Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 2

“አሸባሪነትን” ማን ያገኛታል...

ስለ ህዝቡ በፅናት የታገለ አይደለምን?


አቤ ቶኪቻው
abeto2007@yahoo.com

ወዳጄ እንዴት ሰነበቱልኝ? ሁሉ ሰላም ሁሉ መልካም ይሆን ዘንድ አጥብቄ እመኝልዎታለሁ። “አጥብቆ የተመኘ ከሰጠ እኩል ነው”
የሚለውን አባባልም እመርቅልዎታለሁ። አንተስ እንዴት ነህ? ካሉኝ፤ የእኔ ነገር እንግዲህ ገና ሚናው ያለየለት ስደተኛ አይደለሁ?
አንዴም ሲጨንቀኝ፣ አንዴም ሲጨምቀኝ ብቻ አለሁ እንደምንም፤ እግዜር የሰጠውን ሰው አልችል አይልም! እልዎታለሁ።
ይህንን ከመሰለው ሰላምታችን ቀጥሎ በአዲስ መስመር የዛሬው ጨዋታ ይጀመራል።

በመጀመሪያም የተረሱ አጫጭር ጨዋታዎችን እንቃመሳቸው፤

አንድ

ባለፈው ጊዜ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን ጥቂት አውግተን ነበር። ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስለ ብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት መከበር
ሲነግረን ብዙ ግዜ እንደ ማስረጃ የሚያቀርብልን ሙዚቃና ጭፈራውን ነው። ባለፈው ሳምንት ወዳጃችን ክንፉ አሰፋ “የብሔር
ብሔረሰብ መብት እስከ መጨፈር” ብሎ የፃፈውን ካነበቡ ነገሩ ብዙዎችን የከነከነ መሆኑን ያውቁልኛል። የመንግስት ሚዲያ የሆነው
ኢቲቪ ከዚህ የበለጠ መብት ከየት ይመጣል? እያለ የዶርዚኛ ውዝዋዜ፣ የኦሮምኛ ረገዳ፣ የአማርኛ እስክስታ የጉራጌ ጭፈራ እና
የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን ሙዚቃ ያስኮመኩመናል። ደግሞም፤ “ይህ ነፃነት በርካታ ዋጋ የተከፈለለት እና የብዙዎች ደም የፈሰሰለት
ነው” ይለናል። እኛም ጮክ ብለን እንጠይቃለን “ያ ሁሉ ትግል (ነጠላ ሰረዝ) ያ ሁሉ ደም መፋሰስ (ድርብ ሰረዝ) ኮንሰርት ለማዘጋጀት
ነበር እንዴ?” ብለን በትምህርተ ስላቅ እንጠይቃለን? ስንጨምርም እናንት በሰማህታት ደም እና ትግል የቀለዳችሁ ወዮላችሁ! እናላለን።

ሁለት

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሩ ዶክትር ቴውድሮስ አድሃኖምን ጆርጅ ቡሽ ሲያንቆለጳጵሷቸው ነበር። “በአፍሪካ አለ የሚባል የጤና ጥበቃ
ሚኒስቴር” ሲሉም አሞካሽተዋቸዋል። በርግጥ ጆርጅ ቡሽ ስለ ሀገሪቱ የጤና ሁኔታ በቂ መረጃ እንዳላቸው ጥርጣሬ አለኝ። ለምሳሌ
በቅርቡ “አንድም እናት በወሊድ አትሞትም” በሚባለባት ኢትዮጵያ እውቋ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ፅጌሬዳ ሀይሉ ለዛውም አዲሳባ ከተማ
ውስጥ ነው በወሊድ ምክንያት የሞተችው። በነገራችን ላይ ይቺ ጋዜጠኛ በህይወት ዘመኗ በተደጋጋሚ ጤና ጥበቃዎች በተለይ ከወሊድ
ጋር በተያያዘ ከቀልባቸው እንዲሰሩ ስትመክር የኖረች ነበረች። ምን ዋጋ አለው ለሌሎች የፈራቸው የወሊድ ክትትል ችግር የራሷንም
ህይወት ቀጠፋት። ዶክተር ቴውድሮስ የነዚህ ሰዎች አለቃ ናቸው። “አንድም ሰው አይሞትም!” እያሉ የሚፎክሩ ግን በየቀኑ ሰው
የሚገድሉ ሰዎች አለቃ! ነገር ግን ይህ መረጃ በሌላቸው ጆርጅ ቡሽ ተሞካሹ። “ቁጥር አንድ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር!” ተባሉ። (የጤና
ጠንቅ ሚኒስቴር ቢባሉ ጥሩ ነበር!) አሉኝ እንዴ? ይተው ወዳጄ እንዲህም አይባልም።

