Professional Documents
Culture Documents
ጭለማና ብርሃን
ጭለማና ብርሃን
ጭለማና ብርሃን
ጭለማና ብርሀን
ለስብሀት ገብረእግዚአብሄር
የመሬታችን ወዘናው እስከመጨረሻዋ ጠብታ ተሟጧል። እንኳን አዝርእት የራሱም ሳርና ቅጠል
በላዩ ላይ አልበቅል ብሎ፤ የሚበቅለውም ጫጭቶና መንምኖ ፍሬ አልሰጥ በማለቱ መሬቱ አሸዋና
ድንጋይ ብቻ ከሆነ ቆይቷል። ጎርፍና ንፋስ የቻለውን ያህል በየጊዜው ተሸክሞ እየሄደ አገሩን
ምድረበዳ አድርጎታል። በየማሳውም የተዘራው እህል አገር ከሚያክል ሁዳድ አራትና አምስት ቁና
እየተመረተ፤ ቢዘንብም ባይዘንብም እርሀብ የህይወታችን የሰውነታችን አካል ከሆነ ቆይቷል።
በቀየው ለወጉ ከብቶች ይሰማራሉ። በሸሆናቸው ድንጋይን ከድንጋይ ሲያጋጩ ሲያንኳኩ ውለው፤
አንጀታቸው እንደተጣበቀ ወደ በረት መመለስ የለት ተለት ህይወት ትእይንት ከሆነ ከርሟል።
ሁሉም ከአጥንትና ቀንድ ብቻ የተፈጠሩ ይመስሉ ነበር። ከብቶች። ምሽት ላይ የመንገዱን አቧራ
እንደጉም እያናኙ ወደመንደር ይነዳሉ።
አባቴም ቢሆን እርሻ ላይ ወይፈን እገራ ብሎ፤ ከወይፈኑ ጋር “ቀንበር ትገባለህ አልገባም”
ሲታገሉ፤ ወይፈኑ ማጅራቱ ላይ የተጫነውን ቀንበር ሊጥል ሽቅብ ሽቅብ አናቱን እየወረወረ
ሲመናጨቅ፤ በቀንዱ ያባቴን አፍ አግኝቶት ኖሮ፤ ከላይኛው የፊት ጥርሶቹ አንዲቷን አወለቀ።
ረዘም ያለና አንደንስር አሞራ ምንቃር መሀል ላይ ጎበጥ ያለው አፍንጫው እስከላይኛው ከንፈሩ
ወረድ ያለ ነው። አባቴ ፈገግ ሲል ደስ ማለቱ የጥርሱ ውልቃት ፍንጭት አንጂ አደጋ እንኳ
አይመስልም ነበር። ፊቱ ክብና አጠር ያለ ነው። እስከመሀል አናቱ የዘለቀ በራው ጠይም ፊቱን
ረጂም አስመስሎታል። የተንዠረገገ ሪዙ አንገቱን ሸፍኖታል። አይላጭም። በጣቱ ማፍተልተል
ይወዳል።
እኔ በተወለድኩበት ዓመት ዝናብ ጠፍቶ በየማሳው የነበረ ሰብል በቡቃያው ስለቀረ ረሀብ አገሩን
ወሮት ነበርና እናቴ “በእድሉ ያድጋል ብላ” ስሜን “በድሉ” አለችን አሉ። ሶስተኛ ልጅ ነበርኩ።
አንጋፋ ወንድማችን ዘመድኩን አስራሁለት ዓመቱ ነበር። ተከታዩ ባዩሽ ዘጠነኛዋን ይዛለች። እኔ
ሰባተኛዬን ይዤ ነበር። የኔ ተከታይ አምስተኛዋን፤ የታናሼታናሽ ሶስተኛዋን፤ የታናሼ ታናሽ
ታናሽ አንደኛውን ይዟል። ስድስት አናት ባስራአምስት ዓመት ራስ በራስ ላይ ተወልደን፡
ተኮልኩለን፤ ሁላችንም እንዋደድ ነበር። ሁላችንም አለን።
አባታችን ባንድ ጥማድ በሮች ጫንቃ ላይ የጫነውን ቀንበር ሲያጠብቅ ሲያላላ፤ እርፍ ሲያሳጥር
