Vehicle Weight Regulation Final Doc. January

You might also like

Download as docx, pdf, or txt
Download as docx, pdf, or txt
You are on page 1of 17

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ

መመሪያ ቁጥር ---/2009

የተሽከርካሪዎች ክብደት እና መጠን ቁጥጥር መወሰኛ መመሪያ ቁጥር ---/2009

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የተቋቋመበትን ዓላማ እና ራዕይ ከግብ ለማድረስ


የሚያስተዳድረውን የአዲስ አበባ-አዳማ የፍጥነት መንገድን የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች ከክብደት በላይ ጭነት
በመጫን በመንገዱ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ለመከላከልና ጉዳት አድርሰው የተገኙት ላይ ቅጣት በመጣል
ለወደፊት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ መመሪያ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ፤

 ከተፈቀደላቸዉ የክብደት መጠን በላይ እየጫኑ ወደ ፍጥነት መንገዱ በሚገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ


መመሪያና ደንብን የተከተለ የአሰራርና የቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋት፣
 ከክብደት ቁጥጥር ስራዉ ጋር ተያያዥ እና ተደጋጋፊ የስራ ግንኙነት ያላቸዉን የስራ ክፍሎች ዝርዝር
ተግባራት ለማከናወን በማስፈለጉ፤
 በክብደት ቁጥጥር አሰራር ስርዓት ብልሹነት ረገድ የሚፈጠሩ እንከኖችን ለማስተካከል፤
 በመንግስት የልማት ድርጅት አዋጅ ቁጥር 25/1984 አንቀፅ 14(4) መሰረት ይህ የውስጥ አሰራር ደንብ
ተዘጋጅቷል፡፡

ክፍል አንድ

ጠቅላላ

አንቀፅ 1. አጭር ርዕስ

ይህ መመሪያ “የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የተሽከርካሪዎች ክብደት እና መጠን ቁጥጥር መወሰኛ መመሪያ
ቁጥር --/2009” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

አንቀፅ 2 ትርጓሜ

በዚህ መመሪያ ውስጥ የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር፡-

1) ”ሊፍት አክስል” ማለት አሽከርካሪዉ ለጭነቱ የሚያቀርበዉን የድጋፍ መጠን ማስተካከል የሚችልበት
እንዲሁም ከፈለገም አክስሉን ከፍ አድርጎ ከመንገዱ ጋር ያለዉን ንክኪ ማቋረጥ የሚችልበት ነዉ፡፡

1
2) “ሎቤድ ግማሽ ተሳቢ” ማለት በጎታች ተሸከርካሪ ላይ ተገጥሞ ልዩ ተንቀሳቃሽ መሣሪያ፣ ማሽኖች እና
የመሳሰሉትን ለማጓጓዝ የተሠራ ግማሽ ተሳቢ ነው፤
3) “መንገድ” ማለት የአዲስ አበባ-አዳማ የፍጥነት መንገድ ፣ ከመንገዱ በላይ እና በታች የተሰሩ
የእንስሳት፣የሰዉ እንዲሁም የተሽከርካሪዎች መተላለፊያ ሲሆን በመንገዱ ላይ ያለውን ድልድይ
ይጨምራል፤፡፡
4) ”ሚኒስቴር” ማለት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ማለት ነው፡፡
5) “ኢንተርፕራይዝ” ማለት የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ማለት ነው፡፡
6) “ባለሶስት አክስል” ማለት በመንገድ ላይ የሚያርፈውን ክብደት በተመጣጠነ መልክ እንዲሰራጭ ታስቦ
ዲዛይን የተደረገ ከ 1.2 ሜትር እስከ 2.5 ሜትር በሆነ ርቀት ውስጥ የተሳሰሩ ሶስት አክስሎች ስብስብ
ነው፤
7) “ተሳቢ” ማለት ከተሸከርካሪ ጋር ተገጥሞ ጭነት እንዲያጓጉዝ የተሰራ የተሽከርካሪ አካል ነው፤
8) “ተሽከርካሪ” ማለት ጠቅላላ ክብደቱ ከ 3500 ኪ.ግ በላይ የሆነና እቃን በመንገድ ላይ በማጓጓዝ
አገልግሎት የሚሰጥ ነው፤
9) “አክስል” ማለት የሁለት እና ከዛ በላይ እምብርታቸዉ በአንድ ቋሚ ወለል ላይ የሆነ የጎማዎች
አደረጃጀት ሲሆን ክብደት ወደ መንገድ የሚያስተላልፍ ነዉ፡፡
10) “ነጠላ አክስል” ማለት በአንድ ዘንግ የተያያዙ ቢያንስ ሁለት ጎማዎችን የያዘ አንድ አክስል ነው፤
11) “ የመንገድ ደህንነት ባለሙያ” ማለት በኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ሰራተኛ ሆኖ
በመንገድ ደህንነትና ቁጥጥር ስራ ላይ የተሰማራ ነው፡
12) “ከክብደት በላይ /ትርፍ ጭነት” ማለት በዚህ መመሪያ በአንቀፅ 7(1 ሀ-ሠ) እና በአንቀፅ 8(1) ከተጠቀሰው
የጭነት ወሰን በላይ ሲሆን ነዉ፡፡
13) “የመሪ አክስል” ማለት ተሽከርካሪው የሚጓዝበትን አቅጣጫ ለመቆጣጠር ሲባል አሽከርካሪው
የሚቆጣጠረው መሪ ያረፈበት አክስል ነው፤
14) “የተሽከርካሪ ተሸካሚ ግማሽ ተሳቢ” ማለት ከተሳቢ ጋር የተያያዘ ተሽከርካሪ ለመሸከም ብቻ የተሠራ
ግማሽ ተሳቢ ነው፤
15) “ጠቅላላ ክብደት” ማለት የተሽከርካሪው እና የጭነቱ ድምር ክብደት ነው፤
16) “የተጣመረ ተሽከርካሪ” ማለት የባለሞተር ተሽከርካሪንና ከተሽከርካሪ ጋር የተያያዘውን ተሳቢ
አጣምሮ የያዘ ተሽከርካሪ ነው፤
17) “የአክስል ክብደት” ማለት ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ጎማዎች የያዘ አክስል ወደ መንገድ
የሚያስተላልፈው ክብደት ነው፤
18) “ግማሽ ተሳቢ” ማለት ከጭነት ተሽከርካሪ ጋር ተገጥሞ ጭነት እንዲያጓጉዝ የተሰራ ተሳቢ ነው፤
19) “ጉዳት” ማለት በኢንተርፕራይዙ ንብረት ላይ በመንገድ ተጠቃሚዎች አማካኝነት የሚደርስ የንብረት ጉዳት ነው ፡፡

