Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 39

የመጽሐፍ

ቅዱስ
ጥናት
( አምስተኛ ክፍል)

በአቃቂ መንበረ ሕይወት


መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን
ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት
ቤት ትምህርት ክፍል የተዘጋጀ

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
1
የሚሰጠው የትምህርት ርዕስ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ከተሞችና ሀገሮች

የዕለቱ ጥቅስ፦ “ . . . ከተማም ሠራ። የከተማይቱንም ስም በልጁ ስም ሄኖሕ አላት”ዘፍ 4፥


16-17

ምዕራፍ ስድስት

1 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የውሃ አካላት እና የየብስ ምድር

1.1 ባሕሮች

በሀገረ እስራኤል ሁለት ታላላቅ ባሕሮች ይገኛሉ። አንደኛው የገሊላ ባሕር ሲሆን ሁለተኛው
ደግሞ ሙት ባሕር ነው።

የገሊላ ባሕር

ዛሬ ጥብርያዶስ እየተባለ የሚጠራው ነው። ዮሐ 21፥1 የጌንሳሬጥ ባሕርም ይባላል። ማቴ


4፥18 ፣ ሉቃ 5፥1 ጥብርያዶስ እና ጌንሳሬጥ በባሕሩ ወደብ የሚገኙ ከተሞች ናቸው።
ሄሮድስ አንቲጳስ በገሊላ ባሕር ምዕራባዊ ዳርቻ ከተማ ከመሠረተ በኋላ በጢባርዮስ ቄሣር
ስም ጥብርያዶስ ብሎ ሰየማት። የባሕሩ ርዝመት 4.5 ኪ.ሜ ሲሆን ወርዱ ደግሞ 8 ኪ.ሜ
ነው። የባሕሩ ጥልቀት በአማካይ ከ208.5 ሜትር እስከ 213 ሜትር ከባሕር ጠለል በታች
ነው። የመጨረሻው ጥልቅ ቦታ ግን ከባሕር ጠለል በታች እስከ 254 ሜትር ይጠልቃል።
በባሕር ውስጥ 25 የዓሣ ዓይነቶች ስለሚገኙ በዓሣ ምርት የታወቀ ነው። በዚህ ባሕር ላይ
ጌታችን ለማስተማር ብዙ ጊዜ ተመላልሷል። ብዙ ተአምራትንም አድርጎበታል።

 የጴጥሮስን መረብ እስኪቀደድ ድረስ በዓሣ ሞልቶታል። ሉቃ 5፥1-11 ዓሣው


በባሕሩ ውስጥ እያለ የእነ ስምዖን ጴጥሮስ መረብ ግን ባዶ ሆነ። ጌታችን
ሲመጣ ግን ዓሣና መረብ ተገናኙ። እግዚአብሔር ያልገባበት ኑሮና ሥራ ሁሉ
እንዲህ ነው። ገንዘብ ይዞ መራብ፣ መታመምና መሰቃየት ይኖራል።
እግዚአብሔር ግን ጥቂቱ ይበዛል። የተጣላው ይታረቃል፤ የተራራቀው
ይቀራረባል።

ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚህ ባሕር በታንኳ ሲጓዝ ተነሥቶ የነበረውን የማዕበል
ንውጽውጽታ ጸጥ አድርጎታል። ማቴ 8፥23 ለአምላክነቱ አልገዛም የሚል ፍጥረት የለምና።
ጌታችን በባሕሩ ላይ በእግሩ ተራምዷል። ማቴ 14፥22-23 ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታችን ታዝዞ
ለተጠየቁት ግብር የሚከፍሉትን ሁለት እስታቴር ያገኘበትን ዓሣ አጥምዶ ያወጣው በዚህ

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
2
ባሕር ነው። ማቴ 17፥24-27 በዚህ ባሕር አጠገብ ጌታችን ከትንሣኤ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ
ተገልጧል። ያጡትንም ዓሣ ሰጥቷቸዋል። አብሯቸውም ተመግቧል። ዮሐ 21፥1-14 ቅዱስ
ጴጥሮስ “ግልገሎቼን አሠማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሠማራ” የተባለው በገሊላ ባሕር
አጠገብ ነው። ዮሐ 21፥15-17

ሙት ባሕር

ጨው ይበዛበታልና “ጨው ባሕር” ተብሏል። ከባሕሩ 3 ኪሎ ውኃ ውስጥ 1 ኪሎ ጨው


ይወጣል። “ሙት ባሕር” ይባላል። የባሕሩ ዙሪያ በድኝና በቅጥራን (ዝፍት) የተከበበ ስለሆነ
ሕይወት ያለው ነገር ፈጽሞ አይገኝበትም። ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ በኢያሪኮ
በስተደቡብ የሚገኝ ባሕር ነው። 88 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። ከባሕር ወለል በታች
467 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ታች እየወረደ ነው ይባላል። “ባሕረ
ሎጥም” ይባላል። ሰዶምና ገሞራ ከመጥፋታቸው በፊት የብስ የነበር ቦታ ነበር። ዘፍ 19፥
1-29 የዮርዳኖስ ወንዝ በየቀኑ 6 ሚሊዮን ቶን ውኃ ለባሕሩ ይገብራል። ሌሎችም ወንዞች
ወደ ባሕሩ የሚገብሩ አሉ።

ባሕረ ኤርትራ

እስያና አፍሪካን የሚለያይ ባሕር ነው። ርዝመቱ 2175 ኪ.ሜ ሲሆን ስፋቱ ደግሞ
370 ኪ.ሜ ነው። በአንዳንድ ቦታዎች የ1830 ሜትር ጥልቀት አለው። ወደ ባሕሩ የሚገባ
ምንም ዓይነት ወንዝ የለም። እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ ሲወጡ በዚህ ባህር ውኃው
እንደ ግንብ ቆሞ መሀሉ ደረቅ መሬት ሆኖ ተሻግረው ሀገራቸው ገብተዋል። ዘጸ 14፥15-31

በባሕረ ኤርትራ እና በሜዲትራንያን መካከል የስዊዝ ቦይ (Suez Canal) በመባል የሚታወቅ


ሰው ሠራሽ ልሳነ ምድር ይገኛል። ይህም ግብጽና እስራኤልን በደረቅ መሬት የሚያገናኘው
ቦታ ነው።

1.2 ወንዞች

ወንዝ ማለት ከአንድ ቦታ ተነሥቶ ወደ ሌላ ስፍራ የሚፈስ (ፈሳሽ) ውኃ ነው። ሁለት


ዓይነት ወንዞች አሉ። ክረምት ከበጋ የማይደርቁ ወንዞች እና በዝናብ ጊዜ ብቻ የውኃ ፈሳሽ
የሚገኝባቸው ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የታወቁ ወንዞች አሉ። እነዚህ ወንዞችም
በእስራኤል ምድርና መጽሐፍ ቅዱስ በሚያነሣቸው ሀገሮች ይገኛሉ።

የዮርዳኖስ ወንዝ

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
3
ከአርሞንኤም ተራራ ግርጌ ተነሥቶ በገሊላ ባሕር በማለፍ ወደ ጨው ባሕር ይፈሳል።
የወንዙ ስፋትና ጥልቀት እንደ ዝናቡ መጠን ይለዋወጣል። ይኸውም ከአንድ ሜትር እስከ
ሦ ስት ሜትር ጥልቀትና እስከ ሠላሳ ሜትር ስፋት የሚደርስበት ወቅት ይኖራል። በዮርዳኖስ
ወንዝ በተለያዩ ጊዜያት ገቢረ ተአምራት ተፈጽመውበታል።

 የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሲገቡ የሞላው ውኃ


ከሁለት ተከፍሎ በሩቅ በመቆሙ እስራኤል በኢያሱ መሪነት በደረቅ ተሻገሩ።
 ነቢዩ ኤልያስም በመጎናጸፊያው ከፍሎት ተሻግሯል። 2ኛ ነገ 2፥8
 ነቢዩ ኤልሳዕም በኤልያስ መጎናጸፊያ ከፍሎት ተሻግሯል። 2ኛ ነገ 2፥14
 ንዕማን የተባለ የሶርያ የሠራዊት ዓለቃ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ከለምጽ
ነጽቷል። 2ኛ ነገ 5፥10-14
 ታላቁ የእግዚአብሔር ሰው ኢዮብ በሰውነቱ ላይ ከወጣበት ደዌ የተፈወሰው
በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ነው።
 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ አርአያ ሊሆነንና የጥምቀትን ሥርዓት ሊሠራልን
ምስጢረ ሥላሴንም ሊገልጥልን የተጠመቀው በዚህ ወንዝ ነው። ማቴ 3፥13-17

ግዮን

በኢትዮጲያ የሚገኝ ወንዝ ነው። የጣናን ሐይቅ ከሁለት ከፍሎ ይጓዛል። በተለያዩ የመጽሐፍ
ቅዱስ ክፍሎች የዓባይ ወንዝ ተብሎ ተጠቅሷል። ኢሳ 19፥7-8 ፣ 23፥3 በበረሃማው የግብጽ
ምድር የዓባይ ወንዝ የሚያልፍበት ቦታ ሁሉ ለምለም ነው። ሱዳንና ግብጽን አጠጥቶ ወደ
ሜዲትራንያን ባሕር ይገባል። ከመነሻው እስከ መድረሻው ያለው ርቀት 6470 ኪሎ ሜትር
ያህል ነው። የሙሴ ወላጆች ከፈርዖን ትእዛዝ የተነሣ ሙሴ እንዳይሞትባቸው ከዓባይ ወንዝ
ዳር ሸሽገውታል። ዘጸ 2፥1-10 ፈርዖን እስራኤልን አልለቅም ብሎ ልቡን ባጸናበት ወቅት
ከእግዚአብሔር በታዘዘው መሠረት በግብጽ ምድር ብቻ የዓባይ ውኃ ወደ ደምነት ተቀየረ።
ዘጸ 7፥20-21

ተግባር

1. አዛርያ የምትባለው ከተማ የት ትገኛለች?


2. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ፋጌ በተባለችው ከተማ ምን አደረጋ?
3. በመሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱትና ከእስራኤል ምድር ውጪ የሆኑ አምስት ከተሞችን
ከነታሪካቸው አቅርባችሁ ተወያዩባቸው።
4. ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ያረፉት በየት ከተማ ነው?
5. በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ብዙ ተአምራት የተፈጸመበት ወንዝ የትኛው ነው።
6. በግዮን ወንዝ የተፈጸሙ ታሪኮችን አስረዱ

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
4
የሚሰጠው የትምህርት ርዕስ፦ ተራሮች፣ ሜዳዎች፣ ምንጮች፣ ዋሻዎች

የዕለቱ ጥቅስ፦ “ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ማን ይሰጠኛል?” 1ኛ ዜና 11፥15-19

1.3 ተራሮች

ተራራው ከሜዳውና ከደልዳላው መሬት ከፍ ያለ የመሬት ክፍል ነው። በመጽሐፍ ቅዱስም


ብዙ ተራሮች ተጠቅሰው ይገኛሉ።

1. ደብረ ሲና
ደብር ማለት ተራራ ማለት ነው። ደብረ ሲና ማለት የሲና ተራራ ማለት ነው። ኮሬብ
እየተባለም ይጠራል። ዘጸ 3፥1 ፣ ዘዳ 4፥9-10 የእግዚአብሔር ተራራም ይባላል። ዘጸ
3፥1 ፣ 1ኛ ነገ 19፥8 ከግብጽ በስተምሥራቅ ከእስራኤል ደግሞ በስተደቡብ ይገኛል።
እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጠለት በዚህ ተራራ ነው።
ዘጸ 3፥2-12 እግዚአብሔር በሙሴ በትር አማካኝነት ከዓለት ውኃ አፍልቆ ለሕዝበ
እስራኤል ያጠጣው በኮሬብ ተራራ አጠገብ ነው። ዘጸ 17፥5-7 እግዚአብሔር በዚህ
ተራራ ለሙሴ በደመና በነጎድጓድና በመብረቅ ተገልጦለታል። ዘጸ 19፥16-25
በሁለት የድንጋይ ጽላት የተጻፉት ዐሠርቱ ትእዛዛት ለሙሴ የተሰጡት በዚህ ተራራ
ነው። ዘጸ 34፥28 ለሁለተኛ ጊዜ ጽላቱን ለመቀበል ወደ ተራራው ወጥቶ አርባ ቀንና
አርባ ሌሊት በጾም ቆይቷል። ዘጸ 34፥28 በዚህ ሥፍራ ግሪኮች “ቤተ ክርስቲያን”
ሠርተዋል።
2. ሞሪያ
ከኢየሩሳሌም ከተማ በስተምሥራቅ ይገኛል። አብርሃም በስተርጅና ያገኘውን ልጁን
ሊሠዋበት የሄደበት ተራራ ነው። ዘፍ 22፥2 ጠቢቡ ሰሎሞንም በዚህ ተራራ
ቤተመውደሱን እንደሠራ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። 2ኛ ዜና 3፥1
3. ደብረ ታቦር
ከገሊላ ባሕር በስተደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከናዝሬት
ደግሞ በስተ ምሥራቅ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ የሚገኝ ተራራ ነው። ከባሕር
ጠለል በላይ 572 ሜትር ከፍታ አለው። የዛብሎንን፣ የይሳኮርንና የንፍታሌምን ርስት
ያዋስናል። እንግልጣሮች (እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች) Transfiguration Mount
ይሉታል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን እንደገለጠበት
ሲያጠይቁ ነው። ዐረቦች ደግሞ ጀበል ቶር (Djebol Tor=Mountain of the bull)
ይሉታል። በዚህ ተራራ ባርቅና ዲቦራ የእስራኤል ጠላት ሆኖ የተነሣውን ሲሣራን
ድል አድርገውበታል። መሳ 4፥4-24 በልምላሜ የተሞላ ተራራ መሆኑ ይነገርለታል።
በሐዲስ ኪዳን ስሙ አይጠቀስ እንጂ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ረጅም

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
5
ተራራ የተባለው እርሱ ነው። ማቴ 17፥1-9 ፣ መዝ 88፥12 በዚህ ምክንያት ሊቀ
ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “ቅዱስ ተራራ” ብሎታል። 2ኛ ጴጥ 1፥18 በደብረ ታቦር
ግሪኮችና ላቲኖች (ሮማውያን) በ1923 ዓ.ም እ.ኤ.ዕ “ቤተ ክርስቲያን” ሠርተዋል።
4. ደብረ ዘይት
የዘይት ታራራ ማለት ሲሆን በወይራ ዛፍ የተሸፈነ በመሆኑ የተሰጠው ስያሜ ነው።
800 ሜትር ያህል ከባሕር ጠለል በላይ ከፍታ አለው። ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ
በቅርብ የሚገኝ ቦታ ነው። ጌታችን ቀን ቀን ኢየሩሳሌም ከተማ ሲያስተምር ውሎ
ወደ ማታ በደብረ ዘይት ተራራ በኩል ወደ አልዓዛር ቤት ቢታንያ ለማደር ይሄድ
ነበር። ማር 11፥19 ፣ ማቴ 21፥17 ከተራራው ግርጌም ቤተ ፋጌና ቢታንያ የሚባሉ
መንደሮች ይገኛሉ። ከፍታ ያለው ተራራ በመሆኑ ከጫፉ ላይ ሆኖ ኢየሩሳሌምን፣
ኤዶምያስን፣ ሞዓብንና አሞንን ማየት ይቻላል። ጌታችን ማታ ማታ ያድርበት የነበረ
ሲሆን ጥንት መቃብረ ነቢያት እንደነበር ይነገራል። ጌታችን ስለነገረ ምጽአት
ያስተማረው በዚህ ተራራ ነው። ማቴ 24፥3 ፣ 25፥31-46 ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም
ጌታችን በደብረ ዘይት ዓለምን ሊያሳልፍ እንደሚመጣ ተስፋ ታደርጋለች። ዘካ 14፥
4 ጌታችን በሆሳዕና ዕለት በአህያ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ከዚህ ተራራ ተዳፋት
ተነሥቶ ነው። ማር 11፥1 ጌታችን የተያዘውም ከተራራው ግርጌ በምትገኘው
ጌቴሴማኒ ነው። ማቴ 26፥30-36 ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣበትን የቤዛነት ሥራ
ከፈጸመ በኋላ ያረገው በዚህ ተራራ ነው። ሉቃ 24፥51-52 ፣ ሐዋ 1፥12 ዛሬ ግን
ቦታው በመሐመዳውያን እጅ ይገኛል። ጌታችን አቡነ ዘበሰማያትን (አባታችን ሆይ
የሚለውን ጸሎት) ያስተማረው በዚህ ሲሆን ዛሬ ግን በ35 ቋንቋዎች ጸሎቱ ተጽፎ
ይገኛል። ከእነዚህም ቋንቋዎች አንዱ ግእዝ ነው።
5. ደብረ ጽዮን
ጽዮን ማለት አምባ ማለት ነው። 770 ሜትር ከፍታ አለው። ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ
ምሥራቅ ከቄድሮስ ወንዝ በስተምዕራብ ይገኛል። ቅዱስ ዳዊት በዚህ ተራራ ላይ
ከተማ መሥርቶ ነበር። ታቦተ እግዚአብሔርንም አምጥቶ በዚህ ስላስቀመጣት ጽዮን
እየተባለች መጠራት እንደጀመረች እንጠራለን። 2ኛ ሳሙ 5፥6-9 ፣ 6፥10-12 ጽዮን
የሚለው ቃል መላውን ኢየሩሳሌምን የሚያመለክትበት ጊዜ አለ። 2ኛ ነገ 19፥21 ፣
መዝ 47፥2 ፣ 68፥35

