Download as doc, pdf, or txt
Download as doc, pdf, or txt
You are on page 1of 4

***ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትና አስተምህሮአቸው ***

(ክፍል #1)

✍. ታሪካዊ ዳራ

'የዘመኑ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት እንቅስቃሴ መነሻው በ 19 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበረው


የዳግም ምጽአት እንቅስቃሴ/Advent movement/ ነበር። ብዙ ሰባኪዎች በአውሮፓና በሌሎችም የአለም ክፍሎች
የክርስቶስን በቶሎ መምጣት እየሰበኩ በነበሩበት ሰአት ይህ እምነት በሰሜን አሜሪካ በከፍተኛ ሁኔታ ተጽእኖ አሳደረ።
የዚህ የሰሜን አሜሪካ የዳግም ምጽአት እንቅስቃሴ ዋና አንቀሳቃሽ የነበረው የባፕቲስት ቤ /ክያን ፈቃደኛ ወንጌላዊ
የነበረው ዊሊያም ሚለር ነበር'(1)፡፡

ዊሊያም ሚለር(1782_1849) ከክርስቲያን ቤተሰብ የተወለደ ሲሆን በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ በተነሳው
የደይዝም ፍልስፍና አማካኝነት እምነቱን በመተው በግሉ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ።

ሚለር ለሁለት ተከታታይ አመታት ማለትም እ.ኤ.አ ከ 1816_1818 ዓ.ም ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ካጠና በኋላ

“በ 25 አመታት ውስጥ አሁን ያለንበት ሁኔታ ወደ ፍጻሜ ይመጣና ክርስቶስ በድጋሚ ይመጣል” ወደሚል
ድምዳሜ ደረሰ።

ሚለር ወደዚህ ድምዳሜ የደረሰው በ ዳን 8፡14 ጥቅስ ተመስርቶ ሲሆን በዚህም ጥቅስ ላይ ያለውን ቤተ መቅደስ
ይህች የምንኖርባት ምድር እንደሆነችና የቤተ መቅደሱ መንጻት ደግሞ የዚህች ምድር በእሳት መንጻት እንደሆነ
በመተርጎም ሚለር በ 2300 ቀናት ማብቂያ ላይ በ 1843 ዓ.ም ክርስቶስ ወደዚች ምድር ይመለሳል ወደሚል
ድምዳሜ ደረሰ። ነገር ግን በጊዜው የነበሩ ክርስቲያኖች በሙሉ ይህ አይነት መረዳት ስለሌላቸው ምናልባት
የደረስኩበት ድምዳሜ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል ከሚል ፍርሃት የተነሳ ይህንን ትምህርቱን ለሌሎች መንገር ፈርቶ
ነበር። ስለሆነም ተጨማሪ አምስት አመታትን (1818_1823) መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ድምዳሜው ትክክል
እንደሆነ ካረጋገጠ በኋላ ትምህርቱን ሀ-ብሎ ለጎረቤቶቹ መናገር ጀመረ። ሆኖም ግን በጊዜው የሚያዳምጡት ሰወች
በጣም ጥቂት ነበሩ(2)

ሚለር በመቀጠል ለሌላ ዘጠኝ አመታት(1823_1832) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ቀጠለ። ከዚህ ጥናቱ በኋላ ስለሆነው
ነገር የአድቬንቲስት ቤ/ክያን ታዋቂ የታሪክ ጸሃፊ የሆኑት ጆርጅ አር ናይት እንዲህ ይላሉ፦

