Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 7

ጸሎት

በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

ጸሎት ጸለየ፡- ለመነ፣ ጠየቀ አማለደ፣ ማለደ ካለው የግዕዝ ቃል የወጣ ቃል ነው፡፡ ጸሎት ማለት ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው
ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር እግዚአብሔርን ማመስገን መለመን፣ መጠየቅ፣ መማለድ፣ መማፀን ነው፡፡ “ጸሎት ብሂል ተናግሮ ምስለ
እግዚአብሔር፡፡” አባታችን አዳምም ከመላእክት ተምሮ በየሰዓቱ ይጸልይ ያመሰግን ነበር፡፡ ዲያብሎስ በእባብ አድሮ ወደ አዳም በመጣ
ጊዜ ጸሎት እያደረገ ስለነበር ዲያብሎስን ድል ነሥቶታል ሔዋንን ግን ሥራ ፈትታ እግሯን ዘርግታ ስለአገኛት ድል ነስቷታል፡፡

ጸሎት ሰማእታት ከነደደ እሳት፣ ከተሳለ ስለት፣ ከአላውያን መኳንንት፣ ከአሕዛብ ነገሥታት ከዲያብሎስ ተንኮል እና ሽንገላ ዲያብሎስ
በእነርሱ ላይ ከአጠመደው አሽከላ የዳኑበት ጋሻ ነው፡፡ ኤፌ.6፥10 21 ጸሎት፣ ሰው አሳቡን ለእግዚአብሔር የሚገልጥበት እግዚአብሔርም
የሰውን ልመና ተቀብሎ ፈቃዱን የሚፈጽምበት ረቂቅ ምስጢር ነው፡፡
ከዚህ በታች በቀረቡት ጥቅሶች ውስጥ ስለምን እንደተጸለየ በመለየት እግዚአብሔር እኛንም በምን ጉዳዮች ላይ እንድንጸልይ
እንደሚያበረታታን አመልክት፡፡

1ዜና 4፡10

መዝሙር 18፡1

መዝሙር 22፡1-2

መዝሙር 143፡9

ማቴዎስ 6፡11

ፊሊጵሲዮስ 4፡6-7

የጸሎት መሠረቱ “ዕሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኋል ደጁ ምቱ ይከፈትላችኋል” የሚለው የጌታችን ትምህርት ነው ማቴ.7፥7

ጸሎት፡- በሦስት ክፍል ይከፈላል

ጸሎተ አኰቴት

ጸሎተ ምህላ

ጸሎተ አስተብቊዖት
ጸሎተ አኰቴት፡- ማለት እግዚአብሔርን ከሁሉም አስቀድሞ ስለተደረገልን ነገር በማመስገን የሚጀመር ጸሎት ነው ይህም ዓይነት ጸሎት
የቅዱስ ባስልዮስን የምስጋና ጸሎት የመሰለ ነው፡፡

“ነአኲቶ ለገባሬ ሠናያት ላዕሌነ እግዚአብሔር መሐሪ”

“ለእኛ በጎ ነገርን ያደረገ ይቅርባይ እግዚአብሔር አምላካችንን እናመሰግነዋለን” ይልና ምክንኀያቱን ሲገልጥ ጠብቆናልና፥ አቅርቦናልና፥ ወደ
እርሱም ተቀብሎናልና፥ እስከዚችም ሰዓት አድርሶናልና” ይላል፡፡ /ሥርዐተ ቅዳሴ/ ይህ ጸሎት የምስጋና ጸሎት /ጸሎተ አኰቴት/ ይባላል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን የምስጋና ጸሎት ለፊልጵስዮስ ክርስቲያኖች ሲጽፍላቸው “ነገር ግን በሁሉ ነገር ጸልዩ ማልዱም እያመሰገናችሁም
ልመናችሁን ለእግዚአብሔር ግለጡ” ይላል፡፡ ፊል.4፥6 ዳግመኛም “ስለእናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ
ስለተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር እግዚአብሔርን አመስግነዋለሁ” 1ቆሮ.1፥4 ብሎ ከመለመን አስቀድሞ እግዚአብሔርን ማመስገን አስፈላጊ
መሆኑን አስተምሯል፡፡ በዚህ መሠረት ሰው የተደረገለትን በጎ ነገር ሁሉ በማሰብ ፈጣሪውን ማመስገን ከማመስገንም ቀጥሎ
የሚያስፈልገውን ከፈጣሪው መለመን አስፈላጊ ነው፡፡

