Download as docx, pdf, or txt
Download as docx, pdf, or txt
You are on page 1of 14

በእንተ መስቀል

የመስቀሉ ሚስጥር በመጽሐፍ ቅዱስና የሃይማኖት አባቶች ፦


"ቅዱስ መስቀል ስንል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን ከሞት ኃጢአት ለማዳን በቀራንዮ የተሰቀለበት የተመሳቀለ ዕፁ
ማለታቸው ነው። መስቀል ለክርስቲያኖች የሕይወትና የደኅንነት ምልክት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን
ከኃጢአትና ከሞት በቀራኒዮ የተስቀለበትን ዕፀ መስቀል ከሌላው መስቀል የሚለየው ቅዱስ መሆኑ ነው። ይህም መስቀል ቅዱስ
መስቀል ይባላል፡፡ ደኅንነት አግኝተንበታልና ስለዚህ የደኅንነት ምልክት ነው። የነጻነታችን አርማ አድርጎ መመኪያችን መዳኛችን
ትምክህታችን አድርገን እንይዘዋለን። ነገር ግን ከዚያ በፊት መስቀል የእርግማን ምልክት የሆነ የወንጀለኞች መቀጫ ነበር።
«በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነው" ዘዳግም. 21፥23 በእንጨት የተሰቀለ ኹሉ የተረገመ ነው ተብሎ
ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጀን። ገላትያ. 2፥13
መስቀል የክርስቶስ ምልክት ነው። ጌታችን ስለ ዓለም መጨረሻ ሲናገር " የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል" ብሎአል ። የሰው
ልጅ ምልክት የተባለ መስቀል መሆኑን ዮሐንስ አፈወርቅ እና ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም አስተምረዋል። ማቴዎስ. 24፥30
ጌታችን በትምህርቱ መስቀልን ከክርስቲያኖች ሕይወትና ጉዞ ጋር አያይዞ አስተምሯል
”ማንም ሊከተለኝ የሚወድደኝ ቢኖር መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ "ማቴዎስ 16፥24
“ማንም መስቀሉን ተከትሎ በኃላዬ የማይወጣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም ሉቃስ 14፥26"
ጌታችን ከሙታን በተነሣ ጊዜ በመቃብሩ አካባቢ የነበሩት መላእክት ጌታችንን የጠሩት በመስቀሉ ነው፡፡
"እናንተስ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁ "ማቴዎስ 28፥5
ሐዋርያትም ጌታችንን በመስቀል ይገልጡት ነበር ፡፡ " ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበት ከጌታችን መስቀል
በቀር ሌላ ትምክሕት ከእኔ ይራቅ።" ገላትያ 6፥14
በመስቀል ስናማትብ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ እንመሰክራለን።
በኒቂያ ጉባኤ በ፫፻፳፭ ዓ.ም በተወሰነድ መሠረት ከግንባራችን ወደ ሆዳችን ስናማትብ የጌታችንን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል
ማርያም መወለዱን÷ ከግራ ወደ ቀኝ ስናማትብ ደግሞ ከሲኦል ወደ ገነት እኛን ማስገባቱን እንመሰክራለን።
" በእንጨት ምክንያት ለዕዳ ተሰጠን በእንጨትም ምክንያትም ከዕዳችን ነፃ ሆንን" በማለት ቅዱስ ሄሬኔዎስ እንዳስተማረው
መስቀል ከዕዳ ነጻ የሆንበት ነው።
በብሉይ ኪዳን ሕዝበ እስራኤል ከአማሌቃዎያን ጋር በሚዋጉ ጊዜ ሙሴ እጁን ዘርግቶ በመስቀል አምሳል ቆሞ ነበር ሙሴ እጁን
ባነሳ ጊዜ እስራኤል ድል ያደርግ ነበር። መስቀል በሙሴ እጅ በምሳሌው ይህንን ያህል ኃይል ከነበረው በክርስቶስ ደም ከተዋጀ
በኋላ አማናዊውማ እንዴት ታላቅ የሆነ ኃይል አያደርግ።
ዘጸአት. 17፥16
"እግዚአብሔር በከተማይቱ በኢየሩሳሌ መካከል እለፍ።በመካከልዋም ስለተሰራው ርኩሰት ኹሉ በሚያለቅሱና በሚተክዙ ሰዎች
ግንባር ላይ ምልክት ፃፍ አለው። በአማርኛ "ምልክት"
የተባለው በግሪኩ "tau" የተባለው ምልክት ነው። ይህም በእንጊሊዝኛው የ "ተ" ቅርፅ ያለው ምልክት ነው።ሕዝ. 9፥4
ጣት የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው። በሉቃስ ወንጌል 11 ፥ 20 ላይ "እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንኩ"
ያለውን የማቴዎስ ወንጌል ግን በእግዚአብሔር መንፈስ ብሎታል ፡፡ ማቴዎስ 12፥28 እኛም በጣታችን ስናማትብ በመንፈስ ቅዱስ
ኃይል ሰይጣንን ድል ለመንሳት ማማተባችን ነው።
አስቀድሞ ልብ አምላክ ዳዊት "ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩ ምልክትን ሰጣቸው" መዝሙር 59፥4 ብሎ እንደተናገረለት
ከዲያብሎስ ቀስት የምናመልጥበት ምልክት መስቀል ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ቅዱስ ደሙ ሰላምን አወጀ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ታላቅ ምስጢር
ሲናገር
"በመስቀሉ ደም ሰላምን አደረገ በሰማያትም በምድርም ላሉት እርቅን ሰላምን አደረገላቸው " ቆላ. 1፥19 ጌታችን በመስቀል
ጠላታችን ዲያብሎስን እንደ ገደለ ማለት እንዳሸነፈና ተለያይተው የነበሩትን ሕዝብና አሕዛብን አንድ ማድረጉን አስመልክቶ
በሌላው መልክቱ ሲናገር፦
ኤፌሶን 2፥13-18 " አሁን ግን ቀድሞ እርቃችሁ የነበራችሁ እናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ሆናችሁ የክርስቶስ ደም ቀረባችሁ፡ እርሱ
ክርስቶስ ሰላማችን ነው" እርሱ ኹሉን ያዋሐደ የትዕዛዙን ሕግ ሕዝቡንና አሕዛብ የመባል ትእዛዝ ሽሮ በመካከል የነበረውን የጥል
ግድግዳ በሥጋው አፈረሰ።
ይኸው ከኹለታችሁ አንድ አዲስ ሰውን ይፈጥር ዘንድና ሰላምን ያደርግ ዘንድ ጥልን በመስቀሉ ገደለ። በእርሱም ኹለታችሁን
በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀን መጥቶም እርቃችሁ ለነበራችሁትና ቀርበውም ለነበሩትም ሰላምን ሰጣቸው በማለት
ነው።
ከዚህ በላይ እንደተመለከትነው ጌታችን ስለ ዓለሙ ቤዛ የተሰዋበት ቅዱስ መስቀል ክቡር ነው። ጠላት ዲያብሎስን ያሸነፈበት
ቅዱስ መስቀል ክቡር ነው። ደሙ በከበረው ቅዱስ መስቀል ለምድራውያን ለሰማያውያን ሰላምን አውጇል። ሐዋርያው እንዳለው
ቅዱስ መስቀል የሰላም የድኅነት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ዙፋን ነው። "የእግዚአብሔር አብ ፀጋ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው
ኸለሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ይልቅ በጥቂቱ አንሶ በሞት አንሶ የነበረውን ከሞት የተነሣ የምስጋናን ዘውድ አክሊል
ስብሐት ጭኖ ደፍቶ እነሆ እናየዋለን"ዕብራውያን 2፥8-9
ለዚህ ቅዱስ መስቀል ንጉሥ ስብሐት ክርስቶስ ምሥጋናን ንጉሥ ክርስቶስ የተሰዋበት ክርስቶስ አምላካችን በቅዱስ ደሙ
ያከበረውና መለኮታዊ ደሙም የፈሰሰበት ስለሆነ በአማን በእውነት ክቡር በእውነት ቅዱስ ነው። በመሆኑም በእውነት
ክርስቶሳዊያን የሆን ኹሉ በጌታችንና በክቡር መስቀሉ እንመካለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስተምር ገላትያ 6፥14
“እኔስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ" ብሎአል።
1 ኛ. ጴጥሮስ 2፥24-25 "ለኃጢአት ሞተን ለፅድቅ እንድንኖር፣ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤
በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ"
ቆላስይስ. 2፥14 "በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትዕዛዝ የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው ። እርሱንም በመስቀል
ጠርቆ በመንገድ አስወግዶታል"
ኤፌሶን 2፤16 "ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ኹለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቀን ዘንድ ነው"
ቆላስይስ 1፥20.....በመስቀሉ ባፈሰሰው ደመም ሰላምን አደረገ"
1 ኛ. ቆሮ ፣ "የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ማኝነት፣ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና ''
ፊልጶስ 3፥18 "ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና ፣ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ ፣ አሁንም እንኳን
እላለሁ"
"የመስቀሉ ቃል ለሚጠፋት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና " 1 ኛ ቆሮ. 1÷18 "ብዙዎች ለክርስቶስ
መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሣሉና ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ እላችኹአለኹ አሁንም አሁንም እንኳን እያለቀሥኩ እላለው" ፊሊጵ.
