MA Ge, Ez Article, The Problem of Gudit Seminar 1, Session 1, Mesfin Tekeste.

You might also like

Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 16

Article Review (የመጣጥፍ ዳሰሳ)

THE PROBLEM OF GUDIT


(የጉዲት ችግር/ጥፋት)

 Academic Year: - 2015/2022/23


 Program: - Regular Ge’ez M.Th. Degree 1th year 1st semester
 Faculty: - Ethiopian Church Studies
 Department: - Ge’ez Language
 Course Title: - Ge’ez seminar I, session 1
 Course Teachers: - Dr. Andualem, Mr, Abenet, Mr, Beniyam

 Formulate’s Name: - Mesfin Tekeste


 Id. No: - MGL-031/15
 Place: - Addis Ababa Region / Arat Kilo
፳፻፲፭ ዓ.ም፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፡፡
THE PROBLEM OF GUDIT

መክሥተ አርእስት

፩) መግቢያ (Introduction) ..................................................................................................................... 2


፩.፩) የመጣጥፉ አጠቃላይ ዳራ (Overview) .......................................................................................... 2
፩.፩.፩) የመጣጥፉ አዘጋጅ ማንነት (የመጣጥፉ ጸሓፊ ማን ነው?) .......................................................... 2
፩.፩.፪) መጣጥፉ መቼና የት ተዘጋጀ? (ጊዜውና ቦታው)፡- .................................................................. 4
፩.፩.፬) መጣጥፉ የተጻፈበት ምክንያት፡- .............................................................................................. 4
፩.፩.፭) የመጣጥፉ ዓላማ፡- ................................................................................................................. 5
፪) ዋና ሐሳብ (Main Body) .................................................................................................................... 7
፪.፩) የመጣጥፉ ይዘት: - .................................................................................................................... 7
፪.፩.፩) አጠቃላይ ይዘት፤ ................................................................................................................... 7
፪.፩.፪) ዝርዝር ይዘት፤........................................................................................................................ 7
፪.፪) በመጣጥፉ ውስጥ በተጠቀሰው ግእዝ ብራና ላይ ትኩረት የሚያሻቸው ዐውደ ገጸ ንባባትና ሐሳቦች:
- ....................................................................................................................................................... 8
፪.፫) የመጣጥፉ ጠቀሜታ፡-.................................................................................................................. 14
፫ ማጠቃለያ፡-......................................................................................................................................... 14
ስምዐት (ዋቢ መጻሕፍት) ......................................................................................................................... 14

ገጽ| 1
THE PROBLEM OF GUDIT

፩) መግቢያ (Introduction)

፩.፩) የመጣጥፉ1 አጠቃላይ ዳራ (Overview)


 የመጣጥፉ ርእስ፡- The Problem of Gudit (የጉዲት ችግር/ጥፋት)
 የመጣጥፉ አዘጋጅ (ጸሓፊ)፡- ፕ/ሮ ስርግው ሐብለ ሥላሴ
 የመጣጥፉ መገኛና አሳታሚ (Periodical)፡- Journal of Ethiopian Studies, Vol. 10,
No. 1 (JANUARY 1972), pp. 113-124, Institute of Ethiopian Studies

 መጣጥፉ የተጻፈበት ቋንቋ፡- እንግሊዝኛ


 የመጣጥፉ ተተኳሪ ቦታና ዐይነት፡- ኢትዮጵያ፤ ታሪክና ፍለጋ (History and Exploration)
 መጣጥፉ የሚገኝበት ድኅረ ገጽ ማስፈንጠሪያ (External link of The Article) ፡-
 Stable URL: http://www.jstor.org/stable/41965849 Accessed: 03-08-2016 17:01 UTC

፩.፩.፩) የመጣጥፉ አዘጋጅ ማንነት (የመጣጥፉ ጸሓፊ ማን ነው?)


መጣጥፉን ከመዳሰስ በፊት የመጣጥፉን አዘጋጅ (ጸሓፊ) ማንነት ማወቅ ተገቢ ነውና በዐጭሩ የመጣጥፉን
ጸሓፊ ማንነት መናገር ያስፈልጋል፤ ይኽ መጣጥፍ የዶ/ር ስርግው ሐብለ ሥላሴ ነው፡፡
ዶ/ር ስርግው በኢትዮጵያ ከነበሩ ግንባር ቀደም አንጋፋ ኢትዮጵያውያን የሥነ መለኮት፡ የታሪክና ሥነ ድርሳናት
ጥናት ት/ት ባለሞያዎች መኻከል አንዱ ናቸው፡፡ ዶ/ር ስርግው ሐብለ ሥላሴ ሠኔ 8 ቀን 1921 ዓ.ም በዐዲስ
አበባ ከተማ ተወለዱ፡፡ እድሜአቸውም ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ዐዲስ አበባ በሚገኘው የማኅደረ ስብሓት ቅድስት
ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኀኒት መድኀኔዓለም አብያተ ክርስቲያን የንባብ ትምህርትን ከፊደል ቈጠራ ዠምሮ
ሙሉ የንባብ ትምህርትን ተምረዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ዘመናዊ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ቅድስት ሥላሴ
ት/ቤት አጠናቀቁ፡፡ በጊዜው ተመርጠው ከቀረቡት የኢትዮጵያ ተማሪዎች አንዱ ኹነው ግሪክ አገር ቆሮንቶስ
ከተማ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እዚያ ከሚገኘው መንፈሳዊ ትምህርት ቤት 1941 ዓ.ም
ተላኩ፡፡ ትምህርቱን አጠናቅቀው እዚያው ግሪክ አገር ባለው አቴና ዩኒቨርስቲ ገብተው ከአራት ዓመት በኋላ
የባችለር ዲግሪያቸውን በቲዎሎጂ ጥናት ተቀበሉ፡፡ ከፍተኛ ትምህርታቸውን በመቀጠል ከ1950 እስከ 1952
ዓ.ም ድረስ በጀርመን አገር በሚገኘው ቦን ዩኒቨርስቲ በጥንታዊ ታሪክ ምርምር የዶክትሬታቸውን ማዕረግ
ተቀበሉ፡፡ ከዚያም በኋላ አገራቸውን ለማገልገል ወደ ዐዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ ከዚኸ ጊዜ ጀምሮ እስከ 1970
ዓ.ም ድረስ ለ17 ዓመታት በጊዜው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ (የዛሬው ዐ/አ/ዩ) የጥንታዊና መኻከለኛ
ዘመን ሥልጣኔና ታሪክ የመዠመሪያ ምሁር ኹነው ሠርተዋል፡፡ በተጨማሪም ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ
የቲዎሎጂ አስተማሪ በመኾን አገልግለዋል፡፡

1 ይኽን Article የሚዳስሰው ተማሪ ‹መጣጥፍ› ሲል ‹Article› የሚለውን አቻ ቃል ተጠቅሞ እንደኾነ ልብ ይሏል፡፡
ስለዚኽ ‹Article Review - የመጣጥፍ ዳሰሳ› ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ገጽ| 2
THE PROBLEM OF GUDIT

አገልግሎታቸውን በመምህርነት ብቻ ሳይወስኑ ተመራማሪነታቸውንም አጣምሮ በተመለከተ እንደ London


University፤ በአሜሪካንም አገር እንደ Harvard University እና Princeton Univeristy፤ በጀርመን አገር
Heidlberg University፤ እንዲኹም በሆላንድ Lieden University በመሳሰሉት በዓለም በታወቁ
ዩኒቨርስቲዎች በፌሎሽፕ እየተመረጡ በተለያየ ጊዜያት በከፍተኛ ደረጃ ልዩ ልዩ ጥናቶችንና ምርምሮችን
አከናውነዋል፡፡ ዶ/ር ስርግው በትምህርት ዓለም ካሳለፏቸው ዘመናት ሰፊውን ጊዜ በመምህርነትና በምርምር
እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ሠርተዋል፤ በዚኽም መሠረት ለተማሪዎችና ለተመራማሪዎች እጅግ ጠቃሚ
ኹነው የሚገኙ መጻሕፍትንና ሥነ ጽሑፋትን አዘጋጅተዋል፡፡

