Download as docx, pdf, or txt
Download as docx, pdf, or txt
You are on page 1of 11

ምዕራፍ ሦስት

3. ምሥጢረ ሥላሴ

መግቢያ

የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ከአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት አንዱ ሲሆን የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት
የሚያስረዳ ክፍል ነው፡፡ እግዚአብሔር በባሕርይው አንድ ነው ግን ደግሞ ሦስትነት አለው፡፡ ይህ ክፍል የሥላሴን አንድነትና
ሦስትነት አውቀህ(ሽ) እንድታምን(ኚ) የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር የሚገለጥበትና የሚብራራበት ዓምድ ነው፡፡
እግዚአብሔር በአንድነቱ ምንታዌ /መንታነት፣ሁለትነት/ የሌለበት ስለሆነ አንድ ሲባል ሁለት የሚል ቁጥር
አይከተለውም። ወይም እርምጃውን አይገታውም፡፡ አንድ ተብሎ ሦስት ይባላል። በሦስትነቱም ርባኤ /አራትነት/ የሌለበት
ስለሆነ አራት የሚባል ቁጥር አይከተለውም፣ሁለት የሚባል ቁጥርም አይቀድመውም፣መሠረቱንም አያናውጠውም፡፡ ስለዚህ
ሦስቱ አንድ ተብሎ ይታመናል፡፡
ይህ አንድነትና ሦስትነት እኛ ከምናውቀው የሒሳብ ደንብና የቁጥር ሕግ ውጭ ነው። በፍጥረት ሥርዓትና ደንብም
አይወሰንም። በሥጋዊ ዕውቀት የማይመረመርና የማይደረስበት ረቂቅና ምጡቅ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ መጽሐፍ
ቅዱስ የሚለውንና አበው ሊቃውንት ቅዱሳት መጻሕፍትን በመመርመር ያስተማሩትን ትምህርት ማዕከል በማድረግ
ልናጠናው እንችላለን፡፡

ይህ ምሥጢር የሁሉ ምሥጢራት መጀመሪያ ብቻ ሳይሆን መሠረትም ነው ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ምንነትና


ባሕርይውን በጥንቃቄ የምናጠናበት ክፍል በመሆኑ ነው፡፡ ምሥጢረ ሥላሴን የምንማርበት ዋናው ምክንያት የሥላሴን
አንድነትና ሦስትነት አውቀንና ተረድተን እግዚአብሔርን በተገቢ ክብሩና መዓርጉ ለማምለክ ነው፡፡

የሚጠበቅ ብቃት /Expected Outcomes/

ተማሪዎች ይህንን ምዕራፍ ሲጨርሱ

 የምሥጢረ ሥላሴን ምንነትና ጽንሰ ሐሳብ ይረዳሉ፡፡

 ስለ ምሥጢረ ሥላሴን በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጹ ማስረጃዎችን ይተነትናሉ፡፡

1
 ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የሚያስረዱ የተፈጥሮ ምሳሌዎችን ያጤናሉ፡፡

 የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት ያስረዳሉ፡፡

3.1. የምሥጢረ ሥላሴ ምንነት

ሀ.ሦስትነት፡-

ቅድስት ሥለሴ ስንል የተለየች ሦስትነት ማለታችን ነው፡፡ በዚህ የሦስትነት ማመናችን ሦስት አማልክት ማለታችን
አይደለም፡፡ አንዱን አምላክ ወይም አንዱን እግዚአብሔር በስማ በአካል በግብር ሦስት ብለን ማመናችን እንጂ፡፡ "…በአንድ
አምላክ አምናለሁ አንድነት በሦስትነት ሦስትነት በአንድነት እንዳለ አውቃለሁ…" እንዲል /ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ /
ምዕ.90 ቁ.5/

አሁን ሦስትነቱን በዝርዝር ተመልከት(ቺ)

የአካል ሦሰትነት

ሥላሴ በአካል ሦስት ናቸው ስንል ምን ማለታችን ነው?

 ለአብ ፍፁም ገጽ ፍፁም መልክ፣ ፍፁም አካል አለው፤


 ለወልደም ፍፁም ገጽ ፍፁም መልክ ፍፁም አካል አለው ፤
 ለመንፈስ ቅዱስም ፍፁም ገጽ ፍፁም መልክ ፍፁም አካል አለው፡፡ ማለታችን ነው እነኚህ አካላትም የየራሳቸው
ግብራት አላቸው፡-
 የአብ ግብሩ መውለድ ማስረጽ(ማውጣት)
 የወልድ ግብሩ መወለድ
 የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መስረጽ(መውጣት) ነው፡፡
ስለዚህም በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት አብ ወላዲ፣ አሥራጺ ማለትም ወልድን የወለደ መንፈስ ቅዱስን ያሰረጸ/ያስገኘ/
ሲሆን ወልድ ተወላዲ ማለትም ከአብ የተወለደ መንፈስ ቅዱስም ሠራጺ ማለትም ከአብ የተገኘ /የወጣ/ ማለት ነው፡፡
እዚህ ላይ ግን አብ ወልድን የወለደው በልብነት፣ ወልድም ከአብ የተወለደው በቃልነት ስለሆነ፤ አብ ወልድን ወለደ፣
ወልድም ከአብ ተወለደ ተብሎ ይነገራል፡፡
አብ መንፈስ ቅዱስን ያሰረጸው በልብነት፣ መንፈስ ቅዱስም ከአብ የሰረጸው በእስትንፋስነት፣ ስለሆነ አብ መንፈስ ቅዱስን
አሰረጸ፤ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ሠረጸ ይባላል፡፡ ስለዚህ ሦስቱ አካላት የማይቀላቀሉ ሦስት ግብራት እንዳላቸው እናምናለን፡፡

