Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 18

በምርመራ ወቅት በፖሊስ ጣቢያ የተሰጠ የምስክሮች ቃል በፍርድ ቤት እንዲቀርብ

ስለሚደረግበት የህግ አግባብ፣ በፍርድ ቤት ያለው ተቀባይነትና ተግባራዊ አፈጻጸሙ በአማራ


ክልል ፍርድ ቤቶች፡፡

በሰለሞን ተገኘወርቅ1

አጽርኦተ ይዘት

ይህ አጭር ጽሁፍ ትኩረት የሚያደርገው በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ ቁጥር (ወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ.)


145 ስር ተደንግጎ የሚገኘው ለፖሊስ የተሰጠ የምስክርነት ቃል ክሱን በሚሰማው /በሚያከራክረው/
ፍርድ ቤት ፊት ተቀባይነት የሚኖረውና ፍርድ ቤቱ ማስረጃውን እንደ ማስረጃ የሚቀበለው በምን
ሁኔታና ለምን ዓላማ ነው የሚለውን ነጥብ የሚመለከት ነው፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ
በግልጽ እንደተመለከተው ለፖሊስ የተሰጠ የምስክርነት ቃል በፍርድ ቤት ሊታይና እንደ ማስረጃ
ሊወሰድ የሚችል መሆኑ አከራካሪ ጉዳይ አይደለም፡፡ አከራካሪው ጉዳይ ፍርድ ቤት ይህን ማስረጃ እንደ
ማስረጃ የሚቀበለው ምን ሁኔታ ሲያጋጥምና በምን መልኩ ነው? የሚለው ነው:: የዚህን ድንጋጌ
አፈጻጸም በሚመለከት በባለሙያዎች ዘንድ የተለያዩ ግንዛቤዎች እንዳሉ ይስተዋላል፤ በተግባርም
በፍርድ ቤቶች ዘንድ የተለያዬ ትርጉም እየተሰጠ ሲሰራ እንመለከታለን፡፡ በብዙ ባለሙያዎች ዘንድ
ያለው ግንዛቤና በተግባርም በስፋት የሚሰራበት ለፖሊስ የተሰጠ የምስክርነት ቃል ፍርድ ቤት
ሊመለከተው የሚችለውና እንደ ማስረጃ የሚቀበለው ቀደም ሲል ስለወንጀሉ ፈጻሚና አፈጻጸም ማስረጃ
በመሆን ለፖሊስ ምስክርነታቸውን የሰጡ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ጉዳዩን ለማየት /ለማከራከር/ ስልጣን
ባለው ፍርድ ቤት በበቂ ምክንያት ቀርበው መመስከር ሳይችሉ ሲቀሩ ለፖሊስ የተሰጠው ምስክርነት
ፍርድ ቤቱ እንደሚመለከተውና ከማስረጃ ሚዛን ውስጥ በማስገባት ማስረጃውን መዝኖ እንዲሰራበት
ተብሎ የተደነገገ እንደሆነ የሚከራከሩ አሉ፤ በዚሁ ግንዛቤ መሰረትም ይሰራሉ:: በሌላ በኩል ይህንን
ሀሳብ የሚቃወሙ ባለሙያዎች እንደሚሉት ለፖሊስ የተሰጠ የምስክርነት ቃል ፍርድ ቤት ሊቀበለውና
ድንጋጌውም ተፈጻሚ የሚሆነው የዐቃቤ ህግ ምስክሮች የሰጡት የምስክርነት ቃል ጉዳዩን በሚያየው
ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው የሰጡት የምስክርነት ቃል ለመርማሪ ፖሊስ ከሰጡት ቃል ጋር ተቃራኒ
/አስጠቂ/ በሆነ ጊዜ ነው በማለት ሀሳባቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

በባለሙያዎች ዘንድ ከላይ የተመለከቱት ሁለት ዓይነት ግንዛቤዎችና አሰራሮች ቢኖሩም የህግ አውጭው
ሀሳብና የድንጋጌው አላማ በፖሊስ የተሰጠ የምስክርነት ቃልን ፍርድ ቤት ሊመለከተው የሚችለው
ሰነዱ ኮፒ ተደርጎ እንደ ጽሁፍ ማስረጃ ዓይነት ሳይሆን የዓቃቤ ህግ ምስክሮች በፍርድ ቤት ቀርበው
የሰጡት ቃል ቀደም ሲል ለመርማሪ ፖሊስ ከሰጡት ቃል ጋር የሚቃረን /አስጠቂ/ ሲሆን ይህንኑ

1
ሰለሞን ተገኘወርቅ (LLB, LLM) ቀደም ሲል በአብክመ ፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና ህግ ምርምር ኢንስቲትት የሰሩ ሲሆን
በአሁን ወቅት በአብክመ ፍትህ ቢሮ የክልል ዐቃቤ ህግ ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
በፍርድ ቤት የተሰጠውን ምስክርነት ውሸት መሆኑን ለማስተባበል ሲባል ፍርድ ቤቱን አስፈቅዶ ዐቃቤ
ህግ ወይም ተከሳሽ በመሪ ጥያቄ ወይም በመስቀለኛ ጥያቄ አማካኝነት የተሰጠውን የምስክርነት ቃል
ማስተባበል እንዲችሉ በማሰብ የተቀረጸ ድንጋጌ እንደሆነ ግንዛቤ መያዝ ይገባል፡፡

1. ስለምስክርነት አንዳንድ ነጥቦች

ማስረጃ የአንድን አከራካሪ ጭብጥ መኖር ወይም አለመኖር በማረጋገጥ የዳኛን አእምሮ
በማሳመን ወደ አንድ ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ ፍሬ ነገር ነው2፡፡ በወንጀል ምርመራ ሂደት
ውስጥ ጠንካራ የሆነ የወንጀል ምርመራ ስርዓት አለ ሊባል የሚችለው ስለወንጀሉ አፈጻጸም
በሚመለከት በዝርዝር ሊያስረዱ የሚችሉ ማስረጃዎችን ሰብስቦ አጥፊውን ፍርድ ቤት አቅርቦ
ጥፋተኛ ለማስባል የሚያስችል አሳማኝና በቂ ማስረጃ በህግና በስርዓት መሰብሰብ ሲቻል ነው፡፡
በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ውስጥ የአንድን የወንጀል ድርጊት መፈጸምና አለመፈጸም፣
የወንጀል ፈጻሚውን ማንነት ለመለየት የሚያስችል አግባብነትና ተቀባይነት ካላቸው ከተለያዩ
የማስረጃ ዓይነቶች ውስጥ ምስክርነት (የሰው ማስረጃ) ዋነኛው ነው፡፡ ስለሆነም ምስክርነት
ከአንድ የወንጀል ድርጊት ጋር በተያያዘ የወንጀል አድራጊውን ሁኔታ በአግባቡ ለዳኛው
በማስረዳትና አጥፊን ከንጹህ በመለየት ሂደት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው ነው፡፡ ምክንያቱም
ምስክርነት በወንጀል ጉዳይ ክርክር በሚደረግበት ጊዜ ወንጀሉ መቼ ተፈጸመ፣ የት ተፈጸመ፣
እንዴት ተፈጸመ፣ በምን ተፈጸመ፣ በማን(እነማን) ተፈጸመ፣ በምን ምክንያት ተፈጸመ
የሚሉትን የወንጀል ድርጊቱን ዋና ዋና ማቋቋሚያ ፍሬ ነገሮችና ጭብጦች ለመለየትና በግልጽ
ለማሳየት የሚያስችል በመሆኑ ነው3፡፡

ምስክርነት ከሌሎች ማስረጃዎች አንጻር ሲታይ ምናልባትም ረጅም እድሜ ያስቆጠረና በፍርድ
ቤትም የወንጀሉን አፈጻጸም በአግባቡ በማረጋገጥ በኩል አግባብነት ያለው ማስረጃ ነው4፡፡
በተለይም ምስክርነት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት በወንጀል ፍትህ ስርዓቱ ውስጥ
ክርክሮችን ለማስረዳት ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም በሀገራችን ሳይንሳዊ የወንጀል
የምርመራ ዘዴን ተጠቅሞ የቴክኒክ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ ከፍተኛ የሆነ የእውቀት፣
የዘመናዊ መሳሪያ እና የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት የሚታይ በመሆኑ ነው፡፡ ታዲያ
ምስክርነት አጥፊን ከንጹህ ለመለየት እንዲያስችል በፍርድ ቤት የሚቀርቡ ምስክሮች የስነ-

2
ታጠቅ ታደሰ፣ የማስረጃ ህግ መሰረተ ሀሳቦች፣ አዲስ አበባ ዩ ኒቨርስቲ መጻህፍት ማእከል፣ 1997 ዓ.ም፣ገጽ 1
3
ዝኒ ከማሁገጽ 161-163
4
ዝኒ ከማሁ ገጽ 161-165
ስርዓት ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ምስክሮቹ እውነት ለመናገራቸው ቃለ-መሀላ ፈጽመው
ምስክርነታቸውን መስጠት ይኖርባቸዋል፤ ምስክርነታቸውም ስነ-ስርዓት ህጉ በሚፈቅደው
መሰረት የተለያዩ ጥያቄዎችን በማለፍ የተፈተነና ተዓማኒ መሆን ይገባዋል፡፡

