2015

You might also like

Download as docx, pdf, or txt
Download as docx, pdf, or txt
You are on page 1of 13

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት


ቀ ስመ ቅዱሳን

1 ልደታ ለእግዝእትነ ማርያም፣ ተዝካሩ ለሐዋርያ በርተሎሜዎስ
2 ኢዮብ ጻድቅ፣ ቅዱስ ቴዎድሮስ ረድኡ ለአባ አጳኩሚስ፣ እለተ ስምዖሙ ለአባ ኤሲ ወ ለወ ነፋሳት
3 ዕረፍቱ ለሐዋርያ ያሶን፣ እለተ ስምዑ ለአባ ብሦይ፣ ዕረፍታ ለቡርክት ወለተ ማርያም
4 ዕረፍቱ ለአባ ዮሐንስ፣ እለተ ስምዖሙ ለሶሲማ ወአባ ኖዳ አግብርቲሁ ለቡሩክ ፊቅጦር
5 ዕረፍቱ ለነቢይ ኤርምያስ
6 እለተ ስምዑ ለአባ ይሥሐቅ፣ ዕረፍቱ ለአባ መቃርስ ዘእስክንድርያ፣ እለተ ስምዑ ለበንደላዖስ፣ ዕረፍታ
ለቅድስት ሰሎሜ፣ ዕረፍቱ ለዲዮናስዮስ
7 ዕረፍቱ ለቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ፣ ዮሐንስ ጻድቅ
8 ዕርገቱ ለእግዚእነ፣ ዕረፍቱ ለቅዱስ ዮሐንስ ዘሀገረ ስንሑት፣ ሰማዕታት ዘማኅበረ ዮሐንስ፣ ዕረፍቱ ለአባ
ዳንኤል ዘገዳመ አስቄጥስ፣ ዕረፍቱ ለመክሲሞስ መስተጋድል
9 ዕረፍታ ለቅድስት ዕሌኒ ንግሥት
10 ተዝካረ ሠለስቱ ደቂቅ፣ እለተ ስምዑ ለአብርሃም ጸራቢ፣ ተዝካረ ቤተ ክርስቲያኑ ለአባ ሚካኤል፣ እለተ
ስምዑ ለአባ ኖብ ወብዙኅ ነፍሳት ምስሌሁ
11 እለተ ስምዐ ለቅድስት ታውክልያ፣ ዕረፍቱ ለቅዱስ በፍኑትዮስ ኤጲስ ቆጶስ፣ እለተ ስምዑ መምህር
አሤር፣ ተዝካረ ቅዱስ ያሬድ፣ ዕረፍታ ለአርሴማ ቅድስት፣ እለተ ስምዐ ለቅድስት ኤፎምያ፣ እለተ
ስምዖሙ ለቅድስት ሶፍያ ወቅድስት ኤፎምያ፣ ተዝካረ አባ በኪሞስ ወአብላዲን
12 ተፈንዎተ ቅዱስ ሚካኤል ኀበ ዕንባቆም ነቢይ፣ ዕረፍቱ ለእስክንድር ንጉሠ ኢትዮጵያ፣ ዕረፍተ ቅዱስ
ዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ አስተርእዮቱ ለብርሃነ መስቀል በሀገረ ኢየሩሳሌም፣ ተዝካሮሙ ለዲያቆን
እስጢፋኖስ ወቅዱስ ሚናስ፣ ዕረፍተ ያሬድ ወልደ መላልኤል፣ ፍልሰተ ሥጋሁ ለአባ ተክለ ሃይማኖት፣
ዕረፍትየ አባ አብርሃም ዘደብረ ሊባኖስ
13 ዕረፍቱ ለአርሳንዮስ
14 ዕረፍቱ ለአባ ጳኩሚስ፣ እለተ ስምዑ ለቅዱስ ሶሲማስ
15 እለተ ስምዑ ለሐዋርያ ናትናኤል፣ እለተ ስምዖሙ ለሰብአ ደንደራ፣ ተዝካሮሙ ለሚናስ ዲያቆን ወአባ
ሖር ወሰማዕት ቀርጢኖስ ወበሲቱ ወማኅበራነ ኤስድሮስ
16 ዕረፍቱ ለኢያሱ ወልደ አልዓዛር፣ ተዝካረ ቅዱስ ዮሐንስ ወድንጌላዊ
17 ዕረፍቱ ለኤጲፋንዮስ ዘደሴተ ቆጵሮስ
18 ርደተ መንፈስ ቅዱስ ላዕለ ሐዋርያት፣ ዕረፍቱ ለአባ ገዓርጊ፣ ተዝካረ ሲኖዳ ሰማዕት
19 ዕረፍተ ለአባ ይሥሐቅ፣ እለተ ስምዑ ለቅዱስ ኤስድሮስ ወብዙኅ ሰብእ ምስሌሁ፣ ዕረፍቱ ለአባ ዮሴፍ
20 ዕረፍቱ ለንጉሥ ካሌብ ዘኢትዮጵያ፣ ዕረፍቱ ለአባ አሞንዮስ፣ ዕረፍተ አባ ሖር ወአባ ድርማ ወአባ ሄሮዳ
ወዘካርያስ፣ ዕረፍቱ ለአባ በትረ ወንጌል
21 ደብረ ምጥማቅ፣ ዕረፍቱ ለአባ መርትያኖስ፣ ዕረፍቱ ለአባ አሮን ሶርያዊ፣ ተዝካሮሙ ለአሞጽ ነቢይ
ወለመዶራ
22 ዕረፍቱ ለሐዋርያ እንድራኒቆስ፣ ተዝካሩ ለያዕቆብ ምሥራቃዊ
23 ዕረፍቱ ለቅዱስ ዮልዮስ፣ ተዝካሮሙ ለብዙኅ ሰማዕታት
24 ምጽአተ ክርስቶስ ኀበ ብሔረ ግብጽ፣ ዕረፍተ ዕንባቆም ነቢይ፣ እለተ ስምዑ ለአብቍልታ፣ ዕረፍቱ
ለአልዓዛር ካህን
25 ዕረፍተ ቅድስት ሰሎሜ እኅተ እግዝዕትነ ማርያም፣ እለተ ስምዑ ለቅዱስ ኮጦሎስ ዘእንዴናው፣ እለተ
ስምዑ ለአባ ሄሮዳ፣ ተዝካረ ቅዱሳን ብዙኃን አምኍልቍ
26 እለተ ስምዑ ለሐዋርያ ቶማስ፣ ተዝካሮሙ ለአፋውስ ሰማዕት ወለዘካርያስ ባሕታዊ ወለቅድስት አርሶኛ
27 ዕረፍቱ ለአባ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳሳት ዘእስክንድርያ፣ ዕረፍቱ ለአልዓዛር ጻድቅ
28 እለተ ስምዖሙ ለአባ ጌርሎስ ወደቂቁ፣ ዕረፍቱ ለአባ መርቆሬዎስ፣ ብጽሐተ ሥጋሁ ለቅዱስ ኤጲፋንዮስ
ኀበ ሀገረ ቆጵሮስ፣ ተዝካሮሙ ለአባ ሰንጣ ወአጋቦስ ሰማዕት
29 ተዝካረ ልደቱ ለእግዚእነ፣ ዕረፍቱ ለአባ ስምዖን ዘአንጾኪያ፣ ተዝካሮሙ ለአባ አፍጼ ወአባ ጉባ ፣ ዕረፍተ
እስክንድር ንጉሥ ወልደ ፊልጶስ፣ ዕረፍቱ ለመነኮስ ይሥሐቅ
30 ዕረፍቱ ለአባ ሚካኤል ዘሀገረ እስክንድርያ፣ ዕረፍቱ ለቅዱስ ሐዋርያ ቆሮስ ወአርድዕቱ፣ ዕረፍታ
ለተጋዳሊት አርዋ

ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አዕላፈ


እም እለ ተጸምዱከ ዘልፈ
ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ
እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፋ
እም እለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ

ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባክያን


ሰማዕት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉኀን
ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ሔራን
ባርኩ ባርኮ ጉባዔ ዛቲ መካን
እስከ አረጋዊ ሊቅ ወንዑስ ሕጻን

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ


ለዘአንበቦ ወለዘተርጎሞ በልሳን ሐዲስ
ወለዘሰምዓ ቃሎ በዕዝነ መንፈስ
በጸሎተ እሙ ማርያም ዓራቂተ ኵሉ እምባእስ
ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ

አሜን
ሕያዋን ድንጋዮች( ቅዱስ ጴጥሮስ )

“ ሕያዋን ” ብሎ “ ድንጋዮች ” ? እንዴት ያለ ነገር ነው ? ቅዱስ ጴጥሮስ የሚለን ምንድር ነው ?

“ እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ
ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ፡፡ ” ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ በመጀመሪያው መልእክቱ በሁለተኛው ምዕራፍ ቁጥር
አምስት ላይ ሲናገር እናገኘዋለን፡፡ እዚህ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ 4 ነገሮችን እንድንሆን ይፈልጋል፦

ሕያዋን ድንጋዮች

መንፈሳዊ መሥዋዕት

ቅዱሳት ካህናት

መንፈሳዊ ቤት ናቸው፡፡ እነዚህን ነገሮች ለመረዳት ወደ ብሉይ ኪዳን ሥራዓተ አምልኮ መመለስ አለብን

በብሉይ ኪዳን ዘመን እስራኤል እና እግዚአብሔርን ስናመልክ በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለው የአምልኮ ማሠሪያ መሥዋዕት
ማቅረብ ነው፡፡ አምላኪ ለአምላኩ መሥዋዕትን ያቀርባልና፤ መሥዋዕቱ ግን የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ለምሣሌ የምሥጋና መሥዋዕት ፡፡
በብሉዩ ሥራዓት በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል ላለው ግንኙነት ማሠሪያ የሚሆነው መሥዋዕት የታወቀ፣ በጊዜ የተወሰነ መሥዋዕት
አለ፡፡ ለመቅረብም ሦስት ነገሮች አሉት፡፡

ሀ. መሥዋዕቱ የሚቀርብበት ቦታ፦ ቤተ መቅደስ


በየቦታው የሚሠሩት ቤተ መቅደሶች ሳይሆኑ ምኵራባት ናቸው፡፡
በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ቤተ መቅደስ በአንድ ቦታ መሆኑ ቀረና በየቦታው ሆነ፡፡
በቤተ መቅደስ የሚሠዋው መሥዋዕት እና በምኵራብ የሚቀርበው መሥዋዕት የተለያየ ነው፤ በቤተ መቅደስም ብቻ የሚሠዋ መሥዋዕትም
አለ፡፡ በቤተ መቅደስ ለመላው ሕዝብ ጠዋት አንድ በግ፣ ማታ አንድ በግ ይሠዋል፤ በየምኵራቦቹ ይሠዋ የነበረው ሕዝቡ በየግሉ ለሠራው
ኃጢአት ሥርየት የሚያገኝበት መሥዋዕት ይሠዋል። በቤተ መቅደስ አስቀድመን እንደተናገርን የነግህ እና የሠርክ መሥዋዕት፣ የሰንበት
መሥዋዕት፣ የሠርቀ ወርኅ መሥዋዕት፣ የዓመት በዓላት መሥዋዕት ይሠዉ ነበር። የቤተ መቅደሱ መሥዋዕት ከሌለ የምኵራቦቹ
አይቀርቡም፤ ምክንያቱም ያለ ቤተ መቅደሱ መሥዋዕት የምኵራቦቹ መሥዋዕቶች አያርጉምና።

ለ. መሠዊያ

ሐ. መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ካህን

ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ቦታ የዘረዘራቸው ነገሮች እነዚህን ናቸው፡፡ ከዚህ ምንረዳው ሐዋርያት በሚያስተምሩበት ሰዓት የብሉዩን ከሐዲሱ
እያስማሙ ያስተማሩበትን ድንቅ ጥበብ ነው፡፡

ቤተ መቅደስ በአንድ ቦታ መሠራት ያቆመው በብሉዩ ከነበረችው ቤተ መቅደስ የምትበልጥ አማናዊት የሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም
መጥታለችና ነው፡፡ እርሷም ነቢያት በራእይ የመለከቱት፣ ድምጹን ብቻ ይሰሙት የነበረውን፣ መላእክት በሥራው ብቻ ያዩት የነበረውን
አምላክ በሥጋ ወልዳላቸዋለችና፤ ወልዳላቸዋለችና፡፡ ከእርሷ የተወለደውም ክርስቶስ እኛን ከዘለዓለም የዲያብሎስ የግብር ባርነት ነጻ
አውጥቶን የራሱ ማደሪያዎች አድርጎናልና እኛም ቤተ መቅደስ እንባላለን፡፡ ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የምንለየው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ቤተ
መቅደስ ይሁን፣ አይሁን ምንም ምን አያውቅም፤ ቤተ መቅደስ ያደረጉትም አባቶቻችን ጳጳሳት እና ኤጲስ ቆጶሳት በቡራኬያቸው ነው እንጂ
ወድዶ እና ፈቅዶ አይደለም፡፡ እኛ ግን ራሳችንን የመቀደስም የማርከስም፣ ቤተ መቅደስ የማድረግም ቤተ ጣዖት የማድረግም ሥልጣን እና
ፈቃድ አለንና ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እንለያለን። ቅዱስ ጳውሎስ “ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ ” ያለንም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

በመቀጠልም “ ቅዱሳን ካህናት ” እንድንሆን ይፈልጋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ክህነትን “ ሥልጣነ ክህነት ” እና “ ሀብተ ክህነት ” በሚል
ትገልጸዋለች። ሀብተ ክህነት የምንለው በክህነት የሚሠሩ አንዳንድ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚሰጥ
ሥልጣን እና ሀብትን ሲሆን ሥልጣነ ክህነት ደግሞ በታወቀ ሥራዓት በአንብሮተ እድ እና በንፍሃተ መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ዘንድ
የሚሰጥ ሥልጣንን ይገልጻል፡፡ በብሉይ ኪዳን የሚቀርቡ የእንስሳት መሥዋዕቶችን ለመሠዋት ሥልጣነ ክህነት ያስፈልግ ነበር። ሥልጣነ
ክህነት ኖሯቸውም ደግሞ ከሊቀ ካህናቱ ውጪ መሠዋት የማይችሉት መሥዋዕት ነበረ በብሉይ ኪዳን፡፡ ሌሎቹን ለመፈጸምም ቢሆን ግን
ሥልጣነ ክህነቱ አስፈላጊ ናቸው፤ በብሉዩ ዘመን ሥልጣኑን ንቀው “ ሹመት በተርታ፤ ሥጋ በገበታ ” ብለው ቤተ መቅደሱን ሊያጥኑ የገቡ
ነበሩ፤ እሳት ወርዶ በላቸው፡፡ አሁንም በቤተ መቅደስ የሚከናወኑ የሥርዓተ አምልኮዎች ምሥጢራ ለመፈጸም የግድ ሥልጣነ ክህነት
አስፈላጊ ነው ፡፡ ሥልጣነ ክህነት ሳይኖራቸው ነገር ግን ሀብተ ክህነት የነበራቸው ሰዎች ነበሩ ፤ ለምሣሌ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት፡፡ ልበ
አምላክ ከተሰጠው ሀብታት መካከል ሀብተ ክህነት ነበር፤ ከእርሱም ሌላ ከሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ በፊት የነበሩ አበው በሙሉ መሥዋዕት
አቅርበዋል፤ ለምን ቢሉ ሀብተ ክህነት ነበራቸውና ሥልጣነ ክህነት ግን አልነበራቸውም። በሐዲስም ደግሞ በገዳም ሆነው፣ በአት ዘግተው፣
በምናኔ ዓለም ጸንተው ለሚኖሩ፣ የራሳቸው የሆነ ምንም ነገር ሳይኖራቸው እግዚአብሔርን ብቻ ለሚያስቡ መነኮሳት እግዚአብሔር
ሥልጣነ ክህንተን ይሰጣቸዋል። በሥልጣነ ክህነት ከሚገኙ ጸጋዎች መካከል አንዱ ሀብተ ፈውስ ነው፤ ሥልጣነ ክህነት የሌለው ሰው
ሀብተ ፈውስ ሊሰጠው ይችላል፡፡ ልክ እንዲሁ ደግሞ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብተንም ምሥጢራትን መፈጸም ባንችልም በራሳችን ማቅረብ
የምንችላቸው መሥዋዕቶች አሉ፤ ምሥጋና አንዱ ነው። ምሥጋናን ለማቅረብ የግዴታ ሥልጣነ ክህነት ሊኖረን አያስፈልግምና፤ በማኅሌት
ቆሞ እግዚአብሔርን ለማመሥገን ሥልጣነ ክህነት አያስፈልግምና።
ቅዱስ ጳውሎስም ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ ሲል በተጋድሎ እና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጸንታችሁ ሀብተ ክህነትን ገንዘብ አድርጉ
ሲለን ነው፡፡

ከተቀበልን፣ ሀብተ ክህነትን ገንዘብ ካደረግንስ በኋላ ስንል ደግሞ “መንፈሳዊ መሥዋዕትን አቅርቡ” ይለናል። እኛ ክርስቲያኖች የምናቀርበው
መሥዋዕት ሥጋዊ የሆነ መሥዋዕት ማለትም እንደቀደመው ሥርዓት የበግ፣ የጊደር፣ የላሕም እና የርግብ መሥዋዕት ያይደለ መንፋሳዊ
መሥዋዕት ነውና። ሮሜ. 12 “ እንግዲህ ወንዶች ሆይ አድምጡኝ፣ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ እና ሕያው፣ ቅዱስም
መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፣ እርሱም ለአዕምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው ” ይላል።
ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች የምናቀርበው መሥዋዕት አገልግሎታችንን ነው።

