Professional Documents
Culture Documents
20
20
20
(ሜሪ ፈለቀ)
ግርምታችሁን እና እርግማናችሁን ከማዥጎድጎዳችሁ በፊት ትንፋሽ እየሰበሰባችሁ ከመጀመሪያው
ልጀምርላችሁና ሁለቱንም ላስተዋውቃችሁ።
የመጀመሪያው ባሌ “ባለቤቴ ነው ተዋወቂው!” ብዬ ያስተዋወቅኳት ጓደኛዬ “ወየው በፈጣሪ ባልሽ ሲያምር
አጣብሺኝ!” ያለችለት ውብ ነው።
የገዛ እናቴ ልክ እንደጠበስኩት ስታውቅ “ውይ ልጄ የልጁን ህይወት አታበልሺ አጉል ታደርጊዋለሽ !ይቅርብሽ
በሞቴ!!” ብላ የለመነችለት ስነስርዓታም ነው።
የቤተክርስቲያናችን ፓስተር ጠርቶኝ “ሜሪ ሰይጣን አንቺን ተጠቅሞ ልጁን ከጌታ ቤት ሊያስኮበልል እየተጋ
ነው።” ያለለት የቸርቻችን ዓይን የሆነ አገልጋይ ነው።
እሱስ ብትሉ? መጀመሪያ እጄን የጨበጠ ቀን “ሜሪ እባላለሁ!” ስለው
"ሜሪ ....ሜሪ ? " ብሎ ሰይጣንን ራሱን የጨበጠ ይመስል እንዴት እጄን አሽቀንጥሮ እንደጣለው። የጨበጠኝን
እጁን ልብሱ ላይ ሁላ ቢጠርገው ደስ የሚለው ይመስለኛል።
እሱ ለከተማውም ለቸርቹም አዲስ ነበር። እኔ ደግሞ ከቸርቹም ከወሬውም ገለል ለማለት ክረምት ስለነበር
ሁለት ወር አዲስአበባ ከርሜ መመለሴ ነው። ጫፉን እንኳን ያልነካሁትን ቀድሞ የነበረውን ፓስተር በዝሙት
ጣለችው ተብዬ ተወንጅዬ መሆኑ ነው። ቢችሉ እንደጌታ ቢሰቅሉኝ ደስ ይላቸው ነበር። ያው ጫፉን አልነካሁትም
አልኳችሁ እንጂ ከንፈሩን ነክቼዋለሁ። ከንፈርና ጫፍ ይለያያል አይደል? እኮ!! ነገሩ ውስብስብ ሆኖ
አይደለም ሲያወሳስቡት እንጂ። ስለፓስተሩ በኃላ እመለስላችኋለሁ።
ስለዋናዬ ላውጋችሁ። ክረምቱን ጨርሼ እንደተመለስኩ እቤት ከምላሳቸው ላይ የሱን ስም እንዴት ላውርደው?
ቸርች ውስጥ የማይገባበት የለውም። ይሰብካል ..... ይዘምራል(ውብ ድምፅ ድክመቴ ነውኮ ደግሞ) ........ ፒያኖ
ይጫወታል....... ወላ ኤሌክትሮኒክስ ነገር ሲበላሽ ይጠጋግናል ........ ቸርቹን ያፀዳል የማያደርገው የለውም። በቃ
ምንም ይሁን
እነማሚ ....ቸርች አዲስ የመጣው .... ልጅ እንዲህ ብሎ .... እንዲያ ብሎ .... ሳላየው ብዙ ሰማሁ:: የተዋወቅን
ቀን ደግሞ እሱም ሳያየኝ ብዙ እንደሰማ ገባኝ። ያው ክፉ ክፉውንም ቢሆን......
