Professional Documents
Culture Documents
ጀብሃና ሻቢያ
ጀብሃና ሻቢያ
ጀብሃና ሻቢያ
(1961-1991 G.C.)
ቅጽ አንድ
ታሕሳስ 2006
አዲስ አበባ
እንደ መግቢያ
ክፍል አንድ
== ቅድመ-ታሪክ==
የቢትወደድ አስፋሐ መንግሥት የሚወስደው እርምጃ እለት ተዕለት እየጠነከረ ሄደ፡፡ በ1958
የኤርትራ ሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን የጠራው የስራ ማቆም አድማ በሀይል ተደመሰሰ፡፡ ብዙ ሰዎች
ተገደሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ ኤርትራዊያን “ሓርነት” የሚል ድምጽ ማሰማት ጀመሩ፡፡
ሆኖም የቢትወደድ አስፋሐ መንግሥት የህዝቡን ተቃውሞ ከምንም አልቆጠረውም፡፡ በ1958
የፌዴሬሽኑ የስራ ቋንቋዎች የሆኑት ትግርኛና ዐረብኛ ታግደው በአማርኛ ተተኩ፡፡ በ1959.
የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ ታገደ፡፡ በ1962 ዓ.ል. ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር
መሆኗ ታወጀ፡፡
የኤርትራ ፌዴሬሽን የፈረሰበት ታሪካዊ ሂደት በአጭሩ ይህንን ይመስላል፡፡ ለሰላሳ ዓመታት
የኢትዮጵያ ህዝቦችን ደም ሲያስገብር የነበረው ጦርነት የተለኮሰው ይህንን እርምጃ ተከትሎ
ነው፡፡ ያኔ የተፈጸመው ብዙዎችን ያሳዝናል፤ ያስቆጫልም፡፡ በተለይ የሚያስቆጨው ግን የአጼ
ሃይለ ስላሴ መንግሥት የመካሪዎቹን ጥቆማ አልቀበልም በማለት ሲፈጽማቸው በነበሩት
ስህተቶች የተነሳ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ ለማድረግ መብቃቱ ነው፡፡ ኤርትራን
ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ለማዋሃድ የደከሙት ጸሓፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ
ለንጉሳቸው ሲሰጡት የነበረው ምክር በስራ ላይ ቢውል ኖሮ የዛሬው ሁኔታ ሌላ መልክ በያዘ
ነበር (እኔም ይህንን ጽሑፍ ባልጻፍኩ ነበር)፡፡
*****
የቢትወደድ አስፋሐ እርምጃ በተጠናከረበት በ1956 ገደማ አንዳንድ ኤርትራዊያን
“ፌዴሬሽኑ የፈረሰ እንደሆን ምን እናድርግ” እያሉ በድብቅ የሚወያዩበትን “ማህበር ሸውአተ”
የተሰኘ እድር መሳይ ማህበር መስርተው ነበር (“ማህበር ሸውአተ” በትግርኛ “የሰባቱ ማህበር”
ማለት ነው፤ ማህበሩን የመሰረቱት ሰባት ሰዎች ነበሩ)፡፡ ይህ ማህበር በጅምሩ ላይ ዝግ ብሎ
ይጓዝ ነበር፡፡ በ1959 የኤርትራ ባንዲራ ሲሰረዝ ግን “የፌዴሬሽኑ መፍረስ እውን ነው” በማለት
ደመደመ፡፡ በዚህም የተነሳ የማህበሩ መስራቾች እንቅስቃሴአቸው ድርጅታዊ መልክ እንዲይዝ
አደረጉት፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላም ከዚሁ ማህበር አስኳል “ምንቕስቓስ ሓርነት
ኤርትራ”/Eritrean Liberation Movement ወይንም በአጭሩ “ሀረካ” በሚል ስያሜ የሚጠራ
የፖለቲካ ድርጅት ተወለደ (“ሀረካ” በዐረብኛ “እንቅስቃሴ” ወይም “ንቅናቄ” ማለት ነው፤
ድርጅቱ በሙሉ የዐረብኛ ስሙ “ሀረካት ታህሪረል ኤሪትሪያ” ይባላል፤ “የኤርትራ ነጻነት ንቅናቄ”
ማለት ነው)፡፡
ጀብሃ ወደ ትግሉ ሜዳ የገባው በከረረ ስሜት ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ከኤርትራ ነጻነት
በስተቀር በየትኛውም አማራጭ ላይ ለመደራደር ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ የትግል ዓላማው
ኤርትራን ነጻ ሀገር ማድረግ ከመሆኑ በመለስ ድርጅቱ በምስረታው ዋዜማ የየትኛው የርዕዮተ-
ዓለም አቅጣጫ ተከታይ እንደነበረ በትክክል ለመረዳት ይቸግራል፡፡ በርካታ ጸሓፊያን “ተሓኤ”
(ጀብሃ) ብሄርተኛ ከመሆኑ ውጪ የተለየ ጎራ ተከታይ እንዳልነበረ ያስረዳሉ፡፡ አንዳንዶች ግን
ድርጅቱ ከኢራቅና ከሶሪያ “በዕሥ” (“Ba’th” ) ፓርቲዎች ጋር የነበረውን ጠንካራ ግንኙነት
በመመልከት “ጀብሃ የዐረብ ሶሻሊዝም ፍልስፍና ተከታይ ነበር” ይላሉ፡፡
በርግጥም “ጀብሃ” በዐረቦች ዘንድ ከፍተኛ እውቅናና ድጋፍ አግኝቶ ነበር፡፡ ራሱንም እንደ
ዐረብ ብሔርተኛ ድርጅት የማየት አዝማሚያዎች ነበሩት፡፡ ሆኖም ይህንን ሁሉ ለታክቲክ ሲባል
የሚያደርገው ነው የሚመስለው፡፡ ድርጅቱ ዐረባዊ እየመሰለ እና ዐረብኛን የስራ ቋንቋ በማድረግ
እየተገለገበት እንኳ ዐረብ ካልሆኑ የኮሚኒስት ሀገራትም ጋር ግንኙነት ነበረው፡፡ ለምሳሌ ጀብሃ
ከኩባ፣ ቻይና እና ሶቪየት ህብረት ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቶ ነበር፡፡ እንዲሁም የሶሻሊዝም ጠላት
ናቸው ከሚባሉት ሳዑዲ ዐረቢያን ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር የነበረው ግንኙነት በጣም የጠነከረ
ነው፡፡ ጣሊያንን የመሳሰሉ የምዕራብ ሀገራትም የድርጅቱ ደጋፊዎች ነበሩ፡፡ ከዚህ ሁሉ
እንደምንረዳው ድርጅቱ የታክቲክ ወዳጅ እንጂ የርዕዮተ ዓለም ወዳጅ ነበረው ለማለት
ይከብዳል፡፡
ጀብሃ እስከ 1965 ሲያካሄደው የነበረው ወታደራዊ ኦፕሬሽን በአንድ የዘመቻ ማዕከል ነበር
የሚመራው፡፡ በነዚያ ዓመታት ግንባሩ ነጻ ያወጣው ትልቅ ከተማ ባይኖርም ሳህል እና ባርካ
በሚባሉት ቆላማ የኤርትራ አውራጃዎች ውስጥ ያለው የገጠሩ ክፍል በቁጥጥሩ ስር ገብቶ ነበር፡
፡ ከ1965 ጀምሮ የአጼ ኃይለ ስላሤ መንግሥት የግንባሩን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በሚል
የወሰዳቸው የጅምላ ቅጣቶች ተቃራኒ ውጤቶች ነው የነበራቸው፡፡ በተለይም የኤርትራ ሀገረ
ገዥ የነበሩት ልዑል ራስ አስራተ ካሳ በ1967 “ይህቺን ቆላ ሀገር እንደ ተመለጠ ራስ ምድረ በዳ
አደርጋታለሁ” በማለት በባርካ አውራጃ ከፍተኛ ህዝብ ያለቀበትን ዘመቻ ማካሄዳቸው በታሪክ
ምሁራን ተጽፏል፡፡ በወቅቱ በኤርትራ ክፍለ ሀገር ወታደራዊ ኦፊሰር የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደ
ጊዮርጊስ በጻፉት መጽሐፍ እንደገለጹት ከአምስት ሺህ የማያንሱ ሰላማዊ ኤርትራዊያን ራስ
አስራተ ካሳ ባዘመቱት ሰራዊት ተፈጅተዋል (አጼ ኃይለ ሥላሴ በራስ አስራተ ካሳ የተወሰደውን
ጭካኔ የተመላበት እርምጃ ከሰሙ በኋላ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ እንደሰጧቸው ይነገራል፤
በዚህም የተነሳ ራስ አስራተ በንጉሡ ላይ ቂም ይዘው ከስልጣን ሊያወርዷቸው ሲያደቡ ነበር)፡፡
ሆኖም የራስ አስራተ እርምጃ የትጥቅ አመጹን አባባሰው እንጂ አላቆመውም፡፡ በተለይ
ከመንግስት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የነበራቸው ክርስቲያኖቹ የደጋው ኤርትራ ክፍል ነዋሪዎች
በብዛት ወደ በረሃ እየወረዱ ከጀብሃ ጋር መቀላቀል የጀመሩት የራስ አስራተ ጦር በኤርትራዊያን
ላይ ያደረሰው ፍጅት ከተሰማ በኋላ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነበሩት እንደ
ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ወልዳይ ግደይ፣ ሰለሞን ወልደማሪያም፣ ሙሴ ተስፋዮሐንስ ወዘተ…
የመሳሰሉ ፋኖዎች ጀብሃን የተቀላቀሉት በዚያ ዓመት ነው፡፡ ከምጽዋ አካባቢም እንደ ኢብራሂም
አፋ እና ረመዳን መሐመድ ኑርን የመሳሰሉ ተዋጊዎች ጀብሃን ተቀላቅለዋል፡፡
*****
ጥቅምት 29/ 2006
ጀብሃ እና ሻዕቢያ (1961-1991 G.C)
ክፍል ሁለት
-----
“ጀብሃ” ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፉ የሚዲያ ማህበረሰብ እይታ ውስጥ የገባው በ1965
አንዲት የአሜሪካ ወታደራዊ ሂሊኮፕተርን በባርካ አውራጃ መትቶ በጣለበት ጊዜ ነው፡፡ ድርጅቱ
በወቅቱ “ሂሊኮፕተሯ የተመታችው በይዞታዬ ላይ የስለላ ስራ ስታካሂድ በመገኘቷ ነው” የሚል
መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ወሬው ብዙ ሳይወራ በዚያው ተረስቶ ቀረ፡፡
ከአራት ዓመታት በኋላ ደግሞ የጀብሃ አመራር ድርጅቱን በዓለም ላይ በስፋት ያስተዋውቃል
ያለውን ኦፕሬሽን ለማካሄድ ወሰነ፡፡ ይህንን ለመፈጸም አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው የኢትዮጵያ አየር
መንገድ አውሮፕላኖችን መጥለፍ አሊያም በኤርፖርት ላይ እንዳሉ በቦንብ ማጋየት ነው፡፡ በዚህ
መሰረት በሶስት ከተሞች የሚገኙ ኤርፖርቶች ተመረጡ፡፡ እነርሱም የፍራንክፈርት፣ የሮም እና
የካራቺ (ፓኪስታን) ኤርፖርቶች ነበሩ፡፡ ኦፕሬሽኑን የሚተገብሩ “ፊዳይን” የሚባሉ
ኮማንዶዎችም ተዘጋጁ (“ፊዳይን” የዐረብኛ ቃል ሲሆን “ሰማዕታት” ማለት ነው)፡፡ ቀዳሚ
የሆነው የፈራንክፈርት ኦፕሬሽን በመጋቢት ወር 1969 ተካሄደ፡፡ በኤርፖርቱ ቆሞ የነበረ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ቦይንግ 707 አውሮፕላን በቦንብ ተመታ፡፡ የጀብሃ
ፈዳይኖች እንዳለ አመለጡ፡፡ ሆኖም አውሮፕላኑ እንደተጠበቀው በእሳት አልጋየም
(በተጨማሪም አውሮፕላኑ በሜዳ ላይ ቆሞ የነበረ በመሆኑ የሰው ህይወት አልጠፋም)፡፡
የፓኪስታኑ ኦፕሬሽን በሰኔ 1969 እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡ ለኦፕሬሽኑ የተመረጡት ሶስት ፊዳይኖች
አሊ ሰዒድ አብደላ (ከ2001- እስከ 2005 የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ ያገለገለ)፣
መሀመድ ኢድሪስ እና ፍስሐ አብርሃ ነበሩ፡፡ የኦፕሬሽኑ ዋና አቀናባሪ ደግሞ የጀብሃ የውጪ
ጉዳይ ሀላፊ የነበረው ዑሥማን ሳልህ ሳቤ ነው፡፡ በዕቅዱ መሰረት ሳልህ ሳቤ የሐሰት
የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ይዞ የጦር መሳሪያዎችንና ቦንቦችን ወደ አየር ማረፊያው የባለ ልዩ
መብቶች (VIP) መቆያ ክፍል ይገባል፡፡ ከዚያም ሶስቱ ፈዳይኖች መሳሪያዎቹን ይረከቡና
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በሰዓቱ እስኪያርፍ ይጠብቃሉ፡፡ ዑስማን ሳልህ ሳቤ ግን
ወዲያዉኑ ወደ ሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ ይበርና ሁኔታውን እየተከታተለ ለዓለም ሚዲያ
መግለጫ ይሰጣል፡፡
*****
የጀብሃ ፈዳይኖች ኦፕሬሽኑን ከፈጸሙ በኋላ ማምለጥ አልቻሉም፡፡ መረጃው የደረሰው
