Download as docx, pdf, or txt
Download as docx, pdf, or txt
You are on page 1of 5

ምዕራፍ ስድስት፦ ግጥም

የስነግጥም ምንነት እና ባህርያት

የግጥም ምንነት

ስነግጥም በእጅጉ ጥንታዊነት እንዳለው የሚነገርለት የኪነጥበብ ዘርፍ ነው፡፡ የሰው ልጆች ለብዙ ዘመናት ደስታ
እና ሃዘናቸውን፣ ምኞት እና ፍላጎታቸውን፣ የአኗኗር ሁኔታቸውን እና ልዩ ልዩ ገጠመኞቻቸውን በማንጎራጎር
እና በማዜም ሲገልጹበት ኖረዋል፡፡

ስነግጥም በኪነ-ጥበብ ዘመን ታሪክ ብዙ የቆየ በመሆኑ እንደየዘመኑ ፍልስፍና፣ እንደየዘመኑ ገናን የኪነጥበብ
ፈለግ፣ እንደየገጣሚውና እንደየስነ-ጽሁፍ አዋቂው አተያይና የኪነጥበብ ዝንባሌ የተለያዩ ብያኔዎች
ስለሚሰጡት ሁሉን አቀፍ የሆነ አንድ ወጥ ብያኔ ለመስጠት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ይሁን እንጂ የግጥምን
ምነነት ለመረዳት የቅርጽ እና የይዘት ባህሪያቱን በውል መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡

ስነግጥም አንድን ነገር ወይም ድርጊት አድምቆና አጉልቶ የማሳየት፣ ሀሳብን አክርሮ እና አግዝፎ የማቅረብ
ችሎታ ያለው፣ በጥቂት ምርጥ ቃላት ብዙ ነገሮችን አምቆ የሚይዝ እና በሙዚቃዊ ቃናው የስሜት ህዋሳትን
በቶሎ የሚነካ፣ ለስሜት ቅርበት ያለው ኪነጥበብ ነው፡፡

(ምንጭ፡- ዘሪሁን አስፋው (2005) የስነጽሁፍ መሰረታውያን)

የግጥም ባህርያት

ስነግጥም እንደአንድ ኪናዊ የመግባቢያ ዘዴ በተለይ ከዝርውና ከዕለት የዕለት ንግግር የሚለይባቸው በርካታ
ባህርያት አሉት፡፡ እነዚህም ተጨባጭነት፣ እምቅነት እና ቁጥብነት፣ ሙዚቃዊነት፣ ምናባዊነት እና
ተውኔታዊነት ናቸው፡፡

ሀ. ተጨባጭነት፡- ገጠመኞችን፣ ስሜቶችን፣ አተያዮችን ወይም የገጣሚው ግንዛቤ አንድ የተወሰነ


ተጨባጭ ሁኔታን ወይም ድርጊትን በማቅረብ ወይም በመሳል ይገለጣል፡፡

ለ. እምቅነት እና ቁጥብነት፡- ግጥም ቁጥብ ነው፡፡ ቁጥብነቱም እምቅ ስለሆነ ነው፡፡ ግጥም ቁጥብ ነው
ሲባል ስለአንድ ነገር ለመናገር ዝርዝር ነጥቦችን አያቀርብም፤ እነሱን አይተነትንም፤ አያብራራም ማለት ነው፡፡

ሐ. ሙዚቃዊነት፡- ግጥም ሙዚቃዊ ነው፡፡ አንዱ ሀረግ ተብሎ (ተነቦ) ከትንሽ እረፍት ወይም ቆምታ በኋላ
ተከታዩ ሲቀጥል የሚፈጠረው የአነባበብ ተከታታይነት ምት የጠበቀ ከሆነ ዜማው ሙዚቃዊ ቃናውን ጠብቆ
ይሄዳል፡፡

መ. ምናባዊነት፡- ግጥም በተጻፈው ወይም በተነገረው ቃል ኃይል አማካኝነት አንባቢ በዓይነ ህሊናው
የሚያየውን ሰዕል፣ በእዝነ ህሊናው የሚሰማውን ድምጽ የመፍጠር ሃይል አለው፡፡

(ምንጭ፡- ብርሃኑ ገበየሁ (1999) የአማርኛ ሥነግጥም)

