final teacher dicip;ine Rekik (2) (1)

You might also like

Download as docx, pdf, or txt
Download as docx, pdf, or txt
You are on page 1of 24

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

ትምህርት ቢሮ

የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራር

-
ሙያዊ የስነ ምግባር፤የዲሲፕሊን አፈጻጸምና ቅሬታ አቀራረብ መመሪያ

ረቂቅ

ነሐሴ / 2015 ዓ.ም


አዲስ አበባ

መግቢያ

ትምህርት የዕድገት ሁሉ ቁልፍ መሣሪያ ሆኖ ለሁለንተናዊ ልማት መፋጠን ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ትምህርት
ተመራማሪና ችግር ፈቺ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችልና የህብረተሰቡን አመለካከት ወደ እድገት አቅጣጫ
የሚመራ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ሳይንሳዊ ግኝቶች ጋር በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ባህላዊ
ዕድገቶችን የሚያፋጥን መሣሪያ ነው፡፡

0
ይህንን የትምህርት ሥራ ውጤታማ ለማድረግና የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማሳለጥ በየጊዜው አሰራሮችን
ለማሻሻልና ለማዘመን በየትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ መምህራን ር/መምህራንና ሱፐርቫይዘሮችን
ሚና ከፍተኛ በመሆኑም መምሀራን እና የትምህርት አመራሮች ሙያዊ ሥነምግባርን በመላበስ ውጤታማ
ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡በዚህ ረገድ አልፎ አልፎ በመምህራንና በትምርት ቤት አመራሮች
የሚስተዋሉ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ይታያሉ፡፡

ስለሆነም አሁን በስራ ላይ ያሉ መመሪያዎችን በመፈተሽ ወቅቱን የዋጀ ወጥነት ያለው መመሪያ ማዘጋጀት
አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህ የመምህራንና የትምህርት አመራር ሙያዊ የስነ-ምግባር፤የዲሲፕሊን አፈጻጸምና
ቅሬታ አቀራረብ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡

ክፍል አንድ
1. ጠቅላላ

1.1. አጭር ርዕስ


ይህ መመሪያ "የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራር ሙያዊ የስነ-
ምግባር፤የዲሲፕሊን አፈጻጸምና ቅሬታ አቀራረብ መመሪያ ቁጥር---------- ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

1.2. የተፈጻሚነት ወሰን


ይህ መመሪያ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ስር በሚገኙ ቅድመ አንደኛ ደረጃ፣ አንደኛ ደረጃ
፣ መካከለኛ ደረጃ ፣ ሁለተኛ ደረጃ እና አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራንና
ር/መምህራን እንዲሁም እነዚህን ትምህርት ቤቶች የሚደግፉ በየደረጃው ያሉ ሱፐርቫይዘሮች (የትምህርት
አመራሮች) ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

1
1.3. ትርጓሜ
የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ ውስጥ፡-
1. "ከተማ"፡- ማለት የአዲስ አበባ ከተማ ማለት ነው፡፡
2. "አስተዳደር"፡- ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማለት ነው፡፡
3. "ቢሮ"፡- ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ማለት ነው፡፡
4. "ትምህርት ቤት"፡- ማለት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቅድመ አንደኛ ደረጃ ፣ አንደኛ
ደረጃ፣መካከለኛ ደረጃ ፣ ሁለተኛ ደረጃ እና አዳሪ ትምህርት ቤቶች ማለት ነው ፡፡
5. "የትምህርት አመራር"፡- ማለት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ስር የሚገኙ የትምህርት
ተቋማትን የሚመሩ ምክትል ርዕሳነ መምህራን ፤ ርዕሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች ማለት ነው፡፡
6. "መምህር"፡- ማለት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች
ተቀጥረው በማስተማር ስራ ላይ የሚገኙ ማለት ነው፣
7. "ሙያዊ ሥነ-ምግባር"፡-ማለት መምህሩና የትምህርት አመራሩ ሙያው የሚጠይቀውን መልካም
እሴቶችን ያጎለብቱ ዘንድ እንዲተገብሯቸው የሚጠበቁ ተግባራት ማለት ነው፡፡
8. ሴኩላር፡- ማለት ትምህርት ቤቶች ከሃይማኖታዊ እና ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ነጻ መሆን ማለት ነው፡፡
9. ተገልጋይ፡- በትምህርት ቤት አገልግሎት የሚፈልጉ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች፣
ማህበረሰቡ፣ ልዩ ልዩ ተቋማት የመሳሰሉት ማለት ነው፡፡

1.4. የጾታ አገላለጽ


በዚህ መመሪያ ውስጥ በወንድ ጾታ የተደነገገው የሴትንም ጾታ ያካትታል፡፡

1.5. ሙያዊ የስነ-ምግባር


ማንኛውም መምህርና የትምህርት ቤት አመራር ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ሙያዊ የሥነ-ምግባር ተግባራትን መላበስ
ይኖርባቸዋል፡፡
1.5.1. የመንግስትን ፖሊሲ፣የትምህርት ፕሮግራሞችንና ዕቅዶችን በብቃት ይፈጽማሉ፡፡
1.5.2. በሙያቸው ያምናሉ፤ሙያቸውን ያከብራሉ፤ይንከባከባሉ፡፡
1.5.3. የኢትዮጰያና አለም አቀፍ ህጎች ፣ ደንቦች ፣አዋጆችና መመሪያዎችን ያከብራሉ፡፡
1.5.4. የተማሪዎችን አካዳሚክ ነጻነት ይጠብቃሉ፡፡ (ማንኛውንም ጥያቄ የመጠየቅ፣ ማንኛውንም ሃሳብ
የመግለጽና የማቅረብ)
1.5.5. በሙያ ስነምግባራቸውና በብቁ ዜግነት ስብዕናቸው በአርአያነት ይቀርባሉ፡፡ በፀጉር አቆራረጣቸው
ወይም በአሰራራቸው ፣ በአለባበሳቸው እና በአነጋገራቸው በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ስብዕናቸው
በመልካም አርአያነት ይታያሉ፡፡

2
1.5.6. ሲጋራ አያጨሱም ፣ ጫት አይቅሙም፣ አልኮሆል አይጠጡም ፣ የተለያዩ ሱስ አምጪ እጾችን …
ወዘተ አይጠቀሙም፡፡
1.5.7. የፈተናን ሚስጥራዊነትን፣ አስተዳደርንና አሰራርን ይጠብቃሉ፡፡
1.5.8. ለተማሪዎቻቸው ተገቢውን ምክርና ክብር ይሰጣሉ፡፡
1.5.9. በክፍል ውስጥም ይሁን ከክፍል ውጪ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተግባራዊ ጥናትና ምርምር
ይፈታሉ፡፡
1.5.10. ተማሪዎች ጤንነታቸውንና ደህንነታቸውን ከሚጎዱ ሁኔታዎች እንዲጠበቁ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
1.5.11. ትምህርት ሴኩላር መሆኑን ተገንዝበው ተማሪዎችን ሲያስተምሩ ከስርዓተ ትምህርቱ ውጪ
የግል አመለካከት /ሃይማኖታዊም ሆነ ፖለቲካዊ/ ጉዳዮችን በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ
በጭራሽ አያራምዱም፡፡
1.5.12. ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን መተላለፊያ መንገዳቸውን በመለየት እራሳቸውንና የትምህርት
ማህበረሰቡን ይጠብቃሉ፡፡
1.5.13. የአሰራር ህግና ደንብ በመከተል በተመደቡበት የስራ ቦታ ይሰራሉ፡፡
1.5.14. መደበኛ የሥራ ሰዓትን ሳይሸራርፉ በአግባቡ ሥራ ላይ ያውላሉ፡፡
1.5.15. የትምህርት ውስጣዊ ብቃትን ለመጨመር በተነሳሽነት ይሰራሉ፡፡
1.5.16. ጾታዊ ትንኮሳና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በትምህርት ቤትና ከትምህርት ቤት ውጪ
እንዳይከሰቱ ይከላከላሉ፡፡
1.5.17. ትምህርት የማህበረሰቡን ኑሮ ሊያሻሽል እንደሚችል በማመን ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን
ትምህርት በየአካባቢያቸው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በተግባር እንዲፈቱበት ያደርጋሉ፡፡
1.5.18. ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ልዩ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡
1.5.19. የተማሪዎችን ዝንባሌ እና ችሎታ፤የስነልቦናና የአካል እድገት ጠብቀው ትምህርቱን ይሰጣሉ፡፡
1.5.20. በሰንደቅ ዓላማ ስነ-ሥርዓት ላይ ይገኛሉ ፣ ያስተባብራሉ፡፡
1.5.21. በትምህርት ቤቱ እና በትምህርት ማህበረሰቡ መካከል የሚኖረው መልካም ግንኙነት
ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡
1.5.22. የህጻናት መብት ድንጋጌዎችን ያከብራሉ፡፡
1.5.23. በትምህርት ቤቱ ዙሪያ አዋኪ ጉዳዮች እንዳይኖሩ ያደርጋሉ፤ሲገኙም ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ
በመሆን ችግሮቹን ይፈታሉ
1.5.24. ወቅታዊና ተአማኒነት ያለው መረጃ ይሰበስባሉ፣ ያደራጃሉ፤ይተነትናሉ፡፡ ተፈላጊውን መረጃ
ይሰጣሉ፡፡
1.5.25. የተማሪዎች የምገባ ሂደትን በቅርበት ይከታተላሉ፤ በምግብ ዝርዝሩ (ሜኑ) መሰረት አየተመገቡ
መሆናቸውን ያረጋግጣሉ፡፡
3
1.5.26. አዳዲስ አሰራሮችን ተቀብለው ይፈጽማሉ፡፡
1.5.27. አዲስ ለሚመደቡ መምህራንና የትህርት ቤት አመራሮች ትውውቅ ያደርጋሉ፡፡ ልምድ ያካፍላሉ፡፡
1.5.28. የሙያ ማህበራቸውን ደንብና መርሆቻቸውን ያከብራሉ፡፡
1.5.29. ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር መብታቸውን ያከብራሉ፡፡
1.5.30. ለተማሪዎች ፣ ለሰራተኞችና ለተገልጋዮች ተገቢውን ክብር ይሰጣሉ፡፡
1.5.31. ስራን ማዕከል ያደረገ ጤናማ ፣ግልጽነት ያለበት ግንኙነት ይፈጥራሉ፡፡
1.5.32. በክበባት፣በዲፓርትመንት እና በልዩ ልዩ ኮሚቴዎች በመሳተፍና በማስተባበር ኃላፊነታቸውን
በአግባቡ ይወጣሉ ሌሎች የሚሰጡ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡

ክፍል ሁለት
የዲሲፕሊን አፈጻጸምና ውሳኔ አሰጣጥ
የዲሲፕሊን አፈጻጸም ሁኔታ
2. የዲሲፕሊን ቅጣት መሰረታዊ አላማ
የዲሲፕሊን ቅጣት ዓላማ የተቋሙን (የትምርት ቤቱን) ሥራ ውጤታማ ለማድረግ ሲሆን መምህር ወይም የትምህርት
አመራሩ በፈጸመው ጥፋት ተጸጽቶ ወደፊት ብቁ እና ታማኝ ዜጋ ለመሆን እንዲችል ለመርዳት ፣ ለማረምና
ለማስተማር እንዲሁም የማይታረም በሚሆንበት ጊዜ ስራው እንዳይበደል ከስራ ለማሰናበት ነው፡፡፣
የዲሲፕሊን ጥፋት (ጉድለት) በፈጸመ ማንኛውም መምህር ወይም የትምህርት አመራር ላይ በአዋጅ ቁጥር 56/2010
አንቀጽ 69/1 መሰረት እንደ ጥፋቱ ክብደት ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት ቅጣቶች አንዱ ሊወሰንበት ይችላል፡፡
2.1. የቃል ማስጠንቀቂያ፣
2.2. የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣
2.3. እስከ 15 ቀን የሚደርስ የደመወዝ መቀጮ፣
2.4. እስከ 3 ወር የሚደርስ የደመወዝ መቀጮ፣
2.5. እስከ 2 ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ከስራ ደረጃና ደመወዝ ዝቅ ማድረግ፣
2.6. ከስራ ማሰናበት፣
3. የቅጣት አይነቶች አመዳደብ
በዚህ መመሪያ በክፍል 2 በአንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 2.1 ፣ 2.2 እና 2.3 የተመለከቱት ቀላል የዲሲፕሊን ጥፋት
ቅጣቶች ሲሆኑ የተቀሩት ማለትም በንዑስ አንቀጽ 2.4 ፣ 2.5 እና 2.6 የተዘረዘሩት ከባድ የዲሲፕሊን ጥፋት ቅጣቶች
ተብለው የሚመደቡ ናቸው፡፡

3.1. በቀላል የዲሲፕሊን ጥፋት ላይ ስለሚሰጥ ውሳኔ


በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች የዲሲፕሊን አፈጻጸምና ቅሬታ አቀራረብ ስነስርዓት በደንብ ቁጥር
24/2002 አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 በተገለጸው መሰረት የት/ቤቱ ወይም የተቋሙ ኃላፊ ወይንም

4
የሚመለከተው የበላይ ኃላፊ አንድ መምህር ወይም የትምህርት ቤት አመራር ቀላል የዲሲፕሊን ጥፋት የፈጸመ እንደሆነ
እንደየጥፋቱ ክብደት የቃል ማስጠንቀቂያ ወይም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የመስጠትና እስከ አስራ አምስት ቀን ደመወዝ
የመቅጣት ስልጣንና ሃላፊነት ይኖረዋል፡፡
3.1.1. በተወሰነው ቀላል የዲሲፕሊን ቅጣት ያልተስማማ መምህር ወይም የትምህርት ቤት አመራር ቅሬታውን
ለተቋሙ የበላይ ኃላፊ እና ለቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በቅደም ተከተል ማቅረብ ይችላል፡፡
3.2. በከባድ የዲሲፕሊን ክስ ላይ ከሆነ በዚህ መመሪያ በምዕራፍ 2 ንዑስ ቁጥር 2 በዲሲፕሊን ኮሚቴ ታይቶ የውሳኔ
ሃሳብ እንዲቀርብለት ለት/ቤቱ ወይም ለትምህርት ተቋሙ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ይመራል፡፡ የውሳኔውንም ውጤት
ለሚመለከተው አካል ያቀርባል፡፡
4. መምህር ወይም የትምህርት አመራርን ከስራና ከደሞዝ አግዶ ስለማቆየት

4.1. አንድ መምህር ወይም የትምህርት አመራር ከስራ ሲታገድ የሚታገደው ከስራና ከደሞዝ ይሆናል፡፡
4.2. በአዋጅ ቁጥር 56/2010 አንቀጽ 72 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ከስራና ከደሞዝ አግዶ ማቆት የሚቻለው ከሁለት
ወር ለማይበልጥ ጊዜ ይሆናል፡፡
4.3. በዚህ መመሪያ ንዑስ አንቀጽ 4.2 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ ከታገደበት ሰዓት ጀምሮ ዐዐዐዐዐ ተከታታይ 0000
የሥራ ቀናት ውስጥ ለዲሲፕሊን ኮሚቴ ይቀርባል ፡፡
4.4. መምህሩ ወይም የትምህርት ቤት አመራሩን ከስራ አግዶ ማቆት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እግዱ የሚፈጸመው
በሚመለከተው የበላይ ኃላፊ (ተጠሪ) ይሆናል፤ዋና ርዕሰ መምህርና ሱፐርቫይዘር የሚታገዱት በየደረጃው ባሉት
የትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊዎች ወይም በቢሮ ደረጃ ባሉ ሃላፊዎች ይሆናል፡፡
4.5. የዚህ መመሪያ 4.4 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድን መምህር ወይም ምክትል ርእሰ መምህር ከስራና ከደሞዝ
አግዶ ማቆየት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ መምህሩ ወይም ምክትል ርእሰ መምህሩ የሚታገደው በትምህርት ቤቱ ዋና
ር/መምህር ይሆናል፡፡
4.6. ውሳኔ ሳያገኝ ከሁለት ወራት በላይ የቆየ መምህር ወይም የትምህርት አመራር ያለተጨማሪ ስነ ስርዓት ወደ
ስራው እንዲመለስ ይደረጋል፡፡ እንዲሁም በእግድ ወቅት ያልተከፈለውን ደሞዝ ያለወለድ እንዲከፈለው
ይደረጋል፡፡
4.7. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 4.6 በተገለጸው መሰረት የት/ቤቱን ወይም የትምህርት ተቋሙን መምህር ወይም
የትምህርት ቤት አመራር ወደ ስራው ካልመለሰው በመምህሩ ወይም በትምህርት አመራሩ ላይ ለደረሰው
መጉላላትና በደል ኃላፊነት ይወስዳል፡፡
4.8. በአዋጁ አንቀጽ 72 መሰረት መምህሩን ወይም የትምህርት አመራሩን አግዶ ማቆየት የሚቻለው፡-

ሀ/ ጥፋት ከፈጸመበት ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ማስረጃዎች በማበላሸት በመደበቅ ወይም በማጥፋት
የማጣራት ሂደቱን ያሰናክላል ወይንም

ለ/ በመንግስት ንብረት ላይ ተጨማሪ ጉዳት ያደርሳል ወይም

5
ሐ/ ከተከሰሰበት ጥፋት ክብደት አንፃር የሌሎችን ሞራል የሚነካ ወይም ተገልጋዩ ሕዝብ በተቋሙ ላይ ሊኖረው
የሚገባውን እምነት ያዛባል ወይም

መ/ ተፈፀመ የተባለው ጥፋት ከሥራ ያስወጣል ተብሎ ሲገመት ነው፡፡

4.9. መምህሩን ወይም ወይም የትምህርት አመራርን አግዶ ስለማቆየት

4.9.1. በአዋጅ 56/2010 በአንቀጽ 72 ንዑስ 3 መሰረት ከሥራና ደመወዝ የታገደ መምህር፣ ም/ርዕሰ መምህር ፣
ር/መምህር ፣ ሱፕርቫይዘር ከመደበኛ ሥራው ታግዶ የሚቆይበት ጊዜና ከሥራው የታገደበት ምክንያት
እግዱን በሰጠው ስልጣን ባለው ሀላፊ ወይም የበላይ ሀላፊ በጽሁፍ ይገለጽለታል፡፡
4.9.2. ዕግድ የተደረገበት መምህር፣ ም/ርዕሰ መምህር ወይም የትምህርት ቤት አመራር አድራሻው ያልታወቀ
እንደሆነ ትዕዛዙ በሚሰራበት ትምህርት ቤት ወይም የትምህረት ተቋም የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ለአስር
ተከታታይ ቀናት ተለጥፎ እንዲቆይ ይደረጋል፡፡
4.9.3. ከስራ መታገዱ የሚጸናው የማገጃ ትዕዛዝ በጽሁፍ ከተሰጠው ወይም በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ከተለጠፈበት
ቀን ጀምሮ ይሆናል፡፡
4.9.4. መምህሩ ወይም የትምህርት አመራሩ በተከሰሰበት ጥፋት ምክንያት ከስራ እንዲሰናበት ካልተወሰነበት
በስተቀር በእግዱ ወቅት ሳይከፈለው የቀረው ደሞዙ ያለወለድ ይከፈለዋል፡፡
4.9.5. የዲሲፕሊን ቅጣቱ ውሳኔ የገንዘብ ቅጣት ከሆነ ከደመወዙ አንድ ሶስተኛ (1/3) ብቻ የሚቆረጥ ሆኖ
ተግባራዊ የሚሆነውም መምህሩ ወይም የትምህርት አመራሩ ወደ ስራ ከተመለሰበት ወር ጀምሮ ይሆናል፡፡

5. ቀላል የዲሲፕሊን ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች


በዚህ መመሪያ መሰረት የሚከተሉት ጥፋቶች ቀላል የዲሲፕሊን ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች ናቸው፡፡
በመምህራን ላይ ተፈጻሚ የሚሆን የቀላል ዲሲፕሊን ጥፋቶች
5.1. ለስራው አስፈላጊ የሆኑ የስራ መሳሪያዎችንና መረጃዎችን በአግባቡ አደራጅቶ አለመያዝ፡፡
5.2. ያለበቂ ምክንያት በስራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለሚመለከተው የስራ ሃላፊ ወይም አካል በወቅቱ አለማሳወቅ፡፡
5.3. በቂ ባልሆነ ምክንያት የመማር ማስተማር የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች እና ውይይቶች ላይ
አለመገኘት፣
5.4. በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ እና በክፍል ውስጥ ጋዋን አለመልበስ፣
5.5. ለዓመት የተሰጠውን ክፍለ ጊዜ በወቅቱ አለማጠናቀቅ /portion coverage /
5.6. በመደበኛ የሥራ ሰዓት (8 ሰዓት በቀን) ውስጥ ሌላ የግል ስራ መስራት ፤
5.7. በሰንደቅ ዓላማ ስነ-ሥርዓት ላይ አለመገኘት፣ አለማስተባበርና አለመዘመር፣
5.8. በተለያዩ ምክንያቶች የባከኑ ክ/ጊዜዎችን እቅድ አውጥቶ ያለማካካስ ወይም እንዲካካሱ አለማድረግ፤
5.9. በተጓዳኝ ክበባት ላይ በንቃት አለመሳተፍ
5.10. የተማሪዎች የምገባ ሂደትን በሚወጣው መርሀ ግብር መሰረት በአግባቡ አለመከታተል

