Download as docx, pdf, or txt
Download as docx, pdf, or txt
You are on page 1of 10

በሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ረገድ የታዩ እመርታዎች

ሴቶች የአንድ ሀገር የእድገት መሰረትና የማህበረሰቡም የጀርባ አጥንት መሆናቸው ቢታወቅም ባለፉት ስርዓቶች በነበሩ
ኢ-ዴሞክራሲያዊ አገዛዞች፣ በህብረተሰቡ ዘንድ በነበሩ ኋላ ቀር አመለካከቶችና እስካሁን በዘለቀው የተዛባ የስርዓተ ጾታ
ግንኙነት ሳቢያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው ዝቅተኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በ 1983 ዓ.ም በሀገሪቱ የስርዓት ለውጥ ከተካሄደ ወዲህ የሀገራችን ሴቶች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች
እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል አግኝተዋል፡፡ በሁሉም መስኮች እንዲሳተፉና በተሳትፎኣቸው መጠንም
እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሀገራችን ሴቶች የተፈጠሩላቸውን ምቹ ሁኔታዎች
ተጠቅመው የደረሱበት እድገትና ለውጥ ለለውጡ የተከናወኑ ተግባራትን ማየት ተገቢ ነው፡፡

መንግስት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን
አከናውኗል፡፡ ያከናወናቸውን ተግባራት የፖሊሲና የህግ ማእቀፎችን ከመቅረጽ፣ የስርዓተ ጾታ ማካተት፣ ዓለም አቀፍ
ስምምነቶች፣ የትብብርና የቅንጅት ስራዎች፣ የነሱን ጉዳይ በበላይነት የሚመራ መዋቅር ከመዘርጋትና በሴቶች ዙሪያ
የሚሰሩ አደረጃጀቶችን በመፍጠርና በማጠናከር ረገድ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና
ተጠቃሚነታቸውን ከማሳደግ አኳያ ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

የፖሊሲና የህግ ማእቀፎችን ማበጀት

ከ 22 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ሴቶችን የሚመለከት ፓሊሲ አልነበረም፡፡ በሀገራችን የሴቶችን እኩል ተሳታፊነትና
ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስትራቴጂዎችም አልነበሩም፡፡ የሴቶችን ጉዳይ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ፕሮግራሞችና
እቅዶች ውስጥ ተካቶ (Mainstream) እንዲሰራ የሚያስችል መመሪያና አሰራርም እንዲሁ፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራችን የሴቶችን ጉዳይ የሚከታተል ፓሊሲ በ 1986 ዓ.ም ተቀርጾ ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡
የፖሊሲው መቀረጽ ዋና ዓላማም የሴቶችን የስርዓተ ጾታ እኩልነት በማስፈንና በቤት ውስጥ ያለባቸውን የስራ ጫና
በመቀነስ የኢኰኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ነው፡፡

ፓሊሲውን ተከትሎ ለሴቶች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት መረጋገጥና ለሴቶች መብት መከበር የመሰረት ድንጋይ
የጣለው ህገ መንግስት በ 1987 ዓ.ም ተቀርጿል፡፡ ህገመንግስቱ በአንቀጽ 25 ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል መሆኑን የደነገገ
ሲሆን መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶችንና ነጻነቶችን በሚደነግገው ምዕራፍ ሦስትም በማንኛውም ሰው ላይ በዘር፣
በሀይማኖት፣ በቋንቋና በጾታ አድሎ የማይደረግ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ በአንቀፅ 35 ንዑሰ አንቀፅ 3 ላይ ለሴቶች የልዩ
ድጋፍ ርምጃን የደነገገ ሲሆን ንዑሰ አንቀፅ 4 በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ማናቸውም ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመፃረር
የሴቶችን መብት ያረጋግጣል፡፡ 35 ንዑስ ቁጥር 6 ደግሞ መንግስት በሚወስዳቸው ማናቸውም ርምጃዎች ላይ የሴቶችን
የማማከር መብት የሚያስከብር ነው፡፡

