Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 6

የሳምንቱ ቁልፍ መልዕክት

አንደበት
ይህ መልዕክት ትኩረት የሚያደርገው ሰላምን ለማስፈን የሃይማኖት አባቶች ባላቸው ከፍተኛ
ሚና ላይ ሲሆን በተለይ የክርስቲያኖች መመሪያ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ፤ አንደበትን በአግባቡ
ካልተጠቀሙት የሚያመጣው መዘዝና በአማኞች ኃላፊነት ላይ ነው፡፡
“ከአንደበት እሳት እንጠበቅ” የመልዕክቱ ክፍል፡- (ያዕቆብ 3፡6-8፣ምሳሌ 16፡27፣ማቴ 15፡11)
ያሳለፍነው ሳምንት በአገራችን ብዙ ሰዎች ማለትም፣የሃይማኖት አባቶች፣ ቀሳውስት፣ መጋቢያን፣
መምህራን፣ ወንጌላውያን፣ ዲያቆናት እንዲሁም አማኞች ወይም ሃይማኖተኞች ነን የሚሉ ብዙ
ወገኖች አንደበታቸው ሲረክስ፣ያልተገባ ንግግር ሲናገሩ፣ የስድብና የእርግማን ናዳ በገዛ
ወገኖቻቸው ላይ ሲያወርዱ፣በትዕቢትና በኩራት ሲናገሩ ያሳለፉበት፣ ብዙዎቻችንም ብዙዎችን
የታዘብንበት እንዲሁም ያዘንበት ሳምንት ነው፡፡ የሰማናቸው የስድብ ናዳዎች በአገራችን ብቻ
ሳይሆን በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት በመላው ዓለም ተዘዋውረዋል፤ደግነቱ በአማርኛ ቋንቋ
ስለሆነ በብዛት ስድቦቹን መታዘብ የቻሉት አማርኛ ቋንቋ የሚሰሙ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡
ስለሆነም በአለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪና ተደማጭ በሆኑ ሚያዲያዎች ስድቦቹ አልተደመጡም፤
ስድቦቹ በእንግልዝኛ ቋንቋ ሆነው ቢሆን ኖሮ ሚዲያዎቹ በብዙ ያራግቡትና አገራችንን ብዙ
ትዝብት ውስጥ ያስገቡ ነበር፡፡ በአገራችን ብዙ ጸያፍ ስድቦች የተለመዱ ቢሆኑም የሰሞኑን ልዩ
የሚያደርገው በአብዛኛው ስድቦቹ የተዘነዘሩት በሃይማኖት አባቶች፣ አገልጋዮችና በአማኞች
አንደበት መሆኑ ነው፡፡ ሳምንቱ ስም ይሰጠው ከተባለ እኔ “የስድብ ሳምንት” ብዬዋለሁ፡፡ ከዚህም
በመነሳት ሁሉም ክርስቲያኖች ያለ ልዩነት የሚቀበሉትና የእምነታቸው መመሪያ ያደረጉት ወይም
ያደረግነው ቅዱሱ መጽሐፍ ስለ አንደበት ከሚያስተምረው ጥቂቱን ለማካፈል ወድጃለሁ፡፡
አንደበት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱሳችን አፍ፣ምላስ እንዲሁም ከንፈር በሚሉ ቃላት በጥቅም
ላይ ውሎአል፡፡ በአለማችን በአንደበት ወይም በምላስ ባልተገባ ሁኔታ በተነገሩ ወይም በወጡ
ቃላት ምክንያት ታላላቅ ጦርነቶች ተከስተዋል፣የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል፣ ቁጥርና ስፍር
የሌለው ንብረት ወድሟል፣ትዳሮች ፈርሰዋል፣ዜጎች ተበትነዋል፣ህጻናት ያለ አሳዳጊ ቀርተዋል፣
አገሮችና መንግስታትም ጭምር ፈርሰዋል፤ ተበትነዋልም፡፡ በተገቢው መንገድ ከተጠቀምን
ምላሳችን/አንደበታችን አዳኝ እንደሆነ ሁሉ ባልተገባ መንገድ ከተጠቀምነው ደግሞ ገዳይም ነው፡
፡የጦርነቶች ሁሉ መጀመሪያና እናት ምላስ ነው ይባላል፡፡ ምላስ ይመርዛል፣ምላስ ይገድላል፣
የሰው ልጅ ምላስን የመሰለ ስለታም ሰይፍ ወይም አንደበትን የመሰለ መድፍና እሳት ተሸክሞ
ይዞራል፡፡ ባልተገባ መንገድ ከተጠቀመ ደግሞ በዚህ ሰይፍ ራሱንም ሌሎችንም ይቆርጣል፣
1|Page
መንደለሩን፣ ሰፈሩን፣ ማህበረሰቡን ያቃጥላል፤አገርንም ያወድማል፡፡ ሰው እንደ ጀልባ ሲሆን
ምላስ ደግሞ እንደ መቅዘፊያ ነው ይባላል፡፡ መቅዘፊያውን በተገቢው መንገድ ካልተቆጣጡሩት
ጀልባው አቅጣጫ መሳቱና በባህር ውስጥ መስጠሙ የማይቀር፣ የብዙዎችን ሕይወት ለአደጋ
መዳረጉ እርግጥ እንደሆነ ሁሉ አንደበቱን ወይም ምላሱን ያልተቆጣጠረ ስው ጥፉቱ እንዲሁ
ነው ይባላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሰው ቤቱን፣ ውሎውን፣ አለባበሱን ብቻ ሳይሆን አንደበቱን ወይም
ምላሱን (ንግግሩን) ይመስላል ይባላል፡፡ በአጠቃላይ ይህን በተመለከተ ቅዱስ ቃሉ ወርቃማ
አስተምህሮዎች አሉት፡፡ ከብዙዎቹ ጥቅቶቹን ብቻ እንመልከት፡-
 “አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን
ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል ነገር ግን አንደበትን
ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው። በእርሱ
ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች
እንረግማለን፤ ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ
ሊሆን አይገባም። ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን?
ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም
ጣፋጭ ውኃ አይወጣም” (የያዕቆብ መልዕክት ምዕ. 3፡6 - 12) ።
 “ምናምንቴ ሰው ክፋትን ይምሳል፥ በከንፈሩም የሚቃጠል እሳት አለ” ( መጽሐፈ ምሳሌ
ምዕ›16፡27) ።
 “ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን
የሚያረክሰው ይህ ነው አላቸው” ( የማቴዎስ ወንጌል ምዕ 15፡11)።
ሐዋሪያው ያዕቆብ አንደበት እሳት ነው፣ዓመፀኛ ዓለም ነው፣ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋል፣የፍጥረትን
ሩጫ ያቃጥላል፣የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ነው…ብሎ ከዘረዘረ በኃላ አንደበትን መግራት
ምን ያህል ከባድና አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግሮአል፡፡ የመጽሐፈ ምሳሌ ጸሐፊ ደግሞ በአንደበቱ
ክፋትን የሚምስ ሰው ምናምንቴ እንደሆነና በከንፈሩም የሚቃጠል እሳት እንዳለ ይናገራል፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባው ሳይሆን
ከአፍ የሚወጣው ነው ብሎ አስተምሮአል፡፡ አንደበቱን የሚገራ/ምላሱን የሚቆጣጠር ሰው ትልቅ
ሰው ነው፡፡ በዚህ ሳምንት አንደበታቸውን መቆጣጠርና መግዛት የተሳናቸውን በትዕቢት
የተወጠሩና በስድብ የተካኑ ብዙ የሃይማኖት መሪዎችን አይተናል፡፡ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች
ከቃሉ ጋር የተቃረነ ሕይወት እንደሚኖሩና ምን አይነት ተከታይ እንደሚያፈሩ መገንዘብ ከባድ
አይደለም፡፡ ከአንደበታቸው ወይም ከምላሳቸው ከሚወጣው ቃል/ስድብ የተነሳ ብዙዎች ትልቅ