ሲያዝረዝም እየዋለ፤ ካባቱ ከወረሳት አራት ጥማድ መሬት ላይ በምናገኛት ሰብል ነበር ውለን
የምንገባው።
Page 1 of 9
አባቴ ማታ ከእርሻ ደክሞት ሲገባ እናቴ በዚያ የማይጠገብ ጎስቋላ ፈገግታዋ ተቀብላ እግሩን፤
እጁን፤ እንዲታጠብ ውሀ ለብ አድርጋ ካቀረበችለት በሗላ፤ ቀድማ እኛን አብልታ ላባቻችን
የድርሻውን ከማጀት ያስቀመጠችለትን እራት አሙቃ ታቀርብለታለች። መጀመሪያ ለሷ ያጎርሳል።
ከዚያ ለሁላችንም ሁለት ሁለቴ፤ ከዚያ የተረፈችውን በላልቶ ያችን የሚወዳትን ቀጭን የገብስ ጠላ
በሽክና ከናቴ ተቀብሎ ወደ መደብ ይወጣል።
“የአምናው ክረምት አለቅጥ ሰምሮ ነበር። ቡቃያው ሁሉ አምሮ ነበር። ምን ያደርጋል አባቴ
ከአባቱ የወረሰው መሬት እኔ ላይ ሲደርስ ታከተው መሰለኝ ከድካም በቀር ፍሬ አልሰጥ ብሏል።
አምና ያዘመርነው ዘንድሮ ለዘር እንኳ አልተረፈም፤ አይደል አትጠገብ?” አለና ወደ እናቴ
ተመለከተ።
“ አዎ ምንም የለም “ አለና ፊቱን ወደኛ መልሶ “ በጋው አለቀ። ልጆቼ መሬታችን ነጥፏል።
ክረምት መግባቱ ነው። ያለ እረፍት አርባ ዓመታት ታረሰ። መሬትም እንደሰው ካልመገቧት
አትሰራም። ፍሬ አትሰጥም። ፍግ የለም። ማዳበሪያ የለም። በሮቼም እኔም አይደክሙ ደክመን
የምናዘምረው ከቁና አልፎ ድብኝትም አልሞላ ብሏል። የዘንድውን ክረምት ልጆቼ ልትራቡ ነው።
ያ ከመሆኑ በፊት ግን አጎቴ አብየ ከልካይ መሬት እሰጥሀለሁ ብለውኛል። ጫካ መንጥረህ አልማ
ብለውኛል። ደጋ ወጥቼ ሁለትም ሆነ ሶስት ጥማድ መሬት እመነጥራለሁ። ዘንድሮ ለም መሬት
አርሼ ለከርሞ ወፍራም አንጀራ እንበላለን ልጆቼ፤ የዘንድሮውን ክረምት ግን የናታችሁ መሶብ ወና
መክረሙ ነው። አንጀታችሁም መራቡ።” አለና በፍቅር አይን እየተመለከተን በቅሬታ ፈገግ አለ።
ረጂም ሪዙን በጣቱ አፍተለተለ።
Page 2 of 9
ይህንን ባለ በሶስተኛው ቀን ነበር አባቴ ተነስቶ ደጋ የወጣው። እንደደረሰም፤ የናቱ ወንድም አጎቱ
አብየ ከልካይ ካንድ መለስተኛ ተራራ ግርጌ ወደሚገኝ ለም መሬት ይዘውት ሄዱ። በለምለም
እጽዋትና በረጃጅም ሳር የተሸፈነው ረግረጋማ መሬት በርቀት ከሚታየው የተራራ ሰንሰለት ድረስ
ፍጹም አረንጓዴ ምድር ነበር።
ማለዳ የተነሳን ዐሀይ ከአናት በላይ ከዋለች በሗላ አዲሱ መሬታችን ደረስን። ከሰዓቱን አባቴ
የለመደውን ምንጠራ ተያያዘው። ዛፎቹን ሲቆርጥ፤ ሲነቅል፤ ሲገነጥል፤ ፍጥነቱና ቅልጥፍናው