የፓኪስታን የጦር ሰራዊት በአጭር ጊዜ ውስጥ ኤርፖርቱን ከበበው፡፡ ኤርትራዊያኑም እጃቸውን
እንዲሰጡ በድምጽ ማጉያ ለፈፈ፡፡ “እጃችሁን ከሰጣችሁ ወደ ፈለጋችሁት ሀገር ትሄዳላችሁ”
የሚል ቃል ተሰጣቸው፡፡ ኤርትራዊያኑ ማምለጥ የማይችሉት ነገር ነውና መሳሪያቸውን
አስረክበው ለፓኪስታን የጸጥታ ሀይሎች እጃቸውን ሰጡ፡፡
ይሁን እንጂ የፓኪስታን መንግሥት ሶስቱን ፈዳይኖች በነጻ አልለቀቃቸውም፡፡ ሶስቱም በሀገሪቱ
ዐቃቤ ህግ ተከሰው ሰኔ 25/ 1969 በካራቺ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት ቀረቡ፡፡ የኢትዮጵያ
መንግሥትም ሶስቱ ፈዳይኖች ተላልፈው እንዲሰጡት ለማግባባት በወቅቱ የውጪ ጉዳይ
ሚኒስትር በነበሩት ሰው የሚመራ ቡድን ወደ ፓኪስታን ላከ፡፡ የፓኪስታን ከፍተኛ ፍርድ ቤት
ሁሉንም ነገር ከመረመረ በኋላ በሶስቱ ፈዳይን ላይ የአስራ አራት ዓመት እስራት በየነ፡፡ በዚህ
መሐል ግን የጀብሃ መሪ የሆነው ዑስማን ሳልህ ሳቤ ትልቅ ሚና ተጫወተ፡፡ የዐረብ ሊግ አባል
ሀገራት ኤርትራዊያኑ በሰላም እንዲለቀቁ የፓኪስታን መንግሥትን እንዲያግባቡለት ያደረገው
ጥረት ተሳካለት፡፡ ከዐረብ ሊግ፣ ከዓለም አቀፍ ተማሪዎች ማህበር፣ ከዓለም አቀፍ ጸረ-
ጽዮናዊነት ህብረት፣ ከፍልስጥኤም ነጻ አውጪ ድርጅትና ከዓለም አቀፍ የኤርትራ ወዳጆች
ማህበር የመጣበትን ጫና ለመቋቋም ያልቻለው የፓኪስታን መንግሥት ሶስቱን ፈዳይኖች
ከአስራ አንድ ወራት እስር በኋላ በነጻ ለቀቃቸው፡፡
ይህ ኦፕሬሽን ጀብሃን በዓለም ዙሪያ ለማስተዋወቅ በእጅጉ ረድቷል፡፡ በርካታ ሀገራት ለግንባሩ
እውቅና ከመስጠት አልፎ የመሳሪያ ድጋፍ ማድረግ የጀመሩት ከዚህ የካራቺ ኦፕሬሽን በኋላ
ነው፡፡ የሚያስገርመው ነገር ደግሞ ጀብሃ ይህንን የተሳካ ኦፕሬሽን ያካሄደው በውስጡ
እየተፈጠረ የነበረው አደገኛ ቅራኔ ወደ ግጭትና እርስ በርስ መጠፋፋት እየተሸጋገረ በመሄድ
ላይ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ የቅራኔው አነሳስና የአፈታት ዘይቤ ምን ይመስላል? እንደሚከተለው
ተጠናቅሯል፡፡
እያደር ደግሞ የጀብሃ መሪዎች የሚፈጽሙት ሰቆቃ በአመራር ደረጃ ካሉት የድርጅቱ መሪዎችም
ተቃውሞ ይገጥመው ጀመር፡፡ በተለይ የድርጅቱ እውቅ መሪ የሆነው የአሳውርታው ተወላጅ
ዑሥማን ሳልህ ሳቤ በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸመውን ደባ በይፋ አወገዘ፡፡ ተራ ተዋጊ የነበሩ
አባላትም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በድርጅቱ ውስጥ የሰፈነውን ወታደራዊ አምባገነንነት
መቃወም ጀመሩ፡፡ ለነጻነት የሚፋለም ድርጅት ተዋጊዎቹን ያለ ፍትሕ ከገደለ ራሱንም ይገድላል
በማለት ተቃውሞአቸውን አሰሙ፡፡ የጀብሃ አንጋፋ መሪዎች የሆኑት እነ ኢድሪስ መሐመድ እና
ኢድሪስ ገላውዴዎስ የተነሳባቸውን ተቃውሞ ለማለዘብ ጥገናዊ የለውጥ እርምጃዎችን መውሰድ
ጀመሩ፡፡ ከነዚህ እርምጃዎች መካከል በታሪክ ምዕራፎች ጉልህ ሆኖ የሚጠቀሰው ግንባሩ
በ1960ዎቹ በስራ ላይ ያዋለው “የዞን አከፋፈል” ነው፡፡ ከዚህ በማስከተል እርሱን
እንመለከታለን፡፡
ጀብሃ የጦር ሀይሉን ሞራል ለማነሳሳትና የውጊያ ብቃቱን ለማጠናከር በሚል በ1966 የዞን
አወቃቀርን በስራ ላይ አዋለ፡፡ ይህ አወቃቀር የተወሰደው ከአልጄሪያው Front de Liberation
Nationale (FLN) ተመክሮ ሲሆን የአልጄሪያ ታጋዮች ሀገራቸውን ነጻ ለማውጣት ሲታገሉ የዞን
ክፍፍሉ በእጅጉ እንደጠቀማቸው በታሪክ ተጽፏል፡፡ በዚህ ክፍፍል መሰረት
ጀብሃ የየዞኑ ወታደራዊ ኮሚሳሮች ወደ ቻይና ሄደው የስድስት ወራት ወታደራዊና ፖለቲካዊ
ስልጠና እንዲያገኙ ረድቶአቸዋል (ኢሳያስ አፈወርቂ በ1966 ጀብሃን ተቀላቅሎ ዓመት
ሳይሞላው ወደ ቻይና የተላከው በዚህ ምክንያት ነው እንጂ አንዳንዶች እንደሚሉት
ሚስጢራዊ ተልዕኮ ስለነበረው አይደለም)፡፡
*****
ጀብሃ በስራ ላይ ያዋለው የዞን አከፋፈል ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ዞኖች በጣም ጠቅሟል፡፡
በዚህም የተነሳ ሁለቱ ዞኖች በወታደራዊ አቅምም ሆነ በገንዘብ በኩል ከፍተኛ ደረጃ ላይ
ደርሰው ነበር፡፡ በተለይ በዑመር እዛዝ የሚመራው “ዞን ሁለት” በሽምቅ ተዋጊ ድርጅቶች ታሪክ
ባልተለመደ መልኩ ለወታደሮቹ ደመወዝ ይከፍል እንደነበር በዘመኑ የጀብሃን እንቅስቃሴ
ለመዘገብ ወደ ኤርትራ በረሃ የተጓዘው አሕመድ ጠይፋር የተባለ ሱዳናዊ ጋዜጠኛ “ሐቂቃት
ጀብሃት ታሕሪረል ኤሪትሪያ” በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፍ ገልጿል፡፡ በተቀሩት ሶስት ዞኖች
ስር የተደራጁት ተዋጊዎች ደግሞ በችግር መጠበስ እጣ ፈንታቸው ሆኖ ቆይቷል፡፡
የሻዕቢያ ሰዎች “የጀብሃ መሪዎች የዞን አሰራሩን በስራ ላይ ያዋሉት ክርስቲያን የሆኑ
ኤርትራዊያንን ወደ ትግል ሜዳ እንዳይወጡ በቤታቸው ለመገደብ፣ ክርስቲያኖቹ ለሀገራችን
እንዋጋለን ካሉ ደግሞ በሀይለ ስላሴ መንግሥት ወታደሮች በእንጭጩ እንዲቀጩ ለማድረግ
ነው” ይላሉ፡፡ ጀብሃዎች ግን ይህንን ያስተባብላሉ፡፡ በነርሱ እይታ የዞን አከፋፈሉ የኤርትራ
ክርስቲያኖች ሲያነሱት የነበረውን ቅሬታ ለማስወገድ ጠቅሟል፤ ምክንያቱንም ሲገልጹ “በዞን
አሰራር መሰረት ክርስቲያኖቹ የሚዋጉት በራሳቸው ክልልና በራሳቸው አመራር ስር በመሆኑ
እጅግ ከሚፈሯቸው ዑመር እዛዝን ከመሳሰሉ ወታደራዊ አዛዦች ከሚደርስባቸው ጥቃት
ለማምለጥ ችለዋል” ይላሉ፡፡ ታዛቢዎች እንደሚሉት ግን ጀብሃ ራሱን መግደል የጀመረው የዞን
ክፍፍሉን በስራ ላይ ካዋለበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጀብሃ ከራሱ ጋር ሲዋጋ
ነው የከረመው፡፡ ይባስ ብሎም የዞን አሰራሩ በርካታ አፈንጋጭ ቡድኖች ከጀብሃ እንዲወጡ
ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚያስ ምን ተከተለ? የጀብሃ መጨረሻስ እንዴት ሆነ? በሚቀጥለው ክፍል
እንዳስሰዋለን፡፡
*****
ጥቅምት 30/ 2006
ጀብሃ እና ሻዕቢያ
ክፍል ሶስት
-----
ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ የሁሉም ዞኖች ወታደራዊ መሪዎች የተገኙበት አስቸኳይ
ኮንፈረንስ “አዶብሃ” በተባለ ስፍራ ተካሄደ፡፡ በኮንፈረንሱ ላይ ዱላ-ቀረሽ ክርክር ከተደረገ በኋላ
ተቀማጭነቱ በሱዳኗ ከሰላ ከተማ የሆነው “ቃኢዳ ሰውራ” (አብዮታዊ እዝ) እንዲፈርስ ተወሰነ፡፡
ከያንዳንዱ ዞን ስምንት ወጣት ሰዎች የተመረጡበትና 40 አባላት ያሉት “ቃኢዳ አል-አማ”
(ጠቅላይ መምሪያ) ተመሰረተ፡፡ ሆኖም የካይሮው ላዕላይ ምክር ቤት በነበረበት ይቀጥል ተባለ፡፡
የድርጅቱ መሪዎች እርምጃውን ህገ ወጥ ቢሉትም የ“አል-አማ” አባላት ግን ህጋዊ ነን በማለት
በእርምጃቸው ቀጠሉበት፡፡
በአዶብሃ ኮንፈረንስ ከተሳተፉት መካከል የሶስቱ ዞኖች (ሶስተኛ፣ አራተኛ እና አምስተኛ ዞን)
ታጋዮች ልብ ለልብ ተግባቡ፡፡ ውለው ሳያድሩም “ወታደራዊ ዞን” የሚባለውን አከፋፈል
ለማፍረስ ተስማሙ፡፡ “የአንዱ ዞን ታጋዮች በሌላኛው ዞን እንዳሻቸው ወታደራዊ ዘመቻ
ማካሄድ ይችላሉ” በማለትም አሰመሩበት፡፡ ሊያጠቃቸው የሚመጣውን የመንግሥት ጦር ሀይል
በህብረት ለመመከትም ተስማሙ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም በነዚህ ዞኖች ውስጥ ያሉ ታጋዮች
“ሰልፊ ነጻነት” እና “ህዝባዊ ኃይሊ” በሚባሉ ቡድኖች ስር ራሳቸውን አደራጁ፡፡
“ህዝባዊ ኃይሊ” በአብዛኛው የምጽዋና የሰምሃር አካባቢ ተወላጆችን ያቀፈ ነው፡፡ ቁጥራቸው
አነስተኛ ቢሆንም በፖለቲካም ሆነ በወታደራዊ ችሎታ አንቱ የተሰኙ ናቸው፡፡ ረመዳን
መሐመድ ኑር፣ ኢብራሂም አፋ እና መስፍን ሐጎስ የቡድኑ መሪዎች ነበሩ፡፡ የዚህ ቡድን
መንቀሳቀሻ ከምጽዋ በስተሰሜን የነበረው የባህር ጠረፍ ነበር፡፡ “ሰልፊ ነጻነት” ደግሞ
በአብዛኛው የሐማሴን እና የአከለ ጉዛይ ተወላጆችን ነው ያቀፈ ነው፡፡ አብርሃም ተወልደ፣
ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ሀብተሥላሤ ገብረ መድህን፣ ሰሎሞን ወልደማሪያም፣ ወልደ ሚካኤል ኃይለ
እና ባራኺ ንጉሡ የቡድኑ መስራቾች ናቸው፡፡ ኢሳያስ አፍወርቂ የዚህ ቡድን ጊዜያዊ መሪ ሆኖ
ተሰይሟል፡፡ የቡድኑ ዋነኛ መንቀሳቀሻ በደቀምሐረ ወረዳ የሚገኘው “የዓላ በረሃ” ነው፡፡ እነዚህ
ሁለት ቡድኖች በይፋ ከጀብሃ መገንጠላቸውን ሳያሳውቁ ትግሉን በየፊናቸው ማካሄድ ጀመሩ፡፡
ጀብሀም ስሙን በድጋሚ ላለማስጠቆር እስከ ቀጣዩ ጉባኤ ድረስ የቡድኖቹን ሁኔታ በዝምታ
መከታተሉን ቀጠለ፡፡
በሌላ በኩል ጀብሃ እስከ ዛሬ ድረስ የሚጸጸትበትን ታሪካዊ ስህተት የፈጸመው በዚሁ ወቅት
ነበር፡፡ ይኸውም የዑሥማን ሳልሕ ሳቤ ከስልጣን መባረር ነው፡፡ የጀብሃ መሪዎች ሳልህ ሳቤ
በደገኞች ላይ የሚፈጸመውን ኢ-ፍትሐዊ ቅጣት በመቃወሙ ቂም ይዘውበታል፡፡ በተጨማሪም
ከዐረቦች የሚሰጣቸው እርዳታ ወደ ኤርትራ ምድር የሚገባው በርሱ በኩል በመሆኑ በቅናት
ዐይን ይመለከቱት ነበር፡፡ ስለዚህ እርሱን አባርረው ሳሊህ አህመድ ኢያይ በሚባል ሰው
ለመተካት ወሰኑ፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ በልባቸው ሳልህ ሳቤ “ሽርሽር እንጂ የበረሃ ትግል
የማይችል ሰው በመሆኑ በሶሪያና ካይሮ ጎዳናዎች ተወስኖ ይቀራል” የሚል አስተሳሰብ
ነበራቸው፡፡ ውጤቱ ግን እነርሱ ከጠበቁት ውጪ ነው የሆነው፡፡ ሳልህ ሳቤ በኤርትራዊያን ዘንድ
ከፍተኛ ከበሬታ ያገኘበትን ገድል ለመፈጸም የተነሳሳው የጀብሀ መሪዎች ይህንን እርምጃ ከወሰዱ
በኋላ ነው፡፡ ሰውዬው ጀብሃዎች እንደገመቱት በዐረብ መዲናዎች አልቀረም፡፡ በቀጥታ ወደ
ሳህል በረሃ መጥቶ “ህዝባዊ ሀይሊ” ከሚባለው ቡድን ጋር ነው የተቀላቀለው፡፡ የቡድኑ
ታጋዮችም ወዲያውኑ በመሪነት ቦታ ላይ አስቀመጡት፡፡
ጀብሃ በ1971 ድርጅታዊ ጉባኤ ጠራ፡፡ የሁለቱ ዞኖች (ዞን አንድ እና ዞን ሁለት) ተወካዮች
በጉባኤው ተገኙ፡፡ ከግንባሩ የወጡት ሶስቱ ቡድኖች ግን በጉባኤው ላይ እንደማይገኙ
አስታወቁ፡፡ ጀብሃ ለጊዜው እነርሱን ችላ በማለት ጉባኤውን በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት
አካሄደ፡፡ በጉባኤው ፍጻሜ ላይ በርካታ ስር-ነቀል እርምጃዎች ተወሰዱ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ
የጀብሃ መለያ ሆኖ የሚታወቀው “ሰውራዊ ባይቶ” (“አብዮታዊ ምክር ቤት” ማለት ነው- በትግረ