3÷18
"እነዚኽ ኹሉ አምነው ሞቱ የተሠጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሣለሙት" ዕብ. 11÷13 ፡፡
ዳን. 6÷10 ማቴ. 10÷ 38 ላይ "የሚወደኝ ቢኖር መስቀሌን ተሸክሞ ይከተለኝ" ነው ያለው፡፡
ለእኛ ኃይላችን እንደሆነ
የመስቀል ምልክት እንደተሰጠንና በሥላሴ ስም በመማተብ ሰይጣንን
ድል ማድረግ እንደምንችል አባታችን ቅዱስ ዳዊት እንዲህ ይለናል ፦
መዝ.ምዕ. 60÷4 "ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው።...በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን እርሱ
የሚያስጨንቁንን
ያዋርዳቸዋልና"
መስቀል በሰማይ
ቅዱሳን መላእክት በሰማይ ትእምርተ መስቀልን በመስራት እግዚአብሔርን
ሲያመሰግኑ ነብይ ኢሳያስ ተመልክቷል። በሰማይ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ በመቅደሱ ያሉ ቅዱሳን ሱራፌል መላእክት
ሲያመሰግኑ ትእምርተ መስቀል እንደሰሩ ይመለከታቸዋል።
" ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ
ነበረው ፤ በኹለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በኹለቱም ክንፍ እግሮቹን
ይሸፍን ነበር ፥ በኹለቱም ክንፍ ይበር ነበር።" ትንቢተ ኢሳይያስ 6:2
ነብይ ሙሴ
ሙሴ ኹለት እጆቹን በመዘርጋት የመስቀል ምልክት በመስራት
እግዚአብሔር በሙሴ ላይ አድሮ አማሌቅን ድል እንዳደረገ የሙሴ እጅ
መዘርጋት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሆን ነው ፣ ኢያሱ
አማሌቅን ድል ማድረጉ ክርስትያኖች በመስቀል ኃይል የሰይጣን ሥራ ድል
እንደሚያደርጉ ያጠይቃል፡፡ ዘጸአት 17÷8 "አማሌቅም መጥቶ ከእስራኤል ጋር በራፊድም ተዋጋ ፡ ሙሴም ኢያሱን ጕልማሶችን
ምረጥልን፥ ወጥተህም ከአማሌቅ ጋር ተዋጋ፤ እኔ ነገ የእግዚአብሔርን በትር በእጄ ይዤ በኮረብታው ራስ ላይ እቆማለሁ አለው፡
ኢያሱም ሙሴ እንዳለው አደረገ፥ ከአማሌቅም ጋር ተዋጋ፤ ሙሴና አሮንም ሖርም ወደ ኮረብታው ራስ ወጡ፡እንዲህም ሆነ፤
ሙሴ እጁን ባነሣ ጊዜ እስራኤል ድል ያደርግ ነበር፤ እጁንም ባወረደ ጊዜ አማሌቅ ድል ያደርግ ነበር፡የሙሴ እጆች ግን ከብደው
ነበር፤ ድንጋይም ወሰዱ፥ በበታቹም አኖሩ፥ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሖርም አንዱ በዚህ አንዱ በዚያ ሆነው እጆቹን ይደግፉ
ነበር፤ ፀሐይም እስክትገባ ድረስ እጆቹ ጠነከሩ፡ኢያሱም አማሌቅንና ሕዝቡን በሰይፍ ስለት አሸነፈ"ይላል፡፡
ቅዱስ ያዕቆብ
ቅዱሳን አባቶቻችን ሲባርኩ ኹለት እጃቸውን በመዘርጋት በመስቀል
አምሳል ነበር። ለምሳሌ አባታችን ቅዱስ ያዕቆብ የዮሴፍ ልጆቹን ኤፍሬምና ምናሴ ሲባርክ እጆቹን በመዘርጋት በመስቀል አምሳል
ነበር።
አባታችን ቅዱስ ያዕቆብ በዘንጎ ጫፍ ተጠግቶ መስገዱ ለመስቀል ስግደት እንደሚገባው ለእግዚአብሔር መስገዱን ያስረዳናል።
እግዚአብሔር ኃይሉን የሚገልጥበት ፡ኃይሉ ያረፈበት መስቀል ስለሆነ በመስቀል አድሮ ኃይሉን ይገልጣልና ።ዘፍጥ. 48÷16
"ከክፉ ነገር ኹሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፤ ስሜም የአባቶቼ ፡ የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ
ይጠራ፤ በምድርም መካከል ይብዙ፡ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ጭኖ ባየ ጊዜ አሳዘነው፤ የአባቱንም እጅ በምናሴ
ራስ ላይ ይጭነው ዘንድ ከኤፍሬም ራስ ላይ አነሣው፡ዮሴፍም አባቱን አባቴ ሆይ እንዲህ አይደለም፥ በኵሩ ይህ ነውና፤ ቀኝህን
በራሱ ላይ አድርግ አለው" ይላል፡፡
"ያዕቆብ ሲሞት በእምነት የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን ባረካቸው፥
በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ።"ወደ ዕብራውያን 11:21
እዚህ ላይ መናፍቃን ስግደት ለእግዚአብሔር ብቻ ነው የሚለው ኢመፅሐፍ ቅዱሳዊ መፈክራቸው ውድቅ ይሆንባቸዋል ዳሩ ግን
መናፍቃን አንድ ቀን ቢሆንም እንኳን ለእግዚአብሔር ሰግደው አያውቁም።
ስለዚህ መስቀልን እንደ አባታችን ቅዱስ ያዕቆብ በቀደመው ዘመን
እንዳሰበው እኛም በመስቀሉ ለእግዚአብሔር እየሰገድን ጠሥጋው ተቆርሶበታል ደሙ ፈስሶበታልና መስቀሉን አክብረን ለመስቀሉ
የጸጋ ስግደት እንሰግድለታለን፡፡
አባታችን ቅዱስ ዳዊት በመዝ. 131:7
ላይ "ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን " ስላለ መድኀኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ለተሰቀለበት
መስቀልማ እንዴታ አንሰግድ እንሰግዳለን እንጂ ።
ቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ
"ትእምርተ መስቀል(የመስቀል ምሳሌ) በኹሉም ፍጥረት ዘንድ ትገኛለች ፤ ፀሐይ በመስቀል አምሳል ብርሃኗን ካልዘረጋች ልታበራ
አትችልም፡ ጨረቃም እንደዚኹ ፡ የሰማይ ወፎችም ክንፉን በመስቀል አምሳል ካልዘረጋች ለመብረር አትችልም" መጽ.ግብረ
ሕማማት ዘዐርብ ገጽ ፫፻፸፩ - ፫፻፸፪፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
"ለመስቀል ስግደት ማለት የአክብሮት ስግደት ይገባል ፤ ይህ መስቀል ነገሥታት መኳንንት መሰፍንት የሚያከብሩት ብፁዕና
ምስጉን ነው ፤ ይህ መስቀል ለሰው ልጅ ኹሉ ማፅኛ መጠንከሪያ ነው፡ በእርሱም አጋንንት ኹሉ ይሸሻሉ ፤ ርጉም ሰይጣንም
ይደነግጣል ፤ እሱን መላእክት ያከብሩታል ፤ ሰማዕታትም ያመሰግኑታል ፤ ሐዋርያትም ዝናውን ይናገሩበታል ፤ መድኃኒአለም
በእርሱ ተሰቅሎአልና ፣ ቤተ ክርስቲያን
ትሸልመዋለች።"ግብረ ሕማማት ገፅ ፸
"ወንድሞች ሆይ ከአሁን ጀምሮ ሁልጊዜ የጌታችን የአምላካችንን
የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ማሰብ አናቋርጥም አናስታጉልም።
መስቀል የመልካም ነገር ኹሉ ራስ ፤ የህይወትና የመድኃኒት መጀመሪያ ፤ የድል አክሊል ነውና ፤ ምክንያቱም መስቀል ከክፉ
ሰይጣን ጥቃት
የምንድንበት ምልክታችን መዳኛችን ነውና። ስለዚህም በመስቀል
ፊታችንን ማማተብ ፣ የመስቀል መስል በዕቃዎቻችን በሰብላችን ማድረግ
ይገባናል ፤ ልባችንም በመስቀል በማማተብ ከጠላት ከሰይጣን
እንጠብቃለን " ግብረ ሕማማት ዘዓርብ ገጽ ፫፻፶፩ - ፫፻፶፪
አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለን ለመስቀል ፦
❖ ምስጋና እንደሚገባው÷
❖የፀጋ ስግደት እንደሚገባው÷
❖ ክብር እንደሚገባው÷
❖ኹልጊዜ ማሰብ እንዳለብን÷
❖መስበክ እንዳለብን÷
❖ መሳለም እንዳለብን ...ነግሮናል።
አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለን መስቀል ፦
❖ ለእኛ ማፀኛመጠናከሪያ ነው÷
❖ አጋንንት ያሸሻል÷
❖ ለሰይጣን ያስደነግጣል÷
❖ የመልካም ነገር ኹሉ ራስ ነው÷
❖ የህይወትና የመድኃኒት መጀመሪያ ነው÷
❖ የድል አክሊል ነው÷
❖ ከክፉ ሰይጣን ጥቃት የምንድንበት ምልክታችን መዳኛችን ነው÷
❖በአንገታችን ላይ ማሰር እንዳለብን..
. አስተምሮናል።
የመስቀል ፍቅር ለማይባቸው መፅሐፍ ቅዱስ ምን ይላል ፦
መጀመሪያ መናፍቃን መስቀልን የማይወዱት የማያከብሩ የማያመሰግኑ
የማይሰግዱለት የሚንቁት ምክንያት ምንድነው? ስንል መልሱ ፦ በ፲፮ኛው ክፍለ ዘመን የሪፎርሜሽን የተሃድሶ እንቅስቃሴ
የአነሳሳው በአብዛኛው የቅዱሳን ሥዕሎችን ፣ ታቦት ፣ የቅዱስ መስቀልን ፣ ቅዱሳት መፃህፍት ፣ ቅዱሳን ሰዎች ፣ ቅዱሳን መላእክት
፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና
ሌሎች አለመቀበል መንፈስ ስለነበረ ነው ። ምክንያቱም ይኸውም ማርቲን ሉተር ከካቶሊኩ ሲወጣ ወደ ፺፰ ነጥቦች አምጥቶ
ሲያመጣ የካቶሊክ እምነት የተቃወመ መስሎት አብዛኛውን የመጽሐፍ ቅዱስንም ትምህርት ተቃውሞ ስለነበረ ፕሮቴስታንቶች
ደሞ የሉተር ተከታዮች ስለሆኑ የፕሮቴስታንት እምነት በሉተር ስለተመሰረተ ነው መናፍቃን ሊያከብሩት ያልቻሉት።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መስቀል ጠላቶች ለሆኑት መናፍቃን እንደዚህ ይላል ፦
" የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ
አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?"ወደ ገላትያ ሰዎች 3:1፡ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች ምዕ. 3÷18 "ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ
ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው
አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው" ይለናል፡፡ ዳግመኛም "የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት
ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።"1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1:18
"ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት" ዕብ. 11፡13-14 ቅዱስ ጳውሎስ በብሉይ ኪዳን የነበሩ አበው በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው
በረድኤቱ ተጎብኝተው ገና ወደ ፊት በዘመነ ሐዲስ ሊደረግ ሊፈጸም ያለውን የማዳን ሥራ ድኅነት የሚፈጸምበትንም መንገድ
በእምነት መነጽርነት ከሩቅ ሆነው ጥንት በዘመነ ፍዳ በዘመነ ኩነኔ) እንዳዩ እንደተሳለሙትም ሲነግራቸው ይህን አለ፡፡ የማዳኑ
ሥራ ሲወሳ ነገረ መስቀሉ ይወሳል ነገረ ድኅነት ከነገረ መስቀሉ ለይቶ ማየት ማሰብም አይቻልም፡፡ በማኅፀነ ድንግል ማርያም
የተጀመረው የማዳን ሥራ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ተፈጽሟልና፡፡ ስለሆነም በብሉይ ኪዳን የነበሩ ቅዱሳን አበው መስቀሉን
በምሳሌ
ገልጸዋል፡፡ አማናዊውን ገና ሳያገኙ በምሳሌው ባርከዋል ተባርክዋል ድልም አድርገዋል፡፡ ቅዱስ ዮሴፍ አባቱ ያዕቆብን ለመጠየቅ
ወደ ከነአን በወረደ ጊዜ ቅዱስ ያዕቆብ የልጅ ልጆቹን አይቶ በመስቀል ምልክት እንዴት እንደባረካቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሲነግረን
“…ዮሴፍም ኹለቱን ልጆቹን ወስዳ ኤፍሬምንም በቀኙ በእስራኤል ግራ ምናሴንም በግራው በእስራኤል /በያዕቆብ ቀኝ አደረገው
ወደ እርሱም አቀረባቸው እስራኤልም /ያዕቆብም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም እራስ ላይ
አኖረው እርሱም ታናሽ ነበር፡፡ ግራውንም ለምናሴ እራሱ ላይ አኖረ እጆቹንም አስተላለፈ…” ይላል ዘፍ. 48፡13-14 ቅዱስ
ያዕቆብ ለምን እጆቹን አመሳቀወሎ ልጆቹን ባረካቸውን በአጋጣሚ ነውን በመጽሐፍ ቅዱስ በአጋጣሚ የሆነ የተደረገ ነገር አለን?
በእስራኤል ዘሥጋ ላይ አማሌቅ በጠላትነት በተነሳባቸው ጊዜ እንዲህ ሆነ ሙሴ በኮረብታው እራስ ላይ ቆመ
እጁን ግንዱን ባነሣ ጊዜ እስራኤላውያን ድል ያደርጉ ነበር እጁንም ባወረደ ጊዜ አማሌቅ ድል ያደርግ ነበር ዘፍ. 17፡11 እስቲ
ይህንን ፡፡ ይኽን ታሪክ በእምነት ሆነን እናስተውለው ሙሴ በመስቀል ምልክት ሲያደርግ እስራኤል ድል ማድረጋቸው ሙሴ
እጆቹን ሲያወርድ መሸነፋቸው ለምን ይሆን ለሐዋርያው ለነገር ኹሉ ጥላ አለው፡፡ ዕብ. 8፡5 ብሎ እንደተናገረ ሙሴ የክርስቶስ፣
እስራኤል የምዕመናን፣ አማሌቅ የዲያብሎ ምሳሌ ሲሆኑ ሙሴ በመስቀል ምልክት እስራኤል ድል እንዲነሱ እንዳደረጋቸው
ምዕመናንም በመስቀል ምልክት አጋንንትን ድል የመንሣታቸው ምሳሌ ነው፡፡ የቅዱሳን አምላክ ከቅዱስ መስቀሉ ረድኤት
በረከት ይክፈለን፡፡
"እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም፡ ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር" እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር የነበረ
የዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ በማዕከለ ምድር ማለት በቀራንዮ ኢየሩሳሌም ተሰቅሎ ባፈሰሰው ደሙ መድኃኒትን አደረገ ይላል ነቢየ
እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት መዝ. 73፡12
ይህ በመጋቢትና በጥቅምት ፳፯ ቀን በየዓመቱ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት የምናከብረው በዓላችን ዓመተ ፍዳው፤ ዓመተ
ኲነኔው አክትሞ የሰው ዘር የሆነው ሁሉ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከኃጢአት ወደ ስርየት፣ ከሲኦል ወደገነት፣ የተመለሰበትና
የተሸጋገረበት ዕለት መሆኑን ለማዘከር ነው፡፡ አዳም በሥላሴ አርአያና አምሳል ተፈጥሮ ጸጋ እግዚአብሔርን ተጎናጽፎ ነጻ የኅሊና
ፈቃድ ያለው ሰው ኹሉ ገነትን ያህል ቦታ ይዞ ሥዩመ እግዚአብሔር፡ ነቢየ እግዚአብሔር፣ ካህነ እግዚአብሔር ሁኖ ለሰባት
ዓመታት በስነ ሥርዓት በገነት ይኖር ነበር፣ ይሁንና "እግዚአብሔር ያደረገውን ኹሉ አየ፤ እነሆም እጅግ መልካም ሆነ አየ" ዘፍ.