መሥዋዕትን ለማቅረብ ደግሞ መሠዊያ ያስፈልጋል። የብሉዩ መሠዊያ የድንጋይ መሠዊያ ነው፤ የሚቀርበው መሥዋዕት የሚቃጠል
መሥዋዕት ስለሆነ መሥዋዕቱ ሲቃጠል አብሮ እንዳይቃጠል መሠዊያው የድንጋይ ሆነ። መሥዋዕቱ ለምን ይቃጠላል ቢሉ

የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው እንዳለ መጽሐፍ በብሉይ የነበሩ ሰዎች ኃጢአት ሲሠሩ መሥዋዕት የዘው ወደ ካህኑ ቀርበው ይናዘዛሉ።
ካህኑም ያ ያቀረቡትን መሥዋዕት አርዶ አወራርዶ ያስቀምጠዋል፤ ይህም ክርስቶስ ስለ ሰዎች ሁሉ ኃጢአት አንደሚሞት እና ስለ እኛ ቤዛ
እንደሚሆን ሲያመለክት ነው። መሥዋዕቱ ታርዶ ተወራርዶ ከቀረበ በኋላ ይቃጠላል፣ ስለ ሰዎቹ ፈንታ እንሣው ተቃጥሎላቸው ነበርና
በሲዖል መቃጠል የለባቸውም፤ ይህስ ለምንድር ነው ቢሉ ከኃጢአት በኋላ የሰው ልጅ በሲዖል እሳት ይጠብቀው ነበር፤ ይህም የሲዖል
እሳት በክርስቶስ እንደሚቀርልን ሲያጠይቅ ይህንን ሥርዓት ሠራ።

በሥርዓተ ቅዳሴ የሚፈተተው ሥጋ እና ደም መለኮት የተዋሐደው መሆኑን ለማጠየቅ ነው።

ይህ የመሠዊያ ድንጋይ ግን ሕይወት የለውም፤ በተፈጥሮው ድንጋይ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ግን ሕያዋን ድንጋዮች እንድንሆን ነው
የፈለገው። በተፈጥሮ ሰው ብንሆንም ራሳችንን መንፈሳዊ መሠዊያዎች አድርገን፣ አግልግሎታችንን መሥዋዕ አድርገን ፣ ሰውነታችንን ቤተ
መቅደስ አድርገን፣ አገልግሎታችንን እንድናቀርብ ( መሥዋዕት እንድናቀርብ ) ያስፈልገናል። ሕያዋን ድንጋዮችም ሁኑ ሲል ሕያዋን
የሆናችሁ መሠዊያዎች ሁኑ ሲል ነው።

ከዚህም በመነሣት በብሉይ ይፈጸሙ የነበሩ ሥርዓቶች በሙሉ ለሐዲስ ኪዳን ሥርዓቶ መሠረት የሆኑ እና ምሥጢራትን ያዘሉ
መሆናቸውን መረዳት እንችላለን።

በመጽሐፍ በርካታ ስለ መሠዊያው የተጻፉ አስፈላጊ ነገሮች አሉ፤ ከእነዚህም መካከል በመጽሐፈ ኢያሱ ላይ የተጠቀሰውን እንመለከታለን።
“ በሙሴ እንደታዘዘ መሠዊያው ካልተወቀረ እና ብረት ካልነካው ድንጋይ ነበረ ” ኢያ.8 ÷ 31። መሠዊያው ብረት ያልነካው እና
ያልተወቀረ ነው፤ እንዴ ታድያ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለማቅረብ ድንጋይ መለያየት ለምን አስፈለገ ? የሚል ጥያቄ ያስነሣል፤ እሳት በላዩ
ላይ ለማንደድ የሚያንስ ድንጋይ የለምና። ይህ አመለካከት ግን የሰው ሰውኛ ነው፤ እውነት ነው ድንጋይ ድንጋይ ነው እሳት ነደደበትም
አልነደደበትም አይቀየርም። ነገር ግን ይህ ነገር የተጻፈው እና የታዘዘው ስለ ድንጋዩ ሳይሆን ስለ እኛ ነው። እግዚአብሔር ትዕዛዝን ሲያዘን
ለእኛ የሚጠቅም ነውና መፈጸም ይገባናል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ እና ቃል ንጹሕ ነውና፤ “ቃለ እግዚአብሔር ቃል ንጹሕ፣ ከመ ብሩር
ጽሩይ ንጡፍ ወፍቱን እምድር፣ ዘአጽረይዎ ምስብዒተ” እንዲል ።

ያልተወቀረ ድንጋይ ይሁን አለ፤ ድንጋይ ቢወቀር ምን ይሆናል ? ለምን ይወቀራል ? ቢሉ ለተለያዩ አገልግሎቶ ሊወቀር ይችላል፤
እየተወቀረ በሄደ ቁጥር ግን መጠኑ እየቀነሰ ይሄዳል። እግዚአብሔር “ አትወቀሩ ” ሲል ከእኛ እንዲቀነስ የማይፈልገው ነገር አለ፤ ንጽሐ
ጠባይዕ። ሕጻናት ሳለን በውስጣችን ምንም አይነት ክፋት አልነበረም፤ ምን የሚያስቀይም ሥራ ቢሠራብን ይቅር እንል ነበር። አሁን በብዙ
የክፋት ሐሳብ እየተወቀርን ከመምጣታችን እና ከማነሣችን የተነሣ የሆነ ቋንቋ ካልተናገረ የማናንግርበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፤ ይልቁንም
የአንዳንድ ሰዎች ጉዳት ብቻ እያሳሰበን የቀረው እልቂት ግን ምንም የማያስጨንቀን እየሆንን መጥተናል፤ ይህ የሆነው በ“ ዘረኝነት ፖለቲካ ”
እየተቀረጽን፣ እየተወቀርን ስለመጣን ነው። ይህንን በልቦናችን ይዘን እግዚአብሔር ይዘን እያሰብን እግዚአብሔር መሥዋዕትን እንድናቀርብ
አይፈልግም። የተበደልን እንደሆነ የበደሉንን ይቅር ማለት፤ የበደልን እንደሆነ ደግሞ ይቅርታ መጠየቅ እግዚአብሔር የሚወደው ነውና
ይህንን እናደርግ ዘንድ ተገቢ ነው።

ብረት ያልነካው ይሁንም ይላል፤ ብረት ባዕድ ነገር ነው። እኛ ክርስቲያኖች ለሥርዓተ አምልኳችን፣ ለክርስቲያናዊ ሕይወታችን ባዕድ የሆኑ
ነገሮችን ማራቅ አለብን። እነዚህ ባዕዳን ነገሮች መንፈሳዊ ሕይወታችንን እና አምልኳችንን ማስነካት የለብንም። የተለያዩ ሐሳቦች፣ የተለያዩ
አመለካከቶች ከክርስትናችን እና ከቤተ ክርስቲያናችን ባዕድ ሆነው ይኖራሉ። ለምሣሌ በዘመናችን ለበርካታ ጋብቻዎች መፍረስ ‘ ምክንያት
’ ሆኖ የሚጠቀሰው ከጋብቻ በፊት ሩካቤ አለመፈጸም ነው፤ ይህንን ብዙ ጊዜ እንሰማዋለን። የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓት ለጊዜው
እናቆየውና በዓለማችን ላይ በርካታ ጥናቶች በጋብቻ ፍቺ ዙሪያ ተጠንተዋል፤ እና እነዚህ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከሚፈጠሩት ፍቺዎች
መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ከጋብቻ በፊት ግንኙነት ነበራቸው። ስለዚህ ከጋብቻ በፊት ሩካቤ ማድርግ ወይም አለማድረግ አይደለም
ማለት ነው። እግዚአብሔር ደግሞ ይህ ነገር ጠቃሚ ቢሆን ኖሮ ይነግረን ነበር፣ እግዚአብሔር የሚጠብቀንን ነገር አያስቀርብንምና።
ለቅድስና ሕይወት ይሄ ሐሳብ ባዕድ ነው። ምክንያቱም ይህ ቀረብን ብለን እንድናስብ ያደርገናል፤ በልቡናችን ክፉ ማሰብ እንጀምራለን፤
እግዚአብሔርንም መጠራጠር እንጀምራለን። እግዚአብሔርን መጠራጠር ደግሞ ለተለያዩ ፈተናዎች ያጋልጣልን፤ ይሄ ሁሉ መዘዝ
የሚመጣው ባዕድ ሐሳብ ወደ ልቡናችን ስናስገባ ነውና እሊህን ሐሳቦች ማራቅ መቻል አለብን። ካራቅነውም በኋላ ያንን ሕይወት መናፈቅ
የለብንም።

