Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 11

Article Review (የመጣጥፍ ዳሰሳ)

Gädlä Bestawros (ገድለ ብስጣውሮስ)

 Academic Year: - 2015/2022/23


 Program: - Regular Ge’ez M.Th. Degree 1th year 1st semester
 Faculty: - Ethiopian Church Studies
 Department: - Ge’ez Language
 Course Title: - Ge’ez seminar I, session 3
 Course Teachers: - Dr. Andualem, Mr, Abenet, Mr, Beniyam

 Formulate’s Name: - Mesfin Tekeste


 Id. No: - MGL-031/15
 Place: - Addis Ababa Region / Arat Kilo

፳፻፲፭ ዓ.ም፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፡፡
Gädlä Bestawros (ገድለ ብስጣውሮስ)

መክሥተ አርእስት

መክሥተ አርእስት...................................................................................................................................... 1
፩) መግቢያ (Introduction) ..................................................................................................................... 2
፩.፩) የመጣጥፉ አጠቃላይ ዳራ (Overview) .......................................................................................... 2
፩.፩.፩) የመጣጥፉ አዘጋጅ ማንነት (የመጣጥፉ ጸሓፊ ማን ነው?) .......................................................... 2
፩.፩.፪) መጣጥፉ መቼና የት ተዘጋጀ? (ጊዜውና ቦታው) ፡- ................................................................ 3
፩.፩.፬) መጣጥፉ የተጻፈበት ምክንያት፡- .............................................................................................. 3
፩.፩.፭) የመጣጥፉ ዓላማ፡- ................................................................................................................. 3
፪) ዋና ሐሳብ (Main Body) ................................................................................................................ 5
፪.፩) የመጣጥፉ ይዘት: - .................................................................................................................... 5
፪.፩.፩) አጠቃላይ ይዘት፤ ................................................................................................................... 5
፪.፪) የመጣጥፉ ጠቀሜታ: - ............................................................................................................. 10
፫ ማጠቃለያ፡-..................................................................................................................................... 10
ስምዐት (ዋቢ መጻሕፍት) ..................................................................................................................... 10

ገጽ| 1
Gädlä Bestawros (ገድለ ብስጣውሮስ)

፩) መግቢያ (Introduction)

፩.፩) የመጣጥፉ1 አጠቃላይ ዳራ (Overview)


 የመጣጥፉ ርእስ፡- Gädlä Bestawros (ገድለ ብስጣውሮስ)
 የመጣጥፉ አዘጋጅ (ጸሓፊ)፡- ረ/ፕ/ሮ አምሳሉ ተፈራ
 የመጣጥፉ መገኛና አሳታሚ (Periodical)፡- Aethiopica 13 (2010) International
Journal of Ethiopian and Eritrean Studies AMSALU TEFERA, Addis Ababa
University Gadla Bastawros Aethiopica 13 (2010), 7-45 ISSN: 1430-1938
Published by Universität Hamburg Asien Afrika Institut, Abteilung
Afrikanistik und Äthiopistik Hiob Ludolf Zentrum für Äthiopistik
 መጣጥፉ የተጻፈበት ቋንቋ፡- ግእዝ / እንግሊዝኛ
 የመጣጥፉ ተተኳሪ ዐይነት፡- የገድል ጥናት

፩.፩.፩) የመጣጥፉ አዘጋጅ ማንነት (የመጣጥፉ ጸሓፊ ማን ነው?)


መጣጥፉን ከመዳሰስ በፊት የመጣጥፉን አዘጋጅ (ጸሓፊ) ማንነት ማወቅ ተገቢ ነውና በዐጭሩ የመጣጥፉን
ጸሓፊ ማንነት መናገር ያስፈልጋል፤ ይኽ መጣጥፍ የዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ነው፡፡

በዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥንታውያን ጽሑፋት ጥናት (ፊሎሎጂ) ረዳት ፕሮፌሰር ኹነው በማስተማርና

በምርምር ላይ የሚገኙት ቀሲስ አምሳሉ ተፈራ የቤ/ክን ልጅ ናቸው፤ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ
ምሩቅና መምህር ኹነውም አገልግለዋል፤፣ በትምህርት በቆዩባቸው በጣልያንና በጀርመን፣ እንዲኹም

ጥናትና ምርምር ባደረጉባቸው ዩናይትድ ኪንግደምና የተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶችም ሰፊ የምርምር

ሥራዎችን አቅርበዋል፤ በበርካታ ጆርናሎችም ላይ ይኽንና መሰል መጣጥፎችን አዘጋጅተው


አቅርበዋል፡፡ በተለይ በሰፊው በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከሚታወቁበት ሥራቸው አንዱ ‹‹ነቅዐ
መጻሕፍት ከ600 በላይ በግዕዝ የተጻፉ ኢትዮጵያ መጻሕፍት ዝርዝር ከማብራሪያ ጋር›› የሚለውን

መጽሐፋቸው ነው፤

1 ይኽን Article የሚዳስሰው ተማሪ ‹መጣጥፍ› ሲል ‹Article› የሚለውን አቻ ቃል ተጠቅሞ እንደኾነ ልብ ይሏል፡፡
ስለዚኽ ‹Article Review - የመጣጥፍ ዳሰሳ› ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ገጽ| 2
Gädlä Bestawros (ገድለ ብስጣውሮስ)

