Professional Documents
Culture Documents
1 5
1 5
አምስተኛ ክፍል
የገበያ ጥናት አመልካቾች [Indicators]
ከዚህ በፊት የነበሩትን የትምህርቱን ክፍል በሚገባ ተረድቶ እዚህ ክፍል ላይ ለደረሰ አንድ አዲስ ትሬደር ቢያንስ መሰረታዊ የሚባለውን እና
ከግማሽ በላይ የሆነው የግብይት ጥናት ምንነት የተረዳ እንደሆነ መናገር ይቻላል። በዚህም አራቱን ክፍሎች በሚገባ ተረድተህ እዚህ
በመድረስህ አድናቆት ይገባሀል። ይሁንና ከግማሽ በላይ “የመሰረታዊ” ቴክኒካል አናሊስስ ጥናት ምንነትን ማወቅ የትሬዲንግን አለም ማወቅ
አለመሆኑ በሚገባ በመረዳት እጅግ ሰፊ የሆነው የፋይናንሳዊ ግብይቶች ጥናትን በማድረግ ትርፋማ ሊያድረጉን የሚችሉ የቻርት ጥናት የገበያ
አመላካች ኢንዲኬተሮችን በመረዳት እንቀጥል። በዚህም ይህ ክፍል በዋናነት በብዙሀኑ ትሬደር ለአመታት በቴክኒካል ጥናት ስራ ላይ ትግበራ
ላይ ውለው ትርፋማ ናቸው የተባለላቸውን እውቅ ኢንዲኬተሮችን መሰረታዊ ምንነታቸውን፤ ጥቅማቸውን፤ አተገባበራቸውን፤ ጉድለታቸው
እና በግብይት ላይ ስራ ላይ በመዋል ትርፍን የሚያስገኙበትን መንገድ ጠለቅ ባለ መልኩ እያንዳንዱን በዝርዝር በመመልከት ለመዳሰስ
ይሞከራል።
በዚህም የሚከተሉት የኢንዲኬተር አይነቶች በጥልቀት ዳሰሳ የሚደረግባቸው ይሆናሉ። በቀጥታ ወደፈለጋችሁት የኢንዲኬተር አይነቶች
ለመሄድ ስሞቹ ላይ ክሊክ በማድረግ በቀጥታ ወደትንታኔያቸው መግባት የምትችሉ ይሆናል።
5.1.የቦሊንገር ባንዶች
5.2. የኬልትነር ቻናል
5.3. የMACD ኢንዲኬተር
5.4. የፓራቦሊክ SAR ኢንዲኬተር
5.5. የስቶካስቲክ ኢንዲኬተር
5.6. ሪሌቲቭ ስትሬንግዝ ኢንዴክስ [RSI]
5.7. የዊሊያም ፐረሰንት ሬንጅ ኢንዲኬተር
5.8. አቬሬጅ ዳይሬክሽናል ኢንዴክስ [ADX]
5.9. ኢቺሞኩ ኪንኮ ሂዮ
ምዕራፍ አንድ
የቦሊንገር ባንዶች
ከላይ በመግቢያው ላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ትሬዲንግ ማለት እጅግ ሰፊ በሂደት የምንጨምረው እውቀት ያለበት እና
የማያልቅ መሻሻል እና የእውቀት አድማስን የማስፋት ሁነትን የሚጠይቅ ዲሲፒሊን ላይ የተመሰረተ ዘርፍ ነው። በቀላሉ
የስኬታማ ትሬዲንግን አካሄድ ተረድቶ ከጫፍ ለመድረስ እንደምሳሌ ቤት ከመስራት ጋር አያይዘን ልናየው ይቻለናል። መቼስ
ቤታችንን በምናቆምበት ሂደት ብሎን ማጥበቅ በሚኖርብን ቅፅበት ድሪሉን ትተን መዶሻ እንደማንጠቀመው ሁሉ፤ አልያም
በአካፋ መዛቅ ሲገባን በዶማው ጫፍ አፈራችንን ለመዛቅ እንደማንሞክረው ሁሉ በትሬዲንግ አለምም በተለያዩ አጋጣሚዎች
የምንጠቀማቸው የተለያዩ መሳሪያዎች አሉን። በዚህም በግብይት ውስጥ ላለ አንድ የታወቀ የገበያ ባህሪይ ጥናት የሚያገለግል
እና ለትርፋማነቱም በሂደት የተረጋገጠ የቴክኒካል ኢንዲኬተር ከሞላ ጎደል በሁሉም አጋጣሚዎች ይኖረዋል። በዚህም የበለጠ
ቁጥር ያላቸውን መሳሪያዎች አጠቃቀም ባወቅን ቁጥር ተቀያያሪነቱ ለቅፅበት እንኳን በማይቆመው በዚህ የፋይናንሱ አለም
የተሻለ እና የተሟላ የገበያ ሁነት መረጃ እንዲኖረን ይረዳናል። አልያም አንድ የገበያ ማጥኛ መሳሪያ ላይ እንኳን ነው ማተኮር
ለሚል ትሬደርም ቢሆን አስቀድሞ የትኛው መሳሪያ የተሻለ የገበያ ትርፋማነትን እንደሚያስገኝለት በማወቅ ለይቶ መምረጥ
አለበትና በባሌም በቦሌም እውቀቱን ይዞ መገኘቱ የብልሆች አካሄድ ተደርጎ ይወሰዳል።
ልክ በቤታችን የኤሌክትሪክ አልያም የቧንቧ ጥገና በሚያስፈልገን ወቅት በሙያው እውቀት ያላቸውን የሰለጠኑ ባለሙያዎች
ከፍለን ወጪ በራሳችን ላይ ከምንጨምር በራሳችን በመማር ከወጪ የምንድን እንደሆነው ሁሉ የቦሊንገር ባንዶችን አልያም
የተንቀሳቃሽ አማካዮችን አልያም ሌላ ይጠቅማል ተብሎ የሚታሰቡ የኢንዲኬተር አይነቶች ላይ ስፔሻላይዝ በማድረግ እውቀትን
መያዙ ጥቅሙ ቢያመዝን እንጂ እዚህ ግባ የሚባል ጉዳት እንደሌለው የታወቀ ነው። በዚህ ምዕራፍ እውቀትን በማስፋቱ ረገድን
የራሳችንን የግብይት ስትራቴጂዎች በመገንባቱ ሂደት በጣሙን የሚጠቅሙንን ዋና ዋና የሚባሉ የኢንዲኬተር አይነቶች
ስለእያንዳንዱ ጥቅም እና አተገባበር በጥልቀት ለመዳሰስ ይሞከራል። ይህም በጊዜ ሂደት ለትርፋችንን የሚጠቀሙንን እና
ከራሳችን የግብይት አካሄድ ጋር በአንድ ላይ በመዋሀድ ስራ ላይ ሊውሉ የሚችሉትን እነዚህን ጠቃሚ ኢንዲኬተሮች ለማየት
በምንሞክርበት ወቅት ሁሉንም ለውይይት የሚቀርቡ ኢንዲኬተሮች ጥቅም ላይ ማዋል አለብን ማለት እንዳልሆነ እና ማወቅ
