በእንተ ውትድርና

You might also like

Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 6

በእንተ

ውትድርና

በመ/ር በትረማርያም አበባው

መጋቢት 2014
ፖለቲካ እርኩስ ነው እያሉ እኛን እንድንርቀው እያደረጉ እነርሱ ገብተው የሚያረክሱ ሰዎች አሉ። ፖለቲካ ሕዝብን የማስተዳደር
ጥበብ ነው። ይህ ጥበብ ደግሞ ከፈጣሪ የተሰጠ ነው።ከፈጣሪ የተሰጠውን ሀብተ መንግሥት እንደ ናቡከደነጾር ከተጠቀምነው
እርኩስ ይሆናል። እንደ ቆስጠንጢኖስ ከተጠቀምነው ይቀደሳል። ስለዚህ አሁን ላይ ያለው ፖለቲካ የተበላሸ ከሆነ ገብተህ
የማስተካከል ድርሻው የአንተ ነው ። የዲዮቅልጥያኖስ አስተዳደር ክርስቲያኖችን በአዋጅ የሚገድል ነበር። ይህንን የተበላሸ
ፖለቲካ የቀየረው እና የክርስቲያኖችን መብት ያስጠበቀው ቆስጠንጢኖስ ነው። ስለዚህ ፖለቲካ በራሱ ርኩስ አይደለም ።
ሥልጣኑን ያገኙ ሰዎች ይህንን ተገን አድርገው ርኩሰት ሊሰሩ ይችላሉ። ይህ ከሆነ ገብቶ ማስተካከል እንጂ ርኩስ ነው ብሎ
መራቅ የፈጣሪን ጸጋ መናቅ ነው። ሀብተ ክህነት ሀብተ መንግሥት ከፈጣሪ የተሰጡ ጸጋዎች ናቸው። እኒህን ገንዘብ ያደረገ ሰው
ክፉ ሊሆን ይችላል። እኒህ ሀብቶች ግን ውድ ስጦታዎች ስለሆነ ከክፉ ሰው ፈልቅቀን ማውጣት ከእኛ ይጠበቃል።በመሠረቱ
አዳም ከተፈጠረ በኋላ ከተሰጡት ሰባት ሀብታት አንዱ ሀብተ መንግሥት ነው። ይኼውም ፍጥረቱን ሕዝቡን በትክክል
እንደሚገባው ማስተዳደር ነው። ይህ ሀብተ መንግሥት በዚያን ዘመን ወደቀጣዩ ንጉሥ የሚተላለፈው በቡራኬ ነበር። አዳም
ሴትን ባርኮ በእርሱ ምትክ እንዲገዛ አድርጎታል። ሴት ሄኖስን እያለ ለብዙ ዘመን በዚህ መልኩ ገዥነት ይተላለፍ ነበር። ጊዮርጊስ
ወልደ ሐሚድ የተባለውን መጽሐፍ መመልከት ይቻላል።