ከሥራዎቻቸውና ዝግጀቶታቸው ውስጥ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያኽል፦ በእንግሊዘኛ ቋንቋ 1961 ዓ.ም
የታተመው ‹Bibliography of Ancient and Medieval Ethiopian History› 1963 ዓ.ም
የታተመው ‹Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270› የተባሉት ይገኙበታል፡፡ እኒኽ ኹለት
መጻሕፍት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙ ዕውቅ በሚባሉ ዩኒቨርስቲዎችና አብያተ
መጻሕፍት ቀርበው የኢትዮጵያን ታሪክ ለሚያጠኑ ኹሉ እንደዋና የምርምር ሰነድ (Reference
document) ኹነው እስከ ዛሬ ድረስ ይገኛሉ፤ እነዚኽም መጻሕፍት ከታተሙ በኋላ ዶ/ር ስርግው
የፕሮፌሰርነት ማዕረግን ለማግኘት በቅተዋል፡፡ ዶ/ር ስርግው በዐማርኛ ቋንቋ ለመዠመሪያ ጊዜ የቀረበውን በ14
ቅጽ የተተነተነውን ሰፊ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክንን መዝገበ ቃላት በአቀናባሪነት ያዘጋጁ ናቸው፤ ይኽም ሥነ ጽሑፍ
እስከ ዛሬ ድረስ ለቤተ ክህነት ሊቃውንት ተማሪዎችና ተመራማሪዎች እንዲኹም ለታሪክ አጥኒዎች ትልቅ
አገልግሎትን በማበርከት ላይ ይገኛል፤ ከላይ ከተጠቀሱትም መጻሕፍት በተጨማሪ የኢትዮጵያን ጥንታዊ የሥነ
ጽሑፍ አቀራረጽንና የመጻሕፍት አጠራረዝን የሚገልጽ ‹Book making in Ethiopia› የተባለ መጽሐፍ
አዘጋጅተው አቅርበዋል፤ በመጨረሻም በ1992 ዓ.ም የዐፄ ምኒሊክን የሕይወት ታሪክ በተለይ የኢትዮጵያ ንጉሠ
ነገሥት ዐፄ ምኒልክ ከውጪው ዓለም ጋራ ኢትዮጵያን እንዴት እንዳገናኟት የሚያብራራ ብዙ ኢትዮጵያውያን
ምሁራን ያደነቁትን ዝግጅት አበርክተዋል፤ ከነዚኽ መጻሕፍት በተጨማሪ ይኽን መጣጥፍ ጨምሮ ከኻያ
የሚበልጡ የኢትዮጵያንና የቤተ ክርስቲያንን ጥንታዊ ታሪክ የሚመለከቱ ልዩ ልዩ ሰፊ የምርምር መጣጥፎችንና
ጥናቶችን በበርካታ የዓለም ቋንቋዎች አዘጋጅተው አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪ ዶ/ር ስርግው ለአገራቸው
ካበረከቷቸው ዋና ሥራዎች አንዱ ኹኖ የሚቈጠረውና ታሪክ የማይዘነጋው የኢትዮጵያ ብራና መጻሕፍት ድርጅት
መሥራች ኹነው ያገለገሉበት ጊዜ ነበር፤ የዚኽ ድርጅት የመዠመሪያ ሥራ አስኪያጅም ኹነው ከ1966 እስክ
1971 ዓ.ም በተለያዩ ገዳማትና አድባራት በመዘዋወር በብዙ መቶ የሚቈጠሩ የጥንት ብራና መጻሕፍት
በማይክሮፊልም ተቀርፀው ለታሪክና ለምርምር ለሚቀጥሉት ትውልድ እንዲቆዩ ያደረጉ ታላቅ የኢትዮጵያ
ባለውለታና ምሁር ናቸው፡፡

ዶ/ር ስርግው ባለትዳርና የዐምስት ልጆች አባት የነበሩ ሲኾን፤ የልጅ ልጆችንም ለማየት ችለዋል፤ ዶ/ር ስርግው
ታኅሣሥ 29 ቀን 1995 ዓ.ም ይኽን ኹሉ ድንቅ ብሔራዊና ሃይማኖታዊ አገልግሎት ፈጽመው በጀርመን ሚዩኒክ
ከተማ ከዚኽ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ስለ አዘጋጁ ይኽን ያኽል ከተነሣ በቂ ነው፤ ወደ ቀጣዩ ሐሳብ እናምራ፡፡

ገጽ| 3
THE PROBLEM OF GUDIT

፩.፩.፪) መጣጥፉ መቼና የት ተዘጋጀ? (ጊዜውና ቦታው)፡-


መጣጥፉ በእርሳቸው እጅ የተጻፈበትን ትክክለኛና ግልጽ ጊዜ ማወቅ ባይቻልም በ Journal of
Ethiopian Studies ላይ የቀረበበትንና የወጣበትን ጊዜ ማግኘትና ማወቅ ይቻላል፤ ይኽም እ.ኤ.አ

JANUARY 1972 ዓ.ም ነው፡፡ መጣጥፉንም በጆርናል ያሳተመውና ያወጣው Institute of Ethiopian

Studies ነው፡፡ እንዲኹም በተጨማሪ መጣጥፉ ከራሳቸው ‹Ancient and Medieval Ethiopian
History to 1270› ከተባለውና 1972 ዓ.ም ከታተመው ዳጎስ ካለ የታሪክ መጽሐፍ ሥራቸው ውስጥ ከገጽ
225 – 237 ያለው ርእሰ ጉዳይ ነው በጆርናሉ ላይ የታተመው፡፡

፩.፩.፫) መጣጥፉ የተጻፈበት ቋንቋ፡-


ከአርእስቱ ዠምሮ የመጣጥፉ ጸሓፊ የተጠቀሙት ቋንቋ እንግሊዝኛ ሲኾን ለመጣጥፉ ዋና ግብአት
የኾነውን ያልታተመ የግእዝ ብራና ጽሑፍ ቅጂ ደግሞ ያቀረበው በግእዝ ቋንቋ እንዳለ ያለምን የቃል
ጭመራና ቅነሳ ሳይኖር ነው፡፡ ይኽ ሲባል ግን በግርጌ ማስታወሻ ጥቂት የማይባሉ ርማቶችንና ማስታወሻ
ሐሳቦችንም አካትተዋል፡፡ በተጨማሪም በግእዝ ያለውን የብራናውን ጽሑፍ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ
ተርጕመው አቅርበዋል፡፡ የአተረጓጐም ኺደቱ ላይም በግእዙ ብራና ቅጂ ላይ ያሉትን መታረም
ያለባቸውን ስሕተተ ጽሕፈትና ሰዋስው ዐርመው፡ መቃናት ያለባቸው ዐውዳዊ ሐሳቦች አቃንተው
ከመደበኛ ምንጩ ሳይርቅ ነው የተረጐሙት፡፡

፩.፩.፬) መጣጥፉ የተጻፈበት ምክንያት፡-


የመጣጥፉ አዘጋጅ ጥናታዊ መጣጥፉን የጻፈበትን ምክንያት በግልጽ በመጣጥፉ ባያስቀምጥም በዋና
የታሪክ መጽሐፍ ዝግጅት ክፍል ውስጥ የተካተተ ርእሰ ሐሳብ በመኾኑ ምክንያተ ጽሕፈታቸውም በዚያ
አንጻር የሚታሰብ ነው፤ ግና እንደ መንደርደሪያ አመክንዮ በዮዲት ጉዲት ታሪክ ላይ ያለውን ውስጣዊ
የጽሑፍ መረጃ ግብአት ዕጥረትና ቃላዊ ትርክቱን ከግምት በማስገባት የብራናው ቅጂ ላይ የተገኘው
መረጃ የሚሰጠውን ተጨማሪ መረጃ በማስተሣሠር ምክንያታቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡2 (Sergew
Hable Selassie (Dr), 1972, pp. 113.) ስለዚኽ አጥኒው ይኽን የመረጃ ትርክት ክፍተት ለመሙላት

ያገኙትን የግእዝ ብራና ጽሑፍ ቅጂ ለዘለቄታው እንደ ዋና ተቀዳሚ ምንጭ ማጣቀሻ አድርገው በማሰብ
ለመጽሐፋቸው ሲጠቀሙት ለጊዜው ደግሞ ለመጣጥፉ ዝግጅት ቀጥታ ለክፍት ምርምር እንዲውል
ደግመው ያዘጋጁት ይመስላል፡፡

2 Sergew Hable Selassie (Dr), 1972, The Problem of Gudit, Journal of Ethiopian Studies, Vol. 10,
No. 1, pp. 113-124,

ገጽ| 4
THE PROBLEM OF GUDIT

ለዚኽ ጥሩ ማሳያ የሚኾነው ስለዮዲት ጉዲት የሚነሡትን አፈ ታሪኮችና ተዛማጅ ታሪኳ የሚገኝባቸውን
የታሪክ መጻሕፍትን ከዜና መዋዕሉ ጋራ መርምረውና አሰናስለው መጥቀሳቸው ነው፡፡ ሌላው ከዚኽው
ጋራ በተያያዘ አዘጋጁ ያገኙትን ብራና ጽሑፍ ስለ ዮዲት ጉዲት ታሪክ ተጨማሪ ግብአት የሚኾን
መረጃ እንዳለው በመገንዘብ ከጥቂት የግል ተውሳከ ጽብረቃ ዕሳቤ (Personal perspective - ግላዊ
ርእይ/ምልከታ) ጋራ በማጐዳኝት በግእዝና በእንግሊዝኛ ለአጥኒዎችና ተመራማሪዎች እንዲኹም ለግእዝ

ቋንቋና ታሪክ ተማሪዎች ለክፍት ንባብና ጥናት ይረዳ ዘንድ መጣጥፉን ያዘጋጁት ይመስላል፡፡

፩.፩.፭) የመጣጥፉ ዓላማ፡-

የመጣጥፉ ዋና ዓላማ በተገኘው የግእዝ ብራና ዜና መዋዕል ቅጂ ስለ ዮዲት ጉዲት ማንነትና ተግባር
ከአፈ ታሪክ ትርክት ሐሳብ ጋራ ያለውን አንድነትና ልዩነት በተጨማሪ ማብራሪያ (Annotation)
በማጠንከር በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተርጕሞ ማሳየት ነው፤ አዘገጃጀቱም የተማረውንና ተመራማሪውን
ማኅበረሰብእ ታሳቢ ያደረገ ይመስላል፡፡