፩.፩.፪) መጣጥፉ መቼና የት ተዘጋጀ? (ጊዜውና ቦታው) ፡-


የዚኽ መጣጥጥፍ ዝግጅት ጊዜው በዐዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ በ2006 ዓ.ም ከሠሩት
የማስተርስ መመረቂያ ጽሑፍ ጋራ የተያያዘ ነው፤2 ከምርምር ሥራቸው ተቀንጭቦ በጆርናሉ ላይ
የቀረበበትንና የወጣበትን ጊዜ ስንመለከት ይኽም እ.ኤ.አ 2010 ዓ.ም ነው፡፡

፩.፩.፫) መጣጥፉ የተጻፈበት ቋንቋ፡-


ከአርእስቱ ዠምሮ የመጣጥፉ ጸሓፊ የተጠቀሙት ቋንቋ እንግሊዝኛ ሲኾን ለመጣጥፉ ዋና ግብአት
የኾነውን ያልታተመ የግእዝ ገድል ብራና ጽሑፍ ቅጂ ደግሞ ያቀረበው በግእዝ ቋንቋ እንዳለ ያለምን
የቃል ጭመራና ቅነሳ ሳይኖር ነገር ግን በጥሩ ርማትና መልክአ ፊደል ሥርዐተ ጽሐፈት ነው፡፡

ይኽ ሲባል ግን በግርጌ ማስታወሻ ጥቂት የማይባሉ ርማቶችንና ማስታወሻ ሐሳቦችንም አካትተዋል፡፡


በተጨማሪም በግእዝ ያለውን የብራናውን ጽሑፍ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተርጕመው አቅርበዋል፡፡

፩.፩.፬) መጣጥፉ የተጻፈበት ምክንያት፡-


የመጣጥፉ አዘጋጅ ጥናታዊ መጣጥፉን የጻፈበትን ምክንያት በግልጽ በመጣጥፉ ባያስቀምጥም በዋና
የጥናታዊ ሥራቸው ክፍል ውስጥ የተካተተ ርእሰ ሐሳብ በመኾኑ ምክንያተ ጽሕፈታቸውም በዚያ አንጻር
የሚታሰብ ነው፡፡

፩.፩.፭) የመጣጥፉ ዓላማ፡-

የመጣጥፉ ዋና ዓላማ በተገኘው የግእዝ ገድል ብራና መጽሐፍ ቅጂ Philological and textual
analysis መሥራት ነው፤ አክሎም በተጨማሪ ማብራሪያ (Annotation) በማጠንከር በእንግሊዝኛ
ቋንቋ ተርጕሞ ማሳየት ነው፤ አዘገጃጀቱም የተማረውንና ተመራማሪውን ማኅበረሰብእ ታሳቢ ያደረገ
ይመስላል፡፡

2 The article is excerpted from my MA thesis, Philological and textual analysis of Gadla Bostawros

Abbot of Dabra Hayq, submitted to the School of Graduate Studies, Addis Ababa University 2006.
The researcher would like to thank Prof. Paolo Marrassini, who spent much time and effort
offering constructive comments, invaluable insights and suggestions while I was writing the thesis.

Moreover, he facilitated the publishing of this paper and dedicated many hours to editing not
only the content but also the language. Thanks also to Dr. Gideon P.E. Cohen and Dr. Alessandro
Gori for their careful editing of this paper.

ገጽ| 3
Gädlä Bestawros (ገድለ ብስጣውሮስ)

፩.፩.፮) የመጣጥፉ መረጃ ምንጭ፡-


ይኽ መጣጥፍ ርቱዕ/ቀጥተኛ/ ቀዳማይ (Primary Source) እና ኢ-ርቱዕ/ቀጥተኛ ያልኾነ/ ካልኣይ
(Secondary Source) የመረጃ ምንጮችን በመጠቀም የተዘጋጀ ጥናታዊ መጣጥፍ ነው፤ መጣጥፉ
በዋነኝነት የቅዱስ ብስጣውሮስን ገድል ጉዳዩ ስላደረገ አጥኒው በመሠረታዊ ዳሰሳ ያልታተሙ የግእዝ
ገድል ብራና መጻሕፍትን በርቱዕ ምንጭነት እንዲፈትሽ አስችሎታል፡፡ እንዲኹም በእርሳቸው ታሪክ
ዙሪያ የተጻፉ መጻሕፍትንና ጥናታዊ ሥራዎችን ተመልክቷል፤ በዚኽ መሠረትም በቀዳማዊ ምንጭነት
ለጥናቱ ዋቢ የኾኑ ዋና የግእዝ ብራና ቅጂዎች ከታች እንደሚከተሉት ያሉት ናቸው፡-

- EMML. no. 703 -Hwalq"a towladda mänäkosat, 'Genealogy of monks.