የሚገርመው አዳም ሴትን ሴት ሄኖስን ባርከው ንግሥናን ሲያስተላልፉላቸው ዋና ንግግራቸው ሕዝቡን በመልካም አስተዳደር
አስተዳድር፣ የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲጠብቁ አስተምር የሚል ነበር። የንጉሥነት ቀዳሚ ሥራ ሕዝቡን በእምነት መጠበቅ
ነበር ። ከዚያ ቀጥሎ ለሁሉም እንደሚገባው ያለ አድልዎ በፍቅር ማስተዳደር ነበር። ይህ ዓይነት ንግሥና እስከ ኖኅ ጊዜ ደርሷል።
ከኖኅ በኋላ ይህች ንግሥና ለሦስት ተከፍላለች። ለሴም፣ ለያፌት እና ለካም ይህ እየበዛ እየበዛ ሄዶ አሁን ከ200 በላይ
መንግሥታት አሉ። ወደፊትም ሊጨምር ይችላል። ወይም ሊቀንስ ይችላል። ወይም ባለበት ሊቀጥል ይችላል፡፡ ፍትሐ ነገሥት
አንቀጽ 44 ከቁጥር 1530 ጀምሮ ስለ ነገሥታት ይናገራል። ቁጥር 1532 ላይ ወይኲን አሚኖቱ ፍጹመ በእግዚአብሔር ይላል።
በእግዚአብሔር ይመን። የኢያሪኮ ግንብ በእምነት ፈርሷልና። በእምነት ጌዴዎን፣ ባርቅ፣ ዮፍታሔ እና ሶምሶን ጠላትን
አሸንፈዋልና። ወኮኑ መዋዕያነ በውስተ ጸብዕ እንዲል። ንጉሡ መናፍቅ ከሆነ ከዘመነ ወንጌል ወዲህ ንጉሥ አይባልም። ዐመፀኛ
ነው እንጂ። ነገሥታትን የሚሾም እግዚአብሔር ነው። ንጉሥ መልካም ከሠራ ልንገዛለት ካልሠራ ልንቃወመው ይገባል። ቁጥር
1544 ወኢትንሣእ ንዋየ መኑሂ በኃይል በጉልበት የማንንም ገንዘብ አትውሰድ። አክአብና ኤልዛቤል የናቡቴን የወይኑን ቦታ በመ
ውሰዳቸው ተቀስፈዋልና ይላል። አስተውል ንጉሥ አመጸኛ ሲሆን መቃወም እንደሚገባን አብነታችን ነቢዩ ኤልያስ ነው።
የናቡቴን ገንዘብ መልስ ብሎ ተቃውሟልና።

ከላይ እንደተቀመጠው የንጉሥ ዳዊት፣ የባርቅ፣ የዮፍታሔ ንግሥና በሐዲስ ኪዳንም ተደንቋል። ቅዱስ ጳውሎስም በዕብ.11፣
32 ገልጾታል። እኒህ የተጠቀሱ ሰዎች ደግሞ በዘመናቸው የነበረውን ጠላት ያሸነፉት ወታደር ይዘው ነው። ያውም ጌዴዎን
ጥራት ያላቸው ወታደሮችን ነው የያዘው። ከብዙ ሺ ወታደሮች እግዚአብሔር በነገረው መሥፈርት ብቁ ሆነው የተገኙትን ነው
የመረጣቸው። ስለዚህ ወታደር በእግዚአብሔር መሥፈርት ማለትም ሕጉን ትእዛዙን የሚሠራ ልበ ሙሉ መሆን አለበት።
በሥርዓተ መንግሥት ውስጥ ወታደር አለ። ዳኛ አለ። ሰብዓ ዓይን ወይም ሰላይ አለ ብቻ ብዙ ክፍል አለ።

ጀግና ወታደር የሚለካው አንደኛው በሥነ ምግባሩ ነው። ከጠላት ጋር ጦር በገጠመ ጊዜ ከጠላት ወገን ሴቶች ጋር ዝሙት
አይፈጽምም። ጦርነት የገጠመው ዝሙት ለመፈጸም ሳይሆን ጠላትን ሊያጠፋ ነውና።ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 44 ቁጥር 1549
ወሶበ ተሐውር ኀበ ጸብዕ ምስለ ሠራዊትከ ለፀቢዐ ጸርከ ተዐቀብ እምኲሉ ግብር እኩይ። ጠላትህን ለመውጋት ክተት ሠራዊት
ምታ ነጋሪት ብለህ በዘመትክ ጊዜ ከዝሙት ተጠበቅ። ክርስቲያናዊ ወታደር በዚህ ይታወቃል። በነገራችን ላይ ማንኛውም
ክርስቲያን ከካህናት ውጭ ወታደር መሆን ይችላል። ካህናት ግን መሣሪያ ይዘው ሰይፍ ይዘው እንዲገጥሙ አይፈቀድም። ካህናት
የማንንም ደም እንዲያፈሱ አልተፈቀደም። ካህናት ክህነት ሲሾሙ የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚፈትቱ ናቸውና። ስለዚህም
ካህናት ሰው ከገደሉ ከክህነታቸው ይሻራሉ። ከካህናት ውጭ ያለ ምእመን ግን ወታደር ሆኖ በጦርነት ጊዜ ጠላትን በመግደሉ
ኃጢኣተኛ አይባልም። ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጠላቱን መክስምያኖስን በመግደሉ ኃጢኣት አልሆነበትምና። ካህናት በጾም በጸሎት
ሊያግዙ ይችላሉ። ከኃጢኣቱ የማይመለስ ሰው ካለ ወደፈጣሪ ጸልየው በጸሎታቸው ጠላትን ሊያጠፉ ወይም ሊገድሉ ይችላሉ።
መሣሪያ ይዘው ሰይፍ ይዘው ግን ማንንም እንዳይገድሉ ሥርዓት ተሠርቷል። በጸሎት ግን ከኃጢኣቱ በማይመለሰው መዝ.34ን
ግፍዖሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍኡኒ ጽብኦሙ እግዚኦ ለእለ ይጸብኡኒ ብለው ይጸልዩበታል።ከኃጢኣቱ ለሚመለሰው ደግሞ አባት
ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብለው ያስምራሉ። ቅዱስ ጴጥሮስ ሐናንያን እና ሰጲራን በጸሎቱ በመግደሉ
በደለኛ አልተባለም። የሊቀ ካህናቱን ጆሮ በሰይፍ በመቁረጡ ግን ተወቅሶበት ነበር። ስለዚህ ካህናት በሰይፍ በጦር ከጠላት ጋር
ገጥመው ሊገድሉ አይገባም። ምእመናን ግን ወታደር ሆነው ጠላትን በመግደላቸው በደል አይሆንባቸውም። ንጉሥ የተሾመ
ያጠፋን ሊቀጣ መልካም የሠራን ሊሾም ነውና።

