Melka Kidane Mihret

You might also like

Download as docx, pdf, or txt
Download as docx, pdf, or txt
You are on page 1of 8

መልክአ ኪዳነ ምሕረት

፩፤ እግዚአብሔር አብ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በአካል ሦስት ሲሆን በመለኮታዊ ባሕርዩ በአንድነቱ ጸንቶ የሚኖር የብርሃን መገኛ
እሱ እግዚአብሔር አብ ለቃል ኪዳንሽ የተሰጠውን ልዩ ክብር ብሩህ አድርጎ ያሳየኝ ዘንድ የቸርነቱ ጸዳለ ብርሃን ዓይነ
ልቡናየን ያብራልኝ፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ከእግዚአብሔር በታች በሰማይም በምድርም አንች የሁሉ እመቤት ነሽ እኮን፡፡

፪፤ ለዝክረ ስምኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በብርሃናዊዉ ኮከብ ለተመሰለው ስም አጠራርሽ ሰላምታ ይገባል፤ በጨለማ ለሚኖሩ
ሕዝቦች ብርሃኑን አብርቶላቸዋልና፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ የአምላክ ቃል ኪዳኑ መዛግብት በዕለተ ዓርብ የተገኘውን የደኅነታችን ተስፋ ያስገኘሽ
ዕውነተኛ መዝገብ ነሽ እኮን፡፡ አባታችን ቀዳማዊ አዳም በጭንቅና በኅዘን ከገነት ወጥቶ በተሰደደ ጊዜ ከልቡናው ኅዘን
ተረጋግቶብሻልና፡፡

፫፤ ለስእርተ ርእስኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ያለማቋረጥ ሰማያዊ ጠል ለረበበትና የሐር ጉንጉን ለሚመስለው ስእርተ ርእስሽ ሰላምታ
ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ሞትን የሚያስከትል፤ እንደ ኤልያስ ሥጋዊ ሕይወት ያይደለ የነፍሴን ሕይወት ይሰጠኝ ዘንድ
በታላቅ ጉባዔ ፊት የምሕረት ቃል ኪዳን በገባልሽ ልጅሽ ዘንድ አማልጅ፡፡

፬፤ ለርእስኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ከተፈጥሮ ባሕርያት ሁሉ በበላይነት ላለውና ለሚኖረው ርእስሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ተገቢ በሆነ ጎዳና ሁሉ ቃል ኪዳን ግቢልኝ፤ ከሞት ጋር ግን ቃል ኪዳን ተጋብተናል የሚሉ ሁሉ
ከንቱ ነገርን ተናገሩ፤ ነፍሳቸውንም አጠፉ፡፡

፭፤ ለገጽኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ከፀሐይና ከጨረቃ የብርሃን ፀዳል ይልቅ የሚያንጸባርቀውና በንጽሕና በቅድስና
ለሚያበራው ለፊትሽ ደም ግባት ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ልዩ ኅብር ባለው ቀስተ ደመና ምሳሌ የቃል ኪዳን ምልክት አድርጎ ይቅር ባይ ከሚሆን ፈጣሪ
ዘንድ አባታችን ኖኅ አንቺን ከተቀበለ ጀምሮ እነሆ ምድርን ዳግመኛ የጥፋት ውሃ አላገኛትም፡፡

፮፤ ለቀራንብትኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ የዓይኖችን እይታና አገላለጥ ለመጠበቅና ለመንከባከብ ለተፈጠሩ ቀራንብቶችሽ ሰላምታ
ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ያለዘርዓ ብእሲ የወለድሽውን ልጅሽን ኃጥኣን እንኳን ቢሆኑ ስምሽን ከጠሩ እምርልሻለሁ
ስትል የገባህልኝ ቃል ኪዳን ወዴት አለ ብለሽ አሳስቢው፡፡

፯፤ ለአእይንትኪ፡፡
እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በታላቅ አዳራሽ ውስጥ በሁለት አንፃር ተተክለው እንደሚያበሩ የቀንዲል መብራቶች
ለተመሰሉ ዓይኖችሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ የይቅርታና የርኅራኄ መገኛ አንች ነሽና በቃል ኪዳንሽ ከጥፋት ሁሉ አድኚኝ ያለአንች ማዳን
የሚቻለው የለምና፡፡

