Urban Agriculture Policy Reform Points From Urban Land Team

You might also like

Download as docx, pdf, or txt
Download as docx, pdf, or txt
You are on page 1of 8

የከተማ መሬት ለከተማ ግብርና ከሚሰጠው አስተዋዕፆ የሚታዩ

ተግዳሮቶች እና ማነቆዎች አንጻር የቀረቡ የፖሊሲ ማሻሻያ ምክረ


ሃሳብ፤

የከተማ መሬት ንዑስ ቴክኒካል ኮሚቴ አባላት ዝርዝር

1/ አቶ ሰለሞን ከበደ ………………………………………. ሰብሳቢ

2/ አቶ አበበ ዘልዑል ………………………………………. አባል

3/ አቶ ቃሲም ፊጤ ………………………………………. አባል

4/ ዶ/ር አቻምየለህ ጋሹ …………………………………… አባል

5/ ዶ/ር ዳንኤል አምባዬ …………………………………… አባል

6/ አቶ አበበ ሙላት ……………………………………….. አባል

ነሐሴ 2012 ዓ.ም.

1
አዲስ አበባ

1. መግቢያ
የከተማ ግብርና የሚባለው እሳቤ የምግብ አቅርቦትን በማሻሻል ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረው አካባቢያቸውን
የሚያስውቡበት ሲሆን፤ በተጨማሪ ለከተማ ነዋሪው ስለግብርና ግንዛቤ በመፍጠር አስተዋዕጾ የሚያበረክት መስክ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ 1996 በተደረገ ሪፖርት በጊዜው ወደ 800 ሚሊዮን የሚጠጉ የከተማ ነዋሪዎች በከተማ እርሻ እና ከብት
እርባታ ህይወታቸውን እንደሚመሩ ያስረዳል፡፡ የከተሜነት መስፋፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጨማሪ የቆዳ ስፋት ያለው
መሬትን ለከተሞች የተቀራረበ የህዝብ ጥግግቶሽ አሰፋፈር በማዋል አዲስ የመሬት አጠቃቀምን እንዲፈጠር ያደርጋል
፡፡ የከተሜነት መስፋፋት አዳዲስ ከተሞች በገጠር የገበያ ማዕከላት አካባቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመንገድ ትራንስፖርት
አውታሮችን ተከትለው እንዲፈጠሩ ያደርጋል፡፡ በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ከተሜነት የከተማ እና ገጠር መስተጋብር
መጠቃቀምን መነሻ ከማድረግ ይልቅ ከተማው የግብርና መሬት ነጣቂ እና አሳዳጅ፤ ገጠሩ ከግብርና ህይወት ተፈናቃይና
ተሳዳጅ ሆነው አንዱ መሬት ወሳጅ ሌላኛው መሬት የሚወሰድበት በሚል አስተሳሰብ የመብትና የተጠቃሚነት ተቃርኖ
ውስጥ መግባታቸው ይስተዋላል፡፡ የመሬት አጠቃቀሙም ሽግግሩ ሲታይ የግብርና የመሬት አጠቃቀምን ወደ ተለያዩ
የከተማ መሬት አጠቃቀም እነዲለወጡ ከማድረግ በመለስ ለከተማ ግብርና ምንም አይነት ትኩረት ያላደረገ ሆኖ
ይታያል፡፡ በመሰረታዊነት የሃገራችን ከተሜነት ሚዛናዊነት በጎደለው የማይገመት ፍላጎት ግፊት ስለሚነዳ በዙሪያው
ያሉትን ነባር ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እውነታዎችን ከግምት ያስገባ መስፋፋትን አይከተልም፡፡ በዚህም ዜጎችን
የማያሳትፍ ከመሆኑም በላይ የገጠሩን አርሶ አደር እና አርብቶ አደር የልማት ተጠቃሚነት በተሻለ ደረጃ የማረጋገጥ
እሳቤ የለውም፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የከተሜነት ተሞክሮ የሚነግረን በማንኛውም ጊዜ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን
መሬት ለከተማነት እስከተፈለገ ድረስ መውሰድ ይቻላል የሚል የገበሬውን የኑሮ ዘይቤ ምርጫ የመድፈቅ ባህርይ
የተዳበለው ነው፡፡

ይህ ከላይ የተገለፀው የከተሜነት እና የገጠር መሬት ፍላጎት ግጭት፤ በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት
ውስጥም ቢሆን የራሱን አሉታዊ አሻራ ማሳረፉ አልቀረም፡፡ በከተሞች ዙሪያ ያሉ የግብርና ሥራዎች ምንም እንኳን
ዘመናዊነትን የተከተሉ ባይሆኑም፤ በተወሰነ ደረጃ ከተማን በመመገብ የሚያገለግሉ የግብርና ሥራዎች በአትክልትና
ፍራፍሬ ልማት እና በእንስሳት እርባታ ደረጃ አስተዋዕፆ ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ ሆኖም በሃገራችን ያለው ከተሜነት
የከተማ ግብርናን ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ለግብርና ሥራ ቢውሉ ዘላቂ ተጠቃሚነት ሊሰጡን የሚችሉትን
መሬቶች ሳይቀር የመሬትን አቀማመጥ ሜዳማነት ብቻ በመመልከት ለከተማ መሬት አጠቃቀም ክፍለ ኢኮኖሚዎች
በማዋል የተፈጥሮ ሃብት ብክነት እንዲፈጠር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በሌላ በኩል የከተሞች እድገትን ታሳቢ በማድረግ እና
ትላልቅ ከተሞች በዙሪያቸው ላሉ የገጠር መሬቶች ያላቸውን ቅርበት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለህገወጥ የመሬት
ወረራ እና የመሬት ይዞታ ልውውጥ እንዲስፋፋ ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡ ይህን ጉዳይ በሰረታዊ ችግሩ በሃገራችን
ሃገራዊም ሆነ ክልላዊ የመሬት አጠቃቀም ፕላን ፖሊስ ባለመኖሩ እና መሬት አጠቃቀምን በእውቀት ለመምራት
ካለመቻሉም በላይ የመሬት አስተዳደሩን እጅግ አስቸጋሪ ስላደረገው ነው፡፡