ለፍጹማን የሚጠቀሰውን ጥቅስ ለወጣንያን እየጠቀሱ የሚያወናብዱ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ በወንጌል ጌታችን ፍጹም ልትሆን
ከፈለግህ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ተከተለኝ ብሏል። ይህ ትእዛዝ ለፍጹማን የተነገረ ነው እንጂ። ይህንን ላልቻለ ሰው ንብረት አፍርቶ
ሚስት አግብቶ ቢኖር ኃጢኣት አይሆንበትም። ጠላትህን ውደድ የሚለው ጥቅስ ለምሳሌ በሁለት መልኩ ሊተረጎም ይችላል።
አንደኛው ለፍጹማን ንብረታቸውን ሁሉ ቢዘርፋቸው ሚስታቸውን ሁሉ ቢቀማቸው እንደ የዋሕ ጳውሎስ አንቺም የተባረክሽ
ሁኝለት አንተም የተባረክ ሁንላት ብሎ ትቶ መሄድ ነው ። ይህንን ማድረግ ያልቻለ ደግሞ ያለፍትሕ የእርሱ ያልሆነውን ገንዘብ
ሌላ ሰው መጥቶ ሲወስድበት ጦር አንስቶ ቢገጥመው በደል አይሆንበትም። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ጣልያንን መግጠሟ በደል
አይሆንባትም። ጠላትህን ውደድ ተብሏልና ምናለበት ያን ጊዜ ጣልያንን ወደን ብትወረንም ዝም ብንል የሚል ሰው ካለ
የመጻሕፍትን ቃል አልተረዳም ማለት ነው።