1፡31 ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደምንረዳው እግዚአብሔር አምላካችን በስድስቱ ቀናት የፈጠረው ኹሉ መልካም ሲሆን
በተለይም በሥላሴ አርአያና አምሳል ለተፈጠረው ሰው የሕይወት እስትንፋስን ሰጥቶ በገነት በሕያውነት እንዲኖር ያስቀመጠው
የከበረ ክቡር ፍጡር ነበር፡፡ "ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ ወተመሰሎሙ" ይላል፡፡ ነቢየ
እግዚአብሔር ዳዊት እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የስሙ ቀዳሽ የክብሩ ወራሽ አድርጎ ቢፈጥረውና የጸጋ ገዥ ቢያደርገው
ያልተሰጠውን የባሕርይ አምላክነትን በመፈለጉ የገዥና የተገዥ፣ የፈጣሪና የፍጡር መለያ የሆነውን ትእዛዘ እግዚአብሔርን
በመጣሱ በዚህ ምክንያት ሞተ ሥጋ፣ ሞተ ነፍስ ተፈረደበት፡ከክብሩ ተዋርዶ ከገነት እንዲወጣ ተደረገ፡፡ተመልሶ ወደ ገነት ገብቶ
ተጨማሪ ኃጢአትን እንዳይሠራም ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን ሜሎስን
በእጃቸው የያዙ ኪሩቤልን በኤደን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ ይላል የሙሴ መጽሐፍ፡፡ ዘፍ. 3፡22-24
አዳም ሳይቸገር በጠላት ከእንቱ ስብከት እንደ እግዚአብሔር ለመሆን ክፉውንና ደጉንም ፈጥኖ ለማወቅ ቸኩሎ ትእዛዘ
እግዚአብሔርን በማፍረሱ ወደቀ፣ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ፡፡ በሰው ሕይወት ላይ አሳፋሪ፣ አስፈሪና አስነዋሪ ታሪክ ፈጸመ፡፡ አዳም
እግዚአብሔር አታድርግ ያለውን የአምላኩን ትእዛዝ በማፍረስ የሞተ ሞት ተፈረደበት፡፡ ከዚህ አሳፋሪና አስፈሪ ታሪክ በመነሣት
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስለሞት ማሰብ ለማንም ሰው ቢሆን ቀላል ነገር አልሆነም፡፡ ያ ሰው የኖረው ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ የኹሉ
እድል ፈንታ በሆነበት ጊዜ ነበርና ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች አንድ ጊዜ መሞተ ከእርሱ በኋላ ፍርድ ተመደበባቸው ይላል፡፡
ዕብ. 9፡27
ነቢዩ ሕዝቅኤልም "እነሆ ነፍሳት ኹሉ የእኔ ናቸው፣ የአባት ነፍስ የእኔ እንደሆነች፣ ደግሞ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት፣ ኃጢአት
የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች" ሕዝ. 18፡4 በማለት የዚህን ማስጠንቀቂያ፣ ኃይለኛነትና ጥብቅነት ያሳያል፡፡ በቀል የእኔ ነው
እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና ደግሞም ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል፣ በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅም
የሚያስፈራ ነው ያላል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዕብ. 10፡30-31
ስለዚህ ሞት የኃጢአት ዋጋ ሆኖ በኃጢአት ምክንያት የመጣ ቢሆንም በኃጢአት ላይ የተሰጠ የመጨረሻ ፍርድ /ቅጣት/
ባለመሆኑ ከሞት በኋላ ሌላ ፍርድ የሚጠበቀን መሆኑን ያስተምረናል፡፡ ይሁንና ቀዳማዊ አዳም በስህተቱ ተጸጽቶ በማዘኑ፣
በማልቀሱና ንስሐ በመግባቱ ለቸርነቱ ወሰን የሌለው አምላክ ንስሐውን ተቀብሎ የተስፋ ቃል ሰጠው፡፡ የተሰጠውም የተስፋ ቃል
"አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ሥጋዬን ቆርሼ ደሜን አፍስሼ አድንኅለሁ" የሚል ነበር፡፡ ይህ
የተስፋ ቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ትንቢት ሲነገር ሱባኤ ሲቆጠር ኖሮ አምስት ሺህ አምስት መቶ የተስፋው ዘመን
ሲፈጸም የተናገረውን የማይረሳ፣ የሰጠውን ተስፋ የማይነሣ እግዚአብሔር "ክርስቶስኒ መጽአ በዕድሜሁ ይሙት በእንተ ኃጢአትነ
እንዘ ኃጥአን ንሕነ" ሮሜ. 5፡6 ይላል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ጊዜው ሲደርስ ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጅ ኃጢአት ሊሞት መጣ፣ ሰው ሆነ በሥጋም ተወለደ፣ በተወለደ በ፴ ዘመኑ በእደ
ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ፣ ዕለቱን ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ዓርባ መዓልትና ዓርባ ሌሊት ጾመ፣ በሰይጣን ተፈተነ፣
ፈታኙ ሰይጣንም ባቀረበው ፈተና ድል ተመታ፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራውን የጀመረው በጥምቀት፣ በጾም በጸሎት በትምህርት በተአምራት ሲሆን
ሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት በይሁዳ፣ በሰማርያና በገሊላ አውራጃዎች በቅድስት ሀገር እየተዘዋወረ ወንጌልን አስተማረ፡፡
ትምህርቱ እየሰፋና እየተዳረሰ ሲሔድ የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ለሕማም፣ ለሞት፣ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ተሰቀለ፣
በሥጋ ሞተ፣ ተቀበረ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ውሎና አድሮ ከሙታን ተለይቶ በመነሣት ሞትን ድል
አደረገ፡፡
ስለሞተ ÷ ነፍስና ሞተ ሥጋ ብዙ ተብሏል፣ እየተባለም ነው፣ እነዚህ ኹለቱም በመጀመሪያው ሰው፣ ሕግ ተላላፊነት በአንድ
ወቅት በሰው ሕይወት ላይ የደረሱ አሳዛኝ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ለማለት እንደሞከርነው በመጀመሪያው ሰው ሕግ
ተላላፊነት ሞተ ነፍስና ሞተ ሥጋ በዚህ አጋጣሚ ኹለቱም በዚያን ጊዜ ተያየዘው የመጡ ሲሆን ሞተ ነፍስ/ጥንተ አብሶ በ፴፬
ዓ.ም በማዕከለ ምድር ቀራንዮ በስግው ቃል ሞተ ሥጋ አክትሞለት ኹሉም የአዳም ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከኃጢአት ወደ
ስርየት፣ ከሲኦል ወደ ገነት በእምነት ተመልሷል፣ ይሁንና ሞተ ሥጋው የክርስቶስን ዳግም ምጽአትን ÷ ትንሣኤ ዘጉባኤን
የሚጠብቅ ኾኗል፡፡ በዚያን ጊዜ ሞተ ሥጋውም ያከትምለታል ፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሞት መደምሰሻ፣ የሰይጣን ድል መንሻ፣ የድኅነት ጋሻ ያደረገው መስቀል
በክርስትና ሕይወት የላቀ ክብርና ቦታ ያለው ሆነ፡፡ሰውን በስቅላት መቅጣት የተጀመረው የፋርስ ባቢሎን እንደነበረ በታሪክ
የሚታወቅ ሲሆን መስቀል ከዘመነ ሥጋዌ በፊት የወንጀለኞች፣ የኃጢአተኞችና የበደለኞች መቅጫ መሣሪያ መሆኑ የታወቀ ነበር፡፡
ጌታ በዚህ ዓለም በተገለጠበት ጊዜ በዓለም ግዛቱን አስፍቶና አስፋፍቶ የነበረው የሮሜው የቄሣሩ መንግሥት ይህን የስቅላት
አሠራር ልምድ ከፋርስ ባቢሎን ወርሶ ምንም ዓይነት ኃጢአት ሳይኖርበት በኃጢአተኞች ይሙት በቃ የተፈረደበት ጌታችን፣
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመሰቀል ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት ፍርድን ተሰጠ፡፡
በዚኹ መሠረትም ቅድስት ድንግል ማርያምን ከገሊላ አውራጃ ከናዝሬት ወደ ይሁዳ አውራጃ ወደ ዳዊት ከተማ ቤተ ልሔም
ምድረ ኤፍራታ የወሰዳት የሮማዊው የአውግስጦስ ቄሣር የሕዝብ ቆጠራ ትእዛዝ ነበር፡፡ ሉቃ. 2፡1-3
የሮሜ ዜግነት የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በሌላ ቦታ ያለ አግባብ የተፈረደበትን እንዲያይለት ወደ ሮሜው ቄሣር
ይግባኝ ቢልም ቄሣር ከጊዜ በኋላ የይሙት ፍርዱን አጽድቆ በሮማውያን አደባባ በሰይፍ እንዲገደል አድርጎታል፡፡ የሐዋ. 25፡11-
13
ከዚህ አንጻር የሮማውያን ሕግ አዋቂነትና አስከባሪነት ደካማ፣ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓትም ከኹሉም አቅጣጫ የተራቆተ
የግሪኮችም ፍልስፍና ከንቱ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሦስት ኃይላትም አቋማቸውን አጠናክረው
በኃይላቸው ተመክተው ለጊዜው የሚያሸንፉ መስለው ቢነሡም ከጊዜ በኋላ ኹሉም ፈርሰውና ወድመው ሲቀሩ ክርስቶስ ግን
በሚወዱትና በሚያፈቅሩት ተከታዮቹ ልብ ለዘለዓለም የማይፈርስ ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን መሥርቷል፡፡ ይህም ወንጌለ
መንግሥተ ሰማያት እስከዓለም ፍጻሜ ሲሰበክ ይኖራል፡፡
ከመጋቢት ፳፯ ቀን 34 ዓ.ም ጀምሮ መስቀል የነፃነት አዋጅ የተነገረበት ሰላማዊ ዙፋን ስለሆነ ለክርስቲያኖች ኹሉ የድልና
የአርነት፣ የፍቅርና የሰላም ምልክት ሆነ፡፡ከዘመነ ሰማዕታት በኋላ በዐራተኛው መቶ ዓመት የተነሣው የቢዘንታይን ንጉሠ ነገሥት
ታላቁ ቆስጠንጢኖስ "በዝንቱ ትእምርተ መስቀል ትመው ፀረከ "በሚል በብርሃን ቅርፅ ያየው መስቀል የድል ምልክት ሆኖ
ይኖራል፡፡ቀደም ሲል በተመሳሳይ እንደተጠቀሰው ሐዋርያት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ቃል መስቀል የእግዚአብሔር የማዳን