ሕያዋን ድንጋዮች ሆነን እግዚአብሔርን የሚያስደስት መሥዋዕት እንድናቀርብ አምላካአችን ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን

አሜን
ልደታ ለማርያም
ትወጸዕ በትር እምሥርወ ዕሴይ
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግንቦት አንድ ቀን (የግንቦት ልደታ) የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት የሚከበርበት
ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም “ አክሊለ ምክህነ ወቀዳሚተ መድኃኒትነ ወመሠረተ ንጽሕነ” (የመመኪያችን
ዘውድ፣ የንጽሕናችንም መሰረት) ያላት ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም የተወለደችበት ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ ድንግል
ትጸንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች ” (ኢሳ 7÷14) ብሎ ትንቢት የተናገረላት ያቺ ድንግል በዚህች ዕለት ተወለደች፡፡ ይህች ቀን ልበ
አምላክ ክቡር ዳዊት “ ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፣ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት ” (የወርቅ ልብስ ተጎናጽፋ ንግሥቲቱ
በቀኝህ ትቆማለች) (መዝ 44÷9) ብሎ የተናገረላት ንግሥት የተገኘችባት ዕለት ናት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ ‹‹ፀሐይን የተጎናጸፈች፣
ጨረቃን የተጫማች፣ አስራ ሁለት የክዋክብት አክሊል በራሷ ላይ ያላት (ራዕ 12÷1)›› ብሎ የመሰከረላት የብርሃን እናቱ ድንግል ማርያም
የተወለደችባት ቀን ናት፡፡ የእርስዋም ልደት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ድንገት የተከሰተ ሳይሆን አስቀድሞ በትንቢት፣ በምሳሌና
በራዕይ የሰውን ልጅ ድኅነት በጉጉት ሲጠባበቁ ለነበሩ ቅዱሳን ሲገለጽ የነበረ ነው፡፡

የድንግል ማርያም ልደት በነቢያት አንደበት

መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን (መሠረቶችዋ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው፡፡) መዝ 86÷1-7

እግዚአብሔር የዝማሬና የትንቢት ጸጋን ያበዛለት ክቡር ዳዊት ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥርወ ልደት አስቀድሞ በመንፈስ
ቅዱስ መነጽርነት ተገልጾለት ‹‹መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን /መሠረቶችዋ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው/›› በማለት ትንቢት
ተናግሯል፡፡ ‹‹የተቀደሱ ተራሮች›› ያለውም የእመቤታችን ሥርወ ልደት ከቤተ መንግሥት እና ከቤተ ክህነት ከሆኑት ከተቀደሱት ከኢያቄም
እና ከሐና የመሆኑን ነገር ሲያመለክት ነው፡፡ ይህንን ትንቢትና እውነተኛውን የእመቤታችንን የትውልድ ሀረግ አስማምታ ቤተክርስቲያን
‹‹የእመቤታችን ማርያም ትውልዷ በአባቷ በኩል ከንጉሡ ከዳዊት ወገን ነው፤ በእናቷም በኩል ከካህኑ ከአሮን ወገን ነው፤ የአባቷ ስም
ኢያቄም ነው፤ የእናቷም ስም ሐና ነው፡፡›› ብላ ታስተምራለች፡፡

ትወፅእ በትር እምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ፡ ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከእርሷ ይወጣል፡፡ኢሳ 11÷1

ቁጥሩ ከዐበይት ነቢያት ወገን የሆነው ነቢዩ ኢሳይያስም ጥበብን እና እውቀትን በሚገልጽ ስለሚመጣውም ነገር ትንቢትን በሚያናግር
በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ከነገደ ዕሴይ እንደሚሆን እና እርሷም ጽጌ (አበባ) የተባለ አካላዊ
ቃል ክርስቶስን በሕቱም ድንግልና እንደምትወልድ ተገልጾለት ‹‹ትወፅእ በትር እምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ /ከዕሴይ ሥር በትር
ትወጣለች፤ አበባም ከእርሷ ይወጣል/›› በማለት ታላቅ ትንቢትን ተናግሮ ነበር፡፡ ይህች በትርም ከእሴይ ዘር የተገኘችው በዚህች ዕለት
ነውና ልደቷን በታላቅ ድምቀት እናከብራለን፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹መልካሟ ርግብ ማርያም ሆይ ደስ
ይበልሽ፤ ከእሴይ ሥር የተገኘሽ መዓዛሽ ያማረ አበባ አንቺ ነሽ›› በማለት በውዳሴ አመስግኗታል፡፡ ‹‹በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ
(መዝ 131÷13)›› የተባለልን የአባቶቻችን ልጆች እኛም እንዲሁ እያልን እናመሰግናታለን፡፡

ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ እምሊባኖስ፡ ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ፡፡ መኃ 4÷8

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት መሰረት የእመቤታችን የትውልድ ስፍራ ሊባኖስ የተባለው ተራራማ ሀገር ነው፡፡
በሊባኖስ ስለመሆኑ አስቀድሞ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ እምሊባኖስ ንዒ ወተወፅኢ እምቅድመ ሃይማኖት እምርእሰ
ሳኔር ወኤርሞን አምግበበ አናብስት ወእምአድባረ አናምርት /ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ ከአማና ራስ
ከሳኔር ከኤርሞን ራስ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች/›› በማለት ተናግሮ ነበር፡፡ የዚህ ትንቢት ምስጢርም የእመቤታችን
መካነ ልደት የሊባኖስ ተራራ ስለመሆኑ የሚያጠይቅ እንደሆነ ምስክርነታቸው የታመነ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ ትንቢቱም
ሲፈጸም ቅድስት ድንግል ማርያም ግንቦት 1 ቀን በ 15 ዓ.ዓ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች፡፡

ኢትዮጵያዊ ቄርሎስ የተባለው የነገረ ማርያም ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እመቤታችን በሊባኖስ እንደምትወለድ አስቀድሞ ሰሎሞን
የተናገረው ቃልም መፈጸሙን ሲገልጽ ‹‹….የአናብስት ልጅ አልኩሽ፡፡ ሰሎሞን እንዲህ ሲል እንደተናገረ፡- ሙሽራዪት ሆይ ከሊባኖስ
ተራራ ነዪ፤ ከአንበሶች ጒድጓድ ወጥተሽ ነዪ፤ ከምርጥ ነገድነት የተነሣ ከሚመካ ወገን የመወለድሽ ዜና እጅግ ግሩም ነው፡፡›› በማለት
አመስጥሮታል፡፡ እመቤታችንም በሊባኖስ ተራራ እንድትወለድ ምክንያት የሆነው በማሕፀን ሳለች የአርሳባንን ልጅ ዓይን በማብራቷና
ሳሚናስ የሚባለውን የጦሊቅን ልጅ ከሞት በማስነሳቷ አይሁድ በቅናት ተነሳስተውባቸው ስለነበር ሐናና ኢያቄም ወደ ሊባኖስ ተራራ
እንዲሄዱ ታላቁ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለኢያቄም ተገልጾ ስለነገራቸው እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

የድንግል ማርያም ልደት በራእይ እና በምሳሌ

ከትንቢቱ በተጨማሪም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት በራእይ እና በምሣሌም አስቀድሞ የተገለጸ ነበር፡፡ ከእነዚህም
መካከል ከእርሷ ሰባት ትውልድ አስቀድሞ ለነበሩት ደጋግ ሰዎች እንዲሁም ለእናትና ለአባቷ የተገለጹት ምሳሌዎች በቅዱሳት መጻሕፍት
በሰፊው ሰፍረው ይገኛሉ፡፡

ሰባተኛዪቱ እንቦሳ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃዋ ደግሞ ፀሓይን ስትወልድ አየሁ (ቴክታ)

በቅድስና የሚኖሩ ነገር ግን መካን የነበሩት ቴክታ እና ጴጥሪቃ ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስትወጣ ፤ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ
ስድስት ስትደርስ ፤ ስድስተኛዪቱ ጨረቃን ጨረቃዋም ፀሐይን ስትወልድ አይተው በሀገራቸው መፈክረ ሕልም (ሕልም ፈች ሊቅ) አለና
ሂደው ነገሩት፡፡ ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ፤ ጨረቃይቱ ከፍጡራን በላይ የምትሆን ልጅ ትወልዳላችሁ፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም፤
እንደ ነቢይ እንደ ንጉሥ ያለ ይሆናል አላቸው፡፡ እነርሱም ጊዜ ይተርጉመው ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ልጅ ወለዱ፡፡ ስሟንም ‹‹ረከብኩ
ስእለትዬ፤ ረከብኩ ተምኔትዬ›› /የተሳልኩትን አገኘሁ፤ የተመኘሁትን አገኘሁ/ ሲሉ ‹‹ሄኤሜን››አሏት፡፡ ሄኤሜን ዴርዴንን፤ ዴርዴን ቶናን፤
ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሔርሜላን፤ ሔርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና ለአካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው
አጋቧት፡፡ ከኢያቄም እና ከሐናም በጨረቃ የተመሰለች ድንግል ማርያም ተወለደች፡፡

