222116

You might also like

Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 4

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት


ሰበር ሰሚ ችሎት

የሰ.መ.ቁ.222116

ጥቅምት 4 ቀን 2015 ዓ.ም

ዳኞች፡-. ተፈሪ ገብሩ (ዶ/ር)

ቀነዓ ቂጣታ

ፈይሳ ወርቁ

. ደጀኔ አያንሳ

ብርቅነሽ እሱባለዉ

አመልካች፡-ሐንሰን ንግድና ኢንዱስትሪ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ጠበቃ ብሩክ ታደሰ ቀርበዋል

ተጠሪ፡- የገቢዎች ሚኒስቴር ነገረፈጅ ሮማን ተሾመ ቀርበዋል

ይህ መዝገብ ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል።

ፍርድ

ይህ የአክስዮን ትርፍ ድርሻ ግብር ክርክር የተጀመረዉ በፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ሲሆን፣ የአሁን አመልካች የሥር ይግባኝ ባይ፣ የአሁን
ተጠሪ የሥር መልስ ሰጪ ሆኖ ሲከራከሩ ነበር። ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ሊቀርብ የቻለዉ የአሁን አመልካች የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት
በመ.ቁ.205904 በ28/3/2014 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲታረምልን በማለት በማመልከታቸዉ
ነዉ።

የጉዳዩ አመጣጥ ሲታይ አመልካች በፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን በአሁን አመልካች ላይ ባቀረቡት የይግባኝ ማመልከቻ አመልካች በ2010
ዓ.ም የአክስዮን ትርፍን ለአክስዮን ካፒታል ማሳደጊያነት መዋሉን በህጉ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ በፌዴራል ሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ በፀደቀ
ቃለ ጉባኤ ያረጋገጥን ቢሆንም የአክስዮኑን ካፒታል ማደግ ባቀረባችሁት የንግድ ፍቃድ ላይ የተመዘገበው በህጉ ከተቀመጠው ጊዜ በኋላ ህዳር
18/2012 ዓ.ም በመሆኑ፣ የትርፍ ድርሻ ግብር ቅጣትና ወለድን እንዲንከፍል የአሁን ተጠሪ ያሳወቀንን የተጠሪ ቅሬታ ሰሚ ጽ/ቤትም ያጸናብን
ዉሳኔ አግባብነት ያለው ባለመሆኑ እንዲሻርልን በማለት ዳኝነት ጠይቋል፡፡

የአሁን ተጠሪ ባቀረበዉ መልስ፡ የፌዴራል የገቢ ግብር በአዋጅ ቁ.979/2008 ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ ቁጥር 7/2011ም ሆነ ከዚያ
በፊት በነበረው መመሪያ ቁጥር ገ/ኢ/1/2/3 መሰረት የአሁን አመልካች የትርፍ ድርሻቸውን ለአክስዮን ማሳደጊያነት ማዋላቸውን የግብር ዘመኑ
ካበቃ በ12 ወራት ውስጥ በሚመለከተዉ የመንግስት አካል የፀደቀን ቃለ ጉባኤና የአክስዮን ካፒታሉ ማደጉን የሚያሳይ የንግድ ፍቃድ በጋራ
የማቅረብ ግዴታ ሲኖርባቸዉ፣ አመልካች ይህን ማቅረብ ያለባቸውን ሰነዶች በጣምራ ባለማቅረባቸው መብታቸውን እንደተውት ተቆጥሮ
ያልተከፋፈለ ትርፍ እንዳላቸው ተቆጥሮ ፍሬ ግብር ወለድና መቀጫ ሊከፍሉ ይገባል በማለት የተሰጠዉ ዉሳኔ በሕግ አግባብ ነዉ በማለት
ተከራክሯል፡፡