ከቅዱስ ጳውሎስ የምንማረው ለእኛ ስለተደረገልን ብቻ ማመስገንን አይደለም፤ ሌሎች ስለተደረገላቸውም ማመስገን ተገቢ መሆኑን እንጂ፡፡
“ለእናንተ ስለተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ሲል ለወገኖቹ ስለተደረገላቸው በጎ ነገር በደስታ ማመስገኑ ነው፡፡
ክርስትና ማለት ለእኔ ብቻ ማለት ሳይሆን ለሌሎችም መኖር፣ ለሌሎች በተደረገው የእግዚአብሔር ስጦታም ደስ መሰኘት ነው፡፡ ይህን
የምስጋና ጸሎት /ጸሎተ አኮቴት/ ብዙ አባቶች፣ እናቶች ተጠቅመውበታል፡፡ ለምሳሌም ያህል ዘካርያስንና ኤልሳቤጥን መመልከት
እንችላለን፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥ እግዚአብሔር ያደረገላትን በጎ ነገር ስትመሰክር “እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ
በጎበኘን ጊዜ እንዲህ አደረገልኝ” ብላለች፡፡ ሉቃ.1፥25 እግዚአብሔር ጎበኘኝ ብላ ቸርነቱን አደረገለኝም በማለት የተደረገላትን መልካም
ስጦታ ዮሐንስን መጽነሷን ገልጣ አመስግናለች፡፡ ዘካርያስም እንዲሁ አመስግኗል፡፡ “ያን ጊዜም አፉ ተከፈተ አንደበቱም ተናገረ
እግዚአብሔርንም አመሰገነ” ሉቃ.1፥65 “ከዚህ ጊዜ ያደረስከኝ፥ ከደዌ የፈወስከኝ፥ ዮሐንስን የሰጠኸኝ ብሎ ፈጣሪውን አመስግኗል
በመቀጠልም ይቅር ያለን ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን ከባሪያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን
ቀንድ አስነሣልን፡፡” ሉቃ.1፥68 በዘካርያስ ጸሎት ውስጥ ምስጋናውን አስቀድሞ ትንቢቱን አስከትሎ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ምስጋናውና
ትንቢቱ አምላክ ለእኛ ያደረገው የቤዛነቱን ሥራ በመግለጥ ሲያመሰግን እንመለከታለን፡፡

2. ጸሎተ ምህላ፡- ጸሎተ ምህላ ስለፈውሰ ሕሙማን …… ስለ ሀገርና ስለነገሥታት ስለ ጳጳሳት፣ ካህናት ዲያቆናት፣ ምዕመናን ሕይወት
ቸነፈር፣ ጦርነት፣ ረሀብ፣ ድርቅ ወይም ሌላ አስጊ ነገር በሆነ ጊዜ በብዛት፣ በማኅበር የሚጸለይ ጸሎት ነው፡፡ የምህላ ጸሎት ሲጸለይ
በእስራኤል ላይ ቸነፈር በተነሣ ጊዜ አሮን በሽተኞን ባንድ ወገን ጤነኞችን ባንድ ወገን አድርጎ የክህነት ልብሱን ለብሶ ማዕጠንተ ወርቁን ይዞ
በራስህ የማልክላቸውን አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን አስበህ የወገኖችህን ኀጢአት ይቅር በል” እንደጸለየላቸው ነው፡፡ ዘኁ.16፥46-
50

ዛሬም ካህናት ከጠቀስናቸው አስጊ ነገሮች ማንኛውም በሀገር ላይ ቢመጣ ወደ ሀገር እንዳይገባ ገብቶ ቢሆን ከፍ ያለ ጉዳት እንዳያመጣ
የክህነት ልብስ ለብሰው ማዕጠንቱ ይዘው ሥዕለ ማርያም፣ መስቀል አቅርበው ማኅበረ ክርስቲያንን ሰብስበው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን “ስለእኛ
ከድንግል ማርያም መወለድህን ስለእኛ መሠቀል መሞትህን አስበህ የህዝብን ኀጢአት ይቅር በል ከመዓት ወደ ምሕረት ተመለሰ” እያሉ
በምህላ ይጸልያሉ፡፡

የምህላ ጸሎት መአትን መቅሰፍትን ይመልሳል ጦርን፣ ቸነፈርን ያስታግሳል መሠረቱም፡፡


“ጾም ለዩ ምህላ ስበኩ” ያለው ቃል ነው፡፡ ይህ ጸሎት በሰላም ጊዜ ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆን በጦርነት ጊዜ ለመከላከያነት ዋና መሣሪያ ነው፡፡
ስለዚህ አጥብቀን ልንከተለው ይገባል፡፡

የምህላ ጸሎት ነገሠታት ከዙፋናቸው ወርደው ወንድ ሙሽራ ሴት ሙሽራ ከጫጉላቸው፣ ከመጋረጃቸው ለምግብ የደረሱ ልጆች ከምግብ
ለምግብ ያልደረሱ ከጡት ተከልክለው ሕዝብ ሁሉ ምንጣፍ ለብሰው አመድ ነስንሰው የሚጸልዩት ከፍተኛ ጸሎት ነው ኢዩ.2፥12-18፣
ዮና.3፥5

