510

You might also like

Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 23

የመሬት ይዞታ ይገባኛል እና የይርጋ መከራከሪያ በአማራ ብሔራዊ ክልል የመሬት አዋጅ

ከፌደራል መንግስት የህግ ማዕቀፍ አንጻር፡

ጋሻዬ ቢያድግ§

አህጽሮተ ይዘት
በንብረት ህግ ማዕፍ ዉስጥ ተቀባይነት ያላቸዉ ንብረት የሚገኝባቸዉ መንገዶች ዉስጥ አንዱ
ባለ እጅ (ይዞታ) (adverse possession) አንዱ ነዉ፡፡ ይህ መንገድ ረጅም ታሪክ ያለዉ ሲሆን
በሮማዊያን ህዝቦች ዘንድ መነሻ ሲኖረዉ በእንግሊዝ የመሬት ህግ እንደስረዓት እንደተዘረጋ
መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ አሰራር የራሱ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አመክኒኦ
(justifications) አሉት፡፡ ይህ አሰራር ከይርጋ ህግ ጋር ቀጥተኛ ትስስር ስለአለዉ የይርጋ ህግ
የተመሰረተባቸዉ አጠቃላይ ምክንያቶች ለዚህ አሰራር በአመክኒኦነት ይወሰዳሉ፡፡ ከመሬት
ይዞታ ጋር በተያያ ህገ ወጥ ይዞታን የሚበረታታ ነዉ በሚል የሚቀርብበት ትችት ቀላል
አይደለም፡፡ ለመሆኑ በኢትዮጵያ የህግ ማዕቀፍ ዉስጥ የዚህ አሰራር ትርጉምና ተቀባይነት ምን
ይመስላላ? በተለይም፣ የመሬት ይዞታን አስመልክቶ ጥበቃ ለማድረግ የፌደራል የህግ ማዕቀፍ
እና የአማራ ብሔራዊ ክልል የመሬት አዋጅ ቁጠር 252/2009 ያላቸዉ አkም አብሮ የሚሄድ
ነዉ፣ የሚሉትን ጥያቄዎች በዚህ ጽሁፍ የተዳሰሱ ሲሆን የሌሎች ሀገራት ህግና ተሞክሮን
መሰረት በማድረግ የፌደራል እና የክልሉን የህግ ማዕቀፎች ላይ ዓይነታዊ በሆነ የጥናት ዘዴ
ትንታኔ በማድረግ፤ የባለእጅ(ይዞታ) አሰራር በፌደራል ደረጃ በህግም ይሁን በፍርድ ቤት ዉሳኔ
የተዘረጋ ሲሆን የአማራ ብሄራዊ ክልል በበኩሉ ይህን አሰራር ቀሪ እንዲሆን በግልጽ
አስቀምጧል፡፡ ክልሉ መነሻ ያደረገዉ የዜጎች የመሬት ይዞታን የተሻለ ጥበቃ ለማድረግ አስፈላጊ
ነዉ ብሎ በማሰብ ይመስላል፡፡ ነገር ግን የፌደራሉም ይሁን የክልል ህግ ማዕቀፍ ሲታዩ ህገ
ወጥ የሆነ የመሬት ወረራን ለመከላከልና የዜጎችን የይዞታ መብት የሚጠብቁ የወንጀልም
ይሁን የፍታብሄር ጥበቃዎች በቂ ናቸዉ፡፡ እነዚህን አማራጮች ተጠቅሞ ይዞታዉን በወቅቱ
ያላስከበረ ባለይዞታ ደግሞ አጠቃላይ ከህዝብ ጥቅም አንጻር፣ ከኢኮኖሚያዊ እና መህበራዊ
ምክንያቶች አንጻር በመመዘን ይህ ስርዓት ሊዘረጋ ይገባል፡፡ ስርዓቱ ሲዘረጋ ግን የተለያዩ
የጥንቃቆ ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጥና የጊዜ ደገቡን ረዘም በማድረግ ያሉትን ችግሮች
መቅረፍ ይገባል፡፡

ቁልፍ ቃላት፡- ባለእጅ (ይዞታ)፣ ህገ-ወጥ ይዞታ፣ ይርጋ፣ ሰባዊ ብት፣ የህዝብ ጥቅም ፣ አመክኒኦ
1. ባለ እጅ (ይዞታ) የማድረግ የማድረግ አሰራር ጽንሰ ሀሳብ
ባለእጅ (ይዞታ) (dverse Possession) ማድረግ ማለት ለተከታታይ ጊዜ በንብረቱ በመጠቀም
የሚገኝ የይዞታ መብት ነዉ፡፡ይህ አሰራር የቀድሞ የንብረት ባለቤትን ግልጽ ወይም በተዘዋዋሪ
መንገድ ባለቤትነቱን የሚቃረን ወይም የሚያሳጣ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ባለሀብት
የሚሆንበት አንዱ መንገድ ነዉ፡፡1የህግ መዝገበ ቃላት የሆነዉ ብላክስሎዉ ባለ እጅ ማድረግ
አሰራርን ሲተረጉም የማይንቀሳቀስ ንብረት የባለቤትነት ማግኛ መንገድ ሲሆን ይህም በጊዜ እና
ቅድመሁኔታዎችን ማሟላትን ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ቅድመሁኔታዎችም ማንም ሳይፈቅድለት
በንብረቱ ሲጠቀምበት የቆየ መሆኑን ማስረዳት፣ ይህን ንብረት የተጠቀመበት ሁኔታ ደግሞ
በግልጽና በባለቤትነት ስሜት መጠቀምና በህግ የተቀመጠዉን የጊዜ ገደብ ማሟላቱን ማሳየት
አለበት ይላል፡፡2ከዚህ መዝገበ ቃላት ትርጉም ጋር የሚመሳሰል አገላለጽ በአንድ ታዋቂ
የእንግሊዝ የፍርድ ቤት ዉሳኔ የሚከተለዉ ተመልክቶ ስራ ላይ ዉሏል፡፡
Adverse possession means possession of the land which is
inconsistent with the title of the true owner: this inconsistency
necessarily involves an intention to exclude the true owner, and all
other persons, from enjoyment of the estate or interest which is
being acquired የሚል ነዉ፡፡3
ወደ አማረኛ ሲመለስ ባለእጅ (ይዞታ) ማለት መሬትን በይዞታ ስር በማድረግ የቀድሞ
ባለቤትን በሚቃረን ወይም በሚጋፋ መልኩ ይህ ባለእጅ (ባለ ይዞታ) ያደረገ ሰዉ ይንን
መሬት በባለቤትነት ስሜት እና የቀድሞ ባለቤትና ሌሎችን የሚያገል አጠቃቀም ስርዓት
ነዉ የሚል ይሆናል፡፡ ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያ ባለእጅ የማድረግ አሰራር (Adverse
Possession) አንድ ጸሀፊ ሲገልጽ ‹የሌላ ሰዉ መሬት መያዝ ሲሆን በተለይም በእርግጥም
መሬቱን በእርሱ ቁጥጥር ስር በማድረግ በግልጽ እና በባለቤትነት ስሜት ማለትም ሌሎችን
በማግለል ለተከታታይነት ሲጠቀምበት የቆየ መሆኑን እና በህግ የተቀመጠዉን የጊዜ ገደብ

§LLB, LLM, በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ህግ ምርምር ኢንስቲትዩት የህግ
ጥናትና ምርምር አስተባባሪ ፡፡ ማንኛዉም አስተያየት በgashayebiadge@yahoo.com ላይ ማድረስ ትችላላችሁ፡፡
1
The Doctrine of Adverse Possession Law Essays LawTeacher, UK (November 2013)
የተገኘዉ<http://www.lawteacher.net/free-law-essays/land-law/the-doctrine-of-adverse-possession-law-
essays.php?cref=1> (መጋቢት 16 2010 ዓ.ም) የተገኘ፡፡
2
ዝኒ ከማሁ፡፡
3
Murphy v Murphy [1980] IR 183 የሚለዉን የፍርድ ቤት ጉዳይ ይመልከቱ፡፡
ካሟላ ባለመሬት ይሆናል›4 በማለት ያስቀምጣል፡፡ ከላይ የተመለከቱት ተቀባይነት ያላቸዉ
የባለእጅ የማድረግ አሰራር ትርጉም የጋራ ነጥቦች አሉ፡፡ እነርሱም መሬቱን በእርግጥም
መቁጥጥር ስር ማድረግ፣መሬቱን በህግ የተቀመጠዉን የጊዜ ገደብ ማሟላት እና መሬቱን
በግልጽና ሌሎችን በሚያገል መንገድ በመሬቱ መጠቀምን ያጠቃልላል፡፡5በዚህ መሰረት ባለእጅ
መሆን አሰራርን ተግባራዊ ከማድረግ በፊት እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች በጥንቃቄ መመርመርን
እና መሟላታቸዉን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡
2. ባለእጅ (ይዞታ) አሰራር ታሪካዊ ዳራ
ባለእጅ የማድረግ አሰራር የረጅም ጊዜ ታሪክ ባለቤት ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2250
ዓመተ ዓለም በሀሙራቢ ህግ ነዉ፡፡6 በጥንታዊ የግሪክና ሮማዊያን ህዝቦች ዘንድ የሰዎች
መንፈስ በሚቀመጡበት ወይም በሚይዙት መሬት ላይ ይወሰናል የሚል ነበር፡፡7 በዚህ
አመክኒኦ ይህ ሰዉ በህግ የዚህ መሬት ባለቤት ይሆናል ማለት ነዉ፡፡ ይህ የዳበረ አሰራር የህግ
ድጋፍ በማግኘቱ ሰዎች በተወሰነ የጊዜ ገደብ የተጠቀሙበትን መሬት ባለቤት እንዲሆኑ
አስችሏል፡፡ይህ ህግ የሮማዊያን የንብረት ህግ መነሻ ያደረገ ሲሆን በሲቪል የህግ ስርዓትም
የዳበረ ነዉ፡፡8 በሮማዊያን ህግ ዩስካፒዮ (Usucapio የሚል የላቲን ቃላል ሲሆን በሌሎች
የኮመን ሎዉ ተከታይ ሀገራት ደግሞ አድቨርስ ፖሰሽን (adverse possession) በሚባል
ይታወቃል፡፡ ይህን ለማየት የሚከተለዉን ጥቀስ ይመለከቷል፡፡
<The Usucapioof Roman law, as adoptedincivil law systems, represents what is often
called acquisitive prescriptionin the sense that adverse possession conferred a positive
title>9..ስለሆነም አንዳንድ ጸሀፊዎች ባለእጅ ማድረግ (adverse possession
ከእንግሊዝ ህግ እንደመነጨ ይነገራሉ፡፡10በእንግሊዝ የይርጋ ህግ በ1632 እንደ


4
Larissa Katz, “Exclusion and Exclusivity in Property Law” (2008) 58 U.T.L.J. 275
5
Madson, T.S. 1989. Rhode Island Real Property LawGainesville: LSS Publishing Company
6
Barry Nicholas, an IntroductiontoRoman law (Oxford University Press, 1962) 107–15. በተጨማሪ The Twelve