የ 1994 ቱ የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲም ቢሆን የከተማ ግብርናን እና በከተማ ዙሪያ ያሉ ከተማ ቀመስ የመሬት
የዞታዎችን አስመልክቶ ግልጽ የፖሊሲ አቅጣጫ ባለመቅረጹ እና የከተማ ግብርናን ከግምት ካለማስገባቱም በላይ
በከተማ እና በገጠር መካከል ያለው ትስስር ጤናማ እንዳይሆነ የራሱን አስተዋዕፆ አበርከቷል፡፡ ከተማ ቀመስ የከተማ
ዙሪያ አካባቢዎችን ሆኑ ወደ ከተማ ወሰን የተካለሉ የአርሶ አደርና አርብቶ አደር ይዞታዎች ቀድሞ ከግብርና ተቋማት
የሚያገኙትን የኤክስቴንሽን አገልግሎት ስለማያገኙ፣ ቀድሞ ይመሩት የነበረውን ህይወት ማስቀጠል የሚችል ሁኔታን
ማስጠበቅ እንኳን እንዳልተቻለ ይስተዋላል፡፡ ይህ የግብርና ኤክስቴንሽን ጉድለት፣ የገጠር መሬት አስተዳደር አገልግሎት
በከተማ ቀመስ አካባቢዎች መጓደል እና በከተሞች የሚታየው የከተማ መሬት አጠቃቀም ፕላን አዘገጃጀት ለከተማ
ግብርና ትኩረት አለመስጠቱን ጨምሮ፤ የገጠር መሬት ይዞታን ወደ ከተማ መሬት ይዞታ የማሸጋገር ሥርዓት ጉድለትም

2
ተዳምሮ የከተማ ግብርና ምርታማነትን በማጎልበት ከተሞችን በትኩስ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችም ሆነ በእንሰሳ
ውጤቶች እንዳያግዙ አድረጎት ቆይቷል፡፡

2. የከተማ መሬት ለከተማ ግብርና አቅርቦት ጋር ያሉበት ተያያዥ ቁልፍ ተግዳሮቶችና


ማነቆዎች

የከተማ ግብርና በግለሰቦች ግቢ እና ወንዞችን ተከትሎ በግል ተነሻሽነት ከሚደረግ ጥረት በመለስ በተወሰነ መልኩ ለሥራ
ዕድል ፈጠራ ለእንሰሳት እርባታ ቦታ ከማመቻቸት ያለፈ በባለሙያ እና በእቅድ እየተመራ ውጤታማ እንዲሆን የማድረግ
ዝንባሌው አልነበረም፡፡ ከተሞችን በፕላን ለመምራት በሚደረገው ጥረትም ቢሆን የከተማ ግብርና መሬት አጠቃቀም
እና ለዚህ ተግባር የሚውል መሬትን መበጀት ላይ ችግር ይስተዋላል፡፡ በከተማ ዙሪያ ያሉ የአርሶ/አርብቶ አደር የመሬት
ይዞታ መብት ሽግግርም ቢሆን ለከተማ ግብርና መጠናከር ማነቆ ከመሆን ያለፈ አስተዋፆ አልነበረውም፡፡የከተማ ግብርና
ቀድሞውኑም የፖሊሲ ድጋፍ የሌለው ከመሆኑም በላይ በግል ተነሳሽነት የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያግዝ ተቋማዊ ድጋፍ
የለውም፡፡