2. የምስክሮች ቃል የሚፈተን ስለመሆኑ

ምንም እንኳን ምስክርነት ለወንጀል ክርክር ትልቅ የማስረጃ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ቢሆንም
በተለይም በአሁኑ ወቅት የምስክር ቃል በባህሪው ብዙ ህጸጾች ያሉበትና ተዓማኒነቱን ሊቀንሱ
የሚችሉ ምክንያቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ምስክርነት በተፈጥሮው በሰዎች የስሜት ህዋሳት ላይ
ተመስርቶ የሚሰጥና በሰው የማስታወስ ችሎታ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ የራሱ ጉድለት ያለበት
ነው፡፡ ስለሆነም የሰው ምስክርነት እንደ ማስረጃ ከመወሰዱ በፊት የተለያዩ ስርዓቶችን ማለፍ
ይኖርበታል፡፡ አንድ ምስክር በፖሊስ ጣቢያ ወይም በፍርድ ቤት ቀርቦ ምስክርነቱን ከመስጠቱ
በፊት ምስክሩ በአካልና በአእምሮ ብቁ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህም ማለት ምስክሩ
የተፈጸመውን ድርጊት ለመረዳት የሚችል መሆኑ፣ ድርጊቱን ተገንዝቦ በማስታወስ
ለሚመለከተው አካል (ለፍርድ ቤት ወይም ለመርማሪ ፖሊስ) እንደገና ለመግለጽ የሚችል
መሆኑ፣ ምስክሩ ቃለ-መሀላ የሚፈጽም (ፍርድ ቤት) እና እውነት በመመስከርና ሀሰት
በመመስከር መካከል ያለውን ልዩነት የሚረዳ መሆን ይገባዋል፣ የምስክሩ የአካልና የአእምሮ
ብቃት የሚቀርብለትን ጥያቄ ለመረዳትና ለመመለስ የሚያስልች መሆኑ መታየት እንዳለበት
ጠቅላላ የማስረጃ ህግ መርህ ያስገነዝባል5፡፡

ምስክርነት የተለያዩ እንከኖች እንዲኖሩበት የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡


ከእነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ምስክሩ ሰው በመሆኑ ምክንያት ድርጊቱ በተፈጸመ ጊዜ
የተመለከተውን ወይም የሰማውን ወይም በሌሎች የስሜት ህዋሳቶቹ አማካኝነት የተረዳውን
ነገር ለመርማሪ ፖሊስ ወይም ክርክሩን ለሚያየው ፍርድ ቤት ቀርቦ ሲመሰክር ቀድሞ
የሚያውቀውን እውነታ አስታውሶ ላይመሰክር ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የሰው ምስከርነት ጉድለት
የሚመጣው በምሰክሩ ከውስጡ በመነጨ ወይም በተካራካሪ ወገኖች ተጽእኖ በመነሳት ቀደም
ሲል ለፖሊስ የሰጠውን ቃል በመቀየር ሀሰት ሊመሰክር የሚችልበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡
በተጨማሪ ምስክሮች በቂም በቀልና በጥላቻ በመነሳሳት ወንጀል ያልፈጸመ(ሙ) ግለሰብን(ቦችን)

5
Gary L. wells and Elizabeth A.፣ Eye witness testimony፣ https// public.psych iastate edu/glweslannual review፣ 2003 ገጽ 53
የተወሰደው ሰኔ 15/2010 ዓ.ም
በሀሰት በመደራጀት አላግባብ በሀሰት በመክሰስ /በመመስከር/ እንዲቀጡ ሊያደርጉ ይችላሉ፣
በተመሳሳይ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች ለድርጊታቸው ተገቢውን ቅጣት እንዳያገኙ በማሰብ
በሀሰት በመከላከያ ምስክር በመደራጀት ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ነጻ እንዲወጡ ሊያደርጉ
ይችላሉ6፡፡ እንዲሁም ምስክሮች ጉዳዩን በሚመለከተው ፍርድ ቤት ቀርበው ከመመስከራቸው
በፊት በሞት ሊለዩ ይችላሉ፣ በጽኑ ህመም ምክንያት ፍርድ ቤት ቀርበው መመስከር
የማይችሉበት ሁኔታ ያጋጥማል፣ ከሀገር ሊወጡ ይችላሉ፣ ቀደም ሲል ካስመዘገቡት አድራሻ
ሊጠፉ ወይም ሊሰወሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህና ሌሎች መሰል ምክንያቶች በሰው ምስክር ላይ
የሚታዩ ጉድለቶች ናቸው፡፡

ታዲያ ምስክርነት እንደዚህ ዓይነት ህጸጾች የሚታዩበት ስለሆነ ችግሩን ለመቀነስ የወንጀል ስነ-
ስርዓት ህጉ የምስክሮች ቃል የሚጣራበትንና የሚፈተንበትን ስርዓት ዘርግቶ እናገኘዋለን፡፡
የምስክሮች ቃል ተዓማኒ እንዲሆን ምስክር በሚሰማበት ወቅት በአግባቡ መፈተን ይኖርበታል፡፡
ማስረጃው የሚፈተነው በዋና ጥያቄ፣ በመስቀለኛ ጥያቄ፣ በመሪ ጥያቄ ወይም በማጣሪያ ጥያቄ
ሊሆን እንደሚችል በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ ላይ ተመልክቷል፡፡ በመስቀለኛ ጥያቄ
ወይም በመሪ ጥያቄ የምስክር ቃል ሲፈተን የጥያቄው ዋና ዓላማ የተሰጠውን ምስክርነት
ማስተባበልና በፍርድ ቤቱ ዘንድ ተዓማኒ ተደርጎ እንዳይታይ ለማድረግ ነው፡፡ የምስክርነትን
ቃል በመስቀለኛ ጥያቄ ወይም በመሪ ጥያቄ የሚፈተንበትና የሚስተባበልበት ዘዴ
በእንግሊዘኛው “impeachment” ተብሎ የሚታወቅ ነው7፡፡ የምስክሩ ቃልም የሚፈተነው የስነ-
ስርዓት ህጉ ምስክር በሚሰማበት ወቅት በተከራካሪ ወገኖች በኩል የቀረቡ ምሰክሮች
የሚጠየቁበትንና የምስክርነት ቃሉ የሚፈተንበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ በተቀመጠው ስርዓት
መሰረት ነው፡፡

3. በምርመራ ወቅት ለፖሊስ የተሰጠን የምስክርነት ቃል ፍርድ ቤት


ስለሚመለከትበት ሁኔታ እና የወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ ድንጋጌ

አንድ ወንጀል የተፈጸመ መሆኑን መርማሪ ፖሊስ መረጃ በደረሰው ጊዜ ምንም ዓይነት ጊዜ
ሳያጠፋ ወንጀሉን ያስረዳሉ የተባሉ ማስረጃዎችን ሁሉ እንደየአግባብነታቸው መሰብሰብና
መተንተን እንደሚገባው የወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ ያስገነዝባል፡፡ ከሚሰበሰቡት
ማስረጃዎች ውስጥ የምስክር ቃል አንዱና ዋነኛው ሲሆን በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ

6
ሀብታሙ በቃሉ፣ በአብክመ ፍትህ ቢሮ የደብረ ብርሀን ቋሚ ምድብ ዐቃቤ ህግ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ፣ ሰኔ 9/2010 ዓ.ም
7
ከላይ በግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 4
አንቀጽ 30 ስር መርማሪ ፖሊስ የምስክር ቃል እንዴት መቀበልና መመዝገብ እንዳለበት
ዝርዝር ስርዓቱን የሚያመለክት ድንጋጌ እናገኛለን፡፡ ማስረጃዎችም ተሰብስበው ካለቁ በኋላ
የምርመራ መዝገቡ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት ትይዩ የሆነ ስልጣን ላለው
የዐቃቤ ህግ መስሪያ ቤት እንደሚላክና እንደሁኔታው የምርመራ መዝገቡን የሚመለከተው
ዐቃቤ ህግ ክስ የመመስረት፣ ለተጨማሪ ምርመራ የመላክ ወይም የክስ አላቀርበም ውሳኔ
ሊሰጥ እንደሚቸል የስነ-ስርዓት ህጉ ያስገነዝባል8፡፡ የምርመራ መዝገቡም ክስ የሚያስመሰረት
ሆኖ በተገኘ ጊዜና ዐቃቤ ህግ ክስ ከመሰረተ በኋላ ክርከር እንደሚጀምር በክርክር ሂደትም ዐቃቤ
ህግና ተከሳሽም የየራሳቸውን ምስክሮች እንደሚያሰሙ ስነ-ስርዓት ህጉ ያስቀምጣል፡፡ ምስክሮች
በሚሰሙበት ጊዜ ተከራካሪዎቹ ወገኖች ስነ-ስርዓት ህጉ እንዳስቀመጠው እንደ አግባብነቱ የዋና
ጥያቄ፣ የመስቀለኛ ጥያቄና የመሪ ጥያቄ የሚጠይቁበት ስርዓት ተዘርግቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም
ማጣሪያ ጥያቄ የሚጠይቅበት ሁኔታ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም ፍርድ ቤቶች ለትክክለኛ
ፍትህ አሰጣጥ አስፈላጊ ነው ብለው ሲያምኑ በዐቃቤ ህግ ወይም በተከሳሽ የማስረጃ ዝርዝር
ውስጥ ያልተጠቀሱ ምስክሮችን ማስቀረብና መስማት እንደሚችሉ ህግ አውጭው ስልጣን
ሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሹ ወይም ዐቃቤ ህጉ ሲያመለክቱ የዐቃቤ ህግ
ምስክሮች ለፖሊስ የሰጡትን ቃል ፍርድ ቤቱ ሊመለከተው የሚችልበት እድል እንዳለ
በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ በቁጥር 145 ስር እንደሚከተለው ተደንግጎ ይገኛል፡፡