ወንድሜ አጠገቡ ነበረ “እህቴ ናትኮ!” ይለዋል
“ሜሪ ያንተ እህት ናት?” አባባሉ ይህቺ አጋንንት እንዴት ብላ ከእናንተ ቤተሰብ ተፈጠረች? እንዴት ነው
መልዓክና ሰይጣን ተስማምታችሁ አንድ ቤት የምትኖሩት? አይነት ለዛ ነው። የለመድኩት ነገር ስለሆነ ስቄ
ለወንድሜ ምግቡን አቀብዬ ተመለስኩ።
ከዛ በኋላ እኔ አልደረስኩበትም። ስለእውነቱ ጭራሽ በሀሳቤም በልቤም የለም። ለራሴ በአንድ ፓስተር ከንፈር
ጦስ ሳቢያ መፅሃፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ክፉ ሴቶች መንፈስ ሁላ ስም (የኤልዛቤል መንፈስ የደሊላ መንፈስ ሲወጋ
የሚውለው የሴቶች መንፈስ ብዛት ) እየተጠቀሰልኝ እጅ በመጫን ፀሎት ብዛት ሌላ አገልጋይጋ መድረሻ እጅም
እግርም ፍላጎትም የለኝም።
ከወንድሜጋ ሁሌ እሁድ ከቸርች በኋላ እቤት ይመጣሉ። እሱ ማውራት ሲጀምር እቤት አፉን የሚከፍት የለም።
ፀጥ ብለው ይሰሙታል። ስለምንም ርእስ ይነሳ ይቀዳል የቸርቹ ወሬ ብዙም ስለማይጥመኝ አልሳተፍም።
ድንገት በሆነ ሰበብ ወደሳሎን ብቅ ካልኩ በገዛ ቤቴ ይገላምጠኛል። ወይ በነገር ይተናኮሳል። ቤቴ ነው ብዬ
አልፈዋለሁ።
“ቸርች ለምንድነው የማትመጪው?” አለኝ የሆነ ቀን ኮስተር ብሎ ውጪ ተቀምጬ የማነብበት መጥቶ
“ለምንድነው የምመጣው?”
“ለመፀለይ ..... ጌታን ለማምለክ ..... ጌታን ለመፈለግ .... ወንድሞች በህብረት ቢቀመጡ መልካም ነው እነሆም
ያማረ ነው!!”
“ዌል ወንድም አይደለሁም እንደምታየው!”
“የምሬን ነው!” አለ ፈገግ ብሎ:: „ጥርስህኮ ሲያምር በየሱስ ስም! ምን ሆነህ ነው ሁሌ የምትኮሳተረው?‟ ልለው
ነበር። ያው በደህና አያይብኝም ብዬ ዋጥኩት
“ሲገባኝ ቸርች የምትሄደው ሸክምህን ለማራገፍ ነው። ፈራጅ በየመንገዱ ሞልቷል። ለምን ብዬ ቸርች ሄጄ
የፈራጆቼን አይን እያየሁ ራሴን እኮንናለሁ? አምላክ ፍቅር ነው እኔ እስከገባኝ። ፍቅርን ፍለጋ የምሄድበት ቸርች
ገና እግሬ ሲረግጥ ዘማዊት ናት ትወገር የሚሉ አይኖች እና እኛ ካንቺ የተሻልን ፃድቃን ነን ብለው የሚመፃደቁ
ሰዎች ጋር ተቀላቅዬ ራሴን ለምን አሳንሳለሁ? Am ok where I am now. “
ዝም አለኝ። ሁለታችንም ዝም ከምንል ብዬ ቀጠልኩለት
"ታውቃለህ ያቺ ዘማዊት ሴት መፅሃፍ ቅዱስ ላይ ስትዘሙት አጊንተናት ነው ብለው ወደእየሱስ ያመጧት? ህም
ሁሌ የሚገርመኝ ነገር ከሆነኛው ሰውዬጋ ነውኣ ስታመነዝር ያዩዋት? እሱን 'በል ሱሪህን ታጠቅና አምልጥ
ብለውት ነው እሷን ብቻ ይዘዋት የመጡት? ለምን እሷን ብቻ ኮነኗት? ምናልባት ሰውየው ወዳጃቸው ነው?
አልያም ክብሩ የማይነካ ስም ያለው ሰው ነው? ለሁለት ባጠፉት ጥፉት እሷ ብቻ እንድትወገር ለምን ተፈለገ?"
ብዙ ዝም አለኝኛ "የሚወራው ግን እውነት ነው?" አለኝ
"አይገርምህም ግን ማንም ሰው እውነት ነው ወይ ብሎ ጠይቆኝኮ አያውቅም! ቤተሰቤን ጨምሮ የተፈጠረውን
እንኳን ሳያውቁ ነው ሲወጉ የሚውሉት" ድክም ብሎ ሳቀ
"እውነት ነው ግን?"
"ግማሹ እውነት ነው። እውነት የሆነው ክፍል 'የሆነ ነገር ነበራቸው' የሚለው ነው። 'በሷ ምክንያት ነው
ከአገልግሎት የታገደው!' የሚለውም እውነት ነው። እርግጥ 'አሳሳተችው' የተባለውም እውነት ነው ያው
የተሳሳተው ምን ድረስ ነው የሚለውን ነው ልክ ያልሆኑት።"
እንደሆነ ተዓምር ያየኛል። ...... ፈገግ ይላል። እሱ እንደሚለው ይሄን ቀን ነው ነፍሴን የወደዳት ....
