Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 22

12ኛ ትምህርት

ዮሴፍ፡ የግብፅ ልዑል

ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን
ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 41:37–46፣ 1ነገሥ. 3:12፣
ዘፍ. 42፣ ሮሜ 5:7–11፣ ዘፍ. 43፣ ዘፍ. 44፣ ዘፍ. 45።

የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ከዚያም ፈርዖን ዮሴፍን፣


‘በመላይቱ የግብፅ ምድር ላይ ኃላፊ አድርጌሃለሁ’ አለው”
(ዘፍ. 41፡41)።

አ ሁን ዮሴፍ የግብፅ መሪ በመሆኑ፣ ማንነቱን


የማያውቁት ወንድሞቹ በፊቱ ይሰግዳሉ (ዘፍ. 42)።
ዮሴፍ ወንድሞቹ ከታናሽ ወንድማቸው ብንያም ጋር
ተመልሰው እንዲመጡ ሲያስገድዳቸው በትህትና
እሺታቸውን ያሳያሉ (ዘፍ. 43)። የብንያም ደኅንነት ጉዳይ
ቢያሳስባቸውም (ዘፍ. 44) ይህ “እንደ ፈርዖን”
የተመለከቱትን ብርቱ ሰው በጎነት ያሳያቸው ዘንድ ተማጽኖ
ያቀርባሉ። በመጨረሻ ዮሴፍ ማንነቱን ሲገልጥላቸው፣
እነርሱ ያን ቢያደርጉም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያን ሁሉ
ወደ መልካም እንደለወጠው ይገነዘባሉ።

የሚገርመው፣ ይህ እንደ ዮሴፍ ስኬት የታሰበው


ተያያዥነት ያለው አጠቃላይ ክስተት፣ በአብዛኛው
የሚያወሳው በወንድሞቹ ንስሐ ዙሪያ ነው። ከዮሴፍ ወደ
አባታቸው ያደረጓቸው የጉዞ ምልልሶች፣ እንዲሁም
የገጠሟቸው መሰናክሎች በዮሴፍ እና በአባታቸው ላይ
ያደረጓቸውን ዕኩይ ድርጊቶች እንዲያስታውሱና
በእግዚአብሔር ላይ የፈጸሙትን ዐመጻ እንዲገነዘቡ
አድርጓቸዋል። የዮሴፍ ወንድሞች እነዚህን የገጠሟቸውን
ፈታኝ ተሞክሮዎች እንደ መለኮታዊ ፍርድ ቆጥረዋቸዋል።
ሆኖም የክስተቱ መደምደሚያ የሁሉንም ስሜት ፈንቅሎ
በደስታ ዕንባ ያራጨ ቢሆንም፣ ኢ-ፍትሐዊ የክፋት ድርጊት
ለፈጸሙት፣ ለእነርሱ፣ የይቅርታ መልዕክት ይዟል።

እሁድ:- ሰኔ 5

የዮሴፍ ወደ ሥልጣን ከፍታ መውጣት

ለዮሴፍ፣ የፈርዖን ሕልሞች እግዚአብሔር በምድሪቱ


“ሊሠራው ያለውን” (ዘፍ. 41፡28) ነገር የገለጠ ነበር።
ይሁን እንጂ ዮሴፍ--ንጉሡ ፈርዖን እርሱ በሚያምነው
እግዚአብሔር አምላክ እንዲያምን ጥሪ አላደረገለትም።
ከዚህ ይልቅ ዮሴፍ በተግባር የተገለጠ ፈጣን ምላሽ
ይሰጥ ነበር። ዮሴፍ የምጣኔ ሀብት መርኀ ግብር ንድፈ
ሀሳብ ለንጉሡ አቅርቧል። የሚገርመው በፈርዖን አእምሮ
የቀረው ይህ ዮሴፍ ምጣኔ ሀብትን አስመልክቶ
የተናገረው ክፍል ብቻ ነበር። በዚህም ያየው ህልም
ከነበረው መንፈሳዊ ትርጉም እና ሕልሙን በመስጠት
ዙሪያ ካለው አምላካዊ ሚና ይልቅ፣ በምጣኔ ሀብት
አስተምህሮዎቹ ፋይዳ ላይ ይበልጥ ፍላጎት የነበረው
ይመስላል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 41፡ 37-57። በዮሴፍ ስኬት


ውስጥ የእግዚአብሔር ቦታ ምንድን ነው?