፰፤ ለአዕዛንኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ባሕርይሽን ባሕርይ አድርጎ ሥጋሽን ከለበሰ ፈጣሪ ልጅሽ ዘንድ የቃል ኪዳን ምሥራች
ለተነገራቸው አዕዛኖችሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ለጽድቅ የሚያበቃ በጎ ምግባር ባይኖረኝም እንኳ የገሃነምን ደጅ እንዳታሳይኝ እማልድሻለሁ
ቃል ኪዳንሽ እንዲሁ በከንቱ አይደለምና፡፡

፱፤ ለመላትሕኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ የጽጌረዳ አበባ ለሚመስሉ ጉንጮችሽ ሰላምታ ይገባል፡፡ ነገር ግን በአምስቱ ኅዘናት እንደ
እሳት በሚያቃጥል ዕንባ ጠወለጉ ኦ ወዮ እኔን እኔን!!

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ የሁለቱ እህትማማቾች የሐሊና የሐላ ነፍሳት በገሃነም ተጥለው ከሚያለቅሱበት ከዚያ
እንዳልወድቅ በቃልኪዳንሽ ተድላ ደስታ ወደአለበት ቦታ አሳርጊኝ፡፡

፲፤ ለአእናፍኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በአምላካዊ እደ ጥበብ ግራ ቀኝ የሕይወት መሳክው ለወጣላቸው አዕናፎችሽ
(አፍንጮችሽ) ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ በቃል ኪዳንሽ ጽኑ አጥርነት ከጠላት ጥፋት ጠብቂኝ፡፡ ያ ክፉ አውሬ ዲያብሎስም ሊውጠኝ
አፉን በከፈተ ጊዜ በበትረ መዓት ራስ ራሱን ቀጥቅጠሸ አጥፊው፡፡

፲፩፤ ለከናፍርኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ስለ ኃጥኣን ለምነው ማልደው ይቅር ባይ ከሚሆን አምላክ ዘንድ የምሕረትን ቃል ኪዳን
ላስገኙ ከናፍሮችሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ለዕውነተኛዋ ቃል ኪዳንሽ በየክብረ በዓሏ ከገሊላ እስከ ጎልጎታ የተመላለሽበትን የክብር
አክሊል በኔ በኃጥኡ አገልጋይሽ ራስ ላይ አቀዳጅኝ፡፡

፲፪፤ ለአፉኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ቅዱስ መጽሐፍ ለሚነገርበትና የትሩፋትን በረከት ለሚያስገኝ አፍሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ አንደበት በታሠረ አፍም በተዘጋ ጊዜ በተወደደው ልጅሽና የብዙ ብዙ የሚሆኑ በመላእክቶቹ
ፊት እንዳላፍር በተቀበልሽው ቃል ኪዳን እማፀናለሁ፡፡

፲፫፤ ለአስናንኪ፡፡

ለትክክለኛ አበቃቀላቸውና ተሸልተው እንደ ነፁ እንደ በጎች መንጋ ንጹሓን ለሆኑ ጥርሶችሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ እኔን አገልጋይሽን የቃል ኪዳን ካሳ ዓሥራት አድርጊልኝ በደልን የሚወድ ጠላቴ ግብፃዊውን
የጸሎትሽ ክንድ ሙሴ በአሸዋ ውስጥ ይቅበረው፡፡

፲፬፤ ለልሳንኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ከሥላሴ ፊት በሚቆሙ ከሰማይ ካህናት ከሱራፌል ይልቅ ምስጋናን አብዝቶ ለሚናገር
አንደበትሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ስለ እስራኤል አርእስተ አበው ማለት የአብርሃምን፤ የይስሃቅን የያዕቆብን ቃል ኪዳንና
የሙሴንም ባለሟልነትን እንዳሳሰበ ስለኔም በመከራ ዘመን ጊዜ የመታሰቢያ ቃል ኪዳንሽን አሳስቢልኝ፡፡