"ፓስተር የመጣ ጊዜ እኔ ዼንጤነቱን እርግፍ አድርጌ ትቼው ነበር:: ... ማሚ በስንት ጉቦ የሆነ ቀን ይዛኝ
ስትመጣ ... ሸበላ .. ወጣት ... ሲናገር የሚጣፍጥ አዲስ ፖስተር እየሰበከ ነው:: ከጏደኞቼጋ ነበር የመጣነው::
ተያየን ... 'በየሱስ ስም ይሄ ዼንጤ ብሆን ራሱ ሲኦል ደርሶ መልስ ትኬት ያስቆርጠኛል' አልኳቸው:: 'በፍፁም
አይደረስበትም ... ፓስተርኮ ነው!' ተባባልን:: ከዛ በብር አስያዝን ... እጠብሰዋለሁ ብዬ!! ... ያው አባቢ ፓስተር
ስለሆነ መግባባት ጊዜ አልፈጀብኝም:: ... እንዳልኩትም ጠበስኩት:: ችግሩ እሱ የምሩን የጌታ ሰው ነው.... ልክ
የደፈርኩት አስመስለው የሚያወሩት (ልክ ልፉ ነገር አስመስለው) ... እሱ እወድሻለሁ ካለኝ በኃላ ራሱ ንሰሃ
የሚገባ ነው የሚመስለኝ::"
ድክም ብሎ እየሳቀ ይሰማኛል:: .... ይኼኛው ዼንጤው እሱ አይደለም:: ሰው የሆነው እሱ ነው:: ከቤት እየወጡ
ቼክ እያደረጉ ስላስቸገሩን ወክ እያደረግን ወሬውን ቀጠልኩለት::
"ከዛማ በቃ ... የሆነ ቀን ስሞኝ .... በፀፀት አለንጋ ሲዠለጥ ከረመ:: ... እኔ ብሬን በላሁ:: እሱ አመረረ ... ጭራሽ
በቅድስና ፍቅራችንን እንድንኖር እንጋባ አለ:: ... ከዛ እውነቱን ነገርኩት:: ... መልቀቂያ አስገብቶ ወደአዲስ አበባ
መሄዱን ሰማሁ.... ከዛ እዛም እንዳያገለግል መታገዱን ሰማሁ !! ከዛ የማውቀው ታሪክ የለም:: ... ምን
እንዳላቸውም አላውቅም:: ብቻ በኔ ምክንያት መሆኑን ነግሯቸዋል!! .... "
ሳናውቀው ብዙ መንገድ ተጏዝን!! .... ስንመለስ እጁን ትከሻዬ ላይ ጣል አድርጎ .... እብድ እንደሆንኩ እየነገረኝ
ነበር::
"ይቅርታ በጣም! በሰማሁት ልዳኝሽ አይገባም ነበር::" አለኝ እቤት ልንደርስ አካባቢ
"እሺ ይኸው እኔ እውነቱን ነግሬህ የለ? ምንድነው የሰማኸው?"
"ካንቺ በጣም መጠንቀቅ እንዳለብኝ:: ካለበለዚያ እንደምታባልጊኝ " እየሳቀ ነው...
ማሚ በሩጋ ቆማ እየጠበቀችኝ ነው:: ..... አስተያየቷ 'ደሞ በምን አገኘሽው?" አይነት ነው::
........ አልጨረስንም......
ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው !!
(ክፍል ሁለት)
የሳመኝ ቀን "በናትህ ይሄን ነገር በምስክር ፊት አድርግልኝ" ብለው ደስ ባለኝ። ስሜ መራራ ነዋ። ሳመችው እንጂ
ሳማት አይባልልኝማ! እርግጥ የሳመኝ እለት ያልኳችሁ ቀን ማለት በዋዛ የተገኘ እንዳይመስላችሁ
"ጌታ ሆይ ይሄ ሰው በወንድምነት ይሁን በባልነት ፍቅር የሚወደኝ መለየት የምችልበት ፀጋ ስጠኝ! .... ወይ
ምልክት ነገር አሳየኝ! ..... ቢያንስ በህልሜ አንድ ጋቢ ለሁለት ስንለብስ ምናምን ....... አለ አይደል የሆነ ምልክት
በቃ ...... እኔ ልጅህ በውዝግብ ስንገላታ በቤትህም እንደሚገባህ እያገለገልኩህ አይደለም! (ይሄኛው በእርግጥ
ለራስህ ስትል ባሪያህን አስባት አይነት ልምምጥ ነው። ውለታዬ አለብህ በዚህ እንኳን ክፈለኝ አይነት ሰፋጣም
ነው።) ብዬ ፆም ፀሎት ልይዝ ትንሽ ሲቀረኝ ነው ያው ምልክት መሆኑ ነው መሳሙ!!