3. ጸሎተ አስብቊዖት

ይህ ጸሎት አንድ ሰው ስለሚፈልገው ነገር ቦታ ለይቶ ሱባኤ ገብቶ የሚጸልየው ጸሎት ነው፡፡ ይህ ጸሎት በተለይ ጣዕመ ጸጋን በቀመሱ
በተባሕትዎ፣ በምናኔ በገዳም በሚኖሩ አበው ዘንድ የተለመደና የሚደረግ ጸሎት ነው፡፡ ወጣንያን እግዚአብሔርን ጠይቀው አድርግ
አታድርግ የሚል መልስን አይጠብቁም፡፡ ፍጹማን አባቶች ግን እግዚአብሔር ጠይቀው አድርግ ወይም አታድርግ የሚል ፈቃደ
እግዚአብሔርን ሳይቀበሉ የሚያደርጉት ነገር የለምና ቦታ፣ ጊዜ ወስነው ፈቃደ እግዚአብሔር ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ጸሎተ አስተብቊዖት
ይባላል፡፡ ይህም ማለት መላልሶ ደጋግሞ ያለ ዕረፍት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚደረግ ጸሎት ነው፡፡ ለምሳሌ ትልቁ መቃርስ ዓለምን ዞሮ
ለመጎብኘት ለተከታታይ አምስት ዓመታት እግዚአብሔርን ከለመነ በኋላ እየዞረ መካነ ቅዱሳንን እንዲጎበኝ ከእግዚአብሔር ፈቃድ
አግኝቷል በዚህም ከእርሱ ከገድል በትሩፋት የሚበልጡ መናንያን በማግኘቱ መነኮሳትማ እነርሱ እንጂ እኔ ምንድን ነኝ? እያለ ራሱን
እየወቀሰ እንደተመለሰ በመጽሐፈ መነኮሳት ተጽፎ እናገኛለን፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን “መስተበቊዕ” የሚባል የጸሎት ክፍል፡፡ አለ ይህ
ጸሎት በካህናት አባቶቻችን ስለሙታን፣ ስለሕያዋን፣ ስለነገሠታት፣ ስለ ጳጳሳት ስለ ንዑሰ ክርስቲያን፣ ስለ ምእመናን መባዕ ስለሚያቀርቡ
ስለነጋድያን፣ ስለዝናም ስለ ወንዞች የሚጸለይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የጸሎት ክፍል ነው፡፡

ጠቅላላውን በቤተ ክርስቲያን የሚጸልዩ ጸሎታት ጸሎተ ፍትሐት፣ ጸሎተ ተክሊል፣ ጸሎተ ህሙማን፣ ጸሎተ ቅዳሴ፣ ጸሎተ ሰዓታት፣ የግል
ጸሎት፣ የማኅበር ጸሎት እነዚህ ሁሉ ከላይ ከዘረዘርዓቸው ሦስቱ የጸሎት ክፍሎች አይወጡም፡፡ ከጸሎተ አኰቴት ከጸሎተ ምህላ፣ ከጸሎተ
አስተበቊዖት ይመደባሉ፡፡ እነዚህን ጸሎታት በሰቂለ ኅሊና በአንቃዕድዎ /ዐይንን ወደ እግዚአብሔር በማንሳት/ መጸለይ ታላቅ ዋጋ
የሚያሰጥ ከሰይጣን ወጥመድ የሚታደግ ሕይወትን የሚስተካከል ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ አጋንንትን የሚያርቅ ኀይለ
እግዚአብሔርን ለሚጸልየው የሚያስታጥቅ መላእክትን የሚያስመስል ነው፡፡

እኛም ሰውነታችን ከበደል ልቡናችን ከቂም ከበቀል እንዲሁም ከተንኮል ንጹሕ አድርገን ብንጸልይ እንጠቀማለን ጸሎታችን ተሰሚ
ልመናችንና ጩኸታችን ግዳጅ ፈጻሚ ይሆናል፡፡ የአባቶቻችን ጸሎት የተቀበለ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታችንን ይቀበለናል፡፡

