አምስቱ ስጦታዎች

You might also like

Download as docx, pdf, or txt
Download as docx, pdf, or txt
You are on page 1of 4

አምስቱ ስጦታዎች

በመጋቤ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ

ሥርዓተ አምልኮ ከሚገለጥበት መንገድ አንዱ ስጦታ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከራሱ የሆነ አንዳች የለውም በጎ የሆነው ሁሉ
ከፈጣሪ ዓለማት ከእግዚአብሔር ያገኘው ነው፡፡ በመሆኑም ፈጣሪያችን መስጠትን እንዳስተማረን ሁሉ እኛም
ተገዥነታችንን ከምንገልጥበት አንዱ ከርሱ የተቀበልነውን በፈቃደኝነት በደስታ በመስጠት ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ይህን
ሲያስረዳ ‹‹ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፡ ከእጅህ የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ልናቀርብልህ የቻልን ማነን? ..
በፈቃዴ ይህን አቅርቤአለሁ›› በማለት ከእግዚአብሔር ያገኘውን ሀብት በደስታ በፈቃዱ ለቤተ መቅደስ ሥራ
እንዲውል መስጠቱን በመግለጽ ስለ ስጦታ ጽፏል /1 ዜና 29÷9-16/.

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ነገር ግን ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን›› በማለት እንዳስተማረን ለእግዚአብሔር
የምንሰጠውን የአምልኮ መግለጫ በሥርዓት ልናደርገው እና ከልብ ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ መሠረቱ የስጦታ
ዓይነቶችንና የአቀራረብ ሥርዓቱን ማወቅ ነው፡፡በዚህች አጭር ጽሑፍም በሥርዓተ ቤተክርስቲያን መሠረት
መንፈሳዊ ምግባራት የሆኑት አምስቱ የስጦታ ዓይነቶች ምጽዋት፡ መባዕ፡ ስዕለት፡ በኩራት እና ዐሥራትን
እንመለከታለን፡፡

1.ምጽዋት፡-

ምጽዋት መስጠት ከገንዘብ፡ ከዕውቀት ፡ ከንብረት… ላይ ለእግዚአብሔር ቤት መለገስ ነው፡፡ መድኃኒታችን እየሱስ
ክርስቶስ በአንቀጸ ብጹአን ትምህርቱ ‹‹ብጹዓን መሐርያን ፡ የሚምሩ ብጹአን ›› ናቸው ያለውን ለምጽዋት
ሰጥተውት ሊቃውንት ሲተረጉሙት በሦስት መንገድ ያስቀምጡታል፡፡ እነዚህም፡-

ሀ/ምህረት ሥጋዌ፡- ይህ የሚያስረዳው ለሥጋ የሚሆን ነገርን መለገስን ሲሆን

ለ/ምሕረት መንፈሳዌ፡- በምክር፡ በትምህርት…. ሥነ ልቡናን የሚያንጽ (የሚያበረታታ) ማድረግን ነው፡፡

ሐ/ምሕረት ነፍሳዊ፡- ደግሞ ራስን እስከ መስጠት ‹‹መጥወተ ርእስ›› መድረስን ነው /ማቴ 5÷7 ትርጓሜ ወንጌል/፡፡

ምጽዋት ካለን ነገር ላይ ማካፈልን ያመለክታል፡፡ለፍጹምነትም የሚያበቃ ምግባር መሆኑ የተመሰከረለት ነው፡፡‹‹
ፍጹም እንድትሆን ለድሃ ስጥ›› እንዲል /ማቴ 19-21/፡፡‹‹የሚሰጥ ብጹዕ ነው›› የሚለውም ሃይለ ቃል ይህን
ያስረዳል፡፡/ሐዋ 20÷35/፡፡ በነገረ ምጽአትም ከሕይወት ቃል አንዱ በምጽዋት የሚገኝ መሆኑ እሙን ነው /ማቴ.25-
35/፡፡