የሆነ ሆኖ ከዚህ ጋር ተያይዞ አቶ መለስ ጨንቋቸዋል አሉ። ያስታውሱ እንደሆነ አቶ አርከበን እንዲያ ጥምድ አድርገው የያዟቸው
ተቀባይነታቸው እየጨመረ ሲመጣ ነበር። አሁንም የዶክተሩ መወደስ ጓድ መለስን እንቅልፍ ነስቷቸዋል አሉ! (አሉ ላይ ይሰመርልኝ)
ታድያልዎ ይህንን የሰማ አንድ ወዳጄ ምን አለኝ መሰልዎ...? “እኒህ ሰውዬ እንዲህ ቀናተኛ ከሆኑ ከባለቤታቸው ጋር እንዴት ኖሩ?”
አለኝ። እኔ ግን ዝም አልኩት። ዝምታ ይሻላላ ወዳጄ። አለበለዛማ የአቶ ክንፈ አሟሟት ይጣራ ልል ነው ማለት ነው። ስለዚህ “ከነገሩ
ጦም ይደሩ” ብዬ ዝም አሁን ዋናው ወጋችን ተጀምሯል።

በቅርቡ ከአንድ ወዳጄ ጋር ስለ አሸባሪነት እያወራን ነበር። ታድያ የአንዳንድ ሰዎችን አሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ መግባት አስመልክቶ
እያወጋን እያለ በጨዋታ በጨዋታ ማነው ስሙ...? እንዴት አሸባሪ ሳይባል ቀረ? ብዬ ወዳጄን ጠየቅሁት። ይሄን ጊዜ ወዳጄ ቆጣ ብሎ
ምን አለኝ መሰለዎ...? እሱ ደግሞ ለሀገሩ ምን ሰራ እና ነው አሸባሪ የሚባለው? እሱ ደግሞ ለህዝቡ ምን አስተዋፅኦ አደረገና ነው የ
“አሸባሪነትን” ክብር የሚያገኘው...? ብሎ አይጠይቀኝ መሰልዎ?

ቆይማ አንድ ጊዜ አዲሳባ እንሂድ...

አዲሳባ ድሮ ድሮ “አሸባሪ” ሲባል ሰዉ ትንሽ ትንሽ ደንገጥ ይል ነበር። ከእለት እለት “አሸባሪ” የሚባለው ዘወትር ሲሞክር የሚያዝ
እንጂ የማያፈነዳ፤ የማይጎዳ መሆኑን ሲያይ አዲሳቤ ስለሽብር ቢነሳ ትንሽም ደንገጥ ማለቱን ተወው። ይህንን ልብ ያሉት የመንግስታችን
ዋና የስራ ሂደት ባለቤቶች አንድ ዘዴ ዘየዱ። ሰው “ሽብር” ሲባል ይደነግጥ ዘንድ ማፈንዳት! (ይሄኔ እርስዎ ለነገሩ እንግዳ ከሆኑ “ይሄ
እብደት ወይም ቅጥፈት ነው” ሊሉ ይችላሉ። ስለዚህ ለዝርዝሩ ወደ ዊክሊንክ እመራዎታለሁ።)