“በዚህ ወቅት ሊመጣ ስላለው የማይቀረው ፍርድ ለሌሎች የማጋራት የህሊና ጫና እየበዛበት መጣ። 'ሂድና ለዓለም
እየመጣ ስላለው አደጋ አስጠንቅቅ' የሚል ሃሳብ ያለማቋረጥ ማስጨነቁን ቀጠለ። ሚለር 'ይህንን የህሊና ወቀሳ
ላለመስማት ማድረግ የምችለውን ሁሉ አደረግኩ' ይላል። ነገር ግን ከህሊናው ሸሽቶ ማምለጥ አልቻለም ነበር።
በመጨረሻም እግዚአብሔር መንገድ ከከፈተለት ስራውን እንደሚሠራ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ገባ።
ከማንኛውም ስፍራ ለህዝብ እንዲሰብክ ጥሪ ከመጣለት እንደሚቀበልና የክርስቶስን ዳግም ምጽአት መልእክት
እንደሚያስተላልፍ ቃል ገባ። ሁኔታውን እንዲህ ብሎ ጽፎታል፦ 'በቅጽበት ሸክሜ ሁሉ ከላዬ ወረደ። ከዚህ በፊት
እንዲህ አይነት ጥሪ በፍጹም መጥቶልኝ ስለማያውቅና ማንም ይጠራኛል ብየ ስላላሰብኩ ሐሴት አደረግኩ።' ነገር ግን
ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን በመፈጸም በተስማማበት በተኩል ሰዓት ውስጥ በዳግም ምጽአት ላይ እንዲሰብክ
የመጀመሪያ ጥሪ መጣለት፡፡ በዚህን ጊዜ የተሰማውን ስሜትና የወሰደውን እርምጃ እንዲህ ገልጾታል፦ 'ከእግዚአብሔር
ጋር ስለፈጸምኩት ቃል ኪዳን በራሴ በጣም ተናደድኩ ወዲያውኑ በእግዚአብሔር ላይ በማመጽ ላለመሄድ ወሰንኩ።'
ከዚያ በኋላ በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር ለመታገል ከቤት ወደ ውጪ ወጣ። ከአንድ ሰዓት በኋላ ተሸነፈና መልእክቱን
ለማስተላለፍ ወሰነ።”(3)
ከዚህም የተነሳ ብዙ ሰወች የሚለርን(ኢየሱስ በ 1843 ዓ፡ም ዳግም ይመጣል የሚለውን) አስተምህሮ ተቀብለዋል።
የዳግም ምጽአትን መልእክት ሰምተው እምነቱን ከተቀበሉ ሰወች መካከል ጆሹዋ ቪ ሃይምስ አንዱ ነው። የዚህም
ሰው(ሀይምስ) አስተምህሮውን መቀላቀል በሚለር ለተጀመረው እንቅስቃሴ የጀርባ አጥንት ሆኗል ማለት ይቻላል።
ህዝብን የማነሳሳት ችሎታ እንደነበረው የሚነገርለት ሀይምስ ይህንን አስተምህሮ(በ 1843 ዓ.ም ክርስቶስ ወደዚች
ምድር ይመለሳል የሚለውን) በ 3 ወር ጊዜ ውስጥ በመላው አለም በፍጥነት ማዳረስ ችሎ እንደነበር ናይት
ይመሰክራሉ። ለዚህም ይረዳው ዘንድ በዋናነት የተተቀመው የመገናኛ ብዙሃንን ነበር። በተለይም የህትመት
ውጤቶችን ተጠቅሞ አስተምህሮውን አስተዋውቋል። ታሪክ ጸሃፊው ናታን ሀች ይህን ሁኔታ እንዲህ ነበር የገለጸው፤
“ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የመገናኛ ብዙሃን ወረራ”
ሀይምስ አስተምህሮውን ለማስፋፋት የተጠቀመበት መንገድ በዋናነት የህትመት ውጤቶችን ይሁን እንጂ ነገር ግን
ከህትመት ውጤቶች በተጨማሪ የተለያዩ ኮንፈረንሶችንና ስብሰባዎችን በማዘጋጀት የዳግም ምጽአትን ትምህርት
አስተውውቆ ነበር።

ነገር ግን 1843 ዓ.ም ኢየሱስ እንደጠበቁት ሳይመጣ ስለቀረ ሚለር ወዲያውኑ አስተምህሮውን በመቀየር ዳን 8፡14
ላይ ባለው የ 2300 ቀናት ትንቢትና የአይሁድን የቀን አቆጣጠር መሰረት በማድረግ ክርስቶስ የሚመጣው ከመጋቢት
21/1843 እስከ መጋቢት 21/1844 ድረስ ነው በማለት መስበክ ጀመረ። የኋላ ኋላ ግን በዚህም አመት የኢየሱስ
ምጽአት ሳይሆን ቀረ። ጠበቁት እርሱ ግን የውሃ ሽታ ሆነባቸው። በዚህ ጊዜ ነበር ሚለርም ሆነ ሀይምስ እንዲሁም
ሚለራውያን(የሚለርን አስተምህሮ የተከተሉት) በትልቅ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የወደቁት። ይህም ክስተት
በቤተክርስቲያኒቷ ታሪክ “ታላቁ ተስፋ መቁረጥ”(The Great Disappointment) በመባል ይታወቃል።

በመጋቢት 21/1844 ይመጣል ያሉት ጌታ ሳይመጣ በመቅረቱ ሚለራውያን ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ገቡ።
እንቅስቃሴውንም ይመራ የነበረው ሚለር በማግስቱ ማለትም በመጋቢት 25/1844 ዓ.ም ለሀይምስ በጻፈው ደብዳቤ
እንዲህ ብሎ ነበር፤
“በአሮጌ መቀመጫየ ላይ ተቀምጫለሁ። ከአሁን በኋላ የዚችን ምድር ህዝብ እንዳስጠነቅቅ እግዚአብሔር መንገድ
ያዘጋጅ ይሁን ወይም አይሁን የማውቀው ነገር የለኝም።” ነበር ያለው።

