Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 10

የመንፈስ ፍሬዎች

አዘጋጅ ፦ መምህር በትረ ማርያም አበባው


2015 ዓ/ም
ፍቅር

ፍቅር የአንዱን ድካም አንዱ ሲሸከም ነው። ሰማዕትነት የሌለበት ፍቅር ፍቅር አይባልም። በአፍ ብቻ
እወድሃለሁ እወድሻለሁ ማለት ውሸት ነው። ይህንንስ ባላገሩ "የአፍ ዘመድ ከገበያም አይገድ" ብሎ
ተርቶበታል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሐ. ፲፭፣፲፫ "ነፍሱን ስለወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ
ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም" ብሎ የፍቅርን ትርጓሜ አስተማረን። ፍቅር በአፍ የሚናገሩት ብቻ
አይደለም በሕይወት የሚኖሩትም ነው እንጂ። ለዚያም ነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን በቃል ከተናገረ በኋላ
በተግባር ደግሞ አዳምን ለማዳን በመስቀል የተሰቀለ። መስቀል ፍቅር በተግባር የተገለጠበት አደባባይ ነው።
ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት ብሎ ሊቁ የገለጠው ይህንን ነው። ፍቅር ራሱ
እግዚአብሔር ነው። ፩ኛ ዮሐ.፬፣፰-፳ "ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም እግዚአብሔር ፍቅር
ነውና----ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው" ይላል። ይህ የሚነግረን
በፍቅር ጥላቻ እንደሌለ ነው። ፍቅር ሌላውን እንደ ራስ መውደድ ነው። ማቴ. ፯፣፲፪ "ሰዎች ሊያደርጉላችሁ
የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው" ተብሎ እንደተጻፈ ሰውን መውደድ በእኛ
ሊደረግብን የማንፈልገውን በሌላውም እንዲደረግ አለመፈለግ ሲሆን እግዚአብሔርን መውደድ ደግሞ
ትእዛዙን በመፈጸም ይገለጣል።ዮሐ. ፲፬፣፳፩ "ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ
እርሱ ነው" እንዲል።

ማቴ. ፯፣፳፩-፳፫ "በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ


መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት
አልተናገርንምን በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን ይሉኛል።
የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም እናንተ አመፀኞች ከእኔ ራቁ ብየ እመሰክርባቸዋለሁ" እንዲል የጌታን ስም
ብዙ ጊዜ ብትጠራ፣ በስሙ ተአምራትን ብታደርግ፣ በስሙ ትንቢትን ብትናገር፣ በስሙ አጋንንትን ብታወጣ
ይህ የፍቅር ምልክት ተደርጎ አይያዝም። እግዚአብሔርን የመውደድ ዋናው ምልክቱ ፈቃዱን መፈጸም ነው።
ፈቃዱ ምንድን ነው ከተባለ ዘጸ. ፳፣፩ ጀምሮ ያሉ አስሩን ሕግጋት መፈጸም ነው። ማቴ. ፲፱፣፲፯ "ወደ
ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ" እንዳለ። ዮሐ. ፲፪፣፶ "ትእዛዙም የዘለዓለም ሕይወት
እንደሆነች አውቃለሁ"እንዲል።

ቅዱስ ጳውሎስ ፍቅርን ጠቅለል አድርጎ ሲያቀርበው እንዲህ ብሎታል። ፩ኛ ቆሮ. ፲፫፣፪-፰ " ትንቢትም
ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ቢኖረኝ ፍቅር
ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድኾችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ
ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። ፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፣ ፍቅር አይቀናም፣ ፍቅር
አይመካም፣ አይታበይም፣ የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልን
አይቆጥርም፣ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለዓመፃ ደስ አይለውም። ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣
ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል። ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም" ብሎ ገልጾታል።
ራስን መግዛት

ራስን ከመግዛት የበለጠ ንጉሥነት የለም። ራስን መግዛት በምን ከተባለ በእግዚአብሔር ሕግ ነው። ራስን
መግዛት ስሜታችንን አሸንፎ እውነት በሆነው ቃለ እግዚአብሔር መመራት ነው። ከስሜት በላይ መሆን
ነው። ነፍስን በሥጋ ላይ ማሰልጠን ነው። ራስን በራስ መቆጣጠር ነው። ለሰውነታችን ሕግ መሥራት ነው።
ዓይናችን ክፉ እንዳያይ፣ ጆሯችን ክፉ እንዳይሰማ፣ እጃችን ክፉ እንዳይዳስስ፣ ምላሳችን ክፉ እንዳይናገር፣
አፍንጫችን ክፉ እንዳያሸት መቆጣጠር ነው። አንድ ነገር ክፉ የሚባለው ፍጻሜው የእግዚአብሔርን ሕግ
ወደመሻር የሚያደርስ ከሆነ ነው። ዓለምን ከመግዛት ራስን መግዛት ይበልጣል። ራሱን የገዛ ሰው ፍጻሜው
መንግሥተ ሰማያት ነውና። ንዴትን፣ ሐሜትን፣ ቁጣን፣ ስሜትን መግራት ነው። አርምሞ (ዝምታ) አንደበትን
ለመግዛት ዋናው መሳሪያ ነው። የፈቲው ጾርን (አመንዝራነትን) ለማስወገድ መጾም፣ ውሃ አለማብዛት እና
እንቅልፍን መቀነስ ዋና መድኃኒቶች ናቸው። ራሳችንን በጾም፣ በጸሎት መግራት መልካም ነው። ራስን
መግዛት ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነው። ገላ. ፭፣፳፪።

