Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 3

የአሸዋና የድንጋይ ጽሑፍ

አንድ ወዳጄ ከላከልኝ መጽሐፍ ላይ ይህንን አነበብኩ፡፡

ሁለት እጅግ የሚዋደዱ ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ የትም ቦታ ሲሄዱ አይለያዩም ነበር፡፡ እንደለመዱትም አብረው ወደ
አንድ ሀገር በእግራቸው ይጓዙ ነበር፡፡ መንገድ በዝምታ ይረዝማልና እየተጨዋወቱ ነበር የሚጓዙት፡፡ አንዳንድ
ጨዋታ በድካም መንፈስ ከተጫወቱት ለጠብ ይዳርጋል፡፡ ድካም የትዕግሥትን ዐቅም ይፈታተናልና፡፡ ለዚህ ነው
የሀገሬ ሰው የድካም ና የዕረፍት ጨዋታ ለየቅል ነው የሚለው፡፡

እነዚህም ወዳጆች የዕረፍቱን ጨዋታ ለድካም አምጥተውት ኖሮ አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ አንደኛው ታድያ ብልጭ
ሲልበት በቦክስ ድንፉጭ የማድረግ ልማድ ነበረበትና በጓደኛው ላይ ታይሰን የማይችለው ቡጢ ሠነዘረበት፡፡
ቡጢውን የቀመሰው ጓደኛም የፊቱን ደም ጠርጎ፣ እያበጠ የሄደውን ግንባሩን ዳሰሰው፡፡ እጅግም አዘነና መንገዱን
አቋርጦ በበረሃው አሸዋ ላይ ተቀመጠ፡፡ አንገቱን ግራና ቀኝ እያወዛወዘ ኀዘኑን ገለጠ፡፡ ንዴቱ ከውስጥ እንደ ልቅሶ
ቤት ሽሮ ቡልቅ ቡልቅ ይልበት ጀመር፡፡ መልሰህ ‹በለው፣ በለው› እያለ ወንድነቱ ያስቸግረው ነበር፡፡

ያን ጊዜ ዓይኑን አማተረና አንዳች እንጨት ፈልጎ አገኘ፡፡ በአሸዋም ላይ ‹‹ዛሬ እጅግ የምወድደው ወዳጄ ግንባሬ
ላይ በቡጢ መታኝ›› ብሎ ጻፈ፡፡ ቀና ብሎ ሲያይም ጓደኛው ጥሎት በመሄድ ላይ ነበር፡፡ እርሱም ያንን ጽሑፍ
በአሸዋው ላይ ትቶት ጓደኛውን ተከትሎት ሄደ፡፡

ብልጭ ብሎበት የተማታው ጓደኛው እጅግ ተፀፀተ፡፡ በጓደኛው እግር ላይ ወድቆም ይቅርታ ጠየቀው፡፡ የተመ
ታውም ይቅርታውን ተቀብሎ አብሮት ተጓዘ፡፡ የነበረውን ሁሉ ረስተው ደስ የሚል ጨዋታ እየተጫወቱ ተጓዙ፡፡
በዚህ መንገዳቸው ላይ አንድ ወንዝ ነበረ፡፡ በአሸዋውና በሙቀቱ የተነሣ ተዳክመውና በላብም ተጠምቀው ስለነበር
ልብሶቻቸውን አውልቀው ወደ ወንዙ ገቡ፡፡ ወዲያና ወዲህ እየዋኙ ድካማቸውን በመርሳት ላይ ሳሉ ያ በቡጢ
የተመታውን ጓደኛ ወንዙ ነጥቆ ይዞት ሄደ፡፡

ሁኔታውን ያየው ሌላው ጓደኛውም ያለ የሌለ ጉልበቱንና ብልሃቱን ተጠቅሞ እየዋኘ ጓደኛውን በወንዝ ከመወሰድ
ታደገው፡፡ በአንድ እጁ እየሳበም ወደ ዳር አደረሰው፡፡ ያኛው ጓደኛም ከተወሰደበት ወንዝ ከወጣ በኋላ በዓይኑ
ማተረ፡፡ እነሆም አንድ ድንጋይ አገኘ፡፡ ቀጥሎም አንድ ባልጩት አመጣ፡፡

