Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 10

እንታረቅ

የልጆች የዕርቅ ስርዓት

አዘጋጅ፡- ነፃነት ሰለሞን (ሙሉ)

የመወዳደሪያ ቁጥር፡- 0406

ሰኔ 7, 2012 ዓ.ም

“የዕርቅ ሀሳብ አለኝ” ቲኪቫህ ኢትዮጲያ


ምስጋና

ከሁሉም በቅድሚያ የዕርቅ ምሳሌ ሆኖ በልጁ የታረቀንን እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ፡፡ ተበዳዩ


እሱ ሆኖ በመስቀል ሞት ታርቆናልና ምስጋናና ክብር ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ይሁን፡፡
በመቀጠልም ይህን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ሰዓት በምክር እና በማበረታታት ለደገፉኝ ለእናቴ ሙሉ
ኢያሱ፣ እህቶቼ ስጦታና አዲስህይወት፣ ፍቅረኛዬ ከጸባኦት፣ ወንድሜ ካሌብ ታገሰ፣ እጅግ ናዓለምነሽ
ከልቤ የሆነ ምስጋና ይድረሳችሁ፡፡ ድጋፋችሁ ከንቱ አልሆነም፤ ይኸው ዛሬ ተወልዷል፡፡
ይህንን “የዕርቅ ሀሳብ አለኝ” የተሰኘ ራዕይ ሰንቆ ለተነሳው ቲኪቫህ ኢትዮጲያ ከልብ የሆነ
ምስጋና ይድረሰው፡፡

i
መሿለኪያ

ዕርቅ ለሀገራችን ኢትዮጲያ እንግዳ አይደለም፤ ቤተኛ ሆኖ ለዘመናት አብሮን ኖሯል፡፡


አብዛኛውን የዕርቅ ስርዓት መኖሩን እንኳን ሳንገነዘብ እና ተገቢውን ቦታ ሳንቸረው ጊዜያቶች
ተቆጥዋል፡፡ ከነዚህም አንዱ በልጆች መሃከል የሚደረግ የዕርቅ ስርዓት ነው፡፡ በጥናት የተደገፈ
የዕርቅ ስርዓት ባይሆንም፤ ቢጠና ግን ለሀገራችን ሰላም የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ በሙሉ
ልብ በማመን ነው፡፡
በዚህ “እንታረቅ” በተሰኘ ጽሁፍ በአብዛኛው የኢትዮጲያ ክፍል፣ በልጆች መካከል
ስለሚደረግ የዕርቅ ስርዓት በጥቂቱ ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ፡፡ ይህን የዕርቅ ስርዓት ባህላዊም ሆነ
ዘመናዊ ብሎ መፈረጅ እጅጉን አዳጋች ነው፡፡ ልጆች አብሮ የመኖር ምልክቶች፤ ሀይማኖትንና
ዘርን የሚያልፍ ሰዋዊ ግንኙነት ምሳሌ ናቸው፡፡
በዚህ መሿለኪያ ሁላችንም ወዳለፍንበት የልጅነት ዕርቅ ስርዓት፣ ወደ ልጆች ዓለም አብረን
እንድንዘልቅ ስጋብዛችሁ ከመልካም ንባብ ምኞት ጋር ነው፡፡

መልካም ንባብ
ነፃነት ሰለሞን (ሙሉ)

ii
ማውጫ
ምስጋና .................................................................................................................... i

መሿለኪያ ............................................................................................................... ii

እንተዋወቅ .............................................................................................................. 1

አካባቢው ................................................................................................................ 1

እንታረቅ ................................................................................................................. 1

መንስኤ ............................................................................................................... 2

ዕርቅ ................................................................................................................... 2

የዕርቅ ስነ-ስርዓቱ ................................................................................................ 2

የእንታረቅ አሁናዊ ገፅታ.......................................................................................... 3

ተቀባይነቱ ........................................................................................................... 3

ስለ እንታረቅ የኔ ዕይታ ....................................................................................... 3

አጠቃላይ በሀገራችን ስላሉ የዕርቅ ስርዓቶች .............................................................. 5