Tables ህግን ይመለከቷል፡፡


7
ዝኒ ከማሁ
8
የግርጌ ማስታወሳ ቁጥር
9
የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 6፡፡
10
Boudewijn Bouckaert etal ADVERSE POSSESSION TITLE SYSTEMS, Center for Advanced
Studies in Law and Economics Researcher, University of Ghent, Faculty of Law. በዚህ ጽሁፍ
አውሮፓዊያን አቆጣጠር የባለእጅ ወይም adverse possession እንደተጀመረ
ጸሀፍት ይናገራሉ፡፡
ነገር ግን የቃላት ለዉጥ ካልሆነ በስጠቀር በሮማዊያን ህግ 2250 ዓመተ ዓለም ዩስካፕዮ
በመባል ከሚታወቀዉ የላቲን ቃል የመጣ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ይህም በሮማዊያን
ዘንድ ዩስካፕዮ የነበረዉ ወደ እንግሊዝ የመሬት ህግ ሲደርስ አድቭርስ ፖሰሽን (adverse
Possession የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ተመሳሳይ
መሆናቸዉን ማየት ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ የፍትሀብሄር ህግ የተቀበለዉ የሲቪል ሀገራት አገላላጽ ሲሆን በቁጥር 1168
ላይ እንደተመላከተዉ ባለእጅ (ይዞታ (usucaption) የሚል ነዉ፡፡ በተለይም የእንግኛዉ ቅጅ
በትክክል እንደሚያሳየዉ የኢትዮጵያ የፍታብሄር ህግ በዚህ ረገድ ከሮማዊያን ህግ የተወሰደ
መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጅ ከላይ እንደገለጽሁት በኮመን ሎዉና በሲቪል ሎዉ
መካካል የቃላት ልዩነት ካልሆነ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ አንድ አይነት ናቸዉ፡፡ ስለሆነም በዚህ
ጽሁፍ ቃላቶቹ በዓማራጭ የተጠቀምሁባቸዉ መሆኑን መግለጽ እፈልጋልሁ፡፡
ለብዙሀኑ ህዝብ ጥቅም (utilitarianism) ሲባል የንብረት ህግ መሰረት ሲሆን ንብረት ጥበቃ
ሊደረግለት የሚገባ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ጽንሰ ሀሳቡም ንብረት ለህብረተሰብ ጥቅም ሲባል
በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት ያስረዳል፡፡ ጥቅም ላይ ያልዋለ ንብረት ወይም ጦም
ያደረ መሬት በመጨረሻ የሚጎዳዉ ህብረተሰቡን ስለሆነ ይህን የሚከላከል አሰራር ንብረቱን
ባለእጅ ያደረገዉን ሰዉ መብት እዉቅና በመስጠት ነዉ፡፡11ይህ የሮማዊያን ህግ እንዳስቀመጠዉ
የንብረት ባለቤት የሆነ ሰዉ በአንድ በኩል ያልተገደበ መብት ያለዉ ሲሆን ነገር ግን ይህ
መብት ፍጹም ገደብ የማይጣልት አይደለም፡፡ በመርህ ደረጃ በህግ የንብረት ባለመብቱ
ያለማንም ጣልቃ ገብነት ያልተገደበ መብት አለዉ፡፡ ነገር ግን የመሬት ባለቤት የሆነ ባለሀብት
መሬቱን አላግባብ እንዳያባክነዉ እና ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማዋል እንዳለበት በልዩ ሁኔታ

የሚከተለዉን ዓረፍተ ነገር እንገኛለን፡፡ <Adverse possession was formalized in English common law in
1632 in the Statute of Limitations>.ከዚህ አገላለጽሁለት መልዕክት መገንዘብ ይቻልል፡፡ አንደኛዉ ባለእጅ
ማድረግ እና የይርጋ ህግ ያላቸዉን ግንኙነት ሲሆን ሌላኛዉ ደግሞ የኮመን ሎዉ ህግ በእንግሊዝ ሀገር
እንደተጀመረዉ adverse possession የሚል ቃላት መጠቀማቸዉን ይገልጻል፡፡ በዚህም የእንግሊዝ የመሬት ህግ
ለኮምን ሎዉ ባለእጅ የማድረግ አሰራር መነሻ በመሆን ያገለግላል፡፡
11
Itzchak Tzachi Raz, Use It or Lose It: Adverse Possession and Economic Development
Working Paper August 2017
ግዴታ ይጥላል፡፡ የመሬት ባለቤት የሆነ ሰዉ መሬቱን በአግባቡ ሳይጠቀም የቀረ እንደሆን
የባለቤትነት መብቱን የሚያጣበት ስርዓት ነዉ፡፡ ይህ አሰራር በዘመናዊ የንብረት ህግ በሁሉም
ሀገራት ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አሰራር ነዉ፡፡12
የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንዳጠኑት ባለ እጅ (adverse possession በጊዜ ገደብ መሆንና
ከይዞታ ያለመፈናቀል ወይም የይዞታ ዋስትና መስጠት ያላቸዉን ግንኙነት በተመለከተ
የሚያሳየዉ ጠንካራ የይዞታ ዋስትና ካለ ምርታማነት ይቀንሳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ
ባለይዞታዎች በጥብቅ የጊዜ ገደብ የተቀመጠላቸዉ ከሆነ እና መሬታቸዉን በአግባቡ
የማይጠቀሙበት በሆነ ጊዜ መብታቸዉ ወደ ሌላ ሰዉ እንደሚተላለፍ ባወቁ ቁጥር ምርትና
ምርታማነት ይጨምራል፡፡ ለዚህ ዋና ምክንያት ደግሞ መሬቱን በአግባቡ የመጠቀምና ስራ ላይ
የማዋል ሁኔታ ስለሚጨምር ነዉ፡፡13 ስለሆነም ይህ አሰራር መዘርጋቱ የመሬት ባለቤት የሆኑ
ሰዎች መሬታቸዉን በአግባቡ እንዲከባከቡ፣ እንዲያለሙ፣ እና ምርትና ምርታማነትን
ለመጨመር አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
በንብረት ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ሰፊ እና ዝርዝር ምርምር ያደረገዉ ጸሀፊ ጆን ሎክ ስለ ንብረት
መብት እና ስለሚኖሩት ገደቦች ሲያስቀምጥ ንብረትን ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻለዉ ንብረቱን
በአግባቡ እና ከብክነት በጸዳ መልኩ የተጠቀምንበት እንደሆነ ነዉ፡፡14ጆን ስቱዋርት ሚል
በበኩሉ በመሬት ላይ ብቸኛ ባለመብት ለመሆን መሬቱን በተግባር መጠቀምና በመሬቱ ላይ
ምርት ማምረት ይጠበቅበታል፡፡15እነዚህ የሞራል ፈላስፋዎች ስለ ባለእጅ የማድረግ አሰራር
(adverse possession) በሚገባ እንዳስቀመጡት የመሬት ባለመብት መሬቱን በአግባቡ
ሳይጠቀሙበት ከቀረ ይዞታዉን ሊያጣ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
3. ከይርጋ ህግ ጋር ያለዉ ግንኙነት
የባለእጅ (ይዞታ) የማድረግ አሰራር አንደኛዉ ገጽታ ይርጋ ነዉ፡፡ የባለእጅ ማድረግ አሰራር
ከቅድመ ሁኔታዎች ዉስጥ በህግ የተቀመጠዉ የጊዜ ገደብ መሟላት አለበት የሚለዉ ነዉ ፡፡


12
የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 11
13
የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 11
14
John Lock, The Second Treatise of Government (2002) በ Tzachi Raz በግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 11
ላይ እንደተጠቀሰዉ፡፡
15
John Stuart Mil, Principles of Political Economy (1848), በ Tzachi Raz በግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 11
ላይ እንደተጠቀሰዉ፡፡
ይህ ደግሞ ቀጥተኛ የይርጋ ጽንሰ ሀሳብ የሚያመለክት ነው፡፡16 የይርጋ ዓላማ ሰዎችን ለረጅም
ጊዜ ከቆዩ ክሶች ለመከላከል ነዉ፡፡ የአማረኛ መዝገበ ቃላት ላይ ስለ ይርጋ የተቀመጠዉ ቃላት
‹ረጋ› ሲሆን ‹የሰዉ ሀሳቡ ከመዉጣቱ ከመዉረድ በሀሳብ ከመዞር ከመባከን ከመናወጥ ጸጥ›
አለ በሚል ይገለጻል ፡፡17 ከሳሽ ለረጅም ጊዜ ክሰ ባለማቅረቡ ምክንያት ማስረጃዎች ሊጠፉ
ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ተከሳሽን ለረጅም ጊዜ ከቆየ ክስ ለመከላከል ዓላማ አለዉ፡፡ በንብረት ህግ
ጽንሰ ሀሳብ የንብረትን የባለቤትነት መብት የሚያረጋግጡ ሰነዶችን በጊዜ ገደብ ቀሪ የሚሆኑ
ከሆነ ይህንን መብት መጠየቅ አይቻልም፡፡ይህም የተረጋጋ መብት እንዲኖረን፣በህግ የበላይነት
ላይ እምነት እንዲኖር እና ክርክሮች መቋጫ እንዲኖራቸዉ ለማድረግ ነዉ፡፡18
ይርጋ ክስ እንዳይቀርብ ወይም ይዞታን ለማስመለስ የሚቀርብ ክስን የሚከለክል ነዉ፡፡ በመብቱ
ላይ የሚተኛ ከሳሽ መብቱ በጊዜ ገደብ መታገድ ይገባዋል በሚል አመክኒኦ ይህ ህግ በሁሉም
የህግ ስርዓት ተቀባይነት አለዉ፡፡19 በህግ በተቀመጠዉ የጊዜ ገደብ ክስን አለማቅረብ መብት
የመሬት ባለቤትነትን ሊያሳጣ ይችላል፡፡ ስለሆነም የመሬት ይዞታን ባለእጅ ያደረገ ሰዉ እና
በቀድሞ የመሬት ባለቤት መካከል በህግ በተቀመጠዉ የጊዜ ገደብ ላይ ክርክር በማድረግ ዉሳኔ
መሰጠት አለበት፡፡ በህግ የተቀመጠዉ የጊዜ ገደብ ካለፈ መሬቱን ባለእጅ ያደረገዉ ሰዉ የመሬቱ
ባለመብት ሲያደርግ በሌላ በኩል ደግሞ ባለመሬት መሬቱን የሚያጣበት አሰራር ነዉ፡፡ ይርጋ
የቀድሞ ባለመሬት መብት እንዲቋረጥ ያደርጋል፡፡ መሬቱን ባለእጅ ያደረገ ሰዉ ደግሞ መብት
ያጎናጽፋል፡፡ ነገር ግን የቀድሞ ባለመሬት መብቱ የተቋረጠዉ ባለእጅ ካደረገዉ ሰዉ አንጻር ብቻ
እንጅ በአንጻራዊነት ከሌሎች ሰዎች የተሻለ መብት ሊኖረዉ ይችላል፡፡ ይህ ማለት በአጋጣሚ
ይህ የመሬት ይዞታ አሁን ባለእጅ ካደረገዉ ሰዉ ቁጥጥር ዉጭ ቢወጣ እና በሌላ ሰዉ እጅ
ቢገባ የቀድሞ ባለመሬት መብቱን የሚጠይቅበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፡፡ መብቱ የተቋረጠዉ