2
20) “ግዙፍ ጭነት” ማለት ከጭነቱ ከፍተኛነትና ያለመነጣጠል ባሕርይ የተነሳ የተለየ መስመርና የተለየ
ተሽከርካሪ እንዲሁም ልዩ ፈቃድ የሚጠይቅ ጭነት ነው፡፡ ይህም እንደ ክሬንና ተገጣጣሚ እቃን የመሳሰለ
ጭነትን ይጨምራል፤
21) “ቅጣት” ማለት በዚህ መመሪያ በአንቀጽ 4፣5፣6፣7 እና 8 ከተጠቀሰዉ በላይ ጭኖ በተገኘ አሽከርካሪ ላይ
የሚጣል ቅጣት ማለት ነዉ፡፡
22) “ጥንድ አክስል” ማለት በመንገድ ላይ የሚያርፈው ክብደት በተመጣጠነ መልክ እንዲሰራጭ ታስቦ
ዲዛይን የተደረገ ከ 1.2 ሜትር እስከ 2.5 ሜትር በሆነ ርቀት ውስጥ የተሳሰሩ ሁለት አክስሎች ስብስብ
ነው።
23) “ሚዛን” የተሽከርካሪዎች ክብደት የሚፈተሽበት ቋሚ ወይም ተንቀሳቃሽ የክብደት መለኪያ መሳሪያ
ማለት ነው፡፡
24) “የክብደት ተቆጣጣሪ” የክብደት ቁጥጥር ስራን የሚያከናዉን የኢንተርፕራይዙ ሠራተኛ ወይም የትራፊክ
ፖሊስ ማለት ነዉ፡፡
25) “ትርፍ ጭነት” ማለት ተሽከርካሪዉ ከተፈቀደለት የጭነት ክብደት ወሰን በላይ ሆኖ ሲገኝ ነዉ፡፡
26) “የክብደት ቁጥጥር ስራ” ማለት በቀን ለ 24 ሰዓት በሳምንት ለ 7 ቀናት ሳይቋረጥ በክብደት መቆጣጠሪያ ሲስተም እና
በተቆጣጣሪ ሰራተኞች እገዛ የሚሰራ የሥራ ዓይነት ነዉ፡፡
27) “የክብደት መቆጣጠሪያ ጣቢያ” ማለት የከባድ ተሸከርካሪዎች ክብደት ፍተሻ በሲስተም እና በተቆጣጣሪ ሰራተኞች
አማካኝነት ቁጥጥር የሚደረግበት ቦታ ነዉ፡፡
28) “አደገኛ ቁሶች ”ማለት በባህሪያቸዉ አደገኛ ወይም መርዛማ የሚባሉ ሲሆኑ በመንገዱ ደህንነት ላይ የአደጋ ስጋት
የሚፈጥሩ ዓይነት ናቸዉ፡፡
29) “ የክብደት መስፈርት”ማለት በመንገዱ ዲዛይን ወቅት የአስፓልቱ ክብደትን የመሸከም አቅም በጥናት ታዉቆ
በተሽከርካሪዎች የክብደት ቁጥጥር መመሪያ ዉስጥ እንደመለኪያ የሚካተት መስፈርት ማለት ነዉ፡፡
30) በወንድ ፆታ የተገለጸው አነጋገር የሴትን ፆታ ያጠቃልላል፡፡

አንቀፅ 3. የተፈፃሚነት ወሰን

ይህ መመሪያ በሞተር ሀይል በሚሰሩ በሁሉም ተሸከርካሪና ተሳቢ ጠቅላላ ክብደታቸዉ ከ 3500 ኪሎ ግራም
በላይ ጭነት ጭነው የፍጥነት መንገዱን የሚጠቀሙ ተሸከርካሪዎች ላይ ተፈፃሚነት አለው፡፡

አንቀፅ 4. የተሸከርካሪዎችን መጠን ስለመወሰን

ማናቸውም ባለሞተር ተሽከርካሪ፣ ተሳቢ ወይም ግማሽ ተሳቢ ጭነት ቢኖረውም ባይኖረውም፡-

ሀ. የተሽከርካሪ፣ የተሳቢ ወይም የግማሽ ተሳቢ ጠቅላላ የጎን ስፋት ከውጭ በኩል ተለክቶ ከ 2.65
ሜትር መብለጥ የለበትም፡፡

3
ለ. የተሸከርካሪ፣ ተሳቢ ወይም ግማሽ ተሳቢ ጠቅላላ ከመንገድ ከፍታው ጭነቱን ጨምሮ ከ 4.60
ሜትር መብለጥ የለበትም፡፡

ሐ. የማናቸውም ነጠላ ባለሞተር ተሽከርካሪ ፣ የፊትና የኋላ መከላከያዎቹን ጨምሮ ጠቅላላ


ርዝመቱ ከ 12.50 ሜትር መብለጥ የለበትም፡፡

መ. የተጣመረ ተሽከርካሪ ወይም ባለሞተር ተሸከርካሪ ከነተሳቢው ጭነት ቢኖረውም


ባይኖረውም የፊትና የኋላ መከላከያዎቹን ጨምሮ ጠቅላላ ርዝመቱ ከ 19 ሜትር መብለጥ
የለበትም፡፡

ሠ. የተሽከርካሪ መጫኛ ከነተሳቢው ወይም ጎታች ተሸከርካሪ ለተሸከርካሪ መጓጓዣ ብቻ


ከተሠራ ግማሽ ተሳቢ ጋር ወይም ጎታች ተሸከርካሪ ከሎቤድ ግማሽ ተሳቢ ጋር ጭነት
ቢኖረውም ባይኖረውም ከፊትና ከኋላ መከላከያዎቹ ጭምር ተለክቶ ጠቅላላ ርዝመቱ
ከ 22 ሜትር መብለጥ የለበትም፡

ረ. ማንኛቸውም ተቀጣጣይ የሆኑ ተሸከርካሪዎች፣ ተሳቢዎች ወይም ግማሽ ተሳቢዎች


በአንድ ጊዜ ተቀጣጥለው ሲጓዙ ቁጥራቸው ከሁለት መብለጥ የለበትም፡፡

ሰ በዚህ መመሪያ ከተፈቀደው የበለጠ ስፋት ወይም ርዝመት የተገኘበት ተሽከርካሪ ባለንብረት
ብር 5000 ይቀጣል፡፡

አንቀፅ 5. ያፈነገጠ ወይም የተንጠለጠለ ጭነት እንዳይጫን ስለመከልከሉ

ማናቸውም ጭነት ከተሸከርካሪ ፊት መጨረሻ ካለው አካሉ ከአንድ ሜትር በላይ ማለፍ የለበትም እንዲሁም
ማናቸውም ተሸከርካሪ፣ ተሳቢ፣ ግማሽ ተሳቢ፣ ሎቤድ ግማሽ ተሳቢ ወይም የተሸከርካሪ ማጓጓዣ ግማሽ
ተሣቢ ከመጫኛ አካሉ ከበስተኋላው ከሁለት ሜትር ተርፎ ውጭ የዋለ ጭነት ይዞ ማጓጓዝ አይችልም፡፡ ይህም
ሲሆን በዚህ መመሪያ አንቀጽ 10 መሰረት በተሰጠ ልዩ ፈቃድ ካልሆነ በቀር ተሸከርካሪው ከነጭነቱ ጠቅላላ
ርዝመቱ ከ 22 ሜትር መብለጥ የለበትም፡፡

አንቀፅ 6. የተሽከርካሪዎችን የመጫን አቅም ስለመወሰን

አንድ ተሸከርካሪ ለምዝገባ ሲቀርብ የክብደት መጠኑ የሚወሰነው አምራቹ የሚያቀርበውን የቴክኒክ
መመዘኛ ማንዋል ታሳቢ ያደረገ ሆኖ፤ በዚህ መመሪያ ከተገለፀው የክብደትና የመጠን ወሰን መብለጥ
የለበትም፡፡

4
አንቀፅ 7. የተሽከርካሪዎችን ክብደት ስለመወሰን (የተፈቀደ የተሽከርካሪ አክስል ክብደት)

1. በማንኛውም የኢትዮጵያ መንገድ ላይ እንዲነዳ የተፈቀደ የተሸከርካሪ አክስል ክብደት ወሰን


እንደሚከተለው ነው፤

ሀ) የመሪ አክስል 8 ቶን

ለ) የማይነዳ ነጠላ አክስል 8 ቶን

ሐ) የማይነዳ ነጠላ አክስል ጥንድ ጎማዎች 10 ቶን

መ) ጥንድ አክስል 18 ቶን

ሠ) ባለ ሶስት አክስል 25 ቶን

2. ከላይ ከተቀመጠው የአክስል ጭነት በላይ በአጫጫን ምክንያት በትርፍነት ቢገኝ የሚፈቀደው
ትርፍ ክብደት እንደሚከተለው ሆኖ፤ ነገር ግን በአንቀጽ 8 ከተቀመጠው የተፈቀደ ጠቅላላ
ክብደት ወሰን መብለጥ የለበትም፤