፩.፩.፮) የመጣጥፉ መረጃ ምንጭ፡-

ይኽ መጣጥፍ ርቱዕ/ቀጥተኛ/ ቀዳማይ (Primary Source) እና ኢ-ርቱዕ/ቀጥተኛ ያልኾነ/ ካልኣይ


(Secondary Source) የመረጃ ምንጮችን በመጠቀም የተዘጋጀ ጥናታዊ መጣጥፍ ነው፤ መጣጥፉ
በዋነኝነት የዮዲት ጉዲትን ታሪክ ጉዳዩ ስላደረገ አጥኒው በመሠረታዊ ዳሰሳ ያልታተሙ የግእዝ ብራና
መጻሕፍትን በርቱዕ ምንጭነት እንዲፈትሽ አስችሎታል፡፡ (Sergew Hable Selassie (Dr), 1972,
pp. 113.) እንዲኹም በእርሷ (ዮዲት) ታሪክ ዙሪያ የተጻፉ መጻሕፍትንና ጥናታዊ ሥራዎችን
ተመልክቷል፤ ሌላው ደግሞ የቃል ትውፊታዊ ትርክት (oral tradition) በመረጃ ምንጭነት
አገልግሏል፡፡ በዚኽ መሠረትም በቀዳማዊ ምንጭነት ለጥናቱ ዋቢ የኾኑ ዋና የግእዝ ብራና ቅጂዎች፡-

- ዜና መዋዕል ዘኢትዮጵያ - Chronicle of Ethiopia, an unpublished Ms. pp. 44-45;


- ገድለ አብርሀ ወአጽብሐ - Gädlä Abreha and Asbeha,
- C. Conti Rossini, compiled various traditions from a number of works and
published them under the title: "La caduta della dinastia Zague e la versione
amarica del Be 'eia Nägäst": Rendi- conti della Accademia dei Lincei, (1922), XXXI

ገጽ| 5
THE PROBLEM OF GUDIT

በተለይ ዶ/ር ስርግው የተጠቀሙት ብራና ‹ዜና መዋዕል ዘኢትዮጵያ፤ ገድለ አብርሀ ወአጽብሐ›
የተባሉት ያልታተሙ ብራና ሰነድን (an unpublished Ms) ነው፡፡3

በካልኣይ ምንጭነት ደግሞ አስፈላጊ ግብአት እንዲኾን በዛ ያሉ የተለያዩ በኢትዮጵያ ታሪክ ዐውድ ላይ
የተዘጋጁ ከዐሥርና ዐሥራ ዐምስት በላይ መጻሕፍትና ጥናታዊ የምርምር ሥራዎችን መጣጥፉን
የሚያበለጽጉ ሥራዎች እንዲኾኑ ወስደዋቸዋል፡፡ ለምሳሌ ያኽል ከእነዚኽ መኻከል፡-

- E. Littmann, Deutsche Aksum - Expedition (Berlin, 1913), IV,


- Sergew Hable Selasie, "Church and State in the Aksumite Period"; Proceedings of
the Third International Conference of Ethiopian Studies (Addis Abäba, 1969), I. 5
- R. Basset, Histoire de la conquête de VAbyssinie (Paris, 1897), Märed Wäldä
Arägay, Southern Ethiopia and the Christian Highlands 1508-1708, with Special
Reference to the Galla Migrations. (London University, 1971. Ph. D. dissertation),
- W. Budge, The Queen of Sheba and her Only Son Menylik (London, 1922)
- The Book of the Saints of the Ethiopian Church I
- C. Conti Rossini, Storia ď Etiopia (Bergamo, 1928,)
- J. Perruçhon, Les chroniques de Zera Ya'eqob et de Ba'eda Mariam, rois d'Ethiopie
1434-1478, (Paris, 1893) ………… ሊጠቀሱ ይችላል፡፡

እንደመግቢያ እነዚኽን አርእስተ ሐሳቦች በመጣጥፉ ላይ ከተነሣ ቀጣይ ደግሞ የመጣጥፉን ዋና ይዘትና
ቅኝት፡ ጠንካራና ደካማ ጎን፡ እንዲኹም ጠቀሜታውንና አስተዋጽዖውን በዐጭሩ ለመቃኘት
ይሞከራል፡፡

3 ዶ/ር ስርግው ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ የኾናቸውን ዜና መዋዕል ብራና ያገኙት በባለቤትነት ንብረት ከአኵስም ቄሰ ገበዝ
አባ ተክለ ሃይማኖት ከሚባሉ አባት በኩል እንደኾነና የብራናው መገኛም የኹለቱ ወንድማማቾች አብርሀና አጽብሐ ትግራይ
ግማድ ካለው ገዳማቸው እንደኾነ በመጣጥፋቸው ግርጌ ማስታወሻ (footnote) ቊጥር 2 እና 4 ላይ አመስግነው ይናገራሉ፡፡

ገጽ| 6
THE PROBLEM OF GUDIT

፪) ዋና ሐሳብ (Main Body)


፪.፩) የመጣጥፉ ይዘት: -

፪.፩.፩) አጠቃላይ ይዘት፤


ይኽ መጣጥፍ 12 (113-124)4 ገጻት ያሉት ሲኾን አጥኒው ባገኘው የግእዝ ብራና ቅጂ መሠረት የዮዲት
ጉዲትን ዜና ታሪክ ወደ እንግሊዝኛ ተርጕሞ የታሪኩን ዋና ምንጭ ቀጥታ ከራሱ ማጣቀሻ ሐሳቦች ጋራ
እያዛመደ ነው የሚያቀርበው፤ የመጣጥፉ ይዘት ዘውግም ‹Pure (orginal) Article› አጻጻፍ ዘዴን
የተከተለ ነው፡፡ ዝርዝር ይዞታውም እንደሚከተለው ነው፡፡

፪.፩.፪) ዝርዝር ይዘት፤

 ገጽ 1 (113) - በኢትዮጵያ የጨለማ ታሪክ5 የሚባለውንና በዚያ ዘመን ስለተነሣችውና ተተኳሪ


ርእሰ ጉዳይ ስለኾነችው ዮዲት ጉዲት ዐጭር ገለጻና የነበረችበትን6 ጊዜ በግርድፉ ከሦስት ግርጌ
ማስታወሻዎች ጋራ ያነሣል፤

 ከ ገጽ 2 - 3 (114 - 115) - ከግእዙ ብራና ዜና መዋዕል የተገኘውን አነስተኛ ቀዳሚ


የዮዲትን ክፍለ ዜና ታሪክ ከቃላት ማስተካከያ ግርጌ ማስታወሻ ርማት ጋራ ያቀርባል፤

 ከ ገጽ 3 - 5 (115 - 117) - ቀዳሚውን የግእዙን ብራና ዜና መዋዕል የዮዲትን ታሪክ


በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከዐሥራ ዘጠኝ ግርጌ ማስታወሻ ርማትና ተጨማሪ ሐሳቦች ጋራ ዋቢ
መጻሕፍትን በሚገባ በመጠቀም ያቀርባል፤

4 መጣጥፉ በጆርናሉ ውስጥ ያለውን ገጽ ቊጥር የሚያመለክት ነው፡፡


5 በአገራችን የታሪክ ኺደት ከአኵስም መንግሥት መዳከም ዠምሮ እስከ ዛጔ ሥርወ መንግሥት መነሣት ድረስ ያለው ጊዜ

‹የጨለማው ዘመን› በመባል ይታወቃል፤ ለስያሜው መነሻ የኾነው ዋና ምክንያት በወቅቱ ስለነበረው አጠቃላይ ታሪካዊ
ክሥተት የሚገልጽ ምንም ዐይነት መረጃ ሊገኝ ባለመቻሉ ነው፤ በዚኽ ዘመን ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን

በኹለት ዐበይት ፈተናዎች ተወጥረውና ተውጠው የተዳፈኑ እሳት ይመስሉ ነበር፤ እነዚኽም ፈተናዎች፡- ከውጪ የእስልምና
እምነት መስፋፋት፡ ከውስጥ ደግሞ የዮዲት ጉዲት መነሣትና የጥፋት ዘመቻዋ ነው፤ በእርሷም ምክንያት አብያተ

ክርስቲያናት ፈርሰዋል፡ መጻሕፍት ተቃጥለዋል፡ አባቶች ካህናት፡ የነገሥታት ልጆችና ቤተሰቦች ተገድለዋል፤ ንጹሓን
ተሰደዋል፤ ሙተዋል (ዲ/ን መንግሥቱ ጎበዜና ዲ/ን አሳምነው ካሣ፤ 2000 ዓ.ም፤ 64 – 68)፡፡

6 ዮዲት የነበረችበትና የኖረችበት ጊዜ በውል ባይታወቅም ከስምንተኛው እስከ ዘጠነኛው መ/ክ/ዘ እንደነበረች የታሪክ
መዛግብት አጥኒዎች ያስረዳሉ፤ አኵስምን ወርራና ንጉሡ አንበሳ ውድምን አባርራ በአኵስም ግዛት የነገሠችበትና
የዠመረችበት ዘመን 842 ሲኾን የገዛችውም ለ40 ዓመታት ያኽል ነው፤ በዚኽ ስሌት ከተኼደ 882 ዓ.ም ነው የሞተችው፤