1
የሴቶች ጉዳይ ስትራቴጂክ ትኩረት እንዲያገኝ ደግሞ በፕሮግራም ደረጃ የሴቶች የልማትና የለውጥ ፓኬጅ ተቀርጾ
እየተተገበረ ይገኛል፡፡ የሴቶች የልማትና የለውጥ ፓኬጅም ሴቶች በሀገሪቱ በሚካሄደው ልማት ንቁ ተሳታፊና
ከውጤቱም እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ በየደረጃው እኩል ፖለቲካዊ ተሳታፊና የውሳኔ ሰጪነት ስልጣን እንዲኖራቸው፣
በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና በህገመንግስቱ ዙሪያ በዘላቂነት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በ 1998 ዓ.ም
ተዘጋጅቶ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ በዚህም ባለፉት ዓመታት በሴቶች ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት አበረታች
ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ለሴቶች መብት መከበር የወጡ ሌሎች ህጐችም አሉ፡፡ በ 2000 ዓ.ም ተሻሽለው የወጡት የፌደራልና የክልሎች የቤተሰብ
ህጐች ይገኛሉ፡፡ የቤተሰብ ህጐቹ እንዲሻሻሉ መደረጋቸው የነበሩ የህግ ክፍተቶችን በመቅረፍ የሴቶችን ጥቅም
አስጠብቋል፡፡ ቀደም ሲል በፍታብሄር ህጉ ሴት በ 15 እና ወንድ በ 18 ዓመት እድሜ ጋብቻ እንዲፈጽሙ የተቀመጠውን
ድንጋጌ በመሻር ለሁለቱም ጾታዎች የጋብቻ እድሜ 18 ዓመት እንዲሆን መደረጉና የቤተሰብ ህጉ ሴቶች ጋብቻ
ሲመሰርቱ ጋብቻው ፀንቶ በሚቆይበት ጊዜና ጋብቻው ሲፈርስ ያላቸውን መብት በግልፅ ማስቀመጡ፣ በንብረት
አስተዳደርም ሆነ በንብረት ክፍፍል ላይ እኩል መብት ያላቸው መሆኑንና ከመደበኛው ጋብቻ ውጪ አብረው የሚኖሩ
ሴቶችን መብት ማረጋገጡ ለዚህ አስረጂ ነው፡፡ በተለይም በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ወንጀል
ናቸው ብሎ ከመፈረጁ ባሻገር የሚያስከትላቸውን ቅጣት አስቀምጧል፡፡ በድሮው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ የተቀመጡ
የቅጣት ደረጃዎችንም አሻሽሏል፡፡ በድሮው የወንጀል ህግ ጠለፋን ወንጀል እንደሆነ ቢደነግግም ካገባት ወንጀል አይሆንም
በሚል ነበር ያስቀመጠው፡፡ በተሻሻለው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ግን ቢያገባትም ተጠያቂ እንደሚሆን አስቀምጧል፡፡

የአሰሪና ሰራተኛ ህጉም በህገ-መንግስቱ የተቀመጡትን የሴቶች መብቶች አስከብሯል፡፡ በዋናነትም ከወሊድ ጋር ተያይዞ
ተገቢውን የዕረፍት ጊዜ በመስጠት ምቹ የስራ ሁኔታ እንዲኖር አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የሲቪል ሰርቪስ አዋጅ
ሴቶች በቅጥር፣ በወሊድና በስራ ውድድር ጊዜ ለሴቶች ቅድሚያ በመስጠት የልዩ ድጋፍ እርምጃ ያደርጋል፡፡

ተሻሽሎ የወጣው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 691/2003 ማንኛውም ተቋም በተለይ የፌደራል
ተቋማት የሴቶችና ወጣቶችን ጉዳይ በፕሮግራሞቻቸውና በእቅዶቻቸው አካተው እንዲተገብሩ የጣለው ግዴታ የሴቶች
ጉዳዮች ይበልጥ ትኩረት አግኝተው በፖሊሲና እቅዶች አተገባበር ውስጥ ትኩረት እንዲሰጣቸው አድርጓል፡፡

የስርዓተ ጾታ ብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር (National action plan on Gender) ከ 2006 እስከ 2010 ድረስ ይተገበር
ነበር፡፡ በድህነት ማስወገጃ ስትራቴጂ (PASDEP) በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ (GTP)
የሴቶች ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ትኩረት እያገኘ መጥቷል፡፡

የሴቶችን ጉዳይ የሚከታተሉ መዋቅሮች ዝርጋታ

መንግስት የሴቶች ጉዳይ ልዩ ትኩረት አግኝቶ /በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ/ በአግባቡ ምላሽ እንዲሰጠውና ሀገራዊ
የሴቶች የልማት እንቅስቃሴ ወጥ በሆነ፣ በተጠናና በተቀናጀ አሰራር እንዲመራ የሚያስችሉ ተቋማትን በፌዴራልና
በክልል ደረጃ ፈጥሯል፡፡ ይህ ተግባር በ 1985 ዓ.ም ሲጀመር በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የሴቶችን ጉዳይ የሚመራበት
አካል ሴቶችን በልማት /women in development በሚል በጽ/ቤት ደረጃ እንዲቋቋም የተደረገ ሲሆን ይህም የሴቶችን

2
የልማት ጥያቄዎች፣ ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ ሊሰሩ ስለሚገቡ ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጥና በኋላም ብሄራዊ የሴቶች
ፖሊሲ እንዲቀረጽ በር ከፍቷል፡፡