6
5.11. በሚያስተምሩት የትምህርት ይዘት ላይ በቂ ዝግጅት አለማድረግ (የተመጠነ ማስታወሻ ፣ የትምህርት
መርጃ መሳሪያ … ወዘተ) አዘጋጅቶ አለማስተማር ፤
5.12. የተከታታይ ሙያ ማሻሻያ እና አጀመ በአግባቡ አለመከታተል ፖርት ፎሊዮ አደራጅቶ አለመያዝ እና
በተያዘለት ጊዜ አለማጠናቀቅ፤
5.13. በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ጋዋን አለመልበስ፣
5.14. በተቀመጠው እቅድ መሰረት የእርስ በርስ የክፍል ውስጥ ምልከታ አለማድረግ፤
5.15. በትምህርት ቤቱ ወይም በትምህርት ተቋሙ ብልሹ አሰራር ወይም ድርጊት ሲፈጸም ተመልክቶ ያለማጋለጥ ፡፡
5.16. የወንድ መምህራን የፀጉር ርዝመት ከ 5 ሴ.ሜትር ከበለጠ ፤
5.17. የ ሴት መምህራን የፀጉር አሰራር ንጽህናውን ያልጠበቀና ለተማሪዎች መልካም አርዓያ ያልሆነ
5.18. የወንድ መምህራን ሱሪ የተቀደደ ፣ የተተለተለ ፣ የቬል ስፋት ከ 16 ሴ.ሜትር ያነሰ ከሆነ ፣ ነጠላ ጫማ ያደረገ ፣
5.19. የሴት መምህራን ቀሚስ ከጉልበት በላይ የሆነ ፣ እንብርት የሚያሳይ ቲ-ሸርት ፣ የተተለተለ ሱሪ/ቀሚስ
መልበስ ፣ የከንፈር ቀለም መቀባት፣
5.20. ማንኛውንም ዓይነት ንቅሳት (Tattoo) በሰውነት ላይ መነቀስ ፣
5.21. የተለያዩ አርማ፣ ጽሁፍ ያላቸው አልባሳት መልበስ

6. በርዕሳነ መምህራን ላይ ተፈጻሚ የሚሆን የቀላል ዲሲፕሊን ጥፋቶች


6.1. ለስራው አስፈላጊ የሆኑ ህጎች፣ ደንቦች ፤መመሪያዎች የስራ መሳሪያዎችንና መረጃዎችን በአግባቡ አደራጅቶ
አለመያዝ፡፡
6.2. ለተገልጋይ የሚሰጠውን አገለግሎት በተቀመጠው ስታንዳርድ ጊዜ ፣ ጥራትና መጠን መሰረት አለመፈጸም፤
6.3. ለስራ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ማለቃቸውን ወይም አለመሟላታቸውን እያወቀ ወይም በቸልተኝነት
እንዲሟሉ አለማድረግ፡፡
6.4. በትምህርት ቤቱ ወይም በትምህርት ተቋሙ ብልሹ አሰራር ወይም ድርጊት ሲፈጸም ተመልክቶ ያለማጋለጥ እና
ያለማስቆም ፡፡
6.5. የወንድ ፀጉር ርዝመት ከ 5 ሴ.ሜትር አስበልጦ ማሳደግ ፤
6.6. ለሴት ንጽህናውን ያልጠበቀ የፀጉር አያያዝ
6.7. ለወንድ ሱሪ የተቀደደ ፣ የተተለተለ ፣ የቤል ስፋት ከ 16 ሴ.ሜትር ያነሰ መልበስ ፣ ነጠላ ጫማ ማድረግ ፣
6.8. ለሴት ከጉልበት በላይ የሆነ ቀሚስ፣ እንብርት የሚያሳይ ቲ-ሸርት ፣ የተተለተለ ሱሪ/ቀሚስ መልበስ ፣
የከንፈር ቀለም መቀባት፣
6.9. ማንኛውንም ዓይነት ንቅሳት (Tattoo) በሰውነት ላይ መነቀስ ፣
6.10. በዓመት ውስጥ የተቀመጠውን የትምህርት ክ/ጊዜ በአግበቡ ሥራ ላይ መዋሉን አለመከታተል
6.11. በመደበኛ የሥራ ሰዓት (8 ሰዓት በቀን) ውስጥ ሌላ የግል ስራ መስራት፤መምህራኖች ሲሰሩ
አለመከታተል
6.12. በተለያዩ ምክንያቶች የባከኑ ክ/ጊዜዎችን እቅድ አውጥቶ እንዲካካሱ አለማድረግ፤

7
6.13. መምህራን በሚያስተምሩት የትምህርት ይዘት ላይ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ በቂ እገዛና ክትትል
አለማድረግ፤
6.14. ፡፡
6.15. በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ጋዋን አለመልበስ፣
6.16. በተቀመጠው እቅድ መሰረት የክፍል ውስጥ ምልከታ አለማድረግ፤
6.17. የት/ቤቱን ዓመታዊ እቅድ በወቅቱ ባለድርሻ አካላትን ሳያሳትፉ ማቀድ ፤
6.18. ትምህርት ቤቱ ወይም የትምህርት ቤቱ ተቋም የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ የአሰራር ስርዓት፤ ቅድመ ሁኔታ

የአገልግሎት አሰጣጥ ስታንዳርድና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች ለተገልጋዮች ግልጽ አለማድረግ፡፡

6.19. በተቀመጠው እቅድ መሰረት ድጋፍና ክትትል አለማድረግ፤


6.20. በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ መካከል የሚኖረው ግንኙነት /መስተጋብር/ ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን
አለማድረግ ፤
6.21. የመምህራንን ክፍተት እየለዩ የአቅም ግንባታ ስልጠና አለመስጠት ወይም እንዲሰጥ አለማድረግ፤
6.22. ከወላጅ ወይም ከማንኛውም ሌላ ተገልጋይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችንና አቤቱታዎችን በማጣራት
አፋጣኝ እና አጥጋቢ ውሳኔ ወይም ምላሽ አለመስጠት፡፡
6.23. የእቅድ አፈጻጸም ተግባራት ስራዎችን ለሚመለከተው አካል ወቅቱን ጠብቆ አለመላክ ፤

6.24. በዚህ አንቀጽ ከተዘረዘሩት ቀላል አስተዳደራዊ ጥፋቶች ጋር ተመሳሳይ ክብደት ያላቸውን ሌሎች ጥፋቶች
መፈጸም ናቸው፡፡
7. በሱፐርቫይዘር ላይ ተፈጻሚ የሚሆን የቀላል ዲሲፕሊን ጥፋቶች

7.1. የመምህራንን ክፍተት እየለዩ የአቅም ግንባታ ስልጠና አለመስጠት


7.2. ለስራው አስፈላጊ የሆኑ ህጎች፣ ደንቦች ፤መመሪያዎች የስራ መሳሪያዎችንና መረጃዎችን በአግባቡ አደራጅቶ
አለመያዝ፡፡
7.3. የወንድ ፀጉር ርዝመት ከ 5 ሴ.ሜትር አስበልጦ ማሳደግ ፤
7.4. ለሴት የፀጉር አሰራር ንጽህናውን ያልጠበቀና ለተማሪዎች መልካም አርዓያ ያልሆነ
7.5. ለወንድ ሱሪ የተቀደደ ፣ የተተለተለ ፣ የቤል ስፋት ከ 16 ሴ.ሜትር ያነሰ መልበስ ፣ ነጠላ ጫማ ማድረግ ፣
7.6. ለሴት ከጉልበት በላይ የሆነ ቀሚስ፣ እንብርት የሚያሳይ ቲ-ሸርት ፣ የተተለተለ ሱሪ/ቀሚስ መልበስ ፣
የከንፈር ቀለም መቀባት፣
7.7. ማንኛውንም ዓይነት ንቅሳት (Tattoo) በሰውነት ላይ መነቀስ ፣
7.8. በዓመት ውስጥ የተቀመጠውን የትምህርት ክ/ጊዜ በአግበቡ ሥራ ላይ መዋሉን አለመከታተል
7.9. መምህራን በሚያስተምሩት የትምህርት ይዘት ላይ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ በቂ ክትትል አለማድረግ
7.10. የት/ቤቱን ዓመታዊ እቅድ በወቅቱ ባለድርሻ አካላትን ሳያሳትፉ ማቀድ ፤

8
7.11. በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ መካከል የሚኖረው ግንኙነት /መስተጋብር/ ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን
አለማድረግ ፤
7.12. የእቅድ አፈጻጸም ተግባራት ስራዎችን ለሚመለከተው አካል ወቅቱን ጠብቆ አለመላክ ፤ወይም

7.13. በዚህ አንቀጽ ከተዘረዘሩት ቀላል አስተዳደራዊ ጥፋቶች ጋር ተመሳሳይ ክብደት ያላቸውን ሌሎች ጥፋቶች
መፈጸም ናቸው፡፡
8. ከባድ የዲሲፕሊን ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች
በዚህ መመሪያ መሰረት የሚከተሉት ጥፋቶች ከባድ የዲሲፕሊን ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች ናቸው፡፡
9. በመምህራን ላይ ተፈጻሚ የሚሆን የከባድ ዲሲፕሊን ጥፋቶች
9.1. የበላይ ኃላፊ ትዕዛዝ ባለማክበር ፤ በቸልተኝነት ፣ በመለገም ፣ ወይም ሆነ ብሎ የአሰራር ሥነ- ስርኣት ወይም
የመንግስትን ፖሊሲ ባለመከተል በስራ ላይ በደል ማድረስ፤
9.2. ጉዳዮችን ሆነ ብሎ ማዘግየት ወይም ባለጉዳዮችን ማጉላላት ወይም ማመላለስ፤
9.3. ተገልጋዩ ህብረተሰብ ወይም ባለጉዳዮችን በአግባቡ አለማስተናገድ ፣ ማመነጫጨቅ ፣ መሳደብ ወይም ተገቢውን
አክብሮት አለመስጠት፤
9.4. የተገልጋዩን ሰነድ ወይም ማህደር ሆነ ብሎ መደበቅ ወይም በቸልተኝነት እንዲጠፋ ማድረግ፤
9.5. ለተገልጋዩ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ አድሎ መፈጸም፣
9.6. ስራ እንዳይሰራ ሆን ብሎ ማወክ ወይም ከሚያውኩት ጋር መተባበር፤
9.7. ውሳኔዎችና ትዕዛዞች በወቅቱ እንዳይፈጸሙ እንቅፋት መሆን፤
9.8. አካላዊም ሆነ ስነልቦናዊ ቅጣት በተማሪዎች ላይ ማድረስ፣
9.9. በስራ ቦታ ጠብ መጫር መደባደብና አንባጓሮ መፍጠር፤
9.10. በስካር ወይም በአደንዛዥ ዕጽ ሱስ በመመረዝ በስራ ቦታ ላይ መገኘት፤
9.11. ጉቦ መቀበል ወይም እንዲሰጠው መጠየቅ ወይም ለሌላ ሰው ጉቦን ማቀባበል ወይም መደለያ መቀበል ወይም
መጠየቅ፤
9.12. የሌብነት ወይም የእምነት ማጉደል ወይም የማጭበርበር ድርጊት መፈጸም፤
9.13. በስራ ቦታ ለህዝብ ሞራል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት መፈጸም፤
9.14. በትምህርት ቤቱ ወይም በትምህርት ተቋሙ ንብረት ላይ ሆነ ብሎ ወይም በቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ፡፡
9.15. በስልጣን አለአግባብ መጠቀም፤
9.16. በስራ ቦታ ላይ ጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳ መፈጸም፡፡
9.17. በህግ ወይም በአሰራር የተሰጠውን የስራ ኃላፊነት መሸሽ ወይም አለመቀበል
9.18. የትምህርት ቤቱን ንብረት መሸሸግ፤መደበቅ ፤ማባከን፤ ያለአግባብ ለግል ጥቅም ማዋል፤ በጥንቃቄ ያለመያዝ
ወይም በቸልተኝነት ለብልሽት እንዲደረጉ ማድረግ
9.19. የትምህርት ቤቱን ወይም የትምህርት ተቋሙን ሃብትና ንብረት ለማይመለከተው አካል አሳልፎ መስጠት ፡፡
9.20. የመማር ማስተማር ስራን የሚያደናቅፉ ተግባራትን መፈጸም፡፡
9.21. የፈተናን ሚስጥራዊነትን አለመጠበቅ ፣
9
9.22. ትምህርት ሴኩላር መሆኑን በመገንዘብ በት/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሃይማኖታዊም ሆነ
ፖለቲካዊ እንቃስቃሴ ማድረግ ወይም ሲደረግ በቸልተኝነት መመልከት
9.23. ማንኛውንም የፖለቲካ አመለካከት በትምህር ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥም ሆነ በት/ቤት አካባቢ
ማራመድ፤
9.24. የማንኛውም ኃይማኖታዊና ፖለቲካዊ መገለጫ የሆኑትን ዓርማ ይዞ መገኘት፤አልባሳትን
መልበስ፤ውይይት ቅስቀሳ የመሳሰሉትን ማካሄድ፤
9.25. የሃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ ጽንፈኝነት አስተሳሰብን በሌላው ላይ መጫን፤
9.26. በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የግል የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት አቋም በመያዝ ግጭት ወይም
ብጥብጥ እንዲነሳ ሙከራ ማድረግ ወይም መፈጸም፤
9.27. ከጽንፈኛ ሃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር መረጃ መስጠት፤
9.28. መንግስት በአሸባሪነት ከፈረጃቸው ግለሰቦች ፤ቡድኖች እና ድርጅቶች ጋር ግንኙነት መፍጠር፤
9.29. ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን (ኤች አይቪ ኤድስ ፣ ኮቪድ-19 … ወዘተ) መተላለፊያ መንገዳቸውን
እያወቀ በትምህርት ማህበረሰቡ ላይ ጉዳት ማድረስ ወይም ጉዳት እንዲደርስ ተባባሪ መሆን ፤
9.30. በተደጋጋሚ በተሰጡ ቀላል የዲሲፕሊን ቅጣት እርምጃዎች አለመታረም
9.31. በዚህ አንቀጽ ከተዘረዘሩት ከባድ የዲሲፕሊን ግድፈት ጋር ተመሳሳይ ክብደት ያለውን ሌላ የዲሲፕሊን ጉድለት
መፈጸም