ኃይል የተገለፀበትና የሚገለፅበት መሣሪያ መሆኑን ያስረዳል፡፡" እስመ ነገረ መስቀሉስ ዕበድ ውእቱ በኃበ ኅጉላን ወበኃቤነሰ ለእለ
ድኅነ ኃይለ እግዚአብሔር ውእቱ" የመስቀሉ ቃል ወይንም የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድነው ግን
የእግዚአብሔር ኃይል ነውና ይላል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ 1 ኛ ቆሮ. 1፡18 የመስቀሉ ነገር ሞኝነትና ኃይል በሆነላቸው
ሰዎች መካከል እንደ መለኪያና መለያ ያለ ነገር ይሆናል ማለት ነው፡፡ለአይሁድ የመርገም፣ ለአማልክት አምላኪዎች የሞኝነት፣
ለክርስቶስ ቤተሰቦች /ወገኖች የእግዚአብሔር ኃይል የሆነውን የመስቀሉን ትርጉም ለማስተማር ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ቆሮንቶስ ድረስ ለኹለት ለሦስት ጊዜያት ረጅም ሐዋርያዊ ጉዞ ያደረገው በዚኹ ነበረ፡፡
መስቀል በብሉይ ኪዳን ለሐዲስ ኪዳን ምሳሌነት የነበረው ሲሆን ይህም የኖኅ መርከብ የተሠራችበት እንጨት፣ ሙሴ የፈርዖንን
መሰግላን ድል ያደረገበት ÷በትረ ሙሴ የመስቀል ምሳሌዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡ ምእመናን በክርስቶስ አምነው በመስቀል
አማትበው ከማየ ደምሳሴ ኃጢአት፣ ከአምልኮተ ጣዖት ድነዋል፣ በመስቀለ ክርስቶስ አጋንንትን፣ መናፍቃንን፣ ፍትወታት እኩያትን
ድል ሲያደርጉ ይኖራሉ፡፡ከዚህም የተነሣ የክርስትናው ጥበባት ኹሉ ምልክቱ መስቀል ሆኗል፡፡
ስለሆነም "እግዚአብሔርስ ንጉሥ ውእቱ እመቅድመ ዓለም፣ ወገብረ መድኃኒቲተ በማዕከለ ምድር ... እግዚአብሔር ከዓለም
አስቀድሞ ንጉሥ ነው፣ በምድር መካከልም መድኃኒትን አደረገ" በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የዘመረውንም በመነሻው
አሰምተናል፡፡ መዝ. 73፡12 ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ማዕከለ ምድር ያለው ቀራንዮ ጎልጎታን ነው፡፡ የጌታችን የአምላካችን
የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀሉና የመቃብሩ ቦታ ቀራንዮ ጎልጎታ መባሉ ነው፡፡ ይህም ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በዕፀ መስቀል፣ በሥጋ የተሰቀለበት፣ በሥጋ የሞተበትና የተቀበረበት፣ ሦስት
መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ውሎና አድሮ በዕለተ እሑድ የተነሣበት ነው፡፡
የክርስቶስ ቅዱስ መስቀል በዕለተ ዓርብ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ድል የተነሣበት ሆነ፡፡ እንኳን አማናዊው የክርስቶስ መስቀል
ይቅርና የእርሱ ምሳሌ የሆነው፣ ሙሴ ከእግዚአብሔር መመሪያን ተቀብሎ በምድረ በዳ የሰቀለው አርዌ ብርት እንኳ ሳይቀር ብዙ
ተአምራትን ሠርቷል፡፡ እባብ የነደፈው እስራኤላዊ ኹሉ በዓላማ ላይ የተሰቀለውን የናሱን እባብ በእምነት ለተመለከተው ኹሉ
ሕይወትን አግኝቷል ከደዌው ተፈውሷል፣ ከኀዘኑ ተጽናንቷል ዘኁቁ. 21፡6-9 ይህን ያህል ተአምር የሠራው ይህ የመስቀለ
ክርስቶስ ምሳሌ የነበረው ነው፡፡
መስቀል የተባረከ መድኃኒት በመሆኑ ክርስቲያን የሆነ ኹሉ በመስቀሉ ይመካል፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዓለም ለእኔ
የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበት ከጌታችን ከአምላካችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ
ትምክህት ከእኔ ይራቅ ይላል፡፡ ገላትያ. 6፡14 ይህ ከዚህ በላይ የሰማነው ትምህርት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በስህተት ትምህርት
ለተወናበዱት የገላትያ ሰዎች ትክክለኛውን የክርስትና እምነትና ሕይወት ለማሳወቅ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
እኛም ስለነገረ መስቀሉ መናገር ያለብን በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ ዘይቤ መሆን አለበት፡፡ዛሬ የምናከብረው ዓመታዊ በዐላችን
ዓለም ኹሉ ክብር ያገኘበትና ከግብርናተ ዲያብሎስ ነጻ የወጣበት ስለሆነ ይህን የመንፈስ ነጻነት በአል ስናከብር የሚሰማን ደስታ
ከፍተኛ ነው፡፡ቃለ እግዚአብሔር ወልድ በገሊላ አውራጃ በናዝሬት ከተማ ሰው ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም በይሁዳ አውራጃ
በዳዊት ከተማ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተወልዶ እስከ ማዕከለ ምድር ቀራንዮ፣ ጎልጎታ መስቀል
አደባባይ የደረሰበትን መከራ ስንመለከት ሕማማተ መስቀሉን ተቀብሎ፣ ተሰቅሎ፣ ሞቶ ተነሥቶ ሰውን ያዳነበት ዕለት መሆኑን
እንረዳለን፡፡
ከፅንሰት ከልደት ከጥምቀት ከትምህርት አሰጣጡ ከተአምራቱ ድርጊት ሒደት አንሥቶ እስከ ቀራንዮ ጎልጎታ ድረስ በመጨረሻም
በመስቀል ላይ ሆኖ "ወይቤ ተፈጸመ ኩሉ" ብሎ የአዳምን የክብሩን ፍጻሜ በመስቀሉና በትንሣኤው እስከ አጠቃለለው ድረስ
የተቀበለው እያንዳንዱ ጸዋትወ መከራ የሰውን ክቡርነት፣ መንፈሳዊ ሕይወት ልዕልና የሚገልጽ ነው፡፡ከላይ እንደተጠቀሰው
ቀዳማዊ አዳም የአምላኩን ትእዛዝ በማፍረሱ ምክንያት ከአንዲት የበለስ ቅንጣት በፈሰሰው ደም በተፈጥሮው ንጹሕ የነበረው
የሰው ሕይወት በኃጢአት አድፎ እንዳይቀር የዚህን አጸፋ የሚመልስ መከራ ተቀብሎ ባፈሰሰው ደሙ የአዳምን ፍዳ ለማስወገድና
ወደ ቀደመው ክብሩ ለመመለስ ስለሰው ሕይወት ብሎ በፍርድ አደባባይ መቆምና መወቀስ፣ መገረፍ፣ መውደቅ፣ መነሣት፣
መጸፋትና መመታት፣ መስቀልን ተሸክሞ መጓዝን መገፋት፣ መራራ ሐሞትን ለጥማቱ መቀበል ይህን ኹሉ በእኛ በፍጡራን ደረጃ
ስንመለከተው ከሰው ትዕግሥትና ችሎታ በላይ መሆኑን እንረዳለን፡፡
ሰለሆነም ከዚህ በላይ የተጠቀሰውን መከራና ስቃይ ከተቀበለ በኋላ ዓርብ በዕለተ ዓርብ በማዕከለ ምድር ቀራንዮ አኅዜ ዓለም የሆነ
እጁን በመስቀል ላይ ዘርግቶ በፈቃዱ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ፡፡ መለኮት በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ በአዳምና
በሔዋን፣ በልጆቹ ኹሉ ስም ተጽፎ የነበረውን ስመ ተዋርዶ አጥፍቶ በሲኦል ተግዘው የነበሩትን ነፍሳት ነጻ አውጥቶ ገነትን
አወረሳቸው፡፡ ስለዚህ ይህ በዓላችን የሰው ፍጹም ክብሩ የተመለሰበት፣ የሞትና የኃጢአት እንዲሁም የዲያብሎስ ሥልጣን
የወደቀበትና የተሻረበት ቀን ስለሆነ ዓለም ኹሉ ትንሣኤ ዘለክብርን ወደሚያድለው ወደ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ በአንቃእድው ልቡና ዕደ ኅሊናውን ሰቅሎ ምስጋና ማቅረብ ይገባዋል፡፡እስከዚህ የተገለፀው ዛሬ መታሰቢያነቱን
የምናከብረው በዓላችን የሰው ልጆች አባት የሆነው ቀዳማዊ አዳም በዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ፍርድ ወደ
ዘለዓለማዊ ሕይወት የተመለሰበት፤ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዳዊት ከተማ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ
ልደቱ ጀምሮ እስከ ቀራንዮ ጎልጎታ ድረስ ለሰው ልጅ ያደረገውን ቸርነት የምናዘክርበት፤ ከጌታችን ከአምላካችን ከመድኃኒችን
ከኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው የተሰጠ የደኅነት ጸጋ የተረጋገጠበት፤በዓለም ኹሉ ሰላም የወረደበትና ፍጡር ከፈጣሪው ፍጹም
ሕይወትን ያገኘበት ዕለት ነው ብለን ነው፡፡
ስለዚህ ይህ ዕለት የሰላማችን፣ የደስታችንና የድል በዓላችን ስለሆነ በየዓመቱ በዝማሬ፣ በውዳሴና በቅዳሴ እናከብረዋለን፡፡ከዚህ
ዕለት አድርሶ በዓላችንን ለማክበር እንዳበቃ ኹሉ ዘወትር ወደፊትም እንድናከብር እግዚአብሔር አምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ
ይሁንልን፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታችንን፣ ድካማችንን ተቀብሎ ምሕረቱን፣ ቸርነቱን ያድርግልን፡ እግዚአብሔር አምላካችን
ለሀገራችንና ለዓለሙ ኹሉ ሰላሙን ይስጥልን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ይባርከን ይቀድሰን፡፡
መስቀለ ክርስቶስ
❖መስቀሉን ያስወጣችው የእሌኒና የልጇ የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ታሪክ
ይኽ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የአባቱ ስም ቊንስጣ የእናቱ ስም እሌኒ ነው፤ ከሓዲው መክስምያኖስ በሮሜ በአንጾኪያ እና በግብጽ
ነግሦ በነበረ ጊዜ አባቱ ቊንስጣ በራንጥያ ለሚባል አገር ንጉሥ ነበር፤ እሌኒ ከእርሱ ቆስጠንጢኖስን ከወለደችው በኋላ አባቱ
ቊንስጣ እነርሱን ሮሐ (ሶርያ) ላይ ትቷቸው ወደ በራንጥያ ተመለሰ፡፡
❖“ወይእቲ ነበረት እንዘ ተሐጽኖ ለወልዳ ወመሀረቶ ትምህርተ ክርስትና ወኮነት ዘትዘርዕ ውስተ ልቡ ምሕረተ ወሣሕለ ላዕለ