2.1. የከተማ መሬት አጠቃቀም ፕላን እነ የከተማ ግብርና መሬት በጀት ጉድለት፤

በከተሞች ሥራ ላይ የዋለው የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ፖሊሲና ስትራቴጂ፤ የመሬት አጠቃቀም ፕላን
ዝግጅት እና የመሬት ማኔጅመንትን አስመልክቶ በተቀረጸው ሰነድ የከተማ መሬት አጠቃቀም በ 40፣ 30፣ 30 በሚል
የድርሻ ቀመር ክፍፍል ለህንጻ ገንባታ፣ ለትራንስፖርት መሰረተ ልማት እና ለከተማ አረንጓዴ ሥፍራዎች ግልጽ መርህን
ያስቀመጠ ቢሆንም፤ አረንጓዴ ከሆነው የመሬት በጀትም ሆነ ተጨማሪ የመሬት በጀት በመያዝ ለከተማ ግብርና የሚሆን
ድርሻ አለማካተት ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ከአረንጓዴ የመሬት አገልግሎትም በጊዚያዊነት ለግብርና ስለሚውለበት ሁኔታ
የተቀመጠ የፖሊሲ አቅጣጫ የለም፡፡ የከተሜነት አኗኗር የከተማ ነዋሪዎች ለጤና የሚሰጡትን ትኩረት ከአመጋገባቸው
ጋር ከጊዜ ወደ ጊዜ በንቃት እንዲያሳድጉ አድረጎአቸዋል፡፡ ይህን ተከትሎ፤ ትኩስ የአትክልት፣ ፍራፍሬ እና የእንሰሳት
ተዋዕፆ ፍላጎታቸው መጨመሩ የከተማ ግብርና ውጤት ተፈላጊነትን የመጨመሩን ያህል በከተማ አስተዳደርም ሆነ
በግብርና ዘርፍ ለከተማ ግብርና ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አመላካች ነው፡፡ ሆኖም በከተማ መሬት ልማት ዘርፍ
የከተማ መሬት አጠቃቀም ፕላን ዝግጅት ይህን ትልቅ ቁምነገር ያገናዘበ ፖሊሲ የሌለው ከመሆኑም በተጨማሪ፣
በግለሰቦች የራስ ጥረት በአነስተኛ ይዞታ ወንዝን ተከትሎ ለሚካሄዱ የከተማ ግብርና ሥራዎች የሚያግዝ የከተማ
ግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ፖሊሲ የለም፡፡ በከተማ መሬት አጠቃቀም 30 በመቶ ለአረንጓዴ ይመደብ እንጂ ከዚህ
ውስጥ ለከተማ ግብርና እና ደን የሚውሉ ተስማሚ መሬቶችን በመለየት በኩል እና የመሬት ስሪቱ የከተማ ግብርና
ይዞታን እንዲያስተናግድ የመብት ፈቃድ ስለመስጠት የሚያነሳው ነገር የለም፡፡ በመሆኑም በከተማ መሬት ልማትና
ማኔጀመንት በመሬት አጠቃቀም እቅድ ዝግጅት እና ለከተማ ግብርና የሚውል ተገቢ መሬት በጀት በመያዝ መመደብ
ላይ ጉድለት ይታያል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የከተማ መሬት አጠቃቀም ፕላን ዝግጅትም ቢሆን የከተማ ፍላጎትን ብቻ መነሻ ከማድረግ ተሻግሮ
ሃገራዊ እና ክልላዊ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲን እና ፕላንን መነሻ ካላደረገ ሁሉን አቀፍ መፍትሄ ማምጣት ያስቸግራል፡፡

2.2. ለከተማ ግብርና የሚውል መሬት አቅርቦትን በተመለከተ፤

በከተማ መሬት የማስተላለፍ ድንጋጌ ውስጥ የከተማ መሬት በሊዝ የማስተላለፍ ሥርዓት በጨረታ፣ በልዩ ጨረታ እና
በምደባ በሚል ዘዴዎች እንደሆነ ወስኗል፡፡ በሊዝ መሬትን በማስተላለፍ ድንጋጌ ውስጥ የከተማ ግብርና መሬት
የሚተላለፍበትን ዘዴ ምን መሆን እንዳለበት አላካተተም፡፡ ሆኖም ለአነስተኛና ጥቃቅን ሥራ ዕድል ፈጠራ፤ በምደባ

3
በተወሰነ ደረጃ ከሚቀርብ መሬት በቀር ለከተማ ግብርና ቦታ ተዘጋጅቶ በመደበኛም ሆነ በልዩ ጨረታ ዘርፉ
የሚስተናገድበት ሁኔታ የለም፡፡ በከተማ ውስጥ ግብርናን ለቅይጥ በተመደበ ቦታ ከሚጠበቀው የሕንጻ ከፍታ ግንባታ
ገደብ በተጨማሪ የኢኮኖሚ አዋጪነት ኖሮት በመጫረት መሬት በጨረታ ማግኘት አያስችልም፡፡ በከተማ ወሰነ ደረጃም
በፕላን ለከተማ ግብርና የመሬት ምደባ አስገዳጅ ምጣኔ ካለማስቀመጡም በላይ በሊዝ ህጉም በራሱ የሚቀርብ መሬት
ለምን ለምን ግልጋሎት ሚዛን ጠብቆ መቅረብ አንደሚገባው ባለመደንገጉ፤ ከሁሉም በላይ ለዘርፉ ካለው ግንዛቤ እጥረት
የተነሳ በከተማ የግብርና መሬት አቅርቦት የሚተላለፍበትን ዘዴ ባለመቀረጹ፣ በከተማ ግብርና ልማት መሰማራት
የሚፈልጉ ባለሃብቶችን በከተማ መሬት ገበያ ውድድር ውስጥ አቅም በማጣት እየተገፉ እንዲወጡ ሲያደርጋቸው
ይስተዋላል፡፡ በከተሞች የሊዝ አዋጁ የከተማ ግብርናን ከግምት ውስጥ ያስገባ የመሬት አቅርቦት አድርጎ አያውቅም፡፡
በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት እንደሌሎቹ የልማት ሥራዎች የከተማ ግብርናም በቂ ሚዛን አግኝቶ በጨረታ መቅረብ
ይኖርበታል፡፡