- EMMI. no. 1710 -Nägärä Haymanot - Mäshäfä Istǝgbu".
- EMML no. 1836-Mar Yasǝhaq-copied by Bastawros.
- EMML no. 2059 -Ta'ammara Maryam - copied by Bastawros.
- EMML no. 2060 - Ta'ammora Maryam-copied by Bastawros.
- EMML no. 2812 - Gadla Bastawros.
- EMML no. 2840 - Psalter [ff. 194r-197r, 199v] materials on the theology
of Qǝb'at. Bastawros (copyist), Sankassar, Dabra Hayq, Abuna Iyasus
Mo'a Monastery, unpub- lished MS, Däbrä Hayq.
- Qerlos Istagbu", "Compilation of Cyril' (Ethiopic version), unpublished
MS, possession of mamber Dawit Barhanu, Addis Ababa.

በተለይ ዶ/ር አምሳሉ የተጠቀሙት ብራናዎች ተአማኒነት ያላቸውና ቅቡልነታቸው የሰፉትን ነው፡፡
በካልኣይ ምንጭነት ደግሞ አስፈላጊ ግብአት እንዲኾን በዛ ያሉ የተለያዩ ከቅዱስ ብስጣውሮስ ታሪክ
ጋራ ተያያዥነት ያላቸውን ከአርባ ዐምስት በላይ መጻሕፍትና ጥናታዊ የምርምር ሥራዎችን እንዲኹም
ጆርናሎችን በመመልከት ለጥናታዊ ሥራቸውና ለመጣጥፉ በግብአትነት አገልግለዋል፡፡

መጣጥፉ ጠብሰቅ ባለ በ103 የግርጌ ማስታወሻ ተጨማሪ ማብራሪያ ሐሳቦችና ትንተናዎች የበለጸገ
የጥናትና ምርምር ዘዴን የተከተለ ሥራ ነው፡፡

እንደመግቢያ እነዚኽን አርእስተ ሐሳቦች በመጣጥፉ ላይ ከተነሣ ቀጣይ ደግሞ የመጣጥፉን ዋና ይዘትና
እንዲኹም ጠቀሜታውን በዐጭሩ ለመቃኘት ይሞከራል፡፡

ገጽ| 4
Gädlä Bestawros (ገድለ ብስጣውሮስ)

፪) ዋና ሐሳብ (Main Body)


፪.፩) የመጣጥፉ ይዘት: -
ይኽ መጣጥፍ በዋነኝነት በደብረ ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም ከ17ኛው መ/ክ/ዘ/ መጨረሻ ዠምሮ
እስከ 18ኛው መ/ክ/ዘ/ መዠመሪያ ድረስ የኖሩትን የታላቁን ቅዱስ ብስጣውሮስ ዜና ሕይወት የሚናገር
ገድል ጥናት ነው፡፡

፪.፩.፩) አጠቃላይ ይዘት፤


ይኽ መጣጥፍ 45 ገጻት ያሉት ሲኾን አጥኒው ባገኘው የግእዝ ብራና ገድል ቅጂ መሠረት Philological
and textual analysis በማድረግ ያዘጋጀው ነው፡፡

አቡነ ብስጣውሮስ ዘሐይቅ ሙሉ ስማቸው ዐቃቤ ሰዓት አቡነ ብስጣውሮስ ተብለው የሚጠሩ ሲኾን
የትውልድ አገራቸው መቅደላ ነው፡፡ አባታቸው ፍተ ድንግል እናታቸው ጽዮን ሞገሳ የሚባሉ ደጋግ
ቅዱሳን ናቸው፡፡ አቡነ ብስጣውሮስ በ17ኛው መ/ክ/ዘ የነበሩ ታላቅ ጻድቅ ሲኾኑ የታላቁና የጥንታዊው
ትምህርት ቤትና የሥርዐተ ገዳም ተቋም የደብረ ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞአ ገዳም
አበምኔት ነበሩ፡፡ በልጅነታቸው ትምህርት ቤት ገብተው የሐዋርያትን ሥርዐትና የቅዱሳት መጻሕፍትን
ትርጓሜ በሚገባ ተምረዋል፡፡

በዘመናቸው የሃይማኖት ስደት ስለነበር አባታቸው ፍተ ድንግል ስለ ሃይማኖታቸው በዐላውያን ሰማዕት


ኹነው ሲገደሉ አቡነ ብስጣውሮስ የአባታቸውን ዐፅም ይዘው በመሸሽ ወደ ላስታ ኺደው በእመቤታችን
ስም በተሠራች ገዳም በደብረ ዠመዶ ወስደው ቀበሯቸው፡፡ በኋላ በዐፄ ፋሲል ዘመን ሃይማኖት ሲመለስ
ዐፅማቸውን አፍልሰው አምጥተው አገራቸው ቀብረዋቸዋል፡፡ ከዚኽም በኋላ እናታቸው በግድ ሚስት
ዐጭተውላቸው የነበረ ቢኾንም ብዙ ሳይቆዩ ሚስታቸው ስለሞተች ቀድሞም የተመኙትን የምንኵስና
ሕይወት ለመኖር ወሰኑ፡፡