ማ ስታወሻ፡- ይህ የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለጥናትና ምርምር ሥራ ወይም ለግንዛቤ እንጂ
ለፍርድ አፈጻጸም ዓላማ አያገለግልም
ከዚህ በኋላ የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን የግራ ቀኙን ክርክር በመመርመር ባሳለዉ ዉሳኔ በገንዘብ ሚኒስቴር የወጣዉ መመሪያ ቁጥር
7/2011 መሰረት የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ በ12 ወራት ዉስጥ አመልካች ያገኙትን ትርፍ ለካፒታል ማሳደጊያነት ማዋላቸዉን የሚያረጋግጥ
በሚመለከተው አካል በጸደቀ ቃለ ጉባኤ ለተጠሪ ያሳወቁ መሆኑን ግራ ቀኙም የተማመኑት ጉዳይ በመሆኑ፣ ይህ ከሆነ ደግሞ ለካፒታል
ማሳደጊያነት የዋለን ትርፍ ባለአክስዮኖች ሊከፋፈሉበት የሚችሉበት አግባብ ባለመኖሩ፤ በንግድ ፍቃዱ ላይ መመዝገቡ የአሰራር ጉዳይና
ከአመልካች ቁጥጥር ዉጪ በመሆኑ እንደተከፋፈለ ትርፍ ተቆጥሮ የትርፍ ድርሻ ግብር ሊጠየቅ አይገባም፡፡ ሆኖም በመመሪያው በተቀመጠው
አግባብ ለተጠሪ ባለማሳወቁ አስተዳደራዊ መቀጫ ብቻ እንዲቀጡ በማለት የተጠሪን ዉሳኔ በመሻር ወስኗል፡፡

የአሁን ተጠሪ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረበ ቢሆንም ፍ/ቤቱ የቀረበዉን ይግባኝ በትዕዛዝ በመሰረዝ
የኮሚሽኑን ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል፡፡

የአሁን ተጠሪ አሁንም በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙን በማከራከር ባሳለፈዉ
ዉሳኔ አመልካች ባቀረበዉ ክርክር በ2010 ዓ.ም የበጀት ዓመት ያገኘዉን ትርፍ ለካፒታል ማሳደጊያነት ያዋልኩኝ በመሆኑ የትርፍ ግብር
መክፈል የለብኝም የሚል ነዉ፡፡ በፌዴራል የገበ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀጽ 61 መሰረት በገንዘብ ሚኒስቴር የወጣዉ መመሪያ
ቁጥር 7/2011 አንቀጽ 5 (2) መሰረት አንድ ድርጅት ባልተከፋፈለ ትርፍ ላይ ግብር እንዲከፍል የማይጠየቀዉ በአንድ የበጀት ዓመት ጊዜ
ዉስጥ የተገኘዉን ያልተከፋፈለ ትርፍ የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ በ12 ወራት ገዜ ዉስጥ የአባላቱን የአክስዮን ድርሻ መጠን እና የድርጅቱን
ካፒታል በተገኘዉ የተጣራ የትርፍ መጠን ካሳደገ ብቻ መሆኑን ይድነግጋል፡፡ ያልተከፋፈለ ትርፍ መኖሩን ለማስረዳት ደግሞ በሰነዶች ምዝገባና
ማረጋገጫ ጽ/ቤት የጸደቀ ቃለ ጉባኤ እና ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ካፒታሉ ማደጉን የሚያሳይ ሰነድ ተሟልቶ መቅረብ እንደሚገባዉ
ነዉ፡፡ በዚህ መሰረት አመልካች የ2010 ዓ.ም የበጀት ዓመት በተጠናቀቀ በ12 ወራት ዉስጥ ትርፍን ለካፒታል ማሳደጊያነት ያለዉ መሆኑን
የሚያሳይ በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ የተመዘገበ ቃለ ጉባኤ ያቀረበ ቢሆንም፣ በዚህ መሰረት ካፒታሉ ማደጉን የሚያሳይ ከንግድ ቢሮ የተሰጠ
ማስረጃ ባለመኖሩ፣ በሕጉ የተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት፣ ኮሚሽኑ የአመልካች ድርጅት ትርፉን ለካፒታል ማሳደጊያነት አዉሏል
በማለት የደረሰበት ድምዳሜና የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጠዉ ትዕዛዝ የህግ ስህተት ነዉ በማለት በመሻር፤ የተጠሪ መ/ቤት አመልካች
ያገኘዉን ያልተከፋፈለ ትርፍ ላይ ግብር፣ ወለድ እና ቅጣት እንደከፍል የሰጠዉን ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል፡፡ የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ
በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ለማስለወጥ ነዉ፡፡

