1 6

You might also like

Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 30

ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ ግንቦት ፳፻፲፮

ተናዳፊ ትንፋሾች መጽሐፈ ሄኖክ ጦሳና ለቅሶ በዶርዜ

ሸክላ ሠሪ የፊልም ግብዣ የተዘነጋው ታሪካችን

ፍለጋ ና ዝናብ የኛ ሰው ነብይ ልክ


1
ቅጽ ፩ ቁጥር ቅጽ፮ ፩|ግንቦት ፳፻፲፮
ቁጥር ፮ |ግንቦት ፲ ፳፻፲፮

ተናዳፊ ትንፋሾች
ውብአረገ አድምጥ ...3
ሸክላ ሠሪ
ሲራክ ወንድሙ ...9
ፍለጋ ና ዝናብ
ብርሃን ደርበው ...10
መጽሐፈ ሄኖክ
ዙበይር ኢብራሂም ...11
የፊልም ግብዣ
ኪሩቤል ሰለሞን ...15
የኛ ሰው ነብይ
ሩት ሃብተማርያም ...16
ጦሳ እና ለቅሶ በዶርዜ
ወልደሐዋርያት ዘነበ ...20
የተዘነጋው ታሪካችን
ልዑልሠገድ አስማማው ...23
ልክ
ሳምራዊት ንጉሤ ...29 ግራፊክስ ዲዛይን
ብርሃን ደርበው
2 09 23 34 24 25
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

ተናዳፊ ትንፋሾች ውብአረገ አድምጥ

ከትንፋሽ ውበት ረቂቅ የዋሽንት አልበም


የተመዘዙ የዘመን መልኮች
ረቂቅ ሙዚቃ ማለት…


ቂቅ ሙዚቃ ማለት በሙዚቃ መሳሪያዎች ብቻ የሚጫዎቱት የሙዚቃ አይነት ነው። ድምጽ (vocals) ሳይገቡበት
የሙዚቃ መሳሪያዎች ብቻ ስልት ባለው መልኩ ተዋህደው ይቀርቡበታል። በሃገራችን ረቂቅ ሙዚቃ እንግዳ
አይደለም። ከድምጽ ጋር የሚዘፈኑትን ያህል ተደማጭ ባይሆንም ለአድማጭ ግን እንግዳ አይደለም።
ለአብነትም እነ ጌታቸው መኩሪያ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ፣ ግርማ ይፍራሽዋ፣ ዳዊት ፍሬው
እንዲሁም ሞሰብ ባንዶች ከዚህ ቀደም ረቂቅ ሙዚቃዎችን ለአድማጭ እንዳደረሱ ስራቸው ምስክር ነው። እዚህ ላይ
ስማቸው ያልተዘረዘሩ ሌሎች እንዳሉም መዘንጋት የለበትም። በቅርቡም ጣሰው ወንድም የትንፋሽ ውበት የሚሰኝ
የዋሽንት አልበሙን ለአድማጭ አድርሷል።

ጥቂት ስለ ጣሰው
ልጁ ከስንጥርጥይ ጋር የነፍስ ቁርኝት አለው። በትንፋሹ
ይክምነመናል። የአንጀቱን ብሶት በአየር ሰረገላ እየጫነ ከዘመኑ
ጋር ይቆናቋል። ከሸንበቆ አገዳ በራሱ ውብ ጣቶች የተቀረጸችዋ
ዋሽንት በገዛ ጣቶቹ የዜማውን ዥረት ታወርደዋለች።

ልጁም ልቡ ለዋሽንት የተሰጠች የዘመን መናኒ ነው። ጣሰው


ወንድም ይባላል። በሀገረ ኢትዮጵያ በጎጃም ምድር በጎዛምን
ወረዳ ከውብ የገጠር ቀዬ እንደተወለደ በራሱ አንደበት ሲመሰክር
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ሰምቷል። ልጅነቱን በእረኝነትና በቡረቃ
ያሳለፈው ጣሰው የዋሽንት ልክፍቱ ከቤተሰብ ይጀምራል።

በአምባውና በቀየው እንደ ቆላ ወፍ ሲሽሞነሞን እንደ አፋፍ ላይ


ገዴ ሲነሰነስ አደገ። ልጅነቱን ከተፈጥሮና ከእንስሳት ጋር ሲተሻሽ
ከቆቅና ከጅግራ ጋር ሲተናነቅ ቦርቆበት ከነፈ።

የዋሽንትን ነዛሪ ድምጾች በልቡ ቡጥ ስር አስቀምጦ ጣቶቹንና ትንፋሹን ሲያናግር እንደ ዋዛ ተመነደገ። ድንገት ከአዲስ
አበባ ያመጣው እግሩ በለመዳት ዋሽንት ደግሞ ጉርሱንና ነፍሱን ሊያስተሳስሩለት ሲዳዱ አጋጣሚን ብቻ ነበር የጠበቁት።
ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ሞሰብ ባህላዊ የሙዚቃ ባንድን ሲመሰርት ጥቂት ትውቂያና ጥረት ነበር የጠየቀው። ሞሰብ ባንድ
ከተመሰረተ ከ10 ዓመት በላይ ሆኖታል። በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተዘዋወሩ በጥበብ ነፍስ አውግተው የሃገራቸውንም ስም
አስጠርተዋል። ሞሰብ የባህል ማዕከል የሚልም ከፍተው ሰርክ ሙዚቃን ያናግራሉ። ይሄው ባንድ “ጥሞና” እና “ኃይለ
ጊዜ” የተሰኙ ሁለት ረቂቅ አልበሞችንም አስደምጦናል።

3
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

ጣሰው ከምሽት ቤቶች እስከ ታላላቅ የዓለም የጃዝ መድረኮች


ድረስ በእረኝነት ዘመኑ የተዋወቃትን ዋሽንት ይዞ ለጥበብ
ተንፍሷል። ከአፍሪካ ጃዝ አባቱ ከሙላቱ አስታጥቄ ጋር ሳይቀር በዚያች
አራት አንጓ ዋሽንት ከሰው ልጅች ነፍስያ ጋር ስለ እውነት ተነጋግሯል።
የልቡን፣ የነፍሱን፣ የአንጀቱን ዋይታም ሆነ ሆታ በንጽህና ዘምሯል።

ይሄ የዘመን መንገዱም ከእድሉ ጋር በተጣባችው በዋሽንቱ ላይ አድሮ


አልበምን በሌላ ማዕዘን እንድናየው አደረገ። በመጋቢት 17- 2016 ዓ/ም
የትንፋሽ ውበት የተሰኘ አዲስ የማሲንቆ አልበሙን አበርክቶልናል። በራሱ
የዩቱብ ቻናልም የጀንበርን ማዘቅዘቅ ተከትሎ በዕለተ ሐሙስ ለነፍስ በሚደርስ
ቋንቋ ተናገረን።

እኔም ሙያዊ በሆነ መልኩ ሳይሆነ አልበሙን ደጋግሜ ሳዳምጥ የተሰሙኝን


አንዳንድ ሰሜቶች እንደ አንድ አድማጭ ለማጋራት ተነሳሳሁ። ሰምቶ ዝም
ከሚል ፍርጃ ለመዳን ይመስላል።

የትንፋሽ ውበትአልበም
የ ትንፋሽ ውበት አልበም 10 የሙዚቃ ትራኮችን የያዘ ነው። በሁሉም ትራኮች
ላይ ዋናውን ድምጽ ወክሎ የሚያናግረን ዋሽንት ነው። የሚከተሉት ሰዎችም
አብረው ተሳትፈውበታል።
ፒያኖ ቀረጻ እና ሚክሲንግ- ዐቢይ ወልደ ማርያም
ፐርከሽን- ተፈሪ አሰፋ
ክራር- ቢኒያም ዳኛቸው
ቤዝ- እዮስያስ ታመነ
ኤዲቲንግ- ዘመኑ አዳነ

በአስር ትራክ የተከፋፈሉት ረቂቅ ሙዚቃዎች አንዳች የዘመን መልክ የተጎናጸፉ


ናቸው። ጥሪአቸውም ወደ አንድ መንገድ ያስጉዛል። መዳረሻው ከሰው ልጅ
ባይሻገርም መንገዱ ግን ግለሰባዊ ነው።
ሁሉንም አንድ በአንድ ማቅረብ ፈታኝ መሆኑ እሙን ነው። የሁሉም የወል
ጥሪ የሰው ልጅና የልብ እውነት ቢሆንም መንገዱ ግን ግለሰባዊና ለየቅል ነው።
ጣሰውም በቃል የማይቀነበቡትን የስሜት ዜማዎች ስም ለመስጠት ሙከራ
አደርጓል። ስም ይመርሆ ለግብር ብሎ ይሆናል።
አንድም የወለዱትን በስም መጥራት የአባት ነው ብሎ ይሆናል። እኔም ለነፍሴ በጣም የቀረቡትንና አንዳች ሞጋች ምስል በመጨረሻም አምስቱም
ትራኮች የሰጡኝን የጋራ ቀለማቸውን ጠቅልዬ ለማስቀመጥ ሞክሬአለሁ። ይሄ ሁሉ መፍጨርጨር እንደ አድማጭ የተሰማኝን ለሌሎችም
ለማጋራት ብቻ ነው።
4
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

አምባሰል
አምባሰል በፒያኖ ምጥ ጀምሮ ሽቅብ እየተንጠራራ የሚመነደግ የትንፋሽ ውበት ነው።ከሩቅ ከአድባር ወዲያ የከተመን
እንቅልፋም የሰው ልጅ ይጣራል። የሚርገበገብ ብላቴና ከቁዘማው እየተላቀቀ ለአንዳች መማለል ከሩቅ የሚጣራ የአልፎ
ሂያጅ ሳይሆን የቀዬ ልጅ ጥሪ።
በዋሽንቱ ተወርዋሪ ድምጽ የሚቃትተው የወንዜ ልጅ እኔን የሚጠራኝ ይመስለኛል። እንደ ጉዱ ካሳ በድፍረት የሚወርፍ
ስል አንደበት ያለው የጋራ ላይ ንስር ነው። ከአምባሰል ላይ ሆኖ የሚጣራው ድምጽም የተኛን በሙሉ ከድባቴው የሚነቀንቅ
የነብይን ድምጽ ይስተካከላል።

ነነዌ
በወፍራም የዋሽንት ጥሪና በቀጭን የዋሽንት ቅጭልጭልታ ድንገት እንደ ብራ መብረቅ በሚወጡ አልቃሽ ዋሽንቶች
ይጀምራል። የወዮታ፣ የሃዘን፣ የልመና፣ እንዲሁም የዝማሬ መንፈስ ይታይበታል። በበደልና በስርዬት መካከል ያለች
አንዳች ሽንቁር።
ያቺን በቃላት ወይም በንግርት የማይደርሷትን የነፍስ ቡጥ በትንፋሽ እንባ ለመንካት የሚደረግ መንጠራራት። እያንዣበበ
በሚገኘው የእሳት ነበልባል መካከል ላይ ቆሞ ለትውልዶቹ የሚገደው ንቁ ሓዋርያ እስትንፋስ። ከላዕላይም ይሁን ከታህታዊ
መለኮት ግርጌ እጁን ዘርግቶ የሚማጸን ልባም ዘመነኛ።

አሁንነትን በስንጥርጥይዋ ድምጸት ንቡር ጠቃሽነት ከትናንት ጋር አያይዞ ለማስታረቅ የሚዳዳው የጥበብ ሰው የትንፋሽ
ሞገዶች! ሞትና መሰንበትን፣ ሃዘንና ዋይታን ጠንቅቆ በሚያውቅ የሙዚቃ ሰው ትንፋሾች የተገመዱ የድምጽ አለንጋዎች
ናቸው። ዳሩ ይሄ ጥሪ ለእኔው ዘመን እንጂ ለማን ነው? መዓትና ምህረቱን ለመለየት ለሚታትር የዘመን ምንደኛ የተወረወሩ
ሸንቋጭ ትንፋሾች።

ጉዞ
በወፍ ጫጫታና በሰማይ ወገግታ የሚጀምር የሚመስል መንከብከብ ይፈከርበታል። መንገዱ እንደ አሻል ፈረስ ለጥ ባለ
ሜዳ ላይ የሚከንፉበት አይነት አይደለም። ይልቅስ ጥቅጥቅ ባለ ጫካና የደኖች ውበትና ፍርሃት በሚጥበረበሩበት አይነት
ግርማዊ መንገድ ውስጥ የሚደረግ እርምጃ። መራመድ፣ መሮጥ፣ መፍጠን፣ ማናፋት፣ መኳተን፣ ብርክ ብርክ ማለት፣
መንደፋደፍ፣ መደናገጥ፣ መደናበር ሁሉ የተጣቡት ያቀበት መንገድ ይመስላል።

በጣሰው ዋሽንት የሚፈከረው ጉዞ


ተራ መንከራተት አይደለም።
ከአንድ ቦታ ተነስቶ ወደ አንድ
ቦታ ፈፋውን አቆራርጠው
የሚተምሙት መናኛ መንገድ
አይደለም። በአእዋፋትና በንፋሳት
ሹክሹክታ ታጅበው እየተራወጡ
የሚምዘገዘጉት አንዳች መቃተት
ብቻ አይደለም።

5
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

የሰውን ልጅ ከፍጥረት እስከ ክስመት ድረስ የሚፈክር፤ ከኩኩ መለኮቴ እስከ ሞተ ተጎደጎደ ድረስ የሚያቅፍ ሰው የመሆን
መባዘን የተሸከመ ነው እንጂ። ከመትበስበስ እስከ መነስነስ፤ ከመንከላዎስ እስከ መንፈላሰስ ድረስ በትንፋሽ ተራዳኢነት
የሚራቀቁበት ህያው ሜዳ አይደለምን?