ቋንቋ) የሚባለው የግንባሩ ላዕላይ ምክር ቤት በዚያ ጉባኤ ውሳኔ መሰረት ተፈጠረ፡፡ እነ ህሩይ
ተድላ ባይሩን የመሳሰሉ ታዋቂ ደገኛ ግለሰቦች ወደ አመራሩ መጡ (ህሩይ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ
እስከ አሁን ድረስ የጀብሃ ምክትል ፕሬዚዳንት ነው)፡፡ ተቀማጭነቱ ከሰላ ላይ የሆነው
“አብዮታዊ እዝ” (ቃኢዳ ሰውራ) ህጋዊ ስለሆነ በዚያው ይቀጥል ተባለ፡፡ ሆኖም አላግባብ ሰው
ገድለዋል የተባሉ የጦር መሪዎች ከስልጣን ተባረው በአዳዲስ ሰዎች ተተኩ፡፡
የጀብሃ መሪዎች ራሳቸውን እንዲህ ከቀያየሩ በኋላ “በድርጅቱ ውስጥ የነበረው ችግር ሙሉ
በሙሉ ተፈቷል፤ ከዚህ በኋላ የሚያንገራግር ወይንም ቅሬታ አለኝ የሚል አካል ለኤርትራ ነጻነት
እንቅፋት ነው” የሚል አዋጅ አወጁ፡፡ በተጨማሪም በብዙዎች አንደበት ተደጋግሞ
የሚጠቀሰውን “የኤርትራ መሬት ከአንድ ድርጅት በላይ አይችልም” የሚለውን የድርጅታቸውን
መርህ በይፋ አሰሙ፡፡ በዚህም መሰረት በጉባኤው ላይ ካልተሳተፉት ሶስት ቡድኖች መካከል
“ዑበል” እና “ህዝባዊ ኃይሊ” በሚባሉት ላይ ጥቃት ለመክፈት ወሰኑ፡፡ በ“ሰልፊ ነጻነት” ላይ
የሚወሰደው እርምጃ ግን ለጊዜው እንዲዘገይ ተወሰነ (እንዲህ የተደረገው፣ በሁለት ምክንያት
ነው ይባላል፤ አንደኛው ምክንያት “አብርሃም ተወልደ” የሚባለው የቡድኑ ዋነኛ ሰው ከጀብሃ
ጋር ለመደራደር ፍላጎት እንዳለው በድብቅ መልዕክት ልኳል የሚል ነው፤ ሁለተኛውና ዋነኛው
ምክንያት ደግሞ ቡድኑ በአብዛኛው ክርስትያን የሆኑ ታጋዮችን ያቀፈ በመሆኑ ከባድ እርምጃ
ከተወሰደበት “ጀብሃ ጸረ-ክርስቲያን ነው” የሚለው ፕሮፓጋንዳ ይጠናከራል በማለት ስለተፈራ
ነው ይባላል)፡፡
ህዳር 2/2006
ጀብሃ እና ሻዕቢያ
ክፍል አራት
-----
ባለፈው ክፍል እንደገለጽኩት “ሻዕቢያ” (ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ) በ1977 ባካሄደው
የመጀመሪያ ጉባኤው ረመዳን ሙሐመድ ኑር እና ኢሳያስ አፈወርቂን የግንባሩ ዋና ጸሓፊ እና
ም/ዋና ጸሓፊ አድርጎ መርጦአቸዋል፡፡ 37 አባላት ያሉት ማዕከላዊ ኮሚቴ እና 13 አባላት ያሉት
የፖሊት ቢሮም ሰይሟል፡፡ ሆኖም “ሻዕቢያ” ወደዚህ ደረጃ የደረሰው እንዲሁ በቀላሉ
አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ከሚያደርገው ውጊያ በተጨማሪ በግንባሩ ውስጥ
የተነሳውን የስልጣን ትግል እና የተሃድሶ ንቅናቄዎችን ጸጥ ካደረገ በኋላ ነበር ጉባኤውን
ለማካሄድ የቻለው፡፡ እነዚያ ንቅናቄዎች ምን ይመስላሉ? ለዛሬ አንዱን ላውጋችሁ፡፡
*****
በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ግንባር ቀደም ተራማጅ
ተማሪዎች አብዮታዊ ድርጅት ለመመስረት ከሀገር መሰደድ ጀምረው ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲው
የነበሩ ኤርትራዊያን ተማሪዎችም የነጻነት ትግሉን ለመቀላቀል ወደ ሜዳ በብዛት ወጥተዋል፡፡
በጊዜው በውህደት ሂደት ላይ ከነበረው የመጀመሪያው “ሻዕቢያ” (ELF-PLF) ጋር ከተቀላቀሉት
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ሙሴ ተስፋ ሚካኤል፣ ዮሐንስ ስብሐቱ፣ አፈወርቂ ተክሉ፣
ደበሳይ ገብረ ሥላሤ፣ ዶ/ር ርዕሶም ወልዱ፣ ደሀብ ተስፋጽዮን፣ አበራሽ መልኬ የመሳሰሉት
ይገኙባቸዋል (ዮሐንስ ስብሐቱ ከነ ብርሃነ መስቀል ረዳ እና ሀይሉ “ገሞራው” ጋር ከትምህርቱ
ሲባረር የኖረ አንጋፋ አብዮተኛ ተማሪ ነበር)፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ወደ ሜዳ በወጡበት ወቅት
ከጀብሃ ይልቅ ወደ ሻዕቢያ የሄዱት “ይህ አዲሱ ግንባር ተራማጅና ውስጣዊ ዲሞክራሲ
የሰፈነበት ነው” በሚል እሳቤ ነው፡፡ እዚያ ሄደው ያዩት እውነታ ግን ከጠበቁት ውጪ ነው
የሆነባቸው፡፡ ውስጣዊ ዲሞክራሲ የሚባል ነገር በድርጅቱ አይታወቅም፡፡ በታጋዮችና በአመራሩ
መካከል ያለው ግንኙነት ከረር ያለ ነው፡፡ አመራሩ ጥፋት ባጠፉ ታጋዮች ላይ የጭካኔ ፍርድ
ይሰጣል፡፡ በመሪዎቹ መካከልም ስምምነት የለም፡፡ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ታፍኗል፡፡
የንቅናቄው ጀማሪዎች ከተራ ታጋዩ ከፍተኛ ድጋፍ አገኙ፡፡ በዚህ የተደፋፈሩት አብዮተኞች
ተሰባስበው ከተወያዩ በኋላ “መጀመሪያ አመራሩን መለወጥ ይገባል” የሚል ግብ አስቀመጡ፡፡
“ሰልፊ ነጻነት” እየተባለ ወደሚጠራው መሪዎች ዘንድ ሄደው “እናንተ በአመራሩ ላይ ያላችሁ
ሰዎች ለምን ትናከሳላችሁ? ለምን ተግባብታችሁ አትሰሩም?” በማለት ጠየቋቸው (ልብ አድርጉ፤
እስከዚህን ጊዜ ድረስ “ሰልፊ ነጻነት” እና “ህዝባዊ ኃይሊ” የተባሉት ቡድኖች በይፋ
አልተዋሃዱም፤ ሆኖም ሁለቱም “ሻዕቢያ” ወይንም “ሕዝባዊ ሓርነት ኃይልታት” በሚለው
መጠሪያ መጠቀሙን ቀጥለዋል፤ የአብዮተኞቹ ንቅናቄ ያተኮረውም በአብዛኛው ደገኞችን
ባቀፈው የ“ሰልፊ ነጻነት” ቡድን ላይ ነው)፡፡ የ“ሰልፊ ነጻነት” መሪዎችም “ጥያቄው ተቀባይነት
አለው፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በታጋዩ ፊት እርቅ እናወርዳለን” በማለት ስሜታቸውን ገለጹ፡፡
በዚያን ጊዜ ጥያቄው በተለይ ያነጣጠረው ሰለሞን ወልደማሪያም፣ ተወልደ እዮብ እና አስመሮም
ገብረ እግዚአብሄር በተባሉት መሪዎች ላይ ነበር፡፡ የሰልፊ ነጻነት የበላይ መሪ የነበረው ኢሳያስ
አፈወርቂም ከንቅናቄው መሪዎች የቀረበውን ጥያቄ ደግፏል፡፡
*****
ይህ በሻዕቢያ ውስጥ የፈነዳው አብዮት በታሪክ ምዕራፎች “ምንቕስቓስ መንካዕ” ይባላል፡፡
“የመንካዕ ንቅናቄ” እንደማለት ነው፡፡ “መንካዕ” የሌሊት ወፍ ማለት ነው ይባላል (ቃሉ የ“ትግረ”
እንጂ “ትግርኛ” አይመስለኝም፤ እስቲ በደንብ የምታውቁ ሰዎች አስረዱን)፡፡ ንቅናቄውን
“መንካዕ” በማለት የጠሩት የንቅናቄው ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡ “የንቅናቄው መሪዎች ቀን ቀን ከኛ
ጋር እየዋሉ ማታ ማታ በኩራዝና በፋኖስ ሀይል ጽሑፋቸውን እየጻፉ ይበትኑ ነበር” በሚል
ምክንያት በዚህ ስም እንደጠሩት ይነገራል፡፡ በእውነትም የመንካዕ ንቅናቄ መሪዎች እጅግ
ቀስቃሽ የሆኑ አብዮታዊ ጽሑፎችን ማታ ማታ እየጻፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በስፋት በትነዋል፡፡
እዚህ ዘንድ ግርታ የፈጠረብኝን ነገር ላውጋችሁ፡፡ ሁሉም ምንጮች የኮሚቴውን መቋቋም
በትክክል ይገልጹታል፡፡ ኮሚቴው ከዚህ በላይ ሄዶ የድርጅቱን ስልጣን ስለመቆጣጠሩ ግን
አይጠቅሱም፡፡ በኤርትራዊያን የተጻፉትም ይህንኑ ነው የሚናገሩት፡፡ አቶ ተስፋሚካኤል ጆርጆ
የጻፉት ታሪካዊ ጽሑፍ ግን “የመንካዕ መሪዎች የድርጅቱን ስልጣን ለአስር ቀናት ይዘዋል”
ይላል፡፡ ትክክለኛው የትኛው እንደሆነ መወሰን ያስቸግራል፡፡ እንደኔ አስተያየት በኤርትራዊያን
የተነገረውን መቀበሉ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም የታሪክ ምሁራን እውነታውን
መርምረው ሊያሳውቁን ይገባል፡፡
*****
በ“መንካዕ” ንቅናቄ ግፊት የተመሰረተው ኮሚቴ ታጋዮች ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ አቀረበ፡
፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም በሺ የሚቆጠሩ አቤቱታዎችን ሰበሰበ፡፡ ከነዚያ አቤቱታዎች መካከል
400 ያህሉ በተጨባጭ የሚታዩ ችግሮችን ያንጸባርቃሉ በማለት አጸደቃቸው፡፡ በአቤቱታዎቹ
ላይ በመመርኮዝም አስር ያህል የርዕዮተዓለም፣ የዲሞክራሲ፣ የፍትሕና የህጋዊነት ጥያቄዎችን
አዘጋጅቶ በተራ ቁጥር አስቀመጠ፡፡ ጥያቄዎቹ ከሞላ ጎደል የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ድርጅቱ እና አመራሩ የሚታገሉለትን ሰፊ ህዝብ እንዳይገፉ (በህዝብ ላይ በደል
እንዳይፈጽሙ)
2. የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም በአስቸኳይ እንዲታወጅ፣ (የድርጅቱ
ታጋዮች የርዕዮተ ዓለም ትጥቅ እንዲታጠቁ ማለት ነው)
3. ድርጅቱ የነጠረ የትግል ታክቲክና ስትራቴጂ እንዲያወጣ (ወዳጅና ጠላትን ሲለይ
ጥንቃቄ እንዲያደርግ)
4. የድርጅቱ ጉባኤ በአስቸኳይ ተደርጎ መሪዎቹ በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲመረጡ
5. በድርጅቱ ውስጥ የሰፈነው ወታደራዊ አምባገነንነት እንዲወገድ
6. የድርጅቱ መሪዎች በሞኖፖል የያዙአቸውን ሃላፊነቶች ለሌሎች እንዲያከፋፍሉ
7. የጸጥታው ክፍል በእስረኞች ላይ የሚፈጽማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እንዲያቆም
8. ሁሉም ታጋዮች ወደ ፍርድ ሲቀርቡ በእኩል ዐይን እንዲታዩ
9. በድርጅቱ ህገ-ደንብ የሚሰጠው የሞት ፍርድ እንዲቀር (ታጋዩ ቢያጠፋ በማስተማር
እንጂ ነፍስ በማጥፋት መቅጣት ትግሉን የባሰ ይጎዳዋል)
10. በአመራሩና በታጋዩ መካከል የሚታየው የአኗኗር ልዩነት እንዲስተካከል (ታጋዩ
ጦሙን እያደረና እየታረዘ አመራሩ ሆዱን እየሞላ መንጎማለሉን ያቁም)
በጅምሩ ላይ የንቅናቄው ደጋፊ መስለው የታዩት የሰልፊ ነጻነት መሪዎች ጥያቄዎቹ እንዲህ
ተደርድረው ሲመጡላቸው የሚመልሷቸው ሆነው አልተገኙም፡፡ በተለይ ከአመራር ወርዶ
በጉባኤ ምርጫ ማካሄድ በጭራሽ የሚቀበሉት ነገር አልነበረም፡፡ ስለዚህ እንቅስቃሴውን
ከማጨናገፍ ውጪ የተሻለ ምርጫ አልታያቸውም፡፡ በመሆኑም ሁሉም መሪ ብልሃት
ያውጠነጥን ገባ፡፡ በመጨረሻም እንቅስቃሴው ከሸፈ፡፡ እንዴት? አሁንም እንቀጥል፡፡
*****
የሰልፊ ነጻነት መሪዎች እርስ በርስ ይሻኮቱ ነበር ብያለሁ፡፡ ታዲያ ታጋዩ ወደነርሱ ጣቱን
ሲቀስር ሽኩቻውን ለጊዜው ማቆም ግድ ሆነባቸው፡፡ ታጋዩ “ተስማምታችሁ ምሩን” ያለውን
እነርሱ የስልጣናቸው መድህን አደረጉት፡፡ ታጋዩ ለአውራጃዊነት በጣም ስሜታዊ ስለነበር በዚሁ
ደካማ ጎኑ ሊገቡበት ወሰኑ፡፡ በተለይ በጊዜው በጣም የሚፈራውና የጸጥታና የወታደራዊ ክፍሉን
በበላይነት የሚመራው ሰለሞን ወልደማሪያም ስለነበር ንቅናቄዉን የማዳፈኑ ተግባር በርሱ
እንዲመራ ተደረገ፡፡ ከማንም በፊት ንቅናቄውን “ዲሞክራሲያዊ ነው” በማለት ያወደሰው
ሰለሞንም አቋሙን ገልብጦ ንቅናቄውን ለማጥፋት ቆርጦ ተነሳ፡፡ ወደ ሀማሴን ልጆች እየቀረበ
“ይህ እኮ የአከለ ጉዛይ ልጆች አድማ ነው፤ እንዴት ከነርሱ ጋር ትሰለፋላችሁ?” አላቸው፡፡ ወደ
ሙስሊሞቹ ተጠግቶም “እነዚህ ክርስቲያኖች ሊያጠፏችሁ ተነስተዋል፤ ከነርሱ ጋር