ሀ) የመሪ አክስል 1 ቶን

ለ) የማይነዳ ነጠላ አክስል 1 ቶን

ሐ) የማይነዳ ነጠላ አክስል ጥንድ ጎማዎች 1 ቶን

መ) ጥንድ አክስል ተሸከርካሪ 2 ቶን

ሠ) ባለ ሶስት አክስል ተሸከርካሪ 2.5 ቶን

3. በዚህ መመሪያ በአንቀፅ 7(1 እና 2) መሰረት ትርፍ የተገኘበት ተሽከርካሪ የሚጣልበት ቅጣት
በሚከተለው ሰንጠረዥ ላይ በሰፈረው መሰረት ይሆናል፡፡

ትርፍ ጭነት በቶን የቅጣት መጠን በብር


እስከ 1 ቶን 2000
ከ 1 በላይ- እስከ 2 4200
ከ 2 በላይ- እስከ 3 6500

5
ትርፍ ጭነት በቶን የቅጣት መጠን በብር
ከ 3 በላይ- እስከ 4 9000
ከ 4 በላይ- እስከ 5 12000
ከ 5 በላይ- እስከ 6 16000
ከ 6 በላይ- እስከ 7 20000
ከ 9 በላይ- እስከ 8 25000
ከ 8 በላይ- እስከ 9 30000
ከ 9 በላይ- እስከ 10 36000
ከ 10 ቶን በላይ 42000

አንቀፅ 8. የተፈቀደ ጠቅላላ ክብደት ወሰን

1. በዚህ መመሪያ አንቀጽ 7 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም ተሽከርካሪ ከነተሣቢው፣ ግማሽ


ተሣቢው፣ ሎቤድ ግማሽ ተሣቢ ወይም የተሽከርካሪ ማጓጓዣ ግማሽ ተሣቢ ጭነቱን ጨምሮ ጠቅላላ
ክብደቱ ከዚህ በታች እንደተመለከተው ሲሆን በማንኛውም ሁኔታ ከ 59 ቶን መብለጥ የለበትም፡፡

ተ.ቁ የተሸከርካሪው የአክስል አቀማመጥ የተሸከርካሪው ጠቅላላ ክብደት በቶን


1 1.2 8+10 18
2 1.22 8+18 26
3 1.1.22 8+8+18 34
4 1.2.2 8+10+10 28
5 1.2.22 8+10+18 36
6 1.22.22 8+18+18 44
7 1.2.222 8+10+25 43
8 1.22.222 8+18+25 51
9 1.2+2.2 8+10+10+10 38
10 1.2+2.22 8+10+10+18 46
11 1.22+2.2 8+18+10+10 46
12 1.22+2.22 8+18+10+18 54
13 1.1.22.222 8+8+18+25 59

2. በዚህ መመሪያ ላይ ከተፈቀደው ጋር ሲነፃፀር በተሽከርካሪው ጠቅላላ ክብደት ትርፍ የተገኘበት


ተሽከርካሪ ለትርፉ ጭነት የሚጣልበት ቅጣት በሚከተለው ሰንጠረዥ ላይ በሰፈረው መሰረት
ይሆናል፡፡

ትርፍ ጭነት በቶን የቅጣት መጠን በብር ትርፍ ጭነት በቶን የቅጣት መጠን በብር
እስከ 1 ቶን 1000 ከ 10 በላይ- እስከ 11 18600
ከ 1 በላይ- እስከ 2 2100 ከ 11 በላይ- እስከ 12 22200

6
ትርፍ ጭነት በቶን የቅጣት መጠን በብር ትርፍ ጭነት በቶን የቅጣት መጠን በብር
ከ 2 በላይ- እስከ 3 3200 ከ 12 በላይ- እስከ 13 26400
ከ 3 በላይ- እስከ 4 4400 ከ 13 በላይ- እስከ 14 31000
ከ 4 በላይ- እስከ 5 5600 ከ 14 በላይ- እስከ 15 36400
ከ 5 በላይ- እስከ 6 7200 ከ 15 በላይ- እስከ 16 42000
ከ 6 በላይ- እስከ 7 9000 ከ 16 በላይ- እስከ 17 47800
ከ 7 በላይ- እስከ 8 11000 ከ 17 በላይ- እስከ 18 54000
ከ 8 በላይ- እስከ 9 13200 ከ 18 በላይ- እስከ 19 60800
ከ 9 በላይ- እስከ 10 15800 ከ 19 በላይ- እስከ 20 68000
ከ 20 ቶን በላይ 80000
አንቀፅ 9 ከተፈቀደው ውጪ የሆነ ተሽከርካሪን መንዳት ስለ መከልከሉ

በአንቀጽ 10 መሠረት በተሰጠ ልዩ ፈቃድ ካልሆነ በቀር ማንኛውም ሰው ክብደትና መጠኑ በዚህ ደንብ
የተወሰነውን የማያሟላ ማናቸውንም ተሽከርካሪ በፍጥነት መንገዱ ላይ ለመንዳት ወይም እንዲንዳ
ለማድረግ ወይም ለመፍቀድ አይችልም፡፡ እንዲሁም ማንኛዉም የተቆጣጣሪ ሰራተኛ በመንገዱ ላይ
እንዲጓዝ መፍቀድ አጥብቆ የተከለከለ ነዉ፡፡

አንቀፅ 10 ስለ ልዩ ፈቃድ አሰጣጥ

ሀ. ኢንተርፕራይዝ መ/ቤቱ በቅድሚያ በሚቀርብለት አግባብነት ያለዉ ጥያቄ መሰረት በዚህ ደንብ
ከተወሰነው በላይ የሆነ መጠን ወይም ክብደት ያለው ተሽከርካሪ የፍጥነት መንገዱንና ድልድዩን አደጋ ላይ
ሊጥል በማይችል መልኩ በአንድ የመንገድ መስመር ላይ ለመጓዝ እንዲችል አስፈላጊና ትክክል መስሎ
በሚታየው አኳኋን ልዩ ፈቃድ ለመስጠት ይችላል፡፡

ለ) ለተሽከርካሪው የሚሰጠው ልዩ ፈቃድ የተሽከርካሪውን አክስሎች ክብደት ወይም የተሽከርካሪውን


ጠቅላላ ክብደት፤ ጭነቱን፤ የአጃቢ አስፈላጊነትን፤ የማስጠንቀቂያ መብራትና መሳሪያ መጠቀምን፤ ጉዞው
የሚከናወንበትን ጊዜ፤ እንዲሁም ጭነቱን የመንገድና የአካባቢ ደህንነት በተጠበቀበት ሁኔታ ለማጓጓዝ
አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎችን የሚገልጽ መሆን አለበት፡፡

ሐ) ልዩ ፈቃድ መጠየቂያ ማመልከቻ በጽሁፍ በፋክስ ወይም በኢሜል የሚቀርብ ሲሆን በውስጡም
የጭነቱ አስፈላጊነት፤ የተሸከርካሪውን መጠን፤ የጭነት ክብደት፤ የሚጓዝበትን መንገድ፤ የሚጓጓዝበት
ተሸከርካሪ የአክስል ብዛትና አቀማመጥ፤ የሚንቀሳቀስ አካልና ኢንተርፕራይዝ መ/ቤቱ የሚጠይቃቸውን
ሌሎች መረጃዎች መያዝ አለበት፡፡

መ) ልዩ ፈቃዱ የሚሰጠው ለአንድ ተሸከርካሪ ወይም በጣምራ ለሚጓዙ ተሸከርካሪዎች ለአንድ ጉዞ


ወይም በተወሰነ ወቅት ለሚደረግ ጉዞ ሊሆን ይችላል፡፡

7
ሠ) የተሰጠው ልዩ ፍቃድ በጉዞ ጊዜ ከተሽከርካሪው ጋር መኖር ያለበት ሲሆን ማንኛውም የመንገድ
ደህንነት ባለሙያ ወይም ትራፊክ ፖሊስ በጠየቀ ጊዜ መቅረብ አለበት፡፡