ዶ/ር ስርግው ባገኙት ዜና መዋዕል ላይ እንደተዘገበው ዮዲት የሞተችበትን ዘመን 910 ዓ.ም ያደርገዋል፤ በኹለቱ ዘመናት
መኻከል የ28 ዓመታት ልዩነት ያሳያል፤ ይኼንና መሰል ተያያዥ ታሪክ ሐሳቦችን የብራናውን ቅጂ መደብ እያደረግን
ከተመለከትነው ጠንካራ ደካማ ጎኑን ለይቶ ማውጣት ይቻላል፡፡

ገጽ| 7
THE PROBLEM OF GUDIT

 ከ ገጽ 6 - 7 (118 - 119) - ሌላኛውን ከግእዙ ብራና ዜና መዋዕል የተገኘውን አነስተኛ


የዮዲትን ክፍለ ዜና ታሪክ ከቃላት ማስተካከያ ግርጌ ማስታወሻ ርማት ጋራ ያቀርባል፤

 ከ ገጽ 7 - 8 (119 - 120) - በገጽ 6 - 7 (118 - 119) የተገለጸውን የግእዙን ብራና ዜና


መዋዕል የዮዲትን ታሪክ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከአንድ ግርጌ ማስታወሻ ርማትና ተጨማሪ ሐሳብ
ጋራ ያቀርባል፤

 ከ ገጽ 8 - 9 (120 - 121) - አጥኒው የውጪ ጸሓፍትን ሥራ በማጣቀስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ


ከስድስት ግርጌ ማስታወሻ ርማትና ተጨማሪ ሐሳቦች ጋራ ዋቢ መጻሕፍትን በሚገባ በመጠቀም
ያቀርብና በገጽ 9 እና 10 (121 - 122) ያሉትን ቀሪ ከግእዙ ብራና ዜና መዋዕል የተገኘውን
የዮዲትን ክፍለ ዜና ታሪክ በግእዝና በእንግሊዝኛ ትርጕሞ ከዐሥራ አንድ ግርጌ ማስታወሻ
ርማትና ተጨማሪ ሐሳቦች ጋራ በጥሩ ኹኔታ ያቀርባል፤

 ከ ገጽ 11 - 12 (122 - 123) - አጥኒው ስለ ኢትዮጵያ አንዳድ ተያያዥ ኩነቶች በእንግሊዝኛ


ቋንቋ የውጪ ጸሓፍትን ሥራ በማጣቀስ ከሦስት ግርጌ ማስታወሻ ርማትና ተጨማሪ ሐሳብ ጋራ
ዋቢ መጻሕፍትን ተጠቅሞ ካቀረበ በኋላ መጣጥፉን ይፈጽማል፡፡

እንግዲኽ የዚኽን በገጽ አነስተኛ በውስጥ ይዘት ግን ሰፊ የኾነውን የመጣጥፉን ዝርዝር ይዘት በዚኽ
መልኩ ካየን ዘንዳ በመቀጠል አጥኒው በመጣጥፉ ውስጥ ያቀረበውን ብራና ጽሑፍ ቅጂ ታሪክና አንዳንድ
ሐሳቦቹን እንቃኛለን፡፡

፪.፪) በመጣጥፉ ውስጥ በተጠቀሰው ግእዝ ብራና ላይ ትኩረት የሚያሻቸው ዐውደ ገጸ ንባባትና ሐሳቦች: -
በግእዝ ብራናው ዜና መዋዕል ላይ ስለ ዮዲት ጉዲት ታሪክ ከተለመደው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ
መምህራን ትርክት ሐሳቦች ወጣ ያለ አንዳንድ እንግዳ ትርክት አገላለጽ ይታይበታል፤ ጉዳዩን እንደ
መረጃ ግብአት ቀጥታ ከመቀበል ይልቅ መርምሮና ፈትሾ ሌሎችንም የታሪክ ሰነዶች በሚገባ ጎን ለጎን
እያነጻጸሩ ማጥናት ያስፈልጋል፤ ሌላው በዚኽ የታሪክ ሰነድ ውስጥ ዐዳዲስ ቃላት ይታያሉ፤ እነርሱንም
እንዲኹ መመርመሩ ጥሩ ነው፤ ለሥነ ጽሑፍ እድገት ጠቀሜታቸው ላቅ ያለ ነውና፡፡ እንደ መነሻ
ዐውደ ገጸ ንባባቱን በሚከተሉት ሐሳቦች ልናየው እንችላለን፡-
 ‹ዮዲት› ከሚለው ስሟ ሌላ ተግባሯን መሠረት ስላደረጉት ሌሎች ስሞቿ ስያሜና ፍቺ፤
 ስለማንነቷ፡ ስለቤተሰቧ፡ ስለጭካኔዋ መንሥኤ ተግባር፤
የተወሰኑ ነጥቦች ማንሣት አስፈላጊ ነውና ዶ/ር ስርግው ያቀረቡትን የግእዙን ዜና መዋዕል መሠረት
አድርገን እንመለከት፡፡7

7 የዚኽ መጣጥፍ ዳሰሳ አቅራቢ ተማሪ የግእዙን ዘርዕ ወደ ዐማርኛ ለመመለስ ሞክሯል፡፡

ገጽ| 8
THE PROBLEM OF GUDIT

 ከ ገጽ 2 - 3 - ከግእዙ ብራና ዜና መዋዕል የተገኘው አነስተኛ ቀዳሚ የዮዲት ዜና ታሪክ፤


“…ወእምዝ፡ ንጽሕፍ፡ ታሪክ፡ ዘዮዲት፡፡ በልሳነ ትግራይ ትሰመይ ጉዲት፡ ወበአምሐራ፡ ትሰመይ፡ እሳቶ፡
ወበልሳነ፡ ጥልጣል፡ ትመሰይ ጋዕዋ፡፡ ዮዲት፡ ብሂል፡ ብፁዕ፤ ብፁዕ፡ ወመንክርት፡፡ አልቦ፡ ዘይትማሰላ፡
በስን፡ ወበላሕይ፡ ዘእንበለ፡ ንግሥተ፡ አዜብ፡፡ ወይእቲ፡ ወለተ፡ ወለቱ፡ ለውድማ፡ አስፈሬ፡ ንጉሥ፡ ወስመ፡

ሀገረ፡ እማ፡ ኃኃይሌ፡፡ ወበእከየ፡ ምግባራሰ፡ ዛቲ፡ ተሠምየት፡ ጉዲት፡ በእንተ፡ ዘአውዐየት፡ መቅደሰ፡ ጽዮን፡
ገበዘ፡ አክሱም፡ ዘተሐንፀ፡ በወርቅ፡ ወበብሩር፡ ወበከደዋ፡፡ ወዛቲሰ፡ ብእሲት፡ መጽአት፡ እምሀገረ፡ ሻም፡
ምስለ፡ ብእሲ፡ ዘኖቢስ፡ ወተዐየነ፡ በድኅኖ፡፡ ወለአከት፡ ሶቤሃ፡ ዮዲት፡ ኀበ፡ ሀገረ፡ እማ፡ ኃኃይሌ፡ እንዘ፡
ትብል፡ አነ፡ አእመርኩ፡ ወመጻእኩ፡ ምስለ፡ ብዙኅ፡ ሠራዊት፡፡ ንዑ፡ ኀቤየ፡ ፍጡነ፡ ለተቀብሎትየ፡
ዘኢመጽአ፡ ዮም፡ ኀቤየ፡ ኢኮነ፡ ፍቁርየ፡ ወይከውን፡ ምስለ፡ ፀርየ፡፡ ወሰሚዖሙ፡ ሰብአ፡ ኃኃይሌ፡ ወጽኡ፡

ለተቀብሎታ፡ ፍኖተ፡ አሣውርታ፡ ወይእቲኒ፡ መጽአት፡ በሹልኩ፡፡ ወእምቅድሜሁ፡ ኢነበረት፡ ፍኖት፡


በምጽዋት፡ አላ፡ ይእቲ፡ አውጽአቶ፡ ለውእቱ፡ ፍኖት፡፡ ወሰበ፡ መጽአት፡ ይዕቲ፡ እንተ፡ ኢተሐዘብዋ፡
ሰመይዋ፡ ለይእቲ፡ ፍኖት፡ ሹልኩ፡ ወአተወት፡ በዳኅና፡ ወእንዘ፡ አልቦ፡ ዘይከልአ፡ ወየኀይዳ፡ ወቦአት፡ ሀገረ፡
አክሱም፡፡ ቀዳሚ፡ አውዐየቶ፡ ለትዕይንት፡ ወለቤተ፡ ክርስቲያንሂ፡ አንሃለቶ፡ እስከ፡ መሠረቱ፡ ዘሐነፅዋ፡