በከተማ መሬት አጠቃቀም ፕላን ውስጥ የከተማ ግብርና ያለው ድርሻ ቀድሞ በፕላን ዝግጅት ካለተካተተ ማቅረብ
ስለሚያስቸግር የከተማ ግብርና መሬት አቅርቦትን ከከተማ መሬት አጠቃቀም ፕላን ጋር የሚያናብብ አሰራር መገንባትን
ይጠይቃል፡፡ ይህ በመናበብ መነሻ የሚወጣው ጨረታ በከተማ ግብርና አልሚዎች መካከል ብቻ በሚደረግ ግልጽ ጨረታ
ካልሆነ፤ ዘርፉ ከሌሎች ክፍለ ኢኮኖሚዎች ጋር በጨረታ ተወዳደሮ በማልማት አዋጪነት ስለማይኖረው የታሰበው
ውጤት ላያመጣ ይችላል፡፡ ከጨረታ ውጭ በምደባ የሚሰጠበት አግባብ ግልጽ አሰራርን ከመሸርሸሩም በላይ ወደ ህገወጥ
የመጠቃቀም አቅጣጫ ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህ የማህበራዊ ደህንነት ጉዳይ ሳይሆነ ቢዝነስ መሆኑ ከግምት ገብቶ በቢዝነስ
ሞዳሊቲ በከተማ ግብርና አልሚዎች መካከል በግልጽ ጨረታ መሬት የማስተላለፍ አሰራር የተከተለ ሂደትን
ካልተከተለም በግልፅ አሰራርና መሬት አስተዳደር ላይ የጎንዪሽ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለከተማ ግብርና መሬት
ከማቅረብ በመለስ በከተሞች ባለው ክፍት የመንግስት የመሬት ይዞታዎች ላይ በጊዚያዊ የመጠቀሚያ ፈቃድ የተለያዩ
ዘዴዎችን በመጠቀም የከተማ ግብርናን ከቋሚ የፍራፍሬ ተክል ሥራዎች በመለስ ማስፋፈት የሚያስችሉ የህግ ድጋፎች
አለመኖሩ ዘርፉን ከመደገፍ አንጻር በእንቅፋነት የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡

2.3. በከተማ ዙሪያ ያሉ መሬቶች እና በከተማ የተካተቱ የአርሶ /አርብቶ አደር የመሬት ይዞታ መብትን
በተመለከተ፤

የሃገራችን ከተሞች በአብዛኛው ትንንሽ በመሆናቸው እና የሃገራችን ከተሜነት ደረጃ ከዓለም ዝቅተኛ በሚባል (ከ 20
በመቶ ያልዘለለ) ደረጃ በመገኘቱ አዳዲስ ከተሞች መቆርቆራቸው ተፈጥሮአዊ ከማድረጉም በላይ ከተሞች በቀጣይም
መስፋፋታቸው አይቀሬ እና ከገጠር ተጨማሪ መሬቶች መፈለጋቸው የግድ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በአለም ላይ ያሉ
ከተሞች በየሃገራቱ ከሚሸፍኑት አማካይ የቆዳ ስፋት ምጣኔ አንጻር የሃገራችን ከተሞች ሃገሪቷ ካላት የቆዳ ስፋት አንጻር
በጣም ያነሰ ሽፋን እንዳላቸው ይገመታል፡፡ በከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽ ሚኒስቴር የተደረጉ ዳሰሳዎች
እንደሚያመለክቱት የሃገራችን ከተሞች አጠቃላይ ቆዳ ስፋት ከኢትዮጵያ ቆዳ ስፋት አንጻር 0.6 በመቶ ነው ተብሎ
ይታመናል፡፡ በአለም ላይ ያለው የከተሞች አማካይ ምጣኔ 3 በመቶ በመሆኑ እና ከዚህ አንጻር ሲታይ የሃገራችን ከተሞች
በጣም አነስተኛ የቆዳ ስፋት ነው ያላቸው ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም የሃገራችን ከተሞች መስፋፋት በከተሞች ውሳኔ እና
ግፊት ምክንያት እንጂ የመሬት አጠቃቀምን ሃገራዊ ጥናት መነሻ ያደረገ ባለመሆኑ ለግብርና ተስማሚ የሆኑትን
መሬቶቻችንን እያመናመነ እንደሆነ በግብርና ሚኒስቴር የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ይህን መሰል ችግር በዘላቂነት
ለመፍታት ሃገራዊ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ በማጽደቅ በጥናት ላይ የተመሰረተ ሃገራዊ የመሬት አጠቃቀም ፕላን
ማዘጋጀት ይጠበቃል፡፡