ሕዝበ ክርስቲያን” ይላል፤ እርሷም ልጇን የክርስትና ትምህርትን አስተማረችው፤ ይቅርታንና ርኅራኄን በክርስቲያን ወገኖች ላይ
እንዲያደርግ በልቡናው መልካም ዘርን ትዘራበት ነበር፡፡
ከዚያም ቈስጠንጢኖስ አካለ መጠን ሲያደርስ ወደ አባቱ ሰደደችው፤ አባቱም ቊንስጣ የጥበቡን ብዛት አይቶ በመደሰት ከበታቹ
መስፍን አድርጎት በመሾም በመንግሥቱ ሥራ ላይ ኹሉ ሥልጣንን ሰጥቶታል፤ “ወእምድኅረ ክልኤቱ ዓመት አዕረፈ አቡሁ
ወተመጠወ ቈስጠንጢኖስ ኲሎ መንግሥተ ወገብረ ፍትሐ ርቱዐ” ይላል፤ ከኹለት ዓመት በኋላ አባቱ በማረፉ ቈስጠንጢኖስ
መንግሥቱን ኹሉ ተረክቦ የቀና ፍርድን የሚፈርድ ኾነ፤ ከእርሱ በፊት የነበሩ የአላውያን እና የአሕዛብ ነገሥታት የጫኑባቸውን
ጽኑ አገዛዝ ከሰዎች ላይ የሚያስወግድ ኾነ፤ በዚኽ ምክንያት ኹሉም ወደደው፤ ዝናውም በብዙ አገሮች ላይ ተሰማለት፡፡
በአንጾኪያ ያሉ ክርስቲያኖችም የቈስጠንጢኖስን ፍርድ መጠንቀቁን፣ ድኻ መጠበቁን እየሰሙ ከከሓዲው ከመክስምያኖስ አገዛዝ
እንዲያድናቸው የልብሰ ተክህኖውን ቅዳጅ፣ የመስቀሉን የጽናውን የጽዋውውን ስባሪ ይልኩለት ነበር፤ እርሱም ስለደረሰባቸው
መከራ በእጅጉ አዘነ ÷ ማዘኑም ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ አይደለም እንዴት ሰው ኾኖ በሰው ላይ እንዲኽ ይጨክናል ብሎ
ነው፡፡ስለዚኽም እያዘነ እንዴት አድርጎ እንደሚያድናቸው ያስብ ነበር።
“ወእንዘ ይነብር ውስተ ዐውድ ወናሁ አስተርአዮ በመንፈቀ መዓልት መስቀል ዘሕብሩ አምሳለ ከዋክብት ወዲቤሁ ጽሑፍ በልሳነ
ዮናኒ ኒኮስጣጣን ዘበትርጓሜሁ በዝንቱ ትመውዕ ጸረከ ወአንከረ ብርሃኖ ለመስቀል ሶበ ርእየ እንዘ ይከድኖ ለብርሃነ ፀሓይ” ይላል
ከዕለታት ባንዳቸው በአደባባይ በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ከቀኑ በስድስት ሰዓት ጊዜ ሕብሩ እንደከዋክብት የኾነ መስቀል
በጸፍጸፈ ሰማይ ላይ ሲታየው፤ በላዩም በዮናኒ ቋንቋ ኒኮስጣጣን የሚል ጽሑፍ ነበረው፤ ትርጓሜውም በዚኽ ጠላትኽን ድል
ታደርጋለኽ ማለት ሲኾን፤ እርሱም የመስቀሉ ብርሃን የፀሓይን ብርሃን ሲሸፍነው አይቶ ተደንቋል፡፡
ይኽነንም ያየውን ለሊቃውንቱ በጠየቃቸው ጊዜ አውስግንዮስ የሚባል ሕጽው በዚኽ መስቀል አምሳል ጠላትኽን ድል ታደርጋለኽ
ማለት ነው ብሎ ተረጎመለት፤ መልአኩም ሌሊት በራእይ ታይቶት አስረዳው፤ “ወነቂሆ እምንዋሙ ጸንዐ ልቡ ወገብረ መስቀለ
ዘወርቅ ወረሰዮ መልዕልተ አክሊለ መንግሥቱ ወአዘዞሙ ለኲሎሙ መኳንንቲሁ ወሐራሁ ከመ ይግበሩ መስቀለ በኲሉ ንዋየ
ሐቅሎሙ” እንዲል ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ልቡ ተጸናና የወርቅ መስቀልም አሠርቶ በነገሠበት ዘውድ ላይ አደረገው፤ መኳንንቱንና
ወታደሮቹን ኹሉ መስቀል አሠርተው በጦር መሣሪያቸው ላይ ያደርጉ ዘንድ አዘዛቸውና እንዳላቸው አደረጉ፡፡
ከዚያም በክርስቲያኖች ጠላት በከሓዲው መክስምያኖስ ላይ ዘመተበት፤ ከዚያም መክስምያኖስ ሰምቶ እኛ ባንሄድበት እርሱ
መጣብን ብሎ ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብሎ ጦሩን ይዞ ገጠመው ፤ በመክስምያኖስ ጦር ላይ ዐድረው ድል ያደርጉ የነበሩ
አጋንንት በቈስጠንጢኖስ ጦር ላይ ያለውን ትእምርተ መስቀል ባዩ ጊዜ ተለይተውት በኼዱ ጊዜ ድል ተነሣ፤ እርሱም ከጥቂቶች
ጋር እራሱን ለማዳን “ወተጽዕኑ ዲበ ተንከተም ወተንከተምኒ ንህለ ወተሠጥመ መክስምያኖስ ምስለ ሰራዊቱ” ይላል ወደ ሮሜ
ለመሻገር በድልድይ ላይ ሲወጡ ድልድዩ ፈርሶ ከሰራዊቱ ጋር ሰጥሟል፡፡
ከዚያም በድል አድራጊነት ንጉሥ ቈስንጢኖስ ወደ ሮሜ በገባ ጊዜ ካህናቱና ሕዝቡ መብራት ይዘው፤ “መስቀል ኀይልን መስቀል
ጽንዕነ መስቀል መዋዔ ጸር” እያሉ እየዘመሩ ተቀበሉት፤ እርሱም እናቱ ቅድስት እሌኒ እያስተማረች ያሳደገችው፤ በኋላም ምእመናን
ይልኩለት የነበረው፤ በሰሌዳ ሰማይም ላይ የተመለከተው፤ አኹንም በአንጾኪያ ምእመናን መስቀል ይዘው የተቀበሉትን አይቶ
ትክክለኛውን ሃይማኖት በመረዳት ከአገሩ ሊቀ ጳጳሱን ጴጥሮስን አስመጥቶ ተጠምቋል ፡፡
ከዚያም ዐዋጁን ባዋጅ በመመለስ “አብያተ ጣዖታት ይትዐጸዋ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኀዋ” አብያተ ጣዖታት ይዘጉ÷ አብያተ
ክርስቲያናት ይከፈቱ የሚል ታላቅ ትእዛዝን አዘዘ፤እርሷም ልጄ ክርስቲያን ከኾነ ኢየሩሳሌም ኼጄ የፈረሱትን አብያተ ክርስቲያናት
አሠራለኊ፤ የጌታዬ መስቀልን ከተቀበረበት አስወጣለኊ ብላ ስዕለት ተስላ ነበርና ያ በመፈጸሙ ደስ ተሰኝታ፤ ለልጇ ነገረችው፤
እርሱም በደስታ ብዙዎች ሰራዊትን ስንቅ አስይዞ የጌታችንንም መስቀል እንድታወጣ እናቱ እሌኒን ወደ ኢየሩሳሌም ላካት፡፡
ይኽስ እንደምንድ ነው ቢሉ የጌታችን መስቀል ከጌታችን ዕርገት በኋላ ሙት እያነሣ፣ ደውይ እየፈወሰ ለክርስያኖች ታላቅ ክብር
በመኾኑ፤ አይሁድ በዚኽ ቀንተው ጒድጓድ ቈፍረው በይሁዳ እና በኢየሩሳሌም ኹሉ ቤቱን የሚጠርግ ጒድፉን አምጥቶ
እንዲያፈስስበት በማዘዛቸው ቦታው የቆሻሻ መጣያ ኾኖ ዕሌኒ ንግሥት እስከ መጣችበት ድረስ ለ፫፻ ዓመታት ያኽል ተቀብሮ
ኖረ፡፡ እርሷም በኢየሩሳሌም በደረሰች ጊዜ ሱባኤን አድርጋ የመስቀሉ ጠላቶችን በጽኑ እስራት አሰረቻቸው፤ በኋላም አሚኖስና
ኪራኮስ የሚባሉ በዕድሜ የጠገቡ ሽማግሌዎችን ብትጠይቃቸው ሊነግሯት ፈቃደኛ አልኾኑምና በጽኑ እስራት ብታስጨንቃቸው፤
ታሪኩን ነገሯት፤ ቦታውንም ጠቆሟት፡፡ከዚያም በጸሎቷ ላይ ቅዱስ መልአክ ተገልጾላት በዕጣን ጢስ አማካይነት እንደ ምታገኘው
ተረድታ፤ መስከረም ፲፮ ደመራን አስደምራ በእሳት እንዲቃጠል አድርጋ እጅግ ብዙ ዕጣንን ብታስጨምር ጢሱ ወደ ሰማያት
ወጥቶ መስቀሉ ካለበት ቦታ ላይ ተተክሎ ሰገደ፤ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ይኽነን ድንቅ ታሪክ ይዞ "ሰገደ ጢስ ኀበ አንጻረ መስቀል ሰገደ
ጢስ ወባረከ" እያለ አመስግኗል፡፡
እርሷም ፈጣሪዋ እግዚአብሔርን በፍጹም ደስታ አመስግና ቊፏሮውን ከመስከረም ፲፯ ዠምሮ እስከ መጋቢት ፲ ድረስ እንዲቈፈር
አስደርጋለች፤ በቊፋሮው ወቅትም የፈያታዊ ዘየማንና የፈያታዊ ዘጸጋም መስቀል ቢገኙም ዕውር አላበሩም፣ ሕሙማንን
አልፈወሱም፡፡ ከዚያም መጋቢት ፲ በ፫፻፳፯ ዓ.ም. ጌታችን ቅዱስ ሥጋው የቆረሰበትን ÷ ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት ቅዱስ መስቀሉ
ተገኘ፤ በዚኽ ጊዜ ከሕሙማን ላይ ቢያደርጉት ኹሉንም ፈወሳቸው፣ ዕዉራን በሩ፣ ሙታንም ተነሡ፡፡ ከዚኹም ጋር የተወጋበት
ጦሩ፣ የተቸነከረባቸው ቅንዋት ኹሉ ተገኝተዋል፤ እርሷም በፈረሷ ልጓም ላይ የመስቀል ምልክትን አስቀርጻበታለች፡፡
እርሷም ጌታችን ተአምራት በሠራባቸው ቦታዎች አብያተ ክርስቲያናትን በማሠራት፤ በተለይም በጎልጎታ የተሠራው ቤተ ክርስቲያን
መስከረም ፲፯ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምእመናን በተገኙበት ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑ ተከብሯልና፡፡ እርሷም ለድኾችና ለጦም አዳሪዎች
ብዙ መልካም ነገርን በማድረግ ግንቦት ፱ በሰላም ዐርፋለች፡፡
ሊቁ አርከ ሥሉስም ስለ ቅድስት እሌኒ በዐርኬው ላይ፡-
“ሰላም ለእሌኒ ውስተ ምድረ ሕይወት ኤልዳ ምክረ መንፈስ ቅዱስ አመ ወሰዳ ለዘሐይወ በድን በለኪፈ መስቀል ቅድመ ዐውዳ
እምአይቴ አንተ ትቤሎ ወእምአይ አንግዳ ዘተረከብከ ግዱፈ በበዳ”ማለት የመንፈስ ቅዱስ ምክር በወሰዳት ጊዜ ኤልዳ ወደ ተባለች
የሕይወት ምድር የኼደች ለኾነች ለዕሌኒ ሰላምታ ይገባል፤ በአደባባይዋ ፊት መስቀልን በመንካት የዳነውን በድን በበረሓ ወድቀኽ
የተገኘኽ አንተ እንግዳ ከወዴት ነኽ አለችው በማለት መስቀሉ ከወጣ በኋላ ስለተደረገላት ተአምር ጽፏል፡፡
"ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ ዕፀ መድኀኒት ኀይልነ ወጸወንነ" አሜን፡፡
ዳግመኛም
❖ደመራ፡- "ደመረ" ከሚለው መነሻ ግሥ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም መሰብሰብ ማከማቸት እንደማለት ነው፡፡ ከዚህ ተነስተን
ደመራ ማለት የመሰብሰብ ወይም የመደመር ሂደት ደመራ፤ ድመራ ልንለው እንችላለን፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኹሉም ከፈፀመ በኋላ እንደ ወንጀለኛ በእንጨት መስቀል ተሰቅሎ ሞተ÷ ጥንት ዘመን መስቀል
የወንጀለኛ መቅጫ ነበር፡፡ጌታ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ የተሰቀለበትን መስቀል አይሁድ እንደ ተራ ነገር አውላላ ሜዳ ላይ
ጣሉት ከጊዜ በኋላ ግን ወደ አይሁዳ ጆሮ አንድ ነገር መጣ ፡፡ እንደ ቀልድ የጣሉት የክርስቶስ መስቀል ህሙማንን እየፈወሰ
እውራንን እያበራ ድንቅ ታእምራትንም እያደረገ እንደሆነ ሰሙ፡፡ በዚህ ጊዜ ክርስቶስን ከከተማው አውጥተው እንደሰቀሉት ኹሉ
መስቀሉንም እንዲሁ ከከተማ ውጭ አውጥተው ጥልቅ ጉድጓድ ቆፍረው ከሌሎች ፪ መስቀል ጋር ቀበሩት እና ቆሻሻም መጣያ
አደረጉት፡፡
እግዚአብሔር ግን ነገርን የሚያከናውንበት ጊዜ አለውና ደግሞ ዘመን መጣ፡፡ በእስጢፋኖስ ሞት የተበተነው የክርስትናው ዘር
ማፍራት ጀመረ በሮም ነግሰው የነበሩት መክሲሚያኖስ እና ዲዮቅልጢያኖስ ክርስቲያኖችን እንደ ሰም እያቀለጡ እንደ ገል