2
የስም ሦስትነት
ሥላሴ ስንል አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሦስት ስም ማለታችን ነው፡፡ ሥላሴ በስም ሦስት ናቸው የስም ተፋልሶ የግብር
ተፋልሶን ስለሚያመጣ አብ አብ ቢባል አንጂ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፣ ወልድም ወልድ ቢባል እንጂ አብ መንፈስ
ቅዱስ አይባልም፣ መንፈሰ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ቢባል እንጂ አብ ወልድ አይባለም፡፡
ይህ የሥላሴ ስም ጥንት መሠረት ሳይኖረው ቅድመ ዓለም ሲኖር የኖረ ነው እንጂ እንደ ተጸውዖ /መጠሪያ/ ስም ኖሮ ኖሮ
የወጣ ስም አይደለም "እንግዲህ ሒዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው
ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው" /ማቴ 28፡19/
የግብር ሦስትነት
የሥላሴ የአካላት ግብር እነዚህ ናቸው ወላዲ፣ ተወላዲ፣ አስራጺ፣ሠራጺ፡፡ በዚህም መሠረት የአብ ግብሩ መውለድና
ማስረጽ ነው፣ የወልድም ግብሩ መወለድ ነው፣ የመንፈስ ቅዱስም ግብሩ መስረጽ ነው፡፡
ስለዚህም አብ ወልድን ይወልዳል መንፈስ ቅዱስን ያስርጻል /ያወጣል/፣ ወልድ ከአብ ይወለዳል፣ መንፈስ ቅዱስ ከአብ
ይሰርጻል "… እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል" እንዲል /ዮሐ. 15፡26/
የአብ መውለድና ማስረጽ፣ የወልድ መወለድ፣ የመንፈስ ቅዱስ መስረጽ እንደምን ነው ቢሉ ከሰው አእምሮ በላይ ነው፡፡
በመሆኑም እንዲሁ ዕጹብ ድንቅ ተብሎ ይደነቃል አንጂ አይመረመርም "….ከአብ የወልድ መወለድ የመንፈስ ቅዱስ
መስረጽ በእፁብ ይወሰናል እንጂ እንዲህ ነው ተብሎ አይነገርም ከህሊናት ሁሉ በላይ ነው አይመረመርም…."
እንዳለ /ሃይማኖተ አበው ዘዲዮናስዮስ ምዕ.10 ቁ.12/
አብ ከወለደ፣ ወልድ ከተወለደ፣ መንፈስ ቅዱስ ከሠረጸ፣ አይበላለጡምን ቢሉ አዎን አይበላለጡም ከሰው ልብ ቃልና
እስትንፋስ ሲገኙ እንዳይበላለጡ እኒህም አይበላለጡም፡፡ በሥላሴ ዘንድ መብለጥ መበላለጥ የለምና፡፡

ለ.አንድነት
የሥላሴ አንድነት ሦስትነታቸውን አይጠቀልለውም፣ ሦስትነታቸውም አንድነታቸውን አይከፋፍለውም፡፡ ሥላሴ
በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስት ቢሆኑም፤ በመለኮት፣ በአገዛዝ፣ በባሕርይ አንድ ናቸው፡፡
መለኮት በአካል ልዩ ሳይሆን በቅድስት ሥላሴ አንድ መለኮት በሦስት አካላት ህልው ነው፡፡ "በዕውቀት ማነስ
የተሳሳቱ ሰዎች / እነ ዮሐንስ ተዓቃቢ/ ልዩ በሆነች ሦስትነት / ቅድስት ሥላሴ/ የመለኮትን ልዩነት የአካላትን አንድነት
አግብተው ይናገሩ ዘንድ አይድፈሩ ለአንድ አምላክ እንስግዳለን እንጂ ለሦስት አማልክት አንሰግድምና አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ
ቅዱስ ብለን በሦሰት ስም እንጠራቸዋለን እኒህም ሦስቱ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በአንድ መለኮትና /ሕይወት/ በአንድ
ህልውና አንድነት የተገናዘቡ ሦስት ሲሆኑ አንድ ባሕርይና ኃይል ናቸው" ሃ.አበው 4፡22
በአጠቃላይ ቅድስት ሥላሴ፡- በፈቃድ፣ በምክር፣ በመፍጠር፣ በእግዚአብሔርነት፣ በልቡና፣ በቃል፣ በእስትንፋስ፣
በአምላክነት፣ በመንግሥት፣ በሥልጣን ፣ በአገዛዝ፣ ቀድሞ ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ በመፍጠር፣ ኋላም
ይህን ዓለም ከመኖር ወደ አለመኖር በማሳለፍ፣ መዓልትና ሌሊቱን በማመላለስ፣ ክረምትና በጋውን በማፈራረቅ፣ ኃያሉን
ድኩም ድኩሙን ኃያል፣ ባለጤናውን ድውይ ድውዩን ባለጤና፣ ድኃውን ባለጸጋ ባጸጋውን ደኃ በማድረግ አንድ ናቸው።