ከምልክቱ አስቀድሞ ከወራት በፊት
ሲሊፐር ያጠለቁ እግሮቼ የቸርቹን በር አልፈው ሲገቡ ራሴን አገኘሁት። ከቤት የወጣሁት ቁምጣዬን ሆዴን
በሚያሳይ አላባሽ ለብሼ ከእግዜሩ የተጣላሁበት የወንድሜ መቃብር ጋር ለመሄድ ነበር። እንደለመድኩት
"የማይሰማ ፀሎት ለምን እፀልያለሁ? ወይም ቁልጭ አድርገህ በዚህ ጉዳይ አትፀልዩ ምናምን ብለህ ህግ
ብታወጣ ጥሩ ...... በደፈናው ብቻ አንኳኩ ...... ብቻ ፀልዩ አልክ ...... ከዛ ግን የማትሰማው ፀሎት ብዛቱ ....."
እያልኩ ከራሱ ከፈጣሪ ጋር እየተነታረኩኝ በእግሬ እስኪደክመኝ ከተጓዝኩ በኋላ ነው ድንገት አቅጣጫዬን
ወደቸርቹ ያዞርኩት ......... ገባሁ።
ለወራት ያላዩኝ አስተናጋጆች በፈገግታ ሰላም እያሉኝና አለባበሴን እየገላመጡ ክፍት ቦታ አሳዩኝ። እሱ መድረኩ
ላይ አይኑን ጨፍኖ ፒያኖውን እየመታ ይዘምራል።
ከተደረገልኝ በጎነትህ
አንዳችም ለእኔ የማይገባ ነበር
በቸርነትህ አድርገሃልና እደነቃለሁ
አብዝቼ ተመስገን እላለሁ ......
እያለ በሚጣፍጥ ድምፁ ይዘምራል:: ህዝቡ ቆሞ ግማሹ እጁን ወዳፈጣሪ አንስቶ .... ግማሹ ወሬ እያየ ግማሹ
ጨፍኖ አብሮት ይዘምራል። መግባቴን ያወቀ ይመስል አይኖቹን ገልጦ አየኝ። ተያየን!! ፈገግ ብሎ አይኖቹን
ጨፍኖ ማስመለኩን ቀጠለ። ያስተዋለ ሰው ምላስ ማሟሻ ሆኜ መክረሜን እያወቅኩት ሳቅ ብዬ ተቀመጥኩ።
የዛን ቀን ስንወጣ ሲንደረደር መጥቶ አቀፈኝ (በጌታ ፍቅር ነው ይህኛው)
"ስለመጣሽ ደስ ብሎኛል። ሳይሽ በጣም ነው ደስ ያለኝ" አለኝ ወደጆሮዬ ጠጋ ብሎ "ምንም እንኳን ቸርች
ለመምጣት አስበሽ ባትመጪም!" አለኝ። አለባበሴን መሆኑ ገብቶኛል።
ከዛን ቀን በኋላ የጌታ ፍቅር ይሁን የሱ ፍቅር መጀመሪያ ሰሞን ባልለየሁት ምክንያት ቸርች እመላለሰው ጀመር።
በሳምንት እሮብና እሁድ መደበኛ የቸርቹ ፕሮግራም አልበቃ ብሎኝ ...... አርብ የአገልጋዩች ፕሮግራም ......
ቅዳሜ የወንድሞች ፕሮግራም ...... ማክሰኞ የማለዳ ፀሎት ..... ብቻ ምንም ይሁን እሱ ካለ እኔ አለሁ!!
ፕሮግራሞቹ ሲያልቁ እስከቤት መንገድ እያራዘምን ወክ እያደረግን የባጥ የቆጡን እናወራለን። ጠዋት ተነስቶ
ትምህርት ቤት ድረስ ሸኝቶኝ ይመለሳል። የማነባቸውን መፅሃፍቶች ተከራይቶልኝ ይመጣል:: ... አንብቦ ነው
የሚሰጠኝ... እኔ አንብቤ ስጨርስ መፈጠራችንን ለማያውቀው ደራሲ ሂስ እንሰጣለን.... እንከራከራለን....