ረ) የልዩ ፈቃድ ቢኖርም እንኳ የተሸከርካሪው ባለቤት በመንገዱ ላይ ለሚደርስ ማንኛዉም አይነት ጉዳት
ተጠያቂ ይሆናል፡፡

ሰ) በመንገዶች እና በድልድዮች ላይ የሚደርሰዉን አደጋ ለመከላከል ሲባል በዚህ አንቀጽ ስለፈቃድ


አሰጣጥ የተደነገገዉ መመሪያ በኢንተርፕራይዙ ወቅታዊ ዉሳኔዎች ላይ በመመስረት
ተለዋዋጭነት ሊኖረዉ ይችላል፡፡

ሸ) እንደኢንተርፕራይዙ አመለካከት አሁን ላይ ያለዉ የፈቃድ አሰጣጥ የማይጣጣም ሆኖ ካተገኘ


ወይም የልዩ ፈቃድ ተሰጪ ተሽከርካሪዎች ከዚህ መመሪያ አሰራር ጋር ተስማሚነት እንደሌላቸዉ
ከተረጋገጠ የልዩ ፈቃዱን በራሱ ዉሳኔ ማሳለፍ ይችላል፡፡ ኢንተርፕራይዙ በልዩ ፈቃዱ መሟላት
የሚኖርበት ሁኔታ ሳይሟላ የቀረ ወይም ተሽከርካሪው በዚህ መመሪያ በሰፈረው መሰረት
እየተንቀሳቀሰ እንዳልሆነ ከተረዳ ልዩ ፈቃዱን ሊሰርዝ ይችላል፤

ቀ) በዚህ አንቀፅ ዉስጥ ከንዑስ አንቀጽ (ሀ) እስከ (በ) ከተጠቀሰዉ ዉጪ ማንኛዉም ተሽከርካሪ
ወይም በአንድ ላይ የተገናኘ ተሽከርካሪ በዚህ መመሪያ በተፈቀደዉ የከፍተኛ ክብደት ወሰን
ዉስጥ ካልተመዘገበ ኢንተርፕራይዙ በዚህ አንቀፅ ስር የተቀመጡትን የልዩ ፈቃዶች አለመስጠት
ይችላል፡፡

አንቀፅ 11. የሚዛን መቆጣጠሪያ ጣቢያ ስለማዘጋጀት

ኢንተርፕራይዙ ለክብደት ቁጥጥር ስራ የሚያገለግሉ ሚዛኖችንና ሌሎች መመርመሪያ


መሳሪያዎችን በተመረጡ የመንገዱ ክልሎች ውስጥ በማዘጋጀትና በትራፊክ ምልክቶች
አማካኝነት በማመላከት ማንኛውንም ተሸከርካሪ የመመዘንና የመመርመር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡

አንቀፅ 12. የመመርመር ሥልጣን

ሀ) ኢንተርፕራይዙ የማናቸውንም ተሽከርካሪ አክስል ክብደት እና ጠቅላላ ክብደት በመለካትና


በመመርመር ይህንን መመሪያ የማስፈጸም ሥልጣን ተሰጥቶታል፤

ለ) ኢንተርፕራይዙ የማናቸውም ተሽከርካሪ የጭነት ከፍታ፣ የጎን ስፋትና ርዝመት በዚህ መመሪያ
ድንጋጌ መሠረት ለመቆጣጠር ሥልጣን ይኖረዋል፡፡

ሐ) ሚኒስቴሩ ይህንን መመሪያ ለማስፈጸም የሚያስችል መመሪያ ሊያወጣ ይችላል፤

8
መ) የክብደት ተቆጣጣሪው፤ ተሽከርካሪውን ለመመዘንና ለመመርመር ተገቢ የሆኑትን ተግባራት
ይፈጽማል፡፡

አንቀፅ 13.የመቆጣጠር ስልጣን

ሀ) የክብደት ተቆጣጣሪ ወይም ትራፊክ ፖሊስ ማንኛውንም የጭነት ተሽከርካሪ ኢንተርፕራይዙ


ባቋቋመው የሚዛን ጣቢያ እንዲገባ በማድረግ ተሽከርካሪው ክብደቱ እንዲመዘን የማድረግ ስልጣን
አለው፡፡

ለ) የክብደት ተቆጣጣሪ ወይም ትራፊክ ፖሊስ ማናቸውም የጭነት ተሸከርካሪ የዚህን መመሪያ
ድንጋጌዎች ያላከበረ መሆኑን ለማመን የሚያስችል ምክንያት ሲኖረው ተሸከርካሪውን በማናቸውም
ስፍራ አስቁሞ የአሽከርካሪውን የመንጃ ፈቃድ ለመጠየቅና ተሸከርካሪው አመቺ በሆነ ስፍራ መጠኑ
እንዲለካና ክብደቱ እንዲመዘን የማድረግ ስልጣን አለው፡፡

ሐ) የክብደት ተቆጣጣሪ ወይም ትራፊክ ፖሊስ ማናቸውም የጫነ ተሸከርካሪ የዚህን መመሪያ
ድንጋጌዎች ተላልፎ ያገኘውን ተሸከርካሪ ጉዞውን እንዲቀጥል ከመፍቀዱ በፊት የምርመራውን
ውጤት፣የተሸከርካሪውን የሰሌዳ ቁጥር፣የባለቤቱንና የአሽከርካሪውን ስም መመዝገቡን እና
አሽከርካሪው ይህን ደንብ በመተላለፍ የሚከሰስ መሆኑን ማሳወቅ አለበት፡፡

መ) በዚህም የጥፋተኛዉን ህጋዊ መረጃዎችን እንዲቆጣጠር እና እንዲረከብ ( ታርጋ ፣ መንጃ ፍቃድ


፣ ሊብሬ ) የመሳሰሉትን ሃላፊነት የተሰጠዉ

አንቀፅ 14. የመለካት ሥርዓት

1. ትርፍ ጭነት በተገኘ ጊዜ የክብደት ተቆጣጣሪው ከሚዛኑ የተገኘውን ንባብ የሚያመለክት ሰነድ
ያዘጋጃል፤ አሽከርካሪውም ጭነቱ በአግባቡ መመዘኑንና ንባቡም ትክክለኛ መሆኑን በማረጋገጥ
ይፈርማል፡፡ አሽከርካሪው በሰነዱ ላይ ለመፈረም ፈቃደኛ ባይሆን እንኳ ኢንተርፕራይዙ
ቅጣቱን እንዳያስከፍል አያግደውም፤
2. የተሸከርካሪው የአክስልና ጠቅላላ ክብደት በሕግ በተቀመጠው መሰረት ሆኖ ከተገኘ
ለአሽከርካሪው የሚሰጠው የሚዛን ንባብ ጉዞውን እስከሚያጠናቅቅ ድረስ እንደ ይለፍ
ሊያገለግለው ይችላል፡፡ ሆኖም ይለፍ ከተሰጠው በኋላም ቢሆን ተሸከርካሪው ተጨማሪ ጭነት
ያለመጫኑን ለማረጋገጥ በየትኛውም ሚዛን ጣቢያ ወይም ተንቀሳቃሽ ሚዛን እንዲመዘን
ሊጠየቅ ይችላል፡፡ በድጋሚ በሚመዘንበት ወቅት ክብደቱ ከቀድሞው ንባብ ልዩነት ያለው ሆኖ
ከተገኘ ሌላ የሚዛን ንባብ ሰነድ ይሰጠዋል፤