4
የአርሶ/የአርብቶ አደር የመሬት ይዞታዎች በከተማ ክልል ውስጥ ሲካተቱ መብትና ግዴታቸው ምን እንደሚሆነ በግልጽ
በህግ አልተደነገገም፡፡ የከተማ ሊዝ አዋጁ እውቅና የሚሰጠው የሊዝና የነባር ስሪቶችን ነው፡፡ በዚህ መነሻ ለአርሶ /አርብቶ
አደር ባለይዞታዎች የሚሰጠው መስተንግዶ ወጥነት የጎደለው ነው፡፡ ወደ ከተማ ወሰን ከተካለለበት ጊዜ አንስቶ የከተማ
መሬት ሆኗል በሚል፤ የአርሶ /አርብቶ አደርን መብት አናውቅም ከሚለው ጀምሮ የተወሰነ መፈናቀያ ካሳ እየከፈሉ
ማስለቅቅ በከተማ የመሬት አስተዳደር ሥርዓታችን ይስተዋላል፡፡ ይህ አሰራር ደግሞ አርሶ/አርብቶ አደሩ ወደ ከተማ
መካለልን እንዲጠላና ቀድሞ በህገወጥ ደላላ እንዲታለል ያደረገና በካሳም ሆነ በህገወጥ ሽያጭ መሬታቸውን ያጡ
አርሶ/አርብቶ አደሮች የልማቱ አካል ከመሆን ይልቅ ለከፋ የኑሮ ሁኔታ እየተገፉ እንዳሉ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ በከተማ
መሬት ምዝገባ ሥርዓት የይዞታ ሰርተፍኬት የሚያሰጥ ድንጋጌ ምንም እንኳ ቢደነገግም፤ ምዝገባው የመብት መነሻ
ማድረግ የሚኖርበት በከተማ መሬት መብት የሚያሰጡ አዋጆች በመሆኑ በከተማ መሬት ምዝገባ የአርሶ አደር መሬት
ይዞታ ተብለው የሚመዘገቡ ምዝገባዎችን ህገወጥ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ ከተሜነት ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀው
የመሬት አጠቃቀም ለውጥ እና መሬትን ለሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ መብት፣ አርሶ/አርብቶ አደሮች እንደማያገኙት ነባሩ
ተሞክሮ ስለሚያሳያቸው፤ አርሶ/አርብቶ አደሮቹ በተለይ መንግስት በርካሽ የማስነሻ ካሳ ከፍሎ ከማስነሳቱ ቀደም
ብለው ለቤት ሰሪ የከተማ ነዋሪዎች በህገወጥ ገበያ በመሸጥ ለከተማ መሬት አስተዳደር አስቸጋሪ እና የመሬት
አጠቃቀምን ለብክነት የሚዳርግ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ አዲስ በተሻሻላ የካሳ ህግ የገጠር መሬትን ለእርሻ ሥራ
ሲሆን ቅድሚያ የማልማት መብት ለአርሶ አደሩ ሲሰጥ ሌላ ልማት ላይ ደግሞ ከአልሚ ጋር በሽርክና አርሶ አደሮች
መሬታቸውን እንዲያለሙ ይፈቅዳል፡፡ ወደ ከተማ የተጠቃለለው መሬት ላይ ያሉ አርሶ አደሮችንም ሆነ አርብቶ
አደሮችን ወደ ከተማ ወሰን ከተጠቃለሉ ጊዜ አንስቶ ይህንን የነበረ መብት እንኳ ያሳጣቸዋል፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች
እንደታየው አርሶ/አርብቶ አደር መሬት ወደ ከተማ ወሰን በመጠቃለሉ መነሻ ብቻ የከተማ አስተዳደሮች መሬቱ
የከተማው ነው በሚል የፍርድ ቤት ክርክር አርሶ አደሩን ከመሬቱ ላይ ሲነቅሉት ይስተዋላል፡፡ በመሆኑም በግልጽ
አርሶ/አርብቶ አደሩ መሬቱ ወደ ከተማ ሲጠቃለል ምን አይነት የመሬት ይዞታ መብት ነው የሚኖረው የሚለው ምላሽ
ሳያገኝ ማስቀጠል በዘርፉ ያለውን ችግር ስለማይፈታው፤ ለጉዳዩ ዘላቂ መፍትሄ ከመስጠት አኳያ የመሬት አስተዳደር
ህግን ወጥ አድርጎ ከመቅረጽ እስከ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ጥናታዊ ውሳኔ መስጠትን ይፈልጋል፡፡ ይህንን ተከትሎ የመሬት
ይዞታ ምዝገባ ሥርዓትን በገጠርና በከተማ ወጥነት እዳይኖረው ያደረጉ የህግ እና የተቋማዊ አደረጃጀትን የሚፈታ
መፍትሄ መመልከት ያስፈልጋል፡፡

2.4 ተቋማዊ ድጋፍ ጉድለትን በተመለከተ፤

የሃገራችን የመሬት አስተዳዳር በሁለት ያልተናበቡ የመሬት አስተዳደር መዋቅሮች ምክንያት በከተማ ዳርቻ ያሉትን
የአርሶ/የአርብቶ አደር መሬት ይዞታዎች አስተዳደር አልባ እንዲሆኑ እንዳደረገ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ እነዚህን
አካባቢዎች ከተሞች በወሰናቸው ክልል ውስጥ ስለማያውቋቸው ምንም አይነት የመሬት አስተዳደር እና ሌሎች
አገልግሎቶችን አይሰጧቸውም፡፡ የግብርናና ገጠር ዘርፍም ቢሆን ወደ ከተማ መግባታቸው አይቀርም በሚል እሳቤ
አገልግሎት ሲሰጧቸው አይስተዋልም፡፡ አስተዳዳራዊ ስራም እየተሰራ አይደለም፡፡ በመሆኑም አርሶ/አርብቶ አደሩም ሆነ
ይዞታቸው ለህገወጥ ደላላ ወጥመድ የተጋለጡ እና ለህግወጥ ግንባታ መስፋፋያ ይዞታዎቹ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ በህገወጥ
ያልተወረረ ከሆነም ወደ ከተማ በመቅረቡ ከተማው የሚሰጠውን የግብርና ውጤት ግብይት ትሩፋት መነሻ አደርጎ
ዘመናዊ የከተማ ግብርናን ከመላመድ ይልቅ ድሮ ከከተማ በራቀ ጊዜ በነበረው ልምድ የመቀጠል አካሄድ ይስተዋልበታል፡፡
የዚህ ችግር መሰረታዊ ምክንያት የከተሞች የምግብ አቅርቦት ፍላጎት ያመጣውን መልካም አጋጣሚ ያማከለ አገራዊ
የግብርና ድጋፍና አሰራርም ያለመኖሩ ነው፡፡