ይቆየን

ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት

ክርስትና የሕይወት መንገድ ነው፡፡ መንገዱም ደግሞ ወደ ዘላዓለማዊ ክብር የሚያደርስ የሕይወት የድኅነትና የቅድስና መንገድ ነው፡፡
ክርስቲያን ለመሆን በ፵ እና በ፹ ቀን በመጠመቅ የሥላሴ ልጅነትን ማግኘት የቤተ ክርስቲያን አባል መሆን ያስፈልጋል፡፡ በመንፈስ
ቅዱስ ዳግመኛ መወለድ ማለትም ነው፡፡ ይህንንም ጌታችን ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር
የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም›› ብሎ ገልጾታል (ዮሐ.፫፥፫)።
ያመነና የተጠመቀ ሰው የእግዚአብሔርን የጸጋ ልጅነት ያገኛል፡፡ የቤተ ክርስቲያንም አባል ይሆናል፡፡ ከክርስቲያን አንድነትም
ይደመራል፤ ከዓለማዊነት ወደ መንፈሳዊነት ከሥጋዊነት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስነት፤ ከውሸት ወደ እውነት እንዲሁም ወደ
ዘለዓለማዊነት ክብርና ጸጋ ይሸጋገራል፡፡ ኦርቶዶክሳዊነት የማደግና የመሸጋገር ሕይወት ነው፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ ‹‹ከክርስቶስ ጋር
አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና›› ያለን (ገላ.፫፥፳፯)።
ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን እውነት እንዲህ ብሎ ገልጾታል ‹‹የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ
እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ
መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ›› (፩ኛቆሮ.፫፥፲፮)። በመሆኑም ራስን ከማንኛውም ክፋት ርኩስትና ኃጢአት ጠብቆ መኖር
የማንኛውም ክርስቲያን ግዴታ መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ ሕይወት ሸክላ ናት፤ ትሰበራለች፤ አሰባበሯ ደግሞ ለዳግም መጠገን
(ለመነሣት) ዋስትና ነውና ማንነታችን እንይዳቆሽሽ እንዳንጠፋ እርሱንም እንዳናሳዝን ጥንቃቄን ልናደርግ ይገባል፡፡
ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት ሕይወትን በእውነት በአርአያነትና በምሳሌነት እንዲሁም በምግባር የመግለጽና የመኖር ሕይወት ነው፡፡
ይህንንም መጽሐፍ እንዲህ ብሎ ገልጾታል ‹‹ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ›› በማለት (፩ኛ ዮሐ.፫፥
፲፰)። የቃልና የአንደበት ሕይወት ሳይሆን የእውነት ሕይወት ነው ኦርቶዶክሳዊነት፡፡ በሃይማኖትና በፍሬ ራስን የመምራት (የመኖር)
ሃይማኖትን በምግባር የመግለጥ እውነትን (ሕይወትን) በተግባር የመግለጥ ዓለምና የዓለም የሆኑ ነገሮችን የመጥላት ዘወትር ስለ ነገረ
እግዚአብሔር ስለ ቅድስና ሕይወት፤ ስለ ዘለዓለማዊ ጸጋና ክብር እያሰቡ የመኖር ሕይወት ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት ሕይወትና
እውነት ነው፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን ‹‹እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው›› ያለን (ዮሐ.፮፥፷፫)፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት ከኢ-ክርስቲያናው ሥነ-ምግባር ሐሳብ ተግባርና ምኞት እራስን የመጠበቅ ማለትም
ከዝሙት፣ ከውሸት፣ ከዘረኝነት፣ ከመከፋፈል፣ ከንፉግነት፣ ከስግብግብነት፣ ከዓለምና ከገንዘብ ፍቅር ተስፋን ከመቁረጥ እምነት
ከማጣት ከአላስፈላጊ ደስታና ሀዘን ከቁጣ ከንዴት፣ ከብስጭት፣ ከምቀኝን፣ ከግብዝነት ከኩራት ከትምክሕት እራስን የመጠበቅ
የመለየት ሕይወትንም በመልካም ምግባራት እራስን የማስተዳደርና የመምራት ማለትም በፍቅር በሰላም በቅድስና በንጽሕና እንዲሁም
በትሕትና በደግነት ብሎም በየዋሕነትና በቅንነት የመኖር ሕይወት ነው፡፡
ይህንን ቅዱስ ጰውሎስ በዝርዝር እንዲህ ሲል ገልጿል፤ ‹‹ጥበበኞች ነን ሲሉ አላዋቂዎች ሆኑ፥ የማይሞተውን የእግዚአብሔርን ክብር
በሚሞት ሰውና በዎፎች፥ አራት እግር ባላቸውም፥ በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ። ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን
ሊያዋርዱ በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵሰት አሳልፎ ተዋቸው፡፡ የእግዚአብሔርን እውነት ሐሰት አድርገውታልና፤ ተዋርደውም ፍጥረቱን
አምልከዋልና፤ ሁሉን የፈጠረውን ግን ተውት፤ እርሱም ለዘላለም ቡሩክ አምላክ ነው፤ አሜን።››
ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ መቅሠፍትን አመጣባቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባቸውን ትተው ለባሕርያቸው የማይገባውን
ሠሩ፡፡ ወንዶችም እንዲሁ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን ትተው በፍትወት ተቃጠሉ፤ እርስ በርሳቸውም እየተመላለሱ፥ ወንዶች
በወንዶች ላይ የሚያዋርዳቸውን ነውር ሠሩ፤ ነገር ግን ፍዳቸውን ያገናሉ፤ ፍዳቸውም በራሳቸው ይመለሳል፡፡ እግዚአብሔርን ለማወቅ
ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር ይህን የማይገባውን ይሠሩ ዘንድ ሰነፍ አእምሮ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ዐመፅን ሁሉ፥ ክፋትንም፣
ምኞትንም፣ ቅሚያንም፣ ቅናትንም፣ ነፍስ ገዳዮች፣ ከዳተኞች፣ ተንኰለኞች፣ ኩሩዎች፣ ጠባያቸውንና ግብራቸውንም ያከፉ ናቸው፡፡