9
3. ጉዞውን ያላጠናቀቀ ተሽከርካሪ በህግ ከተፈቀደዉ የክብደት ወሰን በላይ ብዙ የትርፍ ጭነት
የተገኘበት ከሆነ ትርፉን ጭነት በአቅራቢያዊ በሚገኝ የክፍያ ጣቢያ በመዉጣት አሽከርካሪዉ
ወይም የተሽከርካሪዉ ባለቤት እራሱ ባዘጋጀዉ የጭነት ማራገፊያ ጭነቱን አመጣጥኖ የፍጥነት
መንገዱን ሊጠቀም ይችላል፡፡

አንቀፅ 15. የክብደት ወሰንን ስለማሳየት እና መቀነስ

1. ኢንተርፕራይዙ ለተወሰነ አሳማኝ የጊዜ ገደብ የተፈቀደዉን የተሽከርካሪዎች አክስል ክብደት


ወይም አጠቃላይ የተሽከርካሪዎች ክብደት ሊቀንስ እንዲሁም ላልተወሰነ ጊዜ ዝቅተኛ
የክብደት መጠን ወሰን ተፈጻሚ ሊያደርግ ይችላል፡፡
2. ኢንተርፕራይዙ እንደዚህ ዓይነት የክብደት መጠን ቅነሳ ወይም ያልተወሰነ ጊዜ የክብደት
መጠን ወሰን ማስተካከያ በሚያደርግበት ጊዜ በመንገድ ላይ ምልክቶች አማካኝነት ግልፅ በሆነ
መልኩ ተፈጻሚነት በሚኖርባቸዉ ስፍራዎች ፣ ድልድዮች ወይም መንገዶች ላይ ከተፈቀደዉ
የክብደት ወሰን በላይ ሆነዉ በመንገዱ ወይም ድልድዮቹ ላይ ለሚገለገሉ ተሽከርካሪዎች
ከጥብቅ ማስጠንቀቂያ ጋር ምልክቶችን ማስቀመጥ ይችላል፡፡

አንቀፅ 16. ክብደትን ስለመመዘን

1) ተሸከርካሪ ሲመዘን ከክብደት በላይ ሆኖ ከተገኘ ይህን የሚያሳይ ደረሰኝ ለአሽከርካሪው


ይሰጠውና ባለንብረቱን ወክሎ እንደተስማማ በማሰብ ይፈርምበታል፡፡
2) በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 አሽከርካሪው ባለንብረቱን ወክሎ የሚፈርመው ወረቀት
ተሸከርካሪው ከክብደት በላይ መጫኑና የሚያረጋግጥ ሲሆን አሽከርካሪው ሳይፈርም ቢቀርም
ኢንተርፕራይዙ ቅጣት ከመጣል አያግደውም፡፡
3) አሽከርካሪው በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 የተሰጠውን ደረሰኝ በሚያደርገው ጉዞ እስከ
መድረሻዉ ድረስ ይዞ መንቀሳቀስ ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በሌላ
ሚዛን ጣቢያ እንደገና ስላለመጫኑ ወይም የማጭበርበር ስራ ስላለመፈፀሙ ሊፈተሽ ይችላል፡፡
4) በዚህ አንቀፅ ከ 1-3 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ተሽከርካሪው ከተፈቀደለት ክብደት በላይ
ጭኖ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ከተደረሰበት ተሸከርካሪው ትርፍ ጭነቱን ካልቀነሰ ወይም ለአክስሎቹ
በማከፋፈል መስተካከሉ ካልተረጋገጠ በስተቀር ጉዞውን እንዲያቋርጥ ይደረጋል፡፡

አንቀፅ 17. ይህ ደንብ የማይፀናባቸው

10
1) በዚህ ደንብ ዉስጥ ከአንቀፅ 4-8 የተጠቀሱት የተሸከርካሪዎች የተፈቀደ የአክስል ክብደት ወሰን
፤የተፈቀደ የተሽከርካሪ አጠቃላይ ክብደት ወሰን እና የተፈቀደ የተሽከርካሪ መጠን ወሰን
በሚከተሉት የሞተር ተሸከርካሪዎች ላይ ተግባራዊነት አይኖረዉም፡፡

ሀ. የእሳት አደጋ ለመከላከል በሚሰማሩ ተሸከርካሪዎች፤

ለ. የተፈጥሮ አደጋን ለመከላከል በሚሰማሩ ተሽከርካሪዎች፤

ሐ. ለአደጋ ጊዜ መልሶ ማልማት በሚሰማሩ ተሽከርካሪዎች፤

መ. እንዲሁም ኢትዮጵያ ከሌላ ሀገር መንግስት ጋር በምታደርገው የጋራ ስምምነት መሰረት


ለብሔራዊ ደህንነት ወታደሮችና የመከላከያ መሳሪያዎችን ጭነው የሚንቀሳቀሱ
ተሸከርካሪዎችን አይመለከትም፡፡

2) በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 በተደነገገው ላይ ኢንተርፕራይዝ መስሪያ ቤቱ መመሪያ ሊያወጣ


ይችላል፡፡
3) በመንገድ ግንባታ አካባቢ ስራ የሚሰሩ የመንገድ ግንባታ ማሽነሪዎች በዚህ ደንብ በአንቀፅ 4
ከተቀመጠዉ የተሽከርካሪዎች የመጠን ወሰን ነፃ ናቸዉ ፡፡

አንቀፅ 18. አክስል ስለማነሳት

አክስልን ወደላይ ማንሳት የሚቻለው ተሸከርካሪው ምንም ጭነት ባልጫነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡

አንቀፅ 19. ደንቡን ስለማስፈጸም

1) ማናቸውም ተሽከርካሪ በዚህ ደንብ ከተፈቀደው በላይ ትርፍ ጭነት ጭኖ ከተገኘ ኢንተርፕራይዙ
የክብደት ቁጥጥር በማካሄድ ይህንን ደንብ ያስፈጽማል፤
2) ተሽከርካሪው በአክስሉ ትርፍ ጭነት የጫነ ሆኖ ከተገኘ የተሽከርካሪው ባለቤት በዚህ ደንብ ለትርፍ
ጭነት የተቀመጠውን ክፍያ የመክፈል ሃላፊነት አለበት፡፡
3) ማንኛውም ተሽከርካሪ ትርፍ ጭነት ቢጭንም ባይጭንም የሚዛን ጣቢያ ውስጥ ገብቶ መመዘን
ሲገባው ሳይመዘን ጣቢያውን አልፎ ቢገኝ አሽከርካሪው ብር 2000 ይቀጣል፡፡
4) ተሽከርካሪው ጭነት ጭኖ ሳለ ማንኛውም የተሽከርካው አክስል ወደላይ ተነስቶ ከተገኘ አክስሉ
ወደታች ዝቅ እንዲል ተደርጎ አሽከርካሪው ብር 2000 (ሁለት ሺህ) ብር ይቀጣል ፡፡

11
5) በዚህ ደንብ መሰረት በኢንተርፕራይዙ ወይም በፖሊስ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ያለመፈጸም ጥፋት
ሲሆን ትዕዛዙ እስኪፈጸም ድረስ ተሸከርካሪው ወይም ጭነቱ በተሸከርካሪው ባለቤት ኃላፊነት ተይዞ
ይቆያል፡፡
6) በዚህ ደንብ ለትርፍ ጭነት የተቀመጠው ክፍያ በ 7 ቀናት ውስጥ ካልተከፈለ የተሽከርካሪው ባለቤት
በቀጣይ 15 ቀናት ውስጥ በመጀመሪያ የተጣለውን ቅጣት 1.20 ተባዝቶ የሚከፍል ሲሆን ባለሥልጣኑ
ይህንኑ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ በተሽከርካሪው ላይ ይለጥፋል፡፡
7) የመጀመሪያው ማስጠንቀቂያ በተሰጠ በ 15 ቀናት ውስጥ ክፍያው ካልተከፈለ የተሽከርካሪው ባለቤት
በቀጣይ 15 ቀናት ውስጥ በመጀመሪያ የተጣለውን ቅጣት በ 1.50 ተባዝቶ ተባዝቶ የሚከፍል ሲሆን
ባለሥልጣኑ ይህንኑ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ በተሸከርካሪው ላይ ይለጥፋል፡፡ በዚህ ማስጠንቀቂያ
ላይም የተጠቀሰው ክፍያ ሁለተኛው ማስጠንቀቂያ በተሰጠ በ 15 ቀናት ውስጥ ካልተከፈለ ክፍያው
በመጀመሪያ የተጣለውን ቅጣት እጥፍ ይሆናል፤ ይህም በማስጠንቀቂያው ላይ ይገለጻል፡፡
አንቀፅ 20. ከክብደት በላይ ጭነት ክፍያዎች