ካለማወቅ ይሻላል በሚል መሰረታዊ መነሻ ሀሳብ እንጂ ግዴታ እንዳልሆነ ልብ ይሏል። በቀጣይ በቀጥታ በዝርዝር ለመመልከት
በመጀመሪያ ወደተቀመጠው የቦሊንገር ባንድ ኢንዲኬተር አይነት ምንነት የምናልፍ ይሆናል።
በእውቁ የፋይናንስ ትሬደር ጆን ቦሊንገር አማካኝነት በስራ ላይ የዋለው ይህ የቦሊንገር ባንድ ተብሎ የሚታወቅ የኢንዲኬተር
አይነት በዋናነት በገበያ ውስጥ ያለውን የዋጋ አለመረጋጋት እና ተለዋዋጭ የሆነ እንቅስቃሴ [volatility] የምንለካበት እና የገበያ
ሁኔታው እጅጉን በብዛት የተገዛ [overbought] አልያም የተሸጠ [oversold] መሆኑን ለመለየት የሚረዳን የገበያ ጥናት
ማድረጊያ ግብዓት ነው።
ጆን ቦሊንገር
በመሰረታዊነት ይህ የገበያ ጥናት ማድረጊያ ግብዓት በዋናነት ገበያው ፀጥ ያለ ሁነት ላይ ይሁን አልያም በጣም በፍጥነት
ግብይቶች እየተፈፀሙበት ያለ መሆኑን የሚነግረን የገበያ ጥናት መሳሪያችን ነው። ገበያው ፀጥ ያለ በሚሆንበት ወቅት እነዚህ
በተለምዶ ባንድ ተብለው የሚጠሩት ድንበር ሰርተው የሚንቀሳቀሱ መስመሮች እርስ በእርስ ተጠጋግተው የሚጓዙ ሲሆን
ገበያው በፈጣን ሁኔታ ላይ በሚሆንበት ወቅት ደግሞ እየተራራቁ የሚሄዱ ሆነው እናገኛቸዋለን። ይህ ኢንዲኬተር በቻርቱ
አለም “overlay indicator” ተብለው ከሚመደቡት እና በቻርቱ የገበያ ማመላከቻ ካንድል ስቲክ ላይ ከበላይ ተለጥፎ መረጃን
የሚሰጠን የኢንዲኬተር አይነት ነው።
ከላይ በምስሉ መመልከት እንደሚቻለው ገበያው ቀዝቃዛ እና ፀጥ ያለ በሚሆንበት ወቅት ሁለቱ የኢንዲኬተሩ ሰማያዊ
መስመሮች [ባንዶች] እንዴት ተቀራርበው እንደሚሄዱ እና የገበያ ዋጋው እንቅስቃሴ ማድረግ ሲጀምር ደግሞ እንዴት እርስ
በእርሳቸው እየተራራቁ እንደሚሄዱ መመልከት ይቻላል።
የላይኛው እና የታችኛው የባንድ መስመሮች ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው በዋናነት በአንድ የተወነ የጊዜ ገደብ ውስጥ
ያለውን የገበያ ዋጋ መዋዠቅ፤ መለዋወጥና በተለያዩ የጊዜ ገደቦች የተፈጠሩ የዋጋ እርከኖች ያሳይዋቸውን ለውጦች የሚለኩልን
የኢንዲኬተሩ ክፍሎች ናቸው። ቦሊንገር ባንዶች በዋናነት የገበያ ዋጋ መለዋወጥን ለመለካት የምንጠቀምባቸው የኢንዲኬተር
አይነቶች እንደመሆናቸው እነዚሁ ባንዶች የገበያ ሁነቱ እና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለውጥ በሚያሳዩበት ቅፅበት አብረው
የሚለዋወጡ ሆነው እናገኛቸዋለን።
እንደአንድ አዲስ ተገበያይም ሆነ ከሂሳባዊ ቀመሮች ጋር አዲስ እንደሆነ ግለሰብ መደበኛ ልይይት የምንለውን እሳቤ ገልፀን
ለማለፍ እንሞክር። በዚህም የእዚሁ የመደበኛ ልይይት እሳቤ በቀላል አማርኛ ሲገለፅ በቁጥሮች መካከል ያለን ልዩነት መስፋትና
መጥበብ የሚያመላክተን እና የዚሁ ልዩነታቸውን መጠን የምናውቅበት ሂሳባዊ ስሌት ነው። ለምሳሌ የላይኛው እና የታችኛው
የባንድ መስመሮች የመደብኛ ልይይት መጠናቸው 1 ነው ካልን ይህ ማለት በጊዜ ገደቡ በቅርብ ጊዜያት የነበሩ የዋጋ
እንቅስቃሴዎች ሁሉ በእነዚህ ከገበያው ጋር አብረው በሚንቀሳቀሱ ባንዶች መሀከል የሚሆን/የሚጓዝ ይሆናል እንደማለት ነው።
የመደበኛ ልይይት መጠናቸው 2 ከሆነ ደግሞ ይህ ማለት በቅርብ ከተከሰቱ የገበያ ዋጋ እንቅስቃሴዎች 95 በመቶ የሚሆኑት
የተከሰቱት በእነዚህ ባንዶች መሀከል ላይ ባለ የቻርት ቦታ ላይ ይሆናል ማለት ነው። ምናልባትም ፅንሰሀሳቡን ለመረዳት ይረዳ
ዘንድ የሚከተለውን የመደበኛ ልይይትን የሚገልፅ ምስል ለመመልከት እንሞክር።
ከላይ በምስሉ ላይ መመልከት እንደሚቻለን ከፍ ያለ የመደበኛ ልይይት መጠንን ለባንዶቹ በተጠቀምን ቁጥር በባንዶቹ
መሀከል የሚዋጡ አልያም የሚጠቃለሉ የገበያ ዋጋ እርከኖችም አብረው የሚጨምሩ መሆኑ ነው። እነዚህ ልይይቶች እንዴት
እንደሚሰሩ ካወቅን በኋላ የተለያዩ የመደበኛ ልይይት መጠኖችን ለባንዶቹ በመሰየም ያለውን አጠቃላይ የእሳቤውን መሰረታዊ
ትግበራ መረዳት ይቻላል። እንደእውነቱ ከሆነ ይህ የመደበኛ ልይይት ሂሳባዊ ስሌት በምን መልኩ እንደሚሰራ በጥልቀት ማወቁ
ያን ያህል መሰረታዊ የሚባል እና እንደአንድ አዲስ ትሬደርም ግዴታ ያልሆነ ሁነት መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል። በዚህም
በዚህ ክፍል በተለየ ሁነት የእሳቤውን ምንነት በተወሳሰበ መልኩ ከማቅረብ ይልቅ የተሻለው አማራጭ እንደአጠቃላይ የቦሊንገር
ኢንዲኬተር እንዴት በግይታችን ውስጥ መጠቀ እንዳለብን ለመመልከት እንሞክራለን።
የግርጌ ማስታወሻ፡ ከዚህ ባለፈ ያለውን የጠለቀ የትግበራ ሁነት እና የሂሳባዊ ቀመር አመጣጥ ለመረዳት የራሱ