ኑ በራሳችን ላይ እንንገሥ (ንጉሥ እንሁን)።

እምነት

እምነት አካሌን የሰጠ፣ የሚያስፈልገኝን ነገር ሁሉ የፈጠረ እግዚአብሔር እስከ ዕለተ ሞቴ ይመራኛል ብሎ
ሙሉ ተስፋን በእግዚአብሔር ላይ ማድረግ ነው።እምነት ካለመኖር የፈጠረኝ እግዚአብሔር በመግቦት
ያኖረኛል ብሎ ቁርጥ ሀሳብን ለእግዚአብሔር መስጠት ነው። ብዙዎቻችን እምነት የለንም። እምነት ያለው
ሰው ስለምንም አይጨነቅም። ከምንም በላይ የሆነው እግዚአብሔር አለኝ ብሎ በልቡ ስለሚያምን
የሚያሳስበው የሚፈራው እና የሚያስጨንቀው ጉዳይ አይኖርም። እምነት ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነው።
ገላ. ፭፣፳፪። እምነት ያለው ሰው ተስፋ አይቆርጥም። ምክንያቱም ምንም ዓይነት ፈተና ውስጥ ቢኖር
እግዚአብሔር በጥበቡ ከዚያ እንደሚያወጣው ተስፋ ያደርጋልና። እምነት ያለው ሰው እንደ ዳንኤል አንበሳ
ጉድጓድ ውስጥ ሊጣል ይችላል። ነገር ግን እግዚአብሔር አንበሶች እንዳይበሉት ያደርጋል። እምነት ያለው
ሰው ሰማዕት ሊሆን መከራ ሊደርስበት ይችላል። ነገር ግን ከሁሉም የምትበልጠውን መንግሥተ ሰማያት
ያገኛል። መዓልትና ሌሊትን፣ ክረምትና በጋን እያፈራረቀ የሚመግበን የሚያኖረን እግዚአብሔር ስላለን
አንፈራም አንጨነቅም። ሰው እምነት እያጣ ሲሄድ ይጨነቃል፣ ያዝናል። ነገር ግን ከእኛ የሚጠበቀውን
የድርሻችንን እየተወጣን ረድኤተ እግዚአብሔርን እየጠየቅን በተስፋ እንኑር። እምነታችን አይጉደል። ቀድሞ
ቅዱሳንን የረዳ እግዚአብሔር ነው። አሁንም ያለው ራሱ ነው። እኛንም ይረዳናል። ይረድአነ አምላክነ
ወመድኃኒነ። አምላክነሰ አምላከ አድኅኖ። ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ።
እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችን እንመነው። መልካም የሆነውን ሁሉ ያደርግልናል።