የአሁን አመልካች በ24/6/2014 ዓ.ም በተጻፈ የሰበር አቤቱታ፡ አመልካች ያገኙትን ትርፍ በመመሪያው በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ
በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት የተመዘገበና በጸደቀ ቃለ ጉባኤ የግብር ዓመቱ በተጠናቀቀ በ12 ወር ጊዜ ዉስጥ አቅርበን ያሳወቅን
በመሆኑ፤ በመመሪያ ቁጥር 7/2011 አንቀጽ 5 (2) መሰረት የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ካበቃ በኋላ ይህ መሆኑን የሚያሳይ የንግድ ስራ ፍቃድ
ያቀረብን መሆኑ የተረጋገጠ በመሆኑ፤ አመልካች በዚህ ጊዜ ዉስጥ ትርፉን የባለአክስዮኖችን ድርሻ ለማሳደግ ያዋለዉ ሆኖ ገን በመመሪያ
በተጠቀሰዉ ጊዜ ዉስጥ አለማሳወቁ በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 104 (5) መሰረት አስተዳደራዊ መቀጫ ብቻ
የሚያስቀጣ ሆኖ ሳለ፣ አመልካች በ2010 ዓ.ም ያገኘዉ ትርፍ ለድርጅቱ ካፒታል ማሳደጊያነት መዋሉ ተረጋግጦ እያለ፤ የፌዴራል ጠቅላይ
ፍ/ቤት ለባለአክስዮች እንደተከፋፈለ ትርፍ በመዉሰድ ትርፍ ግብር ሊትከፍል ይገባል በማለት ቅጣትና ወለድ ታስቦ እንዲንከፍል የሰጠዉ ዉሳኔ
መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ እንዲሻርልን በማለት በዝርዝር አመልክቷል፡፡

የሰበር አጣሪ ችሎት ጉዳዩን በማየት ፣አመልካች ንግድ ትርፉን ለካፒታል ማሳደጊያነት ያዋለ ስለመሆኑ ቃለ ጉባኤ በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ
ጽ/ቤት የጸደቀ መሆኑን ተጠሪ እያመነ በ12 ወራት የንግድ ፍቃድ አልታደሰም በሚል ምክንያት ብቻ ታክስና ግብር እንዲከፈል በፌዴራል
ጠቅላይ ፍ/ቤት የወሰነበትን አግባብነትን ለማጣራት ሲባል የሰበር አቤቱታዉ ያስቀርባል በማለት ተጠሪ መልስ እንዲሰጥ ባዘዘዉ መሰረት
ግንቦት 2 ቀን 2014 ዓ.ም የተጻፈ መልስ አቅርቧል፡፡ የመልሱም ይዘት ባጭሩ፡ በመመሪያ ቁጥር 7/2011 አንቀጽ 5 (2) መሰረት በተቀመጠው
የጊዜ ገደብ ውስጥ አመልካች ካፒታላቸውን ማሳደጋቸውን በጸደቀ ቃለ ጉባኤና ንግድ ፍቃድ በአንድነት ማረጋገጥ ያለባቸዉ ቢሆንም
ማስረጃዎቹን በአንድነት ያላቀረቡ በመሆኑ፤ ያቀረቡት የንግድ ፍቃድም ቢሆን በመመሪያዉ የተቀመጠው ጊዜ ካበቃ በኋላ የተሰጠ በመሆኑ፣
አመልካች መብታቸዉን እንደተውት ተቆጥሮ ግብር የመክፈል ግዴታ ያለባቸው በመሆኑ፤ በመመሪያው የተቀመጠው የጊዜ ገደብ በወቅቱ ግብር
እንዲሰበሰብ ለማስቻል ስለሆነ፤ አስተዳደራዊ ቅጣት ብቻ የሚጣለው አመልካች የሚጠበቅባቸውን ማስረጃዎች በመመሪያዉ በተቀመጠው
የጊዜ ገደብ ውስጥ የያዙ ቢሆንም ማስረጃዎቹን በወቅቱ ለግብር ሰብሳቢው ሳያሳውቁ ሲቀር በመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ያስተላለፈዉ
ዉሳኔ አግባብነት በመሆኑ እንዲጻናልን በማለት ተከራክሯል፡፡ አመልካች በ19/9/2014 ዓ.ም በተጻፈ የመልስ መልስ የሰበር አቤቱታዉን
በማጠናከር ተከራክሯል፡፡