ማታ በየቀኑ ደብዳቤ ይፅፍልኛል... እኔም እፅፍለታለሁ ... ጠዋት ስንገናኝ ደብዳቤዎቹን እንቀባበላለን:: ከሰዓት
ከስራ የሚወጣበት ሰዓት ከኔ ጋር ስለማይዛመድ ከሱጋር ሳይክሌን እየገፋሁ በእግሬ 40 ደቂቃ የሚወስድብኝን
መንገድ በሳይክል በ10 ደቂቃ እልሰዋለሁ።
ደጋግመን የሄድንባቸው መንገዶች ኮቴያችንን ሰምተው እስኪያውቁት .... በየመንገዱ ያሉ የንግድ ቤት ዘበኞችና
ቋሚ የኔቢጤዎች እንደወዳጅ ሰላምታ መስጠት እስኪጀምሩ ...... ቤተኞቼም የኔና የእሱን አብሮ መውጣትና
መግባት ከመልመዳቸው የተነሳ እሱ የአጥሩን በር ሲያንኳኳ 'ሜሪ መጥቷል!' ብለው መጥራት እስኪለምዱ .....
ከዚህን ያህል የጊዜ ለውጥ በኋላ ነበር የሳመኝ። (መፀለይ ይነሰኝ?) እንደጠጣ ሰው ጀብረር አድርጎኝ ነበር
አሳሳሙ ሳልዋሻችሁ (ቤተኞቼ አንድም እሱን ስለሚያምኑት 'የጌታ ሰው' ስለሆነ ... ሁለትም ለወትሮው በየቀኑ
የሆነ ጥፋት የማጠፋ የነበርኩትን ልጅ ስላለዘበላቸው ... በተጨማሪም ወደ ቸርች ስለተመለስኩላቸው ....
ከእርሱ ጋር መውጣት መግባቴ ብዙም አልጎረበጣቸውም)
ይሄ በሆነ በጥቂት ቀን "የስራ እድገት አጊንቼ ሌላ ሀገር ልሄድ ነው አለኝ!" እንዴት እንደሚነግረኝ አፉ ላይ
ቃላቶቹን ሲያንገዋልላቸው ቆይቶ
"እኔስ? ስምንት ወር ሙሉ እጅህን ተመርኩዤ ሀዘኔን የረሳሁት እኔስ? ትተኸኝ ስትሄድ ምን ልስራ? በቀን ሁለቴ
የማይህ እኔስ አንተ የሌለህበትን ቀን እንዴት ልለፍ? ምን ልስራ? አንተ ሳትኖር ማነኝ? ንገረኝ ምን ልሁን?"
እንደሚሄድ እርግጠኝነት ነበረው ድምፁ ስለዚህ 'ቅርልኝ' ልለው አቅሙ አልነበረኝም። ምን ያህል በፍቅር ሙክክ
ብዬ እንደበሰልኩ የገባኝ የዛን ቀን ነው። ለወትሮ በሰው ፊት ማልቀስ ያውም ለማልቀስ ምክንያት በሆነኝ ሰው
ፊት ማልቀስ ሽንፈት የሚመስለኝ እኔ ....... በሱ ፊት ተዝረከረኩ።
"በቃ አልሄድም እቀራለሁ::" አለኝ "በቃ አንቺ ትምህርትሽን እስክትጨርሺ የትም አልሄድም ይቅር !" አለኝ
አቅፎ እያባበለኝ። አዲሱ ስራው አዲስ በተከፈተው የአቢሲንያ ባንክ ማናጀር ሆኖ ነው የሚሄድ የነበረው። ገና
እንደተመረቀ ነው አሁን የሚሰራውን ስራ አጊንቶ የጀመረው። በአንድ አመቱ አሁን ያገኘው እድገት ለእሱ ምን
ያህል ትልቅ ነገር መሆኑን አውቃለሁ። 'ትቼልሻለሁ' ሲለኝ የባሰ ሙክክ ከማለት ውጪ ምርጫ ነበረኝ? እኔ
ደግሞ አስራ ሁለተኛ ክፍልን ገና መጀመሬ ነበር። ተስማማን!! በሆነ መልኩ ራስ ወዳድ እንደሆንኩ ገባኝ።
"ይዘኸኝ ሂድ!" አልኩት በነገታው ጠዋት ትምህርት ቤት ሊሸኘኝ እንደመጣ እስክነግረው ጓጉቼ እላዩ ላይ
እየተንጠለጠልኩ ምን እንዳልኩ ገብቶታል። ግን ማመን አልፈለገም።
"የት ነው ይዤሽ የምሄደው? የምትዪው የማስበውን ከሆነ.... አይሆንም!!" አለኝ ኮስተር ብሎ
"ለምንድነው የማይሆነው?"