፲፭፤ ለቃልኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ የተጎናጸፈ በብሥራተ መልአክ በገብርኤል ቃል ቃልን ለተቀበለ ቃልሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ የእግዚአብሔር የልዑል ኃይሉ ማደሪያው ሆነሻልና ኃጥአን መዳን ወይም መጽደቅ
በሚችሉበት ገንዘብ የይቅርታዋ የቸርነቱን ቃል ኪዳን እንኳን ሰጠሽ እሰይ እሰይ እያልን እናመሰግንሻለን፡፡

፲፮፤ ለእስትንፋስኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በከይሲ ዲያብሎስ መርዝ የቆሰሉ የኃጥኣንን ነፍሳት ፈውስና ጤናን ለአስገኘ እስትንፋስሽ
ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ በቃል ኪዳንሽ ኃጢአቴን አስተስርይልኝ ያለቃል ኪዳንሽና አዳኝ የሚሆን ከክርስቶስ መስቀል
በስተቀር ከሲኦል የሚድን ሰው ከቶ አይኖርምና፡፡

፲፯፤ ለጉርዔኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ መራራውን ከጣፋጭ በየወገኑ ለሚለይ ንዑድ ክቡር ለሚሆን ጉረሮሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ እንግዲህ ስለቸርነትሽ ምን ውለታ እከፍላለሁ፡፡ ኃይሌ ደካማ በመሆኑና በሁለት አቅጣጫ
የተደቀነውን ልዩ ፈተና ልወጣው ባለመቻሌ ዓለም ጠባኛለችና፡፡ ነገር ግን እናት ሆይ በቀላል ኪዳንሽ አረጋጊኝ፡፡

፲፰፤ ለክሳድኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በጥበብ አዋቂዎች በተራራ ወይም በከፍተኛ ቦታ ላይ መሠረቷ የተመሠረተ የዳዊትን ቤተ
መንግስት ለሚመስለው ክሣድሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ የአገልጋዬ ሰውነት ማርታ ሆይ ስለምን በብዙ ትደክሚያለሽ ብዙ ከመመራመር ጥቂት
ትሩፋት ይበቃልና ብለሽ ወደ ዕዝነ ልቡናየ ተጠግተሽ ሰውነቴን አረጋጊያት፡፡

፲፱፤ ለመታክፍትኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ከመርገምና ከዘለፋ አገዛዝ የበረከትን ነፃነት ለተጎናጸፉ ትከሾችሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ በእውነተኛው የቃል ኪዳን ትከሻሽ እንኮኮ በይኝ፡፡ ከልጅሽም መንጎች መካከል የድርሻሽን
ዓሥራት አድርገሽ ውሰጅኝ የሃይማኖቴ አለኝታ ፍጹም ተስፋዬ አንቺ ነሽና፡፡

፶፤ ለዘባንኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ አስቀድሞ ወደ ደብረ ቁስቋም በመሰደድ ወራት አምላክ ለአዘለ ጀርባሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ስምሽን በስሙ ላይ የሠየመውን በኋለኛዪቱ የፍርድ ሰዓት ደሙ ባያሠለጥነው አንች ይቅር
ባይ እናቱ የቃል ኪዳን ዓሥራት አድርገሽ ተቀበይው፡፡

፶፩፤ ለእንግድዓኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በእንግድዓሽ አካባቢ ለምትገኘው ሕፅንሽና በግራ በቀኝ ላሉ እጆችሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ምድራዊ ሥጋዊ ሰውነቴ ወደመሬትነቷ በተመለሰች ጊዜ ለነፍሴ አንቺ ካለሽበት መልካሙን
ቦታ ታዘጋጅላት ዘንድ በጎልጎታ በፈሰሰው በልጅሽ ነጸፍጻፍ ደም እማልድሻለሁ፡፡

፶፪፤ ለመዛርዕኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ረቂቅ ባሕርየ መለኮትን ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ሰው የሆነ ክርስቶስን ታቅፈው
ለተንከባከቡት ክንዶችሽና ኩርማዎችሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ከምድራዊያን ጻድቃን ሰማዕታት ከሰማያውያንም መላእክት ይልቅ አንች የተመረጥሽ ነሽ፡፡
በጽኑ ዕምነት መታሰቢያሽን ያደረገ ኃጥእም ቢሆን እንኳ በመንግሥተ ሰማይ ካንች ጋር ነግሶ ይኖራል፡፡