10. በርዕሳነ መምህራን ላይ ተፈጻሚ የሚሆን የከባድ ዲሲፕሊን ጥፋቶች


10.1. የበላይ ኃላፊ ትዕዛዝ ባለማክበር ፤ በቸልተኝነት ፣ በመለገም ፣ ወይም ሆነ ብሎ የአሰራር ሥነ- ስርኣት ወይም
የመንግስትን ፖሊሲ ባለመከተል በስራ ላይ በደል ማድረስ ሲደርስ መመልከት
10.2. ፈተና በሚፈትኑበት ወቅት ተማሪዎችን ከመከታተል ውጭ ፈተናን ሊያውክ የሚችል ማንኛውንም ተግባር
መፈጸም፣ሲፈጸም አፋጣኝ እርምጃ አለመውሰድ
10.3. ዓመታዊና እለታዊ የትምህርት እቅድ በወቅቱ እንዲዘጋጅ ክትትል አለማድረግ
10.4. በዓመት ውስጥ የተቀመጠውን የትምህርት ክ/ጊዜ በአግበቡ ሥራ ላይ አለማዋል እና እንዲውል አለማድረግ ፤
10.5. የተከታታይ ሙያ ማሻሻያ አለመከታተልና ፖርት ፎሊዮ በአግባቡ አደተራጅቶ አለመያዝ ፤መምህራንም
የተከታታይ ሙያ ማሻሻያ እና አጀመ በአግባቡ እንዲከታተሉ ፤ፖርት ፎሊዮ አደራጅተው እንዲይዙ እና
በተያዘለት ጊዜ እንዲያጠናቅቁ ድጋፍና ክትትል አለማድረግ
10.6. ፈተና በሚፈትኑበት ወቅት ተማሪዎችን ከመከታተል ውጭ ፈተናን ሊያውክ የሚችል ማንኛውንም ተግባር
እንዳይፈጸም አለመከታተል፡፡
10.7. ያሉትን መምራን መሰረት ያደረገ የክ/ጊዜ ድልድል በወቅቱ አለመስራት ፣
10.8. ትክክለኛ እና ወቅታዊ የሆነ ሪፖርት አለማቅረብ፡፡
10.9. በመደበኛ የሥራ ሰዓት (8 ሰዓት በቀን) ውስጥ ሌላ የግል ስራ መስራት እና ሲሰራ አለመከታተል
10.10. ሐሰተኛ ሪፖርት ማቅረብ፡፡

10
10.11. ጉዳዮችን ሆነ ብሎ ማዘግየት ወይም ባለጉዳዮችን ማጉላላት ወይም ማመላለስ
10.12. ተገልጋዩ ህብረተሰብ ወይም ባለጉዳዮችን በአግባቡ አለማስተናገድ ፣ ማመነጫጨቅ ፣ መሳደብ ወይም ተገቢውን
አክብሮት አለመስጠት እና ተዘረዘሩት ሲፈጸሙ ማየት
10.13. የተገልጋዩን ሰነድ ወይም ማህደር ሆነ ብሎ መደበቅ ወይም በቸልተኝነት እንዲጠፋ ማድረግ
10.14. ለተገልጋዩ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ አድሎ መፈጸም፣
10.15. ስራ እንዳይሰራ ሆነ ብሎ ማወክ ወይም ከሚያውኩት ጋር መተባበር፤
10.16. ውሳኔዎችና ትዕዛዞች በወቅቱ እንዳይፈጸሙ እንቅፋት መፍጠር ወይም ከመፈጸም መቆጠብ
አካላዊም ሆነ ስነልቦናዊ ቅጣት በተማሪዎች ላይ ማድረስ ወይም ሲደርስ መመልከት

10.17. በስራ ቦታ ጠብ መጫር መደባደብና አንባጓሮ መፍጠር ወይም ሲፈጠር መፈትሄ አለመስጠት፤
10.18. በስካር ወይም በአደንዛዥ ዕጽ ሱስ በመመረዝ በስራ ቦታ ላይ መገኘት ወይም በሚገኙት ላይ ክትትል እና እርምጃ
አለመውሰድ፤
10.19. ጉቦ መቀበል ወይም እንዲሰጠው መጠየቅ ወይም ለሌላ ሰው ጉቦን ማቀባበል ወይም መደለያ መቀበል ወይም
መጠየቅ፡፡
10.20. የሌብነት ወይም የእምነት ማጉደል ወይም የማጭበርበር ድርጊት መፈጸም ወይም ሲፈጸም ለህግ አለማቅረብ፤
10.21. በስራ ቦታ ለህዝብ ሞራል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት መፈጸም ሲፈጸም መመልከት፤
10.22. በትምህርት ቤቱ ወይም በትምህርት ተቋሙ ንብረት ላይ ሆነ ብሎ ወይም በቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ ጉዳት
በሚያደርሱት ላይ እርምጃ አለመውሰድ፡፡
10.23. በስልጣን አለአግባብ መጠቀም፤
10.24. በስራ ቦታ ላይ ጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳ መፈጸም ወይም ሲፈጸም ለህግ አካል አለማቅረብ፤
10.25. በመንግስት ስራ የተሳሳተ ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ በመስጠት በመንግስት ወይም በተገልጋዩ ጥቅም ላይ ጉዳት
እንዲደርስ ማድረግ፤
10.26. በህግ ወይም በአሰራር የተሰጠውን የስራ ኃላፊነት መሸሽ ወይም አለመቀበል፤
10.27. የትምህርት ቤቱን ንብረት መሸሸግ፤መደበቅ ፤ማባከን፤ ያለአግባብ ለግል ጥቅም ማዋል፤ በጥንቃቄ ያለመያዝ
ወይም በቸልተኝነት ለብልሽት እንዲደረጉ ማድረግ ይህንን በሚፈጽሙት ላይ ክትትል በማድረግ እርምጃ
አለመውሰድ፤
10.28. የትምህርት ቤቱን ወይም የትምህርት ተቋሙን ሃብትና ንብረት ለማይመለከተው አካል አሳልፎ መስጠት፤
10.29. የት/ቤቱን ወይም የትምህርት ተቋሙን ህጋዊ ሰነዶችና መረጃዎችን ማጥፋት፤ ማበላሸት ወይም መሰወር፤
10.30. ተገልጋዩ መክፈል የማይገባውን የአገልግሎት ክፍያ ሆነ ብሎ ወይም በቸልተኝነት እንዲከፍል ማድረግ፤
10.31. በየደረጃው ካሉ አመራሮች ወይም በህግ ስልጣን ከተሰጣቸው አካላት ለሚሰጡ ህጋዊ ትዕዛዞች አፋጣኝ ምላሽ
ያለመስጠትና ያለመፈጸም፡፡
10.32. የመማር ማስተማር ስራን የሚያደናቅፉ ተግባራትን መፈጸም ወይም ሲፈጸም እርምጃ አለመውሰድ፤
10.33. የፈተናን ሚስጥራዊነትን አለመጠበቅ ፣

11
10.34. ትምህርት ሴኩላር መሆኑን በመገንዘብ በት/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሃይማኖታዊም ሆነ
ፖለቲካዊ እንቃስቃሴ ማድረግ ወይም ሲደረግ በቸልተኝነት መመልከት
10.35. የማንኛውም እምነት መገለጫ የሆኑትን ዓርማ ፤አልባሳት ወዘተ… የመሳሰሉትን ለብሶ ወይም
ይዞ መገኘት ለብሰው ወይም ይዘው በተገኙት ላይ የእርምት እርምጃ አለመውሰድ፤
10.36. የማንኛውንም ፖለቲካ ፓርቲ መገለጫ የሆኑትን ዓርማ ይዞ መገኘት፤አልባሳትን መልበስ፤ውይይት
ቅስቀሳ የመሳሰሉትን ማካሄድ ወይም ድርጊቱን በሚፈጽሙት ላይ እርምጃ አለመውሰድ፤
10.37. የሃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ ጽንፈኝነት አስተሳሰብን በሌላወ ላይ መጫን ውይም ድርጊቱን
በሚፈጽሙት ላይ እርምት አለመውሰድ
10.38. በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የግል የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት አቋም በመያዝ ግጭት ወይም
ብጥብጥ እንዲነሳ ሙከራ ማድረግ ወይም መፈጸም ድጊቱን በሚፈጽሙት ላይ እርምጃ አለመውሰድ
10.39. ከጽንፈኛ ሃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር መረጃ መስጠት፤
10.40. መንግስት በአሸባሪነት ከፈረጃቸው ግለሰቦች ፤ቡድኖች እና ድርጅቶች ጋር ግንኙነት መፍጠር፤
10.41. ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን (ኤች አይቪ ኤድስ ፣ ኮቪድ-19 … ወዘተ) መተላለፊያ መንገዳቸውን
እያወቀ በትምህርት ማህበረሰቡ ላይ ጉዳት ማድረስ ወይም ጉዳት እንዲደርስ ተባባሪ መሆን ፤
10.42. ወቅታዊና ተአማኒነት ያለው መረጃ ለሚመለከተው አካል አለመስጠት ወይም በማይሰጡት ላይ
የእርምት እርምጃ መውሰድ፤
10.43. የትምህርት ቤቱን ክፍተት ለመሙላት ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ከወላጆች፣መንግስታዊ ካልሆኑ
ድርጅቶች ወዘተ……….ሀብትን አለማሰባሰብ
10.44. በተማሪዎች ምዝገባ ወቅት ከወላጆች ላይ የመመዝገቢያ ገንዘብ መሰብሰብ ፤
10.45. በተደጋጋሚ በተሰጡ ቀላል የዲሲፕሊን ቅጣት እርምጃዎች አለመታረም
10.46. በዚህ አንቀጽ ከተዘረዘሩት ከባድ የዲሲፕሊን ግድፈት ጋር ተመሳሳይ ክብደት ያለውን ሌላ የዲሲፕሊን ጉድለት
መፈጸም
11. በሱፐርቫይዘሮች ላይ ተፈጻሚ የሚሆን የከባድ ዲሲፕሊን ጥፋቶች
11.1. ትዕዛዝ ባለማክበር ፤ በቸልተኝነት ፣ በመለገም ፣ ወይም ሆነ ብሎ የአሰራር ሥነ- ስርኣት ወይም የመንግስትን
ፖሊሲ ባለመከተል በስራ ላይ በደል ማድረስ ሲደርስ መመልከት
11.2. ተገልጋዩ ህብረተሰብ ወይም ባለጉዳዮችን በአግባቡ አለማስተናገድ ፣ ማመነጫጨቅ ፣ መሳደብ ወይም
ተገቢውን አክብሮት አለመስጠት፤
11.3. ለተገልጋዩ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ አድሎ መፈጸም፣
11.4. ስራ እንዳይሰራ ሆነ ብሎ ማወክ ወይም ከሚያውኩት ጋር መተባበር፤
11.5. አካላዊም ሆነ ስነልቦናዊ ቅጣት በተማሪዎች ላይ ማድረስ ወይም ሲደርስ እርምጃ እንዲወሰድ አለማድረግ፤
11.6. በስራ ቦታ ጠብ መጫር መደባደብና አንባጓሮ መፍጠር ወይም ሲፈጠር መፈትሄ አለመስጠት፤
11.7. ስካር ወይም በአደንዛዥ ዕጽ ሱስ በመመረዝ በስራ ቦታ ላይ መገኘት ወይም በሚገኙት ላይ ክትትል አለማድረግ፤

