Language Policy Edited

You might also like

Download as docx, pdf, or txt
Download as docx, pdf, or txt
You are on page 1of 24

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ

የቋንቋ ፖሊሲ ረቂቅ

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር

ክፍልአንድ
መግቢያ

ሀገራችን ኢትዮጵያ የረጅምዘመን ታሪክ ባለቤት እንደመሆኗ መጠን የሕዝቦቿም ሆነ


የቋንቋዎቿ ሥርጭት የዚያኑ ያህል ትልቅ ስፍራ ይዞ ይገኛል። በአህጉራችን ከሚገኙት
አራት የቋንቋ ቤተሰቦች መካከል ኹለቱ ማለትም አፍሮ እስያዊና አባይ ሰሐራዊ
(ናይሎ ሰሐራዊ) በኢትዮጵያ ይገኛሉ። ከአፍሮ እስያዊ ዐቢይ እናት ቋንቋ ከወጡት
ስድስቱ የቋንቋ ቤተሰቦች መካከልም ሦስቱ ማለትም የኩሽ፣ የኦሞና የሴም ቋንቋዎች
በሀገራችን መነገራቸው የሀገራችንን ብዝሀነትና ሕብረ ብሔራዊነት ያሳያል።
ኢትዮጵያ ከሰማኒያ በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ሕብረ ብሔራዊና ልሳነ-ብዙ ሀገር
ትሁን እንጂ ባለፉት ሥርዓቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች
የመንግሥትን እኩል ዕውቅና እና ድጋፍ በመነፈጋቸው ቋንቋዎቹ ለትምህርት፣
ለንግድ፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ሥርፀት፣ ለባህልና ለሥነጽሑፍ እድገት፣ በአጠቃላይ
ለዘመናዊ ሥልጣኔ መሸጋገሪያነት በሚያበቃቸው ደረጃ ሊበለጽጉ አልቻሉም።
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የቋንቋ መብቶችም አልተከበሩም። አነስተኛ
ቁጥር ተናጋሪ ያላቸው ቋንቋዎች በሌሎች ለመዋጥና ከያዙት የባህልና የዕውቀት ቅርስ
ጋር ለመጥፋት አደጋ ተጋልጠዋል።
የቋንቋን መብቶች ጥያቄ በ 1987 ዓ.ም. በጸደቀው፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ
ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ከመቸውም በላቀ ደረጃ ለመመለስ
የሚጠቅም የሕግ ማዕቀፍ ተበጅቷል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለሁሉም ሀገር በቀል ቋንቋዎች
በእኩልነት ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ክልሎች የየራሳቸውን የሥራ ቋንቋ የመምረጥ መብት
እንዳላቸው፣ እንዲሁም ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ
በቋንቋው የመጠቀም፣ ቋንቋውን የማልማትና የመጠበቅ መብት እንዳለው በሕገ
መንግሥቱ ተረጋግጧል፡፡ ሀገሪቱ ልሳነብዙ ብትሆንም አንዳንድ ቋንቋዎች ተዳምረው
በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የሚነገሩ ከመሆናቸው አንጻር ልሳነ-ብዙነትን
በማበረታታት፣ ሕብረ-ብሔራዊነትን በማጎልበት እና አንድ ኢኮኖሚያዊና ማኅበረ-
ፖለቲካዊ ኅብረተሰብ በመገንባት ረገድ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ እንዲሁም
የተወሰኑት ቋንቋዎች ድንበር ተሻጋሪና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአፍሪቃ ቀንድ
ሕዝቦች የሚጋሯቸው በመሆናቸው ኢትዮጵያን ከእነዚህ አጎራባች አገሮችና ሕዝቦች
ጋር በኢኮኖሚ፣ በባህልና በዲፕሎማሲ ይበልጥ ለማስተሳሰር ያላቸው ሚና የላቀ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ለሥራ ቋንቋነት የተመረጠው አንድ ቋንቋ
ብቻ ስለነበረ እነዚህ ቋንቋዎች በሀገረ-መንግሥት ግንባታ የላቀ ሚና እንዲኖራቸው
ሕገ መንግሥቱ አስፈላጊውን ማዕቀፍ አላበጀም፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ ሕገ መንግሥቱ ማንኛውም የሀገሪቱ ሕዝብ በቋንቋው
የመጠቀም መብት እንዳለው ቢያረጋግጥም አፈጻጸሙ ከተግዳሮት የጸዳ አይደለም፡፡
ለምሳሌ፡- በሕገ መንግሥቱ ለኹሉምንዎች የተሰጠው ዕውቅና በትክክል በኹሉም
ክልሎች አልተተገበረም። በዕውቅና አሰጣጥ ኺደት ውስጥ የንዎችና ዘዬዎቻቸው
ልዩነትና የተወሰደው ግንዛቤ ውዥንብር ፈጥሯል። ንዎችን ያለበቂ ዝግጅትና
ጥናት የሥራና የትምህርት ን ማድረጉ ለንዎቹ እድገትና ልማት ዕንቅፋት
ሆኗል። ንዎቻችንን በማልማት የሥራና የትምህርት እንዲኹም የሳይንስና
ቴክኖሎጂ ማስረጫ ለማድረግ እንደማንኛውም የልማት ዘርፍ የን ልማት
በዕቅድና በተማዊ ሥርዓት አልተመራም። ያለበቂ ዝግጅት የቋንቋ ልማት ሥራ
ስለሚጀመርና ለአመራሩ ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጥበት አግባብ ባለመፈጠሩ የአደረጃጀት፣
የአቅርቦትና የቅንጅት ችግር ይስተዋላል።
ስለሆነም በአብዛኛው ሕዝብ የሚነገሩ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ቋንቋዎች
ሕብረ-ብሔራዊነትን ለማጎልበትና አንድ ማኅበረ-ፖለቲካዊ ኅብረተሰብን ለመፍጠር፣
በተጨማሪም ከአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦችና ሀገሮች ጋር ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ትስስርን
ለማጠናከር ካላቸው ከፍተኛ ፋይዳ አንጻር ሚናቸውን በፌዴራል መንግሥት ደረጃ
ማሳደግ በማስፈለጉ፣ እንዲሁም በቋንቋ አጠቃቀም ዙሪያ የሚታዩትን ተግዳሮቶች
በማስወገድ የቋንቋ አጠቃቀም ሥርዓትን ማጥራትና ትክክለኛውን አቅጣጫ ማስያዝ
በማስፈለጉ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51 ንኡስ አንቀጽ (2) እና አንቀጽ 77 ንኡስ
አንቀጽ (6) መሠረት ይኽ የቋንቋ ፖሊሲ ተዘጋጅቷል።
የቋንቋ ፖሊሲው ራዕይ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች ሕዝቦች ቋንቋዎቻቸው
በልጽገው ለኹልአቀፍ ልማት ተጠቃሚነት የሚበቁበት፤ በሕዝቦች መካከል መከባበር፣
ብሔራዊ መግባባትና አንድነት የጎለበተበት ዲሞክራሲያዊ ሕብረተሰብ ተፈጥሮ
ማየት ነው።
ይኽ የቋንቋ ፖሊሲ በሚከተሉት ሦስት ክፍሎች የተደራጀ ነው። በመጀመሪያው
ከፍል ፖሊሲውን ለምን ማውጣት እንዳስፈለገ፣ የፖሊሲው መሠረታዊ መርሖች
ምን ምን እንደሆኑ እና ስለፖሊሲው ዓላማ ተዘርዝሯል። በኹለተኛው ክፍል
የፖሊሲው የትኩረት አቅጣጫዎች ከነስትራተጂያቸው ቀርበዋል።በዚኽ ክፍል
ትኩረት የተደረገባቸውም የቋንቋ መብቶችና በተለያዩ ምሕዳሮች ውስጥ የቋንቋ
አጠቃቀም ጉዳይ ናቸው። በሦስተኛው ክፍል የፖሊሲው አተገባበር ስልቶች
ቀርበዋል።ከዚኹ አንጻር የቋንቋ ዕቀዳና ልማት አካኼድ፣ ፖሊሲውን በማስፈጸም
ረገድ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ሌሎች ተቋሞችና ባለድርሻ አካላት
የሚኖራቸው ሚናና ኃላፊነት፣እንዲኹም ለፖሊሲው ስኬታማ አፈጻጸም
2
የሚያስፈልጉ ዝርዝር ሕጎች፣ የሀብት ግብዓቶችና የክትትል ሥርዓት
ተብራርተዋል።
በዚኽ ፖሊሲ መሠረት ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት የሚወከሉበት የቋንቋ ጉዳዮች
ምክርቤት፣እንዲኹም በቋንቋና ተዛማጅ መስኮች ጥናትና ምርምር የሚያደርግ
አንድ ሀገራዊ ተቋም፣ እና በትርጉም መስክ የሀገሪቱን ፍላጎት ለማርካት ሙያዊ
ብቃት ያላቸውን የመስኩን ምሁራን በማካተት የትርጉም ተቋም ይቋቋማል።

1. የፖሊሲው ራዕይ
የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች ሕዝቦች ቋንቋዎቻቸው በልጽገው
ለኹልአቀፍ ልማት ተጠቃሚነት የሚበቁበት፤ በሕዝቦች መካከል መከባበር፣
ብሔራዊ መግባባትና አንድነት የጎለበተበት ዲሞክራሲያዊ ሕብረተሰብ
ተፈጥሮ ማየት።

2. የፖሊሲው አስፈላጊነት

1) በአብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝቦች የሚነገሩ፣ ለመንግሥታዊ ሥራ በሠፊው አገልግሎት