ከላይ እንደተወረወረ ተንከላዋሽ፤ በመንገድ ማጣት ውስጥ አንዳች ቅን መንገድ መሪን የመፈለግ መቅበዝበዝ የሚደመጥባቸው
የህይወት አዙሪቶችን ሁሉ የሚያራቅቅ የህይወት ውል ነው።

Life is a journey that must be traveled no matter how bad the roads and accommodations. እንዲል
ኦሊቨር ጎልድስሚዝ (Oliver Goldsmith) የጣሰው ተናዳፊ ትንፋሾችም በፍለጋ ውሰጥ እስከ ህይወት ስቅታ ድረስ
የሚደርስ አንዳች መብሰክሰክን ያትታሉ።

ታዲያ የዚህ ሁሉ መባከን ውሉ ምንድን ነው? የዚህ ሁሉ የመንገድ ቱማታስ ዳሩ ምን ሊሆን ነው? የዚህ ሁሉ የነፍሳት
ህብረ ዝማሬና የመንገደኛ መብከንከንስ እስከ መቼ ነው? የሚል ጥያቄ ቢኖር የትንፋሽ መልስ ግን ከረቀቀ ሙዚቃ ባሻገር
ምንም ነው። ያ የረቀቀ ሙዚቃ ግን ከነፍስ ይደርሳል። በዚያ የነፍስ መጠራት ደግሞ ሰው የመሆንን እውነት እናገኛለን።

ትዝታ
ትዝታ የትናንት ድባብ ነው። ያለፈ ህልማዊ ቅንጥብጣቢ። የሚያመላልስ
ደግሞም የሚያስጉዝ፣ ልያዘው ሲሉት እንደ ብናኝ የማይጨበጥ የሚመስል
የህይወት ውል ነው።

ዛሬን ጠፍጥፎ የሚሰራ እሰኪመስል ድረስ የሚያባባ የትናት ህይወት ቅምምስ


ነው።

ጣሰው በትዝታ ትራክ የተነፈሳቸው ነዳፊ ትንፋሾች የአንድ ተራ ሰው ኑባሬ


ቅጦች አይደሉም። እንደ ፈላስፋ ልሳን መናገር የሚያምራቸው፣ አተነፋፈሳቸው
ሁሉ ለየቅል የሆነ ግን ደግሞ የጋራ ህልውና ያላቸው ህያዋን የጋራ መብሰክሰኮች
ናቸው። ዝብቅርቅ የሚመስሉ ግን ደግሞ የወል ወዮታዎች።

አንዳች የሳቱት መንገድ እንዳለ የገባቸው፤ ጸጸት የሚጋፋቸው የሚያባቡ


ድምጾች ናቸው።

እጣቸው መኖር እንደሆነ የገባቸው፤ በልዩነት ውስጥ የጋራ ሰማይ ሊጎናጸፉ


የሚያሰፈስፉ ግን ደግሞ ኩርምት ብለው ተቀምጠው አንዳች የሚያነሱት ጉዳይ
ያላቸው ናቸው። ከፍ ብሎ የሚሰማው አብረክራኪ የዋሽንት ድምጽ ከሩቅ ሃገር
ሊጠራው ያሰበው አንዳች እውነት እንዳለ የሚያሳብቅበት ሲቃ የሚታገለው
የትንፋሽ እንፋሎት ነው።

ታዲያ ጣሰው የጋራ እጣችንን፣ ሰው የመሆን ከፍ ሲልም ሃገር የመባል ዘሃችንን


ይዞ ከኋላ እየጠራ የሚመልሰን አይደለምን?

6
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

ዋሽንቶቹ

የዚህ ትራክ መልክ ደግሞ ሌላ ነው። የተለያየ ቅርጽና ድምጽ ወይም ህልውና ያላቸው ዋሽንቶች የጋራ ዋይታቸውን
ብሎም ሆታና ቱማታቸውን እያሰሙ ህብርና አንዳች ጥሪ የያዙበት መድረክ ነው። የታፈነ የጋራ ህመም እንዳላቸው
ዋይታቸው ይመሰክራል። በአንድ መልካቸው ደግሞ በፈንጠዝያ ህቅታ የሚሰግሩ ይመስላሉ።

ይሄ የሲቃ ድምጻቸው ደግሞ ከከያኒው ፍላጎት የመነጨ ሳይሆን የራሳቸው ተፈጥሮ ነው። እንዲያ ሆነው ተፈጥረዋልና
የከያኒው ሃላፊነት የተሰጠውን መልዕክት ከማቅረብ ላይ ነው።

ታዲያ እኒህ የሚቅበዘበዙ ብሎም የሚያናፉ ህብር ድምጸቶች የእኛው አይደሉምን? የአንተ፣ የአንቺ፣ የእኔ የጋራችን
የየግል እሪታዎች ብሎም ሆታዎች አይደሉም ማለት እንዴት እንችላለን? እነዚህ የጋራ ንፍረቃችንና ፍንደቃችን
አይደሉም ወይ መኖር የሚባለውን የወል ድንኳን ያላበሱን። ከዚህ የወል ድንኳናችን ውስጥ የሚወረወሩ ተስረቅራቂ
ድምጾችን ከያኒው ሰብስቦ እንደ ሰበዝም ሰብዞ ህብር ያለው መልካችንን ከዓይናችን ወደ ጆራችን አመጣው። ይሄ ነው
ከያኒ መሆን እንጂ።

የማይጠቀለለው ሲጠቀለል
የጣሰው የትንፋሽ ውበት ሌላም እልፍ ተናዳፊ ትንፋሾችን አምቆ ይዞ ቆይቶ በዜማ መልክ እንደ እንባ የሚያወርድ
የዘመናችን ሂስ ነው ብዬ አምናለሁ። ያ እንባ የደስታም የመታመምም ሊሆን ግድ አለበት። ከያኒውም ጋራ ለጋራ እየሮጠ
እንደ ለፋፊ አንዳች ሰው የመሆን መንገድን ሊመራመር የሚባክን መንደኛ ነው።

ትንፋሾቹ እንዲሁ ለቁዘማና ለዋል ፈሰስ የተተነፈሱ ሳይሆን ድርሳን ሰንደው፣ ከትውልድ ጋር ሊፋረዱ ከአደባባይ የቆሙ
አጋፋሪዎች ናቸው። አንዳች ሊናገሩት ያሰቡት ሰዋዊ ብሎም ሃገራዊ ጉዳይ እንዳላቸው ከግብራቸውና ከስማቸው ማዎቅ
ይቻላል።

7
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

በሃገራችን ብዙም ባልተለመደው በረቂቅ ሙዚቃ መልክ መጥተው ወዮታቸውን የሚያወርዱት ለቃል የለገመን አንደበት
የሚወርፉ ሳይሆኑ ይቀራሉን? ተራናገሪ የዘነጋውን የእኛነት ደብር በትንፋሹ ሊያንኳኳልን እንደ ዘመን ጠሪ የተላከ
መሲሃችን አይደለም ማለት እንደምን ይቻላል?

ህልው የመሆነ ምልክት የሆኑት እስትንፋሶች በሸንበቆ ጉሮሮ እያለፉ ህይወትን በዚህ ምልዓትና ቁጭት ልክ ማቅረባቸው
የእነሱስ ሃገራቸው ልብ ነው አለማለት እንችላለን?

ህይወት አንዳች ህብርን የመፍጠርና የዚያን ህብር ትርጓሜ በመፈለግና አንዳች ምሉዕ የምናብ ዓለምን በመፈለግ ውስጥ
በሚደረግ መንከራተት የሚገታ አይደለምን? ያን ፍለጋ እኮ ነው ጥበብ የምንለው። የእነዚህ ተናዳፊ ትንፋሾች የመጨረሻ
ወደብም መልክን ፍለጋ ነው። ህይወትን እየተናደፉ አንዳች ምሉዕነትን ለማግኘት የሚደረግ ኅሰሳ።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ህይወት በመኖር ሃቲት የሚገለጽ መሆኑን ለመናገር የድምጸቶች ውበትና መልክ ምስክር ነው።
እንደ ታላቁ ገጣሚ ሮበርት ፍሮስት (Robert Frost) የህይወትን በይቀጥላል ውስጥ እንደመረዳት ያለ ቀለም አላቸው።
በእሱ አባባልም የማያልቀውን ህይወት በማያልቅ ህብር ልዝጋ።

"In three words I can sum up everything I've learned about life: It goes on."
እስኪ የትንፋሽ ውበትን ሰምታችሁ ፍረዱ!

8
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

ሸክላ ሠሪ ሲራክ ወንድሙ

ከመቃብሩ አፋፍ ላይ ነፋስ የሚያወዛውዛት


እንቡጥ ፅጌረዳ እያየሁ ቁጭ ብዬ ነበር።
በውበቷ ፈዝዤ አፈር ገላዬን እየገፋሁ ወደ
እሷ ልንፏቀቅ ባቆበቆብኩበት ሽራፊ ቅፅበት
በረባሷቸው ዱር ዱር የሚሸት፣ የለበሱት
ብጭቅጫቂ ካቦርት ከገፃቸው ጋር ሞት
የሚያስበረግግ ሁለት መናጢ ሰዎች መጡና
አጠገቤ ቆሙ።
ቀና ብዬ አየኋቸው። ሸክላ ሰሪዎች ናቸው።
ይሄን የመቃብር አፀድ እንደ ደጃቸው
ተመላልሰውበታል።

አካፋቸውን ሲመዙ ደነገጥኩ። ከቀናት በፊት ሶስት እነሱን መሳይ መናጢዎች ለአበባ ማስቀመጫነት ሊጠቀሙኝ ሲወያዩ
ሰምቻለሁ። እነዚህ ደግሞ ለጀበና ሊያበጃጁኝ ነው።

ቀና ብዬ ዓይን ዓይናቸውን እያየሁ « ተዉ ከቀናት በኃላ ለአበባ ማስቀመጫነት አፈር እኔነቴን ይወስዱታል። ተዉ
ለጀበና አታርጉኝ! አትውሰዱኝ !» አልኋቸው።
አልሰሙኝም።

በአካፋው ዝቀው ባነገቱት ኮረጆ ውስጥ ዶሉኝ። የዘላለም የመክሸፍ ቅዝቃዜ ተሰማኝ። በኮሮጇቸው ውስጥ ገብቼ
መንደራቸው እስክገባ የማስበው የዚያችን አበባ ዝምታ ነው! የእነዚያ ከመቃብር ሀውልት ላይ የሚፀዳዱ ጥቋቁር
አሞራዎችን ፍዘት እና ድንግዘት ነው።

ዋ!
የእንቁራሪቷ ተረት!

ዛሬ ከጎናቸው አለምኞት ፍላጎቴ ስጋዝ ዝም ብሎ ለውድቀት የዳረኝ ልሳን ነገ የራሱን ውድቀት በራሱ የመዳፍ ፊርማ
ያረጋግጣል። አበባዋ የመርገፍ ሲሳይ ካልገጠማት በቀር ውበት ያለተመልካቿ አንቡላም ህይወት በመሆኗ፣ ነገ አፈር
ዘጋኝ ቢረግጣት እንጂ እንደማይቀጥፋት እሙን ነው።

ለአሞራውም የአዳ’ኝ የደጋን ቀስት በጉረሮው አቀበት እንደሚቀበቀብ እርግጠኛ ነበርሁ።


ሰማዩስ ደምኖ ስለምን ዝም አለ?

እህ! ደከመኝ........

9
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

ፍለጋ ና ዝናብ በብርሃን ደርበው

ይዘንባል... ይዘንባል...
ስማዩ ያነባል ደሞ ጭጋግ
በእግሮች እርግጫ የዝናብ ሽል የውኃ ልጋግ
በሰማዩ ኩርኩም
አበቦች አልፈኩም ከደመና ወረደ ጠል
*** ዛፍ ሊታደስ ጣለ ቅጠል

ይዘንባል... ይዘንባል... ደሞ አባራ


ስማዩ ያነባል ፀሐይ ፈካች ምድር በራ
በሰማይ ነጎድጓድ
በምድር እሪ-ኩም በግፍፍ ደመና በርጥብ ፀሐይ መካከል
ፍጥረታት አልረኩም ፍጥረት ሁሉ ይጨሳል
*** ደመና ሊሠራ ፀሐይ ሊከላከል
ዘነበ... ዘነበ...
በንፋስ ሽውታ እርቃን ተገለበ የፀሐዩን ምሥል
ፊታችን፣ ገላችን፣ አፈሩ ረጠበ የብርሃን ነጸብራቅ
*** (የጀንበሩን ቁስል)
ይዶፋል...ይዶፋል... በምዕራብ በምሥራቅ
ገለባና ፍሬ አንድላይ ይረግፋል ከልሎት ደመና
በድፍርስ ጭቃውኃ ጎዳናው ያድፋል ከልክሎት ደመና
በአፈር ጎደፈ አፈሩ ጎዳና
በጎርፍ ታጠበ ጥላውን ሲነጥቀው
የርምጃ ትዝታ የእግሮቻችን ዳና ጥላ ይዘረጋል
*** በመብረቅ ብልጭታ
በዝናብ ክለላ
ደሞ ውሽንፍር አምሳል ይሰንጋል
ደሞ ወጨፎ
ወደ ጎሬው ይራኮታል እኔ...
ፍጥረት ግሳንግስ ሸክፎ ለሰማዩ እንባ መሃረብ ይመስል
*** ሄዳለሁ... በዝናብ
ሄዳለሁ... በምናብ
ያካፋል...ያካፋል... ዛፉ ሲገነደስ
ደመናው ይስፋፋል ፍጡር ሲተራመስ
ፍጥረቱ ሲታደስ
ከጨለመ ሰማይ ከሰፋ ደመና
ጠጥሮ ወረደ ውኃ እንደመና በተራራው መሐል ልፈልግ አንድ አገር
ጎርፍ እከተላለሁ ወንዙን ለመሻገር
ወረደ...ወረደ...
የሰፋ ደመና ፀሐይን ጋረደ እጓዛለሁ.........