(1) ዐቃቤ-ህጉ ወይም ተከሳሹ ሲያመለክት በፖሊስ ምርመራ ጊዜ የተሰጠውን የምስክርነት ቃል


ፍርድ ቤቱ ሊመለከተው ይችላል፡፡

(2) ከዚህ በኃላ ለትክክለኛ ፍርድ አሰጣጥ የሚጠቅም መስሎ ከታየው የዚህ ቃል ግልባጭ
ለተከሳሹ እንዲደርሰው አድርጎ በዚህ መሰረት ምስክሩ የሰጠውን ቃል ለማስተባበል ይቻላል፡፡

ከላይ በተመለከተው አንቀጽ በንኡስ ቁጥር 1 ስር የተገለጸው ዓረፍተ ነገር እንደሚያመለክተው


ዐቃቤ ህጉ ወይም ተከሳሹ ሲያመለክቱ በፖሊስ ምርመራ ወቅት የተሰጠ የምስክሮችን ቃል
ክሱን የሚያየው /የሚያከራክረው/ ፍርድ ቤት የምርመራ መዝገቡን አስቀርቦ ሊመለከተው
እንደሚችል በግልጽ የተቀመጠና ጥያቄ የማያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡ አከራካሪው ነጥብ ዐቃቤ ህጉ
ወይም ተከሳሹ በምርመራ ወቅት በፖሊስ ጣቢያ የተሰጠው የምስክርነት ቃል እንዲቀርብላቸው
የሚያመለክቱትና ፍርድ ቤቱም እንዲመለከተው የሚደረገው በክርክር ሂደት ምን ሁኔታ

8
የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት፣ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ፣ 1954 ዓ.ም፣ አንቀጽ 37፣አንቀጽ 38(ሐ)፣ አንቀጽ 42(1-ሀ) ስር
የተመለከተውን ዝርዝር ድንጋጌዎች ይመልከቱ፡፡
ሲያጋጥም ነው የሚለው ነጥብ ነው፡፡ እንዲሁም በዚሁ ድንጋጌ በንኡስ ቁጥር 2 ስር
በተመለከተው ዓረፍተ ነገር ላይ ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ የሚጠቅም በሆነ ጊዜ የምስክሩ(ሮቹ)
ቃል ግልባጭ ለተከሳሹ እንዲደርሰው በማድረግ ዐቃቤ ህግ የምስክሩን ቃል “ለማስተባበል”
ይችላል ተብሎ የተደነገገው ነው፡፡ ከላይ በተገለጸው ድንጋጌ ስር የሚታየው የክርክር መነሻና
በባለሙያዎች ዘንድ የሚታየው የግንዛቤ ልዩነት የሚመነጨው ዐቃቤ ህግ ወይም ተከሳሽ
የዐቃቤ ህግ ምስክር ቀደም ሲል ለፖሊስ የሰጠውን የምስክርነት ቃል ፍርድ ቤቱ
እንዲመለከትላቸው አቤቱታ የሚያቀርቡትና ፍርድ ቤቱም እንደ ማስረጃ የሚወስደው መቼና
በምን ዓይነት መንገድ ነው የሚለው ነው፡፡ ይህን ነጥብ በሚመለከት በክልላችን በሚገኙ ፍርድ
ቤቶች በሚሰሩ ዳኞች፣ ዐቃብያነ ህግና ጠበቆች ዘንድ በዋናነት በሁለት ሊከፈል የሚችል
አረዳድና አተረጓጎም እንዳለ ይስተዋላል፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚገልጹትና በተግባርም
ሲሰሩ የሚታየው በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ ቁጥር 145 (1፣2) ስር የተቀመጠው
ድንጋጌ ተፈጻሚ የሚሆነውና ለፖሊስ የተሰጠ የምስክርነትን ቃል ፍርድ ቤት ሊመለከተው
የሚችለው ቀደም ሲል ስለወንጀሉ አፈጻጸምና የወንጀሉን ፈጻሚ ማንነት በሚመለከት
በቀጥታም ይሁን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ምስከሩ አውቃለሁ በማለት ለመርማሪ ፖሊስ
ምስክርነቱን የሰጠ ምስክር ክሱን ለማየት ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ፊት ቀርቦ መመስከር
ሳይችል በቀረ ጊዜ ተፈጻሚ የሚደረግ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ማለት ምስክሩ ክርክሩ
በሚሰማበት ጊዜ የዐቃቤ ህግ ምስከር በህይወት ከሌለ፣ ከሀገር ከወጣ፣ ቀደም ሲል
ባስመዘገበው አድራሻ ካልተገኘ ወይም በጽኑ ህመም ምክንያት ፍርድ ቤት ቀርቦ መመስከር
ካልቻለ የዓቃቤ ህግ ምስከር/ሮች/ ባለሰማታቸው /ባለመቅረባቸው/ ክርክሩ መቋረጥ
ስለማይገባው ወይም የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን በማፈላለግ ምክንያት ፍትህ እንዳይጓተት ሲባል
ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ የተሰጠውን የምስክርነት ቃል ሊመለከተውና በማስረጃነት ተቀብሎ
ከማስረጃ ምዘና ውስጥ በማስገባት ውሳኔ ሊሰጥ የሚችልበትን እድል የሚፈጥር ስነ-ስርዓት
ነው በማለት ያስቀምጣሉ፤ በዚሁም አረዳድ በተግባር ሲሰሩ ይታያል9፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች
ለክርክራቸው ማጠናከሪያና ማነጻጸሪያ የሚያደርጉት በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ ቁጥር
144 ስር የተደነገገውን የቀዳሚ ምርመራ ዓላማ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-
ስርዓት ህጉ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው ቀዳሚ ምርመራ የሚደረግበት ዋናው ዓላማ ማስረጃ
ጠብቆ ለማቆየት (preservation of evidence) ነው፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ

9
በሰሜን ሽዋ ዞን ፍትህ መምሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሚሰሩ ከተወሰኑ የወንጀል ዐቃብያነ ህጎችና ዳኞች ጋር የተደረገ ውይይት
ሰኔ 13፣ 2010 ዓ.ም
ቀዳሚ ምርመራ በአስገዳጅነት እንዲደረግ የተቀመጠው ለከባድ ሰው መግደል ወንጀልና ለከባድ
ውንብድና ወንጀሎች ነው፡፡ በሌሎች ወንጀሎች ዐቃቤ ህግ ቀዳሚ ምርመራ እንዲደረግ ካላዘዘ
በስተቀር ቀዳሚ ምርመራ የሚደረግበት አግባብ እንደማይኖር መገንዘብ ይቻላል፡፡ ታዲያ ከከባድ
ሰው መግደልና ከከባድ ውንብድና ወንጀሎች ውጭ በሆኑ ወንጀሎች ቀዳሚ ምርመራ
ስለማይደረግ የምስክር ቃል የማይጠበቅበት (preservation of evidence) ስለማይኖር የክርክር
ሂደቱ እንዳይቋረጥ ወይም እንዳይጓትት በማሰብ በስነ-ስርዓት ህጉ የተቀየሰ ስልት እስከሌለ
ድረስ በክርክር ሂደቱ ላይ እንቅፋት እንደሚያጋጥም የሚታወቅ ነው፡፡ እንደነዚህ ባለሙያዎች
አረዳድ ለዚህ ችግር መፍትሄ የሚሆን የወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ በአንቀጽ 145 ስር
የተመለከተውን ድንጋጌ ህግ አውጭው ያስቀመጠበት ምክንያት፡፡ ይሄውም ቀዳሚ ምርመራ
እንዲደረግ ህጉ በማያስገድድበት ጊዜና ዓቃቤ ህግም ቀዳሚ ምርመራ እንዲደረግ ባላዘዘበት
ወቅት ምስክሮች ባለመቅረባቸው ምክንያት ክርክሩ እልባት ሳያገኝ መቅረት የለበትም በሚል
እምነት ለፖሊስ የተሰጠ ምስክርነት በቀዳሚ ምርመራ ወቅት እንደተሰጠ ምስክርነት ዓይነት
ተቆጥሮ በፍርድ ቤት እንደ ማስረጃ እንዲወሰድ በማሰብ የተቀረጸ ድንጋጌ ነው10፡፡ እንደነዚህ
ባለሙያዎች አረዳድ ከሆነ ቀዳሚ ምርመራ ባልተደረገባቸው ወንጀሎች ስለወንጀሉ ያስረዳሉ
ተብለው ምስክርነታቸውን ለፖሊስ የሰጡ ምስክሮች ጉዳዩ በሚታይበት ወቅት በሞት
በመለየት፣ በጽኑ ህመም ምክንያት ለመመስከር ብቁ አለመሆን፣ ከሀገር በመውጣት ፍርድ ቤት
አለመቅረብ ወይም ምስክሩ በአድራሻው ባለመገኘት ፍርድ ቤት መቅረብ ካልቻሉና ምስክሮቹ
ቀርበው ባለመመስከራቸው ክርክሩ መቋረጥ ስለማይገባው ህግ አውጭው ይህንን ክፍተት
ለመሙላት በሚል ለመርማሪ ፖሊስ የተሰጠው የምስክርነት ቃል እንደ ማስረጃ ተወስዶ
ማስረጃው እንዲመዘን በማሰብ የተቀመጠ ነው በማለት ሀሳባቸውን ይገልጻሉ11፡፡