12
11.8. ጉቦ መቀበል ወይም እንዲሰጠው መጠየቅ ወይም ለሌላ ሰው ጉቦን ማቀባበል ወይም መደለያ መቀበል ወይም
መጠየቅ፡፡
11.9. የሌብነት ወይም የእምነት ማጉደል ድርጊት ወይም የማጭበርበር ድርጊት መፈጸም ወይም ሲፈጸም ለህግ
አለማቅረብ
11.10. በስራ ቦታ ለህዝብ ሞራል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት መፈጸም ወይም ሲፈጸም መመልከት
11.11. በስልጣን አለአግባብ መጠቀም፤
11.12. በስራ ቦታ ላይ ጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳ መፈጸም ወይም ሲፈጸም ለህግ አካል አለማቅረብ
11.13. በህግ ወይም በአሰራር የተሰጠውን የስራ ኃላፊነት መሸሽ ወይም አለመቀበል
11.14. የትምህርት ቤቱን ወይም የትምህርት ተቋሙን ሃብትና ንብረት ለማይመለከተው አካል አሳልፎ መስጠት ፡፡
11.15. ተገልጋዩ መክፈል የማይገባውን የአገልግሎት ክፍያ ሆነ ብሎ ወይም በቸልተኝነት እንዲከፍል ሲደረግ እርምት
አለመውሰድ
11.16. በየደረጃው ካሉ አመራሮች ወይም በህግ ስልጣን ከተሰጣቸው አካላት ለሚሰጡ ህጋዊ ትዕዛዞች አፋጣኝ ምላሽ
ያለመስጠትና ያለመፈጸም፡፡
11.17. የመማር ማስተማር ስራን የሚያደናቅፉ ተግባራትን መፈጸም ወይም ሲፈጸም ማስተካከያ እርምጃ
አለመውሰድ
11.18. የፈተናን ሚስጥራዊነትን አለመጠበቅ ፣
11.19. በሚያስተባብሩበት ትምህርት ቤት ወይም ክላስተር ማእከል ብልሹ አሰራር ወይም ድርጊት ሲፈጸም
ተመልክቶ ያለማጋለጥ
11.20. መምህራን የተከታታይ ሙያ ማሻሻያ እና አጀመ በአግባቡ እንዲከታሉ ፖርት ፎሊዮ አደራጅተው
እንዲይዙ እና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ክትትል አለማድረግ
11.21. በተቀመጠው እቅድ መሰረት ድጋፍና ክትትል አለማድረግ፤
11.22. ትምህርት ሴኩላር መሆኑን በመገንዘብ በት/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሃይማኖታዊም ሆነ
ፖለቲካዊ እንቃስቃሴ ማድረግ ወይም ሲደረግ በቸልተኝነት መመልከት
11.23. የማንኛውም እምነት መገለጫ የሆኑትን ዓርማ ፤አልባሳት ወዘተ… የመሳሰሉትን ለብሶ ወይም
ይዞ መገኘት ለብሰው ወይም ይዘው በተገኙት ላይ የእርምት እርምጃ አለመውሰድ
11.24. የአንድን ፖለቲካ አመለካከት በትምህር ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ማራመድ በሚያራምዱት ላይ
እርምጃ አለመውሰድ
11.25. የአንድን ፖለቲካ ፓርቲ መገለጫ የሆኑትን ዓርማ ይዞ መገኘት፤አልባሳትን መልበስ፤ውይይት ቅስቀሳ
የመሳሰሉትን ማካሄድ ወይም ድርጊቱን በሚፈጽሙት ላይ እርምጃ አለመውሰድ
11.26. የሃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ ጽንፈኝነት አስተሳሰብን በሌላወ ላይ መጫን ውይም ድርጊቱን
በሚፈጽሙት ላይ እርምት አለመውሰድ

13
11.27. በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የግል የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት አቋም በመያዝ ግጭት ወይም
ብጥብጥ እንዲነሳ ሙከራ ማድረግ ወይም መፈጸም ድርጊቱን በሚፈጽሙት ላይ እርምጃ
አለመውሰድ
11.28. ከጽንፈኛ ሃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር መረጃ መስጠት፤
11.29. መንግስት በአሸባሪነት ከፈረጃቸው ግለሰቦች ፤ቡድኖች እና ድርጅቶች ጋር ግንኙነት መፍጠር፤
11.30. ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን (ኤች አይቪ ኤድስ ፣ ኮቪድ-19 … ወዘተ) መተላለፊያ መንገዳቸውን
እያወቀ በትምህርት ማህበረሰቡ ላይ ጉዳት ማድረስ ወይም ጉዳት እንዲደርስ ተባባሪ መሆን ፤
11.31. ወቅታዊና ተአማኒነት ያለው መረጃ ለሚመለከተው አካል አለመስጠት ወይም በመይሰጡት ላይ
የእርምት እርምጃ አለመውሰድ
11.32. በተማሪዎች ምዝገባ ወቅት ከወላጆች ላይ የመመዝገቢያ ገንዘብ መሰብሰብ ፤
11.33. በተደጋጋሚ በተሰጡ ቀላል የዲሲፕሊን ቅጣት እርምጃዎች አለመታረም
11.34. በዚህ አንቀጽ ከተዘረዘሩት ከባድ የዲሲፕሊን ግድፈት ጋር ተመሳሳይ ክብደት ያለውን ሌላ የዲሲፕሊን ጉድለት
መፈጸም
12. ከደረጃና ከደመወዝ ዝቅ በማድረግ የሚሰጥ የቅጣት አወሳሰን
ማንኛውም መምህር እና የት/ቤት አመራር በመንግስት ሰራተኞች አዋጅ 56/2010 አንቀጽ 72 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት
ከስራ ፣ ደረጃና ከደመወዝ ዝቅ በማድረግ የትምህርት ተቋሙ ቅጣት ወስኖበት የቅጣቱ ጊዜ ገደብ እንዳለቀ
12.1. የቅጣት ቆይታ ጊዜው ጨርሶ ሲመለስ ከመቀጣቱ በፊት ይዞት ከነበረው የስራ ደረጃ ጋር ተመሳሳይ ክፍት የስራ
ደረጃ ካለ ካለምንም ተጨማሪ ስነ-ስርዓት ወደ ስራ ደረጃው እንዲመለስ ይደረጋል፤
12.2. ከመቀጣቱ በፊት ይዞት የነበረው የስራ ደረጃ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የስራ ደረጃ ካልተገኘ ክፍት የስራ ደረጃ በተገኘ
ጊዜ ያለ ምንም ተጨማሪ ስነ-ስርዓት በስራ ደረጃው ላይ እንዲመደብ ይደረጋል፡፡
12.3. ከመቀጣቱ በፊት ይዞት ከነበረው የስራ ደረጃ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ክፍት የስራ ደረጃ እስከሚገኝ ደመወዙን እያገኘ
ይጠብቃል፡፡
13. የቅጣት ቅደም ተከተሉን ባለመጠበቅ ስለሚሰጥ ውሳኔ
14. በአዋጅ አንቀጽ 69 ንዑስ አንቀጽ (1) መሰረት የተፈጸመው የዲሲፕሊን ጥፋት ክብደት ተመዝኖ በዚህ መመሪያ
አንቀጽ 2 ስር ከተዘረዘሩት የቅጣት አይነቶች መካከል ቅደም ተከተሉ ሳይጠበቅ አንዱን ለመወሰን ይቻላል፡

ምዕራፍ ሁለት
ስለዲሲፕሊን ኮሚቴ መቋቋምና አሰራር
2. የዲሲፕሊን ኮሚቴ ስለ መቋቋም

በደንብ ቁጥር 24/2002 ምዕራፍ 3 አንቀጽ 24 መሰረት በየትምህርት ቤቱ ወይም በየትምህርት ተቋሙ
የዲሲፒሊን ጉዳዮችን እየመረመረ የውሳኔ ሃሳብ እንደየትምህርት ቤቱ ወይም የትምህርት ተቋሙ ተጠሪነት
ለትምህርት ቤቱ ርዕስ መምህር ወይም ምክትል ርዕስ መምህር ወይም ለተቋሙ ሃላፊ ወይም ለሚወክለው