ነገሥት፡ አብርሃ፡ ወአጽብሐ፡ ጻድቃን፡ በወርቅ፡ ወበብሩር፡ ወበዕንቁ፡፡ ወለሐውልትኒ፡ ዘሐነፅዋ፡ ጠቢባነ፡
ጽርዕ፡ በብዙኅ፡ ንዋይ፡ ገንጰለቶ፡ ወሠበረቶ፡ በኀፂን፡ ወለነቅዓ፡ ማይኒ፡ ደፈነቶ፡ ከመ፡ ኢይስተይዎ፡ ሰብእ፡
ዳግመ፡፡ ወለሀገርኒ፡ ረሰየቶ፡ በድወ፡ ከመ፡ ዘኢነበረ፡ ሰብእ፡፡

ወአሐተ፡ ዕለተ፡ ከመ፡ ታርኢ፡ ብዙኅ፡ ሠራዊታ፡ አዘዘቶሙ፡ ለሠራዊታ፡ ከመ፡ ይንሥኡ፡ አሐዱ፡ አሐዱ፡

ዕብነ፡ ይዕርጉ፡ ውስተ፡ ዓቢይ፡ ደብር፡ ዘስሙ፡ ጉቦድራ፡ ወይግድፍዋ፡፡ ወኮነ፡ ዓቢየ፡ ደብረ፡፡ ውእቱ፡

ዕብን፡ ዘተዓለደ፡ ሀሎ፡ እስከ፡ ይእዜ፡፡ ወእምዝ፡ አዖደት፡ ዐዋዴ፡ እንዘ፡ ትብል፡ አብያተ፡ ክርስቲያናት
ይትዓፀዋ፡ እስመ፡ አነ፡ ኮንኩ፡ አይሁዳዊት፡ ወብእሲየኒ፡ አይሁዳዊ፡ ውእቱ፡ ወነግሠት፡ አርብዓ፡ ዓመት፡፡

ወእምድኅረዝ፡ ኮነ፡ ስደቶሙ፡ ዓቢይ፡ በላዕለ፡ ካህናት፡ ሌዋውያን፡ ወበላዕለ፡ ሕዝብ፡፡ ጽዮንሂ፡ ታቦተ፡
ሕግ፡ ተሰደት፡ ምስሌሆሙ፡ ወበጽሐት፡ ውስተ፡ አሐቲ፡ ሀገር፡ እንተ፡ መንገለ፡ ምሥራቅ፡ ዘትሰመይ፡

ዝዋይ፡፡ ወአንበርዋ፡ በክብር፡ ኀበ፡ ማኅደር፡ ንጹሕ፡ በጽኑዕ፡ ዑቃቤ፡ መጠነ፡ አርብዓ፡ ዓመት፡ ወእምድኅረ፡
አርብዓ፡ ዓመት፡ ሞተት፡ ጉዲት፡ ወነግሠ፡ አንበሳ፡ ውድም፡ ወኮነ፡ ዘኅን፡ ወሰላም፡፡ ወተመይጡ፡ ውስተ፡

ሀገሮሙ፡ አክሱምሃ፡ ካህናት፡ ሌዋውያን፡ ምስለ፡ ጽዮን፡ ታቦተ፡ ሕግ፡ በዓቢይ፡ ክብር፡ ወበፍሥሐ፡ ብዙኅ፡
በተሰዓቱ፡ ምዕት፡ ወዓሠርቱ፡ ዓመተ፡ ምሕረት፡፡ ተፈጸመ፡ ታሪክ፡ ዘጉዲት፡፡”

ትርጕም፡-

“የጉዲትን ታሪክ እንጽፋለን፡፡ በትግርኛ ‹ጉዲት› በዐምሐርኛ ‹እሳቶ› በአፋርኛ (ጥልጣል) ‹ጋዕዋ› ተብላ

ትጠራለች፡፡ ዮዲት ማለት እውነተኛ ዕፁብ ድንቅ ማለት ነው፡፡ ከአዜብ ንግሥት (ሳባ) በቀር በመልክና ደምግባት
ማንም የሚመስላት (የሚወዳደራት) የሌለ ማለት ነው፡፡ ይኽችም የውድማ አስፈሬ ንጉሥ የሴት ልጁ ልጅ ናት፡፡
የእናቷ አገር ስምም ኃኃይሌ ነው፡፡ በመጥፎ ተግባሯ (ሥራዋ) በወርቅና በብር በከበረ ማዕድን የታነጸውን የገበዘ

አኵስም የጽዮን መቅደስን ስላቀጠለች ‹ጉዲት› ተባለች፡፡ ይኽችም ሴት ከሻም(ምፅዋ) አገር ዘኖቢስ (ዘይቢስ)
ከሚባል ሰው ጋራ እየገሰገሰች መጣች፡፡ በደረሰች ጊዜም ወደ እናቷ አገር ኃኃይሌ መልእክተኛ ላከች፡፡

ገጽ| 9
THE PROBLEM OF GUDIT

እንዲኽ ስትል ከእኔ ጋራ በብዙ ሺሕ የሚቈጠር ሰራዊት አስከትዬ መጥቻለኹና በአፋጣኝ ወጥታችኹ ተቀበሉኝ

ያልመጣ ወዳጄ አይደለም፤ ከጥላቴ ጋራ እንደተባበረ እቈጥረዋለኹኝ፡፡ የኃኃይሌ ሰዎችም ይኽን በሰሙ ጊዜ
ወጥተው አሣውርታ(አሥመርቴ) ከተባለ መንገድ ተቀበልዋት፤ እርሷም ሹልኩ (ሲልኪት) በተባለች ቦታ መጣች፤
ከዚያም በፊት መንገድ አልነበረም፤ መንገዱን እርሷ አወጣችው እንጂ፡፡ በመጣችም ጊዜ ሳይታዘቧት መንገዷን
ሹልኩ ብለው ጠሯት፤ በደኅናም ተወቻቸው፤ አንድም ነገር የሚከለክላት ሳይኖር ወደ አኵስም ሀገር ገባች፡፡
በመዠመሪያ ከተማዪቱንና ጻድቃን ነገሥታቱ አብርሀና አጽብሐ በወርቅና በብር በከበረ ዕንቊ ያነጹትን ቤተ

ክርስቲያን አቃጠለች አፈረሰችም፤ በብዙ ገንዘብ የጽርዕ ጥበበኞች ያነጹትን ሐውልትንም በብረት ሰብራ
ገለበጠችው፤ ዳግመኛ ሰዎቹም እንዳይጠጡ የውሃ ምንጩን ደፈነቻቸው፤ አገሪቷንም ሰው እንዳልነበረባት ወደ
ምድረበዳ ቀየረቻት፡፡

አንድ ቀን የሠራዊቷን ብዛት ለማሳየት ስለፈለገች እያንዳንዳቸውም አንድ አንድ ደንጋይ ተሸክመው ጉቦድራ
ወደሚባል ረጅም ተራራ ይዘው እንዲወጡት አዘዘች፡፡ እንደ ትልቅ ተራራም (ክምር) ኾነ፡፡ ይኽም የደንጋይ
ክምር እስከ ዛሬ ድረስ ይገኛል፡፡ ከዚያ በኋላ 'እኔ አይሁዳዊት ስለኾንኹ ባለቤቴም አይሁዳዊ ስለኾነ አብያተ

ክርስቲያናት እንዲዘጉ' የሚል አዋጅ አወጀች፡፡ እርሷም አርባ ዓመት ነገሠቸች (ገዛች)፡፡ ከዚኽም በኋላ
በሌዋውያን ካህናት ላይ ታላቅ ስደት ኾነ፤ የሕግ ድንኳን የኾነችው ጽዮንም ከእነርሱ ጋራ ተሰደደች፤ ወደ
ምሥራቅ ወደምትገኘው ዝዋይ ወደምትባለው አገር ደረሰች፤ በክብርም በንጹሕ ማደሪያ ውስጥ አስቀመጧት፤
ለአርባ ዓመታትም በጽኑዕ ይጠብቋት ነበር፡፡ ከአርባ ዓመት በኋላ ጕዲት ሞተችና አንበሳ ውድም ነገሠ፡፡ ከዚያም

ሰላምና ፀጥታ ኾነ፡፡ ሌዋውያን ካህናትም በታላቅ ክብርና በብዙ ደስታ ወደ አገራቸው አኵስም የሕግ ድንኳን

ከኾነችው ጽዮን ጋራ ተመለሱ፡፡ በ910 ዓመተ ምሕረት የጕዲት ታሪክ ተፈጸመ፡፡ …”

በዚኽ የብራና ገጸ ንባብ ውስጥ በሰፊው እንደምንመለከተው አኵስም ላይ ያድረሰችውን ጥፋት ነው፡፡
ከዚኽ ጋራም በተያያዘ ‹ጕዲት› የሚለው የስሟ ትርጕምና መንሥኤ ምክንያቱ የሚያስኼድ ይመስላል፡፡
በእርሷም ጥፋት ምክንያት ሌዋውያን ካህናት ታቦተ ጽዮንን ይዘው ወደ ምሥራቅ ዝዋይ እንደተሰደዱና
ዮዲት ስትሞትና አንበሳ ውድም ሲነግሥ እንደተመለሱ ዜና መዋዕሉ ይነግረናል፡፡

