Professional Documents
Culture Documents
መንፈሳዊ ወግ
መንፈሳዊ ወግ
መንፈሳዊ ወግ
ገና በጎዳና
ሁለት የጎዳና ልጆች የገና ዋዜማ አመሻሽ ላይ፣ ጎዳና ዳር ቁጭ ብለው አላፊ አግዳሚው ለዓመት
በዓሉ ሲራወጥ ያያሉ፡፡ ዶሮ ያንጠለጠለ፣ በግ የሚጎትት፣ ቄጤማ የቋጠረ፣ በሬ የሚነዳ፣ እህል ያሸከመ፣
‹የገና ዛፍ› የተሸከመ፣ አብረቅራቂ መብራት የጠቀለለ፣ ዋዜማ ሊቆም ወደ ቤተ ክርስቲያን ነጭ ለብሶ
የሚጓዝ፣ ምሽቱን በዳንስ ሊያሳልፍ ሽክ ብሎ ወደ ጭፈራ ቤት የሚጣደፍ፣ ብቻ ምኑ ቅጡ፣ ከተማዋ
ቀውጢ ሆናለች፡፡
እነርሱ ደግሞ የተበጫጨቀች ልብስ ለብሰው፣ የደረቀ ዳቦ ይዘው፣ በቢል ቦርድ ላይ የተለጠፈውን
የጥሬ ሥጋ ሥዕል እያዩ፣ መጣሁ መጣሁ የሚለው የገና ብርድ እያቆራመዳቸው፣ የቆሸሸ
ሰውነታቸውን እየፎከቱ፣ የቀመለ ፀጉራቸውን እያከኩ፣ በታኅሣሥ 15 እና በታኅሣሥ 29 መካከል
ያለው ልዩነት ጠፍቷቸው፣ የበግ ድምጽ እንጂ ሥጋው ርቋቸው፣ የበሬው ፎቶ እንጂ ሥጋው
ጠፍቶባቸው፣ ያገኙትን ወረቀት እያነደዱ ጎዳናው ዳር ተቀምጠዋል፡፡
‹ካመጣኸውማ ገናኮ የመውረድ በዓል ነበር፡፡ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወረደ የሚባልበት በዓል
ነበር፡፡ አሁን ግን የሚወጣ እንጂ የሚወርድ የለም፡፡ ወደ እኛ የሚወርድ የለም፡፡ ሰው አምላክ
መሆን ቢያቅተው አምላክ ሰው ሆነ ይላሉ፡፡ እኛ እንደነርሱ መሆን አቅቶናል፤ ታድያ ምናለ
እነርሱ እንደኛ ቢሆኑ፡፡ በጣም የሚገርመው ሰብአ ሰገል ስጦታ የሰጡት ራቁቱን ለነበረው፣ ቤት
ላጣው፣ የቤተልሔም ሰዎች አላስጠጋ ላሉት፣ ከሰው ወገን ጠያቂ ላልነበረው ለክርስቶስ ነበረ
እንጂ ሁሉ በእጃቸው፣ ሁሉ በደጃቸው ለሆኑት ለቤተልሔም ሰዎች አልነበረም፡፡ ዛሬ ግን
ስጦታው ለቤተ ልሔም ሰዎች ሆነ፡፡››
‹አንድ ቀን አንድ ሰው ሲያስተምር ምን ሰማሁ መሰለህ፡፡ ክርስቶስ ‹ተርቤ አላበላችሁኝም፣
ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም› ይላል፡፡ የሰሙት ሰዎች ‹የት አግኝተን እናብላህ እናጠጣህ› ቢሉት
‹ለታናናሾቹ ካላደረጋችሁ ለእኔ አላደረጋችሁትም፣ ለታናናሾቹ ካደረጋችሁ ለእኔ
አድርጋችሁታል› አላቸው አሉ፡፡ ታድያ ከኛ የባሰ ታናሽ ማን አለ? ያኔምኮ ክርስቶስ ተራ፣
ድኻ፣ እዚህ ግባ የማይባልና የተናቀ መስሎ ስለመጣ ነው የቤተልሔም ሰዎች ያላስጠጉት፡፡ ዛሬስ
ድንገት ከእኛ መካከል ቢኖርስ፣ እዚህ ጎዳና ዳር ከውሾቹ ጋር ተኝቶ ቢሆንስ፤ በገዛ የልደቱ ቀን
ሰዎች እርሱን ንቀው እያለፉ፣ ተጸይፈው እያለፉ፣ በጽድና በከረሜላ፣ በበግና በዶሮ፣ በጠላና
በጠጅ፣ በፖስት ካርድና በስጦታ የራሱን በዓል እያከበሩለት ቢሆንስ፤ ››
(በዳንኤል ክብረት)