Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 4

አወሊያ አጠ/ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አማርኛ ትምህርት ክፍል

ዘይቤ
1. የዘይቤ ምንነት
- ዘይቤ ማለት ለአገላለፅ ትኩስነትና ጥንካሬ ለመስጠት ሲባል ከመደበኛው የቃላት ፍች ወይም የቃላት አደራደር ስርዓት ሆን
ብሎ ማፈንገጥ ነው ፡፡
- ዘይቤ የምናስተላልፈው መልዕክት ምስል በመፍጠር መልዕክቱ ጎልቶ፣ቦግ ብሎ፣አምሮና ደምቆ እንዲታይ ለማድረግ
የምንጠቀምበት አባባል ወይም የአነጋገር ስልት ነው ፡፡
- ዘይቤ አንድን ሁኔታ የሚገልፀው የቃላትንና የሀረጋትን ትርጉምና አገባብ ከተለመደው እና በውል ከታወቀው ወጣ ወይም
ለየት በማድረግ ለሀሳብ ላቅ ያለ ደረጃ ወይም ከፍታ በመስጠት ነው ፡፡
2. የዘይቤ አይነቶች
ሀ. አነፃፃሪ ዘይቤ
- ሁለት በተፈጥሮ የማይመሳሰሉ ነገሮችን በመውሰድ በማወዳደር ወይም በማነፃፀር በመካከላቸው ያለውን አንድነትና ልዩነት
በማውጣት አንዱን በሌላው አጎልብተን ሀሳባችንን የምንገልፅበት የዘይቤ አይነት ነው ፡፡
- አነፃፃሪ ዘይቤ እንደ፣መሰለ፣ይመስል፣ይመስላል፣ያህል፣ያህላል …. በሚሉ የማነፃፀሪያ ቃላት የሚመሰረት የዘይቤ አይነት ነው
፡፡

ምሳሌ ፡-
1. ጉንጫቸው ጎንና ጎኑ የተጠራመሰ የጉልት ጣሳ ይመስላል፡፡
2. የቤቱ በር ጋኔን እንዳጣመመው አፍ ስልቱን ስቶ በቅጡ አይገጥምም፡፡
3. ጥቁር ከንፈራቸውን ብልጥጥ ሲያደርጉት ጥርስ አልባው ድዳቸው ከከሰል ጫፍ ላይ ያለ ፍም መሰለ፡

4. ጥበቃው እንደውሻ ጅራቱን መቁላት ይወዳል፡፡
5. እሺም አላለችኝ እምቢም አላለችኝ፤
እንደ ጠመዥ ቆሎ ስቃ ዝም አለችኝ፡፡

ለ. ተለዋጭ ዘይቤ

- የአንዱን ባህሪ ለሌላ በመስጠት የሚፈጠር የዘይቤ አይነት ነው፡፡

ምሳሌ ፡-
1. ሽማግሌው ሽንቁር ጋን ናቸው፡፡
2. ጓደኛዬ የቀን ጅብ ነው፡፡
3. በቅሎ ነች፡፡
4. የልጁ እግር ብረት ነው፡፡
5. ነገር ያላምጣል፡፡
6. ትርንጎ ነሽ አሉ የምትገመጪ፤
ከሆዴ ገብተሻል አርፈሽ ተቀመጪ፡፡

ሐ. ሰውኛ ዘይቤ

- የሰውን ልዩ ልዩ ባህርያት፣ ድርጊትና ችሎታ ሰው ላልሆኑ ነገሮች ለእንስሳት፣ለተክሎች እና ለግዑዛን በመስጠት የሚፈጠር
ዘይቤ ነው፡፡

ምሳሌ ፡-
አዘጋጅ ፡- መምህር ዩሱፍ
ሚያዚያ 19/ 2015 ገፅ- 1
አወሊያ አጠ/ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አማርኛ ትምህርት ክፍል

1. ጀምበር አንገቷን ደፋች፡፡


2. እሳቱ ሳቀ፡፡
3. ታሪክ በድዱ ሳቀብኝ፡፡
4. ሰማዩ ለምቦጩን ጥሏል፡፡
5. ደብተሩ አፍጥቶ ተመለከተኝ፡፡
6. የጎበዝ ማጭድ ታስታውቃለች፤
ራሷን ታማ ሻሽ ጠምጥማለች፡፡

መ. እንቶኔ ዘይቤ

- በአጠገብ የሌለን ሰው ወይም ሰው ያልሆነን ነገር በቅርብ እንዳለ እንደሚሰማና መልስ እንደሚሰጥ በመቁጠር ጥያቄ
በመጠየቅ፣በመማፀን፣ በማወያየት፣ በመውቀስ፣ በማስተዛዘን፣ በመለመን ወይም በማሳሳቅ ላይ የሚመሰረት የዘይቤ አይነት
ነው፡፡

ምሳሌ ፡-
1. ተናገር አንተ ሀውልት!
2. መስክሪ አንቺ ፀሐይ!
3. ምነው ፀሐይቱ ፊትሽ ጠቆረ?
4. አጫውተኝ እንጂ ተራራው!
5. ኧረ ጥራኝ ጫካው ኧረ ጥራኝ ዱሩ
ላንተም ይሻልሀል ብቻ ከማደሩ፡፡