ከላይ የተዘረዘሩት ተራራዎች በተጨማሪ በሰማርያ በሴኬም አቅራቢያ ጌባልና ገሪዛን


የተባሉ ተራሮች ይገኛሉ። ጌባል 292 ሜትር ገሪዛን ደግሞ 946 ሜትር ከባሕር ጠለል በላይ
ከፍታ አላቸው። ዘዳ 11፥29 ፣ 27፥12-13 ፣ 8፥30-35

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
6
1.4 ምንጮች

ትናንሽ የሆኑና ለመጠጥነት የሚያገለግሉ ውኃማ ቦታዎች ምንጮች ይባላሉ።

የአጋር ምንጭ

የሣራ አገልጋይ የነበረችው አጋር ከአብርሃም እንዳረገዘች ባየች ጊዜ ሣራን ናቀቻት።


በዚህ የተነሣ ከአብርሃም ቤት ተባርራ ወጣች፤ በምድረ በዳ ውኃ ጥም ጸንቶባት በተቸገረችና
ባለቀሰች ጊዜ መልአከ እግዚአብሔር ወደ ሱር በምትወስደው መንገድ አጠገብ ባለች ምንጭ
ጎን ተገለጠላት። የዚያችም ምንጭ ስም ብኤርለሃይሮኢ ተባለ።ዘፍ 16፥1-14

የያዕቆብ ምንጭ

ሲካር በምትባለው የሰማርያ ከተማ ትገኛለች።ሲካርም ከሴኬም በስተደቡብ በአንድ


ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። የዕቆብ ከአጎቱ ሀገር ከሶርያ ሲመለስ በከንዓን
ምድር ወዳለችው ወደ ሴኬም ከተማ መጣ። ድንኳኑን ተክሎበት የነበረውን የእርሻ ማሳ
ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ በጎች ገዛ። በዚያም ያዕቆብ ለራሱ ያስቆፈራት ምንጭ
ነበረች። ያዕቆብና ቤተሰቦቹ ሁሉ ከዚያች ምንጭ ሲጠጡ ኑረዋል። ዘፍ 33፥18-20 ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይሑዳን ትቶ ወደ ገሊላ በሔደበት ወቅት በሰማርያ ወደ
ምትገኘው ወደ ሲካር መጣ የሥጋን ገንዘብ ባሕርይው አድርጓልና ከመንገዱ ርዝመት፣
ከዋዕዩ ብርታት የተነሣ ደከመው፤ ተጠማም በሲካር ወደ ምትገኘው የያዕቆብ ምንጭ ቀርቦ
ከአንዲት ሣምራዊት ሴት ውኃ ለመነ። እርሱ የሕይወት ውኃ እንዳለውና እርሱ ከሚሰጠው
የሕይወት ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደማይጠሙ አስተማራት። የተሠወረ ሕይወቷን ገልጦ
በማስተማሩም ሳምራዊቷ ሴት በእርሱ ከማመኗም በላይ የከተማውን ሰው በሙሉ ጠርታ
ከእርሱ ተምረው አምነውበታል። ይህ ሁሉ የተከናወነው በያዕቆብ ምንጭ አጠገብ ነው።
ምንጩ 32 ሜትር ያህል ጥልቀት አለው። ዮሐ 4፥1-32

የቤተልሔም ምንጭ

ከሰሊሆም መጠመቂያ በስተምሥራቅ በዳዊት ከተማ ከበሩ አጠገብ ትገኛለች። ዳዊት


ከፍልስጤማውያን ጋር በተዋጋና በራፋይም ሸለቆ ባለው ምሽግ በተሸሸገ ጊዜ ፍልስጤማውያን
የቤተልሔምን ምንጭ ያዙ። ንጉሡ ዳዊትም ከቤተልሔም ምንጭ ይጠጣ ዘንድ ፈለገ።
“ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ማን ይሰጠኛል?” በማለት ወታደሮቹን ጠየቃቸው። በዚህን ጊዜ
ሦ ስቱ ወታደሮቹ ኢዮአብ፣ አሣሄልና አቢሳ ከፍልስጤማውያን ጋር ተዋግተው
የፍልስጤማውያንን ምሽግ ቀድደው በመግባት ዳዊት ሊጠጣ የወደደውን ውኃ ከቤተልሔም
ምንጭ አምጥተውለታል። ጻድቅ ዳዊት ግን ወታደሮቹ ስለ እርሱ ፍቅር ሲሉ ሰውነታቸውን

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
7
ለጦር ሰጥተው ተዋግተው ያመጡለትን ውኃ አልጠጣም። ነፍሳቸውን ለሞት እንኳ ሰጥተው
ያመጡት በመሆኑ “ደማቸውን መጠጣት ይሆንብኛል” ሲል ያን የወደደውን ውኃ አፈሰሰው።
1ኛ ዜና 11፥15-19

1.5 ሜዳዎች

ሜዳዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዛት ተጠቅሰው አይገኙም።

የአርማጌዶን ሜዳ

ከቀርሜሎስ ተራራዎች በስተደቡብ ከደብረ ታቦር ተራራዎች ፊት ለፊት የሚገኝ


ሜዳ ነው። ቀድሞ በቀርሜሎስ ተራራዎች ከሰሜን ወደ ደቡብ ጋዛንና ደማስቆን
የሚያገናኘውን መንገድ ለመጠበቅ የተመሸገ ከተማ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ሜዳ ሰዎች
አይኖሩበትም። ዲቦራና ሲሣራን ድል ያደረገችው፣ ፈርዖን ኒካውም ኢዮስያስን የገደለው
በዚሁ በአርማጌዶን ሜዳ አጠገብ ነው። መሳ 5፥19 ፣ 2ኛ ነገ 23፥29-30 የዓለም መጨረሻ
ምልክት የሚሆን ጦርነት ይደረግበታል። ራእ 16፥12-16 አርማጌዶን ማለትም መካነ
ድምሳሴ (የመደምሰሻ ቦታ)፣ መካነ ስራዌ (የመነቀያ ቦታ) ማለት ነው። ዘካ 12፥11-14

የሰናዖር ሜዳ

በባቢሎን ዙሪያ ያለ ሰፊ ሜዳ ሲሆን ከኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ በኃላ የተነሡ ሰዎች


ግንብ መገንባት የጀመሩት በዚህ ሜዳ ነው። የሰው ልጆች ቋንቋ የተለያየበት
(የተደበላለቀበት) ስለሆነ ባቢሎን ተብሏል። ባቢሎን ማለትም ድብልቅልቅ ማለት ነው። ዘፍ
11፥1-9

1.6 ሸለቆዎች

ሸለቆ ማለት ጎድጓዳ የሆነና የሚሞቅ፣ ሐሩር የበዛበት ቦታ ማለት ነው።

የሄኖም ሸለቆ

ስያሜውን ሄኖም ከተባለው ሰው እንዳገኘው ይነገርለታል። ከቄድሮስ ወንዝ በታች


ከጥንታዊው የኢየሩሳሌም ከተማ በምዕራብና በደቡብ በኩል ይገኛል። ይሁዳና ብንያም በዚህ
ሸለቆ ይዋሰናሉ። ኢያ 15፥8 ከኢዮስያስ በፊት የነበሩ ነገሥታት በሄኖም ሸለቆ የጣዖት
መስገጃዎችን ሠርተው ሴቶችና ወንዶች ልጆቻቸውን ሳይቀር ይሠዉቡት ነበር። ኤር 19፥
1-9 ፣ 2ኛ ዜና 28፥1-4 ፣ 2ኛ ዜና 33፥1-7 ፣ 2ኛ ነገ 16፥3 ይሁን እንጂ ኢዮስያስ በነገሠ

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
8
ጊዜ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር መንገድ በመሔዱ በሄኖም የነበሩ የማምለኪያ
ዐጸዶችንና መሠዊያዎችን አጠፋቸው። 2ኛ ነገ 23፥10-14

የኢዮሳፍጥ ሸለቆ

ኢዮሳፍጥ ከ870 እስከ 845 ከክርስቶስ ልደት በፊት በይሁዳ የነገሠ አራተኛው ንጉሥ
ነው። እግዚአብሔር ጠላቶቹን ያሸንፍ ዘንድ ኃይል ስለሰጠውና ጠላቶቹንም ድል
ስላደረጋቸው፣ ምርኮአቸውንም ከወሰደ በኋላ በዚህ ሸለቆ ፈጣሪውንም ስላመሰገነበት
የኢዮሳፍጥ ሸለቆ ተባለ። የኢዮሳፍጥ ሸለቆ በኢየሩሌምና በደብረዘይት መከከል የቄድሮን
ወንዝ ይፈስበታል። በአሁኑ ጊዜ ብዙ የአይሁድና የእስላም መቃብር ይገኝበታል። ነቢዩ
ኢዩኤል በኢዮሳፍጥ ሸለቆ በሕዝብና በአሕዛብ ላይ እግዚአብሔር የሚፈርድባቸው መሆኑን
ተናግሯል። ኢዩ 3፥2-12 በኢየሩሳሌም ነግሠው የነበሩ ነገሥታት ሥጋ በዚሁ ሸለቆ የተቀበረ
መሆኑም በተለያዩ መጽሐፍት ተገልጧል።

የራፋይም ሸለቆ

ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ ከቤተልሔም 5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል። ንጉሥ ዳዊት


ፍልስጥኤማውያንን ሁለት ጊዜ ያሸነፈው በራፋይም ሸለቆ እንደሆነ ተጽፏል። 2ኛ ሳሙ 5፥
17-25

1.7 ዋሻዎች

ዋሻ ማለት በተፈጥሮም ሆነ በሰው ኃይል የተቦረቦረ፣ የተፈለፈለ መሬት ቋጥኝ ነው። ብዙውን
ጊዜ ዋሻ መናንያን ገብተው ይጸልዩበታል። ስደተኞች ይጠጉበታል። አራዊትም
ይኖሩበታል። በመጽሐፍ ቅዱስም የተለያዩ ዋሻዎች ተመዝግበዋል።

የኤልያስ ዋሻ

በይሁዳ በረሃ ይገኛል። በዐረብኛ ዋዲከልት ይባላል። ነቢዩ ኤልያስ ለእግዚአብሔር


ቀንቶ አምልኮቱን የዘነጉትን አክዓብንና ኤልዛቤልን ከነሠራዊታቸው ለመቅጣት ሲልሰማይ
ዝናብ ለዘር፣ ጠል ለመከር እንዳትሰጥ ለጎመ። በዚህ የተነሣ አክዓብ እንዳይገድለውና
በረሃብም እንዳይጎዳ ልዑል እግዚአብሔር “ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሒድ፣
በዮርዳኖስም ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተሸሸገ። ከወንዙም ትጠጣለህ ቁራዎችም
በዚያ ይመግቡህ ዘንድ አዝዣለሁ” አለው። እንደተናገረውም ቁራዎች በጠዋትና በማታ
ኅብስትና ሥጋ እያመጡ ኤልያስን ይመግቡት ነበር። ያቺ ኤልያስ የተሸሸገበት ፈፋ (ዋሻ)
የኤልያስ ዋሻ ትባላለች። 1ኛ ነገ 17፥1-7

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
9
የሴዴቅያስ ዋሻ

ሴዴቅያስ በይሁዳ ላይ ከነገሡት ከኢዮስያስ ልጆች ሦስተኛው፣ በኢየሩሳሌም ከነገሡት ዘሮች


የመጨረሻው ነው። ዓመተ ንግሥናውም ከ597 – 587 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ይገመታል።
በይሁዳ ከነገሠ በኋላ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ። በነገሠ በዐሥር ዓመቱ
አልገብርም በማለቱ ናቡከደነፆር ዘመተበት። በዚህ ወቅት ሴዴቅያስ ሸሽቶ የተደበቀባት ዋሻ
የሴዴቅያስ ዋሻ ትባላለች። ሴዴቅያስ ከዋሻይቱ በሌሊት ወጥቶ ቢያመልጥም በናቡከደነፆር
ሠራዊት ኢያሪኮ ላይ ተያዘ፤ ልጆቹ ተገደሉ፤ እርሱም ዐይኖቹ እንዲወጡ ተደረገ። 2ኛ ነገ
25፥1-7 ፣ ኤር 52፥8 የሴዴቅያስ ዋሻ በአሁኑ ጊዜ ከደማስቆ በር በስተግራ በኩል በ180
ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ከሴዴቅያስ ዋሻ የምትመነጭ ምንጭ አለች። በአካባቢውም
ኅብረተሰብ ዘንድ “የሴዴቅያስ እንባ” ተብላ ትጠራለች።

ተግባር

7. በመጽሐፍ ቅዱስ ባሕል መሠረት ተራራ ምንን ያመለክታል?


8. ተማሪዎች ስለ አርሞንኤም፣ ቀርሜሎስ እና ሊባኖስ ተራሮች በመጽሐፍ ቅዱስ
የተጻፈውን ይዛችሁ በመምጣት ለተማሪዎችና ለመምህሩ አንብቡላቸው
9. በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ታላላቅ አምካዊ ሥራዎቹን
የሠራው በተራሮች ላይ ነው ለምን ይመስላችኋል?
10. የሲና ተራራ የእግዚአብሔር ተራራ ለምን ተባለ?
11. በገሪዛን የታወጁ የበረከት ትእዛዛትና በጌባል የታወጁ የመርገም ትእዛዛት ምን የሚሉ
ናቸው?
12. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የሕይወት ውኃ መሆኑን ያስተማረው
በየትኛው ምንጭ አጠገብ ነው?
13. ብኤርለሃይሮኢ በመባል የምትታወቀው ምንጭ የት ትገኛለች?
14. የሚተሉት ሜዳዎች የት እንደሚገኙና የተፈጸሙባቸውን ታሪኮች አስረዱ።
ሀ የዱራ ሜዳ
ለ የሳሮን ሜዳ
15. ሸለቆ ማለት ምን ማለት ነው?
16. በሸለቆ አካባቢ የሚኖሩ ምን ሰዎች ዓይነት ሰዎች ናቸው?
17. ነቢዩ ሕዝቅኤል በመንፈስ ያየው የአጥንት ሸለቆ (ሕዝ 37፥1) ምንን
ያመለክታል?
18. በዋሻና በሸለቆ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
19. በሀገራችን ዋሻ ለሰው ልጅ የሚሰጠውን አገልግሎት አስረዱ።
20. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያዩ ዋሻዎችን በመፈለግ ተወያዩባቸው።

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
10
የሚሰጠው የትምህርት ርዕስ፦ የሕብረተሰብ ክፍሎች በመጽሐፍ ቅዱስ

የዕለቱ ጥቅስ፦ “ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ አሸንክታባቸውን


ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፤ በምሳም የከበሬታ ወንበር በገበያም ሰላምታና፣ መምህር ሆይ
ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ” ማቴ 23፥4-7

ምዕራፍ ሰባት

2 የሕብረተሰብ ክፍሎች በመጽሐፍ ቅዱስ


መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብ ሰው የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ያገኛል። መጽሐፍ
ቅዱስ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ያደረገባት ሀገረ እስራኤል የብዙ ዓይነት ሕዝቦች መናኸሪያ
ነበረች። በዚህ ክፍል የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በነገዳቸው፣ በሥራቸውና ባላቸው
የተለያየ ሃይማኖታዊ አመለካከት ከፋፍለን እንመለከታቸዋለን።