አሁን ባለው የሃገራችን የመሬት አስተዳደር የገጠር መሬት ፖሊሲ እና የከተማ መሬት ፖሊሲው ካለመናበባቸውም በላይ

5
በተለያዩና በማይመጋገቡ አዋጆች የሚመሩ መሆናቸው በከተማ መሬት አስተዳደር እና በገጠር መሬት አስተዳደር
መካከል ያለመናበብን ፈጥሯል፡፡ የከተማ መሬት አስተዳደር ህጎች እና የገጠር መሬት አስተዳደር ህጎች መነጣጠል
በመካከላቸው የሚያርፈውን የከተማ ቀመስ የገጠር መሬት እንዲዘነጋም አድረጓል፡፡

በሌላ በኩል በከተሞች ውስጥ ለሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በተለይ ለግንባታ የሚውሉ ግብአቶችን በከተሞች
ዙሪያ ከሚገኘው የገጠር መሬት ይዞታዎች ነባሩን የመሬት አጠቃቀም በመጋፋት የሚመረት በመሆኑ፤ የአካባቢውን
ስነምህዳር በማዛባት የሚፈጸም ተግዳሮት በመሆን ቀጥሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከተሞች የሚያመነጩት የተበከለ
ፍሳሽ ቆሻሻ በአግገባቡ በማከም ለመስኖ አገልግሎት መጠቀም ሳይቻል ወደ ከተማ ዳርቻ በሚገኙ የገጠር መሬት
ይዞታዎች ስለሚለቀቅ፤ በግብርና ሥራ እና በጤንነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ መሆኑ ልዩ ትኩረት ካላገኘ
ለከተማ ሆነ በዙሪያው ለሚታሰበው ግብርና ቀጣይ ተግዳሮት መሆኑ አይቀርም፡፡

3. የፖሊሲው ማሻሻያ አስፈላጊነት

በከተማ ዙሪያ እና በከተማ ወሰን ክልል ውስጥ ያሉ የመሬት ይዞታዎችን ከከተማ ግብርና ልማት ጋር በማስተሳሰር
ለከተሞች የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት አስተዋጽኦ ማድረግ በሚችሉበት አግባብ የመሬት አስተዳደራቸውን ለመምራት
እና የአርሶ/አርብቶ አደሩን የልማት ተጠቃሚነት ከከተሞች መስፋፋት ጋር በማስተሳሰር ወደ ላቀ ተጠቃሚነት ደረጃ
ለማሸጋገር በቀደሙት የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲዎች ሆነ በከተማ ልማት ፖሊሲዎች ላይ የተባለ ነገር የለም፡፡
እንዲሁም በከተሞች አካባቢ አሁን የሚታየውን የከተማ ግብርና እሳቤ ጉድለት ውጤታማ በሚያደርግ የከተማ መሬት
አጠቃቀም ፕላን እና መሬት ህግ በመደገፍ ለዘርፉ የመሬት አቅርቦት እና የመሬት ይዞታ መብት ዋስትና በሚያረጋግጥ
ሥርዓት የከተማ ግብርና ኢንቬስትመንትን ማበረታታት በሚያስችል አግባብ መምራት አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን
የፖሊሲ ማሻሻያን ማውጣት ተገቢ ያደረገዋል፡፡

በሌላ በኩል በከተማ ዙሪያ ባሉ የገጠር አካባቢዎች የተጀመሩ ለከተሞች የሚቀርቡ የትኩስ አትክልት፣ ፍራፍሬዎች እና
የእንስሳት ውጤቶች ልማት ከከተሞች የመሬት አስተዳደር ጋር የሚጣጣም የመሬት ስሪት እንዲኖረው በማድረግ
የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት ከገጠር ወደ ከተማ የሚያደርገውን የመሬት ይዞታ ሽግግር የተናበበ ለማድረግ የፖሊሲ
ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሚሆን በተደረገው ሙያዊ ግምገማ በመገምገሙ፤ በከተማ እና በገጠር መሬት
አስተዳደር ተሞክሮ ባላቸውም የዘረፉ ባለሙያዎች ተደጋጋፊ ምክረ-ሃሳብ ስለቀረበና ስለታመነበት በፖሊሲ
ቀረጻ/ማሻሻያ ረቂቅ ውስጥ ማካተት ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም ቀጥሎ የቀረቡት አራት ጉዳዮችን ማመላከት አስፈልጓል፡፡