እንዳትወግኑ” በማለት መከራቸው፡፡ ከሌሎች አውራጃዎች በመጡትም ላይ ተመሳሳይ ዘዴ
በመጠቀም “እንቅስቃሴው የአከለ ጉዛይ ልጆች በአውራጃዊነት ስሜት ያፈነዱት ነው፤
ዓላማቸው ድርጅቱን ማጥፋት ነው” ተብሎ እንዲወራ ተደረገ፡፡ እነ ስብሐት ኤፍሬም እና
ጴጥሮስ ሰለሞን የመሳሰሉትን የሐማሴን ልጆችን ደግሞ ኢሳያስ አፍወርቂ ራሱ እየተጠጋቸው
“መንካዕ የአከለ ጉዛይ ንቅናቄ ስለሆነ በቶሎ እጃችሁን አውጡ” አላቸው፡፡
*****
የመንካዕ ንቅናቄ ታሪክ በአጭሩ ይህንን ይመስላል፡፡ ይህ ንቅናቄ የተቋጨበት መንገድ
በየቦታው ሲሰማ እጅግ ከባድ የሆነ ነቀፌታና ውግዘት ገጥሞታል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ
ተማሪዎች እንቅስቃሴ ትልቅ ስም የነበረውና በ1957 (እንደ ሐበሻ አቆጣጠር) በዩኒቨርሲቲ
ተማሪዎች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከትምህርት ገበታ ከተባረሩት ሰባት ተማሪዎች አንዱ የነበረው
የዮሐንስ ስብሐቱ አሟሟት የብዙዎችን ልብ አቁስሏል፡፡ የሚገርመው ታዲያ ይህ በአሳዛኝ
ፍጻሜ የተቋጨው ንቅናቄ የተካሄደው የኢህአፓ መስራቾች በ“ህዝባዊ ሓርነት ኃይልታት” ቃል
በተገባላቸው መሰረት ለወታደራዊ ስልጠና በኤርትራ ምድር በነበሩበት ወቅት ነው፡፡ ክፍሉ
ታደሰ እንደጻፈው የ“ሰልፊ ነጻነት” መሪዎች እንቅስቃሴውን የቀለበሱበት አካሄድና በተራማጅ
አብዮተኞች ላይ የወሰዱት የቅጣት እርምጃ በስፍራው በነበሩት የኢህአፓ ታጋዮች ላይ የማይሽር
የስነ-ልቦና ቀውስ አድርሷል፡፡ አንዳንድ ታዛቢዎች ደግሞ ለሽምቅ ውጊያ ጫካ የገቡ በርካታ
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ለውስጣዊ ተሃድሶ የሚታገሉ አብዮተኞችን “አንጃ ፈጥራችኋል”
እያሉ መጨፍለቅን የተማሩት “ሻዕቢያ”(“ሰልፊ ነጻነት”) የ“መንካዕ” ንቅናቄን ከደመሰሰበት ስልት
ነው ይላሉ፡፡
ህዳር 3/2006
*****
ጀብሃ እና ሻዕቢያ
ክፍል አምስት
በትናንትናው ጽሑፌ ስለ“መንካዕ” ንቅናቄ ታሪክ አውግቼአችሁ ነበር፡፡ የዛሬው ጽሑፍ ደግሞ
ከመንካዕ በኋላ በሻዕቢያ ውስጥ በታዩ ሁለት መለስተኛ ንቅናቄዎች ላይ ያተኩራል፡፡ እነዚህ
ንቅናቄዎች የመንካዕን ያህል ጥንካሬ አልነበራቸውም፡፡ ሆኖም ከሻዕቢያ ጋር ሁሌ የሚጠቀሱ
በመሆናቸው ልንዳስሳቸው ግድ ይለናል፡፡
ያ ታጋይ ጎይቶም በርሄ ይባላል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሩቅ ነው፡፡ ሻዕቢያን
የተቀላቀለው በ1972 ነው፡፡ ይህ ሰው ከፍተኛ የሆነ የስነ-ጽሑፍና የርዕዮተ ዓለም ትንታኔ
ችሎታ ነበረው፡፡ በዘመኑ እጅግ በጣም ይፈለጉ የነበሩትን ማርክሳዊና የዲያሌክቲክ ፍልስፍና
መጻሕፍትን ከውጪ ቋንቋዎች ወደ ትግርኛ ተርጉሟል፡፡ እርሱ ራሱ ከጻፋቸው ኦሪጂናል
ጽሑፎች መካከል ደግሞ “መን እዩ ብፅአዊ? መን እዩ ሰውራዊ?” (“ጓድ” ማለት ማን ነው?
አብዮታዊውስ ማን ነው?) የሚል ርዕስ ያለው ባለ 30 ገጽ መጣጥፍ ከፍተኛ ተቀባይነት
እንደነበረው የታሪክ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ሻዕቢያ የርሱን ጽሑፎች ታጋዩን ለማስተማር
ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ይህ ሰው በዕድሜውም ሆነ በተሰጥኦው አንቱታን ያገኘ ስለሆነ ሁሉም
ታጋዮች “ብጽአይ” (ጓድ) በማለት ነበር የሚጠሩት፡፡
“ብጽአይ” ጎይቶም በመንካዕ ንቅናቄ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ አላደረገም፡፡ ሆኖም ውጥረቱን
እንዲሸመግሉ ከተመረጡ ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ እነ ኢሳያስ የመንካዕ መሪዎችን
በከባድ ቅጣት ዝም ሲያሰኟቸው ግን “የተሰጠው ፍርድ ኢ-ፍትሓዊ ነው” በሚል ተቃውሞ
አሰምቷል፡፡ በዚህም ከሃላፊነት እንዲወርድ ተደርጓል፡፡ ታዲያ ብፅአይ ጎይቶም ስልጣኔን
ተቀማሁ ብሎ ወደ ኩርፊያ አልሄደም፡፡ ድምጹን አጥፍቶ በድርጅቱ ውስጥ ዲሞክራሲ
የሚሰፍነበትን መንገድ ያውጠነጥን ነበር፡፡ በ1975 መጨረሻ ላይም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
ተማሪዎች የነበሩ ጥቂት ጓዶች ግንባሩን ሲቀላቀሉ ከነርሱ ጋር መቀራረብ ጀመረ፡፡ ከተማሪዎቹ
ጋር ባደረገው ውይይትም “ድርጅቱን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ አለብን” የሚል አጀንዳ
አስታጠቃቸው፡፡ እነዚያ ወጣቶችም የርሱን ሀሳብ ማቀንቀን ጀመሩ፡፡ በዚህ ነጥብ ዙሪያ ታጋዩን
ማወያየትና ድጋፍ ማሰባሰብ ሞከሩ፡፡ አንዳንዶች ወደነርሱ ተጠጉ፡፡ ብዙዎቹ ግን የመንካዕ
ትውስታ ከአዕምሮአቸው ያልጠፋ በመሆኑ ወደ ብጽአይ ጎይቶምና ጓዶቹ ለመጠጋት
አልፈቀዱም፡፡ እነ ብጽአይ ግን ጥረታቸውን ቀጠሉ፡፡ በርካታ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች
ድጋፍ ሰጡአቸው፡፡ ሆኖም ዓላማቸውን በሚያስፈጽሙበት መንገድ ላይ በመምከር ላይ ሳሉ
በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ የስለላ መረቡን በሁሉም የሻዕቢያ ታጋዮች ላይ እንደ ሸረሪት ድር ያደራው
የ“ሀላዋ ሰውራ” አዳኞች በቀላሉ “ቀጨም” አደረጓቸው፡፡ የንቅናቄው መሪዎችና ተባባሪዎች
የተባሉት በሙሉ እየተፈለጉ ታሰሩ፡፡
የ“ሀለዋ ሰውራ” ኃላፊዎች ብጽአይ ጎይቶምንና ጓዶቹን ለአራት ዓመታት በእስር ካቆዩአቸው
በኋላ በ1980 በሞት ቀጡአቸው፡፡ ብጽአይ ጎይቶም የተረጎማቸው መጻሕፍትና በራሪ
ወረቀቶችም ከያሉበት እየተሰበሰቡ ተቃጠሉ፡፡ በጎይቶም ጽሑፎች የተበላሸውን የታጋይ አዕምሮ
ለማደስ በሚልም ስታሊናዊ የሶሻሊዝም ፍልስፍና ድርሰቶች በብዛት እንዲተረጎሙ ተደረጉ
(የትርጉም ስራውን በዋናነት ያከናወነው በ1985 ገደማ በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር
የነበረውና አሁን በሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕክተኛ ሆኖ የሚያገለግለው ሀይሌ
መንቆርዮስ እንደሆነ ይነገራል)፡፡
*****
ይህ ብዙ ሳይራመድ በእንጭጩ የተቀጨው ንቅናቄ “ብፅአይ ምንቕስቓስ” ይባላል፡፡ “የጓዱ
እንቅስቃሴ” ማለት ነው፡፡ “ጓድ” ወይንም “ብፅአይ” ተብሎ የሚጠራው ጎይቶም በርሄ ነው፡፡
ከርሱ ጋር በቅርበት ሆኖ እንቅስቃሴውን መርቷል የሚባለው ደግሞ ዓለም አብርሃ የተባለ ታጋይ
ነው፡፡ እነዚህ ጓዶች እንደ “መንካዕ” ንቅናቄ መሪዎች “የድርጅቱ አመራር ከስልጣን ይውረድልን”
አላሉም፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ለመጠየቅ ብቻ ነበር የተነሱት፡፡ ሆኖም
የሰልፊ ነጻነት መሪዎች በእንቅስቃሴው አልተደሰቱም፡፡ እንዲያውም የድርጅቱን ህልውና
የሚያናጋ መናፍቃዊ ንቅናቄ አድርገው ነው የወሰዱት፡፡ ሻዕቢያዎች “የብፅአይ ምንቕስቃስ”
መሪዎች “የኤርትራ አብዮታዊ ፓርቲ (ERP) የተባለ ህገ-ወጥ ፓርቲ በግንባሩ ውስጥ
አቋቁመዋል፤ የታወቀውን የግንባሩን ሶቪየት ቀመስ የርዕዮተ ዓለም አቅጣጫ በመቀልበስ
የሊቀመንበር ማኦ ዜዱንግን መስመር ለማስፈን ሞክረዋል፤ በመሆኑም የሞት ቅጣት መፈጸሙ
በግንባሩ ህግ መሰረት ተገቢ ነው” ይላሉ፡፡ ሆኖም ይህ “የኤርትራ አብዮታዊ ፓርቲ” የተሰኘ
ፓርቲ በግንባሩ ውስጥ ስለመፈጠሩ ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
በዚህ ንቅናቄ ገፍቶ የወጣው ዋነኛ ጥያቄ “በግንባሩ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣው ሙስናና
ብልሹ አሰራር ይወገድ” የሚል ነው፡፡ ይሁንና የዚህ ንቅናቄ ጀማሪ ማን እንደሆነ በትክክል
አይታወቅም፡፡ በንቅናቄው ውስጥ ከተሳተፉት ግንባር ቀደም መሪዎች መካከል ዶ/ር እዮብ
ገብረ-ልዑል፣ መሓሪ ግርማ-ጽዮን፣ ገብረ-ሚካኤል መሐሪ-እዝጊ፣ ህብረት ተስፋ-ጋብር፣ ኪዳኔ
አቤቶ፣ ፍሥሐዬ ኪዳኔ፣ አርአያ ሰመረ፣ አማኑኤል ፊላንሳ የተባሉት ይጠቀሳሉ (ብዙዎቹ
በአውሮጳ ሀገራት የተማሩ ናቸው)፡፡
ኢሳያስ አፈወርቂ ሰለሞንን ከስልጣኑ ያስነሳው “ይህ ወጣት በድርጅቱ ውስጥ ቁልፍ የሆኑ
ቦታዎችን በመዳፉ ጠቅልሎ በመያዙ ወደፊት ከሊቀመንበርነቴ ያባረኛል” የሚል ስጋት ስለገባው
መሆኑን ታሪኩን የሚያውቁ ምስክሮች ያስረዳሉ፡፡ በርግጥም ሰለሞን በሰልፊ ነጻነት ውስጥ
ፈላጭ ቆራጭ ሰው ነበር፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ የቡድኑ መሪ ሆኖ ቢቀመጥም ድርጅቱን በቀጥታ
የሚመራው ሰለሞን ወልደማሪያም ነበር፡፡ በወቅቱ የድርጅቱ አባል የነበሩት አቶ አድሓኖም
ፍትዊ የተባሉ ኤርትራዊ በጊዜው የነበረውን የስልጣን ክፍፍል ሲያስረዱ “ሰለሞን ሁሉንም ነገር
ነበር፤ የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሐፊ ነው፡፡ ወታደራዊ አዛዥም ነው፤ የስልጠና ማዕከል ሀላፊም
ነው፤ የጠቅላይ እዙ የበላይ አዛዥም ነበር፤ በግንባር ያለውን ጦር የሚያንቀሳቅሰው እርሱ ነው፡፡
ኢሳያስ አፈወርቂ ለስም ብቻ ነው ሊቀመንበር ሆኖ የተቀመጠው” በማለት አስረድተዋል፡፡
ህዳር-10/2006
ጀብሃ እና ሻዕቢያ
ክፍል ስድስት
“ሀለዋ ሰውራ” የተሰኘ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት በበዓሉ ግርማ “ኦሮማይ” ውስጥ ነው፡፡
የኦሮማዩ “ስዕላይ በራኺ” የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሓፊ ነው በሚል በድርሰቱ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡
ነገሩ ግን ልብ ወለድ ነው፡፡ ስዕላይ በተሰኘ ስም የተጠቀሰው ገጸ-ባህሪ የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሃፊ
ሆኖ አያውቅም፡፡ ሆኖም የእስር ቤቱ ሃላፊ ነበር፡፡ ታዲያ ስለሻዕቢያ ሀለዋ ሰውራ
የሚያውቀውን ሚስጢር ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ለህዝብ የገለጸው ይኸው በበዓሉ ብዕር
“ስዕላይ በራኺ” ተብሎ የተጠራው ሰው ነው፡፡ የዚህ ሰው ትክክለኛ ስም ተክላይ ገብረማሪያም
ነው፡፡ በሻዕቢያ ውስጥ ይበልጥ የሚታወቀው ግን “ተክላይ አደን” በተሰኘው የበረሃ ስም ነው፡፡
ተክላይ የሻዕቢያ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበር፡፡ በ1981 (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1973)
