Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 5

የብድር ውል (የፍትሐብሔር ሕግ ከቁጥር 2471-2489)

የብድር ውል ምንነት፡- የተለያዩ ፅሑፎች እንደሚያስረዱት ብድርን በተመለከተ ሁሉንም


ሊያግባባ የሚችል አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም አናገኝለትም፡፡ የፍትሐብሔር ሕጋችን
የሚከተለውን ትርጉም ሰጥቶታል፡- “የሚያልቅ ነገር ብድር ማለት ከተዋዋዮቹ አንዱ ወገን
አበዳሪው ሌላውን ተበዳሪ ሰው የተበደረውን ነገር በዓይነቱ ለመመለስ ተገዳጅ በማደረግ
ገንዘብ ወይም በማገልገል የሚያልቅ ሌላ ነገር ለተበዳሪው ለመስጠትና ሀብትነቱን
ለማስተላለፍ የሚገደድበት ውል ነው” ይላል፡፡ ከዚህ ትርጓሜ መረዳት እንደሚቻለው ብድርን
በሚመለከት ሕጉ በሚያልቅ ነገር ላይ ብቻ እንጂ ከዛ ባለፈ ማለትም በማያልቅ ነገር ወይም
ቋሚ የሆነ ንብረትን የማያካትት መሆኑን ነው፡፡ የድንጋጌውን አጠቃላይ ይዘት ስናይ አመላለሱ
በዓይነት ወይም በአገልግሎት ሊሆን እንደሚችል እና ውሉ አስገዳጅ መሆኑንም ያሳያል፡፡

የዉል አመሠራረት፡- የብድር ውል የውል አንድ አካል እንደመሆኑ መጠን አመሰራረቱም ሆነ


አፈፃፀሙ በጠቅላላው የውል ሕግ መርሆች የሚገዛ በመሆኑ የብድር ውልን ዝርዝር
ድንጋጌዎች ከማየታችን በፊት ስለውል አመሰራረት ባጭሩ አይተን ብናልፍ የተሻለ ግንዘቤን
ይፈጥራል፡፡ ዉል ስምምነት ቢሆንም ከሌሎች ስምምነቶች የሚለየዉ በአፈፃፀሙ
ከበስተጀርባዉ የሕግ ድጋፍ ያለዉ ስምምነት መሆኑ ላይ ነዉ፡፡

አንድ ውል የሚፀና ውል ነው ለማለት የሚከተሉትን መርሆች ማሟላት አለበት፡- 1ኛ ዉል


የሚፈፀመዉ ለመዋዋል ችሎታ ባላቸዉ ሰዎች መካከል ብቻ መሆኑ (እድሜዉ ለአቅመ
አዳም/ሄዋን ያልደረሰ ወይም አይምሮዉ ህመም ያለበት ሰዉ ወይም በፍርድ ቤት የተከለከለ
ሰዉ ችሎታ እንደሌለዉ ይቆጠራል፡፡) 2ኛ ዉል የሚደረገው በተወያያቹ ነፃ ፍቃድ ብቻ የሚደረግ
መሆኑ፡፡ 3ኛ ተወያይ ወገኖች የሚዋዋሉበት ጉዳይ በእርግጠኝነት የሚቻል እና ህጋዊና
ሞራላዊ ጉዳይ ላይ መሆን የሚገባው መሆኑ፡፡ 4ኛ የዉል አቀራረጹ ወይም አፃፃፉ (ፎርም)
በህግ ተለይተዉ የተቀመጡ ወይም ተዋዋይ ወገኖች ተለይቶ እንዲቀመጥ ከተስማሙበት
የዉል ጉዳይ በቀር የተለየ የዉል ፎርም አያስፈልግም፡፡

Page - 1 -
የአበዳሪና ተበዳሪ ግዴታዎች፡- አበዳሪና ተበዳሪ የራሳቸው የሆኑ ሊያከብሯቸው የሚገቡ
ግዴታዎች አሉባቸው፡፡ በቅድሚያ የአበዳሪው ግዴታዎችን ስናይ ሕጉ የአበዳሪውን ግዴታዎች
በተመለከተ የሽያጭ ውልን በሚደነግገው ክፍል ላይ የሻጩ ግዴታዎች ተብለው የተገለፁት
ደንቦች በአበዳሪ ላይ ተግባራዊ ይሆናሉ ይላል፡፡ በፍትሐብሔር ሕጉ የሻጭ ግዴታዎች ናቸው
የተባሉት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡

1ኛ ዕቃ የማስረከብ ግዴታ፡- የሽያጭ ውል ከተከናወነ በኋላ ሻጭ የግብይት ምክንያት የሆንውን


ዕቃ/ንብረት ለገዥ የማስረከብ ግዴታ አለበት፡፡ 2ኛ ስመ-ሀብት የማስተላለፍ ግዴታ፡- ከላይ
ለማንሳት እንደተሞከረው የሽያጭ ውል ልዩ መገልጫ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ ሻጩ የሽጭ
ምክንያት የሆነውን ንብረት ስመ-ሀብትን የማስተላለፍ ግዴታ ያለበት መሆኑ ነው፡፡ የባለቤትነት
መብት መተላለፍን በተመለከተ የብድር ውል ከሽያጭ ውል ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር
የብድር ውሉ በትርጉም ክፍሉ ላይ እንደሰፈረው አላቂ ዕቃን ብቻ የሚመለከት በመሆኑ ዕቃውን
ለተበዳሪው በሚያስረክብበት ወቅት የባለቤትነት መብትም አብሮ መተላለፍ መቻሉ ነው፡፡ 3ኛ
ዋስትና የመስጠት ግዴታ፡- ሌላኛው የሻጭ ግዴታ ከተሸጠው ዕቃ ጋር በተገናኘ ለሚፈጠሩ
ችግሮች ለገዥው ዋስትና የመስጠት ግዴታ ነው፡፡

የተበዳሪውን ግዴታዎች በተመለከተ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ዕዳውን መልሶ ከመክፈል ጋር


የሚገናኝ ነው፡፡ ተበዳሪ የብድር ውል ውስጥ ሲገባ የተበደረውን ነገር በዓይነቱ ለመመለስ
ወይም በገንዘብ የሚመለስ ሲሆን እነዚህን በወቅቱ የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ የብድሩ
አመላለስ በማገልገል የሚያልቅ ሲሆን ደግሞ ለአበዳሪው ተገቢውን)

የብድር ማስረጃ፡- ማስረጃ ማለት አንድ በፍርድ ቤት ምርመራ ላይ ያለ በጭብጥ የተያዘ


አከራካሪ ጉዳይ እውነት መሆንና አለመሆኑን በሚያሳምን ሁኔታ ማረጋገጥ እንዲያስችል
በግብአት የሚቀርብ ፍሬ ነገር ስለመሆኑ ብ/ጀነራል ታጠቅ ታደሰ “የማስረጃ ሕግ መሰረተ
ሀሳቦች” በሚለው መፅሐፋቸው ገልፀውታል፡፡ ማስረጃ ማለት ይህ ከሆነ በሁለት ሰዎች
መካከል የብድር ውል ተደርጓል ወይስ አልተደረገም የሚለውን ጥያቄ በምን ማረጋገጥ
እንችላለን? የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ ቀጥለን እናያለን፡፡ የፍ/ሕጋችን በአን. 2472 ስር

Page - 2 -
የብድር ማስረጃ በሚል ርእስ የሚከተለውን ደንግጓል፡-

(1) በብድር የተሰጠው ገንዘብ ከብር 500 በላይ ሲሆን የብድሩን ውል በፅሑፍ ወይም በፍርድ
ቤት በተደረገ የእምነት ቃል ወይም መሐላ ካልሆነ በስተቀር ለማስረዳት አይቻልም፡፡

(2) ለብድር ውል ማናቸውም ሌላ ዓይነት ማስረጃ ለማቅረብ አይቻልም ፡፡ (3) እንዲሁም ከብር
500 የበለጠ ገንዘብ የመክፈል ነገር በዚህ ዓይነት ይፈፀማል፡፡ በዚህም መሰረት የብድሩ
መጠን ብር 500 እና ከዛ በታች ከሆነ በማንኛውም ዓይነት ማስረጃ ለምሳሌ በቦታው የነበረ
የሰው ምስክር በመስማት ማረጋገጥ የሚቻል መሆኑን እና መጠኑ ከዛ በላይ ከሆነ ግን ከሦስቱ
የማስጃ ዓይነቶች መካከል በአንዱ ካልሆነ በስተቀር በሌላ በምንም መንገድ ማረጋገጥ
የመማይቻል መሆኑን ነው መረዳት የሚቻለው፡፡ እነዚህን ሦስት የማስረጃ ዓይነቶች ቀጥለን
እንመልከት፡፡