ታሪኩ ከተለመደው አተራረክ እንብዛም ባይርቅም የጕዲት ታሪክ ተፈጸመ የተባለበት ጊዜ ላይ ግን


ከሌሎች የታሪክ መጻሕፍትና ትረካ ልዩነት ይታይበታል (ተክለ ጻዲቅ መኵሪያ፤ 1951፤ 383 –
385፡፡ ሥርግው ገላው፤ 2012፤ 118 – 119፡፡ ሎሌ መልአኩ፤ 1997፤ 50 – 52፡፡ ምክረ
ሥላሴ ገ/ዐማኑኤል፤ 2002፤ 98 – 102፡፡ አባ ጎርጎርዮስ፤ 1974፤ 29 – 31፡፡ መንግሥቱ ጎበዜና
አሳምነው ካሣ፤ 2000፤ 67 – 68፡፡ ካሣኹን ደምሴ፤ 2009፤ 85 – 92፡፡)፡፡

በተጨማሪም በዚኽኛው ዜና መዋዕሉ ክፍል ውስጥ ዐዳዲስ እንግዳ ቃላትና ስሞች ይገኙበታል፡፡
እኒኽም፡-

 ዐዳዲስ ቃላትና ስሞች፡-


ጥልጣል፡ ጋዕዋ፡ ኃኃይሌ፡ ሻም፡ አሣውርታ፡ ሹልኩ፡ ጉቦድራ

ገጽ| 10
THE PROBLEM OF GUDIT

 ከ ገጽ 6 - 7 - ከግእዙ ብራና ዜና መዋዕል የተገኘው ኹለተኛው የዮዲት ዜና ታሪክ፤


“ወሶበ፡ ኃጥአት፡ ሲሳየ፡ ዕለት፡ ቦአት፡ ሀገረ አክሱም፡ ከመ፡ ትንሣእ፡ ዐስበ፡ ደነሳ፡ ወሶበ፡ ነጸረ፡ ብእሲ፡
ወሬዛ፡ ወሰአለ፡ ከመ፡ ይስክብ፡ ምስሌሃ፡ ወትቤሎ፡ አንተ፡ ካህን፡ ወአነ፡ እምደቂቀ፡ ንጉሥ፡ ወበምንት፡
ንትራከብ፡፡ ወአውሥአ፡ ወይቤላ፡ ውእቱ፡ ዲያቆን፡ እስመ፡ መንግሥት፡ ወክህነት፡ ዕሩያን፡ እሙንቱ ወይቤላ፡

ካዕበ፡ ንግርኒ፡ ዘትፈቅዲ፡ ከመ፡ አምጽእ፡ ለኪ፡፡ ወትቤሎ፡ ቅድሙ፡ አምጽእ፡ እምኃየ፡ ጽላለ፡ ወርቅ፡
ወእሣዕነ፡ ዘወርቅ፡ ወበይእቲ፡ ትረክብ፡ አንተ፡፡ ወይቤላ፡ ቅድመ፡ አመጽእ፡ ለኪ፡ አሣዕነ፡ ዘወርቅ፡ ወድኅረ፡
አሁበኪ፡ ውእተ፡ ዳዕሙ፡ በልኒ፡ ኦሆ፡ ወአውጽአቶ፡ ወትቤሎ፡ ሑር፡ አምጽእ፡ ቅድመ፡ ፍጡነ፡ ወድኅረ፡
እነግረከ፡፡ ውእቱኒ፡ ተነድፈ፡ በሐፀ፡ ዝሙት፡ ወሖረ፡ ውስተ፡ መዛግብቲሃ፡ ለጽዮን፡ ወሰጠጠ፤ መንጠላዕተ
ወርቅ መጠነ፡ አሣዕነ፡ እግራ፡ ዘአገበሩ፡ ነገሥታት፣ ጻድቃን፡ አብርሃ፡ ወአጽብሐ፡፡ ወሶበ፡ ርእይዎ፡ ሰብእ፡

ለመንጦላዕተ፡ ወርቅ፡ ስጡጠ፡ ወተበሃሉ፡ በበይናቲሆሙ፡ መኑ፡ ሰጠጠ፡ መንጦላዕተ፡ ጽዮን፡ ወስጠቱ መጠነ፡
አሳዕነ፡ እግር፡፡ ወተጋብኡ፡ ሰብአ፡ ትዕይንት፡ ወሐተቱ፡ መጠነ፡ ሠለስቱ፡ ዕለት፡ እንዘ፡ ይኔጽሩ፡ አሳዕነ፡
እግሩ፡ ለሰብእ፡ እንዘ፡ ይከይድ፡፡ ዓቢየ፡ ይከውን፡ ዓቢይ፡ ሥጠቱ፣ ወእንዘ፡ ይከይድ፡ ንዑስ፡ ይከውን፡
ንዑስ፡ ሥጠቱ፡፡ ወእምድኅረዝ፡ መጽአት፡ ጉዲት፡ መጠነት፡ እገሪሃ፡ ወኮነ፡ ዕሩየ፡ ወአኀዝዋ፡ ሰብእ፡

ወይቤልዋ፡ አይድዒነ፡ ዘንተ፡ ነገረ፡ ዘከመ፡ እፎ፡ ኮነ፡ በመጠነ፡ እግርኪ፡ ዝንቱ፡ ሥጠት፡፡ ወአውሥአት፡
ወትቤሎሙ፡ አንሰ፡ ሀለወኒ፡ አሣዕነ፡ ወርቅ፡ ዘአምጽአ፡ ሊተ፡ ሰብእ፡፡ ወባሕቱ፡ ኢየአምር ፡ እምኀበ
አምጽአ፡፡ ወይቤልዋ፡ እስኩ፡ አርኢይነ፡ ወአርአየቶሙ፡፡ ወሶበ፡ ርእይዎ፡ ኮነ፡ እሙነ፡ ወይቤልዋ፡ መኑ፡
ውእቱ፡ ብእሲሁ፡ ዘወሀበኪ፡፡ ወነገረቶሙ፡ ወትቤሎሙ፡ ዘወሀበኒ፡ አሐዱ፡ ወሬዛ፡ ውእቱ፡፡ ወተጋብኡ፡

ዐበይተ፡ ሀገር፡ ወሊቃውንት፡ ወፈትሑ፡ ፍትሐ፡ በዘይደልዎ፡፡ ወይቤሉ፤ ምንተ፡ ይግበር፤ ዝንቱ፡ ሕፃን፡

እንዘ፡ ምስሌሁ፡ ዕሥራ፡ ዓመት፡ ለእመ፡ ርእያ፡ ሥነ፡ ላሕያ፡ ወይእቲኒ፡ አንበረቶ፡ ከመ፡ ይግበር፡ ዘንተ፡፡
ንጹሕ፡ ውእቱ፡ እምዝንቱ፡ ነገር፡ ሕፀፀ፡ መዋዕሊሁ፡ ያድኅኖ፡፡ ወይእቲኒ፡ ይደልዋ፡ ኵነኔ፡ በእንተ፡
ዘተሀበለት፡ ወተሥዕነት፡ መንጦላዕታ፡ ለጽዮን፡፡ ወፈትሑ፡ ፍትሐ፡ እንዘ፡ ይብሉ፡ ይምትሩ፡ አጥባቲሃ፡
ዘየማን፡ ወይስድድዋ፡ እምሀገር፡ ወገብሩ፡ ከማሁ፡፡ ወሰደድዋ፡ ወአውጽእዋ፡ እስከ፡ ወሰነ፡ ባሕረ፡ ኤርትራ፡

እንተ፡ ይእቲ፡ ወሰነ፡ ምስር፡፡ ወረከባ፡ ወልደ፡ ንጉሠ፡ ሻም፡ ዘስሙ፡ ዘኖቢስ፡ ወሶበ፡ ርእየ፡ ተሰአላ፡
ወይቤላ፡ አይቴ፡ ብሔርኪ፡ ወመኑ፡ ዘአምጽአኪ፡ ዝየ፡፡ ወአውሥአት፡ ወትቤሎ፡ አልብየ፡ ሀገር፡ ወአልብየ፡
ዘመድ፡ እስመ፡ ተገብረ፡ ብዙኅ፡ ግፍዓ፡ ላዕሌየ፡ ወይቤላ፡ ምንተ፡ ኮንኪ፡ ወአርአየቶ፡ አጥባቲሃ፡፡ ወሶበ፡
ርእየ፡ ደንገፀ፡ ወኀዘነ፡ ወነሥኣ፡ ምስሌሁ፡ ወፈወሳ፡ ቊስሊሃ፡ ወረሰያ፡ ብእሲቶ፡ ወኀደገት፡ ክርስትና ፡
ወኮነት ፡ አይሁዳዊተ፡፡ እስመ፡ አይሁዳዊ፡ ውእቱ፡ ብእሲሃ፡፡ ወእምድኅረዝ፡ ሰአለቶ፡ ጉዲት፡ ለውእቱ፡