በጎነት
በጎነት ለራስም ለሌላውም መልካም መሆን ነው። ደግነት እና ቅንነት ይመሳሰሉታል። ነገር ሁሉ ለበጎ ነው
ሲባል ለመልካም ነው ለማለት ነው። የመልካምነት መለኪያው የእግዚአብሔር ቃል ነው። አንድ ሰው በጎ
የሚባለው እንደ እግዚአብሔር ቃል ሲኖር ነው። በሌሎች ሰዎች ክፉ አለማድረግና ለሌሎች ሰዎች መልካም
ማድረግ በጎነት ነው። ስለሌሎች ሰዎች ጥሩ አስተያየት አነጋገር ካለው በጎ ነው ይባላል። ብናጠፋ፣ ብንበድል
እንኳ እግዚአብሔር ፈጥኖ አያጠፋንም። ለእኛ በጎ ስለሆነ የንሥሓ እድሜን ይሰጠናል። እንዲህ ከሆነ ታድያ
አንዳንድ ክፉዎችን እግዚአብሔር ፈጥኖ የሚያጠፋቸው ስለምንድን ነው? ቢባል ቢቆዩ ኃጢዓትን
አብዝተው ስለሚሰሩ በሰማይም ፍዳቸው ይቀንስ ዘንድ ቶሎ ያጠፋቸዋል። አንዳንድ መልካሞችንስ ወዲያው
የሚያጠፋቸው ለምንድን ነው? ከተባለ ከቆዩ ኃጢዓት ሊሰሩ ይችላሉና። በአሁኑ ጽድቃቸው ዋጋቸውን
ለመስጠት ነው። አንዳንድ መልካሞች ብዙ ዘመን ይቆያሉ ለምንድን ነው? ከተባለ ለክብር የሚያበቃቸውን
ሥራ አብዝተው ይሰሩ ዘንድ እና ለኃጥዓን ተግሣጽ ይሆኑ ዘንድ ነው። አንዳንድ ክፉዎችን ደግሞ ብዙ
ያቆያቸዋል ለምንድን ነው? ቢሉ የሰሯት መልካም ሥራ ካለች እርሷን በዚህ ምድር በድሎት እንዲኖሩ
አድርጎ በሰማይ ፍዳቸው ይበዛ ዘንድ ነው። አንዳንድ ኃጢዓተኞች በዚህ ምድር ደስተኛ ሆነው ይኖራሉ
አንዳንድ ኃጢዓተኞች ደግሞ በዚህ ምድር በመከራ ይኖራሉ ለምንድን ነው? ከተባለ። በዚህ ምድር ደስተኛ
የሆኑት እንደ ነዌ በሰማይ ፍዳቸው የሚበዛ ሰዎች ናቸው። በዚህ ምድር ኃጢዓተኛ ሆነው በመከራ
የሚኖሩት ደግሞ የኃጢዓታቸውን ፍዳ ጥቂቱን በዚህ ምድር ስለተቀበሉ በሰማይ ይቀልላቸዋል።ድኃው
አልዓዛር በዚህ ምድር ለምን ተሰቃየ ቢሉ ምንም እንኳ ጻድቅ ቢሆን ሰው ከድንግል ማርያም በስተቀር ጽነት
አያጣውምና ለዚያ ፍዳውን በዚህ ምድር ተቀብሎ በሰማይ ዋጋው ይበዛለት ዘንድ ነው። ሰው በዚህ ምድር
እስካለ ድረስ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ስለማያውቀው ሁልጊዜም ለሁሉም ሰው በጎ ሊሆን ይገባል።
አንዳንዱን በደለኛ እግዚአብሔር ወዲያው ይቀስፈዋል ለምን ቢሉ በሕይወተ ሥጋ ላሉት ምሳሌ ይሆን ዘንድ
ነው። አንዳንዱን በደለኛ እግዚአብሔር በዚህ ምድር ያቆየዋል ለምን ቢሉ ንሥሓ ይገባ ዘንድ ነው።
በማንኛውም ጊዜ በማንኛውም ቦታ በማንኛውም ሁኔታ በጎ እንሁን።

የዋህነት

የዋህ ማለት ኀዳጌ በቀል ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ለቅዱሳን፣ ለቅድስት ድንግል ማርያም፣ ለእግዚአብሔር
ይነገራል። እግዚአብሔር የዋህ ነው ብትል ኀዳጌ በቀል ነው መሓሪ ነው ማለት ነው። ቅድስት ድንግል
ማርያምን የዋሂት የሚያሰኛት ርግብየ ሠናይትየ የሚያሰኛት ኀዳጌ በቀልነቷ፣ መሓሪትነቷ ነው። ኀዳጌ በቀል
ማለት ተበድሎ እንዳልተበደሉ መሆን፣ በደልን ይቅር ማለት ማለት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ፍሬዎች
ብሎ ከጠቀሳቸው ውስጥ ገላ. ፭፣፳፪ የተጠቀሰው የውሃት ይህኛው የውሃት ነው። የዋህነት
(Mildness) ጠቢብነትንም (Wisdom) የያዘ ነው። ኩኑ የውሃነ ከመ ርግብ ወጠቢባነ ከመ አርዌ ምድር
እንዲል። እባብ ጠቢብነቱ "ዕፀ ዘዌ የምትባል ዕፅዋት አለች። ፍሬዋን ይወዳታል። ነገር ግን ጥላዋ ካረፈበት
መንቀሳቀስ ስለማይችል ጠዋት በምሥራቅ ሆኖ ማታ በምዕራብ በኩል ሆኖ ፍሬዋን ይበላል" ተብሏል።

በዚህ በመጀመሪያው ትርጓሜ አንድ ሰው የዋህ ነው ሲባል ገራገር ነው። መልካም አሳቢ (Positive
thinker) ነው ማለታችን ነው። የዋህ ነው ማለት ክፉ ላደረጉባት እንኳ ቂም፣ ጥላቻ፣ በቀል የሌለበት ማለት
ነው። የዋህ ማለት ሰውን እንደራሱ የሚያይ ደግ ሰው ማለት ነው። ንኩን የዋሃነ። የዋሃን እንሁን። ባለፈው
የደረሰብንን በደል እንተወው። የወደፊቱን ሕይወት በጋራ ሆኖ በፍቅር ሆነን ያማረ የሰመረ እናድርገው።

ሁለተኛው ትርጓሜ የላይኛው ተቃራኒ ነው። በግእዝ አንድ ቃል ለሁለት ተቃራኒ ነገሮች ሊያገለግል ይችላል።
ለምሳሌ ባረከ "ባረከም ይሆናል ረገመም ይሆናል" ወባረከ ኢዮብ ዓመተ ልደቱ ሲል ረገመ ማለት ነውና።
የዋህ ማለት ሞኝ፣ አላዋቂ ማለት ነው። የዋህ ብእሲ ኵሎ ዘነገርዎ የአምን እንዲል። ሞኝ ሰው፣ አላዋቂ ሰው
የነገሩትን ሁሉ ያምናል እንደማለት ነው። ነገርን እንደወረደ የሚያምን፣ የማይመረምር፣ በራሱ ሳይሆን
በመንጋ የሚያስብ የዋህ ይባላል። ይህ የየዋህ ሁለተኛ ትርጉም ነው። የዚህ ተቃራኒ ብልጥ ነው። ብልጥ
የሚባለው ራስ ወዳድ ለራሱ ብቻ የሚያስብ፣ ራሱን ለመጥቀም የዋህ የሆኑ ሰዎችን የሚያታልል ተንኮለኛ
ማለት ነው።