መደምደሚያ ........................................................................................................... 6

iii
እንተዋወቅ

ነፃነት ሰለሞን (ሙሉ) እባላለሁ፡፡ ትውልዴም እድገቴም የስኳር ምርት በማምረት ቀዳሚ
በሆነችው ወንጂ ነው፡፡ ከወለጋ ዩንቨርስቲ በኤሌክትሪካል እና ኮምፒውተር ምህንድስና
የመጀመሪያ ዲግሪ በ2010 ዓ.ም አግኝቻለሁ፡፡ አሁን ከወንጂ በትንሽ ኪ.ሜ ላይ ርቃ በምትገኝ
ሸዋ በምትባል ከተማ፣ በአማኑኤል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በእንግሊዘኛ መምህርነት
እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡

አካባቢው

ኢትዮጲያ በብዙ ባህላዊ ዕሴቶች የበለጸገች ማህፀነ ለምለም ሀገር ነች፡፡ በብዙሀኑ
ከታወቁትና ከተጠኑት በላይ ያልታወቁትና በጥናት ያልዳበሩ ብዙ ዕሴቶች አሏት፡፡ ከሰማንያ በላይ
ብሄር ብሄረሰቦች ያሉባት፣ ሰዎችን በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር አያይዛ የምትኖር ሀገር ነች፡፡
ማህበራዊ ትስስርና ማህበራዊ ግንኙት የበዛባት ሀገራችን፣ አብሮ በመኖር የመሚጡ ግጭቶችን
የተለያዩ ባህሎች ባፈራቸው ውጤታማ የግጭት አፈታት እና ዕርቅ ስርዓቶች እየፈታች በሰላማዊ
መንገድ መኖር መቀጠሏ አሁን ምስክር ነው፡፡
የልጆች የእርቅ የዕርቅ ስርዓት መገኛ ሀገራችን ኢትዮጵያ ነው፡፡ በቦታ እና በባህል የተገደበ
አይደለም፡፡ የዚህ ዕርቅ ስርዓት በመላው ሀገሪቱ ባሉ ልጆች መካከል የሚከናወን ሲሆን ዘር፣
ቀለም፣ ሀይማኖት፣ ጾታን መሰረት ያላደረገና ሰው በመሆን ብቻ የሚካሄድ የዕርቅ ስርዓት ነው፡፡
ስለዚህ አብዛኛውን የሀገራችንን ክፍል የሚሸፍን የዕርቅ ስርዓት ስለሆነ ስለተወሰነ ቦታ ከመግለጽ
ተቆጥቤያለሁ፡፡ “እንታረቅ” በልጆች ውስጥ የተደበቀ የአንድነታችን ምስክር ነው፡፡

እንታረቅ

ልጆች ከየትኛውም ዕድሜ በላይ ለጨዋታ፣ ለሳቅ፣ ለደስታ በአጠቃላይ ከሰው ጋር


ለሚደረግ ግንኙነት ቅርብ ናቸው፡፡ በበዛ ግንኙነት ውስጥ የሚፈጠር የግጭት መንስኤ፣ ሰላምን
ለማውረድ የሚደረገው የዕርቅ ስርዓትና ዕርቁን ለማፅናት የሚደረገውን ምልክት እንደሚከተለው
በዝርዝር ቀርቧል፡፡

1
መንስኤ
በተለምዶ በልጆች ዕቃቃ ተብሎ በሚጠራውና በልጆቹ መሀከል በሚደረገው ጨዋታ
በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶች ይነሳሉ፡፡ በአብዛኛውና በሁሉም ማለት በሚቻልበት ሁኔታ በልጆች
መሀል ግጭት የሚፈጠረው ከልጆቹ መሃከል አንደኛው ራስ ተኮር እንቅስቃሴ ማድረግ ሲጀምር
ነው፡፡ የሚጫወቱበትን ዕቃ አንደኛው ለብቻው ለማድረግ ሲጣጣር፤ የሚበሉትን ምግብ አንደኛው
ብቻዬን ልብላ ሲል፣ የራሱ ያልሆነን ንብረት በጉልበት ለኔ ነው የሚገባው ብሎ ለመንጠቅ
ሲሞከር እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ግጭት ይፈጠራል፡፡ እኔነትን ያጎላ ህጻን የግጭቱ መንስኤ
ይሆንና ከልጆቹ ማህበር እስከ መገለል የሚደርስ ቅጣት ይደርስበታል፡፡ በልጆች ግጭት መሃል
አልፎ አልፎ እስከ መደባደብ የደረሰ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ግን ከመኮራረፍ የዘለለ አይደለም፡፡