ሲሰጡ የነበሩ፣ ልሳነ-ብዙነትን በማበረታታት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን
በማሳለጥ፣ ሕብረ-ብሔራዊነትን በማጎልበት፣ የአንድ ማኅበረ-ፖለቲካዊ
ኅብረተሰብን በመገንባት እና በድንበር ተሻጋሪነታቸው ከአጎራባች ሕዝቦችና
ሀገሮች ጋር ቀጠናዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ የላቀ ዕድል ያላቸው የኢትዮጵያ
ቋንቋዎች በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ተገቢው ቦታና ሚና እንዲኖራቸው
የሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍ መፍጠር ስለሚያስፈልግ፤

2) የቋንቋ መብቶች ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ቢያገኙም ራሱን የቻለ ግልጽ የቋንቋ


ፖሊሲ ስላልነበረ በቋንቋ አጠቃቀም፣ ጥበቃና ልማት ረገድ የሚነሱ ችግሮች
የሚፈቱበትን ሀገራዊ የአሠራር ሥርዓትና መርሕ ማበጀት ስለሚያስፈልግ፤

3) የቋንቋ ፖሊሲያችን ከመብትና ከእኩልነት አንጻር ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር


ከምንፈልገው አንድ የጋራ ማህበረሰብ ግንባታና ከምንጋራው ራዕይ ጋር ሊቆራኝ
ስለሚገባ፤

4) ሀገራዊ፤ ቀጠናዊ፤ አህጉራዊና እና አለምአቀፋዊ ትስስርን የሚያሳልጡ


ቋንቋዎቻችንን ማጎልበትና ማብቃት ስለሚያስፈልግ፤

3
5) ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥርፀትና ለዘመናዊ ኑሮ ማራመጃ ኹሉም ቋንቋዎች ብቁ
እንዲሆኑ የሚጎለብቱበትን ማዕቀፍ መፍጠር ስለሚያስፈልግ፤

6) ትኩረት የተነፈጋቸው ቋንቋዎች ለምተው ለመንግሥታዊ ሥራ ማካሄጃ፤


ለሳይንስና ቴክኖሎጂ መሸጋገሪያ፤ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ
የትምህርት መስጫ እና የበለጸገ የሥነጽሑፍ ቋንቋ ማድረግ ስለሚያስፈል
7) ሕገ መንግሥታዊ የቋንቋ መብቶችን በየመስተዳድር ዕርከኑና በየመንግሥት የሥራ
ዘርፎች በተሟላ መልክ በተግባር ለመተርጎም የሚያስፈልገው የተቋማትና የሰው
ኃይል አደረጃጀት፣እንዲኹም የገንዘብና የቁሳቁስ አቅርቦት የሚሟላበትን
ሥርዓት ለመፍጠር፤

8) የቋንቋ ዕቀዳና ልማት እንቅስቃሴ በኹሉም የመስተዳድር ዕርከንና በሀገር ደረጃ


እንደ ማንኛውም የልማት ዘርፍ የድርጊት መርሐ ግብርና የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለት
የሚተገበርበትን ሥርዓት ለመፍጠር፤

9) የመንግሥታዊሥራናየትምህርት መስጫቋንቋ እንዲኹም የሥርዓተ


ጽሕፈትምርጫና አጠቃቀም ኺደት በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ያገኙ የግልና የወል
መብቶችን ባገናዘበና ደረጃውን በጠበቀ ሀገራዊ መስፈርትና ቅንጅት
የሚከናወንበትን ሥርዓት ለመቀየስ፤

10) በመጥፋት ላይ ያሉ ቋንቋዎች የሚሰነዱበትን፤ የሚጠበቁበትንና


የሚያንሰራሩበትን ኹኔታ ለማመቻቸት፤

11) ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡት የኢትዮጵያ የጽሑፍ


ቅርሶች የሚጠበቁበትን፣ የሚጠኑበትንና ለባህል ልማት የሚውሉበትን ኹኔታ
ለማመቻቸት፤

12) በመገናኛ ብዙኃንና በመዝናኛ ኢንዱስትሪ ድርጅቶች አማካይነት የሚመጣውን


የባዕድ ባህል ወረራ ለመቋቋም፣ ማንነትን ለመጠበቅ እና በራስ የመተማመን
ባህልን ለማጎልበት።

3. የፖሊሲው መሠረታዊ መርሖች


1/ ሕገ መንግሥታዊ መርሖችንና መብቶችን ማክበርና ማስከበር፤
2/ ለኹሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተሰጠውን እኩል ዕውቅና
ማረጋገጥ እና ልሳነብዙነትን እንደ ሀገራዊ ሀብት መቀበል፤
3/ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን፣ ሕብረ-ብሔራዊነትን እና ቀጠናዊ ትብብርን
በማሳለጥ ረገድ የላቀ ዕድል ላላቸው ቋንቋዎች በፌዴራል መንግሥት
ደረጃ ቦታና ተልእኮ በመስጠት ሀገራዊ ፋይዳቸውን ማጎልበት፤
4
4/ ከቋንቋ መብቶች ጋር ተያይዘው በሚነሱ ጉዳዮች ለኹሉም ዜጎች
ማኅበራዊ ፍትሕን ማስፈን፤
5/ የሀገሪቱን ቋንቋዎችና ሥርዓተ ጽሕፈቶች እንደ ብሔራዊ
ሀብትና ቅርስ መቀበል፤
5/ ቋንቋን ለዜጎች የግልና የወል ብቁነትና ለሀገራዊ ልማት
ማራመጃ ማድረግ።

4. የፖሊሲው ዓላማዎች

አጠቃላይ ዓላማዎች
1/ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግስት
የተረጋገጡትን የቋንቋ መብቶች በተሟላ ሁኔታ በተግባር ለመተርጎም
እንዲቻል አስፈላጊ መዋቅሮችንና ተቋማትን፣ እንዲሁም የአፈጻጸም
ሥርዓትን መዘርጋት፤
2/ ልሳነብዙነትን በማበረታታት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጎልበትና አንድ
ማኅበረ-ፖለቲካዊ ኅብረተሰብን በመገንባት፣ እንዲሁም ሀገሪቱ ከአጎራባች
አገሮች ጋር ያላትን ትብብርና ትስስር በማሳደግ ረገድ ትልቅ ፋያዳ ያላቸው
ቋንቋዎች በፌዴራል መንግሥት ደረጃ የሚኖራቸውን ሚና ለማጠናከር
የሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍ መፍጠር፤

3/ ለመንግስት ሥራ በቋንቋ አጠቃቀም ዙሪያ ላጋጠሙና ወዳፊትም


ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች የመፍትሄ አቅጣጫ መጠቆም እንዲሁም
ከህዝብ የሚነሱ ዘለቄታዊና ሕጋዊ ምላሽ የሚያገኙበትን የሊሲ ማዕቀፍ
ማበጀት፤
4/ የቋንቋ አጠቃቀምን፣ዕቀዳ እና ልማትን በገር አቀፍ ደረጃ ሥርዓት ማስያዝና
ቋንቋዎቹን ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥርፀት በሚመች መልክ የሚያድጉበትን
ኹኔጸሸ ማመቻቸት፤

ዝርዝር ዓላማዎች
1/ ትኩረት ያላገኙ ወይም የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው ቋንቋዎች
ሥርዓታዊና ተቋማዊ እንክብካቤ የሚያኙበትንና ቋንቋዎቹ
የያዟቸው ባህላዊ ዕሴቶችና ዕውቀቶች ለየትውልዱ
የሚተላለፉበትን ኹኔታ ማመቻቸት፤
2/ የኢትዮጵያን የምልክት ቋንቋ ጨምሮ፣ የቋንቋና የሥርዓተ
ጽሕፈት ሀብታችንና ቅርሶቻችንን በምርምር፣በትምህርትና
በቴክኖሎጂ በመታገዝ መጠበቅ፣ ማልማትና ለሀገራዊ ልማት
መጠቀም፣
5
3/ የቋንቋ ልማት ለዜጎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ብቁ
ተሳትፎ የሚያገልግልበትን፣ ለሕዝቦች መቀራረብና አንድነት፤
እንዲኹም ዜጎች ኑሮዋቸውን ለመምራት የሚያስፈልጋቸውን
መረጃ የማግኘት ዕድል የሚያሰፋበትን ስልት መቀየስ፤
4/ የቋንቋ ልማት ሀገራዊ፤ ቀጠናዊ፤ አህጉራዊና እና አለምአቀፋዊ
ትስስርን ለማሳለጥና ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተጨማሪ የስራ
ቋንቋዎችን ማካተት፤
5/ በቋንቋ ጥናት መስክ የተሰማሩ ተመራማሪዎች ለቋንቋ ልማት
የተሻለ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን የተቀናጀ አሠራር ማስፈን፤
6/ ስለቋንቋዎችና ዘዬዎቻቸው ማበልጸግ አስፈላጊነት በተመለከተ
በተወሰኑ የሕብረተሰቡ ክፍሎች ውስጥ ያለውን የተዛባ አመለካከት
ለማስተካከል የተጠናከረ የግንዛቤ ማዳበርያ ሥራ የሚካሄድበትን
ስልት መቀየስ፤
7/ ጥንታዊ የኢትዮጵያ የጽሑፍ ቋንቋዎች በሀገሪቱ ውስጥ በጥልቀት
የሚጠኑበትንና ለባህልና ለቋንቋ ልማት የበለጠ አስተዋጽኦ
የሚያደርጉበትን፤ በእነዚህ ቋንቋዎች ውስጥ የሚገኘው ሀገር በቀል
ዕውቀት ለሕዝብ ተደራሽ የሚሆንበትን ኹኔታ ማመቻቸት፤
8/ ኢትዮጵያ ለኹሉም ቋንቋዎች እኩል ዕውቅና በመስጠትና
ልሳነብዙነትን በማበረታታት፣ ቋንቋዎች የጽሕፈት፣ የመንግሥታዊ
ሥራና የትምህርት መስጫ እንዲኹም የትምህርት ቋንቋ ማድረግ
የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፡፡