በመጀመሪያ ትርጉም ያለውን የዋህ እንሁን። ኢየሱስ ክርስቶስ መፍቀሬ የውሃት እምተቀይሞ እንዳለ ደራሲ
የዋህ ስንሆን ክርስቶስን እንመስለዋለን።

ቸርነት

ቸርነትን ግእዙ "ምጽዋት" ይለዋል። ከተቀባዩ ምንም ሳይፈልጉ የሚሰጡት ስጦታ ነው። አሁን ያሉ
የኢትዮጵያ የአብነት መምህራን በችግር ተምረው ያገኙትን እውቀት በነጻ ያስተምራሉ። እውቀት
ይመጸወታል። ገንዘብ ይመጸወታል። ጉልበትም ይመጸወታል። ሁሉም የቸርነት ሥራዎች ናቸው። ቸሩ
እግዚአብሔር እንዲምረን እኛም ቸር እንሁን። ሰው በቸርነት ፈጣሪውን ይመስላል። እግዚአብሔር ቸር
ስለሆነ እኛነታችንን፣ አካላችንን፣ ተፈጥሮን ሰጥቶናል። ከዚህ በኋላ በታናናሾች አድሮ ምጽዋትን እየተቀበለ
ሰማያዊ ዋጋን ይሰጠናል። በኋላ በምጽአት ጻድቃንንና ኃጥዓንን ሲለይ በዋናነት የሚጠይቀው ቸርነትን
(ምጽዋትን) ነው። ብራብ አብልታችሁኛል፣ ብጠማ አጠጥታችሁኛል፣ ብታረዝ አልብሳችሁኛል፣ እንግዳ
ብሆን ተቀብላችሁኛል፣ ብታመም ጠይቃችሁኛል፣ ብታሰር አስፈትታችሁኛል የሚሉት ቃላት
ምሥጢራቸው ቸርነት ነው። ምጽዋት (ቸርነት) ሰው ፈጣሪን የሚመስልበት መልካም ሥራ ነው። ፈጣሪ
ሁሉን በነጻ እንደ ሰጠን የሚመጸውት ሰውም ፈጣሪ ከሰጠው ጸጋ በነጻ የሚሰጥ ነው። ቸርነት (ምጽዋት)
በከንቱ ዘነሳእክሙ በከንቱ ሀቡ ያለውን የሐዋርያውን ቃል በተግባር ማዋል ነው። ቸርነት ሰው ሌላውን ሰው
እንደራሱ ከመውደዱ የተነሳ የሚደረግ የመንፈስ ፍሬ ነው። ለዚያ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች
የመንፈስ ፍሬዎችን ሲነግራቸው አንዱ ቸርነት ነው ያላቸው። ገላ. ፭፣፳፪። የቸርነት ሥራዎች ለከንቱ ውዳሴ
ከዋሉ ዋጋ አያሰጡም። ጌታ ሲያስተምር ቀኝህ የሰጠችውን ግራህ አትወቅ ምጽዋትህ ሰው ይይልኝ ብለህ
ሳይሆን በስውር ይሁን ያለን። አሁን ሰው መጽውቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ካልተነገረለት ይከፋል። መምህር
አስተምሮ ማስተማሩ በሁሉ ካልታወቀለት ይከፋዋል። ቸርነትና ውዳሴ ከንቱ አይስማሙም። በአደባባይ
ከመወደስ በአደባባይ መሰደብ ይሻላል። ቸሩ መድኃኔዓለም ይቅር እንዲለን ቸርነትን ገንዘብ እናድርግ።