እናም ባለፈው ግዜ ዊክሊንክ እንደነገረን መንግስት ሆዬ ራሱ “ዷ!” እያደረገ ኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ ኦጋዴን ነፃነት ግንባር፣ አርበኞች
ግንባር፣ እና ግንቦት ሰባት አፈነዱ ይለን ጀመር። (በቅንፍ ማሳሰቢያ፦ መንግስት እስከ አሁን ዝርዝሩ ውስጥ ያላካተታችሁ ድርጅቶች
እኔ ከጠቀስኩት ውስጥ ገብታችሁ ከሆነ ወደፊት “አፈነዱ” መባላችሁ አይቀርምና ታገሱ... ብዬ ፈገግ እላለሁ ከዛም ቅንፌን ዘግቼ ወጌን
እቀጥላለሁ!) እናልዎ ወዳጄ ዊክሊንክ ምስጋና ይግባውና ነገሩን ፍርጥርጥ አድርጎ እያፈነዳ የመጣው መንግስት አሁንም አልፎ አልፎ
የቦንብ ሽታ ሲናፍቀው “ድው!” እያደረገ ተቃዋሚዎቹ ላይ እንደሚያላክክ ነገረን። ዊክሊንክዬ... እግዜር ይስጥልን! (ያሉ ብዙ ናቸው)
መንግስታችን አሁንም መሸበሩንም ማሸበሩንም ቀጥሏል።(አሉን ረሳኋት መሰል!) የአገሬ ሰውም ዛሬ ዛሬ “አሸባሪ” ሲባል ከቁብም
መቁጠሩን ትቶታል። አንዳንድ አሽሟጣጮች እንደሚሉት ከሆነ፤ “የብልጣ ብልጧን ጦጣ ታሪክ በተረት መልኩ ሲሰሙ ያደጉ
ባለስልጣኖቻችን የውሸታሙ እረኛን ተረት እንዴት እንዳልሰሙት እንጃ” ይሏቸዋል። ውሸታሙ እረኛ “ቀበሮ መጣብኝ” ሲል ውሸት
ሆኖ ሲገኝ፤ አሁንም “ቀበሮ መጣብኝ” ሲል ቅጥፈት ሆኖ ሲገኝ የእውነቱ ቀበሮ የመጣ ግዜ ነበር ጉድ የሆነው። አሁንም ይላሉ፤
አሽሟጣጮች። አሁንም መንግስታችን “አሸባሪ” ሲል። ውሸት ሆኖ ሲገኝ፤ ቀጥሎም “አሸባሪ” ሲል ውሸት ሆኖ ሲገኝ... ዛሬ ላይ ድፍን
አበሻ መንግስት “አሸባሪ መጣብህ!” ቢለው “ያ ሰው ወይ ለህዝቡ ሲታገል የኖረ የመንግስት ተቃዋሚ፣ ወይ ደግሞ ጋዜጠኛ፣ ካልሆነ...
ካለሆነ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ነው ማለት ነው።” ብሎ ደምድሟል እልዎታለሁ።

የምር ግን ወዳጄ ልብ ብለውልኛል? መንግስታችን “አሸባሪ” ያላቸው ልጆች እኮ አብዛኛዎቹ ከእስክሪብቶ የዘለለ ሌላ የጥቃት መሳሪያ
አጠቃቀም ... የምን አጠቃቀም አመጣሁኝ ስሙን እንኳ ለይተው መጥራት የማይችሉ ናቸውኮ! በበኩሌ ርዕዮት አለሙ እና ውብሸት
ታዬን በቅርበት የማውቃቸው ሰዎች ናቸው። አሉ የሚባሉ ብዕረኞች እንደሆኑ አውቃለሁ። ያኔ እነርሱ “አሸባሪ” ተብለው የታሰሩ ግዜ
አንድ ወዳጄ ምን አለኝ መሰልዎ... “መንግስት እጅግ በጣም ቦቅቧቃ! ሆኗል ማለት ነው።” አለኝ እንዴት? አልኩት... “እንዴት ማለት
ጥሩ ጥያቄ ነው...” ብሎ መልሱን ጀመረ። “እነዚህን አንድ ፍሬ ብዕረኛ ልጆች እንዲህ ከፈራ በቋፍ ያለ መንግስት መሆኑን ያሳያል።”
አለኝ።

የምር ግን ወዳጄ አሁንስ ኢህአዴግዬ ያሳዝነኝ ጀምሯል። የድሮ ፈሪዎች “ኮሽ” ሲል ነበር የሚደነብሩት አሁንኮ መንግስታችን አዲስ
የፍርሃት ሪከርድ ነው እያስመዘገበ ያለው! ሰው እንዴት ምንም ሳይፈጠር...? ሰው አልኩ እንዴ? ይቅርታ አስተካክዬ እደግመዋለው
አንድ ድርጅት ምንም ነገር ኮሽ ሳይል እንዴት በፍርሃት ይርዳል? ወይስ መንፈስ ጭንቀት የሚባል ህመም ታመመብን? ይሄኔ አቡኑም
በድርጅቱ ላይ ቅሬታ ቢኖራቸው ነው እንጂ፤ አጠቃላይ ድርጅቱን ወስደው “ሁለት ሰባት” ቢያስጠምቁት ለርሳቸውም እንደ ፅድቅ ስራ
ይቆጠርላቸው ነበር...!