፶፫፤ ለእመታትኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሳለሽ የሐሩን ፈትልና ወርቁን አስማምተው ለፈተሉ
ክንዶችሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ የምሕረት ቃል ኪዳንሽን በእኔ ላይ አስፈጽሚ፤ ተራጋሚ የነበረ ሳሚን ሰሎሞን በጥበቡ
በሞት እንዳስወገደው የኔንም ጠላት በልዩ ተአምራትሽ ከመኖር ወደ አለመኖር አስወግጅው እሱ ተራጋሚ ነውና፡፡

፶፬፤ ለእራኅኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በታላቋ መቅደሰ ኦሪት ሳለሽ ሰማያውያን መላእክት ያመጡልሽን ሰማያዊ ኅብስትና
ሰማያዊ መጠጥን ለተቀበሉ ለእጆችሽ መዳፍ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ እነደዚሁም ሁሉ ጥርኝ ውሃ ለተጠማ አጠጥቼ ብገኝ ጥቂቷን ስጦታየን እንደተመረጠ የሠርክ
መሥዋዕት አድርጎ ቃል ኪዳንሽ ይቀበልልኝ፡፡

፶፭፤ለአጻብዕከ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ንጹሓን ለሚሆኑ ጣቶችሽና እንደ በረዶ ለሚነጹ አጽፋሮችሽ እንዲሁም ያማረ የጣፈጠ
የወተት መፍለቂያ ለሆኑ ሁለቱ ጡቶችሽም ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ በዘመነ በልግ የተገኘሽ የጽጌረዳ አበባ ነሽ እኮን፡፡ ስለዚህም ለሰይጣንና ለተከታዮቹም
ከተዘጋጀ ገሃነም እሳት በቃል ኪዳንሽ ኃይል እድን ዘንድ የድንግልና ወተትን በሚያመነጩ ጡቶችሽና እጅግ
በሚያስደንቀው ደም ግባትሽ እማፀናለሁ፡፡

፶፮፤ ለገበዋትኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በማይጠወልግና በማይረግፍ የወርቅ ሐመልማል በግራ በቀኝ ለተሸለሙ ጎኖችሽ ሰላምታ
ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ኃጥአን ወደ ሲኦል ጨለማ በወረዱ ጊዜ እኔን አገልጋይሽን ከነሱ ነጥለሽ በቃል ኪዳንሽ ጎን
አቁሚኝ ኃጥአን በሕይወታቸው ሣሉ ከጻድቃን ጋር መተባበርን ጠልተዋልና፡፡

፶፯፤ ለከርሥኪ፡፡
እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ የከርሠ መላእክት ወገን ለሚሆንና በመጠነ ክብሩ ሰማያዊ ኅብስትን ለሚመገብ ብሩክ
ከርሥሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ የእግዚአብሔር የሕጉ ታቦት የተባልሽ ጽዮን ማርያም አንች ነሽ እኮን፡፡ ስለዚህም የቃል
ኪዳንሽ የፏፏቴ ውኃ ከፍቅረ ንዋይ ፈጽሞ ይጠበኝ ገንዘብ ወዳድነት ከሰይጣን ወጥመድ ያስገባልና፡፡

፶፰፤ ለልብኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ከኩላሊትና ከመሰሎቹ ጋር ተባብሮ ለሚገኝ ልቡናሽ ሰላምታ ይገባል፡፡ ለአማዑትሽና
ለውስጣዊ ገንዘቦችሽም ሁሉ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ የፍቅርሽን መና እየመገብሽ በቃል ኪዳንሽ የብርሃን ፋና ጎዳናውን እየመራሽ በቀስተ ደመና
ጭነሽ ደስታ ካለበት ገነት አግቢኝ፡፡