ወታደር ሞትን የማይፈራ ልበ ሙሉ ቆራጥ መሆን አለበት።ዮሐ.15፣13 "ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ
ፍቅር ለማንም የለውም" እንዳለ ወታደር ሌላውን ሕዝብ ለማዳን ራሱን ለሞት አሳልፎ የሚሰጥ ነው።ለሌላው ሰው ሰላም እርሱ
በውርጭ፣ በቀን፣ በሌሊት፣ በበረሃ፣ በደጋ ሳይሰቀቅ የሚዋጋ ነው።ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 44 ቁጥር 1550 ለእመ ወጻእከ ለጸብዕ
ላዕለ ጸርከ ጠላትህን ለመውጋት ብትወጣ። ወርኢከ አፍራሰ ወሰረገላተ ወሕዝበ ዘይበዝኁ እምኔከ ኢትፍራኅ እምኔሆሙ።
ከአንተ የሚበዙ ብዙ ሕዝብ ብዙ ሠረገላ ብዙ ፈረስ ብታይ ከብዛታቸው የተነሳ አትፍራ። እስመ እግዚአብሔር አምላክከ
ምስሌከ። እግዚአብሔር ፈጣሪህ በረድኤት ከአንተ ጋራ ነውና። መዋጋት በጀመርክ ጊዜ ካህን እነሆ ጠላታችሁን ለመውጋት
ትሄዳላችሁና ልቡናችሁ አይሸበርባችሁ ወኢትትገሐሡ እምቅድመ ገጾሙ። ከፊታቸው አትሽሹ ይበላቸው።ቁጥር 1551
ምእመናን ወደ ጦር ሲሄዱ በፊታቸው መስቀል አቁመው ይስገዱለት። ወታደር ብዙ የጠላት ወገን ሲመጣ የሚርበተበት የሚርድ
መሆን የለበትም።ካህናት ጦር አንስተው ጠላትን መግጠም እንደማይገባቸው ተመልክተናል። ነገር ግን ከጦሩ ጋር ሄደው የቆሰለ
ማከም፣ ምግብ ማቀበል እና የመሳሰሉ ሥራዎችን ይሰራሉ። በጎንደር ዘመነ መንግሥት ንጉሡ የካቶላክ እምነትን በሀገሪቱ
ለማስፋፋት ባሰበ ጊዜ የንጉሡ ባለሟሎችና አብዛኛው ሕዝብ ጦርነት ገጠመ። ጳጳሱ አቡነ ስምዖን ከኦርቶዶክስ ምእመናን ጋር
ሆነው ንጉሡን ጦርነት ገጠሙት። በዚህ ጊዜ ጳጳሱ ጦር አላነሱም። ከጦሩ መካከል ተገኝተው ግን ወታደሮችን አይዟችሁ
በርትታችሁ ተዋጉ። ሃይማኖትን ለመለወጥ የተነሳን ንጉሥ ስትዋጉ ብትሞቱ ሰማእት ናችሁ እያሉ ያበረታቱ ነበር። በዚህ ጦርነት
እሳቸውም በጠላት ጦር ተገድለዋል። በፋሺስት ዘመንም በኢትዮጵያ የሆነው ይሄው ነው። ሰማእቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ
ከአርበኞች ጋር ሆነው ሀገራቸውን ከጠላት ለማዳን ይጥሩ ነበር። ነገር ግን እሳቸው ጳጳስ ስለሆኑ ጦር ይዘው ማንንም መግደል
አይችሉም። የቆሰለን ማከም፣ የደከመን ማበርታት ግን ይችላሉ። ይህንን የተመለከተ ፋሽስት አቡነ ጴጥሮስን በአደባባይ
ገድሏቸዋል። ወታደር ሞት አይፈሬ መሆን አለበት። ሌላውን ሰው ለማዳን እርሱ ደረቱን ለጦር ሰጥቶ የሚዋጋ መሆን አለበት።
ይህም ስለሌላው ራሱን አሳልፎ የመስጠት ፍቅር ነው።