ሰላም
ቅድስት ድንግል ማርያምን ሰላማዊት ይላታል። ልጇም ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ይባላል። አንድ ሰው
ውስጣዊ ሰላም ይሰማኛል ሲል ብትሰማው የሐሳብ ስምምነት የአእምሮ ዕረፍት እንዳገኘ ትረዳለህ። ውስጣዊ
ሰላም የሕዋሳቶቻችን ስምምነት ውጤት ነው። ሰላም ተሳለመ_ተፈቃቀረ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ
ዘመድ ዘር ነው። ሰላም ፍቅር ማለት ነው። ምሥጢራዊ ትርጓሜው ግን ከተሰናእዎ ጋር ይቀራረባል። የነገር
እና የሐሳብ ስምምነት ማለት ነው። ሰላም ሆነ ማለት ስምምነት ላይ ተደረሰ ማለት ነው። አምላከ ሰላም
ክርስቶስ ሰላምን እሰጣችኋለሁ ብሏል። ለሰውነታችን የተስማማች ገነትን ሰጥቶም አረጋገጦልናል። ሲኦል
ግን ለእኛ ሰውነት የማይስማማ ቦታ ነው። በሲኦል ሰላም የለም። ሁከት ብጥብጥ ዋይታ ለቅሶ ይበዛል።
ውስጣዊ ሰላም የሚገኘው በድለን ከነበረ ንሥሓ ገብተን ኃጢዓታችንን አስወግደን መልካም ሥራ ስንሰራ
ነው። ነገር ግን ሌላውን እያስቀየምን፣ እያናደድን፣ እየተሳደብን ውስጣዊ ሰላም ይሰማናል ብንል ውሸታም
እንባላለን። ነቢዩ ኤርምያስ እንደተናገረው "ወይቤሉ ሰላም ሰላም ወአልቦ ሰላም" እንዳሉት ሐሰተኛ ነቢያት
እንሆናለን። የልቡና ሰላም የሚገኘው እውነትን ፍቅርን ትሕትናን ስንይዝ ነው። ፍጹም ሰላማዊት ወደ
ሆነችው መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ከተጣላናቸው ጋር በይቅርታ ታርቀን፣ የበደልነውን ክሰን በፍቅር
እንኑር።

ክርስቶስ ሰላምን የሰጠን በደላችንን ይቅር ብሎ ነው። እኛም በትክክለኛ ፍትሕ ያጠፋው ክሶ፣ የተበደለው
ተክሶ በሰላም እንኑር። ውስጣዊ ሰላም ለማግኘት ከፈለጉ የተጣሉትን ይታረቁ፣ ቂም በቀል ጥላቻ ዘረኝነት
ካለብዎ ያስወግዱ። ከእርስዎ የሚጠበቀውን መልካምነት ያድርጉ። የድርሻዎትን ይወጡ። ከመንፈስ ፍሬዎች
አንዱ ሰላም ነው። ገላ. ፭፣፳፪።

ደስታ

አራት ዓይነት ደስታዎች አሉ። እነዚህም:-


፩) ፍሥሓ መላእክት
፪) ፍሥሓ ኖሎት
፫) ፍሥሓ ቍንጽል (የቀበሮ ደስታ)
፬) ፍሥሓ መስቴማ
ናቸው። ፍሥሓ መስቴማ ማለት የሰይጣን ደስታ ማለት ነው። ሰይጣን ሌሎች ሰዎች ሲሳሳቱ፣ ሲወድቁ፣
ሲሞቱ፣ ሲጎዱ በጣም ይደሰታል። በሌሎች ሰዎች ኀዘን እና ጉዳት የሚደሰቱት ደስታ የሰይጣን ደስታ
ይባላል። ሁለተኛው የደስታ ዓይነት የቀበሮ ደስታ ነው። ቀበሮ የጣዝማ ማር ስታገኝ ከደስታዋ ብዛት የተነሳ
ማሩ እስኪጠፋት ትዘላለች። የደስታዋ ምንጭ የሚበላ አገኘሁ ብላ ነው። የሰው ልጅ በሥጋዊ ነገሮች
የሚደሰተው ደስታ የቀበሮ ደስታ ይባላል። ሦስተኛው ደስታ የእረኞች ደስታ ነው። እኒህም ጌታ
በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ የተደሰቱት ደስታ ነው። ይህ ደስታ ነፍሳዊ ደስታ ነው። በጌታ መወለድ በሲኦል
ተግዞ የነበረ አዳም ወደ ገነት የሚመለስበትን የምሥራች ከመልአኩ የሰሙበት ነውና። እስመ ናሁ ተወልደ
ለክሙ ዮም መድኅን ዘይከውን ፍሥሓ ለክሙ እንዲል። የመላእክት ደስታ የፍጹማን ደስታ ነው። መላእክት
አንድ ኃጥእ ንሥሓ በገባ ጊዜ በሰማያት ታላቅ ደስታ ይሆናል ተብሎ የተነገረላቸው ናቸው። የመላእክት
ደስታ ከግላዊ ጥቅም የተለየ ደስታ ነው። ሌላው ሲጠቀም፣ ሌላው ሲያገኝ፣ ሌላው ሲሾም፣ ሌላው ሲደሰት
የሚደሰቱት ደስታ ነው። እንግዲህ ገላ. ፭፣፳፪ ደስታ የመንፈስ ፍሬ ነው የተባለው በሁለቱ ዓይነት ደስታዎች
ነው። እነዚህም ፍሥሓ ኖሎት እና ፍሥሓ መላእክት ናቸው። ትክክለኛው ደስታ የሚገኘው በቁስ
አይደለም። በእግዚአብሔር ነው። መዝ. ፺፬፣፩ "ኑ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን" ተብሏል። ቅዱስ ጳውሎስም
በመልእክቱ ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ ብሏል። በሌላ ቦታ ቅዱስ ዳዊት "ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ
ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ" ብሏል። ደስታ የሚገኘው ከእግዚአብሔር ቤት ነውና። ደስታ የራቃችሁ ሰዎች ወደ
እግዚአብሔር ቅረቡ። ያን ጊዜ ደስ ይላችኋል። ሰማእታት እየተገደሉ ግን ደስተኞች ነበሩ። ለምንድን ነው
ስንል የደስታቸው ምንጭ እግዚአብሔር ስለሆነ ነው። እግዚአብሔር ደግሞ ሕይወተ ሕይወት ብርሃነ ብርሃን
መሠረተ መሠረት ስለሆነ ነው። ደስታችንን በእግዚአብሔር እናድርግ።

