Download as doc, pdf, or txt
Download as doc, pdf, or txt
You are on page 1of 3

"በበጎ ሥራ በመፅናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ህይወት ለሚፈልጉ የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል።"

ሮሜ 2፥7

ክርስትና ሕይወት ውስጥ ካሉ አጣብቂኞች መካከል ዋነኛው የሚከተለው ነው። ድኅነት ለሌሎች መትረፍ አለበት። ቅዱስ
ዮሐንስ አፈወርቅ ለሌሎች መዳን ያልሆነ ድኅነት ዋጋ የለውም እንዳለው ነው። የጌታ ወንድም የተባለ ያዕቆብ
በመልዕክቱ ምዕራፍ አምስት ቁጥር ሃያ ላይ ተመሳሳይ መልዕክት አስቀምጦልናል።

"ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ።"

ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ታሪኮችን እንመልከት። ቅዱስ ጴጥሮስ በምሴተ ሐሙስ ላይ"ጌታ ሆይ ሁሉ አሳሎፈው ቢሰጡህ
እንኳ እኔ አሳልፌ አልሰጥህም" በማለት በተናገረ ጊዜ ክርስቶስ "እውነት እልሃለሁ ዶሮ ሁለቴ ሳይጮህ ሦስቴ
ትክደኛለሁ።" በማለት መለሰለት። በሆነ መልኩ ቅጣት ነው። የሐዋርያት አለቃ የተባለ ቅዱስ ጴጥሮስ የሰራው ስህተት
ሁለት ነው። አንደኛ ሁሉን ነገር በራሱ ላይ መጣሉ እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ መጠየቅ መርሳቱ ነው። በኋላ በባሕረ
ጥብርያዶስ ይህንን ስህተቱን አርሞታል። ክርስቶስ ሦስት ጊዜ እንደካደው ሊያስታውሰው ሦስት ጊዜ መላልሶ የዮና ልጅ
ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን? ብሎ ሲጠይቀው እንደድሮው 'እንዴታ ጌታ ሆይ! እወድሃለሁ' ብሎ ሙሉ ለሙሉ በራሱ ላይ
በመተማመን ፈንታ 'ጌታ ሆይ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ' ብሎ ይመልስለታል። ቅዱስ ጴጥሮስ ሁለተኛው የምሴተ
ሐሙስ ስህተቱ ራሱን ከሐዋርያቱ መለየቱ ነው። ክርስትና ውስጥ እኔ ብቻ የሚባል ነገር አይሰራም። ከሐዋርያት
መጠራት ጀምሮ ያየነው እርሱን ነው። ክርስቶስን ከቅዱስ ዮሐንስ ተከታዮች መካከል የተከተሉት የመጀመርያዎቹ
ደቀመዛሙርት እኔ ብቻ ልዳን አላሉም። ቅዱስ እንድርያስ ታላቅ ወንድሙን ቅዱስ ጴጥሮስን ሲጠራ ታናሹ ቅዱስ
ዮሐንስ ደግሞ ቅዱስ ያዕቆብን ጠሮቶታል። ያልተማረው ቅዱስ ፊልጶስ ምሑረ ኦሪት የሆነውን ቅዱስ ናትናኤልን
የጠራው ለዚህ ነው። ያገኘውን ድኅነት ለራሱ ብቻ ሊያስቀር አልፈለገም። ተከራክሮ የሚያሳምንበት ዕውቀት
ባይኖረውም ባልንጀራው ቅዱስ ናትናኤልን ናና እይ ብሎ ጠራው። ከክርስትና መነሻ ጀምሮ ይኼ ለድኅነት የመጠራራትና
የመሳሳብ ጉዳይ ነበር። ሐዋርያዊ ሕይወት የሚባለውም ይኼ ነው። ሁሉ በአንድነት የሚኖሩበት፣ የሰሩትን ሁሉ
አምጠው ለሕብረቱ የሚሰጡበትና በአንድነት የሚመገቡበት ሕይወት ማለት ነው። ይህ ሕይወት ነው በኋላ ዘመን
ብዙዎችን ወደክርስትና የሳባቸው። አስቀድሞ ቅዱስ ዳዊት በትንቢት መነጽር "ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም ሶበ ይኄልዉ
አኃው ኅቡረ፤ ወንድሞች በአንድነት ቢቀመጡ እንዴት መልካም እንዴትስ ያማረ ነው።" ያለው ስለዚህ ክርስትያናዊ
ሕብረት ነው። ሐዋርያቱንም በየአሕጉራቱ እየዞሩ ለመስበክ ያነሳሳቸው ይኼ ድኅነትን የማካፈል ፍላጎት ነበር። ቆይቶ
ይሆ ሐዋርያዊ ሕይወት በመነኮሳስ የማኅበር ኑሮ እስከ ዘመናችን ድረስ ቀጥሏል። በገድለ ቅዱስ ዞሲማስ ላይ
እንደተጠቀሰው በብሔረ ብጹዓን ውስጥ ያሉ ቅዱሳንም ኑሯቸው እንዲህ ያለ ሐዋርያዊ ነበር።