በጻሕክሙ ኀበ ሀገር አው ኀበ ብሔር ከመ ትትቃተልዎሙ ለሰብአ ዚኣሃ ጸውዕዎሙ ለከዊነ ዕርቅ። በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን
ጠላቶች ለመውጋት ወደሀገሪቱ ብትሄዱ መጀመሪያ እንታረቅ በሏቸው። ከጠብ ምንም እንደማይገኝ ጠቅሶ መታረቅ እንደሚገባ
የእርቅ ጥያቄ አቅርብ። እርቁን አንፈልግም ብለው በጠላትነቱ ከቀጠሉ ግን ግጠማቸው። ቁጥር 1554 ወለእመ ኢተወክፉክሙ
ለከዊነ ዕርቅ ወተጋደሉክሙ ወተጻብኡክሙ ጽብእዎሙ ወአዕፅቁ ላዕሌሆሙ አንታረቅም ብለው ቢወጓችሁ ግን አስጨንቃችሁ
ውጓቸው። ቢገቡላችሁ እጃቸውን ቢሰጧችሁ ይቅር በሏቸው። እስመ እግዚአብሔር ይቤ ብጹዓን መሐርያን። እግዚአብሔር
የሚምሩ ብጹዓን ናቸው ብሏልና። እጅ ለሚሰጥ ወታደር ምሕረት ይደረጋል። ጀግና ወታደር እጅ ለሚሰጥ ምሕረት የሚያደርግ፣
እጅ ለማይሰጥ ሰው ደግሞ እስከ ሞት ድረስ የሚፋለም ነው። ወታደር ወደ ጠላት ሀገር ገብቶ ሲገጥም ሽማግሌዎችን፣ ሕጻናትን፣
ባልቴቶችን፣ ካህናትን ሊገድላቸው አይገባም። ተዋጊውን ጠላት ለይቶ መፋለም ይገባል እንጂ። ቁጥር 1556 ወለእመ አገትካ
ለሀገር ወነበርከ ላእሌሃ ብዙኀ መዋእለ ከመ ትትቃተል እስከ ያርኅው ለከ። ኢትግዝም አእዋሚሃ። ዛፎቿን ተክሏን አትቁረጥ
አለ ካህናቱን ሕጻናቱን ባልቴቶቹን ሽማግሌዎችን አታጥፋ እስመ ዕፀወ ገዳም ኢይክሉ ጎይይ እምኔክሙ። እነዚህ ከእናንተ መሸሽ
አይቻላቸውምና። ወለእፅሰ እንተ ኢትፈሪ ግዝምዋ።አርበኞችን ግን አጥፏቸው።ድል እስክትነሷቸው ድረስ ሰዎቿን ውጓቸው።
ስለዚህ ወታደር እጅ ለሚሰጥ መሐሪ፣ እጅ ለማይሰጥ እስከ ሞት የሚፋለም መሆን አለበት ። ጠላቱን ለይቶ የሚመታ መሆን
አለበት። ሽማግሌዎችን እና ሰላማውያን ሰዎችን የማያስጨንቅ እና የማይጎዳ መሆን አለበት።