ሐሜተኞች፣ እግዚአብሔርን የሚጠሉ፣ ተሳዳቢዎች፣ ትዕቢተኞች፣ ትምክሕተኞች፣ ክፋትን የሚፈላለጉ፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ
ናቸው፡፡ የማያስተውሉ፣ ዝንጉዎች፣ ፍቅርም፣ ምሕረትም የሌላቸው ናቸው፡፡ ይህን እንዲህ ላደረገ ሞት እንደሚገባው እነርሱ ራሳቸው
የእግዚአብሔርን ፍርድ እያወቁ፥ እነርሱ ብቻ የሚያደርጉት አይደለም፤ ነገር ግን ሌላውን ያነሣሡታል፤ ያሠሩታልም›› (ሮሜ.፩፥፳፪፥
፴፪)።
ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ሰው በእምነቱ ጸንቶ በምግባሩ የሚያድግ ሰው ነው፡፡ ምክንያቱም ኦርቶዶክሳዊነት የእድገትና የለውጥ ሕይወት
ነውና፡፡ እኔ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ እያለ የማያድግ የማይሻሻል የመንፈስ ተግባራትን የማይሠራ ከትላንትናው ሕይወትና ኑሮው
የማይመለስ እራሱን የማይፈትሽ የማይመረምር ሃይማኖትን በሥራ በእውነትና በተግባር የማይለውጥ ሰው እርሱ ኦርቶዶክሳዊ
አይደለም፡፡
ሃይማኖተኛ (የሃይማኖት ተከታይ) ሰው መሆን ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ ሃይማኖት በሥራና በተግባር መገለጥ አለበትና፡፡ ‹‹ወንድሞቼ ሆይ፥
እምነት አለኝ የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ወንድም ወይም እኅት
ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥ ከእናንተ አንዱም፦ በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን
የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፤ ነገር ግን አንድ
ሰው፦ አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፥ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል።
እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል። አንተ ከንቱ ሰው፥
እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? ብሎ ነግሮናል›› (ያዕ.፪፥፲፬-፳)።
ኦርቶዶክሳዊነትና ዘረኝነት በፍጹም አይገናኙም፤ ማንኛውም ክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊና መንፈሳዊ ሰው (የእግዚአብሔር ሰው ሆኖ)
ዘረኛ፣ ብሔርተኛና ጎጠኛ መሆን አይችልምና፡፡ ይህ የአረማውያን ተግባር ነው፡፡ እኛን የሚገልጸን ፍቅር ሰላም አንድነት አቃፊነት
መተባበር መደጋገፍ ፍትሕ እኩልነት መቻቻል መረዳዳት መደማመጥ መግባባትና በውይይት ማመን ልዩነትንም በመገነዛዘብና
በመነጋገር የመፍታት እሴት ነው፡፡
ይህንን ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ ገልጾታል ‹‹እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤
ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ
እንዳይኖር ታውቃላችሁ። እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን
አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል። ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገው ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም
ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል?›› (፩ኛ ዮሐ.፫፥፲፬-፲፯)፡፡
ኦርቶዶክሳዊነት የእምነት የእውነት የምስጋና ሕይወት ነው፡፡ ለእውነት የመኖርና ለእውነት የመገዛት ጭምር ነው፡፡ ውሸት አስመሳይነት
ማጭበርበር መከፋፈል ማታለል ቃልን ያለማክበር ያለመተማመን ከእኛ መራቅ ያለባቸው የሥጋውያን ባሕርያት ናቸው የጥፋትና የሞት
መገለጫ የአውሬውም መንፈስ ጭምር ናቸው፡፡
ለዚህ ነው መጽሐፍ ‹‹ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥
ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር
የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥
በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ
ራቅ። ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትም የሚወሰዱትን ሁል ጊዜም እየተማሩ እውነትን
ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና›› ብሎ የገለጸው (፪ኛጢሞ.፫፥፩-፯)።
ገንዘብ ጣዖት የሚሆንባቸው (የሆነባቸው) ሰዎች አሉ፡፡ ዓለምን የሚገዛው የገንዘብ ኃይል ነው፡፡ ገንዘብ የጥፋትም የልማትም ኃይል
ነው፡፡ ፍቅረ ንዋይ መንፈሳዊነትን ያሳጣል፡፡ ሃይማኖትንም ያስክዳል፡፡ ከኦርቶዶክሳዊነት ዕሳቤና ክህሎትም እንዲሁም ጸጋና ክብርም
ይለያል፡፡ ዛሬ ለገንዘብ ፍቅር ብለው የሰውን ነፍስን የሚያጠፉ፤ ሰላምን የሚያናጉ፤ ቤተሰብን የሚበትኑ፤ ሀገርን የሚያፈርሱ ስግብግብ
ግለሰቦች አሉ፡፡ ይህ እምነት ካለው ፈጣሪውን ከሚፈራ ከሀገርና ለትውልድም ከሚያስብ ሰው የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ክርስቲያን ከዚህ
አይነት ክፉ ሐሳብና ተግባር በፍጹም ሊርቅ ይገባል፡፡ በገንዘባችን መልካምነትን እንጅ ክፋትን መዝራት የለብንም፤ አንድነትና ፍቅርን
እንጅ ልዪነትን ማስፋት የለብንም፡፡ መልካምነትን እንጅ ክፋትን መዝራት የለብንም፡፡ ጭካኔን ከራሳችን ማራቅ አለብን፡፡ መልካምነትና
ደግነትንም ርህራሄንም ገንዘብ ልንደርግ ይገባል፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ ‹‹ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን
ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና
እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል። መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥
የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ›› ያለን (፩ኛጢሞ.፮፥፲፩-፲፪)።
በሌላም በኩል ‹‹ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥ከእናንተ አንዱም፦ በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥
ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ
የሞተ ነው›› (ያዕ.፪፥፲፭-፲፯)።
ኦርቶዶክሳዊነት በእውነተኛ ሃይማኖት የመኖርና የማመን እውነታ ነው፡፡ (ይሁ.፩፥፫) መንፈሳዊነት ማለት መንፈሳዊ ሰው መሆን ማለት
ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው ደግሞ የራሱ አስተሳሰብና አካሔድ አለው፡፡ መንፈሳዊ ካልሆነ ሰው ግብሩ የተለየ ነው፡፡ መንፈሳዊነት ምናባዊ
የሃይማኖት ሕይወት አይደለም፡፡ መንፈሳዊነት እግዚአብሔርን በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የሚያምኑበት አይደለም፡፡ በሕይወት በእውነት
በምግባር በሃይማኖት የሚገልጡት ነው እንጂ፡፡ መንፈሳዊ ሰው ከሥጋ ሰው በግልጽ የተለየ ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው በውስጡ የመንፈስ
ቅዱስ ኃይል አለው፡፡ ሥጋዊ ሰው ግን ነፍስና ሥጋ እንጂ ለነፍሱ ሕይወትን የሚሰጠውን መንፈስ ቅዱስን የተቀበለ አይደለም፡፡ ይህን
መጽሐፍ እንዲህ ብሎ ገልጾታል ‹‹ለሥጋዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር
ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም››። (፩ኛ ቆሮ.፪፤፲፬-
፲፭) (፩ኛቆሮ.፴፩፥፫፤ሮሜ.፰፥፲፪-፲፮)
መንፈሳዊ ማለት በውስጡ ላደረው መንፈስ ቅዱስ ምስክር የሆነ ሰው ማለት ነው፡፡ በስሜት በወሬና በአሉባልታ የማይመራ ሰው ነው፡፡
ስሜቱን መግታትም የሚችል አርቆ ማሰብ ማየት የሚችል ሰው ነው፡፡ በእምነትና በእውቀት የሚመራ ሰው ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ
መሆኑንም ያውቃል፤ በዚህም ንጽህናና ቅድስናውንም ጠብቆ የሚኖር፤ የምሥጢር ተሳትፎ ያለው፤ ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚቀበልና
አክብሮም የሚኖር ሰው ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መሆኑን ያውቃል፤ ከሰው ጋርም በፍቅርና በአንደነት
በመቻቻልና በመረዳዳት በመደማመጥ በመግባባት የሚኖር ሰው ነው፡፡ ትዕግስት ያለው በእምነትና በተስፋ የሚመራና ችኩል ያልሆነ
ነው፡፡ ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን በመፈለግ ሕይወት ውስጥ የሚኖር ሰው ነው ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊ ሰው፡፡ ከእርሱም ጋር አንድነት
አለው፡፡ በአጭሩ መንፈሳዊ ሰው ማለት መንፈስ ቅዱስ ያደረበትና የመንፈስ ቅዱስም ማደሪያም የሆነ ሰው ማለት ነው፡፡ ሁል ጊዜ
ባልተቋረጠ ተዘክሮተ እግዚአብሔር ውስጥ የሚኖር ሰው ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው ማለት ከማሕጸነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ
በጥምቀት የተወለደ አዲሱ ሰው ነው፡፡
መንፈሳዊ ሰው ጠንቃቃ፣ ትሁት ይቅር ባይና የዋሕ የሆነ፣ በጸሎትና ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ግንኙነት የበረታ ሰው፣ እንቅስቃሴው
ሁሉ በመንፈስ የተቃኘ ሰው ነው፡፡ እርሱ ከሁሉ ከፍ ብሎ ፍጹም የሆነ መንፈሳዊ ሰው ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው የጸጋ መንፈስ ቅዱስ
ተካፋይ የሆነና በእግዚአብሔርም ሕያው የሆነ ነው፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለን አንድነት ሥጋዊውን ሰው መንፈሳዊ ያደርገዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ቅዱስ ሰውም ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና›› የሚለን
(፩ኛ ተሰ.፬፥፯)።
ቅድስና የኦርቶዶክሳዊያን መንፈሳዊነትን ለዓለማዊያን የማሳወቂያ (ማሳያ) መንገድ ነው፡፡ ቅዱሳን በእግዚአብሔር እየኖሩ ስለ
እግዚአብሔር የመሰከሩ ናቸው፡፡ ቅዱሳን ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት በሕይወት የመሰከሩና የኖሩ ሕያዋን ቤተ መቅደሶች ናቸው፡፡
ቅዱሳን ማለት መልካም ሰዎች፤ ምግባራቸው የቀና፤ እራሳቸውን ለመንፈስ ቅዱስ ያስገዙ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከኦርቶክሳዊ
ምግባራት የሚገኝ በረከት (ጸጋ) ነው፡፡ ቅዱሳን የእግዚአብሔርን መገለጥ ተቀብለዋል መስክረዋልም፡፡
ኦርቶዶክሳዊነት ዕውቀት ብቻ አይደለም፡፡ የመረጃ ሰው መሆንና ተከታይ የመሆን ጉዳይም አይደለም፡፡ ኦርቶዶክሳዊነት እውነት፤
ሕይወት፤ ቅድስና እና ፍቅር ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው በውስጡ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያለው ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው ለመሆን አንድነትና
ብርታቱን ይስጠን፤ በሃይማኖት መጽናትን፤ የምግባር ሰው መሆንን እርሱ ያድለን፤ አሜን፡፡