በሌላ በኩል ከላይ የተገለጸውን አተረጓጎም የማይቀበሉ ባለሙያዎች አንደሚሉት


በወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ 145(1፣2) ስር የተቀመጠው ድንጋጌ ተፈጻሚ የሚሆነው የዐቃቤ ህግ
ምስክር/ሮች/ ፍርድ ቤት ቀርበው መመስከር ባልቻሉ ጊዜ ሳይሆን የቀረቡት የዐቃቤ ህግ
ምስክሮች ቀደም ሲል ፖሊስ ለይ ከሰጡት ምስክርነት ጋር የሚቃረን ወይም አስጠቂ የሆነ
ምስክርነት በሰጡ ጊዜ ዐቃቤ ህግ ወይም ተከሳሹ በፍርድ ቤት የተሰጠውን ምስክርነት
ለማስተባበል የሚችሉበትን እድል ለመፍጠር ሲባል የተቀረጸ ድንጋጌ ነው በማለት
መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች እንደሚሉት የድንጋጌውን ዓላማና የህግ

10
11
´’> ŸTG<
ዝኒ ከማሁ
አውጭውን ሀሳብ ለመረዳት ድንጋጌውን በአግባቡ መረዳት እንደሚገባ ያስቀምጣሉ፡፡ ይሄውም
በአንቀጽ 145 (2) ስር በአማርኛው ቅጂ ላይ እንደተመለከተው “….. ለትክክለኛ ፍርድ አሰጣጥ
የሚጠቅም ሆኖ ከታየው …. ምስክሩ የሰጠውን ቃል ለማስተባበል ይቻላል” በሚል የተቀመጠ
ሲሆን ይሄው ድንጋጌ በእንግሊዘኛው ቅጂ ላይ “… such statement may be used to
impeach the creadit of the witness…” በሚል ተቀምጧል፡፡ ከላይ ከተገለጸው ዓረፍተ
ነገር መረዳት እንደሚቻለው ፖሊስ ላይ የተሰጠውን ምስክርነት ፍርድ ቤቱ የሚመለከተው
ምስክሩ የሰጠውን ቃል ለማስተባበል እንዲቻል እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ምስክሩ
ጉዳዩን በሚያው ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደመሰከረ ያስገነዝባል፡፡ የሚስተባበለውም ቃል ቀደም
ሲል የዐቃቤ ህግ ምስከር በመሆን ፖሊስ ላይ ምስክርነቱን የሰጠ ምስክር ክሱን በሚሰማው
ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲመሰክር ሲጠየቅ ቀድሞ ለመርማሪ ፖሊስ ከሰጠው ቃል የሚቃረን
/አንዳንድ ጊዜም አስጠቂ/ ምስክርነት የሰጠ እንደሆነ አሁን በፍርድ ቤት የተሰጠው ምስክርነት
ተዓማኒነት የሌለው መሆኑን ዐቃቤ ህግ ወይም ተከሳሽ ለማስተባበል እንዲችል በማሰብ
የተቀመጠ እንደሆነ የሚያስገነዘብ ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ ስለሆነም ፖሊስ ላይ የተሰጠ
የምስክርነት ቃል በፍርድ ቤት ተቀባይነት የሚኖረው ፍርድ ቤቱ ምስክሩ ቃሉን ቀይሮ
ምስክርነት የሰጠ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ምስክርነቱ አስጠቂ የሆነበት ወገን ምሰክርነቱን
ለማስተባበል እንዲችል እድል ለመስጠት በሚል ህግ አውጭው ያስቀመጠው ነው ሲሉ
ክርክራቸውን ያጠናክራሉ፡፡ ይህን መከራከሪያ የሚያቀርቡ ባለሙያዎች እንደሚሉት በወንጀለኛ
መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ ቁጥር 145 ስር በፍርድ ቤት የተሰጠውን ምስክርነት ማስተባበል
የሚችለው ዐቃቤ ህግ ብቻ ሳይሆን ተከሳሽም ሊያስተባብል የሚችልበት ጊዜ እንዳለ
ያስቀምጣሉ፡፡ ይሄውም የዐቃቤ ህግ ምስከር ፖሊስ ላይ የሰጠው ቃል ፍርድ ቤት ቀርቦ
ከሰጠው ቃል ጋር የሚቃረን ከሆነና ፍርድ ቤት ቀርቦ የሰጠው ቃል ተከሳሽን የሚጎዳ ወይም
ለመርማሪ ፖሊስ ከሰጠው የተለየ ከሆነ ተከሳሹ የዐቃቤ ህግ ምስክር ቀደም ሲል ለመርማሪ
ፖሊስ የሰጠው አሁን ፍርድ ቤት በመሰከረው ዓይነት አይደለም በማለት ለፍርድ ቤቱ
በማመልከት የምርመራ መዝገቡ እንዲቀርብለት እንደሚያመለክትና ፍርድ ቤቱም ልዩነት
መኖሩን ከተረዳ ተከሳሹ ምስክሩ የሰጠውን ቃል ማስተባበል እንዲችል መፍቀድ ያለበት
መሆኑን ያመለክታል በማለት ይከራካራሉ12፡፡ ይህንንም ሀሳብ የሚያጠናክሩት በአንቀጽ 145
በአርእስቱ ላይ “በፖሊስ የተሰጠ ቃል በማስረጃነት ሊቀርብ ስለመቻሉ” በሚል የተገለጸው

12
በላቸው ኪዳኑ፣በአብክመ ፍትህ ቢሮ የደብረ ብርሀን ቋሚ ምድብ ዐቃቤ ህግ ሰኔ 10፣2010 ዓ.ም፡፡ ሀብታሙ ትርፌ፣ ሰሜን ሽዋ ዞን ፍትህ
መምሪያ ዐቃቤ ህግ፣ ሰኔ 12፣2010 ዓ.ም
ጥቅል አገላለጽ ዐቃቤ ሀግም ሆነ ተከሳሽ ባመለከቱ ጊዜ ተፈጻሚ መሆኑን ያሳያል፡፡
በተጨማሪም የዚሁ ድንጋጌ 145(1) ስር “ዐቃቤ ህጉ ወይም ተከሳሹ ሲያመለክት በፖሊስ
ምርመራ ጊዜ…..” በማለት የተቀመጠው ሀሳብ ዐቃቤ ህግም ሆነ ተከሳሹ እንደአግባብነቱ
የምርመራ መዝገቡ እንዲቀርብላቸው ሲያመለክቱ ለሁለቱም እድሉ የተሰጠ መሆኑን
የሚያመለክት ነው በሚል ነው፡፡

የወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ ቁጥር 145 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በሚመለከት