አሸዋው ላይ ተቀምጦ በዚያ ባልጩት ያንን ድንጋይ መቀጥቀጥ ጀመረ፡፡ ለብዙ ሰዓታት ከቀጠቀጠ በኋላ በድንጋዩ
ላይ ‹‹ዛሬ እጅግ የምወደው ጓደኛዬ ሕይወቴን ከሞት ታደጋት›› ብሎ ጻፈ፡፡

አስቀድሞ የተማታው፣ በኋላም ጓደኛውን ያተረፈው ጓደኛም በሆነው ነገር ሁሉ ተገረመ፡፡ ጓደኛውንም እንዲህ
ሲል ጠየቀው ‹‹ ቅድም ግንባርህን በቡጢ ስመታህ፡- የምወድደው ጓደኛዬ ግንባሬን በቡጢ መታኝ ብለህ በአሸዋ
ላይ ጻፍክ፡፡ አሁን ግን በወንዙ ከመወሰድ ሳድንህ፡- የምወድደው ጓደኛዬ ሕይወቴን ከሞት ታደጋት ብለህ
በድንጋይ ላይ ጻፍክ፡፡ ያኛውን በሚጠፋ አሸዋ ላይ፣ ይህንን ግን በማይጠፋ ድንጋይ ላይ ጻፍከው፡፡ ለምን?››

ጓደኛውም መለሰ፡፡ ‹‹ቅድም ጉዳት አደረስክብኝ፤ እኔም አዘንኩብህ፣ ተቀየምኩብህም፤ ተሰምቶኛል፤


ተናድጃለሁም፡፡ ነገር ግን የእኔና ያንተ ወዳጅነት እንዲቀጥል ከተፈለገ መርሳት መቻል አለብኝ፡፡ ስለዚህም በአሸዋ
ላይ ጻፍኩት፡፡ አየህ ሰዎች በእኛ ላይ ክፉ ሲያደርሱብን የይቅርታ ነፋስ ጠርጎ ሊወስደው ይችል ዘንድ በአሸዋ ላይ
ብንጽፈው መልካም ነው፡፡

‹‹በኋላ ሕይወቴን ከሞት ስትታደጋት ግን ዘወትር እንዳስታውሰው ስለምፈልግ በማይጠፋ ድንጋይ ላይ ጻፍኩት፡፡
ሰዎች የሚያደርጉልንን በጎ ነገር ሁሉ ማንም ሊያጠፋው በማይችል ልብ ላይ መጻፍ አለብን፡፡ ሰውን መውደድ
የምትችለው በጎ ነገሩን አዘውትረህ ካስታወስክ ብቻ ነው፡፡››

ጓደኛው አቀፈው፡፡

‹የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ› የሚል አባባል አለ፡፡ ልክ ነው፡፡ አንዱ በሌላው ላይ የሚያደርገውን ግፍና መከራ
መርሳት ከባድ ይሆናል፡፡ አንዳንዱ ሰው ደግሞ የሚያደርሰው ጉዳት እንዳይረሳ አድርጎ የሚፈጽመው ነውና
ለመርሳት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

ቢሆንም ግን ግፍንና በደልን እያስታወሱ መኖር ተበዳዩን ይበልጥ ይጎዳዋል፡፡ ምክንያቱም የደረሰብን በደልን
ይበልጥ ባስታወስነው ቁጥር ጥላቻችን ይበልጥ እየጨመረ ይመጣልና፡፡ የደረሱብንን ነገሮች ብቻቸውን ልናስታ
ውሳቸው አንችልም፡፡ ከዚያ በፊት ከነበሩትና ከዚያም በኋላ ከተፈጸሙት ነገሮች ጋር እናያይዛቸዋለን፡፡ እንተነትና
ቸዋለን፣ የራሳችንንም ሥዕል እንሰጣቸዋለን፡፡ ‹እባብ ያየ በልጥ ይደነግጣል› የሚለው አባባል በአንድ ወቅት
የተፈጸመ ነገር በተፈጸመበት ሰው ላይ ጥሎት የሚሄደውን ጠባሳ የሚያሳየ ነው፡፡