ዕርቅ
ከጨዋታው እና ከልጆቹ ዕቃውንና ሌላን ግዑዝ ነገር በማስበለጡ መገለል የደረሰበት ልጅ
ለጥቂት ሰዓትታ በአሸናፊነት መንፈስ ይኩራራል፤ ከሁሉም የተሻለ ነገር እንደያዘ እና ብቻውን
በዚህ ነገር መደሰት እንደሚችል ለማሳየት ይሞክራል፡፡ በግጭቱ ምክንያት የቀዘቀዘው የሌሎቹ
ልጆች ጨዋታ ግን ለመሞቅ ደቂቃዎች አይፈጁበትም፡፡ ህብረቱን የመረጡት ከህብረቱ ጋር
ዕቃውንም የመረጠው ከዕቃው ጋር መጫወታቸውን ቀጥለው፤ በእኔነት ስሜት ዕቃን መርጦ
የግጭት መንስኤ የሆነው ልጅ ለጥቂት ደቂቃዎች ደስታን ቢያገኝም ደስታውን ከሌሎች ልጆች
ጋር ሲጫወት እንደነበረው አይነት አልሆን ይለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ግጭት ፈጣሪው ከዕቃ ጓደኞቹ
እንዲበልጡበት ሲረዳ ድጋሚ በመሄድ “እንታረቅ” ይላል፡፡ የዕርቁ ስያሜም የመጣው ከዚህ ለዕርቅ
ከሚደረግ ጥሪ የተነሳ ነው፡፡

የዕርቅ ስነ-ስርዓቱ
በዕርቅ ስነ ስርዓቱ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ብዙ ጊዜ አይስተዋልም፡፡ በተጋጩት
ልጆች ተነሳሽነት የሚከናወን የዕርቅ ስርዓት ነው፤ እንደውም ሶስተኛ ወገን ከገባ ግጭቱ ሊካረር
ይችላል፡፡ የግጭቱ መንስኤ የሆነው ልጅ ጥፋቱን በመረዳቱ ትንሿን ጣት በመቀሰር ሌሎቹን
ጣቶች ደግሞ በማጠፍ “እንታረቅ” ብሎ ይጠይቃል፡፡ የተበደለው ልጅ ለመታረቅ መስማማቱን
ጣቶቹን እንደዛኛው ልጅ በማድረግ ይዘረጋል፡፡ የዕርቅ ስርዓቱም ሙሉ የሚሆው የተቀሰሩትን
ትንንሽ ጣቶች ጫፍና ጫፍ በማነካካት፣ ከዚያም ሁለቱም ልጆች ያቺኑ ጣት በመሳም
መስማማታቸውን (መታረቃቸውን) ያረጋግጣሉ፡፡ ተበዳዩ ልጅ ጨዋታንና አብሮነትን
ስለሚያስበልጥ ብዙ ጊዜ አልታረቅም አይልም፡፡ ዕርቁ በዚህ ሁኔታ ከተደረገ በኋላ ድጋሚ ወደ

2
ቀደመው ጨዋታቸው በሙሉ ልብ ይመለሳሉ፡፡ ድጋሚ እንኳን ተመሳሳይ ግጭት ቢመጣ ቂም
መያዝ የሚባል ነገር ፈፅሞ በልጆች ልብ ውስጥ አይታሰብም፡፡

የእንታረቅ አሁናዊ ገፅታ

በአሁኑ ጊዜ “እንታረቅ” በአንዳንድ አካባቢዎች ይስተዋላል፡፡ ማህበራዊ መስተጋብር በተለይ


ወደ ከተሜዎች አካባቢ እየቀነሰ መምጣቱ በህጻናትም ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ
ይገኛል፡፡ የልጆች አሁናዊ ጨዋታ ነገ አብሮ ለመኖር ምሳሌ ነው፡፡ አብሮ መኖርን ከልጅነቱ
ያልተለማመደና ያላጎለበተ ልጅ፣ በዕድገት ውስጥ የሚመጡን አብሮነትና አንድነት ለማስተናገድ
ይቸገራል፡፡ ከእኩያው ጋር መጋጨትንና አፈታቱን በልጅነቱ ያላወቀ ልጅ፣ አድጎ ግጭቶችን
ለማስተናገድ እና ለመፍታት አዳጋች ይሆንበታል፡፡ የበዛ ግለኝነት ለዚህ የ”እንታረቅ” ዕርቅ ስርዓት
ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡ ቤተሰብ በግለኝነት በሚኖርበት እና ጎረቤትን ማወቅ በተመናመነበት በዚህ
ጊዜ በጋራ መኖርን ማበረታታት መፍትሄ ነው፡፡ ከአዋቂዎች አብሮ መኖር በዘለለ ግን ለልጆች
ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በጋራ የሚጫወቱበትን መድረክ ማመቻቸት፣ ነገ ላይ ተስማምቶ እና
ተዋድዶ በሰላም የሚኖር ማህበረሰብን መገንባት ነው፡፡ ቤተሰብ ልጁ በተገቢው መንገድ
እንዲጫወት መፍቀድ ለልጅ ደስታን ከመስጠት በላይ ሀገርን መጥቀም ነው፡፡