3
"አሐቲ ልቡና፣ አሐቲ ቃል፣ አሐቲ እስትንፋስ፣ አሐቲ መንግሥት፣ አሐቲ ሥልጣን፣ አሐቲ ክብር፣ ወአሐቲ ምኲናን
= አንድ ልብ፣ አንድ ቃል፣ አንድ ሕይወት፣ አንድ አገዛዝ፣ አንድ ስልጣን፣ አንድ ክብር፣ አንድ አገዛዝ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ
በቅዳሴ ማርያም
ከላይ በዝርዝር እንዳየነው ሥላሴ፦
 በአብ ልብነት ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሕልዋን ናቸው ስለዚህም በአብ ልብነት ያስባሉ፤
 በወልድ ቃልነት አብ መንፈስ ቅዱስ ሕልዋን ናቸው ስለዚህ በወልድ ቃልንት ይናገራሉ፤
 በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት አብ ወልድ ሕልዋን ናቸው ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት ህያዋን
ሆነው ይኖራሉ፤
አካላት ለየራሳቸው ልብ፣ ለየራሳቸው ቃል፣ ለየራሳቸው እስትንፋስ የላቸውም፡፡ ስለዚህ መጠቅለል፣ መቀላቀል
የሌለባቸው ሦስት አካላት በሕልውና እየተገናዘቡ በባህርይ፣ በመለኮት፣ በፈቃድ፣ በሥልጣን፣ በመንግሥት፣ በአምላክነትና
በጌትነት በአንድነት ፀንተው ይኖራሉ፡፡ በመሆኑም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ እናላለን፡፡
እስኪ ይህንን ሰንጠረዥ ተመልከት(ቺ) በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ሊጠኑና ሊያዙ የሚገባቸው ዋና ዋና ነጥቦች ናቸው
ሰንጠረዥ.2

አንድነት ሦስትነት
ባሕይር ስም
መለኮት አካል
ህልውና ግብር
አገዛዝ ኩነታት(መሆኖች)
እግዚአብሔርነት
አኗኗር

3.2. ሦስቱ ኩነታት(መሆኖች)


በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት በአንድ መለኮት ሦስት ኩነታት(መሆኖች) አሉ እነዚህም ልብ መሆን፣ ቃል መሆን፣
እስትንፋስ መሆን ናቸው፡፡ አብ ለራሱ ልብ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው ፣ ወልድም ለራሱ ቃል ሆኖ ለአብና
ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፣ መንፈስ ቅድዱም ለራሱ እስትንፋስ / ሕይወት/ ሆኖ ለአብና ለወልድ እስትንፋሳቸው ነው፡፡
የሥላሴ አካል እኛ ከምናስበው አካላዊ ዕውቀት ፍፁም የራቀ ነው በምሥጢረ ሥላሴ አካላት መጠቅለልና
መቀላቀል ሳይኖርባቸው በተከፍሎ፣ በተፈልጦ፣ በፍፁም ገጽ፣ በፍፁም መልክዕ፣ በየራሳቸው የቆሙ ናቸው፡፡ ኩነታት ግን
መከፈልና መለየት ሳይገባቸው በተዋሕዶ፣ በአንድነት አካላትን በህልውናና በአኗናር እያገናዘቡ በአንድ መለኮት የነበሩ ያሉና
የሚኖሩ ናቸው፡፡ እነዚህም ከዊነ ልብ /ልብ መሆን/ ከዊነ ቃል፣ /ቃል መሆን/ ከዊነ እስትንፋስ /ህይወት መሆን/ ነው፡፡፡
መከፋፈል የሌለባቸው ሦስቱ ኩነታት
ሰንጠረዥ 3.

4
ከዊነ ልብ (ልብ መሆን) በአብ መሠረትነት ለራሱ ለባዊ(አሳቢ) ሆኖ ለወልድና
ለመንፈስ ቅዱስ ዕውቀት ማወቂያ መሆን ነው
ከዊነ ቃል (ቃል መሆን) በአብ መሠረትነት ለራሱ ነባቢ(ተናጋሪ) ሆኖ ለአብና ለመንፈስ
ቅዱስ ንባብ (መናገሪያ) መሆን ነው
ከዊነ እስትንፋስ (እስትንፋስ መሆን) በአብ መሠረትነት ለራሱ ሕያው ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወት
መሆን ነው