4. የሚታዩ ቁልፍ ተግዳሮቶችና ችግሮችን ለመፍታት መንግስት የሚከተሉትን የፖሊሲ


አቅጣጫዎች ይከተላል፡፡

በገጠር እና በከተማ ያለውን የመሬት አስተዳደር መስተጋብር ተመጋጋቢ እንዲሆን የሚያደርግ የመሬት አስተዳደር በማስፈን ከተሞች
ለከተማ ግብርና መሬት የሚበጅት የመሬት አጠቃቀም ፕላን እና አቅርቦት እንዲያሰፍኑ የሚያደርግ ሥርዓት ይገነባል፡፡ በመሆኑም
የከተማ ግብርና ተግዳሮቶች እንደሆኑ ከቀረቡት ማነቆዎች በመነሳት በምግብ ራሳችንን ለመቻል ከሚደረገው ሁለገብ ጥረት እና የዜጎች
ተጠቃሚነት አንጻር መንግስት ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን አራት የፖሊሲ አቅጣጫዎች መከተል ይኖርበታል፡፡

4.1. የከተማ መሬት አጠቃቀም ፕላን እና ለከተማ ግብርና መሬት በጀት ምጣኔ ማድረግን በተመለከተ፤

6
ለከተማ ግብርና የሚውል የመሬት አጠቃቀም እና የመሬት በጀት እንዲኖር በከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት
ፖሊሲ እና ስትራቴጂ እንዲሁም የከተማ መሬት አጠቃቀም ስታንዳርድ ውስጥ የግብርና መሬት አጠቃቀም ድልድል
እንዲኖር በማድረግ የከተማ ግብርና መሬት ይዞታ ባለቤትነት የህግ ዋስትና የሚሰጥ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት
ይገነባል፡፡ የከተማ ግብርና መሬት አጠቃቀም የድርሻ ቀመር በዋናነት በመሬት አፈር ተስማሚነት ላይ በመመስረት
በምግብ አቅርቦት ሃገራችን ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት መደገፍ በሚችል አግባብ የመሬት ተስማሚነት
ልየታው ሥራ ለእርሻ፣ ለደን እና ለእንሰሳት እርባታ በጥናት እንዲለይ ይደረጋል፡፡ ይህም ልየታ መነሻውን ሃገራዊ እና
ክልላዊ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ እና ፕላንን በማድረግ ይሆናል፡፡

4.2. በሊዝ አዋጅ ለከተማ ግብርና የሚውል የመሬት አቅርቦት እንዲካተት ማድረግን በተመለከተ፤

ለከተማ የሚውለው መሬት በሃገራችን የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲና ፕላን እንዲመራ መደረግ አለበት፡፡ የሊዝ ህጉ
በሚፈቅደው መሰረት እንደልማቱ ስፋት በከተማ ክልል ውስጥ ያሉና በመሬት ባንክ የተከማቹ መሬቶች ለጨረታ
በሚቀርቡበት ጊዜ ለከተማ ግብርና ተስማሚ መሆናቸው በተለዩ መሬቶች በከተማ መሬት አጠቃቀም ፕላን
መሠረት በከተማ ግብርና አልሚዎች መካከል በሚደረግ መደበኛ እና ልዩ የጨረታ ውድድር መሠረት የመሬት
አቅርቦት እንዲኖር ይደረጋል፡፡ በተጨማሪ በከተማ ውስጥ ከግብርና ውጭ ለሚውል አገልግሎት የተመደቡና
በአጭርና መካከለኛ ጊዜ ለተወሰነላቸው ዓላማ የማይውሉ መሬቶችን በምደባ ጊዚያዊ የመጠቀምያ ሥርዓት
በማመቻቸት የከተማ ግብርና ማስፋፋት የሚያስችል የኤክስቴንሽን ፓኬጅ ቀርጾ በህግ በመደገፍ እንዲተገበር
ይደረጋል፡፡

4.3. በከተማ ዙሪያ ያሉ መሬቶች እና በከተማ የተካተቱ የአርሶ/አርብቶ አደር መሬት የይዞታ መብት
በተመለከተ፤

የገጠር መሬት ወደ ከተማ መሬት አጠቃቀም ሲቀየር የአርሶ/የአርብቶ አደሩን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ
የመሬት ይዞታ መብት ሽግግር ያቀፈ ሃገራዊ የመሬት ፖሊሲ ክለሳ ይደረጋል፡፡ በካሳ ህጉ በተቀመጠው አግባብ ቢያንስ
አርሶ/አርብቶ አደሩ የመኖሪያ ይዞታውን በከተማ ሲካለል ተጠቃሚ የሚያደርገውን የሊዝ መብት በመስጠት
የማልማት ቅድሚያ እና ከአልሚ ጋር በሽርክና የማልማት መብት እንዲረጋገጥ ይደረጋል፡፡

