Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 3

118ኛው

118ኛው ፓትርያርክ መንገድ ላይ ናቸው


የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን 118ኛውን ፓትርያርክ የመምረጡ ሂደት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተሻግሯል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት አዲስ ፓትርያርክ ለመምረጥ አራት ሂደቶችን ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ የጥቆማና
ማጣራት፣ የመጨረሻዎቹን አምስት ዕጩዎች የመወሰን፣ ለዕጣ የሚቀርቡትን ሦስት አባቶችን መምረጥና
የመጨረሻውን አባት በዕጣ መምረጥ ናቸው፡፡

በዚሁ መሠረት ከተጠቆሙት ወደ አሥራ ሰባት አባቶች መካከል የማጣራቱና አምስቱን የመወሰኑ ሂደት እጅግ
ረዥም ጊዜ የወሰደ መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህ ሂደት ሁለት ከባባድ ችግሮች ተጋርጠውበት ነበር፡፡ የመጀመርያው
ፈተና በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና ከተጻፈውና የግብጽ ቤተ ክርስቲያንም ሕግ ከሚደነግገው ውጭ ሀገረ ስብከት
ያላቸው አባቶች ራሳቸውን ሳይቀር ለዕጩነት መምረጣቸው፣ ከዚህ በፊት አንዳንድ ችግሮች ተከስተውባቸው
የነበሩ አባቶችም በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ መግባታቸው ነበር፡፡

ይህ ሁኔታ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናና ሕግ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ራሳቸውን ከዕጩነት እንዲያገልሉ በአስመራጭ
ኮሚቴውና በቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ አባቶችና ሽማግሌዎች የማግባባትና የማረም ሥራ ሲሠራ ነበር፡፡ ለሁለት
ጊዜ ያህል ሱባኤ ታውጆ፣ ጳጳሳቱም ሁሉ ወደ አባ ብሶይ ገዳም ገብተው በጸሎትና በውይይት ችግሩን ለመፍታት
ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የተወሰኑት አባቶች ‹እኔ በሺኖዳ መንበር መቀመጥ የለብኝም› እያሉ
ራሳቸውን ከዕጩነት አግልለዋል፡፡

ከዚያ በኋላም ቢሆን የዕጩዎቹ ቁጥር በመብዛቱና በምእመናኑም ዘንድ በአንዳንድ ዕጩዎች ላይ ቅሬታ በመፈጠሩ
የምርጫ ኮሚቴው ጊዜ ወስዶ ችግሮቹን ለመፍታት ሞክሯል፡፡ እጅግ የባሰው ሁለተኛውም ፈተና የተጀመረው
በዚህ ጊዜ ነበር፡፡

አንዳንድ ዕጩዎች በቴሌቭዥን ፕሮግራም ሳይቀር ልክ እንደ ፖለቲካ ተመራጮች የምረጡኝ ዘመቻ ጀመሩ፡፡
ሕዝቡ ግራ ተጋባ፡፡ ዐቃቤ መንበሩ አባ ጳኩሚስ አንዳንድ ክርስቲያን የቴሌቭዥን ጣቢያዎችን እስከ ማስጠንቀቅ
ደረሱ፡፡ በዚህ ጊዜ ምእመናኑና አባቶች በወሰዱት ቆራጥ አቋምና ግፊት አንዳንድ እጩዎች ከዕጩነት እንዲወጡ
ተደረገ፡፡ በመጨረሻም አምስት አባቶች ቀሩ፡፡ በዚህ ሂደትም አምስት ጳጳሳትና ሰባት መነኮሳት ከዕጩነት ወጡ፡፡
በሂደቱ ከዕጩነት ከወጡት መካከል የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ አቡነ ቢሾይ፣ የቀድሞው ፓትርያርክ ረዳት የነበሩት
አቡነ ቡትሮስና የመንበረ ፓትርያርኩ ዋና ጸሐፊ አቡነ ዮሐንስ ይገኙበታል፡፡