ማ ስታወሻ፡- ይህ የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለጥናትና ምርምር ሥራ ወይም ለግንዛቤ እንጂ
ለፍርድ አፈጻጸም ዓላማ አያገለግልም
የጉዳዩ አመጣጥ ከፍ ሲል የተመለከተዉ ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር አግባብነት ካላቸዉ የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንደሁም
የሰበር አቤቱታዉ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘዉ ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለዉ መርምሮታል፡፡ እንደመርመርነዉ የግራ ቀኙን ክርክር መሰረት
በማድረግ በሥር ፍ/ቤቶች የተረጋገጠዉ ፍሬ ነገር ሲታይ የአመልካች ድርጅት የ2010 ዓ.ም በጀት ዓመት በተመለከተ የበጀት አመቱ
እንደተጠናቀቀ በ12 ወራት ጊዜ ዉስጥ ትርፉን ለድርጅቱ ካፒታል ማሳዲያ ለማዋል የተወሰነዉን ቃለ ጉባኤ በፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና
ምዝገባ ጽ/ቤት በማስመዝገብ ያጸደቀ መሆኑን እና በዚህ ጊዜ ዉስጥ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስተር አቅርቦ ካፒታል ማሳደጉን የሚያሳይ የንግድ
ፈቃድ ማስረጃ አለመዉሰዱ የተረጋገጠ ጉዳይ ነዉ፡፡ አመልካችም ቢሆንም ባቀረበዉ ክርክር ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የበጀት ዓመቱ
በተጠናቀቀ በ12 ወራት ጊዜ ዉስጥ ማስረጃዉን አቅርቦ ትርፉ ለድርጅቱ ካፒታል ማሳደግነት የዋለ መሆኑን የሚያመለክት የንግድ ፈቃድ
አለመዉሰዱን ክደዉ የተከራከረዉ ነገር የለም፡፡

እንደሚታወቀዉ የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀጽ 61 መሰረት ሚኒስትሩ በሚያወጣዉ መመሪያ መሰረት በአንድ የግብር
ዓመት ግብር ከተከፈለ በኋላ ለአባላቱ ያልተከፋፈለ እና መልሶ ኢንቨስት ያልተደረገ የተጣራ የድርጅቱ ትርፍ 10% (አስር በመቶ) ግብር
እንደሚከፈልበት ይደነግጋል፡፡ እንዲሁም ይህን ድንጋጌ ተግባራዊ ለማድረግ የወጣዉ የአፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 7/2011 አንቀጽ 5 (2)
መሰረት ባልተከፋፈለ ትርፍ ላይ ግብር እንዲከፈል የማይጠየቀዉ ድርጅቱ በአንድ የሂሳብ ዓመት ጊዜ ዉስጥ የተገኘዉን ያልተከፋፈለ ትርፍ
የሂሳብ ጊዜዉ በተጠናቀቀ በ12 ወራት ዉስጥ የአባላቱን የአክስዮን ድርሻ መጠንና የድርጅቱን ካፒታል በተገኘዉ የተጣራ ትርፍ መጠን ካሳደገ
እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን አንድ ድርጅት የድርጅቱን ትርፍ የባለአክስዮኖቹን ድርሻ ለማሳደግ ያዋለዉ የሂሳብ ጊዜዉ በተጠናቀቀ ከ12
ወራት በኋላ ከሆነ መብቱን እንደተወዉ እና ያልተከፋፈለ ትርፍ እንዳለዉ ተቆጥሮ ግብር መቀጫ እና ወለድ መክፈል እንደሚገባዉ በዚህ
መመሪያ አንቀጽ 7 (3) ሥር ተመልክቷል፡፡