ክፍል ኹለት
የፖሊሲው የትኩረት አቅጣጫዎችና ማስፈጸሚያ ስልትዎች

5. የቋንቋ መብቶች ጥበቃ


የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት
ለኹሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎችእኩልነት በሰጠው ዕውቅና መሠረት
የሚከተሉት የቋንቋ መብቶች ተግባራት ተፈጻሚ ይሆናሉ።
1/ አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብየተናጋሪዎቹ ቁጥር አነስተኛ
ቢሆንም በቋሚነት በሚኖርበት አካባቢ አፍ መፍቻ ቋንቋውን
የመጠቀም፣የመጠበቅ፣የማልማት፣ ለቋንቋው የሚስማማ ሥርዓተ
ጽሕፈት የመምረጥ ወይም ደረጃውን ጠብቆ የመቅረጽ መብት
አለው።
2/ አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የተናጋሪዎቹ ቁጥር አነስተኛ
ቢሆንም በሚኖርበት አካባቢ በአፍ መፍቻ ቋንቋው ወይም
6
በመረጠው የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ሕዝባዊ አገልግሎቶችን
በሚኖርበት አካባቢ የማግኘት መብት አለው፡፡

3/ አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብየተናጋሪዎቹ ቁጥር አነስተኛ


ቢሆንም በአፍ መፍቻ ቋንቋው ወይም በመረጠው የጋራ
መግባቢያ ቋንቋ ልጆቹን ቢያንስ ከአፀደ ሕጻናት እስከ 1 ኛ
ደረጃ ትምህርት መጨረሻ ድረስ የማስተማር፣ አፍ መፍቻ
ቋንቋውን ልጆቹ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲማሩለት
የመወሰን፣ ልጆቹ በመረጠው ቋንቋ የሚማሩበትን ትምህርት
ቤት የመምረጥ ወይም ደረጃውን ጠብቆ በራሱ የማቋቋም
መብት አለው።
4/ አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብአባላቱ በተለያየ ክልል፣ ዞን፣
ወረዳ ወይም በሌሎች ልሳነብዙ ማኅበረሰቦች መካከል
ተሰባጥረው የሚኖሩ ቢሆንም፤ በዚኹ ዓንቀጽ ከቁጥር 1 እስከ 3
የተዘረዘሩትን መብቶች በከፊል ወይም በሙሉ ለአፈጻጸም
በሚመች መልኩ የመጠቀም መብት አለው።
5/ በተለያየ ተጽዕኖ ምክንያት አብዛኞቹ አባላቱ የአፍ መፍቻ
ቋንቋቸውን ትተው ወደ ሌላ ቋንቋ የተሸጋገሩበት ብሔር፣
ብሔረሰብና ሕዝብ የመጀመሪያ ቋንቋውን እንዲያንሰራራ
ለማድረግና በዚኹ ዓንቀጽ ከቁጥር 1 እስከ 3 የተዘረዘሩትን
መብቶች ለመጠቀም እንዲችል የመንግስትን ልዩ ድጋፍ
የማግኘት መብት አለው፡፡
6/ የተከሰሱ ሰዎች የፍርድ ሂደቱ በማይገባቸው ቋንቋ በሚካሄድበት
ኹኔታ ክርክሩ በሚገባቸው ቋንቋ እንዲተረጎምላቸው የመጠየቅ
መብት አላቸው፡፡
ሌሎች ተያያዥ መብቶች
1/ መስማት የተሳናቸው ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ በኢትዮጵያ
የምልክት ቋንቋ የመማር፣ ለመግባቢያ የመጠቀም፣ የማልማትና
ከመንግሥት መረጃ የማግኘት፤ የተስማሚ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ
የመሆን፤ እንዲኹም በዚኽ መብት ለመጠቀም እንዲችሉ
የመንግሥትን ልዩ ድጋፍ የማግኘት መብት በምት አላቸው።
2/ ዓይነ ስውራን ዜጎች በተዳሳሽ ሥርዓተ ጽሕፈት (ብሬይል)
የመማር፣ ከመንግሥት መረጃ የማግኘትና የተስማሚ ቴክኖሎጂ
ተጠቃሚ የመሆን፤ እንዲኹም ይኽን መብት ለመጠቀም
እንዲችሉ የመንግሥትን ልዩ ድጋፍ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
ተቋማዊ መብት

7
1/ ማንኛውም ሕዝባዊ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ለአካባቢው
ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ከተረጋገጡ የቋንቋ መብቶች ጋር
በሚጣጣም መልክ የመጠቀም መብት አለው፡፡

ስትራተጂዎች

1/ ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ ሕዝብ በቋንቋው እንዲጠቀም ዓቅም


እስከፈቀደ ድረስ ቋንቋው ለመደበኛ አግልግሎት የሚበቃበት፣ ወይም
በአስተርጓሚ አማካይነት የመንግሥታዊ አገልግሎትና የጠቃሚ
መረጃዎች ተደራሽ የሚሆንበት ሥርዓት ይዘረጋል።

2/ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እንዲጠበቁና እንዲለሙ የቋንቋዎች ጥናትና


ምርምር፣ ስነዳና የሥርዓተ ጽሕፈት ቀረጻ የአጠቃላይ ሀገራዊ ልማቱ
አንድ አካል ሆኖ በዕቅድ እንዲመራ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍና
ተቋም ያደራጃል።

3/ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተስማሚ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚሆኑበት


ኹኔታ ይመቻቻል።

4/ ሕገ መንግሥታዊ የቋንቋ መብቶች መከበራቸው የሚረጋገጥበት


የክትትል ሥርዓት ይዘረጋል።

6. የሥራ ቋንቋ

1/ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋዎች


(ሀ). የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋዎች አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣
ትግርኛ፣ ሶማልኛ፣ አፋርኛ ናቸው፡፡ ልሳነብዙ የፌዴራል ቋንቋ
ሥርዓት ሕጋዊነት ወደፊት በሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ
ይረጋገጣል፡፡

(ለ) ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በጊዜ ሂደት የፌዴራል


መንግሥት የሥራ ቋንቋ የሚሆኑበት ኹኔታ በጥናት ላይ
ተመሥርቶና አቅምን ባገናዘበ መልክ ይመቻቻል፡፡

(ሐ) እያንዳንዱ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚሰጥ የፌዴራል


መንግሥት አካል አማርኛም ሆነ ሌሎች የፌዴራል የሥራ
ቋንቋነት ዕውቅና ያገኙ ቋንቋዎችን የማይችሉና
አገልግሎቱ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚስተናገዱበትን
የግንኙነትና የመግባቢያ ስልት ከሕገ መንግሥታዊ
መብቶች ጋር በሚጣጣም መልክ ይቀይሳል።
8
2/ የክልል መንግሥታት የሥራ ቋንቋ
ሀ) የክልል መንግሥታት የሥራ ቋንቋ በየምክር ቤታቸው
በሕግ የተወሰነው ይኾናል።
ለ) ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በጊዜ ሂደት የፌዴራል መንግሥት
የሥራ ቋንቋ የሚሆኑበት ኹኔታ በጥናት ላይ ተመሥርቶና
አቅምን ባገናዘበ መልክ ይመቻቻል፡፡

ሐ) ማንኛውም የክልል መንግሥት የክልሉን የሥራ ቋንቋ


የማይችሉ ዜጎች የሚስተናገዱበትን የግንኙነትና
የመግባቢያ ስልት ከሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው ጋር
በሚጣጣም መልክ ይቀይሳል።
መ) በኹለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች መካከል ድንበር
ተሻጋሪ ቋንቋን በሚመለከት በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት
የተረጋገጡት መብቶች እንደተጠበቁ ሆነው ቋንቋው
ከሚነገርባቸው ክልሎች መስተዳድሮች ጋር በመመካከርና
በመቀናጀት ስለ ቋንቋው አጠቃቀምና ልማት በጋራ
ይወስናሉ።
ሠ) ማንኛውም የክልል ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ የሚገኙትን
ቋንቋዎች ዕቅድና የልማት መርሐ ግብር ሕገ መንግሥታዊ
መብትንና ዓቅምን በማገናዘብ ያፀድቃል።
ረ) በአንድ ክልል ውስጥ በተዋረድ ላለ የአስተዳደር ዕርከን
የሥራ ቋንቋ ምርጫ እና የአፈጻጸም ኺደት በዚያ ቋንቋ
መንግሥታዊ ሥራዎችን በተሟላ ደረጃ ለማከናወን
የሚያስችል በቂ የባለሙያ አቅርቦት እንዲኖር ያደርጋል።