የኢንዲኬተሩ ፈልሳፊ ጆን ቦሊንገር የፃፈውን “Bollinger on Bollinger Bands” የተሰኘ መፅሀፍ ማንበብ የተሟላ
እይታን የሚፈጥር ሆኖ እናገኘዋለን።
ምዕራፍ ሁለት
የኬልትነር ቻናል [Keltner’s Channel]
ይህ የኬልትነር ቻናል የተባለ የገበያ ዋጋ ለውጥ እና መዋዠቅ መጠንን[Volatility] የሚያመላክተን የኢንዲኬተር አይነት
ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ጥቅም ላይ እንዲውል ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ የቀረበው የእህል ነጋዴ የነበረው ቼስተር ኬልትነር እኤአ
በ1960 ባሳተመው “How to Make Money in Commodities” በተሰኘ መፅሀፉ ነበር። የዚህ መፅሀፍ የተከለሰ ህትመት
በኋላ ላይ በ1980ዎቹ በሊንዳ ራስቼክ ለንባብ በቅቶ እንደንበር አይዘነጋም። የዚህ የተከለሰው የሊንዳ ራስቼክ ህትመት
የኬልትነር ቻናልን በይበልጥ በመግልፅ እና በማስረዳት የተሻለ እንደሆነ የሚነገርለት እና በብዙሀንም ምስክርነት የተሰጠበት
ሲሆን በዋናነት የኬልትነር ቻናል የግብይት እሳቤ ከቦሊንገር ባንዶች ጋር በተመሳሳይ ሶስት መስመሮችን የሚጠቀም ሆኖ
የግብቶችን እንቅስቃሴ ቅድመ ሁነት እንድናውቅ የሚረዳ የኢኒዲኬተር አይነት እንደሆነም ያትታል።
ይሁንና በኬልትነር ቻናል ኢንዲኬተር ላይ የምናገኘው የመሀለኛው መስመር የቦሊንገር ባንድ ኢንዲኬተር ላይ በስራ ላይ
ከሚውለው የሲምፕል ተንቀሳቃሽ አማካይ ይልቅ የኤክስፖኔንሺያል ተንቀሳቃሽ አማካይን ነው። በተጨማሪነት ሁለቱ ውጪያዊ
መስመሮች ደግሞ መሰረታቸውን ያደርጉት በመደበኛ ልይይት ወይም Standard Deviations ላይ ሳይሆን በተለምዶ
Average True Range [ATR] ብለን በምንጠራው በአማርኛው በግርድፉ አማካይ እውነተኛ መዳረሻ የሚል ትርጉም
በሚሰጠን የገበያ አሀዝ ላይ ነው። ይህ ቻናል የሚመሰረተው በዋናነት ATR የተባለውን በራሱ የገበያ መዋዠቅ[Volatility]
መለኪያ የሆነን አሀዝ መሰረት በማድረግ በመሆኑ ምክንያትነትም የኬልትነር ቻናልም ከገበያው የመዋዠቅ እንቅስቃሴ ጋር
አብሮ እየሰፋ እና እየጠበበ የሚሄድ ሆኖ ይገኛል። እዚህ ጋር ማስታዋስ ያለብን ጉዳይ ቢኖር የኬልትነር ቻናል የመጥበብ እና
የመለጠጠ እንቅስቃሴ እንደቦሊንገር ባንዶች የፈጠነ የገበያ መዋዠቅ እንቅስቃሴ [volatile move] ሲያሳዩ አይስተዋልም።
የኬልትነር ቻናሎች በዋናነት በግብይታችን ውስጥ የሚጠቅሙን በገበያው ውስጥ የምንገባበት እና የምንወጣበት የዋጋ
እርከንን መለየት ላይ ነው። ይህ ኢንዲኬተር ከልክ በላይ ግዢ የተደረገባቸው[overbought] እና ሽያጭ
የተደረገባቸውን[oversold] የዋጋ እርከኖች ለመለየት የሚጠቅመን ሲሆን ይህ ሁነት በተለይ ከተንቀሳቃሽ አማካይ መስመሮች
ጋር በአንፃራዊነት በጥናት ላይ በሚውልበት እና የገበያ ትሬንዱ በተለምዶ “Flat” ብለን የምንጠራው አይነት ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ
በሚኖረው ወቅት ጥሩ የሆነ ቅድመ ግምትን እንድወስድ የሚያደርገን ኢንዲኬተር ነው።
በተጨማሪነት ይህ ኢንዲኬተር አዲስ ትሬንድ ሊመሰረት ስለመሆኑም ምንጭ ሆኖ ሊያገለግለን የሚችል ኢንዲኬተር ነው።
ቻናል የሚለውን እሳቤ ወደላይ አልያም ወደታች እየሄደ እንዳለ ሰርጥ አስቡት። ይህ ቦይ መሰል ሰርጥ ከገበያው ዋጋ መዋዠቅ
ጋር አብሮ የሚዋዥቅ ሲሆን ቀጥ ያለ መስመር ሊሆን የማይችል ሁሌም ተቀያያሪ ቅርፅ እና አካሄድ ያለው ሆኖ እናገኘዋለን።
በእርግጥም በዚህ ክፍል የመጀመሪያ ክፍል ላይ ያለው የቦሊንገር ባንድ እሳቤ የኬልትነር ቻናል ኢንዲኬተር እሳቤ ተመሳሳይነት
ቢኖራቸውም በየራሳቸው የሚሰጡን የተናጠል የግብይት ጥናት አይነቶች፤ በሚጠቀሙት ተጨማሪ ኢንዲኬተር አይነት እና
በአጠቃላይ የሚሰሩበት የሂሳብ ቀመር ለየቅል የሆነ እሳቤን የያዙ መሆናቸውም ልብ ይሏል። እንደ አንድ አዲስ ተገበያይ እነዚህ
ኢንዲኬተሮች የተገኙበትን ሂሳባዊ ቀመር በዚህ ክፍል ማቅረቡ ውስብስብነቱን የሚጨምር ሆኖ ስለሚገኝም በአጠቃላይ
በቀጥታ በግብይታችን ውስጥ የሚሰጠንን ጥቅም እና በምን መልኩ ይህንን ኢንዲኬተር በመጠቀም ትርፍን ማግኘት
እንደምንችል ለማየት እንሞክር።
ወደላይ እየተጓዘ ባለ በተለምዶ uptrend በምንለው የገበያ እንቅስቃሴ ውስጥ የዋጋ እርምጃው በላይኛው የቻናሉ ክፍል