በባለሙያዎች ዘንድ ከላይ የተቀመጡት ሁለት ዋና ዋና ክርክሮች የተቀመጡ ሲሆን የዚህን
ድንጋጌ ዓላማና የህግ አውጭውን ሀሳብ በሚመለከት እንደዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ እምነት ከሆነ
ድንጋጌው ተፈጻሚ የሚሆነው የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ክሱን በሚሰማው ፍርድ ቤት ቀርበው
መመስከር ሳይችሉ ሲቀሩ ሳይሆን ፍርድ ቤት ቀርበው የሰጡት ቃል ፖሊስ ላይ ቀርበው
ከመሰከሩት ጋር ሲቃረን ወይም አስጠቂ ምስክር በሆኑ ጊዜ የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም
በወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ. 145 ስር የተቀመጠውን ድንጋጌ ይዘት ስንመለከት በንኡስ ቁጥር 1 ስር
የተቀመጠው ዓረፍተ ነገር እንደሚያሳየው ለፖሊስ የተሰጠውን ቃል ፍርድ ቤቱ ሊመለከተው
ይችላል ካለ በኋላ በንኡስ ቁጥር 2 ስር ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ “…..የሰጠውን ቃል
ማስተባበል…” ይችላል በሚል ከተቀመጠው ሀሳብ መገንዘብ የሚቻለው ፍርድ ቤቱ የምስክሩን
ቃል የሚመለከተው በቀጥታ በማስረጃ በመቀበል ሳይሆን ምስክሩ ለመርማሪ የሰጠው ቃልና
በፍርድ ቤት ቀርቦ በዋና ጥያቄ ወቅት የሰጠው ቃል ልዩነት ካለው ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ
እንዲረዳ ቃሉን በመስቀለኛ ጥያቄ ለማስተባበል እንዲችል የተፈቀደ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ማለት
በአንቀጹ 145(1) ስር እንደተመለከተው ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን ተመልክቶ ፖሊስ
ላይ በተሰጠው ምስክርነትና ፍርድ ቤት በተሰጠው ምስክርነት መካከል ልዩነት ከሌለ መዝገቡን
ተመልከቶ በአንቀጹ 145(2) ስር ወደ ተመለከተው ላይሄድ እንደሚችልና ዐቃቤ ህጉ ወይም
ተከሳሹ በመስቀለኛ ጥያቄ ማስተባበል እንዳይችሉ ለማድረግ እንደሚችል ስልጣን የተሰጠው
መሆኑን ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል ከላይ እንደተመለከትነው አንዳንድ ባለሙያዎች
እንደሚሉት የአንቀጽ 145(1፣2) ዓላማ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች በበቂ ምክንያት ፍርድ ቤት
ቀርበው መመስከር ባልቻሉ ጊዜ ፖሊስ ላይ የተሰጠውን ምስክርነት በቀዳሚ ምርመራ
እንደተሰጠ ማስረጃ አድርገው ይውሰዱት ቢባል የሚቀርበው መከራከሪያ የተሳሳተና የተከሳሹን
ህገ መንግስታዊ መብት የሚጋፋ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ
መንግስት አንቀጽ 20(4) ላይ እንዲሁም በሲቭልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም ዓቃፍ ቃል ኪዳን
አንቀጽ 14(1-ሠ) ስር በግልጽ እንደተመለከተው ማንኛዉም በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች
“የቀረቡባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የማወቅና
የመጠየቅ…”መብት ያለቸው ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም ለፖሊስ የተሰጠው
የምስከርነት ቃል እንዳለ እንደ ማስረጃ ሆኖ ይወሰድ ከተባለ የተከሳሽን መስቀለኛ ጥያቄ
የመጠየቅ ህገ መንግስታዊ መብቱን ይጋፋል፤ የተሰጠውም ምስክርነት በመስቀለኛ ጥያቄ እና
በማጣሪያ ጥያቄ ተፈትኖ ያለፈ ባለመሆኑ ተዓማኒነት ሊኖረው አይችልም፡፡ በሌላ በኩል
በወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ 144 ስር የተቀመጠው በቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት የተሰጠው ቃል
ስንመለከት ምስክሩ ቃለ መሀላ ፈጽሞ የሰጠው እንዲሁም መስቀለኛ ጥያቄና ማጣሪያ ጥያቄ
የተጠየቀበት ያለቀለት ማስረጃ ስለሆነ ፍርድ ቤቱ እንዳለ ቢቀበለው የተከሳሽን መብት የማይጎዳ
ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንድ በምስክርነት የተጠራ ሰው የሚሰጠው ቃል እንደ ማስረጃ
ለመቆጠር ከሚያስፈልጉት ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ምስክሩ እውነት
ለመናገር በቃለ-መሀላ ማረጋገጥ ይኖርበታል13፡፡ በወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ 145 ስር ወደተደነገገው
ስንመጣ በፖሊስ ምርመራ ወቅት ምስክሮች ቃላቸውን ከመስጠታቸው በፊት የሚሰጡት ቃል
እውነት ስለመሆኑ ቃለ-መሀላ የሚፈጽሙበት ሁኔታ የሌለ በመሆኑ ፍርድ ቤቶች ያለ ቃለ-
መሀላ የተሰጠን የምስክርነት ቃል ሊቀበሉ የማይገባ ስለሆነ የወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ. 145 ስር ያለው
ድንጋጌ ዓላማ ለፖሊስ የተሰጠ ምስክርነት እንዳለ ይወሰድ ከተባለ ይህን መሰረታዊ የወንጀል
ስነ-ስርዓት ሂደት ከግምት ያላስገባ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በፖሊስ ጣቢያ ለመርማሪ ፖሊስ
የሚሰጥ ምስክርነት ገለልተኛ በሆነ ተቋምና በግልጽ የተሰጠ እንዲሁም እውነት ለመናገር ቃለ
መሀላ ተፈጽሞ የተሰጠ ምስክርነት ዓይደለም፡፡ በአንጻሩ በቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት
የተሰጠ ምስክርነት ዋና ጥያቄ፣ መስቀለኛ ጥያቄና ማጣሪያ ጥያቄ ተጠይቆ የምስክሩ ቃል
ተፈትኖ ያለፈ በመሆኑና ተከሳሽም በህገ መንግስትና በሌሎች ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች
የተሰጠውን ምስክሮቹን የመጠየቅ መብቱን ተጠቅሞ መስቀለኛ ጥያቄ የጠየቀ በመሆኑ
ማስረጃውን እንዳለ ፍርድ ቤቱ ቢወስደው ተዓማኒ የሆነና ተቀባይነት ያለው ማስረጃ ነው፡፡
በቀዳሚ ምርመራ ጊዜ ምስክሮቹ ዋና ጥያቄ መስቀለኛ ጥቄና ማጣሪያ ጥያቄ በመጠየቅ
የምስክርነት ቃል አሰጣጥ ስርዓቱ መደበኛ ችሎት በሚሰማበት ዓይነት የተሰጠ ምስክርነት
ስለመሆኑ በወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ. ከአንቀጽ 84-86 ካሉት ድንጋጌዎች መረዳት እንችላለን፡፡ በዚሁ
ህግ አንቀጽ 88 ላይ በቀዳሚ ምርመራ የተሰጠ ምስክርነት እንዲመዘገብ የተፈለገበት ዋናው
ምክንያት የተሰጠው ምስከርነት በአንቀጽ 147(3) መሰረት መስቀለኛ ጥያቄ እንደሚቀርብበት

13
ከላይ በግርጌ ማስታወሻ ቁጥር5፣ አንቀጽ 136(3)
ለማረጋገጥ ነው14፡፡ በዚህም ዓይነት ሂደት ውስጥ ያለፈ ማስረጃ በሌላ ፍርድ ቤት ማስረጃ ሆኖ
ሊቀርብ ቢችል ህጋዊና ስነ-ስርዓት ህጉን የጠበቀ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ለመርማሪ ፖሊስ
የተሰጠ ቃል ልክ እንደ ቀዳሚ ምርመራ ጥብቅ ስርዓቶችን አልፎ ባልመጣበት ሁኔታ የዐቃቤ
ህግ ምስክሮች ፍርድ ቤት ቀርበው መመስከር ባልቻሉ ጊዜ ለፖሊስ የሰጡትን ምስክርነት
በቀጥታ እንደ ማስረጃ መውሰድ ህግ አውጭው በወ.መ.ስ.ስ.ህ.ጉ 145 ስር ያስቀመጠውን
ዓላማ በአግባቡ ያገናዘበ ዓይደለም፤ምስክሩ ፍርድ ቤት ባልቀረበበት ሁኔታ ለመርማሪ ፖሊስ
የተሰጠው ቃል እውነትነት አጠራጣሪ ከመሆኑም በላይ የተከሳሹን ሰብዓዊና ህገ መንግስታዊ
መብት የሚነፍግ ነው15፡፡ ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን ሀሳብ በሚያጠናክር መልኩ የተሻሻለው
የጸረ ሙስና ልዩ የስነ-ስርዓትና የማስረጃ ህግ አዋጅ በአንቀጽ 44 ስር በሚከተለው መልኩ
ተደንግጎ ይገኛል16፡፡

1. በዐቃቤ ህግ ወይም በመከላከያ ምስክርነት የቀረበ ማንኛውም ሰው በምስክርነት


በተጠረጠረበት ጉዳይ እውነቱን ለመናገር ባለመፈለግ ቀድሞ ከሰጠው የምስክርነት ቃል
ጋር የሚቃረን ቃል የሰጠ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ምስክሩን ያቀረበውን ወገን መሪ ጥያቄ
እንዲጠየቅ ሊፈቅድለት ይችላል፡፡

2. ፍርድ ቤቱ መሪ ጥያቄ እንዲጠይቅ ከመፍቀዱ በፊት ተቃራኒ የምስክርነት ቃል የሰጠ


መሆኑን ምስክሩን ይጠይቀዋል፡፡ ምስክሩ ተቃራኒ የምስክርነት ቃል መስጠቱን ካመነ
መሪ ጥያቄውን ይፈቅዳል፡፡

3. ምስክሩ ተቃራኒ የምስክርነት ቃል መስጠቱን የካደ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ምስክሩ


ተቃራኒ ቃል መስት አለመስጠቱን ይወስናል፡፡

ከላይ በተገለጸው አዋጅ በአንቀጽ 44(1) ስር ከተመለከተው መረዳት እንደሚቻለው በዐቃቤ ህግ


ወይም በተከሳሹ በኩል የቀረበ ምስክር ላቀረበው ወገን አስጠቂ ምስክር በሆነ ጊዜ ምስክርነቱን
ለማስተባበል እንዲችል ፍርድ ቤቱ መሪ ጥያቄ እንዲጠይቅ ሊፈቅድ የሚችልበትን ስርዓት የያዘ
ነው፡፡ የዚሁ ድንጋጌ ንኡስ ቁጥር 2 እንደሚያመለክተው ፍርድ ቤቱ መሪ ጥያቄ እንዲጠይቅ
ከመፍቀዱ በፊት ምስክሩ ሀሰት የመሰከረ መሆን አለመሆኑን ይጠይቀዋል፤ ምስክሩ ካመነ መሪ
ጥያቄ እንዲጠይቅ ይፈቅዳል፡፡ ምስክሩ መዋሸቱን ካላመነ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ማጣራት
እንደሚያደርግ በንኡስ ቁጥር 3 ተመልክቷል፡፡ እዚህ ላይ በአጽንኦት ማየት የሚገባን ጉዳይ
14
ከላይ በግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 1፣ ገጽ 183
15
ዝኒ ከማሁ
16
የተሻሻለውየጸረ-ሙስናልዩየስነ-ስርዓትናየማስረጃህግአዋጅቁጥር 434/1997
ቢኖር ጉዳዩ የሙስና ወንጀል በሆነ ጊዜ ዓቃቤ ህግ በምርመራ ወቅት ለፖሊስ የተሰጠውን
የምስክርነት ቃል ማቅረብ ሳያስፈልገው መሪ ጥያቄ እንዲጠይቅ እንዲፈቀድለት ሊያመለክት
የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ መገንዘብ ይገባል፡፡ ከላይ ከተገለጸው የጸረ ሙስና ልዩ የስነ-ስርዓትና
የማስረጃ ህግ በተጨማሪ ረቂቅ የወንጀል ስነ-ስርዓት ህጉ በአንቀጽ 287 ስር ተመሳሳይ ይዘት
ባለው መልኩ እንደሚከተለው ተደንግጓ እናገኘዋለን፡፡