የግጥም አይነቶች

1
በአማርኛ ግጥም ተዘውታሪነት ያላቸው የተለያዩ የምጣኔ ስልቶች አሉ፡፡ የግጥም ዓይነቶች በሀረግ ወይም
በስንኝ ከሚይዟቸው የምጣኔ ስልትና የቀለማት መጠን አኳያ በተለያዩ ክፍሎች ይመደባሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት
ከግጥም ዓይነቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

ሀ. ቡሄ በሉ ቤት፡- ቡሄ በሉ ቤት በሕረግ (ከ 1_4) ቀለሞችን የሚይዝ የስንኝ ምጣኔ ነው፡፡ ምጣኔው “ቡሄ
ቡሄ” ከሚባለው የልጆች ጭፈራ ዜማ መጠሪያውን ያገኘ ይመስላል፡፡ ሃረጎች ፈጣኖች፣ ዜማው ቁርጥ ቁርጥ
የሚል በጥድፊያ የሚከወን ስንኝ ነው፡፡

ምሳሌ፡- እዘያ ማዶ / ጭስ ይጨሳል

አጋፋሪ / ይደግሳል

ለ. ሰንጎ መገን ቤት፡- የሰንጎ መገን ምጣኔ በሕረግ 5 ቀለማት አሉት፡፡ ይህ የምጣኔ ስልት በፈጣንና እልህ፣
ኃይልና ግለት በተቀላቀሉበት ሁኔታ ይከወናል፡፡ብዙ ጊዜም የጀግንነት ሙያ ይነገርበታል፡፡

ምሳሌ፡- ውረድ እንውረድ / ተባባሉና፣

አስደበደቡት / አፋፍ ቆሙና፡፡

ሐ. የወል ቤት፡- ይህ የግጥም ዓይነት በአብዛኛው በሀረግ ስድስት ቀለማት አሉት፡፡

ምሳሌ፡- እስከ ጊዜው ድረስ / እስኪሞላ ልኩ፣

የጀግና ፈረስ ነው / የሰው ሁሉ መልኩ፡፡

የዘይቤ ምንነትና ዓይነቶች

ዘይቤ አንድን ሃሳብ ወይም ድርጊት፣ የአንድን ነገር ቅርጽ፣ የሰውን ባህሪ፣ ስሜትና መልክ አጉልቶና አድምቆ
ለአንባቢም ሆነ ለአድማጭ ምናባዊ ፍስሃ በመስጠት የሚቀርብ የአነጋገር ስልት ሲሆን በግጥምም ሆነ በዝርው
ጽሁፍ ውስጥ ሊቀርብ ይችላል፡፡

የዘይቤ ዓይነቶች

በቋንቋው ውስጥ በርካታ የዘይቤ ዓይነቶች አሉ፡፡ ዋና ዋና ከሚባሉት ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

1. ሰውኛ ዘይቤ፡- የሰውን ልዩ ልዩ ባህርያት፣ ድርጊት፣ መልክ፣ ችሎታ፣ ወዘተ. ሰው ላልሆኑ ህይወት ላላቸውና
ለሌላቸው ነገሮች በመስጠት፣ የሰውን ባህርይ በማላበስ፣ እንዲሁም አንደበታዊ በማድረግ የሚገለጽ ነው፡፡

ምሳሌ-1፡- እህል ዱር አደረ ብቻውንም ዋለ፣

ጠላት እንደሌለው ሰው እንዳልገደለ፡፡

ምሳሌ -2፡- ብዕሩ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡

2. እንቶኔ ዘይቤ፡- ከሰውኛ ዘይቤ ጋር ተቀራራቢ ሲሆን በአጠገባችንና በቅርብ የሌለን ረቂቅና ግዑዝ ነገር፣
በህይወት የሌለ፣ እንዲሁም የማይናገሩ እጽዋትና እንሰሳት በቅርብ እንዳሉና መልስ እንደሚሰጡ በመቁጠር
2
የሚመሰረት የዘይቤ ዓይነት ነው፡፡ ይህ ዘይቤ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች በመማፀን፣ በመለመን፣ በማመስገን፣
በመመረቅ ወይም በመርገም፣ በመጠየቅ፣ በማዋየትና መልስ እንደሚሰጡ በመቁጠር የሚፈጠር ዘይቤ ሲሆን፣
በሁለተኛ መደብ (አንተ፣ አንቺ፣ እናንተ) ተውላጠ ስም ይቀርባል፡፡

