Download as txt, pdf, or txt
Download as txt, pdf, or txt
You are on page 1of 1

ሕገ ወጥ ግንባታ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ቅሬታ እያስነሳ ነው

15 Dec 2017 የሀገር ውስጥ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍና የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር ባደረገው እንቅስቃሴ በ 11 ዙሮች በዕጣ
ከ 175 ሺህ ቤቶች በላይ ለተጠቃሚው አስተላልፏል፡፡ቤቶቹን ለተጠቃሚዎች ካስተላለፈ በኋላም ረጅም የአገልግሎት ዘመን እንዲኖራቸው
የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፡፡

በንፋስስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ አንድ ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ዋና የሥራ ሂደት መሪ ወይዘሮ ጥሩ መኮንን እንደነገሩን
ወረዳው ከ 18 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ያስተዳድራል፡፡ቤቶቹ በህገወጥ ግንባታና በፍሳሽ ችግሮች እንዳይጎዱ በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ
ከተደራጁ ማህበራት ጋር በመሆን ቀድሞ በመከላከል ላይ ይሰራል፡፡ችግር ተከስቶ ሲያገኝም ያደረሰው አካል ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ማስጠንቀቂያ
ይሰጣል፡፡ከአቅም በላይ ሲሆንም ለክፍለ ከተማው በማሳወቅ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡

ወይዘሮ ጥሩ ይህን ይበሉ እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው ቤቶችን የሚጎዳ ተግባር ቀድመው የተሰሩ ሥራዎችን የሚያሳይ እንዳልሆነ
አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልፃሉ፡፡የዛሬ ስድስት ዓመት የቤት ዕድለኛ ሆነው ጀሞ አንድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሠፈረ ሰላም በሚል
ስያሜ በተቋቋመው ማህበር ውስጥ በሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪ ከሆኑት መካከል ለደህንነታቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ
አንዳንድ ነዋሪዎች እንዳስረዱት ህገወጥ ግንባታው ገና ሲጀመር ለማህበራቸው፣ለወረዳው እና ክፍለከተማው አሳውቀዋል፡፡

በወቅቱ እርምጃ ባለመወሰዱ አንዱ ሌላውን እያየ በላሜራ በማጠር በህንፃው ላይ ጉዳት የሚያደርስ ተግባር እየተፈፀመ ነው፡፡የመወጣጫ
ደረጃን በመዝጋት የሚከናወነው ግንባታ ከምድር በላይ የሚኖሩት ሰዎች ደረጃ ለመውጣትና ለመውረድ እየተቸገሩ መሆኑን፤ ከፎቅ ላይ ዕቃ
በገመድ ለማውረድና ለማውጣት መገደዳቸውን፣ ህገወጥ ግንባታው የቤቶቹን ውበት ማሳጣቱን፣ አደጋ ቢከሰት፣የጤና ችግርም ሆነ ኀዘን
ቢያጋጥም ከፎቅ ለመውረድ አስቸጋሪ እንደሆነ በማስረዳት፤ የሚመለከተው አካል መፍትሄ ባለመስጠቱ ችግሩን ባሳወቁና ድርጊቱን በፈፀሙ
ነዋሪዎች መካከልም ፀብ እየተፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ወይዘሮ ጥሩ የነዋሪዎቹ ቅሬታ አግባብ መሆኑንና የደረሰውን ችግር ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል፡፡እርሳቸው እንዳሉት በጋራ መኖሪያ ቤቶች ሥር
በሚገኙ የንግድ ቤቶች እና መኖሪያ ቤቶች ከ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ከአቅም በላይ የሆኑትን 457 ህገወጥ ድርጊቶች ለይተው ለክፍለ
ከተማው ቤቶች ጽህፈት ቤት አሳውቀዋል፡፡ለ 116 ሰዎችም የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ቢሰጥም መፍትሄ አልተገኘም፡፡

በንፋስስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎበዜ ዳምጤ እንዳስረዱት ጀሞ አንድና ቆጣሪ ተብሎ በሚጠሩ
የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢዎች ህገወጥ ድርጊቱ በስፋት በመኖሩ ችግሩ የከፋ ነው፡፡የጋራ የሆነን ነገር ከልሎ መያዝ እንደማይቻል በጋራ
መኖሪያ ቤት የተደራጁትን ማህበራትና ነዋሪዎች ባለቤት አድርጎ ቀድሞ አለመሰራቱ እንዲሁም ወረዳው፣ክፍለ ከተማውና ደንብ ማስከበር
ተናብበው ባለመንቀሳቀሳቸው በነዋሪዎች የፍትሀዊነት ጥያቄ አስነስቷል፡፡
ችግሩ የመልካም አስተዳደር እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ጎበዜ በጉዳዩ ላይ አጠቃላይ ግምገማ ተካሂዶ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አመራሮችን
ከኃላፊነታቸው የማንሳት እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል፡፡ጽህፈት ቤቱ ህገወጥ ተግባራትን የመለየት ሥራዎች መጀመሩንና እስከ ታኀሣሥ
30/2010 ዓ.ም. ድረስ መፍትሄ ለመስጠት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የንፋስስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክላይ አረጋዊ በጀሞ አካባቢ በረንዳን በመከለል ተጨማሪ ቤት
መስራትና የተለያዩ ህገወጥ ድርጊቶች ሥር የሰደዱ በመሆናቸው በተደራጀ አሰራር እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡

የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ግርማ ተሰማ እንዳስረዱት ለተጠቃሚዎች የተላለፉ ቤቶች ተጨማሪ ግንባታ እንዳይከ
ናወንባቸውና ጥበቃም የሚያደርጉት በጋራ መኖሪያ ቤቶች ማህበራት የተቋቋሙ ሲሆን፣ ቤቶቹን የሚያስተዳድሩበት ደንብና መመሪያም
አላቸው፡፡ ኤጀንሲው የመማማሪያ መድረክ በማዘጋጀት መልካም ተሞክሮ ያላቸው ማህበራት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉና የተለያየ እገዛና ድጋፍ
ያደርጋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ህገወጥ ግንባታዎችን የሚከላከልበት የራሱ አሰራር እንዳለውም አመልክተዋል፡፡

ዜና ሐተታ
ለምለም ምንግሥቱ

You might also like