ፀዓዳ ርግብ ሰባቱ ሰማያትን ሰንጥቃ መጥታ በማኅፀኔ ስታድር አየሁ (ቅድስት ሐና)

ኢያቄምና ሐና መካን ስለነበሩ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ጸልየው፤ ሲሰጣቸውም መልሰው ለእርሱ እንደሚሰጡ ስዕለትን
ተስለው ነበር፡፡ ጸሎታቸው ሲደርስ ለሐና በሕልም ተገልጾላት ለባለቤቷ ለኢያቄም ‹‹ብእሴሃ አነኑ ርኢኩ በሕልምየ ርግብ ጸዐዳ መጽአት
ኀቤየ ወነበረት ዲበ ርእስየ ወቦአት ውስተ እዝንየ ወኀደረት ውስተ ከርሥየ /ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ
በጆሮዬ ገብቶ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁ፡፡›› ብላዋለች፡፡ የዚህ ራእይ ምስጢርም ርግብ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
ስትሆን፤ ፀዓዳ (ነጭ) መሆኗ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ዘላለማዊ ድንግልናዋ ነው፡፡ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ
በጆሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁ›› ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን የምትፀንሰውን
ንጽሕት ርግብ የተባለችውን እመቤታችንን የምትወልድ መሆኗን ሲያጠይቅ ነው::

ከሰባተኛው ሰማይ ነጭ ዖፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ (ቅዱስ ኢያቄም)

በተመሳሳይ ኢያቄምም በሕልሙ ያየውን ለባለቤቱ ለሐና ‹‹እንዘ ይትረኀዉ ሰብዐቱ ሰማያት ዖፍ ጸዐዳ መጽአ ኀቤየ ወነበረ ዲበ ርእስየ
/ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ዖፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› ብሎ በሕልሙ የተገለጸለትን
ነግሯታል፡፡ የዚህም ራዕይ ምስጢር ዖፍ የተባለው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባሕርዩ ነው፡፡ ኢያቄም ‹‹ከላይ
ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› ማለቱ የኢያቄምን ባሕርይ ባሕርይ እንደሚያደርግ የሚያጠይቅ ሲሆን ሰባቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን
ልዩ ባህርይው፣ ምልአቱ፣ ስፍሃቱ፣ ርቀቱ፣ ልእልናው፣ ዕበዩና መንግስቱ ናቸው:፡

የድንግል ማርያም ልደት በሐዲስ ኪዳን ሊቃውንት

የሐዲስ ኪዳን ሊቃውንትም ትንቢተ ነቢያትንና ወንጌልን በማጣጣም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት አመስጥረው
አስተምረዋል፤ አመስግነዋል፤ ተቃኝተዋልም፡፡ የእርሷን ልደት እጅግ ብዙ ሊቃውንት በስፋትና በጥልቀት ያመሰጠሩት ሲሆን ለምሳሌ ያህል
የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች (ቅዱስ ያሬድ)

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ስለእመቤታችን ልደት ‹‹ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ/ ማርያምስ
(ማርያም ግን) ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች፡፡›› በማለት እርሷ በደፈረሰው ዓለም በንጽሕና፣
በቅድስናና በድንግልና ስታበራ እንደነበርና ኋላም የዓለም ብርሃን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን መውለዷን አመስጥሮ ተናግሯል፡፡
በተጨማሪም ስለ ሥርወ ልደቷ ‹‹እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አዕጹቂሃ…ሐረገ ወይን/ ሥሮቿ በምድር ጫፎቿም በሰማይ ያሉ…
የወይን ሐረግ›› በማለት የተወለደችው በምድር ከነበሩት ኢያቄምና ሐና መሆኑን የወለደችው ግን ሰማያዊውን ንጉሥ እንደሆነ በማመስጠር
ዘምሯል፡፡ በዚህም ሰውና እግዚአብሔርን ያገናኘች መሰላል መሆኗል ገልጾ አስተምሯል፡፡

ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐናና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ (አባ ሕርያቆስ)

የብህንሳው ሊቀ ጳጳስ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም ‹‹ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና
ወኢያቄም ተወለድኪ/ ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐናና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ››
በማለት የድንግል ማርያም ጽንሰትና ልደት እንዴት እንደነበር በድርሰቱ አስፍሮታል፡፡ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት የሚላት የሁላችን እናት
ድንግል ማርያም በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐናና ከኢያቄም ነሐሴ 7 ቀን ተፀንሳ ከዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በኋላ ግንቦት 1 ቀን ተወልዳለች፡፡
እርስዋም ስትፀነስ ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ከጥንተ አብሶ (original Sin) ጠብቋታል፤ አበሳው አልነካትም፡፡ ይህንንም ነቢየ እግዚአብሔር
ኢሳይያስ በኃጢአት በተከበበ፣ መርገም በሞላበት ዓለም ውስጥ ከኃጢአት ከበደል ርቃ (ተለይታ) እንደ ጌዲዮን ጸምር በንጽህና የጠገኘች
ንጽህት ዘር መሆኗን ሲያስረዳ ‹‹የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር
(ኢሳ 1፡19)፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ እንዲሁም ጠቢቡ ሰሎሞን ንጽህናዋን በትንቢት መነጽር አይቶ “ወዳጄ ሆይ፣ ሁለንተናሽ ውብ ነው፣
ምንም ነውር የለብሽም፡፡ ሙሽሪት ሆይ ከሊባኖስ ነዪ፡፡” (መሓልይ 4፡7-16) በማለት በንጽህና በቅድስና ያጌጠች፣ መርገመ ሥጋ መርገመ
ነፍስ ያልነካት፣ የድህነታችን ምክንያት፣ የንጽህናችን መሰረት የሰው ባህርይ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲዋሀድ ምክንያት የሆነች ንጽሕት
የሰርግ ቤት ድንግል ማርያም በሊባኖስ የመወለዷን ነገር አስቀድሞ ነግሮናል፡፡

ይህች ዕለት ትልቅ ሕንፃ የታነጸበትና ፍጡር የፈጣሪ ማደሪያ ለመሆን የተዘጋጀባት ዕለት ናት (ቅዱስ እንድርያስ)

የቀርጤሱ ቅዱስ እንድርያስ የከበረ ስለሆነው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ታላቅነት ‹‹ይህ በዓል በሐዲስና በብሉይ
ኪዳን መካከል መገኛ ሆነ፡፡ ምሳሌዎቹ በእዉነታ፣ አሮጌው በአዲስ ቃል ኪዳን ተተኩ፡፡ ፍጥረት ሁሉ በደስታ ይዘምራል፤ የዚህን ቀንም
ደስታ ይካፈላል፡፡ ይህ ዕለት (ጌታ) መቅደሱን የሰራበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ትልቅ ሕንፃ የታነጸበትና ፍጡር የፈጣሪ ማደሪያ ለመሆን
የተዘጋጀበት ዕለት ነው፡፡” በማለት ገልጾታል፡፡ በእውነት የእርሷ ልደት የልዑል ማደሪያው መቅደስ የተሰራበት ዕለት ነውና ሁላችን
እናከብረዋለን፡፡ በዚህም ዕለት ‹‹ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም/ እነሆ ዛሬ በእመቤታችን ልደት ደስታ ሆነ›› እያልን
እንዘምራለን። ይህችን የልዑል ማደሪያ እናቷ ሐናና አባቷ ኢያቄምም በእጅጉ ተደስተው በተወለደች በስምንተኛ ቀኗ ስሟን ‹‹ማርያም››
ብለው ሰይመዋታል፡፡
የእመቤታችን የልደት በዓል አከባበር