ቅዱስ ጴጥሮስ ራሱን ከሐዋርያቱ ነጥሎ ሁሉ ቢክዱህ እኔ አልክድህም ማለቱ ይህን ሐዋርያዊ ሕይወት አንድነት የሚጥስ
ነበር። በዚህም ምክንያት ክርስቶስ ሊያስተምረው ስለፈለገ ዶሮ ሳይጮህ ሦስቴ እንደሚክደው ነገረው። በካደውም ጊዜ
የንስሐ እንባን አለቀሰ። በከባዱ መንገድ ተማረ። በኋላ በባሕረ ጥብርያዶስ ላይ ጌታ እንዴት ባለ ሞት እግዚአብሔርን
እንደሚያከብረው ሲነግረው የራሱን መጨረሻ ብቻ ጠይቆ አልቆመም። ዞሮ ከጀርባው ቆሞ ስለነበረው ስለ ቅዱስ
ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ይጠይቃል። "ይህስ እንዴት ይሆናል?" ብሎ። እኔ ብቻ ከሚል አስተሳሰብ መላቀቁን የምናውቀው
በዚህ ነው።

እንዲህ ባለ ደስ የሚያሰኝ ኅብረት ውስጥ ግን ሁልጊዜ መሰናክል አይጠፋም። ለምሳሌ በመጀመርያው የሐዋርያት ኅብረት
ውስጥ ከአሕዛብነት ወደክርስትና በመጡትና ከአይሁድ ወደክርስትና በመጡት መካከል በፉክክር መንፈስ የተነሳ ጥል ነበር።
ከአይሁድ ወደ ክርስትና የመጡት ከአረማዊነት ወደክርስትና የመጡት እንደኛ ሸሆናው ክፍት የሆነ እና የሚያመሰኳ ነው
መብላት ያለባቸው ሲሉ ከአረማዊነት ወደክርስትና የመጡት ደግሞ እንደሙሴ ኦሪት ያለ ሕግ ስላልነበራቸው ያገኙትን
ቢያመሰኳም ባያመሰኳም፤ ሸሆናው ክፍት ቢሆንም ባይሆንም አንዳንዴም እንደባህላቸው የሞተ ጭምር ይመገቡ ነበር።
በዚህ ምክንያት የተነሳው ግርግር በመጀመርያው የሲኖዶስ ስብሰባ እልባት ቢያገኝም ጦሱ ግን በኋላ በቢጽ ሐሳውያን
በኩል ለቤተክርስትያን ፈተና ሆኖ ቆይቷል። ቢጽ ሐሳውያን ይህን በክርስትያኖች መካከል ያለውን መቃቃር ቀመጠቀም
ምንፍቅናቸውን አስፋፍተዋል። ከአይሁድ የመጡት ክርስትያኖች ከአሕዛብነት የመጡት እንደእኛ መገረዝ አለባቸው ይሉ
ስለ ነበረ ይህንን ተጠቅመው ጥምቀት ያለ ግዝረት፣ ወንጌል ያለ ኦሪት አትረባም የሚል ምንፍቅና አመጡ። ቅዱስ
ጳውሎስም በተያየ ጊዜ እንደሮሜ መልዕክት፣ እና እንደዕብራውያን መልዕክት ያሉ ደብዳቤዎችን በመጻፍ ይህንን ቀውስ
ለማስታገስ ሞክሯል።