ያለፈን በደል አዘውትሮ ማሰብ ፈጻሚውን ለመበቀል ያለንን ፍላጎት ይጨምረዋል፡፡ ያንን ሰው ወይም አካል
እንከታተለዋለን፡፡ ዐውቀንም ይሁን ሳናውቀው ስለዚያ ሰው ወይም አካል መስማት እንፈልጋለን፡፡ ያ ሰው ወይም
አካል የሚያደርገው ክፉ ነገር ብቻ ሳይሆን በጎ ነገሩ ራሱ ያበሳጨናል፡፡ ወድቆና ተንኮታኩቶ፣ ደኽይቶና ተጎሳቁሎ
የማየት ፍላጎት ያድርብናል፡፡ የኛን ትክክለኛነት በዚያ ሰው ውድቀት ለማረጋገጥ እንመኛለን፡፡ የሰውየው ውድቀት
ተፈጥሯዊውን መንገድ ተከትሎ የማይመጣ ከሆነ እኛው ራሳችን ወደ መፈጸሙ እናመራለን፡፡

በአንድ ወቅት የተፈጸመ ነገር ረዥሙን የሕይወታችን ጉዞ የሚያበላሽበት ጊዜም አለ፡፡ ጉዳዩ የተፈጸመው አንድ
ጊዜ ሆኖ ሳለ እንደ ወር በዓል በኅሊናችን ተደጋግሞ እየመጣ ዘላቂውን ሕይወታችንን ይበጠብጠዋል፡፡ ሌላው
ቀርቶ ሌሎችን ሰዎችም በእነዚያ ክፉ አድራጊ ሰዎች ዓይን ማየትም እንቀጥላለን፡፡ ‹‹አይ ወንዶች፣ አይ ሴቶች››
የሚሉ አባባሎች ያለፉ ግንኙነቶቻቸው በተበላሹ ሰዎች የተፈጠሩ ሳይሆኑ አይቀርም፡፡ አንዳንዶችም ያኛው ጠባሳ
እንዳይጠፋ አድርገው በዐለት ላይ ስለጻፉት ከዚያ ጋር የሚመሳሰሉ ገጠመኞች ሲያጋጥሟቸው ያ ነገር ተመልሶ
እንዳይመጣ በመፍራት የጀመሩትን ያቆሙታል፡፡

ያለፈን ክፉ ነገር ማስታወስ ውሳጣዊ ሰላማችንንም ያናጋዋል፡፡ ሰላም ከውስጥ ወደ ውጭ እንጂ ከውጭ ወደ
ውስጥ አይገባም፡፡ ሰላማዊ ልቡና በሌለበት ሰላም ተዘርቶ አይበቅልም፡፡ ድስቱ ውስጥ ጥቂትም ብትሆን መርዝ
እስካለች ድረስ የሚገባበት ማንኛውም ዓይነት የወጥ እህል መበላሸቱ የማይቀር ነው፡፡ ከውጭ የሚገባው የወጥ
እህል ንጹሕ ቢሆን እንኳን የድስቱ ውስጥ ንጹሕ እስካልሆነ ድረስ እርሾ እየሆነ ይበክለዋል፡፡ አንድ መቶ ኩንታል
ዱቄትን እፍኝ የምትሞላ እርሾ ታቦካዋለች፡፡ በልብ ውስጥ የተቀመጠች የቂም ቁርሾም የሚመጡትን በጎ ነገሮች
ሁሉ ስታቦካቸው ትኖራለች፡፡ ይህ ደግሞ ውሳጣዊ ሰላማችንን ያናጋዋል፡፡ ያ ደግሞ ተናዳጅ፣ ነጭናጫና ማንም
ሳይረብሸን የምንረብሽ ያደርገናል፡፡
የደረሱብንን ነገሮች በአሸዋ ላይ መጻፍ ያለብን ያደረሱት ሰዎች ትክክል ስለሆኑ አይደለም፡፡ በደልን ለማበረታ
ታትም አይደለም፡፡ ለዘብተኛ ለመሆንም አይደለም፡፡ ለይቅርታና ለዕርቅ ዕድል ለመስጠት እንጂ፡፡ ለሌላም ሲባል
አይደለም ለራስ ሲባል እንጂ፡፡