2.1 በነገዳቸው

ሞዓባውያን፦ ሞዓብ ሎጥ ከታላቂቱ ልጅ የወለደው ነው። የእርሱ ልጆች የሆነት


በአባታቸው በሞዓብ ሞዓባውያን ተብለዋል። ዘፍ 19፥37 የሚኖሩበትም አካባቢ ሞዓብ ይባል
ነበር። ከጨው ባሕር /ከሙት ባሕር/ በስተ ምሥራቅ የሚገኝ ቦታ ነው።

እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ የሞዓብ ንጉሥ እንዲያሳልፋቸው ቢጠይቁትም አልፈቀደላቸውም።


መሳ 11፥17-18 በዚህም ምክንያት አጭሩ መንገድ ረዘመባቸው። ባላቅ የተባለው የሞዓብ
ንጉሥ አልተሳካለትም እንጂ እስራኤልንም ለማስረገም ሀብተ መርገም የነበረውን በለዓምን
በወርቅና በብር አባብሎታል። በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ክፋታቸውን ቆጥሮ እስከ
ዐሥር ትውልድ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ እንዳይገቡ ተደርገዋል። ዘኁ 22፥4-24 ፣ ዘዳ
23፥3-6 “ብዔልፌጎር” የሚባል ጣዖት ነበራቸው። እስራኤል በሰጢም ተቀምጠው ሳለ ከሞዓብ
ልጆች ጋር በማመንዘራቸው 24,000 ሰዎች ተቀስፈዋል። ዘኁ 25፥1-9

“ካሞሽ” የሚባልም ጣዖት ነበራቸው። ንጉሥ ሰሎሞንም ለዚህ ጣዖት ሰግዷል። 1ኛ ነገ


11፥7 ብዙ ጦርነቶችን ከእስራኤል ጋር አድርገዋል። መሳ 3፥12-30 ፣ 1ኛ ሳሙ 14፥17 ፣
2ኛ ሳሙ 8፥2 ፣ 2ኛ ዜና 20፥1-30 ሩት ሞዓባዊት ስትሆን ከወገኖቿ ተለይታ
እግዚአብሔርን ያመነች ሴት ናት። ሩት 1፥4 እርሷም የዳዊት ቅማንቱ (ቅድመ አያቱ)
ናት። ማቴ 1፥6 በዚህም ምክንያት ሞዓባውያንን ዳዊት ሳያጠፋቸው ትቷቸዋል። ኋላ ግን
ናቡከደነጾር በተነሣ ጊዜ ለመጨረሻ ጊዜ አጥፍቷቸዋል።

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
11
አሞናውያን፦ ሎጥ ከወለዳቸው ልጆች መካከል አንዱ ከታናሺቱ ልጁ የወለደው አሞን
ይባላል። በአሞንም ልጆቹ አሞናውያን ተብለው ተጠሩ። ዘፍ 19፥38 ይኽኛው አሞን የይሁዳ
ንጉሥ ከነበረው ከምናሴ ልጅ ከንጉሡ አሞን ይለያል።

ከዮርዳኖስ ወንዝ ሸለቆ በስተምሥራቅ በያቦቅና አርኖን ወንዞች መካከል የሚገኝ ቦታ አሞን
ተብሎ ይጠራል። ይህም የዛሬው የዮርዳኖስ ዋና ከተማ አማን ያለችበት ዙሪያ ነው። አማን
የሚለው ስምም አሞን ከሚለው የተወሰደ ይመስላል። እደሞዓባውያን ሁሉ እስራኤልን
አናሳልፍም በማለታቸው እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እግዚአብሔር ረግሟቸዋል። መሳ 11፥
12-28 መስፍኑ ዮፍታሔም በእርሱ ዘመን አናሳልፍም በማለታቸው ተዋግቶ ድል
ነሥቷቸዋል። መሳ 11፥29-33 “ሞሎክ” ወይም “ሚልካ” እየተባለ የሚጠራ ጣዖት ያመልኩ
ነበር። 1ኛ ነገ 11፥7-33 ንጉሥ ሰሎሞን እንደ ካሞሽ ሁሉ ለዚህኛውም ጣዖት ሰግዷል።
እግዚአብሔር ግን ቀጥቶታል። ለዚህ ጣዖታቸው መስዋዕት እያሉ የሰው ልጆችን ያቃጥሉ
ነበር። ዘሌ 18፥21

አማሌቃውያን፦ የዔሳው የልጅ ልጅ በሆነው በአማሌቅ የተጠራ ነገድ ነው። ዘፍ 36፥12፣


16 ከዘመነ ሙሴ እስከ ንጉሥ ሕዝቅያስ ድረስ የእስራኤል ቀንደኛ ጠላቶች ሆነው
ቆይተዋል። ዘፀ 17፥8-13 ሊቀ ነቢያት ሙሴ እስራኤል ከእነዚህ ጋር በተዋጉ ጊዜ በመስቀል
አምሳያ እጁን በመዘርጋት በእግዚአብሔር ኃይል እስራኤል ለማሸነፍ በቅተዋል። ዘፀ 17፥
10-13

ነገር ግን እስራኤል ኃጢያት በመሥራታቸው ምክንያት እግዚአብሔር ቢለያቸው የሞዓብ


ንጉሥ አሞናውያንን እና አማሌቃውያንን ከእርሱ ጋር አሰልፎ ድል አድርጓቸዋል። መሳ
3፥12-14 በኋላ ግን ግራኙ መስፍን ናዖድ ተነሥቶ አሸንፏቸዋል። መሳ 3፥15-31
የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሳዖል አማሌቃውያንን እና የእነርሱ የሆነውን ሁሉ አጥፋ
ብሎ እግዚአብሔር ያዘዘውን ትዕዛዝ ለአማሌቅ የሰቡ ፍሪዳዎች ሳስቶ ባለመፈጸሙ
መንግሥቱ ለሌላ ተላልፎ ተሠጠ። 1ኛ ሳሙ 15፥1-31

ኢያቡሳውያን፦ የካም ልጅ የሆነው የከንዓን ዝርያዎች ናቸው። ዘፍ 10፥16 እጅግ ኃይለኛ


ተዋጊዎች ስለነበሩ የእስራኤል ልጆች በኢየሩሳሌም በጽዮን አምባ የነበሩትን ኢያቡሳውያንን
አላስለቀቋቸውም ነበር። ኢያ 15፥63 በኋላ ግን ቅዱስ ዳዊት በጦርነት ድል አደርጎ
አስለቀቃቸው። 2ኛ ሳሙ 5፥6-10

ኤዶማውያን፦ ዔሳው በሴይር ተራራ ተቀምጦ በነበረበት ጊዜ የወለዳቸው ልጆቹ ሲሆኑ


ዔሳው ኤዶም ተብሎ ይጠራ ስለነበር በእርሱ ኤዶማውያን ተባሉ። ዘፍ 36፥9 ኤዶም ማለት
ቀይ ማለት ነው። ይህም ዔሳው የያዕቆብን ቀይ ምስር ወጥ አይቶ ስለጎመጀ ነው።

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
12
ኤዶም ከሙት ባሕር በስተደቡብ ምሥራቅ፣ በምዕራብ በኩል ደግሞ ዓረብን አዋሳኙ ያደረገ
ቦታ ነው። ይህ አካባቢ የዛሬዋ ደቡባዊ የዮርዳኖስ ግዛትን ያመለክታል። ኤዶማውያን
እስራኤል ከግብጽ በወጡ ጊዜ በእነርሱ በኩል እንዲያልፉ አልፈቀዱላቸውም። ዘኁ 2፥14-
21 ቅዱስ ዳዊት ኤዶማውያንን አስገብሯቸዋል። 2ኛ ሳሙ8፥13-14 ሰሎሞን ከጣዖት
አምላኪዎች ከፈርዖን ልጅ፣ ከሞዓባውያን፣ ከአሞናውያን፣ ከኤዶማውያንና ከኬጤያውያን
ሴቶች ጋር በዝሙት በወደቀ ጊዜ የአባቱን ድል በኤዶምያስ ንጉሥ በሃዳድ ተነጠቀ። 1ኛ
ነገ 11፥1-2

ኤዶማውያን ከክርስቶስ ልደት በፊት 587 ዓመት አካባቢ ኢየሩሳሌም በመጥፋቷ


ተደስተዋል። መዝ 136፥7 ሰቆ.ኤር 4፥21

ዔናቃውያን፦ አባታቸው ዔናቅ ይባላል። ቁመተ ረጃጅሞች በመሆናቸው እስራኤል ከግብጽ


ሲወጡ ሙሴ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከላካቸው ዐሥሩ (ከኢያሱና ካሌን ውጪ ያሉትን)
እነዚህን ሰዎች አይተው እጅግ በጣም የሚያስፈራ ወሬ አመጡ። “የኔፍሊም ወገኖች የነበሩ
በዚያ ይኖራሉ” ብለው ተናገሩ። ዘኁ 13፥30-33 ይሁን እንጂ ኢያሱ ብዙዎችን
አጥፍቷቸዋል። ካሌብም ደግሞ ኬብሮንን አስለቅቆ አባርሯቸዋል። ከእነዚህም ጦርነቶች
የተረፉት በፍልስጤም አገር ይኖሩ ነበር። ኢያ 11፥21-22 ፣ 14፥6-15 ቁመቱ ስድስት
ክንድ ከስንዝር (ሦስት ሜትር ከሩብ) የሆነው ጎልያድ ከእነዚህ ቁመተ ረጃጅም ዝርያዎች
የተወለደ እንደሆነ ይታመናል። 1ኛ ሳሙ 17፥4

2.2 በሥራቸው

ዓሣ አጥማጆች፦ ከጥንት ጀምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ የታወቀ ተወዳጅም ምግብ


በመሆኑ ዓሣ አጥማጆችም ነበሩ። በእስራኤልም በገሊላ ባሕር አጠገብ ይኖሩ የነበሩ ዓሣ
አጥማጆች ነበሩ። የተናቁ ድሆች ለማለት ዕብራውያን ኤቢኦኔቲ ይሏቸዋል። እነዚህ ሰዎች
ያልተማሩና የተናቁ ናቸው። 1ኛ ቆሮ 1፥28 ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ፣
ቅዱስ እንድርያስ ቅዱስ ዮሐንስ እና ቅዱስ ያዕቆብ ከዓሣ አጥማጅነት የተጠሩ ናቸው። ሉቃ
5፥1-11 ፣ ማር 1፥16-20 ያዕቆ 2፥5

ኅብረተሰቡ “ኃጢያተኞች” ይላቸው ስለነበር ራሳቸውን አዋርደው የሚኖሩ እንደነበሩ


ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን ተአምራት ካሣየው በኋላ የተናገረው ቃል ያስረዳል። እርሱም “ስምዖን
ጴጥሮስ ግን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጉልበት ላይ ወድቆ ጌታ ሆይ እኔ ኃጢያተኛ ነኝና ከእኔ
ተለይ” አለው። ሉቃ 5፥8

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
13
ቀራጮች፦ የቄሣር መንግሥት በሀገረ እስራኤል ግብር እንዲሰበስቡ ዘንድ የሾማቸው ሰዎች
ቀራጮች ይባላሉ። እንደ ባንዳ በእስራኤላውያን ዘንድ በጣም የተጠሉ ነበሩ። በዚህም እንደ
ኃጢያተኛ ይቆጠሩ ነበር። ሉቃ 18፥17 ጌታችን ግን ምንም እንኳ በኅብረተሰቡ ዘንድ
የተጠሉ በሆኑም አብሯቸው ተመግቧል። ማቴ 9፥11 ከእነዚህ ወገን የሆነውን ወንጌላዊው
ማቴዎስንም ይከተለው ዘንድ ጠርቶታል።

ወደ መጥምቁ ዮሐንስም ሊጠመቁ ከመጡ ሰዎች መካከል ቀራጮችም ስለነበሩ “ጌታ


ሆይ ምን እናድርግ?” ቢሉት “ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ” ሲል መክሯቸዋል።
ሉቃ 3፥13 ኅብረተሰቡ ቀራጮችን ኃጢያተኞች ያደርጋቸው ስለነበር “መምህራችሁ
ከኃጢያተኞችና ከቀራጮች ጋር አብሮ ለምን ይበላል?” ተብሎ ጌታችን ተከስሷል። ማቴ
9፥11 ጌታችንን ከብዙ ሕዝብ መካከል ለመመልከት ከዛፍ ላይ የወጣው ዘኬዎስ የቀራጮች
አለቃ ነበር። ሉቃ 19፥1-9 ጌታችንም ወደ ቤቱ ገብቶ ተስተናግዷል።

2.3 በሃይማኖታዊ ልዩነታቸው (በአመለካከታቸው)

ፈሪሳውያን፦ በአፍአ (በመናገር) ብቻ የሙሴን ሕግ ጠብቀን እንኖራለን የሚሉ በሥራ


ግን የማይፈጽሙ የአይሁድ ወገኖች ናቸው። ሰዎች የሙሴን ሕግ እንዳይተላለፉ በሚል
በሕጉ ላይ ብዙ ሥርዓትን ጨማምረዋል። ማቴ 15፥1-14 ፣ 23፥1-4 ። ዋና አስተሳሰባቸው
ሰው የሚጸድቀው በግል ሕይወቱና ሕግን በመፈጸም ነው የሚል ነበር። ሐዋ 15፥5

በእነዚህ መካከል ግን እንደ ኒቆዲሞስና ቅዱስ ጳውሎስ ያሉ እውነተኛ ታዛዦችና ቅን ሰዎች


ነበሩ። ብዙዎች ግን በሙሴ ሕግ ላይ የተጨመሩትን የአባቶች ወግ እየተመለከቱ ዋናውን
የሕግ አርእስት እየረሱ ራሳቸውን ብቻ ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ሌላውን ግን የሚንቁና
የሚያንቋሽሹ ሆኑ። በዚህም ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዞች
በማለት በተደጋጋሚ ጊዜ ነቅፏቸዋል።

ስለራሳቸው ክብር ሲሉ ሕገ እግዚአብሔርን ያጣምሙ ነበር። ማር 7፥9-13


የሚመሩትንም ሕዝብ እጅግ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ትእዛዞች ያስጨንቁ ስለነበር ጌታችን
“ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ
ሊነኩት አይወዱም። ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ
አሸንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፤ በምሳም የከበሬታ ወንበር በገበያም
ሰላምታና፣ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ” በማለት አስነዋሪ ሥራቸውን ነቅፏል።
ማቴ 23፥4-7

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
14
በጌታችን መዋዕለ ስብከት 6000 የሚያህሉ ፈሪሳውያን እንደነበሩ ይነገራል። እነርሱም
በየሙክራቦቹ መሪዎች የነበሩ ሲሆኑ ሀብታሞችም ናቸው። ፈሪሳውያን ባዕለ ጸጋ እስከ መሆን
የደረሱት ሕዝቡን በመበዝበዝ ሲሆን ጌታችን ማቴ 23፥23-24 ጌታችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሰቀል ምክንያት እየፈለጉ ይከሱት ነበር። በመጨረሻም ጲላጦስ “ምን
ላድርግላችሁ?” ብሎ ሲጠይቅ “ስቀለው ስቀለው” እያሉ ጮኸዋል።

ጸሐፍት፦ በዘመነ ብሉይ በቤተ መንግሥት አካባቢ አገልጋዮችና አማካሪዎች በመሆን


ያገለግሉ የነበሩ የተማሩ ሰዎች ናቸው። 1ኛ ዜና 27፥32 በዘመነ ሐዲስ ግን ከፈሪሳውያን
ጋር ግንባር በመፍጠር ጌታችንና ተከታዮቹን ሁሉ ይቃወሙ ነበር። ሐዋ 23፥9

ግብዞች ከመሆናቸው የተነሣ እንደ ፈሪሳውያን ሁሉ ጌታችን ገሥጿቸዋል። “እናንተ ግብዞች


ጻፎችና ፈሪሳውያን በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጥ ግን የሙታንም አጥንት እርኩሰትም
ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ
በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ። በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና አመጸኝነት
ሞልቶባችኋል።” በማለት ማንነታቸውን ነግሯቸዋል። ማቴ 23፥27-36

የሕግ መርማሪዎች ነን ስለሚሉም ክርስቶስን እንመረምራለን ብለው አስቀርበውታል። ሉቃ


22፥26 የሚሠሩትን ክፉ ሥራ ስለተናገረባቸው በበቀል ስሜት ጌታን ለማጥፋት ተነሥተው
ከነበሩት መካከል ዋነኞቹ ናቸው። ከዚህም የተነሣ የሐሰት ፍርድ ፈርደውበታል። ማቴ 26፥
54-68 ቅዱስ ጳእሎስንም መርምረውታል። ነገር ግን ምንም እንዳላገኙበት እራሳቸው
ተናግረዋል። ሐዋ 23፥9 አስቀድመውም የጌታችንን ደቀ መዛሙርት ሰብሰበው በክርስቶስ
ስም እንዳያስተምሩ ዝተውባቸዋል። ሐዋ 4፥5-22 ሐዋርያት ግን “ያየነውን የሰማነውን
ከመናገር ዝም ማለት አንችልም” አሏቸው።