መነሻ ያደረግነው ጥቅስ የሚገኘው በሮሜ መልዕክት ላይ ነው። በመልዕክቱ ላይ ከአይሁድ ወደክርስትና የመጡት
ምዕመናን ከአረማዊነት የመጡት ላይ ትችታቸው ስለበረታ በሌሎች ላይ ከመፍረዳቸው በፊት መጀመርያ ራሳቸውን
እንዲመለከቱ ያስተምራቸዋል። ይኼ አስቀድሞ ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት ነው።

"እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል።


በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? ወይም
ወንድምህን። ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፥ በዓይንህ ምሰሶ አለ። አንተ ግብዝ፥
አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።"

ማቴ 7÷1-5

ቅዱስ ጳውሎስም የሚያነሳው ይህንኑ የ'እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ' ትምህርት ነው። ገና ሲጀምር እንዲህ ይላል።

" ስለዚህ፥ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፥ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን
ትኰንናለህና፤ አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና።" ሮሜ 2:1

ወረድ ብሎም እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንደማያዳላና ለአይሁዱም ለግሪካዊውም(ለአረሚው) ለሁሉም እንደየሥራው


እንደሚሰጠው ይገልጻል።

በሰንበት ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ውስጥ የሚታየው ትልቁ ችግር ይኼ ነው። በተለይ ከውጪ ሆኖ ለሚያይ ሰው
የሰንበት ተማሪዎች የመጥፋት ምክንያት እየሆኑ ነው። እንዳጠቃላይ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በሙሉ በተለይ
በአትሮንስ የሚታይ አገልግሎት ላይ ያሉ ካህናት፣ መምህራን፣ ዘማርያን ወዘተ መረዳት ያለባቸው ጉዳይ የሚያያቸው
ብዙ ሰው እንዳለ ነው። ስለዚህ የነርሱ አለመጾም ለብዙ ሰዎች ላለመጾም ሰበብ ይሰጣቸዋል። የነርሱ የተበላሸ መግባር
ለሌሎች ምግባር መበላሸት ሰበብ ሊሆን ይችላል። ሲወድቁ ብቻቸውን አይወድቁም። አብረዋቸው የሚወድቁ ብዙ
ናቸው።

ለምዕመናኑ ደግሞ ይህ ጉዳይ ተገቢ እንዳልሆነ ማሳየት አለብን። ግለሰብን የሚከተሉ አንዱን አጥማቂ ወይ ሰባኪ ወይ
ዘማሪ የሚከተሉ ሰዎች በዝተዋል። በመንና አስተሳሰብ አድርጉ የተባሉትን ከቤተክርስቲያን እና ከክርስትና አንጻር
ሳያስተውሉ ያደርጋሉ። ይሄ ብዙ ጥፋት ባለፉት ዓመታት ከማስከተሉም አልፎ በመናፍቃኑ ዘንድ ቤተክርስትያንን
ማብጠልጠያ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል። ይህን የሰጠናቸው እኛ ነን። ቤተክርስቲያንን የምናሰድባት እኛ ነን። ከዚህ መቆጠብ
አለብን።

