Download as pdf or txt
Download as pdf or txt
You are on page 1of 5

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የሰ.መ.ቁ. 238127

ታህሳስ 26 ቀን 2016 ዓ.ም


ዳኞች፡- 1. ብርሃኑ አመነዉ
2. በእዉቀት በላይ
3. ቀነዓ ቂጣታ
4. ብርሃኑ መንግስቱ
5. ማርታ ተካ
አመልካች፡……አቶ ኢብራሂም ዛኪር
ተጠሪ፡………….አቶ ኤፍሬም ይኩኖ
መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ
ይህ የከተማ ይዞታ ክርክር የተጀመረዉ በኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ
ፍ/ቤት ሲሆን የአሁን አመልካች የሥር ተከሳሽ፣ የአሁን ተጠሪ የሥር ከሳሽ ሆኖ ሲከራከሩ ነበር፡፡
ይህ ጉዳይ ለዚህ ችሎት ሊቀርብ የቻለዉ አመልካች የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ.ቁ.230304
በ15/03/2015 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲታረምልኝ
በማለት በማመልከታቸዉ ነዉ፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ ሲታይ የአሁን ተጠሪ በሥር ፍ/ቤት ባቀረቡት የክስ አቤቱታ የሱሉልታ ከተማ
አስተዳደር በሊዝ ስምምነት ስፋቱ 1500 ካ.ሜ የተሰጠኝን ይዞታ፣ የአሁን አመልካች ከዚህ ቀደም
ተከራክረን የተወሰነበትን፣ በድጋሚ የመሬት ይዞታዉን በመያዝ የመጋዘን ቤቱን ሰብሮ ገብቶ
እየተገለገለበት ስለሆነ አመልካች ከቅጥር ግቢዉ እና ከመጋዘን ቤት ለቆ እንዲወጣልኝ
እንዲወሰንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቋል፡፡

ማስታወሻ፡- ይህ የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለጥናትና ምርምር ሥራ ወይም ለግንዛቤ እንጂ
ለፍርድ አፈጻጸም ዓላማ አያገለግልም !
የአሁን አመልካች በዚህ ክስ ላይ ባቀረበዉ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን የማየት
ስልጣን የለዉም፤ ተጠሪ ከዚህ ቀደም በዚህ ጉዳይ ክስ አቅርቦ ተከራክረንበት ዉሳኔ የተሰጠ
በመሆኑ ይህ ክስ አሁን በድጋሚ ለሁለተኛ ጊዜ የቀረበ ጉዳይ በመሆኑ ክሱ ዉድቅ እንዲደረግልን
በማለት ተከራክሯል፡፡ ተጠሪ በአመልካች በተነሳዉ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ባቀረበዉ
ክርክር አመልካች ለክርክር መነሻ የሆነዉን የመሬት ይዞታ በድጋሚ ስለያዘብኝ የቀረበ ክስ በመሆኑ
ድጋሚ የቀረበ ክስ አይደለም በማለት ተከራክሯል፡፡

ከዚህ በኋላ የሥር የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት የተነሳዉን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በመመርመር
በሰጠዉ ዉሳኔ ግራ ቀኛቸዉ ቀደም ሲል በዚህ ጉዳይ ተከራክረዉ ዉሳኔ ያገኘ በመሆኑ አሁን
ድጋሚ የቀረበ ክስ ተቀባይነት የለዉም በማለት ዉድቅ በማድረግ ወስኗል፡፡

የአሁን ተጠሪ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን
ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙን በማከራከር ባሳለፈዉ ዉሳኔ ተጠሪ አሁን ባቀረበዉ ክስ የጠየቀዉ ዳኝነት
ቀደም ሲል መሰረታዊ በሆነ የክስ ጭብጥ ላይ ዉሳኔ የተሰጠበት መሆኑን በማስረጃ ያልተረጋገጠ
ስለሆነ አሁን የቀረበዉ ክስ ቀደም ሲል ዉሳኔ ባገኘ ጉዳይ ላይ በድጋሚ የቀረበ ነዉ ሊባል
ስለማይችል የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዉ ተቀባይነት የለዉም በማለት የሥር ፍ/ቤትን ዉሳኔ
በመሻር፣ የሥር ፍ/ቤት በዋናዉ ጉዳይ ግራ ቀኙን አከራክሮ ዉሳኔ እንዲሰጥበት መልሶለታል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የቀረበለትን ይግባኝ በትዕዛዝ ዉድቅ በማድረግ የሥር የዞኑ ከፍተኛ
ፍ/ቤትን ዉሳኔ በማጽናነት ወስኗል፡፡ የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ በዚህ ዉሳኔ እና ትዕዛዝ
ቅር በመሰኘት ለማስለወጥ ነዉ፡፡