፶፱፤ ለኅንብርትኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ የተኮላ የብር ጉትቻ ፈርጥ ለሚመስለው ሕንብርት እንዲሁም ለቡሩክ ማኅፀንሽና
ለንጹሑ ወገብሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ክብርት የአምላካችን የክርስቶስ እናት እንደመሆንሽ ቀናዒ መልአክ በአየር ላይ
እንዳይቃወማት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ነፍሴን ተንከባክበሽ ሸኛት፡፡

፴፤ ለድንግልናኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ለአምስቱ ሕዋሳተ አካል መመኪያ ለሆነው ድንግልናሽ ሰላምታ ይገባል፡፡ የነባቢት መቅደስ
አዕማድ (ምሰሶ) ለሚሆኑ አቁያጾችሽም ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ የእግዚአብሔር የሕጉ ታቦትና የሐዲስ ኪዳን ጽላት አንች ነሽ እኮን፡፡ አሁንም መድኃኒተ ሥጋ
ወነፍስ የሚሆን የልጅሽን ደም የነፍስን ደዌ ይፈውሳልና፡፡

፴፩፤ ለአብራክኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በስግደትና በማማለድ ጊዜ ከእግሮችሽ ጋር ለሚተባበሩ አብራኮችሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ የአብን አካላዊ ቃል ተቀብለሽ በማኅፀንሽ የወሰንሽው ኃጥኣን ወደ ገሃነም እንዲጣሉ በፈረደ
ጊዜ ለነፍሴ ይቅርታውን ያደርግላት ዘንድ አጥብቀሽ ለምኝ ማልጅ፡፡

፴፪፤ ለሰኮናኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ የሄሮድስ ጭፍሮች የቤተ ልሔምን ሕፃናት በፈጁ ጊዜ በእሾሁና በዕንቅፋት እየተሠቃዩ
ከቤተ ልሔም እስከ ደብረ ቁስቋም ለገሠገሡ አብራኮችሽና ጫሞችሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት የቅስራ ልጅ ሆይ፤ አንተን የምትወድህን ነፍስ ስለ ሦስት ባሕርይዋ ብለህ በውኑ ትኮንናታለህን
ብለሽ የሰማይን አምላክ ትጠይቂልኝ ዘንድ እማፀንሻለሁ፡፡

፴፫፤ ለአጻብዕኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ እያንዳንዳቸው በብርሃናዊ አጽፋ፤ ለተሸለሙ ከጫሞችሽ በፊት በተቀዳሚነት ለሚገኙ
ለሁለት እግሮችሽ ጣቶች ሰላምታ ይገባል፡፡
የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ለእንደኔ ያለ ሟች ሰው ቢነግሩት ደሜን በአንደበቱ ጽዋ ቀድቶ እየጠጣ ወሬን ስለሚያዘምት
አንች በቃል ኪዳንሽ ኃጢአቴን ሸሽገሽ ንጹሕ አድርጊኝ፡፡

፴፬፤ለቆምኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ የትሩፋት ዓየር ለአሳደገውና የኃጢአት ኃይለ ነፋስ ፈጽሞ ለማያናውጸው አካለ ቆምሽ
ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ በቃል ኪዳንሽ ክንፍ ሠውረሽ ከኩነኔ አድኚኝ፡፡ ቃል ኪዳንሽ የማዳን ሥልጣን ባይኖረውስ ኖሮ
የበላዔ ሰብእን ነፍስ ማዳን ባልተቻለውም ነበርና፡፡

፴፭፤ ለመልክእኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ከኤልሳቤጥና ከሐና መልክ ይልቅ በደም ግባቱ በወዘናውና በልምላሜው ልዩ ለሆነ መልክሽ
ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ በሥጋ በነፍስ በአፍአበውስጥ ድንግል የምትሆኝ ክብርት እመቤቴ ነሽና በፈጣሪ ፊት ፍጹም
ባለሟልነት ያለው ቃል ኪዳንሽ የንግድ ወራት አልቆ ወረት በተቋጠረ ጊዜ መጠጊያ ይሁነኝ፡፡