ፈርዖን ዮሴፍን የመረጠው ሕልሙን በትክክል


ስለተረጎመና መጪውን የምድሪቱን ችግር ስለገለጠ ብቻ
ሳይሆን ለችግሩ መፍትሔ ስለነበረው እና “ዕቅዱ
መልካም” (ዘፍ. 41፡37) ስለነበር ጭምር ሲሆን፣ ይህ
ደግሞ የፈርዖን ሹማምንት በአንድነት የተጋሩት ሀሳብ
ነበር። የፈርዖን ምርጫ ከመንፈሳዊው ይልቅ በተጨባጭ
ጉዳይ ነገር ላይ የሚያመዝን ይመስላል። ሆኖም
“አስተዋይና ብልኅ” (ዘፍ. 41፡39) በሆነው ዮሴፍ ላይ
“የእግዚአብሔር መንፈስ” (ዘፍ. 41፡38) መኖሩን ፈርዖን
ተገንዝቦ ነበር። መግለጫው ይህ ዓይነቱ ብልሃትና
ማስተዋል በተለይ ከእግዚአብሔር ብቻ እንደሚሰጥ
ያሳያል። (ያስተያዩ፡ ዘፍ. 41፡33 እና 1ነገሥ. 3፡12)።

በመጽሐፍ ቅዱስ የቀረቡት ዝርዝር ጉዳዮች በሙሉ


ከወቅቱ የግብፅ ታሪካዊ ሁኔታ ጋር የሚስማሙ ናቸው።
ከፖለቲካ ውሳኔ አኳያ ፈርዖን ዮሴፍን ከፍተኛ ባለሥልጣን
አድርጎ መመደቡ በጥንታዊቷ ግብፅ ያልተለመደ አሠራር
አልነበረም።

ቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት የተትረፈረፉ ምርቶች


የተሰበሰቡባቸው ከመሆናቸው አኳያ “ልኩን መስፈርና
መመዝገብ” (ዘፍ. 41፡49) የማይቻል እህል መገኘቱ
የአምላካዊው መግቦት ምልክት ነበር። “እንደ ባሕር
አሸዋ” (ዘፍ. 41፡49) በሚል የቀረበው ማነጻጸሪያ ይህ
የእግዚአብሔር በረከት (ዘፍ. 22፡17) መሆኑን ያሳያል።
ዮሴፍ ሥራውን ውጤታማ አድርጎ የባረከለት ከእነዚህ
ሁለት ክስተቶች በስተጀርባ ያለ አንድ አምላክ እንደሆነ
ያንጸባርቃል። ዮሴፍ ስሞቻቸው እግዚአብሔር ለእርሱ
ያደረገለትን በጎነትና ህመም ያለውን ትውስታ ወደ ደስታ
(ምናሴ) መቀየሩን እና የቀድሞው መከራ ወደ ፍሬያማነት
(ኤፍሬም) መለወጡን የሚያሳዩ ሁለት ወንዶች ልጆች
ወልዷል። እግዚአብሔር መጥፎውን ወደ መልካም
የቀየረበትን የሚያሳይ እንዴት ያለ ታላቅ ምሳሌ ነው!

ሌሎች አምላካችንን በተጨባጭ እንዲያዩ የሚያስችለው


የትኛው የሕይወታችን ክፍል ነው?

ሰኞ:- ሰኔ 6

ዮሴፍ ወንድሞቹን ፊት ለፊት መጋፈጡ

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. ምዕ. 42። እዚህ ላይ ምን


ተከሰተ? ሰብዓዊው ፍጡር በክፋትና ስህተት የተሞላ
ቢሆንም ይህ አምላካዊውን በጎነት እንዴት ይገልጻል?
ረሃቡ ያዕቆብ ልጆቹ ወደ ግብፅ ወርደው እህል ይገዙ
ዘንድ እንዲልካቸው አስገደደው። የሚገርመው ይህን
ሀሳብ ያመነጨው ያዕቆብ ነበር (ዘፍ. 42፡1)።
ከቁጥጥሩ ውጭ በሆኑ ሁናቴዎች ሰለባ የሆነው አሳዛኙ
አዛውንት፣ ከብዙ ጊዜ በፊት አልቅሶ እርሙን ካወጣበት
ልጁ ጋር እንደገና የሚገናኝበትን አስገራሚ ሁናቴ
ሳያውቀው ይቀይሳል።