የወገንን የጦር መረጃ ለጠላት የሚያቀብል ወታደር ወይም ጠላት ያሸንፍ ዘንድ መሣሪያ ለጠላት የሚሸጥ ቅጣቱ መቃጠል ነው።
ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 44 ቁጥር 1561 ጠላቶች ድል እንዲያደርጉ የተመከረውን ምክር ለጠላት የሚናገር ቢኖር ወይም
ወደእነርሱ ሸሽቶ ሂዶ መሣሪያ የሸጠላቸው ሰው ቢኖር ሰቅለው ያቃጥሉት። ጠላት የወገንን ጦር መረጃ ካወቀ ወገንን ለማጥቃት
የሚረዳውን ዘዴ ያገኛል። ይህ እንዳይሆን ወታደር ምሥጢረኛ መሆን አለበት። ቢማረክ እንኳ ምሥጢሩን ከሚያወጣ ተገድሎ
ሰማእትነትን ቢቀበል ይሻለዋል። ወታደር ለወገን መናገር ያለበትን ምሥጢር ይናገራል ። ለሚመራው የጦር አዛዥ መናገር
ያለበትን ምሥጢር ለአዛዡ ይናገራል። የራሱ ብቻ ምሥጢርም ሊኖረው ይችላል። ወታደር አይዋሽም። እውነትንም ግን
በምሥጢር ይይዛታል እንጂ አይናገራትም። ለምሳሌ አንድ መንግሥት 100,000 ወታደር ቢያስመርቅ ይህ እውነት ቢሆንም
መቶ ሺ ወታደር አስመረቅሁ ማለት ግን የለበትም። ምክንያቱም ጠላት የወታደሩን ብዛት ታሳቢ ያደረገ እና በቁጥር ብልጫ ይዞ
ሊያጠቃ ይችላልና ነው። ወታደር ያለበትን መልክአ ምድር ማሳወቅ የለበትም። ለጠላት Geographical Advantage
መስጠት ይሆናልና። ወታደር ጠላትን ለማሸነፍ የተለያዩ ዘዴዎችን ሊጠቀም ይችላል። ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ በመጽሐፈ
መሳፍንት እንደተነገረው 300 ቀበሮ ሰብስቦ በጅራታቸው መካከል ችቦ አብርቶ ጠላትን ያሸነፈ አለ ። በሌላም በሌላም ዘዴ
ጠላታቸውን ያሸነፉ አሉ። ስለዚህ ወታደር ለጠላት ሊጠቅሙ የሚችሉ ጂኦግራፊያዊ መረጃዎችን፣ የጦር መሳሪያ መረጃዎችን፣
የቁጥር መረጃዎችን እና የመሳሰሉት ነገሮች አሳልፎ ሊሰጥ አይገባም። እኒህን አሳልፎ የሰጠ ወታደር ከተገኘ በፍትሐ ነገሥቱ
መሠረት ለሌላው ትምህርት ይሆን ዘንድ ሰቅለው በእሳት ያቃጥሉታል። ይህም ፍትሕ ሥጋዊ ነው። ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 43
ቁጥር 1562 ኃጢኣት ስለሠራችሁ እግዚአብሔር በጠላቶቻችሁ እጅ አሣልፎ ቢሰጣችሁ ማርከው ወደ ሀገራቸው ቢወስዷችሁ
በሃይማኖታችሁ መጽናት ሕጋችሁን መጠበቅ ይገባችኋል። በመብል በመጠጥም ቢሆን መጽሐፍ ባዘዘው ሥርዓት መጽናት
ይጠበቅባችኋል። በከመ ዳንኤል ወሠለስቱ ደቂቅ። ሠለስቱ ደቂቅና እነ ዳንኤል ተማርከው ባቢሎን በወረዱ ጊዜ ጥሬ በልተው
ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ቆይተዋልና። ስለዚህ ወታደር ቢማረክ እንኳ ሃይማኖቱን የማይለውጥ፣ ሥነ ምግባሩን የማይለውጥ
መሆን አለበት። የማረኩት አካላት ከሃይማኖቱ የሚቃረን ነገር አድርግ ቢሉት እንኳ እምቢ ብሎ እስከ ሞት ድረስ መጽናት
አለበት ።መዝ.136 ውስተ አፍላገ ባቢሎን ህየ ነበርነ ወበከይነ ሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን። በባቢሎን ወንዞች አጠገብ ሆነን ጽዮንም
ባሰብናት ጊዜ አለቀስን። ... ይልና ወበህየ ተስእሉነ እለ ጼወውነ ነገረ ማኅሌት በዚያም የማረኩን ሰዎች ዘምሩልን አሉን። እፎ
ነሐሊ ማኅሌተ እግዚአብሔር በምድር ነኪር። የእኛ ባልሆነ ምድር በምርኮ ቦታ እንዴት እንዘምራለን ብለዋል ። ይህ ዝማሬ
በተለየ በቤተመቅደስ የሚባል ዝማሬ ነው። ቤተመቅደስ ደግሞ ፈርሷልና እንዲህ አሉ።

መማረክ ብቻውን ኃጢኣት አይሆንም። ወታደር የተቻለውን ያህል ተዋግቶ አልሆንለት ሲል ሊማረክ ይችላል። ነቢያቱ እነ ነቢዩ
ኤርምያስ፣ እነ ነቢዩ ዳንኤል፣ እነ ነቢዩ ሕዝቅኤል ተማርከው ሄደው ነበርና። በጦርነት ጊዜ ተስፋ መቁረጥ አይገባም። እስከ
መጨረሻው ጠላትን መዋጋት ይገባል እንጂ። ተስፋ ቆርጠን ራሳችንን ማጥፋት እና የመሳሰሉ ከእግዚአብሔር ሕግ ተቃራኒ የሆኑ
ነገሮችን ልናደርግ አይገባም። እስከ ሞትክ ድረስ የፈጣሪን ሕግ ጠብቀህ ልትኖር ይገባል እንጂ። ስለዚህ ለወታደር
ከእግዚአብሔር ውጭ የሚበልጥ ምንም ነገር ስለሌለበት የፈጣሪን ሕግ መጠበቅ አለበት። በመጽሐፈ ነገሥት እንደተጻፈው
ኢዮስያስ ታላቅ ንጉሥ ነበረ። ነገር ግን በኋላ በጦርነት ሞቷል። በጦርነት መሞቱ ግን ክብሩን አልቀነሰበትም። ወታደር ክብር
ያለው ነው። ስለዚህ ክብሩን መጠበቅ አለበት።