ነፈሰ...ነፈሰ…
በሐኖሱ ሰማይ ውኃ እየነገሠ
ዛፍ ሁሉ ይንሿሿል
ውኃ ለበስ ፍጡር ውኃዉን ይሸሻል
10
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

መጽሐፈ- ሄኖክ በዙበይር ኢብራሒም

ሄ ኖክ በቀለ ለማ ይህንንም ድንቅ መጽሐፍ አበረከተ። በመጽሐፉ ታማሚውን


ገጸ ባህሪ ጤናው፣ ፍጹም እድለ ቢሱን እድሉ ቀና፣ ዘመኑን ሙሉ በጭንቀት
የኖረውን ደስታ ወ.ዘ.ተ… በሚል ሰይሞ ስም ሌላ ማንነት ሌላ ብሎ ቢሞግትም፤
ስምን መልአክ አያወጣውም፣ ቢያወጣውም ሆን ብሎ በዚያ በኩል ሊሳለቅ ሲፈልግ
ነው፣ የሚል አይነት ሀሳብ ቢያነሳም፤ ደራሲው ራሱ ግን ስሙን በመጠኑም ቢሆን
ከመምሰል አልዳነም( እኔ አልኩ)።
ዓለማዊው የኛ ዘመኑ ሄኖክ እንደ ቅርስ አስቀምጠን በሂደት እየተረተርነው የምንኖረውን ዳጎስ
ያለ ሸማ እንካችሁ ብሎናል። ታድያ ይሄኛው ሄኖክ በሀሳብ እንጂ በስጋ ሰማየ ሰማያትን
አልፎ አልተጓዘም።

"ሄኖክ ሆይ ቋንቋህ ከበደን ምናለ ቀለል ብታደርገው?" የሚል ጥያቄ ላነሱ አንባቢዎቹ
የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል።
"ራሳችሁን ወደዚያ ደረጃ አሳድጉ እንጂ እኔን እንዴት ውረድ ትሉኛላችሁ"(ቃል በቃል
አይደለም ታድያ የደገምኩላችሁ ሀሳቡን ነው)
ስለዚህ የኛ ዘመኗን፣ ደፋሯን፣ ዓለማዊቷን መጽሐፈ-ሄኖክ ለጊዜው ባለንበት ደረጃና በገባን
ልክ ዳበስ እናደርጋታለን። ስናድግ ደግሞ እናሳድጋታለና።

አማኙ አብዘርዲስት ሄኖክ በቀለ “ሀገር ያጣ ሞት” በሚል ርእስ በ208 ገጽ በቀነበባት ሁነኛ
ሰነዱ ተንፍሶ አስተንፍሶኛል። ለድብርት ጊዜ ቆጥቤ አስቀምጬ እንደ ህመም ማስታገሻ
የምወስዳቸው የቃላት ዲጂታል መጽሔት ስራዎቹን ከፍ ባለ ዶዝ ይዞ መጥቷል። መፍትሔ
ቢስ የሚመስለውን አዙሪታም ቁስል ሀያሲ ቴዎድሮስ ድንቅ በሆኑ ቃላትና አገላለጾቹ
ልሶልናል። "አዎንታዊ አስተሳሰብ አራማጆች ነን" የሚሉ ሰዎች መጽሐፉ ጨለምተኛና
"pathos" እንደሚባለው አይነት አካሄድ ያለው ነው ብለው ሊደመድሙ ይችላሉ። ለእኔ ግን
"ሀገር ያጣ ሞት" "pathos" አይደለም ከአዳም ስህተት ጀምሮ፣ ሰው የመሆን እጣ ፋንታ
ከገጠመን ጊዜ ጀምሮ የታደልነውን ህመም ሲደመር ዘመን አመጣሽ ህመም የምንተነፍስበት
ቴራፒ ነው።
በመጽሐፉ ገጽ 189 ላይ እንዲህ ይላል…

"የሀዘንም ቢሆን ኑሮ በስነ ጽሑፍ ውስጥ እንዴት ያባብላል?"

***
በእነዚህ 208 ገጾች ያልተላሰ ቁስል ጠይቁኝ። ሁሉም ተነክቷል። ፖለቲካው፣ ስነ ልቦናው፣
የማህበረሰብ ምስቅልቅሉ፣ዘመን አይሽሬው የህልውና ቀውስ ህመም፣ ዘርዝሬ አልጨርሰውም።
ሁሉም ላይ የሀሳብ ድንጋይ ተወርውሯል። ድንጋዩ ፈጣሪንም አልማረም።በአግባቡ ተሞግቷል
ስላችሁ!

“የዲያቢሎስ ምራቅ የነካት” የተባለችው ምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገርም ራቁቷን ተደርጋ


አንድ በአንድ ተበልታለች። በድርሰት ዓለም ስር ማንም ከማንም አይበልጥም በሚል አዋጅ
የተነሳው ደሪሲ የፈጣሪን ትርክት ሆምጠጥ ያለ ተረት፣ ዲያቢሎስን ደግሞ የመጀመርያው
አብዮተኛ እስከማለት የደረሰ ደፋር መንገድን ተጉዟል።

11
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

ከዚህ ሁሉ በፊት ግን በመግቢያው ፈጣሪን


“አይ የልጅ ነገር ብለህ ስለምታልፈኝ” የምትል የፈሪ ቀብድ አስይዞ ነው የጀመረው።
ማን? ከእኛ ከሁላችንም እንደ አንዱ የሆነው አማኙ አብዘርዲስት ሄኖክ በቀለ።
እኛም “አይነኬው” ውስንነታችንን፣ አቅመ ቢስነታችንን ያውቃልና “አይ የልጅ ነገር” ብሎ ችላ እንዲለን በመመኘት
ውስጥ ጉዟችንን እንቀጥላለን። ተከተሉኝማ።

“በምድር ፊት ስላቃችን ማለቂያ አልነበረውም” እንዲል ጥርስ የማታስገልጥ መራር ስላቅ ስለሆነችው ህይወትና ወለፈንዲ
ህልውናዋ (ህልውናችን)በሰፊው አንስቷል። እስኪ ለዛሬ ከተነሱት እልፍ ሀሳቦች መካከል የህልውና ቀውሶቻችንን በእጣፋንታ
መስኮት በኩል ያስመለከተበትን መንገድ መዘዝ አድርጌ ላስቃኛችሁ።

በመጽሐፉ በሚያስቀና መልኩ እንደልብ ወደኋላ ወደፊት ሲያስጉዝ (time travel) ፣ ዘለዓለማዊነትን እና ሞትን
ሲሰጥ ሲነሳ የተመለከትነው “ሀያሉ ጊዜ” ራሱ የመፈጠር እጣ ፋንታ እንደገጠመው ይነግረናል።
“ፈጣሪም ንጥር ታሪኩን ሳይጀባን ሆምጠጥ ያለ ተረቱን እያሳሳቀ ሳይነግረን አስቀድሞ ያቆመው የመቼ እና የት ቢጋሩን
ነበር” ይለናል የመጀመርያው ገጽ ላይ።
ጊዜና ቦታን ተከትሎ የአዳም ዘር ገጽ 65 ላይ በተቀመጠው መልኩ “ለኗሪነት ቀንበር፣ ለህያውነት ጫና ተዳረገ”
ይለናል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ለእጣፋንታ እንጂ ለምርጫ አልታደለም። የሰው ልጅ ምርጫ ቢስነት የሚጀምረው እንግዲህ እዚህ ጋር
ነው። በነፍስ ወከፍ የእያንዳንድህ ምርጫ ቢስነት ደግሞ ከውልደትህ ይጀምራል ይላል ሄኖክ። ይህንንም ገጽ 68 ላይ
ድንቅ በሆነ አገላለጽ እንዲህ ያስቀምጠዋል።

“ሚሊየን የወንድ ሀጢአት ተጋፍቶ ከመካከላቸው አንድ አሸናፊ የተባለ ጎረምሳ ዘር፣ የሴቴ እንቁላል አሽኮርምሞ ሲያፋፋ
ተፈጠርሁ። አሸናፊ ምን ስለሆነ አሸነፈ? ባላባት ነው የመኳንንት ዘር? ደጃዝማች ነው ፊታውራሪ? የሰለሞን ዘር ነው
የላልይበላ? ከአረብ መጣ ከፋርስ? ከጤግረስ ጠጣ ከግዮን? ከከሸፈ ትውልድ መሐል እንዴት መከናወን አወቀበት?
ከእልፍ ለምን ተመረጠ? የእግዜሩ ነው የእሱ ጥረት? ደቁሶ ካስቀራቸው መሐል እንደው ከእርሱ የተሻለ ጠፍቶ ነው?
እንደኔ አይነት ልጅ ለመውለድ ምን እንዲህ አንገበገበው? የቀሩትስ ምን ሆነው መከኑ? የአርባ ቀን እድላቸው ነው ወይስ
ከሰባት ትውልድ የተላለፈ እርግማናቸው? ጭሰኛ ናቸው ጥሩራ ባርያ? አሕዛብ ናቸው መናፍቅ? ሀጥእ ናቸው ቅንቅናም?
ነጭ ድሀ ናቸው መናጢ?”

ይህንን ሁሉ አትመርጥም። መጥተህ ነው ራስህን የምታገኘው። ከመጣህ በኋላም ይመስልሀል እንጂ አመለካከትህን
አትመርጥም፤ መንገድህን አትመርጥም፤ አመጣጥህ አካሄድህን ይወስናል፤ አካሄድህ አደራረስህን ይወስናል።

በገጽ 146 መጽሐፈ መክብብን ጠቅሶ እንዲህ ይላል


“ህይወቴ የጀመረው ስወለድ አልነበረም”።
የተጀመረ መጽሐፍ ላይ የመጣህ ቅጣይ መስመር እንጂ ራስህን የቻልክ ጥራዝ አይደለህም። ያንን መስመር እንድታሟላ
ተወስኖብህ ከመጣህ ወዲያ መቀየር የምትችለው አንዳች ነገር አይኖርም ነው ሀሳቡ።

“ፍቃዱ አየልኝ” ግርባብ በሚለው መጽሐፉ ብእርን እንዲህ ሲል ያናግራታል


“የማትወጂውንም ሆነ የምትወጂውን መንገድ እኔ አልሄድም እንድትዪ መብት የለሽም። ምክንያቱም ምን ሊጽፍብሽ
እንዳሰበ የሚጽፍብሽ እንጂ ቀድሞውንም አንቺ አላወቅሽም”።

“The value of everything depends on its contribution to a whole of which it can be seen as a
part “Nietzsche.

12
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

እስኪ ደግሞ ገጽ 93 ላይ በሽማግሌ የተወከለው ጊዜና መልከ የተባለው ገጸ ባህሪ የሚያደርጉትን ምልልስ እንመልከት።

መልከ: -”የተወሰኑ ዓመታት ወደ ኋላ መልሰኝ። ህይወቴ ላይ ማስተካከል ያሉብኝ ነገሮች አሉ።”


ጊዜ: -”ብወስድህም የሰራኸውን ስህተት ደግመህ ትኖረዋለህ ልጄ።”
መልከ: -”አላደርገውም።”
ጊዜ: -”ከእድል ፈንታው ማንም አያመልጥም።”
“If one were to live over again one would want the very life one has already had exactly the
same down to its tiniest detail and nothing else”
(Nietzsche)
ካንተ በፊት እየተጻፈ የነበረውን ነገር ለማስቀጠል ብቻ ሳይሆን ካንተ በኋላ ለሚመጣው ገጽ ድልድይ ለመሆንም ጭምር
ተወስኖብህ ነው የምትመጣው። ልትቀይራት የምታስባት መስመር ቀጣዩን ገጽ ልታበላሽ ትችላለችና ነው። ክቡን የማሳት
አቅም ሊኖራት ስለሚችል ነው። ክቡ ላይ ፍቅር የምትባል ነጥብ ትኖር ዘንድ ዱና ዓይኗን መታመም ነበረባት፤ መልከ ያለ
ቅጥ መስከር ነበረበት፤ ተዋቡ የምትባል ነጥብ እንድትሰረዝ ፈጣሪና መፍለጫው ማበር ነበረባቸው።

በአጭሩ
“Not only your past defines your future your future also defines your past.”
(ማንነቱን የረሳሁት ሰው ሀሳብ)
“We could possibly affirm like the untimely death of a loved one or friend or a tragic accident
that kills hundreds of people but perhaps the key were is to zoom out and see such occurrences
as essential to the journey we are on as playing unavoidable roles in a beautiful whole”
Nietzsche

ገጽ 162
“ለእዚህ ሁሉ ቅብዝብዝ የሰው ዘር እንደ ጣቃ
ተቀዶ የተሰፋለት የሕይወት መስመር እንዳለ
ያስባሉ። ለአንዳንድ ሰው ኖሮ መሞት ብቻ
በቂ ታሪክ ሊሆን አይችልም? ከበላ ከጠጣ
ከፈሳ መች አነሰው!? ፈጣሪን በሞት የሚፈርስ
ዐላማ ሲሰፋ ሲጠግን የሚውል ስራ ፈት አድርጎ
ማሰብስ ለማን ጠቀመ!?”