ተቀባይነቱ
የእንታረቅ ዕርቅ ስርዓት ተቀባይነት ለልጆች ከምንሰጠው ቦታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
“ልጆችና ጫማ ወደ አልጋ ስር” በሚል አባባል ውስጥ ለሚኖር ልጅ ልዩ ትኩረት መስጠት
ያልተለመደ ነው፡፡ ልጆች ከበሉ፣ ከጠጡና የሚያስፈልጋቸውን ትምህርትና ስነምግባር ከተማሩ
በቂ ነው በሚል ማህበረሰብ ከልጆች ለመማር ልብን መክፈት ዕድለኝነት ነው፡፡ በሀገር፣
በምሁራን፣ በቤተሰብና በወጣቶች “እንታረቅ” የዕርቅ ስርዓት ቢታወቅም ተገቢውን ትኩረት ግን
አልተሰጠውም፡፡ “እንታረቅ” ማደግ ስንጀምር የተውነውና የረሳነው ነገር ግን ሁላችንም ያለፍንበት
የትላንት ትዝታችን ነው፡፡

ስለ እንታረቅ የኔ ዕይታ
ህፃናት ሁልጊዜም በየትኛውም ቦታ ሲገናኙ ቁጭ አይሉም ይጫወታሉ፤ እዚህም እዚያም
ይሮጣሉ፤ አብሮነታቸው ጨዋታን ይወልዳል፡፡ ይህ ደግሞ ለእነርሱ ትልቅ የደስታ ዓለም ብቻ
ሳይሆን በሌላ ነገር ሊተካ የማይችል ነው፡፡ በዚህ የደስታ ዓለም ውስጥ የሚፈጠር ግጭት ጊዜያዊ
ከመሆኑም በላይ የግጭቱ መንስዔ የሆነው ልጅ፣ የጨዋታው ዓለም ስለሚበልጥበት ልቡ