በዓለ ሆሣዕና
ዲያቆን ዮሐንስ ተመስገን
ፈጣሬ ዓለማት አምላካችን እግዚአብሔር ምድርን ከነልብሱ ሰማይን ከነግሳንግሱ ፈጥሮ ብቻ አልተወም፤ ገዣቸው ይሆን ዘንድ
በመጨረሻው የፍጥረት ቀን አዳምን በእጁ አበጃጀው እንጂ። ፈጥሮም የሕይወትንም እስትንፋስ እፍ አለበት። አዳምም ሕያው ፍጥረት
ሆነ። እንዲነዳቸው፣ እንዲገዛቸው ልዑል እግዚአብሔር አዳምን በፍጥረታት ላይ በመሾም ኃጢአት በማይደርስባት ገነት በግርማ
አስቀመጠው።
አዳም እግዚአብሔር ያዘዘውን ረሳ፤ በእርሱና በእግዚአብሔር መካከል ለመታዘዝ ምልክት እንድትሆን የተነገረውን ዕፀ በለስ ሊቆርጥ
ተነሣ። በመጨረሻም እጁን ልኮ ቆረጠ፤ በላም፤ በመብላቱም ወደቀ፤ ከገነትም ተባረረ።
ከገነት ለተባረረው አዳም በደሉን ይቅር ይለው ዘንድ እግዚአብሔር ከሰው ተወለደ፤ የሰውን ሥጋና ነፍስ ተዋሐደ፤ ወደ ግብጽ ተሰደደ፤
በኋላም በዮርዳኖስ ተጠመቀ፤ ከተጠመቀም በኋላ ብሕትውናንና የገዳም ሕይወትን ሊያስተምር ወደ ገዳመ ቆረንጦስ ሄደ። ከ፵ ቀን
በኋላም ተመልሶ ደቀ መዛሙርትን ማስተማር ጀመረ፤ ይህ ሂደት ሦስት ዓመት ዘለቀ፤ የጌታችን ዕድሜም ሠላሳ ሦስት ዓመት ሞላ።
ጌታችን ከተወለደ ፴፫ የምሕረት ዘመናት ተቆጠሩ። ዕለቱ እሑድ፣ ቀኑ መጋቢት ፳፪ ነበር። በምድር የሚመላለስበትን ዘመን ሊጨርስ
ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት ለደብረ ዘይት ትራራ ቅርብ ወደ ሆነችው ቤተ ፋጌና ቢታንያ መንደር ገሰገሰ፡፡ ከደቀ
መዛሙርቱም ጴጥሮስና ዮሐንስን እንዲህ አላቸው፤ ‘‘በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደ መንደርም በገባችሁ ጊዜ ሰው በላዩ
ያልተቀመጠበት የአህያ ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፍቱና አምጡልኝ፤ ምን ታደርጋላችሁ የሚላችሁ ሰው ቢኖርም ጌታው ይሻዋል
በሉ’’ አላቸው፤ (ማር.፲፩፥፪) ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም እንደታዘዙት አደርጉ፡፡
የታሰሩትን ሊፈታ መጥቱዋልና የታሰርውን ፍቱልኝ አለ፤ ሰውን ሁሉ ከማዕሰረ ኃጢአት የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሰ ሲያጠይቅ ነው።
በአህያ ላይ ሁኖ ሲገባም የሚበዙት ሕዝብ ለጌታችን ክብር ለአህያዋ ልብሳቸውን ጎዘጎዙ፤ ልብስ ገላን ይሸፍናልና ከባቴ አበሳ ነህ ሲሉ።
በፊት በኋላ ሁነው ‘‘ለወልደ ዳዊት መድኃኒት መባል ይገባዋል’’ እያሉ አመሰገኑ፤ ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነውና “ሆሣዕና
በአርያም” ሲሉ ቀኑን ዋሉ፡፡ በፊቱ ያሉት የሐዋርያት በኋላው ያሉት የነቢያት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በሌላም ትርጉም የብሉያትና
የሐዲሳት ምሳሌዎች ሁነዋል። በዚህም የፊተኛውም የኋኛውም ዘመን ጌታ መሆኑ ተገልጧል፡፡