14
ወይም ለወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ወይም ለክፍለ ከተማው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ ወይም ለሚወክለው
የሚያቀርብ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ይቋቋማል፡፡
2.1. የኮሚቴው አባላት ስብጥር
የኮሚቴው አወቃቀር እንደሚከተለው ይሆናል፡፡
ሀ. በርዕሰ መምህር ወይም በተቋሙ ኃላፊ የሚሰየም አንድ ሰው------------------- ሰብሳቢ
ለ. በርዕሰ መምህር ወይም በተቋሙ ኃላፊ የሚሰየም አንድ ሰው ------------------ አባል
ሐ. ከት/ተቋሙ መሰረታዊ የመምህራን ማህበር የሚወከል ተወካይ አንድ -----------------አባል
መ. ከት/ተቋሙ መሰረታዊ የመምህራን ማህበር የሥርዓተ ጾታ ዘርፍ ተጠሪ አንድ ሴት መምህርት
-----------------አባል
ሠ. የወላጅ ፣ የተማሪ ፣ መምህር ህብረት /ወ.ተ.መህ/ተወማ / መካከል አንድ የወላጅ እና አንድ የተማሪ ተወካይ
----------------------------አባል
ረ. የት/ተቋሙ የሰው ኃይል አስተዳደር ተወካይ ---------------------------አባልና ጸሀፊ
2.2. የኮሚቴ አባላት መመዘኛ
ማናቸውም የኮሚቴ አባል፡-
2.2.1. በጠባዩና በስራ አፈጻጸሙ የተመሰገነ፣
2.2.2. ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በዲሲፕሊን ጉድለት ያልተቀጣ፣
2.2.3. ቋሚ መምህር የሆነና በትምህርት ቤቱ ወይም በትምህርት ተቋሙ ግቢ ውስጥ ቢቻል ከሁለት ዓመት በላይ
አገልግሎት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡
2.3. የኮሚቴው የአገልግሎት ዘመን
2.3.1. የተመረጡት የኮሚቴ አባላት የአገልግሎት ዘመን ሁለት ዓመት ይሆናል፡፡
2.3.2. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2.3.1 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለአንድ ጊዜ ብቻ
በድጋሚ ሁሉም ወይም በከፊል ሊመረጡ ይችላሉ
2.4. ከኮሚቴው አባልነት ስለመሰረዝና ከስብሰባ ስለመነሳት
2.4.1. የኮሚቴው ሰብሳቢ ወይም ማንኛውም አባል ክስ ከቀረበበት መምህር ጋር ፀብ ያለው ወይም በስጋ ወይም
በጋብቻ ዝምድና ያለው መሆኑ በማስረጃ ሲረጋገጥ ወይም ከሳሽ በሚሆንበት ጊዜ ለዚያ ጉዳይ ብቻ
ከኮሚቴው አባልነት እንዲነሳ ይደረጋል፡፡
2.4.2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2.4.1 በተገለፀው መሰረት የኮሚቴ ሰብሳቢው ከሰብሳቢነት የሚነሳ ከሆነ
የቀሩት የኮሚቴ አባላት ከመሃከላቸው ለዚህ ብቻ ሌላ ሰብሳቢ ሊመርጡ ይችላሉ፡፡
2.4.3. ማንኛውም የኮሚቴ አባል ራሱን ከጉዳዩ በማግለልና ሌላውን አባል ለማስጠላት ከባለጉዳዩ ጋር እየተገኘ
ሚስጥር ያወጣ ወይም ቃለጉባኤዎችን መረጃዎችንና ጽሁፎችን ለባለጉዳዩ ያሳየ ወይም ያጋለጠ ወይም
የሰጠ እንደሆነ በዚህ መመሪያ ከባድ ጥፋት ናቸው ተብለው የተዘረዘሩትን እንደፈጸመ ተቆጥሮ
የሚወሰደው የዲሲፕሊን ቅጣት አፈጻጸም እንደተጠበቀ ሆኖ ከኮሚቴው አባልነት ይሰረዛል፡፡ በምትኩም
ስልጣን ባለው ኃላፊ ወይም የበላይ ኃላፊ እንዲሰየም ይደረጋል፡፡

15
2.5. የኮሚቴው ምልአተ ጉባኤና ድምጽ አሰጣጥ
2.5.1. በኮሚቴው ስብሰባ ላይ ሰብሳቢውን ጨምሮ ከግማሽ አባላት በላይ ከተገኙ ምልአተ ጉባኤ ይሆናል፤ ከተገኙ
አባላት ቢያንስ አንዱ የመምህራን ተወካይ መሆን ይኖርበታል፡፡
2.5.2. የኮሚቴው ሰብሳቢ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ቢቀር የቀሩት አባላት ከመካከላቸው ለጊዜው ሰብሳቢ
ይመርጣሉ፡፡
2.5.3. አከራካሪ ጉዳይ ሲያጋጥም የኮሚቴው አስተያየት የሚያልፈው በድምጽ ብልጫ ሲሆን የቀረበው ሀሳብ
እኩል በእኩል የተከፈሉ እንደሆነ ሰብሳቢው ባለበት ወገን የቀረበ ሀሳብ ያልፋል ፤ ሆኖም በሃሳብ የተለየ
አባል የተለየበት ምክንያት በቃለ ጉባኤ ይሰፍራል፡፡
2.6. ስለ ዲሲፕሊን ክስ አመሰራረትና ሁኔታ
2.6.1. የዲሲፕሊን ክስ የሚመሰረተው በትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር በኩል ለሰው ኃይል አስተዳደር
ሲመራለት ይሆናል፡፡
2.6.2. የዲሲፕሊን ኮሚቴው ሰብሳቢ በሰው ሃብት አስተዳደር በኩል የዲሲፕሊን ክስ ተዘጋጅቶ
ሲቀርብለት ለተከሳሽ መጥሪያ ይልካል፡፡
2.6.3. የሚላከው መጥሪያ ተከሳሹ ለተጠረጠረበት ዝርዝር ጥፋት በዲሲፕሊን ኮሚቴው ስብሰባ ላይ
የሚያቀርብበትን ቀን ፣ ሰአትና ቦታ በመግለጽ ክሱን በጽሁፍ ማስረጃዎች መያዝ ይኖርበታል፡፡
2.6.4. ተከሳሹ ለቀረበበት ክስ መልስና የመከላከያ ማስረጃ የሚያቀርብበት ጊዜ የክሱ ጽሁፍ ከደረሰው ቀን
ጀምሮ ከሶስት ቀን ማነስ የለበትም፡፡
2.6.5. የተከሳሹ አድራሻ ያልታወቀ እንደሆነ በኮሚቴው ስብሰባ ላይ የሚገኝበት ቀን ሰአትና ቦታ ተገልጾ
የጥሪ ማስታወቂያ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ተለጥፎ እንዲቆይ
ይደረጋል፡፡ ተከሳሹ በተወሰነው ጊዜ ካልቀረበ በሌለበት ክሱ ተሰምቶና ተመርምሮ ውሳኔ ይሰጣል፡፡
2.6.6. የዲሲፕሊን ኮሚቴው ክሱ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የውሳኔ ሃሳብ
ለትምህርት ቤቱ ር/መምህር ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
2.6.7. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2.6.6 የተመለከተው ዘእንደተጠበቀ ሆኖ በከሳሽም ሆነ በተከሳሽ በኩል
ጉዳዩ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ማሰባሰብን የሚጠይቅ ሆኖ ሲገኝ ከሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ
የውሳኔ ሃሳቡን ለር/መምህሩ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
2.7. የዲሲፕሊን ኮሚቴ አሰራር
ኮሚቴው በዚህ መመሪያ የተሰጠውን ተግባር በሚያከናውንበት ጊዜ የሚያስፈልጉትን ማህደሮች፣
መረጃዎችና ሰነዶች አስቀርቦ ማየት እንዲሁም አግባብነት ያለውን የሰው ምስክር መጥራትና
መስማት ይቻላል፡፡
2.8. ኮሚቴው በመምህራንን ወይም በት/ቤት አመራር ላይ የቀረበውን ክስ በሚያጣራበት ጊዜ
2.8.1. የተከሳሹ ሙሉ ስም ከነ አያት
2.8.2. ተከሳሹ የተከሰሰበትን ጭብጥ
2.8.3. ክሱን ያረጋግጣሉ ተብለው የቀረቡትን የጽሁፍም ሆነ የሰው ምስክርነት ማስረጃዎች፣

16
2.8.4. በትምህርት ተቋሙ ውስጥ የሚገኘውን የተከሳሹን የግል ማህደር እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ
ተከሳሹ በሌላ ቦታ ተቀጥሮ ያገለገለ ከሆነ ቀደሞ ይሰራበት ከነበረው የትምህርት ተቋም
የሚገኘውን የግል ማህደር፣
2.8.5. ለቀረበው ክስ አግባብነት ያላቸውን ህጎች፣ ደንቦችና፣ መመሪያዎች
2.8.6. ሰራተኛው ማስረጃዎች ናቸው ብሎ የሚያቀርባቸውን የጽሁፍና የሰው ማስረጃዎች፤
2.8.7. ከላይ ከተመለከቱት ውጭ ሌሎች አግባብነት አላቸው ብሎ የሚገምታቸውን ማስረጃዎች
እንደአስፈላጊነቱ በማስቀረብ መመርመር ይቻላል፡፡
2.9. ኮሚቴው የቀረበውን ክስ በማስረጃ በሚያጣራበት ጊዜ
2.9.1. ለተከሳሹ ክሱና ማስረጃው በጽሁፍ እንዲደርሰውና የመከላከያ መልሶችን በጽሁፍ የማቅረብ መብት
እንዲጠበቅለት
2.9.2. የከሳሹ ምስክሮች ሲቀርቡ ተከሳሹ በተገኘበት ቃላቸውን እንዲሰጡና ተከሳሹም የሚፈልገውን
የመስቀለኛ ጥያቄ እንዲያቀርብ እንዲሁም የተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ በሚሰማበት ጊዜ ከሳሽ
ተገኝቶ የመስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ መብት እንዲጠበቅለት፣
2.9.3. ተከሳሹ የመደመጥ፣ የመከራከርና በበኩሉ የመከላከያ ማስረጃዎችና ክርክሮቹንም የማቅረብ መብቱ
ተጠብቆ ክሱ በማስረጃ እንዲጣራ የማድረግ፣
2.9.4. የዲሲፕሊን ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ ከደረሰው የዲሲፕሊን ጉደለት ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆንና
ለተመሳሳይ ጥፋትም ተመሳሳይ ቅጣት እንዲሰጥ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
2.10. ለዲሲፕሊን ኮሚቴው የሚቀርቡ ጉዳዮችን በተመለከተ በቃለ ጉባኤ ፀሐፊ በኩል የሚከናወን
ተግባራት፡፡
2.10.1. የዕለታዊ አጀንዳ ቅደም ተከተል በዕለቱ ለይቶ የመያዝ
2.10.2. የስብሰባው ቃለ ጉባኤ በትክክል እየተጻፈና እየተዘጋጀ አባላቱም እንዲፈርሙበት ሆኖ በጥንቃቄ
መቀመጥ አለበት፤
2.10.3. ከሳሽና ተከሳሽ እንዲሁም ምስክሮች የሚሰጡትን ቃል በትክክልና በጥንቃቄ መመዝገብና ቃል
ሰጭዎች በስብሰባው መጨረሻ ላይ እንዲፈርሙበት መደረግ አለበት፡፡
2.10.4. በሁለቱም ወገን የሚቀርቡ ማስረጃዎች ተመዝግበውና ለኮሚቴው ቀርበው ከታዩ በኋላ ፋይሉን
አደራጅቶ በጥንቃቄ ማስቀመጥ አለበት፤
2.10.5. ለተከራካሪ ወገኖች፣ለምስክሮችና ለሌሎች አስረጂዎች የሚሰጡ መጥሪያዎች እንዲሁም ሌሎች
ደብዳቤዎች የተዘጋጁና ሰብሳቢው እየፈረመባቸው ለሚመለከተው ሰው ወይም መስሪያ ቤት
መላካቸውን ወይም መድረሳቸውን ማረጋገጥ፣
2.10.6. በማስታወቂያ በሚወጡ ጽሁፎች በተገቢው ቦታ መለጠፋቸውን ወይም ለሚመለከተው ሰው
ወይም ክፍል መድረሳቸውን ማረጋገጥ አለበት፡፡
2.11. ለዲሲፕሊን ኮሚቴው ስለሚቀርቡ የሰውና የጽሁፍ ማስረጃዎች

