መሟላት

እሥራኤላውያን እንዲህ ይተርካሉ፡፡

በኢየሩሳሌም ከተማ የሚኖሩ ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ፡፡ አንደኛው ባለ ትዳርና የቤተሰብ አስተዳዳሪ፣ ሌላኛው ደግሞ
ላጤ ነበሩ፡፡ ሁለቱም የሚተዳደሩት በአንድ የእርሻ መሬት ነው፡፡ ጠንክረው በጋራ በመሥራት ያመርቱና ምርቱን በእኩል
ይካፈላሉ፡፡ በሥራና በኑሮ ያላቸው መተጋገዝና መጠቃቀም ለአካባቢው ሰዎች ሁሉ እጅግ የሚያሰቀና ነበር፡፡ አንደኛው
ለሌላኛው የሚያስበውን ያህል ለራሱ አያስብም ነበር፡፡

አንድ ቀን ላጤው ለባለ ትዳር ወንድሙ እንዲህ አሰበ፡፡ ‹‹ወንድሜ የቤተሰብ ኃላፊ ነው፡፡ ባለቤቱን፣ ልጆቹን፣ የባለቤቱን
ወላጆችና የቤቱን ሠራተኞች ማስተዳደር አለበት፡፡ ምርቱን ከእኔ ጋር እኩል መካፈል የለበትም፡፡ እርሱ ከእኔ የሚበልጥ
ምርት ማግኘት አለበት፡፡ ነገር ግን አሁን ከእኔ የተሻለ እህል ውሰድ ብለው አይቀበለኝም፡፡ ስለዚህ በሌላ መንገድ መርዳት
አለብኝ፡፡››

አውጥቶ አውርዶም በጎተራ ካለው የእርሱ እህል እየወሰደ ማታ ማታ ተደብቆ በወንድሙ ጎተራ ውስጥ ለማስቀመጥ ወሰነ፡፡
ማታ ማታ ተደብቆ በመውጣት ከራሱ ጎተራ ወደ ወንድሙ ጎተራ እህል ይገለብጥ ነበር፡፡ ነገር ግን ጠዋት ጎተራውን ሲያየው
እንኳንስ ሊጎድል ካለፈው የበለጠ ሞልቶ ያገኘው ነበር፡፡ ይህም እጅግ ይገርመው ነበር፡፡ ፈጣሪ በጎ ሥራዬን አይቶ
እየባረከኝ ነው ብሎም አመሰገነ፡፡

ባለትዳሩም እንዲሁ ለብቻው ‹‹ወንድሜ እንደ እኔ አላገባም፡፡ ለወደፊትም ከባድ ኃላፊነት ይጠብቀዋል፡፡ ትዳር መመሥረት
አለበት፣ ልጆች መውለድ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን የሚያገኘው ምርት በቂው አይደለም፡፡ እኔ የራሴን ኑሮ አደላድያለሁ፡
፡፡ እርሱ ግን ገና አዳጊ ነው፡፡ አሁን እርሱን የሚበልጠውን ምርት ውሰድ ብዬ ብነግረው አይቀበለኝም፡፡ ስለዚህ በድብቅ
ልረዳው ይገባኛል›› ብሎ አሰበ፡፡

ወንድሙ ለእርሱ የሚያደርገውን ያላወቀው ባለ ትዳሩ ወንድምም ሊነጋጋ ሲል እየተነሣ ከራሱ ጎተራ ወደ ወንድሙ ጎተራ
እህል ይጨምር ነበር፡፡ ጠዋት ሲነሣ ግን ጎተራው ሳይጎድል ያገኘዋል፡፡ ይህም ሁልጊዜ ይገርመዋል፡፡ መስጠቴን ተመልክቶ
ፈጣሪ ነው የሞላልኝ እያለም ያመሰግን ነበር፡፡