በዘመነ ብሉይ እንደ ካህኑ ዕዝራ ያለ ንጹሕ ሰው ከእነርሱ መካከል ተገኝቷል። ዕዝ 7፥6
በመጀመሪያ ከካህናት መካከል ነበሩ በኋላ ግን ለብቻቸው በመሆን ቡድን መሠረቱ።
በደንባቸው መሠረት ለዕለት ኑሯቸው የእጅ ሥራ በመሥራት ሕግን ደግሞ በነፃ ያስተምሩ
ነበር። በጌታችን ዘመን ግን ከፈሪሳውያን ጋር ሕዝቡን ወደ መበዝበዝ አምርተዋል።
የጸሐፊዎች ሥራ በሦስት ዓይነት ነው።

1. የሙሴን ሕግ መተርጎም፣ ማር 7፥1-13


2. ለሰዎች ሕግን ማስተማር፣ ሉቃ 2፥46
3. ዳኝነት። ሉቃ 22፥66

ሰዱቃውያን፦ የነፍስን ሕያውነት የሚክዱ፣ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ እና


የመላእክትንም ሕልውና የማያምኑ ናቸው። “ሰዱቃውያን ትንሣኤም፣ መልአክም፣ መንፈስም

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
15
የሚሉ ናቸውና ፈሪሳውያን ግን ሁለቱንም ያምናሉ። ሐዋ 23፥8 በዚህም የተነሣ ሁለቱም
ይከራከሩ ነበር። ሐዋ 23፥7-9

ሰዱቃውያን በፈሪሳውያን ይጨማመሩ የነበሩትን ወጎች አይቀበሉም። ስለትንሣኤ ሙታን


ጌታችንን በጥያቄ ሊፈትኑት ቢቀርቡም “እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን
አምላክ አይደለም ተብሎ የጽፏል።” በማለት አሳፍሯቸዋል። ማቴ 22፥23-33 የተነሡትም
በመቃብያን ዘመን ነው።

ሕግን በማጥበቅ ስም እናውቃለን ባዮች በመሆናቸው ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን


“ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” በማለት መክሯቸዋል። ማቴ 16፥
16 ሁለቱም የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን የሙሴን ሕግ ሲሆን ሰዱቃውያን በመሰላቸው
በመተርጎሙ ፈሪሳውያን ደግሞ ወጎችን በመጨማመር ሕጉን ይተላለፉ ነበር።

ጌታችን እንዲሞት ደቀ መዛሙርቱም እንዲያዙ ከፈረዱት የአይሁድ ሸንጎ አባላት መካከል


ሰዱቃውያንም ነበሩበት። ሐዋ 5፥17-18 ኋላም ሐዋርያትን በማሳደድ ተግባር ተሰማሩ።
ሐዋ 4፥1-22

ኤሴያውያን፦ በጾምና በጸሎት ተወስነው በትህርምት፣ ወደ በረሃ በመውጣት በምናኔ ይኖሩ


የነበሩ ወገኖች ናቸው። ከፈሪሳውያን ተከፍለው የወጡ እንደሆኑ ይነገራል። የቁምራን
ጥቅልሎች በመባል የሚታወቁት መጽሐፍት ከእነርሱ የተገኙ ናቸው። ከእነዚህ ጥቅልሎች
መካከል የተወሰኑት በቁፋሮ የተገኙ ሲሆን ስማቸውም ዛሬ የሙት ባሕር ጥቅልሎች (The
Dead Sea Scrolls) በመባል ይታወቃሉ።

ተግባር

20. ተማሪዎች ከላይ ስለተመለከትናቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በመጽሐፍ


ቅዱስ የተገለጹትን ጽፋችሁ በመምጣት ለተማሪዎችና ለመምህሩ
ያንብቡላቸው።

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
16
የሚሰጠው የትምህርት ርዕስ፦ የሥራ መስክ እና መገበያያ በመጽሐፍ ቅዱስ

የዕለቱ ጥቅስ፦ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” 2ኛ ተሰ 3፥14

ምዕራፍ ስምንት

3 የሥራ መስክ እና መገበያያ በመጽሐፍ ቅዱስ


3.1 የሥራ መስክ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያዩ የሥራ መስኮች ተጠቅሰው ይገኛሉ። አዳም


“በሕይወት ዘመንህ ሁሉ በድካም ከእርሷ ትበላለህ” ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጅ ኑሮውን
ለማሸነፍ በተለያዩ የሥራ መስክ እየተሰለፈ ኖሯል። ዘፍ 3፥17 የሰው ልጅ እንደተፈጠረ
ሥራ እንዲሠራ ተደርጓል። ዘፍ 2፥15 ከአስርቱ ትእዛዛት መካከልም አንዱ ሥራ መሥራት
እንደሚገባ የሚናገር ነው። ዘጸ 20፥9

ቅዱስ ጳውሎስ በተሰሎንቄ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ሠርተው እንዲኖሩ


መክሯቸዋል። 1ኛ ተሰ 4፥12 “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” 2ኛ ተሰ 3፥14 ሥራ እንድንሠራ
የታዘዝን ቢሆንም ሥራችንን ሁሉ እንዲያቃናልን ፈጣሪያችንን መማጸን ይኖርብናል።
“በቃል ቢሆን በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አድርጉት” ቆላ
3፥17

ዋናው ቁም ነገር ሥራን ሳይንቁ በሥራ ተሰማርቶ መገኘት እና ረድኤተ


እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ ነው። የሥራ ዘርፎች ከጥንት ጀምሮ ነበሩ። ከእነዚህም ውስጥ
አብዛኞቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰዋል።

ግብርና፦ እርሻን፣ ከብት እርባታንና አደንን የሚያጠቃልል የሥራ መስክ ነው። ገብሬ
የሚለው በአብዛኛው የእርሻ ሥራን ሲያመለክት ይገኛል።

እርሻ፦ በሀገረ እስራኤል እንደ ወይን፣ ስንዴ፣ የወይን ዛፍ፣ ተምር እና በለስ
የመሳሰሉት ይመረታሉ። የእርሻ ሥራ ከአዳም ጀምሮ ተያይዞ የመጣ ነው። ዘፍ 4፥2 ኖኅም
በእርሻ ሥራ ይተዳደር ነበር። ዘፍ 9፥20 አበ ብዙሀን አብርሃምም ገበሬ ነበር። “አብርሃም
በቤርሳቤህ የተምር ዛፍን ተከል” ዘፍ 21፥33 ነቢየ እግዚአብሔር ኤልሳዕም ከመጠራቱ በፊት
በዐሥራ ሁለት ጥማድ በሬ የሚያርስ የሚያጎርስ ገበሬ ነበር። 1ኛ ነገ 19፥19 ኤልዛቤል
በቅናት ያስገደለችው ኢይዝራኤላዊው ናቡቴም የወይን እርሻ የነበረው ገበሬ ነበር። 1ኛ ነገ
20፥1

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
17
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የሰውን ልብ በእርሻ መስሎ አስተምሯል።
ማቴ 13፥1-49

ከብት እርባታ፦ በእስራኤል ጥንታውያን ከሆኑት የሥራ መስኮች ዋነኛው ነው። አቤል
በግ ጠባቂ ነበር። ዘፍ 4፥2 እስራኤላውያን በከፍተኛ ደረጃ የበግ እርባታን ያከናውናሉ።
እስከዛሬም ድረስ ይታወቁበታል። አብርሃምና ሎጥም ከብት አርቢዎች እንደነበሩ ተጽፏል።
ዘፍ 12፥5 ፣ ዘፍ 13፥5-8 ታላቁ ያዕቆብም ለረጅም ዓመታት ከብት ጠባቂ ሆኖ ቆይቷል።
ዘፍ 30፥29 በግብጻውያን ዘንድ በግ ጠባቂ እንደ ርኩስ ይቆጠር ነበርና ዮሴፍ ቤተሰቦችን
ፈርዖን ቢጠይቃችሁ ከብት አርቢዎች ነን በሉት አላቸው። ዘፍ 46፥34 ቅዱስ ዳዊትም ወደ
መንበረ ሥልጣን ከመውጣቱ በፊት በግ ጠባቂ ነበር። 1ኛ ሳሙ 16፥11 ነቢዩ አሞጽም
ለነቢይነት ከመጠራቱ በፊት በከብት አርቢነት ሥራ ተሰማርቶ ይኖር ነበር። አሞ 1፥1

እረኞች በጥንት ጊዜ በፈረቃ ይጠብቁ ነበር። በጌታችን ልደት ጊዜም የተጠሩት


እረኞችም ፈረቃቸው በሌሊት ስለ ነበር በዚያው መንጎቻቸውን ሲጠብቁ ብሥራቱን
ለመስማት ታድለዋል። ሉቃ 2፥8

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በእረኛ መስሎ ተናግሯል።


“መልካምእረኛ እኔ ነኝ” እንዳለው ዮሐ 10፥11 ላይ። ካህናትም በእረኞች ይመሰላሉ።
“እረኞች ሆይ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ” ሲል ካህናትን ነው። ሕዝ 34።7 ጌታችንም
ስምዖን ጴጥሮስን “ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠበቶቼን ጠብቅ እማ በጎቼን አሰማራ እያለ እንደ
ቅደም ተከተሉ አዝዞታል። ዮሐ 21፥15-17

አደን፦ በዱር ውስጥ የሚኖሩ እንሰሳትን አስድዶ መያዝ ወይም መግደል አደን
ይባላል። “ዔሳውም አደን የሚያውቅ የበረሀ ሰው ሆነ” ሲል አደን እንደ አንድ የሥራ መስክ
ይወሰድ እንደ ነበር ያሳያል። ዘፍ 25፥27

ንግድ፦ በጥንት ጊዜ ንግድ ታላቅ የሥራ መስክ ነበር። ታላቁ አባት አብርሃም ከእርሻና
ከከብት እርባታ በተጨማሪ የንግድ ሥራንም ያከናውን ነበር። “አብራምም በከብት፣ በብርና
በወርቅ በለጠገ” ዘፍ 13፥3 ይኖርባት የነበረችው በከለዳውያን ምድር የምትገኘው ዑር
በንግድ የገነነች ሀገር ነበረች።

ግብጽም የንግድ መናኽሪያ ነበረች። ቀደም ሲል የባሪያ ንግድ ከተስፋፋባቸው ሀገሮች


አንዷ በመሆኗም ዮሴፍ ተሸጦባታል። እርሱንም የሸጡት ወደ ግብጽ ይወርዱ የነበሩ
ነጋዴዎች ናቸው። ዘፍ 37፥30

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
18
ሀገረ እስራኤልም ታላቅ የንግድ መናኽሪያ ከመሆኗ የተነሣ ጠቢቡ ሰሎሞን በጊዜው
ከተለያዩ ሀገራት ይመላለሱ ከነበሩት በርካታ ነጋዴዎች ግብር ይቀበል እንደነበር መጽሐፍ
ቅዱስ ያስረዳል። 1ኛ ነገ 10፥11 ነቢዩ ዮናስ ወደ ተርሴስ ለመጓዝ የተነሣው በነጋዴዎች
መርከብ ተሳፍሮ ነበር። ይህም የባህር ንግድ ተስፋፍቶ እንደ ነበር ያመለክታል። በተለይ
ጢሮስ ከፍተኛ ከፍተኛ የንግድ ሀገር ነበረች። “በእንጨት፣ በሸራ፣ በሐር፣ በቆርቆሮ፣ በእርሳስ፣
በብርና በብረታ ብረት፣ በዝሆን ጥርስ፣ በወርቀ ዘቦ፣ በዞጲ፣ በቅመማ ቅመም. . . ንግድ እጅግ
የከበረች ነበረች” ሕዝ 27፥1-25

ንግድ በተስፋፋት ወቅት የዕቃ በዕቃ ለውጥ (Bartering) አንዱ የመገበያያ መንገድ
እንደሆነ ተጽፏል። “ይለውጡ ዘንድ የዝሆን ጥርስና ዞጲ አመጡልሽ” ሕዝ 27፥15 አብርሃም
እና ያዕቆብ በከብት ቦታ ገዝተዋል። ዘፍ 21፥28 ፣ 33፥18-20

ጌታችን በተወለደበት ዘመን እስራኤል የተለያዩ ሀገሮችን የምታገናኝ ታልቅ የንግድ


ሥፍራ ነበረች። ሐዋ 16፥13-15

ጌታችን እንደ ሌሎቹ ሥራዎች ሁሉ በንግድ እየመሰለ አስተምሯል። ማቴ 25፥14-


30 “ደግሞም መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች። ዋጋዋም
እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ ባገኘ ጊዜ ሔዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ገዛት” በማለት አስተምሯል።
ማቴ 13፥45-46 ነጋዴው የምዕመናን ፣ ያለውን ሁሉ መሸጡ ራሱን የመካድ ምሳሌ ናቸው።

በሐዲስ ኪዳን ነጋዴዎች ለንግድ ወደ ተለያዩ ሀገሮች ሲጓዙ ወንጌልን አስተምረዋል።


ምሳሌ፦ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን (ፍሬምናጦስ) ወደ ኢትዮጲያ አስተምረዋል። ንግሥተ ሳባ
ስለጠቢቡ ሰሎሞን በጥንቃቄ የተረዳችውን ታምሪን ከሚባል ኢትዮጲያዊ ነጋዴ መሆኑንም
ነጋዴያን ምን ያህል ቃለ እግዚአብሔርን ለማስፋፋት ምን ያህል የተመቻቸ ሁኔታ እንደ
ነበራቸው ያመለክታል።

ሕክምና፦ መጽሐፍ “ወይስ በዚያ ሐኪም የለም?” ሲል ሕክምና ጥበብ የነበረ መሆኑን
ያመለክታል። ኤር 8፥22 “ዮሴፍም ባለመድኃኒቶች አገልጋዮቹ አባቱን በሽቱ ያሹት ዘንድ
አዘዘ።” ተብሎ እንደ ተነገረ የሕክምና ሥራ ከጥንት ጀምሮ አለ። ዘፍ 50፥2 እንዲሁም
ንጉሡ አሳ እግሩን በታመመ ጊዜ “ባለ መድኃኒቶች እንጂ እግዚአብሔርን አልፈለገም።” 2ኛ
ዜና 16፥12 ባለመድኃኒቶች የተባሉ ሐኪሞች ናቸው። አባታችን ጻዲቁ ኖኅ ከእግዚአብሔር
በተገለጠለት ጥበብ የመጀመሪያው ሐኪም ነው። እግዚአብሔር ከተለያዩ ዕፆች ወይም ዕፅዋት
ብዙ ዓይነት መድኃኒት ሊሠራ እንደሚችል አሳይቶታል።

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
19
ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊው “ባለ መድኃኒቱ” ተብሎ የተጠራው ሐኪም በመሆኑ ነው። ቆላ 4፥
14 ፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረችው ሴትም ከክርስቶስ አስቀድሞ ከብዙ ባለ
መድኃኒቶች ጋር ተገናኝታ ነበር። ማር 5፥26

አናጺነት፦ በአሁኑ ወቅት አናጺ የሚለው ቃል የተወሰነ የሥራ መስክን ብቻ ያመለክታል።


እርሱም ከእንጨት ሥራዎች ጋር ብቻ የተያያዘ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን አናጺነትን
ከመኃንዲስነት ሥራ ጋር ያመላክታል። ሕዝ 40፥3 ፣ ራእ 21፥15 ስለዚህ ነው ቅዱስ
ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሀተኛ የአናጺ አለቃ መሠረት
መሠረትሁ ሌላውም በላዩ ላይ ያንጻል።” ሲል የተናገረው። 1ኛ ቆሮ 3፥10

አናጺዎች የፈረሱ ቤቶችን ይጠግኑ ነበር። 2ኛ ዜና 34፥11 አረጋዊው ዮሴፍ የአናጺነት


ሙያ ነበረው። ማቴ 13፥15 ጌታችንም በልጅነቱ በአናጺነት ሥራ ዮሴፍን ይረዳው ነበር።
ጠቢቡ ሰሎሞን ታላቁን ቤተ መቅደስ ያሠራው የእንጨት ሠራተኞችን (አናጺዎችን)
ከጢሮስና ከሲኖዳ አስመጥቶ ነው። በእነዚህ ሀገሮች ታዋቂ አናጺዎች ነበሩ። 2ኛ ዜና 1፥3-14

