Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 8

ዘጠነኛ ሳምነት

የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ምዕራፍ ስድስት አንድምታ


ጠቅላላ 34 ቁጥሮች እና 2 ንዑሳን ክፍሎች አሉት፡፡
እነሱም፡- 1. ስለ ምጽዋት ጸሎትና ጾም (1-18)
2. ስለ መዝገብ፣ ዓይን፣ ገንዘብ፣ ምግብና ልብስ (19-34)
1. ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታችሁ እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ ያለዚያ
በሰማያት ባው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም
ሀ.1. በፊታቸው ማድረግ ሲል ምን ማለት ነው?
- ሰው ይይልን ብላችሁ እንዳታደርጉ ማለቱ ነው፡፡
2. እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም
እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፉ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡
ሀ.2. በፊት መለከት ማስነፋት ምንድን ነው?
- ሰው ሰብሰቦ ቀን ቆጥሮ አዋጅ ነግሮ ምጽዋት መስጠት ማለት ነው፡
- ውዳሴ ከንቱ ፈልጎ
ሀ.3. ዋጋቸውን ተቀብለዋል ሲል የተቀበሉትን ዋጋ ምንድን ነው?
- ውዳሴ ከንቱውን ነው፡፡
3. አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የሞትሰራውን
4. ግራህ አይወቅ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ያስረክብሃል፡፡
ሀ.4. ቀኝህ የምትሰራውን ግራህ አትወቅ ሲል ምን ማለቱ ነው?
- በቀኝ እጅህ የያዝከውን በግራ እጅህ አትያዘው ምክንያቱም ግራ ጥቂቱን ብዙ
አስመስሎ ልክፈልለት ያሰኛልና፡፡
- ሚስትህ አትወቅብህ
- ልጆችህ አይወቁብህ
- ቤተሰቦችህ አይወቁብህ
ሀ.5. በስውር የሚያይ ሲል ምን ማለቱ ነው?
- ስትመጸውት ተሰውሮ የሚያይህ
- ተሰውረህ ስትመጸውት የሚያይህ
ሀ.6. በግልጥ ያስረክብሃል ሲል ምን ማለቱ ነው?
- በጻድቃን፣ በሰማዕታት፣ በመላእክት፣ በኃጥአን፣ በአጋንንት ፊት ገልጾ ዋጋህን
ይሰጥሃል ማለቱ ነው፡፡
5. ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን
ቆመው መጸለይን ይወዳሉና እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡
ሀ.7. ለሰው መታየት ማለት ምን ማለት ነው?
- ሰው ይደልን ሰው ይስማልን ማለት
6. አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ
ጸልይ በስውር የሚያይ አባትህ በግልጥ ያስረክብሃል፡፡
ሀ.8. ወደ እልፍኝህ ግባ ሲል ምን ማለቱ ነው?
- ወደ ቤትህ ገብተህ ደጅህን ዝጋና ጸልይ
- በሰቂለ ኀሊና በነቂሐ ልቡና ሁነህ ወደ ሰማያዊ አባትህ ወደ እግዚአብሔር አምክት
7. አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ
በከንቱ አትድገሙ
ሀ.9. በከንቱ አትድገሙ ሲል ምን ማለቱ ነው?
- አብዝታችሁ አትጸልዩ (እንደ አሕዛብ)
- ጩሃችሁ አትጸልዩ (እንደ አሕዛብ)
o አሕዛብ አብዝተው ጮኸው በመጸለያቸው የሚሰማላቸው ይመስላቸዋል፡፡
8. ስለዚህ አትምሰኩአቸው ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃና፡፡
ሀ.10. አትምሰሉአቸው ማለት ምን ማለት ነው?
- አብነት አታድርጉአቸው
9. እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ
ሀ.11. እንዲህ ጸልዩ ሲል ያወጣው ጸሎት ምን ዓይነት ነው?
- አብዝታችሁ አትጸልዩ ብሎ ነበርና አጭር ጸሎት
- ጩሃችሁ አትጸልዩ ብሎ ነበርና የህሊና ጸሎት
ሀ.12. ለምን አባታችሁ ሆይ ብላችሁ ጥሩኝ አለ?