1) ተሽከርካሪው ከተመዘገበበት የጭነት ልክ በላይ ትርፍ ጭነት ይዞ ከተገኘ የተሸከርካሪው ባለቤት


ለትርፉ ጭነት በዚህ ደንብ የተቀመጠውን ክፍያ ይከፍላል፡፡
2) ተሸከርካሪው ትርፍ ጭነት የተገኘበት በአክስሉ እንዲሁም በጠቅላላ ክብደቱ ላይ ከሆነ ከሁለቱ
ከፍተኛ የሆነውን የቅጣት ክፍያ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡
3) በዚህ ደንብ ውስጥ ከክብደት በላይ ለተጫነ ጭነት የሚከፈል ክፍያ ከተሸከርካሪው ጋር
በተያያዘ በትራፊክ ህግ በወንጀል ሊያስቀጡ ከሚችሉ ቅጣቶች አያስቀርም፡፡

አንቀፅ 21. ቅጣትን የመጣልና የማስከፈል ሥርዓት

1. በአንቀጽ 14 የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ በሚዛን ጣቢያው በሚዘጋጀው የሚዛን ንባብ ትርፍ


ጭነትን ለመለየትና በዚህ መመሪያ መሰረት የተቀመጠውን ክፍያ ለማስከፈል መሰረት ይሆናል፡፡ ትርፍ
ጭነት በተገኘ ጊዜ ኢንተርፕራይዙ በደንቡ ላይ የተቀመጠውን ክፍያ የማስከፈል ሃላፊነት አለበት፡፡
2. አሽከርካሪው በሚዛን ንባቡ ሰነድ ላይ የተመለከተውን ትርፍ ጭነትና የክፍያ መጠን ለተሸከርካሪው
ባለቤት የማሳወቅ ሃላፊነት ያለበት ሲሆን ክፍያውን የመክፈል ሃላፊነት ያለበት የተሸከርካሪው ባለቤት
ነው፡፡ ሆኖም ክፍያውን በአካል ቀርቦ የሚፈጽመው የተሸከርካሪው ባለቤት ወይም ተወካዩ ወይም
አሽከርካሪው ሊሆን ይችላል፡፡

12
3. ትርፍ ጭነቱ በተጎታቹ ላይ ያረፈ ሆኖ ሲገኝ ለትርፍ ጭነቱ ተጠያቂ የሚሆነውና ለትርፍ ጭነት
የተጣለውን ክፍያ የመክፈል ሃላፊነት ያለበት የጎታቹ ባለሞተር ተሸከርካሪ ባለቤት ነው፡፡
4. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ 2 ተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ክፍያውን የሚፈጽመው የጎታቹ ተሽከርካሪ
ባለቤት ወይም አሽከርካሪው ነው፡፡
5. ለትርፍ ጭነት የሚከፈለው ክፍያ በገንዘብ ወይም በቼክ ገቢ ለመንገድ ፈንድ በተዘጋጀው የባንክ ሂሳብ
ቁጥር ገቢ የሚደረግ ሆኖ ክፍያው ስለመፈፀሙ ባለንብረቱ ደረሰኝ ያቀርባል፡፡
6. ለትርፍ ጭነት የሚከፈለዉን ክፍያ በኢንተርፕራይዙ በተሰየመ ህጋዊ አካል መሰረት የገቢ አሰባሰብ ስራዉ
ይሰራል፡፡
7. ይህንን መመሪያ በማስፈፀም ተግባር ላይ የተሰማራ የኢንተርፕራይዙ ሰራተኛ በደንቡ ላይ ከሰፈረው
በተለየ መልክ ፈጽሞ ቢገኝ በሕግ መሰረት ይቀጣል፡፡
8. ኢንተርፕራይዙ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የክድት

አንቀፅ 22. የምልክት መብራትና መለያ

1 ማንኛውም ጭነት በተሸከርካሪውና በተሣቢው የኋለኛውን ቀይ መብራት እንዳይሸፍን ተደርጎ መጫን አለበት፡፡
2 መብራቱ ከኋላ ለሚከተሉት ተሽከርካሪዎች በግልፅ የማይታይ በሆነ ጊዜ ተሸከርካሪው፣ በሌሊት ሲጓዝም ሆነ ሲቆም
በጭነቱ በስተኋላ ላይ ቀይ መብራት ማድረግ አለበት፡፡
3 ተሽከርካሪው በቀን በሚጓጓዝበት ጊዜ በኋላ በኩል ጭነቱ ከወለሉ ተርፎ ውጭ የዋለ እንደሆነ ቢያንስ 30X30
ሣ.ሜ የሆነ በካሬ ቅርፅ የተሰራ ቀይ ጨርቅ በስተኋላ ከጭነቱ ጫፍ ላይ ማድረግ አለበት፡፡
4 ማንኛውም ጎታች ተሽከርካሪ ከሎቤድ ተሳቢ ጋር በመንገድ ላይ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በጎታች ተሽከርካሪው አናት
ላይ በተገጠመለት ብልጭ ድርግም የሚል ቢጫ መብራት ማሳየቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ቢያንስ 30X30 ሣ.ሜ የሆነ
በካሬ ቅርጽ የተሰራ ቀይ ጨርቅ በተጠቀሰው ጎታች ተሸከርካሪ ተሣቢው የፊትና የኋላ አራት ጫፎች ላይ
ማውለብለብ አለበት፡፡
ክፍል ሁለት