ባለፈው ሳምንት ወዳጃችን መስፍን ነጋሽ “አሸባሪ ያልሆናችሁ እጃችሁን አውጡ” በሚል ርዕስ ቅምሻ የሆነች ፅሁፍ አስነብቦን ነበር።
እውነትም ወዳጃችን እንዳለው በአሁኑ ግዜ “አሸባሪ” ያለተባለ እንኳ ቢኖር እርሱ ወይ የኢህአዴግ ቤተ ዘመድ ነው፤ ወይ ደግሞ
ወደፊት “አሸባሪ” የሚባል ነው። እናም ማንም አሸባሪ ከመባል አያመልጥም ብሎናል። እውነቱን እኮ ነው እንደ አያያዙ ከሆነ ሀገሪቷ
የ”አሸባሪዎች” ሀገር ከመሆን አትድንም።

“የመንግስት አፍ ነኝ!” የሚሉት አቶ ሽመልስ ከማል እንደነገሩን ከሆነ “አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀ ሰው ጋር ሻይ መጠጣት፣ ሰላም
መባባል፣ ፈገግታ መለዋወጥ ሁሉ አይቻልም።” ብለዋል። በነገራችን ላይ አንድ የፌስ ቡክ ወዳጄ፤ አቶ ሽመልስ ከማልን “አቶ ሼምየለሽ
ከማል!” ብሏቸው አይቻለው ወዳጄ የታይፕ ግድፈት ነው ወይስ አሽሙር ነው? ሀቅ ነው እንጂ! እንዳትለኝ ብቻ!

እናም እንደ አቶ “ሼም የለሽ” መንግስት አባባል ከሆነ ማንም ሰው ስለ ሀገር ከሚያስቡ ዘመዶቹ ጋር መገናኘት፣ መደዋወል፣ መጠያየቅ፣
አይችልም ማለት ነው። ይሄ እውነትም “ሼም” ማጣት ነው። ነውር አይደለም እንዴ!? ብለንም እንጨምራለን።

እኔ የምልዎት ወዳጄ የዛሬዎቹ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ድሮ ጫካ በነበሩ ግዜ በወቅቱ የነበረው መንግስት ከአሸባሪ የበለጠ ስም
ተሰጥቷቸው ነበር እኮ! ትዝ አይልዎትም? “ወንበዴ” ነበር የሚባሉት። ከወንበዴም ደግሞ “ተገንጣይ ወንበዴ!” ይሄ እንደውም
መንግስት የሰጣቸው ስም ነው። በነገራችን ላይ በወቅቱ አለማቀፍ ድርጅቶች “አሸባሪዎች” ዝርዝር ውስጥ አስገብተዋቸው ነበር።
ባለፈው አይደል እንዴ የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነው “ነፃነት” ጋዜጣ ላይ ያየሁት? እና ታድያ ትላንት “አሸባሪ ወንበዴ” ሲባሉ የነበሩ
ባለስልጣኖቻችን እኛም ለምን ይቅርብን ብለው ነው መሰል ዛሬም እነርሱን የተቃወመ በሙሉ “አሸባሪ” ነው እያሉ ይገኛሉ። ህዝቡም
“ኢህአዴግን የመሰለ አንጋፋ “አሸባሪ” ማሸበር የቻሉ እኒህ ጎበዞች ከወዴት አሉ!?” እያለ በአድናቆት እየጠየቀ ይገኛል።

በመጨረሻም

በርካታ ወዳጆቼ በአሁኑ ግዜ እያንገበገባቸው ያለ አንድ ነገር አለ። “መንግስት በድሎናል፣ መንግስት አግልሎናል።” የሚሉት እኒህ
ወዳጆቼ፤ “ለሀገራችን ብዙ ሰርተን ለህዝባችን ቀን ተሌት እየለፋን ሳለ መንግስት ግን ምንም እንዳልሰራን አድርጎ ቸል ብሎናል!” ሲሉ
ይከሳሉ። ወዳጆቼ እንደሚሉት ከሆነ “መንግስት እውቅና ባይሰጠንም እኛ ግን ጠንክረን መስራታችንን ለህዝብ እና ለሀገራችን
መልፋታችንን አንተውም!” ባይ ናቸው። የወዳጆቼ ጥያቄ ምን መሰልዎ... “እንዴት አሸባሪ አልተባልንም?” ነው። መካሪዎችም ይላሉ፤
ጠንክራችሁ ስለ ሀገራችሁ ስለ ህዝባችሁ ታገሉ። ተስፋም እንዳትቆርጡ አደራ! ያኔ የ”አሸባሪነትን” ሞገስ ታገኛላችሁ!
“አሸባሪነትን ማን ያገኛታል? ስለ ህዝቡ በፅናት የታገለ አይደለምን!?”

ይበሉ ወዳጄ ለዛሬ ጨዋታችን እዚህ ላይ ይጠናቀቃል። በሚቀጥለው ጨዋታ እስክንገናኝ...

አማን ያሰንብተን!
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com – December 20, 2011

You might also like