3/ በፌዴራልና በክልሎች መካካል የመደበኛ ግንኙነት ቋንቋ


በፌዴራልና በክልል መስተዳድር አካላት መካከል የሚደረግ
መደበኛ የሥራ ግንኙነት በፌዴራሉ የሥራ ቋንቋዎች አማካይነት
ይኾናል።

4/ በየክልሉ ባሉ የአስተዳደር ዕርከን አካላት መካከል የመደበኛ


ግንኙነት ቋንቋ
በአንድ ክልል ሥር የሚገኙ የተለያየ የሥራ ቋንቋ የሚነገርባቸው
ዞኖችና ወረዳዎች አስተዳደር አካላት መካከል ለሚኖረው የሥራ
ግንኙነት የሚጠቀሙበት መደበኛ የሥራ ቋንቋ በክልሉ ምክር
ቤት እና/ እንደ አግባብነቱ በተዋረድ ባሉ የብሔርብሔረሰብ ምክር
ቤቶች/በሚወሰነው አግባብ ይሆናል።

5/ የሥራ ቋንቋንና ልሳነ ብዙነትን ስለማጣጣም


9
ልሳነብዙነት በማንኛውም ዕርከን ላይ ባሉ የመንግሥት መሥሪያ
ቤቶች የሥራ አስፈፃሚዎችና በተገልጋይ ሕዝብ መካከል
በሚደረግ መደበኛ የንግግር እና የጽሑፍ ግንኙነት ይበረታታል።
ስትራተጂዎች
1/ ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የፌዴራል
የሥራ ቋንቋ የሚሆኑበት የሕግ አግባብ በሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ
ይወሰናል፡፡ በፌዴራል ደረጃ የቋንቋዎቹ አጠቃቀም በሕገ መንግሥቱ
ማእቀፍ በሚዘጋጁ ዝርዝር ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች
ይወሰናል፡፡
2/ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት፤ እንዲኹም በተዋረድ የሚገኙ
መስተዳድሮች የሥራ ቋንቋዎች በመንግሥት የሕግ አውጪ፣
አስፈጻሚና የፍትሕ አካላት መደበኛ ሥራዎች በጽሑፍና በንግግር
አማካይነት በሥራ ላይ ይውላሉ።
2/ ሀገራዊ አንድነትን በልሳነብዙነት ለማበረታታት እንዲቻል፣
በፌዴራልና በክልል ደረጃ የሚገኙ አስፈጻሚ አካላት መደበኛ
ሥራቸውን ለማካሄድና ተደራሽ ሕዝባዊ አግልግሎት ለመስጠት
እንዲችሉ ከፌድራሉ ቋንቋዎች መካከል ቢያንስ ኹለቱን
እንዲያውቁና እንዲጠቀሙ ይበረታታሉ።
3/ በፌደራል መንግሥት የሚወጡ ፖሊሲዎች፣ አዋጆች፣ ደንቦች፣
መመሪያዎች፣ የየምክር ቤቱ ዘገባዎች፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ
ተቀብላ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና የሰብአዊ መብት
ሰነድች በክልል መስተዳድሮች እና በፌዴራል መንግሥት የሥራ
ቋንቋዎች ተተርጉመው ለሕዝብ ተደራሽ የሚሆኑበት ኹኔታ
ይመቻቻል።
4/ የክልል መንግሥታት ፖሊሲዎች፣ አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና፣
የየምክር ቤቱ ዘገባዎች በፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋና
በየክልሉ የመስተዳድር ዕርከን የሥራ ቋንቋዎች ተተርጉመው
ለሕዝብ ተደራሽ የሚሆኑበት ኹኔታ ይመቻቻል።
5/ በማንኛውም የግል ዘርፍ የሚሰማሩ ድርጅቶች እና መንግሥታዊ
ያልኾኑ ድርጅቶች በሚሠሩበት አካባቢ በሚነገረው
ቋንቋ/ቋንቋዎች አገልግሎቶቻቸውን ለሕዝብ እንዲሰጡ
ይበረታታሉ።

7. የመገናኛ ብዙኃንና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ቋንቋአጠቃቀም


1/ የማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚተላለፍና በሀገርኛ ቋንቋ
የሚጠቀም መገናኛ ብዙኃን የሕትመትም ሆነ የኤሌክትሮኒክ
ሥርጭት ልሳነብዙነትን የሚያበረታታ እና መልካም ሥነ ምግባርን
የተከተለ ይኾናል።

10
2/ ማንኛውም በኤሌክትሮኒክ የመገናኛ ብዙኃን (ቴሌቨዥን፣
ሬዲዮእናድረ ገጽ) አማካይነት ለመረጃ ማሰራጫ የሚውል ቋንቋ
ሥርዓተ ጽሕፈት እንዲኖረው ይደረጋል።
3/ ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ ለመሥራት ፈቃድ ያለው
የመገናኛ ብዙኃን በሀገርኛ ቋንቋ በሚያሰራጨው ፕሮግራም
ወይም የሚያትመው ዓምድ ውስጥ ሀገርኛ አቻ ቃላት ወይም
ሐረግ እንዲጠቀም፤ የአንድን ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ባህልና
ማንነት፣ ክብር በሚጠብቅ መልኩ እንዲሆን፤ የማዕረግ ስምን
በአግባቡ እንዲጠቀም፤ የአካባቢውን ባህላዊ የአክብሮትና
የጨዋነት የቋንቋ ሥነ ምግባር የተከተለ እንዲሆን ይደረጋል።
4/ ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ
ድርጅት በቃል፣ በጽሑፍ፣ በምስልና በትዕይንት መልክ
በሀገርኛቋንቋዎች የሚያቀርበው የኢንዱስትሪ ውጤት ወይም
ማስታወቂያ የአካባቢውን ባህላዊ የአክብሮትና የጨዋነት የቋንቋ
ሥነ ምግባር የተከተለ እንዲሆን ይደረጋል።
ስትራተጂዎችች
1/ የመገናኛ ብዙኃንና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ የቋንቋ አጠቃቀም
የምልክት ቋንቋን ጨምሮ ልሳነብዙነትን የሚያራምድ እንዲሆን
አግባብ ያለው ሥርዓት ይዘረጋል።
2/ በመገናኛ ብዙኃንና በመዝናኛ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ለተሰማሩ
ባለሙያዎች ስለቋንቋ አጠቃቀም ሥነምግባር አጫጭር ሥልጠና
የሚሰጥበት ስልት ይቀየሳል።
3/ በሥነምግባራዊ የቋንቋ አጠቃቀም ረገድ የግንዛቤ ማዳበሪያ
ሁነቶች፣ የውይይት መድረኮች፣ የመገናኛ ብዙኃን ዝግጅቶች፣
በራሪ ወረቀቶችና ሌሎች የመረጃ ምንጮች ተዘጋጅተው
ለተጠቃሚዎች በስፋት እንዲሰራጩ ይደረጋል።
4/ የመገናኛ ብዙኃንና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች የቋንቋ
አጠቃቀም የሚመራበት የሙያ ደንብ እና የሥነ ምግባር
መመሪያ (ፕሮፌሽናል ኮድ) ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ ይውላል።
5/ የመገናኛ ብዙኃንና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ የፈቃድ አሰጣጥና
ዕድሳት የቋንቋ አጠቃቀም ሥነምግባርን ባገናዘበ መልኩ ይኾናል፤
ለዚሁም ማስፈፀሚያ አስፈላጊው የአሠራር ሥርዓትና ሕግ
ይዘጋጃል።

8. ቋንቋና ትምህርት
1/ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ ሕዝብ ቋንቋውን
ለትምህርት አገልግሎት የማዋል መብቱ የተረጋገጠ ሲሆን
ቋንቋው በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ሲካተት የቋንቋ መብትን
ከትምሀርት ጥራት ጋር ባገናዘበ መልኩ ይኾናል።
11
2/ የትምህርት ሥርዓቱ እያንዳንዱ ተማሪ ከአፍ መፍቻ ቋንቋው
በተጨማሪ አንድ ሌላ የፌዴራል ን የሚማርበትን ሥርዓተ
ትምህርት በመንደፍ ልሳነብዙነትን በኺደት ተግባራዊ ያደርጋል።
3/ ኢትዮጵያ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ከሌሎች ሀገሮች
ጋር ለሚኖራት የውጭ ግንኙነት አገልግሎት በማስፈጸሚያ
ስልታዊ ፍላጎቷ መሠረት የተመረጡ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች
በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲካተቱ ይደረጋል።
4/ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያስፈልገውን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና ግንኙነት
ለማጎልበት የፌዴራሉ ቋንቋዎች የአካባቢ መስተዳድሩንና የትምህርት
ቤቱን አቅም፣ እንዲሁም የአካባቢውን ኅብረተሰብ የቋንቋ አጠቃቀምና
ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ በትምህርትነት ይሰጣሉ።
5/ ብሔሮች ብሔረቦችሕዝቦች አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ
በራሳቸው ቋንቋ ወይም በብሄራዊ ክልላዊና በአገርአቀፍ
ሥርጭታቸውና በተናጋሪ ብዛታቸው መሠረት በሚመርጡት
ቋንቋ ሊማሩ ይችላሉ።