ስም ያላቸውን ሰባኪዎች እንዲሁ በጅምላ የሚከተሉ የአፍ ክርስትያኖች ሌሎች ጥሩ ሰባክያን ደገኛ ትምህርት
ሲያስተምሩ 'አሁን እርሱ ራሱ የሚያደርገው አይመስልም?' የሚል የንቀት መንፈስ ይሞላቸዋል። በየአውደ ምህረቱ
የሚያስተምር እግዚአብሔር ነው የሚለው ሐሳብ ተረስቷል። የሚያስተምር ሕዝቡ የሚወደው ግለሰብ ሆኗል። ዓቢይ
ጉባኤ ይሉት ነገር የመጣው ይኼኔ ነው፤ ንኡስ ጉባኤ ያለ ይመስል። ክርስቶስ ውኃ ጉድጓድ ዳር ሳምራዊቷን ሴት ብቻዋን
ለማስተማር ጉባኤ እንዳልዘረጋ አሁኔ መምህራን የጉባኤን ድምቀት በእልልታ አና በሰው ብዛት መለካት ጀምረዋል። ይኼ
ስህተት ነው። ሰባክያኑ በተቻለ አቅም ከዚህ የግብዝነት ሕይወት ራሳቸውን ለማውጣትና ቢሞክሩ፣ የሚኖሩትን
ቢሰብኩና ለራሳቸውም ለሌሎችም ድኅነት ቢሆኑ መልካም ነው። ካልሆነ ግን ምዕመናን በነዚህ የመድረክ ሰዎች
ምክንያት ከድኅነት መከልከል የለባቸውም።

በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ እንዲህ ያለ ቅርጹን የቀየረና ከቅርበት ትዕቢት የሚመጣ ንቀት በዝቷል።ለአንድ ዓላማ
ያልቆምን እስከሚመስል ድረስ መተቻቸቱ እና በሌላው ላይ ጣት መጠቆሙ በዝቷል። ይህ እናውቃለን ከሚል ድፍረት
የመጣ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ያለው ትዕቢት ስህተት እንደሆነ በመልዕክቱ ያሳየናል። "በእግዚአብሔር ፊት ሕግን
የሚያደርጉት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ ጻድቃን አይደሉምና።" ሮሜ 2:13 ይኼ ፈጽሞ መቅረት አለበት። ሁሉም
በራሱ ሥራ ነው የሚፈረድበት። ማንም ላይ ከመፍረዳችን በፊት መጀመርያ ለራሳችን የሚሆን በጎ ሥራ መስራታችንን
እናጣራ። በርግጥ ድኅነታችን ለሌሎች ድኅነት መትረፍ ነበረበት። አሁን ግን ለራሳችንም የሚበቃ ሆኖ አልተገኘምና
መጀመርያ የራሳችንን ዓይን ጉድፍ እናውጣ። 'ባለመድኃኒት ሆይ መጀመርያ ራስህን አድን!' ነው ነገሩ። ሲቀጥል ከሰዎች
በጎ በጎውን መርጠን የምንማርበትን ሥነ ልቡና ማዳበር አለብን። ማንም ፍጹም የለም።ሁሉም በየራሱ ድክመት አለበት።
የኛ ድክመት ደግሞ ከብዙዎቹ ቢበዛ እንጂ የሚያንስ አይደለም። እንደው ቢያንስም እንኳ ይበዛል ብሎ ማሰብ የተገባ
መተናነስ የሚታይበት ክርስቲያናዊ ትኅትና ነው። ታዲያ እገሌ እንዲህ ነው እገሌ እንዲህ ያደርጋል እያልን ጥላሸት
ከምንቀባባ መልካም ነገሮችን እያየን ራሳችንን ብናዳብር በጎ ሥራን ብናበዛ መልካም ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ መነሻ ባደረግነው ኃይለ ቃል ላይ የሚነግረን እርሱን ነው። "በበጎ ሥራ በመፅናት ምስጋናንና ክብርን
የማይጠፋንም ህይወት ለሚፈልጉ የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል።"

በጎ ሥራን አለመልቀቅ በሰዎች ውስጥ ያለውን ድካም ከማይት ይልቅ ምስጋናና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት
በመፈለግ ለምትበልጠው ጸጋ የሚተጉ ብቻ የዘለዓለምን ሕይወት ይወርሳሉ። ይህን የመፍረድ ሥልጣን ያለው ደግሞ
እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

You might also like