እያደቀቁ ከነፍሰጡሮች ማህፀን ሽል አውጥተው በሰይፋቸው እየሰነጠቁ በስቡ ጎራዲያቸውን በሚወለውሉበት በዚያ አስደንጋጭ
የዘመነ ሰማዕታት የስቃይ ጊዜ ( በነገራችን ላይ ቤተክርስቲያን በዚያ ዘመን ከደረሰባት መከራ የበለጠ እስካሁን አልደረሰባትም
ወደፊትም ይደርስባታል ተብሎ አይገመትም) ብዙ ክርስቲያኖች ዋሻ ውስጥ አበው ግበበምድር ይሉታል ገብተው ተውፊት
ቁሳዊንና ትውፊት መንፈሳዊውን እየጠበቁ በብዙ መከራ የተስፋይቱን ቀን ሲናፍቁ ነበር፡፡
በዚያ የክርስቲያኑ ስደት በተጀመረበት ጊዜ አንዲት ሴት ከነዚህ መከራ ከወረደባቸው ስለ ክርስቶስ መከራ የሚቀበሉት ጋር አብራ
ገፈት ቀማሽ ነበረች ስሟ እሌኒ ይባላል፡፡ በኋላ የመከራው ዘመን ሲያልፍ ንጉስ ቆንስጣን አግብታ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ
ወልዳለች፡፡ እናም ልጄ ክርስቲያን ከሆነልኝ በክርስቶስ ካመነልኝ የጌታችንን መስቀል አይሁድ ከደበቁበት ፈልጌ አስወጣለው ብላ
ስለት ተስላ ነበር። ጌታም ልመናዋን ሰምቶ ልጇ ቆስጠንጢኖስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ለክርስቲያኖች የሚቆረቆር በግፍ
ለሚሰቃዩት የሚደርስ ንጉሥ ሆነ። ንግሥቲቱ እሌኒ በመከራ ውስጥ እግዚአብሔር የለያት ሴት ናት። በንግሥትነት ስትኖር ቤተ
መንግስቱ ስለተመቻት ክርስቶስን አረሳችውም፡፡ ይልቁንም የጌታ ፍቅር እንደ እግር እሳት ስለሚያንገበግባት ፀሎቷም ስለተሰማም
ደግሞም ጌታን በአይነ ሥጋ ባላገኘውም እንኳን መስቀሉን አግኝታ ገላው ያረፈበትን አቅፋ፣ ስማ ፍቅሯን ለማውጣት መንፈስ
ቅዱስ አነቃት ወደ ኢየሩሳሌምም መጣች፡፡
የክርስቶስ መስቀል የተቀበረበት አካባቢ ማንም አያውቅም። በከተማው ስለ ክርስትና የሚያወራ ሰው ከተገኘ ይገደል ነበር። እሷም
አንድ አረጋዊ ሰው ኪሪያኮስ የሚባል አግኝታ ጠየቀችው። እሱም ለማውራት ሲፈራ ጨው የበዛበት ምግብ ሰጠችው እና ቦታው
ካላሳያት ውሃ አልሠጥም አለችው። ኪራኮስም በመጨረሻ አባቶቻችን ከነዚያ ተራሮች በአንዱ ነው ይላሉ የቱ ተራራ ስር እንደሆነ
አላውቅም አላት። ክርስቲያን ነገር ሲከብደው የኹሉ ነገር መፍትሔ ወዳለው ጌታ ይፀልያልና ንግስት እሌኒና አረጋዊ ክሪያኮስ
ሱባዔ ይዘው ወደ ፈጣሪያቸው ማመልከት ጀመሩ፡፡
በመንፈስ ቅዱስ እንደተረዱት እንጨት ሰብስበው ደመራ ደምረው እሳት ሲያነዱ ከእሳቱ ላንቃ በላይ ተምዘግዛጊ ጢስ ወጣ እንደ
ጦር ቀስት ምልክት ያለው፡፡ ጢሱም የጌታችን መስቀል ወደ ተቀበረበት ተራራ አናት ላይ ሄዶ ሰገደ። ሰው እግዚአብሔርን
ማገልገል ሲያቅተው ግዕዛንና እንስሳት ያገለግሉታል ፡የቢታንያ ዲንጋዮች ፣ የሰባ ሰገል ኮኮብ፣ የበልአም አህያ፣ የገሊላ ባህር አሁን
ደግሞ የደመራው ጢስ በአይሁድ በላይ ባለአእምሮ ሆነ ጢሱም ያረፈበት ቦታ የመስቀሉ መገኛ መሆኑን ስላወቁ ደመራውን
በደመሩበት ማግስት መስከረም ፲፯ ቀን ቁፋሮ ተጀምሮ ቅዱሱ የጌታ መስቀል መጋቢት ፲ ቀን ተገኘ፡፡
ንግሥት እሌኒ ጌታን በምቀኝነት የገደሉት አይሁድ የዓለም መድኃኒት
ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል አካሉ ያረፈበት፣ደሙ የፈሰሰበት በመሆኑ
{ሕሙማንን ሲፈውስ ሙታንን ሲያስነሳ በማየታቸው ስለተጨነቁ} ሰውን ተሰቅሎ እንዲሞት ከመፍረድ ይልቅ የተሰቀለበትን
መስቀል መቅበር ይቀላል ብለው በመምከር መሬት ውስጥ ቀብረው የከተማው ሰው የቤት ጥራጊውን እንዲደፋበት አዋጅ
በማሳዎጃቸው ለ፫፻ ዓመታት ያህል የተፈጥሮ ተራራ እስኪመስል ድረስ የቤትና የጓሮ ጥራጊ ሲያስደፉበት ከነበረበት ቦታ
ተራራውን መስከረም ፲፯
ቁፋሮውን አስጀምራ በመጋቢት ፲ ቀን መስቀሉ ተገኝቶ ከተቀበረበት ወጣ።
ደመራ እና የመስቀል በዓል ትርጉሙ ይህ ነው እንግዲ። እኛም እቤታችን ችቦ ለኩሰን ደመራ የምናበራው ሃይማኖታዊ ትሁፊት
ስለሆነ ነው። በዘፈን ፣ በጭፈራ፣ በመጠጣት ሥጋዊ አናድርገው በዓሉን። ስለ መንፈሳዊ ነገር እየተጨዋወትን፣ በመዝሙር፣
የተራቡትን በማብላት ባጠቃላይ መንፈሳዊ ነገር በማድረግ እናሳልፈው ስርአት ባለው መልኩ እናክብረው።
የመስቀሉ በረከት ረድኤት እና ፍቅር ይደርብን.. አሜን.. ወስብሐት ለእግዚአብሔር።
የከበረ መስቀል ዳግመኛ የተገለጠበት መጋቢት ፲ ቀን ነው፤በደመ ወልደ እግዚአብሔር የከበረ፣ ጌታ ቅዱሳት እጆቹን የዘረጋበት፣
ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት፣ መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ የተሻረበት፣ ዘላለማዊ ደዌ የጠፋበት፣ የጥል ግድግዳን ያፈረሰበት፣ ጥንተ
ጠላታችን ዲያብሎስ ድል የተነሣበት የጌታችን መስቀል ከጌታችን ዕርገት በኋላ ሙት እያነሣ፣ ደዉይ እየፈወሰ ለክርስያኖች ታላቅ
ክብር በመኾኑ፤ አይሁድ በዚኽ ክፉኛ ይበሳጩ ነበር።ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵ. 3፡18-19 ላይ “ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል
ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ፤ መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥
ሆዳቸው አምላካቸው ነው ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው” እንዳለ፤ ጒድጓድ ቈፍረው በይሁዳ እና
በኢየሩሳሌም ኹሉ ቤቱን የሚጠርግ ጒድፉን አምጥቶ እንዲያፈስስበት በማዘዛቸው ቦታው የቆሻሻ መጣያ ኾኖ ዕሌኒ ንግሥት
እስከ መጣችበት ድረስ ለ፫፻ ዓመታት ያኽል ተቀብሮ ኖረ፡፡
የእሌኒ ልጇ ቆስጠንጢኖስም በመስቀሉ ኀይል የክርስቲያኖች ጠላት የኾነውን መክስምያኖስን ድል ከነሣ በኋላ በሶል ጴጥሮስ
ተጠምቆ ክርስቲያን ኾነ፤ እርሷም ልጄ ክርስቲያን ከኾነ ኢየሩሳሌም ኼጄ የፈረሱትን አብያተ ክርስቲያናት አሠራለኊ፤ የጌታዬ
መስቀልን ከተቀበረበት አስወጣለኊ ብላ ስዕለት ተስላ ነበርና ያ በመፈጸሙ ደስ ተሰኝታ፤ ለልጇ ነገረችው፤ እርሱም በደስታ
ብዙዎች ሰራዊትን ስንቅ አስይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ላካት፤ በደረሰችም ጊዜ ሱባኤን አድርጋ የመስቀሉ ጠላቶችን በጽኑ እስራት
አሰረቻቸው፤ በኋላም አሚኖስና ኪራኮስ የሚባሉ በዕድሜ የጠገቡ ሽማግሌዎችን ብትጠይቃቸው ሊነግሯት ፈቃደኛ አልኾኑምና
በጽኑ እስራት ብታስጨንቃቸው፤ ታሪኩን ነገሯት፤ ቦታውንም ጠቈሟት፡፡
ከዚያም በጸሎቷ ላይ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጾላት በዕጣን ጢስ አማካይነት እንደምታገኘው ተረድታ፤ መስከረም ፲፮ ደመራን
አስደምራ በእሳት እንዲቃጠል አድርጋ እጅግ ብዙ ዕጣንን ብታስጨምር ጢሱ ወደ ሰማያት ወጥቶ መስቀሉ ካለበት ቦታ ላይ
ተተክሎ ሰገደ፤ “ተተክለ ጢስ ኀበ አንጻረ መስቀል፤ ሰገደ ጢስ ወባረከ” እንዲል ቅዱስ ያሬድ።እርሷም ፈጣሪዋ እግዚአብሔርን
በፍጹም ደስታ አመስግና ቊፏሮውን ከመስከረም ፲፯ ዠምሮ እስከ መጋቢት ፲ ድረስ እንዲቈፈር አስደርጋለች፤ በቊፋሮው
ወቅትም የፈያታዊ ዘየማንና የፈያታዊ ዘጸጋም መስቀል ቢገኙም ዕውር አላበሩም፣ ሕሙማንን አልፈወሱም፡፡
ከዚያም መጋቢት ፲ በ፫፻፳፯ ዓ.ም. ክብር ይግባውና ጌታችን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት ቅዱስ መስቀሉ ተገኘ፤ በዚኽ ጊዜ
ከሕሙማን ላይ ቢያደርጉት ኹሉንም ፈወሳቸው፣ ዕዉራን በሩ፣ ሙታንም ተነሡ፡፡ ከዚኹም ጋር የተወጋበት ጦሩ፣
የተቸነከረባቸው ቅንዋት ኹሉ ተገኝተዋል፤ እርሷም በፈረሷ ልጓም ላይ የመስቀል ምልክትን አስቀርጻበታለች፡፡
ዳግመኛም ንግሥት እሌኒ ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌ ኾኖ ሲመላለክ ተአምራት በሠራባቸው ቦታዎች አብያተ ክርስቲያናትን
በማሠራት፤ በተለይም በጎልጎታ የተሠራው ቤተ ክርስቲያን መስከረም ፲፯ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምእመናን በተገኙበት ቅዳሴ ቤተ
ክርስቲያኑ ተከብሯልና፡፡ እርሷም ለድኾችና ለጦም አዳሪዎች ብዙ መልካም ነገርን በማድረግ ግንቦት ፱ በሰላም ዐርፋለች፡፡
ሊቁ አርከ ሥሉስም ስለ ቅድስት እሌኒ በዐርኬው ላይ፡-
“ሰላም ለእሌኒ ውስተ ምድረ ሕይወት ኤልዳ ÷ ምክረ መንፈስ ቅዱስ አመ ወሰዳ ÷ለዘሐይወ በድን በለኪፈ መስቀል ቅድመ
ዐውዳ
እምአይቴ አንተ ትቤሎ ወእምአይ አንግዳ ዘተረከብከ ግዱፈ በበዳ”
ማለት የመንፈስ ቅዱስ ምክር በወሰዳት ጊዜ ኤልዳ ወደ ተባለች የሕይወት ምድር የኼደች ለኾነች ለዕሌኒ ሰላምታ ይገባል፤
በአደባባይዋ ፊት መስቀልን በመንካት የዳነውን በድን በበረሓ ወድቀኽ የተገኘኽ አንተ እንግዳ ከወዴት ነኽ አለችው በማለት
መስቀሉ ከወጣ በኋላ ስለተደረገላት ተአምር ጽፏል፡፡
ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በተአምኆ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ፡-
“ሰላም ለእሌኒ ንግሥት ዘከሠተት መስቀለ በጎልጎታ ÷ለክርስቲያን ዘይከውን ወልታ፤እምኀበ ወጽአ ጢስ በሃይማኖታ፤ወዓዲ
ረከበት ቅንዋተ መስቀሉ ለክርስቶስ፤ወአግበረት ልጓመ ፈረስ በከመ ይቤ ዘካርያስ”፡፡
ማለት ጢስ በሃይማኖቷ ከወጣ ዘንድ ለክርስቲያን ጋሻ የሚኾን መስቀልን በጎልጎታ ያወጣች ለኾነች ለንግሥት እሌኒ ሰላምታ