16
የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 10ን ይመልከቱ
17
ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ከሰቴ ብርሀን ተሰማ የአማረኛ መዝገበ ቃላት ኩራዝ አሳታሚ ፣ 1972 ዓ.ም ገጽ 280
18
The aim of the period of limitation is to prevent citizens from being oppressed by stale claims,
to protect settled interests from being disturbed, to bring certainty and finality to disputes and so
on. ይህ ዓላማ በሁሉም የይርጋ ህግ የሚደነግግ አዋጅ ዉስጥ ተካቶ ይገኛል፡፡በአብዛኛዉ ሀገራት የይርጋን
ሥርዓት የሚደነግግ እራሱን የቻለ አዋጅ አላቸዉ፡፡በዚህም ስለይርጋ ዓላማ ከላይ በተቀመጠዉ አግባብ
ያስቀምጣሉ፡፡ Limitation Act 1980 (UK) c 58, s 15. በተመሳሳይ ስለ ባለእጅ (ይዞታ እና ስለ ይርጋ
የተቀመጠዉ ግንኙነት ምን ይዘት እንዳለዉ ያሳያል፡፡
19
ለምሳሌ፡- የእንግሊዝ የይርጋ ህግ (sections 3) ፣ የደች ህግ ፣ የፈረንሳይ፣የስፔን፣ ወዘተ የመሳሰሉትን
ይመልከቱ፡፡
ፍጹማዊ በሆነ መልኩ ሳይሆን መሬቱን ባለእጅ ካደረገዉ ሰው አንጻር ብቻ ነዉ፡፡ይህም
ባለእጅና የይርጋ ጊዜ ገደብ የሚመሳሰሉበት ነጥብ ነዉ፡፡ ስለሆነም ባለእጅ አሰራርን በተግባር
ለማዋል የይርጋን ክርክር ማለፍ ይጠይቃል፡፡
ባለ እጅ (ይዞታ) የማይንቀሳቀስ ንብረት ለረጅም ጊዜ በመጠቀም የሚገኝ መብት ሲሆን ይህም
በንብረት ህግ ዉስጥ ንብረት ማግኛ አንደኛዉ መንገድ ነዉ፡፡ በሌሎች ሀገራት ባለ እጅ ማደረግ
(adverse possession) አሰራር መሬት የማግኛ መንገድ ጭምር ነዉ፡፡20 የሚከተለዉን
ዓረፍተ ነገር በዉል ይህን ያሳያል፡፡
<The Usucapioof Roman law, as adopted in civil law systems, represents what is often
called acquisitive prescription in the sense that adverse possession conferred a positive
title to land>21
በኢትዮጵያ የህግ ማዕቀፍ ዉስጥ በባለእጅ (ባለይዞታ) መሆንን የተመከተዉ የፍታብሔር ህግ
ቁጥር 1168-69 ያሉት ድንጋጌዎችን ስንመለከት የባለእጅ (ባለይዞታ) አሰራር እና የይርጋ ህግ
ትስስር እንዳላቸዉ በግልጽ ተመላክቷል፡፡ በፍታብሄር ህግ ቁጥር 1169 ላይ የባለእጅ (ይዞታ)
መካከል ያለዉን ቀጥተኛ ትስስር እንደሚከተለዉ ተደንግጓል፡፡
…ስለ ይርጋ መቋረጥ የተነሩት፣ዉሳኔዎች፡ ስለ ይዞታም ተፈጻሚዎች ይሆናሉ፡፡ እንዲሁም
በይርጋ ህግ ስለ መከራከርና በስራ ላይ ስለ ማዋል፣ በይርጋ መከራከር ስለመተዉ የተነገሩት
የዚሁ አንቀጽ ዉሳኔዎች የተጠበቁ ናቸዉ፡፡
ይህ የህግ ክፍል በሌሎች ሀገራት የባለእጅ (ይዞታ) እና የይርጋ ህግ በአንድ አዋጅ
የሚደነገገዉን ዓይነት በዚህ የፍታብሄር ቁጥር ላይ ተመልክቷል፡፡ ስለሆነም ከመሬት ይዞታ
ጋር የሚነሳ ክርክር በይርጋ ጽንሰ ሀሳብ የሚያልፍ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ
የፍታብሄር ህግ መሰረት አንድ ልዩ ሁኔታ አለ፡፡ ይህዉም የመሬቱ አመጣጥ ከዘርና ርዕስት
የወረደ ከነበረ ይህ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ ይሁን እንጅ ርዕስት የሚለዉ አሰራር በአዋጅ ቀሪ
ስለሆነ ይህ ልዩ ሁኔታ ተግባራዊ አይሆንም፡፡ በተጨማሪም ይህ አሰራር አሁን በስራ ላይ
ካለዉ የመሬት ስሪት አንጻር መታየትና መፈተሽ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ የፍታብሄር ቁጥር 1168
መሰረት ባለእጅ (ይዞታ) አሰራር የንብረት ባለቤትነት ጨምሮ የሚገኝበትና የሚተላለፍበት

20
Kaser M Roman Private Law (trans by Dannenbring R, 3rd ed 1980) 130; Krause LE “The
History and Nature of Acquisitive Prescription and of Limitation of Actions in Roman-Dutch Law”
(1923) 40 South African Law Journal 26-41 3
21
የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 6 ላይ ይመለከቱ፡፡ ሰረዝ ለትኩረት የተጨመረ፡፡
መንገድ ነዉ፡፡ አሁን በስራ ላይ ያለዉ የመሬት ስሪት ደግሞ የመሬት ባሌቤትነት የመንግስትና
የህዝብ22 በመሆኑ በፍታብሄር ህግ በተቀመጠዉ ስርዓት መሰረት የመሬት ባሌቤትነት ወደ
ግለሰብ ሊተላለፍ አይችልም፡፡ ይልቁንም በአሁኑ ሰዓት ግለሰቦች በመሬት ላይ ያላቸዉ መብት
የይዞታና የመጠቀም መብት ብቻ ነዉ፡፡ ስለሆነም የፍታብሄር ህግ ቁጥር 1168-69 ስር
የተመለከተዉ ይዞታ የሚተላለፈዉ ከላይ የተመላከተዉ ግለሰቦች ያላቸዉ መብት ብቻ ነዉ፡፡
ስለዚህ የሚተላለፈዉ የይዞታና የመጠቀም መብት ብቻ ነዉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌደራል
ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከመሬት ይዞታ በተያያዘ በመዝገብ ቁጥር ላይ የመሬት
ይዞታ ክርክር በ10 ዓመት ሊታገድ ይገባል የሚል ዉሳኔ አስተላልፏል፡፡23ይህ ዉሳኔ ከተነሳዉ
ክርክርና ጭብጥ አንጻር ትክክል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በዉሳኔዉ ሀተታ ላይ የተመላከተዉ
ምክንያት ግለጽነት የጎደለዉ ይመስላል፡፡ ሁሉንም የመሬት ይርጋ ክርክር በፍታብሄር ህግ
ቁጥር 1845 ላይ የተመለከተዉ ይሆናል የሚል ድምዳሜ በዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ እምነት ትክክል
አይደለም፡፡ የዚህ ጽሁፍ አላማ ይህን ዉሳኔ ለመተቸት ስላልሆነ ከዚህ በላይ በዝርዝር
አልሄድበትም፡፡ ይሁንና በዚህ ዉሳኔ መሰረት ባለእጅ (ይዞታ) ክርክርን በ10 ዓመት ይታገዳል
ይላል፡፡
ባለእጅ (adverse possession) ለመሆን መሟላት የሚገባቸዉ ቅድ መሁኔታዎች የሚከተሉት
ናቸዉ፡፡
3.1 አዉነተኛ ይዞታ፡ ንብረቱ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሲሆን የመሬት ይዞታ መሆን መቻል
አለበት፡፡ ባለ እጅ (adverse possession) ያደረገዉ ሰዉ ይዞታዉን በእርግጥም
በእርሱ ቁጥጥር ስር በማድረግ የሚጠቀምበት መሆኑን ማሳየት ይኖርበታል፡፡


22
የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት፣ አዋጅ ቁጥር 1/1987፣ አንቀጽ 40(3) የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት ባለቤትነት
መብት የመንግስትና የሕዝብ ብቻ መሆኑን ደንግጓል፡፡
23
ብዙ ጊዜ ከመሬት ጋር በተያያዘ የይርጋ ክርክርን ለማንሳት ያለዉ ችግር በባለሙያዎች ዘንድ የሚነሳዉ ብዥታ
<መሬት ይርጋ> የለዉም የሚል ጠቅላላ አገላለጽ ነዉ፡፡ ይህ ብዥታ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ዉሳኔም
ጭምር የተንጸባረቀ ይመስላል፡፡ይህም የመሬት ይዞታ ክርክር በመሬት ህጎች ስላልተቀመጠ በጠቅላላ የዉል ህግ
1845 ላይ የተመለከተዉ ይርጋ ሊሆን ይገባል በማለት ሀተታዉን አስቀምጧል፡፡ ይህን አገላለጽ በዉል
ከተመረመረ አጠቃላይ ከመሬት ጋር የሚነሳ የይርጋ ክርክር በ10 ዓመት የሚመለስ ነዉ የሚመስለዉ፡፡ ነገር ግን
ከመሬት ጋር በተያያዘ የሚነሱ የክርክር ዘዉጎች የተለያ ናቸዉ፡፡ ከመሬት ጋር በተያያ የዉርስ፣የሰብል ይገባኛል፣
የካሳ ጥያቄ፣ እና ሁከት ይወገድልኝ፣ ይዞታ ይመለስልኝ …ወዘተ. የመሳሰሉት የዳኝነት ጥያቄዎች የይርጋ ክርክር
ለማንሳት በጥያቄዎች አግባብ የተለዩ የይርጋ ገደቦችና ስላለ በዚህ አግባብ ጥያቄዉን በዉል በመረዳትና የይርጋ
ጊዜዉን መለየት የስፈልጋል፡፡
ለሶስተኛ ወገን ግልጽ በሆነ መልኩ የሚጠቀምበትና ከእዚህ ቀደም የዚህ መሬት
ባለይዞታ የነበዉን ሰዉ መብት በሚጋፋና በሚቃረን ሁኔታ ለተከታታይ ጊዜ መጠቀም
መቻል አለበት፡፡ ህጉ በሚያስቀምጠዉ የጊዜ ገደብ ዉስጥ ባለማቋረጥ የተጠቀመበትና
እዉነተኛ ባለይዞታ የነበረዉን ሰዉ መብት በግልጽ የሚቃረን ድርጊት መፈጸም
አለበት፡፡ እዚህ ላይ የቀድሞ ባለይዞታ የነበረ ሰዉ ይዞታዉን በፍጹም ማጣት
ይኖርበታል፡፡ የቀድሞ ባለይዞታ በፈቃዱ ይዞታዉን ቢያስተላልፍ ይህ ድርጊት ይዞታን
አያሳጣዉም ፡፡ ነገር ግን ይህ በፍቃድ ይዞታ ያገኘ ሰዉ በሌላ ጊዜ ሀሳቡን በመቀየር
እናም እዉነተኛ ባለይዞታ የነበረዉን ሰዉ መብት በሚጋፋ መልኩ ይዞታዉን
የሚጠቀምበት፣ በግልጽ ለሶስተኛ ወገንም በሚታይና በሚታወቅ መልኩ ባለይዞታ
መሆኑን ከገለጸ እናም በህጉ የተቀመጠዉ ጊዜ ካለፈ ይህ ሰዉ ባእጅ ወይም ባለይዞታ
የመሆን ጥያቄ ወይም መብት ሊኖረዉ ይችላል፡፡
3.2 ግልጽ እና ተከታታይ የሆነ ይዞታ፡ይህ ቅድመ ሁኔታ ባለእጅ አድራጊ ሰዉ መሬቱን
በምን ሁኔታ ሲጠቀምበት እንደቆየ የሚያጠይቅ ነዉ፡፡ ይህም ባለእጅ አድራጊዉ
መሬቱን የቀድሞ ባለቤትን በሚቃረንና ግልጽ በሆነ መልኩ ለተከታታ ጊዜ መጠቀምን
ያመለክታል፡፡በተለይም ከዚህ በላይ እነድተመለከተዉ ይህ ባለእጅ የማድረግ አሰራር
ከይርጋ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ተከታታይነት የሚታየዉ በይርጋ ህግ ዉስጥ የይርጋ
ማቋረጫ ምክንያችን የሚመለከት ነዉ፡፡
3.3 የባለቤትነት ስሜት ፡ ይህም ባለእጅ መብት ጠያቂዉ መሬቱን ሲይዝ የሀሳብ
ሁኔታዉ ምን መሆን እንደአለበት ያሳያል፡፡ ስለሆነም የባለእጅ መብት ጠያቂዉ የሀሳብ
ክፍል መሬቱን በባለቤትነት (animus possidendi) የሀሳብ ሁኔታ መሆን አለበት
የሚለዉን ያሳያል ፡፡24 የቀድሞ ባለቤትን የሚቃረን፡ ከላይ እንደተገለጸዉ ባለእጅ
አድራጊዉየ ቀድሞ ባለቤትን የሚቃረን ተግባር መፈጸምን የሚመለከት ነዉ፡፡ እነዚህ
ከዚህ በላይ የተመላከቱት ቅድመ ሁኔታዎችን በአጠቃላይ በአንድ ላይ ተሟልተዉ
መገኘት ይገባቸዋል፡፡ ስለሆነም ቅድመ ሁኔታዎችን ስመረምር ሁሉንም በአጠቃላይ
(Cumulatively) እንጅ በተናጠል አይደለም፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱን ቅድመ ሁኔታ እርስ
በዕርስ የተያያዙ ስለሆኑ በአጠቃላይ መመርመር አለበቻዉ፡፡
3.4 ባለእጅ የማድረግ አሰራር የማይሰራባቸዉ ሁኔታዎች