ኦሪት ዘኊልቁ ምዕራፍ 13 ኢያሱ እና ካሌብ ሰላይ (ጉበኛ) ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል። ይህም ሊዋጉት ያሰቡትን ጠላት
መረጃ አስቀድሞ ለማወቅ ይጠቅማል።ታላቁ እስክንድር ዓለምን ሲገዛ ኢትዮጵያን አልገዛትም። እስክንድር ዓለምን ለመግዛት
በዋናነት የጠቀመው ስለላ ነው። አስቀድሞ ወደዚያ ሀገር ተመሳስሎ ይገባና የሀገሪቱን መረጃ አጥንቶ ይመለሳል። ከዚያ ወታደር
ይዞ ሀገሪቱን በእርሱ ሥር ያደርጋት ነበር። ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ግን የሆነው ያልጠበቀው ነገር ነው። እስክንድር ስሙ ገናና
ስለነበር የኢትዮጵያ ንግሥት ሰላይ አስልካ መልኩን አስቀርጻ አስመጥታ ታውቀው ነበርና ገና ሲገባ ተይዞ ማንነቱ ሲነገረው
ተደንቋል ይባላል። ችግሩ አሁን አሁን ስለላ (ጉበኝነት) ለሀገር ሳይሆን ለጥቂት ፖለቲካዊ ቡድኖች ባሪያ እንዲሆን ሆኗል።
ሰላዮችም አለማቀፋዊ እና አህጉራዊ መረጃን አይሰበስቡም። እዚያው እርስ በእርስ ሕዝቡ እንዲለያይ ባል ሚስቱን ሚስት ባሏን
እንድትሰልል ነው እየተደረገ ያለው። ስለዚህ ደህንነት ወይም ስለላ የጥቂት ፖለቲካዊ ቡድኖች ባሪያ መሆን የለበትም። ሕዝባዊ
እና ሀገራዊ መሠረት ሊኖረው ይገባል።

ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ያጠፋን እንዲቀጣበት ያለማን እንዲሾምበት ብለው 318ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት ፍትሕ ሥጋዊን
ሰርተውለታል። በፍትሕ መንፈሳዊ ካህናት፣ ጳጳሳት ምእመናንን ይመሩበታል። በፍትሕ ሥጋዊ ነገሥታት መኳንንት ሕዝቡን
ይመሩበታል። በፍትሕ መንፈሳዊ መግደል የለም። በፍትሕ መንፈሳዊ የመጨረሻው ቅጣት ከቤተክርስቲያን አውግዞ መለየት
ነው። በፍትሕ ሥጋዊ ግን የመጨረሻው ቅጣት እስከ መግደል ይደርሳል። ነገሥታቱ መኳንንቱ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘውን ሳያዳሉ
በሕጉ መሠረት መታሰር የሚገባውን ያሥሩታል። መገደል የሚገባውን ይገድሉታል ። በንግሥና እና በፍርድ ወንበር ተቀምጠው
በትክክል ካልፈረዱ ግን ሰማያዊ ቅጣት ይቆያቸዋል። ፈጣሪ ያነገሣቸው ጥፋተኛን ይቀጡ ዘንድ ሕዝቡን በሰላም ያስተዳድሩ
ዘንድ ነውና። ስለዚህ ክርስቲያኑ በእያንዳንዱ የመንግሥት መስሪያ ቤት ገብቶ ሕዝቡን በመልካም አስተዳደር ሊመራው ይገባል።
እንጂ ከሥልጣኑም ከውትድርናውም ከሁሉም እየሸሸን ቦታውን ለሌላ አሳልፎ መስጠት አይገባም። እመሰ ተአምር ባቲ ገረገራ
ዋልድባ ይእቲ እንዲሉ። ከታወቀበት ሁሉም ለጽድቅ ይሆናል።

You might also like