የመጀመሪያውና የበለጠ አስተማማኝ የሆነው ማስረጃ የፅሑፍ ማስረጃ ነው፡፡ ይህም ማለት ገና
ከጅምሩ የብድር ውሉ ሲደረግ በፅሑፍ የተደረገ ሲሆን ያንን ፅሑፍ ለፍርድ ቤት በማቅረብ
ማስረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ አነጋገር ከብር 500 በላይ የሆነ የብድር ውል በፅሑፍ እንዲሆን ሕጉ
አስገዳጅ የሚመስል ድንጋጌ ያስቀመጠ በመሆኑ ከላይ ካነሳነው የውል አመሰራረት መርሆች
መካከል የተለየ ፎርም የሚፈልግ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ሁለተኛው የማረጋገጫ መንገድ
በፍርድ ቤት በተደረገ የእምነት ቃል ነው፡፡ ይህም ማለት ተበዳሪው በፍርድ ቤት ቀርቦ በከሳሹ
የቀረበበትን ክስ ማለትም ከከሳሹ ገንዘብ የተበደረ መሆኑን፣ መጠኑ ምን ያክል እንደሆነ
በማያሻማ መንገድ ካመነ በቀላሉ የብድሩ መኖር የሚረጋገጥ ይሆናል፡፡ ሦስተኛውና
የመጨረሻው የማረጋገጫ መንገድ በመሐላ የማረጋገጥ ሂደት ነው፡፡ መሐላ ማለት በክርክር
ወቅት አንድ ተከራካሪ ወገን በሚያቀርበው ማስረጃ ወይም በሚናገረው ፍሬ ነገር እውነትነትን
ለማረጋገጥ ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ ቅፅ ላይ የሚሰጡት ማረጋገጫ ነው፡፡

የብድር መመለሻ ጊዜ፡- ብድር ውል እንደመሆኑ መጠን ለተዋዋይ ወገኖች ሰፊ ነፃነት መሰጠት
አለበት፡፡ በመሆኑም ሕጉ ስለብድር መመለሻ ጊዜ በተዋዋይ ወገኖች የተወሰነ ጊዜ በሚኖርበት
ወቅት ይህንኑ ዕውቅና በመስጠት ክፍያው በዛ ጊዜ መሆን እንደሚገባው ሕጉ አፅንኦት

Page - 3 -
ሰጥቶበታል፡፡ ከዚህም ባለፈ ብድሩ ወለድ የሌለበት ከሆነ የተበደረውን ገንዘብ ለመመለስ
ማሰቡን ለአበዳሪው ከአንድ ወር በፊት አስታውቆ የመመለሻ ጊዜው ከመድረሱ በፊት
ሊመልስለት እንደሚችልም ሕጉ ይደነግጋል፡፡ የብድሩ መመለሻ ጊዜ በተዋዋይ ወገኖች
ያልተወሰ በሚሆን ጊዜ ሕጉ ብድሩ በምን ያክል ጊዜ ውስጥ ሊከፈል እንደሚገባው ደንግጓል፡፡
ይኼውም አበዳሪው መልስልኝ ሲል ከጠየቀበት ቀን አንስቶ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መመለስ
እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ተበዳሪውም በአበዳሪው ሳይጠየቅ መክፈል ቢፈልግ ለመክፈል
ያለውን ሀሳብ ከአንድ ወር በፊት ካስታወቀ በኋላ ዕዳውን መመለስ እንደሚችል እንዲሁ
ተደንግጓል፡፡