24
Jourdan S Adverse Possession (2003) ከዓረፍተ ነገር 8-01–8-25 ጀምሮ ያለዉን ይመልከቱ ፡፡
መሬቱ የመንግስት ከሆነ ብዙ ጊዜ ሀገራት የመንግስት የመሬት ይዞታ በተመለከተ በጊዜ ገደብ
የማይቋረጥ ነዉ በማለት ይበይናሉ፡፡ ለዚህ ብይን መነሻ በመሆን የሚጠቀሱ ሁለት ምክንያቶች
አሉ፡፡ እነዚህም 1/ በመንግስት ይዞታ ስር ያለ መሬት መንግስ ህብረተሰቡን በመወከል የያዘዉ
እና የቀጣዩ ትዉልድ ሀብት በመሆኑ በይርጋ ህግ ይህ ይዞታ በመቋረጥ ወደ ግለሰቦች
ሊተላለፍ አይገባም የሚል ነዉ፡፡2/ በመንግስት ይዞታ የሚያዙ መሬቶች ሰፋፊና ለቀጥጥር
የማይመች እና አሰተዳደራዊ ወጭ ከፍተኛ በመሆኑ የመንግስት ይዞታዎችን ላይ የይርጋ ህግ
ወይም ባለ እጅ የማድረግ አሰራር ተግባራዊ አይደረግም፡፡25
3.5 የዉል ግንኙነት ካለ
ባለእጅ የማድረግ አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ መሟላት ካለባቸዉ ቅድመ ሁኔታዎች ዉስጥ
አንዱ መሬቱን በቁጥጥትር ስር በማድረግ እየተጠቀመበት የሚገኘዉ ሰዉ በባለቤትነት ሀሳብ
መያዝ አለበት የሚለዉ ነዉ፡፡ ይህ ማለት የሌላ ሰዉ መሬትን በዉል ወይም በኪራ በመያዝና
በህግ የተቀመጠዉ የጊዜ ገደብ በማለፉ ብቻ የባለእጅ መብት ማቅረብ እንደማይችል
ያስገነዝባል፡፡ ይህም ባለእጅ መብት ጠያቂዉ መሬቱን ሲይዝ የሀሳብ ሁኔታዉ ምን መሆን
እንደአለበት ያሳያል፡፡ ስለሆነም የባለእጅ መብት ጠያቂዉ የሀሳብ ክፍል መሬቱን በባለቤትነት
(animus possidendi) የሀሳብ ሁኔታ መሆን አለበት፡፡26 ከዚህ ዉጭ በኪራይ ወይም በሌላ
አግባብ የሌላ ሰዉ መሬት በመያዝ ለረጅም ጊዜ በመቆየት ብቻ የባለእጅ መብት የመጠየቅ
መብትን አያጎናጽም፡፡
የብዙ ሀገር የይርጋ ህግ ሲዳሰስ ባለእጅ መብት የማይጠየቅባቸዉ ልዩ ሁኔታዎች (execptions
ተዘርዝረዋል፡፡ ለምሳሌ፤ ባለመሬቱ በሀገር መከላከያ ጥሪ በተሰማራ ወቅት ከሆነ፣ከዕድሜ ልክ
በታች በመታሰር በማረሚያ ቤት ከሆነ፣ በፍርድ በዕድሜ ከ18 ዓመት በታች ከሆነ የሚሉትን
ልዩ ሁኔታዎች በባለእጅ መብት የማይጠየቅባቸዉ ወይም የይርጋ ህግ የማይሰራባቸዉ ናቸዉ፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች የመሬት ባለመብት ያላቸዉን የጥበቃ መጠን የሚያሳዩ ሲሆን በሌላ በኩል
ደግሞ ባለእጅ አሰራር ተግባራዊ የሚሆንባቸዉ ሰዎች በህግ የተሠጣቸዉን መብት መጠቀም
እየቻሉ ነገር ግን ሳይጠቀሙ በቀሩት ላይ እነደሆነ ልብ ይሏል፡፡
4. ህገ- ወጥ የመሬት ወረራ (squatter) እና ባለእጅ (ይዞታ) የማድረግ አሰራር (adverse
possession) ያለቸዉ ግንኙነት

25
Krause LE “The History and Nature of Acquisitive Prescription and of Limitation of Actions in
Roman-Dutch Law” (1923) 40 South African Law Journal 26-41 31
26
የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 24 ላይ ይመልከቱ ፡፡
መሬት ወረራ ማለት ሳይፈቀድለት የሌላ ግለሰብ መሬት መያዝ ነዉ፡፡ መብት ሳይኖርህ በሌላ
ሰዉ መሬት ላይ ህግ ከሚፈቅድልህ ዉጭ በመያዝ ለመጠቀም መሞከርን ይመለከታል
፡፡ይህምበብዙ ሰዎች ዘንድ ትልቅ ማህበራዊ ችግር ሲሆን የመሬት ዝርፊያ በማለት
ይገልጹታል፡፡ ብላክስ ሎዉ ስለመሬት ህገ ወጥ ወራራ (squatter) ትርጉም ሲያስቀምጥ
እንደሚከተለዉ ነዉ፡፡
‹[o]ne who settles on another's land, without legal title or authority. A person
entering upon lands, not claiming in good faith the right to do so by virtue of
any title of his own or by virtue of some agreement with another whom he
believes to hold the title. Under former laws, one who settled on public land in
order to acquire title to the land በተመሳሳይ አንድ ዳኛ ስለመሬት ወረራ እንዲህ ሲል
አስቀምጧል፡፡„…a squatter…is one who, without colour of right, enters on an
unoccupied house or land, intending to stay there as long as he can>
ስለሆነም ህጋዊ ህገወጥ የመሬት ወረራ ትርጉም ሳይፈቀድለት ወይም ህጋዊ ምክንያት
ሳይኖረዉ የሌላ ሰዉ መሬት በመያዝ መጠቀምን ይመለከታል፡፡ ይህ ትርጉም የመንግስት
መሬትም ይሁን የግለሰብ ይዞታን ሳይፈቀድለት መጠቀምን ይመለከታል፡፡ ይህን ድርጊት
ሀገራት በወንጀል ህግም ይሁን በፍታብሄር ህግ ጥበቃ ያደርጋሉ፡፡ ስለሆነም የዜጎች የይዞታም
ይሁንን የባለቤትነት መብት ከፍተኛ ጥበቃ ስለሚያስፈልግ በተሟላ መልኩ አስፈላጊዉን ሁሉ
ማድረግ መሰረታዊ የሰባዊ መብት ተገርጎ ይወሰዳል፡፡ ለምሳሌ፡ የአዉሮፓ ህብረት
የሚከተለዉን ደንግጎ ይገኛል፡፡
‹Protocol 1 Art.1 of the European Convention on Human Rights provides (1)
every natural or legal person is entitled to the peaceful enjoyment of his
possessions. No one shall be deprived of his possessions except in the public
interest and subject to the conditions provided for by law and by the general
principles of international law›
ይህ ድንጋጌ እንዳስቀመጠዉ የሰዎች በንብረት ላይ ያላቸዉ ይዞታ በሰባዊ መብት ደረጃ
በመፈረጅ ጥበቃ ያደረግለታል፡፡ የዚህ ስምምነት ፈራሚ ሀገራት ደግሞ ይህን የማክበር ግዴታ
አለበቸዉ፡፡27 ስለሆነም ሀገራት በህጎቻቸዉ ለይዞታ ጥበቃ ለማድረግ በወንጀልና በፍታብሄር
ህግ ጥበቃያ ደርጋሉ፡፡28

27
European Convention for the Protection of Human Rights and Fundamental Freedoms 1950
28
ለምሳሌ፣Criminal Law Act 197 of England and walse ::
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን የህግ ማዕቀፍ ስንመለከት የኢፊድሪ የወንጀል የወንጀል ህግ አንቀጽ
685-88 ላይ እንደተመለከተዉ የወንጀል ህግ የሰዎችን ይዞታ ሁከት እንዳይፈጠርባቸዉ ጥበቃ
የሚያደርግ ነዉ፡፡ ስለሆነም የሰዎችን የመሬት ይዞታ በህገ ወጥ መንገድ በመያዝም ይሁን
በሌላ በማናቸዉም መንገድ ሁከት የተፈጠረበት ከሆነ ይህ የወንጀል ህግ አጥፊዎች ላይ ቅጣት
እንዲተላለፍ በማድረግ ጥበቃ ያደርጋል፡፡ በተመሳሳይ በ1952 የወጣዉ የፍታብሄር ህግ ከቁጥር
1146-48 ላይ እንደተመለከተዉ ይዞታ ላይ ስለሚፈጠር ሁከት መፍትሄ አስቀምጧል፡፡29
ስለዚህ የግለሰቦች ይዞታ በህገ ወጥ መልኩ እንዳይያዝ የተሟላ ጥበቃ የሚያደርግ የህግ
ማዕቀፍ አለ ማለት ይቻላል፡፡ በህገ ወጥ መልኩ የግለሰቦች ይዞታ እንዳይያዝ ጥበቃ
የሚደረግለት ከሆነ በተግባር የሚታየዉን ለማንሳት ያህል ብዙ ጊዜ የፍታብሄራዊ ክርክሮች
በተለይም ሁከት ይወገድልኝ የሚል ክርክር የተለመደ ሲሆን በወንጀል ህግ ግን ጥበቃዉ
በተግባር እየተሰራበት አይደለም፡፡30
የንብረት መብት እዉቅና ከተሰጠዉ ጀምሮ ይህ መብት ከሰባዊ መብት ጋር አበሮ መታየት
አለበት ወይስ የለበትም የሚለዉ ሀሳብ አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለዚህ በምክንያትነት
የሚጠቀሰዉ ንብረት የጥቂት ባለጸጎች ነዉ ስለሆነም አብዛኛዉን ድሀ ማህበረሰብ ለማግለል
የሚያገለግል መሳሪያ ነዉ በሚል ነዉ፡፡31 ሁሉን ዓቀፍ ዓለም አቀፍ የሰባዊ መብት ብያኔ
በ1948 ሲታወጅ የንብረት መብትን ልክ እንደ አንድ የሰባዊ መብት በማካተት ነበር ፡፡32በዚህ
መሰረትም ማንኛዉም ሰዉ ከህግ ዉጭ በሆነ አሰራር ወይም በዘፈቀደ የንብረት መብቱን
አያጣም በሚል ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን የሰባዊ መብትን በአስገዳጅ ሁኔታ የደነገገዉ የሲቭልና
የታለቲካ መብቶች እና የኢኮኖሚ፣ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ሰነድ ስለንብረት መብት
ምንም ያስቀመጠዉ ነገር የለም፡፡33