አንድ ቀን አንዱ የደብረ ሐይቅ መነኲሴ የገዳሙን ምርት ገበያ ለመሸጥ ይዘው እንደኼዱ አንድ ቀማኛ
ወንበዴ አግኝቶ ሊቀማቸው ሲል አቡነ ብስጣውሮስ ደርሰው አዳኑት፡፡ መነኵሴውንም ወደ ቤታቸው
ወስደው በመልካም መስተንግዶ አሳደሯቸው፡፡ መነኵሴውም በዚያች ሌሊት ስለ አቡነ ብስጣውሮስ
ብዙ ነገር ከተመለከቱ በኋላ አቡነ ብስጣውሮስን ስለ ምንኵስና አስተማሯቸው፡፡ መነኵሴው በማግስቱ
ሲኼዱ ወደ ሐይቅ አቡነ ኢየሱስ ሞአ ገዳም መጥተው እንዲጎበኟቸውና እንዲባረኩ ነግረዋቸው ኼዱ፡፡
አቡነ ብስጣውሮስም እግዚአብሔር መንገዳቸውን ይመራቸው ዘንድ ብዙ ከጸለዩ በኋላ ወደ ሐይቅ ገዳም
ገቡ፡፡

ገጽ| 5
Gädlä Bestawros (ገድለ ብስጣውሮስ)

በገበያ ያገኘውና በቤቱ ያሳደረውም መነኵሴ ሲያያቸው ደስ ተሰኝቶ የገዳሙ አበምኔት ዐቃቤ ሰዓት አባ
ዘወልደ ክርስቶስ ዘንድ ወሰዳቸው፡፡ አበምኔቱም አቡነ ብስጣውሮስን ገና እንዳዩአቸው ጸጋ
እግዚአብሔር እንዳደረባቸው ተመልክተው በጣም ደስ ተሰኙ፡፡ አቡነ ብስጣውሮስም መመንኰስ
እንደሚፈልጉ ለአበምኔቱ ሲነግሯቸው አበምኔቱ "የምንኵስና ሥራ ቀላል አይምሰልህ፤ ብዙዎች ወደ
እኛ መጡ ነገር ግን መታገስ ተስኗቸዋል፡፡" በማለት የምንኵስና ሕይወት ከባድ ፈተና እንዳለበት
ነገሯቸው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ብስጣውሮስም "በልዩ ልዩ ዐይነት ፈተናዎች ፈትኑኝና ሥራዬን ካዩ
በኋላ ያመነኵሱኛል" አሏቸው፡፡ ከዚኽም በኋላ አቡነ ብስጣውሮስ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት
እየተጋደሉ ገዳሙን በጉልበት ሥራ ብዙ ካገለገሉ በኋላ ከገዳሙ አበምኔት ከዐቃቤ ሰዓት አባ ዘወልደ
ክርስቶስ እጅ ምንኵስናን ተቀበሉ፡፡ ተጋድሎአቸውንም ከበፊቱ ይበልጥ በማብዛት መኖር ጀመሩ፡፡

እናታቸውም የልጃቸውን መመንኰስ ሰምተው ወደ ሐይቅ መጡ ነገር ግን አቡነ ብስጣውሮስ እናታቸውን


ወጥተው ላለማየት ተሠወሩ፡፡ አበምኔቱም በብዙ ፍለጋ አግኘተዋቸው "ልጄ እናትኽ አንተን ለማየት
ከሩቅ አገር መጥታለችና ኼደኽ አግኛት፡፡" ሲሏቸው አቡነ ብስጣውሮስም "አባቴ ሆይ ጌታችን
በወንጌል ያለውን አያስታውሱምን? "እነሆ እናትኽና ወንድሞችኽ በውጭ ቁመዋል ባሉት ጊዜ ጌታችን
በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ ከሚፈጽም በቀር እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?"
ብሎ ተናግሮ የለምን? ስለዚኽ ወደ እናቴ አልኼድም" ብለው ለአበምኔቱ መለሱላቸው፡፡ አበምኔቱም
"ከመንገዱ ርቀት የተነሣ እናትኽ በብዙ ድካም መጥታለችና ልታያት ይገባል" ብለው ግድ አሏቸው፡፡
አቡነ ብስጣውሮስም ኺደው እናታቸውን ካገኟቸው በኋላ እናታቸውም በዛው መንኵሰው በባሕሩ ዙሪያ
ካለው ከሴቶች ገዳም ገብተው ማገልገል ዠመሩ፡፡