ስትራተጂዎች
1/ የክልል መስተዳድሮች ከክልሉ የሥራ ቋንቋ ውጪ ያሉ ሌሎች የፌዴራሉ
መንግሥት የሥራ ቋንቋዎች እንደየአካባቢው ኅብረተሰብ ምርጫ እና
አቅምን ባገናዘበ ኹኔታ በትምህርትነት ወይም በትምህርት
መስጫነት በነሱ ቁጥጥር ሥር ባሉት የትምህርት ተቋማት እንዲሰጡ
አስፈላጊውን ዝግጅትና አቅርቦት ያሟላሉ፡፡
2/ የማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ ሕዝብ ቋንቋ ለትምህርት መስጫም
ሆነ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ተመርጦ በተለያየ
የትምህርት ዕርከን ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ከመካተቱ
አስቀድሞ ለቋንቋው የሚስማማ ሥርዓተ ጽሕፈት፣ የቋንቋው
የሰዋስው ሥርዓት ጥናት፣እንዲኹም የመማሪያና የማስተማሪያ
መጻሕፍት፣ ደጋፊ የንባብ ጽሑፎችና በቋንቋው የሠለጠኑ በቂ
መምህራን መኖራቸው ይረጋገጣል።
3/ በትምህርት መስጫ ቋንቋ ልዩነት ምክንያት የትምህርት ጥራት
መጓደል እንዳይከሠት፣ በኹሉም ክልላዊ መስተዳድሮች የየዕርከኑ
ሥርዓተ ትምህርት አቀራረጽና የአተገባበሩም ኺደት
ተመጣጣኝና ሀገር አቀፍ የጥራት ደረጃን የሚያሟላ መሆኑን
ለማረጋገጥ የክትትል፣ የግምገማና የባለድርሻ አካላት የምክክር
ሥርዓት ይዘረጋል።
4/ በአንድ ክልል ውስጥ ከክልሉ የትምህርት መስጫ ቋንቋ ውጭ
በሌላ አፍ መፍቻ ወይም የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ትምህርት
እንዲሰጥ ከአካባቢው ብሔር፣ ብሔረሰብ ሕዝብ ሲቀርብ
በሕገመንግስቱ በተቀመጡለሚነሳጥያቄ የቋንቋ ድንጋጌዎች
መሰረት የሚስተናገድ ይሆናል፡፡
12
5/ የአንድ ብሔር፣ ብሔረሰብ ሕዝብ ተማሪዎች ከአፍ መፍቻቸው
ወይም ከመረጡት የአካባቢው የጋራ መግባቢያ ቋንቋ በተጨማሪ
አንድ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት
ዓይነት በተጠናከረ መልክ እንዲማሩት ይደረጋል።
6/ የአፀደ ሕፃናት እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የትምህርት
መስጫ ቋንቋ የተማሪዎቹ አፍ መፍቻ ቋንቋ ይኾናል።
7/ የአንድ ብሔር፣ ብሔረሰብ ሕዝብ ተማሪዎች ከአፍ መፍቻቸው
ወይም ከመረጡት የአካባቢው የጋራ መግባቢያ ቋንቋ በተጨማሪ
የፌዴራል መንግሥቱን የሥራ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት
ዓይነት በተጠናከረ መልክ እንዲማሩት ይደረጋል።
8/ የጎልማሶች ተግባራዊ ትምህርት የትምህርት መስጫ ቋንቋ
በተቻለ መጠን የጎልማሶቹ አፍ መፍቻ ቋንቋ ይኾናል። ይሁን
እንጂ የጎልማሶቹ ምርጫ ትምህርቱ በሌላ በደንብ በሚረዱት
የጋራ መግባቢያ ን እንዲሰጥ ከሆነ ዓቅም እስከፈቀደ ድረስ
ትምህርቱ በመረጡት ቋንቋ እንዲሰጥ ኹኔታዎች ይመቻቻሉ።
9/ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና
የከፍተኛ ትምህርት የማስተማሪያ ቋንቋ ከእንግሊዝኛ ወደ
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ቋንቋ/ዎች እንደየ
ቋንቋዎቹ የእድገት ደረጃ እየታየ በአማራጭነት የሚሸጋገርበት
የጊዜ ሰሌዳና ስትራተጂ ይዘጋጃል።
10/ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ለተለያየ ተግባራዊ አግልገሎት
የሚያስፈልገውን የቋንቋ ክህሎት በሚያስጨብጥ መልኩ
ተጠናክሮ በማንኛውም የትምህርት ዕርከን ባለ ሥርዓተ
ትምህርት ውስጥ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ተካትቶ
እንዲሰጥ ይደረጋል።
11/ ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ የሀገሪቱን ማስፈጸሚያ ስልትያዊ
ፍላጎት መሠረት በማድረግ ከሚመረጡ ሌሎች ዓለም አቀፍ
ቋንቋዎች መካከል ቢያንስ አንድ ሌላ ቋንቋ መርጠው
ተማሪዎች ከተወሰነ የትምህርት ዕርከን ጀምሮ መማር
በሚያስችላቸው ኹኔታ ሥርዓተ ትምህርቱ ይዘጋጃል።
12/ በኹለተኛ ሀገርኛ ቋንቋ እና በውጭ ቋንቋ ትምህርትነት
የተመረጡት ቋንቋዎች በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ
የሚጀምሩበት የክፍል ደረጃ በሀገሪቱ ውስጥ ተመሳሳይ እንዲሆን
ይደረጋል።
13/ የብሔሮችብሔረሰቦችሕዝቦች የቋንቋ መምህራን ሥልጠና
ዘመናዊና ውጤታማ የቋንቋ ማስተማሪያ ዘዴዎችን ያካተተ
መሆኑ፣ መምህራኑ የሚሠለጥኑበት ቋንቋ ለትምህርት ዕርከኑ
ከተወሰነው የትምህርት መስጫ ወይም በትምህርትነት
ከተመረጠው ቋንቋ ጋር ተመሳሳይ መሆኑ፣እንዲኹም
የሠልጣኞቹ መምህራን ቁጥር በየትምህርት ዕርከኑ ካለው

13
ፍላጎት ጋር የተጣጣመ መሆኑ እና ለትምህርት ደረጃው
ተመጣጣኝ የሆነ የሙያ ብቃት ያላቸው መሆኑ ይረጋገጣል።

9. ሥርዓተ ጽሕፈት

ማንኛውም የብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ ቋንቋ ለመደበኛ አገልግሎት


እንዲውል ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ ጽሕፈት ይዘጋጅለታል፤ ጥራቱ
ተጠብቆም በስፋት አገልግሎት ላይ የሚውልበት ኹኔታ ይመቻቻል።

ማስፈጸሚያ ስልቶች
1/ በልሳነብዙ ክልል ውስጥ በአካባቢው ለሚነገር ጽሑፍ-አልባ ቋንቋ
በዕቅድና በቋንቋው ሥነድምፅ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ሥርዓተ
ጽሕፈት እንዲዘጋጅለት ይደረጋል።
2/ በአገልግሎት ላይ የዋሉትን የኢትዮጵያ ሥርዓተ ጽሕፈቶች
ደረጃና መደበኛነት ለመጠበቅ በተለይ መንግሥታዊ ተቋማት፣
የትምህርት ተቋማትና መገናኛ ብዙኃን ልዩ ኃላፊነት
ይኖርባቸዋል።ይኽን ለማስፈጸምም የክትትል ሥርዓት ይዘረጋል።
3/ ለማንኛውም ቋንቋ ሥርዓተ ጽሕፈት ቀረጻ ወይም የማሻሻል
ሥራ እንደ ምንጭ እንዲያገለግል አንድ ማዕከላዊ የፊደላት ቋት
ይደራጃል፤ በየጊዜው ይዳብራል፤ ለተጠቃሚዎችም ተደራሽ
እንዲሆን ይደረጋል።
4/ የቋንቋዎቹን ተናገሪ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦችባሳተፈ
መንገድ ዝምድና እና ከፍተኛ የሥነድምፅ ተመሳሳይነት ባላቸው
ቋንቋዎች ወይም ዘዬዎች መካከል ያሉትን መጠነኛ ልዩነቶች
በማቻቻል ሥርዓተ ጽሕፈታቸው እንዲጣጣም ይደረጋል።
5/ ለትምህርት ወይም ለሥራ ቋንቋነት አገልግሎት ላልዋሉና
ሥርዓተ ጽሕፈት ለሌላቸው ቋንቋዎች ለሥርዓተ ጽሕፈት
ቀረጻ መሠረት የሚሆነውን ፊደል የክልሉ ምክር ቤት
በቋንቋዎቹ ሥነድምፅ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ያፀድቃል።
በአግልግሎት ላይ ያለውን ፊደልም ሆነ ሥርዓተ ጽሕፈት
የማሻሻል ሐሳብ ለምክር ቤቱ በየዕርከኑ የሚገኘው አግባብ
ያለው የሥነልሳን ባለሙያዎች አካል ያቀርባል።
10. የአደባባይ ቋንቋ አጠቃቀም
የአደባባይ የቋንቋ አጠቃቀም ሕገ መንግሥታዊ መብቶችንና የሀገሪቱን
ባህሎች በሚያከብር፤ እንዲኹም ኢትዮጵያዊ ማንነትንና በራስ
መተማመንን በሚያንፀባርቅ መልክ እንዲመራ ይደረጋል።
ማስፈጸሚያ ስልቶች
1/ በማንኛውም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት
መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚደረግ የንግግርም ሆነ የጽሑፍ
ግንኙነት፣እንዲኹም የውስጥ ሰሌዳ ማስታወቂያ ሰብእናን ያከበረ
እና ትሕትናን የተላበሰ ይኾናል።
14
2/ በውጭ ሀገር የሚገኝ የኢትዮጵያ ውክልና ያለው ማንኛውም
ድርጅት፤ የየብስ፣ የባሕርና የአየር መጓጓዣ መለያ ስም (በዓለም
አቀፍ አሠራር አስገዳጅ ምክንያት ከሌለ በስተቀር) መጀመሪያ
የፌዴራሉ መንግሥት በመረጠው አንድ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ
በጉልህ ይጻፋል፤ እንደ አስፈሊጊነቱ ከሀገርኛው ስም ግርጌ ወይም
ቀጥሎ አግባብ ባለው ሌላ ቋንቋ ይጻፋል።
3/ ማንኛውም ዓይነት በአደባባይ ላይ የሚቀርብ ሕዝባዊ
መልእክትም ሆነ የንግድ ማስታወቂያ የሚጻፍበት የአካባቢውን
ቋንቋ በማስቀደምና በማጉላት የሚጻፍና በይዘቱም ከአካባቢው
ባህልና ሥነ ምግባር ጋር የሚጣጣም ይኾናል።
4/ ማንኛውም በዓለም አቀፍ መደበኛ መድረክ ላይ ንግግር
የሚያደርግ ማንኛውም የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካይ አስገዳጅ
ኹኔታ ከሌለ በስተቀር የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ
ከሆኑት በአንዱ ሐሳቡን ያቀርባል።