29
የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የፍትሐ ብሔር ሕግ፣ 1952 ከቁጥር 1168-69 ላይ ይመልቱ፡፡
30
ይሁን እንጂ በኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 685-88 ላይ በተግባር እየተሰራበት አይደለም፡፡
31
Cheneval, “Property Rights as Human Rights”, in H. de Soto and F. Cheneval, Realizing
Property Rights, Rueffer & Rub, Swiss Human Rights Book, Vol. I, 2006, at 11
32
Universal Declaration of Human Rights (UDHR), which in 1948 proclaimed in its Article 17 that
“[e]veryone has the right to own property alone as well as in association with others” and that
“*no one shall be arbitrarily deprived of his property.”
33
International Covenant on Civil and Political Rights, International Covenant on Economic, Social
and Cultural Right በዚህ የሰባዊ መብት ሰነድ ላይ የንብረት መብት በተለየ ሁኔታ ግልጽ የሆነ ድንጋጌ
አልተሠጠዉም፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሳዊ ህገ መንግስት አንቀጽ -40 (4) ስለንብረት መብት
የሚከተለዉን ያስቀምጣል፡፡ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች መሬት በነጻ የማግኘትና ከመሬታቸዉ
ያለመነቀል መብታቸዉ የተከበረ ነዉ፡፡ አፈጻጸሙን በተመለከተ ዝርዝሩ በህግ ይወጣል፡፡
ስለሆነም ከህገ መንንግስቱ ጀምሮ ትልቅ ትኩረት የተሰጠዉ ከመሆኑ ባሻገር ይህ ክፍል የሰባዊ
መብት ተደርጎ የተቀመጠ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ፡፡ ይህም የመሬት የይዞታ መብት
ከሰባዊ መብት ጋር የተመደበና ትኩረት የተሰጠዉ መሆኑን ያስረዳናል፡፡
ከዚህ በላይ የተመለከቱት የህግ ማዕቀፎች የግለሰቦችን የይዞታ መብት ከህገ ወጥ ይዞታ
የሚከላከሉ ከሆነ ባለእጅ (ይዞታ) የማድረግ አሰራር እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል? የሚል
ጥያቄ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ በህግ ወጥ መልኩ የሰዎች ይዞታ የተያዘ እንደሆነ ጥበቃ
የሚያድርግ ሲሆን ወደ ባለእጅ (ይዞታ) የሚሸጋገረዉ በህግ የተቀመጠዉ የጊዜ ገደብ ያለፈ
ከሆነ ብቻ ነዉ፡፡ ስለዚህ ግለሰቦች ይዞታቸዉን ከህገ ወጥ ይዞታ የማይከላከሉ እና መብታቸዉን
በአግባቡ ሳይጠቀሙ የቀሩ እንደሆነ ባለእጅ (ይዞታ) የሚለዉ አሰራር የተግባራዊ ይደረጋል፡፡
ይህም የሚያሳየን በመርህ ደረጃ የሰዎች የይዞታ መብት ጥበቃ የሚደረግለትና ግለሰቦችም
በይዞታቸዉ ሰላማዊ በሆነ መልኩ የመጠቀም እንደ አንድ የሰባዊ መብት ተደረጎ ይወሰዳል፡፡34
ነገር ግን ይህ መብት ፍጹማዊ (absolute) ነዉ ወይ? የዚህ ጥያቄ መልስ በአሉታዊ መልኩ
የሚታይ መሆኑን የሚያሳዩ የተለያዩ ሁኔታዎችን ወስደን ልንመለከት እንችላለን፡፡
የመጀመሪያዉ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ግለሰቦች በመሬትም ይሁን ሌላ ንብረት ላይ ያላቸዉን
የይዞታ መብት የሚያጡበት ስርዓት አለ፡፡ በዚህም መንግስት ካሳ በመክፈል የግለሰቦችን ይዞታ
የሚወስድበት ስርዓት ነዉ፡፡ ይህ የሚያሳየን የግለሰቦች ይዞታ በልዩ ሁኔታ ሊታጣ
የሚችልበትን ነዉ ፡፡ በተመሳሳይ የባለእጅ (ይዞታ) አሰራር የተዘረጋ ከሆነ በአንድ በኩል
አንደኛዉ ይዞታ የሚገኝበት መንገድ ነዉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የግለሰቦችን የይዞታ መብት
የሚያሳጣ ነዉ፡፡ ስለሆነም የባለእጅ አሰራር የሚዘረጉ ሀገራት ይህንን ልክ እንደ ህዝብ ጥቅም
በመቁጠር ግለሰቦች በህግ ይዞታቸዉ ህገ ወጥ በሆነ አያያዝ እንዳይወሰድባቸዉ ካደረጉ በ|ላ
ይህን በመጠቀም መብታቸዉን ሳያስከብሩ ከቀሩና ጊዜ ያለፈባቸዉ ከሆነ ይዞታቸዉን ሊያጡ
ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የባለእጅ(ይዘታ) ማብራሪያ (Justification) በመዉሰድ ሰዎች በልዩ ሁኔታ


34
የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 27 ላይ ይመልከቱ፡፡
ይዞታቸዉን የሚያጡበት ስርዓት ይዘረጋል፡፡ ይህ ስርዓት ለረጅም ጊዜ ተቀባይነት ያገኝ አሰራር
እና በሁሉም ሀገራት በሚባል ሁኔታ የሚሰራበት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡35
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ አሰራር የዜጎችን የይዞታ መብት የሚጋፋ ነዉ በሚል ክርክር
ሲቀርብበት ይስተዋላል፡፡36 በተለይም ይህ አሰራር ህገ ወጥነትን የሚያበረታታ ነዉ ስለሆነም
ተቀባይነት ሊኖረዉ አይገባም የሚል ሰፊ ተቃራኒ ክርክር ሲቀርብበት ይስተዋል፡፡37 ከዚህ ጋር
በተያያዘ በኢትዮጵያ የፌደሬሽን ምክር ቤት በተወሰነ ደረጃ አከራካሪ ዉሳኔ ወስኗል፡፡38 ይህን
ዉሳኔ ተከትሎ የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግስት የመሬት ይዞታን በተመለከተ በህገ ወጥ
መልኩ የተያዘ ይዞታ የይርጋ መከራከሪያን በማንሳት መከራከር አይቻልም የሚል በአዋጅ
ቀጥር 252/2010 ላይ አካትቶ ይገኛል፡፡39 ይህ ደግሞ ባለእጅ ማድረግ አሰራርን ሙሉ በሙሉ
የሚያስቀር ነዉ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዓላማም የዚህን አዋጅ ተገቢነት በምክንያት መገምገም ነዉ፡፡
ይህ አዋጅ ባለእጅ(ይዞታ)ን ለማስቀረት የደረሰበት ድምዳሜ ተገቢነት በዉል መመርመር እና
ከሌሎች ሀገራት ልምድ አንጻር መተቸት ነዉ፡፡ ለዚህ ንጽጽር የሚያግዘን የሚከተለዉን
የእንግሊዝ የፍርድ ቤት ጉዳይ ማየት እንሞክር፡፡ የኢትየጵያና የእንግሊዝ የመሬት ስሪት
አንጻር የተለየ መሆኑን ብገነዘብም ጉዳዩ ከይዞታ ጋር የተያያዘ ስለሆነ አንደምታዉ ተመሳሳይ
ነዉ፡፡
በእንግሊዝ ህግ ይህ አሰራር የመሬት ክርክሮችን በመፍታት ቁልፍ መርህ ሆኖ ቆይተል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ አሰራር በእንግሊዝ ህዝብ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የለዉም፡፡
40
በመሬት ወረራ ምክንያት ባለይዞታዎች ይነቀላሉ፣ የመንግስት ይዞታም ወደ ግለሰቦች
እንዲተላላፍ መንገድ የሚከፍት አሰራር ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ይህ አሰራር የመሬት ይዞታ


35
በሲቭል ሎዉ እና በኮመን ሎዉ ተከታ ሀገራት ተቀባይ ነት ያለዉ አሰራር መሆኑን ከግርጌ ማስታወሻ ቁጥር
6 ላይ ይመልከቱ፡፡በተጨማሪም Dixon MJ “Adverse Possession in Three Jurisdictions” 2006
Conveyancer 179-187
36
JA Pye (Oxford) Ltd and Another v Graham and Another [2000] Ch 676 ፣ JA Pye (Oxford)
Ltd v Graham [2001] Ch 804 ፣ JA Pye (Oxford) Ltd v Graham [2003] 1 AC 419 እነዚህን
የእንግሊዝ የፍርድ ቤት ጉዳይ ይመልከቱ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ክርክር የተደረበት ሁኔታ ያሳያሉ፡፡
37
Stake JE “The Uneasy Case for Adverse Possession” (2001) 89 Georgetown Law Journal
2419-2474
38
የኢፌዴሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት 4ኛ የፓርላማ ዘመን ፣5ኛ ዓመት፣ 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ሰኔ 18 ቀን 2007
ዓ.ም፡፡
39
የተሻሻለው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መወሰኛ አዋጅ ቁጥር
252 /2009 ዓ.ም
40
Dixon M “Adverse Possession and Human Rights” 2005 Conveyancer 345-351
ስርቆትን የሚፈቅድ ነዉ በሚል ይተቻል፡፡ ይህ መሰረታዊ ክርክር በመስተዋሉ ምክንያት
የሰዎችን ሰባዊ መብት የሚጥስ ስለሆነ የመሬት ምዝገባ ሥርዓት ባለበት ሁኔታ ጠቀሜታዉ
እየቀነሰ መጥቷል የሚሉ ትችቶች አሉበት፡፡ በሌላ በኩል ትችቶች ይኑሩ እንጅ ህጋዊ እዉቅና
ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል፡፡ የአሰራሩ መነሻ አንድ ይዞታ በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ በሆኑ
ባለይዞታዎች ቁጥጥር ስር ሊሆን አይችልም የሚል ነዉ፡፡

ባለእጅ (ይዞታ) የሚጠይቅ ሰዉ በህግ ዕዉቅና የተሰጠዉ ሁከት ፈጣሪ ነዉ፡፡ ይህ ሰዉ


በይዞታዉ የመጠቀምና ሌሎችን የመከልከል (እዉነተኛ) ባለይዞታዉን ጭምር መብት
ያጎናጽፈዋል፡፡ ስለዚህ በህግ እዉነተኛ ባለይዞታዎች መብት የሚያጡበት በአንጻሩ ደግሞ ሁከት
ፈጣሪዉ የይዞታ መብት የሚያገኝበት አሰራር ነዉ፡፡ ይህም ግለሰቦች በንብረት ላይ ያላቸዉን
የመብት አድማስ የሚያጠብ ነዉ፡፡በዚህ አሰራር ላይ ጠንከር ያለ ትችት የሚቀርብበት በተለይ
አጠቃላይ ከህግ ፍልስፍና አንጻር ሲታይ ነዉ፡፡ አንድ ጸሀፊ እንዳስቀመጠዉ ህግ የሚወጣዉ
ፍትህን ለማስተዳደር ነዉ ይላል፡፡ ስለሆነም ባለእጅ ( ይዞታ)ን አሰራር የሚፈቅድ ህግ ፍትህን
ከማስተዳደር አኳያ ሲታይ ፍታዊነቱ ጥያቄ ዉስጥ ይገባል ይላል ፡፡41 ይህም ህጉ ራሱ ሌቦችን
ጥበቃ በመስጠት ባለይዞታ የሚያደርግ አሰራር ነዉ፡፡ እዉነተኛ ባለይዞታዎች መብት
የሚቀጡበት በአንጻሩ ደግሞ የሰዉችን መሬት በወረራ የያዙ ሰዎች መብት የሚያገኙበት
አሰራር ፍታዊነቱን የሚቃወሙ ሰዎች አሉ፡፡42
የእንግሊዝ ፍርድ ቤት ዉሳኔ እና የአዉሮፓ የሰባዊ መብት ፍርድ ቤት እይታ
ሁለት የግል ኩባንያዎች ጀ.ኤ ፔይ(ኦክስፎርድ) ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ እና ጀ.ኤ
ፔይ (ኦክስፎርድ) መሬት ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ በስማቸዉ የተመዘገበ 23 ሔክታር
መሬት ባለቤት ነበሩ፡፡ በአዋሳኝም አቶ ግርሀም የተባለ ግለሰብ በግጦሽ ስምምነት
መሬቱን ይዞት ይቆያል፡፡ እንደ አዉሮፓዊያን አቆጣጠር ሕዳር 31ቀን 1983 የግጦሽ
ዉል ስምምነቱ የሚያበቃበት እና አቶ ግርሀምም መሬቱን የሚለቅበት ጊዜ ነበር፡፡
ይሁን እንጅ መሬቱ በአቶ ግርሀም እጅ ሆኖ ቀጠለ፡፡ ጥር 1984 እንደገና ዉል
ይታደስልኝ የሚል ጥያቄ ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ይሁንና አቶ ግርሀም
መሬቱን እንደያዘዉ እስከ 1999 ከባለቤቶች ፍቃድ ዉጭ በእርሻ ስራ ሲጠቀምበት ቆየ፡፡