እንዲህ እያደረጉ ለብዙ ጊዜ ከኖሩ በኋላ በአንድ ሌሊት አንደኛው እህሉን ተሸክሞ ወደሌላው ጎተራ ሲሄድ በድንገት መንገድ
ላይ ተገናኙ፡፡ ሁለቱም በነገሩ ተገርመው ተቃቅፈው እየተላቀሱ የነበረውን ነገር ተነጋገሩ፡፡ ከበፊቱ ይልቅም ፍቅራቸው እጅግ
ጸና፡፡ እግዚአብሔርም ተገኝቶ ለዚህ ፍቅራቸው መታሰቢያ እንዲሆን በእነርሱ የእርሻ ቦታ ላይ ቤተ መቅደሱ እንደሚሠራ
ቃል ገባላቸው፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን ታላቁን ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ውስጥ የሠራው በእነዚህ ወንድማማቾች የእርሻ ቦታ
ላይ ነው ይባላል፡፡

ከፍቅር መገለጫዎች ዋናው መሟላት ነው፡፡ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ዘርዐ ያዕቆብ ሰው ማለት የሚሟላ ፍጡር ነው
ይላል፡፡ ሙሉ እንዲሆን እንጂ ተሟልቶ አልተፈጠረም፡፡ ለመሟላት ሌላ ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ሰው የፈለገውን ያህል የበቃ
የነቃ ቢሆንም ሙሉ ሰው ለመሆን ግን ሌላ ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ሰውን በመተቸት፣ ስሕተቱን በመግለጥ፣በመውቀስና
ጎደሎነቱን በማሳየት ከምናርመውና ከምናስተካክለው በላይ የጎደለውን በመሙላት እናስተካክለዋለን፡፡ የምንወደው ሰው፣
የምናስብለት ሰው፣ የምናወቀው ሰው፣ ማለት የምናሟላው ሰው ማለት ነው፡፡
በወዳጅና ወዳጅ ባልሆነ መካከል ያለው አንዱ ዋና ልዩነት አብሮ ከመብላት፣ አብሮ ከመጠጣት፣ ልቅሶና ደስታ ከመደራረስ፣
ከመደዋወልና ከመጠያየቅ፣ ከመዛመድና አብሮ ከመኖር የሚመጣ አይደለም፡፡ ሰውን ለምን እናውቀዋለን? ለምንስ ማወቅ
እንፈልጋለን? ለምንስ እንቀርበዋለን? ሰው ስለሆንን፣ የሚጠይቅ ኅሊና የሚያስብ ልቡና ስላለን ማወቅ የመጀመሪያው ነው፡፡
ይህንን መከላከል አንችልም፡፡ የግድ ከልዩ ልዩ ምንጮች ስለ አንድ ሰው እናውቃለን፡፡ ይህ ማወቅ ግን መተዋወቅን
አይፈልግም፤ መቀራረብንም የግድ አያመጣም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መተዋወቅ ነው፡፡ ይኼኛው መቀራረብን ያስከትላል፡፡
መስተጋብርን ይፈጥራል፡፡ በዚህ መልኩ የምናገኘው መተዋወቅ ኃላፊነትን ይወልዳል፡፡ የመሟላትን ኃላፊነት፡፡

መተዋወቅ ለመሟላት ካልሆነ ስለ ሰዎች ያለንን ፋይል መቀነስ ያስፈልገናል፡፡ ዐወቅኩት፣ ቀረብኩት፣ እገሌንኮ ዐውቀዋለሁ፣
እቀርበዋለሁ ለማለት መተዋወቅ አያስፈልገንም፡፡ ግንኙነታችን መሟላትን የማያመጣ ከሆነ ዕውቀት መቀነስ ታላቅ ብልሃት
ነው፡፡ ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት በሦስት መልኩ ብናደርገው ግንኙነታችን የታሰበበትና የተሟላ ይሆንልናል፡፡

የማናውቃቸው ሰዎች፡፡ እነዚህ ሰዎች ከኛ ጋር ለመተዋወቅም ሆነ በእኛ ለመታወቅ ዕድል የሌላቸው ወይም ዕድል የሌለን
ናቸው፡፡ የሚበዙትም እነርሱ ናቸው፡፡ በማወቃችን የምናተርፈው ወይም የሚያተርፉት ነገር ከሌለ አለማወቃችን ምንም
ጉዳት የለውም፡፡ ያገኙትን ሰው ሁሉ ስልክ የሚቀበሉ፣ ደግመው የማያገኙትን ሰው የሚተዋወቁ ሰዎች ሊያውቋቸው
በማይገቡ ሰዎች ፋይላቸውን የሚያጨናንቁ ናቸው፡፡