ምሳሌ 1፡- አዕዋፍ በጠዋቱ ተነሳ እምትሉኝ ለምን ይሆን ከቶ፣

ባማረ ድምጻችሁ መስኮቴ ተንኳኩቶ፡፡

በሉ እኔስ ተነሳሁ ነቃሁኝ ታግየ፣

አዎ! በእርግጥ ነግቷል የሰው እግር ታየ፡፡

ግን ልጠይቃችሁ አዕዋፍ በያይነቱ፣

ነጋ ጠባ ባዮች ሰርክ በየጠዋቱ፡፡

ያነጋችሁት ቀን ባማረ ዜማችሁ፣

ለማን እንደጠባ ግን ታውቁታላችሁ?

ምሳሌ 2፡- አጫውተኝ እንጂ ተራራው፡፡

3. ተለዋጭ ዘይቤ፡- በነገሮች መካከል የባህሪ ምስስል በመፍጠር የአንዱን ባህሪና መልክ ለሌላው በመስጠት
የሚፈጠር የዘይቤ ዓይነት ነው፡፡ ይህ ዘይቤ አንድ ቃል ወይም ሀረግ የአንድን ሰው፣ እንስሳ፣ ተክል ወይም ግዑዝ
አካል ባህርይ፣ መልክ፣ ቅርጽ ወይም ድርጊት ወስዶ ለሌላ በመስጠት ተገላጩን የበለጠ እንዲጎላና ምስል
እንዲፈጥር የሚያደርግ ነው፤ የማነፃፀሪያ ቃላትም በግልፅ አይታዩበትም እንጂ የማነጻጸር ባህሪም አለበት፡፡

ምሳሌ-1፡- ጓደኛዬ ሲበላ አህያ ነው፡፡

ምሳሌ-2፡- ገንዘብ ሰርገኛ ነው ሰው ሲያቀርብ ሰብስቦ፣

ድህነት ግን ሲያርቅ ይመስላል ተስቦ፡፡

4. አነጻጻሪ ዘይቤ፡- ሁለት ነገሮች፣ ባህሪዎች፣ ድርጊቶችና ሃሳቦች በሚመሳሰሉባቸው ገጽታዎችና የጋራ
ባህርያት እየተነጻጸሩ የሚቀርቡበት የአገላለጽ ስልት ነው፡፡ ይህ የዘይቤ ዓይነት እንደ፣ ያህል፣ ይመስል፣
ወዘተ.የማነጻጸሪያ ቃላትን ይጠቀማል፡፡

ምሳሌ-1፡- ሽማግሌው ሰካራም ይመስል ይወላገዳሉ፡፡

ምሳሌ-2፡- ብቸኝነት ጥምቡሳሱ፣

የፍርሀት ግሳንግሱ፡፡

እንዳልተገራ ፈረስ ሲያደባየኝ፣

እንደ ደራሽ ውሃ ሲያፍነኝ፡፡

እንደተጋለጠ ሐሜት ሲሰብረኝ፣

3
አለ! በርታ ጠና በል የሚለኝ፡፡

5. ግነት ዘይቤ፡- ነገሮችንና ሁኔታዎችን ካላቸው ነባራዊ ሁኔታ በላይ ሆን ብሎ በማግዘፍና በማግነን የማቅረብ
ሁኔታ ነው፡፡

ምሳሌ 1፡- አልማዝ ያስነጠፈች

ወርቅ ያስጎዘጎዘች

በቫነር በዲዩር ሽቱ የታጠበች

በጌጥ ተብረቅርቃ

ጌጥ ሆና ጌጥ ይዛ

ጨረቃ ታፍራለች

ፀሀይ ትጠፋለች

ፀዳል፣ ብርሃን፣ ንጋት ሁሉን ታስንቃለች፡፡

ምሳሌ 2፡- ቤቱ ፈረስ ያስጋልባል፡፡

የቅስቀሳና የማነቃቂያ ንግግር

የቅስቀሳ ንግግር፡- አጠቃላይ ዓላማ ሰዎች አንድን ነገር እንዲያደርጉ በመገፋፋት ላይ ያተኮረ ነው፡፡
በሂደቱም ተናጋሪው ከአድማጩ የተወሰነ ወይም የሚታይ ተግባራዊ ምላሽ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል፡፡
ለዚህም ተናጋሪው አድማጩን የማነሳሳት ወይም የማሳመን ስልት ሊጠቀም ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜም
ተግባራዊ ምላሽ ሳይፈልግ ለማነሳሳት ወይም ለማሳመን ብቻ ንግግሩ ሊከናወን ይችላል፡፡