3.3. ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎች


የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት አፈ ታሪክ /Legend/ የሆነና መሠረት የሌለው ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ
በቅዱሳን መጻሕፍት ምስክርንት የከበረ ነው። ይኽ ብቻም አይደለም የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት በራሱ በልዑል
እግዚአብሔር የተጀመረ መሠረታዊ ትምህርት ነው፡፡ ይህንንም የሚያረጋግጥልን መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡
ሀ. በብሉይ ኪዳን
ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አንዱ በሆነው ብሉይ ኪዳን የቅድስት ሥላሴን አንድነትና ሦስትነት በምስጢርና በምሳሌ ካልሆነ
በቀር በገሃድ ተገልጦና ተብራርቶ አናገኘውም። ይሁን እንጂ በዚኽ ሁኔታ እንኳ ቢሆንም በሐዲስ ኪዳን ፍንትው ብሎ
ለሚገለጠው፣ ረቂቅና ጥልቅ ስለሆነው የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ትምህርት መቅድም ሆኖ ያግዛል። እስኪ ጥቂቱን
ተመልከት(ቺ)
 "እግዚአብሕርም አለ ሰውን በመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር" /ዘፍ 1፡26/
ይህ ጥቅስ በራሱ በእግዚአብሔር ባሕርይ አንድነትና ሦስትነት እንዳለ ይነግረናል ያስተምረናልም፡፡
ይኸውም እግዚአብሔር አለ የሚለው አንድነቱን፣ እንፍጠር የሚለው ቃል ደግሞ ሦስትነቱን ያመላክታል።
 "እግዚአብሔር አምላክ አለ እነሆ አዳም መልካሙንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ…" /ዘፍ.3÷22/
በዚህ ጥቅስ ውስጥ አንድነቱን የሚያስራዳው ቃል የቱ ይመስልሃል?(ሻል) እስኪ ለመምረጥ ሞክር(ሪ)
እግዚአብሔር አምላክ አለ፤ የሚለው ቃል ነው ካልክ(ሽ) ትክክል ብለሃል(ሻል)፡፡ ሦስትነቱን የሚያስራዳው ቃል ደግሞ ከእኛ
እንደ አንዱ ሆነ…የሚለው ነው። ይኽ ክፍል የሚነግረን ከቅድስት ሥላሴ (ሦስቱ አካላት) አንዱ አካል ወልድ በተለየ አካሉ
በኋለኛው ዘመን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው መሆኑን ነው። ከላይ
ባነበብካቸው(ሻቸው) ጥቅሶች ምሳሌ መሠረት እስኪ እነዚህን ሁለት ጥቅሶች ተመልከትና(ቺና) የቅድስት ሥላሴን አንድነትና
ሦስትነት እንዴት እንደሚያስረዱ አረጋግጥ(ጪ)
 "ኑ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው" /ዘፍ 11፡7/
 "… እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞለቶትነበር፡፡
ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለቱም ክንፍ ፊቱን ይሸፍን
ነበረ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበረ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር..." አንዱም ለአንዱ ቅዱስ፣

5
ቅዱስ፣ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኸ ነበር፡፡ /ኢሳ 6፡1-
3/
እጅግ በሚገርም መልኩ እግዚአብሔር ለአባታችን አብርሃም በአንድነትና በሦስትነት ይገለጥና ይነጋገር ነበር፡፡ ይህንንም
የምንረዳው ከአብርሃም ንግግር ነው እስኪ ከዚህ በታች በሰንጠረዥ የተቀመጠውን ተመልከት(ቺ) ታዲያ የንግግሩን
በነጠላና በብዙ መሆን በማየት ብቻ አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር ያልተነጋገረ እንዳይመስልህ(ሽ) ልብ በል(ዪ)። ለዚሁም
ጠቋሚ የሆነውን ቃል ላስታውስህ(ሽ) ይህ ምዕራፍ ሲጀምር "እግዚአብሔር ተገለጠለት” ብሎ ይጀምርና ሲጨርስ
"እግዚአብሔርም ከአብርሃም ጋር ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሔደ…" ብሎ ያጠናቅቃል፡፡ ይኼ ማለት ደግሞ አባታችን
አብርሃም የተነጋገረው ከእግዚአብሔር ጋር ነበር ማለት ነው፡፡

የእግዚብሔር /ሥላሴ/ እና የአባታችን አብርሃም ንግግር (ኦ.ዘፍ.18፥1-33) ሰንጠረዥ 4.

አንድነት ሦስትነት
"እግዚአብሔር… ተገለጠለት" "… እነሆ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ"
"… ተነስቶ ወደ ምድር ሰገደ.. አቤቱ በፊትህ ሞገስ “ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ እግራችሁን ታጠቡ
አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ ከዚህችም ዛፍ በታች እረፉ…"
እለምንሃለሁ"
" ለውሺውም እንጎቻም አድርጊ…" " ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ"
”እርሱም የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ወደ አንተ "እነርሱም ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት አሉት"
በእውነት እመለሳለሁ…”
"እግዚብሔርም አለ እኔ የማደርገውን ከአብርሃም -
እሰውራለሁን"
"እግዚአብሔርም ከአብርሃም ጋር ንግግሩን በጨረሰ -
ጊዜ ሔደ…"

ሰንጠረዡን በሚገባ ተመለከትክ(ሽ) እንዴት እገኘኽው(ሺው)? በነገራችን ላይ የአብርሃሙ ሥላሴ ሲባል


ሰምተህ(ሽ) ታውቃለህ(ቂያለሽ)? ይኽንን ክፍል ተረጋግተህ(ሽ) ብታነብ(ቢ) ሁሉንም ልትረዳ(ጂ) ትችላለህ(ያለሽ)

እጅግ በሚገርም መልኩ አግዚአብሔር ከአባታችን ከአብርሃም ጋር በአንድነትና በሦስትነት ተገልጦ ይነጋገር ነበረ ።
በምሥጢር ካልሆነ በስተቀር ተብራርቶ ያላየነው የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ከላይ ባየነው የአባታችን የአብርሃም ታሪክ
ላይ ፍንትው ብሎ ተቀምጧል። አባታችን አብርሃም በትህትና በታጀበ ንግግሩ ቆይታ ያደረገው በባሕርይው አንድነትና
ሦስትነት ካለው ከሰማይና ምድር ፈጣሪ ከልዑል እግዚብሔር ጋር ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ምዕመናን

6
እግዚአብሔር በአንድነትና ሦስትነት ለአብርሃም እንደተገለጠለት በማወቃቸውና ከአብርሃም ጋር ባደረገው ቆይታ
ምክንያትም ይህንኑ የምሥጢረ ሥላሴን ትምህርት በመረዳታቸውን ሲገልጡ ሥላሴን የአብርሃሙ ሥላሴ ሲሉ
ይጠሯቸዋል፡፡ አሁንስ የአብርሃሙ ሥላሴ የሚለውን ቃል መነሻ ተረዳህ(ሽ)?