ትኩረት የሚስብ ነገር እስካላደረግን፣ ከተራራ


ጫፍ ላይ ወጥተን እስካልታየን የኖርን
አይመስለንም አይደል? መኖር ማለት ለሆነ
ለሚታይ፣ ለሚጨበጥ ለሚቆለል፣ አላማ መሮጥ
አይደል የሚመስለን።

ተሳስታችኋል እያለ ነው ሄኖክ። ወደዚህች ምድር


ስትመጣ ለፍተህ እንድትወጣ የሚጠበቅብህ
የተራራ ጫፍ የለም። የመጣኸው ልትኖር
ነው። መኖር ማለት ደግሞ በቃ መኖር ነው።
እጣፋንታህ ባንተ ውስጥ እንዲያልፍ መፍቀድ
ነው።

13
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮
አበቃ! ብላ ፣ጠጣ፣ ፍሳ አዲዮስ!
“ ሁለት ታሪኮች ተቃቅፈው ተሳሳሙ” እንዲል ራስ አሊ፣ ራስ ካሳ፣ ራስ እንቶኔ መሆን ካለብህ ሁነው ።
ገጽ 133 “የሱሲንዮስ ጋሻ ጃግሬ ማን ይባላል? የሰለሞን እቁባት ለህይወቷ ምን አደረገች? ስሟ እንኳን
አልተጻፈም። ሰለሞን ሰባት መቶ እቁባት ቢኖረው የእሱ ታሪክ ብቻ ነው። እነርሱ የታሪኩ ማሟያ ብቻ ናቸው።
እንደጊዜና ቦታ ያሉ የመተረኪያ አጥቆች።”
እንዳለው ጋሻ ጃግሬ፣ እቁባት፣ ውታፍ ነቃይ እና ወዘተ የታሪክ ማሟያ መሆን ካለብህም ሁነው። እጣፋንታህን
ታግለህ አታሸንፈውምና።
***
እስኪ ደግሞ መለስ ብለን ገጽ 101 ላይ ስላነሳው ሀሳብ እናውራ
“ፍቅርም ስራዋን የወረሰችው ከእኔ ነው ከእናቷ። ካልሆነ ሌላ ከየት አባቷ ታመጣዋለች? ግልሙትናን ያወረስኳት
እኔ ነኝ። ፈጣሪ አሁን ሁለታችንን አኩል እሳት ነው የሚከተን? ከመፍረዳችን በፊት የምናውቀውን ከማናውቀው
የሰማነውን ካልሰማነው ብናበላልጠው አፋችንን እንከፍታለን? ድንጋይ ይዘን ከወጋሪዎች መሐል እንሰለፋለን?”
ያለ ሸንጎ የፈረንድባቸው ሀጢአቶች፣ ለወገራ ድንጋይ ያነሳንባቸው ወንጀሎችን መለስ ብለን እንይ እያለን ነው።
ፍርግርግ ብረት ውስጥ ያስገባነው ወንጀለኛ በፈራነው ባንፈራውም በአካል ማግኘት ባልቻልነው አህያ ቦታ የተተካ
ዳውላ ቢሆንስ?
***
በስተመጨረሻም አማኙ አብዘርዲስት ሀሳቡን እንዲህል ሲል ያጠቃልላል።
“ባልተኖረበት በኩልም ቢኖር ህይወት ተመሳሳይ ነው። በክብ ውስጥ እንዳለ አዙሪት ዙርያ ጥምጥም። ከየትም
መነሳት ይቻላል። የትም ግን አትደርስም። መድረሻም መነሻ መድረሻም መነሻ ነው። ወይም መነሻና መድረሻ
የለም።
ይህች ሀሳብ የኒቼን recurrence of time principle ታስታውሰናለች።
“Time repeats itself in an infinite loop and that exactly the same events will continue to
occur in exactly the same way over and over again for eternity.”
“የነበረው ነገር እንደገና ይሆናል፤የተደረገውም ተመልሶ ይደረጋል፤ ከፀሐይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም።”
መክብብ 1:9
***
እና ምን ተሻለን ካልን
ለጊዜው ያለን ብቸኛ አማራጭ የኒቼን የ”amor fati principle”መቀበልና መተግበር ብቻ!
“Amor fati (love of fate) let that be my love hence forth I do not want to wage a war
against which is ugly. I do not want to accuse. I do not even want to accuse those who
accuse. looking away shall be my own negation. and all in all, and on the whole someday.
I wish to be only a yes-sayer.”
ከእድል ፈንታህ ጋር በፍቅር መውደቅ፤ ለእጣፋንታህ በፍቃደኝነት መሞኘት። ነጻነት መታሰርህን በማመንና
በመቀበል ውስጥ ነው ያለው። ነጻነት የምትመካበት አእምሮህ ከምንም እንደማያስጥልህ አምነህ ለእድልህ ራስህን
በሞኝነት አሳልፈህ በመስጠት ውስጥ ነው የምትገኘው።
ይህንን ልሰብስብህ ብለው የማይሰበስብ ሀሳብ በዚህች የመጽሀፍ ቅዱስ ጥቅስ ልዝጋው
“ሌላም ነገር ከፀሐይ በታች አየሁ። ሩጫ ለፈጣኖች ውጊያም ለሀያላን አይደለም። እንጀራ ለጥበበኞች ወይም
ባለጠግነት ለብልሆች ወይም ሞገስ ለአዋቂዎች አይሆንም። ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል”
መክብብ 9:11
ምንም አልልም፤ በቃ ይነበብ። ይደገም፤ ይደጋገም። በቅርብ ዓመታት አንብቤ በፍቅር ከወደቅኩባቸው መጽሐፎች
መካከል ነው። ከተነሱት እጅግ በርካታ ሀሳቦች አንዷን ነው ነጥዬ ያወጣሁላችሁ። ያው ብዙ የመጀመርያ
መጽሐፋቸውን የሚጽፉ ደራሲዎች ላይ እንደማየው ያለ፣ ያለኝን ሁሉ ልተንፍሰው አይነት እጭቅ ያሉ
እያንዳንዳቸው አንድ መለስተኛ ጥራዝ ሊወጣቸው የሚችሉ ሀሳቦች ተሰግስገውበታል። እንደ ዳገት ቀስ እያላችሁ
ውጡት።
እንግዲህ እኔንም እድልና ጊዜ እጃቸውን አጠላልፈው አድርሰውኝ ይሆንን ጻፍኩ። እድልና ጊዜ ያደረሷችሁ ሰዎች
አንብቡና አንድ በሉኝ።
ቢበቃኝ ጥሩ አይመስላችሁም!?

14
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

የፊልም ግብዣ በኪሩቤል ሰለሞን

ርዕስ - Dead poets society


ዘውግ - Drama
አዘጋጅ/Director - Peter wier
መሪ ተዋናይ - Robin Williams
ለዕይታ የበቃበት ጊዜ - 1989 G.C
ፊልሙ የሚፈጀው ጊዜ 2፡08hr

Dead poets society በአንድ ወግ አጥባቂ(conservative setting) ይትበሃል በተቃኘ ዌለተን አካዳሚ በሚሰኝ
አዳሪ ት/ቤት ውስጥ ባሉ ተማሪዎች ላይ ያለውን የለውጥ ሂደት ያስቃኛል:: Mr. Jhon Keating በተባለ የእንግሊዝኛ
መምህር አማካኝነት ወይም ገፋፊነት ውስጣዊ ፍላጎታቸውን ለማግኘት አንድ ምስጢራዊ ክበብ ይመሰርታሉ።

የግጥምን አስደናቂ ውበት የሚያስሱበት፣ የማህበረሰብን ባሕል የሚሞግቱበት፣ ተነጥሎ በነፃነት በማሰብ ውስጣዊ
ፍላጎታቸውን ለማግኘት ሲጥሩ የሚያሳይ ድንቅ ፊልም ነው::

ስነ-ጽሑፍን እንደ መሳሪያ በመገልገል ራስን ገልጦ መናገርን(self-expression) እና ጠንካራ የሆነ ጓደኝነትን (Sense
of camaraderie) ይፈጥራሉ:: በዚህ ምክንያት በሚፈጠር አዲስ አስተሳሰብ እና መንገድ ከት/ቤቱ ወግ አጥባቂ ስርዓት
እና የወላጅ እንዲ መሆን አለባችሁ ጥያቄ (family expectation) ጋር ሲጋጩ ያሳያል::

አጠቃላይ ፊልሙ የሚያጠነጥንበት ጭብጥ


1. ራስን ማግኘት (self-discovery)
2. የስነግጥም ኃያልነት (power of poetry)
3. Conflict between conformity and individuality
4. The weight of societal expectations

ይሄንን ራስን ማገኝት በጥሩ መልኩ የተገለጠበትን ፊልም ባይራ ዲጅታል መጽሔት ለዚህ ዕትም ትጋብዛለች::

15
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

የኛ ሰው ነብይ ሩት ሃብተማርያም

ስለ እሱ ብዙ ነገር ማለት ይቻላልና ጽሑፌን ስጀምር ምንም የምቸገር አልመሰለኝም ነበር። ግን ወደ ነገሩ ስገባ ከየት
እንደምጀምር ግራ ገብቶኝ ብዙ ቆየሁ። እናም ስለ ታላቅ ማንነቱ በትንሽ ብዕሬ ለመከተብ እናንተን ዋስ ጠርቼ
ጀመርኩ። ከየት እንጀምር? አብዝቶ ከሚያወራላቸው እናቱ እና ናዝሬት? … ወይስ ትልቅ አበርክቶ ስላበረከተበት
የእስር ቤት ቆይታው? አልያም ስለ ጣፋጭ ወጎቹ እና መጻሕፍቱ? … ሁሉም የእሱ መልኮች ናቸው እንጀምር።

ጋሽ ነብይ ጋዜጠኛ ፣ ጸሐፌ ተውኔት ፣ ገጣሚ እንዲሁም ተርጓሚም


ነው። በእስር ቤት ቆይታው ወቅት ወይም በእስር ቤት በነበረበት ወቅት
የማርጋሬት ሚሼልን ‹ Gone with wind › “ነገም ሌላ ቀን ነው” ብሎ
የተረጎመ ሲሆን በቅርብ ጊዜያት ደሞ ‹The Last Lecture› የተሰኘ የአንድ
የዓለማችንን እውቅ ሳይንቲስት የሕይወት ታሪክ ‹ የመጨረሻው ንግግር›
ብሎ ተርጉሟል።

ጋሽ ነብይ “ስውር ስፌት 1 እና 2” እንዲሁም “ጥቁር ነጭ ግራጫ”


የተሰኙ የግጥም መድብሎች አሉት። በአንድ ወቅትም ፖለቲከኛ ነበር።
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ መስራች እና ዋና አዘጋጅም ነው። በተለያዩ የዓለም
ሀገራት ተዟዙሮ ያያቸውን ትዝብቶች በመከተብ በየሳምንቱ በአዲስ አድማስ
ጋዜጣ ላይ ሲያወጣቸው ቆይቶ በኋላም “የኛ ሰው በአሜሪካ” ብሎ ሰብስቦ
አሳትሟቸዋል። “ናትናኤል ጠቢቡ” የተሰኘ የመድረክ ተዉኔት እንዲሁም
“ባለጉዳይ” የተባለ የቴሌቪዥን ድራማ ተርጓሚና ጸሐፊ ነው። ብዙዎች
እንደሚስማሙበት ደግሞ ጨዋታ አዋቂም ነው። እስኪ እሱ አብዝቶ
ስለሚናገርላቸው እኛ ትንሽ ትንሽ እንበል።

16
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

ነብይና ናዝሬት
“ኧረ ናዝሬት ናዝሬት ረባዳው መሬት
ታበቅያለሽ አሉ ሸጋ እንደ ሰንበሌጥ”


ላይ ያለውን ስንኝ የጻፈው ጋሽ ነብይ “እሱ እንዲህ ይላል …
አማርኛ ያስተማረው ሰው ጥሩ የተገራ ጸሐፊ “አየርና ነፋስ፣
ይወጣዋል” ሲል የሚናገርለት መምህር ምጽላለ ውሃው ሆነ ህዋው፣ የብስና ውቂያኖስ
ሙሉ ነው። ወይም (ከላይ ያለው ስንኝ ጋሽ ነብይ አያጉዘው የለ፣ አጉዞሽ አጉዞሽ
“እሱ አማርኛ ያስተማረው ሰው ጥሩ የተገራ ጸሐፊ አሜሪካን ሰፈር፣ የሰው ሀገር ገባሽ
ይወጣዋል” የሚልለት መምህር ምጽላለ ሙሉ የፃፈው ስመ ሞክሼ እህቴ፣ ዋ ሚስጥሩን ባወቅሽ
ነው።) እዚህም ያመጣሁት ጋሽ ነብይ ስለናዝሬት ሲናገር ያን ያህል ሳትሄጂ፣
የሚያስቀድማት ስንኝ በመሆኗ ነው። ጋሽ ነብይ በአንድ አሜሪካን ግቢ፣ ናዝሬት ነበረልሽ
ቃለ መጠይቁ ላይ “የአንድ ሰው መሀንዲሱ አካባቢው ፈረስ የሚያስጋልብ፣ የኳስ ሜዳ ያለው
ነው።” ይላል። በትክክልም የአንድን ሰው ባህሪም ሆነ ዘይቱን ያዘለ፣ ትላልቅ ዛፍ ያለው
አስተሳሰብ ለመቅረጽ የሚያድግበት ማህበረሰብ የስነልቦና ሽቦ የታጠረ፣ ማንም የማይደፍረው
ውቅር ወሳኝነት አለው። ጋሽ ነብይ ትውልዱ ናዝሬት ተርኪኒዎች ያሉት፣ ደግሞም ዶሮ ርቢ
ነው። በመንሰፍሰፍ የሚጠራት ናዝሬት ለማያውቃት እና ነበር እኮ ናዝሬት፣ አሜሪካን ግቢ”
ከእሱ አፍ ስለእሷ ለሚሰማ “ምን ቢኖራት ነው?” ብሎ
ያስጠይቃል። …እያለ አያሌ የናዝሬት ትውስታዎቹን እና በረከቶችን
ያስዳስሰናል። ይህ “ራኬብ ለራኬብ”
የተባለው ግጥሙ በጣም የምወደው
ግጥም ነው። ምክንያቱም በአንድም
በሌላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያደግን እኛ
በዚህ ግጥም ውስጥ የተባሉት ነገሮች
ሁሉ ዳስሰውን አልፈዋልና። ታዲያ
ያለፈ እንደሆንስ ቢባል “ታላቅ ዘፋኝ
የውስጣችንን ዝምታ የሚያዜምልን
ነው።” እንዲል ካሕሊል ፤ የውስጣችን
ዜማ ተዚሞልን እንላለን።
እዚህ ጋር ራኬብ ስል አንድ ቀን
ጋሽ ነብይ የነገረኝ ወግ ትዝ አለኝ።
ለራኬብ አባቷ ነብይ መኪና ገዛላት።
እናም መኪናዋ ቀለም መቀባት ኖረበትና
“ይድረስ ከራኬብ ለራኬብ” በሚል ግጥሙ ታዲያ ጓደኛዋ ቆንጆ አድርጎ ቀባላት። እንድታየው ተጠራች።
በናዝሬት በኩል አድርጎ ኢትዮጵያን ሲኩላት እናየዋለን። ከቤታቸው ደረጃ ላይ ወደታች ስታየው ግን ከላይ በደንብ
እኔ እንደምረዳው ሰው ትልቁን ምስል የሚያየው እንዲሁም አልተቀባም። ትንሽ መነጫነጭ ነገር … “አባዬ ከላይ
ስለትልቁ ምስል ግድ ሊለው የሚችለው አጠገቡ ያለውን እኮ አልተቀባም” ትላለች። ከዛስ የነብይ ጓደኛ ምን
ሲወድ ነው ብዬ አስባለሁና ነብይም ናዝሬትን በጣም አለ? “ራኪዬ ሰው ለሚያየው እንጂ እግዜር ለሚያየው
በመውደድ ኢትዮጵያን አፈቀረ። ግጥሙ ራኬብ መኮንን አትጨነቂ!” አላት ብሎ ነግሮኝ ረጅም ሳቅ እንደሳቅሁ
እና ራኬብ ነብይ ለተባሉ ቤተሰቦቹ እንደተጻፈ ይነግረናል። ትዝ ይለኛል። ዛሬ ስለ ናዝሬት አይደለም። ስለ ነብይ
በእርግጥ ግጥሙ በእነሱ አይቆምም ፤ ለኢትዮጵያውያን ነው ።
ሁሉ ነው።
17
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