የሚሆን ሲሆን ያም በዋናነት የመሀለኛውን መስመር እንደ ሰፖርት እርከን እንዲሁም የላይኛውን መስመር ደግሞ እንደ
ሬዚስታንስ እርከን የሚወስድ ይሆናል።
ወደታች እየተጓዘ ባለ በተለምዶ downtrend በምንለው የገበያ እንቅስቃሴ ውስጥ የዋጋ እርምጃው በታችኛው የቻናሉ ክፍል
የሚሆን ሲሆን ያም በዋናነት የመሀለኛውን መስመር እንደ ተለዋዋጭ የሬዚስታንስ የዋጋ እርከን እንዲሁም የታችኛውን
ወደጎን እየሄደ ባለ ቀዝቀዝ ባለ የገበያ ሁኔታ ላይ የገበያ ዋጋው በአብዛኛው በላይኛው እና በታችኛው መስመር መካከል
በመንዠዋዠው የሚንቀሳቀስ ይሆናል።
እየተምሰረቱ ያሉት የካንድል ስቲኮች ከታችኛው ኬልትነር መስመር በታች ለመውረዳቸው ጥረት በሚያደርግበት አብዛኛው
አጋጣሚ የገበያ አካሄዱ ተጠናክፎ መውረድ ሊቀጥል ስለመሆኑ የምናይበት ነው።
እየተመሰረቱ ያሉት የካንድል ስቲኮች ከላይኛው ኬልትነር መስመር በላይ ለመውጣት ጥረት በሚያደርግበት አብዛኛው አጋጣሚ
የገበያ አካሄዱ ተጠናክሮ ማደግ ሊቀጥ ስለመሆኑ የምናይበት ነው።
በእርግጥም እነዚህን የቻናሉ ድንበሮች መሰበር አጋጣሚዎች የምናገኛቸውን አጋጣሚዎች በመጠቀም ጥሩ የሆነ ትርፍን
ማግኘት የሚቻል ሆኖ እናገኘዋለን።
ምዕራፍ ሦስት
የMACD ኢንዲኬተር
MACD ምንድነው?
MACD የሚለው ቃል በተለምዶ Moving Average Convergence Divergence ለሚለው ቃል እንደምህፃር ጥቅም ላይ
የሚውል ሲሆን በዋናነትም አዲስ የሆነ የትሬንድ ምስረታዎችን የሚያሳዩ የተንቀሳቃሽ አማካዮችን ለመለየት እና እነዚሁ
አማካዮችም ቡሊሽ አልያም ቢሪሽ የሆነ የገበያ ባህሪይ እንዳላቸው የሚያስዩ ቴክኒካል ኢንዲኬተሮች ናቸው። በእርግጥም
በአጠቃላይ የአንድ ትሬደር ዋናው አላማው የትሬንድ ምስረታን አስቀድሞ በመገመት ትርፍን ማግኘትም አይደል?
MACDን ያማከለ ቻርት ላይ በኢንዲኬተሩ ሴቲንግ ውስጥ ሶስት መሰረታዊ ቁጥሮች ጥቅም ላይ ውለው እንመለከታለን።
- የመጀመሪያው ፈጣኑን የተንቀሳቃሽ አማካይ ለማግኘት የወሰደብንን የጊዜ ገደብ መጠን የሚያሳየን ነው።
- ሁለተኛው ከሁሉም ቀርፋፋ የተባለውን የተንቀንሳቃሽ አማካይ ለማግኘት የወሰደብንን የጊዜ ገደብ መጠን
የሚያመላክተን ነው።
- የመጨረሻው እና ሶስተኛው ደግሞ በፈጣኑ እና በቀርፋፋው የተንቀሳቃሽ አማካዮች መካከል ያለውን ልዩነት ለማስላት
የምንወስዳቸው የካንድል ስቲኮች ብዛትን የሚያመላክተን ነው።
ለምሳሌ በአብዛኛው የቻርት ሶፍትዌሮች ላይ የምናገኘውን የMACD እክባይ[Parameter] “12, 26, 9” እንደምሳሌ በመውሰድ
ሁነቱን ለመረዳት እንሞክር። በዚህም እነዚህ ሶስት ቁጥሮች በዚህ ኢንዲኬተራችን ላይ የሚያሳዩንን የገበያ ክስተቶች ለመዘርዘር
ያህልም ፡-
- 12 የባለፉትን 12 የግብይት ክፍለ ጊዜያት[ካንድል ስቲኮች/ባሮች] ተንቀሳቃሽ አማካይ ተመን ያመላክተናል።
- 26 የባለፉትን 26 የግብይት ክፍለ ጊዜያት[ካንድል ስቲኮች/ባሮች] ተንቀሳቃሽ አማካይ ተመን ያመላክተናል።
- በሁለቱ የተንቀሳቃሽ አማካዮች መካከል ያለውን የተንቀሳቃሽ አማካይ ልዩነት የሚያሳየን ሆኖ እናገኘዋለን።
የMACD መስመሮችን በተመለከተ ደግሞ በብዙሀን አዳዲስ ትሬደሮች ዘንድ የሚፈጠር አንድ እሳቤ አለ። ለመሆኑ ግን እነዚህ
የMACD መስመሮች ምንድናቸው። በአጠቃላይ ሁለት በዚህ ኢንዲኬተር ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሁለት መስመሮች አሉ።
እነሱም ፡-
1. የMACD መስመር እና
2. የሲግናል መስመር የምንላቸው ናቸው።
እነዚህ ሁለት መስመሮች ታዲያ የገበያ ዋጋው ተንቀሳቃሽ አማካይ መስመሮች እንዳልሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። የMACD
መስመር በሁለት ተንቀሳቃሽ አማካዮች መካከል ያለ ልዩነት አልያም ርቀትን የሚመዝንልን እና የሚያመላክተን መስመር ነው።
ይህ መስመር የሚተመንባቸው ሁለት የተንቀሳቃሽ አማካይ መስመሮች በብዛት የኤክስፖኔንሺያል ተንቀሳቃሽ አማካይ
አይነቶችም ሲሆኑ ይስተዋላል። ኢንዲኬተሩን በምንመለከትበት ወቅትም ይህ የMACD መስመር እንደፈጣኑ የተንቀሳቃሽ
አማካይ ተደርጎ ይወሰዳል። ከላይ በምሳሌነት በወሰድነው በብዙ የቻርት ሶፍትዌሮች ላይ የምናገኘውን ሴቲንግ በድጋሚ
ለማስረጃነት እንውሰደው እና የMACD መስመራችን ማለት በ12 እና በ26 የጊዜ ገደብ ተንቀሳቃሽ አማካዮች መካከል ያለውን
ልዩነት/ርቀት የሚለካ እና የሚያመላክተን መስመር ነው ማለት ይቻለናል።
የሲግናል መስመር የምንለው ደግሞ የራሱ የMACD መስመራችንን ተንቀሳቃሽ አማካይ የሚያሳየን መስመር ነው።