ብእሲ፡ ወትቤሎ፡ ለእመ፡ አፍቀርክኒ፡ ንሑር፡ ብሔርየ፡ ከመ፡ ታጥፍእ፡ ፀርየ፡፡ ወአውሥአ፡ ወይቤላ፡ አንሰ፡
ኢይክል፡ ሐዊረ፡ ውስተ፡ ብሔርኪ፡ እስመ፡ ኃያላን፡ እሙንቱ፡ ነገሥታት፡ ኢትዮጵያ፡፡ ወይእቲኒ፡ ኢኀደገት፡
ስኢለ፡ ወትፌኑ፡ ሰብአ፡ ዓይን፡ ለሐውዖ፡ ብሔረ፡ ተመሲሎሙ፡ ነጋድያን፡፡ ወአሐተ፡ ዕለተ፡ ነገርዋ፡ ሰብአ፡
ዓይን፡ ከመ፡ ዳግናዣን፡ ነገሠ፡ በኢትዮጵያ፡፡ ሖረ፡ ብሔረ፡ ዓረብ፡ ወተውሕጠ፡ በሆፃ፡ ወሐልቁ፡ ሠራዊቱ፡
በጽምአ፡ ማይ፡ ምስለ፡ ንጉሦሙ፡፡ ወሰሚዓ ጉዲት፡ የበበት፡ እንዘ፡ ትብል፡ እግዚአብሔር፡ ሰምዓ፡ ስዕለትየ፡
ነፀረ፡ ግፍዕየ፡፡ ወሰአለቶ፡ ብዙኃ፡ ከመ፡ ይሑር፡ ብሔራ፡ ውእቱኒ፡ አስተጋብአ፡ ብዙኃ፡ ሠራዊተ፡ ወተጽዕነ፡
በሐመር፡ ወወጽእ፡ በፍኖተ ምጽዋዕ፡ ወተዐየነ፡ በድኆኖ፡፡

ገጽ| 11
THE PROBLEM OF GUDIT

ትርጕም፡-

“…የዕለት እንጀራን ባጣች ጊዜ ሥጋዋን ሽጣ ለመተዳር ወደ አኵስም አገር ገባች፤ አንድ ጐረምሳ ወጣት ዐውቆ

ባያት ጊዜ ከእርሷ ጋራ ይተኛ ዘንድ ለመናት/ጠየቃት፤ አለችውም፡- ‹አንተ ካህን ስትኾን እኔ ግን ከነገሥታት
ልጅ (ወገን) ነኝ በምን እንገናኛለን?›፡፡ ያ ዲያቆንም መለሰላት እንዲኽም አላት፡- ‹ መንግሥትና ክህነት አንድ
ናቸው፡፡›› ዳግመኛም፡- ‹አመጣልሽ ዘንድ የምትፈልጊውን ንገሪኝ› አላት፤ ‹በቅድሚያ የወርቅ ዣንጥላና የወርቅ
ጫማ ስጦታዬን አምጣ፤ ከዚያም የፈለግኸውን ታገኛለኽ› አለችው፡፡ ‹እሺ በዪኝ እንጂ በቅድሚያ የወርቅ ጫማ

አመጣልሻለኹ፤ ከዚያም እሰጥሻለኹ፤› አላት፡፡ እንዲኽ ስትል መለሰችለት ‹ኺድ በፍጥነት ቅድሚያ አምጣ

ከዚያም በኋላ እነግርሃለኹ፡፡› እርሱም በዝሙት ፍቅር ተነድፏልና ወደ ጽዮን ግምጃ ቤት ኸደ፡፡ ጻድቃን
ነገሥታት አብርሀና አጽብሐ ያሠሩትን እስከ እግር ጫማ መርገጫ ድረስ የሚወርደውን የወርቅ መጋረጃ ቀደደ፡፡

ሰዎችም የወርቁ መጋረጃ ተቀድዶ ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው፡- ‹የጽዮንን መጋረጃ ማን ቀደደው?› ተባባሉ፤
ቅደቱም ከላይ ዠምሮ እስከ እግር ጫማ መርገጫ ድረስ ነበርና፡፡ የከተማው ሰዎችም ተሰበሰቡ እስከ ሦስት ቀናት

የሚኼደውን ሰው የእግሩን ጫማ ሲመለከቱና ሲመረምሩ፤ ትልቅ እግር ትልቅ ነው ቅደቱ፤ አነስተኛ እግር
አነስተኛ ነው ቅደቱ፡፡ ከዚኽ በኋላ ጕዲት መጣች፡፡ የእግሯ መጠንም ትክክል ኾነ፤ ሰዎችም ያዟት፤ ‹ይኽ
ነገር ቅደቱ በእግርሽ ልክ እንዴት ሊኾን ቻለ? አስረጂን› አሏት፡፡ መለሰችም፡- ‹ለእኔ ወርቅ ጫማ ያመጣልኝ
ሰው አለ፤ ነገር ግን ከየት እንዳመጣልኝ አላውቅም› አለቻቸው፡፡ ‹እስኪ አሳዪን› አሏት፤ አሳየቻቸውም፡፡

ባዩትም ጊዜ እውነት ኾነ፤ ‹የሰጠሸ ሰውዬ ማን ነው?› አሏት፡፡ ‹አንድ ጐረምሳ ወጣት ነው የሰጠኝ፤› ባላ

ነገረቻቸው፡፡ የአገሩ ታላላቆችና ሊቃውንት ተሰበሰቡ ተገቢ የኾነውን ፍርድም ፈረዱ፡፡ እንዲኽ አሉም፡- ‹ይኽ
የኻያ ዓመት ሕፃን ምን ያድርግ? ውበቷን (ደምግባቷን) ቢያይ እርሷም ይኽን ያደርግ ዘንድ አነሣሣችው፡፡

ስለዚኽ የእድሜው ማነስ ከዚኽ ነገር ያድነዋል፤ ንጹሕ ነው፤ እርሷ ግን የጽዮንን መጋረጃ ስለተደፋፈረችና
ስላጠፋች ፍርድ ይገባታል፤›፡፡ ፍርድንም እንዲኽ ሲሉ ፈረዱ፡- ‹የቀኝ ጡቷን ይቊረጡ፤ ከአገርም

ያባርሯት፡፡› እንዲኹም አደረጉ፡፡ እስከ ኤርትራ ባሕር ወሰን ድረስ አውጥተው ሰደዷት(አባረሯት)፤ ይኽችም
የግብጽ ወሰን ናት፡፡ የምፅዋ (የሻም) ንጉሥ ልጅ ስሙ ኖቢስ የሚባል አገኛት፤ ባያትም ጊዜ ‹አገርሽ የት ነው?

ወደዚኽስ ማን አመጣሽ?› ብሎ ጠየቃት፡፡ እንዲኽም ብላ መለሰችለት፡- ‹አገርም ዘመድም የለኝም፤ ብዙ ግፍ


በኔ ላይ ተደርጓልና(ተሠርቷ)፡፡ ‹ምንን ኾንሽ?› አላት፤ ጡቶቿንም አሳየችው፡፡ ባየም ጊዜ ደነገጠ፤ ዐዘነም፤

አቀፋት፤ ቊስሏንም አከማት፤ ሚስቱም አደረጋት፤ ክርስትናንም ተወች፤ አይሁዳዊትም ኾነች፡፡ እርሱ ባለቤቷ
አይሁዳዊ ነውና፡፡ ከዚኽም በኋላ ጕዲት ባለቤቷን እንዲኽ ብላ ለመነችው፡- ‹ካፈቀርኸኝ ጠላቶቼን ታጠፋ ዘንድ

ወደ አገሬ እንኺድ፡፡› አለቸው፡፡ እንዲኽ ብሎ መለሰላት፡- ‹እኔ ወደ አገርሽ መኼድን አልችልም፤ የኢትዮጵያ

ነገሥታት ኀያላን (ብርቱዎች) ናቸውና!›፡፡ እርሷም መለመንን ተወች፤ ነጋዴዎችን መስለው አገሩን ለመጐብኘት

ሰላዮችን ለመላክ ዐሰበች፡፡ አንድ ቀንም ሰላዮች ደግናዣን በኢትዮጵያ እንደነገሠ ነገርዋት፡፡ ወደ ዐረብ አገር
እንደኼደና በዚያም ሰራዊቱ ከንጉሣቸው ጋራ በውሃ ጥም እንዳለቁና በአሸዋ እንደተዋጠ ጕዲት በሰማች ጊዜ
እንዲኽ ስትል አመሰገነች፡- ‹እግዚአብሔር ልመናዬን ሰማ፥ ግፌንም ተመለከተ፡፡› ብላ፡፡ ባለቤቷንም ወደ

አገሯ እንዲኼድ በጽኑዕ ለመነችው፤ እርሱም ብዙ ሠራዊቶችን አሰባሰበና በመርከብ ተሳፍሮ በምፅዋዕ መንገድ
በድኅኖ ከተማ በኩል አድርጎ ወጣ፡፡”