- ከግብርናተ ዲያቢሎስ እንዳወጣን ሲያጠይቅ ነው፡፡
- የማታልፍ ርስቱን መንግስተ ሰማያትን ያወርሰናልና ነው፡፡
- አባት ለልጁ እንደሚራራ ይራራልና
ሀ.13. ለምን በሰማያት የምትኖር አለ?
- ከምድራዊ አባት ሲለይ ነው፡፡
- ጌታ በሁሉ ምሉዕ ሲሆን ስለ ልዕልናው በሰማይ አለ ይባላልና ነው፡፡
- ጸሎቱ በሰቂለ ሕሊና ይሁን ሲል ነው፡፡
ሀ.14. ስምህ ይቀደስ ሲል ምን ማለቱ ነው?
- ስመ ወላዲ፣ ስመ ተወላዲ፣ ስመ ሰራፂ ይለይልን በሉኝ ሲል ነው፡፡
- ስሜ መሐሪና ይቅር ባይ ነው ያልኸው ይድናልና በሉኝ ሲል ነው፡፡
- እንደ መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለን አመሰግነንህ ቅድስትናህን ተሳትፈን
እንድንኖር አድርገን በሉኝ ሲል ነው፡፡
10. መንግስትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን
ሀ.15. መንግሥትህ ትምጣ ሲል ምን ማለት ነው?
- መንግስተ ሰማይ ትምጣልን በሉኝ ሲል ነው፡፡
- መንግስተ ሰማይ ትገለጥልን በሉል ሲል ነው፡፡
- ልጅነት ትሰጠን በሉኝ ሲል ነው፡፡
ሀ.16. ፈቃድህ በምድርም ትሁን ማለቱ ነው
- መላእክት በሰማይ ሊያመሰግኑህ ፈቃድህ እንደሆነ እኛም እናመሰግንህ ዘንድ ፈቃድህ
ይሁን
- ኋላ ሙተን ተነስተን ልናመሰግንህ ፈቃድህ እንደሆነ ዛሬም በሕይወተ ሥጋ ሳለን
እናመሰግንህ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን፡፡
11. ዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን
ሀ.17. ዕለት እንጀራ የተባለ ምንድን ነው?
- የዕለት ምብግ (ለፍጹማን)
- ያመት ልብስ ያመት ምግብ (ለሰብዓ ዓለም)
- ሥጋህን ደምህን፣ ንስሀን ትምህርትን አስበህ ጸሎታችንን ስጠን፡፡
12. እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን
ሀ.18. ይቅር እንደምንል ሲል ምን ማለቱ ነው?
- የበደለንን ይቅር እንል ዘንድ
- ይቅር ማለቱ ራሱ ያላንተ ፈቃድ አይሆንም ሲል ነው፡፡
13. ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን መንግስት ያንተ ነውና ኃይልም ክብርም
ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
ሀ.19. ፈተና የተባለው ምንድን ነው?
- አለመጽናትና መወላወል ነው
ሀ.20. ክፉ የተባለው ምንድን ነው?
- ኃጢአት፣ ክህደት፣ መከራ፣ ገሃነም
ሀ.21. ኃይልና ክብር ምንድን ናቸው?
- ከሃሊነት፣ ጌትነት
ሀ.22. አሜን ማለት ምን ማለት ነው?
- በእውነት ይደረግልን ማለት ነው፡፡
14. ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር
ይላችኋልና
- ይቅር ይላችሁ ዘንድ ይቅር በሉ ማለት ነው፡፡
15. ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም
ሀ.23. በዚህ አጭርና የህሊና ጸሎት ላይ ምን ማለት አለበት?