ምጽዋትን በልብስ፡ በገንዘብ፡ እንጀራ በመቁረስ የመሳሰሉትን ለደሃ በመስጠት፡ በማካፈል መግለጽ ይቻላል፡፡
በእየሩሳሌም የሚኖሩ ምእመናን ሀብታቸውን ለደሃ ያካፍሉ ነበር /ሐዋ 4÷32 6÷1-6/፡፡እንደዚሁም እውቀትን
ማካፈል፡ ምክር መለገስ ከምጽዋት የሚቆጠር ሲሆን ፡ ለእግዚአብሔር ቤትም በገንዘብ፡ በጉልበትና በስጦታችን
ማገልገል የምጽዋትን ዋጋ ያስገኛል /ኢሳ 58÷7 ፡ ሮሜ 12÷8 ፡ ዘዳ. 15÷11-15 ፡ ምሳ 3÷27/፡፡ በረከተ ሥጋ ወነፍስ
የሚያስገኘውንና በደልን የሚያስወግደውን የልግስና ስጦታ /ምጽዋትን/ ልማዳችን ማድረግ ይገባናል /ዳን. 4÷27/፡፡

2.መባዕ፡-

ለአምላካችን ለልዑል እግዚአብሔር ከሚቀርቡ የስጦታ ዓይነቶች አንዱ መባዕ ነው/ ዘሌ 1÷3፡ ዘኁ.7÷12/፡፡ ነቢዩ
ዳዊት መባ ለእግዚአብሔር ቤት እንደሚገባ ሲገልጽ ‹‹እበውእ ቤተከ ምስለ መባእየ፡ መባዬን በመያዝ ወደቤትህ
እገባለሁ›› ብሏል /መዝ 65÷13/፡፡ መባዕ ለቤተመቅደስ መገልገያ የሚሆንና ንዋያተ ቅድሳትን በመስጠት የሚፈጸም
ሲሆን ለምሳሌ ጧፍ፡ ዕጣን፡ ዘቢብ፡ … የመሳሰሉት በአጥቢያችን እና በተለያዩ ገዳማት ስንሔድ ይዘን መግባት
ይጠበቅብናል፡፡ /ዘዳ. 13÷35 ፡ 34÷20/፡፡

መባዕ ማቅረብ የተገዥነት መገለጫ በመሆኑ በረከት የሚያስገኝ ምግባር ነው፡፡ በቤተክርስቲያንም በጸሎተ መባዕ
በካህኑ በሚደርስው ሥርዐተ ጸሎት መሠረት የመንፈሳዊ ጸጋ ተሳታፊ ያደርጋል /ማቴ. 5÷24 ፡ ማር 7÷10-12/፡፡

3.ስዕለት፡-

ስዕለት ሰው በፈቃዱ አንድ ነገር ለእግዚአብሔር ለማድረግ /ደስታውን ለመግለጥ/ ቃል የሚገባበት ሥርዓት ነው፡፡
በእግዚአብሔር ቸርነት በቅዱሳን አማላጅነት በማመንና በመማጸን ‹‹ ይህ ቢደረግልገኝ ይህን አደርጋለሁ›› በሚል
አገላለጽ ቃል የሚገቡበት የስጦታ ዓይነት ነው፡፡ ስዕለት እምነታችንን የምንገልጽበትም በመሆኑ በሥርዐት እና ከልብ
ሆነው ስእለት ሊሳሉ ይገባል፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን ይህን‹‹ ለእግዚአብሔር በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ፡
የተሳልከውን ፈጽም፡የማትፈጽም ከሆነ አትሳል›› በማለት አስረድቶአል/መክ 5÷4/፡፡ እመሳሙኤል ሐና
እንደተሳለችና ስእለቷን እንደፈጸመች ይህም ምግባር ቀድሞ የነበረና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ የሚያስተምረን
ነው/ 1 ገኛ ሳሙ.1-1/፡፡ በረከት ለመቀበልና ፍላጎታቸው እንዲሟላ የሚሳሉም ነበሩ፡፡/ዘፍ. 28÷20 ፡ ዘሌ 20 7 ፡ ዘኁ.
21÷1-3፡ መሳ. 11÷30/፡፡

ስእለትን በአግባቡ መሳል እና በቃላችን መሠረት መፈጸም የሚገባ ሲሆን ነገር ግን ቃልን አለመጠበቅ ደግሞ ኃጥያት
ስለመሆኑ እንዲህ ተጽፏል ‹‹ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ
ፈጽሞ ይሻዋልና ኃጥያትም ይሆንብሃልና መክፈሉን አትዘገይ፡፡ ባትሳል ግን ኃጥያት የለብህም በአፍህ የተናገርኸውን
ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፈቃድህ ተስለሃልና ከከንፈርህ የወጣውን ታደርግ ዘንድ ጠብቅ›› /ዘዳ. 23÷21-23፡
ምሳ. 20÷25/፡፡