ሕዝቡ ሲዘምሩ የያዙት የዘንባባ ዝንጣፊም ጥንቱን አባቶቹ በብሉይ በዘንባባ ይገለገሉበት የነበረውን ያሳያል፤ እነ አብርሃምና እነ
ይስሐቅ ሲወለዱ የዘንባባ ሰሌን ይዘረጋላቸው ነበርና። እሥራኤል ከግብጽ በወጡ ጊዜ ዮዲት ሆሎፎርኒስን በገደለች ጊዜ ሰሌን ይዘው
አመስግነው ነበርና። እሾህ አለው ትእምርተ ኃይል ትእምርተ መዊዕ አለህ ማለታቸው ነው። (ትር. ወን. ዘማቴዎስ)
ወደ ቤተ መቅደሱ ሲደርስም ሁለት ክፋቶች ተስተውለዋል። ቤተ መቅደሱን ለንግድ መገበያያነት ያዋሉት እና ለጌታችን ምስጋና
እንዳይቀርብ ሲከለክሉ የታዩ የቤተ መቅደሱ አካባቢ ሰዎች ነበሩ፡፡ ጌታችን ለሁለቱም መልስ ሰጠ። የምስጋና መቅደሱን ለመገበያያነት
ያደረጉትን ‘‘ቤቴ የጸሎት ቤት ነው’’ ብሎ እርግብና ዋኖሳቸውን ገለባብጦ አባረራቸው፡፡ (ዮሐ.፪፥፲፮) ምስጋና የከለከሉትንም አስገድዶ
ራሱን አያስመልክምና “እናንት ባታመሰግኑኝ የቢታንያ ድንጋዮች ያመሰኙኛል” ብሎ ምስጋናው በፍጥረት ሁሉ ዘንድ እንጂ ከሰው ወገን
ብቻ አለመሆኑን ግዑዛኑን ድንጋዮች ለምስጋና አስነሥቷል፡፡ ካህናቱ ቢከለክሉም ሕፃናቱን አበረታቸው። በዚህም ማንም
የእግዚአብሔርን ምስጋና ሊከለክል እንደማይችል በሚገባ አሳያቸው።
ቤተ ክርስቲያንን ለግል ጥቅም የሚያውሉ ሰዎች ከቤተ ፋጌ ነጋዴዎች መማር አለባቸው። ጌታም በዕለተ ሆሣዕና ያስተማረው ይህን
ነው። በሐዋርያት እግር የተተኩ ጳጳሳትና ሊቃውንት ባያስቆሙ እንኳን በገነት መግቢያ ሚዛን ተመዝነው መውደቃቸው እሙን ነው።
ማንም የአገልግሎት ስፍራን ከጸሎት ይልቅ ለጥቅም፣ ከምስጋና ይልቅ ለክርክርና ጭቅጭቅ ቢያውል እንደ ቤተ ፋጌዋ ቤተ መቅደስ
እግዚአብሔር ፈታሒ በርትዕ ኮናኒ በጽድቅ ነውና በጥበቡ ለይቶ ያባርራል። መች እንድሚቀጣ እርሱ ያውቃል።
እግዚአብሔር ለምስጋና የሚሰለፉትን እየመረጠ ምስጋናውን የሚያስተጓጉሉትን በሌሎች እየተካ ዓለም ታልፋለች። ለምስጋና
ለሚሰለፉት መንግሥተ ሰማይ ትተካለች። ምስጋናውን ሲያደናቅፉ ለነበሩ እንደ ቤተ ፋጌ ነጋዴዎችና አናመሰግንም ብለው አፋቸውን
እንደዘጉ ምቀኞች ከርስታቸው ሰማያዊቷ ቤት ወጥተው ከእግዚአብሔር ቤት ተለይተው ገሃነመ እሳት ይወርዳሉ። ጉልበት ሳይደክም
ወደ ገዳማት ማጓዝ፣ ዐይን ሳይፈዝ ለጸሎት መትጋት፣ ጀሮ ሳይደነዝዝ ቃለ እግዚአብሔርን መስማት፣ ምላስ ሳይታሰር ለምስጋና
መትጋት ይገባል። ይህ ከሆነ ወደ በእግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንጂ በሆሣዕና እንደሆነው ሁሉ ወደፊት ገነትን በሚጠብቁ
ልዑላን መላእክት በእሳት ሰይፍ እየተባረሩ በሰይጣን ሠራዊት እየተንገላቱ ወደ ሲዖል መውረድ የለም። ምስጋናውን ሲከለክሉ
ዕድላቸው እንደተወሰደባቸው ሳይሆን ለምስጋና የዘንባባ ዝንጣፊ እንድያዙት ያድርገን። ቤተ መቅደሱን ለንግድ ሳይሆን ያለንን ጨርቅ
እንኳን ለጌታችን ክብር የምናነጥፍበት የተሰበረ ልብ ያድለን፤ አሜን!

You might also like