3
ሁልጊዜም ለይቅርታና ለሰላም ክፍት ነው፡፡ በሀገራችን ሁልጊዜም አብሮ መኖርን እንደ ትልቅ
ነገር አድርገን የመናገር ልማድ አለን፡፡ አብሮነት መልካምና ጥሩ ቢሆንም በአብሮነት ውስጥ ግን
አንድነታችንን የሚያጎለብት ነገር በብዛት አይታይም፡፡ አብሮ በመኖር ውስጥ የጋራ የሆነ ነገር
ያስፈልገናል፡፡ ልጆች አብረው እንደሚጫወቱ ሁሉ እኛም አብሮ መስራትና በስራችንም መደሰትን
ማጎልበት አለብን፡፡ በዘር፣ በቀለም፣ በጾታ እና በሀይማኖት ግጭቶች የሚፈጠሩት፣ አብሮነታችን
የፈጠረውን ዕድል ወደ ስራ ከመቀየር በላይ ለወሬ ስለተጠቀምንበት ነው፡፡ አብረን በመኖራችን
የበዛ ማህበራዊ ትስስርን ስለሚፈጥር፣ እንኳን ሰው ከሰው “እግር ከእግርም ይጋጫል” እንዲሉ
አበው፣ ግጭቶችና አለመግባባቶች መፈጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ የአብሮነታችን ግብ ስራ ካልሆነ
ግጭቱ ዘላቂነት ይኖረዋል፡፡ ለምንድነው አብረን የምንኖረው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ነገር ግን ስራ ልባችንን ከገዛና የደስታችን ምክንያት ካደረግነው ግጭት ቢፈጠር እንኳን ዘላቂነት
አይኖረውም፡፡ በመጽሃፍ ቅዱስ ላይ ጠቢቡ ሰለሞን የዕድሜው ጭማቂ በሆነው መፅሃፈ መክብብ
ላይ “ስለዚህ ለሰው ዕጣ ፈንታው ስለሆነ፣ በስራው ከመደሰት የተሻለ ነገር እንደሌለው አየሁ”
ይላል፡፡ ስራን በአብሮነታችንና በአንድነታችን ማላቅ እና የደስታ ምንጭ ማድረግ የዘላቂ ሰላም
ጅማሬ ነው፡፡
በልጆች ግጭት ውስጥ የግጭቱ መንስኤ የሆነው ልጅ ሁልጊዜም ከልጆቹ ቡድን ይገለላል፡፡
መገለል የደረሰበት ልጅ ለጊዜው እንደ አሸናፊ ራሱን ቢቆጥርም እየቆየ ሲሄድ ግን ብቸኝነቱ
ስለሚከብደውና ጨዋታው ስለሚበልጥበት ድጋሚ በእንታረቅ ይመለሳል፡፡ ሁልጊዜም በሚሰራው
ስራ የሚደሰት እና ስራው ልቡን የገዛ ሰው አብሮነትንና አንድነትን ያስቀድማል፤ ምክንያቱም
ያለ ሌላው ምንም እንደሆነ ስለሚገነዘብ ነው፡፡ በስራ ግን ራስ ተኮር እንቅስቃሴ ሲጀመር ሌላውን
መበደል እና የራስ ጥቅም ብቻ ማስቀደም ይጀመራል፡፡ በዚህ ጊዜ ከብዙሃኑ ራሱን ብቻ እያየ
የሚንቀሳቀሰውን ሰው በይፋ ማግለል ከልጆች የ”እንታረቅ” ዕርቅ ስርዓት የምንማረው ነገር ነው፡፡
ልጆች ከዕቃና ከግዑዝ ነገር አብረው የሚጫወቱትን ልጅ ያስበልጣሉ፡፡ የሚያምር መጫወቻ ይዞ
ለማስቀናት በሚሞክር ሌላ ልጅ ልባቸው ትንሽ ይከጅል ይሆን እንጂ ከሌላው ልጅ በፍጹም
አያስበልጡም፡፡ በሀገራችን ስልጣንን እና ገንዘብን ከሰው የሚያስበልጡ ሰዎችን በይፋ ማግለል
የተለመደ አይደለም፤ እንደውም ለነዚህ አይነት ሰዎች ማሸርገድ የሚቀናቸው ጥቂቶች
አይደሉም፡፡ ይህም ሰው መሆንን እየቀነሰ በገንዘባቸውና በስልጣናቸው ሌላውን መግዛት የሚችሉ
የሚመስላቸውን ሰዎች እያፈራ ይሄዳል፡፡ ከሰው ሌላን ግዑዝ ነገር አስበልጦ የሄደን ሰው ማግለል፣
ምን እንዳጣ ማሳያ ትልቅ የልጆች ትምህርት ነው፡፡

4
የልጆችን የዕርቅ ስርዓት መደምደሚያ የሆነውና ሌሎቹን ጣቶች አጥፎ ትንሿን ጣት
በመቀሰር ከዚያም ትንሿን ጣት ጫፍና ጫፍ በማነካካት በመቀጠልም ጣቷን በመሳም የሚካሄደው
ስርዓት የዕርቁ ማፅኛ ነው፡፡ ይህ የልጆች የዕርቅ መደምደሚያ የስምምነት መግለጫ፤ በአንዳንድ
ባህላዊ የዕርቅ ስርዓቶች እንደሚከናወኑት የእንስሳን ደም በጋራ መጠጣት፣ ምንሽር መሬት ላይ
ተቀምጦ ቦታ እንደ መቀያየር፣ የገንዘብ ካሳ እንደ መክፈል ዓይነት የሆነ ነው፡፡ ይህንን ስርዓት
አልፈፅምም ያለ ልጅ ለመታረቅ አለመፈለጉን ያሳያል፡፡ ይህ ስርዓት በድብቅ የሚከናወን
አይደለም፤ ሌሎች ልጆች እያዩ በይፋ የሚደረግ ነው፡፡ ሰዎች ለግጭት ሳያፍሩ፣ የዕርቅ ስርዓት
ግን በድብቅ እንዲከናወን ይፈልጋሉ፡፡ የበደለን ይቅር ማለት ይህንንም በአደባባይ መፈፀም ከዚያም
ልጆች በሙሉ ልብ ወደ ጨዋታቸው እንደሚመለሱ በሙሉ ልብ ይቅር ተባባሎ አብሮነትን
መቀጠል የልጆች ዕርቅ ማሳያ ነው፡፡ ቂም መያዝ በማደግ የሚመጣ በሽታ ነው፤ ልብን ሁልጊዜም
እንደ ልጆች ልብ ንጹህ ማድረግ ከትልቅነት በላይ ትልቅነት ነው፡፡