4.በኩራት

በኩር ማለተ የመጀመሪያ ማለት ሲሆን የበኩራት ስጦታ ከልጅ፤ከከብት፤ከንብረት… ከመሳሰለው የመጀመሪያውን
መስጠት ነው፡፡የአዳም ልጅ አቤል መስዋዕት ሲያቅርብ ‹‹ የመጀመሪያውን ለየ›› የሚለው በኩራቱን ስለማቅረቡ
ሲያስረዳ ሲሆን፡ ይህም የተወደደ መሥዋዕት ሆኖለታል /ዘፍ 4፤4/ ፡፡ከዘመነ ኦሪት ጀምሮ ሕዝበ እግዚአብሔር
አምልኮታቸውን ከሚገልጹበት አንዱ በኩራት ነበር፡፡ከልጆቻቸው፤ከምርታቸው.... በኩር የሆነውን ለእግዚአብሔር
ቤት ይሰጣል፡፡ /ዘኁ 3፤42፤ 1 ሳሙ 2፤ ዘኁ 18፤15-17/፡፡

በኩራትን ማቅረብ እጅግ የተወደደ እና ከሁሉ የሚበልጥ የስጦታ ዓይነት ነው /ዘዳ.23÷19፤ ዘዳ.26/፡፡ክርስቲያኖችም
ሁላችንም ሥርዓተ አምልኮ የምንገልጥበት አንዱ የሆነውን በኩራቱን በማቅረብ ሕገ አምላክን ልንጠብቅ ይገባል፡፡
ይህንንም ከመጀመሪያ ምርታችን፡ ከመጀመሪያ ደሞዛችን ለእግዚአብሔር ቤት በመስጠት የተናገረውን
ከማያስቀረው አምላካችን በረከት እንደምናገኝ በማመን ልንፈጽም ይገባናል /ዘዳ 28÷1-15/፡፡

5.ዐሥራት

ዐሥራት አንድ አሥረኛ ማለት ነው፡፡ከሚያገኙት ገቢ አንድ አሥረኛውን ለእግዚአብሔር ቤት መስጠትን


ያመለክታል፡፡ከሙሴ በፊት በዘመነ አበው የተጀመረ የእግዚአብሔር ሕግ ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዐሥራት በስፋት
ይገልጻል፡፡ከነዚህም ለአብነት ያህል በጥቂቱ እንመልከት፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዐሥራት አበ ብዙሓን አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከ ጼዴቅ በሄደ ጊዜ ዐሥራት
ማውጣቱን ‹‹አብርሃምም ከሁሉ ዐሥራት ሰጠው›› በማለት ዐሥራትን አበው እነደጀመሩት ያስረዳናል/ዘፍ
14÷20/፡፡ ያዕቆብ ከአባቶቹ የወረሰውን ሕገ አምላክ የሆነውን ዐሥራት ማውጣትን ሲገልጽ ‹‹ከሰጠኸኝ ሁሉ
ለአንተ ከዐሥር አንዱን እሰጣለሁ›› ብሏል /ዘፍ 28÷ 1-22/፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዐሥራት ሲያስረዳን
ከእግዚአብሔር የታዘዘ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ነው፡፡ ‹‹ከምታገኘው ሁሉ ዐሥራትን ታወጣለህ›› የሚለው
‹‹ዐሥራት አስገቡ›› ማለቱ እነደዚሁም የምድር ዐሥራት የእግዚአብሔር መሆኑን የሚገልጹ ማስረጃዎች ሁሉ
ዐሥራት ሕገ አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ /ዘዳ. 14÷22፤ ዘሌ.27÷30፤ ዘዳ.12÷17፤ ዘዳ.14÷23፤ ሚል.3÷10/፡፡

መድሓኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ›› ማለቱ አምላካዊ
ትዕዛዝ መሆኑን ያስገነዝበናል /ማቴ 22÷17/፡፡እንደዚሁም አንድ ቀራጭ ወደ ጌታችን ቀርቦ ‹‹ከማገገኘው ዐሥራት
አመጣለሁ›› ማለቱ ቀድሞ የነበረ ሕግ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን ጌታችንም ቀራጩን በዐሥራት ጉዳይ ላይ
መልስ አለመስጠቱ ዐሥራት ተገቢ የሆነ ሥርዓት መሆኑን የሚያመለክት ነው /ሉቃ 18÷12/፡፡

ዐሥራት በመስጠታችን የምናገኘው ጥቅም ምንድን ነው?