አባታችን አዳም በኃጢአት ከወደቀ በኋላ፣ ንስሃ በገባ ጊዜ አምላካችን ጌታ እግዚአብሔር የድህነት ቃል ኪዳን ገባለት፡፡ ቃል ኪዳኑም
“ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” የሚል ነበር፡፡ ስለሆነም አዳም 5500 ዘመን የሕይወት ምክንያት የሆነች የልጅ ልጁ እመቤታችን
ድንግል ማርያም ከአብራኩ ከተከፈሉ ቅዱሳን ልጆቹ የምትወለድበትን ቀን ተስፋ እያደረገ ኖረ፡፡ የእመቤታችንን የድንግል ማርያምን
የመወለዷን ዜና ተስፋ በማድረግ “ሴት” ይላት የነበረውን ሚስቱን ሔዋንን በእመቤታችን ምሳሌነት “ሔዋን”፣ የሕያዋን ሁሉ እናት ብሎ
ሰየማት፡፡ (ዘፍ. 3፡20) ዳግማዊ አዳም የተባለ ክርስቶስም የአዳምን ተስፋ በመስቀል ላይ በፈጸመ ጊዜ እውነተኛዋን ሔዋን (ዳግሚት፣
አማናዊት ሔዋንን) ድንግል ማርያምን በዮሐንስ ወንጌላዊ በኩል ለሕያዋን ምዕመናን ሁሉ እናት አድርጎ ሰጠ፡፡ (ዮሐ. 19፡26) ይህን የከበረ
ምስጢር የማይረዳ “ክርስቲያን” እንዴት ያሳዝናል!? እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ግን የቀዳማዊ አባታችንን የአዳምን፣ እንዲሁም
በዳግም ተፈጥሮ ያከበረንን ዳግማዊ አዳም የተባለ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ተቀብለን “የሕያዋን ሁሉ እናት”
ድንግል ማርያምን ልደቷን በፍፁም ደስታ እናከብራለን፣ ከተወደደ ልጇ ምሕረትን ትለምንልን ዘንድም ወደ እርሷ እናንጋጥጣለን፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለን ምዕመናን ከጌታችን ልደት ቀጥሎ በታላቅ ድምቀት የምናከብረው የልደት በዓል
የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያም የልደት ቀን ነው፡፡ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል (ሉቃ 1፡14)››
ከተባለ የድንግል ማርያም ልደት ምንኛ የሚያስደስት ይሆን?! የነቢያቱ ትንቢት የተፈፀመበት፣ የታየው ራዕይም በገሀድ የተከናወነበት፣
የብሉይ ኪዳን ማብቂያ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ ናትና ልደቷ ለሰው ልጆች ሁሉ (ለሕያዋን ሁሉ) ታላቅ የደስታ ቀን ነው፡፡ ሰማያውያን
ቅዱሳን መላእክትም በንጽህናዋ በቅድስናዋ ተደንቀው “እህትነ ነያ/እህታችን እነኋት” ብለው ያመሰግኗታል፡፡ በዘመናችን ያሉ የሰዎች ልደት
በድምቀት የሚከበር ከሆነ ለሰው ልጅ መዳን ምክንያት የሆነች የአምላክ እናት የተወለደችበት ቀን ምንኛ ሊከበር ይገባው ይሆን?! ቤተ
ክርስቲያን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት በታላቅ ድምቀት የምታከብረው ከዚህ ታላቅ በዓል በረከት ረድኤትን እንድናገኝበት ነው፡፡
የሕይወት ክርስቶስ እናት ዛሬ ተወልዳለችና፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትዉፊት መሰረት ሐና እና ኢያቄም ከአይሁድ ለማምለጥ ተሰደዉ በአድባረ ሊባኖስ ስር
እመቤታችንን ወለዱ፡፡ በወቅቱ ከቤት የወጡት ለሽሽት ነበርና ስንቅ ስላልያዙ ምግባቸዉ ‹‹ንፍሮና ጥራጥሬ›› ነበር፡፡ይህንን ትዉፊት
በመያዝ በዓሉ ከቤት ዉጭ ንፍሮ እየተበላ ይከበራል፡፡ነገር ግን በበጎ ነገሮች ሰበብ ክፉ ዓላማዉን ማስፈጸም የሚፈልገዉ ዲያቢሎስ በማር
መካከል መርዝን ከሚጨምርባቸዉ መንፈሳዊ በዓላት አንዱ የግንቦት ልደታ (የእመቤታችን የልደት በዓል) ነዉ፡፡ በዚህ ዕለት አንዳንዶች
ባለማወቅ ሌሎች ደግሞ በድፍረት ‹‹ለአድባር አዉጋር ነዉ፤ ቆሌዉን ለመለመን ነዉ›› እያሉ ለማያውቁት አምልኮ ንፍሮ የሚበትኑ፣ ቡና
የሚረጩ፣ ቅቤ የሚቀቡ፣ የከብት ደም የሚያፈሱ አሉ፡፡ እውነታው እነዚህ በእርግጥም ጣዖት አምላኪዎች ናቸው፡፡ እኛ ኦርቶዶክሳውያን
ክርስቲያኖች ግን እነዚህን የሃይማኖት ለዋጮች ሥራቸውን እንጸየፋለን፡፡ ስለሆነም ከእንደዚህ ዓይነቱ ባዕድ አምልኮ በመለየት ይህንን
ታላቅ በዓል በተገባና በተረዳ ነገር ልናከብረው ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በሠራችልን ሥርዓት መሰረት በቀናች በተዋሕዶ እምነት ሆነን፤
በምሕረቱ የጎበኘንን አምላካችንን ብቻ እያመለክን፤ የድኅነታችን ምክንያት የሆነችውን ድንግል ማርያምንም እያመሰገንን ልናከብረው
ይገባል፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ከእመቤታችን ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡ አሜን፡፡

ዕርገተ እግዚእነ
በክብር በምሥጋና ወደ ሰማይ ዐረገ
ዕርገት ከጌታችና ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ “ዕርገት” የሚለው ቃል “ዐርገ”
ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ከታች ወደ ላይ መውጣት፣ ክፍ ከፍ ማለት፣ ማረግ ማለት ነው፡፡ ዕርገት (Ascension)
ሲባልም ማረግን፣ ከፍ ከፍ ማለትን፣ ወደ ላይ መውጣትን ያመለክታል፡፡ በዓለ ዕርገትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ
ዓለም የነበረውን የማዳኑን ሥራ ጨርሶ ወደ ላይ መውጣቱና በቀደመ ክብሩ በአብ ቀኝ መቀመጡ የሚከበርበት በዓል ነው፡፡ ለዚህም
መሰረት እንዲሆን አርዮስን ለማውገዝ በኒቅያ የተሰበሰቡት ቅዱሳን አበው “ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ…/ በክብር
ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ…” ብለው ዕርገቱን በቅዱሳት መጻሕፍት ዋቢነት አስረግጠው ደንግገዋል፡፡

ዕርገቱ የትሕትና ሥራው የመፈጸሙ ምልክት ነው

አምላካችን ምሉዕ በኩለሄ (ሁሉን የሞላ እና በሁሉም ቦታ የሚኖር) ነዉ። ስለዚህ ጌታችን በባሕርይው መውጣት መውረድ የለበትም::
‘ወረደ፣ ተወለደ’ ሲባል ፍጽም ሰው መሆኑን የትህትና ሥራ መፈጸሙን ከመናገር ውጪ ከዙፋኑ ተለየ ማለት እንዳልሆነ ሁሉ ዐረገ ወጣ
ሲባልም ከሰማያዊዉ ዙፋኑ ተለይቶ ነበር ማለት አይደለም:: በምድር ላይ ሊሰራ ያለውን ሁሉ መፈጸሙን ያመለክታል እንጂ:: እንዲሁም
ጌታችን በዕርገቱ ምክንያት ከቤተክርስቲያን የተለየበት ጊዜ የለም። ነገር ግን ዕርገቱ በሥጋዉ የተደረገዉን ዕርገቱን ያመለክታል። ይህም
ዕርገት ቅዱስ ሥጋዉ በምድር የስበት ቁጥጥር (Gravitational force) የማይዘው ለመሆኑ አስረጅ ነዉ። በሌላ በኩል ደግሞ አምላካዊ
ስልጣኑን ያሳያል።

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገቱ በምድር ላይ የሚሠራውን የትሕትና ሥራ የመፈጸሙ ምልክት ነው፡፡ ዕርገቱም ልበ
አምላክ ክቡር ዳዊት “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ/ በዕልልታና በመለከት ድምፅ ላረገ
ለአምላካችን፣ ለጌታችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና አቅርቡ (መዝ ፵፮፥፭፡፮) እንዳለው በታላቅ ክብር እልልታና ምስጋና
ነው፡፡ እንዲሁም “ዓረገ ውስተ አርያም ጼዊወከ ጼዋ፣ ወወሀብከ ጸጋከ ለእጓለ እመሕያው – ምርኮን ማርከህ ወደ አርያም ወጣህ፣ ለሰው
ልጆችም ጸጋህን ሰጠሃቸው”(መዝ.፷፯፣፲፰) እንዳለው ጌታችን የድል ዕርገትን ያረገው ወደ ባሕርይ አባቱ ቀኝ ነው፡፡ በእርሱ ዕርገት የጸጋ
መንፈስ ቅዱስና የዳግም ምጽአት ተስፋዎች ተሰጥተውናል፡፡ የእርሱ ዕርገትም ለነፍሣችን ዕርገት /ለዕርገተ መንግሥተ ሰማያት/ አርአያ
ሆኖናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው ክታቡ ይህንን ሲያስረዳ “ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን
የምንቀረው ጌታችንን በአየር እንቀበለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን” (፩ተሰ. ፬፡፲፯) ብሏል፡፡