41
Dockray M “Why do we Need Adverse Possession?” 1985 Conveyancer 272-284
42
Pascoe, Susan, 2011. Europe, human rights and land law in the 21st century: an English
example. Available from Middlesex University’s Research Repository
በ1997 አቶ ግርሀም ለመሬት ምዝገባ ባለስልጣን መሬቱ በስሙ እንዲመዘገብለት እና
መሬቱን ባለእጅ ያደረገዉ መሆኑን አመለከተ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የቀድሞ የመሬት
ባለቤቶች መሬቱን እንደሚያጡ አስታወቀ፡፡ይህን በመቃወም የመሬቱ ባለቤቶች የመሬት
ምዝገባዉ እንዲሰረዝላቸዉ አመለከቱ፡፡ አቶ ግርሀምም በይርጋ መቃወሚያነት በ1980
በተደነገገዉ የእንግሊዝ አዋጅ መሰረት ክርክር አቀረበ፡፡ ይህም አዋጅ አንድ ሰዉ
መሬቱን በ12 ዓመት ዉስጥ በእጁ ካላደረገ የይመለስልኝ ጥያቄ ማቅረብ አይችልም፡፡
የከፍተኛ ፍርድ ቤቱም በየካቲት 4/2000 በሰጠዉ ዉሳኔ አቶ ግርሀም መሬቱን
በይዞታዉ ስር በማድረግ ሲጠቀምበት በመቆየቱ ይህም በስሙ የማስመዝገብና ባለቤት
የመሆን መብት ስለሚያጎናጽፈዉ ጥያቄዉን ሳይቀበለዉ ቀረ፡፡ የኩባንያዉ ባለቤቶችም
ይግባኝ በመጠየቅ ይህን ዉሳኔ ማሻር ቻሉ፡፡ነገር ግን አቶ ግርሀም ይግባኝ ለ ሀዉስ ኦፍ
ሎርድስ በማቅረብ እንደገና የከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ዉሳኔ እንዲጸና ተደርጓል፡፡
ይህንን ዉሳኔ በመቃወም ለአዉሮፓ የሰባዊ መብት ፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ፡፡
የቅሬታዉ ምክንያትም የእንግሊዝ የባለእጅ (adverse possession) ህግ የአዉሮፓን
የሰባዊ መብት ኮንቬንሽን ፕሮቶኮል 1 አንቀጽ 1 የሚቃረን ነዉ በሚል ነዉ፡፡ ፍርድ
ቤቱም በእንግሊዝ ፍርድ ቤት በጊዜዉ ማቅረብ መብታቸዉን ባለመጠቀምና ለጠቅላላ
ህዝብ ጥቅም የተቀመጠዉን የይርጋ ህግ ከአዉሮፓ የሰባዊ መብት ኮንቬንሽ ፕሮቶኮል
1 አንቀጽ 1ላይ የተመለከተዉን በንብረት በሰላም የመጠቀም መብትን (Right to
peaceful enjoyment of property) ላይ የተለየ ተጽኖ የለዉም የሚል ዉሳኔ
አስተላልፋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በአብላጫ ድምጽ በሰጠዉ ዉሳኔ ሀገራት ለጠቅላላዉ ለህዝብ
ጥቅም ሲባል የሚያወጡዋቸዉ ህጎች ንብረትን በሰላም የመጠቀም መብትን
የሚያጣብቡ ቢሆንም ሚዛን ዉስጥ ለማስገባትና ገደብ ለመጣል መብት አላቸዉ፡፡
ስለሆነም በእንግሊዝ የይርጋ ህግ 1908 ላይ የተቀመጠዉ ባለእጅ (adverse
possession) የአዉሮፓዊያን የሰባዊ መብት ኮንቬንሽ ፕሮቶኮል 1 አንቀጽ 1 ጋር
የሚጣረስ አይደለም በማለት ምክንያት አስቀምጧል፡፡
ከዚህ ዉሳኔ የምንገነዘበዉ ባለእጅ (ይዞታ) አሰራር በራሱ የሰዎችን የንብረት መብት የሚጋፋ
አይደለም የሚለዉን ድምዳሜ ነዉ፡፡ ምንም እንኳ ይህ ስርዓት መዘርጋቱ ጥያቄ የሚያነሱ
ሰዎች ቢኖሩም ሀገራት ከህዝብ ጥቅም አንጻር በመመዘን ይህን ስርዓት አስፈላጊነት ላይ ባለዉ
ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ43 ጠቀሜታዉ ቢተገብርት የሰዎችን መብት የሚጋፋ አይደለም፡፡
ይህ አሰራር በክርክር የተፈተሸ ስርዓት ካለዉ ጠቀሜታ አንጻር በልዩ ሁኔታ ተግባራዊ ሊሆን
የሚገባዉ ስርዓት ነዉ፡፡ በእንግሊ የመሬት ህግ እንደ አዉሮፓዊያን አቆጣጠር በ2002 ላይ
ሲሻሻል ስርዓቱን ያስቀጠለ ሲሆን አንድ ጥብቅ ማሻሻያ ግን ተጨምሮበታል፡፡ይህም ስነ-
ስርታዊ ሲሆን ባለእጅ (ይዞታ) ተጠቃሚዉ ሰዉ ይህ መብቱን ያገኘዉ በይዞታ ስረዓት መሆኑን
ለመሬት መዝጋቢ ባለስልጣን ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡44
በአዲሱ ህግ (2002) መሰረትም አንድ ሰዉ ባለእጅ የማድረግን አሰራር በመጠቀም የመሬት
ባለቤት ለመሆን ስለመሬቱ የቀድሞ ባለቤት ማስታወቂያ መስጠት ይኖርበታል የሚል ግዴታ
ያስቀምጣል፡፡ ይህ ባለእጅ አድራጊ መሬቱን በስሙ ከማስመዝገቡ በፊት ለቀድሞ ባለቤት
ማስታወቂያ በመሬት መዝጋቢዉ ባለስልጣን በኩል ይነገረዋል፡፡ ማስታወቂያ ተነግሮት
የማይቃወም ከሆነ መሬቱን በፈቃዱ እንደለቀቀዉ ተቆጥሮ ለአዲሱ ባለመሬት ይመዘገብለታል፡፡
ይህ አሰራርም የሰዎችን መሰረታዊ መብት የሚጠብቅ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ መሰረታዊ
ዓላማዉም የመሬት ባቤቶችን በተለያየ ምክንያት ከእጃቸዉ የወጣዉን የመሬት መብት ጥበቃ
በማድረግ ነዉ፡፡
በኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግስታዊ ዉሳኔ ባለእጅ (ይዞታ)ን አስመልክቶ
የኢፊድሪ ህገ መንገስት ህገ መንገስታዊ ትርጉም የሚያስፈልጋቸዉን ጉዳዮች በህገ-መንግስት
አጣሪ ጉባዔ ከተጣራና ህገ-መንግስታዊ ትርጉም የሚያስፈልገዉ ከሆነ የመጨረሻ ዉሳኔ
እንደሚሰጥ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ መሰረት መጋበት 2 ቀን 2007 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር 682/04
ላይ የህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ የህገ መንግስት ትርጉም የሚያስፈልገዉ መሆኑን ስለተረዳ
ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የዉሳኔ ሀሳብ በማቅረብ ልኮታል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ ስንመለከት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግት ሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር
ዉስጥ ሙሌ ወረዳ ፍርድ ቤት የተጀመሬ የመሬት ይዞታ ይገባኛል ክርክር ነዉ፡፡ ክርክሩ
በወ/ሮ ማሚቱ ሰብለ እና ወ/ሮ ሙሉ ጉርሙ መካከል ሲሆን ወ/ሮ ማሚቱ ሰብለ በ1971 ዓ.ም

43
Land Registration for the Twenty-First Century: A Conveyancing Revolution – Number 271
(July 200) section 4.3.2 በዚህ የእንግሊዝ የመሬት ምዝገባ አዋጅ ላይ የባለእጅ (ይዞታ) አሰራር ዓላማ
ጠቀምጧል፡፡እነዚህም (adverse possession encourages owners not to sleep on their rights፣to
ensure that a possessor can feel confident that his right cannot be called into question after a
certain period of time has elapsed) የሚሉት ሲታዩ በአዲሲ የመሬት ምዝገባ አዋጅም ከቀድሞ አሰራር ጋር
ተመሳሳይ ዓላማ ይዞ የተቀረጸ ነዉ፡፡
44
የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 42 ላይ ይመልከቱ፡፡
ከባለቤታቸዉ ጋር በጋራ የተመሩት የእርሻ መሬት እያረሰ ከሚሰጣቸዉ ልጃቸዉ በኪራይ
ሰጥተዉት ይኖሩ ነበር፡፡ ይሁን እጅ ይህ ግለሰብ በሞት ከተለየ በ|ላ የሟች ሚስት የአሁን
ተጠሪ ሰብሉን ስለከለከለችንና መሬተሁንም አለቅም በማለቷ ወደ ፍርድቤት ከርክር ይገባሉ፡፡
የሟች ሚስት ወ/ሮ ሙሉ ገርሙ በበኩላቸዉ መሬቱን በስማቸዉ የተመዘገበና ለ12 ዓመት
በስማቸዉ ተመዝግቡ ሲጠቀሙበት የቆዩ መሆኑን ከወረዳዉ የመሬት አስተዳደር ጭምር
ማስረጃ በማቅረብ ተከራክረዋል፡፡ በየደረጃዉ የሚገኙ የኦሮሚያ ፍርድ ቤትም የወ/ሮ ማሚቱ
የይዞታ ጥያቆ በ10 ዓመት ይርጋ የተገደበ በመሆኑ ወ/ሮ ሙሉ ጉርሙን ልትጠየቅ አስችልም
በማለት ዉሳኔ አሰተላልፈዋል፡፡45 ይህን ዉሳኔ በመቃወም ወ/ሮ ማሚቱ ሰብለ ለህገመንግስት
አጣሪ ጉባዔ አቅረበዋል፡፡ አጣሪ ጉበዔዉም የኦሮሚ ፍርድ በቶች የሰጡት ዉሳኔ በህገ-መንግሰቱ
አንቀጽ 40(4) ላይ የተመለከቱን አርሶ አደሮች መሬት በነጻ የማግኘትና ከይዞታቸዉም
ያለመነቀል መብትን የመቃረን ነዉ በማለት ለፌደሬሽን ምክርቤት ህገ መንግስታዊ ትርጉም
እንዲሰጥበት የዉሳኔ ሀሳብ አቀረበ፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤትም ዉሳኔዉን ከመረመረ በ|ላ
በተከራካሪዎች መካከል የኪራይ ዉል ስለአለ የይዞታ ክርክር የሚያስነሳ አይደለም የሚል
ድምዳሜ እና የህገ መንግስቱን አንቀጽ 40 (4) ን የሚቃረን እንዲሁም የሴቶች ከወንዶች
የእኩልነት መብት የሚቃረን ዉሳኔ ስለሆነ በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 9 መሰረት ዉድቅ
አደርጎታል፡፡
1. ይህ የፌዴሬሽን ምክርቤት ወሳኔ ከባለእጅ (ይዞታ) ወይም የይርጋ ክርክር ጋር የሚገናኝ
ነዉ ወይስ አይደለም የሚለዉ ክርክር በባለሙያዎች ዘንድ ልዩነት አለ፡፡ ስለሆነም
ይህንን ወሳኔ ከይዞታ ክርክር ጽንሰ ሀሰብ ጋር መመርመር አስፈላጊ ነዉ፡፡ የባለእጅ
(ይዞታ) ይመለስልኝ ጥያቄ ሲቀርብ መሬቱን በእጁ ያደረገዉ ሰዉ ደግሞ የሚያነሳዉ
መከራከሪያ መሬቱን በባለቤትነት ስሜት በእዉነተኛ ቀጥርር በማድረግና የቀድሞ
የመሬቱ ባለቤትም ይሁን ሌሎችን በሚያገል ሁኔታ ስጠቀምበት የቀየሁና በህግ
የተቀመጠዉ የጊዜ ገደብ ያለፈ ስለሆነ ይህ የመሬት ይዞታ ወደእኔ የተላለፈና የቀድሞ
ባለይዞታም መብቱን በወቅቱ ባለመጠየቁ ከዚህ በ|ላ መብት የሎለዉ ስለሆነ ሊጠይቀኝ
አይችለም የሚል ይዘት አለዉ ፡፡ ይህ መከራከሪ የህግና የፍሬ ነገር ክርክር የያዘ
ጭብጥ ነዉ፡፡ ስለሆነም የምናረጋግጣቸዉ ፍሬ ነገሮችን ማጣራት እና በህግ መልስ