የመንፈስ ፍሬዎችን በአጭር በአጭር ተማምረን ጨርሰናል። አነሳስቶ ላስጀመረን፣ አስጀምሮም ላስፈጸመን
ልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይገባል።

ትዕግሥት

አሁን አሁን ከትዕግሥተኞች ይልቅ ስለ ትዕግሥት የሚያወራው ይበልጣል። ትዕግሥት የክብር እናት ናት።
ከክርስቶስ መስቀል በረከትን ማግኛ ነው። ክርስቶስ እኛን ለማዳን በመስቀል ተሰቀለ። እስኪ ራስህን አድን
እያሉ አይሁድ ሲሳለቁበት፣ ምራቃቸውን ሲተፉበት፣ ተነበይ ለነ ክርስቶስ መኑ ጸፍዐከ እያሉ በጥፊ ሲመቱት
እነርሱን ማጥፋት እየቻለ ለእኛ ትዕግሥትን ያስተምረን ዘንድ መከራውን ሁሉ በዝምታ ተቀበለ። ሰማዕታት
ስለ እውነት መራራ ሞትን ታገሡ። ወተዐገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት እንዲል። የታገሠ የድል
አክሊል ያገኛል። ይህችውም መንግሥተ ሰማያት ናት። አባቶቻችን ዕጉሣን ነበሩ። ለመናገር የዘገዩ ለመስማት
የፈጠኑ ነበሩ። ታጋሽ ሰው ሕይወቱ የተረጋጋ ነው። አርምሞ (ዝምታ) የትዕግሥት አጋዥ ነው። ትዕግሥት
የጠብ ማብረጃ ነው።

ትዕግሥትን እንለማመዳት።
ሲታገሡ ያማል። ሕመሙ ግን አጭር ነው። ከሕመሙ በኋላ ያለው ደስታ ልዩ ነው። እናት ልጇን ስትወልድ
የምጥ ጊዜዋ አስጨናቂ ነው። ነገር ግን ልጇን ከወለደች በኋላ ወንድ ልጅ ወለድሽ ብለው ሲያስታቅፏት
ያለፈውን መከራ ሁሉ በልጇ ትረሳዋለች። ስንሰደብ ዝም ስንል ልናዝን እንችላለን። ነገር ግን እየቆየ ሲሄድ
ምን ስድብማ አየር የሚወስደው አይደለምን ብለን ደስ ይለናል። ቅዱሳንም ይህችን ዓለም ያሸነፏት
በትዕግሥት ነው። ሊቁ መዋዕያነ ዓለም አንትሙ በብዙኅ ትዕግሥት ያለው ይህንን ነው።

ታጋሽ ሰው የሰማእታቱ የእነ ቅዱስ መርምህናም፣ የእነ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የእነ ቅዱስ ፊቅጦር፣ የእነ ቅዱስ
መርቆሬዎስ፣ የእነ ቅዱስ ፋሲለደስ፣ የእነ ቅዱስ ገላውዴዎስ፣ የእነ ቅዱስ ቂርቆስ እንዲሁም የቅዱሳን
ሰማእታት ሁሉ ወዳጅ ነው። ታጋሽ ሰው የመነኮሳቱ የእነ ቅዱስ መቃርስ፣ የእነ አባ እንጦንስ እንዲ የቅዱሳን
መነኮሳት ሁሉ ወዳጅ ነው። ታጋሽ ሰው የቅዱሳን ሁሉ ወዳጅ ነው። እግዚአብሔር ይወደዋል። በሉ ኑ
ታጋሽነትን እንለማመድ። ታጋሽ እንሁን።
ተጨማሪ መንፈሳዊ ምግባራት

ትሕትና
ትሕትና "እኔ ደካማ ነኝ፣ እኔ ኃጢዓተኛ ነኝ___ወዘተ ማለት ብቻ አይደለም። ሲሰድቡህ አለመመለስ፣
"ኃጢዓተኛ ነህ፣ ደካማ ነህ" ሲሉህ አዎ ነኝ ማለት ነው። የትሕትና መለኪያው ይህ ነው። አንድን ሰው
ሰድበኽው፣ መትተኽው፣ ተናግረኽው ነገር ግን ለአንተ ያለው ፍቅር ካልቀነሰ በትክክል ትሑት ሰው ነው
ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ አሉልህ እኔ ኃጢዓተኛ ስለሆንኩ ወደፊትም ልፋታ ስለምችል በቁርባን
አላገባም የሚሉ። እኒህ ሰዎች ያልተረዱት ነገር ይህ ትሕትና ሳይሆን ውንብድና መሆኑን ነው። ጋብቻ
የሚጸናው በቁርባን ሲሆን ነው። ፍትሐ ነገሥታችን ያለ ቁርባን የሚደረግ ጋብቻ ቁጥሩ ከዝሙት ነው
ብሎታል። ስለዚህ ኃጢዓተኛ ነኝ ያለ ሰው እንኳ ቢሆን ንሥሓ ገብቶ በቁርባን ያገባል እንጂ በኃጢዓት ላይ
ኃጢዓትን አይጨምርም።