ለ. በሐዲስ ኪዳን

የቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በተሻለ፣ በታወቀና በተረዳ መልኩ ተብራርቶ የተገለጠውና የተቀመጠው ከብሉይ
ኪዳን ይልቅ በሐዲስ ኪዳን ነው። ምክንያቱ ደግሞ የአምላክ ሰው መሆን ምሥጢር የተገለጠው በዚሁ በሐዲስ ኪዳን
በመሆኑ ነው። ከዚኽ ቀጥሎ በጣም ጥቂቶቹን ብቻ የሐዲስ ኪዳን ማስረጃዎችን እናያለን

 "ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ
እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ
የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ" /ማቴ.3÷16-17/

 "እንግዲህ ሒዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፣በወልድ፣በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ


እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው" /ማቴ.28÷19/ ተመልከት(ቺ) ተናጋሪው ወልድ ነው
ስለዚህም ሒዱና በእኔ ስም ብቻ አጥምቁ ማለት ይችላል ነገር ግን የአንድነትና ሦስትነቱን ነገር ሲያስረዳን ነው እንዲህ
ያለን፡፡

 "የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም ግን እሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት
ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይነግራችኋል፡፡ እሱ ያከብረኛል ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና፡፡ ለአብ ያለው
ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ" /ማቴ.16; 12-15/ አንድ ነገር አስታውስ "ለእኔ ካለኝ
ወስዶ የነገራችኋል" የሚለው ንግግር ሥላሴ በወልድ ቃልነት ይናገራሉ ላልነው ማረጋገጫ ነው፡፡
 "በመንግሥተ ሰማያት የሚመሰክሩት ሦስቱ ናቸው፡፡ አብ፣ወልድ፣መንፈስ ቅዱስ እነዚህም ሦስቱ አንድ ናቸው"
(for there are three that bear record in heaven; The Father, The Word, and The Holy
Ghost. And ther are one.) /the holy Bible the British and Foreign Bible Society
1611 ዓ.ም.ዕትም/
ይሔ ደግሞ ምንም ማብራሪያ የማያሻው የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ጥቅስ ነው፡፡
በተጨማሪም እነዚህን ጥቅሶች ማንበብ ይጠቅማል
 የዮሐንስ ወንጌል ምዕ.1 ቁ. 1-3 እና ቁ.14/
 የዮሐንስ ወንጌል ምዕ.8 ቁ.5
 የዮሐንስ ራዕይ ምዕ.22 ቁ.16
 የዮሐንስ ወንጌል ምዕ.14 ቁ.8

7
ሐ.በሊቃውንት መጻሕፍት
የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በርካታ ሊቃውንት የትምህርተ ሃይማኖት መሠረት ስለሆነው የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት
ባፍም በመጣፍም መስክረዋል ለአብነትም እስኪ ጥቂቱን ተመልከት(ቺ)፡፡
 "ከሥራው ሁሉ አስቀድሞ ሦስት አካላት ባሉት በአንድ መለኮት እንመን፤ በባሕርይ አንድ፤ በአካል ሦስት የሚሆኑ
አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፤ አንድ ሲሆኑ ሦስት ናቸው፤ ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው" ቅዱስ ባስልዮስ
ዘቂሣርያ/ሃይማኖተ አበው ምዕ.33 ቁ.2
 "አብ ወላዲ ነው እንጂ ተወላዲ አይደለም፡፡ ወልድ ግን ተቀዳሚ ተከታይ ሳይኖረው ቅድመ ዓለም ከብቻው ከአብ
ተወለደ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ሠረጸ፤ በቀዳማዊነት፣ በአገዛዝ፣በሥልጣን፣በከሀሊነት፣ ፍጥረትን ሁሉ በመፍጠር ከአብ
ከወልድ ጋር አንድ ነው፡፡ በመለኮት አንድ የሚሆኑ ሦስት አካላት ከመወሰን፣ከቁጥር ሕግ ሁሉ የራቁ ናቸው" ቅዱስ
ዘካርያስ ዘእስክንድርያ/ሃይማኖተ አበው ምዕ.108 ቁ.2
 "አብ አዳምን እንደፈጠረ ወልድም በአርያውና በአምሳሉ ፈጥሮታል፤ ወልድ አዳምን በአርያውና በአምሳሉ
እንደፈጠረው መንፈስ ቅዱስም በራሱ መልክ ፈጥሮታል" አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምስጢር ገጽ 39/
 "አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ በአካል ሦስት እንደሆኑ በባሕርይ ሦስት ብለን የምናምን አይደለንም፡፡ በአካል ሦስት ብለን
በባሕርይ አንድ ብለን እናምናለን እንጂ፡፡ አሐዱም(አንድ) ስላልን ከፍጥረት ሁሉ አስቀድሞ የነበረ አዳም በአካል አንድ
እንደሆነ በአካል አንድ ብለን የምናምን አይደለም፡፡ በባሕርይ አንድ ብለን በአካል ሦስት ብለን እናምናለን እንጂ" ቅዱስ
ኤፍሬም ሶሪያዊ/ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ/
 "የሚሰገድላቸው ሦስት ስሞች የማይቀላቀሉ ሦስት አካላት በአንድ ፈቃድ፣በአንድ ጌትነት፣በአንድ ሥልጣን፣ በአንድ
ሥራ ጸንተው የሚኖሩ እንደሆኑ እንታመናለን" ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ሊቀ ጳጳስ ዘአንጾኪያ/ሃይማኖተ አበው ምዕ.92 ቁ.2/