ከሻዕቢያ ከድቶ ለደርጎች እጁን ከሰጠ በኋላ ከኢትዮጵያ ሬድዮ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ
“ሀለዋ ሰውራ” ስለሚባለው የሻዕቢያ ሚስጢራዊ ተቋም የሚያውቀውን ሁሉ ዘርዝሯል፡፡
ሌሎችም እንደዚሁ ስለ “ሀለዋ ሰውራ” የሚያውቁትን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የተዘረዘረው
መረጃ የተገኘው ግን ከልዩ ልዩ የኤርትራ ድረ-ገጾች፣ ከመጽሔቶችና ከጋዜጦች ነው፡፡
*****
የኤርትራ ተወላጆች “ሀለዋ ሰውራ” የሚባለውን ተቋም Gestapo ከሚባለው የናዚ ጀርመኖች
የስለላና የአፈና ድርጅት ጋር ያመሳስሉታል፡፡ ሆኖም “ሀለዋ ሰውራ”ን በዚያ ደረጃ ለመፈረጅ
ያዳግታል፡፡ ቢያንስ ጉልበቱና አቅሙ ከዚያ ያንሳሉ፡፡ ይሁንና በርካታ ሰዎች በሀለዋ ሰውራም
መሰቃየታቸውን ይናገራሉ፡፡
“ሀለዋ ሰውራ” በቀጥታ ሲተረጎም “አብዮት ጥበቃ” ማለት ነው፡፡ በዚህ ስም የሚጠራው
የሻዕቢያ የስለላና የምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በስሩ ሶስት ክፍሎች አሉት፡፡
1. የመረጃ ክፍል፡- ማንኛውም የሻዕቢያ አባል አመራሩን የሚቃወም ንግግር ሲናገር እና
ጽሑፍ ሲያሰራጭ ቢገኝ ሪፖርት የሚያደርገው ይህ ክፍል ነው፡፡ እንደሚባለው
በትግሉ ዘመን ሻዕቢያ በሺህ የሚቆጠሩ ሰላዮችን በታጋዮቹ መካከል አሰማርቶ ነበር፡፡
እነዚያ ሰላዮች ከታጋዩ የቃረሙትን ወሬ ወደ ዋና ክፍሉ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ ታዲያ
ሻዕቢያ የመንካዕ እና የብፅአይ ንቅናቄዎች ከመከሰታቸውም በፊት አባላቱን እርስ
በራስ እንዲጠራጠሩ አድርጎ አቆላልፎአቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ አንድ ታጋይ
ዕድሜው እንዲረዝም ከፈለገ አመራሩን ማሞገስ ወይንም ዝም ማለት ይገባዋል፡፡
2. የምርመራ ክፍል፡- በሀለዋ ሰውራ ሰላዮች ተጠቁሞ የተያዘ ሰው ወደዚህ ክፍል
ይተላለፋል፡፡ ይህ ክፍል ጥፋት ተገኝቶባቸዋል ተብለው የተያዙ ተጠርጣሪዎች
ሚስጢር እንዲያወጡ በማለት በልዩ ልዩ የምርመራ ቴክኒኮች ይጠቀማል፡፡ ዋነኛው
ስልት ግን ተጠርጣሪዎችን መግረፍና ማሰቃየት ነው፡፡
3. የእስረኛ ክፍል፡ እስረኞች በምርመራ ላይ እያሉ የሚቆዩበት ክፍል ነው፡፡
በምርመራው ጥፋተኛ ተብለው ፍርድ የተላለፈባቸው ተጠርጣሪዎችም የሚታሰሩት
በዚሁ ክፍል ነው፡፡ ታዲያ ታሳሪዎቹ በሰላም አይቆዩም፡፡ በየጊዜው ሰቆቃና ስቃይ
ይፈጸምባቸዋል፡፡ ከሻዕቢያ እስር ቤት በህይወቱ የወጣ ሰው ዕድለኛ ነው-ታዛቢዎች
እንደሚሉት፡፡
በትግሉ ዘመን ከ3000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በሀለዋ ሰውራ እስር ቤቶች ተሰቃይተው እንደሞቱ
የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ቡድኖች በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡ ሻዕቢያ
በትግል ዘመኑ አምስት ያህል እስር ቤቶች የነበሩት ሲሆን ሁሉም የሚገኙት በሳህል አውራጃ
ነው፡፡ ከነዚህ እስር ቤቶች መካከል “አራግ” እና “ሀክሺብ” በተባለ ቦታ የሚገኙት ከፍተኛ
የስቃይ ቦታዎች እንደሆኑ ይነገራል፡፡
1. ሰለሞን ወልደማሪያም፡ ከሰልፊ ነጻነት ቡድን መስራቾች አንዱ ነው፡፡ ከኢሳያስ በፊት
ከጀብሃ ከተገነጠሉት አስራ አንድ ወጣቶች መካከል ይመደባል፡፡ ይህ ሰው የሀለዋ
ሰውራ መስራች እና ዋና ጸሓፊ ነው፡፡ ለብዙ ወጣቶች ህይወት መጥፋት ተጠያቂ
እንደነበረ ይነገራል፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ሰለሞን በ1973-74 የተካሄደውን
የመንካዕ ንቅናቄ ያዳፈነ ሰው ነው፡፡ ሆኖም በሻዕቢያ ውስጥ የነበረው ስልጣን
መጨመሩ ያሰጋው የኢሳያስ ቡድን በዘዴ ካስወገደው በኋላ በሚስጢር ገድሎታል፡፡
2. ሀይሌ ወልደሚካኤል፡ የምርመራ ክፍሉ ሃላፊ ነበር፡፡ በመንካዕ ንቅናቄ የተሳተፉትን
ከመረመረ በኋላ “ወንጀል አልተገኘባቸውም፤ የጦር ሜዳ ደንብ በመተላለፍ ግን
ሊጠየቁ ይችላሉ” የሚል ሪፖርት አሳልፏል፡፡ ሆኖም አመራሩ የርሱን ሪፖርት
ስላልተቀበለ በርሱ ቦታ ሌላ ሰው ተክቷል፡፡ እርሱን ወደ ከረን አካባቢ ከመደቡት
በኋላ በውጊያ ላይ ከራሱ ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት እንደሞተ ይነገራል፡፡
3. ሀይሌ ጀብሃ፡- በጭካኔው ብዙ የተነገረለት መርማሪ ነው፡፡ የመንካዕ ንቅናቄ
መሪዎችንና ሌሎችንም በድብደባ፣ በግርፋትና በልዩ ልዩ ዘዴዎች በብዛት አሰቃይቷል፡
፡ ብዙ ሰዎችን በእጁ እንደረሸነም ይወሳል፡፡ በኋላ ግን ግንባሩ ራሱ “ያንተ ቶርች
በዝቷል” በማለት ረሽኖታል፡፡
4. አሽኣል ወዲ ዘረ፡ የሀይሌ ጀብሃ ምክትል የነበረ መርማሪ ነው፡፡ እርሱም “ለእስረኛ
የማይራራ ጨካኝ መርማሪ” ተብሎ በ1980 ተገድሏል፡፡
5. ተክላይ አደን (ተክላይ ገብረማሪያም)፡ ኦሮማይ ውስጥ ያለው “ስዕላይ ባራኺ”
በከፊል እርሱን ይወክላል (ግማሹ ታሪክ የተስፋሚካኤል ጆርጆ ነው)፡፡ ተክላይ
የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና በሀለዋ ሰውራ የእስረኞች ክፍል ሃላፊ ነበር፡፡ ቀደም ብዬ
እንደገለጽኩት ይህ ሰው ብዙ እስረኞችን ሲያሰቃይ ከቆየ በኋላ ህሊናው በጸጸት
ስለተነካ አጋጣሚ ጠብቆ ለደርግ እጁን ሰጥቷል፡፡
6. ዓሊ ሰዒድ አብደላ፡ ጀብሃ በዓለም ላይ የታወቀበትን የካራቺ ኦፕሬሽን የመራ ፈዳይን
ነበር፡፡ ከዚያ በኀላ “ህዝባዊ ሀይሊ” የሚባለውን የሳላህ ሳቤ ቡድን ተቀላቅሎ ከጀብሃ
ኮብልሏል፡፡ ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) ከተመሰረተ በኋላ ከ1977 እስከ
1987 ድረስ የሀለዋ ሰውራ ዋና ጸሓፊ ሆኖ ሰርቷል፡፡ በርካታ ኤርትራዊያን በርሱ
የአመራር ዘመን ሻዕቢያ በእስረኞች ላይ ለፈጸመው ግድያና ሰቆቃ በዋናነት ተጠያቂ
የሚያደርጉት እርሱን ነው፡፡
ህዳር 12/2006
ጀብሃ እና ሻዕቢያ
ክፍል ሰባት
--------
ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) የመጀመሪያ ጉባኤውን ካካሄደ በኋላ የአመራሩን ቁልፍ
ቦታ እንዲይዙ የመረጣቸው አስራ ሶስት የፖሊት ቢሮ አባላት እነማን እንደነበሩ ታውቃላችሁ?
ካላወቃችኋችሁ እኝሁላችሁ፡፡
ከነዚህ የሻዕቢያ መሪዎች መካከል ሶስቱ በህይወት የሉም፡፡ ሻዕቢያ “የጀግኖች ጀግና” እያለ
የሚያሞካሸው ኢብራሂም አፋ በ1985 ከረን አቅራቢያ በተደረገ አንድ ውጊያ ላይ ሞቷል
(ብዙዎች ኢሳያስ ራሱ ነው ያስገደለው በማለት ቢጽፉም ከነጻ ምንጭ ለማረጋገጥ አልተቻለም)፡
፡ ዓሊ ሰዒድ አብደላ ደግሞ ከ2001- እስከ 2005 ድረስ የኤርትራ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ
ካገለገለ በኋላ ሞቷል፡፡ መሐመድ ሰዒድ በርሄም የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆኖ ካገለገለ በኋላ
በ2007 አርፏል፡፡ ማሕሙድ አሕመድ ሸሪፎ፣ ሀይሌ ወልደ ትንሳኤ፣ ብርሃነ ገብረ እግዚአብሄር፣
ጴጥሮስ ሰለሞን እና ዑቅበ አብርሃ ደግሞ G-15 የሚባለው ቡድን ቀንደኛ መሪዎች ናቸው
ተብለው ከታሰሩ 12 ዓመት ሆኖአቸዋል፡፡ መስፍን ሐጎስ እንዳጋጣሚ ውጪ ሀገር ስለነበር
ከእስሩ አምልጧል፡፡ ረመዳን መሐመድ ኑር ከፖለቲካው ዓለም ራሱን አግልሏል፡፡ በአሁኑ
ወቅት ከኢሳያስ ጋር በስልጣን ላይ ያሉት ስብሐት ኤፍሬም እና አል-አሚን መሐመድ ብቻ
ናቸው (ስብሐት የመከላከያ ሚኒስትር አል-አሚን የህግዴፍ ዋና ጸሐፊ ናቸው)፡፡
እነዚያ ታላላቅ የሻዕቢያ ሰዎች (G-15 የሚባሉት) ለእስር ሊዳረጉ የበቁት አቶ ኢሳያስ
አፈወርቂ የኤርትራን ህገ-መንግሥት በአስቸኳይ በስራ ላይ እንዲያውሉ ፔቲሽን በመፈራረም
ስለጠየቁ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሁለት ጊዜ ያህል “ተው.. እየተሳሳታችሁ ነው… እረፉ…” በማለት
ከመለሰላቸው በኋላ በመስከረም ወር 2001 በቁጥጥር ስር እንዲዉሉ በማዘዝ ወደ እስር ቤት
ወርውሮአቸዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያሉበት ሁኔታ በትክክል አይታወቅም፡፡
*****
ሻዕቢያ የመጀመሪያ ጉባኤውን ያካሄደው በምስራቅና ሰሜን ኤርትራ የሚገኙትን ከረን፣
ደቀምሐረ፣ ጊንዳእ፣ ሰንአፌ፣ ሐሙሲት የመሳሰሉ ከተሞችን በተቆጣጠረ ማግስት ነው፡፡ ሆኖም
ከሁለት ዓመታት በኋላ ከናቅፋ በስተቀር ሁሉንም ከተሞች መልቀቅ ግድ ሆኖበታል፡፡ ጀብሃም
በወቅቱ በምዕራብ ኤርትራ የሚገኙትን መንደፈራ፣ አዲኳላ፣ ተሰነይ፣ አቆርዳትና ባርካን
ተቆጣጥሯል፡፡ ሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ጠንካራ ማጥቃት ሲሰነዝርበት ግን ከተሞቹን
በሙሉ ለቅቋል፡፡ ሻዕቢያ የደርግ ጦርን ጥንካሬ ከመዘነ በኋላ በጊዜው በነበረው አቅም
የማይመልሰው መሆኑን ስለተረዳ የተፈጥሮ መከላከያው ወደሆነው የሳህል በረሃ ገብቶ መደበቅን
ነው የመረጠው፡፡ ጀብሃ ግን በጀብደኝነት ከደርግ ጦር ጋር ሲዋጋ ሀይሉን አስጨርሷል፡፡
“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉም የኔ ደጀን ነው ብሎ የተማመነበት የባርካ ቆላማ
አውራጃም በደርግ ሰራዊት ተይዞበታል፡፡ ስለዚህ ለጊዜው ማምለጫ ከሆነኝ በሚል የሻዕቢያ
አምባ በሆነው የሳሕል ተራራ ውስጥ ራሱን ለመደበቅ ሞክሯል፡፡
ሁለቱ ግንባሮች የርስ በርስ መተላለቁን በ1974 በመጣባቸው የህዝብ ግፊት አቁመው
ስለነበር ሻዕቢያ ከደርግ ሸሽቶ በመጣው የጀብሃ ሰራዊት ላይ ብረት አላነሳም፡፡ እየዋለ ሲያድር
ግን የድሮው ቂም አገረሸባቸው፡፡ ሻዕቢያ “ባርካን አስረክበህ ሳሕልን ልትይዝ መጣህ እንዴ!”
በማለት በጀብሃ ላይ ጠንካራ በትር ሰነዘረ፡፡ ጀብሃም በአልሞት ባይ ተገዳይነት ራሱን ለማትረፍ
ሞከረ፡፡ ለሁለት አመታት ያህልም እየተከላከለ ቆየ፡፡ በመጨረሻ ላይ ግን ተፍረከረከ፡፡ ከደርግ
ጥቃት የተረፈው መለስተኛ ጦሩ በሻዕቢያ ሲቀጠቀጥበት አንዲት መናኛ ምልክት እንኳ ሳይተው
ወደ ሱዳን ተሰደደ፡፡ በ1961 በሀሚድ አዋቴ የተጀመረው የጀብሃ የትጥቅ ትግልም በዚሁ መንገድ
አከተመ፡፡ ድርጅቱም ከ1981 ጀምሮ በስም ያለ፣ በተግባር ግን የሌለ የስደተኞች ማህበር ሆኖ
ቀረ፡፡
በዚህ ዘመን መሰረታቸው “ጀብሃ” የሆነ ከሃያ ፓርቲዎች በላይ አሉ፡፡ ሁሉም
የሚንቀሳቀሱት ከኤርትራ ውጪ ነው፡፡ ጥቂቶቹን ለማስታወስ ያህል እነሆ!