፴፮፤ ለፀዓተ ነፍስኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ የሚያስፈራ መልአክ ሞት ጥቁር ጥላውን ሳይጥልብሽ ኅሱም ራእዩን ሳያሳይሽ የብርሃንን
ጸዳል ለማየት ብቻ ለተለየችው ፀዓተ ነፍስሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ሞት ከሥጋዬ ለይቶ በወሰደኝ ጊዜ ከሦስቱ አስደንጋጭ ነገሮች በቃል ኪዳንሽ ታድኚኝ ዘንድ
በእግዚአብሔር የመለኮቱ ባሕርይ እማልድሻለሁ፡፡

፴፯፤ ለበድነ ሥጋኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ የአብ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ፈጥኖ አስነሥቶታልና በመካነ መቃብር ፈጽሞ
ላልዘገየው በድነ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ጻድቃንን ብታድኛቸው ድንቅ ተብሎ ስለማይነገርልሽ፡፡ ዕፁብ ድንቅ ተብሎ ይነገርልሽ ዘንድ
በቃል ኪዳንሽ ጥበብ ኃጥኣንን ለማዳን ተፋጠኝ፡፡

፴፰፤ ለግንዘተ ሥጋኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በልዩ ምስጋና በበፍታና በሽቱ በጴጥሮስ እጅ ለተገነዘው ግንዘተ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ እኔ የኃጥኣንን ቅባት አልቀባም ብያለሁና ቃል ኪዳኔን ለምን ተስፋ ታደርጋለህ ርዳታዬንስ
ስለምን ትፈልጋለህ ሳትይ በችግሬ ጊዜ ፈጥነሽ በመድረስ ይቅርታ አድርጊልኝ፡፡

፴፱፤ ለመቃብርኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ የምድር አሕዛብ ሁሉ ለሚሰበሰቡባት መካነ መቃብርሽ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ በኔ ሟች የምሆን አገልጋይሽ በሞቴ ሰዓት ፈጥነሽ ድረሽልኝ ከክርስቲያን ወገን አንዱ ወይም
አንዲቱ ስትሞት በዚያ ነፍስን ለማረጋጋት አንች ፈጥነሽ ትደርሻለሽና፡፡

፵፤ ለትንሣኤ ሥጋኪ፡፡
እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል የክርስቶስ የትንሣኤው ምሳሌ ለሚሆን
የሥጋሽ ትንሣኤ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ ባለቤት ሆይ፤ የአባታችን የአዳም የጥንት የመዳኑ ተስፋ አንች ነሽ እኮን፤ ቃል ኪዳንሽና ጸሎትሽ ከርሱ ጋር
ባይኖርስ ኖሮ በነፍሱም በሥጋውም በዚያው በጥፋት ጨለማ ጉድጓድ ውስጥ ተደፍኖ በቀረ ነበር፡፡

፵፩፤ ለፍልሰተ ሥጋኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ከዚህ በፊት የልጅሽ ሥጋ ወደ ፈለሰበት ወደ አዲሱ የሕይወት ሕንፃ አዳራሽ ለተዛወረ
የሥጋሽ ፍልሰት ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ የዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ሆይ፤ ነፍሴን በቃል ኪዳንሽ ታድኛት ዘንድ እማልድሻለሁ፡፡
በመድኃኒት ዐዋቂነትሽ መድኃኒተ ፈውስ ቁስሌን ቀብተሽ አድነሽኛልና፡፡

፵፪፤ ነአኩቶ ለእግዚአብሔር፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በችግረኞች ጉባኤ መካከል የመታሰቢያሽን ቃል ኪዳን እነግር ዘንድ በቸርነቱ ጥሪ
የጠራን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ ስለሆነም እመቤቴ ማርያም ሆይ፤ በዚህ በዐርባ ሁለቱ ድርሳናተ መልክእሽ የሚጸልየውን ሁሉ
በትንሣኤ ጊዜ በክብር ተቀብለሽ በሕያዊት ነፍሱ ራስ ላይ የሰማያዊን አክሊለ መንግሥት አቀዳጂው፡፡

