Download as doc, pdf, or txt
Download as doc, pdf, or txt
You are on page 1of 3

የህዝብ ብዛት፣ የተፈጥሮ ሐብት ወድመት እና የኮቪድ-19 መከሰት

በ 7 አህጉራት እና ከ 212 በላይ ሀገራት የተዋቀረችን ዓለማችን ከ 7.7 ቢሊዮን በላይ ህዝብ ብዛት አላት፡፡
እ.አ.አ በ 1804 ከክርስቶስ ውልደት በኋላ አንድ ቢሊዮን የደረሰው የዓለም ህዝብ ፈጣንና ወጥነት የሌለው
ዕድገት አሳይቷል፡፡ ከ 30 ዓመታት በኋላ ማለትም በ 2050 እ.አ.አ. የዓለም የህዝብ ቁጥር 9.8 ቢሊዮን ይደርሳል
ተብሎ ይገመታል (ተ.መ.ድ. 2017 እ.አ.አ.)፡፡ ከዚህ ዕድገት ከፍተኛውን ድርሻ የኢሲያና የአፍሪካ ሀገራት
ይወስዳሉ፡፡

ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፈጣን የህዝብ ዕድገት ለተለያዩ ችግሮች ይዳርጋል፡፡ ከሚዳርጉ ችግሮች
መካከል የኢኮኖሚ ማሻቀብ፣ የቁጠባ መጣኔ መቀነስ፣ የተፈጥሮ ሐብት መውደም፣ የዓየር ንብረት መለወጥና
የአካባቢ መበከል፣ የቆሻሻ ክምችት መጨመር፣ የአኗኗር ሁኔታ መዛባትና የኑሮ ውድነት መጨመር፣ ሥራ-
ዓጥነት መብዛት፣ የነፍስ ወከፍ ገቢ መቀነስ እና የማህበራዊ መስተጋብር መዛባትና ማህበራዊ ችግሮች
(ወንጀል፣ ስርቆት፣ ዝርፊያ፣ ግጭት፣ ጦርነት፣ ድርቅ እና ረሃብ) መበራከት ናቸው፡፡

የህዝብ ብዛት መጨመር የመኖሪያ ቦታዎች መስፋፋትን ያመጣል፡፡ የመኖሪያ ቦታዎች መስፋፋት ለዱር
አራዊት መኖሪያነት የሚገለግሉ ቦታዎች በሰው ልጅ እንዲነጠቁ ያደርጋል፡፡ እንዚህ የሚነጠቁ ቦታዎች የሚኖሩ
አራዊት ከሰው ልጅ ጋር ንክኪ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሁኔታም የሰው ልጅ እና የዱር እንስሳት ንክኪ እንዲፈጥሩ
ያደርጋል፡፡ በንኪኪው ከእንስሳት ወደ ሰው ያልታወቁና አዳዲስ የበሽታ አምጪ ተህዋሶች ይተላለፋሉ፡፡ እነዚህ
በሽታ አምጪ ተህዋሶች የዘረ-መል ባህሪያቸውን ለውጠው የሰው በሽታ አምጪዎች ይሆኑና ከሰው ወደ ሰው
ይተላለፋሉ፡፡

ከባለፉት አሥርት አመታት ወዲህ ነበር በረሃማ አካባቢ ያሉ ደኖች እና ከሰው ልጅ ጋር ምንም ንክኪ
ያልነበራቸው አካባቢዎች አዳዲስ ቫይረሶችና በሽታ አምጪ ተህዋሶዎች እንደ ኢቦላ፣ ኤችአይቪና ደንግዩ ያሉ
በሽታዎች ተያያዥነት እንዳላቸው ጥናቶች ማሳየት የጀመሩት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጥሮ ሐብት
መውደም ከአዳዲስ ቫይረሶች መነሳት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ብዙ ተመራማሪዎች ማሰብ ጀምረዋል፡፡
በታህሳስ ወር በ 2012 ቻይና ውስጥ ብቅ ያለው የኮቪድ-19 በሽታ አንዱ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ የአካባቢ
ሳይንቲስቶች የሰው ልጅ፣ የዱር እንስሳት እና ስነ-ምህዳር የሚፈጥሩት ግንኙነት ለአዳዲስ በሽታዎች መነሳት
ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡

የሰው ልጅ የሚያከናውናቸው ተግባራት ማለትም፦ የመንገድ ግንባታ፣ የማዕድን ማውጣት ሥራ፣ የዱር
አራዊት አደና እና የደን ጭፍጨፋ ስነ-ምህዳርን በማዛባት የኢቦላ ወረርሽኝ እንዲከሰት እንደረዳ በ 1990 ዎች
የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የሰው ልጅ በረሃማ አካባቢዎች ያሉ ደኖችን በመጨፍጨፍ ያልታወቁ የዱር
አራዊት መኖሪያዎችን ያወድማል፡፡ በዚህም ምክንያት ላልታወቁ የቫይረስ ዝርያዎች ተጋላጭ ይሆናል፡፡ እኛ
የሰው ልጆች ዛፎችን በመቁረጥ የተፈጥሮ ስነ-ምህዳሩን እናዛባና በቦታው የሚኖሩ ቫይረሰችን ተፈጥሯዊ
መኖሪያቸውን ስናጠፋ መኖሪያ ያጡና እኛ የሰው ልጆች መኖሪያቸው እንሆናለን፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንስሳት-ወለድና ተዛማጅ በሽታዎች ለምሳሌ ኢቦላ፣ ሳርስ፣ በርድ-ፍሉ እና ኮቪድ-19
አከሳሰታቸው ጨምሯል፡፡ በሽታ አምጪ ተህዋሶች ከእንስሳት ወደ ሰው እየተላለፉ እና ብዙዎች በፍጥነት ወደ
አዳዲስ ቦታዎች እየተላለፉ ነው፡፡ እንደ የአሜሪካው ሲዲሲ ግምት ¾ ኛ የሚሆኑ አዳዲስ በሽታዎች
ከእንስሳት ተነስተው በመጀመሪያ ከተከሰቱበት አካባቢ አልፈው ሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን ማጥቃት
ችለዋል፡፡
እንደ ሬቢስ እና ፕላግ ያሉ በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰዎች ከ 100 ዓመታት በፊት የተላለፉ ናቸው፡፡ ሌሎች
ለምሳሌ ማርበርግ (ከሌሊት ወፍ እንደሚተላለፍ የሚታመን) አሁን ላይም አልፎ አልፎ አለ፡፡ ዘንድሮ በታህሳስ
ወር በውሃን ቻይና የተነሳው ኮቪድ-19 ለሰው ልጅ አዲስና በአለም-ዓቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ ያለ ወረርሽኝ ነው፡፡
ሌሎች በሽታዎች ለምሳሌ ላዛ ፌቨር በናይጄሪያ እ.አ.አ 1969 ነበር የታወቀው፤ ኒፓህ በማሌዥያ፤ ሳርስ
በቻይና፤ ዚካና ዌስት ናይል-ቫይረስ በአፍሪካ ተነስተው ዘረ-መላቸውን ለውጠው ቋሚ በሽታዎች ሆነዋል፡፡

በከተሞች አካባቢ ያለው የህዝብ ጥግግት ለወረርሽኝ በሽታዎች በፍጥነት መስፋፋት አመቺ ነው፡፡ የሰው
መኖሪያ ቤቶች የተጠጋጉና የተያያዙ በመሆናቸው ከአንድ መኖሪያ ቤት ወደ ሌላው ቤት ለመስፋፋት አመቺ
ነው፡፡ በአንድ ውስን ስፍራ ብዙ ሰዎች መኖራቸው ከሰው ወደ ሰው በሽታዎች ለመተላለፍ ያመቻል፡፡
በተጨማሪም በሽታ አምጪ ተህዋሶች መመሸጊያ እንደ ደን ያለ ስፍራ አለመኖሩ በከተማ የሚኖረው የሰው
ልጅ ማረፊያው ይሆናል፡፡

እነዚህ እንደ አዲስ የሚነሱት እንስሳት-ወለድና ተዛማጅ በሽታዎች የዓለም የጤና ሁኔታ፣ ድህንነት እና
ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ሥጋት ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ሁናቴም ለብዙ ሰዎች መታመምና መሞት፣ ሰላምና ደህንነት
መናጋት እና የኢኮኖሚ ግሽፈት ይዳርጋል፡፡ ከወረርሽኝ መከሰት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው አደጋ የዓለም
ኢኮኖሚን በሰፊው ያናጋል፡፡ የትራንስፖርት መቆምና የንግድ እንቅስቃሴዎች መገታት የዓለም ኢኮኖሚ
ይጎዳና የኢኮኖሚ ማሻቀብ ያመጣል፡፡ የኢኮኖሚ ማሻቀብ ረሃብና ድርቅ ያመጣል፡፡ ማህበራዊ ችግሮች
ይበረክቱና ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ብዙ ከጤና ጋር በቀጥታ ተያያዥ ያልሆኑ ማህበራዊና
ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ይበረክታሉ፡፡

የዱር አራዊት መኖሪያዎችን መንካት ከበሽታዎች አልፎ ለአካል ጥቃትም ይዳርጋል፡፡ ለምሳሌ የእባቦች መኖሪያ
ቦታ ሰዎች ቢሄዱ በእባቦች ይነደፋሉ፡፡ አዞና ጉማሬ ያለባቸው ሐይቆችም ለዋናና አሣ ለማስገር ሰዎች
ሲሞክሩ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ የአራዊት መኖሪያ ቦታዎች መንካት ለጥቃት ከበሽታዎች በተጨማሪ
ይዳርጋል፡፡

ከላይ በዝርዝር ለማብራራት እንደሞከርኩት የህዝብ መብዛት የከተማ መስፋፋትና የደን ስፍራዎች መከበብና
መሯቀት ስለሚያመጣ የተፈጥሮ ሐብታ እንዲወድም ያደርግና የዱር አራዊት መኖሪያ ቦታዎች በሰው ልጅ
ይነጠቃሉ፡፡ ይህ አጋጣሚ የደን ስፍራዎች የሚኖሩ የዱር አራዊት ከሰው ልጅ ጋር ንክኪ ይፈጥሩና የእንስሳት-
ወለድና ተዛማጅ በሽታዎች ከአራዊት ወደ ሰው ይተላለፋሉ፡፡ ከአራዊት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች
የዘረ-መል ባህሪያቸውን ይለዋውጡና የሰው ልጅ በሽታዎች ሆነው ይቀራሉ፡፡ ስለዚህ የህዝብ ዕድገትን
መግታት፣ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ መሥራት፣ የማህበረሰብ ግንዛቤን ማሳደግ፣ የዱር አራዊት መኖሪያ
ቦታዎችን መጠበቅ እና የሰው ልጅ ከዱር አራዊት ጋር ያለውን ንክኪ መቆጣጠር ሊሠሩ የሚገባቸው የመፍትሄ
አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ አበቃሁ፡፡
(የአሜሪካው ሲዲሲ፣ የአለም ጤና ድርጅት እና ተ.መ.ድ. - የመረጃ ምንጮች ናቸው)

በላይ አበራ - ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ

አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2012

You might also like