ሁለተኛዎቹ የምናውቃቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱ ሊያውቁንም ላያውቁንም ይችላሉ፡፡ ያ ደግሞ የእነርሱ ፋይል ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች የሥራ ባልደረቦቻችን፣ ጎረቤቶቻችን፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ደንበኞቻችን፣ ዕውቀትን የምንሸምትባቸው ሰዎች፣ በልዩ
ልዩ ምክንያት የምናገኛቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከእነርሱ የምንፈልገው፣ ለእነርሱም የምንሰጠው ነገር ስላለ እናውቃቸዋለን፡፡
አንዳንዶቹንም ማወቅ የግድ ይለናል፡፡ ሌሎቹን ደግሞ አለማወቅ አንችልም፡፡ እነዚህን ሰዎች የግድ መቀራረብ፣ መተዋወቅ፣
ወይም የተለየ ተግባቦት መፍጠር ላያስፈልገን ይችላል፡፡ ግንኙነታችን አንድን ጉዳይ፣ ተግባር፣ ኃላፊነት፣ መሥመር ወይም
ደግሞ ሁኔታ መሠረት ያደረገ ነውና፡፡

ሦስተኛው መተዋወቅ የሚባለው ነው፡፡ መቀራረብንና መግባባትን የሚያመጣው፡፡ በውስጡም መዋደድ ያለበት፡፡ ከላይ
በሚገኙት ሁለቱ መውደድ እንጂ መዋደድ የለባቸውም፡፡ የማናውቃቸውንም ሰዎች፣ የምናውቃቸውንም ሰዎች ልንወዳቸው
እንችላለን፡፡ ግንኙነት የሚያመጣው መዋደድ ግን ላይኖር ይችላል፡፡ እኛ ስለ እነርሱ እናስብ ይሆናል፣ እነርሱ ስለ እኛ
እንዲያስቡ አይጠበቅምና መተሳሰብ ላይኖር ይችላል፡፡ በመተዋወቅ ውስጥ ግን ሦስቱም አሉ፡፡ መግባባት፣ መተሳሰብና
መዋደድ፡፡ እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ወዳጃዊ ኃላፊነትን ያስከትላሉ፡፡ አንዱ ለሌላው በጎ መሆን፣ ስኬትና ደኅንነት ኃላፊነት
ይሰማዋል፡፡ ይህ ኃላፊነት ከመጠየቅ፣ ከመለመን ወይም ከመወትወት የሚመጣ አይደለም፡፡ ከመተዋወቅ የሚመጣ ራስ
ወሰድ ኃላፊነት ነው፡፡

ለሌላው ሕይወት የማይገደን ወይም ኃላፊነት የማይሰማን ከሆነ የተሻለው መንገድ ዕውቀት መቀነስ ነው፡፡ ለምን
እንቀራረባለን? ለምን እንወያያለን? ለምንስ የማንሸከመውን የሰው ‹ውስጥ› እናውቃለን? ለምንስ የማንጋራውን የሰው ችግር
እናውቃለን? ለምንስ የማንሞላውን ጉድለት እንሰማዋለን? ለምንስ የማናክመውን ቁስል እንመረምረዋለን? አንዳንድ ሰው
አመል ሆኖበት ‹‹ይህ ነገር አይመለከተኝም፣ ይህ ነገር ልሸከመው አልችልም፣ ይህንን ነገር መስማት የለብኝም፣ ይህ ነገር
የሰውየው የራሱ ብቻ ነው›› ማለት አይችልም፡፡ በሁሉም ነገር ውስጥ ይገባል፣ ሁሉም ነገር ይመለከተኛል ይላል፣ ሁሉንም
ነገር በዝርዝር ያውቃል፣ የሁሉም ሰው ጓዳ ዘው ይላል፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ኃላፊነት አይወስድም፡፡ ከማወቅና ሲወራ
አብሮ ከማውራት፣ ባስ ሲልም ‹ገመናን ከማጋለጥ› ያለፈ ሚናም የለውም፡፡ መሸሽ እንዲህ ካለው ሰው ነው፡፡