በዚህ አምላካዊውን ቸርነት ባህሪ የተላበሰ ዳግም


መገናኘት ውስጥ ሁለት መሠረታዊ ባህሪያት ጎልተው
ይታያሉ። በመጀመሪያ፡ የዮሴፍ ሕልም ፍጻሜ ሆኖ
ይታያል። “ ‘…የእናንተ ነዶዎች ዙሪያዋን ከበው ለእኔ ነዶ
ሰገዱላት’ ” (ዘፍ. 37፡7) በሚል በዮሴፍ ትንቢታዊ
ሕልሞች አስቀድመው የተነገሩት ክስተቶች አሁን ፍጻሜ
እያገኙ ነው። ዮሴፍ “የምድሪቱ ገዥ” (ዘፍ. 42፡6) እና
“የአገሩ ጌታ” ነበር (ዘፍ. 42፡30፣33)። ዮሴፍ የነበረው
ከፍተኛ ማዕረግ ወንድሞቹ ይገኙበት ከነበረው ችግረኛ
ሁናቴ በእጅጉ የተለየ ነበር፡ “የዮሴፍ ወንድሞችም እንደ
ደረሱ፣ ከፊቱ ቀርበው ወደ ምድር ለጥብለው እጅ ነሱት”
(ዘፍ. 42፡6)። ይህን ያደረጉት በዮሴፍ ሕልም ያፌዙት እና
ፍጻሜ ማግኘቱን የተጠራጠሩት እነዚያው 10 ወንድሞቹ
ነበሩ (ዘፍ. 37፡8)።

በሁለተኛ ደረጃ፡ ይህ በአምላካዊው ቸርነት እውን መሆን


የቻለ ዳግመኛ መገናኘት እንደ ምላሽ ሆኖ ተገልጾአል።
በሁለቱ ክስተቶች መካከል ያስተጋባው አነጋገርና ጭብጥ
ለሠሩት በደል ቅጣት የመቀበል ባህሪ እንዳለው ያሳያል።
“ተባባሉ” (ዘፍ. 42፡21) የሚለው ቃል፣ በዮሴፍ ላይ
ማሴር ሲጀምሩ ጥቅም ላይ ውሎ ነበር (ዘፍ. 37፡19)።
ወንድማማቾቹ በእስር ቤት እንዲቆዩ መደረጉ (ዘፍ.
42፡17) የዮሴፍን በእስር ቤት መቆየት ያስተጋባል (ዘፍ.
40፡ 3-4)። እንደውም፣ የዮሴፍ ወንድሞች አሁን በእነርሱ
ላይ እየደረሰ ያለውን ነገር ከ20 ዓመታት በፊት
በወንድማቸው ላይ ካደረጉት ጋር ያነጻጽራሉ። “እርስ
በርሳቸውም፣ ‘ይኸው በወንድማችን ላይ ባደረስነው
በደል ምክንያት ቅጣታችንን እየተቀበልን ነው። እርሱ
እንደዚያ ተጨንቆ ስለ ሕይወቱ ሲማጠነን፣ እኛ
አልሰማነውም ነበር፤ ይህ መከራ የደረሰብንም በዚሁ
ምክንያት ነው’ ተባባሉ።” (ዘፍ. 42፡41)።

“ ‘ደሙ ከእጃችን ይፈለጋል’ ” (ዘፍ. 42፡22) ሲል ሮቤል


የተናገራቸው ቃላት “ ‘የሰው ደም አታፍስሱ’ ” (ዘፍ.
37፡22) በማለት ቀደም ሲል የሰጠውን ማስጠንቀቂያ
የሚያስተጋባ ሲሆን፣ አሁን እየተጋፈጡ ባለው ሁናቴና
ቀደም ሲል ባደረጉት መካከል ላለው ግንኙነት አጽንኦት
ይሰጣል። አብዛኞቻችን ይቅርታ እንድንጠይቅ
የሆንባቸውን በእርግጠኝነት አድርገናል። ላደረግነው
ነገር፣ በተቻለ የምንችለው እንዴት ነው? በተጨማሪ
እግዚአብሔር አማካኝነት የሰጣቸውን የይቅርታ ተስፋዎች
መቀበላችን ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው (ሮሜ
5፡7–11)? ነገሮች ልንክስ በየሱስ በእጅጉ
ማክሰኞ:- ሰኔ 7