1. የዐቃቤ ህግ ምስክር በፍርድ ቤት ቀርቦ የሚሰጠው የምስክርነት ቃል በፖሊስ ምርመራ ጊዜ


ከተሰጠ የምስክርነት ቃል ጋር የሚጣረስ እንደሆነ የምስክሩን ቃል ለማስተባበል ዐቃቤ ህግ
ወይም ተከሳሹ ሲያመለክት ፍርድ ቤቱ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ሊመለከተው ይችላል፡፡
2. ፍርድ ቤቱም የዚህ ግልባጭ ለተከሳሹ እንዲደርሰው ያደርጋል በማለት ያስቀምጣል

ከላይ ከተገለጹት ሁለት አዋጆች መነሻ በማድረግ የወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ. 145 ስር የተገለጸውን


ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ ሲያደርጉና ሲተረጉሙ በምርመራ ወቅት በፖሊስ የተሰጠን
የምስክርነት ቃል እንደ ማስረጃ ቀጥታ በመቀበል ሳይሆን የዐቃቤህግ ምስክር ቀድሞ ከሰተው
ቃል ጋር የሚጋጭ ምስክርነት በሰጠ ጊዜ ይህንኑ ለማስተባበል መሪ ጥያቄ እንዲጠይቅ እድል
ለመስጠት መሆን ይገባዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉትና በተግባርም
እንደሚሰራው የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ፍርድ ቤት መቅረብ ባልቻሉ ጊዜ ዓቃቤ ህግ የምርመራ
መዝገቡን በማቅረብ ቀደም ሲል ለፖሊስ የተሰጠው ምስክርነት ፍርድ ቤቱ እንዲይዝልን
በማለት የሚያቀርበው አቤቱታና አንዳንድ ዳኖችም ይህንኑ ተቀብለው የሚሰሩበት አግባብ ከስነ-
ስርዓት ህጉ ፍላጎት ጋር የማይጣጣም ስለሆነና ለፍትህ አስተዳደርም ስለማይረዳ ሊታረም
የሚገባው ነው፡፡ በተጨማሪ በወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ 145(1፣2) ስር ያለው ተፈጻሚ መሆን ያለበት
የዐቃቤ ህግ ምስክሮች አስጠቂ ሲሆኑ ብቻ ሳይሆን ተከሳሽም የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ፖሊስ ላይ
ከሰጡት ቃል ጋር የሚቃረን ቃል ሰጥተዋል ብሎ ሲያምን የምርመራ መዝገቡ እንዲቀርብለት
ሊያመለክት ይችላል፤ ፍርድ ቤቱም መፍቀድ እንደሚገባው ከላይ በተጠቀሱት የጸረ ሙስና ልዩ
የስነ-ስርዓት ህግ፣ ከረቂቅ ስነ-ስርዓት ህጉና ከወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ ድንጋጌዎች
መገንዘብ ይገባል፡፡
3. በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ያለው ተግባራዊ አሰራር

በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባሉ የቀጥታም ሆነ የይግባኝ
ክርክሮች ላይ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ ቁጥር 145 ስር የተደነገገውን ድንጋጌ
ተፈጻሚ በማድረግ በኩል ወጥ የሆነ አሰራር አይታይም17፡፡ በዚህም የተነሳ ለመርማሪ ፖሊስ
የተሰጠን ምስክርነት እንደማስረጃ የሚወሰደው በምን ሀኔታ ነው የሚለውን ጉዳይ በሚመለከት
የተለያዬ አሰራር እንዳለ ባለሙያዎችም ይገልጻሉ፤ መዛግብትም ይጠቁማሉ፡፡ በክልሉ በብዙ
ፍርድ ቤቶች ወይም ችሎቶች በወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ. 145 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በሚመለከት
ፍርድ ቤቶች ለፖሊስ የተሰጠን የምስክር ቃል የሚመለከቱትና እንደ ማስረጃ የሚወስዱት
የዐቃቤ ህግ ምስክር/ሮች/ በቂ ተብሎ በሚገመት ምክንያት ማለትም ምስክሩ በህይወት ከሌለ፣
በከፍተኛ የጤና ችግር ምክንያት ምስክርነቱን መስጠት ካልቻለ፣ ምስክሩ ከሀገር ከወጣ ወይም
ምስክሩ በአድራሻው ሊገኝ ካልቻለ ዐቃቤ ህግ ምስክሩ ቀደም ሲል ለፖሊስ የሰጠው ቃል እንደ
ማስረጃ ይያዝልን በማለት ያመለክታል፤ ፍርድ ቤትም ይህንኑ በመቀበል ፖሊስ ላይ ምስክሩ
የሰጠውን የምስክርነት ቃል ኮፒ ተደርጎ ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝ ካደረገ በኋላ ማስረጃ ሚዛን
ውስጥ በማስገባት ውሳኔ ሲሰጥ በስፋት ይታያል18፡፡ ይህንን ሀሳብ በሚደግፍ መልኩ የተወሰኑ
ውሳኔዎችም እንዳሉ መዛግብት ያሳሉ፡፡ ለምሳሌ በከሳሽ የሰሜን ሽዋ ዞን ዓቃቤ ህግ በተከሳሽ
ንጉስ ተክለዮሀንስ መካከል በነበረው ከባድ ሰው መግደል ወንጀል የዓይን ምስክር የነበረው
ግለሰብ በሞት በመለየቱ ምክንያት ዐቃቤ ህግ ምስክሩ ፖሊስ ላይ የሰጠው ቃል እንዲያዝለት
ባመለከተው መሰረት ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ላይ የተሰጠውን ቃል ኮፒ ተደርጎ ከመዝገቡ ጋር
እንዲያያዝ አድርጎ ተከሳሽን ጥፋተኛ ለማለት ፖሊስ ላይ የተሰጠው ምስክርነት የማስረጃ ሚዛን
ውስጥ በማስገባት ፍርድ ቤቱ እንደተጠቀመበት የፍርድ ቤቱ መዝገብ ያለመክታል19፡፡ እዚህ
ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ ምስክሩ ፖሊስ ላይ ቀርቦ የሰጠውን ቃል ከሌሎች የሰው
ምስክሮች ቃል ጋር በማጣመር ፍርድ ቤቱ ሲመዝን የማስረጃውን ክብደትና የማስረዳት አቅም
በተመለከተ ፍርድ ቤቱ እንደየሁኔታው የሚመዝነው መሆኑ ግምት ውስጥ ሊገባ የሚገባው
ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በከሳሽ የሰሜን ሽዋ ዞን ዐቃቤ ህግ በተከሳሽ እነ አይደፈር

17
ፍቃዱ አንዳርጌ፣ የሰሜን ሽዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ፣ሰኔ 12/2010 ዓ.ም የተደረገ ቃለ መጠይቅ
18
ሀብታሙ በቃሉና በላቸው ኪዳኑ፣ በአብክመ ፍትህ ቢሮ የክልል ዐቃቤ ህግ ጋር በተደረገ ውይይት በክልሉ ውስጥ በተለያዩ

ዞኖችና ወረዳዎች በሰሩበት አጋጣሚ በጽሁፉ ላይ በተቀመጠው ዓይነት እንደሚሰራ ይጠቁማሉ ቃለ መጠይቁ የተደረገው ሰኔ

10/2010 ዓ.ም
19
የሰሜን ሸዋ ዞን ከ/ፍ/ቤት የወ/መ/ዝ/ቁ. 02-40140 ይመልከቱ፡፡
መታፈሪያ20 መካከል በነበረው ክርክር እንደተመለከተው ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹን አሰምቶ ከጨረሰ
በኋላ ለፍርድ ቤቱ አስተያየት አቅርቧል፡፡ ይሄውም ሁለተኛና ሶስተኛ የአቃቤ ህግ ምስክሮች
ፖሊስ ላይ የሰጡትን ምስክርነት ቀይረው የሰጡ ስለሆነ ምርመራውን ላጣራው ፖሊስ የሰጡት
ቃል ይያዝልኝ በማለት አሳስቧል፡፡ በዐቃቤ ህግ አስተያየት ላይ መልስ እንዲሰጥ የተጠየቀው
የተከሳሽ ጠበቃ እንደገለጸው ምስክሮች ለፖሊስ የሰጡት ቃል ለፍርድ ቤት ሊቀርብ የሚችለው
ምስክሩ ከሞተ፣ ከአገር ከወጣ ወይም በማንቻውም ሁኔታ ችሎት ቀርቦ መመስከር ካልቻለ
እንጂ ምስክሩ ቀርቦ በመሰከረበት ሁኔታ ፖለስ ላይ የሰጠው ቃል ይቅረብልኝ በማለት የቀረበው
አስተያየት የስነ-ስርዓት ህጉን ዓላማ ያልተከተለ ስለሆነ ውድቅ ሊደረግ ይገባል በሚል
ተከራክሯል፡፡ ፍርድ ቤቱም በቀረበው የግራ ቀኙ ክርክር ላይ ብይን ሳይሰጥ በዝምታ
እንዳለፈው የፍርድ ቤቱ መዝገብ ያመለክታል፡፡