4.4 በከተማ ዙሪያ ያሉ መሬቶች እና በከተማ የተካተቱ የአርሶ/አርብቶ አደር መሬት የይዞታ መብት
በተመለከተ፤

የከተማ መሬት አስተዳደርን እና የገጠር መሬት አስተዳደርን በአንድ ጥላ ሥር በማሰባሰብ፣ የገጠር መሬት ወደ
ከተማ መሬት አጠቃቀም ሲቀየር የአርሶ/የአርብቶ አደሩን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የመሬት ይዞታ
መብት ሽግግርን ያቀፈ ሃገራዊ የመሬት ፖሊሲ ክለሳ ይደረጋል፡፡ ይህን ወደ ሥራ የሚያስገባ የከተማ እና በገጠር
መሬቶችን ለማስተዳደር የሚያስችል ሃገራዊ የመሬት ህግ በማዘጋጀት እና በሃገራችን የሚገኙ የመሬት ይዞታ
መብቶችን በሙሉ በሚያስተናግድ አግባብ አገር አቀፍ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ይገነባል፡፡

ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል አርሶ/አርብቶ አደሩ የሚጎናጸፋቸው መብቶች መስፋት የራሳቸው በጎ ሚና
እንዳላቸው ስለሚታመን በዚህ ረገድ በመሬት አጠቃቀም መብት ሽግግር ላይ የፖሊሲና ህግ ማሻሻያ ይደረጋል፡፡
የመሬት አጠቃቀም ለውጥ ሳያስፈልጋቸው በከተማ ግብርና የሚቀጥሉ የገጠር የመሬት ይዞታዎች ከተማው

7
የሚሰጠውን የገበያና ግብይት ትሩፋት መሰረት አደርገው ወደ ዘመናዊ የከተማ ግብርና እንዲቀየሩ የተቀናጀ ፓኬጅ
ተቀርጾ እንዲተገበር ይደረጋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከተሞች የሚያመነጯቸው ቆሻሻዎች ታክመው ለከተማ ግብርና
ግብአትነት የሚውሉበት ሥርዓት ይገነባል፡፡

5. የሚያስተገብርበት ስልት፤

 የከተማ ግብርናን በከተሞች እና በአካቢቢያቸው እንዲተገበር ለማድረግ ህጋዊ ማዕቀፎችን እና ተቋማዊ


አደረጃጀቶች በመፈተሸ አሁን ያለውን የመሬት አስተዳደር ሥርዓት እና ተቋማዊ አደረጃጀት የሚያሻሽል
የህግ ማዕቀፍና ስታንዳርድ መቅረፅ፤

 ከህግ ማዕቀፍ አንጻር በከተሞች የከተማ ግብርናን የሚያስተናግድ የመሬት አጠቃቀም እና ይዞታ ሥሪትን
ሁሉን አቀፍ በሆነ የመሬት ህግ መደንገግ፤

 የከተማ ግብርና አንዱ የሃገራችን ግብርና ዘርፍ መሆኑን እውቅና የሰጠ መዋቅራዊ አደረጃጀት እና አሰራር
ሥርዓት ይዘረጋል፤

 የከተማ ግብርናን ስትራቴጂ ማዘጋጀት

በዚህ የመሬት አጠቃቀመና እና አስተዳደር ህግ ማዕቀፍ ማሻሻያ ውስጥ የአርብቶ አደር መሬት ስሪት፣ የአርሶ አደር
መሬት ስሪት፣ የሰፋፊ እርሻዎችና እንስሳት እርባታ መሬት አጠቃቀም፣ በከተማ ግብርና መሬት አጠቃቀም፣
በኢንደስትሪ ይዞታዎች የመሬት አጠቃቀም፣ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ እና ኢኮኖሚ ዞን መሬት አጠቃቀም፣ ከመሬት በታች
ላሉ መሰረተ ልማቶች እና ሌሎች ልማቶች በሚያመች የመሬት ይዞታዎች የመሬት አጠቃቀም በጥናት ታይተው
በማካተት በምስራቅ ኤሽያ ሃገራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ግስጋሴን ያመጣውን ሂደት የሚያስተናግድ
መስተጋብር በልማቱ እና በመሬት አስተዳደሩ በመፍጠር ህጉን አካታች ማድረግ፡፡ ይህን የመሬት ህግ ወደ ሥራ
የሚያወርድ አቃፊ የሆነ ተቋማዊ አደረጃጀት ከፌደራል ጀምሮ እስከ ከተማ እና ወረዳ ድረስ እንዲዋቀር ማድረግ፡፡
በከተማ እና በከተማ ዙሪያ ለሚካሄዱ የከተማ ግብርና የኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲቀረጽ በማድረግ በአነስተኛ እና
መካከለኛ ደረጃ የከተማ ግብርና በተቋም የሚደገፍበትን ስርዓት መከተሉ አተገባበሮችን ለመምራት ይረዳል፡፡ የገጠር
መሬት ወደ ከተማ ወሰን ከመካተቱ በፊትም ሆነ ከተካተተ በኃላ ለሽርክና የከተማ ግብርና መዋጮነት በሚያገለግል
መልኩ የካፒታል መዋጮን ለመገመት፣ አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ በዘመናዊ የልማት ሥራ ውስጥ የመሬት
ይዞታውን አቅርቦ የልማት ተጠቃሚነት ድርሻ እንዲያገኝ የሚያስችል ምቹ ሥርዓት እንዲፈጠር የይዞታ ዋጋ ግመታ
ማካሄድ የሚያስችል ሥርዓት በጥናት ላይ ተመስርቶ መገንባት ተገቢ ይሆናል፡፡

You might also like