ዮሴፍ እና ብንያም

ያዕቆብ ከራሔል የወለደውና ከእርሱ ጋር ያለው ብቸኛ


ልጁ ብንያም፣ አብሯቸው እንዲሄድ በቀላሉ ሊፈቅድ
አልቻለም። ዮሴፍን እንዳጣ ሁሉ፣ እርሱንም እንዳያጣ
ፈራ (ዘፍ. 43፡6-8)። ሆኖም የመጣውን እህል በልተው
ከጨረሱና (ዘፍ. 43፡2) ይሁዳ ለብንያም መመለስ
ኃላፊነት ከወሰደ በኋላ (ዘፍ. 43፡9)፣ በመጨረሻ
ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ግብፅ እንዲወርዱና ብንያምም
አብሯቸው እንዲሄድ ያዕቆብ ፈቀደ።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. ምዕ. 43። የብንያም መገኘት


በክስተቶች ሂደት ላይ ምን ተጽእኖ ነበረው?
የብንያም መገኘት በክስተቶቹ ላይ ሚዛን እንዲደፋ
አድርጓል። ሁሉም ወንድሞቹ በዮሴፍ ፊት ቆመው ሳለ፣
ዮሴፍ የሚመለከተው ብቸኛ ሰው ብንያም ነበር (ዘፍ.
43፡16)። “ወንድሜ” ብሎ በብቸኝነት የጠራው ብንያምን
ነው (ዘፍ. 45፡12)። ብንያምን በስሙ የጠራው ሲሆን፣
ሌሎቹን ግን በስም አልጠቀሰም። ይልቁንም “ሰዎች”
በሚል እንደተጠቀሱ እንመለከታለን (ዘፍ. 43፡16)።

ዮሴፍ ብንያምን “ ‘ልጄ’ ” ብሎ የጠራው ሲሆን፣ ይህ


ደግሞ ለእርሱ ያለውን የተለየ ፍቅር ያሳያል (ጥቅሶቹን
ያነጻጽሩ፡ ዘፍ. 43፡29 እና ዘፍ. 22፡ 8)። የዮሴፍ
ብንያምን መባረክ “ጸጋን” (ዘፍ. 43፡29) የሚያሳይ
ሲሆን፣ እርሱ ከሌሎቹ ወንድሞቹ ያላገኘውን ጸጋ
ለብንያም ይመልስለታል።

የዮሴፍ ወንድሞች በተመለሰው ገንዘብ ምከንያት እስር


ቤት እንዳይገቡ ቢፈሩም፣ ዮሴፍ ግን የብንያምን መገኘት
አስመልክቶ ግብዣ አዘጋጀላቸው። ሁኔታው ብንያም
ለአጠቃላዩ ክስተት የመዋጀት ውጤት ያስገኘ ያህል
ነበር። ወንድማማቾቹ የተቀመጡት እንደየ ዕድሜአቸውና
የተዋረድ ክብራቸው ቢሆንም፣ ነገር ግን ለታናሹ
ወንድማቸው ብንያም ከሌሎቹ አምስት እጥፍ የላቀ
መስተንግዶ ተደረገለት (ዘፍ. 43፡33-34)። ይህም ሆኖ፣
ከብዙ ዓመታት በፊት ዮሴፍ የአባቱ ተወዳጅ በነበረበት
ወቅት፣ በግማሽ ወንድማቸውና በገዛ አባታቸው ላይ
እንዲፈጽሙ ከገፋፋቸው ዘግናኝ ድርጊት በተቃራኒ፣ አሁን
የተመለከቱት አድልዎ አልረበሻቸውም (ዘፍ. 37፡3-4)።

“ዮሴፍ ለብንያም ይህን የተለየ ውለታ መፈጸሙ


ወንድሞቹ ከዚህ በፊት ለእርሱ ያሳዩትን ቅናትና ጥላቻ
አሁንም በብንያም ላይ ይደግሙት እንደሆን በማየት
ለማረጋገጥ ነበር። ወንድማማቾቹ የሚነጋገሩበትን ቋንቋ
ዮሴፍ አይረዳም በሚል አስተሳሰብ እርስበርሳቸው
በነጻነት ይጨዋወቱ ነበር። ይህ ደግሞ የእነርሱን እውነተኛ
ስሜት ለመረዳት ይችል ዘንድ ለዮሴፍ ጥሩ አጋጣሚ
ፈጠረለት። አሁንም ተጨማሪ ፈተና ሊፈትናቸው ስለፈለገ
ወደ አገራቸው ለመጓዝ ከመነሳታቸው አስቀድሞ በታናሽ
ወንድማቸው ስልቻ ውስጥ የራሱ የብር ዋንጫ
እንዲቀመጥ ትዕዛዝ ሰጠ።”--ኤለን ጂ. ኋይት፡
የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ፡ 254።