ቅዱስ ያሬድም ዝማሬ በተባለው መጽሐፍ የጌታችንን ማዳን ከፅንሰቱ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ብሎም እስከ ዳግም ምጽአቱ ከብሉያትና
ከሐዲሳት እያጣቀሰ አምልቶና አስፍቶ በተናገረበት የምስጋና ክፍል “ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና፤ ለድንግል ዘፈትሐ ማኅፀና፤ ለደቂቀ
እስራኤል ዘአውረደ መና፤ ውእቱኬ ዘአድኃና ለሶስና እም እደ ረበናት፤ ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና / በደመና ወደ ሰማይ ዐረገ፤ የድንግልን
ማኅፀን የፈታ፣ ለእስራኤል ልጆች መናን ያወረደ፣ ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነ፣ በደመና ወደ ሰማይ ዐረገ/” ብሏል፡፡ ‘ዐረገ’ መባሉ የሌለበት
ቦታ ኑሮ ካለበት ቦታ ወደ ሌለበት ቦታ ሔደ ማለት አይደለም፡፡ የማዳን ሥራውን ፈጽሞ ወደ ባሕርይ አባቱ መመለሱን፣ የማዳን ሥራውን
መፈጸሙን፣ በሥጋ በክብር ማረጉን ለመግለጽ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደመና ዐረገ ሲል በክብር ማረጉን፣ ልዕልናውን መግለጹ ነው፡፡ ደመና ክብሩ ልዕልናው ነውና።
በደመና ዐረገ መባሉ በእመቤታችን ጀርባ መታዘሉን ለመግለጥ ነው። ደመና ተብላ የተገለጠችው እመቤታችን ድንግል ማርያም ናትና።
ከማርያም በነሣው ሥጋ ዐረገ ማለት ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደ ግብፅ
ይመጣል” (ኢሳ.፲፱፥፩) ብሎ አስቀድሞ በትንቢቱ የተናገረላት ደመና እመቤታችን ናት። ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “ደመናሰ ዘይቤ ይእቲኬ
ማርያም እንተ ጾረቶ ዲበ ዘባና፤ ደመናስ የሚላት አምላክን በጀርባዋ የተሸከመችው ማርያም ናት” በማለት ያስረዳል። ስለዚህ በደመና
ዓምድ ዐረገ ሲል ከድንግል ማርያም በተዋሐደው ሥጋ ወደ ሰማይ ዐረገ ማለት ነው። ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “በምሥራቅ በኩል ወደ
ሰማየ ሰማያት ለወጣ (ላረገ) ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ የኀይል የኾነውን ቃሉን እነሆ ይሰጣል”(መዝ.፷፯፥፴፫) ብሎ የዘመረው ይህንኑ
ያጠይቃል፡፡ ምሥራቅ የተባለች የድንግል ሥጋ ተዋሕዶ ዓርጓልና።

እስከ ቢታንያም አወጣቸው


በዓለ ዕርገት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ በታላቅ መንፈሳዊ ክብር ከሚከበሩት በዓላት አንዱ ነው፡፡ በዓሉ
የሚውልበት ዕለት ሐሙስን (ከበዓለ ትንሣኤ አርባኛው ቀን) አይለቅም። የጌታችን ዕርገት ከትንሣኤ በኋላ በአርባኛው ቀን (በስድስተኛው
ሐሙስ) የሚከበረው ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ “ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥
በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው” (ሐዋ. ፩፡፫) በማለት የጻፈውን መሠረት በማድረግ ነው፡፡
ቤተክርስቲያንም ይህንን ትምህርት ኪዳን ብላ ትጠራዋለች። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ በኋላ
ለሐዋርያት የነገራቸው መጽሐፈ ኪዳን ይባላል፡፡

ዕርገቱም የተፈጸመው ስለ ምጽአቱ ባስተማረበትና ዳግም ይመጣል ተብሎ በሚጠበቅበት በደብረ ዘይት ተራራ ነበር፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ
ሉቃስ ይህንን “እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ” (ሉቃ ፳፬፡
፶) ብሎ በወንጌሉ እንዲሁም “በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት
መንገድ ያህል የራቀ ነው” ብሎ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፩፡፩፪ አስፍሮታል፡፡

በልደቱና በትንሣኤው የተገኙትና ለሰው ልጆች መልካሙን ዜና ያበሰሩት ቅዱሳን መላእክት በዕርገቱም ተገኝተው ለአሥራ አንዱ ሐዋርያት
የዳግም ምጽአቱን ነገር አሳስበዋቸዋል፡፡ ቅዱስ ሉቃሰ ይህንን ሲገልጽ “እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥
ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም። የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል?
ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው ” (ሐዋ ፩፡፲-፲፩) ብሏል። ቅዱስ
ዮሐንስም እንደተናገረው እርሱ ዳግም ሲመጣ ሐዋርያቱ ብቻ ያይደለ የወጉት ጭምር ያዩታል (ራዕ ፩፡፯)፡፡

ሐዋርያት እያዩት ከፍ ከፍ አለ

የጌታችን ዕርገት በመርቀቅ /በርቀት/ ሳይሆን ቀስ በቀስ ሐዋርያት እያዩት በመራቅ /በርኅቀት/ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ይህንን ሲያስረዳ
“ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው ” (ሐዋ ፩፡፱) በማለት ገልፆታል፡፡ ይህም
የሚያመለክተው የሚታይ የሚዳሰስ ሥጋን ይዞት እንዳረገ ነው፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ በቅዳሴው “በአካል ወደ ሰማይ ባረግህበት
ዕርገትህ ላይ” እንዳለው በአካል ነው ወደ ሰማይ ያረገው። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በቅዳሴው “በዚያች ሥጋ በመለኮት ኃይል ወደ
ሰማይ ወደ ቀድሞ አኗኗሩ ዐረገ” ያለው ይህንን ለማመልከት ነው፡፡ ይህንን ሲያብራራ “ሕማም የሚስማማው ግዙፍ ሥጋን ተዋሕዶ ሳለ
ከስቅለቱ አስቀድሞ በባሕር ላይ ከሔደ፣ ዛሬ ነፋስን ከፍሎ ሲያርግ ቢታይ ማንም ማን አይጠራጠር፡፡ ሥጋው አልተለወጠምና” በማለት
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞቱና ከትንሣኤው አስቀድሞ በውኃ ላይ እንደተራመደ ሁሉ፣ በለበሰው ሥጋ ወደ ሰማይ
ማረግም እንደሚቻለው አስረድቷል /ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ፣ ክፍል ፲፫ ምዕ.፥፹፯፡፲፪-፲፫/፡፡ ቅዱስ ሉቃስም “እያዩት ከፍ
ከፍ አለ” ማለቱ በእርግጥ ዕርገቱ በአካል እንደነበር ያስረግጥልናል፤ ምክንያቱም ሰው መለኮትን መመልከት አይችልምና ።

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ስለ ጌታችን ዕርገት “በደብረ ዘይት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሲመገብ እጁን በደቀ መዛሙርቱ ላይ አኖረ፤
እያንዳንዳቸውንም ባረካቸው ከዚያም የእሳት ደመና ተቀበለው፤ ከእነርሱም ሰወረው፤ በጨርቅ የጠቀለሉት ይህ ሥጋ በኪሩቤል ክንፎች
ተጋረደ፤ በጒልበት ያቀፉት ይህ ሥጋ በእሳት ሠረገላ ተቀመጠ፤ በዚህ ዓለም የተራበና የተጠማ ይህ ሥጋ እህል መብላት፤ ወይን መጠጥን
ውሃም መጠጣት ወደ ማይሻበት ወደ አርያም ከፍታ ወጣ፤ በሊቀ ካህናቱ አገልጋዮችና በጲላጦስ አደባባይ ራቁቱን የቆመ ይህ ሥጋ
በምስጋና መብረቅ ተሸፈነ፤ በእሳት ደመናም ተጋረደ፤ ጉንጮቹን በጥፊ የተመታ ይህ ሥጋ ከፍ ከፍ አለ” ብሏል፡፡

ቅዱስ ማርቆስ የጌታችንን ዕርገት በገለጸበት አንቀጽ “ጌታችን ኢየሱስም ከተነጋገራቸዉ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፥ በአባቱም በእግዚአብሔር
ቀኝ ተቀመጠ፡፡” (ማር. ፲፮፡፲፱) ብሏል፡፡ “ወደ ሰማይ” የሚለው ቃል ወደ ሰማየ ሰማያት ማለት ነው ። ይህም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን
ቤተ መቅደስ በሚሠራበት ወቅት በጸለየው ጸሎት ውስጥ እግዚአብሔርን “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥
ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ!” (፩ኛ ነገ. ፰፡፪፯) ብሎ
በጸለየው ይታወቃል። “ዐረገ” የሚለውም ( መላእክት አሳረጉት አላለም) በራሱ ኃይል ሥልጣንና ማረጉን ያሳያል፡፡ ከጌታችን በቀር በራሱ
ኃይል ያረገ የለም። ሌሎች ቅዱሳን፡ ለምሳሌ ኤልያስ እና ሄኖክም ቢሆኑ እግዚአብሔር ዐሳረጋቸው እንጂ በራሳቸው ስልጣን ዐላረጉም ።

ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ይህንን “የእግዚአብሔር ልጅ ግን ያለ መሰላል በሚንቦገቦግ የደመና ተን (ጉም) ዐረገ፤ መለኮቱ
ይተጋለታልና ወደ አየራትም ነጥቆታልና፤ ነገደ መናብርት ሊያሳርጉት አልመጡም ርሱ ራሱ በመለኮቱ ኀይል አብን ተካክሎ በቀኝ በኩል
ተቀመጠባቸው” ሲል ገልጾታል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግም ስለ ዕርገት በተናገረበት አንቀጽ “በራሱ ሥልጣን ተነሣ፤ ርሱን ያስነሣው ማንም
አይደለም፤ በሚያርግም ጊዜ ማንም ርሱን ያሳረገ አይደለም፤ ኤልያስን አስመልክቶ ዕርገቱ በጌታ አማካይነት የኾነ ነውና እንዲያርግ
ያደረገው ጌታ ነው፤ ከዚኽም የተነሣ በሠረገላ እና በእሳት ፈረስ የከበረ ሥነ ሥርዐት ተደረገለት (፪ኛ ነገ ፪፥፲፩)፤ ምክንያቱም ወደ ዐረገበት
ቦታ በራሱ ማረግ አይቻለውምና፤ የጌታችን ግን እንደተጻፈው ተለየ፤ ወደ ላይ ለመነሣት ምንም ዐይነት መንኰራኲር አላስፈለገውም፤
በአንድ ቦታ በተወሰነ ጊዜ የሚቀመጡት ሰው በአጋዥ መውጣት ያስፈልገዋል፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ ብቻ ነውና፤ የእግዚአብሔር ልጅ
ግን ራሱ እግዚአብሔር ነውና መንኰራኲር አያስፈልገውም” በማለት የእርሱ ዕርገት በራሱ ስልጣን መሆኑን አብራርቶታል፡፡

በአብ ቀኝ ተቀመጠ

ጌታችን በዕርገቱ “በአብ ቀኝ ተቀመጠ” መባሉ ለእግዚኣብሔር ግራና ቀኝ ፥ታችና ላይ ኖሮት ሳይሆን ወደ ቀደመ ክብሩ መመለሱን
በስልጣን እኩል መሆናቸዉን የሚያስረዳ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ፪፡፯ “ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰዉም ምሳሌ
ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ። እንደ ሰዉም ሆኖ ራሱን አዋረደ” የሚለዉ ቃል ጌታችን በሥጋዌው ራሱን በፈቃዱ ዝቅ አደረገ እንጅ በክብር
ከአብ ከመንፈስቅዱስ እንደማይለይ ያስረዳናል፡፡ በቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሰረት በአብ ቀኝ ተቀመጠ ማለት በሥልጣን አንድ መሆንን
ያሳያል፡፡ ስለዚህም ነቢዩ ዳንኤል በትንቢቱ “በሌሊትም ራእይ አየሁ፤ እነሆም የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ፤
በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና
ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት ነው፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፡፡” (ዳን. ፯፡፲፫-፲፬) ሲል ተናግሯል፡፡

ስለዚህ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀመጠ ስንል በክብር በልዕልና ከአብ ጋር እኩል ነው ማለታችን ነው። ይህም
ከተዋሕዶ በፊት ደካማ፣ በደለኛ እና ውርደት ይስማማው የነበረው የእኛ ሥጋ ከተዋሕዶ በኋላ ጸጋን የሚያድል፣ እውነተኛ ፍርድን
የሚያደርግ፣ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል ሥልጣን ያለው እውነተኛ ፈራጅ አምላክ እንደሆነ ለመግለጽ ነው እንጂ በመለኮቱስ ከአብ
ሥልጣን ዝቅ ያለበት የዐይን ጥቅሻ ያህል ጊዜ እንኳ የለም። “ቀኝ” የሚለው ቃል ኃይልን ቅድስናን ወይም ክብርን የሚያመለክት ነው ።
ኃይልን ከመግለፅ አኳያ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት “የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች” (መዝ. ፩፲፯፡፲፭) ሲል ተናግሯል፡፡ ክብርም
ከመግለጽ አኳያ “ጻድቃንን በቀኙ ያቆማቸዋል” (ማቴ. ፳፭፡፴፫) እንላለን፡፡ ስለዚህም “የእግዚአብሔር ቀኝ “ማለት የእግዚአብሔር ኃይል
፣ ጽድቅ ፣ ክብር ማለት ነው፡፡ ይህም በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ያህልም ያህልም የሚከተሉትን
ማየት ይቻላል፡፡

ጌታ ጌታዬን፡- ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው። (መዝ. ፻፱፡፻)

ከእንግዲህ ወዲህ የሰውን ልጅ በኀይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ አለው። (ማቴ ፳፮፡፷፬)

እነሆ፥ ሰማይ ተከፍቶ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ። (ሐዋ ፯፡፶፮)

ኀጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ፣ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፡፡ (ዕብ ፩፡፫)

በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፡፡ (ዕብ ፰፡፩)


እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና፡፡ (ዕብ ፲፪፡፪)

የጻድቃንን ዕርገት ያስገነዝብ ዘንድ ዐረገ

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤው በተስፋ ለምንጠብቀው ትንሣኤያችን አርአያ እንደሆነው ዕርገቱም ለዕርገተ ነፍሳችን፣ መንግሥተ
ሰማያትን ለመውረሳችን አርአያ ምሣሌ ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የጻድቃንን ዕርገት ያስገነዝብ ዘንድ ዐረገ፡፡ ከእኛ የተዋሐደዉን ሥጋ
በዕርገቱ ከአባቱ ቀኝ በእግዚአብሔርነቱ አስቀመጠው፡፡ እንግዲህ በዕርገቱ የእኛን ሥጋ ከመላዕክት ሁሉ በላይ አክብሮ በሰማያት ከአብ
ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አስተካክሎ ካስቀመጠውማ እንደምን እኛን መንግሥተ ሰማያትን አያወርሰንም ሊባል ይችላል? (፩ተሰ. ፬፡፲፯)
ክርስቲያኖች በሰማያት ስፍራ ከጌታችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረን እንደምንቀመጥ የጌታችን ዕርገት ያረጋግጥልናል።
የጌታችን ዕርገት ዓይነ ልቡናችንን እሱ ወደ አለባት መንግስተ ሰማያት ይመራል።

ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ሲያስረዳ እንዲህ ሲል ይላል፡፡ “ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ በአለበት በላይ
ያለውን ሹ፡፡ የላይኛውን አስቡ ፤ በምድር ያለውንም አይደለም። እናንተ ፈጽማችሁ ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋራ
በእግዚአብሔር ዘንድ የተሰወረች ናትና። ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ ያንጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በፍጹም ክብር
ትገለጣላችሁ።” (ቆላ. ፫፡፩-፬)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዕርገቱ የተስፋ ቃል ኪዳን ሰጥቶ ነበር። ለምሳሌ “እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፤ እኔ ካልሄድሁ
ጰራቅሊጦስ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ከሄድሁ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ፡፡” (ዮሐ. ፲፮፡፯) ብሏል፡፡ እርሱ በአካል ስለሚለያቸው
የሐዘን ሰሜት እንዳይሰማቸው የሚያጽናና መንፈስ እንደሚልክላቸው ከሞቱ አስቀድሞ “አብ በስሜየሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው
አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል”(ዮሐ ፲፬፥፮) ብሎ ነግሯቸዋል።

ከምድራዊ አስተሳሰብና ከስጋ መንፈስ እንዲላቀቁ “እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ እናንተ ግን ኃይልን ከላይ እስክትለብሱ
ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ሉቃ ፳፬፥፵፱ ብሏቸዋል። ይህንን ተስፋ በማመን ጌታችን ሲያርግ ወደ ሰማይ ትኩር ብለዉ ይመለከቱ
የነበሩት ደቀ መዛሙርት በሃምሳኛዉ ቀን መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸዋል። እኛም ዕርገቱን እያሰብን ዓይናችንን ወደ ሰማይ እናነሳለን።
የራሳችንንም ዕርገት ተስፋ እያደረግን ልባችንን ወደ ሰማያዊዉ ህይወት ከፍ ከፍ እናደርጋለን። በክብር ያረገ አምላክ ከትንሣኤ ሙታን
በኋላ ያለውን ዕርገታችንን የክብር ያድርግልን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

You might also like