ኢንዲኬተሩን በምንመለከትበት ወቅት የሲግናል መስምሩ ቀርፋፋው የተንቀሳቃሽ አማካይ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን
መመልከት ይቻለናል። ይኸው ቀርፈፍ ያለ የተንቀሳቃሽ አማካይ በዋናነት ያለውን ተመን የሚያገኘው በመሰረታዊነት ከዚህ
ቅፅበት በፊት ከተመዘገቡት የMACD መስመሩ ተመኖች ነው። በምሳሌያችን የ9 ጊዜ ገደብ ተንቀሳቃሽ አማካይ ብለን
የምንወስደውም ይህንኑ ነው። ሁሉም የቻርት ሶፍትዌሮች ማለት በሚቻልበት ሁነት የምናገኘው የኤክስፖኔንሺያል አማካይ
ተመንም 9 ሆኖ እናገኘዋለን። ይህም ማለት ያለፉትን 9 የጊዜ ገደቦች/የግብይት ወቅቶች[Periods] ፈጣን የMACD መስመር
አማካይ በመውሰድ ቀርፈፍ ያለ አዲስ የተንቀሳቃሽ መስመር የሚሰራበት ሁነት የሚኖረውም ለዚህ ነው። በዋናነትም የዚሁ
የሲግናል መስመር ዋነኛ ጥቅም የMACD መስመሩ ለገበያው የሚኖረውን ጤናማ ያለሆነ ትብነት[Sensitivity] ለማረጋጋት
አልያም ለማለሳለስ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።
ሌላው የዚህ ኢንዲኬተር ክፍል የሆነው ግጥም ጥርብ ግርፍ ወይም በተለምዶ “Histogram” ብለን የምንጠራውን ክፍል ነው።
ይህም በዋናነት በMACD መስመሩ እና በሲግናል መስመራችን መካከል ያለውን ልዩነት እግር በእግር እየተከተለ የሚከትብልን
የኢንዲኬተሩ ክፍል ነው። ይህ ሂስቶግራም የምንለው ሁነት በሁለቱ መስመሮች መካከል ያለውን ርቀት በግራፍ መልክ እየከተበ
የሚምያስቀምጥልን የኢንዲኬተራችን ክፍል ነው። በእርግጥም በትክክለኛው መንገድ እና እይታ ልንመለከተው ከቻልንም
የመስመሮች እርስ በእርስ የመጠላለፍ ሁነት ሊፈጠር ስለመሆኑም አስቀድመን ግምታችንን ልንወስድበት የምንችልበት ሆኖ
እንገኘዋለን። ከላይ በምስል በቀረበው ምሳሌያችን ላይ ለመመልከት እንድሚቻለንም የMACD እና የሲግናል መስመሮቻች
ተንቀሳቃሽ አማካዮች እርስ በእርሳቸው እየተራራቁ በሚሄዱበት ወቅት ሂስቶግራሙ መጠኑ ከፍ እያለ ሲሄድ መመልከት
ይቻላል። ይህ የገበያ ላይ ክስተት በተለምዶ የMACD ልዩነት [MACD Divergence] ብለን የምንጠራው ሲሆን ይህም በዋናነት
ፈጣን የሆነው የMACD ተንቀሳቃሽ አማካያችን ቀርፈፍ ካለው የሲግናል መስመራችን ተንቀሳቃሽ አማካይ እየራቀ እና
እየተለያየ ስለሚሄድ ነው። በሌላኛው ሁነት ደግሞ ሁለቱ መስመሮቻችን እርስ በእርሳቸው እየተቀራረቡ በሚሄዱበት ወቅት
የሂስቶግራሙ መጠን አነስተኛ እየሆነ የሚሄድ ሲሆን ይህም በተለምዶ የMACD ግንኝት[MACD Convergence] ብለን
የምንጠራውን የገበያ ሁነት ያመላክተናል። ይህም ስያሜ የተሰጠበት ዋነኛ ምክንያት የMACD እና የሲግናል መስመሮቹ
ተንቀሳቃሽ አማካዮች እርስ በእርሳቸው እየተቀራረቡ የሚመጡ ከመሆኑ አንፃር ነው። በዚህም ነው እንግዲህ MACD
የተሰኘውን ምህፃር ያስገኘልን Moving Average Convergence Divergence የሚል ስያሜ ሊሰጠው የቻለው። እስካሁን
ባለው የዚህ ምዕራፍ ትምህርት ላይ MACD ኢንዲኬተር ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት አድርገናል። አሁን ደግሞ ይህ
ኢንዲኬተር በግብይታችን ውስጥ እንዴት ትርፍን እንድናገኝ ሊረዳን እንደሚችል ለመመልከት እንሞክራለን።
ከላይ በቀረበው ቻርት ላይ እንደምንመለከተው በሰማያዊ ቀለም የተቀለመው ፈጣኑ የMACD መስመር ቀዩን የሲግናል
መስመር ሰብሮ በሚያልፍበት ወቅት ጊዜያዊም ይሁን ዘላቂ፤ ብቻ አዲስ የገበያ ትሬንድ ስለመመስረቱ የሚነግረን ይሆናል።
በዚህ ሂደት ልክ እነዚህ ሁለት መስመሮች እርስ በእርስ በሚጠላለፉበት ቅፅበት የሂስቶግራማችን መጠን ምንም የማይታይ
አልያም እጅግ በጣም አነስተኛ ሲሆን መመልከትም ይቻለናል። ይህም በዋናነት በእነዚህ ሁለት መሰምሮች መካከል ያለው
ልዩነት ለዜሮ የቀረበ በመሆኑ ነው። ልክ ፈጣኑ የMACD መስመር ከሲግናል መስመራችን ሰብሮ ወደታች ርቀቱን እያሰፋ
በሄደበት ቅፅበት ሂስቶግራሙ እየገዘፈ ሲሄድ መመልከት የሚቻለን ሲሆን ይህም በዋናነት በአዲስ መልክ እየተመሰረተ ያለው
ትሬንድ ጥንቅካሬው እየጨመረ ስለመምጣቱ ማመላከቻ ሆኖ እናገኘዋለን። ለዚህ እሳቤ እንደተጨማሪ ማሳያ ይሆነን ዘንድ
የሚከተለውን የዩሮ የአሜሪካን ዶላር የግብይት ጥንድ የአንድ ሰዓት ቻርት ለምሳሌነት እናንሳ።
በቻርቱ ላይ መመልከት እንደሚቻለው በፈዛዛ ሰማያዊ ቀለም የተቀለመውን የኢንዲኬተር ቦታ ከተመለከትን ፈጣኑ የMACD