በሌላ በኩል አንዳንድ ፍርድ ቤቶች ወይም ችሎቶች የዓቃቤ ህግ ምስክር መቅረብ ስላልቻለ
ምስክሩ ፖሊስ ላይ የሰጠውን ቃል ይያዝልን በሚል ዐቃቤ ህግ የሚያቀርበውን ክርክር ሲቀበሉ
አይታይም፡፡ ለምሳሌ በከሳሽ የመርሀቤቴ ወረዳ ዐቃቤ ህግ በተከሳሽ ባዩ ጌታቸው መካከል
በነበረው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክርክር የግል ተበዳይ የነበረችው የዓይን ምስክር
በአድራሽዋ ልትገኝ ባለመቻሏና ፍርድ ቤት ቀርባ ባለመመስከሯ ዐቃቤ ህግ ለችሎቱ ለፖሊስ
የሰጠችው ቃል እንዲያዝለት ቢያመለክትም በመጀመሪያ ደረጃ ጉዳዩን ሲመለከት የነበረው
የወረዳው ፍርድ ቤትም ሆነ ክርክሩን በይግባኝ የተመለከተው የሰሜን ሽዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ
ቤትና የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ክርክሩን ሳይቀበሉት ቀርተው
ተከሳሽ በነጻ እንደተሰናበተ መዝገቦቹ ያመለክታሉ21፡፡

ከላይ ከተመለከተው በተጨማሪ በአማራ ክልል ባሉ አንዳንድ ፍርድ ቤቶች በወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ


145 ስር የተቀመጠውን ድንጋጌ ተፈጻሚ የሚያደርጉት የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ለመርማሪ
ፖሊስ የሰጡትን ቃል ጉዳዩን በሚያየው ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው ከመሰከሩት ቃል ጋር
የሚቃረን ሲሆን ዐቃቤ ህግ ለመርማሪ ፖሊስ የሰጡት ቃል የምርመራ መዝገቡ ይያዝልኝ
በማለት ያመለክታል፤ ፍርድ ቤቱም ይህንን ተቀብሎ የምርመራ መዝገቡ እንዲቀርብ በማድረግ
ማስረጃወን በመቀበል ከማስረጃ ሚዛን ውስጥ በማስገባት ውሳኔ እንደሚሰጥ ባለሙያዎች

20
የሰ/ሽ/ዞን ከ/ፍ/ቤት የወ/መ/ዝ/ቁ. 02-41118 ይመልከቱ
21
የሰሜን ሽዋ ዞን ፍትህ/መ/የወ/ይ/መዝ.ቁ. 20/2010፣ የሰ/ሽ/ዞ/ከ/ፍ/ቤት የወ/መዝ.ቁ 02-16151
ይጠቁማሉ22፡፡ ይህ የባለሙያዎቹ አስተያየትም በክርክሮች (በመዛግብት) ላይ ተፈጻሚ ሲሆን
ይታያል፡፡ ለምሳሌ በከሳሽ ዐቃቤ ህግ በተከሳሽ ወርቅዬ ዘገዬ መካከል በነበረው የውንብድና
ወንጀል የዓቃቤ ህግ ምስክር በሀሰት በመመስከሩ ቀደም ሲል ምስክሩ ለፖሊስ የሰጠው ቃል
እንዲያያዝ ተደርጎ ውሳኔ የተሰጠ መሆኑን የፍርድ ቤቱ መዝገብ ያመለክታል23፡፡ እዚህ ላይ
ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ነጥብ ዐቃቤ ህግ ምስክሬ አስጠቂ ስለሆነብኝ ለመርማሪ ፖሊስ
የሰጠው ቃል ይያዝልኝ በማለት ሲያመለክት ፍርድ ቤቱም የምርመራ መዝገቡን ካስቀረበ በኋላ
አስጠቂ ምስክር ተመስክሮብኛል ያለው ዐቃቤ ህግ መስቀለኛ ጥያቄ ወይም መሪ ጥያቄ
እንዲጠይቅ በማድረግ አስጠቂ የሆነበትን ምስክርነት እንዲያስተባብል ማድረግ ሲገባው ፍርድ
ቤቱ ከምርመራ መዝገቡ ላይ የምስክሩ ቃል ኮፒ ተደርጎ ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝ በማድረግ
ውሳኔ ሲሰጥ ይታያል፡፡ ይህም ከድንጋጌው ዓላማና ሀሳብ ውጭ ነው፡፡ የድንጋጌው ዓላማ
አስጠቂ ምስክር ሲሰጥ ወይም ተከሳሽ የዐቃቤ ህግ ምስክር ፖሊስ ላይ ከሰጠው ቃል ጋር
በሚቃረን መልኩ በፍርድ ቤት መሰከረብኝ በማለት ሲያመለክት በፍርድ ቤት የተሰጠውን ቃል
ለማስተባበል ዐቃቤ ህግ ወይም ተከሳሽ መስቀለኛ ወይም መሪ ጥያቄ እንዲጠይቅ በማሰብ
የተደነገገ ድንጋጌ ነው፡፡ በሌላ በኩል የዐቃቤ ህግ ምስክሮች በፍርድ ቤት ቀርበው ሲመሰክሩ
ሀሰት ስለመሰከሩ ቀደም ሲል ለፖሊስ የሰጡት ቃል ይታይልን በማለት ዐቃቤ ህግ
የሚያቀርበውን መከራካሪያ የማይቀበሉ ችሎቶችም እንዳሉ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ በከሳሽ
የሰሜን ሽዋ ዞን ፍትህ መምሪያ በተከሳሽ መኮንን በላቸው መካከል በነበረው የሰው መግደል
ወንጀል የወንጀሉን ፈጻሚ በቀጥታ አይቻለሁ በማለት የዓይን ምስክር ሆና የቀረበችው ግለሰብ
ጉዳዩን በሚመለከተው ፍርድ ቤት ቀርባ ስትመሰክር አላየሁም በማለት ቃሏን ቀይራ
የመሰከረች በመሆኑ ዐቃቤ ህግ ለፖሊስ የሰጠችው ምስክርነት ይታይልኝ በማለት አቤቱታ
አቅርቦ ገዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ ሰልጣኑ ሲመለከት የቆየው የሰሜን ሽዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ
ቤት ሳይቀበለው ቀርቷል24፡፡ በዚሁ ብይን ቅር በመሰኘትና ተከሳሽም ነጻ በመሰናበቱ አግባብ
አይደለም በማለት ይግባኙን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደብረ ብርሀን ቋሚ ችሎት አቅርቦ
የክልሉ ዐቃቤ ህግም የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዐቃቤ ህግ ምስክር የነበረችው ለፖሊስ
የሰጠችውን ቃል በመቀየሯ ምክንያት ዐቃቤ ህግ ምስክሯ ለፖሊስ የሰጠችው ቃል ፍርድ ቤቱ

22
ፍቃዱ አንዳርጌ፣ የሰሜን ሽዋዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ጋር ሀምሌ 2፣ 2010 ዓ.ም የተደረገ ቃለ መጠይቅ እንዲሁም
ከሀብታሙ አዲስ፣ የምእራብ ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ የባህር ዳር ክላስተር ምድብ የወንጀል የስራ ሂደት አስተባባሪ፣ ሰኔ 15
2010 ዓ.ም የተደረገ ቃለ መጠይቅ
23
የሰ/ሽ/ዞ/ከ/ፍ/ቤት የወ/መዘ/ቁ. 02-39159 ከሳሽ ዐቃቤ ህግ ተከሳሽ ወርቅ ዘገዬ
24
የሰሜን ሽዋ ዞን ከ/ፍ/ቤት የወ/መዝ.ቁ 0236732
ይመልከትልኝ በማለት የተከራከረ ቢሆንም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ የቀረበውን
ይግባኝ አልተቀበለውም25፡፡ በሌላ በኩል አንዳንድ ጊዜ ተከሳሽ የዐቃቤ ህግ ምስክር የመሰከረው
አላግባብ ነው ፖሊስ ላይ የሰጠው ምስክርነት አሁን ፍርድ ቤት በሰጠው ዓይነት አይደለም
በማለት ሲያመለክት የምርመራ መዝገቡን ፍርድ ቤት አስቀርቦ የሚመለከትበት ጊዜም እንዳለ
ይታያል26፡፡

የወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ. 145 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በሚመለከት የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎተ27