ረቡዕ:- ሰኔ 8

የብር ዋንጫው

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. ምዕ. 44። ዮሴፍ የብር ዋንጫው


በሌሎቹ ወንድሞቹ ስልቻ ሳይሆን፣ በብንያም ስልቻ
ውስጥ እንዲከተት ለምን አደረገ?

ይህ ታሪክ ቀደም ብሎ ከቀረበው ጋር ይመሳሰላል።


ቀደም ሲል እንዳደረገው ዮሴፍ ዝርዝር መመሪያዎችን
ለቤቱ አዛዥ በመስጠት አሁንም በድጋሚ በየሰዎቹ ስልቻ
እህል እንዲቋጠር ያደርጋል። በዚህ ጊዜ ግን ውድ የሆነው
የእርሱ መጠጫ ዋንጫ በብንያም ስልቻ ውስጥ
እንዲከተት ዕንግዳ ትእዛዝ ይሰጣል።

ይህን ተከትሎ ነገሮች የተለየ መልክ እንዲይዙ ይሆናሉ።


በከዚህ ቀደሙ ጉዞአቸው ወንድማማቾቹ ወደ ከነዓን
የተመለሱት ብንያምን ይዘው ለመምጣት ሲሆን፣ አሁን
ግን ዮሴፍን ለመጋፈጥ ወደ ግብፅ መመለስ አለባቸው።
ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ ሁሉም በየስልቻዎቻቸው
ውስጥ ተመሳሳይ ነገር አግኝተው የነበረ ሲሆን፣ አሁን
ግን የዮሴፍ ጽዋ በብንያም ስልቻ ውስጥ ተገኝቷል
በሚል እርሱ ብቻ ተለየ። በዮሴፍ ገበታ የክብር
ዕንግድነት የተሰጠውና ዋንጫውን የማግኘት ዕድል
የነበረው ብንያም፣ አሁን ያንን ውድ ዋንጫ ሰርቋል በሚል
ተጠርጥሮ ክስ ተመሠረተበት። ወደ እስር ቤት ያመራል።
የብር ዋንጫው ስርቆት በወንድሞቹ ልብ ውስጥ
የጥፋተኝነት ስሜት እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆነ። ይሁዳ
ዮሴፍ የተናገረውን የተረጎመበት መንገድ ይኸው ነበር።
ምክንያቱም እግዚአብሔር በእነርሱ ውስጥ ያገኘውን
በደል ይጠቅሳል (ዘፍ. 44፡16)። በተጨማሪ የዚህ ውድ
ጽዋ መሰረቅ ከባድ ቅጣት የሚያስከትል ከመሆኑም
በላይ፣ የሌሎች ወንድሞቹን አስተሳሰብም የሚፈትን
ይሆናል።

በወንድማማቾቹ የተስተዋለው ጥልቅ ስሜትና ለጉዳዩ


የሰጡት ምላሽ ከፍ ያለ ትርጉም አለው። ብንያም እንደ
ወንድሙ ዮሴፍ መጥፋቱ ነው ብለው በመስጋት ሁሉም
ተመሳሳይ ህመም ተጋሩ። ምንም እንኳ ዮሴፍ እንደ
ብንያም ንጹህ የነበረ ቢሆንም፣ እነርሱም በግብፅ ባሪያ
እንደሚሆኑ አስበዋል። ዐውራው በግ በይስሐቅ “ፈንታ”
መሥዋዕት እንደሆነ ሁሉ (ዘፍ. 22፡13) ይሁዳም
በብንያም “ፈንታ” (ዘፍ. 44፡33) ባሪያ ሆኖ እዚያው
ለመቅረት ሀሳብ አቀረበ። ይሁዳ ራሱን እንደ መሥዋዕት፣
እንደ ምትክ አድርጎ ያቀረበበት ዓላማ፣ በአባቱ ላይ
የሚደርሰውን “መከራ” ለመጋፈጥ በማሰብ ነው (ዘፍ.
44፡ 34)።

በይሁዳ ምላሽ ስለ ምትክነት በምሳሌነት የተገለጸው


የትኛው የፍቅር መሠረታዊ ሥርዓት ነው? እንዲህ ዓይነቱ
ፍቅር መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የድነት ሥነ መለኮታዊ
አስተምህሮ እንዴት ያብራራል (ሮሜ 5፡8)?