፵፫፤ ስብሐት ለኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ወላዲ በሚሆን እግዚአብሔር አብ፤በሚመሰገንበት ገንዘብ ላንቺ ምስጋና ይገባል፡፡ ተወላዲ
በሚሆን እግዚአብሔር ወልድ በሚመሰገንበት ገንዘብ ላንቺ ምስጋና ይገባል፡፡ ያልተወለደ ሠራፂ
በሚሆን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በሚመሰገንበት ገንዘብ ላንቺ ምስጋና ይገባልና ከጠላት ሰይጣን መከበብ
በየቀኑና በየሰዓቱ ትጠብቂኝ ዘንድ ለዘላለሙ ደግሜ ደጋግሜ በቃል ኪዳንሽ እማፀናለሁ፡፡

፵፬፤ ሰላም ለኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ ሰላምታ ላንቺ ይገባል፡፡ አለኝታ ተስፋዬ ነሽና ሰላምታ ላንቺ ይገባል፡፡ ኃጥኣንን አማልደሽ
የምታጸድቂ ላንቺ ሰላምታ ይገባል፡፡ ከዘጠናው በጎች ተለይቶ የጠፋ በግ አዳምን የምትፈልጊ ላንቺ ሰላምታ ይገባል፡፡

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ፤ የምሕረት ቃል ኪዳን ምልክት ትሆኝ ዘንድ ጌታ እንደጽኑ ሐውልት አድርጎ ያቆመሽ ላንቺ
ሰላምታ ይገባል፡፡ ፍቅርን የሚያጸና ለፍጥረቱ ሁሉ የማዳን ምልክት ለሆንሽ ላንች ሰላምታ ይገባል፡፡

፵፮፤ ሰላም ለኪ፡፡

እመቤቴ ማርያም ሆይ፤ ከገንዘብ ሁሉ ክብር ያለው ወርቅ ነሽና ሰላምታ ላንች ይገባል፡፡ የችግረኞች መዝገብ የሰማያዊም
ብልጽግና ነሽና ሰላምታ ላንች ይገባል፡፡

፵፯፤ ሰላም ለኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ የሚዛኑ ክብደት በውሃ የምታስለውጭ ላንቺ ሰላምታ ይገባል፡፡ ድንግል ሆይ በአንቺ
መታመኔን እንደ ልዩ ትሩፋትና ሥነ ተጋድሎ አድርገሽ ቁጠሪልኝ፡፡

፵፰፤ ሰላም ለኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ በጎ ሥራ በመሥራትና በትሩፋተ ገድል ለመጽደቅ በተሳነኝ ጊዜ አንቺን መጠጊያ መከታ
አድርጌሻለሁና ላንቺ ሰላምታ ይገባል፡፡ ድንግል ሆይ የቃል ኪዳነ ባለቤት ነሽና ነፍሴን ከጥፋት አድኛት፡፡
፵፱፤ ሰላም ለኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ የሰማያዊ መንግሥት መገኛ መድኅን ነሽና ላንቺ ሰላምታ ይገባል፡፡

ድንግል ሆይ፤ አንችን የሚወድ ፍጹም ዋጋውን ለማግኘት በተስፋ ይኖራልና ሰላምታ ይገባሻል፡፡

፶፤ ሰላም ለኪ፡፡

እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት ሆይ፤ እንደ ቃል ኪዳንሽ ምስጋናሽ የሚነገርበትን ቤተ ክርስቲያን በስምሽ ያሳነፀውን
መታሰቢያሽን ያደረገውን በስምሽ የጸለየውን ከበረከትሽ ታሳትፊውና ይቅር ባይ ከሚሆን ልጅሽ ይቅርታን ታሰጭው
ዘንድ ሰላም እያልኩ ከፊትሽ ወድቄ በቃል ኪዳንሽ እማፀንሻለሁ፡፡

፶፩፤ እመቤቴ ማርያም ሆይ፤ በክፉ ሰዎች እጅ ከመውደቅ በቃል ኪዳንሽ ጠብቂኝ፡፡ በልዩ ጠላት በዲያብሎስ ወይም
በሰይጣን ኃይል ተይዞ ከመቀጥቀጥ በእግረ አጋንንት ከመረገጥና ከመጠቅጠቅ አድኚኝ ለዘላለሙ አሜን፡፡

You might also like