ይኽ የብራና ገጸ ንባብ በሰፊው የሚነግረን የዮዲትን የጥፋት መንሥኤ ምክንያት የኾነውን ታሪኳን ነው፡፡

ገጽ| 12
THE PROBLEM OF GUDIT

የዮዲት ጥፋት መንሥኤው በደረሰባት የፍርድ መጓደል ምክንያት እንደኾነ ጽሑፉ በስፋት ያትታል፤
ታሪኩ ላይም እንግዳ የሚመስል ነገር ይታያል ቢኾንም ታሪካዊ ጉዳዩ ይበልጥ ጥናትና ምርምር
እንደሚያስፈልገው አመላካች ነው፡፡ ሌላው ዮዲት በደረሰባት ፍርደ ግምድልነት ምክንያት እንጂ
ቀድሞ ክርስቲያን እንደነበረችና በኋላም ክርስትናን ትታ የአይሁድ እምነትን እንደተከተለች በጽሑፉ
ውስጥ እንመለከታለን፡፡ ይኽም ከነባሩ ትርክት ወጣ ያለና ያልተለመደ ኹኖ ይገኛል፡፡ ዮዲት
በደረሰባት በደል በቀል ማሰቧ አልቀረም፤ አስባም ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ዝግጅት መዠመሯንም
ይነግረናል፡፡ ከዚኽ በኋላ መጥታ የፈጸመችውን ጥፋት በመዠመሪያው የብራና ክፍል ተጽፏል፡፡
በዚኽኛው ዜና መዋዕል ክፍል ውስጥ ዐዳዲስ እንግዳ ቃላትና ስሞች ብዙ ባይኖሩም አንድ ተገኝቷል፡፡
ይኽም፡- ‹ድኆኖ› የሚለው ነው፡፡

 ከ ገጽ 10 - 11 - ከግእዙ ብራና ዜና መዋዕል የተገኘው ሦስተኛው ታሪክ፤


“ወውእቱ፡ ብእሲ፡ (ዳግናዣን)፡ አስተጋብአ፡ ሠራዊቶ፡ መጠነ፡ ዐሠርቱ፡ እልፍ፡ ወሖረ፡ ብሔረ፡ ዓረብ፡

እንተ፡ ምዕራቢሃ፡ ለኢትዮጵያ፡ ከመ፡ ይቅኒ፡ ካልአ፡ ሀገረ፡ ተመኪሖ፡ በብዝኃ፡ ሠራዊቱ፡፡ ተውኀጠ፡ በሆፃ፡

ወኢያእመረ፡ ውእቱሂ፡ እስመ፡ መሰለቶ፡ ምድር፡ ርኂብ፡ ወኢተመይጠ፡ አሐዱሂ፡ እምሠራዊቱ፡ ዘይዜኑ፡
ዜናሁ፡፡

ወአንገሠ፡ ለዳግናዠን፡ በመዋዕሊሁ፡ ዘአውጽአ፡ ምእት፡ ወሃምሣ፡ ካህናተ፡ አክሱም፡ ኀበ፡ አምሐራ፡

ወሰመዮሙ፡ ደብተራ፡ ወአመ፡ ወጽአ፡ እምትግሬ፡ ገብረ፡ መዲና፡ በወይና፡ ደጋ፡ እንዘ፡ ምስሌሁ፡ ስሣ፡

ታቦታት፡ እለ፡ ይዘምቱ፡ አሜሃ፡ ሠራዊቱ፡ ሰትዩ፡ ማየ፡ ፊቅ፡ እምባሕር፡ ዘምድረ፡ ደርግንዳ፡ እምተከዜ፡
ቀኝ፡ እምታኅያ፡ ግራ፡ እምርብ፡ መንክር፡ ውእቱ፡ ለዘየአምሮ፡ ብሔሩ፡፡ ዓዲ፡ ርዕየ፡ ግባት፡ በርብ፡፡ ወሶበ፡

ኈለቆ፡ ሐራሁ፡ ተረክቡ፡ ዓሠርቱ፡ ወሰመንቱ፡ እልፍ፡ ወሃምሣ፡ ምዕት፡ ልቡሳን፡ ጽሩር፡ አትለዎሙ፡
ወወደሶሙ፡ ኀበ፡ አቡሁ፡ ወአቡሁ፡ በከየ፡ በከመ፡ ኀደጐ፡ ለወልዱ፡ ድልነዓድ፡፡ ወእምኔሁ፡ ተኀይደት፡

መንግሥት፡ ወተውህበት፡ ለካልዓን፡ እለ፡ ኢኮኑ፡ እምእስራኤል፡፡

ትርጕም፡-

“ይኽ ሰው (ዳግናዣን) በሠራዊቱ ብዛት ተመክቶ ወደ 100,000 ሺሕ የሚጠጉ ሠራዊቶቹን ሰብስቦ እንደ ኹለተኛ
አገር ይገዛ ዘንድ የኢትጵያ ምዕራብ ወደኾነችው ዐረብ አገር ኼደ፡፡ ነገር ግን አላወቀም ነበርና ሰፊ መሬት

መስሎት በአሸዋ ላይ ጠፋ፤ ወሬውን ለመናገር (ታሪኩን) ከሠራዊቱ አንድም እንኳ አልተረፈም፡፡

ዳግናዣንም ነገሠ፤ በዘመኑም 150 ካህናትን ከአኵስም ወደ ዐምሐራ ወስዶ ደብተራ ብሎ ሰየማቸው፡፡ ከትግሬ
በወጣ ጊዜ ዋና ከተማውን በወይና ደጋ ከእርሱ ጋራ ከሚዘምቱ ስልሳ ታቦታት ጋራ አደረገ፤ ያን ጊዜም ሠራዊቱ
ከምድረ ደርግንዳ ከተካዜ ውሃ ጠጡ፤ ይኽም በታኅያ በስተቀኝና ከ ርብ በስተግራ ምድሩን ለሚያውቀው ድንቅ
ነች፡፡ ወይም ሬብ ውስጥ አንዳንድ ዋሻዎችን ዐየ፡፡ ወታደሮቹን ሲቈጥር 185,000 የጦር ጥሩር የለበሱ ተገኙ፡፡

እንዲከተሉትም አዘዛቸው ወደ አባቱም ወሰዳቸው፤ አባቱም ልጁን ድልነዓድን ስለተወ አለቀሰ፡፡ ከእርሱም በኋላ
መንግሥቱ እስራኤላውያን ላልኾኑ ለሌሎች ተላለፋ ተሰጠች፡፡”

ገጽ| 13
THE PROBLEM OF GUDIT

የብራናው የመጨረሻ ክፍልም ስለዳግናዣን መንገሥና ወደ ዐረብ አገር ሠራዊቱን ሰብስቦ ለመውረር
እንደኼደና በዚያም በአሸዋ ተውጦ እንደጠፋ ይናገራል፤ ሌላም የታሪክ ሐሳብ በውስጡ ይገኛል፡፡

፪.፫) የመጣጥፉ ጠቀሜታ፡-

ይኽ የዶ/ር ስርግው ሐብለ ሥላሴ መጣጥፍ በዋነኘነት ሦስት ዐበይት ጠቀሜታዎች ይኖሩታል ተብሎ
ይታሰባል፤ እኒኽም፡-

- ለግእዝ ቋንቋ ትምህርት ጥናት (የቋንቋውን ሰዋስዋዊ አካኼድ ለመቃኘት)


- ለታሪክና የድርሳናት ትምህርት ጥናት (ለኢትዮጵያ ታሪክ)
- ለሥነ ጽሑፍ ትምህርት ጥናት (የሥነ ጽሑፉን ውበት ለመመርመር)

፫ ማጠቃለያ፡-
ይኽ መጣጥፍ የታሪክ ክፍተትን አንድ ጐን ይሞላል ብሎ ተማሪው ያምናል፤ የታሪክ ገጽታው ብዙ
ቢኾንም ለተሻለ ምርምርና ጥናት የሚጋብዝ ነው፡፡

ስምዐት (ዋቢ መጻሕፍት)


 Journal of Ethiopian Studies, Vol. 10, No. 1 (JANUARY 1972), pp. 113-124, Institute

of Ethiopian Studies

 ተክለ ጻዲቅ መኵሪያ፤ 1951 ዓ.ም፤ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ኑብያ-አክሱም- ዛጉዌ፤ እስከ ይኩኖ አምላክ

ዘመነ መንግሥት፤ ዐዲስ አበባ፡፡


 ሥርግው ገላው (ዶ/ር)፤ 2012 ዓ.ም፤ የኢትዮጵያ ታሪክ በተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፤ ዐዲስ አበባ፡ ዜኤ

ማተሚያ ድርጅት፡፡
 ሎሌ መልአኩ (ፕ/ር)፤ 1997 ዓ.ም፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ታሪክ፤ ዐዲስ አበባ፤

ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፡፡


 ምክረ ሥላሴ ገ/ዐማኑኤል (ዶ/ር)፤ 2002 ዓ.ም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በምድር ላይ

(ጠቅላላ የቤ/ክ ታሪክ)፤ ኹለተኛ መጽሐፍ፤ ዐዲስ አበባ፤ ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፡፡
 አባ ጎርጎርዮስ፤ 1974 ዓ.ም፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ታሪክ፤ ዐዲስ አበባ፤ ትንሣኤ

ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፡፡


 ዲ/ን መንግሥቱ ጎበዜና ዲ/ን አሳምነው ካሣ፤ 2000 ዓ.ም፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቊጥር ፪፤ ዐዲስ

አበባ፤ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ፋር ኢስት ማተሚያ ቤት፡፡

ገጽ| 14
THE PROBLEM OF GUDIT

 ካሣኹን ደምሴ፤ 2009 ዓ.ም፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ዐበይት ፈተናዎች፤ (ከቅድመ
ንጉሥ ኢዛና እስከ ዘመነ ኢሕአዴግ)፤ ዐዲስ አበባ፤ ዛክ አታሚ፡፡

ገጽ| 15

You might also like