1. ነገሮች አሊበት እነሱም፡-
1. ሃይማኖት፡- ያላዩትን እግዚአብሔርን አባታችን ማለት
2. ተስፋ፡- መንግስትህ ትምጣ ማለት
3. ፍቅር፡- ለኛ ብሎ አንድ ላንዱ መጸለይ
4. ትሕትና፡- ቅዱሳን ከበቁ በኋላ በደላችንን ይቅር በለን
5. ጸሎት፡- መላው (ጠቅላላ ይዘቱ)

አስረኛ ሳምንት
16. ስትጦሙም እንደግብዞች አትጠውልጉ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን
ያጠፋሉና እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸው ተቀብለዋል፡፡
ሀ.24. ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ሲል ምን ማለት፡፡
እንደ ጾሙ ሰው እንዲያውቅላቸው እየፈለጉ ማለት ነው፡፡
17. አንተ ግን ስትጦም በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች
18. እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ
ያስረክብሃል፡፡
ሀ.25. ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ ሲል ምን ማለት ነው?
- የተቀባና የታጠበ እንደማይታወቅበት አይታወቅብህ ሲል ነው፡፡
ሀ.26. ራስን በመቀባት ፊትንም በመታጠብ እንዳይታወቅ ማድረግ የሚገባው በየትኛው ጾምና
በየት ነው?
- በጾመ ፈቃድና በከተማ ነው፡፡
- በጌታ ጾምና በገዳም ውዳሴ ከንቱ የለበትም
ሀ.27. ራስህን ተቀባ የሚለውን ምን ተብሎ ሊተረጎም ይችላል?
- ፍቅርን ያዝ
- ንጽሕናን ገንዘብ አድርግ
- ትህትናን ያዝ
ሀ.28. ፊትህን ታጠብ የሚለው ምን ተብሎ ሊተረጎም ይችላል?
- በእንብዓ ንስሀ ታጠብ
19. ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦች ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ
መዝገብ አትሰብስቡ፡፡
ለ.1. ይህን አንቀጸ ምጽዋት ስለምን አመጣው?
ስለ 3 ነገሮች እነሱም፡-
1. እህሉን ነዳያን ከሚበሉት ብለው አኑረውት ነቀዝ ቢበላው ምቀኝነት ነውና፡፡
2. ልብሱን ነዳያን ከሚለብሱት ብለው አኑረውት ብል ቢበላው ምቀኝነት ነውና፡፡
3. ለክፉ ጊዜ ይሆነኛል ብሎ ማኖር እግዚአብሔርን ከዳተኛ ማድረግ ነው፡፡
- ምንም እጅ እግር ባያወጡለት ገንዘብ ማኖር ጣዖት ማኖር ነውና ህልፈት፣ ጥፋት
ያለበትን ምድራዊ ድልብ አታደልብ፡፡
20. ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ
በሰማይ መዝገብ ሰብሰቡ
21. መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚህ ይሆናልና፡፡
ለ.2. ብልና ዝገት የሚጣጠፉት መዝገብ፣ ሌቦች፣ የተባሉት ትርጓሜ ምንድን ነው፡፡
- ውዳሴ ከንቱ ያለበት ምጽዋት አጋንንት
22. የሰውነት መብራት ዓይን ናት እንግዲህ ጤናማ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፡

- የስራህ መከናወኛ ዓይንህ ስለሆነ የቀና እንደሆነ ሥራህ ሁሉ የቀና ይሆናሉ፡፡
23. ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል እንግዲህ በአንተ ያለው
ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማውስ እንዴት ይበርታ፡፡
- በተፈጥሮ የተሰጠህ ዓይንህ የታመመ ከሆነ ጨለማ እንደምን ይጸናብህ ይሆን
24. ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም
ይወዳል ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል፡፡ ሁለተኛውንም ይንቃል ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ
መገዛት አትችሉም፡፡
- አንድ ቆላ ውረድ ሲለው ሌላው ደጋ ውጣ ቢለው እንዴት ለሁለቱም ሊታዘዝ
ይችላል
25. ስለዚህ እላችኋለሁ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት ወይም ስለሰውነታችሁ
በምትለብሱት አትጨነቁ ነፍስ ከመብል ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን?
ለ.3. መብል መጠጥን ለነፍስ ልብስን ለሰውነት ሰጥቶ ለምን ተናገረ?
- የበሉት የጠጡት ደም ይሆናልና በዚህ ምክንያት ነፍስ ከስጋ ጋር ተዋሕዳ
ትኖራለችና ለዚህ ነው፡፡
- ምንም የምታፍር ነፍስ ብትሆን አጊጦ ከብሮ የሚታይ ሥጋ ነውና
ለ.4. ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ እንዴት ሊበልጥ ይችላል?