አቡነ ብስጣውሮስ ከመልካም የጉልበት ሥራ ጋራ ቀን ቀን የዳዊትን መዝሙር፣ የነቢያትን መጻሕፍትና


መሐልየ መሓልይን ሲደግሙ ይውላሉ፤ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ገብተው እጅግ አብዝተው ሲጸልዩ
የብርሀን ዐምድ ተተክሎ ይታይ ነበር፡፡ ጸሎታቸውንም ሲዠምሩ ሰማያት ይከፈቱ ነበር፡፡ ቅዱሳን
መላእክትንም ሲወጡ ሲወርዱ ያዩአቸዋል፡፡ አቡነ ብስጣውሮስ በእንደዚኽ ዐይነቱ ተጋድሎ ብዙ
ሲያገለግሉ ዜና ትሩፋታቸው በኹሉ ዘንድ በዓለም ተሰማ፡፡ አስተዳዳሪው ዐቃቤ ሰዓቱ አቡነ ዘወልደ
ክርስቶስም እርጅና ሲጫናቸው ማኅበሩን ሰብስበው "በእኔ ቦታ አባት የሚኾናችኹን ምረጡ" አሏቸው፡፡
እነርሱም "እግዚአብሔር ያመለከተኽን አንተ ሹምልን" አሏቸው፡፡ አባ ዘወልደ ክርስቶስም በጸሎት
ከጠየቁ በኋላ "እግዚአብሔርና እኔ አባት ይኾኑላችኹ ዘንድ አቡነ ብስጣውሮስን መርጠንላችኋል"
አሏቸው፡፡ ቀጥሎ አበምኔቱ ስለ አቡነ ብስጣውሮስ እንዲኽ በማለት ትንቢት ተናገሩ፡- "እርሱ
ሃይማኖቱ የቀና ምግባሩ ያማረ በተጋድሎም የጸና በጸሎቱ አገርን ይጠብቃል፣ ድንቅ ድንቅ ተኣምራትን

ገጽ| 6
Gädlä Bestawros (ገድለ ብስጣውሮስ)

በነገሥታቱና በመኳንንቱ ፊት ያደርጋል" እያሉ ለማኅበሩ በነገሯቸው ጊዜ እጅግ ደስ ተሰኙ፡፡ አቡነ


ብስጣውሮስ ግን ይኽን ሲሰሙ የመረረ ልቅሶን አለቀሱ፤ ከእነርሱም ዘንድ ይሸሹ ዘንድ ወጥተው
በመርከብ ተጭነው ኼዱ፡፡ ነገር ግን ደርሰው ይዘው በእግዚአብሔር ፈቃድ ይሾሟቸው ዘንድ ይዘው
አሰሯቸው፡፡ በዚኽም ጊዜ ከሰማይ "ብስጣውሮስ የአባትኽን የአበምኔቱን ቃል አታስተሐቅር" የሚል
ቃል ተሰማ፡፡ ማኅበሩም ይኽንን ከሰማይ የመጣውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ተደስተው እግዚአብሔርን
አመሰገኑ፡፡ ከዚኽም በኋላ አቡነ ብስጣውሮስን እንደ ሕጋቸውና እንደ ሥርዐታቸው የሐይቅ እስጢፋኖስ
ገዳም አበምኔትና ዐቃቤ ሰዓት በማድረግ ሾሟቸው፡፡

አቡነ ብስጣውሮስም በአቡነ ኢየሱስ ሞአ ወንበር በተቀመጡ ጊዜ የተሰወረውን ኹሉ የሚያዩ ኾኑ፡፡


ፊታቸውም እንደ ጨረቃ የሚያበራበት ጊዜ ነበር፣ ለአገልግሎትም ወደ ቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ ቅዱሳን
መላእክት ክንፋቸውን እየጋረዱ ይቀበሉት ነበር፡፡ ጻድቁ ጸሎተ ዕጣን ሲያሳርጉ እያለቅሱ ነበር፤
የጌታችንን መከራ እያሰቡ ሰውነታቸውን በድብቅ ይገርፋሉ፤ ድኆችንና ጦም ዐዳሪዎችን ኹሉ
የሚንከባከቧቸው አባት ኾኗቸው፡፡ ገዳሙንም አፍርሰው ሊዘርፉ የመጡትን ወራሪዎች አባታችን ወደ
መቅደስ እየገቡ በጸሎት እያሰሯቸው አሳፍረው ይመልሷቸው ነበር፡፡

አቡነ ብስጣውሮስ በእንዲኽ ዐይነት ተጋድሎ ገዳሙንና አገራችንን እየጠበቁ ሲኖሩ በመኻል የቅብዐት
እምነት ነገር በገዳሙ ተነሣ፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንን አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን
"ከትስብእት ጋራ ከተዋሐደ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ተቀባ፣ በዚኽም ቅብዐት በጸጋ ልጅ፣ ንጉሥም፣
ነቢይም፣ ሊቀ ካህናትም ተባለ" የሚሉ ከሓድያን ተነሡና የእግዚአብሔር ሰው ብፁዕ አባታችን
ብስጣውሮስ ይኽንን የክሕደት ትምህርት ሰምተው እጅግ እያዘኑና እያለቀሱ የካዱትን ሰዎች በብዙ
ምሳሌ እያደረጉ ማስተማር ዠመሩ፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዐት በጸጋ ልጅ
እንዳልኾነ፣ ነገር ግን በባሕርይው የአብ ልጅ እንደኾነ፣ እርሱ ራሱ ቅብ፣ እርሱም ራሱ ቀቢ፣ እርሱ
ራሱ ተቀቢ እንደኾነ በብዙ ምሳሌ እያደረጉ የቀደሙ የአባቶቻችንንም ትምህርት ኹሉ እየጠቀሱ
አስተማሯቸው፡፡ ነገር ግን ሰይጣን አንድጊዜ አስክዷቸዋልና አንዳንዶቹ እምቢ አሏቸው፡፡ በዚኽም
ጊዜ ሐዋርያት ከመሠረቷት አንዲት ቤተ ክርስቲያን አውግዘው ለዩአቸው፤ ቤተ ክርስቲያንም ሰላም
ኾነች፡፡ በዚኽም አባታችን ከሓድያንን የሚዘልፉ ዳግማዊ ቄርሎስ ተባሉ፡፡ ይኽም ክሕደት መዠመሪያ
ሰይጣን ለጳውሎስ ሳምሳጢን ያስተማረው ነው፡፡ ጳውሎስ ሳምሳጢን በገዳም ቅጠል እየበላ የሚኖር
ተሐራሚ መናኝ ነበር፡፡ በጾም በጸሎት ሲኖር ሰይጣን ራሱን ሰውሮ መጥቶ ተገለጠለትና "ጸሎትኽ
በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰምቶልሃል፤ ነገር ግን አምላክ ያለሩካቤ በድንግልና የተወለደ አይምሰልኽ
በሩካቤ ተወለደ እንጂ፤ ይኽም ልጅ ደግ ሰው ኾነ፣ በ30 ዘመኑ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፣