በሂደት በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን በኃላፊነት
ይዞ የሚመራ ተቋም በሚኒስቴር ደረጃ በ 1998 ዓ.ም ተቋቋመ፡፡ የተቋሙ መመስረትና ከፌደራል እስከ ወረዳ ድረስ
መዋቅር መዘርጋት መንግስት ሴቶች በየደረጃው ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብትና በውሳኔ ሰጭነት እንዲሳተፉ
ቁርጠኛ መሆኑን ያረጋገጠበት ነው፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ቀደም ሲል ቀድሞ የማህበራዊ ጉዳይ ኮሚቴ አሁን ደግሞ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች
ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በማቋቋም የአስፈጻሚውን አካል እንቅስቃሴ በመከታተልና በመደገፍ በኩል እየተሰራ ይገኛል፡፡

በእንባ ጠባቂና በሰብአዊ መብት ኮሚሽን ውስጥ የሴቶችን ጉዳይ የሚከታተል መዋቅር ራሱን ችሎ እንዲቋቋም
ተደርጓል፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የሴቶች ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ከማድረግ አንፃር የስርዓተ ጾታ ጽ/ቤቶች
ተቋቁመዋል፡፡ በፍትህ አካላትም ለሴቶች ራሳቸውን የቻሉ የምርመራና የፍትህ አሰጣጥ ችሎቶች ተቋቁመው
አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡

በስርዓተ ጾታ ማካተት

የኢፌዴሪ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ሴክተር መስሪያ ቤቶች አቅም ኑሯቸውና ራሳቸውን ችለው
የስርአተ ጾታ ጉዳይን አካተው በአግባቡ እንዲሰሩ ያግዛል፡፡ ለዚህም የማካተት ስራ ማስፈፀሚያ መሳሪያዎችን
በማዘጋጀት፣ በስልጠናና በሌሎች ዘዴዎች አቅማቸውን የማጐልበት፣ ድጋፋዊ ክትትል የማድረግና የማበረታታት
ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ሌላው ለስርአተ ጾታ ማካተት የሚረዱ ማስፈጸሚያ መሳሪያዎችን የማዘጋጀትና ማሰራጨት ስራም በመስራት ላይ
ነው፡፡ እስካሁንም የስርዓተ ጾታ ጉዳይ ማካተቻ መመሪያ፣ የስርዓተ ጾታ ኦዲት መመሪያ፣ ስርዓተ ጾታ ትንተና ኦዲት፣
የስርዓተ ጾታ ምላሽ የሚሰጥ በጀት መመሪያ ከሚመለከታቸው አከላትና ከተለያዩ ሴክተሮች ጋር በጥምረት
በማዘጋጀትና በማስተርጐም ሴክተር ተቋማትና ክልሎች እንዲጠቀሙበት እያደረገ ነው፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተጨማሪም ሴክተር መስሪያ ቤቶችን በስርአተ ጾታ ማካተት ዙሪያ ይደግፋል፣ ይከታተላል፡፡
በተለይ የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በስርአተ ጾታ ዙሪያ ግንዛቤያቸው እንዲያድግ፣ ስርአተ ጾታን አካተው
እንዲሰሩ፣ የራሳቸው የስርአተ ጾታ ማካተት ማስፈጸሚያ መሳሪያዎችን እንዲያዘጋጁ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም
ለባለሙያዎችና ለስራ ሃላፊዎች ስልጠና ይሰጣል፡፡ ወደ ተግባር ከገቡ በኋላም አፈጻጸማቸውንና የተገኘውን ለውጥ
በመገምገም ስርአቱ እንዴት እየተተገበረ እንደሆነ ድጋፋዊ ክትትል ያደርጋል፡፡

ክልሎችም በቅተው የማካተት ሚናቸውን እንዲወጡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየጊዜው ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በተለይም ልዩ
ድጋፍ ለሚሹ ክልሎች በስርዓተ ጾታ ማካተት፣ በሴቶችና ወጣቶች ፖሊሲዎችና ፓኬጆች ስልጠና በመስጠት ያላቸውን
ግንዛቤ የማሳደግ ስራ ተሰርቷል፡፡

3
አደረጃጀቶችን በመፍጠርና በማጠናከር

ባለፉት ስርዓቶች ርእዮተዓለማዊና ፖለቲካዊ አደረጃጀት በመንግስት ጥገኛ የሆነና ከሴቶች ይልቅ ላደረለት ፖለቲካዊ
ሀይል የሚንቀሳቀስ አደረጃጀት ስለነበር ሁሉንም ሴቶች በተደራጀ አግባብ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርጉ
እንቅስቃሴዎች አልነበሩም፡፡ በወቅቱ የነበሩት እንቅስቃሴዎችም መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት የሚካሄዱ ስለነበሩ ውስን
ዓለማዎችን ብቻ ለማሳካት የተደራጁ ከመሆናቸውም በላይ በከተሞች ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ በመሆኑም አደረጃጀቶቹ
በመንግስት በሚነደፉ ሕጐችም ሆነ ፖሊሲዎች ወይም የልማት ኘሮግራሞች ላይ የሴቶችን ጥቅም ለማስጠበቅ ምንም
ዓይነት ተፅዕኖ ሊያደርጉ የሚችሉበት ድርጅታዊ አቋምም ሆነ ኃይል አልነበራቸውም፡፡

ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት መንግስት ሴቶች በአንድ ድርጅት ብቻ ሳይወሰኑ ይጠቅመናል ያመቸናል ባሉት መንገድ
ሙያዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ራሳቸውን በማደራጀት ለችግሮቻቸው መፍትሄ እየፈለጉና
ፍላጎታቸውን እያራመዱ ይገኛሉ፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በገጠርና በከተማ የተለያዩ የሴት አደረጃጀቶች
ተፈጥረዋል፡፡ እነዚህ ማህበራት በፌዴሬሽን ጥላ ስር ህብረት ፈጥረው ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን እንዲሁም
መብታቸውን በሚፈለገው ደረጃ ለማረጋገጥ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

ይህም ሴቶች በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ እንዲንቀሳቀሱና ድምጻቸውን እንዲያሰሙ በማስቻሉ ተሳትፎና
ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግና ለሀገራቸው የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እንዲጎለብት መንገድ ከፍቷል፡፡

ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ የትብብርና ቅንጅት ስራዎች

ኢትዮጵያ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የተቀበለች ቢሆንም የሚከተሉትን ለዓብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የወጣው (CEDAW) በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ማናቸውንም አድሎዎችን የሚከለክለው
ስምምነት ኢትዮጵያ የተቀበለችው ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሲሆን በሴቶች መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ
ሊያሳድሩ የሚችሉ አድሎአዊ አመለካከቶችን እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ የተደረጉት ጥረቶች የሴቶችን
መብት አስከብሯል፡፡

ቤጂንግ ዲክላሬሽን ፕላት ፎርም የሴቶችን እኩልነት ማስፈን፣ ልማትና ሰላም ለሁሉም ሴቶች እንዲመጣ ያለመ ነው፡፡
ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶችን በማስፈጸም የምእተ ዓመቱን ግብ ለማሳካት የሚጥር ነው፡፡

የአፍሪካ ሶልመን የስርዓተ ጾታ እኩልነት ዲክላሬሽን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች መብት ዙሪያ የወጡ
ስምምነቶች፣ዲክላሬሽንና ፕሮቶኮል አፈጻጸም የሚያጠናክር ነው፡፡

የትብብርና የቅንጅት ስራን በተመለከተ የሴቶችን ጉዳይ በኃላፊነት የሚመራው የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ
ሚኒስቴር የሴቶችን ሁለንተናዊ ችግር ለመቅረፍ ከህብረተሰቡ ከተለያዩ አለም አቀፍና አገር አቀፍ ባለድርሻና አጋር
አካላት እንዲሁም ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ከሀይማኖት ተቋማት ጋር በትብብርና በቅንጅት ይሰራል፡፡ ከሌሎች ሀገራት
የሴቶች ማህበራትና ከሀገራት ጋር ልምድ ልውውጥ፣ በሀገር ውስጥ መልካም ተሞክሮ ማስፋት ፣ በአለም አቀፍ
መድረኮች በሴቶች በኩል ሀገሪቱ ያለችበትን ደረጃና ያሉባትን ችግሮች የማካፈል፣ ሴቶችን በሚመለከቱ አለም አቀፍና
አህጉራዊ መድረኮች ለሴቶች እኩልነትና መብቃት የሚያግዙ ዓላማዎችን በአተገባበራቸው የመሳተፍ ሁኔታ አለ፡፡

4
መንግሰት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባከናወናቸው በርካታ ተግባራት የመጣውን ውጤት
በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና ማህበራዊ ከፋፍለን እንመልከት፡፡

በኢኮኖሚው ዘርፍ

ቀደም ሲል ሴቶች ሀብት በማያስገኙ በቤት ውስጥ ስራዎች የሚያፈሱትን ጊዜና ጉልበት ሀብት መፍጠር በሚችሉበት
ስራ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ መንግስት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
በእጅ በመፍጨት፣ ረጅም ርቀት ተጉዘው ውሀ በመቅዳትና እንጨት በመልቀም የሚያባክኑትን ጊዜ በመቆጠብ
ስራቸውን የሚያቃልሉ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ባለፉት ሶስት
የእድገትና ትራንስፎርመየሽን እቅድ ዓመታት ውስጥ ብቻ አምስት ሚሊዮን ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች ተሰራጭተዋል፡፡
ስምንት ሚሊዮን ለሚሆኑ ሴቶች ደግሞ የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ተመቻችቶላቸዋል፡፡ በተወሰነ ኪ.ሜ ርቀት
የወፍጮ አገልግሎት እንዲኖር ተደርጓል፡፡ ይህም ሴቶች ከቤት ውጭ ስራ በዘለለ በተለያዩ ገቢ የሚያስገኙ የስራ መስኮች
በስፋት እንዲሰማሩ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡

ከግብርና ጋር ተያይዞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች የመሬት ባለቤት ሆነዋል፡፡ ሴቶችና ወንዶች በትዳር ውስጥ ካሉ በአንድ
ላይ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በመስጠት የመሬት ባለቤትነታቸው እንዲረጋገጥ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም
ሴቶች በግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አኳያ እ.ኤ.አ በ 2013 3‚389‚000 የገጠር ሴቶችና
14‚879 የከተማ ሴቶች በግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍም እ.ኤ.አ በ 2011 48.4% ሴቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በስራ ፈጠራ በገጠርና በከተማ
የሚኖሩ ሴቶችን እንዲደራጁ በማድረግና በተናጠል በገቢ ማስገኛ ተግባራት እንዲሰማሩ ከማድረግም ባሻገር
ለሚያመርቷቸው ምርቶች የገበያ ትስስር በመፈጠሩ ሴቶች ከድህነት በተጨባጭ ወጥተዋል፡፡

የሴቶችን ገቢ ማሳደግ ብቻም ሳይሆን እንዴት መምራትና ማስተዳደር እንደሚችሉ የህይወት ክህሎት ስልጠናዎች
በየጊዜው እተሰጣቸው ይገኛል፡፡ ሴቶች ብድር ወስደው ገበያቸውን እንዲያሳድጉና የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ
በየአቅራቢያቸው ብድር የሚሰጡ ተቋማት ተመቻችተው አገልግሎት እያገኙ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በ 2005 በጀት
ዓመት በ 9 ወር ብቻ 1.2 ቢሊዮን ብር ለሴቶችና ለወጣቶች ብድር የተሰጠ ሲሆን ከ 1.2 ቢሊዮን የብድር አገልግሎት
ውስጥ ከ 48% በላይ የወሰዱት ሴቶች ናቸው፡፡ ባለፉት 22 ዓመታት በርካታ ሴቶች በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በብድር
ወስደው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣት ችለዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን አሳድገው ከድህነት
የወጡ አልፎ ተርፎም ሀገራዊ ሚናቸውን እየተወጡ ያሉ እንስቶች ተፈጥረዋል፡፡

በማህበራዊ ዘርፍ

ሴቶች ለማህበራዊ አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆኑና ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግ ባለፉት ሁለት
አስርት ዓመታት በተለያዩ መስኮች በርካታ ተግባራት ሲተገበሩ የቆዩ ሲሆን በዚህም አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ትምህርት

5
መንግስት ትምህርት ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት የሚበጁ ዜጎችን የሚያፈራና የፈጣን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት
መሆኑን በማመን "ትምህርት ለሁሉም" በሚል መርህ በተለይም በትምህርት ዘርፍ የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ
ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ከገቡ በኋላም እንዳያቋርጡ ጥረት እየተደረገ
ነው፡፡ በተለይም ለሴት ተማሪዎች እንቅፋት የሆኑ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስቀረት፣ በትምህርት ቤቶች ውስጥ
የሴቶች ክበባት እንዲቋቋሙ በማድረግ ትምህርት ቤቶች ለሴት ተማሪዎች ምቹ እንዲሆኑ በርካታ ተግባራት
ተከናውነዋል፡፡

ሌላው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል፡፡ በየቀበሌው አንድ የመጀመሪያ ት/ቤት
ለማቋቋም ግብ ጥሏል፡፡ ከዚህ አኳያ በ 2004/5 16,513 የነበረውን የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ቁጥር በ 2011/12 ወደ
29,482 አሳድጓል፡፡ በ 1995/96 3.8 ሚሊዮን የነበረው የተማሪዎች ቁጥርም በ 2006/07 14 ሚሊዮን እና በ 2011/12
ወደ 16.6 ሚሊዮን አድጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ 43.5% ሴቶች ናቸው፡፡ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ያለው የሴቶችና የወንዶች
ቁጥር በመመጣጠኑ ግቡን ማሳካት ተችሏል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርትና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉበት
ደረጃም እንዲሁ አድጓል፡፡ የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ በንጽጽር እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