ሀ. በረከት ይበዛልናል

ዐሥራት ማውጣት ትዕዛዝን መፈጸም ነውና በአምላካዊ ቃሉ መሠረት በረከቱን ያበዛልናል፡፡‹‹ ቃሌን ብትሰማ
በረከቶች ሁሉ ላንተ ይሆናሉ›› በማለት ቃል እንደገባልን ዐሥራት በማውጣት ለቃሉ ብንገዛ ሀገር፤በት፤ትዳር፤ልጆች
ወዘተ ሁሉም እንደሚባረኩ የታመነ ነው /ዘዳ 28÷1-20/፡፡በነብዩ በሚልክያስ የተጻፈው ቃለ እግዚአብሔር
እንደሚያረጋግጥልን የእግዚአብሔር ገንዘብ የሆነውን ዐሥራት በማውጣት ብንታዘዝ ‹‹የሰማይ መስኮትን
እከፍታለሁ በረከትን እሰጣለሁ›› በማለት አስገንዝቦናል /ሚል 3÷10/፡፡

ለ. ለጽድቅ ያበቃል

‹‹ሕግን የሚሰሩ ይጸድቃሉ›› እንዳለ ዐሥራት ሕግን መፈጸም ነውና ለጽድቅ የሚያበቃ መሆኑን ልናምን ይገባል
/ሮሜ 12፤12/፡፡ሕገ እግዚአብሔርን በመፈጸም ምሕረተ ሥጋ ወነፍስ የምናገኝ መሆኑንም በማይሻር ቃሉ እንዲህ
ብሏል ‹‹ትዕዛዜን ለሚጠብቁ ምሕረትን የማደርግ እኔ ነኝ›› /ዘዳ 20÷6/፡፡ቅዱሳን ሐዋርያትም ከልብ በሆነ
ፈቃደኝነት ዐሥራት በመስጠት ክርስትናችንን እንድንገልጽና ለጽድቅ እንድንበቃ መክረውናል፡፡በመሆኑም
ከምናገኘው ገቢ ላይ ከዐሥር አንድ አስበን ለእግዚአብሔር ቤት በመስጠት ለመንፈሳዊ ዋጋ ልንተጋ
ይገባል፡፡‹‹በበረከት የሚዘራ በበረከት ያጭዳል›› ተብሏልና /1 ቆሮ 16÷14፤ 2 ቆሮ 9÷6-12/፡፡

ነገር ግን በተቃራኒው ዐሥራት በስስትና በተለያዩ ምክንያቶች አለመክፈል ከእግዚአብሔር ጸጋ ያርቃል፡ መርገምንም
ያመጣል፡፡‹‹ሰርቃችሁኛል…..ይኽም ዐሥራትና በኩራቴን ነው›› የሚለው ሃይለ ቃል የሚያስረዳውም ዐሥራት
አለመክፈል ከእግዚአብሔር ገንዘብ ላይ መስረቅ መሆኑን ነው፡፡በነብዩ በኢሳያስ የተነገረውም ያለመታዘዝን ጉዳት
ያስረዳል ‹‹እምቢ ብትሉ ሰይፍ ይበላችኋል›› /ኢሳ.1÷19/ እንዲል፡፡

ዐሥራት አከፋፈል

ዐሥራት መክፈል አምልኮተ እግዚአብሔርን ከምንገልጽበት ተግባር አንዱ መሆኑን ከተገነዘብን፡ አከፋፈሉንም
በማስተዋል ልንፈጽም ያስፈልጋል፡፡ዐሥራት ከገቢ /ከደመወዝ/ ከዐሥር አንዱን በየወሩ ለቤተክርስቲያን በመምህር
ንስሐ በኩል ወይም በቀጥታ በመሔድ በየወሩ ልንከፍል ይገባል፡፡ የምንከፍለውን ዐሥራት ለገጠርም ሆነ ለአጥቢያችን
ስናበረክት ማረጋገጫ መቀበልም ሳንዘነጋ ነው፡፡