ግንበኝነት፦ የሰናዖርን ግንብ ከተሰሡት ሰዎች ጀምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው ተጠቅሶ
የሚገኝ የሥራ መስክ ነው። ዘፍ 11፥1-9 እስራኤላውያን በዚህ ሥራ የታወቁ ነበሩ።
በተለይም ወደ ግብጽ በተሰደዱበት ጊዜ ዓለም የሚያደንቃቸውን ፒራሚዶች እንደሠሩ
ይነገራል። ምክንያቱም በኦሪት የተጻፉት ታሪኮች ከዚህ ጋር የተያያዙ ናቸው። ጡብ
በመሥራት ለፈርዖን ፊቶምና ራምሴ የተባሉ ጽኑ ከተማዎችን እንደከተሙ ተጽፏል። ዘፍ
1፥8-14

ጌታችን “ግንበኞች የናቁት ድንቃይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ” ተብሏል። ማቴ 21፥


42 “እንሆ የተመረጠና የተከበረ የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን
አያፍርም” ተብሎ ተጽፏል። ሮሜ 9፥23

ዕብራውያን ለበርካታ ጊዜ በተካሄዱ ጦርነቶች ወደ ተለያዩ አገሮች ሲሰደዱ እንደ


መኖራቸው ከልዩ ልዩ ሕዝቦች የተግባረ ዕድ ጥበብን ቀስመዋል። 2ኛ ነገ 18፥1-7 ፣ 1ኛ
ዜና 24፥5

በተግባረ ዕድ /በእጅ ሥራ/ የተሰማሩ ሰዎች ጥንት በባልጩት /ስለታም ድንጋይ/ እና በናስ
ሥራዎቻቸውን ማከናወን ጀመሩ። ዘፍ 4፥22 ከዚያም ብረትን ማቅለጥ እና መቀጥቀጥ
ሰቻል የተለያዩ መሳሪያዎች ተገኙ። ከእነዚህም መሳሪያዎች የሚከተሉት ይገኛሉ። መራጃ፣
መጥረቢያ፣ መቅረጫ፣ መዶሻ፣ መጋዝ፣ ምሳር፣ ቢላዋ፣ ካራ፣ ማጭድ፣ ማረሻ፣ ወስፌ፣ መርፌ
. . . ወዘተ። 1ኛ ነገ 6፥7 ፣ ኢሳ 44፥13 ፣ መሳ 5፥26 ፣ 2ኛ ሳሙ 12፥31 ፣ ዘዳ 19፥5 ፣
2ኛ ነገ 6፥5 ፣ ዘፍ 22፥6 ፣ ምሳ 30፥14 ኢሳ 2፥4 ፣ ዘጸ 21፥6 ፣ ማቴ 19፥24

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
20
ተግባር

21. ተማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጎላ ብሎ ከተነገረላቸው


/ከተጻፈላቸው/ የሥራ መስኮች መካከል አንጥረኝነት እና ቀጥቃጭነት፣
ልብስ ሥራ፣ ሸክላ ሥራ፣ ሽቱ ቀማሚነት፣ ቁርበት ፋቂ እና ቀንድ
አንጣጭ ይገኛሉ። ስለ እነዚህ የሥራ መስኮች በመጽሐፍ ቅዱስ
የተጻፈውን ጽፋችሁ በመምጣት ለተማሪዎችና ለመምህሩ
ያንብቡላቸው።

የሚሰጠው የትምህርት ርዕስ፦ መገበያያ በመጽሐፍ ቅዱስ (. . . የቀጠለ)፣ የጦር መሣሪያ

የዕለቱ ጥቅስ፦ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” 2ኛ ተሰ 3፥14

3.2 የገንዘብ መስፈሪያ፣ የጦር መሣሪያ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ የርዝመት /Length/፣ የክብደት /Weight/ እና ይዘት


/Volume/ መስፈሪያዎች /Measuring Units/ አሉ። እነዚህም ከጥንት ጀምሮ የነበሩ ናቸው።
“በፍርድ በመለካትም፣ በመመዘንም፣ በመስፈርም አመፃ አታድርጉ።” ዘሌ 19፥36-37

3.2.1 መስፈሪያ

የደረቅ ነገር መስፈሪያ፦ ለደረቅ ነገሮች የይዘት መለኪያ ነው። እነዚህም፦

 ቆሮስ፦ በዛ ያለ የእህል ሸክም የሚሰፈርበት መስፈሪያ ነው። ዘሌ 27፥16 ፣ ወደ 400


ሊትር አካባቢ ነው።
 ኢፍ፦ ዐሥር የኢፍ መስፈሪያ አንድ ቆሮስ የሚያህል ነው። ወይም አንድ ቆሮስ
አንድ ዐሥረኛ ሲሆን ይህም 40 ሊትር ይሆናል። ሕዝ 45፥11
 ጎሞር፦ ዐሥር የጎሞር መስፈሪያ አንድ ኢፍ ይመዝናል። ይህም ዐራት ሊትር ነው።
ዘጸ 16፥16-36

የፈሳሽ ነገር መስፈሪያ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሦስት ዓይነት የፈሳሽ መለኪያዎች
ይገኛሉ። አብዛኛውን ጊዜ ውኃ፣ ወይን እና ዘይት ይገኛሉ።

 ባዶስ፦ ባዶስና ኢፍ እኩል ይዘት አላቸው። የቆሮስ አንድ ዐሥረኛ ክፍል ነው። ሕዝ
45፥11 ፣ 14 አንድ ባዶስ የ40 ሊትር ይዘት አለው።
 ኢን፦ የባዶስ አንድ ስድስተኛ ክፍል ነው። 6 ሊትር ተኩል አካባቢ ነው። ሕዝ 4፥
1 ፣ ዘጸ 29፥40 ፣ ዘሌ 23፥13

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
21
 ሎግ፦ የባዶስ አንድ ዐሥራ ሁለተኛ ወይም የኢን አንድ ሁለተኛ ክፍል ነው። 3
ሊትር አካባቢ ነው። ዘሌ 14፥10

የክብደት መለኪያ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ሰባት ዓይነት የክብደት መለኪያዎች ተጠቅሰዋል።


እነዚህም፦

 ምናን፦ አንድ ምናን ከ500 እስከ 700 ግራም ክብደት እንዳለው ይነገራል። ዕዝ 2፥
69 ፣ 1ኛ ነገ 10፥17
 ዳሪክ፦ ለቤተ እግዚአብሔር መስሪያ የተበረከተው ወርቅ የተለካው በዳሪክ ነው።
“ስድሳ አንድ ሺህ የወርቅ ዳሪክ” እንዲል። ዕዝ 2፥69
 ሰቅል፦ ከ12 – 14 ግራም ያህል ክብደት አለው። ጎልያድ የለበሰው የነሐስ ጥሩር
5000 ሰቅል ያኽል ነበር። 1ኛ ሳሙ 17፥5 ይህም ወደ 65 ኪሎ ግራም አካባቢ
ይመዝን ነበር። “አብርሃም በ400 ሰቅል ለሣራ መቃብር በኬብሮን ገዛ” ዘፍ 23፥1-
16 ፣ 1ኛ ነገ 10፥16
የንጉሥ፣ የመቅደስና የሕዝብ የሚባል ሰቅል እንደ ነበር በመጽሐፍ ተገልጧል። 2ኛ
ሳሙ 14፥26 ዘጸ 30፥12-14
 አቦሊ፦ አንድ አቦሊ የሰቅል አንድ ሃያኛ ነው። ዘጸ 30፥14
 መክሊት፦ አንድ መኤክሊት ሠላሳ ኪሎ ግራም ነው። 2ኛ ነገ 18፥14 ፣ 1ኛ ነገ 10፥
14 እና 15
 ንጥር፦ አንድ ንጥር 327.45 ግራም አካባቢ ይመዝናል። ዮሐ 19፥39
 ታላንት፦ አንድ ታላንት 3 ፈረሱላ አካባቢ ወይም 50 ኪ.ግ ያህል ይመዝናል።

የርቀት /የርዝመት/ መለኪያ


 ዘንግ፦ ቁመቱ 2.7 ሜትር እና ከዚያም በላይ ሲሆን እንደ ሸምበቆ ካለ እንጨት
የሚሠራ ነው። ሕዝ 40፥5 ፣ ራእ 21፥15-16
 ክንድ፦ 50 ሴ.ሜ ወይም ግማሽ ሜትር ያህላል። ዘዳ 3፥11 ፣ ዘጸ 25፥10-11 ፣ 1ኛ
ሳሙ 17፥4
 ጋት፦ አውራ ጣትን ሳይጨምር የአራት እጅ ጣቶች ነው። ውፍረትንም ለመካት
ይጠቅም ነበር። ዘጸ 25፥25 ፣ 1ኛ ነገ 7፥26
 ስንዝር፦ የእጅ ጣቶችን በተለይም በተለይም አውራ ጣትንና መካከለኛ ጣትን
በተቃራኒ አቅጣጫ በመወጠር /በመቀሰር/ ከአንዱ ጫፍ እስከ ሌላው ጫፍ ያለው
ርቀት ወይም ርዝመት ስንዝር ይባላል። ዘጸ 28፥16 ይህ መለኪያ የክንድ ግማሽ
ነው። አንድ ስንዝር 25 ሳ.ሜ አካባቢ ነው።
 ምዕራፍ፦ አንድ ምዕራፍ 200 ሜትር ያህላል። ሉቃ 24፥13

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
22
 የሰንበት መንገድ፦ 6 ምዕራፍ ወይም 1200 ሜ /1.2 ኪ.ሜ ያህል ነው። በብሉይ
በሰንበት ቀን ከዚህ ርቀት በላይ መጓዝ አይፈቀድም ነበር። ዘጸ 16፥29 ፣ ሐዋ 1፥
12
 የሰው ቁመት፦ አራትክንድ ወይም ስድስት ጫማ ያህላል። ለባሕር ጥልቀት
መለኪያም ይውል ነበር። ሐዋ 27፥28

3.2.2 ገንዘብ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ገንዘብ የሚለው ቃል ሁለት ዓይነት አገባብ አለው። አንደኛው
ለመገበያያ ይሆን ዘንድ ከተለያዩ ዓይነት ማዕድናት /ከወርቅ፣ ከብር፣ ከመዳብ እና ከነሐስ/
በተለያየ መጠን የሚሠራውን ሲያመለክት፣ ሁለተኛው ደግሞ በአ ጠቃላይ ሀብትን ወይም
ንብረትን ያመለክታል። ሆኖም የመጀመሪያውን የገንዘብ ዓይነት በተመለከተ መጽሐፍ ምን
እንደሚል እንመለከታለን።

ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ 700 ዓመት ድረስ ምንዛሬ ያለው ገንዘብ እንዳልነበር ብዙዎች
ይስማማሉ። ሆኖም ግን ከወርቅ፣ ከብር፣ ከመዳብ እና ከነሐስ የተሠሩ ልዩ ልዩ የግሪክና
የሮማውያን ገንዘቦች በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ የታወቁ መገበያያዎች እየሆኑ መጡ።
ጌታችን “ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ . . . አታግኙ ያለው ከእነዚህ
መዓድናት የተሠሩ ገንዘቦች እንደነበሩ ያመለክታል። ማቴ 10፥9 አይሁድም በግሪኮችና
ሮማውያን ቅኝ ግዛት ሥር ሆነው ስለነበር የእነዚህን መንግሥታት ገንዘቦች ጥቅም ላይ
አውለዋል። እነዚህም ገንዘቦች

የግሪክ ገንዘቦች
1. መክሊት፦ የወርቅ መሐለቅ ነው። በእስራኤል ዘንድ የታወቀ የመገበያያ ገንዘብ ነው።
ጌታችንም እየመሰለ በተናገረባቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ ተጠቅሞበታል። ማቴ
18፥24 ፣ ማቴ 25፥14-15 አንድ መክሊት 2100 የኢትዮጲያ ብር ያህል ይመነዘራል።
2. ምናን፦ 35 የኢትዮጲያ ብር ያህል ይመነዘራል። ጌታችን በማቴዎስ ወንጌል ላይ
በመክሊት መስሎ ያስተማረው በሉቃስ ወንጌል ደግሞ በምናን ተተክቶ መነገሩ
ሁለቱም የገንዘብ መጠን መናገሪያዎች በመሆቸው ነው። ሉቃ 19፥13-27
3. ድራክማ፦ ድሪም እየተባለ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰው ገንዘብ ነው።
ዲናር ተብሎ የሚጠራው የሮማውያንን ገንዘብ ያህል ዋጋ አለው። ዕድሜው ከሃያ
ዓመት በላይ የሆነው አይሁዳዊ ሁሉ በየዓመቱ ለቤተ መቅደስ ሁለት ሁለት ድሪም
/ድራክማ/ ግብር ይከፍል ነበር። ሉቃ 15፥8

የሮም ገንዘቦች

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
23
1. ዲናር፦ የብር መሐለቅ ነው። አንድ ዲናር የአንድ ቀን ሠራተኛ ዋጋ ነበር። ማቴ
20፥9-10 በጌታችን መዋዕለ ስብከት በዲናሩም ላይ የሮማ ነገሥታቶች /ቄሣሮች/
ምስል ይታተምበት ነበር። ማር 12፥15-17 ፣ ሉቃ 10፥35
2. እስታቴር፦ አንድ እስታቴር ዐራት ዲናር ያህል ነው። ማቴ 17፥27
3. አሣርዮን፦ የቄሣር መልክ ያለበት የመዳብ ገንዘብ ነው። በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ
ውስጥ አምስት ሳንቲም የተባለው አንድ አሣርዮን ነው። “ሁለት ድንቢጦች በአምስት
ሳንቲም ይሸጡ የለምን?” ማቴ 10፥29
4. ካድራንስ፦ የአሣርዮን ሩብ ነው።ይህም በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሳንቲም
የተባለው ነው። ማር 12፥42
5. ሌፕቶን፦ እስካሁን ከተጠቀሱት ሁሉ የሚያንስ ሲሆን የኳድራንስ ግማሽ ነው።
በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ግማሽ ሳንቲም ተብሎ የተጠቀሰው ነው። ሉቃ 12፥59
፣ ማቴ 5፥26 ፣ ማር 12፥42

3.2.3 የጦር መሣሪያ

የሰው ልጅ እርስ በእርሱም ሆነ ከአራዊት ጋር መታገል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ


የተለያዩ የጦ ር መሳሪያዎችን ሲገለገልባቸው ኖሯል። ከድንጋይ ጀምሮ እስከ አጥንት፣
እሳትና የተለያዩ ብረታ ብረቶች ሁሉ በጥንት ጊዜ እንደ ጦ ር መሳሪያ አገልግለዋል።
የመጀመሪያው ሟች አቤልም የሞተው በድንጋይ ነው። ዘፍ4፥8 ሶምሶም ፍልስጤማውያንን
ሸነፋቸው በአንድ የአህያ መንጋጋ ነው። መሳ 15፥15 ከዚህ ቀጥሎ በመጽሐፍ ቅዱስ
የተጠቀሱትን አንዳንድ የጦር መሳሪያዎች እንመለከታለን።

ወንጭፍ፦ በዘመነ መሳፍንት እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅመውበታል። መሳ 20፥16 ቅዱስ


ዳዊትም ጎልያድን አሸንፎበታል። 1ኛ ሳሙ 17፥40-49 ፣ 1ኛ ዜና 12፥2

ጦር፦ ጎልያድ ዳዊትን ለመግደል ጦር ይዞ ወጥቶ ነበር። ከጦሩም ጋር አብሮ ጭሬ ይዞ


ነበር። 1ኛ ሳሙ 17፥6-7 ጭሬ ቀጭንና አጭር ጫፉ ጠባብ የሆነ የጦር ዓይነት ነው። ሳዖል
ባይሳካለትም ዳዊትን ለመግደል ጦር ወርውሯል። 1ኛ ሳሙ 18፥11 ሌንጊኖስ የተባለው
የሮማውያን ወታደር የጌታችንን ጎን የወጋው በጦር ነው። ዮሐ 19፥34 ፣ ዮሐ 18፥3