እ.ኤ.አ. በ 1989 የነበረው የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ

ተ.ቁ ደረጃ ተሳትፎ በፐርሰንት


1 በአንደኛ ደረጃ 30%
2 በመለስተኛ 2 ኛ ደረጃ 41%
3 በሁለተኛ ደረጃ 30%
4 በዲፕሎማ 14.5%
5 በዲግሪ 8.2%
6 በድህረ ምረቃ 6.4%

እ.ኤአ በ 2011/12 በየደረጃው የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ

ተ.ቁ ደረጃ ተሳትፎ በፐርሰንት


1 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት 92.9%
2 ሁለተኛ ደረጃ /9 - 10/ 34.6%
3 ሁለተኛ ደረጃ /11 - 12/ 42.9%
4 ቴክኒክና ሙያ ስልጠና 47.7%
5 በቅድመ ምረቃ 28.2%
6 ድህረ ምረቃ 20.11%

6
በየደረጃው የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ በማሳደግ የሴቶችንና የወንዶችን ቁጥር እንዲመጣጠን ከማድረግ ጎን ለጎን ሴቶች በሳይንና
በሂሳብ ትምህርቶች እንዲሳተፉና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያበረታቱ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡

ጤና፡-

በሀገራችን የስነተዋልዶ ጤና እና የጤና አገልግሎቶችን ለሴቶች ተደራሽ ለማድረግ የፖሊሲና የፕሮግራም ማእቀፎች
ተዘጋጅተዋል፡፡ ብሄራዊ የጤና ፖሊሲ፣ የጤና ሴክተር ስትራቴጂ፣ ብሄራዊ የስነ ተዋልዶ ጤና ስትራቴጂ /2000- 2015/
እንዲሁም መከላከልን መሰረት ያደረገው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም መተግበርና የጤና ተቋማት መስፋፋት በዋናነት
ይጠቀሳሉ፡፡

በተጨማሪም የጤና መሰረተ ልማት ከማስፋፋት አኳያ በተለይም ህብረተሰቡ በ 10 ኪሜ ርቀት ላይ የጤና ኬላ
አገልግሎት ተጠቃሚ እየሆነ መምጣት፣ በጤና ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ቁጥር ማደግ፣ ሴቶች በአንድ ለ አምስት
አደረጃጀት ተደራጅተው በመንቀሳቀሳቸው፣ የስነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤ እያደገ መምጣት፣ ሴቶች ለኤች አይ ቪ/ኤድስ
ያላቸውን የበለጠ ተጋላጭነት ለመቀነስ በቫይረሱ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች ላይ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ
ተሰርቷል፡፡ እንዲሁም ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ
ተፈጥሯል፡፡ የተላላፊ በሽታዎችን በመቆጣጠር ረገድ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ
መጥቷል፡፡

በዋናነት መከላከልን መሰረት ባደረገው የጤና ፖሊሲ ስር የሚገኘው የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ተግባራዊ መደረግ
ከጀመረ ወዲህ የጤና ኤክስቴንሽ ባለሙያዎች ቤት ለቤት በመሄድ የገጠሩን የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ሴቶችን
በ 16 ቱም የጤና ፓኬጆች ላይ የመረጃና የእውቀት ባለቤት አድርገዋል፡፡ ግንዛቤያቸው አድጎ ሙሉ በሙሉ ለውጥ ያመጡ
ቤተሰቦችንም በሞዴልነት በማስቀመጥ አርአያ እንዲሆኑና እርስ በእርሳቸው የሚማማሩበትን እድል ፈጥሯል፡፡ በገጠር
አካባቢ ተግባራዊ ሆኖ ውጤታማ የሆነውን የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተሞች እንዲተገበር
በመደረጉም ለጤና ልማቱ መሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

የነዚህ የጤና ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ተግባራዊ በመደረጋቸውና የጤና ተቋማት መስፋፋት እንዲሁም ሌሎች
ተግባራት በመከናወናቸው በጤና ልማት ዘርፉ የሚበረታታ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ እናቶች ከወሊድና ከእርግዝና ጋር
ያላቸው ግንዛቤ አድጓል፡፡ በእርግዝና ወቅትና ከወሊድ በኋላ ክትትል የሚያደርጉና በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች
ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከዚህ አንጻር በ 2005 ዓ.ም የነበረው 83% የቅድመ ወሊድ አገልግሎት በ 2006 ዓ.ም ወደ
97% እና 43% የነበረው የድህረ ወሊድ አገልግሎት ሽፋን ወደ 51.7% ሊድግ ችሏል፡፡ በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች እገዛ
የሚወልዱ እናቶች መጠንም በ 2005 ዓ.ም የነበረው 16.4% በ 2006 ዓ.ም 29% መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር
የስድስት ወር እቅድ አፈጻጸም ያመለክታል፡፡ ይሀም የእናቶችና የህፃናትን ሞት በእጅጉ ቀንሷል፡፡ እ.ኤ.አ በ 2011
የተካሄደው የስነ ህዝብና ጤና ጥናት በ 2000/01 871 የነበረውን የእናቶች ሞት በ 2010/11 ወደ 676/100,000 ዝቅ እንዳለ
አሳይቷል፡፡