የስራ ክፍሎች ሃላፊነት

አንቀፅ 23. የክብደት ተቆጣጣሪ ሰራተኛ ሃላፊነቶች እና ተግባራት

ተጠሪነቱ ለክብደት ቁጥጥር ክፍል ሃላፊ ሲሆን የሚከተሉትን ዝርዝር ተግባራት ያከናዉናል፡፡

1 ለስራዉ የሚያስፈልጉትን የስራ ግብዓቶች በመያዝ ወደ ስራ ቦታዉ /ገበታዉ/ በመሄድ ለስራዉ ቅድመ ዝግጅት
ማድረግ ፡፡

13
2 ተቆጣጣሪ ሰራተኛዉ የክብደት ሚዛን ሲስተሙን መግቢያ በር ክፍት በማድረግ ለተጠቃሚዎች ወደ መቆጣጠሪያዉ
እንዲገቡ ምልክት ይሰጣል፡፡
3 ተመዛኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች የፍጥነት ገደባቸዉን በመቀነስ ወደ መቆጣጠሪያ ሲስተሙ እንዲገቡ መመሪያ
ያስተላልፋል፡፡
4 ማንኛዉንም ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ (ክብደቱ ከ 3500 ኪ.ግ. በላይ የሆነ ከባድ ጭነት የጫነ ተሽከርካሪ ) ሳይመዘን
እንዳያልፍ በንቃት መቆጣጠር፣ ተሽከርካሪዉ ወደ ክብደት ሚዛን ጣቢያዉ ከመድረሱ ቢያንስ ከሠላሳ ሜትር
አስቀድሞ ተሽከርካሪዉ ሳይመዘን እንዳያልፍ የሚከለክለዉን የትራፊክ ምልክት በማሳየት ወደ ክብደት መቆጣጠሪያዉ
እንዲገባ ያደርጋል፤
5 የሚመዘነዉ ተሸከርካሪ ሙሉ በሙሉ አክስሎቹን በሚዛኑ ላይ ማሳረፉን በማረጋገጥ የመረጃ ሰጪ ሰሌዳዉን
ይከታተላል፡፡
6 በተቀመጠዉ የክብደት መጠን መረጃ እና የአዉቶማቲክ ማገጃ ዘንግ (Automatic Railing) እንቅስቃሴ በመታገዝ
መኪናዉ የትርፍ ጭነት መጫን አለመጫኑን በማረጋገጥ ትክክለኛ ዉሳኔ ያስተላልፋል፡፡
7 አንድ ተሽከርካሪ በክብደት መቆጣጠሪያ ሚዛን ተመዝኖ ትርፍ ጭነት ጭኖ ሲገኝ ተሽከርካሪዉ የክፍያ መንገድ ክልል
ዉስጥ እንዳይገባ መከልከል አለበት፤
8 የቋሚ እና የተንቀሳቃሽ የክብደት ቁጥጥር ስራን በህጉ መሰረት የማስፈፅም እንዲሁም የመቆጣጠር ዓቢይ ሃላፊነት
አለበት ፤
9 ኢንተርፕራይዙ በሚያወጣዉ መምሪያ መሰረት ድንገተኛ የተንቀሳቃሽ ሚዛን ክብደት ቁጥጥር እንዲደረግ ትዕዛዝ
ሲተላለፍ የቁጥጥር ስራዉን የመስራት ግዴታ አለበት፤
10 ለቁጥጥር ስራዉ የተዘጋጁ የስራ ግብዓቶችን ወይም መሳሪያዎችን እና የክብደት ሚዛን ጣቢያ ንብረቶችን በአግባቡ
የመጠበቅ እና የመቆጣጠር እንዲሁም በሌላ አካል ንብረቶቹ ላይ አደጋ ሲደርስ በስራዉ ላይ የነበረ ተረኛ ተቆጣጣሪ
ሰራተኛ ለጣቢያ አስተባባሪ ሪፖርት የማድረግ ግዴታ አለበት፤
11 WIM (weigh-in-motion) ወይም የክብደት መቆጣጠሪያ ሚዛን ሲስተሙ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን በፍጥነት
ለቴክኒክ ባለሙያዎች ሪፖርት ማድረግ ወይም ለተረኛዉ ጣቢያ አስተባባሪ ማሳወቅ ይጠበቅበታል ፤
12 ተጠቃሚዎች በአካል በመገኘት ስለ ክብደት መቆጣጠሪያ ሲስተሙ ግድፈት እና ስለ ጫኑት ጭነት መጠን ለሚያነሱት
ቅሬታ ወይም አስተያየት በአግባቡ ትክክለኛ የሆነ ሙያዊ ምላሽ የመስጠት ሃላፊነት ሲኖርበት ሆኖም ችግሩን
ለመፍታት ካልቻለ ለሚቀጥለዉ የስራ ክፍል ወይም ለጣቢያ አስተባባሪ ሪፖርት ማድረግ ይኖርበታል፤
13 ከ መጠን (ክብደት፣ስፋት፣እርዝመት፣ቁመት) በላይ ጭነዉ የሚመጡ አሽከርካሪዎች ላይ ስለ ጉዳዩ የግንዛቤ
ማስጨበጫ ስራዎችን ይሰራል፤
14 ማንኛዉም ተረኛ የክብደት ሚዛን ተቆጣጣሪ ሰራተኛ ፈረቃዉ ከመድረሱ ከ ሰላሳ ደቂቃ በፊት በስራ ገበታዉ ላይ
አስቀድሞ መገኘት ይኖርበታል፡፡
15 የሚቀይረዉ ሰዉ የዘገየበት ወይም ያልመጣለት ተቆጣጣሪ ሰራተኛ ለጣቢያ አስተባባሪዉ ሪፖርት አድርጎ ዉሳኔ
መጠበቅ ይኖርበታል ሆኖም የሚዛን ጣቢያዉን በራሱ ዉሳኔ ዘግቶ እንዲሄድ አይፈቀድለትም፤

14
16 ማንኛዉም ሰራተኛ ፈቃድ ሲያስፈልገዉ ቢያንስ ከሁለት ቀናት በፊት ማሰወቅ አለበት እሱ በሚቀርበት ፈረቃ ሌላዉ
የስራዉ ባለደረባ የሚሸፍንለት ይሆናል፡፡
1. የቀን እና ማታ ተቆጣጣሪ ሰራተኞች ማድረግ የሚገባቸዉ
1 የቀን ፈረቃ የክብደት ተቆጣጣሪ ሠራተኛ ግዴታዎች
ሀ. የትራፊክ ማስቆሚያ ምልክት መያዝ፤
ለ. አንፀባራቂ ልብስ (የደንብ ልብስ) መልበስ ይኖርበታል፤
2 የማታ ፈረቃ የክብደት ተቆጣጣሪ ሠራተኛ ግዴታዎች
ሀ. ከትራፊክ ማስቆሚያ ምልክቱ በተጨማሪ በእጅ የሚያዝ ሆኖ በባትሪ ሃይል የሚሰራ የቅድመ ማስጠንቀቂያ
መሳሪያ ይዞ መገኘት ይኖርበታል ፤
ለ. አንፀባራቂ ጃኬት (የደንብ ልብስ) መልበስ ይኖርበታል፤
2. የጣቢያ አስተባባሪ ኃላፊነቶች እና ተግባራት

ተጠሪነቱ ለቶል ማኔጅመንት ቡድን ሆኖ የሚከተሉትን ዝርዝር ተግባራት ያከናዉናል፡፡

1 ተቆጣጣሪ ሰራተኛዉ በስራ ገበታዉ ላይ መገኘት አለመገኘቱን ማረጋገጥ በተጨማሪም በቀሪ ሰራተኛ የተነሳ የስራ
ክፍተት እንዳይፈጠር የሰራተኞ ሽግሽግ ያደርጋል፤
2 ከኢንፎርሜሽን ሞኒተሪንግ ክፍል ጋር በመተባበር የክብደት ቁጥጥር ስራዉን በካሜራ ዕይታ በመታገዝ በቅርበት
ይከታተላል፤
3 ተጠቃሚዎች በአካል በመገኘት ስለ ክብደት ሚዛኑ ትክክለኝነት እና ስለ ጫኑት ጭነት ክብደት ለሚያነሱት
ቅሬታ እና አስተያየት አግባብነት ባለዉ መልኩ ምላሽ ይሰጣል፤ ሆኖም ችግሩን በአቅሙ መመለስ ካልቻለ ጉዳዩን
ለበላይ የስራ ክፍል ኃላፊ ያስተላልፋል፤
4 በአሰራር ላይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ወይም ክፍተቶች መፍትሄ መስጠት ወይም ለቀጣይ አስተዳደር ክፍል ችግሩ
እልባት እንዲያገኝ በፍጥነት ያሳዉቃል፤
5 በክብደት መቆጣጠሪያ ሚዛን (Overload Detecting System) ላይ ለሚታዩ ጉልህ የቴክኒክ ብልሽቶች እና
ግድፈቶች በአስቸኳይ ለቴክኒክ ባለሙያዎች ሪፖርት ያደርጋል፤
6 በየቀኑ የቁጥጥር ስራ ሂደቱን በትኩረት ይቆጣጠራል፤ ከበላይ ሃላፊ የሚሰጡ መመሪያዎችን ወደ ተቆጣጣሪ
ሰራተኛዉ በማዉረድ ያስተገብራል እንዲሁም ይተገብራል፤
7 የተቆጣጣሪ ሰራተኞችን የስራ አፈጻጸም የመገምገም እና የመመዘን ጉልህ ሃላፊነት አለበት ፤
8 በሁሉም የክብደት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ለሚገኙ ሰራተኞች የግብዓት አቅርቦት በጥያቄያቸዉ መሰረት
ያቀርባል፤ከሚመለከታቸዉ የስራ ክፍሎች ጋር በመሆን የግዢ ፍላጎትን በማሳወቅ ግዢ እንዲፈፀም ያደርጋል፤
9 በተንቀሳቃሽ ሚዛን በመታገዝ የአክስል ሎድ ቁጥጥር ስራን ከሚመለከተዉ የበላይ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመነጋገር
እና በመወያየት በተቀናጀና ወጥነት ባለዉ የአሰራር ስርዓት ስራዉ እንዲሰራ ያስተባብራል፤ከሚመለከታቸዉ
ሌሎች የስራዉ ክፍሎች ጋር አብሮ ይሰራል፤