ሰይፍ፦ በሁለት በኩል የተሳለ ከብረት የሚሠራ የጦር መሣሪያ ዓይነት ነው። ከጎራዴ
የሚለየው በሁለት በኩል የተሳለ እና አጠር ያለ በመሆኑ ነው። በአንድ በኩል ብቻ የተሳሉ
አንዳንድ ሰይፎችም ይኖራሉ። 1ኛ ሳሙ 13፥19-22 ፣ ሉቃ 22፥53 ጌታችን በተያዘ ጊዜም
ቅዱስ ጴጥሮስ የሊቀ ካህናቱን የቀያፋን ባሪያ /የማልኮስን/ ቀኝ ጆሮ በሰይፍ መትቶ

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
24
ቆርጧል። ዮሐ 18፥10 ቃለ እግዚአብሔር በሰይፍ ይመሰላል። “የመንፈስን ሰይፍ ያዙ
እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።” ኤፌ 6፥17 ፣ ዕብ 4፥12 ፣ መዝ 149፥6

ጥሩር፦ ከአንገት እስከ ጉልበት የሚጠለቅ ከቆዳ ወይም ከተለያዩ ብረታ ብረት የሚሠራ
መከላከያ ነው። 1ኛ ሳሙ 17፥38-39 ፣ 1ኛ ነገ 22፥34 ፣ ነህ 4፥16 ጥሩር የጽድቅ ምሳሌ
ነው። “የጽድቅ ጥሩር ለብሳችሁ” ኤፌ 6፥13-15

ጋሻ፦ ከብረት፣ ከናስ ወይም ከቆዳ የሚሠራ በእጅ የሚያዝ ለሚወረወርም ሆነ ለሚሰነዘር
የጦር መሳሪያ መከላከያ ወይም መመከቻ የሚውል ነው። ነህ 4፥16 ጋሻ በእምነት
ይመሰላል። “እናንተ መሳፍንት ሆይ ተነሡ፣ ጋሻውን አዘጋጁ” ኢሳ 21፥5 “የእምነት ጋሻ
አንሱ” ኤፌ 6፥16 ፣ መዝ 34፥2 ፣ ዘፍ 15፥1

ቁር፦ በራስ ላይ የሚጠለቅ ከናስ፣ ከብረትና ከሌላም ቁሳቁስ ሊሠራ የሚችል የጦር መከላከያ
ነው። “በራሱም ላይ የጦር ቁር ደፋለት። 1ኛ ሳሙ 17፥38 ፣ ቁር የመዳኛ ምሳሌ ነው።
“የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ” ኤፌ 6፥17

ቀስትና ፍላፃ፦ ቀስት ከእንጨት ወይም ከሌሎች ብረታ ብረት የሚሠራ እንደ ደጋን ያለ
ቅርጽ ያለው ሲሆን ከአንዱ ጫፍ እስከ ሌላው ጫፍ ከጅማት ወይም ከጭራ የተገመደና
የተወጠረ ክር ያለው መሣሪያ ነው። ፍላፃ ደግሞ በቀስቱ አማካኝነት እንዲፈናጠር ሆኖ ዘንጉ
ብረት ወይም እንጨት የሆነ ጫፉ ግን ሹል ብረት ያለው መሣሪያ ነው። ዘፍ 21፥20 ፣ 1ኛ
ዜና 5፥18 ፣ 1ኛ ዜና 12፥2

ተግባር

22. ተማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰላጢን፣ ቀጭኔና ካራ፣ ጎመድ እና ጎራዴ
ስለተሰኙት የጦር መሳሪያዎች የተገለጸውን ጽፋችሁ በመምጣት ለተማሪዎችና
ለመምህሩ ያንብቡላቸው።

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
25
የሚሰጠው የትምህርት ርዕስ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ እንስሳት እና እጽዋት

የዕለቱ ጥቅስ፦ “እንደ እባብ ብልሆች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ” ማቴ 10፥16

ምዕራፍ ዘጠኝ

4 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ እንስሳት እና እጽዋት


4.1 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ እንስሳት እና የእንስሳት ምሳሌ በመጽሐፍ
ቅዱስ

ከትናንሽ እንሰሳት እስከ ታላላቅ ፍጥረታት ድረስ በተለያየ ሁኔታና ምሳሌ የተጠቀሱ
እንስሳት በመጽሐፍ ቅዱስ ይገኛሉ።

ርግብ
መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ የሚያነሳት ከአዕዋፍ ዝርያ የሆነች እንስሳ ናት። የመንጻት
ወራት ሲፈጸም ለመስዋዕት ትቀርብ ነበር። ዘሌ 12፥6-8 ፣ ሉቃ 2፥22-24

የርግብ ጠባያትና ምሳሌ


1. የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ናት፦ ጌታችን በባሕረ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ተጠምቆ
ሲወጣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መንፈስ ቅዱስ በላዩ ላይ ዐርፏል። ማቴ 3፥
16 ለምን በርግብ አምሳል ተገለጠ? ቢባል
 ርግብ ኃዲጊተ በቀል (በደልን የማትቆጥር) አባረሩኝ ብላ የማታዝን ናት።
መንፈስ ቅዱስም ኃጢአት ሠርተዋል አሳዝነውኛል ብሎ በንስሐ የሚመለሱትን
አልቀበልም የማይል ኃዳጊ በቀል ነውና።
 ርግብ በኖኅ ዘመን ውኃ ጎደለ ስትል የወይራ ቅጠል ይዛ ተመልሳለች። ዘፍ
8፥11 መንፈስ ቅዱስም ተስፋ መስቀልን (ድኅነትን) ያበሥራልና።
 ርግብ ክንፏን ቢመቷት፣ እንቁላሏን ቢሰብሩባት ጎጆዋን ካላፈረሱባት
አትሔድም፤ መንፈስ ቅዱም ኃጢአት ቢሠሩ ፈጽመው ካልካዱት
አይለይምና።
2. የእመቤታችን ምሳሌ ናት፦
 ርግብ ሁለት ክንፍ አላት እመቤታችንም ንጽሐ ሥጋ እና ንጽሐ ነፍስ
ተሰጥቷታልና። ራእ 12፥14 ፣ መኃ 6፥9

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
26
 የኖኅ ርግብ የጥፋት ውኃ ጎደለ ስትል የለመለመ የወይራ ቅጠል እንዳመጣች
ድንግል ማርያምም በእግረ አጋንንት ይቀጠቀጥ ለነበረው ዓለም የሰላም አለቃ፣
የብዙዎች ደስታ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወልዳዋለች። ሉቃ 2፥
14
 የኖኅ ርግብ በተላከች ጊዜ በጎ ምላሽ ይዛ እንደመጣች ሁሉ ድንግል ማርያምም
በአማላጅነቷ ለሚተማመኑ ሁሉ ምሕረትን ከእግዚአብሔር ታመጣለች።
3. የየዋሕት ምሳሌ፦ “እንደ እባብ ብልሆች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ” ማቴ 10፥16
ርግብ ከየዋሕነቷ የተነሣ በጥፋት ውኃ ጊዜ በእባብ አፍ ውስጥ እንቁላል ጥላለች።
ነገር ግን በፍጹም የዋሕነት በእግዚአብሔር ቸርነት ተጠብቃለችና። እናንተም
በየዋሕነት ተጠበቁ ሲል ነው።

በግ
አራት እግር ያለው፣ ቆዳው በጠጉር የተሸፈነ፣ ሥጋቸው ለምግብነት ከሚውሉ የቤት
እንስሳት መካከል አንዱ ነው። ከምግብነት ባሻገርም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ይቀርቡ
ከነበሩት እንስሳትም የመጀመሪያው ነው። ዘፍ 4፥4 ፣ ዘሌ 22፥19

እስራኤል በበጉ ደም ድነው ከግብጽ ባርነት እንደወጡ ነፍሳትም በክርስቶስ ደም


ከሲኦል እሥራት ተፈትተው ወደ ዘጸ 12፥1-51 የበግ ምሳሌነት በመጽሐፍ ቅዱስ

1. በግ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ፦ በግ በብሉይ ኪዳን ስለ


ሰው ልጆች ኃጢአት ይሠዋ እንደ ነበር እውነተኛው መሥዋዕት ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ቤዛ ራሱን መስዋዕት አድርጓልና።
“የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ዮሐ 1፥29
 በግ ሲደበድቡት፣ ሲሸልቱትም ሆነ ሲያርዱት አይጮህም ጌታችንም ያን ሁሉ
መከራና ስቃይ ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ ሲያደርሱበት ዝም ብሏልና። ኢሳ
53፥7 ፣ 1ኛ ጴጥ 2፥22-23
 አብርሃም ስለ ይስሐቅ ፈንታ የሠዋው በግ የክርስቶስ ምሳሌ ነው።
እግዚአብሔር ያዘጋጀው በግ በዱር ውስጥ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ መገኘቱ ክርስቶስ
ያለ ዘርዐ ብእሲ (ያለወንድ ዘር) ለመፀነሱ ምሳሌ ነው። በጉ ስለ ይስሐቅ ፈንታ
እንደታረደ አማናዊው በግ ክርስቶስም ስለ አዳምና ልጆቹ ተሠዋ።
2. የምዕመናን ምሳሌ፦ ሕዝ 34፥11-16 በወንጌል በተደጋጋሚ ምዕመናን በበጎች
ተመስለዋል። “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም
ነበርና አዘነላቸው።” ማቴ 9፥36 ፣ ዮሐ 10፥14-15 “ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም።
በጎቼ ድምጼን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል።” ዮሐ 10፥27

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
27
 በእስራኤል በግ ጠባቂ ከበጎቹ ፊት ፊት ይሄዳል። እነርሱም መሪያቸው፣
ጠባቂያቸው መሆኑን ለይተው እርሱ በሄደበት ሁሉ ይከተሉታል። መልካም
ማሰማሪያ ላይ ሲደርስም በትሩን ይተክላል። እነርሱም ይሰማራሉ። ድምጹንም
ሲያሰማቸው ወደ እርሱ ይሰባሰባሉ። ወደ ሌላ ቦታ መሔድ ሲያስፈልጋቸውም
እረኛው እየመራቸው እነርሱ ይከተሉታል። ምዕመናንም በእረኛ የተመሰለ
ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጣሪያቸው ጠባቂያቸው መሆኑን ያውቃሉ። ቃሉንም
ይሰማሉ። የእርሱን ፈለግ ተከትለው ርስት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ።
እረኛ የሚጠብቃቸውን በጎች እየመራ ሔዶ ለምለም መስክ ሲያገኝ በትሩን
ይተክላል እነርሱም ይህን ዐውቀው ይሰማራሉ፣ በትሩን ሲነቅልም ወደ እርሱ
ይሰበሰባሉ። ጌታችንም የማዳን ጉዞውን በቀራንዮ በተተከለው መስቀል በፈጸመ
ጊዜ የአዳም ተስፋው ሞላለት ወደ ቀደመ ክብሩም መለሰው። ምዕመናንም
በመስቀሉ ሰላምን ወደ ሰጠው ወደ ጌታቸው ይሰበሰባሉ። ዮሐ 21፥15-17
3. የጻድቃን ምሳሌ፦ ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ ጊዜ “በጎችን በቀኙ . . . ያቆማቸዋል”
ተብሏል። ማቴ 25፥33
 በግ ወደ ምድር እያየ ይሔዳል፤ ጻድቃንም ዕለተ ሞታቸውን ግብአተ
መሬታቸውን እያሰቡ ንስሐ ገብተው ለሞት ተዘጋጅተው ይኖራሉ።
 በግ በላቷ ኃፍረቷን ትሸፍናለች (ትሰውራለች) ጻድቃንም የራሳቸውን ኃጢአት
በንስሐ የሌላውን ኃጢአት በትዕግሥት ይሠውራሉና።
 በግ ጭቃ አይጸየፍም ጻድቃንም በሃይማኖት የሚመጣባቸውን መከራ
አይሰቀቁም። በግ ኑሮው በደጋ ነው። ጻድቃንም ኑሯቸው በደጋ መንግሥተ
ሰማያት ነውና።

ንሥር
በሰማይ ከሚበርሩት እና ታላላቅ ከሚበሉት አእዋፍ አንዱ ነው። የባሮክን ደብዳቤ
ከኢየሩሳሌምን ወደ ባቢሎን በምርኮ ወደ ነበረው ነቢዩ ኤርምያስ ያደረሰው ንሥር ነው።
ተረ.ኤር 10፥12 ፣ 11፥8 በመጽሐፍ ቅዱስ ከሚታወቅባቸው ጠባያት አንዱ ፈጣንነት ነው።
“ከንሥር ይልቅ ፈጣኖች ነበሩ” እንዲል 2ኛ ሳሙ 1፥23 ፣ ንሥር በሰማይ ሲበርር ከመንገዱ
የሚያስታጉለው እንቅፋት የለበትም። እግዚአብሔርም እግዚአብሔርን ከግብጽ ሲያወጣ
የቀትር ሐሩር እንዳያቃጥላቸው ደመና ጋርዶ፣ የሌሊቱ ግርማ እንዳያስደነግጣቸው ብርሃን
አብርቶ፣ ባሕረ ኤርትራ እንዳያሰጥማቸው በሕሩን ከፍሎ፣ ከእ ንቅፋት ሁሉ ጠብቆ በቸርነቱ
እንዲወጡ አድርጓቸዋል። ዘጸ 19፥4

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
28
ንሥር የኃይለ እግዚአብሔር ምሳሌ ነው። “እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን
ኃይላቸውን ያድሳሉ። እንደ ንሥር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፣ አይታክቱም፣ ይሔዳሉ፣
አይደክሙም” ኢሳ 40፥31

ከ4ቱ ወንጌላውያን አንዱ የሆነው ነባቤ መለኮት /ታኦጎሎስ/ ቅዱስ ዮሐንስ በሚከተሉት
ምክንያቶች በንሥር ይመሰላል።

 ንሥር ከሌሎቹ አእዋፍ ተለይቶ ወደ ላይ መጥቆ ጉኖ ይበራል። ቅዱስ ዮሐንስም


ወንጌሉን ሲጽፍ ከሌሎቹ ወንጌላውያን ተለይቶ ምስጢረ መለኮትን ማለትም ምስጢረ
ሥላሴ እና ምስጢረ ሥጋዌን በመተንተን በረቀቀ ሰማያዊ ምስጢር ጀምሯልና።
 “ንሥር ዐይኑም በሩቅ ትመለከታለች” ኢዮ 39፥27-29 እንዳለ ኢዮብ። ንሥር ምንም
እንኳ እጅግ ወደ ላይ መጥቆ ቢበርም ባለበት ሆኖ ወደ ምድር ሲመለከት ጥቃቅን
ነገሮችን በሚገባ መመልከት ይችላል። ዮሐንስ ወንጌላዊውም ረቂቅና ጥልቅ የሆኑትን
“እግዚአብሔር ፍቅር፣ እግዚአብሔር ብርሃን፣ ክርስቶስ የሕይወት እንጀራ” የሚሉትን
ትምህርቶች አስተምሯል።

የሥላሴን መንበር ከሚሸከሙት አርባዕቱ እንስሳት (አራቱ እንስሳት) ከኪሩቤል የአንደኛው


መልክ የንሥር ነው። ራእ 4፥7 ይህም በሰማይ ለሚበርሩት አዕዋፍ ጠባቂ ነው።

ላም
ከለማዳ የቤት እንስሳት መካከል አንዷ ስትሆን ግዙፍና ታዛዥ ለምግብነት የምትውል እንስሳ
ናት። የላምና የበሬ ሥጋቸው እንዲሁም ጉልበታቸው፣ ቆዳቸውና ቀንዳቸው ለሰው ልጆች
የተለያየ ጥቅም ይዘጣል። የላም ወተትም በአብዛኛው ክፍለ ዓለም በምግብነት ያገለግላል።

በብሉይ ኪዳን ወይፈን ለመሥዋዕት ይቀርብ ነበር። ዘሌ 22፥19 ፣ ዘኁ 7፥3 ጌታችን


በተወለደ ጊዜ እንስሳት ትንፋሻቸውን ገብረውለታል። ከእነዝህ እንስሳት መካከል ከእረኞች
ጋር ላሞችም ነበሩ። ኢሳ 1፥3 የላም ምሳሌነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ

1. የጌታችን ምሳሌ፦ “ጥበብ ቤትዋን ሰራች፣ ሰባቱንም ምሰሶዎች አቆመች። ፍሪዳዋን


አረደች፣ የወይን ጠጅዋን ደባለቀች” በማለት ጠቢቡ ሰሎሞን ተናግሯል። ምሳ 9፥1-
2
ጥበብ ቤተ ክርስቲያን ናት፣ ሰባቱ ምሰሶዎች ሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፣
ፍሪዳ የተባለ ሥጋ መለኮት /የጌታችን ሥጋ/ ፣ ወይን ጠጅ የተባለው ደግሞ ደመ
መለኮት /የጌታችን ደም/ ነው።