መስመር ቀርፈፍ ካለው የሲግናል መስመራችን በላይ ሰብሮ ሲያልፈው መመልከተ ይቻለናል። በዚህ የገበያ ቅፅበት የተፈጠረው
ሂስቶግራም ጭራሹን ሲጠፋ የሚታይ ሲሆን ይህም በዋነኝነት በጠንካራ መልኩ ገበያውን ወደታች ሲጎትተው የነበረው ሀይል
እይተዳከመ እና የነበረው ወደታች አቅጣጫ ይጓዝ የነበረ የገበያ ትሬንድ መዳከሙን አለፍ ሲልም አቅጣጫም ሊቀይር
ስለመሆኑ እንደማሳያ ሊወሰድ የሚችል ሁነት ሆኖ እናገኘዋለን። ከዚህ የMACD የሲግናል መስመሮች እርስ በእርስ የመጠላለፍ
ክስተት በኋላ የዩሮ ዶላር ጥንድ በጠንካራ ሁኔታ ጉዞውን በአዲስ ወደላይ አቅጣጫ የሚሄድ ትሬንድ ላይ ሲመሰርት
ይስተዋላል። ከዚህ መጠላለፍ በኋላ ያለውን ቅፅበት በገበያው የግዢ ትዕዛዝ ፈፅሞ የገባ ትሬደር በቀላሉ እስከ200 ፒፕስ
የሚሆን ትርፍን ማግኘት የሚችልበት ሁነት ሊፈጠር መቻሉንም ማየት ይቻለናል።
ምንም እንኳን በጠቃሚነታቸው እጅጉን ተቀባይነት ካገኙ ኢንዲኬተሮች መካከል በግምባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት መካከል
ይሁን እንጂ ልክ እንደማንኛውም የገበያ ውስጥ ጥናት ማካሄጃ ግብዓት ይኸው የMACD ኢንዲኬተር አንድ አሉታዊ ጎን
እንዳለው መታሰብ ይኖርበታል። እንዲሁ በደፈናው የተንቀሳቃሽ አማካዮች አሁን ካለው የገበያ ዋጋ አንፃር እየተንቀራፈፉ
የሚሄዱ እና ቅድመ ግምታችንም በተወሰነ መልኩ የተንቀራፈፈ እንዲሆን የሚያደርጉ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ የመንቀራፈፍ
እና በገበያው ውስጥ ያለውን ሁነት በፈጠነ መልኩ እንድንገምት ያለማድረግ ባህሪይው የዚህን ኢንዲኬተር ሙሉነት
የሚያጓድል ሆኖ በብዙ ትሬደሮች ዘንድ ሲነሳ ይስተዋላል። በዛውም ልክ በዚሁ አንቀፅ ላይ ለማመላከት እንደተሞከረው ይህ
የኢንዲኬተር አይነት ከሌሎች የገበያ ጥናት ኢንዲኬተሮች በተሻለ ሁነት ምናልባትም በግምባር ቀደምትነት የኢንዲኬተሮችን
ጥቅም ላይ በሚያነሱ ትሬደሮች ሳይቀር ትግበራ ላይ ሲውል የምናየው እጅግ ጠቃሚ ግብዓታችን ነው። በምዕራፉ የተነሱትን
በዋናነት የኢንዲኬተሩን ምንነት ለመግለፅ ያነሳናቸውን እሳቤዎች እንደክለሳዊ ማጠቃለያ ለማንሳት ያህልም ይህ ኢንዲኬተር
ሶስት መሰረታዊ ክፍሎችን የያዘ ሲሆን በዋናነትም፡
1. የMACD መስመር ፡ በሁለት ተንቀሳቃሽ አማካዮች መካከል የያለውን ልዩነት የሚገልፅልን
2. የሲግናል መስመር ፡ የMACD መስመራችን የተንቀሳቃሽ አማካይ ስሌት የሚገልፅልን እንዲሁም
3. ሂስቶግራም የምንለውን በሁለቱ መስመሮች መካከል ያለውን ርቀት ልኬት በግራፍ መልክ የሚገልፅልን ክፍሎች
ናቸው።
እንደአጠቃላይ ይህን የገበያ ጥናት አማላካች ጥቅም ላይ በምናውልበት ወቅት ልክ እንደሌሎች የቴክኒካል ጥናት አካሄዶቻችን
ሁሉ በአባሪነት በገበያው ውስጥ ልንመለክታቸው የምንችላቸውን ተጨማሪ የገበያ ውስጥ ማመላከቻ የገበያ ሁነቶች ከግምት
በማስገባት እና ጥናት በማድረግ የግብይት ውሳኔዎቻችንን ማድረግ እንደሚገባን ሁሌም ማስታወስ የሚገባን ጉዳይ ሆኖ
እናገኘዋለን።
ምዕራፍ አራት
ፓራቦሊክ ሳር [Parabolic SAR]
እስካሁን ባለው የዚህ ክፍል ትምህርት ላይ በቀደሙት ሶስት ምእራፎች በዋናነት የአዲስ ትሬንድ ጅማሬን የሚያመላክቱንን
የቴክኒካል ኢንዲኬተሮች ለመመልከት ሞክረናል። ምንም እንኳን እነዚህ አዲስ የገበያ ትሬንድ ጅማሬ የገበያ ዋጋ እርከኖች
ማወቁ እጅጉን ጠቃሚ የሆነ ትርፋማ ሁነት ቢሆንም በዛውም ልክ ከገበያው የምንወጣበትን የገበያ ሁነቶች እና ክስተቶች
አውቀድሞ መገመት መቻልም ለትርፋማነታችን ዋናና መሰረታዊ ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን። እንደእውነቱ ካሰብነው ጥሩ የገበያ
መውጫ የዋጋ እርከናችንን መለየት ሳንችል የመግቢያውን የዋጋ እርከን ብቻውን ማወቃችን ያን ያህል ተጠባቂውን ትርፍ
ላያስገኝልን እንደሚችል ማሰብ ብልህነት ነው።
ታዲያ ይህንን መሰሉ ከገበያ ልንወጣ የምንችልባቸውን የገበያው ውስጥ የዋጋ እርከኖች አስቀድመን ለመገመት ከሚረዱን
የቴክኒካል ኢንዲኬተሮች መካከል አንዱ በተልምዶ ፓራቦሊክ ሳር [Patabolic SAR / Stop And Reversal] ብለን
የምንጠራው የኢንዲኬተር አይነት ነው።
ፓራቦሊክ ሳር በቻርት ላይ በዋናነት በገበያ እንቅስቃሴው ዋጋ አካሄዱን በመለወጥ አቅጣጫውን ሊገለብጥ ይችልባቸዋል
ተብሎ የሚታሰቡ የዋጋ እርከኖችን በነጥቦች ለይቶ የሚያሳይ የኢንዲኬተር አይነት ነው። ከላይ በምሳሌነት በቀረበው የቻርት