ሐሙስ :- ሰኔ 9

“ ‘እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ’ ”

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. ምዕ. 45። በዚህ


ታሪክ ውስጥ የምናገኛቸው የፍቅር፣ እምነት እና የተስፋ
ትምህርቶች ምን ይመስላሉ?
ይሁዳ “ ‘በአባቴ’ ” ላይ ሊደርስ ስለሚችለው “ ‘መከራ’ ”
(ዘፍ. 44፡34) ብሎ እንደ ተናገረ፣ ዮሴፍ “ ‘ድምፁን ከፍ
አድርጎ አለቀሰ’ ” (ዘፍ. 45፡1)፣ ከዚያም “ራሱን”
ለወንድሞቹ “ገለጠላቸው”። እንዲህ ያለው አነጋገር
እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበትን መንገድ ለማውሳት
ተደጋግሞ ጥቅም ላይ ከመዋሉ አኳያ (ዘፀ. 6፡3፣ ሕዝ.
20፡9) በዚህ ስፍራ እግዚአብሔር ራሱን መግለጡንም
እንዲሁ ይጠቁማል። ይህ ማለት ሰብዓዊው ፍጡር
የቱንም ዓይነት እንከን ቢኖርበትም፣ የጌታ በጎነት
እንደሚነግሥ ያሳያል።

የዮሴፍ ወንድሞች የሚሰሙትንም ሆነ የሚያዩትን ፈጽሞ


ማመን አልቻሉም። ስለዚህ “ ‘እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ’
” (ዘፍ. 45፡4) ብሎ በድጋሚ ለመናገር ተገደደ። ሆኖም “
‘ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ’ ” (ዘፍ. 45፡4) የሚለውን ቁርጥ
ያለ አነጋገር ሲሰሙ ብቻ አመኑ።
ከዚያም ዮሴፍ እግዚአብሔር “ ‘እኔን ወደዚህ ልኮኛል’ ”
(ዘፍ. 45፡5) ሲል ይናገራል። ይህ እግዚአብሔር
የተጠቀሰበት መንገድ ድርብ ዓላማ አለው። አንዱ፡ ዮሴፍ
ስለ እነርሱ መጥፎ ስሜት እንደሌለው ወንድሞቹን
ለማረጋጋት ሲሆን፤ ሌላው ጥልቅ የሆነ የእምነት ኑዛዜ
እና የተስፋ መግለጫ ነው። ምክንያቱም እነርሱ ያደረጉት
ነገር አስፈላጊ ነበር። እንዴት ቢባል እግዚአብሔር እነርሱን
“ ‘በታላቅ ማዳን ለመታደግና ዘራቸው እንዳይጠፋ
በማሰብ’ ” (ዘፍ. 45፡7) ይህ እንዲሆን ፈቀደ።

ከዚያም አባታቸው ወደ ግብፅ እንዲመጣ ያዘጋጁት ዘንድ


ዮሴፍ በፍጥነት ወደዚያው እንዲያመሩ ያደርጋል።
ጥሪውን የሚያጅበው ለግጦሽ የሚሆን መስክ
የታደለውንና “ ‘እጅግ ለም’ ” (ዘፍ. 45፡18፣20) የሆነውን
ጌሤም ለመኖሪያነት እንደሚሰጣቸው በመጥቀስ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ለጉዞ የሚሆን ሠረገላ እንዲዘጋጅ ሆነ።
ይህ ደግሞ ልጆቹ ስለገጠማቸው ነገር እየዋሹት
እንዳልሆነ ያዕቆብን የሚያሳምን ይሆናል (ዘፍ. 45፡27)።
ያዕቆብ ይህን የቀረበለትን ግልጽ ትዕይነት--ዮሴፍ
በሕይወት ለመኖሩ እንደ ተጨባጭ ማስረጃ ወሰደው።
ዮሴፍ በሕይወት መኖሩን ማወቁ ብቻ ለእርሱ በቂ ነበር
(ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዘፍ. 37፡35 እና ዘፍ. 44፡29)።