ገጽ| 7
Gädlä Bestawros (ገድለ ብስጣውሮስ)

መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ተቀመጠ፣ ያን ጊዜም ይኽ ሰው በጸጋ የሥላሴ ልጅ ኾነ"
ብሎ አስተማረው፡፡ ጳውሎስ ሳምሰጢንም ሰይጣን የነገረውን ነገር በልቡ አምኖ ለደቀ መዝሙሩ
ለተያስሮስ አስተማረው፡፡ ተያስሮስም ለድያድርስ አስተማረው፡፡ ድያድርስም ለንስጥሮስ
አስተማረው፡፡ ንስጥሮስም ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንን አምላካችንን "መንፈስ
ቅዱስ ያደረበት ዕሩቅ ብእሲ ነው" ብሎ ለልዮንና ለመርቅያን አስተማራቸው፡፡

ንስጥሮስ ይኽን ዐዲስ የክሕደት ትምህርት እንዳመጣ በሰሙ ጊዜ 200 ኤጲስ ቆጶሳት በቅዱስ ቄርሎስ
ዘእስክንድርያ መሪነት በኤፌሶን ተሰብስበው ሲያስተማሩት እምቢ ቢላቸው አውግዘው ለዩት፡፡
ንስጥሮስም ሰውነቱ መግሎ ክፉ አሟሟት ሞተ፡፡ በኋላም መርቅያን ሲነግሥና ልዮንም የሮም ሊቀ
ጳጳስ ሲኾን ኹለቱም አባታቸው ንስጥሮስ ያስተማራቸውን ሃይማኖት ማስፋፋት ቻሉ፡፡ እነ ልዮንም
ንስጥሮስ በተወገዘበት ጉባኤ ላይ የነበሩትና አኹን ለሥጋቸው የፈሩ አባቶችን ይዘው ከንስጥሮስ ክሕደትና
ከቅዱስ ቄርሎስ ትምህርት አወጣጥተው የራሳቸውን የረከሰ ሃይማኖታዊ ድንጋጌ አወጡ፡፡ "ክርስቶስ
ኹለት አካል ነው፣ አንዱ የማርያም ልጅ አንዱ የእግዚአብሔር ልጅ በመቀራረብ አንድ ኾኑ ያለውን
አውጥተው ከቅዱስ ቄርሎስም ቃልና ከንስጥሮስ ክሕደት ቀላቅለው መለኮት የመለኮትን ሥራ ይሠራል፣
ትስብእትም የትስብእትን ሥራ ይሠራል፤ በኹለት መንገድ አንዱ ተኣምራትን ያደርጋል ኹለተኛው
መከራን ይቀበላል፤ ስለዚኽም ትስብእት ከመለኮት ያንሳል" ብለው ጻፉ፡፡ ይኽንንም የክሕደት
ጽሕፈታቸውን ለቅዱስ ዲዮስቆሮስ ላኩለት፡፡ እርሱም ኺዶ ከክሕደታቸው እንዲመለሱ
አስተማራቸው፡፡ "በአንዱ ክርስቶስ ላይ ለምን የኹለትነት ነገር ትናገራላችኹ? ወደ ሰርግ ቤት ተጠርቶ
የኼደው ውሃውንም የወይን ጠጅ ያደረገው እርሱ አንዱ ክርስቶስ ነው…" እያለ በብዙ ምሳሌ
ካስተማራቸው በኋላ ልዮንንና መርቅያን የጻፉትን የክሕደት ጽሕፈት በፊታቸው ቀደደው፡፡ እነርሱ ግን
አንድ ጊዜ ክደዋልና የቅዱስ ዲዮስቆሮስን ፂሙን ነጭተው ጥርሱን አውልቀው ብዙ አሰቃዩት፡፡
እርሱም የነጩትን ፂሙንና ያወለቁትን ጥርሱን ሰብስቦ "እነሆ የሃይማኖቴን ፍሬ ተቀበሉ" ብሎ
ለእስክንድርያ ክርስቲያኖች ላከላቸው፡፡ ከሓድያኑም ወደ ጋግራ ደሴት አጋዙትና በዚያው ዐረፈ፡፡