45
በየደረጃዉ የሚገኙ የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶችም ለዉሳኔያቸዉ መነሻ ያደረጉት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር
ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 69302 ቅጽ-13 ላይ የሰጠው የመሬት ይዞታ ጥያቄ በ10 ዓመት የተገደበ ነው
የሚለዉ አሰደዳጅ ዉሳኔ ነዉ፡፡
የሚያገኙትን ደግሞ መልስ መስጠትን ይመለከታል፡፡ ይህን ስናደርግ የተሟላ የይዞታ
ይገባኛል ክርክር ይሆናል፡፡ በሌላኛዉ ወገን የተነሳዉ ወይም በአሁኑ ጉዳይ ወ/ሮ ሙሉ
ጉርሙ የሚያነሱት መከራከርያ ደግሞ መሬቱን በባለእጅ (ይዘታ) ((adverse
possession)) ያገኘሁት ነዉ የሚለዉ ክርክር ቀጥታ የይርጋ ጉዳይ እንደሆነ ቀደም
ሲል አይተናል፡፡46 ስለዚህ በአሁኑ ጉዳይ ወ/ሮ ሙሉ የሚያነሱት መከራከርያ 12
ዓመት በስሜ ተመዝግቦ ባለእጅ(ይዞታ) አድርጌ የተጠቀምሁበት ነዉ የሚለዉ
መከራከርያ ሲታይ ለዉሳኔ መሰረት የሚሆነዉ ጭብጥ በትክክልም የባለእጅ(ይዞታ)
ክርክር ስለሆነ የይርጋ ክርክር እንዳለዉ መዉሰድ ተገቢ ነዉ ብሎ ጸሀፊዉ ያምናል፡፡
ከፌደሬሽ ምክርቤት ዉሳኔ ጋር የማልስማዉ ፍሬ ነገሩን የተገነዘበበት ሁኔታ ነዉ፡፡
ማለትም በመካከላቸዉ የኪራይ ዉል ስለ አለ የይዞታ ክርክር አይደለም በማለት
የደረሱበት ድምዳሜ የፍሬ ነገር አረዳድ ላይ ይሆናል፡፡ በእርግጥ በትክክል
በተከራካሪዎች መካከል የኪራይ ዉል ካለ የይዞታም ይሁን የይርጋ ክርክር አያስነሳም
የሚለዉ ነጥብ ላይ ልዩነት የለኝም ወይም የፌደሬሽ ምክርቤት ዉሳኔ ትክክል ነዉ፡፡
ነገር ግን በየደረጃዉ ከሚገኙ የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች ዉሳኔ መረዳት የሚቻለዉ
መጀመሩያ ወ/ሮ ማሚቱ በኪራይ የሰጠችዉ የእርሻ መሬት መሬትን በሚያስተዳድረዉ
የወረዳዉ መሬት አስተዳድር አማካኝነት ወደ ወ/ሮ ሙሉ የተላለፈ እና 12 ዓመት
የሞላዉ መሆኑን ነዉ፡፡ ይህን ፍሬ ነገር የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተረዳበት ሁኔታ
አጠቃላይ የዉሳኔዉን ጭብጥ ቀይሮታል፡፡ ስለሆነም ወ/ሮ ሙሉ ጉርሙ ባለእጅ
(ይዞታ) መብት ለማንሳት ቅድመ ሁኔታወችን አለሟላችም የሚል ድምዳሜ ያስይዛል፡፡
ስለሆነም ይህ የፌደሬሽን ህገ መንግስታዊ ዉሳኔ ሲታይ ባለእጅ (ይዞታ) አሰራር የህገ
መንግስቱን አንቀጽ 40(4) ላይ የተመለከተዉን የአርሶ አደሮችን ያለመነቀል መብት
የሚቃረን ነዉ የሚል ድምዳሜ ላይ በግልጽ አልደረሰም፡፡ የዚህ ዉሳኔ ፋይዳ ሲታይ
ልክ በአዉሮፓ ህብረት የሰባዊ ፍርድ ቤት አንደ ተሰጠዉ ዉሳኔ በማያሻማ ሁኔታ
ባለእጅ አሰራር ወይም በፍታብሄር ቁጥር 1168-69 ላይ የተመለከተዉ አሰራር ከህገ
መንግስቱ ጋር የሚቃረን መሆን ወይም አለመሆን በአግባቡ በጥኛትና በመረጃ ላይ
የተመሰረተ ህገ መንግስታዊ መልስ የሚያስፈልገዉ ሆኖ ሳለ በአግባቡ የቀረበዉን እንኳ
የፍሬ ነገር ሁኔታ ሳይረዳ የተሰጠዉ ዉሳኔ ለብዙ ክርክር ዳርጓል፡፡

46
የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 6 እንዲሁም የፍታብሄር ህግ ከቁጥር 1168-69 ላይ ይመልከቱ፡፡ በተለይም የሌሎች
ሀገራት የመሬት ይዞታ ይገባኛል ወይም ባለእጅ(ይዞታ) እና የይርጋ አዋጅን ይመልከቱ፡፡
2. ይህን የፌደሬሽን ወሳኔ ተከትሎ የአማራ ብሄራዉ ክልል በአዋጅ ቁጥር 252/2009
የመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀምን ለመሻሻል በወጣዉ አዋጅ ላይ በህገ ወጥ መልኩ
የተያዘ መሬት ይዞታ የይርጋ መከራከሪያ ሊቀርብበት አይችልም የሚል መርህ
አስቀምጧል፡፡ የአንቀጽ 55 <ስለ ይርጋ> የሚለዉ ክፍል ሙሉ ይዘት የሚከተለዉ
ነዉ፣
‹የገጠር መሬትን በወረራ ወይም በሌላ በማናቸውም ሕገ-ወጥ መንገድ ይዞ
በመገልገል ላይ የሚገኝ ማንኛውም ሰው መሬቱን እንዲለቅ በማንኛውም ሌላ
ሰው ወይም ሥልጣን ባለው የመንግሥት አስተዳደር አካል ሲጠየቅ ወይም
በመደበኛ ፍርድ ቤት ሲከሰስ የይርጋ ጊዜ ገደብን በሥነ-ስርዓት መቃወሚያነት
ሊያነሣ አይችልም›፡፡

የዚህን ድንጋጌ ትርጉም እና ፋይዳ በመረዳት ስራ ላይ ለማዋል በአግባቡ መመርመር አስፈላጊ


ከሆኑት ምክንያች አንዱ ይህ ድንጋጌ በፍታብሄር ህግ ቁጥር 1168-69 ላይ የተመከተዉን
የመሬት ይዞታ ባለእጅ (ይዞታ) የማድረግ አሰራርን ነዉ፡፡ ድንጋገዉ ግልጽነት የሚጎድለዉ
በመጀመሪያ <የገጠር መሬት> የሚለዉ ቃል የገጠር መሬት በአሁኑ የመሬት ስሪት መሰረት
በመንገስት፣በግል እና የጋራ ይዞታ የሚያዝ በመሆኑ ይህ ክልከላ ለየትኛዉ የይዞታ ዓይነት
ነዉ የሚለዉ ይሆናል፡፡ የመንግስት ይዞታን በህገ ወጥ መልኩ በመያዝ የባለእጅ ክርክር
ሊነሳበት ወይም የይርጋ ክርክር ሊቀርብበት እንደመይገባ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ
ያሳያል፡፡47በኢትዮጵያ የህግ ማዕቀፍ ይህንን ጉዳይ የሚመልስ ግልጽ ህግ ባለመኖሩ በፌደራል
ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር የተሰጠ ዉሳኔ አለ፡፡48 የዚህ አዋጅ
አላማም ይህ ለማጠናከር ከሆነ በጥሩ ጎኑ የሚይ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የህግ አዉጭዉ ሀሳብ
በተለያዩ አዋጁ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች ላይ የተገለጸዉ የህግ አዉጭዉ ሀሳብ
በአጠቃላይ የግለሰቦችም ይሁን የመንግስት የመሬት ይዞታን በህገ ወጥ መንገድ በመያዝ
የይርጋ ክርክር ሊቀርብበት አይችልም የሚል ነዉ፡፡49 ስለሆነም የዚህ ድንጋጌ ይዘት በግለሰቦች
መካከል የሚነሳዉን የባለእጅ (ይዞታ) ወይም የይርጋ ክርክር የሚያስቀር መሆኑ አይቀርም፡፡