እያስገረመኝ ላፍታ ቆም አልኩና ካየሁት በሗላ እኔም ወደስራዬ ሄድኩ። ከርሱ ስርስር
እየተከተልኩ፤ ትንንሽ ቅርንጫፎችን እየሰበሰብኩ፤ ጎጆ ቤቶችን እየሰራሁ ጨዋታ ቀጠልኩ።
ነፍሳትና ቢራቢሮ ሳይ እየተከተልኩ፤ እያሳደድኩ፤ አንዷን ስይዝ አንዷን ስለቅ እናም አባቴ
መኖሪያቸውን ሲያተረማምሰው ከየስብሳቡ ውስጥ ቱር እያሉ የሚያመልጡ እናትና ልጅ
ጥንቸሎችን እያየሁ ስደነግጥ፤ አንዳንዴም ስደነቅ፡ ሂደቱ ቀጠለ። የሚኖሩበት ዛፍ ከስር
በመጥረቢያ ሲናጋ፤ ጎጆአቸው ሲፈርስ፤ እንቁላላቸው ሲረግፍ፤ የፈለፈሉአቸው ጫጩቶች ሲበተኑ፤
እናትና አባት ወፎች ይመስሉኛል፤ ተናደው፤ ተቆጥተው፤ በንዴትና በሀይል ይመስለኛል ለኔ፤ ወደ
ሰማየሰማያት ብርርርር… ይላሉ። በቀጥታ ሽቅብ። ካይኔ አስኪሰወሩ አንጋጥቼ እመለከታቸው
ነበር። እኔም እንዳንጋጠጥኩ አነሱም ሽቅብ ተናደው አንደከነፉ እልልል…ም ብለው ደመናው
ውስጥ ገብተው ከአይኔ ይሰወራሉ። እኔም ወደ አባቴና ወደ ምንጠራው እመለሳለሁ።
Page 3 of 9
በዚያ የልጅነት አእምሮዬ ቤታቸው ሲናድ መድረሻ ፍለጋ የሚሯሯጡት ፍጥረታት መጨረሻቸው
ምን እንደሚሆን ለማወቅ ያስጨንቀኝ ነበር።
“ሌላ ቦታ ሲያፈርሱባቸውስ?”
አልገባኝም። ከሁሉም አቅጣጫ ፍጥረታት መኖሪያ ቀያቸው ሲፈርስ ሲናጋ የመጨረሻ መሄጃቸው
የት አገር እንደሆነ።
አንዲት ነጭ ቢራቢሮ ስትውለበለብ ድንገት አየሁና እሷን ላሳድድ ሄድኩ። ነገር ግን ወዲያው
ንፋስ ይዟት ካጠገቤ ጥርግ አለ። ወዲያውም አንዲት ቢጫ ወፍ ከፊቴ ቱር አለች። ከታች
በመጥረቢያ የነበረችበትን ግንድ አባቴ ሲቆርጠው ቀጥ ብላ ወደ ሰማየሰማያት ከነፈች። ሽቅብ
እየከነፈች አየር ላይ ቆም አያለች፤ ሽቅብ እየከነፈች ቆም እያለች ወደላይ ወጣች ። አንጋጥቼ
መድረሻዋ የት እንደሚሆን እስከጠፈሩ ተከተልኳት። ወጣች ወጣችና ካይኔ ተሰወረች። ከደመና
ውስጥ ፈለኳት። የለችም።
ድንገት ነበር አባቴ የሲቃ ጩኸት ሲያሰማ መብረቅ የጮኸብኝ ያክል ደንግጬ ዘወር ያልኩት።
አንዲት ትልቅ ውሻ የምታክል ፍጥረት አፏን አስከመጨረሻ ከፍታ እግሩን፤ ባቱን፤ በሙሉ ጎርሳ፤
የነከሰችውን ሙዳ መንጭቃ ለማምለጥ ይመስላል እያናፈረች ልትነጭ ስትታገል አባቴም “ኡኡ”
እያለ ሊያስለቅቃት በያዘው የእንጨት ግንጣይ ሲደበድባት እኔ ወደምደርስበት ጠፋኝ። መላ
ሰውነቴ፤ የልጅነት አካላቴ እየተንቀጠቀጠ፤ እየተንዘረዘረ ስጮህ፤ አባቴም ሲጮህ፤ አውሬዋም
ስታናፍር፤ ስትጮህ፤ ምድር ተከፍታ አትውጠኝ፤ ሰማይ ተከፍቶ አይውጠኝ፤ “አባባ! አባባ!”