ትሕትና ትልቅነትን ይዞ ከትልቅነት ሳይወርዱ ታናሽ መሆን ነው። ይህንንም ራሱ ክርስቶስ አስተምሮናል።
አምላክ ሲሆን ሰውን ለማዳን አምላክነቱን ሳይለቅ ሰው ሆነ። ለሰው ልጅ የትሑት ሰብእናው ምክንያት
ደካማነቱ፣ ሁሉን አዋቂ አለመሆኑ፣ በእግዚአብሔር ቸርነት የሚኖር መሆኑ እና የመሳሰሉት ናቸው። ትሕትና
ክብርን ለእግዚአብሔር መስጠት ነው። ትሑት ሰው ከራሱ ይልቅ ሌሎችን ያስቀድማል። ልክ ቅዱስ ጴጥሮስ
በደብረ ታቦር ጌታ ሆይ አንድ ለአንተ አንድ ለሙሴ አንድ ለኤልያስ ቤት እንስራ ብሏል። ቅድስት ድንግል
ማርያምም የትሕትና እናት ስለሆነች እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ያለውን የኢሳይያስ
ትንቢት ስታነብ "እኔ ብሆን" አላለችም። ከዚህችስ ከዘመኗ ደርሼ ባገለገልኳት ነው ያለች። እስመ
ምሥጢራት ይትከሠታ ለትሑታን እንዲሉ እውቀት ጸጋ ለትሑታን ይሰጣል።

ትሑታን ሲሰደቡ የማይሳደቡ ስድብ የማያውቁ ሆነው አይደለም። ነገር ግን በትሕትናቸው ይገባኛል ብለው
ያስቡና አፋቸውን እንዳይሳደብ ተቆጣጥረውት ነው። በሌላ ምክንያት ደግሞ ፍቅር ስለሚበልጥባቸው ነው።
በትእግስታቸው ጸጋ እንደሚያገኙም ስለሚያውቁ ነው። ፍትሐ ነገሥት "ሰው ሁሉ ከአንተ የከበረ እንደሆነ
አስብ" ይላል። ቅዱሳን በዚህ መርሕ ለሁሉ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ኖረዋል።

አንድነት
"ሐንካስ በእግረ እውር ሖረ።
እውርኒ በዓይነ ሐንካስ ነጸረ።
ወበክልዔሆሙ ወይንየ ተመዝበረ።"

የእባብና የሰይጣን ኅብረት የክፉ አንድነት ምሳሌ ነው። ምክንያቱም አንድ የሆኑት ሁለቱም ሌላውን
ለመጉዳት ነውና። ይህ ቅኔ የክፉ ኅብረትን ምሳሌ ይነግረናል። "አንካሳ በዕውር እግር ሄደ፣ ዕውርም በአንካሳ
ዓይን አየ፣ በሁለቱ አንድነት ምክንያት ወይኔ ተዘረፈ" ማለት ነው። የሁለቱ አንድነት ወይን ለመዝረፍ ነበር።
ይህን የመሰለ አንድነት በጎንደር ዘመነ መንግሥት ሆኖ ነበር። ሁለት ንጉሡ ያሳደጋቸው ሰዎች ንጉሡን
በመፈንቅለ መንግሥት ሊጥሉ ሲዘጋጁ በሌሎች በቁጥጥር ስር ይውላሉ። ይህን ጊዜ ንጉሡ ባለቅኔ ስለነበሩ
እንዲህ አሉ ይባላል:-

ዕፅ ወሳእር እለ በዝናም ልሕቁ።


ለዝናም ዘአልኀቆሙ ከመ ይክልእዎ ተላጸቁ።

በዝናም ያደጉ ሣር እና እንጨት ያሳደጋቸው ዝናምን ለመከልከል አንድ ሆኑ ማለት ነው። የሳር ቤት
የሚሰራው ከእንጨትና ከሣር ነው። ከተሰራ በኋላ ዝናም አያስገባም። ከዚህ ላይ ሣርና እንጨት ተባብረው
ዝናም የማያስገቡት መጀመሪያ እነርሱም ሕይወት አልባ ሆነው ነው። እነርሱ ሕይወት አልባ ሆነው ለሌሎች
ሕይወት የሚሆነውን ዝናም ይከለክላሉ እንደማለት ነው። ከክፉ አንድነት እንራቅ።