2|Page
ቢሆኑም ምናምንቴ መሆናቸውን ታዝበናል፡፡ ከአፋቸው ከሚወጣው ቃል የተነሳ ብዙዎች ጻድቅ
ቢመስሉም ምን ያህል የረከሱ መሆናቸውን ተገንዝበናል፡፡ አገርንና ሕዝብን ያስማማሉ፣
የተጣሉትን ያስታርቃሉ፣ የሰላም አምባሳደሮችና ለፈጣሪ የሚኖሩ ናቸው ተብለው የሚታሰቡት
የሃይማኖት መሪዎች ተሳዳቢዎች ከሆኑ ሃገር ምን ተስፋ አላት? ትውልዱስ ከእነዚህ አባቶች
ምን ይማራል? በፓለቲከኞችስ ላይ ለምን እንፈርዳለን? ከዚህም በመነሳት ዋናው ነገር የሃይማኖት
መሪ መባልና መሆን ሳይሆን እውነተኛ መንፈሳዊነት ወይም የልብ መለወጥ መሆኑን በተግባር
ተረድተናል፡፡ ምክንያቱም ሰዎች መንፈሳዊ ሳይሆኑ ወይም በቃሉ እውነትና በመንፈሱ ሳይለወጡ
የሃይማኖት መሪ፣መጋቢ፣አስተማሪ፣ወንጌላዊ፣ ቄስ፣ ዲያቆን…ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሕይወትና ኑሮ
ከተግባር ጋር ከተፋታ የሃይማኖት አባት መባል ዋጋ የለውም፡፡ በለብነት ጣሪያ የነኩ የሃይማኖተ
አስተማሪ ነን የሚሉ ሰሞኑን በተሌቪዥን ቀርበው ስለ ሙስና ጥፋትና ክፋት ሲናገሩ ብዙዎቻችን
አንገሽግሾናል፡፡ የሚከበሩ፣የሚደመጡ አባቶች የሚሰብኩና የሚያስተምሩ ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን
በተግባር የሚኖሩ ናቸው፡፡ ለዚህ ይመስለኛል ፈረንጆቹ “walk your talk” የሚትናገረውን ኑር
እንደማለት ነው፡፡
የክርስቶስ ተከታይ ነን የሚሉ አማኞችና አገልጋዮች ሁሉ የክርስቶስን ፈለግ መከተል
እንዳለባቸውና ክርስቶስ ምሳሌውን ለተከታዮቹ እንደተወ ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስ በጥሩ ሁኔታ
አስተምሮአል፡፡
“የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ
እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤
ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው
ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን
በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ” (1ጴጥሮስ 2፡21-24) ።
ጌታችን መድኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በቆየባቸው ጊዜያትና በአገልግሎቱ ሁሉ በቃል
መስበክና ማስተማር ብቻ ሳይሆን በሕይወቱ ምሳሌነቱን አሳይቶአል፤ያስተማረውን ኖሮአል፤
የኖረውንም አስተምሮአል፡፡ ሐዋሪያው ጴጥሮስ ያነሳቸውን ነገሮች ብንመለከት ክርስቶስ ፍለጋውን
እንድንከተል ምሳሌውን ትቶልን እንደሄደ፣ ኃጢአትን ሳያደርግ ተንኮልም ሳይገኝበት ስለ እኛ
ሲል መከራን እንደተቀበለ፣ ተንኮል በአፉ እንዳልተገኘበት፣ሲሰድቡት መልሶ እንዳልተሳደበ፣
መከራን ሲቀበል እንዳልዛተ፣ ስለ እኛ እንደተገረፈ እንደቆሰለና የእኛን ኃጢአት በመስቀል ላይ
እንደተሸከመ ነው፡፡ ይህን መጽሐፍ የሚያነብና የሚያስተምር የሃይማኖት መሪ እንዴት ተሳዳቢ