ምስል ላይ እንደቀረበው የፓራቦሊክ ሳር ኢንዲኬተራችንን የሚወክሉትን ነጥቦች ከተመለከትናቸው ወደላይ እየሄደ ባለ የገበያ
ትሬንድ ላይ ነጥቦቹ ከካንድል ስቲኮቹ በታች የነበሩ ሲሆን የገበያ ትሬንዱ አቅጣጫ ቀይሮ ወደታች መጓዝ በጀመረበት ሁነት
ደግሞ ከካንድል ስቲኮቹ በላይ ሲመሰረቱ መመልከት ይቻለናል።
በእርግጥም ይህን ኢንዲኬተር በመጠቀሙ ሂደት ቅለቱ በገበያ ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ውስብስብ የሆኑ የገበያ አካሄዶች
የሚያቀልልን እና ገበያው ወደላይ አልያም ወደታች አቅጣጫ ሊጓዝ ስለመሆኑ ብቻ ቀለል አድርጎ የሚያሳየን የኢንዲኬተር
አይነት ነው። ይህንን ኢንዲኬተር በዋናነት ትርፋማ ለመሆን ጥቅም ላይ ማዋል አለብን ተብሎ የሚታሰበው ጠንካራ በሆነና
ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳያ ባለ የገበያ አካሄድ ላይ ነው። ተያይዞም ይህን ኢንዲኬተር ቀርፋፋ በሆነ እና የጎንዮሽ አካሄድን እያሳየ
ባለ የገበያ አካሄድ ላይ መጠቀም ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዘነ የሆነ እና ይህን መሰሉን የትሬንድ አካሄድ ከመጠቀም መቆጠቡ
የተሻለው አማራጭ መሆኑን ማስታወስ ግድ ይላል።
ከላይ በቀረበው የአንድ ቀን የዩሮ የአሜሪካን ዶላር ጥንድ የግብይት ቻርት ላይ በኤፕሪል የመጨረሻ ቀናት የገበያ ዋጋው
በተጠናከረ መልኩ ወደታች መጓዙን የቀጠለ መሆኑን እና በዛው ጠንካራ አወራረዱ የሚቀጥል እንደሚመስል እንዲሁ በቀላሉ
በመመልከት ማስተዋል ይቻለናል። በዚህ የገበያው ቅፅበት ላይ የሽያጭ ትእዛዝን ያደረገ ተገበያይ ታዲያ ገበያው እስከየትኛው
የገበያ ዋጋ እርከን ድረስ መውረዱን ሊቀጥል እንደሚችል ጥያቄ ሊጭርበት እንደሚችል ግልፅ ነው። በምሳሌው ላይ፤ በጁላይ
የመጀመሪያ ቀናት ከገበያ ዋጋው በታች ሶስት የፓራቦሊክ ነጥቦች መመስረታቸውን መመልከት እንችላለን። ይህም በዋናነት
ገበያው ጠንካራ የሆነ ወደላይ አቅጣጫ ሊከሰት የሚችል [ጊዜያዊም ሆነ ረጅም ሊሆን የሚችል] የገበያ ትሬንድ እየተፈጠረ
ስለመሆኑ በተጨማሪነትም ከዚያ የገበያ ሁነት በፊት የነበረው የዳውንትሬንድ መገባደዱን እና በ”short’ ፖዚሽን ከነበረን
ግብይት መውጣት ጊዜው መሆኑን የሚያመላክተን ሆኖ እናገኘዋለን። በእርግጥም በምሳሌው ላይ እንደተመለከተው በዚህ
ትሬደር ቦታ ብትሆኑ እና የዩሮ አሜሪካን ዶላር ግብይት ዋጋ መውረድ ስለመቀጠሉ አስባችሁ ከገበያው ባትወጡ ገበያው
ባሳየው መልሶ ወደላይ የተደረገ ጉዞ የተገኘ የነበረውን ትርፍ መልሳችሁ የምታጡበት ይሆን ነበር ማለት ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ልክ ሌሎች የትኛውንም ኢንዲኬተሮች በመጠቀሙ ሂደት ልንከተውለው የሚገባንን የግብይት ቅድመ
ጥንቃቄ በዚህ ኢንዲኬተር አጠቃቀምም ላይ መተግበር ያለብን መሆኑን መዘንጋት የሌለብን እና ተጨማሪ የገበያ ላይ
ማረጋገጫ የገበያ ጥናት ውጤቶችን መመለከት ያለብን መሆኑን ሁሌም ማስታወስ የሚገባን መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ
ሆኖ እናገኘዋለን።
ምዕራፍ አምስት
የስቶካስቲክ ኢንዲኬተር
የስቶካስቲክ ኦሲሌተር የምንለው የኢንዲኬተር አይነት ልክ እንደፓራብሊክ ሳር ሁሉ የአንድን ትሬንድ መጨረሻ መድረስ
አለመድረስ አስቀድመን ቅድመ ግምታችንን የምንሰጥበት የኢንዲኬተር አይነት ነው።
ይህ በተለምዶ ኦሲሌተር በሚል መጠሪያ የሚታወቅ የኢንዲኬተር አይነት በዋናነት በሚከተሉት መሰረታዊ ፅነሰሀሳቦች ላይ
በመመርኮዝ ተግባራዊ የሚደረግ የኢንዲኬተር አይነት ነው።
1. ወደላይ እየተጓዘ ባለ የገበያ ትሬንድ ላይ የገበያ ዋጋው ከዚህ በፊት ከነበረው የካንድል መዝጊያ ዋጋ እኩል አሊያም
በላይ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል።
2. ወደታች እየተጓዘ ባለ የገበያ ትሬንድ ላይ የገበያ ዋጋው ከዚህ በፊት ከነበረው የካንድል መዝጊያ ዋጋ እኩል አሊያም
በታች ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል።
ይህ የእርድርድረት ዥዋዥዌ [Momentum Oscillator] ለመጀመሪያ ጊዜ በስራ ላይ የዋለው በታዋቂው የፋይናንስ ሊቅ ጆርጅ
ሌን አማካኝነት በ1950ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ነበር። ይኸው የዚህ እሳቤ ቀማሪ የስቶካስቲክ ኢንዲኬተር በዋናነት የገበያ ዋጋ