ይገባል፤ ዳግመኛም የክርስቶስን የመስቀሉን ችንካሮች አገኘች፤ ዘካርያስ እንደተናገረው ለፈረስ ልጓምን አሠራች በማለት
ይጠቅሳል፡፡
የነገረ መስቀሉን ነገር ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ሲያመሰጥረው፡- “መስቀልከ ዕፅ ዘኢይነቅዝ መስቀልከ ዕፅ ዘኢየዐብር መስቀልከ
ዕፅ ዘኢይማስን…” ማለት መስቀልኽ የማይነቅዝ ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ የማይዋጋ (የማይደርቅ) ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ የማይጠፋ ዕፅ
ነው፤ መስቀልኽ የፀሓይ ሙቀት የነፋሳትም ግርፋት የማያደርቀው ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ ውሆችና የነፋሳት ንውጽውጽታዎች
ሊያነዋውጡት የማይቻላቸው ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ የባሕር ሞገዶች ሊገፉት የማይቻላቸው ዕፅ ነው፤መስቀልኽ የዝናማት ክብደት
ሊጥሉት የማይቻላቸው ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ ርኩሳን መናፍስት ሊቀርቡት የማይቻላቸው ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ ከገነት ዛፎች
መኻከል የሚመስለው የሌለ፤ ከበረሓ ዕንጨቶች መኻከልም የሚተካከለው የሌለ ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ ከዐርዘ ሊባኖስ መኻከል
የሚመስለው ከምርስኔም ዛፎች መኻከል የሚተካከለው የሌለ ዕፅ ነው፤ የኢላጤኖስ ዛፎችም እንደ አበቃቀሉ አይኾኑም፤ የቄድሮን
ዛፎች በውበት አይተካከሉትም፤ የጳውቄናም ዛፎች አይመስሉትም፤መስቀልኽ በሌሎች ዛፎች ላይ የማይመካ ለስላሳ ዕፅ ነው፤
መስቀልኽ በእርሱ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይል ዘንድ የወደደው ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ ከቅርንጫፎቹ የወይንን ዝናማት ያንጠባጠበ
ዕፅ ነው፤ ደመናውም ከአርያም የኾነ የብርሃን ደመና ነው፤ እርሱም ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤
ምእመናንም ከእርሱ ከሚንጠባጠበው የምሕረት ዝናብ እንዲረኩ አደረገ፤ ከእርሱም ምእመናን የጥምቀት ማኅተም ወሰዱ…
በኪሩቤል ጀርባ በእሳት ሠረገላ ላይ የምትቀመጠው በሊቶስጥሮስ ግን በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቀልኽ፤ መስቀልኽም በደምኽ
ነጠብጣብ ተቀባ፤በአምላኩ ደም የተቀደሰ ከፈጣሪው ጎን በወጣ ውሃም የተጠመቀ ዕፅ እንዴት ያለ ነውን÷ ለገነት ዛፎች አክሊል፤
ለገዳም ዛፎችም ክብር የኾናቸው ዕፅ እንዴት ያለ ነውን÷ ለአሸናፊ የእግዚአብሔር በግ መሠዊያ የኾነው ዕፅ እንዴት ያለ ነውን÷
ለእስራኤል አምላክ የፋሲካው መሠዊያ የኾነ ዕፅ እንዴት ያለ ነውን÷ የጎልጎታዊዉ የምስጢር ወይን መፍለቂያ የኾነ ዕፅ እንዴት
ያለ ነውን÷ ከእርሱ ምእመናንን ለማተም የሚኾን የሕግንና የሥርዐት ደምን ያንጠባጠበ ዕፅ ምን ዐይነት ነውን÷ ቡሩካን በጎችን
ለማጠቢያ የሚኾን ምንጭን ያወጣ ዕፅ ምን ዐይነት ነውን÷ምድርን የቀደሳት ሰማይንም ያማተበበት፤ ዓለምንም ኹሉ በአብ
በወልድና በመንፈስ ቅዱስ በረከት የባረከ ዕፅ እንዴት ያለ ነውን÷ ሰማያውያንን ከምድራውያን ያስተባበራቸው ዕፅ እንዴት ያለ
ነውን ÷ አዳምን ከስሕተት ያዳነው ሔዋንንም ከሞት ጻዕረኛነት ነጻ ያወጣት ዕፅ እንዴት ያለ ነውን÷ ስለ እርሱ በኦሪትና በነቢያት
የተነገረ በሐዋርያትም በገሐድ የተሰበከ ዕፅ እንዴት ያለ ነውን÷ የተከሉትን የበተናቸው ያመኑትንም የሰበሰባቸው ዕፅ እንዴት ያለ
ነውን÷ ቤተ ክርስቲያንን በኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት ላይ የመሠረታት ዕፅ እንደምን ያለ ነው"፡፡ በማለት ስለ ክብረ መስቀል
ጽፎታል፡፡
“ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ ፅፀ መድኀኒት ኀይልነ ወጸወንነ”
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በመስቀልኽ ኀይል ዕጠረን፡፡
ዜናውን በዚህ ዕለት ፅፈነዋል፡፡
መስቀሉ የተገኘው በመጋቢት ፲ ቀን ቢሆንም በታላቁ በዐቢይ ጾም ተድላ ደስታ ማድረግ በሥርዓተ ቤተክርስቲያን የተከለከለ
በመሆኑ የመስቀሉን በዓል ማክበር የማይቻል ሆነ፡፡ በአበው ውሳኔም ቁፋሮው የተጀመረበትንና ቅዳሴ ቤቱ የከበረበትን መስከረም
፲፯ በደስታና በተድላ እንዲከበር ተደረገ፡፡
የቅድስት ዕሌኒ ባለቤቷ ተርቢኖስ ይባላል፤ በቅድስና ተፋቅረው ነበር የሚኖሩት፤ ተርቢኖስ የሚል ጽሁፍ ያለበት የአንገት ሀብል
አሰርቶላት ነበር። ተርቢኖስ ነጋዴ ስለነበር ከጓደኞቹ ጋር በመርከብ ተሳፍረው እሩቅ አገር ለንግድ ሄደው ከ ፫ ዓመት በኋላ
ይመለሳሉ፤ታዲያ መርከብ ላይ እንዲህ እያሉ ይጫወታሉ፤ እኛስ በሰላም ወደ አገራችን ተመለስን ሚስቶቻችን ግን በሰላም
ይጠብቁን ይሆን ሌላ ወንድ ወደውና ለምደው እንዳይጠብቁን አሉ፤ ተርቢኖስ ደግሞ የእኔ ሚስት ዕሌኒ ከኔ ሌላ ማንንም
አትወድም አትለምድም ይላቸዋል፤ ያንተ ሚስት ከሔዋን ሴቶች ትለያለችን "ሴት ከተመቻት ምን ቁም ነገር አላት" እንዲሉ ፡፡ እኔ
ሄጄ ወድጃት ወዳኝ ለምጃት ለምዳኝ ብመጣ ምን ትሰጠኛለህ ይለዋል ንብረቴ ኹሉ ላንተ ይሁን ይለዋል በወረታቸው
ተወራርደው ይሄዳል፤ የዕሌኒን ገረድ አስጠርቶ ጥሪልኝ ይላታል አረ እመቤቴን እኳን ሌላ ወንድ ፀሐይም አያውቃት ትለዋለች÷
፳ ወቄት ወርቅ እሰጥሻለሁ ይላታልገብታ ትነግራታለች እርሷም ትሰፋለች ቢሉ በወስፌ ትፈትላለች ቢሉ በእንዝርት አደማቻት
ደሟን እያፈሰሰች ወጥታ ይኸው አይሆንልኽም ብልኽ አለሰማ አልከኝ እኔንም አስመታኸኝ ትለዋለች እንግዲያውስ ኹለቱ ብቻ
የሚተዋወቁበትን አንድ ነገር ስጪኝ ይላታል፤ እርሷም እሺ ይኼስ ቀላል ነው አንተ "ነጋዴያን መጡ ፡ ከበሐር ወጡ የብስ
እረገጡ" እያልክ ለፍፍ ትለዋለች፤ እንዳለችው እየዞረ ለፈፈ፤
ገረዷም ወደ ዕሌኒ ቀርባ እመቤቴ ነጋዴዎች መጡ ከበሐር ወጡ የብስ ረገጡ እየተባለ ነው ገላሽን ታጠቢ ሽቶም ተቀቢ
ትላታለች፤ዕሌኒም ይኼን የምታረጊኝ አንቺ አይደለሽ ትላታለች የአንገት ሀብሏን አስቀምጣ ገላዋን ልትታጠብ ትገባለች ይህን ጊዜ
ገረድዋ ወስዳ ትሰጠዋለች፤እርሱም ተርቢኖስ ጋር ሄዶ እየው አፍቅራኝ ወዳኝ ውድ ስጦታ ሰጠችኝ ብሎ ያሳየዋል፤ ሀብሉን
ተመለከተው ተርቢኖስ የሚል ፅሁፍ አለበት ሳይመረምር አመነው፤ እያዘነ ፫ ዓመት የደከመበትን ንብረት አስረክቦ እየተበሳጨ
ወደ ቤቱ ገባ፤ምን ሆነሃል አለችው ንብረቴን ማእበል ወሰደብኝ አላት፤አትዘን አንተም እኔም ብዙ ወዳጆች አሉን ተበድረን
ትነግዳለህ ትለዋለች፤ እርሱም በአሽሙር ልክ ነሽ
ያንቺ ወዳጆች ብዙ ናቸው እኔ ግን ወዳጅ የለኝም ደግሞም ባበደርኩበት አገር ተበድሬ በከበርኩበት አገር ተዋርጄ አልኖርም ፡ ወደ
ሌላ አገር እሄዳለሁ ይላታል፤ "ባልና ሚስት አንድ አካል ናቸው" ካንተ አልለይም ትለዋለች፤ በስውር ሳጥን በልኳ አሰርቶ
በመርከብ ተሳፍረው ይሄዳሉ ፡ በህሩ መሀል ሲደርሱ ሀብሉን አውጥቶ ያሳያታል ስወድሽ ጠላሽኝ ሳምንሽ ካድሽኝ ይላታል፤
ልታስረዳው ሞከረች አላመናትም በብረት ሳጥን ውስጥ አድርጎ ካረግሽው አሣ ይዋጥሽ፡አዞ ይብላሽ ካላረግሽው ለክብር ያብቃሽ
ያንግስሽ ስራሽ ብሎ ከባህር ጣላት ቅዱስ ሚካኤል እየጠበቃት ሳጥኑ ተንሳፎ ሄዶ ባህር ዳርቻ ያርፋል አገሩ ሮም ነው ቆንስጣ
የተባለ አገር ገዢ ከባሕር ሲዝናና ያየዋል የነጋድያን ሳጥን ነው ብሎ አስመጥቶ ቢከፍተው እጅግ የምታምር ሴት አገኘ፤የኢየሱስ
እናት ማርያም የምትባይው አንቺ ነሽን ይላታል፤እኔ ÷ የእርሷ የእግሯ እጣቢ መሆን የማይገባኝ ገረዷ ነኝ እንጂ እርሷን
አይደለሁም፤ ቀን የጣለኝ ብኩን ጊዜ ያዋረደኝ ወቅት የጣለኝ ሴት ነኝ
ትለዋለች፤ወደ ቤተ መንግስቱ ይዟት ገባ፤ አሕዛብ ለፍትወት አይቸኩሉምና ሽቶ እየቀባ በክብር እስከ ፮ ወር ጠበቃት ከዚያም
አገባት በግብርም አወቃት፤መስከረም ፲፪ ቆስጠንጢኖስ ተወለደ፤ በድብቅ የሃይማኖት ትምህርት እያስተማረች አሳደገችው ÷
እንዲኽ ኹን እንዲኽ አትኹን ፡ ክርስቲያኖች እንዲኽ ናቸው እያለች አሰደገችው ምክንያቱም ባለቤቷ ጣኦት አምላኪ ነበርና
ከአወቀ ይገለዋል ብላ፤ ልጇም በ፳፭ ዓመቱ በሮም ነገሠ ክርስትናንም ተቀበለ፤ የንጉሥ ቆስጠንጢኖስን ነገር ከዚኽ ይናገሩታል፡፡
በ፪፻፸፪ ዓ.ም ሰርብያ ውስጥ አሕዛብ ከነበረው አባቱ ከቁንስጣና አይሁዳዊት ከነበረችው እናቱ እሌኒ የተወለደው ታላቁ
ቆስጠንጢኖስም በሮማ ነገሥታት በመክስምያኖስና በዲዮቅልጥያኖስ ስር የምስራቁ ክፍል በነበረው አካባቢ አገረ ገዥ ነበር።
ዲዮቅልጥያኖስና መክስምያኖስ የተባሉት የሮማ ነገሥታት በክርስቲያኖች ላይ ሲያደርሱት የነበረው አሰቃቂ ግፍ ሲያሳዝነው ይኖር
ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ‘’በዝንቱ ትእምርተ መስቀል ትመውእ ፀርከ በዚህ የመስቀል ምልክት ጠላትህን
መክስምያኖስን ድል ማድረግ ትችላለህ’’ የሚል ራእይ በግሪክ ቋንቋ ተጽፎ በሰማይ ላይ ታየው። ወዲያውኑ በሠራዊቱ ትጥቅና
መለዮ ልብስ ላይ የመስቀል ምልክት በማድረግ መክስምያኖስን በሮም አካባቢ በሚግኘው ትቤር ወንዝ ሚልብያን ከተባለው
ድልድይ ላይ በ 312 ዓ.ም ገጥሞ ድል አደረገው። ከዚያም በ 313 ዓ.ም ሚላን ከምትባል ከተማ ላይ ሁኖ ለክርስቲያኖች