3|Page
ይሆናል?፣ እንዴት በወንድማማቾች መካከል ጸብ ይዘራል? እንዴት የአገርና የሕዝብ ሰላም
እንድደፈርስ ጥፋት ያውጃል? አሳፋሪ ነው፡፡
ሐዋሪያው ጳውሎስ ደግሞ ለኤፈሶን አማኞች በጻፈው መልዕክት፤ የምንናገረው ቃል ለሚሰሙት
ጸጋን የሚሰጥ፣የሚያንጽና በጎ እንዲሆን እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችን ከቶ እንዳይወጣ አጥብቆ
ተናግሮአል፡፡
“ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል
እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ” (ኤፌ 4፡29) ።
ታዲያ ይህን ጌታ የምንከተልና የምናገለግል ከሆነ እንዴት እንሳደባለን?፣ እንዴት እንዝታለን?
እንዴት ሌሎችን ለማቅናትና ለመመለስ ዋጋ መክፈል ያቅተናል? እንዴት ምሳሌነት የጎደለውን
ሕይወት እንኖራለን? እንዴት ክፉ ቃል ከአንደበታችን እናዘንባለን? ለሚሰሙት ጸጋን የማይሰጥ፣
የማይጠቅም፣ የማያንጽ ቃልና ንግግር ለምን የእኛ መታወቂያ ይሆናል?