መልካም አንድነትን ቅዱስ ጳውሎስ አብራርቶታል። ሁላችንም የአንድ የክርስቶስ አካል ነን ብሏል። ቅዱስ
ዳዊት ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም ሶበ ይሄልው አኃው ኅቡረ ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ መልካም ነው
ብሏል። አንድነት ኃይል ነው። ለአንድነት መሰረቱ የተመሳሳይ ግብ መኖር ነው።የሰው ልጅ ኅብረታዊ ነው።
ሰው ግላዊ ሲሆን ከእውነት ያፈነግጣል። ምክንያቱም ለማንነቱ መሠረት የእናት አባቱ አሳዳጊነት፣
የማኅበረሰቡ ባህልና ወግ ይጠቀሳልና። ለሰው ልጅ የማንነቱ መሠረት ቤተሰቡ፣ ማኅበረሰቡ ነው። ስለዚህ
ሰው ከግላዊነት ወጥቶ ኅብረታዊ ሲሆን ከእውነት ጋር ታረቀ ይባላል። በኅብረት/በተቋም ውስጥ
የእያንዳንዱ አባል የተለያዩ ውስንነቶች ይኖሩታል። እነዚያን ውስንነቶች ግን ኅብረትን ለማፍረስ መጠቀም
የለብንም። ኅብረታዊነት/ተቋማዊነት ግቡ ሰላማዊ ሕይወትን መምራት ነው።

ለአንድነት መሰናክል የሆነውን ግላዊ ስሜታችንን እንዲሁም እኔ ያልኩት ካልሆነ ባይነትን ትተን
እግዚአብሔር ያዘዘንን ሥራ እንስራ። ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ሳይሆን ከፍ ያሉ ጉዳዮች ላይ እናተኩር። ግለሰብ
ተኮር ሳይሆን ጉዳይ ተኮር እንሁን።

ይቅርታ

ዘመን ሲከፋ መልካሙ ነገር እንደ ውርደት፣ ክፉው ነገር እንደ ጥሩ ሥራ ይታያል። በእርግጥ ዘመንን
የሚያከፋውም የሚያሳምረውም ሰው ነው። እውነታው "ይቅርታ" የታላላቆች እና የአሸናፊዎች ምልክት
ነው። አሁን ላይ ግን "ይቅርታ"ን መጠየቅ የተሸናፊዎች ምልክት ተደርጎ ይታያል። ብዙዎችም ጥፋታቸውን
አምነው ይቅርታ እንዳይጠይቁ ታናሽ እንባላለን በማለት ከነጥፋታቸው በኩራት ይኖራሉ። በዚህም
ምክንያት ትልልቅ ትንሾች ተፈጠሩ። ታዋቂ ትንሾች በዙ። በእርግጥ የይቅርታን ዋጋ የሚያውቁት የክርስቶስ
ፍቅር የገባቸው እና የክርስቶስን ሁሉን አዋቂነት የተረዱ ናቸው። በተጨማሪም የይቅርታን ዋጋ የሚያውቁት
የራሳቸውን ውስንነት የተረዱ ትሑታን ናቸው።

ብዙዎች ይቅርታ ሲጠየቁ አሸናፊ የሆኑ ይመስላቸዋል። ይቅርታ የጠየቀው ደግሞ ተሸናፊ ይመስላቸዋል።
ይህ ትንሽነት የወለደው ክፉ ሐሳብ ነው። ለክፋት ለውሸት ማስተባበያ ከመስጠት ይልቅ እውነታውን
ተቀብሎ ጥፋትን አምኖ ይቅርታ መጠየቅ ትልቅነት ነው። ከቅድስና መንገዶች አንዱ "ተአምኖ ኃጣውእ"
ነው። ትርጉሙ ኃጢኣትን አምኖ ይቅርታ መጠየቅ ማለት ነው። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ይህንን አድርጓል።
መዝ. ፮ "ተሣሀለኒ እግዚኦ እስመ ድውይ አነ_ድውይ ነኝና አቤቱ ማረኝ" ብሏል። በደልን አምኖ ይቅርታ
መጠየቅ ትልቅነት ነው።

በእርግጥ ሰሚ በሌለበት መናገር ትርፉ ድካም ነው። የዐቢየ እግዚእ ጉባኤ ቤት መምህር የነበሩት የኔታ ፀሐይ
ብዙ ችግር እያዩ ዝም ይሉ ነበር ይባላል። ለምንድን ነው ዝም የሚሉ ሲሏቸው "ሰሚ በሌለበት መናገር ምን
ይጠቅማል" ይሉ ነበር ይባላል። አንድ ሊቅም "እመ ተናገርኩ ጽድቀ ሰብአ ዛቲ ዓለም ይጸልኡኒ።ወከመ
ኢይንብብ ሐሰተ ኩነኔ ዚኣከ ያፈርሀኒ።ወእምኩሉሰ አርምሞ ይኄይስ ወይሤኒ"።ብለዋል ይባላል። ትርጉሙ
እውነትን ብናገር የዚህ ዓለም ሰዎች ይጠሉኛል። ሐሰትንም እንዳልናገር ጌታ ሆይ የአንተ ፍርድ ያስፈራኛል።
ከሁሉም ግን ዝምታ ይሻለኛል" ማለት ነው። እውነት፣ ትሕትና፣ ፍቅር አይለየን።

You might also like