ሀይልን የሚለካልን የኢንዲኬተር አይነት እንደሆነ የሚገልፅ ሲሆን ልክ አንድ ሮኬትን ወደላይ ተወንጮፍ በምንመለከተው
ወቅት በመሬት ስበት ሳቢያ አቅጣጫውን ወደምድር ከማዞሩ በፊት የሚሄድበት ፍጥነት እና ሀይል እየቀነሰ መሄዱ የማይቀር
እንዳልሆነው ሁሉ የገበያ ዋጋ እንቅስቃሴ ሀይል[momentum] አቅጣጫም ሆነ ሀይል ከገበያ ዋጋው በፊት ለውጥን ማሳየቱ
አይቀርም የሚል እሳቤንም ጨምሮ ያብራራል።
የስቶካስቲክ ኦሲሌተር ኢንዲኬተር አሁን ያለውን የገበያ ትሬንድ ቀጣይነት አስቀድሞ ለመገመት የስኬል ልኬትን በመጠቀም
በሁለት የካንድል ስቲክ መዝጊያ ዋጋ ልዩነቶች ላይ ያለውን የዲግሪ ለውጥ የሚለካለን የኢንዲኬተር አይነት ነው። በእርግጥም
በዚህም ኢንዲኬተር ላይ ያሉን ሁለት መስመሮች ልክ እንደMACD ኢንዲኬተራችን በእሳቤ ደረጃ በፍጥናቸው አንደኛው ፈጣን
እና አንደኛው ቀርፈፍ ያሉ ሆነው እናገኛቸዋለን።
ሲሆን የስቶካስቶክ መስመሮቹ በሰማያዊ ነጠብጣብ ከተሰመረው የ20 የስቶካስቲክ ስኬል በታች በሚሆኑበት ወቅት በገበያው
ውስጥ ያሉ ሻጮች እየተዳከሙ ገዢዎቹ ደግሞ በተራቸው አቅማቸው ጎልብቶ የገበያውን ዋጋ የማውጣት እድላቸው የሰፋ
መሆኑን የሚያመላክተን ሆኖ እናገኘዋለን። ከላይ በምሳሌነት በቀረበው ምስል ላይ እንደተመለከተውም የስቶካስቲክ
መስመሮቹ ከ80 ስኬል በላይ ሲሆኑ የካንድል ስቲኮቹ አካሄድም ከጠንካራ uptrend ወደተለሳለሰ የገበያ እርማት ሲጓዝ
እንዲሁም የስቶካስቲክ መስመሮቹ ከ20 ስኬል በታች ሲሆኑ ደግሞ የካንድል ስቲኮቹ እንቅስቃሴ ቡሊሽ ፓተርን ከመመስረት
ጀርሞ በጠንካራ አካሄድ ወደላይ ጉዟቸውን ሲያደርጉ መመልከት ይቻለናል። ከዚህ በመነሳትም ይህንን ኢንዲኬተር
በመጠቀሙ ሁነት ልናደረገው የሚገባው የግብይት ውሳኔ በዋናነት በመስመሮቹ መቼት ላይ ያተኮረ ሲሆን ይህም ማለት
ገበያው ከልክ በላይ ሽያጭ የተደረገበትን ሁነት ኢንዲኬተሩ በሚያመላክተን ጊዜ የግዢ ትዕዛዝ በመፈፀም እንዲሁም ገበያው
ከልክ በላይ ግዢ እንደተደረገበት ኢንዲኬተሩ በሚያመላክተን ወቅት ደግሞ የሽያጭ ትዕዛዝ በመፈፀም ትርፍን ልናገኝ
የሚቻለን ይሆናል ማለት ነው።
ከዚህ በላይ የቀረበውን የካንድል ስቲክ ቻርት በመመልከት ኢንዲኬተራችን ገበያው ከልክ በላይ ግዢ እየተፈፀመበት ስለመሆኑ
[Overbought] የሚያሳይበትን ባህሪያት ለተወሰኑ ጊዜያት ሲያሳየን እንደቆየ በምስሉ በቀይ ቀለም በተጠቆረው ቦታ ላይ
መመልከት ይቻለናል። ከዚህ መረጃ በመነሳት የገበያ ዋጋው ወዴት አቅጣጫ የሚሄድ ይመስላችኋል?
መልሳችሁ ዋጋው የመውረድ እድሉ የሰፋ ነው የሚል ከነበረ ትክክለኛውን ምላሽ አግኝታችሁታል። ገበያው ከልክ በላይ የግዢ
ትዕዛዞች ረዘም ላለ ጊዜ የተፈፀሙበት በመሆኑ መዳከሙ የማይቀር እና የገበያ ዋጋ አካሄድ አቅጣጫ ለውጥ ማምጣቱ
የማይቀር ነበር። በዚህ ምዕራፍ ጅማሬ ላይ በዋናነት ለማሳየት የተሞከረው ምሰረታዊው የስቶካስቲክ ኢንዲኬተር ጥቅም እና
አተገባበርም ይህን ይመስላል።
የተለያዩ የፎሬክስ እና የክሪፕቶ ከረንሲ ትሬደሮች የስቶካስቲክ ኢንዲኬተርን በተለያየ መንገድ ሲጠቀሙት ይስተዋላል። ይሁንና
የኢንዲኬተሩ ዋነኛ አላማ እና ጥቅም በገበያው ውስጥ ባለው የዋጋ እንቅስቃሴ ገበያው ከልክ በላይ ግዢ አልያም ሽያጭ
የተፈፀመባቸውን የዋጋ እርከኖች እና የገበያ ቅፅበቶች አስቀድመን እንድንመለከት ነው። ተያይዞም በምሳሌዎቻችን ላይ
በማስተዋል ለተመለከተው የስቶካስቲክ መስመሮቻችን ከ20 ስኬል በታች ወይም ከ80 ስኬል በላይ ላለተወሰነ ጊዜ ሊዘልቅ
እንደሚችል ማየት ይቻላል። በዚህም ኢንዲኬተሩ ከልክ በላይ የመገዛት ሁነትን[Overbought] ስላሳየ ብቻ መሸጥ አልያማ
ከልክ በላይ የመሸጥ [Oversold] ባህሪን ስላሳየ ብቻ መግዛት አለብን ማለት እንዳልሆነ በደማቁ ተሰምሮበት ሊታለፍ የሚገባ
ጉዳይ ነው። በስተመጨረሻም በሂደት በቻርት ላይ በሚኖር ልምምድ እና ከራሳችን ስትራቴጂዎች ጋር የሚሄዱ የታይም ፍሬም
እና የግብይት አካሄዶችን ከስቶካስቲክ ኢንዲኬተሩ ጋር ተጣምረው ትርፋማ የሚያረጉበትን ሁነት የተለያዩ ሁነቶች ከግምት
በማስገባት እና የግብትይ ሙከራዎች [back-test] በማድረግ የተሻለ ትርፍ የምናመጣበትን ሁነት መፍጠር የምኖርብን
ይሆናል ማለት ነው።
ለተጨማሪ የክሪፕቶከረንሲ እና ፎሬክስ ግብይት እንዲሁም የብሎክቼይን ቴክኖሎጂ የአማርኛ መማሪያ ግብአቶች
ቀጣይ በተቀመጡት ሊንክ ላይ የኮሚዩኒቲያችንን አጠቃላይ የማህበራዊ ሚዲያ መገኛዎች በአንድ ላይ ማግኘት
ይችላሉ። https://www.linktr.ee/cryptotalket