ምና እናድርግ?
 ከአንደበት እሳትና መርዝ ራሳችንን እንጠብቅ!
 ተራ ንግግሮችን በመናገርና በመሳደብ ምናምንቴ ሰው አንሁን!
 በአንደበታችን ቃልና ንግግር አንርከስ!
 የክርስቶስን ምሳሌነት እንከተል እንጅ ለተከታዮቻችን ክፉ ምሳሌ አንሁን!
 ጸጋን የማይሰጥ፣ የማያንጽ፣ የማይጠቅም ማንኛውንም ክፉ ቃል ከአንደበታችን አናውጣ!
 “ክርስቲያኖች ነን፣ አማኞች ነን፣ አገልጋዮች ነን፣ የሃይማኖት መሪዎች ነን”… የምንል
ሁሉ ስለ ስድባችን እና ክፉ ንግግራችን በእግዚአብሔር ፊት እውነተኛ ንስሃ እንግባ!
ሕዝባችንንም ይቅርታ እንጠይቅ!
 መለያየትን፣ጸብን፣ሁከትን፣ጥፋትን የሚዘሩትን የሃይማኖት አባቶች እውቅና አንስጥ
የሚፈጽሙት ተግባር ወንጄል ስለሆነ በህጋዊ መንገድ ለህግ እናቅርብ!
እግዝአብሔር ማስተዋልን ይስጠን! ሕዝባችንና ምድራችንን ይባርክ! ኢየሱስ ክርስቶስ ያድናል!!!

4|Page
ስለ ምላስ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገራቸውን የተወሰኑ ጥቅሶች ከእግዚአብሔር ቃል ለተጨማሪ
ዕውቀት እንመልከት፡-
ምላስ
በመጽሐፍ ቅዱሳችን ምላስ የሚለው ቃል ከ126 (አንድ መቶ ሃያ ስድስት) ጊዜ በላይ ተጽፎ
እናገኛለን፡፡ በአሉታዊም ሆነ በአዎችነታዊ መልኩ ብዙ ትምህርት የሚሰጡ ጥቅሶችን ማየት
እንችላለን፡፡ መናገር ስለቻልን ብቻ እንዳንናገርና ምላሳችንን በአግባቡ እንድንጠቀም እመክራለሁ፡
፡ በአገራችን ክፉ ንግግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ መምጣታቸው አሳስቦኛል፤የሃይማኖት
መሪዎችና ሰባኪዎች ደግሞ ወደዚህ ጎራ መቀላቀላቸው አስደንግጦኛል፡፡ እንደ ወንጌል
አስተማሪና የሰላም ሰው የእኔ ስራ ማስተማር የማስተምረውን ደግሞ መኖር ስለሆነ ከቃሉ
በላይ ደግሞ አስተማሪ ስሌለለ፤ የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት ! ከተማርን ደግሞ ለሌሎች
እናካፍል!
 “ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፤ጥፋትም ሲመጣ አትፈራም” (ኢዮብ 5፡21) ።
 “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፤ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው” (ምሳሌ 12፡
18) ።
 “የጠቢባን ምላስ እውቀትን ያሳምራል፤ የሰነፎች አፍ ግን ስንፍናን ያፈልቃል” (ምሳሌ
15፡2) ።
 “ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ነው፤ የጠማማ ምላስ ግን ነፍስን ይሰብራል” (ምሳሌ 15፡
4) ።
 “ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው፤ የሚወድዱአትም ፍሬዋን ይበላሉ” (ምሳሌ 18፡
21) ።
 “የሰሜን ነፋስ ወጀብ ያመጣል፤ ሐሜተኛ ምላስም የሰውን ፊት ያስቈጣል” (ምሳሌ 25፡
23)
 “የደከመውን በቃል እንዴት እንደምደግፍ አውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር የተማሩትን
ምላስ ሰጥቶኛል፤ ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፥ እንደ ተማሪዎችም ትሰማ ዘንድ ጆሮዬን
ያነቃቃል” (ኢሳ. 50፡4)።
 “የእስራኤል ቅሬታ ኃጢአትን አይሠሩም፥ ሐሰትንም አይናገሩም፥ በአፋቸውም ውስጥ
ተንኰለኛ ምላስ አይገኝም፤ እነርሱም ይሰማራሉ፥ ይመሰጉማል፥ የሚያስፈራቸውም
የለም” (ሶፎ. 3፡13) ።

5|Page
 “አንደበትም(ምላስ) እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤
ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል” (ያዕቆብ
3፡6) ።

አንዳንድ የአማርኛ አባባሎች ልጨምር!


 ምላስ እንጂ ምግባር የለም!
 ምላስ ከስጋ ነው የተሰራው ነገር ግን አጥንት የመስበር ችሎታ አለው ስለዚህ
ስለምትናገረው ነገር ሁሉ ተጠንቀቅ!
 ዱላ አካልን ያቆስላል ምላስ ግን አዕምሮን!

አዳነ ደቻሳ (ወ/ዊ)


የነገረ መለኮትና የነገረ ሰላም ከፍተኛ ባለሙያ
ታኅሳስ 16/2015 ዓ/ም
አዲስ አበባ

6|Page

You might also like