ሠ. አያዎ ዘይቤ

- ሁለት ተቃራኒ ሀሳቦችን በሚይዙ ሀረጎች ወይም አረፍተ ነገሮች ውስጥ የሚታይ የዘይቤ አይነት ነው፡፡
- አያዎ ዘይቤ አይ ወይም አይደለም እና አዎ ከሚሉ ሁለት ቃላት የተመሰረተ ዘይቤ ነው፡፡

ምሳሌ ፡-
1. እያዩ አለማየት
2. የጠገበ ርሃብተኛ
3. የጠኔ ቁንጣን
4. ላለመማር መማር
5. እየፈጩ ጥሬ
6. የትኛው ነው ፅድቁ የመኖር ክልሉ፤
እያሉ አለመኖር መኖር እየሌሉ፡፡

ረ. ምፀት ዘይቤ

- ምፀት ዘይቤ ያመሰገነ መስሎ ማውገዝን፣ የደገፈ መስሎ መቃወምን፣ ያከበረ መስሎ ማዋረድን፣ ….. የሚያመለክት ዘይቤ
ነው፡፡
- ምፀት ዘይቤ በግልፅ የሚታየውንና ፊት ለፊት የሚገለፀውን ሀሳብና ድርጊት በተገላቢጦሽ ወይም በተቃራኒው የምንገልፅበት
የዘይቤ አይነት ነው፡፡

ምሳሌ ፡-

አዘጋጅ ፡- መምህር ዩሱፍ


ሚያዚያ 19/ 2015 ገፅ- 2
አወሊያ አጠ/ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አማርኛ ትምህርት ክፍል

1. ወፍራሙን ሰው ቀጮ
2. ጥቁሩን ሰው ፈረንጁ/ ቀዮ
3. አጭሩን ዛፉ
4. ፈሪውን ጀግናው/ደፋሩ
5. መላጣውን ጎፈሬው

ሰ. ግነት ዘይቤ

- ግነት ዘይቤ አንድን ሀሳብ ከዘወትራዊው በተለየ ሁኔታ አግዝፈንና ኳሽተን በመግለፅ አድማጭን ወይም አንባቢን ለማሳመን
የምንጥርበት ዘይቤ ነው፡፡
- ግነት ዘይቤ ያለውን ነገር በቋንቋ አማካኝነት በአይነ ህሊናችን እንዲታይና ፈክቶ እንዲታየን የሚያደርግ ነው፡፡

ምሳሌ ፡-
1. የክፍል አለቃችን ሲቆም የፀሐይ ግርዶሽን ይፈጥራል፡፡
2. የቆዳዋ ንጣት ከውስጥ የሚዘዋወረውን ደሟን ያሳያል፡፡
3. ቤቱ ፈረስ ያስጋልባል፡፡
4. የእጅ ጣቷ ያለ አጥንት የተሰራ ነው፡፡
5. አንገቷን ቢቆርጧት ሆድ እቃዋ ይታያል፡፡
6. ደብረ ታቦር ሆና ድምጿን ብታሰማኝ፤
እኔን ጉለሌ ላይ ጨርቄን ንፋስ ቀማኝ፡፡

መልመጃ - 1

ሀ. የሚከተሉት አረፍተ ነገሮች የያዙት ሀሳብ በየትኛው የዘይቤ አይነት እንደተዋቀረ ግለፁ ፡፡

1. አየሽ አንቺ እናት አለም ቃል የእምነት እዳ እንጂ የአባት የእናት እኮ አይደለም፡፡


2. ደመኛውን ጃርት የበላው ዱባ አስመሰለው፡፡
3. ዉቢት እሁድ ጠዋት ከቤት ውልቅ ያለች አፍታም ሳትቆይ ሰኞ ከሰዓት ተመለሰች፡፡
4. ጥርሷ ወደ ውጭ የገፋው ከንፈሯ አሞጥሙጦ ሊናድ የደረሰ የኩበት ክምር ይመስላል፡፡
5. የቅንድቤን አንዲት ፀጉር ነቅዬ ወደ ወለሉ ብጥላት የምታወጣው ድምፅ ውንጌት ይሰማል፡፡
6. ለወሬ/ለነገር ሲሉህ ጆሮህ መቃብር ውስጥ ያለ የምስጥ እንቅስቃሴ ይሰማል፡፡

ለ. የሚከተሉት የግጥም ስንኞች በየትኛው የዘይቤ አይነት እንደተዋቀሩ አመልክቱ፡፡

1. አለምን መውቀሱ ይቅርብን ተነቅፏል፤


ሰው ሲስቅ ማልቀሱ መሆኑ ተገልጿል፡፡
2. ጉልበቱ እንደ አንበሳ ነብር የመሰለ፤
እንደ ጦር ተሰብቆ ስንቱን አቆሰለ፡፡
3. እያየም ለማያይ ማየት ላልፈለገ፤
በራስ መውደድ እበት አይኑን ለመረገ፡፡
4. በዱልዱም ቢቀርፁት ብዕር አለቀሰ፤
ጥቁር ቀለም ሳይሆን ደም እያፈሰሰ፡፡

አዘጋጅ ፡- መምህር ዩሱፍ


ሚያዚያ 19/ 2015 ገፅ- 3
አወሊያ አጠ/ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አማርኛ ትምህርት ክፍል

አዘጋጅ ፡- መምህር ዩሱፍ


ሚያዚያ 19/ 2015 ገፅ- 4

You might also like