እ.ኤ.አ 2000/01 የመጀመሪያ አመት ልደታቸውን ሳያከብሩ የሚሞቱ ህጻናት ከአንድ ሺህ ህጻናት 97 የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ
2005/06 ወደ 77 2009/10 ደግሞ ወደ 45 ቀንሷል፡፡ ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናት ሞት መጠን ከአንድ ሺህ ህጻናት

7
ውስጥ እ.ኤ.አ 2000/01 167 የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ በ 2005/06 ወደ 123 እ.ኤ.አ በ 2011 ደግሞ ወደ 88 ዝቅ ብሏል፡፡ በዚህ
ውስጥ በርካታ ሴት ህጻናት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

የሴቶች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት አጠቃቀም ግንዛቤ እያደገ የመጣ ሲሆን በዚህም በ 2010/11 የቤተሰብ ምጣኔ
አገልግሎትም 29% መድረሱን ጥናቱ ያሳያል፡፡ ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚጠቀሙ በተለይም እድሜያቸው በ 15
ና በ 49 መካከል የሚገኝ ሴቶች እ.ኤ.አ በ 2000 6.3% የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ በ 2011 ወደ 18.7% ከፍ ብሏል፡፡

ከኤች.አይ ቪ/ኤድስ ጋር በተያያዘ አበረታች ለውጥ መጥቷል፡፡ እድሜያቸው በ 15 እና 24 ዓመት መካከል የሚገኙ
ነፍሰጡር ሴቶች በቫይረሱ የመጠቃት መጠን እ.ኤ.አ በ 2005 ከ 5.6% የነበረው እ.ኤ.አ በ 2007 ወደ 3.5% እና እ.ኤ.አ
በ 2011 2.6% ዝቅ ብሏል /2012 HAPCO/ ፡፡ ሌላው በ 2010 9.3% ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የነበረው
ሽፋን በ 2011 ወደ 25.5% ከፍ ሊል ችሏል፡፡

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ከመከላከልና ከማስወገድ አኳያ በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በዚህም
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል፡፡ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አስወጋጅ ኮሚቴ እ.ኤ.አ በ 2008 ባካሄደው ሀገር
አቀፍ ጥናት 74% የነበረው የሴት ልጅ ግርዛት ወደ 53% ቀንሷል፡፡ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የ 2010 ጥናት
ወደ 37% የወረደ ሲሆን በቀጣይም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን ወደ 0.7% ለመቀነስ ግብ ተጥሏል፡፡

ያለእድሜ ጋብቻና ጠለፋ በተመለከተም እንደሀገር የሚበረታታ ውጤት የመጣ ቢሆንም ለውጡ ከክልል ክልል ይለያያል፡፡
እ.ኤ.አ በ 2008 በተካሄደ ጥናት በደቡብ ክልል 18.7% የነበረው ያለእድሜ ጋብቻ ወደ 9.9% እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ
ክልል 50.1% የነበረው የሴት ልጅ ግርዛት 31.9% ወርዷል፡፡

እ.ኤ.አ በ 2008 በተካሄደ ጥናት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠለፋ ከነበረበት 26% ወደ 11% የቀነሰ ሲሆን በትግራይ ክልል
ደግሞ ከ 13.9% ወደ 5.9 % ቀንሷል፡፡

በፖለቲካው ዘርፍ፡-

በፖለቲካው ዘርፍም የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገና እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ቀደምት የነበሩት ስርዓቶች የልማት
ሀይል የሆኑትን ሴቶች ያላቸውን እምቅ እውቀትና አቅም በቤት ውስጥ ብቻ ታጥሮ እንዲቀር ከማድረጋቸው የተነሳ
ከትንሽ የአካባቢ ጉዳይ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ጉዳዮች ውስጥ በሀሳብም ሆነ በውሳኔ ሰጭነት ተሳትፏቸው
እጅግ አነስተኛ ነበር፡፡

በአሁኑ ሰዓት ግን ተጭኗቸው ከነበረው ተጽዕኖ ቀስ በቀስ እየተላቀቁ በመምጣት በቤተሰብ፣ በህብረተሰብና በተቋማት
የውሳኔ ሰጭነትና የአመራር ሚናቸው እያደገ ይገኛል፡፡ በቤተሰብ ደረጃ የመደራደር አቅማቸው ያደገ ሲሆን በማህበራዊ
ጉዳዮች ዙሪያ የሚጫወቱት ሚና እየጎለበተ መጥቷል፡፡ በተቋማት ረገድ በህግ አውጪው፣ በህግ ተርጓሚው እንዲሁም
በአስፈጻሚ አካላት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ ይገኛል፡፡ በየደረጃው የሴቶች የውሳኔ ሰጭነትና የአመራር ብቃት
ከመጎልበቱም በላይ ከአመት አመት ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል፡፡