"ስለምወድሽ ነው የማይሆነው!! ...የኔ ሚስት በስነስርዓት ለቤተሰቦቿ ሽማግሌ ልኬ .... ቸርች ቆሜ በጌታ ፊት
ቃል ገብቼላት .... በቤተዘመድ ተመርቀን ..... ነው የማገባሽ! በፍፁም እንደወመኔ ብድግ አድርጌ ይዤሽ
አልሄድም። ትምህርትሽን በጥሩ ውጤት ትጨርሻለሽ .... እንደህልምሽ ህግ ትማሪያለሽ ..... ስትመረቂ ከፈለግሽ
የምርቃትሽ ቀን ሰርጋችንን ማድረግ እንችላለን።" አለኝ ኮስተር ብሎ ቀጠል አድርጎ "አንቺ ግን የምርሽን ነው?"
"እሱማ የምሬን ነው። ቆይ ምንድነው ያልከውን ሁሉ ከማድረግ የሚያግደኝ? ሰሞኑን ሽማግሌ ትልካለህ .... ከዛ
ቸርች ሄደን ቃል እንገባባለን.... ይዘኸኝ ትሄዳለህ .... አንተም ስራህን እኔም ትምህርቴን ..."
"እ እ አይሆንም አልኩ አይሆንም!" አለኝ ከአፌ ቀምቶ "እብድ እኮ ነሽ ..."
ማታ ምን አቅብጦኝ እንደሆነ ሳላውቅ ለማሚ ነገርኳት። በቤቴኮ 'እንዴት ያለ የተባረከ ልጅ ነው::' ብላ
እንድታሞግስልኝ ነበር:: ቦንብ ማፈንዳቴ አልታወቀኝም። ከዛን ቀን በኋላ እሱ እኛ ቤት በምንም ሰበብ ቢሆን
እንዳይመጣ ለእርሱም ለወንድሜም ማስጠንቀቂያ ተሰጠ። ትምህርት ቤትም ሆነ ቸርች ወይ ማሚ ወይ አባቴ
ሆኑ የሚያደርሱኝ። ቸርች የምሄድባቸው ቀናት ተወሰኑልኝ። እሱም ቸርች ማስጠንቀቂያ ደረሰው። አንድ
ሳምንት ሳናገናኝ አለፈ። ... እንደዛ እንደመልዓክ የሚያዩት ቤተኞቼ .... ሲያዩት ሁላ የሞት መንፈስ እንዳዩ
ይሸሹት ጀመር ... ማሚ ጭራሽ ተከርብታ 'ባንተ ተመስሎ ልጄን ከአላማዋ ሊያሰናክል ያለ መንፈስ ወጋሁ!!"
ብላዋለች ለትምህርት ቤት ሁላ ማንም ቢጠራኝ እንዳያስጠሩኝ መልእክት ተላለፈ። በርቀት መድረክ ላይ
ብቻ አየዋለሁ።
(ምንም አልገቡኝም:: ቀላሉ መንገድ ከኔጋር ማውራት ነበርኮ ... እውነቱንኮ ነግሬያቸዋለሁኝ... )
ከዛ ግን ያቺ እንቢ ባዩዋ እኔ ሁሉንም "የራሳችሁ ጉዳይ!" አለች ከትምህርት ቤት አሞኛል ብዬ አስፈቅጄ ስራ
ቦታው ስበር ደረስኩ ሲያየኝ ሊጮህ ሁላ ዳዳው በደስታ ከመሬት አንስቶ አየር ላይ አሽከረከረኝ።
"የማብድ መስሎኝ ነበር::" አለኝ ፀጉሬን.. አንገቴን .. ጉንጬን ... ከንፈሬን ... እየሳመ... እንደሌላው ቀን
ለሚያየው ሰው ሁላ ሳይጨነቅ
"አሁንስ ይዘኸኝ አትጠፋም?" አልኩት
ፈገግ ብሎ "መቼ?" አለኝ
........ አልጨረስንም ......
(ደሞ ከዚህ ስርም የሚቀጥለው ክፍል አሁን ይሁን እንዳትሉ)