47
የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 25
48
93013 ጥር 30, 2006 የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የመዝገብ ቁጥር
49
በዉይይት የተሳተፉ የአብክመ ፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና ህግ ምርምር ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች
እንደገለጹት ይህ ድንጋጌ የግለሰቦችን የመሬት ይዞታ ከህገ ወጥ ሰዎች ለመከላከል ታስቦ የተቀረጸ ድንጋጌ ነዉ፡፡
ይህም በፍታብሄር ህግ ከቁጥር 1168-69 ላይ የተመለከተዉን አሰራር የሚቃረን ይሆናል፡፡
ቀደም ሲል ይህ አሰራር ከዜጎች የንብረት መብት አኳያ በተለይም ፍታዊ ያልሆነ ንብረት
የማጣት ሁኔታ የተከለከለ ስለሆነ ይህ ዜጎች በንብረታቸዉ ላይ ያላቸዉን በሰላም የመጠቀምና
ያለ መነጠቅ (arbitrary deprivation) ነዉ የሚል ከርክር በእንግሊዝ የፍርድ ቤት ዉሳኔ ላይ
አዉሮፓ ህብረት የሰባዊ መብት ፍርድ ቤት መርምሮ ይህ የይርጋ ጉዳይ የራሱ የሆነ አሳማኝ
ማህባራዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት (justification)50 ስለ አለዉ የዜጎች ንብረት መብትን
አይቃረንም የሚል ዉሳኔ ሰጥቷል፡፡ ከፍ ሲል እንዳየነዉ የፌደሬሽን ምክር ቤትም በዚህ ጉዳይ
ላይ ግልጽ አkም በመያዝ ህገ መንግስታዊ ትርጓሜ አልሰጠበትም፡፡ ሌላዉ በ1952 ዓ.ም
የወጣዉ ኢትዮጵያ የፍታብሄር ህግ አልተሻሻለም፡፡ ምን አልባት ከመሬት ጋር በተያያዘ
በፌደራል ህገ መንግስት አንቀጽ-40 መሰረት የመሬት ባለቤትነት የህዝብና የመንግስት ስለሆነ
የፍታብሄር ህጉ ከቁጥር 1168-9 ላይ ተመለከተዉ የመሬትን ባለቤትነት ሊያስገኝ አይችልም፡፡
ከባለቤትነት በመለስ ያለዉን <የይዞታ መብት> በተመለከተ በይርጋ አማካኝነት በግለሰቦች
መካከል ያለዉን ክርክር ሊፈታ የሚችልበት አጋጣሚ ግን አለ፡፡ እዚህ ላይ የፌደራል ጠቅላይ
ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የወሰነዉ አስገዳጅ ዉሳኔ እድተጠበቀ ሆኖ በዚህ ጸሀፊ እምነት
የመሬት ይዞታ ይገባኛል ጥያቆ ይርጋን በተመለከተ 10 ዓመት ሳይሆን በ1168-9 ላይ
የተመከተዉ የ15 ዓመት የይርጋ ጊዜ ነዉ ብሎ ያምናል፡፡ቀደም ሲል እንደገለጽሁት በአጠቃላይ
አገላለጽ የመሬት ይርጋ 10 ዓመት ይሆናል የሚለዉ የፌደራል ጠቅላይ ፍረድ ቤት ሰበር ሰሚ
ችሎት ዉሳኔ ተገቢ ነዉ ብዬ አላምንም፡፡ በተጨማሪ የመሬት ይዞታ ይገባኛል ጥያቀን
በተመለከተ የሌሎች ሀገራት የዳበረ ልምድ የሚያሳየን ረዘም ያለ የጊዜ ገደብ ሊቀመጥለት
ይገባል፡፡ የአብዛኞች ሀገራት የየርጋ ህግ ከ30-60 ዓመት የሚደርስ ነዉ፡፡ ይህ ጊዜ ሲቀመጥ
የራሱ አመክኒኦ አለዉ፡፡ የግለሰቦች ይዞታ በህገ ወጥ መልኩ እንዳይያዝ ይዞታቸዉ እና ላይ
ሁከት እንዳይፈጠር ረዘም ያለ ጊዜ መቀመጡ ትክክል ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል ግን የለባእጅ (ይዞታ) አሰራርን ጭራሹን ክልከላ ማድረግ የይዞታ ዋስትና
የሚያሳጣ ስርዓት፣ ሰዎች ረጅም ጊዜ በቆየና አላስፈላጊ ክርክር እንዲያደርጉ መፍቀድ፣ ሰዎች
በይዞታቸዉ እርገጠኛ በመሆን መሬቱን በአግባቡ እንዳያለሙ (ከዛሬ ነገ ይዞታዬን ሊወሰድብኝ
ይችላል በሚል) ፣ ምርትና ምርታማነት እንዳይጨምር የሚያደርግ ስርዓት ይሆናል፡፡ ስለዚህ
በግልጽ ከላይ እንዳየነዉ የባለእጅ(ይዞታ) አሰራር በሁለት ተቃራኒ ጥቅሞች መካካል የሚዘረጋ

50
Goodman MJ “Adverse Possession of Land – Morality and Motive” (1970) 33 Modern Law
Review 281-288 281.
ስርዓት ስለሆነ በአንድ በኩል የግለሰቦችን የይዞታ መብት ጥበቃ በአግባቡ ማድረግ እነዚህ
የጥበቃ ዘዴዎች ላይ ችግር ካለ ይህንኑ መመርመርና ማስተካከል ይገባል፡፡ እነዚህ ጥበቃዎች
ዘተርግተዉ ነገር ግን ይህ መብቱን ሳይጠቀም የቀረና ሰነፍ የይዞታ ባለመብት ዘላለማዊ ጥበቃ
ማድረግ የአብዛኛዉን ህዝብ ጥቅም የሚጎዳ ስርዓት ይሆናል፡፡ ይህም ከጥንት ጀምሮ በንብረት
ህግ ስርዓት ተቀባይነት የነበረዉና በምክንያት የተደገፈ ስርዓትን የሚቃረን ነዉ፡፡
የአማራ ብሄራዊ መንግስ በመሬት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 252/2009 ላይ ከህገ ወጥ ይዞታ
ጋር በተያያዘ የይርጋ መከራከሪያ ሊሆን አይችልም የሚለዉ ክፍል ከፌደራል የህግ ማዕቀፍ
ጋር የመይጠጣም ሲሆን ለትርጉም ክፍት የሆነ ነዉ፡፡ በኢትዮጵያ ፌገራሊዝም መሰረት
የፌደራልና የክልል ህግ ቅራኔ ካለዘቸዉ እንዴት መተርጎም አለበት የሚል ጥያቄ ሚያስነሳ
ነዉ፡፡ በዚህ ክርክር ዙሪያ ግልጽ የሆነ ሥርዓት የተዘረጋ ስርዓት ባይኖርም ከፌደራል ህገ
መንግስት እና አዋጅ ቁጥር 25/88 ትርጉም ተነስተን የፌደራልና የክልል ህግ መካከል ቅራኔ
ካለ የፌደራል ህግ ተፈጻሚ መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለሆነም አዋጅ ቁጥር 252/2009 አንቀጽ 55
ላይ የተመለከተዉ ሀሳብ ህጋዊነት ጥያቄ የሚስነሳ ይሆናል፡፡

ማጠቃለያ
ከሮማዊያን ህዝቦች አንድ እንደተመሰረተ እና በእንግሊዝ ሀገር በስረዓት ደረጃ የተዘረጋዉ
ባለእጅ (ይዞታ) (adverse possession) በሁሉም ሀገራት ተቀባይነት ያለዉ ነገር ግን በስያሜ
ደረጃ በሮማዊያን ዘንድ ዩዝካፕሽ የሚባል ሲሆን በእንግሊዝና በኮመን ሎዉ ሀገራት ዘንድ
አድቨርስ ፖሰሽ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ሥርዓት የራሱ የሆነ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ
አመክኖዎች አሉት፡፡ በሌላ በኩል ግን የንብረት ይዞታ በአንድ በኩል የሚያሳጣ በሌላ በኩል
ደግሞ የሚያጎናጽፍ ገጽታ አለዉ፡፡ ይህን ስርዓት ተግባራዊ ከማድረጋችን በፊት በጥንቃቄ
የሚመረመሩ ቅድመ ሁኔታዎችን መሟላታቸዉን መረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ ይህም ይዞታዉን
በእዉን በቁጥጥር ስር በማድረግ የቀድሞ የንብረቱ ባለቤትንም ይሁን ሌሎችን በሚያገል
ሁኔታ፣ በግልጽ ለተከታታይ ጊዜ በህግ የተቀመጠዉን የጊዜ ገደብ ማለፍ ይኖርበታል፡፡

ይህ አሰራር ከይርጋ ህግ ጋር ከጥተኛ የሆነ ቁርኝት ስላለዉ የመሬት ይዞታ ይገባኛል እና


ሌሎች የይርጋ መከራከሪያዎች በይርጋ አዋጅ (አክት) ተመላክቶ ይገኛል፡፡ ስለሆነም የይዞታ
ይገባኛል ክርክር ካለ እና የጊዜ ገደብ ጥያቄን መልስ መስጠት አስፈላጊ ነዉ፡፡ ህገ ወጥ ይዞታ
እና የይዞታ ይገባኛል ክርክር የሚገኛኙበት ነጥብ የለም፡፡ ይህም በህገ ወጥ መልኩ የሌላ
ግለሰብ ይዞታ የሚይዝ ከሆነ በወንጀል እና በፍታብሄር ጥበቃ ስለሚደረግለት በእነኝህ
መንገዶች በመጠቀም መብቱን ማስከበር ይገባወል፡፡ ይዞታ መብት ከንብረት ጋር የተያያዘ
በመሆኑ አንዳንድ ዓለማቀፍና ክልል ዓቀፍ እንዲሁም የሀገራት ህጎች እንደ ሰባዊ መብት
በመቁጥር ጥበቃ ያደርጉለታል፡፡
በተመሳሳይ በኢትዮጵጣ የህግ ማዕቀፍም ከህገ መንግስቱ ጀምሮ የወንጀል ህግ፣የፍታብሄር ህግ
ለመሬትም ይሁን ሌሎች ይዞታዎች ጥበቃ ያደርጋሉ፡፡ ስለሆነም እነዚህን አማራጮች
ተጠቅመዉ ግለሰቦች ያላቸዉን የይዞታ መብት ሊያስከብሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ይህን
መብታቸዉን ባግባቡ ካልተጠቀሙ ለአጠቃላይ የህዝብ ጥቅም ሲባል የባለእጅ አሰራር
በመዘርጋት ህብረተሰቡን ካለአስፈላጊ ክርክሮች መካላከል፣ የሀገሪቱም ይሁን የክልሉ ዉስን
ሀብት የሆነዉን መሬት ኢኮኖሚያዊ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ የሚያዉል ስርዓት ሊዘረጋ
ይገባል፡፡
የባለ እጅ(ይዞታ) አሰራር የረጅም ጊዜ ታሪክ ባለቤት ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ክርክር
እያስነሳ መጥቷል፡፡ ይህም ከግለሰቦች የይዞታ መብት ጋር የሚቃረን ነዉ የሚል ሲሆን
ለመጀመሪያ ጊዜ ክርክር የተደረገበት በእንግሊ ሀገር የፍርድ ቤት ዉሳኔ በአዉሮፓ ህብረት
የሀባዊ መብት ፍርድ በት ነዉ፡፡ ይህ ፍርድ ቤት ክርክር ካደረገ በ|ላ አሰራሩ ለህብ ጥቅም
ሲባል የተደረገ ከሆነ ከሰዎች መብት ጋር የሚቃረን አይደለም የሚል ብይን ሰጥቷል፡፡ ከዚህ
ዉሳኔ ጭብ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ጉዳይ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ ጉዳዩን በአግባቡ
ሳይመረምር ስለቀረ የይዞታ ክርክር አይደለም የሚል ዉሳኔ በመስጠቱ ዕድሉን ሳይጠቀምበት
ቀርቷል፡፡ ስለሆነም የፍታብሄር ህግ ከቁር 1168-9 ላይ የተዘረጋዉ የባለእጅ(ይዞታ) የማድረግ
አሰራር ተግባራዊነት ይቀጥላል ወይም አልተሻሻለም የሚልዉን መገንዘብ አስፈላጊ ነዉ፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመሬት አሰተዳደር አዋጅን ለማሻሻል 252/2009 ሲያወጣ
የህገ ወጥ ይዞታን በተመለከተ የይርጋ መከራከሪያ ሊሆን እንደማይችል ክልከላ አስቀምጧል፡፡
ይህ ክልከላ ከፍታብሔር ህግ 1168-9 ላይ ከተመለከተዉ ስርዓት ጋር የሚቃረን ምክንያታዊ
ያልሆነ እና ተፈጻሚነቱ ጥያቄ ዉስጥ ያለ ነዉ፡፡

You might also like