በግንቦት ወር የተጀመረው 118ኛውን ፓትርያርክ የመምረጡ ሂደት ባለፈው ሰኞ ወደ መጨረሻው ደረጃ


ተሸጋግሯል፡፡ ሰኞ ዕለት በካይሮ አባስያ በሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ከአምስቱ አባቶች ሦስቱን በድምጽ
የመለየት ሂደት ተከናውኗል፡፡

የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሕግ እንደሚፈቅደው ብቃት ያላቸው የሚባሉት ድምጽ ሰጭዎች ቁጥራቸው 2411 ነው፡፡
እነዚህ ድምጽ ሰጭዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ሥር ያሉ ካህናት፣ የገዳማት ተወካዮች፣ የምእመናን
ተወካዮች፣ በግብጽ ፓርላማ ወንበር ያላቸው የኮፕት ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን
ተወካዮችና ክርስቲያና ጋዜጠኞችን ያካተተ ነው፡፡
እንደ ዐቃቤ መንበር ጳኩሚስ መግለጫ ከሆነ ከጠቅላላው የበቁ ድምጽ ሰጭዎች መካከል 93% ያህሉ በሰኞ
ዕለት ድምጽ ሰጥተዋል፡፡ ምርጫው ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት የተጀመረ ሲሆን ከቀኑ 11 ሰዓት ተጠናቅቋል፡፡ ይህንን
ሂደት እንዲታዘቡ ጋዜጠኞች ከመላው ዓለም የተጋበዙ ሲሆን የምርጫ ሳጥኑ በመስተዋት ተሠርቶ በግልጥ ቦታ
እንዲታይ ተደርጓል፡፡ ሂደቱን ምእመናንና ጋዜጠኞች በግልጥ ሲከታተሉት የነበሩ ሲሆን ለዚሁ ርዳታ ለመስጠትና
እንግዶችን ለመርዳት 300 የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በቦታው በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡

የድምጹ ቆጠራ በዚያው ዕለት ተከናውኗል፡፡ በዚህም መሠረት አቡነ ራፋኤልና አቡነ ታዋድሮስ የተባሉ ሁለት
ጳጳሳትና አባ ራፋኤል አቫ ሚና የተባሉ መነኮስ ለመጨረሻው የዕጣ ሥነ ሥርዓት ተመርጠዋል፡፡ አቡነ ራፋኤል
በሚዲያዎች የቅድሚያ ግምት የተሰጣቸው የ54 ዓመት አባት ናቸው፡፡ እኤአ በ1981 ዓም ከአይን ሻምስ
ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ፋኩልቲ የተመረቁት እኒህ አባት ከዚያ በኋላ ወደ ነገረ መለኮት ኮሌጅ ገብተው
ተመርቀዋል፡፡ ክህነት የተቀበሉትም እኤአ በ1984 ዓም ነው፡፡

አቡነ ራፋኤል በመካከለኛው ካይሮ የፓትርያርኩ ረዳት ጳጳስ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የወጣቶችን ጉዳይ ጉዳያቸው
በማድረግና ከወጣቶች ጋር በመሥራትም ይታወቃሉ፡፡ አቡነ ራፋኤል ብዙ ጊዜ በከተማ ከሚገኙ ድኾች ጋር
በመሥራታቸውና ችግራቸውንም ለመፍታት በመጣራቸው ‹የድኾች አባት› እስከመባል ደርሰው ነበር፡፡

አቡነ ራፋኤል ሥራ አጥነትና ድኽነትን በሚመስሉ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በሚያቀርቧቸው ሃሳቦች ይታወቃሉ፡፡
በሃይማኖቶች መካከል የሚደረገው ሽኩቻና ጥላቻ ‹ለእግዜር የለሽነት› መንገድ ከመክፈት ያለፈ ጥቅም የለውም
በሚለው አቋማቸው ብዙዎች ያውቋቸዋል፡፡