11. የስያሜ አሰጣጥ


1/ ማንኛውም መንግሥታዊ፣ የግል ወይም መንግሥታዊ ያልሆነ
ሀገር በቀል ድርጅት ለራሱም ሆነ ለምርቱ ወይም ለአገልግሎቱ
መጠሪያነት የሚመርጠው ስም ኢትዮጵያዊ ማንነትንና ባህልን
መሠረት ባደረገ ሀገርኛ ቋንቋ ይሆናል።
2/ የግለሰቦች መጠሪያ ስሞች በተቻለ መጠን የሀገርኛ ቋንቋንና
ባህልን መሠረት ያደረጉ እንዲሆኑ የተጠናከረ የግንዛቤ ማዳበሪያ
ሥራ በተከታታይነት ይሰራል።
ስትራተጂዎች
1/ የመንግሥት ድርጅቶች ለራሳቸውም ሆነ ለአገልግሎቶቻቸው
ወይም ለምርቶቻቸው የሚያወጧቸው ስያሜዎች ኢትዮጵያዊ
ማንነትንና ባህልን መሠረት ባደረገ ሀገርኛ ቋንቋ መሆኑን
የሚያረጋግጡበት ሥርዓት ይዘረጋሉ።
2/ መንግሥታዊ ያልኾኑና የግል ድርጅቶች ለራሳቸውም ሆነ
ለአገልግሎቶቻቸው ወይም ለምርቶቻቸው የሚያወጧቸው
ስያሜዎች ኢትዮጵያዊ ማንነትንና ባህልን መሠረት ባደረገ
ሀገርኛ ቋንቋ መሆኑ የሚረጋገጥበት የፈቃድ አሰጣጥ፣ የምዝገባና
የቁጥጥር ሥርዓት አግባብ ባለው መንግሥታዊ አካል ይዘረጋል።
3/ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ለልጆቻቸው መጠሪያ የሚያወጧቸው
ስሞች በተቻለ መጠን የሀገርኛ ቋንቋንና ባህልን መሠረት ያደረገ
መሆኑ በኢትዮጵያዊ ማንነታቸውና በባህላቸው የሚኮሩበት፣
በራሳቸው እንዲተማመኑ የሚያበረታታና ሰብእናቸውን
የሚያጎለብት እንዲሆን በማዋለጃ የጤና ተቋማት፣ በመገናኛ
ብዙኃን፣ በሕዝባዊ ውይይት፣ በድራማ፣ በሥነጽሑፍና ሌሎች

15
ትምህርታዊ ዘዴዎች የተጠናከረና ተከታታይ የግንዛቤ ማዳበሪያ
ሥራዎች ይሠራሉ።

12. ቋንቋና ዘዬን ስለመለየትና ስለማጣጣም


የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ዘዬዎቻቸው ብዛትና ዓይነት በውል ተለይቶ ዘዬዎቹ
የሚጣጣሙበትና ቋንቋዎቹ የሚለሙበት ሥርዓት ይዘረጋል።
ማስፈጸሚያ ስልቶች
1/ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ዘዬዎች በቅደም ተከተል በዝርዝር
የሚጠኑበት፣ የሚቆጠሩበትና በውል የሚታወቁበት ዕቅድ፣ የድርጊት
መርሐ ግብርና የጊዜ ሰሌዳ ይዘጋጃል።
2/ የተለያዩ ዘዬዎች የአንድ ቋንቋ አካል መሆናቸው በሥነልሳናዊ ጥናት
በሚረጋገጥበት ጊዜ ዘዬዎቹን የማጣጣምና ወደመበኛነት የማሸጋገር
ሥራ በዕቅድ ተግባራዊ ይኾናል።

13. የትርጉምና የአስተርጓሚነት ሙያ ብቃት፣ ዕውቅና እና ደረጃ

የትርጉምና የአስተርጓሚነት ሙያ ዕውቀትን ለማሰራጨት፣ ፍትሕን


ለማስፈንና ቋንቋን ለማልማት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በመገንዘብ
የሙያ መስኩ እንዲጎለብት አስፈላጊው ተቋማዊ ድጋፍ ይደረጋል።

ማስፈጸሚያ ስልቶች
1/ የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋን ጨምሮ የትርጉምና
የአስተርጓሚነት ሥራዎች ራሳቸውን የቻሉ የሙያ መስኮች
መሆናቸውን በመገንዘብ መንግሥት በነዚህ መስኮች ለሚሠለጥኑ
ባለሙያዎች በየደረጃው የሥልጠና መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ
በሥራ ላይ የሚውልበትን ስልት ይቀይሳል።
2/ የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋን ጨምሮ በትርጉምና
በአስተርጓሚነት ሥራ ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሙያዎች ወደ
መደበኛ ሥራ ከመሠማራታቸው በፊት በመስኩ ሙያዊ የብቃት
ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ ይደረጋል።
3/ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ለሚሠሩ የኢትዮጵያ
የምልክት ቋንቋ፣ የትርጉምና የአስተርጓሚነት ባለሙያዎች
የሙያ መደብና ደረጃ ይወጣል።

14. የቋንቋ፤የሀገር በቀል ዕውቀትና የነገረ ወግ (ፎክሎር) ስነዳ


የኢትዮጵያ ቋንቋዎች፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ነገረ ወጎች (ፎክሎር)
እየተሰነዱ የሚጠበቁበትና ለትውልድ የሚተላለፉበት ሥርዓት ይዘረጋል።

ማስፈጸሚያ ስልቶች
1/ የቋንቋዎች፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ነገረ ወጎች (ፎክሎር)የስነዳ
ሥርዓት፣ የድርጊት መርሐ ግብርና ዕቅድ በከፍተኛ ትምህርት
ተቋማት፣ በጥናትና ምርምር ተቋማትና አግባብ ባላቸው ሌሎች

16
የመንግሥት አካላት ይነደፋል፤ ይኽን ለማስፈጸም የሚያስፈልገውን
ተቋማዊ ዓቅም መንግሥት በየደረጃው በኺደት ይፈጥራል።
2/ የግልና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እንዲኹም ሌሎች የልማት
አጋሮች፣ በቋንቋዎች፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ነገረ ወጎች (ፎክሎር)
የስነዳ ተግባራት የሚሳተፉበት ማዕቀፍና ሥርዓት ይዘጋጃል።
3/ በቋንቋዎች፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ነገረ ወጎች (ፎክሎር) ስነዳ
የተሰበሰቡ መረጃዎች ለምርምር፣ ለትምህርትና ለልማት ዕቅድ
ተደራሽ በሚሆኑበት ስልት የሚከማቹበት ማዕከል በየዕርከኑ
ይደራጃል።
4/ በመጥፋት ላይ ያሉ ቋንቋዎች የሚሰነዱበት፤ የሚጠበቁበትና
የሚያንሰራሩበት ኹኔታ ይመቻቻል፤

15. ጥንታዊ የጽሑፍ ቋንቋዎች


የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ታሪክ፣ አገር በቀል እውቀትና
ባህል ለማጥናት፣ ለመጠበቅና ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ እነዚህ
የተዘከሩባቸው ጥንታዊ የጽሑፍ ቅርሶች በሥርዓት ይመዘገባሉ፤ ይጠበቃሉ፤
ለምርምርና ለቋንቋ ልማት አገልግሎት ይውላሉ። የጽሑፍ ቅርሶቹ
የተጻፉባቸውን ቋንቋዎች ለመመርመር የሚችሉ ባለሙያዎችም
ይሠለጥናሉ።
ማስፈጸሚያ ስልትዎች
1/ የኢትዮጵያን ጥንታዊ የታሪክ፣ የአገር በቀል እውቀት፣ የባህል፣
የሃይማኖትና የሥነ ጽሑፍ ቅርስ ለመመርመር፣ ለመጠበቅና
ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚችሉ ባለሙያዎችን በብዛት
ለማፍራት ይኽ ጥንታዊ ቅርስ የተመዘገበባቸው የግዕዝ፣
የዐረብኛ እና የዕብራይስጥ ቋንቋዎች በትምህርት ሥርዓቱ
ውስጥ እንደ አማራጭ የሥልጠና መስክ የሚሰጡበት የትምህርት
መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ ይውላል።
2/ በጥንታዊ የኢትዮጵያ የጽሑፍ ቅርስ ቋንቋዎች ላይ
ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ፣
የጥናትና ምርምሩ ግኝት ለሀገር ልማት፤ ለጋራ ዕሴቶች መዳበር
እና ለሕዝቦች መቀራረብና መግባባት፣እንዲኹም ለአዳዲስ
ስያሜ ቃላት ዝግጅትና ሥርዓተ ጽሕፈት ለሌላቸው ቋንቋዎች
በፊደል ምንጭነት እንዲውል ይደረጋል።