ነብይና ማዕከላዊ
“ከዚያ የሚያውቁ የሚያውቁትን እጅግ አቅርቦ በሀሳብ እያጎሉ ማየት … ከዚያ የገዛ ሰፈር ፣ የገዛ ቤት ፣ የገዛ ጓዳ የገዛ
ማጀት እናት አባት ልጅ ሚስት ምኑ ቅጡ ዋ! ያጡት ማማሩ?! ማሳሳቱ?! የታባቱ! ላንድ አፍታ በሀሳብ ቢሸፍቱና
በምናብ ቢፈቱ እንዲህ ሀገር መታየቱ ፣ እንዲህ አገር መወሳቱ ደሞ ጣሩ ለሱው ሲሉ መታሰሩ” ይላል “ነገም ሌላ ቀን
ነው” የተሰኘ መጽሐፉን ለሁለተኛ ጊዜ ሲያሳትም ባካተተው መግቢያ …።

ስለ እስር እና እስረኝነት ሰቀቀን ሲያወሳ። ጋሽ ነብይ “እስር ቤት ላልተማረበት ስቃይ ለተማረበት ደግሞ ት/ቤት
ነው!” ይላል። ይሄንንም በተግባር ያስመሰከረ ይመስለኛል። በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት በኢህአፓነት ተጠርጥሮ
ለስምንት አመታት እስር ቤት ቆይቷል። በእስር ቤት ቆይታው 3000 በሚደርሱ የሲጋራ ወረቀቶች ላይ በኋላ “ነገም
ሌላ ቀን ነው” ብሎ ስም የሰጠውን የማርጋሬት ሚሼል ‹Gone with the wind> መጽሐፍ ተርጉሟል። ለምን
መጽሐፉን “ነገም ሌላ ቀን ነው” ሊለው እንደፈለገ ሲገልፅ “ለመጻፍ የሚያስፈልገኝ ነገር ለማሟላት አራት ጥያቄዎችን
መመለስ ነበረብኝ።

1. በምን ልጻፍ --- ወረቀት አይገባማ


2. በምን ልጻፍ --- እስክሪብቶ ከቤት ተጠሪው እጅ አይወጣማ።
3. የት ልጻፍ --- ቦታ የለማ
4. ጽፌስ --- ማውጫ የለማ በመጨረሻ ግን እንደ ‹ Gone with the wind> መሪ ገጸ ባህሪዋ እስካርሌት ኦሃራ
አባባል ነገም ሌላ ቀን ነው! ብዬ ጉዞውን ጀመርኩ።” ይለናል።

እሱ ራሱ እንደሚለው እስርቤቱን ተምሮበታልና ጥሩ ጎኑ ላይ ፣ በረከቱ ላይ እናተኩር ብለን እንጂ ከዓለም ተነጥሎ


በአስከፊ ሁኔታ መታሰር ደስ የሚል ቅንጣት ነገር የለውም። እሱም እንዲህ ይላል “ጡር ተናገርክ አትበሉኝ እንጂ
ይቺን እስር ለሁሉም የውጪ ዓለም ዜጋ በሾርባ ማንኪያ ማዳረስ ቢቻልና ሦሥት ሦሥት ወር እንኳ ቢቀምሳት ስንት
ነገር መማማር በተቻለ!”

በትክክል መረዳዳትን ያሳየ ቆይታ እንደነበረው በተለያዩ ጊዜያት ይናገራል። ምናልባት በትንሹ የመተባበራቸው ውጤት
ምስክር አሁን የምንወደው “ነገም ሌላ ቀን ነው” መጽሐፍ ነው። ወይም (አሁን የምንወደው “ነገም ሌላ ቀን ነው”
መጽሐፍ የመተባበራቸው ውጤት ነው። ነብይ “አጫሹ ሁሉ አጭሶ አጭሶ ባኮውን ከመወርወሩ በፊት ለዚያ ተኮራምቶ
ለሚጽፍ ዜጋ እንስጠው ማለትን ለመደው “ ይላል። እንኳንም ተባበራችሁ። ትውልድ ያመሰግናችኋል።

18
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

የኛ ሰው በአሜሪካ በነብይ ዐይን

“ጋዜጠኝነት ህዝባዊ አገልግሎት ለመስጠት፤ የማሕበረሰብን ህመም ለመታመም እና ተጽዕኖ ለመፍጠር ጥሩ መንገድ
ነው።” ይላል አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ቦብ ሺፈር። ነብይ በትክክል ይሄንን መንገድ የተጠቀመ ይመስላል። ጋሽ ነብይ
በአንድ ወቅት በአንድ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋም በቀረበለት ግብዣ ወደ ሰሜን አሜሪካ አቅንቶ ነበር። የብዙ
ሰዎች የሳምንት ጉጉት የሆነችው “የኛ ሰው በአሜሪካ” ጽሑፍ የተጠነሰሰችው እዛ ሄዶ ያየውን በመጻፍ ነው። እዛ
በፖለቲካ ትኩሳቱ መሃል ያጣቸውን አልፎም ሞተዋል ብሎ ያሰባቸውን ጓደኞቹን አግኝቷል።

የኛ ሰው አሜሪካ ውስጥ እንዴት እንዴት እንደሚኖር ቁልጭ ባለ ቋንቋ እና ባማረ ለዛ ጽፎልናል። ለዚህም ትጋቱ
እናመሰግነው ዘንድ ግድ ይለናል። የሰሜን አሜሪካ ቆይታውን ሲጨርስ ወደ
ተለያዩ ሀገራት ተዟዙሮ የዓለሙን ሁሉ አኗኗር አይቷል። ባህልን ባለመረዳት
ግራ ተጋብቷል። ይሔንንም በጋዜጠኛ እና ወገኛ ዓይኑ አይቶ አሳይቶናል።
ከዚሀም አንዱን እነሆ፡-

ጋሽ ነብይ መኮንን ጀርመን ሄዶ አንድ ባር ውስጥ ከባለቤቱ እህት ጋር


እየጠጡ ነው። ታድያ በጀርመን ባህል የድራፍት ጥራት የሚለካው
ሲቀዳ አረፋው በዛ ብሎ ከታየ ነው። እና ጋሽ ነብይ ይሔ ነገራቸው
አልጣመውምና የተቀዳለትን ጨልጦ ቀና ብሎ ባሩን ሲገረምም ሰው አፉ
በአረፋ ነጭ ሆኖ ያብረቀርቃል።

እነ ጋሽ ነብይ የሚጠጡት ሲያልቅባቸው አስተናጋጅ ለመጥራት


ከጎኑ ያለውን ደውል የባለቤቱ እህት ትጫነዋለች። እነሱ ያላወቁት
ነገር ቃጭሉ የተዘጋጀው አስተናጋጅ ለመጥራት ሳይሆን ከበር መልስ ቤቱን ሁሉ ለመጋበዝ ነው። መልዕክቱ
"በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ነገር ተከናውኖልኛል ወይም ትልቅ ሃብት አግኝቻለሁ። ነፃ ግብዣዬን በመቀበል ደስታዬን
ተካፈሉ" ነው። ጀርመኖቹ ነፃ መጠጥ ማግኘታቸውን ለማክበር ቤቱን በሁካታ ሞሉት። ነብይ የጀርመን አፍ
አያውቅም፤ የጀርመን ባህል አያውቅም። ምን እንደተፈጠረ አልገባውም። በኋላ የባሩ ባለቤት እነ ነብይን አናግሮ
በስህተት መሆኑን ሲሰማ ለደንበኞቹ የተፈጠረውን ስህተት ካስረዳ በኋላ ይቅርታ ጠየቀ። ጀርመናውያኑ ገንዘባቸውን
ከፍለው ወደሚጠጡት ተመለሱ።

እነዚህን እና መሰል ፈገግ የሚያሰኙ ግን ደግሞ መልዕክታቸው ጠንካራነት ያልጎደላቸውን ጽሑፎች ያስኮመኮመን
ነብይ ነው። ጥሩ ጋዜጠኛ በቦታው ያልነበረን ሰው እንኳ እንደነበረ እንዲሰማዉ የሚያደርግ ነው እንደሚባለው እኛም
ስራዎቹን አንብበን ለጥሩ ጋዜጠኝነቱ እጅ እንነሳለን።
እናም በመጨረሻ!
ነብይ ሆይ! ለግጥሞችህ እናመሰግናለን!
ለመጻሕፍትህ ወይም ለመጽሐፎችህ እናመሰግናለን!
ለጋዜጠኝነትህ እናመሰግናለን!
ለሰጠኸን እንዲሁም ለምትሰጠን ሁሉ እናመሰግናለን!

19
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

ጦሳ (xoossa) እና ለቅሶ
በዶርዜ
ወልደሐዋርያት ዘነበ

ዶርዜና በውሰጡ የሚኖሩ ሕዝቦች ስለ ፍጥረታት ማለትም ሰማይ፣ መሬት፣ ውሃ ፣ሰውና እንስሳት አፈጣጠር ያላቸው
ዕምነት አንድ ነው። እነዚህ ሁሉ በአንድ መለኮታዊ ሀይል እንደተፈጠሩ ኅብረተሰቡ ያምናል። ይህንንም መለኮታዊ
ኃይል ጦሳ(xoossa)ጾሳ በማለት ይጠሩታል። ይህ መለኮታዊ ኃይል የሁሉም ነገር ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ሁሉን ማድረግ
የሚችልና በሁሉም ቦታ የሚገኝ መሆኑን ያምናሉ። መኖሪያውም ሰማይ (salo) እንደሆነና ምድርን ለፍጥረታት መኖሪያ
ወስኖ የሰጠ መሆኑን ያምናሉ።

ለዚህ ፈጣሪ አምላካቸው በየጊዜው የዕለት ተግባራቸውን ካከናወኑ በኋላም ሆነ በጥዋት ምስጋና ማቅረብና መለመን
የተለመደ ተግባር ነው። ለምሳሌ እግዚአብሔር ወዳለበት ሰማይ አንጋጦ ጥዋት ጥዋት በሰላም ያሳደርከኝ አምላክ በሰላም
አውለኝ (Xoosso saron ayssiddayso saro peshsha) ወይም ማታ ማታ በሰላም ያዋልከኝ በሰላም አሳድረኝ
(Xoosso saron peshshiraysso saron ayssa) ማለት የተለመደ ነዉ።

ይህ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለመስራት ያቀዱትን ነገር በ “Xoossa” መልካም ፈቃድ የሚፈጸም መሆኑን ለመግለጽ
“ጦስ” ካለ (Xoossi giikko) ስለ አንድ ነገር የእውነትነት ቃላቸውንም ሲሰጡ “ጦስ” ኤሮ’ (Xoossi Ero) በማለት
ይምላሉ።
ከዚህ መለኮታዊ ኃይል የበታች ከሰው ልጅ ግን የበላይ ሆነው ሰውንና መለኮታዊ ኃይልን የሚያገናኙ የተለያዩ
መናፍስት(Ayyaana) እንዳሉ ያምናሉ። ፀሎታቸውም ወደ መለኮታዊ ኃይል የሚደርሰው በነዚህ መናፍስት አማካኝነት
እንደሆነ ስለሚያምኑ ለመናፍስቱ መስዋዕት ያቀርባሉ።

በሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸው በጎም ሆነ ክፉ ነገር


በመለኮታዊ ኃይል መልካም ፈቃድ ወይም ቁጣ
እንደሚመጣ ያምናሉ። በሽታ ከክፉ ነገሮች አንዱ
ሆኖ አንድ ሰው መለኮታዊ ኃይል የማይፈቅደውን
ኅብረተሰቡ ያወገዘውን ነገር “ጎሜ”(ግፍ) በመፈጸም
የሚመጣ አድርገው ይመለከታሉ።
ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት (life after death)
ያላቸው እምነት አንድ ሰው አንዴ ከሞተ በኋላ ነፍሱ
ወደ ፈጣሪ ትሄዳለች የሚል ሲሆን፤ የሞተ ሰው
ነፍሱ በሰማይ እንደምትኖርና ሌላ ዘመድ ሞቶ ወደ
ሰማይ ነፍሱ ስትሄድ እዚያ መገናኘት እንደሚቻልም
ያምናሉ።
ለዚህም እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው አንድ ሰው ሲሞት የሚባልለት አባባል: - በሰማይ ቤት ነፍሱን ይማረው (Salo
keethan shemppo maaro) የሚለው ነው። ይህም በሰማይ ቤት ምህረት እንዳለ እንደሚያምኑ ያሳያል። የሞተን
ሰው ስም ጠርተው ከማውራታቸው በፊት “ነፍሱን ይማረውና እከሌ” (Shemppo maaroshin oonakoy) የሚለው
አባባል ለዚህ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። የሞተ ሰው መንፈሱ ቤተሰቡንና ቤተዘመዱን በተለያየ ጊዜያት ተመላልሶ
እንደሚጎበኝ በሕብረተሰቡ ዘንድ ይታመናል። በመሆኑም የሟች ታላቅ ወንድ ልጅ በየስድስት ወሩ ወይም በየዓመቱ
ለአባቱ መንፈስ “ኣዋ (Addee ayyaana)” መስዋዕት ያቀርባል ይህም የሞተ ሰው በአካል ባይሆንም በመንፈስ
እንደሚኖር እንደሚያምኑ ያሳያል።

20
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

በአከባቢው አንድ በሽተኛ በሕይወት እንደማይቆይ ያከፋፍላል። የሰው ዕዳ ካለበትም እንዲከፍል ያዛሉ።
ሁኔታውን አይተው አዋቂዎችና ሽማግሌዎች የበሽተኛው ለሰው ያበደረው ወይም ያዋሰው ገንዘብና ንብረት ካለም
ቤተሰብ ራሱን እንዲያዘጋጅ ያሳስባሉ። ይህ ማሳሰቢያ ይገልጻል። እንደዚሁም ለራሱ ለቅሶ ማድመቂያ እንዲሆን
እንደተሰጠ የሚቀጥለው ተግባር ቤተሰቡ የለቅሶ ቅድመ ገንዘብ ወይም ንብረት ለህዝቡ የኑዛዜ ቃል ይሰጣል። ይህም
ዝግጅት ማድረግ ነው። ወደፊት በውርስ ጉዳይ ላይ ጭቅጭቅ እንዳይነሳና ዕዳ
ከሚደረጉ ቅድመ ዝግጅቶችም ዋና ዋናዎቹ፦ ሳይከፈል ቀርቶ “ጎሜ”(ግፍ) ሆኖ ቤተዘመዱን እንዳይጎዳ
የምግብ ዝግጅት ለማድረግ እህል መግዛት፥ለጠላ(Da- በማሰብ የሚደረግ ጥንቃቄና ቅድመ ዝግጅት ነው።
na) የሚሆኑ እህሎችን መውቀጥ፥ማስፈጨት፥እንጨት
መፍለጥ፥ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል። አንድ ሰው ሲሞት ለቅሶ ከመጀመሩ በፊት የሚደረገው
በርቀት ያለ ሰውን ስለ ለቅሶው እንዲሰማ ማድረግ ነው።
መልዕክት(kita) መላክ፦ ይህ ሩቅ ላሉ ቤተዘመድ ይህም የሚደረገው በሽተኛው በጠና በታመመበት ወቅት
የሚላክ መልዕክት ሲሆን ይህ መልዕክት ሲላክ ሰውየው መልዕክት በመላክ ዘመድ አዝማድ እንዲመጣ በማድረግ
አለመትረፉ ሲታወቅ “እከሌ በጣም ታሟል በነፍስ ድረሱ ሲሆን ይህ ካልተደረገ በሽተኛው ከሞተ በኋላ ቤተሰቦቹና
ራሳችሁን አስባችሁ ኑ” ተብሎ ሰዎች በባህሉ የሚፈፀመውን ቤተዘመድ ሩቅ ላለ ዘመድ መልዕክተኛ ይልካሉ። በባህሉ
ለማድረግ ተዘጋጅተው እንዲመጡ ይደረጋል። መልዕክተኞች ሁለት ሲሆኑ ከሟች ጋር የደም ዝምድና
የሌላቸው መሆን ይገባል።
በቤተዘመድ በኩል የሚታረድ ከብት ማዘጋጀት፥መከፈኛ
ልብስ ማዘጋጀት ፡ በሽተኛው እንደሞተ ወዲያው ለጎረቤትና የለቅሶ አለቃቀስ ሥርዓት ደግሞ እንደሟቹ ሁኔታ
ለአካባቢው ሰው የስራ ድርሻ መስጠት የመሳሰሉት ይሆናሉ። ይለያያል።ይህም እንደ እድሜው፡ እንደ የማህበራዊ
ከበሬታው ይለያያል። ለምሳሌ ለህጻናት፥ለወጣትና ጎልማሳ
ከዚህ ቅድመ ዝግጅት ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችለው የሚደረገው ለቅሶ፤ ለሽማግሌ ወይም ለአረጁ ሰዎች
የበሽታውን የኑዛዜ ቃል ወይም (Baza) መቀበል ነው። የሚለቀስ ለቅሶና ለጀግና፥ ለባላባት፥ ለአለቃ፥ለካዎና
ይህንን አንዳንድ በሽተኛ በራሱ ሽማግሌዎችን አስቀምጦ ለደሙሳ የሚለቀስ ለቅሶ አንድ አይነት አይደለም። ይህም
የሚያደርገው ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን በሽተኛው ካልተናገረ ለቅሶው የሚወስደው ቀን፥ የሀዘኑ ክብደትና ቅለት፤
ሽማግሌዎች ከዘመዶቹ ከተወከሉት ጋር በመሆን እንዲናዘዝ የቅድመ ዝግጅቱ ሁኔታና የመሳሰሉት ይለያያሉ።
ይገፋፉታል። በዚህ ጊዜ ሀብቱን ለልጆቹና ለባለቤቱ

21
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

ከታች በምስሉ ላይ እንደምትመለከቱት በአንድ ወቅት በዶርዜ ሐይዞ አካባቢ አንድ ንጉሥ ወይም (Halaka) በሞቱበት
ጊዜ የተነሱት ፎቶ ነው።
ከላይ እንደተጠቀሰው በአካባቢው
ለጀግና።፥ለአለቃ ፥ካዎና ለደሙሳ ለቅሶ
ሥነሥርዓቱ ይለያል። እናም ለእነዚህ
"ኮይሳ" (koysaa) የሚባል የለቅሶ
ዜማ እያዜሙ ራቅ ባሉ ቀበሌዎችና
አካባቢዎችን በመሄድ የተለያዩ
ቅጠላቅጠሎችን፥ሐዴ፥(hade) የነበር
ቆዳ፡የአንበሳ ቆዳ፥ የሰጎን ላባ(guch-
che) ወንዶች ጦርና ጋሻም ይይዛሉ።

የለቅሶ ዜማዎች ደግሞ፦


ለሴት፦ ችግር ቻይዋ-Dandayee
meto dandaye
ታሳዝኝያለሽ-hoo miiggee michees
ታስለቅሻለሽ-hoo miiggee yeessees
ለወንድ ሲሆን፦ የሰማዩ እንቁላል-phuu-
phulee salo phuuphulee
ታሳዝናለህ-hoo miiggee michees
ታስለቅሳለህ-hoo miiggee yeessees እያሉ ያዜማሉ።

ማሳሰቢያ!
በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች "፣መንግስታዊ "፣መንግስታዊ ባልሆኑ ህጋዊ የሶሻል ሚዲያ ገፆች እንዲሁም በተለያዩ
የሀገር ውስጥም ፣ከሀገር ውጭ አስጎብኚ ድርጅቶች። ይህ ሰፊ ማህበረሰብ "መንደር ብሎ "የመጥራት ልማድ አለ።
ማህበረሰብ ለመባል ጎሳ ፣አያት ከቅደመ አያት የሚወረስ የዘር ሐርግ ፣የዘር ሀረጉን ከሁለት ወይንም ከዚያ በላይ
የሚከፍል መንደር ፣እና የእድሜ እርከን ፣የሚያሟላ ማህበረሰብ እንጂ መንደር አይባልም ። በአከባቢው ከሚገኘው
የቱሪስት መዳረሻዎች ውስጥ አንዱ የሆነው 'ዶርዜ መንደር ሎጅ እንጂ "አከባቢው ማህበረሰብ ከመንደር በላይ ነው።
ምንጭ ፦ከአከባቢው ሽማግሌዎች ፣
(ፆሲ ኢንጎ ረጅም ዕድሜ ከጤና ጋር "ለዶርዜ ሽማግሌዎች ተመኘሁ )

22
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

የተዘነጋው ታሪካችን
(ክፍል አንድ) ልዑልሠገድ አስማማው

የሰውን
ልጅ ታሪክ ስናነሳ በቀደምትነት የሚነሱት የሰው ልጅ ኑሮን ለማሻሻል ስለ ሄደባቸው
መንገዶች፣ ተመራምሮ ስለ ደረሰባቸው የተፈጥሮ እውነታዎች፣ ፈጥረውኛል እና
ይጠብቁኛል ብሎ ስለ ሚያመልካቸው እና መስዋዕት ስለሚያቀርብላቸው አማልክት፣
እንዲሁም ግዛቱን ለማስፋፋት ስላደረጋቸው አያሌ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ናቸው።

ምንም እንኳ በታሪካችን ውስጥ ጎልተው የሚነሱት እና የሚወሱት ዋና ዋና ነጥቦች እነዚህ ቢሆኑም በሰው ልጅ ታሪክ
ውስጥ ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች በተጨማሪ እምብዛም ሲገለጽ የማይታይ ነገር ግን በሰው ልጅ ላይ በብዙ መልኩ
ተጽዕኖ ሲያሳድር የቆየ እሁንም እያሳደረ ያለ ታላቅ ነገር አለ።

በሽታ!
ከጭቃ ተድበልብሎ፣አልያም ከእንጨት ተቀረጾ ወይንም ደግሞ በዝግም ለውጥ ከዝንጀሮ ተመዝዞ የመጣው የሰው ልጅ
እዚህች ምድር ላይ ከመጣበት ግዜ ጀምሮ ከበሽታ ጋር ሲታገል እዚህ እንደደረሰ ይነገርለታል።

ምናልባትም በሽታ የሰው ልጅ ፈጥረውኛል ብሎ ወደሚያስባቸው


አማልክት እንዲቀርብ እና ከእነርሱ ጋር ያለውን ቁርኝት እንዲያጠብቅ
ከሚያደርጉት ዋነኛ ነገሮችም መሃል ነው ብንል ማጋነን አይሆንብንም።

ከጥንት ጀምሮ ምናልባትም እስከዛሬም ድረስ የሰው ልጅ ስለሰራው ክፉ ስራ ወይንም ስለተላለፈው ህግ ከአማልክቱ
የሚተላለፍበት ቅጣት ወይንም ደግሞ ክፉ መንፈስ በመኖሪያ አካባቢው ሲሰፍር በሽታ እንደሚከሰት ይታመናል።
ለዚህም ማስረጃ ይሆነን ዘንድ የግሪኩን የፓንዶራን ታሪክ እና የሞንጎሊያኖችን ሃተታ ተፈጥሮ እንመልከት።

23
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

የፓንዶራ ታሪክ
ብዙ መልክ እና ታሪክ ያለው የግሪኮቹ ሃተታ ተፈጥሮ ስለሰው
ልጅ አፈጣጠር ከሚያትታቸው ታሪኮች መሃል አንደኛው የ
ፕሮሚቲዩስ እና የመጀመሪያው ሰው የፌይኖን ጉዳይ ነው።
ታሪኩም በአጭሩ እንደሚከተለው ነው።
ከቀደምቶቹ አማልክት ከታይታን ጎራ የሚመደበው ፕሮመቲዩስ
ሰው የመፍጠር ሃሳብ በውስጡ ጸነሰ። ጸንሶም አልቀረ ውሃን እና
ሸክላን አቀላቅሎ ከሸክላ ጭቃ የመጀመሪያውን ሰው ፈጠረ።
ስሙም ፌይኖን ይባል ነበር። የዚውስ ልጅ የሆነችው ሴቷ
አምላክ አቴና ደግሞ በፌይኖን ላይ የህያውነትን እስትንፋስ
ተነፈሰችበች።

ሰውም ከዚያን ግዜ ጀምሮ ህያው መሆን ቻለ። ፕሮሚትየስ


ግን በዚህ ብቻ የሚረካ አምላክ አልነበረም እና ለሰው ሌላ ነገር
ሊጨምርለት በልቡ አሰበ። ሰው እንደ አማልክቱ ቀጥ ብሎ
ይቆም እና ይራመድ ዘንድ አደረገው። በተጨማሪም እራሱን
ከኣደጋ ይጠብቅበት ዘንድ፣ ለብርድ ጊዜ ሙቀት እና ለጨለማም
ብርሃን ይሆነው ዘንድ እሳትን ለሰው ልጅ ገጸ፟በረከት አድርጎ
ሰጠው።

በዚህ ሁኔታ የተናደደው ዚውስ ደግሞ እሳትን ከሰው ልጅ ነጥቆ ደበቀው። ፕሮሚቲዩስ ግን ለፈጠራቸው የሰው ልጆች
ጥልቅ ፍቅር ነበረው እና የተደበቀውን እሳት ከተደበቀበት አውጥቶ መልሶ ለሰው ልጆች ሰጣቸው። ዚውስም የሰው ልጅ
እሳትን ሲጠቀምበት በተመለከተ ግዜ እንደተከዳ እና ህጉም እንደተጣሰ አወቀ።