እያልኩ በሲቃ ለራሱም ፈተና ላይ ወደወደቀው አባቴ እቅፍ የነፍስ ይዞኝ ብርርር እያልኩ ሮጥኩ።
አባቴና አውሬዋ የሞት የሽረት ትግል ይዘዋል። ከእግሩ ደም ይንፏፏል። ከዱላ ብዛትም ይሁን
ወይም አውሬዋ የምትፈልገውን ስላገኘች ብቻ ለኔ ሊገባኝ በማይችል ሁኔታ ድንገት አባቴን
ለቀቀችና ወደኔ አቀናች። እርሱም የሞት ሞቱን ዘለለና ሳትቀድመው መሀል መንገድ ላይ
ደረሰባት። የያዘውን መጥረቢያ ሲሰነዝር አንገቷን አገኘው። ዝልፍልፍ ብላ ወደቀች። መንፈራገጥ
ማጉዋራት ጀመረች። ከዚያ ባንድ እጁ እፍስ አድርጎ ደረቱ ላይ ጥብቅ አድርጎ አቀፈኝና
ያባብለኝ፤ እንባዬን እየጠራረገ ይስመኝ፤ ይደባብሰኝ ገባ። አውሬዋ ጥቂት በጣእር ከተንፈራገጠች
በሗላ ዝልፍልፍ ዝም አለች። እኔም ጥቂት ቆይቼ የተረጋጋሁ ብመስልም ሰውነቴ መንቀጥቀጡን
ቶሎ አላቆመም ነበር። አባቴ ከእግሩ ላይ የሚንፏፏውን ደም በእራፊ እየጠራረገና ህመሙን
Page 4 of 9
አንድም ቀን አለፈ፤ ሁለትም፤ ሶስትም፤ አራትም። አባቴ እየባሰበት አንጂ እየተሻለው ሊሄድ
አልቻለም። እናቴ በየገጠሩ መድሀኒት አዋቂዎች ዘንድ ስትሮጥ ከርማ ነበር። ያልታዘዘለት
ስራስርና ቅጠላቅጠል አልነበረም። ሁሉንም እየጨቀጨቀች አጠጥታው ነበር። “ጥቁር ዶሮ
በጭንቅላቱ አዙራችሁ ማታ ልቀቋት” ተብሎ ነበር። ሁሉም ተደረገ። ሁሉም አልሰራም።
ቀናት ቀናትን እየተኩ ነጎዱ። በቤታችን የሀዘን ድባብ ካጠላ ሁለተኛው ሳምንት ተገባደደ።
በልጅነት አእምሮዬ ልሸከመው የማልችለው ጭንቅ እየመጣ ነው። አባቴ ከ እለት እለት እየደከመ
ከመኝታው መንቀሳቀስ ተስኖታል። መጸዳዳቱም በእናቴ ድጋፍ ሆኗል። ሌሊትና ቀን በቤታችን
የማያቋርጥ እንባ ይፈሳል። አባቴ ያቃትታል። ያቃስታል። በቤታችን ተስፋ ጨለመ። እናቴ
ሌሊትም ቀንም በማልቀሷ አይኗ ነፈረ።
ቢቸግራት አንዲት ባለውቃቢ ወይዘሮ ዘንድ መፍትሄ ፍለጋ ሔዳ ነበር። ጭንቀቷን ያዋየቻቸው
ወይዘሮም “ቀይ አውራ ዶሮ አርደሽ፤ በደሙ ሰውነቱን አሻሺውና ከቤት አርቀሽ ሰው
በሚመላለስበት ቀጭን መንገድ ላይ፤ ቂጣ ቆሎ ጨምረሽ፤ ወፍ ሳይንጫጫ፤ ጭለማው ሳይፈታ፤
Page 5 of 9
ያባቴ ሁኔታ ይብሱን አስደንጋጭ እየሆነ ሲመጣ የሰፈሩ ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት ተሰብስቦ
መከረ። ቢሞትም ቢድንም ሀኪም ዘንድ ደርሶ እንደሆነ ይሁን ተባለ። ሰፈርተኛው በሙሉ እኛ
ቤት ተሰበሰበና ያለውን ነገር ሊያዋጣ መከረ። አዋጣም። ለጊዜው በጁ ላይ ምንም ገንዘብ