3.4 ምሥጢረ ሥላሴን የሚያስረዱ ተፈጥሮአዊ ምሳሌች


ምሥጢረ ሥላሴን በምሳሌ ማስተማር ይቻላልና አይቻልም የሚሉ ሁለት አሳቦች አሉ፡፡ አንዳንድ ሊቃወንት
የሥላሴ ባሕርይ ረቂቅና የማይመረመር ስለሆነ በምሳሌ ማስተማር ጉዳዩን ስለሚያቀለው በፍፁም በምሳሌ ማስተማር
አይገባም፡፡ ሲሉ አብዛኛው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ደግሞ ምሳሌ ከሚመስልለት ነገር ቢያንስም በምሳሌ ማስተማር ይገባል
በማለት አሳባቸውን ይገልጣሉ፡፡
ለዚህም ክብር ምስጋና ይግባውና የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በምሳሌ ማስተማር አብነት
ያደርጋሉ፡፡ "መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፡፡ ያለ ምሳሌ ግን
አልነገራቸውም" እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ /ማር. 4፡33/ እንዲል፡፡
ስለዚህ ምንም ምሳሌና ወደር የሌለውን፣ ረቂቅና ከአእምሮ በላይ ምጡቅ የሆነውን፤ ባሕርየ ሥላሴን፤ ምሳሌ
ከሚመሰልለት ነገር ያንሳል /ምሳሌ ዘየኃጽጽ/ ብለን የሰው አእምሮ በሚረዳው መጠን አበው ሊቃውንት ምሥጢረ ሥላሴን
ሲያብራሩ የተጠቀሙባቸውን ምሳሌያት በጥቂቱ በማንሳት እናስረዳለን፡፡

8
ሀ. የሰው ነፍስ
ነፍስ በአካሏ ከሦስት የማትከፈል አንዲት ናት፡፡ አንዲት ስትሆን ግን በባሕርይዋ እንደ ቅድስት ሥላሴ ሦስት
ከዊን(መሆን) አላት እነዚህም ከዊነ ልብ፣ ከዊነ ቃል፣ ከዊነ እስትንፋስ ናቸው። ነፍስ በባሕርይዋ ሦስት ከዊን ስላላት አካሏን
ከሦስት አይከፍለውም፡፡
ስለዚህ፡-
 የልብነቷ ከዊን(ልብ መሆን) ከቃሏና ከእስትንፋሷ ከዊን ሳይለይ በራሱ ከዊን ከሥጋዊ ልብ ጋር ይዋሐዳል
 የቃልነቷ ከዊን ከልብነቷ ከዊንና ከእስትንፋሷ ከዊን ሳይለይ በራሷ ከዊን ከሥጋ አንደበት ጋር ይዋሐዳል፡፡
 የእስትንፋስነቷ ከዊን (ህይወት መሆኗ) ከልብነቷ ከዊንና ከቃልነቷ ከዊን ሳይለይ በራሷ ከዊን ከሥጋ እስትንፋስ ጋር
ይዋሐዳል "ንግበር ሰብአ በአርዓያነ ወበአምሳልነ = ሰውን በመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር "መባሉ ለዚህ ነው /
ዘፍ 1፡26/
የተወደዳችሁ ኦርቶዶክሳዊያን ይህቺ ነፍስ አንዲት ስትሆን ሦሰት ኩነታት(መሆኖች) ይታዩባታል እነዚህም ልብ መሆን፣
ቃል መሆን፣ እሰትንፋስ መሆን፡፡ ይሁን አንጂ ሦሰት ነፍስ አትባለም፡፡ ለዚህም ነው ሰው ማሰብ፣ መናገር፣ መተንፈስ (ህያው
ሆኖ መኖር) የተቻለው፡፡ ስለዚህ ማሰቡ በአብ፣ መናገሩ በወልድ፣ መተንፈሱ በመንፈስ ቅዱስ ይመሰላል ማለት ነው፡፡
"ሐሳብ ወይም ልቡና ንግግርን ይዋሐዳል፣ ሰው ዝም ብሎም ኾነ ወይም እየተናገረ ቃላት ዘወትር ከአርሱ ጋር ናቸው እንጂ
ከሐሳቡ አይለዩም ወይም አይቋረጡም፡፡ በዚሁ ዓይነት ዘልዓለማዊው ወልድ ከአብ የሚወለደው ሳይለያዩ አንጂ ከተወለደ
በኋላ ተለያዩ አይባልም፡፡
በሰው ባሕርይ ልቡና ወይም አሳብ እንዲሁም የንግግር ቃላት ነፍስ ያላቸው መሆናቸውና ይኸውም ነፍስ ሕይወታቸው
መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ እንደዚሁም አብና ወልድ መንፈስ ወይም ሕይወት ማለት እስትንፋስ አላቸው፡፡ እርሱም መንፈስ ቅዱስ
ነው፡፡
ቃል ወይም ንግግር የሚገኘው አሳብና ሕይወት ሲኖር ነው፡፡ አሳብ ወይም ልቡና የሚኖረው በልቡና ውሰጥ ካሉት
ቃላትና አስትንፋስ ጋር ነው፡፡ እንዲሁም ሕይወት ወይም እስትንፋስ ካለ አሳብ፣ የንግግርና ቃላት ይኖራሉ፡፡
እንግዲህ እነዚህ ሦስቱ ኹኔታዎች ማለት አሳብ፣ የንግግር ቃላትና እስትንፋስ ወይም ሕይወት አብረው እንደሚኖሩ፤
ማለት ያንዱ መኖር ሌላውም ያለ ለመሆኑ ማስረጃ ስለሚሆን ሦስቱም በአንድነት ይኖራሉ እንጂ አንዳቸውም ከሌላው በፊት
አይደሉም፡፡ ወይም ደግሞ ሌላው በኋላ ተገኘ ማለት አይቻልም በዚሁም ዓይነት አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ለቅጽበተ ዐይን
ያህል ጊዜ እንኳ አይቀዳደሙም" / አሥራት ገ/ማርያም፣ ትምህርተ መለኮት፣ 1983 ዓ.ም/ ዮሐ.14፡8-11
ለ. እሳት
እሳት የማይከፋፈል ሦስት ከዊን(መሆን) አለው እሳቱ ግን አይከፋፈልም እነዚህ ኩነታትም(መሆኖችም)፦
ከዊነ ነበልባል፣ ከዊነ ብርሃን፣ ከዊነ ዋዕይ (ነበልባል መሆን፣ብርሃን መሆን ሙቀት መሆን) ናቸው፡፡
በነበልባሉ አብ፣ በብርሃኑ ወልድ፣ በዋዕዩ(ሙቀቱ) መንፈስ ቅዱሰ ይመሰላሉ፡፡የእሳቱ ነበልባል ከእንጨት ወይም
ከፈትልና ከዘይት ጋር ተዋሕዶ ብርሃንና ሙቀትን ይሰጣል፡፡ብርሃን ከነበልባልና ከዋዕየ ተከፍሉ/መለየት/ ሳይኖርበት በራሱ