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
29
የጠፋው ልጅ ታሪክም እንደሚያስረዳን የጠፋው ልጅ አባት የእግዚአብሔር አብ፣
የጠፋው ልጅ የአዳም፣ ፍሪዳው የጌታችን ሥጋና ደም ምሳሌዎች ናቸው።
2. የምዕመናን ምሳሌ፦ የላም መንጋ በአንድ መሪ ይጓዛል፤ ምዕመናንም በአንዱ
በኢየሱስ ክርስቶስ መሪነት በሥርዓት ይጓዛሉና። ላሞች ጉልበት እያላቸው ለጌታቸው
ይታዘዛሉ፤ ምዕመናንም እንደ ሰብእ ዓለም ኃጢአት መሥራት ሲችሉ ስለጌታቸው
ፍቅር ብለው ኃጢአትን ከመሥራት ይቆጠባሉና።
ከ4ቱ ወንጌላውያን አንዱ የሆነው ቅድስ ሉቃስ በላም ይመሰላል። ይኸውም ቅዱስ
ሉቃስ ጌታችን በከብቶች በረት ስለመወለዱ እና ጌታችን በፍሪዳ መስሎ ያስተማረውን
ጽፏልና።

ዋላ
ረጅም ቀንድ ያለውና የፍየል ዝርያ ያለው በተራራማ ቦታ የሚኖር የዱር እንስሳ ነው።
በዘልማድ ዋልያ እየተባለ የሚጠራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከሀገራችን ከኢትዮጲያ በስተቀር
በየትኛውም የዓለማችን ክፍል አይገኝም። በተራራ አካባቢ ይኑር እንጂ ውኃ ካለበት አካባቢ
ርቆ መኖር አይችልም። ስለዚህ ከግርጌው ውኃ በሚመነጭ ተራራ አካባቢ ይኖራል። ውኃ
ሲጠማው ለመጠጣት ከታራራው ይወርዳል። ከጠጣ በኋላ ተመልሶ ተራራውን ሲወጣ ቆዳው
ስስ ነውና አብዛኛው የጠጣው ውኃ በላብ ይወጣል። እንደገናም ውኃ ለመጠጣት ይናፍቃል።
መዝ 41፥1 ዋላ ከውኃ ምንጭ ርቆ መኖር እንደማይችል ምዕመናንም የሕይወት ውኃ (ስቴ
ሕይወት) ከሆነው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ርቀው መኖር አይችሉም። ሁል ጊዜ የእርሱን
የሕይወት መጠጥ ደመ መለኮትን ለመጠጣት ይናፍቃሉ።

ፍየል
በቆላማ አካባቢ የምትኖር ቆዳዋ ስስ በሆነ ጠጉር የተሸፈነ ለማዳ የቤት እንስሳ ስትሆን
ሥጋዋ ልምግብ ቆዳዋ ደግሞ ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውላል። በተለይም ቆዳዋ ለብራና
በጣም ተፈላጊ ነው። ለልብስነትም ያገለግላል። ዕብ 11፥37

ለመሥዋዕትነት ይቀርቡ ከነበሩት እንስሳት መካከል አንዷ ፍየል ነበራች። ዘፍ 15፥9 ፣ ዘሌ


22፥19 ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለት አውራ ፍየሎች እንዲቀርቡ ይደረግና በሁለቱ ፍየሎች
ላይ ዕጣ ይጣላል። በዕጣውም መሠረት አንዱ ለመሥዋዕት ሲቀርብ ሌላው ወደ በረሃ
ይለቀቃል። ዘሌ 16፥7-22

 ፍየል የኃጥኣን ምሳሌ ናት። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ


ለፍርድ ሲመጣ በግራው የሚቆሙት ኃጥኣን በፍየል ተመስለዋል። ማቴ 25፥33

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
30
 ፍየል ሁል ጊዜ ቀና ብላ ትሔዳለች እንጂ በአትኅቶ ርእስ /ራስን ዝቅ በማድረግ/
መጓዝ አትችልም፤ ኃጥኣንም ከእኛ ይልቅ ወንድማችን ይሻላል እኛ ዝቅ ብለን
እናገልግለው አይሉም። በትዕቢት ከማን እንሳለን ሲሉ ይኖራሉና።
 ፍየል ኃፍረቷን በጅራቷ አትሸፍንም ኃጥኣንም በደላቸውን ጥፋታቸውን በንስሐ
አጥበው ለመንጻት በእግዚአብሔር ቸርነት ለመከለል አይሹምና።
 ፍየል ዝናቡን ጭቃውን ትመረራለች /ትጸየፋለች/ ኃጥአንም አምነው መከራን
መቀበል ይመረራሉና።
 ፍየል ለጠባቂ አስቸጋሪ ናት፤ ኃጥኣንም የመምህራንን ቃላቸውን ሰምተው ትእዛዘ
እግዚአብሔርን ለመፈጸም አስቸጋሪዎች ናቸው።
 ፍየል በሆነው ባልሆነው መጮህ ታበዛለች፣ ኃጥኣንም የምሬት ድምጽ በማሰማት፣
ሰዎችን ለማንቋሸሽ በሆነው ባልሆነው ንግግር /ጽርፈት/ ያበዛሉና።

አህያ
ከማይበሉት የእንስሳት ወገን ስትሆን የጋማ ከብት እየተባሉ ከሚጠሩት ውስጥ ትመደባለች።
እንደ ፈረስና በቅሎ በቤት እንስሳነት የጭነት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛውን ደረጃ
ይዛለች። “እነርሱም እህሉን በአህያዎቻቸው ላይ ጫኑ” ሲል ከጥንት ጀምሮ አህያ የሸክም
ሥራ ትሠራ እንደነበር ያሳያል። ዘፍ 42፥26 ለሰው መቀመጫነትም ታገለግላለች። 2ኛ ነገ
4፥22 ፣ 1ነገ 13፥11-25

1. አድገ በለዓም /የበለዓም አህያ/፦ ሀብተ መርገም የተሰጠው በለዓም ባላቅ ከተባለው
የሞዓብ ንጉሥ ጋር በመስማማት በመስማማት እስራኤልን ለመርገም በአህያ ላይ
ተቀምጦ ጉዞ በጀመረ ሰዓት ከፊቷ የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ መልአክን አህያዋ
በመመልከቷ በመሬት ላይ በመደፋት ለመልአኩ በመስገድ ሰግዳለች። ይህንንም
ያልተረዳው በለዓም አብዝቶ ቢደበድባት አንድበት አውጥታ “ሦስት ጊዜ የመታኸኝ
ምን አድርጌብህ ነው? . . . እስከ ዛሬ ድረስ የምትጠቀምብኝ አህያህ አይደለሁምን?
በውኑ እንዲህ አደርግ ዘንድ ልማዴ ነበርን?” ብላዋለች። ዘኁ 22፥21-35
ከዚህም የምንረዳው የእግዚአብሔርን ምስጢር ሰዎች ተረድተው መናገር
ባይችሉ ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታትን አስነሥቶ ሊያናግር እንደሚችል ነው። በዕለተ
ሆሳዕናም የቢታንያ ድንጋዮች አመስግነዋልና።
ኋላ ግን እግዚአብሔር የበልዓምን ዐይኖች ከፈተ፣ መልአኩንም ለማየት በቃ፣
በግንባሩም ተደፍቶ ሰገደለት። በለዓም ዐይኖቹ የተከፈቱለት ዐይነ ሥውር ስለነበር
አይደለም። የተከፈተለት ዐይነ ልቡናው ነው።ያኔ ነው መልአኩን ያየው፣ የሚገባውንም
የጸጋ ስግደት በግንባሩ ተደፍቶ ለጥ ብሎ የሰገደለት። ከዚህም የቅዱሳን መላእክትን
ክብር ዐውቆ መስገድ የሚቻለው እግዚአብሔር ዐይነ ልቡናን ሲያበራ ብቻ ነው።

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
31
2. የቤተልሔም አህዮች፦ “በሬ የገዥውን አህያም የጌታውን ጋጣ ዐወቀ” ኢሳ 1፥3
ተብሎ እንደተነገረ ጌታችን በተወለደ ጊዜ በበረት ከነበሩት እንስሳት መካከል አንዷ
አህያ ትንፋሿን ለአምላኳ ገብራለች።
3. የሆሳዕና አህዮች፦ በዕለተ ሆሳዕና ጌታችን በቤተ ፋጌ ታሥረው የነበሩትን እናትና
ልጅ አህዮች አስፈትቶ ወደ ኢየሩሳሌም እየተዘመረለት ገብቷል። ጌታችንም በአህያ
ላይ ተቀምጦ መጓዙ እና የታሰሩትን ማስፈታቱ ምስጢር አለው። ይኸውም፦
 የምዕመናን ምሳሌ፦ ፈትታችሁ አምጡልኝ ማለቱ ሰው ሁሉ ከማዕሠረ
ኃጢኣት የሚፈታበት ጊዜ ደርሷል ሲል ነው። እነዚህ አህዮች ተሰርቀው
የታሠሩ ነበሩ ቢሉ ዲያቢሎስ ሰርቆ በሲኦል አሥሯቸው የነበሩት ነፍሳት ነፃ
ይወጣሉና። ጌታችንም ገና ማንም ባልተቀመጠባት ውርንጫዋ
እንደተቀመጠባት ሁሉ በንጹሐን መሃይምናን (አማንያን) አድሮባቸው
ይኖራልና። በአካባቢውም የነበሩ ሰዎች ልብሳቸውን ጎዘጎዙለት ይኸውም፦
ኮርቻ ሲቀመጡበት ይቆረቁራል ልብስ ግን አይቆረቁርም፤ አንተም
የማትቆረቁር መልካሟን ሕገ ወንጌልን ሰጠኸን ሲሉ ነው። አንድም ልብስ
የሰውነትን ነውር ይሸፍናል፤ አንተም ከባቴ አባሳ (በደልን የማትቆጥር) ነህ
ሲሉ ነው። ጌታችን በአህዮቹ ላይ በመቀመጡ አህዮቹ በተነጠፈ ልብስ ላይ
ለመጓዝ በቁ። ሰዎችም እግዚአብሔር ካደረባቸው እንዲህ ይከብራሉ።
 የሰላም ምሳሌ፦ በዘመነ ብሉይ ነቢያት የጠብ ዘመን የመጣ እንደሆነ በፈረስ
ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ይታያሉ። ዘመነ ሰላም የመጣ እንደሆነ ደግሞ በአህያ
ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታያሉ። ጌታችንም በአህያ ተቀምጦ ወደ
ኢየሩሳሌም የመጣው ሰላምሽ እኔ ነኝ ሲል ነው። ሉቃ 19፥42 አንድም ለሰው
ልጅ ሁሉ ሰላምና ደስታ የሚሆንበት ጊዜ ደርሷልና ሲል ነው። ለዚህም ነው
ከትንሣኤ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ያለው። ዮሐ 20፥
19 ፣ ቆላ 1፥20
ፍጥነቷ ደካማ ከመሆኗ የተነሣ በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም
አሳድዶም አይዝም፤ ጌታችንም ካልፈለጉኝ አልገኝም ከፈለጉኝ አልታጣም
ሲል በአህያ ተቀምጧል።
 የእስራኤልና የአህዛብ ምሳሌ፦ እናቲቱ አህያ (ዕድገት) የእስራኤል ምሳሌ
ናት። እናት አህያ የሠረገላ ቀንበር መሸከም የለመደች እንደሆነች ሁሉ
እስራኤልም ሕግን (ኦሪትን) መጠበቅ ለምደዋልና ነው። ውርንጫዋ (ዕዋል)
የአሕዛብ ምሳሌ ናት። ውርንጫዋ ቀንበር መሸከም ገና ያልለመደች እንደሆነች
ሁሉ አሕዛብም ሕግመጠበቅ ያልለመዱ ናቸውና። ቢሆኑም ግን በአምላክነቱ
ካመኑ ልቡናቸውን ለእርሱ ማደሪያነት ከቀደሱ በእስራኤልም በአሕዛብም ላይ
አድራለሁ ሲል ነው።

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
32
ዓሣ
በባሕር ውስጥ የሚኖር እና በምግብነቱ እጅግ ተወዳጅ የሆነ እንስሳ ነው።
የሚተነፍሰው በጊል (በስንጥብ) ነው። ከባሕር ውስጥ ከወጣ ከጥቂት ሰኮንድ በኋላ ይሞታል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምዕመናን ምሳሌ ሆኖ ተጠቅሷል። ጌታችን ጴጥሮስንና ወንድሙ
እንድርያስን ዓሣ ሲያጠምዱ አገኛቸው። ከዚያም “በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ
አደርጋችኋለሁ።” አላቸው። ማቴ 4፥19 ሰውን እንደ ዓሣ፣ ወንጌልን እንደ መረብ፣ ዓለምን
እንደ መረብ አድርጋችሁ እንድታስተምሩ አደርጋችኋላሁ ሲላቸው ነው።

በማቴ 14፥17-21 ላይ እንደ ተጻፈው ጌታችን ሁለቱን ዓሣ እና አምስቱን እንጀራ አበርክቶ


አብልቷል። አምስቱ እንጀራ የአምስቱ አዕማደ ምስጢራት ምሳሌ ሲሆኑ ሁለቱ ዓሣ ደግሞ
የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ ምሳሌዎች ናቸው። ዓሣ ከባሕር ሲወጣ ይሞታል
ምዕመናንም ከሕገ እግዚአብሔር ሲወጡ በነፍስም በሥጋም ይሞታሉ።

ተግባር

23. ተማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዋኖስ፣ አንበሳ፣ ሰጎን፣ የሜዳ አህያ፣
ገብረ ጉንዳን፣ ሽኰኰ፣ አንበጣ፣ እንሽላሊት፣ ውሻ፣ እርያ፣ ቁራ፣ ቀበሮ፣
ተኩላ፣ እባብ፣ እፉኝት ስለተሰኙት እንስሳት የተገለጸውን እንዲሁም
ምሳሌነታቸውን ጽፋችሁ በመምጣት ለተማሪዎችና ለመምህሩ
ያንብቡላቸው።

የሚሰጠው የትምህርት ርዕስ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ እንስሳት እና እጽዋት ( . .


. የቀጠለ)

የዕለቱ ጥቅስ፦ “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ” ዮሐ 15፥1

4.2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ እጽዋት እና ምሳሌዎቻቸው

ልዩ ልዩ የዕፅዋት ዓይነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰዋል። ምንም እንኳን


በፍጥረት ጊዜ ዕፅዋት በአንድ ስም ተጠቃለው መፈጠራቸው ቢነገርም እንደ ሚሰጡን
አገልግሎት እና እንደየአስፈላጊነቱ እጅግ የተወሰኑት ብቻ ከዚያ በኋላ በስም ተጠርተዋል።
ከእነዚህም መካከል ለቤተ መቅደስ አገልግሎት፣ ለምሳሌነት፣ ለምግብነት፣ ለመድኃኒትነት .