ሰይጣን ለመዠመሪያ ጊዜ ለጳውሎስ ሳምሳጢን ያስተማራትን ያችን ክሕደት በእንደዚኽ ዐይነት ኹኔታ
ሰይጣን የሚያድርባቸው ሰዎች እየተቀባበሏት እስከ ንስጥሮስንና እስከ ልዮን ድረስ ከደረሰች በኋላ
የልዮን ልጅ በኾነው በአውፍንስ አማካኝነት በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን ለመዠመሪያ ጊዜ ወደ አገራችን
ኢትዮጵያ ገባች፡፡ አውፍንስም ክሕደቱን ለኹለት የአገራችን መነኰሳት አስተማራቸው፡፡ ለአንደኛው
"ወልድ ሦስት ልደት አለው፣ በመዠመሪያ ከአብ ተወለደ፤ ዳግመኛም በመንፈስ ቅዱስ ሥጋ ከድንግል
ተወለደ፤ ሦስተኛም በቤተልሔም ተወለደ" ብሎ ካስተማረውና ካስካደው በኋላ ስሙን "ተክለ ሃይማኖት"

ገጽ| 8
Gädlä Bestawros (ገድለ ብስጣውሮስ)

ብሎ ጠራው፡፡ ኹለተኛውንም መነኵሴ ለብቻው ጠርቶት "ልጄ ሆይ ስማኝ ልብ አድርገኽም ዕወቅ፣


ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዐት የከበረ ነው፣ ይኸውም ሳይዋሐድ ማደር ነው" ብሎ ካስተማረውና
ካስካደው በኋላ ስሙን "ኤዎስጣቴዎስ" ብሎ ጠራው፡፡ እነዚኽም የካዱ ኹለቱ መነኰሳት በየአገሩና
በየአውራጃው እየዞሩ አገራችን ኢትዮጵያን በክሕደት ትምህርታቸው አጥፍተዋት ነበር፤ ነገር ግን ብዙ
ቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ይኽን ክሕደት በትምህርታቸውና በተኣምራታቸው እንዲገታ
አድርገውታል፡፡

አቡነ ብስጣውሮስም እነዚያን ከሓዲዎች አውግዘው ለዩአቸው፡፡ ከዚኽም በኋላ ከሓድያኑ አባታችንን
ከሰሷቸውና ከጐንደሩ ንጉሥ ጋራ አጣሏቸው፡፡ ንጉሡም የእነዚያን ከሓዲዎች እምነት አምኖ ተቀብሎ
ነበርና አባታችንን ወደ ጐንደር እንዲያመጧቸው ጭፍሮቹን ላከ፡፡ አቡነ ብስጣውሮስም ነገሩን ዐውቀው
ስለ ቀናች ሃይማኖት ይመሰክሩ ዘንድ አንደበት እንዲኾናቸው ጌታችንን በጸሎት ሲጠይቁ ጌታችንም
"ልጄ ብስጣውሮስ ሆይ አይዞኽ እኔ ከአንተ ጋራ ነኝ፣ እኔ ስለመሠረትኳት አንዲት ሃይማኖት ጽና"
አላቸው፡፡ አባታችንም ወደ ንጉሡ ዘንድ ኼዱና ንጉሡ ሰዎቹን ስለማውገዙ ጠየቃቸው፡፡ አባታችንም
ንጉሡን ስለ ቀናች ሃይማኖት እየመሰከሩለት አስተማሩት፡፡ ንጉሡም በብዙ ስጦታና ሽንገላ
ሊያታልላቸው ሞከረ ነገር ግን አባታችን አጥብቀው ተቃወሙት፡፡ ንጉሡም ዕውቀታቸውንና
ጽናታቸውን ባየ ጊዜ አባታችንን በእግር ብረት አሳስሮ እስር ቤት ውስጥ ጣላቸው፡፡ በዚኽም ጊዜ
የእግር ብረቱ እንደሰም ቀልጠ፡፡ ወታደሮቹም ይኽንን ተኣምር ዐይተው ፈርተው ኼደው ለንጉሡ
ነገሩት፡፡ ንጉሡም ሰምቶ ደነገጠ፤ እየፈራና እየተንቀጠቀጠ ወደ አባታችን መጥቶ ሰገደና "አባቴ ሆይ
ይቅር በሉኝ የሃይማኖትንም ነገር እንደገና አስተምሩኝ" አላቸው፡፡ እሳቸውም አስተምረው ባረኩት፡፡
በመከራቸውም ታግሰው ለልጆቻቸውና ለእኛም የሐዋርያትን ሃይማኖት አጸኑልን፡፡ እድሜአቸውም 90
ዓመት በኾነው ጊዜ ዕረፍታቸው እንደደረሰ ዐውቀው የቀናች ሃይማኖት በአገራችን ለዘለዓለም ጸንታ
ትኖር ዘንድ ጌታችንን አጥብቀው ለመኑት፡፡ ጌታችንም በደሙ የመሠረታት የቀናች ሃይማኖት
በአገራችን ጸንታ እንደምትኖርና ሌላም የምሕረት ቃል ኪዳን ከገባላቸው በኋላ ግንቦት 19 ቀን ዐረፉ፡፡
ይኽ የታሪካቸው መተታሰቢያም በስንክሳር ላይ ታስቧል፡፡