በብድር ላይ ሊኖር ስለሚችል ወለድ፡- በብድር ውል ላይ ሊኖር ስለሚችል ወለድም ለተዋዋይ


ወገኖች ነፃ ፈቃድ የተተወ ጉዳይ ነው፡፡ ብድሩ ወለድ የሚከፈልበት ስለመሆኑ በውሉ በግልፅ
ካልተገለፀ ግን ተበዳሪው በምንም መልኩ ወለድ እንዳይከፍል ሕጉ ጥበቃ ያደርግለታል፡፡ ሕጉ
በብድር ውሉ ላይ ወለድ ይኑር አይኑር የሚለውን ጉዳይ በተዋዋይ ወገኖች እንዲወሰን ነፃነት
የሰጠ ቢሆንም በወለድ መጠኑ ልክ ላይና ስለሚከፈልበት ጊዜ ወይም ወለዱ ስለሚሰላበት
ጊዜ ግን ገደብ አስቀምጧል፡፡ በዚህም መሰረት ተዋዋይ ወገኖች የወለዱን መጠን በዓመት
ከ12 በመቶ በላይ ማድረግ እንደማይችሉ ገደብ ጥሏል፡፡ እንዲሁም የወለዱ መጠን በውሉ
ላይ ካልተገለፀ እና ወለድ የሚከፈልበት ብድር መሆኑ ብቻ ተገልፆ ከሆነ ወይም ወለዱ ከ12
በመቶ በላይ ይሆናል የሚል የውል ቃል ካለ መከፈል የሚችለው የወለድ መጠን በዓመት 9
በመቶ ብቻ እንደሚሆንና የሚሰላውም ተቃራኒ የሚሆን የውል ቃል ከሌለ ብድሩ ከተሰጠበት
ጊዜ ጀምሮ በሚቆጠር በየዓመቱ መጨረሻ ላይ መሆን ይገባዋል ይላል ሕጉ ፡፡

የብድር አከፋፈል (የሚከፈለው ነገር)፡- በብድር አመላለስ ወቅት ሌላው ግለፅ መሆን ያለበት
ጉዳይ ብድሩ በየትኛው ሀገር የገንዘብ ዓይነት ነው? ከብድሩ በኋላ የምንዛሬ ዋጋ መለዋወጥ
ቢያጋጥምስ ምን ይሆናል? የሚለው ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የፍትሐብሔር ሕጉ ግልፅ
ድንጋጌዎች አሉት፡፡ በዚህም መሰረት የብድር ውሉ የተደረገው በኢትዮጵያ ብር ከሆነ ብድሩ
በሚመለስበት ወቅት ባለው ሕጋዊ የኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘብ ወይም ለዚህ የገንዘብ መጠን

Page - 4 -
የሚተካ የውጭ ምንዛሬ በማቅረብ ከዕዳው ነፃ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ የሚከፈለውን የገንዘብ
መጠን በተመለከተ የብድር ውሉ በሚከናወንበት ጊዜ በትክክል የተበደረውን ያክል እንጂ ሌላ
ነገር እንደማያካትትና በመሀል ሊያጋጥም የሚችለውን ወይም ያገጠመውን የገንዘቡ ዋጋ
መለዋወጥ ግምት ውስጥ መግባት እንደሌለበትም ሕጉ አያይዞ ይገልፃል፡፡ ብድሩ በውጭ
አገር ገንዘብ ተደርጎ ከነበረ ደግሞ ብድሩ በሚከፈልበት ጊዜ በዛ አገር ሕጋዊ መገበያያ በሆነው
የገንዘብ ኖት መከፈል ያለበት ሲሆን መጠኑም የተበደረውን ያክል ብቻ መሆን እንዳለበት ሕጉ
አመልክቷል፡፡ የብድር ውሉ የተደረገው ከገንዘብ ውጪ ባሉ የሀብት ዓይነቶች በሚሆንበት ጊዜ
ለምሳሌ፡- ለምግብ የሚሆኑ ነገሮች፣ ሸቀጦች ወይም መአድናት ሲሆኑ ተበዳሪው በተበደረው
ልክ ብዛቱንና ዓይነቱን በመክፈል ከዕዳው ነፃ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ከብድሩ በኋላ
በሚኖር የዋጋ መለዋወጥ የብድድር አመላለሱን መጠንና ዓይነት ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ
የለም፡፡

Page - 5 -

You might also like