ያልነበረውም ዶሮ ያለው ዶሮውን፤ ፍየል ያለውም ፍየሉን ሸጦ ሊያመጣ ተስማማ። ገሚስ አባቴ
የጀመረውን ምንጣሮ ሊጨርስና የዘር ሰአት ሳያልፍ ያለንን እርሻ አርሶ ሊዘራልን ተስማምቶ ሰው
መረጠ። በሶስተኛው ቀን ሁሉም የገባውን ቃል ሳያጥፍ ያገኘውን ገንዘብ ይዞ መጣ። ወዲያውም
አብሮት ሀኪም ዘንድ የሚቆይ ተብሎ አንድሰው ተመረጠ። እናቴን “አንቺ ልጆቹን ይዘሽ እቤት
ቆይ” ብለው መከሯት።
አንድ ቀን ጠዋት ማለዳ አባቴን በወሳንሳ ተሸክመው የሰፈሩ አርሶ አደሮች ይዘውት ከቤት ወጡ።
ሰላሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኝ ከተማ ሊወስዱት ነበር።
የበልግ ዝናብ መጣል ጀምሮ ነበር። አባቴ ህልሙም ቅዠቱም ሁሉ ስለ አዲሱ መሬት ሆኖ ነበር።
ከልክ በላይ ይቃዣል። “የተገመሰውን ማሳ አልዘራሁትም እኮ” ይላል። “የበልግ ዝናብ
እንዳያልፍብኝ ነገ በጠዋት ተነስቼ ዘር እበትናለሁ፡ አትጠገብ በጧት በጧት አስነሸኝ። ባይሆን
ስነሳ አርመዋለሁ። እኮተኩተዋለሁ። እባክሽ ጎረቤት እንዲዘራልኝ አድርጊ….አትጠገብ..አትጠገብ..
”
አባቴ ይህን ሁሉ ቅዠት በሁለት ሳምንት ልክፍት ሲቃዥ ከእለት እለት እየደከመ ከመኝታው
መነሳት አቅቶት ነበር። የሚያተኩሰው ትኩሳት ውሀ ያፈላ ነበር። እራሴ ተፈለጠ ይል ነበር።
ይበረግግ ነበር። ውሀ ሲፈስ ኡኡ ይል ነበር። ሁለመናዬን አመመኝ ይል ነበር። አፉ ያልታወቀ
ልክፍት።
አሁን ቤታችን በጭንቅና በሀዘን ተውጧል። አባታችንን ሰዎች ተሰብስበው በወሳንሳ ይዘውት
ወተዋል። አንድቀን ካደርን በሗላ እናታችን ለብቻዋ ማንሾካሾክ ማውራት ጀምራለች። የምትለውን
ነገር ሁሉ እሰማታለሁ።
አይኖቿን አፍጣና መሬት ላይ ተክላ ለረጂም ደቂቃዎች የሚያስጨንቅ ዝምታ ዝምምም ትላለች።
ድንገት ደሞ ሳናስበው ፍንድት ብላ ስቅስቅ እያለች ታለቅሳለች። እኛም ተከትለናት መንጫጫት
እንጀምራለን። ደረቷ ላይ ተለጥፎ እየጠባ ያለው ትንሹ ወንድማችንም መጥባቱን ይተውና በለቅሶ
ከኛ ይቀላቀላል። ከልክ በላይ ስንንጫጫባት የራሷን ለቅሶ ለመዋጥ እየተናነቀች ዝም እንድንል
ታባብለናለች። አንዳንዴም አንሰማሽ ስንላት ቆጣ ትላለች። እኛ ዝም ስንል ትንሹ ወንድማችን
ግን አያቆምም ነበር። እንደገና ደሞ እሱን ተከትለን አናለቅሳለን። በቤታችን ተስፋ ጨለመ።
እናቴ ሌሊትም ቀንም በለቅሶ አይኗ ነፈረ።
Page 6 of 9
አባቴ ለህክምና ከተወሰደ አንድ ሳምንት አለፈ። ምንም ወሬ ከከተማ አልመጣም። አብየ ከልካይ