ለዚህም መተላለፍ የሰው ልጅን ሊቀጣ አሰበ እና ብረት ቀጥቃጩ ሄፋስቲየስን አንዲት ውብ
ሴት እንዲሰራ አዘዘው። ከሴቷ በተጨማሪም ስጦታ መያዣ የሚሆናትን ሳጥን እንዲሰራም
ነገረው። ሴቲቷም ተሰራች ስሟም ፓንዶራ ተባለ። በኦሊምፐስ ተራራ ያሉ እንስት
አማልክት ሁላ በውበቷ ተደነቁ።

ዚውስም ይህቺን ውብ እንስት ለፕሮሚቲዩስ ወንድም ኢፒሚትዩስ ስጦታ አሰይዞ ላካት።


እንዲህ ሲልም ትዕዛዝን ሰጣት “ሂጂና የፕሮሚትየስ ወንድም የሆነውን ኢፒሚትየስን
አግኝው። ከልቡ እና ከቤቱ ይሁኝታን ታገኚ ዘንድ ደግሞ ይሄንን ሳጥን ስጦታ ይሆነው
ዘንድ አቅርቢለት። ነገር ግን አንቺ በምንም ተዓምር ይሄንን ሳጥን እንዳትከፍች።”

ፓንዶራም ትዕዛዟን ተቀብላ ወደ ኢፒሜቲየስ ቤት አመራች። ኢፒሜቲየስም ባያት ግዜ


በውበቷ ተረታ፤ ወደቤቱም ትገባ ዘንድ ፈቀደላት። ሚስቱ ትሆነው ዘንድም አሰበ።
ኢፒሚትየስ ቤት ከገባች በኋላ ፓንዶራ ሳጥኑ ውስጥ ያለውን ነገር የማወቅ ጉጉቷ እያየለ
መጥቶ አንድ ቀን ትዕዛዟን አፍርሳ ሳጥኑን ከፈተችው።

ከሳጥኑ ውስጥም ረሃብ፣ በሽታ፣ ህመም፣ ጥላቻ እንዲሁም ሌሎች መጥፎ የተባሉ ነገሮች
ሁሉ ወጥተው ከሰው ልጅ መኖሪያ ከተሙ። ከሳጥኑ ውስጥ መጨረሻ ላይ ግን ተስፋ ቀርቶ
ነበር።

ከዚህ ታሪክ እንደምንረዳው የሰው ልጅ መጀመሪያ ሲፈጠር ከሃዘን፣ ከመከራ፣ ከችግር፣ ከበሽታ እና ከሌሎችም
አስጨናቂ ነገሮች ነጻ ሆኖ ነበር። ነገር ግን አማልክቱ ደስ ባለመሰኘታቸው በሰው ልጅ ላይ ከተላለፈበት ቅጣት መሃል
አንደኛው ከበሽታ ጋር መተዋወቅ ሆኖ እናገኘዋለን።
24
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

የሞንጎሊያኖች ሃተታ ተፈጥሮ


“በህዋችን ላይ ውሃ እና የሁለት ልጆች አባት
ከሆነው የሁሉ ገዢ እና የሰማዩ አምላክ በቀር ማንም
አልነበረም።” ብለው ያምናሉ የጥንት ሞንጎላውያን።
የዚህ የሰማይ አምላክ ልጆቹም ኡልገን እና ኤርለግ
ይባላሉ። የሰማዩ ገዢም ለልጆቹ ግዛት ይሆናቸው ዘንድ
ከህዋ እኩሌታውን ወደ ላይ ለኡልገን እኩሌታውን
ወደ ታች ለ ኤርለግ ሰጣቸው። ኡልገን የራሱን ዓለም
ይፈጥር ዘንድ አሰበ።

ከዚያም ጠላቂ ወፍ ከወደ ጥልቁ ውሃ ገብታ ለፍጥረት


መነሻ ይሆነው ዘንድ ጭቃ እንድታመጣለት አዘዘ።
ጠላቂ ወፏም ትእዛዙን ትፈጽም ዘንድ አልተቻላትም
ነበር።

ከዚያም ኡልገን ድጋሜ ዳክዬን ከጥልቁ ገብታ ጭቃ ታመጣለት ዘንድ አዘዛት። ዳክዬም ከጥልቁ ገብታ ጥቂት የጭቃ
ርዝራዥ በአፏ ይዛ ተመለሰች። ኡልገንም ዳክየዋ ካመጣችው ጭቃ ላይ አረፍ አለ። በዚያው እንቅልፍ ወሰደው።
የዚህን ግዜ ወንድሙ ኤርለግ ጭቃውን ሰርቆ የኡልገንን ስራ ያደናቅፍ ዘንድ አሰበ። አስቦም አልቀረ አደረገውም።
ጭቃው ግን ከላዩ ላይ ሲቀነስለት መጠኑ ሊያንስ ሲገባ በተቃራኒው በመጠኑ ይገዝፍ ጀመር።

የጭቃው መስፋፋትም ኡልገንን ከእንቅልፉ ቀሰቀሰው። ኡልገንም ከእንቅልፉ ተነስቶ ከጭቃው ሰውን እና ሌሎች
እንሰሳትን ይፈጥር ዘንድ ሃሳብን በልቡ ጸነሳት። ጸንሶም አልቀረ ወለዳት፤ ከጭቃው ሰውን እና ሌሎች እንሰሳትን ፈጠረ
እናም አካላቸው እስኪደርቅ ከውጭ አስቀመጣቸው።

ነገር ግን ጊዜው የበረዶ ዝናብ የሚዘንብበት ነበር እና ቶሎ ሊደርቁለት አልተቻላቸውም። ኡልገንም የተፈጠሩትን
ፍጥረታት እስኪደርቁ ድረስ እንዲጠብቅ ለውሻ ሃላፊነት ይሰጥ እና ለፍጥረታቱ ነፍስ ይፈጥርላቸው ዘንድ ወደ ሰማይ
ይሄዳል። ኡልገን መሄዱን የተመለከተው ኤርለግ አዲስ የተፈጠሩትን ፍጥረታት ለመመልከት ወደ ተቀመጡበት ቦታ
ሲሄድ ውሻው አደገኛ ነበር እና ሊያስጠጋው አልቻለም። ኤርለግ ለውሻው ከብርድ መከላከያ እንዲሆንለት ወፍራም
እና ጸጉራማ ኮት ይሰጠዋል (ውሾች ቆዳቸው በጸጉር መሸፈን የጀመረው ከዚያን ግዜ ጀምሮ ነው። ከዚያ በፊት መላጣ
ነበሩ።) ውሻውም በተሰጠው ስጦታ ተደስቶ ኤርለግ አዳዲሶቹን ፍጥረታት እንዲያይ ይፈቅድለታል።

ኤርለግም ወደ ፍጥረታቱ እንደቀረበ እላያቸው ላይ ተፋባቸው። ከዚያን ግዜ ጀምሮ ሁሉም የፍጥረታት በሽታ እና ህመም
እንደተወዳጃቸው ይነገራል።
በዚህኛው ታሪክ ደግሞ የሰው ልጅ ሲፈጠር ንጹህ የነበረ ቢሆንም እኩይ ባህሪን የተላበሰ አምላክ በፈጸመባቸው ድርጊት
ከበሽታ እና ህመም ጋር እንደተዋወቀ ማየት እንችላለን። ስለዚህ በሽታ ምንጩ ክፉ መንፈስ ነው ወደሚለው ሃሳብ
ያመጣናል ማለት ነው።
እስኪ አሁን ደግሞ ሳይንሱን መሰረት አድርገን ስለበሽታ አመጣጥ እና ምክንያት ጥቂት ነገሮችን እናንሳ።
ኢቮሉሽንን (ዝግመተ ለውጥ) መሰረት ስናደርግ የዛሬ ሁለት ሚሊዮን ዓመታት አካባቢ የጥንት አያቶቻችን ከዛፍ
ፍራፍሬውን፣ ቅጠላ ቅጠሉንና ስራስሩን እንዲሁም አንዳንድ አነስ ያሉ እና መጠነኛ እንስሳትን እያደኑ እና እየተመገቡ
ከሌሎች ግዙፋን አዳኝ እንስሳት እራሳቸውን እየጠበቁ በታላቅ ፍራቻ ዋሻ ውስጥ ይኖሩ ነበር።

25
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

ነገር ግን ይሸሸጉ እና ይደበቁ የነበረው


በዓይን ከሚታዩት ጠላቶቻቸው ይሁን
እንጂ የእነርሱ እጥቂዎች በዓይን የሚታዩት
አውሬዎች ብቻ አልነበሩም። እንዲያውም
ለመሸሸግም ሆነ ሮጦ ለማምለጥ አልያም
ከድንጋይ ጠርበው በሰሯቸው ስለታም
የጦር መሳሪያዎች ለመከላከል የማያመች፤
በየቀኑ የህብረታቸውን አባል ህይወት
እየነጠቀ የሚያሳቅቃቸው እና በፍርሃት
የሚያር’ዳቸው ስውር ጠላት ነበራቸው ።
እሱም መንስኤውን እንኳ በቅጡ ሊረዱት
ያልቻሉት በሽታ ነበር።

በዚያ ዘመን የነበሩ በሽታዎች አብዛኛዎቹ ከሚያድኗ’ቸው እንስሳት የሚተላለፉ፣ በትላትል የሚከሰቱ፣ ከቅማል
የሚተላለፉ፣ ቴታነስ፣ ብላሃርዚያ የመሳሰሉት ሲሆኑ በዘመናቸው የአያሌዎቹ ህይወት ሲቀጥፉ ነበር።

ወደ በኋላ ላይ ግን ከዛሬ 300,000 ዓመት በፊት እንደነበሩ የሚነገርላቸው ኒያንደርታልስ እና ሆሞ ሳፒያንስ የተባሉት
የጥንት የሰው ልጅ ዝርያዎች ከላይ ከሰማይ በ መብረቅ ብልጭታ አማካኝነት ወይም ከታች ከምድር ውስጥ በእሳተ ገሞራ
ፍንዳታ አማካኝነት ፈልቆ፣ በምድር እጽዋት ነዳጅነት እና በኦክስጅን አጋፋሪነት ተፋፍሞ፣ ከ 400 ሚሊየን ዓመታት
በፊት እንደተከሰተ የሚታሰበውን እሳት እንደሌሎች እንስሳት ከመፍራት ተሻግረው መቆጣጠር እና ለግል ፍጆታቸው
ማዋል ጀመሩ።
እሳትን መጠቀም መጀመራቸው ከብርድ፣ ከጨለማ እና ከግዙፋን እንስሳት ጥቃት ብቻ አልነበረም የታደጋቸው። ከእሳት
በፊት በጥሬው ሲመገቡ የነበረውን የእንስሳት ስጋ አብስለው መብላት በመጀመራቸው በሽታ አምጪ የሆኑትን ትላትል
እና በዓይን የማይታዩ ጀርሞችን መግደል ችሎ ነበር።

በዚህም ከበሽታ ጥቂት ፋታ አግኝተው፣ በበሽታ ሳቢያ የሚሞቱባቸውን አባላት ቁጥር መቀነስ ችለው ነበር። ነገር
ግን የሰው ልጅ ብዛቱ በአያሌው እየጨመረ መጣ። የምድርም የሙቀት መጠን
እየጨመረ፤ ምድርን በበረዶው ዘመን ጊዜ ሸፍኗት የነበረው በረዶም
በሙቀቱ ሳቢያ እየቀለጠ የሰው መኖሪያ የነበሩ አያሌ ደሴቶችን እንዲሁም
አንዳንድ የየብስ ክፍሎችን ማስመጥ ጀመረ። በሙቀቱ መጨመር
ምክንያትም የእንስሳቱ እና የእጽዋቱ ሁኔታ እየተቀያየረ መጣ።
በዚህም የተነሳ የሰው ልጅ ለእለት ጉርስ የሚሆነውን የምግብ ፍጆታ
በአደን እና ለቀማ ላይ ብቻ ተመርኩዞ ለማሟላት የሚቻል አልሆነለትም።

እንዲህ ለተጋረጠበት የህልውና ተግዳሮት መፍትሄ ይሆነው ዘንድ


ጠቢቡ ሰው ከዛሬ 10,000 ዓመታት በፊት እንስሳትን እና የሳር ዝርያ
የሆኑ አዝዕርትን በማላመድ ለእለት ጉርሱ ማዋል እንደጀመረ ይነገርለታል።
ያኔ ደግሞ ከእንስሳቱ እና ከሰብሎች በሚተላለፉ አዳዲስ አይነት በሽታዎች ጋር ለመተዋወቅም
በቅቷል።William McNeill የተባለው አሜሪካዊ የታሪክ ተመራማሪ እንደሚለው “የሰው
ልጅ ከውሾች ጋር 65፣ ከ ቀንድ ከብቶች ጋር 50፣ ከ በግ እና ፍየል ጋር 46፣ ከ አሳማዎች
ጋር 42፣ ከፈረስ ጋር 35 እንዲሁም ከዶሮ ዝርያዎች ጋር ደግሞ 26 የበሽታ አይነቶችን
ይጋራል።”

በተጨማሪም በግብርና መጀመር ምክንያት የሰው ልጅ ቋሚ የመኖሪያ ቦታ ማቋቋም


ችሏል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ለወባ ትንኞች ምቹ የመራቢያ ቦታን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
ይህም የሰውን ልጅ በከፍተኛ ሁኔታ ለወባ በሽታ ተጋላጭ አድርጎታል።
26
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

የሰው ልጅ ከዋሻ ነዋሪነት ወጥቶ፣ የእለት ጉርስን ለማግኘት ከመባዘን ተሻግሮ፣ ከተሞች መመስረት እና መንግስታት
ማቋቋም ከጀመረ በኋላም በሽታ አለ የማይባል አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖውን በሰውልጅ ላይ ሲያሳድር ሰነባብቷል።