አሁን ነገሮች በመልካም ሁኔታ ላይ ናቸው። የያዕቆብ 12


ልጆች በሕይወት አሉ። ያዕቆብ አሁን “እስራኤል” (ዘፍ.
45፡28) ተብሎ የተጠራ ሲሆን፣ በዚህም አምላካዊው
በጎነት በብርቱ መንገድ መገለጥ ችሏል። አዎ፣ ዮሴፍ
ለወንድሞቹ ደግ ነበር። ደግሞም ያን ለማድረግ
የሚያስችል አቅም ነበረው። አንዳንዶች ክፉ
በያደርጉብንም፣ እንደ ዮሴፍ ሁሉ በመጨረሻ
ሊሠምርላቸው ለማይችለው-መልካም መሆንን
የምንማረው እንዴት ነው?

አርብ:-ሰኔ 10
ተጨማሪ ሀሳብ

ኤለን ጂ. ኋይት “ዮሴፍ በግብፅ” ገጽ፡ 237 -247፣


“ዮሴፍ እና ወንድሞቹ” ገጽ፡ 248–270--የኃይማኖት
አባቶችና ነቢያት። “ሦስቱ የእሥር ቀናት ለያዕቆብ ልጆች
መሪር የሐዘን ቀናት ነበሩ። ከዚህ በፊት የተከተሉትን
የተሳሳተ ጎዳና በተለይም በዮሴፍ ላይ የፈጸሙትን
የጭካኔ ድርጊት አሰላስለዋል። ሰላዮች ናቸው ተብለው
ከተፈረደባቸውና ንጽህናቸውን የሚያመለክት ማስረጃ
ማቅረብ ካልቻሉ፣ ሞት ወይም ባርነት እንደሚጠብቃቸው
ያውቁ ነበር። እነርሱ ዮሴፍን ለባርነት በመሸጣቸው
ምክንያት እግዚአብሔር አምላክ ባሪያዎች እንዲሆኑ
በማሰቃየት ሊቀጣቸው እንዳቀደ በማሰብ ፍርሃት
ገባቸው። ዮሴፍ አባቱና ወንድሞቹ በእህል እጦት ሥቃይ
ሳይደርስበቸው አይቀርም ብሎ ሰግቷል። ወንድሞቹ
በእርሱ ላይ ለፈጸሙት ፍጹም ጭካኔ የተሞላው ድርጊት
ንስሐ ገብተዋል የሚል እምነት ስለነበረው፣ ታናሽ
ወንድሙ ብንያም ላይ በምንም መልኩ ተመሳሳይ
መጥፎ ነገር አያደርጉም ብሎ አስቧል።”—Ellen G.
White, Spiritual Gifts, book 3, p. 165.

የመወያያ ጥያቄዎች

1.በሐሙስ ጥናት መጨረሻ በቀረበው ጥያቄ ላይ


ተወያዩ። ዮሴፍ-ነገሮች ወደ መልካምነት ባይቀየሩለት ኖሮ
ለወንድሞቹ ያን ያህል ደግነት ይኖረው ነበር ብለው
ያስባሉ? ለነገሩ ይህን በእርግጠኝነት ማወቅ ባንችልም፣
በዮሴፍ ታሪክ ውስጥ ዮሴፍ ምን ዓይነት ባሕርይ
እንደነበረው የሚጠቁሙ ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?

2.በዮሴፍ ታሪክ ክርስቶስ ያጋጠመውን ሁኔታ


የምናይባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ዮሴፍ
ወንድሞቹን እንደ ፈተነ ሁሉ፣ እግዚአብሔር እኛን
የሚፈትንባቸው ተመሳሳይ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
3.እነዚህ ሁሉ ዓመታት ካለፉ በኋላም እንኳ፣ የዮሴፍ
ወንድሞች በወንድማቸው ላይ በፈጸሙት ድርጊት
በደለኞች መሆናቸውን ተገንዝበው ነበር። የጥፋተኝነት
ስሜት እንዴት ከባድ ጫና ሊኖረው እንደሚችል
አስመልክቶ ይህ ምን ያስተምረናል? በእግዚአብሔር ፊት
ይቅርታና ተቀባይነት ማግኘት ብንችልም፣ ራሳችንን ይቅር
ማለት መማር የምንችለው እንዴት ነው--የቱንም ያህል
ይቅርታው ባይገባንም?

You might also like