- በተፈጥሮ
- በትንሳኤ
ለ.5. የምትበሉትና የምትጠጡት እንዲሁም የምትለብሱት ሲል ምን ዓይነት ትርጓሜ
ይኖረዋል?
- ሥጋወ ደሙና እንዲሁም ልጅነት የሚያሰጥ በመሆኑ
26. ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም የሰማዩ
አባታችሁም ይመግባቸዋል እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?
ለ.6. ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ ማለት ምን ማለት ነው?
- አብነት አድርጎ ማለት ነው፡፡
ለ.7. እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን ሲል በምንድን ነው?
- በተፈጥሮ
ለ.8. የሰማይ ወፎች የሚለው ትርጓሜ (ምሳሌያዊ) ምንድን ነው?
- እስራኤላውያን የሰማይ መና ተመግበዋልና
- ትንቢት ያልተነገረላቸውን፣ ሱባኤ ያልተቆጠረላቸውን፣ ሰማያዊ አባታችሁ ሥጋውን
ደሙን የሚመግባቸው አሕዛብን አብነት አድርጉ፡፡
27. ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማነው?
ለ.9. በቁመቱ አንድ ክንድ መጨመር ማለት ምን ማለት ነው?
- ካላጠርኩ ልርዘም ብሎ አንድ ክንድ ራስን ማርዘም
- በቃሁ ነቃሁ ብሎ ሥልጣነ ክህነትን ለራስ ገንዘብ ማድረግ
28. ስለ ልብስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ልብ
አድርጋችሁ ተመልከቱ አይደክሙም አይፈትሉምም
29. ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ አንድ አንዱ አለበሰም
ለ.10. ሰሎሞን አበባ ያለበት፣ ሐረግ የተሳበበት ወርቀ ዘቦ ግምጃ ይለብስ እንደነበር ለምን
በክብሩ ከነዚህ እንደ አንዱ አለበሰም አለ?
- የሱ የባሕርዩ አይደለም የነሱ ግን የባሕርያቸው ነውና
- እሱ እነሱን አብነት ነው እነዚያ ግን እሱን አብነት አድርገው አይደለፈምና
ለ.11. ስለ ልብስና ስለ የሜዳ አበቦች ያለው ትርጓሜ ምንድን ነው?
- ልብስ ልጅነትን ያሳያል
- የሜዳ አበቦች አህዛብን ያመለክታል
30. እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሳር እንዲህ
የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ እናንተንም ይልቁን እንዴት?
ለ.12. ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን ሲል ምን ማለቱ ነው?
- ማገዶ የሚሆነውን እንጨት (ዛሬ በልምላሜ ያለውን)
- ዛሬ በተድላ የሚኖረው ነገ ወደ ገሃነም የሚጣለው (ከሀድያን)
31. እንግዲህ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ
32. ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ
ያውቃልና
ለ.13. አሕዛብ ሲል ምን ማለቱ ነው?
- ከምግባር ከሃይማኖት ውጪ የሆኑ
33. ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግስት ጽድቁንም ፈልጉ ይህም ሁሉ
ይጨመርላችኋል፡፡
ለ.14. የእግዚአብሔር መንግስትና ጽድቅ የተባሉት ምንድን ናቸው?
- ሀይማኖትና ምግባር
- ልጅነትና መንግሥት ሰማይ
34. ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለገነ አትጨነቁ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል፡፡
ለ.15. ነገ ለራሱ ይጨነቃል ማለት ምን ማለት ነው?
- የነገውን ነገ ታስቡታላችሁ ማለት ነው፡፡
- ለነገ ያጸናናል ብላችሁ አብዝታችሁ አትመገቡ የነገውን ነገ ትመገቡታላችሁና፡፡
- ነገ እንናዘዛለን ብላችሁ ኃጢአታችሁን አታሳድሩ የነገረውን ነገ ትናገሩታላችሁና ሰል
ነው፡፡

You might also like