ከሚለር ባልተናነሰ ሁኔታ ተስፋ ቆርጦ የነበረው ሀይምስ ደግሞ በሚያዝያ 24/1844 ዓ.ም እንዲህ ብሎ ጽፎ ነበር፤
“የአይሁዶች አመት ስላለፈ ጓደኞቻችንና ህዝቡ እኛ ስላለን አቋም የሆነ መግለጫ የመፈለግ መብት አላቸው። እኛ
የጠበቅነውና ይመጣል ብለን ያሳወቅነው ጊዜ ማለፉን መግለጽና ሙሉ በሙሉ አምነን መቀበል አለብን። የአይሁዶች
አመት አልፏል፤ አዳኙም አልመጣም። ትንቢታዊ ወቅቱን በትክክል በማስላት ላይ መሳሳታችንን በተመለከተ
እውነታውን በፍጹም አንሸፋፍንም።”

በ 1844 ዓ፡ም ክርስቶስ ካለመምጣቱ የተነሳ ሚለራውያን በታላቅ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ከመውደቃቸው የተነሳ
ብዙዎቹ እምነቱን ጥለው በመውጣት ሌላ እምነት ሲመሰርቱ ግማሾቹ ደግሞ ወደ ቀድሞ ቤተክርስቲያናቸው
ተመልሰዋል። በአጠቃላይ ግን ሚለራውያን ከ 1844 ዓ.ም በኋላ ለሶስት ተከፍለዋል።
❖. የመጀመሪያው በሀይምስ የተመራው ቡድን ሲሆን ይህም ቡድን በ 1844 ዓ.ም ምንም አይነት ክስተት
አልተከሰተም የክርስቶስ መምጫም በማንኛውም ጊዜ ሊሆን ስለሚችል ሁልጊዜ ነቅተን መጠበቅ አለብን የሚሉ
ሲሆን ዊሊያም ሚለርም ይህንን ቡድን ተቀላቅሏል።
❖. ሁለተኛዎቹ ደግሞ “መንፈሳውያን” (Spritualizers) የሚባሉት ሲሆኑ ይህንንም ስያሜ ያገኙት ለመጋቢት
21 መንፈሳዊ ትርጉም በመስጠታቸው ንው። እነዚህ ቡድኖች ጊዜውም ሆነ ክስተቱ ትክክል ነበር። ግን አመጣጡ
ሳይታይ በመንፈስ ነው የሚል አቋም ያላቸው ነበሩ።
❖. ሶስተኛው ቡድን ደግሞ በጊዜ ቀመራቸው ትክክል እንደሆኑና ይሆናል ብለው በጠበቁት ክስተት ግን ስህተት
መሆናቸውን የሚያምኑ ነበሩ። በሌላ አገላለጽ በመጋቢት 21 የተፈጸመው የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ሳይሆን ሌላ
ክስተት ነው የሚሉ ናቸው። ይህ ቡድን ንው እንግዲህ ዛሬ ላለችው የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤ/ክያን መሰረት
የሆነው። የቤ/ክያኗም ቀደምት ታላላቅ መሪዎች የሚባሉትም (ኤለን ጂ ኃይት፣ ጀምስ ኃይትና ጆሴፍ ቤትስ) እዚህ
ቡድን ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።

ይህንንም ቡድን(አሁን የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤ/ክያን) ይመሩ ከነበሩት መሪዎች በበለጠ መልኩ ቡድኑ ወደ
ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነት እያደረገ ላለው ሽግግር የኤለን ኃይት ሚና ከፍተኛ ነው። ኤለን ኃይት ቡድኑን አቅጣጫ
በማሳየት፣ ምሪትን በመስጠትና አስተምህሮውንም በመቅረጽ አስተዋፅኦዋን አበርክታለች።