አገልግሎቱም፡-
ሀ.ሥርዓተ አምልኮ ለማስፈጸም

የምንከፍለው አሥራት ለሥርዓተ አምልኮ ማስፈጸሚያ ይሆናል፡፡ከዘመነ ኦሪት ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስ
እንደሚያስረዳን የቤተ መቅደስ መገልገያ እና አገልግሎቱ በዓሥራት ስጦታ ይሟላል/ዘዳ 27÷1/፡፡ስለሆነም ለሥርዓተ
ቅዳሴ የሚያስፈልጉ፡ እና ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ ነገሮችን ሁሉ በካህናት አስፈጻሚነት ይሟላበታል፡፡

ለ.አገልጋዮችን ለመርዳት

በዘመነ ኦሪት ሌዋውያን በዐሥራት እንዲጠቀሙና በአግባቡ እንዲያገለግሉ ፈቃደ እግዚአብሔር በመሆኑ
ለአገልጋዮች ይውላል /ዘኁ 18÷21/፡፡በዚህም መሠረት በዘመነ አዲስም በፍትሐ ነገሥት እና በቃለ ዐዋዲ
በተመዘገበው መሠረት የቤተክርስቲያን መደበኛ አገልጋዮች የሆኑ ካህናት ከሚገባው ዐሥራት ላይ ወርኃዊ ደመወዝ
እያገኙ አገልግሎታቸውን እንዲፈጽሙበት ይውላል፡፡ ዐሥራትን ሳናስቀር በአግባቡ ብንከፍል እና አገልጋዮችም
አግባብ ባለው ቦታ ላይ ቢያውሉት ዛሬ የምናየውን የአገልጋዮች መጉላላት፡ የአብነት ትምህርት ቤቶች መፈታት፡
በገጠር የካህናት እጥረት…. የመሳሰሉት ችግሮችን የሚቀርፍ ዋና አማራጭ መፍትሔ መሆኑ ሊስተዋል ይገባል፡፡

ሐ. ነዳያንና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው ይረዱበታል

ነዳያን ከሙዳየ ምጽዋት ብቻ እንደሚረዱ የሚስተምሩ መምህራን ያሉ ቢሆንም ከሕገ ቤተክርስቲያን ክፍል አንድ
በሆነው በቃለ ዐዋዲ ላይ እንደተጻፈው በቤተክርስቲያን ዙሪያ የሚገኙ ደካሞች እና በተለያዩ ምክንያቶች መሥራት
የማይችሉ ነዳያን ከምእመናን ከሚመጣው ዐሥራት ላይ ተቀንሶ በበጎ አድራጎት ክፍል አስተባባሪነት እንዲረዱበት
ያዛል፡፡ በሙሴ እና ሌዋውያንም በስፋት በቤተመቅደስ በሚያገለግሉበት ዘመን ከዐሥራት ላይ ለነዳያን እንዲሰጡ
እግዚአብሔር ስለማዘዙ ተጽፏል፡፡ስለዚህም ዐሥራት ለነዳያን የሚውል መሆኑንም ያረጋግጣል /ዘዳ.14÷28፡
26÷12/፡፡

ማጠቃለያ

መንፈሳዊ ሕይወትን ለመምራት መንፈሳዊ ዕውቀትም ያስፈልገናል፡፡ስለሆነም የመንፈሳዊ ህይወት መገለጫ እና


በረከት ማግኛ የሆኑትን ስጦታዎችን ለማበርከት ዓይነቶቹን እና ሥርዓቱን ለይተን ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡‹‹ ቃሉን
የምትፈጽሙ ሁኑ›› እንደሚል ማወቅ ደግሞ ለመፈጸም ነውና ስጦታዎቹን በረከት ለሕገ እግዚአብሔር በመገዛት
ወደተግባር ልንገባ ያስፈልጋል፡፡ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን ያለስስት፡ እና ያለ ጥርጥር ከልብ ሆነን ለእግዚአብሔር
ቤት ልንሰጥ ይገባል፡፡‹‹በረከት እንደማልሰጥ ፈትኑኝ ›› ያለን አምላካችን በአግባቡ ለምንሰጥ በረከቱን ይሰጠን ዘንድ
የታመነ አምላክ ነው /ሚል 3÷9፡ 1 ቆሮ 9÷6/፡፡

(ውድ አንባቢያን ይህ ጽሑፍ በሐመር መጽሔት የየካቲት 2002 ዓ.ም. ዕትም ላይ ወጥቶ የነበረ መሆኑን እንገልጻለን
!)

You might also like