ግብጽን የስልጣኔዋ ማማ ላይ እንድትወጣ


አድርጓታል ተብሎ የሚታሰበው ፈርኦን
አሜንሆቴፕ ሶስተኛ (Amenhotep III
ruled Egypt from 1386 to 1349 BC
) በነበረበት ዘመን ምንም አይነት የጦርነት እና
የግጭት ምልክት ሳይኖር እንዲሁ የተተዉ እና
የተቃጠሉ ከተሞች እና የመኖሪያ መንደሮች
በቁፋሮ ተገኝተዋል። እንዲሁም በዚያው ዘመን
ምንም አይነት የተመዘገቡ የጦርነት ታሪኮች
ሳይገኙ ያለተለምዷቸው በአንድ ቦታ እጅግ
ብዙ ሬሳዎችን የያዙ የጅምላ መቃብሮችም
በቁፋሮ ተገኝተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ ዘመን አንዳንድ የከፍተኛ ሹማምንት አባላት እና የፈርኦኑ ቤተሰቦችም ሳይቀሩ ከጥንት
ግብጻውያን የአቀባበር ባህል በተለየ ሁኔታ ለሹማምንቱ እና ለፈርኦኑ ቤተሰብ በማይመጥን መልኩ መቃብራቸው
እንደሌሎቹ ሳይዋብ፣ ከሞት በኋላ ላለው ህይወት የሚገለገሉበት ለክብራቸው የሚመጥን ቁሳቁስም ሳይጠቀምበት
ተቀብረዋል።
ለዚህም እንደ ማስረጃ ተደርጎ የሚሰጠው መላ ምት፡- አንደኛ በዘመኑ ከፍተኛ ህዝብ የጨረሰ የበሽታ ወረርሺኝ በመከሰቱ
አያሌ ሰዎችን ስለጨረሰ እና ከሚያልቁት ሰዎች መሃል ደግሞ ቀራጺዎች እና ሌሎች የጥበብ ባለሞያዎችም ስለሚገኙ
ያ የፈጠረው ክፍተ ነው የሚል ነው። ሁለተኛው መላ ምት ደግሞ ወረርሺኙ ክፉኛ አስደንጋጭ እና ተላላፊ በመሆኑ
ራሳቸውን ለመታደግ ሲሉ ሟቾችን በሰላሙ ግዜ እንደነበረው አይነት አቀባበር መቅበር አልቻሉም የሚለው ነው።
በሁለቱም መንገድ ብንሄድ የማይካደው ሃቅ በሽታ ከፍተኛ የሆነ ቀውስ አድርሶ እንደ ነበር ነው።

በሌላ ጎን ደግሞ ከአሜንሆቴፕ ዘመን በፊት ይመለኩ የነበሩ አማልክት የተከታይ ቁጥራቸው ቀንሶ ዝቅተኛ እና ብዙም
የማትታወቅ የነበረች፣ ባለ አንበሳ ፊቷ፣ የጦርነት እና የ ወረርሺኝ በሽታዎች አምላክ ተብላ የምትታወቀው ሴኬምት እና
ሌሎች የማይታወቁ እና ብዙ ተከታይ ያልነበራቸው ንዑስ የፈውስ አማልክት በዘመኑ ዝናችው ገንኖ ነበር። አሜንሆቴፕም
ህዝቡን ከወረርሺኙ ለማትረፍ በሚመስል መልኩ ለሌሎች ዐቢይ አማልክት ወደ 200 የሚጠጉ የድንጋይ ሃውልቶችን
ሲያስቀርጽ ለሴኬምት ብቻ ከ 700 በላይ የድንጋይ ሃውልቶችን ስለማስቀረጹ በቁፋሮ የተገኙ ማስረጃዎች ያመላክታሉ።
በእሱ ዘመንም ይሰሩ የነበሩ ሃውልቶች በፊት ከነበሩት የጥራት ደረጃቸው ዝቅ ያለ እና በውበትም ሆነ በአቀራረጽ
እምብዛም አስደናቂ ያልነበሩ ነበሩ። ይህ ሁሉ የሆነው ግብጽን ለ 8 ዐመታት መትቷታል ተብሎ የሚታሰበው Bubonic
Plague የሚባል የበሽታ ወረርሺኝ በተከሰተበት ዘመን ነበር።

ታላላቅ ስልጣኔዎች እንዲሁም ጽህፈት ሳይቀር እንደተወለዱበት የሚነገርለት የነሃስ ዘመን በወረርሺኞች መስፋፋት እና
ማየል ምክንያት ሊወድቅ እንደቻለ አንዳንድ የታሪክ ምሁራን ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። የበሽታ ተጽዕኖ በዚህ ብቻ
የተገታ አይደለም። የዓለማችን ታላቁ ንጉስ እስክንድር ሳይቀር ግሪክን ለመቆጣጠር የቻለው የወባ ወረርሺኝ ሃገሪቷን
ክፉኛ በመታበት እና ባደከመበት ግዜ ላይ ነበር። እሱ ታላቁ ንጉስ እራሱ ገና በወጣትነት እድሜው፣ ምድርን ሮጦባት
ሳይጠግብ west Nile viral encephalitis በሚባል የአንጎል ኢንፌክሽን ሳይሞት እንዳልቀረ የታሪክ መዛግብት
ያስረዳሉ።

27
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

ምናልባትም የሰውን ልጅ እንደ በሽታ ያጠፋ የለም ቢባል እውነታውን ማሳነስ እንጂ ማጋነን ይሆንም። በእርስ በእርስ
ጦርነት፣ በድርቅ እና ርሃብ እንዲሁም በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከሞተው የሰው ልጅ ቁጥር ይልቅ በበሽታ
ህይወቱን ያጣው የሰው ልጅ ቁጥር ይልቃል። ለማስረጃ ይሆነን ዘንድም በዓለማችን ላይ ከተከሰቱ አያሌ የተላላፊ በሽታ
ወረርሺኞች መካከል ሁለቱን እናንሳ።
በ14ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እንደተከሰተ
የሚነገርለት ጥቁሩ ሞት (Black Death)
በመባል የሚታወቀው የበሽታ ወረርሺኝ
ብቻውን የ አውሮፓን 40-60% የሚሆነውን
ህዝብ ፈጅቷል። እንዲሁም በሰዓቱ እስከ
450 ሚልዮን እንደሚደርስ የሚገመተውን
የዓለማችንን የህዝብ ብዛት ወደ 350 እስከ
375 ሚልዮን ድረስ ዝቅ ሳያደርገው እንዳልቀረ
ይገመታል። የዓለማችን የህዝብ ቁጥርም እስከ
17ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ሊያገግም አልቻለም
ነበር።
በሃያኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ፈንጣጣ (small
pox) እየተባለ የሚጠራው በቫይረስ የሚተላለፍ
በሽታ ከመጥፋቱ በፊት እንደ ወረርሺኝ በተከሰተበት ጊዜ ወደ 300 ሚልዮን የሚሆኑ የሰው ልጆችን ህይወት እየቀጠፈ
ይገመታል። የአሃዙን ግዙፍነት አጥርተን ለመመልከት ያህል በሃያኛው ክፍለ ዘመን በጦርነት ከሞቱት የሰው ልጆች ብዛት
ጋር ስናነጻጽረው ሶስት እጥፍ እንደ ማለት ነው።

እንግዲህ በቅንጭብጫቢ መልኩ ለማቃመስ እንደተሞከረው በሽታ በሰው ልጅ ታሪክ ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖውን
እንዳሳደረ ለማሳየት ተሞክሯል። ለመጠቅለል ያህል በበሽታ ምክንያት ከተሞች ያለነዋሪ ቀርተዋል፣ ነገስታት ያለክብር
ተቀብረዋል፣ አማልክትም ያለ ተከታይ ቀርተዋል። አንዳንድ አማልክትም ደግሞ ስለበሽታው ሲባል ተከታይ በዝቶላቸዋል።
ዓለማችንም በበሽታ ምክንያት ታላላቅ ነገስታትን፣ ጠቢባንን እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎቿን ሳይቀር አጥታለች። በሽታ
በእያንዳንዷ የሰው ልጅ የታሪክ ቅንጣት ውስጥ የራሱ የሆነ አሻራ አለው ብንል የማይገባውን ቦታ መስጠት እንዳልሆነ
ይህች ቅንጭብጫቢ ጽሑፍ አስረጅ ናት ብለንም እናምናለን።

ነገር ግን የሰው ልጅ በበሽታ ተረትቶ፣ ሽንፈቱን አሜን ብሎ ተቀብሎ፣ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ከጥንት ጀምሮ
እስካሁን ዘመን ድረስ የበሽታን መንስኤ ለማወቅ፣ መተላለፊያ መንገዶቹን ለመረዳት እና ለበሽታው ፈውስ የሚሆነውን
መድሃኒት ለመስራት እልህ አስጨራሽ ተጋድሎን ሲያደርግ ቆይቷል።
ታዲያ ለዚህ ጠላቱ መፍትሄ የሚሆነውን ያገኝ ዘንድ ከምድር እጽዋት እስከ ባህር ውስጥ ዋቅላሚዎች፣ ከግዙፋን እንስሳት
እስከ ደቂቃን ዘአካላት ድረስ ተመራምሯል፤ እየተመራመረም ነው። ለዚህ ዘርፍ ሲባልም አያሌ መጠን ያለውን ገንዘብ
ወጪ አድርጓል። ይሄ ተጋድሎውም የሰው ልጅ ህልው ሆኖ እስከቆየ ድረስ የሚቀጥል ነው።

በሚቀጥለው የባይራ እትም የሰው ልጅ ለበሽታ መፍትሄ የሚሆነውን መንገድ ለማግኘት የሄደበትን ርቀት ቀንጨብ
ቀንጨብ አድርገን ይዘን እስክንመጣ ድረስ ቸር ይቆዩን። ለዛሬ ግን እዚህ ላይ አበቃን።

ማጣቀሻዎች(References)

1. Cambridge University, 1996, The Cambridge illustrated history of medicine, Cambridge Universi-
ty Press.
2. Philip Norrie, 2016, A history of diseases in ancient times; more lethal than war, the University of
Washington Press.
3. Cynthia Stokes Brown, 2008, Big History from the Big Bang to the Present, The New Press.
4. Stephen J. Pyne, 2001, Fire A Brief History, Springer Nature.

28
ቅጽ ፩ ቁጥር ፮ |ግንቦት ፳፻፲፮

ልክ ሳምራዊት ንጉሤ
ጊዜ ቢወስድም ልክ አለ!
.... የወደድነውም ሁሉ ልክ
አይደለም!
አንድ አባት ለልጁ ጫማ
ለመግዛት ወደ መሸጫ ሱቅ
ይገባል። ከዛም ለልጁ ይሆናል
ያለውን እያስለካ ያስሞክረዋል።
አንዱ ሲሰፋ እንዱ ሲጠብ
በመጨረሻ ልጁ ዓይኑ ከአንድ
ቆንጆ ጫማ ላይ አረፈ። “አባ
ያ ይሁን?” አለ ለአባቱ ወደ
ጫማው እያመለከተ።

አባቱም “እስኪ አምጣው


ይሞክረው” አለ ለሻጩ።
ጫማው መጣ ሞከረው።
ልጁ ጫማውን በጣም ስለወደደው
አባቱ “እ ይዞሀል?” ሲለው “አይይይ አልያዘኝም ሆኖኛል” አለው። አባቱ “ግን እስኪ ተነስ እና ሄድ ሄድ በልበት”
አለው። የልጁ ፊት ላይ ምቾት የለም ይሄን ያየው አባት በእጁ ጫማውን ነካ ነካ ሲያደርገው እንደያዘው አወቀ “ልጄ”
አለው ቀና ብሎ እያየው....
“ልጄ ጫማ ከሚጠብህ ሀገር ቢጠብህ ይሻላል”
እውነት ነው።
ልክ ጥሩ ነው!

ስለወደድነው ብቻ ብዙ ልክ ያልሆኑ ህይወቶች ውስጥ ያለን አንጠፋም እኮ.... ሲጠብ ቆይ እየቆየ ይለቃል፤ ሲሰፋ
ሳድግ ይሆነኛል አይነት ተስፋ።

ለመቼ ነው የፈለግነው ለአሁን ነው ለወደፊት?


ጊዜ ቢፈጅም ዋጋ ቢያስከፍልም የሚሆነን መፈለግ አይሻልም?
ልጁ ይሁን ያለው አንድም ጫማውን ስለወደደው ሁለትም የሚሆነው ከጠፋ አባቱ የሚሆንህ ጠፋ እኮ ብለው መግዛቱን
እንዳይተውበት ነው።

አባቱ ግን ጫማህ ከሚጠብህ ሀገር ይጥበብህ ነው ያለው። ካልሆነው የሚሆነውን የውስጥ ህመም ቀድሞ ተረድቶታል።
አንዳንዴ ደግሞ እኛ ያላየነውን ከውጪ ሰዎች ያዩልናል።ልክ የአይናችንን ጉድፍ ለማየት መስታወት እንደሚያስፈልገን
አይነት ማለት ነው።

“ይሄ ነገር ልክህ አይደለም” እንዳለው አባት።


ሀገር ቢጠብ ተጠጋግቶ ይኖራል፤ጫማ ቢጠብ መፈናፈኛ የለም።
ሀገር ቢጠብ ይጥበባ የት አባቱ ኧረ ወገን እንተጋገዝ እና ወደዛ እናስፋው ይባላል ፤ጫማ ቢጠብ ህመሙን ለማን
ያጋሩታል?
ልክ ጥሩ ነው።በቃ ልክ ሆኗል በቂ ነው!
የወር ሰው ይበለን!

29
ሃሳብ አስተያየታችሁን በኢሜል አድራሻችን bayradigital@gmail.com
አልያም በማህበራዊ ትስስር ገጾቻችን

Bayradigital ባይራ-ዲጂታል-መጽሔት

በሁሉም የማህበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይወዳጁን።


ቤተሰብ ይሁኑ !

30

You might also like