1. ELF-RC (ጀብሃ- ሰውራዊ ባይቶ) መሪው ከጀብሃ መስራቾች አንዱ የሆነው አብደላ
ኢድሪስ ነው፡፡
2. ELF-PLF (የኢራቅ እና የሶሪያው በዕሥ ፓርቲን የሚመስል ፍልስፍና ይከተላል፡፡
ለረጅም ዓመታት ቡድኑን የሚመራው አብዱልቃዲር ጄይላኒ ነበር)
3. EDM (በህሩይ ተድላ ባይሩ የሚመራ)
4. ELF-United Organization- በዑመር ቡራጅ የሚመራ
5. ሳግም-በነ ተወልደ ገብረሥላሴ የሚመራ ነው፡፡
6. DFLE- በግብረ ብርሃን ዘረ-ሰናይ የሚመራ ነው፡፡
7. ደምሕኤ (መሪው ማን እንደሆነ አላውቀውም)፡፡
------
ህዳር 13/2006
ጀብሃ እና ሻዕቢያ
ክፍል ስምንት
---
በዚህ ክፍል የቀረበው ጽሑፍ በ1970 በኤርትራ ምድር ስለተቀበረው አንድ አደገኛ ፈንጂ
ይተርካል፡፡ ታዲያ ትረካው የኔ አይደለም፡፡ ሚስጢሩን ሁሉ የሚያጫውቱን በፈንጂ ቀበራው
ውስጥ ከፍተኛ የሚና የነበራቸው ግለሰብ ናቸው፡፡ በዚያ አስደማሚ ቴአትር የተሳተፉት በርካታ
ተዋንያን ናቸው፡፡ መሪ ተዋናዮቹ ግን የአሜሪካው ሲ.አይ.ኤ. እና የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ
ነበሩ፡፡
*****
ከአቶ ተስፋ ሚካኤል ጽሑፍ እዚህ የለጠፍኩት በጣም መሰረታዊ ያልኩትን ብቻ ነው፡፡ ሌላው
ፍሬ ነገር እኔ ካወጋኋችሁ ጋር ስለሚመሳሰል መደጋገም ይሆንብኛል ብዬ አስቀርቼዋለሁ፡፡ የአቶ
ተስፋሚካኤልን ኦሪጂናል ጽሑፍ ዳውንሎድ ለማድረግ ካሻችሁ ይህንን ሊንክ ተከተሉ፡፡
http://www.ehrea.org/TesfaMikegiorgioAmarina.pdf
በኤርትራ ክፍለ ሀገር ከዚህ ቀደም የነበረውንና አሁንም በመታየት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ
መሠረት በማድረግ፣ ብዙ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ አገር ደራሲያን፣ የፖለቲካ ተመራማሪዎችና
እንዲሁም ሌሎች በማያዳግም ሆኔታ በፖለቲካ፣ በኤኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች በሰፊው
ተንትነውታል፡፡ በመሠረቱ የሁሉም ጸረ-አንድነት ቡድኖች አጀማመር፣ ከገዥ መደቦች ዓላማና
ፍላጎት ጋር የተቆራኘ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ጸረ-አንድነት ቡድኖች ምንም እንኳ
በተለያዩ ስያሜዎች ቢጠሩም፣ በዓላማ ግን አንድ ናቸው፡፡
ራሱን ጀብሃ ብሎ የሚጠራው ተገንጣይ ቡድን በ1954 ዓ.ም. እነ እድሪስ መሐመድ አደምን
በመሳሰሉ መሳፍንት ከተመሰረተ አንስቶ፣ መሥራቶቹ ለእስልምና ሃይማኖት የምንታገል ዓረቦች
ነን በማለት ፕሮፓጋንዳቸውን ሲያሰራጩ ቆይተዋል፡፡ ይህን መፈክር አንግበውም፣ በጀብሃ
ውስጥ ነበሩትን የደጋውን ሕዝብ ቆሐይን፣ ጽንዓደገል፣ ጋሽና ሠቲት ሀዲዳም በተባሉ ቦታዎች
ከህግ ውጭ በሆነ መንገድ ጨፍጭፈዋል፡፡ ንብረቱን ዘርፈዋል፡፡ ይህም በወንበዴው ድርጅት
ውስጥ ትልቅ ቅራኔን ፈጠረ፡፡ ይህን በደገኞቹና በቆለኞቹ መካከል የተፈጠረውን ችግር
ለማስወገድ፣ ባጋጣሚውም የጀብሃን አጠቃላይ መዋቅርና ፖሊሲ ለመተለም፣ በ1960 ዓ.ም.
አደብሃ (ሳህል አውራጃ) ላይ ስብሰባ ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በስብሰባው ላይ የተላለፉት
አስታራቂ ውሳኔዎች፣ በተግባር ሳይተረጎሙ በመቅረታቸው፣ ኢሳያስ አፈወርቂና ተከታዮቹ
መገንጠል ጀመሩ፡፡ ነገር ግን እነሱ በሙሉ ክርስትያን በመሆናቸው፣ የጀብሃ ደጋፊ የሆኑት
የአረብ አገሮች እርዳታ ተነፈጋቸው፡፡ ይህም ሁኔታ፣ ከመሪዎቹ የንኡስ ከበርቴ ባህሪ ጋር
ተዳምሮ ወደ ኢምፕሪያሊስት ጎራ ጭልጥ አድርጎ ወሰዳቸው፡፡
በዚሁ ወቅት ይኸው ተገንጣይ ቡድን ተመሳሳይ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ቆንስልም [በአስመራ
የአሜሪካ ቆንስላ ጽ/ቤት መሆኑ ነው] ጽፎ ነበር፡፡ የደብዳቤውም ዋና ይዘት ባጭሩ፣
“ኮሚኒስቶች እስላሞችን ስለሚረዱ እናንተ ምዕራባዊያን ደግሞ እኛን ልትረዱ ይገባል” የሚል
ነበር፡፡ ይህ ደብዳቤ የተጻፈው እንደ አውሮጳ አቆጣጠር በ5/4/1970 ሲሆን፣ ቆንስላው
ደብዳቤውን የኤርትራ ከ/ሀገር ምክትል እንደራሴ ለነበሩት ለደጀ/ተስፋዮሐንስ በርሄ ሚያዝያ
1/62 ዓ/ም. አስረክበዋል፡፡ ይህም በመዝገብ ቁ/ሀ/1/1042 ደብዳቤ ቁጥር 1091/18/31 ሰኔ 4 ቀን
1962 ዓ/ም. ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም መንግሥቱ ባይሩ ዑቅቢት በተባለው ግለሰብ
አማካይነት፣ ከሌላ ካልታወቀ የውጭ አገር ሃይል ተመሳሳይ ዕርዳታ ለነ አብርሃ ተወልደና ለነ
ኢሳያስ አፈወርቂ የሚገኝበት መንገድ ተቀይሶ እንደነበረና ከተባሉትም የውጭ ሀገር ሰዎች ጋር
አገናኝቷቸው እንደ ነበረ ሃብተሥላሴ ገብረመድህን ተማርኮ በነበረበት ጊዜ በሰጠው ቃል
አረጋግጡዋል፡፡ ይኸም በመዝገብ ቁ. ሀ/1/1042 ደብዳቤ ቁ. 091/18/31 አሥመራ ሰኔ 4/62 ዓ.ም
ተጠቅሶአል፡፡
ኢሳያስም የእርዳታው ጉዳይ በዓላው ቡድን በኩል ተቀባይነት እንዳለው ገልጾ ጨለማው
መስከረም (Black September) የተባለው ቡድን ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት መከላከል ግን
ከቡድኑ (ተገንጣይ) አቅም በላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡ አሜሪካዊያኑም ንግግራቸውን በመቀጠል
“በታሪክ፣ ኤርትራ በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በደማዊ መተሳሰር ከኢትዮጵያ ሳትነጠል
ቆይታለች፡፡ በኤርትራ ውስጥ የውስጥና የውጭ ቅራኔ ሳቢያ በጉዳዩ ጣልቃ ገብተን ሁኔታውን
ለማረጋጋት በኤርትራ የፌዴሬሽን አቋም ወሰድን፡፡ አሁን ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ስርዓት
በመዳከም ላይ ስለሚገኝና፣ የሚተካውም የተደራጀ ፓርቲ ባለመኖሩ፣ እንደሌሎቹ የአፍሪካ
ሀገሮች ሁሉ ወታደራዊ አስተዳደር ይመጣል ብለን እንፈራለን፤ እምነትም የለንም” በማለት፤
በጊዜው የኤርትራ ክ/ሀገር እንደራሴ የነበረው ራስ አሥራተ ካሣ “ለሰልፊ ነፃነት” ሶስት አማራጭ
ሰጥቷቸው ነበር፦ እነሱም፤
1ኛ/ ሁሉም በምህረት ገብተው በየፊናቸው ትምህርትም ሆነ ሥራ እንዲቀጥሉ፤
2ኛ/ ከጀብሃ ጋር መለያየታቸውን በይፋ ለማሳወቅ ጀብሃን በጦር ሃይል ወግተው መጣላታቸውን
በግልጽ እንዲያረጋግጡ፤ ይህን ካደረጉ የመሣሪያ እርዳታም ሊሰጣቸው እንደሚችል፤
3ኛ/ ሁሉም በምህረት ገብተው ወታደራዊ ትምህርት በመቀበል በጀብሃ ላይ ያላቸውን ቂም
በቀል ከጦሩ ጋር በመተባበር እንዲወጡ፤ የሚሉ ነበሩ፡፡
አሜሪካኖቹም እነዚህን አማራጮች መነሻ በማድረግ ለኢሳያስ ምክራቸውን ለገሱት፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ጀብሃንና የኢትዮጵያን መንግሥት ጦር ባንድነት ለመቋቋም አቅም
እንደሌለው ገለጡለት፡፡ ስለሆነም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የመጀመሪያውን ድርድር፣
በከፊልም ቢሆን፣ እንዲቀጥልበት መከሩት፡፡ ለዚህ የሚሻለው ዘዴ ከቡድኑ መሪዎች መካከል
ጥቂቶቹ በምህረት ገብተው የቀሩት በኢሳያስ መሪነት በበረሃ ጸረ ጀብሃ ትግሉን እንዲቀጥሉ
ማድረግ፤ መሆኑን በዝርዝር አስረዱት፡፡ ይህን ማድረግ ከቻለ አሜሪካኖቹ ከአሥራተ ካሣ ጋር
በመስማማት የኤርትራ ክ/ሀገር ተወላጆች ብቻ የሚገኙበት ጠንካራ የኮማንዶ ሃይል አሰልጥነው
እንደሚልኩለትና ጀብሃን በተጨማሪ ሃይል እንደሚመልሱለት ቃል ገቡለት፡፡
አሜሪካዊያኑም በበኩላቸው “የኤርትራ ጥያቄ የውጭ ጥያቄ እንጂ የውስጥ ጥያቄ አለመሆኑን
የሚያረጋግጡ አንዳንድ ነጥቦች ስለሚኖሩ የጠቀስንላችሁን ሦስት ዓላማዎች ለማሟላት
ከተስማማችሁ ሙሉውን ነፃነታችሁን የምንደግፍ መሆናችንን እንገልጻለን” በማለት “በናንተውና
በምንልከው የኮማንዶ ኃይል ብርታት የጀብሃ ድክመት ከታየ በኋላ በኢትዮጵያ የሚቋቋመው
አዲሱ መንግሥት ኤርትራን በፌደራላዊ ስርዓት በሚያውቅበት ጊዜ እናንተ አትቀበሉ፡፡ በዚሁ
ጊዜ እነኛ አስቀድመው ምህረት ጠይቀው የገቡት ጓደኞቻችሁ እኛ በምናቀርብላቸው የመሣሪያና
የወታደራዊ ስልት እውቀት ደልበው ስለሚጠብቁ በብዛት ወደ እናንተው ይጎርፋሉ፡፡ ከደጋው
ክፍል ወደ ቆላው በመውረድ ደግሞ የባህር ጠረፎችን በቁጥጥራችሁ ሥር ስለምታደርጉ
በቪየትናሙ ጦርነት ከቪየት ኮንግ የማረክነውን የሩሲያ መሣሪያ በሙሉ በመርከብ
እናቀርብላችኋለን፡፡” “አሜሪካ ሠራሽ መሣሪያዎችና ቁሳቁሶች ግን በሶስተኛው ዓለም
የተያያዝነውን ፕሮፓጋንዳ ሊያቀዘቅዝብን ስለሚችል አናቀርብላችሁም፡፡ ጉዳዩ እንዲፋጠንም
በኢትዮጵያ የሚመሠረተው አዲስ መንግሥት የምታውጁትን መንግሥት በይፋ
እስከሚያውቀውና እስከሚቀበለው ድረስ የምንሰጠውን ማተሪያላዊና ሌላም እርዳታ በመጠኑ
በማቋረጥ ተጽእኖ እናደርግበታለን” አሉ፡፡
ኢሳያስም ይህን ፕላን በቲዮሪ ደረጃ ከሰማ በኋላ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ምን ዋስትና አለው?