የሰሎሞን ቤተ መቅደስ በእነዚህ በመሟላት በሚኖሩ ወንድማማቾች እርሻ ላይ እንደተገነባው ሁሉ የኛም የትዳር፣
የወዳጅነት፣ የጓደኛነት፣ የሥራና የጉርብትና መቅደሳችን በመሟላት ላይ ቢመሠረት ኖሮ፣ ተባብሮ ከመውደቅ ተባብሮ ወደ
ማደግ፣ ተያይዞ ከመጠፋፋት፣ ተያይዞ ወደ መመንደግ፤ ጥሎ ከማለፍ ይዞ ወደማለፍ ይሸጋገር ነበር፡፡ ይኼው ሦስቱንም
ታላላቅ እምነቶች(እስልምና፣ ይሁዲነትንና ክርስትና) አስተሳሥሯል የሰሎሞን መቅደስ፡፡ ሁሉም እዚያ ቦታ አለው፤ ልብም
አለው፡፡ ሁሉም እዚያ ይጸልያል፤ ሁሉም ያንን ቦታ ያከብራል፡፡ መግባባትን ከመነጋገር በላይ ይበልጥ የሚያጠነክረው
‹መሟላት› ነው፡፡ አብሮ መኖርን አብሮ ከመሥራት በላይ ‹መሟላት› የተሟላ ያደርገዋል፡፡ ወዳጅነትን አብሮ ከመብላት በላይ
‹መሟላት› ያጸናዋል፡፡

መሟላት መጓደልን የሚያጠፋ ነው፡፡ በመሟላት የሚኖሩ ወዳጆች የሚሞሉትን ያህል ይሞላላቸዋል፡፡ ሳያጎድሉ መስጠት
የሚቻለው በመሟላት ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ተረት እዚህ ላይ ትዝ አለኝ፡፡ በወዳጁ ሀብት የሚቀና አንድ ጎረቤት ከወዳጁ
አሞሌ ጨው ይበደራል፡፡ብድሩን ክፈል ሲባል ‹‹አሞሌውኮ ድንጋይ ሆነብኝ›› ብሎ ይመልሳል፡፡ ያ ጎረቤትም ተንኮሉን
ቢያውቅም የሚያደርገው ስላልነበረው ዝም ብሎ ኖረ፡፡ አንድ ቀንም ‹እባክህ ሴት ልጅህ ባለቤቴን የድግስ ሥራ ታግዛት››
ብሎ ለመነውና የጎረቤቱን ሴት ልጅ ወሰደ፡፡ ልጂቱም ትመጣለች ተበላ ብትጠበቅ በዚያው ቀረች፡፡ ልጂቱን የወሰደው
ጎረቤትም ‹‹ልጂቱማ ዝንጀሮ ሆነችብኝ›› ብሎ መለሰ፡፡ ያም ድሮ በአሞሌው ላይ የሠራውን ያውቅ ነበርና ውጦ ዝም አለ፡፡

ከብዙ ጊዜ በኋላ ሁለቱም ጠዋት ከብት አውጥተው ሲያሠማሩ ተገናኙ፡፡ አስቀድሞም ልጁ ዝንጀሮ ሆነች የተባለበት አባት
እንዲህ ብሎ አንጎራጎረ፡-

‹‹ወይ ዘንድሮ ወይ ዘንድሮ

ልጄ ሆነች ዝንጀሮ››

አሞሌው ድንጋይ የሆነበትም

‹‹ወይ ጉባይ ወይ ጉባይ

አሞሌ ሆነ ድንጋይ››

ሲል መለሰ፡፡

የልጂቱ አባትም

‹‹አሞሌስ አለ ከጎታ

የልጄን ነገር እንዴታ›› ሲል ጠየቀ፡፡

የአሞሌው ጌታም፡-

‹‹አሞሌስ ካለ ከጎታ

ልጂቱም አለች ካጎቷ›› ሲል አበሠረው ይባላል፡፡ ስንሟላ እንጂ ስንባላ አናድግም፡፡

You might also like