17
2.11.1. ተከሳሹ ተነገረበት ለጥፋት ማፍረሻ ወይም መከላከያ የሚሆነውን ተፈቅዶ በስራ ላይ የነበረ
ወይም ያለ አሰራር ደንብ ወይም ሌላ የጽሁፍ ማስረጃ ወይም ምስክሮች ማቅረብ ይችላል፡፡
2.11.2. ተከሳሹ እንዲቀርብለት ወይም ግልባጭ እንዲሰጠው የጠየቃቸው የጽሁፍ ማስረጃዎች ፣ ደንቦች
በትምህርት ተቋሙ ውስጥ የሚገኝ ከሆነ የዲሲፕሊን ኮሚቴው ከጭብጡ ጋር አግባብነት ያላቸው
መሆኑን ሲያምንበት እንዲቀርብ የሚመለከተውን ክፍል ወይም ተቋም ሊጠይቅ ይችላል፡፡
2.11.3. ማንኛውም ፣ ትምህርት ቤት ወይም የትምህርት ተቋም በኮሚቴው ሲጠየቅ ተፈላጊዎቹን ህጎች፣
ደንቦች፣ መመሪያዎችና ሌሎች የጽሁፍ ማስረጃዎችን አቅርቦ የማሳየት ወይም ትክክል ግልባጩን
የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡
2.11.4. ተከሳሹ ጭብጡን የሚያስረዱለት ምስክሮች እንዲጠሩለት ስማቸውንና አድራሻቸውን ዘርዝሮ
ጥያቄውን ካቀረበ ኮሚቴው እንዲጠሩና ቀርበው እንዲመሰክሩ ለማድረግ ይቻላል፡፡
2.12. የዲሲፕሊን ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ አቀራርብ
2.12.1. ኮሚቴው የቀረበለትን የከባድ የዲሲፕሊን ክስ መርምሮ የውሳኔ ሃሳቡን ለመስሪያ ቤቱ የበላይ ሀላፊ
አቅርቦ በኃላፊው እንዲወሰን ያደርጋል ፤ የዲሲፕሊን ክስ ለኮሚቴው ሲቀርብ ኮሚቴው ጉዳዩ በደንብ
ቁጥር 24 አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ (1) መሰረት ክሱ በአዋጅ መሰረት በይርጋ የታገዱ ከሆኑ ወይም
ተፈጸመ የተባለው ድርጊት በዲሲፕሊን ሊያስከስስ የማይችል ከሆነ ወይም በተከሰሰበት ጉዳይ ላይ ቀደም
ሲል ውሳኔ የተሰጠበት ከሆነ ተከሳሹ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ተከሳሹ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያውን ካነሳና
ከተከራከረ ክሱን ውድቅ ሊያደርገው ይችላል፡፡
2.12.2. በምርመራው ውጤት ላይ ተመስርቶ የዲሲፕሊን ኮሚቴው የቀረበለት የዲሲፕሊን ጉዳይ ተቀባይነት
የሌለው ከሆነ ውድቅ መሆኑን ከነምክንያቱ በመዘርዘር የውሳኔ ሃሳብ ለሚመለከተው የበላይ ኃላፊ
ያቀርባል፡፡
2.12.3. የቀረበው ክስ በሙሉ ወይም በከፊል በማስረጃ የተረጋገጠ ከሆነ እንደ ነገሩ ክብደት ለተፈጸመው ጥፋት
ተመጣጣኝ የሆነ የዲሲፕን ቅጣት በዚሁ መመሪያ በተራ ቁጥር 2 ከ 2.4 እስከ 2.6 ከተዘረዘሩት የዲሲፕሊን
ቅጣቶች ውስጥ አንዱን ቅጣት የውሳኔ ሀሳብ ለሚመለከተው የበላይ ሃላፊ ያቀርባል፡፡
2.12.4. የዲሲፕሊን ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ በሚመለከተው ኃላፊ ወይም የበላይ ኃላፊ ውሳኔ ተሰጥቶበት
በጽሁፍ ለተከሳሽ እስኪሰጥ ድረስ በሚስጢር መጠበቅ አለበት፡፡
2.12.5. የዲሲፕሊን ኮሚቴው ባቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ የመስሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ በአስር የስራ ቀናት ውስጥ
ውሳኔ በመስጠት ለተከሳሹ በጽሁፍ እንዲሰጠው መደረግ አለበት፡፡
2.12.6. በአዋጅ አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ (4) (ሐ) በተጠቀሰው መሰረት በትውስት የተዛወረ መምህር ወይም
የት/ቤት አመራር የዲሲፕሊን ጉዳይ በቀጣሪው ትምህርት ቤት ወይም ተቋም የሚታይና የሚወሰን
ይሆናል፡፡
2.13. ውሳኔ አሰጣጥ
2.13.1. በመምህራን ወይም የት/ቤት አመራር ላይ የዲሲፕሊን ክስ ሲቀርብ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱ በሚከተሉት
ድንጋጌዎች መሰረት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ውሳኔ ለመስጠት በዚህ መመሪያ ስልጣን የተሰጠው

18
የሚመለከተው ኃላፊ ወይም የበላይ ኃላፊ በዲሲፕሊን ኮሚቴው ተጣርቶ የሚቀርብለትን የዲሲፕሊን
ቅጣት የውሳኔ ሃሳብ በማጽደቅ ወይም በማሻሻል ወይም በመሻር ውሳኔ ይሰጣል፡፡
የዲሲፕሊን ቅጣት አወሳሰን