8
ሴቶች በፓርላማ ያላቸው ተሳትፎ በ 1987 ዓ.ም በመጀመሪያው ሀገራዊ ምርጫ 15 ሴቶች /2.7%/፣ በ 1992 ዓ.ም
ሁለተኛው ሀገራዊ ምርጫ 42 ሴቶች /7.7%/ ፣ በ 1997 ዓ.ም ሶስተኛው ሀገራዊ ምርጫ 117 ሴቶች /21.4%/፣ በ 2002
ዓ.ም አራተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሴቶች ቁጥር ወደ 152 /27.9%/ ደርሷል፡፡ በክልል ምክር ቤቶች ደግሞ ከ 30% ወደ
50% አድጓል፡፡

ተ/ቁ ፍ/ቤት በቁጥር በፐርሰንት


1 ጠቅላይ ፍ/ቤት 1 4%
2 ከፍተኛ ፍ/ቤት 7 13.7%
3 መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት 24 28.57%
እ.ኤ.አ በ 2012/13 ሴቶች በፌዴራል ፍ/ቤቶች በዳኝነት ያላቸው ተሳትፎ

በመንግስት ተቋማት በፌዴራል ደረጃ በ 2005 ዓ.ም ያለውን የውሳኔ ሰጭነት ድርሻ ስንመለከት ሶስት በሚኒስቴር ፣
አራት በሚኒስቴር ዴኤታና ስምንት በአምባሳደር ደረጃ ተሹመው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከመንግታዊ ተቋማት
ውጪም ሴቶች በህዝብ ተቋማትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በአመራር ቦታዎች ላይ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ሁሉ ለውጦች በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ጥረት ብቻ የመጡ ሳይሆን ሴቶች በተናጠልና
በተደራጀ ሁኔታ የራሳቸውን ተሳታፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባደረጉት ትግል ጭምር ነው፡፡ የሴቶች ማህበራት
ለመብቶቻቸው መከበር፣ ችግሮቻቸውን በመፍታት ረገድ በየጊዜው ያደርጓቸው የነበሩት ትግሎች ለለውጡ አስተዋፅኦ
አድርገዋል፡፡ በተለይ የቤተሰብ ህጉ፣ የወንጀል ህጉ፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ህጉ እንዲሻሻሉና የሴቶችን ጉዳይ የሚከታተል
ተቋም እንዲቋቋም መደረጉ ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡

ያጋጠሙ ችግሮችና የወደፊት አቅጣጫዎች

የሴቶችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድ አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡ
ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃና ፍጥነት አድጓል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በማህበረሰባችን ለዘመናት ተንሰራፍቶና
ስር ሰዶ የቆየው ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የማየት አመለካከት በቀላሉ መቅረፍ አለመቻል፣ እስካሁን ድረስ በተለይም
በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍል የሚገኙ ሴቶች የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሰለባ መሆናቸው እንዲሁም አደረጃጀቶች
የሚጠበቀውን ያህል ያለመጠናከር፣ የፋይናንስ፣ በየደረጃው ያለ የማስፈጸም አቅም ማነስ፣ የቅንጅትና የትብብር
በተገቢው ሁኔታ ያለመኖር ይጠቀሳሉ፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ፈቶ በሚፈለገው ፍጥነት ለውጥ ለማምጣት ካለፉት ሁኔታዎችና ተሞክሮዎች በመማር የሴቶች
ጉዳይ ሲባል ችግሩ የሴቶች ብቻ ሳይሆን መፍትሄውንም ሴቶች ብቻቸውን የሚፈልጉለትና የሚፈቱት አለመሆኑንና
በአጠቃላይ የህብረተሰቡ ችግር እንደሆነ በመገንዘብ ህብረተሰቡ መንግስትና እራሳቸው ሴቶች በአንድነት በተቀናጀ
መልኩ ሲሰሩ ብቻ መሆኑን በማመን ወደፊት በተቀናጀና በተናበበ መልኩ መንቀሳቀስ ይገባቸዋል፡፡

9
መንግስት ሴቶችን በማብቃት ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በጀመረው ፍጥነት ሊራመድ ይገባል፡፡
በተለይ ደግሞ አደረጃጀቶች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ አቅማቸውን በየጊዜው ከማሳደግ ጎን ለጎን ከአጋር
አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር ተገቢ ነው፡፡

10

You might also like