17
ክፍል ሦስት

የፖሊሲው የአተገባበር ስልት


16. የቋንቋ ዕቀዳ እና ልማት
1/ የፌዴራል መንግሥት በፌዴራል ቋንቋነት ዕውቅና እና ሚና
የተሰጣቸው ቋንቋዎች የሚጠበቁበትን፣ የሚለሙበትን እና
የአገልግሎት አድማሳቸው ዘርፈብዙ የሚሆንበትን ሁኔታ
ለማመቻቸት ሳይንሳዊ ጥናቶችን የሚያከናውኑ፣ ጥናታዊ
ጽሑፎችንና መጻሕፍትን የሚያሳትሙ፣ የቋንቋዎቹን ዕድገትና
ልማት በዕቅድ የሚመሩ ማእከላዊ ተቋማትን ያደራጃል፤ በበጀት፣
በሰው ኃይልና በቁሳቁስ ያጠናክራል፤ ሥራቸውን ከሀገራዊ የልማት
ዕቅዶች ጋር አቀናጅቶ ይመራል፤ ይከታተላል፤ ስኬታማነታቸውን
ይገመግማል፡፡
2/ በየመስተዳድር ዕርከኑ አግባብ ያላቸው አካላት በየአካባቢያቸው
የሚነገሩ ቋንቋዎችን እና ዘዬዎችን የአጭር፣ የመካከለኛና
የረጅም ጊዜ የልማት መርሐ ግብርና ዕቅዳቸውን ከተዘጋጀው
ሀገር አቀፍ የልማት መርሐ ግብርና ዕቅድ ጋር በማቀናጀት
ያዘጋጃሉ። የሥነልሳናዊ ጥናት፣ የስነዳ፣ የቆጠራ፣ የጥበቃና
እንዲኹም በተለያየ ዘርፍ ለአገልግሎት ለማዋል የሰዋስው፣
የሥርዓተ ጽሕፈት፣ የመዝገበ ቃላት ዝግጅት የመሰሳሉትን
የቋንቋ ልማት ሥራዎች ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ያከናወናሉ።
3/ በየደረጃው ያለ የመስተዳድር አካል የተጀመረን የቋንቋ ልማት
ሥራ ሙያዊ ድጋፍ በመስጠትና ቅድሚያ ሰጥቶ ከፍጻሜ
በማድረስ ተመሳሳይ የሕብረተሰቡን ጥረቶችና አስተዋጽኦዎች
ያበረታታል።
4/ የየቋንቋውን ተናጋሪዎች አሰፋፈር መሠረት ያደረጉ የቋንቋ
ስታቲስቲክስ እና ካርታዎች አግባብ ባላቸው ባለሙያዎችና
ተቋማት አማካይነት እንዲዘጋጁ ይደረጋል። በየጊዜውም
18
በወቅታዊ መረጃዎች እየዳበሩ ቋንቋን ጨምሮ ለሁለገብ
ልማትና ለምርምር ሥራ ግብአት እንዲሆኑ ይሰራጫሉ።
5/ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን የልማት መርሐ ግብርና ዕቅድ መሠረት
በማድረግ ለዘመናዊ አገልግሎት እንዲበቁ የተስማሚ ቴክኖሎጂ
ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት ይዘረጋል።
6/ ሀገርኛ ቋንቋዎች የጥበባት መገለጫ ሆነው በሥነጽሑፍ፣
በሙዚቃ፣ በትያትር፣ በሲኒማና ተዛማጅ የጥበብ ዘርፎች
እንዲበለጽጉ የቋንቋ ልማት ዕቅዶች የነዚህን ዘርፎች እድገትም
ታሳቢ ያደርጋሉ።በሀገርኛ ቋንቋ የላቀ አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ
ደራሲያንና ሌሎች ተዛማጅ የጥበብ ባለሙያዎች የማበረታቻ
ስልቶች ይቀየሳል።እንዲኹም በየቋንቋው የንባብ ባህል
እንዲጎለብት፣ መጻሕፍት በብዛት እንዲታተሙና ለአንባቢያን
ተደራሽ እንዲሆኑ የሕዝቡን የመግዛት ዓቅም ያገናዘበ የሕትመት
ማስፈጸሚያ ስልትና የመጻሕፍት ፖሊሲ የመሳሰሉ የድጋፍ
መስጫ ስልቶች እንዲቀየሱ ይደረጋል።
7/ የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ ሀገራዊ የልማት መርሐ ግብርና
ዕቅድ ተዘጋጅቶለት በባለሙያዎች የሚጠናበት፣ የሚዳብርበትና
የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚሆንበት ስልት ይቀየሳል።
8/ በየትኛውም የምርምር ተቋምና መንግሥታዊ አካል የሚደረግ
የቋንቋ፣ የነገረ ወግ (ፎክሎር) እና የሀገር በቀል ዕውቀት ስነዳና
ጥናት በተቻለ መጠን በየደረጃው ለተዘጋጀ የልማት መርሐ
ግብር ስኬት፣እንዲኹም ለፖሊሲ ውሳኔ አሰጣጥና አፈጻጸም
ተጨባጭ አስተዋጽኦ በሚኖረው መልክ እንዲታቀድና ወደ
ተግባር እንዲተረጎም ይደረጋል።
9/ የክልል ምክር ቤት በተዋረድ ለሚገኝ የአስተዳደር ዕርከን
የሚያገለግል የሥራ ቋንቋን፤ ለቋንቋው የሚያገልግል ሥርዓተ
ጽሕፈትን፣እንዲኹም በትምህርት ዘርፍ የሚያገለግሉ ቋንቋዎችን
እና የቋንቋ ልማት ዕቀዳን በሚመለከት የማፅደቅ ሥልጣኑን
በየዕርከኑ ላሉ ምክር ቤቶች ማጋራት ይችላል።ይሁን እንጂ
የክልሉ ሕገ መንግሥት በቋንቋ ረገድ የመወሰን ሥልጣን
በተዋረድ ለሚገኝ ምክር ቤት ካጎናፀፈ በዚሁ መሠረት ተፈጻሚ
ይኾናል።
10/ ለዓለም አቀፍ የጋራ መግባቢያነት የሚያስፈልጉት የውጭ
ቋንቋዎች እንደየኹኔታው እየተመረጡ በትምህርት ሥርዓቱ
እንደ አንድ ትምህርት በአማራጭነት እንዲካተቱ የፌዴራል
መንግሥት ይወስናል።
11/ በየትኛውም የመስተዳድር ዕርከን በቋንቋዎች ጉዳይ ላይ
የመወሰን ኺደት ባለድርሻዎችንና የአካባቢውን የቋንቋው ተናጋሪ
ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ አሳታፊና በሳይንሳዊ ጥናትና
አስተማማኝ መረጃ የተደገፈ እንዲሆን ይደረጋል።

19
17. የፖሊሲው አስፈጻሚ አካላት
1/ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የባህልና
ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋ ፖሊሲው ዋና አስፈጻሚ ይኾናል።
2/ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማትና የመስተዳድር ዕርከኖች
ፖሊሲውን በየደረጃው ያስፈጽማሉ።
3/ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ማህበራት፣ የሀይማኖት ተቋማት እና
ሌሎች አጋር አካላት ፖሊሲውን በየዘርፋቸው ያስፈጽማሉ።

18. የፖሊሲው አስፈጻሚ ተቋማት አደረጃጀት


1/ ይኽን ፖሊሲ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፈጸም ዋና ዋና ባለድርሻ
አካላት የተወከሉበት የቋንቋ ጉዳዮች ምክር ቤት ይቋቋማል።
2/ በቋንቋና ተዛማጅ መስኮች ምርምር ላይ የሚሰማራ የቋንቋዎች
ጥናትና ምርምር ተቋም ይቋቋማል።
3/ በሀገር አቀፍ ደረጃ በትርጉም መስክ የሀገሪቱን ፍላጎት ለማርካት
የትርጉም ተቋም ይቋቋማል።

19. ግንዛቤ ስለመፍጠር


ፖሊሲውን በሚመለከት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማዳበር ስለ ፖሊሲው
ዓላማ፣ ይዘት እና አፈጻጸም በተለያየ ደረጃና ስልት ተከታታይነት ያለው
የማስተዋወቅና የመረጃ ሥርጭት ሥራ ይከናወናል።

20. ለፖሊሲው አፈጻጸም የጊዜ ሰሌዳ ስለማዘጋጀት


ፖሊሲው በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየሆነ የሚሄድበት የድርጊት
መርሐ ግብርና የጊዜ ሰሌዳ ይዘጋጃል።

21. የቋንቋ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የሕግ ማዕቀፎች


ፖሊሲውን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች
እንዲዘጋጁ ይደረጋል።

22. ክትትልና ግምገማ


1/ ስለ ቋንቋ ፖሊሲው አፈጻጸም የክትትልና የግምገማ ሥርዓት
ይዘረጋል፤ መስፈርቶችም እንዲወጡ ይደረጋል።
2/ የፖሊሲ አፈጻጸም ሪፖርቶች በግልጽ ከተቀመጡ መስፈርቶች
እና የስኬት አመላካቾች አንጻር እንዲቀርቡ ይደረጋል።
23. የሰው ኃይልና ሥልጠና
20
ለዚህ ፖሊሲ አፈጻጸም አስፈላጊው የዓቅም ግንባታ ሥራ ይከናወናል።
24. የፋይናንስ ምንጭ
1/ የፖሊሲው ማስፈጸሚያ ፋይናንስ ከመንግሥት የሚመደብ እና
ከልዩ ልዩ ምንጮች የሚገኝ ይኾናል።
2/ ፖሊሲን ለማስፈጸም የቋንቋ ልማት ፈንድ ይቋቋማል።
26. የሌሎች ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ
ለፖሊሲው ተግባራዊነት መንግሥት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት
ይሠራል።