9
ከዊን ከዓይን ብርሃን ጋር ይዋሐዳል፡፡ልክ እንደዚሁ ሁሉ ወልድም በቃልነት ከዊን /ቃል በመሆን/ ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣
ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በተለየ አካሉ ሰው ሆነ፡፡
የእሳት ብርሃን ከዐይን ብሌን ጋር በተዋሐደ ጊዜ ነበልባልና ዋዕይ(ሙቀት) እንደማይዋሐዱ አካላዊ ቃል ወልድ ሰው
በሆነ ጊዜ መለኮት አንድ ስለሆነ አብና መንፈስ ቅዱስ ተዋሐዱ አያሰኝም፡፡ በባሕርይ አንድ ሲሆን ከዊን ይለየዋልና፡፡
"አብየ እሳት ውእቱ ወአነ ብርሃኑ ወመንፈስ ቅዱስ ዋዕዩ = አባቴ እሳት ነው እኔም ብርሃኑ ነኝ መንፈስ ቅዱስም ዋዕዩ /
ሙቀቱ/ ነው" ቀሌምንጦስ
"አብ እሳት ወልድ እሳት መንፈስ ቅዱስ እሳት አሐዱ ውእቱ እሳተ ሕይወት ዘእምዓርያም አብ = እሳት ነው ወልድ እሳት ነው
መንፈስ ቅዱስ እሳት ነው በልዕልና ያለ አነድ የሕይወት እሳት ነው" አባ ሕርያቆስ