አንድ ሊቅ ‹‹ይቅርታ መጠየቅ ሁልጊዜም ጥፋተኛነትን አያመለክትም፣ ለወዳጅነት ስንል መሥዋዕትነት መክፈልን
እንጂ፤ እኔ ትክክል ሆኜ ወዳጅነታችን ከሚጠፋ፣ ይቅርታ ጠይቄ ወዳጅነታችን ይቀጥል ብሎ ማሰብን እንጂ›› ብሎ
ነበር፡፡

ክፉ አጋጣሚዎችን መርሳት ለመርሳት ስለተፈለገ ብቻ የሚመጣ አይደለም፡፡ የመርሳት ችሎታንም ይጠይቃል፡፡


ይህንን ለማድረግ ደግሞ የመጀመርያው ርምጃ ለመርሳት መወሰን ነው፡፡ ለመርሳት መወሰን ለመርሳት ለመቻል
በር ይከፍታል እንጂ ለመርሳት አያስችልም፡፡ ለመርሳት ለመቻል ቀጣዩ ምእራፍ የልብ ሕመምን ማውጣት ነው፡፡
በመጻፍ፣ በመናዘዝ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር በማውራት፣ ለፈጣሪ በመስጠት፣ አልቅሶ በማውጣት ያለፈውን ክፉ
ገጠመኝ የመሻርያ መንገድ መተለም ያስፈልጋል፡፡

ሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ያንን ነገር ከሚያስታውሱ ነገሮች መራቅና መቆጠብ ነው፡፡ የሚያስታውሱ ፎቶዎች፣
ዕቃዎች፣ ግንኙነቶች፣ ዜማዎች፣ ቦታዎችና ሌሎችንም ለተወሰነ ጊዜ ማራቅ ይገባል፡፡ እነዚህ ነገሮች ለመርሳት
እንድንችል መንገዱን ያመቻቹልናል፡፡ የልቡናችን ቁስልም ከንክኪ ነጻ ሆኖ እንዲሽር ዕድል ይሰጠዋል፡፡

አንዳንዴ ያለፈውን ጠባሳ የሚያስታውሱ ገጠመኞችና ትውስታዎች ሲመጡ ወዲያውኑ ከዚያ የሚያላቅቁ
ርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ለእነዚህ ክስተቶች ረዘም ያለ ጊዜ መስጠት ነገሩ ወደ ውስጣችን ጠልቆ
እንዲገባና ለመርሳት የምንፈልገውንም ነገር እንዳንረሳው ያደርጋል፡፡

ከትናንት ወጥቶ ነገ ላይ ማተኮር ክፉ ገጠመኝን እንድንረሳውና ከተቀየድንበት የትናንት አዙሪት እንድንወጣ


ያደርገናል፡፡ የክፉ ገጠመኝ አንዱ ችግር ሕይወታችን ወደ ትናንት ብቻ እንድትሄድ ማድረጉ ነው፡፡ ትናንትን
መቀየር አይቻልም፡፡ በትናንቱ ላይም ምንም መድረግ አይቻልም፡፡ በነገ ላይ ግን ብዙ ነገር ማድረግ ይቻላል፡፡
ትናንትን ተምረንበት እንተወው፣ በእጃችን ላይ ባለው ነገም እንሥራ፡፡ ስለትናንት ብቻ ማሰብ ግን ትናንትንም
ነገንም ማጣት ይሆናል፡፡

ለዚህ ሁሉ አንድ ነገር አስቀድሞ ወሳኝ ነው፡፡ በሕይወታችን ምዕራፎች ሁሉ ክፉ ገጠመኞችንን በአሸዋ ላይ፣
በጎዎችንም በዐለት ላይ እየጻፍን መቀጠል፡፡

ላስቬጋስ፣ ኔቫዳ

You might also like