15
አንቀፅ 24. የክብደት መቆጣጠሪያ ሲስተም ባለሙያ ኃላፊነቶች እና ተግባራት

ተጠሪነቱ ለኤሌክትሮሜካኒካል ቡድን ሆኖ የሚከተሉትን ዝርዝር ተግባራት ያከናዉናል፡፡

1 የሁሉንም የክብደት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች መረጃ በአግባቡ በመሰብሰብ እና በመተንተን ስርዓት ባለዉ መልኩ
በሶፍት ኮፒ እና በወረቀት ያስቀምጣል፡፡
2 ከክብደት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች የእለት፣ወርሃዊ፣የዓመት የቁጥጥር መረጃዎችን በመሰብሰብ እና በመተንተን ሪፖርት
ያዘጋጃል ፣በመረጃዉ መሰረት እንደአስፈላጊነቱ ጥናታዊ የመረጃ ትንተና ይሰራል፤
3 ሁሉም የክብደት መቆጣጠሪያ ሚዛኖች ወጥነት ባለዉ መልኩ በተቀመጠላቸዉ የስነ-ልኬት ጊዜ ገደብ ዕዉቅና
በተሰጠዉ የክብደት ሚዛን መስፈርት አረጋጋጭ አካል በተቀመጠዉ የኢትዮጵያ ክብደት መስፈርት (Standard)
መሰረት የማነጻጸር ወይም የማስፈተሽ ስራ (Calibration Work) እንዲሰራ ያደርጋል፤ የፍተሻዉ ዉጤት
መስፈርቱን የሚያሟላ ሆኖ ሲገኝ የስነ-ልክ መስፈርት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት አሰርቶ ያመጣል፤
4 በተጨማሪም በታየዉ የልኬት ግድፈት መሰረት የማስተካከያ ስራዎች እንዲሰሩ ያደርጋል፤ ችግር ያለባቸዉን
መቆጣጠሪያ ሚዛኖች እንዲጠገኑ እና ስራቸዉን በአግባቡ እንሰሩ ከሚመለከተዉ አካል ጋር አብሮ ይሰራል ፡፡
5 የሶፍትዌር ወይም ሃርድዌር ሲስተም ጥገና ስራዎችን መልኩ መርሃ-ግብር በመንደፍ በበላይነት ይቆጣጠራል፣
ይተገብራል፡፡
6 ለክብደት መቆጣጠር ስራ የሚዉሉ አጋዥ ቴክኖሎጂ አዘል መሳሪያዎችን እና የስራ ግብዓቶችን መስፈርት እና ዲዛይን
በማዉጣት ግዢ እንዲፈጸም ያደርጋል ፡፡
አንቀፅ 25. የትራፊክ ፖሊስ ሃላፊነቶች

1 ማንኛዉም ከተፈቀደዉ ህጋዊ የጭነት መጠን በላይ ትርፍ ጭነት የጫነ ተሽከርካሪ ህጋዊ የልኬት መጠኑን
ካላስተካከለ ወደ ፈጣን መንገዱ እንዳይገባ ህግን በማስከበር ይተባበራል፤
2 ትርፍ ጭነት የጫነ ተሽከርካሪ ጭነቱን አመጣጥኖ ወደ ፈጣን መንገዱ መግባት እንደሚችል ለአሽከርካሪዉ ትዕዛዝ
ያስተላልፋል፤
3 አደገኛ ቁሶች ( Hazardous Materials ) የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ፈጣን መንገዱ ሲገቡ ተገቢዉ የጥንቃቄ ቅድመ
ሁኔታ የተሟላላቸዉ መሆኑኑ በማረጋገጥ ዉሳኔዎችን ያሳልፋሉ፤
4 ትርፍ ጭነት የሚጫኑትን እና ደንብ የሚጥሱትን በመቆጣጠር ለክብደት ቁጥጥር በወጣዉ ደንብ መሰረት በጥፋተኞቹ
ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፤
5 ከክብደት በላይ፣ከርዝመት በላይ ፣ከቁመት በላይ እና ከስፋት በላይ ጭነዉ ለሚመጡ አሽከርካሪዎች ተገቢዉን መረጃ
በመስጠት እንዲያስተካከሉ በማድረግ የለዉጥ ስራ መስራት፤
6 ማንኛዉም ከባድም ሆነ ቀላል ጭነት በተገቢዉ ተሸፍኖ መታሰሩን ጥብቅ ክትትል በማድረግ መቆጣጣር እና
መስተካከሉን በማረጋገጥ ወደ ፈጣን መንገዱ የክፍያ ጣቢያ እንዲገባ የማድረግ ስራን በተቀናጀና በተጠናከረ መልኩ
ማከናወን፤

16
7 ማንኛዉም ከባድ ተሸከርካሪዎች አሸዋ ፣ ጠጠር እና አፈር የመሳሰሉትን ጭነቶችን ከእስፖንዳ በላይ የሚጭኑ
ተሽከርካሪዎች ጭነታቸዉን በተገቢዉ መልኩ እንዲሸፈኑ ትዕዛዝ መስጠት ይጠበቅበታል፤
አንቀፅ 26. የመተባበር ግዴታ

ማንኛዉም ኃላፊ፤ የስራ መሪ ወይም ሰራተኛ የክብደት ቁጥጥሩ በደንቡ መሰረት መሆኑን ወይም
አለመሆኑን አቅጣጫ፣ መረጃ እንዲሁም ድጋፍ በመስጠት የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡

አንቀፅ 27. አሰራሩን ስለማሻሻል

የሥራ አመራር ቦርዱ የክብደት ቁጥጥር አሰራሩን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ካገኘዉ


ሊያሻሽለዉ ይችላል፡፡

አንቀፅ 28. የሃላፊነት ወሰን

በዚህ አሰራር ዉስጥ ከስራዉ ጋር ተያያዥነት ያላቸዉ ባለድርሻዎች በአሰራሩ መሰረት


የተጣለባቸዉን ኃላፊነት ያልተወጡ እንደሆነ በኢንተርፕራይዙ ደንብና መመሪያ መሰረት
ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡
አንቀፅ 29. ተፈፃሚነት የሌለው የውስጥ አሠራር ደንብ
ይህንን የዉስጥ የአሠራር ደንብ የሚቃረን ማንኛዉም የውስጥ መመሪያ ወይም ልማዳዊ
አሰራር በዚህ ደንብ በተሸፈኑት ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖረዉም፡፡
አንቀፅ 30. ደንቡን ስለማሻሻል
ይህ የዉስጥ የአሠራር ደንብ በማንኛዉም ጊዜ ሊሻሻል ይችላል፡፡
አንቀፅ 31.ደንቡ የሚጸናበት ጊዜ

ይህ የዉስጥ አሠራር ደንብ ከ-----ቀን ------ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡
አዲስ አበባ…………….መስከረም/2009 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ሥራ አመራር ቦርድ

-----------------------------------------------

17

You might also like