በዚያች ዕለትም ሐይቅ አለቀሰች፤ የሐይቅም ባሕር ሦስት ዓመት በኀይል ስትታወክ አቡነ አላኒቆስ ይኽ
ኹሉ የኾነው ስለ አባታችን ስለ ብስጣውሮስ ማረፍ መኾኑን ዐውቀው ወደ ንጉሡ ኼደው የአባታችንን
ዐፅም እንዲሰጣቸው ጠየቁት፡፡ ንጉሡ ግን "በረድኤታቸው ይጠብቁኛልና አልሰጥም" አላቸው፡፡
ንጉሡ ስለከለከላቸው አቡነ አላኒቆስም ቊስቋም ወደምትባል በወርቅና በከበረ ዕንቁ ወደተሸለመች ወደ
እመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ኼደው በእመቤታችን ሥዕል ሥር ወድቀው አለቀሱ፡፡

ገጽ| 9
Gädlä Bestawros (ገድለ ብስጣውሮስ)

ሥዕሏም በሰው አንደበት አናግራ ካጽናናቻቸው በኋላ የአባታችን ዐፅም ከመሠዊያው በስተቀኝ በኩል
እንደሚገኝ ነገረቻቸው፡፡ አቡነ አላኒቆስም ዐፅማቸውን አፍልሰው ወደ ሐይቅ በተመለሱ ጊዜ የመዓዛው
ሽታ የንጉሡን አገር ኹሉ መላው፤ መቃብሩ በነበረበት ቦታም የብርሀን ዐምድ ተተክሎ ታየ፡፡ ንጉሡም
መነኵሴው የአባታችንን ዐፅም እንደወሰዱ ባወቀ ጊዜ መነኵሴውን ይዘው ከአባታችን ዐፅም ጋራ
ያመጡለት ዘንድ ብዙ ፈረሰኛ ወታደሮቹን ላካቸው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በጥበቡ ሰውሯቸዋልና
አቡነ አላኒቆስን ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡ አቡነ አላኒቆስም የቅዱስ አባታችንን ዐፅም ወስደው በሐይቅ
በመሠዊያው በስተቀኝ በኩል በቀበሩት ጊዜ በፊት ያስቸግር የነበረው የባሕሩ ኀይለኛ ንውጽውጽታ
በአንድ ጊዜ ጸጥ አለ፡፡ ሌላም ብዙ ተኣምራት ተደርገው ታዩ፡፡ ይኸውም ፍልሰተ ዐፅማቸው የካቲት
8 ቀን የተፈጸመ ነው፡፡

እንግዲኽ ከመጣጥፉ አንደምናነበው የገድላቸው ታሪክ ከብዙው በጥቂቱ ይኽን ይመስላል ይዘቱ፡፡

፪.፪) የመጣጥፉ ጠቀሜታ: -


ይኽ የዶ/ር አምሳሉ ተፈራ መጣጥፍ በዋነኘነት አራት ዐበይት ጠቀሜታዎች ይኖሩታል ተብሎ
ይታሰባል፤ እኒኽም፡-

- ለገድላት ትምህርት ጥናት፤


- ለቤተ ክርስቲያን ታሪክና የድርሳናት ትምህርት ጥናት (ለኢትዮጵያ ታሪክ)፤
- ለግእዝ ቋንቋ ትምህርት ጥናት (የቋንቋውን ሰዋስዋዊ አካኼድ ለመቃኘት)፤
- ለሥነ ጽሑፍ ትምህርት ጥናት (የሥነ ጽሑፉን ውበት ለመመርመር)፤

፫ ማጠቃለያ፡-

ይኽ መጣጥፍ የቅዱስ ብስጣውሮስን ዜና ሕይወት በስፋት ስላያዘ በታሪካችንና በሥነ ጽሑፋችን ላይ


አንድ ክፍተትን ይቀርፋል፤ ይሞላል ብሎ ተማሪው ያምናል፤ የሥነ ጽሑፉ ውበትና የታሪክ ፍሰት
ገጽታው ብዙ ቢኾንም ለተሻለ ምርምርና ጥናት የሚጋብዝ ነው፡፡ ገድሉ የተለያዩ ጠቃሚ ገጽታዎች
ቢኖሩትም በተለይ ታሪካዊ ክሥተቶች ላይ ያተኮረው የቅዱሱ ታሪክ ቀልብን ይስባል፤ በጊዜው
በኢትዮጵያ ውስጥ ስለተከሠተው ሃይማኖታዊ ክርክሮችና ውዝግቦች በሚገባ ይናገራልና፡፡

ስምዐት (ዋቢ መጻሕፍት)


Aethiopica 13 (2010) International Journal of Ethiopian and Eritrean Studies AMSALU
TEFERA, Addis Ababa University Gadla Bastawros Aethiopica 13 (2010), 7-45 ISSN: 1430-
1938 Published by Universität Hamburg Asien Afrika Institut, Abteilung Afrikanistik und
Äthiopistik Hiob Ludolf Zentrum für Äthiopistik

ገጽ| 10

You might also like