በዚህ አግባብ አሁን ወደ ተያዘዉ ጉዳይ ስንመለስ አመልካች ምንም እንኳን በ2010 ዓ.ም የድርጅቱን ትርፍ ለካፒታል ማሳደጊያነት ያዋለዉ
መሆኑን የበጀት ዓመቱ እንደተጠናቀቀ በ12 ወራት ጊዜ ዉስጥ በፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት በማስመዝገብ ያጸደቀ ቢሆንም
ከንግድና ኢንዲስትሪ ሚኒስቴር የድርጅቱ ትርፍ ለባለአክስዮኖች ሳይከፋፈል ለካፒታል ማሳደጊያነት ያዋለዉ መሆኑን የንግድ ፈቃድ ማስረጃ
በመዉሰድ ለተጠሪ መ/ቤት ያቀረበዉና ያሳወቀዉ ነገር አለመኖሩ የተረጋገጠ ፍሬ ነገር ነዉ፡፡ እንግዲህ አመልካች በሕጉ በተመለከተ የጊዜ ገደብ
ዉስጥ የ2010 ዓ.ም በጀት ዓመት ትርፍ ለካፒታል ማሳደጊያነት ያዋለዉ መሆኑን የሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ ጽ/ቤት የተመዘገበና የጸደቀ ቃለ
ጉባኤ እና የድርጅቱ ካፒታል ማደጉን የሚያሳይ ማስረጃ ከንግድና ኢንዱስትሪ ጽ/ቤት አንድ ላይ በማሟላት ያላቀረበ እንደሆነ፣ አመልካች
መብቱን እንደተወዉ እና ያልተካፈለ ትርፍ እንዳለዉ የሚያስቆጥረዉ በመሆኑ፣ ከፍሬ ግብሩ በተጨማሪ የግብር መቀጫ እና ወለድ ለመክፈል
የሚገደድ ይሆናል፡፡ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ.መ.ቁ.220213 ላይ በአመልካች ሃጁታ ኢንጂነሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር እና በተጠሪ ገቢዎች
ሚኒስቴር መካከል በነበረዉ የሰበር ክርክር ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም ያሳለፈዉ አስገዳጅ ዉሳኔ አሁን በተያዘዉ ጉዳይ ላይ ተፈጻሚነት
አለዉ፡፡ በመሆኑም የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት አመልካች በ2010 ዓ.ም በጀት ዓመት የተገኘዉን ትርፍ ለካፒታል ማሳደጊያነት ያዋለዉ መሆኑን
ከፍ ሲል በተጠቀሰዉ የሕግ ድንጋጌ መሰረት በሕጉ በተመለከተዉ የጊዜ ገደብ ዉስጥ ማስረጃዉን በማቅረብ ለተጠሪ ያላሳወቀዉ መሆኑ
በማረጋገጡ የፍሬ ግብር፣ ወለድ እና መቀጫ እንዲከፍል ያሳለፈዉ ዉሳኔ የሚነቀፍበት የህግ አግባብ አልተገኘም፡፡ ይህ ችሎት በኢፌዴሪ ሕገ
መንግስት አንቀጽ 80 (3፣ ሀ) እና በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 10 (1) መሰረት ከተሰጠዉ ስልታን አንጻር አመልካች ያቀረበዉ ቅሬታ
ከተያዘዉ ጭብጥ አኳያ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆኑን የሚያመለክት ባለመሆኑ
ተቀባይነት የለዉም ብለናል፡፡

ሲጠቃለል የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት አመልካች የፍሬ ግብር፣ መቀጫ እና ወለድ ሊከፍል ይገባል በማለት ያሳለፈዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ
ስህተት ያልተፈጸመበት በመሆኑ ተከታዩን ወስነናል፡፡

ዉሳኔ

1.የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ.ቁ.205904 በ28/3/2014 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያልተፈጸመበት ስለሆነ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348

2. የዚህ ዉሳኔ ግልባጭ ለሥር ኮሚሽን እና ፍ/ቤቶች ይድረስ፡፡

3. ግራ ቀኙ የሰበር ክርክር ያስከተለዉን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸዉን ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ማ ስታወሻ፡- ይህ የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለጥናትና ምርምር ሥራ ወይም ለግንዛቤ እንጂ
ለፍርድ አፈጻጸም ዓላማ አያገለግልም
አ/ኃ

ማ ስታወሻ፡- ይህ የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለጥናትና ምርምር ሥራ ወይም ለግንዛቤ እንጂ
ለፍርድ አፈጻጸም ዓላማ አያገለግልም

You might also like