አባሪ
የቃላት እና ሐረጋት ፍች

በዚኽ የቋንቋ ፖሊሲ ውስጥ የተገለጹት ጽንሰ ሐሳቦች አገባብ ከዚህ በሚከተሉት
ፍችዎች መሠረት ነው።
1/ “የቋንቋ ፖሊሲ” ማለት አንድ መንግሥት ወይም ሥልጣን የተሰጠው አካል
በሚመራው ሀገር ወይም ተቋም ውስጥ የሚነገሩት ቋንቋዎች እንዴት
በጥቅም ላይ እንደሚውሉ፣ እንደሚጠበቁ፣ እና እንደሚለሙ በሕግ ወይም
በሌላ አግባብ የሚያመለክት አጠቃላይ መርሕና መመሪያ።

21
2/ “የቋንቋ መብት” ማለትአንድ ግለሰብ ወይም ብሔር፣ ብሔረሰብ
ወይምሕዝብ አፍ በፈታበት ወይም በደንብ አውቀዋለሁ በሚለው ሌላ ቋንቋ
የመጠቀም፣ የመማር፣ አገልግሎት የማግኘት፣ ቋንቋውን የመጠበቅና
የማልማት መብት።
3/ “የቋንቋ ዕቀዳ”ማለትበሀገሪቱ ወይም በክልሉ ውስጥ የሚገኙትን ቋንቋዎች
እና ዘዬዎች ማጥናት፣ መሰነድና ማልማት፤ በጥናት ውጤቱ ላይ
ተመሥርቶቋንቋዎቹ እና ዘዬዎቹ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉበትን
ስልትና ደረጃ መቀየስ።
4/ “የቋንቋ ልማት”ማለትቋንቋ ለዘመናዊ ኑሮ፣ኹለገብ እድገትና ሥልጣኔ ብቁ
መግለጫና መግባቢያ እንዲሆን፣ በመዛግብተ ቃላት፣ በሙያዊ የስያሜ ቃላት፣
በሰዋስው፣ በሥርዓተ ጽሕፈት፣ በሥነጽሑፍ፣ ወዘተ፣ እንዲበለጽግ
የማድረግ፣ እነዚህም የሚሰራጩበትን የተለያዩ ዘዴዎች የመለየት፣
የማስፈጸምና የቋንቋውን አጠቃላይ እድገት በዕቅድ የመምራት ተግባር።
5/ “የቋንቋ ስነዳ”ማለትበመጥፋት ላይ ያለን ቋንቋ በውስጡ ከያዛቸው ባህላዊ
ዕሴቶች ጋር በዘመኑ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለትውልድ እንዳለ የሚተላለፍበት
የምዝገባ ሥርዓት ነው።
6/ “የሥራ ቋንቋ”ማለትአንድ መንግሥት ወይም መስተዳድር በሚያስተዳድረው
አካባቢ ለልዩ ልዩ መንግሥታዊ ሥራ የሚመርጠውና የሚገለገልበት ቋንቋ።
7/ “የጋራ መግባቢያ ቋንቋ”ማለትየተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ የአንድ ሀገር
ወይም አካባቢ ሕዝቦች እርስ በርስ የሚግባቡበት ሰፊ ሥርጭት ያለውና
አብዛኛውን ሕዝብ ሊያግባባ የሚችል ቋንቋ።
8/ “የተናጋሪዎቹ ቁጥር አነስተኛ የሆነ ቋንቋ”ማለትበአንድ ልሳነብዙ ሀገር
ውስጥ ከሌሎች ቋንቋዎች ተናጋሪዎች ብዛት አንጻር ሲታይ ቁጥሩ አነስተኛ
የሆነ ተናጋሪዎች ያሉት ቋንቋ።
9/ “የአፍ መፍቻ ቋንቋ”ማለትአንድ ሰው መጀመሪያ የለመደውና ሐሳቡንና
ፍላጎቱን በደንብ የሚገልጽበት፤ ከሌሎች ጋር የሚግባባበት አንደበታዊ
እና/ወይም ምልክታዊ ቋንቋ።
10/ “ኹለተኛ ቋንቋ”ማለት አንድ ሰው አፍ ከፈታበት ቋንቋ ቀጥሎ የሚለምደው
ወይም የሚማረው ቋንቋ።
11/ “ሀገርኛ ቋንቋ”ማለትበአንድ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ
ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የሚነገር ቋንቋ።
12/ “ለመጥፋት አደጋ የተጋለጠ ቋንቋ”ማለት በልዩ ልዩ ምክንያት አብዛኞቹን
አፈ-ፈት ተናጋሪዎቹን እያጣ በመሄዱ ከአገልግሎት ውጪ በመሆን ላይ
ያለ ቋንቋ።
13/ “የትምህርት መስጫ ቋንቋ”ማለት በማንኛውም የትምህርት ዕርከን ላይ
የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶችን ለማስተማርያነት የሚያገለግል ቋንቋ።
22
14/ “በትምህርትነት የሚሰጥ ቋንቋ”ማለት በማንኛውም የትምህርት ዕርከን
እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ተማሪዎች የሚማሩት ቋንቋ።
15/ “የትምህርት መስጫ ቋንቋ ሽግግር”ማለትበማንኛውም የትምህርት ዕርከን
ላይ ለማስተማሪያነት የሚያገለግልን ቋንቋ በሚቀጥለው ዕርከን ላይ
ለሚሰጠው ትምህርት በሌላ የማስተማሪያ ቋንቋ የመተካት ተግባር ወይም
ኺደት።
16/ “ቋንቋና ዘዬ”ማለትዘዬ የአንድ ቋንቋ አካባቢያዊ ወይም ማኅበራዊ ገጽታ፤
ቋንቋ ደግሞ የአንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ዘዬዎች ድምር ውጤት
ወይም ውሁድ መግባቢያ።
17/ “ዘዬዎችን የማጣጣም ሥራ”ማለትሥርዓተ ጽሕፈታዊ የድምፅ አወካከልን፣
የቃላት ትርጉምን እና የአጠቃቀም ዐውድን በማመሳሰል የየዘዬዎቹን
ተናጋሪዎች ወደ ተሻለ የመግባባት ደረጃ እንዲደርሱ የማድረግ ሥራ።
18/ “የቋንቋ መደበኛነት”ማለትበአንድ ቋንቋ ልዩ ልዩ ዘዬዎች ውስጥ የሚታዩ
መጠነኛ የድምፅ፣ የምዕላድ፣ የቃላት፣ የትርጉም፣ የአወቃቀር የመሳሰሉ
ልዩነቶችን በማስማማት አንድ ወጥ የሆነ ቋንቋን ወይም ዘዬን በዋናነት
ማስተዋወቅና ማስለመድ።
19/ “ልሳነ ዋህድነት”ማለትየአንድ ግለሰብ ወይም ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም
ሕዝብ አፍ በፈታበት አንድ ቋንቋ ብቻ የመግባባት ችሎታ።
20/ “ልሳነክልኤነት”ማለትየአንድ ግለሰብ ወይም ብሔር፣ ብሔረሰብወይም
ሕዝብአፍ በፈታበት ቋንቋ እና በአንድ ሌላ ቋንቋ የመግባባት ችሎታ።
21/ “ልሳነብዙነት”ማለትየአንድ ግለሰብ ወይም ብሔር፣ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ
አፍ ከፈታበት ቋንቋ በተጨማሪ ከአንድ በላይ በሆኑ ሌሎች ቋንቋዎች
የመግባባት ችሎታ።
22/ “ሥርዓተ ጽሕፈት”ማለትአንድ የንግግር ብቻ የነበረ ቋንቋ የጽሑፍ ቋንቋ
እንዲሆን ለማድረግ ሲፈለግ የሚዘጋጅለት የምልክት (የፊደል) ገበታና
መደበኛ የአጻጻፍ ሥርዓት።
23/ “ነገረ ወግ (ፎክሎር)”ማለት አንድ ሕዝብ ካለፈው የወረሰው፣ ራሱም
የሚኖረውና ፈጥሮም የሚያስተላልፈው ወጉ፣ ልማዱ፣ ትውፊቱ፣ዕሴቱ፣
እምነቱ፣ ሥነቃሉ፣ አኳኋኑ የመሳሰሉት፤ በአጠቃላይ በሐዘን፣ በደስታና
በሥራ ወቅት የመንፈሳዊና የቁሳዊ ሕይወቱ ባህላዊ መገለጫው።
24/ “ሕዝባዊአገልግሎት”ማለትየግብርናኤክስቴንሽን፣ የፍትሕ፣ የንጹህ ውሃ፣
የጤና፣ የትምህርት፣ የመሳሰሉት አገልግሎቶች።
25/ “ሕዝባዊ መልእክት”ማለትበመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ
ተቋማት ለሕዝብ ማንቂያ እና ትምህርት እንዲሰጡ ታስበው በሚዘጋጁ
የአደባባይ ሰሌዳዎች (ቢል ቦርዶች) የሚተላለፉ መረጃዎችና እና
ሌሎችማስታወቂያዎች።
23
24

You might also like