ያባቴን ሁኔታ ሊያረጋግጡ ከደጋ መተው ነበር። ያለበትን ቦታና ሁኔታ ስንነግራቸው
የበቅሎአቸውንም ኮርቻ ሳያወርዱ “ያለበትን ሁኔታማ ማየት አለብኝ ብለው” ቡና እስኪፈላላቸው
እንኳን አልጠበቁም ወደከተማ አቀኑ። እሳቸውም በዚያው እልም ብለው ቀሩ። ወሬውን እንኳን
ይዞልን የሚመለስ ሰው ጠፋ።
ቀናት ቀናትን ተኩ። ሳምንታት ተከታተሉ። ያባቴ ነገር የውሀ ሽታ ሆኖ ቀረ። እናታችን ነፍስና
ስጋዋ ሲሟገቱ ነው የከረመችው። ቤታችን ጨልሞ ነው የከረመው። አንድ ወር ተቆጠረ።አይደርስ
የለ የጭንቀታችን የመጨረሻው ቀን ደረሰ።
አባቴ ደከም ብሎታል እንጂ ህይወት ከገጽታው ትነበባለች። ህያው ፈገግታ ከፊቱ ይበራል።
የእብድ ውሻ በሽታ እንደለከፈው ሀኪም መናገሩን ነገረን። የተሰጠው መድሀኒት ቁና ሙሉ ነበር።
ያንን እየዋጠ ሶስት ሳምንታት አለፉ። ብርታትና ህይወት በቤታችን ተመልሰዋል። ወር አለፈ።
አባቴ መድሀኒቱን ጨርሷል። ዳነ። በቤታችን ብርሀን በራ።
Page 7 of 9
አንድቀን ጠዋት እደጅ ጨወታ ላይ ነበርን። አባቴ መኮትኮቻ ትከሻው ላይ አድርጎ፤ እናቴ
አገልግል ይዛ ልትሸኘው ከቤት እየወጣ ሳለ ሁላችንንም ከሳመን በሗላ እኔን በፈገግታ
እየተመለከት እንዲህ አለ፤
“ወደ አዲሱ እርሻችን መሄዴ ነው፤ በድሉ አብረኸኝ ትሄዳለህ?” ሳቅ እያለ ጠየቀኝ።
የዚያን እለቱ ሁኔታ ባይምሮዬ ይመላለስ ጀመር። አባቴ ከቤት ወቶ በቅጠላቅጠሉ ውስጥ ቁልቁል
የምትወርደውን ቀጭን መንገድ ሲይዝ ያለፈውን እያሰብኩ ባይኔ ስከተለው ዶማና መኮትኮቻውን
በጀርባው በኩል ትከሻው ላይ እንደጫነ ከአይኔ ተሰወረ። ያቺ አውሬ እንደ ግዙፍ ተራራ ጎልታ
አይኔን ጋረደችው። ወደ ጨዋታዬም ተመለስኩ። አባቴም ነጎደ።
ልመናዬ
ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ በትልቅ እስር ቤት ውስጥ የሚኖር ምርኮኛ ነው።ታንክና መድፍ ከቦት
ነው በመኖር ላይ ያለው።ዙሪያውን በጆሮጠቢ ታጥሮ ነው በመኖር ላይ ያለው።ከውጭ የሚመጣ
ዜና አይሰማም። ኢንተርኔት የለውም።በሀገር ውስጥ የነጻው ፕሬስ ጋዜጦች በሙ ሉ ተዘግተው
ጋዜጠኞቹም ሁሉ ስለተሰደዱ በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን እውነተኛ ነገር የሚያውቅበት
እድል የለውም።ዙሪያውን ሀያ አራት ሰአት እየጮ ሁ የሚያደነቁሩት በውሸት የተሞሉት የወያኔ
ቴሌቪዥንና ሬዲዮ እና ጋዜጣው ናቸው ።
lkebede10@gmail.com
Page 8 of 9
Page 9 of 9