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
33
. . ወዘተ ሥራ ላይ በመዋላቸው የተነሣ የተጠቀሱ አሉ። ከእነዚህም መካከል የተወሰኑትን
ቀጥሎ እንመለከታለን።

ዕጣን
የዕጣን ዛፍየሚገኘው በበረሃ ነው። የቤተ መቅደስ አገልግሎት ከተጀመረበት ጊዜ
አንሥቶ ዕጣን የጸሎት ማሳረጊያ መሥዋዕት ሆኖ በካህናት ይቀርባል። ዘጸ 30፥1 ፣ 7፥27
፣ ዘሌ 16፥12-13 “የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት
ወጣ” ራእ 8፥3-4 ፣ ራእ 5፥8

 ዕጣን የጌታችን ምሳሌ ነው። ሰብአ ሰገል ዕጣን አምኃ አድርገው የሰጡትም እንደ
ዕጣን ትሰዋልናለህ ሲሉ ነው። ማቴ 2፥11 ዕጣን ስለ ሌሎች ጸሎት እንደሚሠዋ
ጌታችንም ስለ ሰው ልጆች ሁሉ ራሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል። ለዚህም ነው
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ምዑዘ ባሕርይ የምትለው። የዕጣኑ መዓዛ የጌታችን
ርኅራኄና ፍቅር ምሳሌ ነው። ዕጣኑን ያሸተተ ሁሉ ደስ እንዲሰኝ የጌታችን
ርኅራኄና ፍቅር የተሞላበት ጉዞ ያስተዋለ ሁሉ ደስ ይሰኛልና።
 ዕጣን የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው። “መዓዛዋም እንደ ከርቤና ዕጣን የሆነችው፣
ከልዩ ከነጋዴ ቅመም ሁሉ የሆነችው ይግች ከምድረ በዳ እንደጢስ ምሰሶ
የወጣችው ማን ናት?” ሲል በምድረ በዳ ከተመሰለችው ዓለም ተለይታ ወደ ሰማይ
ንጉሥ ወደ እግዚአብሔር የምትዘረጋ ጸሎቷም የሚሠማላት ቤተ ክርስቲያንን
በዕጣን መስሏታል። መኃ 3፥6 ደግሞም የእመቤታችን ምሳሌ ነው። ጠቢቡ
ሰሎሞን እንዲህ ሲል የተናገረው ከሰው ልጆች ሁሉ (ከምድረ በዳ) ተለይታ ሰማያዊ
ምግባርን ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ልቡናን፣ ንጽሐ ነፍስን ገንዘብ ያደረገች እመቤታችን
ናት ሲል ነው።
 ዕጣን የምዕመናን ምሳሌ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ
ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ
ለእነዚህም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን” እንዳለ 2ኛ ቆሮ 2፥15-16።
ዕጣን በተሠዋ ቁጥር ወደ ላይ እንደሚወጣ የክርስቲያኖችም ሕይወት ከክብር ወደ
ክብር ወደ ሰማያዊ ማዕረግ ትሄዳለችና። የዕጣን ሽታ አካባቢን እንደሚለውጥ
ክርስቲያኖችም ሥጋዊ ሥራ የነገሠበትን ዓለም በምግባራቸው አሸናፊነት
ይለውጣሉና።

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
34
ወይን
በመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ሥፍራ ከተሰጣቸው ዕፅዋት አንዱና ዋነኛው ነው። በሀገረ
እስራኤል ከጥንት ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ ይመረታል። “ኖኅም ገበሬ መሆን ጀመረ ወይንም
ተከለ” ዘፍ 9፥20 ያለው እና “መለኬጼዲቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ” ዘፍ 14፥15
ያለው ከጥንት ጀምሮ የወይን እርሻ እንደ ነበር ያመለክታል።

የወይን እርሻ በዙሪያው ቅጥር ይቀጠርለታል ወይም አጥር ይታጠርለታል። በእስራኤል


ለወይን እርሻ ጠባቂ አለው። ለጠባቂውም ዳስ ወይም ግንብ ወይም ማማ ይሠራለታል።
ቀበሮዎች ሌቦችና መንገደኞች የወይኑን ተክል ስለሚተናኮሉ በመከር ወራት ጠባቂዎች
ማማቸውን ሠርተው ሌት ተቀን ይጠብቃሉ። “የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ቀበሮዎች፣
ጥቃቅን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን” ሲል ጠቢቡ የተናገረው ምስጢሩ ሌላ ቢሆንም
ቀበሮዎች ወይንን እንደሚተናኮሉ ያሳያል። ማኃ 2፥15 የመጥመቂያ ጒድጓስ እዚያው
ይሠራል። ኢሳ 5፥1-2 ፣ 1፥8 ፣ 12፥1 በየዓመቱም ይገረዛል። የወይን ጠጁን ለማውጣትም
ፍሬው በመጥመቂያ ጒድጓድ ውስጥ ይረገጣል። ኢሳ 16፥10 ሐረጉም በመደገፊያ
ይዘረጋል።

ወይን የሚተከለው ከኮረብታና ከተራራ ጥግ ነው። ኢሳ 5፥1 የወይን ተክል ከሥሩ ውኃ


ያለው ለስላሳ መሬት ይወዳል። ጫካ ተመንጥሮ ከለሰለሰ በኋላ በእርሻው ዙሪያ የድንጋይ
ካብ እየተካበ ከአንድ እስከ አራት ክንድ ስፋት ያለው ደረጃ እየተበጀ ይደለደላል።

የወይን ተክል ቶሎ ያድጋል። ክንዱ እየተቆረጠ ሰባት ሰባት ክንድ ያህል እየተራራቀ
ይተከላል። ቅርንጫፉ እየተከረከመ ተኮትኩቶና ተጠብቆ ሁለት ዓመት ያህል ይቆያል።
በሦስተኛው ዓመት ፍሬ እንዲያፈራ ይተዋል።

 የወይን ተክል የምዕመናን ምሳሌ ነው። “ስለ ወዳጄና ስለ ወይን ቦታው ለወዳጄ
ውኔ እቀኛለሁ። ለወዳጄ በፍሬያማ ኮረብታው ላይ የወይን ቦታ ነበረው። በዙሪያው
ቆፈረ፣ ድንጋዮችንም ለቅሞ አወጣ፣ ምርጥ የሆነውን አረግ ተከለበት፣ በመካከሉም
ግንብ ሠራ ደግሞም የመጥመቂያ ጒድጓድ ማሰለት፣ ወይንንም ያፈራ ዘንድ
ተማመነ፣ ዳሩ ግን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ” ኢሳ 5፥1-2
የወይን ተክል የተባሉ እስራኤል ናቸው። ወዳጄ የተባለ እግዚአብሔር ነው።
ድንጋዮችንም ለቅሞ አወጣ አለ፤ አሕዛብንና እንግዶች አማላእክትን አጠፋ ሲል
ነው። ግንብ ሠራ አለ፤ ከመከራ ከወረራ ጠበቃቸው ሲል ነው። የመጥምቂያ
ጒድጓድ ማሰለት አለ፤ ገነት መንግስተ ሰማያትን አዘጋጀላቸው ሲል ነው። ይህ
ሁሉ ቢደረግም ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ አለ፤ ተመልሰውም በጣኦ አምልኮ በኃጢኣት
ሥራ ተጠመዱ፣ ጌታቸውን ሰቀሉ። ውኃ ቢጠማው ኃሞትና ከርቤ ሆምጣጤም

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
35
አቀረቡለት ሲል ነው። ወይን በየዓመቱ ይገረዛል፤ ምዕመናንም በየጊዜው በንስሐ
ይታደሳሉ።
 ወይን የፍሬ ሃይማኖት ምሳሌ ነው። “አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ
ለገበሬዎችም አከራይቶ ለብዙ ዘመን ወደ ሌላ ሀገር ሄደ በጊዜውም የወይኑ
አትክልት ጌታ ገበሬዎች ካፈሩት ፍሬ እንዲሰጡት አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎቹ
ላከ። ገበሬዎቹ ግን ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት። ጨምሮም ሌላውን ባሪያ ላከ።
እነርሱም ያን ደግሞ ደበደቡት። አዋርደውም ባዶውን ሰደዱት። ጨምሮም
ሦስተኛውን ላከ። እነርሱም ይህን ደግሞ አቁስለው አወጡት። የወይኑም አትክልት
ጌታ ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን አይተው
ያፍሩታል አለ። ገበሬዎቹ ግን አይተው እርስ በእርሳቸው ሲነጋገሩ፦ ወራሹ ይህ
ነው፤ ርስቱ ለእኛ እንዲሆን እንግደለው አሉ። ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ
አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋቸዋል?
ይመጣል፤ እነዚህንም ገበሬዎች ያጠፋል፤ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች
ይሰጣል።” የሚል ምሳሌ ጌታችን ተናግሯል። ሉቃ 20፥9-16
በዚህ ምሳሌ የወይኑ ጌታ የተባለ አብ ነው፣ ገበሬዎች የእስራኤል ዘሥጋ፣ የወይኑ
ፍሬ የምግባረ ሃይማኖት፣ ወራሹ ልጅ የአብ የባሕርይ ልጅ የክርስቶስ፣ ሦስቱ
ባሮች የካህናት፣ የመሳፍንት /የነገሥታት/ እና የነቢያት ምሳሌዎች ናቸው።
እስራኤል በዘመነ ካህናት፣ በዘመነ መሳፍንት /ዘመነ ነገሥታት/ እና በዘመነ
ነቢያት ፍሬ ሊያፈሩ ቀርቶ የእግዚአብሔር መልእክተኞችን አሰቃይተዋልና። ኋላ
ግን አንድ ልጁን ላከላቸው እርሱንም ሰቀሉት።
 ወይን የጌታችን ምሳሌ ነው። ራሱ “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ” እንዳለ።
ዮሐ 15፥1 እመቤታችንም ሐረገ ወይን /የወይን ሐረግ/ ትባላለች። ልጇ ኢየሱስ
ክርስቶስ ደግሞ በወይኑ ፍሬ ይመሰላል። ከወይን ሐረግ የወይን ፍሬ እንደሚገኝ
ድንግል ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስን አስገኝታለችና።
 የወይን ጠጅ ለቁስለ ሥጋ መድኃኒት እንደሆነ /ሉቃ 10፥34 ፣ 1ኛ ጢሞ 5፥
23/ ጌታችን ከቁስለ ሥጋና ከቁስለ ነፍስ የሚያድን እውነተኛ መድኃኒት ነውና።
ወይን በብሉይ ኪዳን ለመሥዋዕት ይቀርብ ነበር። ዘጸ 29፥40 በሐዲስ ኪዳን ግን
በወይን መልክ የምንቀበለው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊው ደሙን ነው።
“ጽዋውንም አንሥቶ . . . የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” ብሎ ራሱ ጌታችን
እንደተናገረ። ማቴ 26፥27-29 ጌታችንም ደሜ አለ አንጂ የደሜ ምሳሌ አላለም።

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
36
ወይራ
በአብዛኛው በእስራኤልና በኢትዮጲያ ይገኛል። በብሉይም ሆነ በሐዲስ የወይራ ዘፍ
በቤተ እግዚአብሔር ውስጥ ከፍተኛ አገልግሎት አለው። ከወይራ ተክል ዘይት ይገኛል።
ሮሜ 11፥17 የወይራ ዛፍ ፍሬ የሚያፈራው በተተከለ በሰባት ዓመት ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን
አንድ አንድ ዓመት እያሰለሰ በሁለት በሁለት ዓመት ፍሬ ይሰጣል። አንድ የወይራ ዛፍ ጥሩ
ሆኖ ከተጠበቀ እና ሥፍራውም ከተመቸው በአንድ ጊዜ ከሃምሳ እስከ መቶ ሊትር ሊገኝበት
ይችላል።

ከወይራ ፍሬ የሚገኘው ዘይት ለምግብነት ይውላል።በመጽሐፍ ቅዱስ ዘይት እየተባለ


የሚጠራው ከወይራ የሚገኘው ነው። 1ኛ ነገ 17፥8-16 የወይራ ዛፍ ከምግብነት ባሻገር
ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውላል።

 ለመሥዋዕት፦ እግዚአብሔር የእስራኤል ልጆች እንዲያመጡለት ካዘዛቸው


ከወርቁና ከብሩ ሌላ የመብራት ዘይትና የቅብዓት ዘይትም አብረው እንዲያቀርቡ
አዝዟል። ዘጸ 25፥6የመብራት ዘይት ካህ ናት በአገልግሎት ጊዜ እንዲያበሩት
/እንዲሠዉት/ ሲሆን የቅባት ዘይት ደግሞ ከእህል ቁርባን ጋር ተደባልቆ
ለመሥዋዕት የሚቃጠል ነው። ዘጸ 27፥20 ፣ 29፥1-2 ፣ 23፥29
 ለመድኃኒት፦ ለምስጢረ ቀንዲል የሚዘጋጀው ቅብዓ ቅዱስም የሚዘጋጀው ከወይራ
ዘይት ነው። ሩኅሩሁ ሳምራዊውም ለቁስለኛው ሰው በቁስሉ ላይ ያፈሰሰለት
የወይራ ዘይት ነው። ሉቃ 10፥34 ፣ ማር 6፥13 ፣ ያዕ 5፥14
 ለሢመት /ለሹመት/፦ ለሥልጣነ ክህነት ለቅብዐ መንግሥት የታጩ ሰዎች
ሥርዓተ ሲመት ሲፈጸምላቸው ከጸሎት ጋር ቅብዐ ቅዱስ ይቀባሉ። ይህም
ሹመታቸው ጸድቋል መንፈስ ቅዱስ ተቀብሎታል ማለት ነው። ዘጸ 29፥7 ፣ 1ኛ
ሳሙ 16፥13
 ለሰውነት ቅባት፦ “ . . . ዘይትም ፊትን ያበራል።” መዝ 103፥15 ፣ ዳን 10፥3
፣ ሉቃ 7፥46

ወይራ የሰላም ምልክት ነው። ኖኅ የላካት ርግም ውኃው እንደጎደለ ለማብሠር


የለመለመ የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ እንደመጣች። ዘፍ 8፥11 ርግሟ የእመቤታችን፣ ይዛ
የመጣችው ቅጠል የጌታችን ምሳሌ ነው።

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
37
ዘንባባ
ዘንባባ የሰሌን ተክል ነው። በብሉይ ኪዳን የዳስ በዓል ሲከበር እስራኤል ለዳስ
መሥሪያ ከሚጠቀሙባቸው ዛፎች መካከል አንዱ ነው። ነህ 8፥14-15

አብርሃም ይስሐቅን፣ ይስሐቅም ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ፣ ዮዲትም ሆሎፎርኒስን በገደለች ጊዜ


የሰሌን ቅርንጫፍ /ዘንባባ/ ቆርጠው አመስግነዋል። በዚያ ል ማድ በሆሳዕና ዕለትም ጌታችንን
ዘንባባ ይዘው ሊቀበሉት ወጡ። ዘንባባ የጻድቃን ምሳሌ ነው። “ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል።
” መዝ 91፥12

በለስ
በለስ ቅጠሉ ሰፋፊ፣ ነጭ ደም ያለው፣ ፍሬው የሚበላ አጭር ዛፍ ወይም ቁጥቋጦ
ነው። እንደ ወይን ሁሉ በተለይ በሀገረ እስራኤል የበለስ ፍሬ ለምግብነት ይውላል። ዘዳ 8፥
8 ፣ ዕን 3፥17 ፣ ሚክ 4፥4

ጌታችን መድኃኒታችን “በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ። በመንገድም አጠገብ


በለስ አይቶ ወደ እርሷ መጣ። ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና ለዘላለሙ ፍሬ
አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያን ጊዜውኑ ደረቀች።” ማቴ 21፥18-21 ደግሞም ለእስራኤል
ምሳሌነት የተነገረም ነው። በለሷ ቅጠል ብቻ እንጂ ፍሬ እንዳልተገኘባት ሁሉ እስራኤልም
የአብርሃም ልጆች ነን ከማለት በስተቀር ምግባረ ሃይማኖት ሳይገኝባቸው ቀርተዋልና።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ዳግም ምጽአት በበለስ ምሳሌ ተናግሯል።


“ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ። ጫፏ ሲለሰልስ፣ ቅጠሏም ሲያቆጠቁጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ
ቀረበ ታውቃላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ (ከላይ የዘረዘራቸውን
ምልክቶች) በደጅ እንደ ቀረበ ዕወቁ” እንዲል ማቴ 24፥32-35 እስራኤል የበጋን መምጣት
ከሚያውቁበት አንዱ ባሕርይ የበለስ ቅጠል ሲያቆጠቁጥና ጫፉ ሲለመልም ነው። ቅጠሏ
ሲረግፍ ደግሞ ክረምት እንደ መጣ ይረዳሉ።

ተግባር

22. ተማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሸምበቆ፣ ከርቤ፣ ሰናፍጭ፣ ስንዴ፣


ስለተሰኙት ዕፅዋት የተገለጸውን እንዲሁም ምሳሌነታቸውን ጽፋችሁ
በመምጣት ለተማሪዎችና ለመምህሩ ያንብቡላቸው።

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
38
መርጃ መሳሪያ እና ማመሳከሪያ
ይህንን ትምህርት መምህሩ

1. መጽሐፍ ቅዱስ
2. ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ራዕይ ድረስ ያሉ የትርጓሜ መጻህፍት
3. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማህበረ ቅዱሳን
4. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በዲ. አባይነህ ካሴ ቁጥር 1 እና 2
5. መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ እና የማጥናት ዘዴ በመ.ቸሬ አበበ
6. በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኙ ከተሞች እና ሀገራት ዲ.ዳንኤል ክብረት
7. የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች
ማስተማሪያ ያዘጋጀው መጽሐፍ
8. መርሐ ህይወት መጽሐፍ እና ሌሎች መጻህፍት

በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት
ክፍል የተዘጋጀ
39

You might also like