በአመልካች የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዓቃቤ ህግ በተጠሪ
ሀብታሙ ካርሎ መካከል በነበረው ክርክር ተጠሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2-ሐ) ስር
የተመለከተውን በመተላለፍ በፈጸመው የድብደባ ወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ አቅርቦ ሲከራከር
ቀደም ሲል ወንጀሉ ሲፈጸም አይተናል በማለት የመሰከሩ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ሀሰት
በመመስከራቸው የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ለፖሊስ የሰጡት ቃል ይያዝልኝ በማለት ዐቃቤ ህግ
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ ለተመለከተው ፍርድ ቤትም ሆነ በየደረጃው ላሉ ለክልሉ የይግባኝና
የሰበር ሰሚ ችሎቶች አቅርቦ አቤቱታው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ዐቃቤ ህግም የሰበር
አቤቱታውን ለፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበ ሲሆን የአቤቱታው መነሻም የዐቃቤ ህግ
ምስክሮች ፖሊስ ላይ የሰጡትን ቃል ፍርድ ቤት ላይ በመቀየራቸው በወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ 145
መሰረት ለፖሊስ የሰጡት ቃል ይያዝልኝ በማለት ባስስብም ፍርድ ቤቶቹ አልተቀበሉኝም
ይህም መሰረታዊ የህግ ስህተት ነው የሚል ነው፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱም አቤቱታው ያስቀርባል
ካራከረ በኋላ በወንጀል ክርክር ወቅት በተከራካሪ ወገኖችም ሆነ በፍርድ ቤት ምስክሮች
የሚጠየቁት ጥያቄዎች አይነታቸው የትኞቹ እንደሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ
ቁጥር 137፣ 138 እና 140 ስር የተመለከተ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ግልጽ ያልሆኑ
ነጥቦችን ለማጣራት በዚሁ ህግ በአንቀጽ 136(4) እና 143(1) ስር የተመለከቱትን ድንጋጌዎች
አስታውሷል፡፡ በተመሳሳይ በወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ. 145 መሰረት ዓቃቤ ህጉ ወይም ተከሳሹ
ሲያመለክቱ ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ የተሰጠውን ቃል ሊመለከተው እንደሚችል ህጉ ቢያመለክትም
የዚህ ድንጋጌ መሰረታዊ ዓላማ በምርመራ ጊዜ የተሰጠውን ቃል በፍርድ ቤት ምስክሩ ቀርቦ
ቢለውጠው ይሄው ምስክርነት እንዲቃናና ፍርድ ቤት ለያዘው ክስ ሁልጊዜ ክብደት እንዲሰጠው
ለማድረግ ነው ተብሎ አይታሰብም በሚል የውሳኔ ሀተታውን ደምድሞ የቀረበው አቤቱታ

25
የአብከመ ፍትህ ቢሮ የወ.መዝ.ቁ. 21/2008፣የአብክመ ጠ/ፍ/ቤት የወ/ይ/መዝ.ቁ 02-16806፣
26
በላቸው ኪዳኑ፣ በአብክመ ፍትህ ቢሮ የደብረ ብርሀን ቋሚ ምድብ ዐቃቤ ህግ ሰኔ 11፣2010 ዓ.ም
27
የፌደራል ሰበር ሰሚችሎት የወ/መ/ ቁ. 111498 ቅጽ 9 ይመልከቱ
ተገቢ እንዳልሆነና የስር ፍርድ ቤቶች መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት እንዳልፈጸሙ በመወሰን
የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ አጽንቷል፡፡ እዚህ ላይ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በዝምታ
ያለፈውና በአግባቡ ሊመለከተው ይገባ የነበረው ጉዳይ ይህ ድንጋጌ አከራካሪ እንደመሆኑ መጠን
ሰበር ሰሚ ችሎቱ ለትርጉም ክፍትና እስካሁን ድረስ ገዢ የሆነ ትርጉም ያላገኘ በመሆኑ ሰበር
ሰሚ ችሎቱ ከተቋቋመለት ወጥ የሆነ የህግ አተረጓጎም እንዲኖር የማድረግ ዓላማ መሰረት
በወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ 145 ስር የተቀመጠው ለፖሊስ የተሰጠ ምስክርነትን ፍርድ ቤት
የሚመለከተው ለምን ዓላማና እንዴት ነው የሚለውን ትርጉም ሰጥቶበት ማለፍ ይገባው ነበር፡፡
አሁንም ቢሆን የዚህን ድንጋጌ አተረጓጎም በሚመለከት በባለሙያው ዘንድ ወጥ የሆነ አቋም
የማይታይና ብዥታ ያለበት በመሆኑ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በህግ የተጣለበትን ሀላፊነት በመወጣት
ወደፊት በድንጋጌው ላይ ተገቢ የሆነ ትርጉም በመስጠት ገዢ የሆነ ውሳኔ ቢሰጥ በበታች
ፍርድ ቤቶች የሚታየውን የተለያዬ አረዳድና አተረጓጎም ለማስቀረት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

4. ማጠቃለያ

በወ.መ.ስ.ስ.ህ.ቁ.145 (1፣2) ስር የተቀመጠውን ድንጋጌ በሚመለከት በባለሙያዎች ዘንድ


ሁለት ዓይነት ግንዛቤ እንዳለና በተግባርም ወጥ የሆነ አሰራር እንደሌለ ለመረዳት ይቻላል፡፡
አንዳንድ ባለሙያዎች ድንጋጌውን የሚረዱትና ተግባራዊ የሚያደርጉት የዓቃቤ ህግ ምስክሮች
በቂ በሚባል ምክንያት ፍርድ ቤት ቀርበው መመስከር ባልቻሉ ጊዜ ቀደም ሲል ለመርማሪ
ፖሊስ የሰጡት ቃል ሊያዝ ይገባል በሚል ዓቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ ያሳስባልም ፍርድ ቤቶችም
ይህንኑ ተቀብለው ማስረጃው ኮፒ ተደርጎ ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝ በማድረግ በማስረጃ ምዘና
ውስጥ በማስገባት ውሳኔ ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ በሌላ በኩል በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ
ቁጥር 145 ስር የተመለከተውን ለፖሊስ የተሰጠ ምስክርነት በፍርድ ቤት ተቀባይነት
የሚኖረው የቃቤ ህግ ምስክሮች ፍርድ ቤት ቀርበው ሲመሰክሩ ቀድመው ከሰጡት ቃል ጋር
የሚቃረን ሲሆን ይህንኑ ለማስተባበል ሲባል ዐቃቤ ህጉ ወይም ተከሳሹ ሲያመለክቱ ለመርማሪ
ፖሊስ የተሰጠውን ምስክርነት ፍርድ ቤቱ ሊመለከተው እንደሚችል ዓላማውም፣ ፍርድ ቤት
ላይ የተሰጠውን ምስክርነት ተዓማኒነት የሌለው ለማድረግ ነው፡፡ ማለትም ፖሊስ በምርመራ
ወቅት የተሰጠ የምስክርነት ቃል በፍርድ ቤት ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባው የዐቃቤ ህግ
ምስክር በመሆን የቀረበው ምስክር ለዐቃቤ ህግ አስጠቂ ሲሆንበት ፍርድ ቤቱን በማስፈቀድ
መስቀለኛ ወይም መሪ ጥያቄ በመጠየቅ በፍርድ ቤት ቀርቦ የሰጠው ቃል ተዓማኒ እንዳልሆነ
በማሳየት ምስክርነቱን ለማስተባበል እንዲችል ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ፍርድ
ቤት ቀርበው ባልመሰከሩበት ሁኔታ ለፖሊስ የሰጡት ቃል ይያዝልን በማለት ዐቃቤ ህግ
የሚሰጠው አስተያየትና አንዳንድ ፍርድ ቤቶች ወይም ችሎቶችም በዚሁ መንገድ ፖሊስ ላይ
የተሰጠው ቃል ኮፒ እንዲደረግና ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝ ተደርጎ የሚሰራበት አግባብ ተገቢ
ያልሆነነና የድንጋጌውን ዓላማ ያልተከተለ ስለሆነ ሊታረም የሚገባው ነው፡፡ የድንጋጌውን ዓላማ
በአግባቡ ለመረዳት የጸረ ሙስና ልዩ የስነ-ስርዓትና የማስረጃ ህግ እንዲሁም ረቂቅ የስነ-ስርዓት
ህጉ ላይ የተቀመጡትን ተመሳሳይ ድንጋጌዎች ከወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ ድንጋጌ ጋር
አጣምሮ መመልከትና መረዳትም ይገባል፡፡ ይህም ማለት ምስክሩ ፍርድ ቤት ቀርቦ
ባልመሰከረበት ሁኔታ ለመርማሪ ፖሊስ የሰጠውን ቃል በቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት
እንደተሰጠ ምስክርነት በማስረጃነት ለመቀበል የሚቀርቡ ሁኔታዎች ተከሳሹ በሌለበት፣
በምስክርነት የቀረበበትን ምስክር የመጠየቅ ህገ መንግስታዊ መብቱ ባልተከበረበት እና
ምስክሮቹ ቃለ-መሀላ ባልፈጸሙበት ሁኔታ በፖሊስ ምርመራ ወቅት የተሰጠ የምስክርነት ቃል
እንደ ማስረጃ በመውሰድ ከማስረጃ ምዘና ውስጥ አስገብቶ ውሳኔ መስጠት ስህተት ነው፡፡
ስለሆነም በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ ቁጥር 145 ስር የተመለከተው ድንጋጌ ተፈጻሚ
መሆን ያለበትና ሊተረጎም የሚገባው የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ፍርድ ቤት ቀርበው ከመሰከሩ
በኋላ አስጠቂ ከሆኑ ዐቃቤ ህጉ ወይም ተከሳሹ የተሰጠውን ምስከርነት ለማስተባበል በመስቀለኛ
ጥያቄ ወይም በመሪ ጥያቄ አማካኝነት የሚያስተባብሉበት ስርዓት ለመፍጠር በማሰብ የተቀረጸ
ድንጋጌ እንደሆነ ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ጠቃሚ ነው፡፡

You might also like