2.14. በዚህ የዲሲፕሊን ኮሚቴ መመሪያ ምዕራፍ ሁለት አንቀጽ 2.1 በተቋቋመው ኮሚቴ ታይቶ የውሳኔ ሃሳብ
የሚቀርብ ሲሆን በሚቀርብለት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ውሳኔ መስጠት የሚችለው በትምህርት ቤቱ አመራር
(ርዕሰ መምህር ፣ ም/ርዕሰ መምህር ወይም በሚወከለው ኃላፊ) ይሆናል፡፡
ሀ. ለወረዳ ተጠሪ የሆነ ትምህርት ቤት አመራር በወረዳው ት/ጽ/ቤት ኃላፊ ወይም በሚወክለው ኃላፊ ይሆናል፡፡
ለ/ ለክፍለ ከተማው ተጠሪ የሆነ ትምህርት ቤት አመራር ለክ/ከተማ ት/ጽ/ቤት ሃላፊ ወይም በሚወክለው ኃላፊ
ይሆናል፡፡
2.15. በዲሲፕሊን የሚወሰን ቅጣት የማናቸውንም ፍ/ቤት የቅጣት ውሳኔ አለመጠበቁ በዲሲፕሊን የሚወሰነው
ቅጣት የማናቸውም ፍ/ቤት የቅጣት ውሳኔ ስለማይከተል ስለዲሲፕሊን ጉድለት አፈጻጸም በዚህ መመሪያ
የተገለጸውን በመከተል የፍ/ቤት ወይም የሌላ መስሪያ ቤት ውሳኔ ሳይጠብቅ ራሱን በቻለ ተለይቶና
ተጣርቶ መወሰን አለበት ፡፡
2.16. የዲሲፕሊን ቅጣት በሪከርድነት ስለሚቆይበት ጊዜ በአዋጁ አንቀጽ 68 ንዑስ አንቀጽ (5) መሰረት
2.16.1. ለቀላል ዲሲፕሊን ቅጣት ቅጣቱ ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ ለሁለት አመት
2.16.2. ከባድ የዲሲፕሊን ቅጣት ከሆነ ቅጣቱ ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ ለአምስት ዓመት ይሆናል
ክፍል ሶስት
የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ስለማቋቋምና የቅሬታ አቀራረብ ስነ-ስርዓት
3. ዓላማ
የቅሬታዎች የማስተናገጃ ስነ-ስርዓት ዓላማ፡-
3.1. ለቅሬታዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት፣
3.2. ለቅሬታዎች መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ስህተቶችንና ድክመቶችን በማረም እና
3.3. ሁሉንም በኩልነት ለማስተናገድ የሚያስችልና ፍትሀዊ የሆነ አሰራር በማስፈን የሰመረ የሰራተኛ ግንኙነት
እንዲዳብር ማድረግ ነው ፡፡
4. የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ስለማቋቋም
በማንኛውም ትምህርት ቤት ወይም የትምህርት ተቋም በአዋጁ አንቀጽ 37 (1) መሰረት መምህርን የት/ቤት
አመራርን እና የትምህርት ተቋም ሃላፊ የሚያቀርበውን የቅሬታ አቤቱታ ተቀብሎ በመመርመር ስልጣን ላለው
ኃላፊ ወይም የበላይ ሀላፊ የውሳኔ ሃሳብ የሚያቀርብ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በዚህ መመሪያ ተቋቁሟል ፡፡ ሆኖም
የዲሲፒሊን ኮሚቴ አባል የሆነ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባል ሆኖ ሊሰየም /ሊወከል/ አይችልም፡፡
4.1. የኮሚቴው አባላት
የመምህራን ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ሰባት አባላት ይሩታል፡፡ የኮሚቴው አወቃቀርም እንደሚከተለው ይሆናል፡፡
ሀ. በርዕሰ መምህር ወይም የተቋም ኃላፊ የሚሰየም …………… ሰብሳቢ
ለ. በርዕሰ መምህር ወይም የተቋም ኃላፊ የሚሰየም አንድ ………….. አባል
19
ሐ. ከት/ቤቱ መሰረታዊ መምህራን የሚመረጡ ሁለት ተወካዮች፡- (አንድ የመ/ራን ማህበር ተወካይና አንድ
ከመሰረታዊ መ/ማ/የሥ/ጾታ ተጠሪ ሴት መ/ት) ------------- አባል
መ. ከወላጅ ፣ የተማሪ ፣ መምህር ህብረት (ወተመህ ምክር ቤት) አንድ የወላጅና አንድ የተማሪ ተወካይ
ሁለት ………… አባል
ሠ. የት/ቤቱ የሰው ሃይል አስተዳደር ደጋ የስራ ሂደት መሪ …………. አባልና ፀሐፊ ይሆናል፡፡
4.2. የትምህርት ቤትአመራር የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ሰባት አባላት ይኖሩታል፡፡ የኮሚቴ አወቃቀርም
እንደሚከተለው ይሆናል፡፡
ሀ. በወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ወይም በክፍለ ከተማ ት/ጽ/ቤት ኃላፊ የሚሰየም--------------ሰብሳቢ
ለ. በወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ወይም በክፍለከተማ ት/ጽ/ቤት የሚሰየም አንድ -------------አባል
ሐ. ከት/ተቋሙ መሰረታዊ መ/መምህራን ተወካይና የሥርአተ ጾታ ተጠሪ ሁለት ተወካዮች፡- ---አባል
መ. ከወላጅ ፣ የተማሪ ፣ መምህር ህብረት (ወተመህ) ተወመ ምክር ቤት አንድ የተማሪ አንድ የወላጅና
ተወካይ ሁለት ………………………አባል
ሠ. የት/ተቋሙ የሰው ሃይል አስተዳደር ደጋ የስራ ሂደት መሪ …………. አባልና ፀሐፊ ይሆናል፡፡
4.3. በበላይ ሃላፊው ስለሚሰየሙ አባላት አሰያየም
በዚህ አንቀጽ 4.2 (ሀ እና ለ) የተመለከቱት የኮሚቴው አባላት የሚሰየሙት ከትምህርት ቤቱ ወይም ከትምህርት
ተቋሙ ይሆናል፡፡ ሆኖም ከትምህርት ቤቱ ወይም ከትምህርት ተቋሙ የሚወከል በሚታጣበት ጊዜ ከሚመለከተው
ኃላፊው ጽ/ቤት ሰራተኞች መካከል ሊሰየም ይችላል፡፡
5. የኮሚቴ አባልነት መመዘኛ
ማናቸውም የኮሚቴ አባል፡-
5.1. በመልካም ስነ ምግባሩና በስራ አፈጻጸሙ የተመሰገነ፣
5.2. ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ በዲሲፕሊን ጉድለት ያልተቀጣ፣
5.3. ቋሚ የመንግስት ሰራተኞች የሆነና በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ከሁለት አመት በላይ አገልግሎት ያለው
ሊሆን ይገባል፡፡
6. የአገልግሎት ዘመን
6.1. በሰራተኛ የተመረጡ የኮሚቴ አባለት የአገልግሎት ዘመን ሁለት አመት ይሆናል፡፡ሆኖም የአገልግሎት ዘመናቸውን
የጨረሱ የመምህራን ተወካዮች እንደገና ለአንድ የአገልግሎት ዘመን ሊመደብ ወይም ሊመረጥ ይችላል፡፡
6.2. ከላይ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 6.1 የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ወይም
የትምህርት ተቋሙ ሃላፊ ወይም በሚመለከተው የበላይ ኃላፊ የሚመደቡ የኮሚቴ አባላት እንደአስፈላጊነቱ
ሊለዋወጥ ይችላል፡፡
7. የኮሚቴ ስብሰባ
7.1. የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ለስራው ባስፈለገ መጠን በማንኛውም ጊዜ ሊሰበሰብ ይችላል፡፡
7.2. በኮሚቴው ስብሰባ ላይ ሰብሳቢውና ሌሎች ሶስት አባላት ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ ይሆናል፡፡
7.3. የኮሚቴው ውሳኔ የሚያልፈው በድምጽ ብልጫ ይሆናል፡፡ ድምጽ እኩል ለእኩል የተከፈለ እንደሆነ ሰብሳቢው
ያለበት ወገን ያቀረበው ሃሳብ ያልፋል፡፡ በሀሳብ የተለየው አካል የተለየበትን ምክንያ በግልጽ ማስፈር አለበት፡፡
20
8. ከአባልነት ስለመሰረዝና ከስብሰባ ስለመነሳት
8.1. ማንኛውም የኮሚቴ አባል ክስ ከቀረበበት ሰራተኛ ጋር ፀብ ወይም የስጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ያለው
መሆኑ ሲረጋገጥ ለዚያ ብቻ ከስብሰባው እንዲነሳ ይደረጋል፡፡
8.2. ማንኛውም የኮሚቴ አባል
ሀ. በኮሚቴው በመለየት ላይ ያለን ጉዳይ በሚመለከት ሚስጥር ያባከነ
ለ. የኮሚቴውን ስራ በማናቸውም አኳኋን ያደናቀፈ ፣ወይም
ሐ. በዚህ መመሪያ አንቀጽ 4 የተመለከቱትን መመዘኛዎች ያጓደለ እንደሆነ ከአባልነት ሊሰረዝ ይችላል፡፡
9. ቅሬታ የማቅረብ መብት
9.1. ማንኛውም መምህር ፣ ርዕሰ መምህርና ሱፐርቫይዘር መብቴ ተጓድሎብኛል ወይም በደል ተፈጽሞብኛል
በማለት ቅር የተሰኘ እንደሆነ ቅሬታውን እንዲታይለትና የመፍትሄ እርምጃ እንዲወሰድለት ቅሬታውን ለቅሬታ
ሰሚ ኮሚቴ የማቅረብ መብት አለው፡፡
9.2. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 9.1 አጠቃላይ አነጋገር እንደተጠበቀ ሆኖ፡-
ሀ. ከህጎችና መመሪያዎች አተረጓጎም ወይም አፈጻጸም
ለ. ከመብቶችና ጥቅሞች አጠባበቅ፣
ሐ. ከስራው አከባቢ ጤንነትና ደህንነት ሁኔታዎች፣
መ. ከስራ ምደባና ደረጃ አሰጣጥ፣
ሠ. ከስራ አፈጻጸም ምዘና
ረ. በስራ መደቡ የስራ ዝርዝር ሳይሸፈኑ እንዲፈጽሙ የሚሰጡ ተግባራት፣
ሰ. በአለቆች ከሚፈጸሙ ተገቢ ያልሆኑ ተጽዕኖዎች
ሸ. ቀላል ዲሲፒሊን እርምጃ አወሳሰድ ወይም
ቀ. የአገልግሎት ሁኔታዎችን ከሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ምክንያት በደል ደረሰብኝ የሚል መ/ር ፣
ር/መምህር ወይም ሱፐርቫይዘር ቅሬታውን ሊያቀርብ ይችላል፡፡
10. የቅሬታ ማመልከቻ
10.1. ቅሬታው እንዲሰማለት የሚፈልግ የመንግስት ሰራተኛ የቅሬታ ማመልከቻውን ለመስሪያ ቤቱ የቅሬታ ሰሚ
ኮሚቴ ለማቅረብ ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው ቅሬታውን በጽሁፍ ለቅርብ ኃላፊው አቅርቦ መፍትሄ ካላገኘ
ነው፡፡
10.2. የቅሬታ ማመልከቻ የሚከተለውን መያዝ አለበት
ሀ. የአመልካች ስምና አድራሻ
ለ. የስራ መደቡ መጠሪያ
ሐ. የቅሬታ የቀረበበት ሰራተኛ /ኃላፊ ስም/
መ. የቅሬታው መንስኤ
ሠ. ደጋፊ ማስረጃዎች /ካሉ/
ረ. አመልካች የሚሻውን መፍትሄ
ሰ. ቀንና ፊርማ መኖር አለበት፡፡

21
10.3. የቅሬታቸው መንስኤ አንድ አይነት የሆነ የቅሬታ ማመልከቻቸውን በተወካያቸው አማካይነት በቡድን ሊያቀርቡ
ይችላሉ፡፡
11. ቅሬታ የማቅረቢያ ጊዜና ገደብ
11.1. ቅር የተሰኘ የትምህርትቤት አመራር ጉዳዩን ለቅርብ አለቃው ወይም ለሚመለከተው የስራ ኃላፊ በጽሁፍ
ካቀረበበት ቀን ጀምሮ በአምስት የስራ ቀናት ውስጥ ማመልከቻውን ለመስሪያ ቤቱ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ
ሊያቀርብ ይችላል፡፡
11.2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 11.1 በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የቅሬታውን
ማመልከቻ ሊያቀርብ ያልቻለ የተ/ቤት አመራር ከአቅም በላይ የሆነው ምክንያት በተወገደ በአስር የስራ ቀናት
ውስጥ ማመልከቻውን ሊያቀርብ ይችላል፡፡
12. ቅሬታውን ስለማጣራት
12.1. የመስሪያ ቤቱ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ማመልከቻ ሲቀርብለት በዚህ መመሪያ አንቀጽ 10.2 የተደነገገውን አሟልቶ
የቀረበ መሆኑን በማረጋገጥ ተቀብሎ ይመዘግባል፡፡
12.2. ኮሚቴው
ሀ. የቅሬታ ማመልከቻውንና አግባብ ያላቸውን ማስረጃዎች በመመርመር ፣
ለ. ከአመልካቹ እና በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ከሰጠው የስራ ኃላፊ ጋር በመወያየት እና
ሐ. አግባብ ያላቸውን ህጎች ፣ ደንቦች መመሪያዎችና የአሰራር ልምዶች በማገናዘብ ፣ የቀረበለትን ቅሬታ ያጣራል፡፡
12.3. ኮሚቴው የምርመራውን ውጤትና የውሳኔ ማመልከቻውን ከቀረበለት ቀን ጀምሮ እጅግ ቢዘገይ ከሰባት እስከ
አስር የስራ ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የሚመለከተው ኃላፊ ወይም የበላይ ኃላፊ የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል፡፡
12.4. ይርጋን በተመለከተ ለቀላል ዲሲፕሊን አንድ ወር እንዲሆንና ለከባድ የዲስፕሊን ጥፋት 3 ወር ይሆናል፡፡
12.5. በሪከርድነት ስለመያዝ፡-
12.5.1. ለቀላል የዲስፕሊን ጥፋት ለመምህራን ለመምህራን አንድ ዓመት እንዲሆንና ለትምህርት ቤት አመራር
ደግሞ ሁለት ዓመት ይሆናል፡፡
12.5.2. ለከባድ የዲስፕሊን ጥፋት ለመምህራን ሶስት ዓመት እንዲሆንና ለትምህርት ቤት አመራር ደግሞ አምስት
ዓመት ይሆናል፡፡

ክፍል አራት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
4.1. የማስረጃ ወጭ
የማስረጃዎች አቀራረብ የገንዘብ ወጭ የሚያስከትል ከሆነ ማስረጃው እንዲቀርብለት የሚፈልገው ወገን ለሚያቀርበው
ማስረጃ የሚያስፈልገው ወጭ ራሱ ይችላል፡፡ ነገር ግን ተከሳሹ ማስረጃ ይሆኑኛል ያላቸው በከሳሹ ትምህርት ቤት
ወይም የትምህርት ተቋም ይዞታ ስር ከሆነና በዲሲፕሊን ኮሚቴ እንዲቀርብ ከታዘዙ የሚያስከትለው ወጪ እንዲሸፍን
አይጠየቅም፡፡
4.2. ተከሳሽ የሚከራከርለት ሰው ለመወከል ስለመቻል

22
ተከሳሽ በዲሲፕሊን ወይም በቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች ላይ በሚከራከርበት ጊዜ የመረጠውን ሰው ይዞ ለመቅረብ ፣
ለመወከል ወይም እንዲከራከርለት ለማድረግ መብት አለው፡፡ ይህንንም ተከሳሽ ኮሚቴው ፊት ቀርቦ በጽሁፍ ማስታወቅ
አለበት፡፡
4.3. የተሻሩ መመሪያዎች
ይህንን መመሪያ የሚቃረን ማንኛውም ሌላ መመሪያና የአሰራር ልምድ በዚህ መመሪያ ውስጥ የተደነገጉትን ጉዳዮች
በሚመለከት ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡
4.4. መመሪያው በስራ ላይ የሚውልበት ጊዜ
ይህ መመሪያ የመምህራን፣ የርዕሰ መምህራን ወይም ሱፐርቫይዘር የዲሲፕሊን አፈጻጸምና ቅሬታ አቀራረብ ስነ ስርዓት
የአፈጻጸም መመሪያ ከነሃሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡
ዘላለም ሙላቱ/ዶ/ር/
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
ትምህርት ቢሮ ኃላፊ

23

You might also like