አጠቃላይ በሀገራችን ስላሉ የዕርቅ ስርዓቶች

ዕርቅ ለሀገሬ ኢትዮጲያ እንግዳ አይደለም፡፡ ዛሬም ኢትዮጲያ የምትባል ሀገር የመኖሯ
እውነት፣ ላለፉት ዘመናት ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆኖ መቆየቷን ሳይሆን በበዛ ግጭትና አለመረጋጋት
ውስጥ ችግሯን በራሷ እየፈታች መቆየቷን ያሳብቃል፡፡
ዘመናዊነት እየበዛ በመጣው የአሁን ማህበረሰባችን ባህላዊ ስርዓቶችን እንደማያስፈልጉ
መቁጠር እየተንሰራፋ ያለ አመለካከት ነው፡፡ ዘመናዊ የፍርድ ቤት ስርዓቶች ወደ ሀገራችን
ከመግባታቸው በፊት የሀገራችን ህዝቦች ግጭቶቻቸውን በውጤታማ መንገድ እየፈቱ ኖረዋል፡፡
ዘመናዊው የዕርቅ ስርዓት የራሱ በጎ ተፅዕኖ ቢኖረውም፤ የራስን ችላ ብሎ ለባዕድ ስርዓት መገዛት
አየጨመረ ስለመጣ በማንነት ቀውስ ውስጥ እንገኛለን፡፡ በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶችና
አለመግባባቶች ለዚህ እንደማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የዕርቅ ስርዓቶችን በተደራጀ መልኩ ማጥናት፣ ማስተንተን፣ ማጎልበትና ለብዙሀኑ ጥቅም
እንዲውል ማድረግ ከሁላችንም የሚጠበቅ ነገር ነው፡፡ ዓይናችንን እና ልቦናችንን ከባዕድ ሀገር
አንስተን፤ በዙሪያችን ያሉትን፣ ተዝቀው የማያልቁና በባህላችን ውስጥ የተደበቁ ዕንቁዎችን መፈለግ
እንጀምር፡፡ “እንታረቅ” የዕርቅ ስርዓትም በፍለጋ ከተገኙት ዕንቁዎች መሃል አንዱ ነው፡፡

5
መደምደሚያ

በዚህች ሚጢጢ ጽሁፍ የልጆችን የዕርቅ ስርዓት በጥቂቱ ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ፡፡


ጨዋታን ባነገሰ ልባቸው፤ ከግዑዝ ነገር በላይ ለሰው ቦታ የሚሰጡ ልጆች፣ ግጭትን በዘላቂነት
የምንፈታበትን መንገድ እንካችሁ ይሉናል፡፡ “እንታረቅ” የዕርቅ ስርዓት በልጆች ውስጥ ነገን
እንድናይ የተደረገ ጥሪ ነው፡፡ ዘላቂ መፍትሄንና ሰላምን ከልጆች ልብ ውስጥ እንሸምት፡፡ ልጆችን
ለማስተማር እንደምንተጋው ሁሉ ጥቂት ትኩረትን በመስጠት ከልጆች ለመማር ልባችንን
እንክፈት፡፡ በሰው ልብ ውስጥ ሰውንና የስራ ክቡርነትን አንግሰን፣ በጊዜያዊነት ሊይዙን ከሚችሉ
መሰናክሎች እንድንወጣ ይህ ጽሁፍ ያሳስባል፡፡
በመጨረሻም “እንታረቅ” የዕርቅ ስርዓት ቢጠና እና ቢጎለብት ለማህበረሰባችንና ለህዝባችን
ትልቅ የዕርቅ መፍትሄን ይለግሳል፡፡ ሀገራችን በሰላም የበለፀገች እንድትሆን፤ የልጆችን ልብ በዘርና
በቀለም እያቆሸሽን ሳይሆን ዕርቅን እና ሰላምን ለልጆች በብዛት እያስተማርን እናሳድጋቸው፤
ምክንያቱም ነገ በልጆች ውስጥ ተደብቋልና፡፡

You might also like