ሐ. ፀሐይ
ፀሐይ በተፈጥሮ አንዲት ስትሆን በባሕርየዋ ግን ሦሰት ከዊን አላት ከዊነ ክበብ፣ ከዊነ ብርሃን፣ ከዊነ ዋዕይ (አካል
መሆን፣ብርሃን መሆን፣ምቀት መሆን) በዚህም መሠረት አብ በክበቡ፣ ወልድ በብርሃኑ መንፈስ ቅዱስ በዋዕዩ /ሙቀቱ/
ይመሰላሉ፡፡ የፀሐይ ብርሃን ከክበቡ(አካሉ)ና ከዋዕዩ ተፈልጦ ማለትም ተከፍሎ ሳይኖርበት በራሱ ከዊን ከዓይን ብርሃን ጋር
ይዋሐዳል፡፡ እንደዚሁም ወልድ በቃልነቱ ከዊን (ቃል በመሆን) ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በተለየ አካሉ ሰው ሆነ፡፡
ብርሃነ ፀሐይ ከዐይን ብርሃን ጋር በተዋሐደ ጊዜ ክበቡና ዋዕዩ እንደማይዋሐዱ ወልድ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን
ከቅድሰት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው በሆነ ጊዜ መለኮት አንድ ስለሆነ አብና መንፈስ ቅዱስ ሰው
ሆኑ /ሥጋ ለበሱ/ አያሰኝም፡፡
"ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል በማኅፀነ ድንግል ማርያም አደረ ብለን የምንናገረው የመለኮት ተዋሕዶ በወልድ ቃልነት ስላለው
ከዊን ነው አንጂ በአብና በመንፈስ ቅዱስ ስላለው ከዊን አይደለም፡፡ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ብቻ ሰው ለመሆን
በማኅፀነ ድንግል ማርያም አደረ እንላለን እንጂ አብ መንፈስ ቅዱስ ሰው ለመሆን አደሩ አንልምና" /አግናጥዮስ 7 ኛ
መልእክት/
ሁልጊዜም ቢሆን የፀሐይ ብርሃንና የፀሐይ ሙቀት ከፀሐዩ አካል(ክበብ) ጋር አብረው ያሉ እንደመሆናቸው ቀዳሚትና
ተከታይነት የላቸውም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንዱ ከአብ የተወለደ አንዱ ከአብ የሰረፀ መሆኑ
ቢታመንም አንዱ ከሌላው የሚቀድም ሌላውም የሚከተል አይደለም "አሐቲ ቅድምናሆሙ ለሥላሴ = ለሥላሴ ቅድምና
አንዲት ናት" እንዲል፡፡
ማጠቃለያ
ምሥጢረ ሥላሴ ከሙሉ በከፊሉ ከብዙ በጥቂቱ ተፈጸመ፡፡ ይህ የመጀመሪያ ምሥጢር የእግዚአብሐየርን አኗኗር
የምናጠናበት እንደመሆኑ ቀላል አይደለም:: ግን ደግሞ ከባድ ነው ተብሎ አይተውም የሩቁን
ለማቅረብ፣የረቀቀውን ለማጉላት ተፈጥሮአዊ ምሳሌዎች እየተጠቀሱ ለማጥናት ተሞክሮአል፡፡ ልክ እንደ
እሳት መሞቅ መሆኑ ነው፡፡ እሳትን ተጠግተው እንሙቅህ ቢሉት ያቃጥላል፤ርቀን እንሙቅህ ቢሉትም
ልምላሜ ሙቀቱን ማግኘት አይቻልም ሳይርቁትና ሳይጠጉት የሞቁት ጊዜ ግን ተፈላጊውን የእሳት ጥቅም

10
ማግኘት ይቻላል፡፡ ልክ እንደዚሁ ካባድ ነው ብለን ሳንተወው፣ቀላል ነው ብለንም ሳንዳፈረው በዕውቀታችን
አቅም ነው ይህንን ምሥጢር ያጠናነው፡፡
በመሆኑም የተረዳኸውን(ሽውን) በሌሎች ጥናቶች እንደምታዳብረው(ሪው) ተስፋ ከማድረግ ጋር እነዚህ
ኦርቶዶክሶች ሦስት አምላክ ያመልካሉ የሚለውን በሬ ወለደ ዓይነት ነቀፋ ውድቅ የሚያደርግ እውቀት
ሸምተሃል(ሻል) ተብሎ ይገመታል፡፡ ከዚህ በኋላ ባለህ(ሽ) አቅም ቅዱሳት መጻሕፍትን በመመርመርና
መምህራንን በመጠየቅ ከራስህ(ሽ) አልፈህ(ሽ) ሌላውን የምታድንበትን(ኚበትን) መንገድ መፍጠር
ይጠበቅብሃል(ሻል)
እንግዲህ የሃይማኖት መሠረት የሆነውን ምሥጢረ ሥላሴን ከተማሩ በኋላ ምሥጢረ ሥጋዌን መማር ይገባል ይህንን
ምሥጢር ሳይማሩና ሳይረዱ ግን ምሥጢረ ሥጋዌን ለመማር መሞከር በክህደት ቁልቁለት ላይ ሆኖ እንደመጫወት ነው።

ዋቢ መጻሕፍት (Biblography)
 መጽሐፍ ቅዱስ፣በአማርኛ ብሉይና ሐዲስ፣ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ፣1980 ዓ/ም።
 The Holy Bible, London, The British and foreign Bible Society Great Britain, Combridge
university press
 ፍኖተ ሕይወት ፣አባ ማትያስ የካናዳ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣(ዓ.ም የለውም)።
 ፍኖተ እግዚአብሔር፣ብፁዕ አቡነ ቶማስ ሊቀ ጳጳስ፣የካቲት ፣1990 ዓ.ም።
 አምስቱ አዕማደ ምሥጢር፣በተስፋ ማ/ቤት የታተመ ፣1959 ዓ.ም።
 መሠረተ ሃይማኖት፣ሊቀ ትጉሃን ኃ/ጊዮርጊስ ዳኘ፣ 2004 ዓ.ም።
 ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፣1990 ዓ.ም. አዲስ አበባ፣ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት
 ወንጌል ቅዱስ ትርጓሜ፣ተስፋ ገብረ ሥላ የታተመ፣1985 ዓ.ም።
 Doctrion of Man (Father Jocy), ያልታተመ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ማስተማሪያ
“ሞጁል”፣ 2006 ዓ.ም።
 ቅዳሴ ማርያም አንድምታ(ትርጓሜ)፣ትንሣኤ ማተሚያ ድርጅት፣1983 ዓ.ም. The Ethiopian
Orthodox Church(E.O.T.C.) Faith and Order,The Enterthronement of the third
Patriarch,Addis Ababa 1968

11

You might also like