በማለት ጠየቀ፡፡ አሜሪካኖቹም “ፖለቲካ የቁማር ጨዋታ ስለሆነ ቁማር ተጫወት” እናንተ
የምትፈልጉት ነጻነት ነው፡፡ እኛ ደግሞ የምንሻው የቀይ ባህር ይዞታችን እንዲጠናከር ስለሆነ፣
ይኸው ዋስትናችን ነው” ብለው መለሱለት፡፡
ክፍል ዘጠኝ
---
እስከ አሁን ድረስ የሁለቱ የኤርትራ ግንባሮች ውስጣዊ እይታ ምን ይመስል እንደነበር
በጥቂቱ ዳስሰናል፡፡ አሁን ደግሞ በደርግ ዘመን የነበረውን የግንባሮቹን ወታደራዊ እንቅስቃሴ
እንቃኛለን፡፡
*****
በ1976 በብዙ ጸሓፊዎችና ምሁራን የተተቸውና በአሳዛኝ ፍጻሜ የተደመደመው የራዛ ዘመቻ
ተካሄደ፡፡ ይህ ዘመቻ ለደርግ በማን እንደተወጠነ አይታወቅም፡፡ አንዳንዶች (ለምሳሌ ባቢሌ
ቶላ) “የመኢሶን ውጥን ነው” እያሉ ቢጽፉም መኢሶን ከጥንስሱ ጀምሮ የዘመቻው ተቃዋሚ
እንደነበር የደርግ ሰዎች ራሳቸው መስክረዋል፡፡ በርካታ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችም “ዘመቻው
ይገታ!” በማለት ጮኸዋል፡፡
ሀ/. 501ኛ ግብረ ሀይል፡- ከሁመራ ተነስቶ በኡምሐጀር በማድረግ ተሰነይ ይገባል፡፡
ለ/. 502ኛ ግብረ ሀይል፡- ከሽሬ ተነስቶ፣ በሸምበቆ አድርጎ ባሬንቱን ከጀብሃ ያስለቅቃል፡፡
ከዚያም ከ501ኘ ግብረ-ኃይል ጋር ይጋጠምና ወደ አቆርዳት ይገባል፡፡
ሐ/. 503ኛ ግብረ ሀይል-ሀ፡- ከመረብ ድልድይ ተነስቶ አዲኳላን በማስለቀቅ አረዛ ከተማ
ይገባል፡፡
መ/. 503ኛ ግብረ-ኃይል-ለ፡- ከገርሁ ሰናይ ተነስቶ በጾረና በኩል በማድረግ ከዘላአምበሳ-
አስመራ የሚያደርሰውን ጎዳና ያጸዳል፡፡
ሠ/. 504ኛ ግብረ ኃይል፡- ከአስመራ ተነስቶ ኃይሉን በሶስት አቅጣጫ በማነቃነቅ በዙሪያው
ያለውን የጠላት ኃይል ወደ ውጪ በመግፋት አረዛ ላይ ከ503ኛ/ሀ፣ ደቀምሐረ ላይ ከ503/ለ፣
ከረን ላይ ከ502ኛ ግብረ-ኃይሎች ጋር መገናኘት ነበር፡፡
ረ/. 505ኛ ግብረ-ሀይል ምጽዋን ሙሉ በሙሉ ከጠላት ከበባ ካላቀቀ በኋላ ኃይሉን ለሁለት
ከፍሎ አንዱ ወገን ዶጋሊን ተቆጣጥሮ ከምጽዋ አስመራ መንገድን ነጻ ማድረግ ሌላው ወገን
ደግሞ በመርከብ ወደ መርሳ ጉልቡብ ተጉዞ አልጌናን መያዝና ከናቅፋ ጀርባ መግባት ነው፡፡
በምዕራብ ኤርትራ የነበረው ሁኔታ ደግሞ ከዚህ ይለያል፡፡ በክፍል ሰባት እንደገለጽኩት ጀብሃ
በርሱ ላይ የዘመተውን ብዙ ሺህ ሰራዊት ከመሸሽ ይልቅ በመጋፈጡ ሀይሉን አስጨርሷል፡፡
ለክፉ ቀን ይሆነኛል ብሎ የያዘው የባርካ ቆላ ሜዳማ በመሆኑ ከሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት
ጥቃት ሊያድነው አልቻለም፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ ልክ እንደ ሻዕቢያ ወደ ሳህል መሸሽ
ነበር፡፡
*****
ህዳር 20/2013
“ጀብሃ” እና “ሻዕቢያ”
ክፍል አስር
-------
ያ ዘመቻ በኦፊሴል “የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ” ተብሎ ነበር የተሰየመው፡፡
የዘመቻው ዓላማዎችም ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ሻዕቢያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ
ነው፡፡ ሁለተኛው በጦርነቱ የፈራረሱ መሰረተ-ልማቶችን መገንባት ነው፡፡ ለዘመቻው “ቀይ
ኮከብ” የሚል ስም የተሰጠው ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ-ማሪያም የአሜሪካ ባህር ሀይል
“ብሩህ ኮከብ” (Bright Star) በሚል ስም በቀይ ባህር ላይ ላደረገው ወታደራዊ ልምምድ ምላሽ
መሆን አለበት በማለት ባደረጉት ውሳኔ መሰረት እንደሆነ በወቅቱ የኤርትራ ክፍለ-ሀገር
ኢሠፓአኮ ተጠሪ የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “ቀይ እምባ” (Red Tears) በተሰኘው
መጽሐፋቸው ገልጸዋል፡፡
የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ ይፋ የተደረገው በሀገር አቀፍ ደረጃ በታወጀ ልዩ
አዋጅ ነው፡፡ ዘመቻውን በበላይነት የሚያስፈጽም ከፍተኛ ስልጣን የተሰጠው ሀገር አቀፍ ምክር
ቤት ተቋቁሞለታል፡፡ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ሲሆኑ ዋና
ጸሓፊው ኤርትራዊው አቶ አማኑኤል አምደሚካኤል ነበሩ፡፡ የሀገሪቱ ምርጥ ምሁራን
የተሳተፉበትና ድርጅታዊ ሀይሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሟላለት የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤትም
አስመራ ላይ ተሰይሞም ነበር፡፡ ለዘመቻው ማስፈጸሚያ ከሁለት ቢሊዮን ብር የሚበልጥ
(በዛሬው የምንዛሬ ተመን ወደ ሀያ ቢሊዮን ብር ያህል የሚሆን) በጀት ተመድቦለታል፡፡
ዘመቻውን ለማስፈጸም በሚልም ከሊቀመንበር መንግሥቱ ጀምሮ ሀገሪቷ ያሏት ከፍተኛ
ወታደራዊና የሲቪል ባለስልጣናት አስመራ ላይ ከትመዋል፡፡
የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ በይፋ የተከፈተው ጥር 17/1974 ነበር፡፡ የዘመቻውን
መከፈት በሚያበስረው ጉባኤ ላይ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገሮች የተወከሉ የሀገር
ሽማግሌዎች፣ ሙያተኞች፣ መለዮ ለባሾች፣ የገበሬ ተወካዮች ወዘተ.. ተሳትፈዋል፡፡ ሊቀመንበር
መንግሥቱ ጉባኤውን የከፈቱበት ንግግር በሬዲዮ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ
ተላልፏል፡፡ የአስራ አራቱ ክፍለ ሀገራት ተወካዮችም በጉባኤው ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
ጉባኤው ጥር 23/1974 ሲጠናቀቅ ሰባት ነጥቦች ያሉት “የአስመራ ማኒፌስቶ” በአቋም መግለጫ
መልክ ይፋ ተደርጓል፡፡
የቀይ ኮከብ ዘመቻ ጉባኤ በተከፈተበት ማግስት በቀይ ባህር ዳርቻ በምትገኘው “ጉርጉሱም”
የተባለች ሰርጥ ላይ የተዘጋጀው የምጽዋ ኤክስፖ በሊቀመንበር መንግሥቱ ተመርቋል፡፡ ዶጋሊ
ላይ ሊገነባ ለታቀደው የራስ አሉላ መታሰቢያ ሀውልት የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡትም
ሊቀመንበር መንግሥቱ ነበሩ፡፡ በምጽዋ ከተማ በሚገኘው “አጼ ካሌብ አዳራሽ” ታሪካዊው
የምጽዋ ሲምፖዚየም ተካሂዷል፡፡ በአስመራና በምጽዋ ከተሞች የሚገኙ በርካታ ፋብሪካዎችም
ተጠግነው የማምረት ተግባራቸውን እንዲጀምሩ ተደርገዋል፡፡ ከምጽዋ-አቆርዳት የተዘረጋው
የባቡር መስመርም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ይህ ሁሉ ከተገባደደ በኋላ ነው
ወታደራዊው ዘመቻ የተካሄደው፡፡
*****
የውቃው እና የናደው እዞች ከፍተኛ ጀግንነት አሳይተው ከናቅፋ ስምንት ኪሎሜትር ርቀት
ላይ ደረሱ፡፡ ይሁንና ባልታወቀ ምክንያት በተሰጠ ትዕዛዝ እንቅስቃሴአቸው ተገታ፡፡ ከዚያ በኋላ
እንንቀሳቀስ ቢሉ የማይቻል ነገር ሆነ፡፡ ሻዕቢያ ተዋጊዎቹን ከያሉበት አሰባስቦ ወደ ኋላ
ይገፋቸው ጀመር፡፡ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ባደረገው መልሶ ማጥቃት በአፋቤት (ከርከበት)
ግንባር በዘመተው ናደው እዝ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ፡፡ ሺዎች ሙትና ቁስለኛ ሆኑ፡፡ በትልቅ
ሞራልና የድል ጉጉት የተጀመረው የቀይ ኮከብ ዘመቻም በከፍተኛ ሽንፈት ተፈጸመ፡፡
*****
የውቃውና የናደው እዞች ከናቅፋ አጠገብ ደርሰው ውጊያ እንዲያቆሙ የተደረገበት ምክንያት
እስከዛሬ ድረስ በግልጽ አይታወቅም፡፡ ሻለቃ ጌታቸው የሮም በጻፉት መፅሐፍ “አንድ ከፍተኛ
የኢሠፓ ባለስልጣን ‘ሻዕቢያ እያዘናጋችሁ ሊፈጃችሁ ስለተዘጋጀ መቆም አለባችሁ’ የሚል
ትዕዛዝ ስለሰጠ ነው” ይላሉ፡፡ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው “የጦር ሀይሎቹ መዋጋት
ያቆሙት ናቅፋን የመያዙ ተግባር ሊቀመንበር መንግሥቱ ረጅም ዕድሜአቸውን ባሳለፉበት
አንበሳው ሶስተኛ ክፍለ ጦር እንዲፈጸም ስለተፈለገ ነው” በማለት ጽፈዋል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ
ግን ይህንን አባባል በከፍተኛ ቁጣ አስተባብለዋል፡፡ “ከሁሉም ጦሮች ቀድሞ ናቅፋ የደረሰውና
ያለቀው ሶስተኛ ክፍለ ጦር ነው” በማለትም ተከራክረዋል፡፡
*****
አንድ ዓመት ሙሉ ዝግጅት የተደረገበት የቀይ ኮከብ ዘመቻ በዚሁ መልክ ነበር
የተደመደመው፡፡ ሁለት ቢሊዮን ብር በሁለት ወር ውስጥ እንደ ጉም ተንኖ ቀርቷል፡፡ ታዲያ
ሊቀመንበር መንግሥቱ የባሰ እልህ ይዞአቸው “ቀይ ኮከብ ሁለት” እና “ቀይ ኮከብ ሶስት”
የተሰኙ ዘመቻዎችን ሞክረው ነበር፡፡ ውጤቱ ግን ሊሰምርላቸው አልቻለም፡፡ በርካታ ታዛቢዎች
እንደሚሉት ዘመቻው እንዳበቃ የናደውና የውቃው እዞች የናቅፋን ዙሪያ አጥረው እንዲቆዩ
ቢደረግና ኮ/ል መንግሥቱም ለኤርትራ ችግር ሰላማዊ መፍትሔ ወደ ማፈላለጉ ቢሄዱ ኖሮ ጥሩ
ውጤት በተገኘ ነበር፡፡ ምክንያቱም ዘመቻው ሻዕቢያንም ክፉኛ ያደከመ በመሆኑ አማጺው
ሀይል ሰላማዊውን አማራጭ ይቀበል ነበር ተብሎ ይታሰብ ስለነበረ ነው፡፡
የቀይ ኮከብ ዘመቻ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ነው ያለፈው፡፡ አብዮታዊ
ሰራዊት በዘመቻው ማብቂያ ላይ ባጋጠመው ውድቀት ክፉኛ ተናግቷል፡፡ የወታደሮቹ ስነ-
ልቦናም በጣም ተቃውሷል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማንኛውም የጦር ሀይል ወደ ናቅፋ መጠጋት
ይፈራ ነበር፡፡ ዘማቾች “ናቅፋ” ከተባለ “ሞት” ብቻ ነበር የሚታያቸው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የቀይ
ኮከብ ዘመቻ ለሻዕቢያ ሀይሎች ከፍተኛ የሞራል ስንቅ ሆኖአቸዋል፡፡ “17,000 ሆነን ከ100,000
የሚልቅ፣ እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀና በአውሮፕላንና በቢ.ኤም የተጠናከረ ግዙፍ ሰራዊት
ድል አድርገናል” በማለት እንዲኩራሩ አድርጎአቸዋል፡፡ ናቅፋንም “ምልክት ጽናትና” (የጽናታችን
ምልክት) በማለት እንዲጠሯት መንስኤ የሆናቸው ይኸው ነው፡፡
------
ህዳር 22/2013
“ጀብሃ” እና “ሻዕቢያ”
===ድህረ-ቀይ ኮከብ===
የቀይ ኮከብ ዘመቻ በሽንፈት ከተቋጨ በኋላ የዘመቻውን መጀመር በከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ
ያበሰሩት የመንግሥት ሚዲያና ፕሬሶች በዝምታ ተዋጡ፡፡ በኤርትራ ምድር ስለሚካሄድ
ወታደራዊም ሆነ ሰብዓዊ እንቅስቃሴ ደፍሮ የሚናገር ጠፋ፡፡ የቀይ ኮከብ ዘመቻም ይፋዊ
ባልሆነ መንገድ በሰኔ 20/1984 ተሰረዘ (የዘመን አቆጣጠሩ እንደ አውሮጳ ቀመር መሆኑን
አትርሱ)፡፡
*****
በመጋቢት ወር 1975 አንዳንዶች “ጸጥተኛው ዘመቻ” በማለት የሚጠሩት ወታደራዊ ኦፕሬሽን
ተጀምሮ ነበር፡፡ ዘመቻው “ጸጥተኛ” ተብሎ የተጠራው በህዝብ ሚዲያ ምንም ዓይነት ቅስቀሳ
ስላልተደረገለት ነው፡፡ በዚህ ዘመቻ የተካፈለው የወታደር ብዛት በቀይ ኮከብ ጊዜ ከነበረው
በጣም ያንሳል፡፡ የዘመቻው ትኩረትም ከከረን ከተማ በስተሰሜን ያለችው “ሐልሐል” የተሰኘች
ስትራቲጂካዊ መንደር ነበረች (“ሐልሐል” በ1969 የጀብሃ እውቅ ኮማንደር የነበረው ዑመር
እዛዝ የሞተባት መንደር ናት)፡፡ በዘመቻው የአብዮታዊ ሰራዊት ሀይሎች የሻዕቢያ ተዋጊዎችን
አሸንፈው ለማባረር ችለዋል፡፡ ሆኖም በሻዕቢያ ላይ የደረሰው ሽንፈት የአማጺውን ቅስም
ለመስበር የሚችል አልነበረም፡፡
====ዘመቻ ባህረ-ነጋሽ====
አብዮታዊው ሰራዊት ሻዕቢያን ከምዕራብ ኤርትራ ለማባረር በቂ ዝግጅት ሲያደርግ ከቆየ በኋላ
በሐምሌ ወር 1984 ለመልሶ ማጥቃት ተዘጋጀ፡፡ በአንደኛው ዙር የብሄራዊ ውትድርና
አገልግሎት የተመለመሉ 60 ሺህ ዘማቾችን ጨምሮ ከመቶ ሀምሳ ሺህ የማያንስ የጦር ሰራዊት