የአሁን አመልካች በ30/3/2015 ዓ.ም በተጻፈ የሰበር አቤቱታ፡ ከዚህ ቀደም ሲል አመልካች በሰበታ
ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት ያቀረበዉን ክስ በተመለከተ በመ.ቁ.10823 ላይ የአሁን ተጠሪ ይዞታዉ የእኔ
ነዉ በማለት በክርክሩ ጣልቃ ገብ ሆኖ ተከራክሮ ዉሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ በመሆኑ፣ የአሁን ተጠሪ
አሁን ክስ ያቀረበዉ በዚሁ ጉዳይ ላይ ድጋሚ የቀረበ ክስ በመሆኑ የሥር ፍ/ቤቶች ክሱን
በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.5 (1) እና 244 (2) (ለ) መሰረት ዉድቅ ማድረግ ሲገባቸዉ ይህ ክስ በድጋሚ
የቀረበ አይደለም በማለት የአመልካችን መቃወሚያ ዉድቅ በማድረግ ያሳለፉት ዉሳኔ መሰረታዊ
የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ እንዲሻርልኝ በማለት በዝርዝር አመልክቷል፡፡

ማስታወሻ፡- ይህ የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለጥናትና ምርምር ሥራ ወይም ለግንዛቤ እንጂ
ለፍርድ አፈጻጸም ዓላማ አያገለግልም !
የሰበር አጣሪ ችሎት ጉዳዩን በማየት ፣የሥር ፍ/ቤቶች ይህ ጉዳይ ቀደም ሲል በመ.ቁ.10823 ላይ
ዉሳኔ ያገኘና ድጋሚ የቀረበ ክስ አይደለም ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት፣ ለማጣራት ሲባል የሰበር
አቤቱታዉ ያስቀርባል በማለት ተጠሪ መልስ እንዲሰጥ ባዘዘዉ መሰረት በ3/5/2015 ዓ.ም የተጻፈ
መልስ አቅርቧል፡፡ የመልሱም ይዘት ባጭሩ፡ ቀደም ሲል በመ.ቁ.10823 ላይ ክስ የቀረበዉ የአሁን
አመልካች ሲሆን ክሱም የሚመለከተዉ ስፋቱ 500 ካ.ሜ ይዞታ የነበረ በመሆኑ፣ ተጠሪ ጣልቃ
ገብ ሆኜ ነዉ የተከራከርኩት በመሆኑ፣ የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት እና ሰበር
ሰሚ ችሎት ለተጠሪ የወሰኑ ሲሆን የአሁን ተጠሪ ክስ ያቀረበበትን ስፋቲ 1500 ካ.ሜ የሆነዉን
ይዞታ በሙሉ አይደለም፤ አመልካች ይህንን ይዞታ በህገ ወጥ መንገድ ስለያዘብኝ እንዲለቅልኝ
የቀረበ ክስ በመሆኑ ቀደም ሲል

ዉሳኔ ያገኘ ጉዳይ ነዉ ለማለት አይቻልም፤ የአመልካች የሰበር አቤቱታዉ ዉድቅ እንዲደረግልኝ
በማለት በዝርዝር ተከራክሯል፡፡ አመልካች በ29/5/2015 ዓ.ም በተጻፈ የመልስ መልስ የሰበር
አቤቱታዉን በማጠናከር ተከራክሯል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ ከፍ ሲል የተመለከተዉ ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር እና ለሰበር


አቤቱታዉ መነሻ የሆነዉን ዉሳኔ አግባብነት ካላቸዉ የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንዲሁም
የሰበር አቤቱታዉ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘዉ ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለዉ መርምሮታል፡፡ በዚህ
መሰረት አመልካች ቀደም ሲል በሰበታ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት በመ.ቁ.10823 ላይ ክስ ያቀረበ ሲሆን
የአሁን ተጠሪ መብቱ እንዳይነካበት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.41 መሰረት ወደ ክርክሩ ጣልቃ በመግባት
ተከራክሮ የተጠሪን የይዞታ መብት የሚያስከብር ዉሳኔ መሰጡትን ከግራ ቀኙ ክርክር መረዳት
ይቻላል፡፡ ቀደም ሲል የተከራከሩበት ይዞታ ስፋቱ 500 (አምስተ መቶ) ካ.ሜ መሆኑን
ያልተካካዱበት ጉዳይ ነዉ፡፡ የአሁን ተጠሪ አሁን ክስ ያቀረበበት ይዞታ ደግሞ ስፋቱ 1500 ካ.ሜ
መሆኑን የሥር ፍ/ቤት የዉሳኔ ግልባጭ ያሳያል፡፡ ተጠሪ ባቀረበዉ ክስ አመልካች ከዚህ ዉሳኔ
በኋላ ይዞታዉን በድጋሚ ተመልሶ ስለያዘብኝ እንዲለቅልኝ የሚል መሆኑን ከሥር ፍ/ቤት የዉሳኔ
ግልባጭ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል በነበረዉ ክርክር ክስ ያቀረበዉ አመልካች መሆኑን
እና ተጠሪ ጣልቃ ገብቶ የተከራከረ መሆኑን፣ የመሬት ስፋቱም ልዩነት ያለዉ መሆኑን፣ ተጠሪ
አሁን ባቀረበዉ ክስ አመልካች ከዉሳኔዉ በኋላ ድጋሚ ተመልሶ ይዞታዉን የያዘበት መሆኑን
በመግለጽ እንሆነ የሚያስገነዝብ ነዉ፡፡ እንዲሁም የክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት በሰጠዉ ዉሳኔ አሁን
የቀረበዉ ክሰ ቀደም ሲል በነበረዉ ክስ መሰረታዊ በሆነ የክስ ጭብጥ ላይ ዉሳኔ ተሰጥቶበታል
ማስታወሻ፡- ይህ የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለጥናትና ምርምር ሥራ ወይም ለግንዛቤ እንጂ
ለፍርድ አፈጻጸም ዓላማ አያገለግልም !
ለማለት የሚያስችል ተጨባጭ ማስረጃ ለአለመኖሩን በማመልከት መወሰኑን የዉሳኔዉ ግልባጭ
ያሳያል፡፡