የማነቃቂያ ንግግር፡- ስሜት መኮርኮርን፣ ማጓጓትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ባብዛኛው የአድማጭን እምነት
ማጠናከር እንጅ እምነቱን እንዲለውጥ የማድረግ ሙከራ አይታይበትም፡፡ የማነቃቂያ ንግግር በአስደናቂ
አባባሎች፣ በስዕላዊ እና ስሜት ኮርኳሪ በሆኑ አገላለጾች የተሞላ ነው፡፡

የቅስቀሳ እና የማነቃቂያ ንግግር በፖለቲካና በእምነት ተቋማት፣ በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች፣


በግለሰቦች፣ ወዘተ. ሊደረግ ይችላል፡፡

የቅስቀሳም ሆነ የማነቃቂያ ንግግር ሲቀርብ የንግግሩ ትኩረት በቀጥታ በሚነሳው ጉዳይ ላይ ሰዎችን
መቀስቀስና ማነቃቃት በመሆኑ የሰዎችን ስሜት በሚነካ፣ በቀላሉ ሊረሳ በማይችል፣ በተዋበና በተመረጠ
አጭር የቋንቋ አጠቃቀም መቅረብ ይኖርበታል፡፡

(መንግስቱ ታደሰ ሞላ (2012) ሜጋ የአማርኛ ሰዋስው አጋዥ መጽሐፍ)

ቅጥያዎች

4
በቃል ላይ ተለጥፈው ወይም ተቀጥለው የሚገኙ ጥገኛ ምዕላዶች ቅጥያዎች ተብለው ይጠራሉ፡፡ ለምሳሌ “ከቤታችሁ”
በሚለው ቃል ላይ “ከ-“ እና “-ኣችሁ” የሚሉት ጥገኛ ምዕላዶች “ቤት” በሚለው ቃል ላይ ተቀጥለው የሚገኙ
ቅጥያዎች

(ጥገኛ ምዕላዶች) ናቸው፡፡

ቅጥያዎች ከሚቀጠሉበት ቦታ አኳያ የሚከተሉትን ስያሜዎች ይዘው ይገኛሉ፡፡ እነሱም፡-

ሀ. ቅድመ ዐምድ ቅጥያ፡- ከሚቀጠልበት ቃል መነሻ (መጀመሪያ) ላይ ታክሎ የሚገኝ ቅጥያ ነው፡፡

ምሳሌ፡- “ከታች” ---> “ከ-“ “ታች” በሚለው ቃል መጀመሪያ ላይ በመቀጠሉ ቅድመ ዐምድ ቅጥያ ተብሎ ይጠራል፡፡

ለ. ውስጠ ዐምድ ቅጥያ፡- በሚቀጠልበት ቃል መካከል (ውስጥ) ላይየሚገኝ ቅጥያ ነው፡፡

ምሳሌ፡- “ሰፋፊ” ---> “-ፋ-“ “ሰፊ” በሚለው ቃል መካከል ላይ በመቀጠሉ ውስጠ ዐምድ ቅጥያ ተብሎ ይጠራል፡፡

ሐ. ድህረ ዐምድ ቅጥያ፡- ከሚቀጠልበት ቃል መድረሻ (መጨረሻ) ላይ ተቀጥሎ የሚገኝ ቅጥያ ነው፡፡

ምሳሌ፡-“ቤታቸው” ---> “-ኣቸው“ “ቤት” በሚለው ቃል መድረሻ ላይ በመቀጠሉ ድህረ ዐምድ ቅጥያ ትብሎ
ይጠራል፡፡

ከላይ በቀረቡት ምሳሌዎች ላይ “ታች”፣ “ሰፊ” እና “ቤት” የሚሉት በየተራ “ከ-“፣ “-ፋ-” እና “-ኣቸው” የሚሉትን
ቅጥያዎች ያስከተሉ በመሆናቸው ምክንያት“ዐምድ” ተብለው ይጠራሉ፡፡

(ምንጭ፡- ጌታሁን አማረ (1989) የአማርኛ ሰዋስው በቀላል አቀራረብ ከሚለው ላይ ለማስተማሪያነት ተሻሽሎ
የተወሰደ

You might also like