አቡነ ታዋድሮስ በበህይራ ሜትሮፖሊስ የፓትርያርኩ ረዳት ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በዝምተኛነታቸውና ነገሮችን
በማግባባትና በዕርቅ ለመጨረስ ባላቸው አቀራረብ ይታወቃሉ፡፡ በሚዲያ ላይ ወጥቶ በማንኛውም ጉዳይ ላይ
መናገርን የማይወዱት አቡነ ታዋድሮስ ከሌሎች እምነቶች ጋር በመግባባትና በመተጋገዝ መኖርን የሚሰብኩ፣
ወጣቶች ራሳቸውን ከሌላው ማኅበረሰብ ማግለል እንደሌለባቸው የሚያስተምሩ ናቸው፡፡

የስድሳ ዓመቱ አባት አቡነ ታዋድሮስ ከእስክንድርያ ዩኒቨርስቲ በፋርማሲስትነት የተመረቁ ሲሆን ከዚያም በኋላ
በፋርማሲ ኢንጅነሪንግና በማኅበራዊ ጤና ከሲንጋፖርና ከእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀዋል፡፡ ከመመን
ኮሳቸውም በፊት በግብጽ የተለያዩ መድኃኒት ካምፓኒዎች ውስጥ ሠርተው ነበር፡፡ አቡነ ታዋድሮስ የሕዝብ በዛት
በተጨናነቀበት የካይሮ አካባቢ ያገለገሉና የሕዝቡን ችግሮች በመካፈል የሚታወቁ አባት ናቸው፡፡

አባ ራፋኤል አቫ ሚና ከ1964 ዓም እኤአ ጀምረው በማር ሚና ገዳም የሚኖሩ አባት ናቸው፡፡ አባ ራፋኤል
እድሜያቸው 70 ሲሆን ከሦስቱም እጩዎች በዕድሜ አንጋፋው ናቸው፡፡ ከሦስቱም እጩዎች ከተፈጥሮ ሳይንስ
ውጭ የሆነ ፊልድ ያጠኑት እርሳቸው ሲሆኑ የተመረቁት በሕግ ዲግሪ ነው፡፡ አባ ራፋኤል የአቡነ ሺኖዳ መምህር
የሆኑት የአቡነ ቄርሎስ ስድስተኛ አንዱ ደቀ መዝሙር ሲሆኑ ዛሬ በጵጵስና ያሉ ብዙዎቹ አባቶች አብረዋቸው
የተማሩ ናቸው፡፡ አባ ራፋኤል በሕዝቡ ዘንድ ‹ብጹዕ ራፋኤል› በመባል ይታወቃሉ፡፡

አቡነ ሺኖዳ ካህናትን ለመሾም ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ማር ሚና ገዳም ሲመጡ የመሰየሚያ በትራቸውን በመንበሩ
ጀርባ ትተውት ሄዱ፡፡ ረዳቶቻቸውም ለምን እንደተውት ሲጠይቋቸው ‹በሚቀጥለው ስመጣ እወስደዋለሁ›
አሏቸው፡፡ ይህም በሕዝቡ ዘንድ ‹ቀጣዩ ፖፕ ከዚህ ገዳም ይሆናል› የሚል ትንቢታዊ ንግግር ተደርጎ ተወሰደ፡፡
ሕዝቡም ምናልባት አባ ራፋኤል ሳይሆኑ አይቀሩም ይላል፡፡

የመጨረሻው የፖፕ ምርጫ የሚከናወነው ጥቅምት ሃያ አምስት ቀን 2005 ዓም እሑድ ነው፡፡ እስከዚያው የሦስቱ
ዕጩዎች ስም መንበሩ ላይ ሆኖ ሲጸለይበት ይሰነብታል፡፡ በዕለተ እሑድ ቅዳሴው በመንበሩ ላይ የሦስቱም
አባቶች ስም እያለ ይከናወናል፡፡ ከዚያም አባቶች፣ምእመናንና ተጋባዦች በተገኙበት ከቅዳሴ በኋላ በመንበሩ ላይ
የተቀመጡት ስሞች ወርደው አንድ ዓይኑን በጨርቅ የተሸፈነ ሕፃን ልጅ በሚያወጣው ዕጣ 118ኛው ፓትርያርክ
ይታወቃል፡፡

እግዚአብሔር ለሁላችንም የሚሆን አባት ያምጣልን፡፡

You might also like