ነገር ግን አንዳንድ የቤ/ክያኒቷ ታሪክ ጸሐፊዎች ይህንን በመካድ ኤለን ኃይት ለሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤ /ክያን
አስተምህሮ ምንጭ እንዳልሆነች ይሞግታሉ። ለምሳሌ ታዋቂው የቤ/ክያኒቷ የጽሪክ ጸሐፊ ጆርጅ አር ናይት እንዲህ
ነበር ያለው፦
“ለእያንዳንዱ ታላቅ የአድቬንቲስት አስተምህሮ ማለት የሚቻለው ነገር ተመሳሳይ ነው። ቀደምት የእምነቱ ፈር
ቀዳጆች አስተምህሮአቸውን መልክ ባስያዙት ጊዜ የተከተሉት የመጀመሪያው ዘዴ ከስምምነት ላይ መድረስ
እስኪችሉ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ነበር። በዚህ ሰአት ባጠኑት ርዕስ ላይ በመጀመሪያ ጥናታቸው ወቅት
የደረሱበት ስምምነት ትክክል እንደነበር ማረጋገጫ ለመስጠትና በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ምክንያት አብዛኞቹ
በደረሱበት ስምምነት ላይ ያልተስማሙትን ለመረዳትና እንዲስማሙ ለማድረግ አንዳንድ ጊዜ ኤለን ኃይት ራእይ
ትቀበል ነበር። ስለዚህ የቤ/ክያኗን አስተምህሮ አመሰራረት በተመለከተ የሚሰስ ኃይትን ሚና እንደማረጋገጫ ሰጪ
እንጂ እንደ ሀሳብ አፍላቂ አድርገን አንመለከትም። ነገር ግን በምዕራፍ 4 ላይ እንደምንመለከተው እሷ
በቤተክርስትያኗ መሰረታዊ አስተምህሮ ከተጫወተችው ይልቅ በአድቬንቲስቶች የአኗኗር ዘይቤ ላይ የበለጠ ወሳኝ
ሚና ተጫውታለች።አንዳንድ ቀደምት የአድቬንቲስት ቤ/ክያን መሪዎች ሰዎች የትንቢት ስጦታን ያለአግባብ ጥቅም
ላይ ሊያዉሉት የሚችሉበት ሁኔታ ስለመኖሩ ይሰማቸው ነበር። ለምሳሌ ሰንበት መቼ እንደሚጀመርና እንደሚያበቃ
በተመለከተ አድቬንቲስቶች ለብዙ አመታት ልዩነት ነበራቸው። ጥልቅ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከተደረገ በኋላ
ሰንበት ከፀሀይ ግባት እስከ ፀሀይ ግባት እንደሆነ በ 1855 ከስምምነት ላይ መድረስ ተቻለ። ነገር ግን ከቀደምት አባቶች
አንዱ የነበረው ቤትስ ሰንበት የሚጀምረውና የሚያበቃው በአስራ ሁለት ሰአት ነው በሚለው አቋሙ ፀና። በዚህን
ወቅት ከዚህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የተደረሰውንና ሰንበት ከጸሐይ ግባት እስከ ጸሐይ ግባት ነው
የሚለውን አቋም የሚያጸናውን ራእይ ሚሰስ ኃይት ተቀበለች። ያ ራእይ ቤትስንና ባልደረቦቹን ከሌሎች ጋር ወደ
ስምምነት ለማምጣት በቂ ነበር። የሚገርመው ነገር ቢኖር ያ ራእይ ኤለን ጂ ኃይት ራሷ በዚህ ዙሪያ ያላትን
አመለካከትም ለውጧል።”(4)

እንግዲህ በጆርጅ ናይት ጥናት መሰረት ኤለን ጂ ኃይት የቤ/ክያኒቷ መሰረታዊ አስተምህሮ (Basic doctrine) ላይ
በቀጥታ ተሳትፎ ባታደርግም ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ለደረሱበት ድምዳሜ የትክክለኛነት ማረጋገጫ
ሰጪ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ወቅት ባልተስማሙበት ርዕስ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ (Infalliable
Interpreter) እንደነበረች አይተናል።

እንግዲህ ደግሞ እዚህ ጋር እንደ ባለአዕምሮ የምናነሳው ጥያቄ ለኤለን ጂ ኃይት በራዕይ የሚገልጥላት አካል ማነው?
የአንድ ቤ/ክያን መሰረታዊ አስተምህሮስ በሁለትና በሶስት ግለሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይቀረጻል ወይ ? እነዚህስ
ሰዎች ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ምን ያህል ነው? ወዘተ... የሚል ናቸው።

ይህ ጥያቄ ደግሞ በቀጥታ ኤለን ጂ ኃይት በእርግጥ ማን ናት? በአድቬንቲስቶችስ ዘንድ ያላት ስፍራ ምን አይነት ነው?
ወደሚለው ጥያቄ ይወስደናል፡፡

✍ . ኤለን ጂ ኃይት በእርግጥ ማን ናት?


በክፍል ሁለት ይጠብቁ!!

------------------------
(1). 'የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች አጭር ታሪክ' በጆርጅ.አር.ናይት/2 ኛ እትም/ትርጉም በታምሬ ሻዕማሎ/ ገፅ 9
(2). ዝኒከማሁ ገጽ 10
(3). ዝኒከማሁ ገጽ 11
(4).ዝኒከማሁ

You might also like