የማምለክ ነፃነታቸውን በግዛቱ ኹሉ ያለምንም ፍርሐት
እንዲፈጽሙ በአዋጅ አጸደቀላቸው።
ኢየሱስ ክርስቶስ ማለት እግዚአብሔር ነው፡፡ኾኖም ወልድ ፍጡር እንጅ ፈጣሪ አይደለም ያለዉን የሊብያውን ተወላጅ አርዮስን
ኒቂያ ላይ 318 ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በ 325 ዓ.ም ሰብስቦ በጉባዔ አስወግዞ ከቤተ ክርስቲያን እንዲለይ አድርጎታል።
በዚህ ጉባኤም
የቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና በግልጽ እንዲቀመጥ ተደርጓል። የጉባኤው መግለጫም ዛሬ በቅዳሴ ጊዜ እምነታችንን
የምናረጋግጥበት ‘’ጸሎተ ሐይማኖት’’ ነው። እምነቱም ‘’ኦርቶ ዶክስ ቀጥተኛ እምነት’’ እንዲባል ተወሰነ። ፍትሐ ነገሥትንና
ሐይማኖት አበውን ይመልከቱ ወደ አርስቱ ስንመለስ ፤ የኒቂያ ጉባኤ በተደረገ በ 2 ኛው ዓመት ማለት በ 327 ዓ.ም
የቆስጠንጢኖስ እናት እሊኒ የክርስትናን እምነት ከተቀበለች በኋላ ብዙ ሠራዊት አስከትላ መስቀሉን ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም
ተጓዘች። መድኅኒታችን ክርስቶስ የተሰቀለበት ክቡር መስቀል ብዙ ታምራትን እየሠራ አይሁድን ስላበሳጫቸው መስቀሉን ጉድጓድ
አስቆፍረው እንዲቀበር ካደረጉ
በኋላ የከተማው ቆሻሻ በዚያ ላይ እንዲጣልበት አድርገው ለ 294 ዓመት አቆይተውት ነበር። ይህም በመሆኑ መስቀሉ የት
እንደተቀበረ ለማወቅ አስቸጋሪ ነበር። ብዙ የእድሜ ባለፀጋ
የነበሩትን የአይሁድ ሽማግሌዎች እሌኒ እያስጠራች በመጠየቅ ብዙ ሙከራ አድርጋ ነበር። በመጨረሻ አንድ ኪርያኮስ የተባለ
ሺማግሌ ‘’ከእኛ የቀደሙ አባቶች መስቀሉ ከዚህ አካባቢ እንደተቀበረ ሲናገሩ እሰማ ነበር ፥ ነገር ግን መቃብሩን ለይተው
አላሳዩንም አላት። እሌኒም ራሱ ክርስቶስ እንዲገልጥላት ጸለየች። ክርስቶስም ልመናዋን ሰምቶ መላኩ ቅዱስ ራጉኤልን ላከላት።
መላኩ ራጉኤልም በሺማግሌ አምሳል ቁሞ ደመራ ኣስደምራ ምህላና ጸሎት አድርጋ እጣን ጨምራ እንድታቃጥልና
ጢሱ ሂዶ የሚያርፍበት ቦታ ላይ እንድታስቆፍር ነገራት። ንግሥት እሌኒም መላኩ እንዳዘዛት ደመራዉን መስከረም 16 ቀን 327
ዓ.ም አስደምራ በበነገው መስከረም 17 ቀን እንዲቃጠል አድርጋ ጢሱ ካረፈበት ቦታ ላይ ማስቆፈሩን ጀመረች። ቁፋሮው 6
ወር ፈጂቶ መጋቢት 10 ቀን መስቀሉ ከተቀበረበት ወጣ።ንግሥት እሌኒም ጎልጎታ ላይ ቤተክርስቲያን አሰርታ በክብር በቤተ
መቅደስ ውስጥ እንዲቀመጥ አደረገች። ይህ በሆነ ከ 287 ዓመት በኋላ ፀሐይ አምላኪ የነበረው ቾስሮኤስ የተባለው የፋርስ
ጀኔራል በ 614 ዓ.ም ኢየሩሳሌምን
ወሮ መስቀሉን ከሌላ ንብረት ጋር ማርኮ ወደ ሀጋሩ ወሰደው። 9 ዓመት በምርኮ ፋርስ ውስጥ ከቆየ በኋላ የቪዛንታዩኑ ንጉሥ
ሕርቃል በ 614 ዓ.ም ወደ ፋርስ ዘምቶ መስቀሉን እንደገና ማርኮ ወደነበረበት ቤተመቅደስ አስገባው። ሕርቃል ይህን በማድረጉ
ለስሙና ለድርጊቱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የቤተ ከርስቲያን አባቶች ከ 40 ጾም ጋር አንድ ሳምንት ጨምረው የመጀመሪያውን
ሳምንት ‘’ጾመ ሕርቃል’’ ብለውታል።
ከ 1374—1406 የኢትዮጵያ ንጉሥ በነበሩት በአፄ ዳዊት ዘምንመስከረም 10 ቀን መዳኅኒታችን ክርስቶስ ቀኝ እጁ
የተቸነከረበት ግማደ መስቀሉ በግብጽ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገባ። አፄ ዳዊት ከብዙ ሠራዊታቸው ጋር ሥናር (ሱዳን) ድረስ ሂደው
ተቀበሉት። ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ሲዘዋወር ከቆየ በኋላ የአፄ ዳዊት ልጅ ታላቁ ንጉሠ ነገሥስት ዘራያዕቆብ (1434—
1468) ‘’አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል=መስቀሌን የመስቀል ምልክት ባለበት ቦታ ላይ አስቀምጥ ‘’ የሚል ራዕይ ስላየ ግሸን
ማርያም ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል። እስከዛሬ ድረስ በዚያው በግሸን ይገኛል።
በመስቀሉ ላዳነን ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በመስቀሉ ሀይልም ሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ይጠብቀን፡፡ ከዚያም በጸሎቷ
ላይ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጾላት በዕጣን ጢስ አማካይነት እንደምታገኘው ተረድታ፤ መስከረም ፲፮ ደመራን አስደምራ በእሳት
እንዲቃጠል አድርጋ እጅግ ብዙ ዕጣንን ብታስጨምር ጢሱ ወደ ሰማያት ወጥቶ መስቀሉ ካለበት ቦታ ላይ ተተክሎ ሰገደ፤
“ተተክለ ጢስ ኀበ አንጻረ መስቀል፤ ሰገደ ጢስ ወባረከ” እንዲል ቅዱስ ያሬድ። ርሷም ፈጣሪዋ እግዚአብሔርን በፍጹም ደስታ
አመስግና ቊፏሮውን ከመስከረም 17 ዠምሮ እስከ መጋቢት 10 ድረስ እንዲቈፈር አስደርጋለች፤ በቊፋሮው ወቅትም የፈያታዊ
ዘየማንና የፈያታዊ ዘጸጋም መስቀል ቢገኙም ዕውር አላበሩም፣ ሕሙማንን አልፈወሱም፡፡
ከዚያም መጋቢት 10 በ 327 ዓ.ም. ክብር ይግባውና ጌታችን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት ቅዱስ መስቀሉ ተገኘ፤ በዚኽ ጊዜ
ከሕሙማን ላይ ቢያደርጉት ኹሉንም ፈወሳቸው፣ ዕዉራን በሩ፣ ሙታንም ተነሡ፡፡ ከዚኹም ጋር የተወጋበት ጦሩ፣
የተቸነከረባቸው ቅንዋት ኹሉ ተገኝተዋል፤ ርሷም በፈረሷ ልጓም ላይ የመስቀል ምልክትን አስቀርጻበታለች፡፡ ርሷም ጌታችን
ተአምራት በሠራባቸው ቦታዎች አብያተ ክርስቲያናትን በማሠራት፤ በተለይም በጎልጎታ የተሠራው ቤተ ክርስቲያን መስከረም ፲፯
ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምእመናን በተገኙበት ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑ ተከብሯልና፡፡ ርሷም ለድኾችና ለጦም አዳሪዎች ብዙ መልካም
ነገርን በማድረግ ግንቦት ፱ በሰላም ዐርፋለች፡፡ሊቁ አርከ ሥሉስም ስለ ቅድስት እሌኒ በዐርኬው ላይ፡- “ሰላም ለእሌኒ ውስተ
ምድረ ሕይወት ኤልዳ ምክረ መንፈስ ቅዱስ አመ ወሰዳ ለዘሐይወ በድን በለኪፈ መስቀል ቅድመ ዐውዳ እምአይቴ አንተ ትቤሎ
ወእምአይ አንግዳ ዘተረከብከ ግዱፈ በበዳ” (የመንፈስ ቅዱስ ምክር በወሰዳት ጊዜ ኤልዳ ወደ ተባለች የሕይወት ምድር የኼደች
ለኾነች ለዕሌኒ ሰላምታ ይገባል፤ በአደባባይዋ ፊት መስቀልን በመንካት የዳነውን በድን በበረሓ ወድቀኽ የተገኘኽ አንተ እንግዳ
ከወዴት ነኽ አለችው) በማለት መስቀሉ ከወጣ በኋላ ስለተደረገላት ተአምር ጽፏል፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በተአምኆ ቅዱሳን
መጻሕፍት ላይ፡-“ሰላም ለእሌኒ ንግሥት ዘከሠተት መስቀለ በጎልጎታ:ለክርስቲያን ዘይከውን ወልታ፤እምኀበ ወጽአ ጢስ
በሃይማኖታ፤ወዓዲ ረከበት ቅንዋተ መስቀሉ ለክርስቶስ፤ወአግበረት ልጓመ ፈረስ በከመ ይቤ ዘካርያስ”፡፡(ጢስ በሃይማኖቷ ከወጣ
ዘንድ ለክርስቲያን ጋሻ የሚኾን መስቀልን በጎልጎታ ያወጣች ለኾነች ለንግሥት እሌኒ ሰላምታ ይገባል፤ ዳግመኛም የክርስቶስን
የመስቀሉን ችንካሮች አገኘች፤ ዘካርያስ እንደተናገረው ለፈረስ ልጓምን አሠራች) በማለት ይጠቅሳል፡፡
የነገረ መስቀሉን ነገር ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ሲያመሰጥረው፡- “መስቀልከ ዕፅ ዘኢይነቅዝ መስቀልከ ዕፅ ዘኢየዐብር መስቀልከ
ዕፅ ዘኢይማስን…” (መስቀልኽ የማይነቅዝ ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ የማይዋጋ (የማይደርቅ) ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ የማይጠፋ ዕፅ ነው፤
መስቀልኽ የፀሓይ ሙቀት የነፋሳትም ግርፋት የማያደርቀው ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ ውሆችና የነፋሳት ንውጽውጽታዎች
ሊያነዋውጡት የማይቻላቸው ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ የባሕር ሞገዶች ሊገፉት የማይቻላቸው ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ የዝናማት ክብደት
ሊጥሉት የማይቻላቸው ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ ርኩሳን መናፍስት ሊቀርቡት የማይቻላቸው ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ ከገነት ዛፎች
መኻከል የሚመስለው የሌለ፤ ከበረሓ ዕንጨቶች መኻከልም የሚተካከለው የሌለ ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ ከዐርዘ ሊባኖስ መኻከል
የሚመስለው ከምርስኔም ዛፎች መኻከል የሚተካከለው የሌለ ዕፅ ነው፤ የኢላጤኖስ ዛፎችም እንደ አበቃቀሉ አይኾኑም፤ የቄድሮን
ዛፎች በውበት አይተካከሉትም፤ የጳውቄናም ዛፎች አይመስሉትም፤ መስቀልኽ በሌሎች ዛፎች ላይ የማይመካ ለስላሳ ዕፅ ነው፤
መስቀልኽ በርሱ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይል ዘንድ የወደደው ዕፅ ነው፤ መስቀልኽ ከቅርንጫፎቹ የወይንን ዝናማት ያንጠጣን፡፡

You might also like