በመሰረቱ አንድ ጉዳይ ቀደም ሲል የመጨረሻ የፍርድ ዉሳኔ ያገኘ ጉዳይ ነዉ ለማለት ቀደሞ
በፍርድ የተወሰነዉ ክርክር ሥረ-ነገርና የተያዘዉ ጭብጥ አንድ ዓይነት ከሆነ በክርክሩ ላይ የነበሩት
ወይም ከተከራካሪዎቹ መብት ያገኙ ሶስተኛ ወገኖች በዚያዉ ነገር ሁለተኛ ክስ ወይም ማናቸዉንም
ዓይነት ክርክር ማቅረብ እንደማይችሉ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.5 (1) ድንጋጌ ሥር ተመልክቷል፡፡

በዚህ አግባብ አሁን ወደ ተያዘዉ ጉዳይ ስንመለስ ቀደም ሲል በነበረዉ ክርክር ክስ ያቀረበዉ
የአሁን አመልካች በመሆኑ፣ ተጠሪ በክርክሩ ጣልቃ ገብቶ መብት የለህም ተብሎ የተወሰነበት
ሳይሆን የይዞታዉ መብቱ ተከብሮ ዉሳኔ የተሰጠ መሆኑን፣ የመሬት ይዞታዉ ስፋቱ ልዩነት

ያለዉ መሆኑን፣ ተጠሪ ባቀረበዉ ክርክር አመልካች ይህን ይዞታ ከዉሳኔዉ በኋላ በድጋሚ
ተመልሶ ይዞብኛል የሚል በመሆኑ፤ እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ሲታዩ ተጠሪ ያቀረበዉ ክስ ቀደም ሲል
ዉሳኔ ባገኘ ጉዳይ ላይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.5 (1) መሰረት በድጋሚ የቀረበ ክስ ነዉ የሚያብል ሆኖ
አልተገኘም፡፡ በመሆኑም የሥር ፍ/ቤቶች በአመልካች የተነሳዉን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ
ዉድቅ በማድረግ ግራ ቀኙ በፍሬ ጉዳዩ ተከራክሮ ዉሳኔ እንዲሰጥበት መወሰኑ የሚነቀፍበት
አግባብ የለም፡፡ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80 (3) (ሀ) እና በአዋጅ
ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 2 (4) (ለ) እና10 (1) (መ) መሰረት ከተሰጠዉ ስልጣን አንጻር
አመልካች ያቀረበዉ ቅሬታ የሥር ፍ/ቤቶች የሰጡት ዉሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት
የተፈጸመበት መሆኑን የሚያመለክት ባለመሆኑ ቅሬታዉ ተቀባይነት የለዉም ብለናል፡፡

ሲጠቃለል የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ተጠሪ ያቀረበዉ ክስ
ቀደም ሲል ዉሳኔ ባገኘ ጉዳይ ላይ በድጋሚ የቀረበ ክስ አይደለም በማለት አመልካች ያነሳዉን
የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ዉድቅ በማድረግ ያሳለፉት ዉሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት
ያልተፈጸመበት በመሆኑ ተከታዩን ወስነናል፡፡

ዉሳኔ

ማስታወሻ፡- ይህ የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለጥናትና ምርምር ሥራ ወይም ለግንዛቤ እንጂ
ለፍርድ አፈጻጸም ዓላማ አያገለግልም !
1. የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ.ቁ.230304 በ15/03/2015 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ
የህግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ በበፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር ሥነ-ሥርዓት
መመሪያ ቁጥር 17/2015 አንቀጽ 9 (1) መሰረት ጸንቷል፡፡
2. የዚህ ዉሳኔ ግልባጭ ለሥር ፍ/ቤቶች ይድረስ፡፡
3. ግራ ቀኙ የሰበር ክርክሩ ያስከተለዉን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸዉን ይቻሉ፡፡
4. ይህ ችሎት ታህሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም የሰጠዉ የእግድ ትዕዛዝ በዚህ ዉሳኔ ተነስቷል፡፡
ይጻፍ፡፡
መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነብብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

ብ/ም

ማስታወሻ፡- ይህ የሰበር ችሎት ውሳኔ ሰነድ ለጥናትና ምርምር ሥራ ወይም ለግንዛቤ እንጂ
ለፍርድ አፈጻጸም ዓላማ አያገለግልም !

You might also like