ለውጊያው ተሰለፈ፡፡ የዘመቻው ፕላን በሶቭየት ህብረት (USSR) ወታደራዊ ኤክስፐርቶች
ተዘጋጀ፡፡ ከሶስት መቶ የማያንሱ ታንኮችና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ዝግጁ ሆኑ፡፡ ዘመቻውም
“ባህረ ነጋሽ” ተብሎ ተሰየመ፡፡
“ዘመቻ ባህረ ነጋሽ” ሻዕቢያን ከምዕራብ ኤርትራ አባርሮ ወደ ሳሕል በረሃ የመመለስ እቅድ
ነበረው፡፡ የዘመቻው እቅድ በመገናኛ ብዙሃን በይፋ ባይታወጅም እንኳ ለዘመቻ በተሰለፈው
የሰው ሀይልና በተመደበለት የጦር መሳሪያ ዓይነትና ብዛት ከቀይ ኮከብ ሁለገብ ዘመቻ ጋር
ይስተካከላል፡፡ ሀገሪቷ የነበሯት ምርጥ የጦር መኮንኖችም በአዛዥነት ተሰልፈዋል፡፡ የዘመቻው
የበላይ አዛዥ እውቁ የጦር ሰው ሜጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ ሲሆኑ በርሳቸው ስር ሜ/ጄ/
ደምሴ ቡልቶ፣ ሜ/ጄ/ አበራ አበበና ሜ/ጄ/ ረጋሳ ጅማ ተሰልፈው ነበር፡፡ የአየር ሀይሉ ሜጀር
ጄኔራል ፋንታ በላይም ከምርጥ አብራሪዎች ጋር ተሰልፈዋል፡፡
*****
ከዘመቻ ባህረ ነጋሽ ፍጻሜ በኋላ በነበሩት ሁለት ዓመታት በኤርትራ ምድር የሚደረገው
ውጊያ ጋብ ብሏል፡፡ በነዚያ ዓመታት ሁለቱም ተዋጊ ወገኖች አጣዳፊ ለሚሏቸው ጉዳዮች
ቅድሚያ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መሰረት የደርግ መንግሥት የመንደር ምስረታ እና ህገ-መንግሥት
ማርቀቅን ለመሳሰሉ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ በነርሱ ላይ አተኩሯል፡፡ ሻዕቢያ ደግሞ ሁለተኛውን
ድርጅታዊ ጉባኤ በማዘጋጀቱ ላይ ነበር ያተኮረው፡፡
*****
ህዳር 25/2006
“ጀብሃ” እና “ሻዕቢያ”
--------
በሳህል በረሃ ደቡባዊ ጠርዝ ላይ አፋቤት የምትባል አነስተኛ ከተማ ትገኛለች፡፡ በዚህች
ከተማ እጅግ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን የታጠቀውና በሎጂስቲክስ አቅራቦት የተደራጀው
የናደው እዝ ጠቅላይ መምሪያ ይገኝ ነበር፡፡ የናደው እዝ ከተማዋን ለመቀመጫነት የያዘው
በበርካታ መንገዶች መጋጠሚያ ላይ ስለነበረች ነው ተብሎ ይወሳል፡፡ በተጨማሪም ከተራሮች
ወርዶ ወደ መሬት ውስጥ እየገባ የተጠራቀመ ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃ ስለነበራት (በርካታ
የውሃ ጉድጓዶች እየተቆፈሩ የሰራዊቱን የውሃ ፍላጎት ለማሟላት በሚያስችል ሁኔታ ስለነበረች)
ለሰራዊቱ መቀመጫነት እንደተመረጠች ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም በትዝታቸው ውስጥ
ገልጸውታል፡፡
በናደው እዝ ስር ይገኝ የነበረው ሰራዊት ከአምስት ክፍለ ጦር በላይ ይሆናል (ወደ ስልሳ ሺ
የሚሆን የሰው ሀይል ነበረው)፡፡ ምርጥ ምርጥ የጦር መሳሪያዎችን ታጥቋል፡፡ የነዳጅና
የመለዋወጫዎች ክምችቱ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በምግብና በሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችም ይህ
ቀረሽ የማይባል እንክብካቤ ይደረግለታል፡፡ የእዙ አዛዦች ግን ተለዋውጠዋል፡፡ በቀይ ኮከብ
ዘመን አዛዥ ሆነው የተሾሙት ጄኔራል ውበቱ ጸጋዬ ነበሩ፡፡ በ1979 ደግሞ ጄኔራል ታሪኩ አይኔ
ተሹመውለታል፡፡
*****
በክፍል አስራ አንድ ጽሑፌ እንደገለጽኩት ለሁለት ዓመታት ያህል በኤርትራ ምድር ጠንከር
ያለ ውጊያ አልተደረገም፡፡ በታሕሳስ 6/1987 (እንደኛ አቆጣጠር ህዳር 27/1980) ግን ህዝባዊ
ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) ሳይጠበቅ ከባድ የማጥቃት እርምጃ ሰነዘረ፡፡ የ15ኛው ክፍለ
ጦር እና የ22ኛው ተራራ ክፍለ ጦር ተዋከቡ፡፡ ለሶስት ቀናት በተደረገ ውጊያ በርካቶች ሙትና
ቁስለኛ ሆኑ፡፡ የየክፍለ ጦሮቹ የመገናኛና የመረጃ መኮንኖችም ተማረኩ፡፡ ሻዕቢያ ይህንን
ድንገተኛ ጥቃት ያደረሰው የናደው እዝ አዛዥ ጄኔራል ታሪኩ አይኔ ዝውውር እንዲፈቀድላቸው
ለመጠየቅ አስመራ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡
ነበሩ፡፡ በአስረጅነትም
*****
የጄኔራል ታሪኩን ጉዳይ ለማጣራት በሚል ምክንያት በወቅቱ የኤርትራ ክፍለ ሀገር ኢሰፓ
አንደኛ ጸሓፊ በሻለቃ ካሳዬ አራጋው የሚመራ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡ ኮሚቴው በአፋቤትና በልዩ
ልዩ ቦታዎች የተበታተኑ የእዙ ክፍሎችን ካነጋገረ በኋላ የጄኔራል ታሪኩ ጥፋቶችን
እንደሚከተለው አስቀመጠ፡፡
1. ተደጋጋሚ ስህተቶችን እየሰሩ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ተነግሯቸው እምቢተኛ ሆነው
መገኘታቸው
2. ለስነ-ስርዓት የማይገዙና አለቆቻቸውን የሚንቁ መሆናቸው
3. በእዛቸው ስር የሚገኙት 15ኛና 22ኛ ክፍለ ጦሮች በጠላት አስገዳጅነት የመከላከያ
ስፍራቸውን ሲለቁ በቦታው ተገኝተው ሁኔታው የሚለወጥበትን መንገድ
ባለመሻታቸው
4. ሰራዊቱ ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ላይ እያለ እሳቸው በራስ ወዳድነት ስሜት
ዝውውር መጠየቃቸው
የጄኔራል ታሪኩን ጥፋት የመረመረው ኮሚቴ “ጄኔራል ታሪኩ የጡረታ መብቱ ተጠብቆለት
ከሰራዊቱ በጡረቱ እንዲገለል” የሚል የውሳኔ ሃሳብ ነበር ያቀረበው፡፡ ሆኖም ውሳኔው
በፕሬዚዳንቱ ተገለበጠ፡፡ በሰራዊቱ ደንብ መሰረት የጦር ፍርድ ቤት ሳይቋቋም፣ ማስረጃ
ሳይመረመር፣ ምስክር ሳይቆጠርና የግራ ቀኝ ክርክር ሳይካሄድ በሞት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው፡፡
ጥር 26/1980 በአስመራ አቅራቢያ በምትገኘው አዲጓእዳድ በተባለች መንደር ጄኔራል ታሪኩ
አይኔና ጄኔራል ከበደ ጋሼ ከወታደሮች ፊት ቀረቡ፡፡ የሁለቱም ጥፋት ከተነበበ በኋላ ጄኔራል
ታሪኩ ተረሸኑ፡፡ ጄኔራል ከበደ ጋሼ ማዕረጋቸው ተገፍፎ ከሰራዊቱ ተባረሩ፡፡
*****
ጄኔራል ታሪኩ ለምን ተረሸኑ? ከላይ የተዘረዘረው ጥፋት ለሞት የሚያበቃ ነበር? ይህ ጥያቄ
እስከ አሁን ድረስ አከራካሪ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ጄኔራል ታሪኩ የተረሸኑት በነዚያ
ጥፋቶች ነው የሚል አቋም ነው ያላቸው፡፡ በርካቶች ግን በመንግሥቱ አንደበት የተነገረውን
ያስተባብላሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ጄኔራል ታሪኩ የናደው አዛዥ በነበሩበት ጊዜ በእዙ ላይ የደረሰው
ጥቃት ከዚያ በፊት ከደረሱትና ከዚያ በኋላ ከታዩትም በእጅጉ ያነሰ እንደሆነ በማመዛዘን
ጄኔራሉ በህዳር ወር ማብቂያ ላይ በተከሰተው ጥቃት ሳቢያ ሞቱ የሚለውን አባባል
እንደማይቀበሉ ይናገራሉ፡፡ በነዚህ ወገኖች አስተያየት ጄኔራል ታሪኩ የተገደሉት ለኤርትራ ችግር
ሰላማዊ መፍትሔ እንዲበጅለት በመጠየቃቸውና በኤርትራ ክፍለ ሀገር ለደረሰው ሽንፈት ሁሉ
ተጠያቂው የፕሬዚዳንቱ የተሳሳተ አመራር እንደሆነ በመናገራቸው ነው፡፡
በርግጥም ጄኔራል ታሪኩን ለአንድ ዙር ጥቃት ብቻ ተጠያቂ አድርጎ መረሸን ሚዛናዊ ፍርድ
አልነበረም፡፡ የሳቸው መገደል ሻዕቢያን የገታበት ሁኔታም አልታየም፡፡ ይልቁንም የሀገሪቱ
ከፍተኛ መኮንኖች ለመፈንቅለ መንግሥት ዱለታ እንዲነሳሱ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ሆኖ
ነው ያለፈው፡፡ ጄኔራል ታሪኩ የተገደሉት ለኤርትራ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት
በመጠየቃቸውና የፕሬዚዳንቱን አመራር በመኮነናቸው እንደሆነ ነው የሚታመነው፡፡ እጅግ
አሳዛኙ ነገር እኝህ እውቅ ጄኔራል ከተገደሉ ከአንድ ወር በኋላ ሻዕቢያ የናደው እዝን ሙሉ
በሙሉ ለመደምሰስ መቻሉ ነው፡፡ ይህ ሻዕቢያ የተቀዳጀው ድል የአብዮታዊ ሰራዊትን ውድቀት
ካፋጠኑ ምክንያቶች አንዱ ሊሆን በቅቷል፡፡ የአፋቤቱ ውድቀት ምን ይመስል ነበር? በቀጣዩ
ክፍል እንዳስሰዋለን፡፡
ህዳር 26/2006
“ጀብሃ” እና “ሻዕቢያ”
(የአፋቤት ሽንፈት)
--------
*****
ይህ የናደው ሽንፈት ብዙ ተብሎለታል፡፡ ብዙም ተጽፎበታል፡፡ በታወቁ የዓለም ዜና
ማሰራጫዎች ግንባር ቀደም ወሬ ሆኖ ተዘግቧል፡፡ በርካታ የአውሮጳና የአሜሪካ ጋዜጠኞች
ጦርነቱ የተካሄደባትን የአፋቤት ከተማ በመጎብኘት ዶክመንታሪ ፊልሞችን ሰርተውበታል፡፡
የታወቁ የጦር ኤክስፐርቶች ሻዕቢያ በአፋቤት ያገኘውን ድል የቪየት-ኮንግ ሽምቅ ተዋጊዎች
በፈረንሳይ ቅኝ ገዥዎች ላይ ከተጎናጸፉት የ“ዲየን ቢየን ፉ” ድል ጋር አወዳድረውታል፡፡
በአጠቃላይ የናደው ሽንፈት ስለሻዕቢያ የሚያውቁትንም ሆነ የማያውቁትን የውጪ ዜጎች
“አደገኛ የጎሪላ ተዋጊ ሀይል ነው” እያሉ በከፍተኛ አድናቆት እንዲመለከቱት የጋበዘ ክስተት ሆኖ
አልፏል፡፡
በሌላ በኩል የናደው ሽንፈት በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የፖሊሲ ለውጥ አስከትሏል፡፡ በናደው
ሽንፈት ማግስት የኢህዲሪ መንግሥት በይፋ ያልታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ ሀገሪቱ
በስራ ላይ አውሏል፡፡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም መጋቢት 31/1988 ለመጀመሪያ ጊዜ
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው በኤርትራ ስለሚካሄደው ጦርነት ተናገሩ፡፡ ሰፊው ህዝብ
ኤርትራን ከመገንጠል እንዲያድናት ጥሪ አቀረቡ፡፡ መንግሥት በሚመድበው በጀት ብቻ
ጦርነቱን ማካሄድ ስላልተቻለ ህዝቡም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት በማለት ማሳሰቢያ
ሰጡ፡፡ የ“አዲስ ዘመን” እና “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች” በፊት ገጾቻቸው ጥግ ላይ “ሁሉም
ነገር ወደ ጦር ግንባር” የሚል መፈክር በቋሚነት ማስነበብ ጀመሩ፡፡ የኢትዮጵያ ሬድዮም
በምሽት ስርጭቱ ከሚያስተላልፈው ዜና ቀጥሎ “አንድነት ሀይል ነው”፣ “ሁሉም ለእናት ሀገሩ
ዘብ ይቁም”፣ “የአባቶቻችንን አደራ አናስደፍርም” እና “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” የሚሉ
አራት መፈክሮችን በመደበኛነት ማሰማት ጀመረ፡፡ ኤርትራ በአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር ስር
ወደቀች፡፡ በኤርትራ መሬት የሚደረገው ቁጥጥር እንዲጠብቅ ትእዛዝ ተላለፈ፡፡ ክፍለ ሀገሩን
ከሱዳንና ከቀይ ባህር ጋር የሚያገናኙ መሬቶች ለሲቪል እንቅስቃሴ ተከለከሉ፡፡
*****
በናደው እዝ ላይ የደረሰው ሽንፈት በአብዮታዊ ሰራዊት ውስጥ ትልቅ ቀውስ መፍጠሩ
እርግጥ ነው፡፡ በዘመኑ የነበሩ የታወቁ ወታደራዊ አዛዦችም “የፍጻሜው መጀመሪያ” በማለት
ገልጸውታል፡፡ በጦርነቱ የተሰለፈው አብዮታዊ ሰራዊት ሃምሳ ሺህ ተዋጊዎችን ይዞ ከአስር ሺህ
ያልበለጠ ሀይል በነበረው የሻዕቢያ ሰራዊት መሸነፉ በጣም አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ በሌላ በኩል
ሻዕቢያ የጦርነቱን ውሎ አለም አቀፍ ዝና ለማግኘትና የአብዮታዊ ሰራዊት ሞራልን ለመስበር
በሰፊው ተጠቅሞበታል፡፡ የሬድዮና የህትመት አውታሮቹ የሻዕቢያን ሀያልነት የሚያሳይ
ፕሮፓጋንዳ እየደጋገሙ ሰርተውበታል፡፡ ለመሆኑ አስራ አምስት ሺህ ያህል የኢትዮጵያ
ወታደሮች ሙት፣ ቁስለኛና ምርኮኛ የሆኑበት የአፋቤት ሽንፈት እንዴት ተከሰተ?
የአፋቤት ውድቀት ከደረሰ በኋላ የሻዕቢያ አስመራ መግባት የጊዜ ጉዳይ እንደሆነ ሁለቱም
ወገኖች ተረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ ተነጣጥለው ሁለት ሀገር እንደሚሆኑ መተንበይ
የተጀመረውም ከዚያ በኋላ ነበር፡፡
ህዳር 27/2006